ምዕራፍ 17 · 24 ደቂቃ ንባብ · 32 ደቂቃ ማዳመጥ
አንቀጽ 2
ሰዎቹ መጥተው ለትምህርታችሁ እንዲገዙ ለማድረግ እነዚህን መንገዶች ከተጠቀማችሁ በኋላ፣ ቀጥሎ በሥራው ውስጥ ከእነርሱ ጋር እጅግ ፍሬያማ በሆነ መንገድ እንዴት ልትሠሩ እንደምትችሉ ልንመረምር ይገባናል። ደግሜም እላለሁ፤ አላዋቂን ሰው በሃይማኖት ዋና ዋና መሠረታውያን ትምህርቶች ለማስተማር በትክክል ከመያዝ ይልቅ መልካም ስብከት አዘጋጅቶ መስበክ እጅግ የቀለለ ነገር ይመስለኛል። ይህ ሥራ በአንዳንዶች ዘንድ የቱን ያህል የተናቀ ቢሆንም፣ የአገልጋዮችን ስጦታና መንፈስ እንደሚፈትን፣ በአንዱ ሰውና በሌላው መካከል ያለውንም ልዩነት ከስብከት ይበልጥ አጥርቶ እንደሚያሳያችሁ አልጠራጠርም። በዚህም ስፍራ ለዓላማዬ ስለሚስማማ፣ እጅግ የተማረ፣ ትክክለኛ እምነት ያለውና እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የሆነው ሊቀ ጳጳስ አሸር በዋንስቴድ በንጉሥ ጄምስ ፊት ኤፌሶን 4:13ን መሠረት አድርጎ በሰበከው ስብከት የተናገረውን ቃል እገለብጣለሁ፦ «ዋና ዋናዎቹ የትምህርተ ሃይማኖት ርእሶች በመደበኛው አገልግሎት በመላው አገር ለሕዝቡ በትጋት እንዲቀርቡና እንዲብራሩ ሥርዓት በማውጣት ግርማዊነትዎ ያደረጉት ጥንቃቄ በበቂ ሊመሰገን ከቶ አይችልም፤ እርስዎ በቅንነት እንዳሰቡት በየስፍራው ሁሉ እንዲሁ በአግባቡ ቢፈጸም ብዬ እመኛለሁ። ታላላቅ ሊቃውንት ምናልባት እንዲህ ዝቅ ብሎ መውረድና የክርስቶስን ትምህርት መነሻዎችና የመጀመሪያ መሠረታውያን ነገሮች በማስተማር ብዙ ጊዜያቸውን ማሳለፍ ለክብራቸው የማይስማማ ሊመስላቸው ይችላል፤ ነገር ግን መሠረትን በብልሃት መጣል በሕንጻው ሁሉ ውስጥ እጅግ ታላቅ ቁም ነገር እንደ ሆነ፣ እንዲሁም ከጥበበኛ አናጺነት ሁሉ የላቀው ድንቅ ሥራ እርሱ መሆኑን ሊያስቡ ይገባቸዋል። ታላቁ ሐዋርያ ‹የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ› ይላል። ከሁላችንም እጅግ የተማረው በፈለገው ጊዜ ይሞክረው፤ ይህን መሠረት በትክክል መጣል (ማለትም ራሳችንን ከተራው አድማጭ የመረዳት አቅም ጋር ማስማማትና አላዋቂውን ሰው እነዚህን ምሥጢራት በመልካም መጠን እንዲያስተውል ማድረግ) በትምህርት ቤቶች ውስጥ ክርክርን ከመመርመር ወይም ረቂቅ የሆነን የትምህርት ነጥብ ከማብራራት ይልቅ ብልሃታችንን እንደሚፈትንና እጅግ አብልጦ እንደሚያደክመን እናገኛለን። ይሁን እንጂ ክርስቶስ የተማርነውንም ያልተማርነውንም ሁላችንን ወደዚህ እምነትና እውቀት አንድነት ያደርሰን ዘንድ ሐዋርያቱንና ነቢያቱን ወንጌልን ሰባኪዎቹንም፣ እንዲሁም መደበኛ እረኞቹንና አስተማሪዎቹን ሰጠ፤ ይህንንም ቸል ማለት የአገልግሎቱን ሥራ ሁሉ ከንቱ ማድረግ ነው። ለሕዝቡ የቱን ያህል ብዙ ስብከቶችን ብንሰብክ፣ ሌላው ትምህርት ሁሉ በላዩ ሊታነጽበት የሚገባው መሠረት ሳይጣል፣ የመጀመሪያዎቹም መሠረታውያን ትምህርቶች ሳይማሩ እስካሉ ድረስ ድካማችን ከንቱ ነውና።»
ሥራውን በትክክል ለማካሄድ መስጠት አስፈላጊ ናቸው ብዬ የማስባቸው መመሪያዎች የሚከተሉት ናቸው፦
1. ሰዎቻችሁ — አንድ ቤተሰብ ወይም ከዚያ በላይ — ወደ እናንተ ሲመጡ፣ ልባቸውን ለማለዘብ፣ ቅሬታን፣ እንቢተኝነትንና ተስፋ መቁረጥን ሁሉ ለማስወገድ፣ ትምህርታችሁንም ለመቀበል እንዲዘጋጁ በአጭር መግቢያ ጀምሩ። እንዲህ ልትሉ ትችላላችሁ፦ «ወዳጆቼ ሆይ፣ ያቀረብሁላችሁ ይህ ጉዳይ ለአንዳንዶቻችሁ ያልተለመደና አስቸጋሪ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን አላስፈላጊ ነው ብላችሁ እንደማታስቡ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እንዲህ ባስብ ኖሮ እናንተንም ራሴንም ከዚህ ድካም ባሳረፍሁ ነበርና። ነገር ግን የነፍሳትን ኃላፊነት መያዝ ምን ማለት እንደ ሆነ፣ የሚጠፉትም ሰዎች ደም ቸል ከሚላቸው አገልጋይ እጅ እንዴት እንደሚፈለግ ሕሊናዬ፣ አዎን፣ እግዚአብሔር ራሱ በቃሉ እጅግ አጽንቶ ስለ ነገረኝ፣ እስከ ዛሬ እንደ ነበርሁት በዚህ በደለኛ ለመሆን አልደፍርም። ወዮ! በዚህ ዓለም ያለን ሥራ ሁሉ በመልካም ወደ መንግሥተ ሰማያት መድረስ ነው፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን ወደዚያ በሰላም እንድናደርሳቸው መሪዎች አድርጎ ሾሞናል። ይህ በመልካም ቢፈጸም ሁሉ ተፈጸመ፤ ይህ ባይፈጸም ግን ለዘላለም ጠፍተናል። እኔና እናንተ አብረን የምንቆይበት ጊዜ የቱን ያህል አጭር ሊሆን እንደሚችል ጌታ ያውቃል፤ ስለዚህ እኔ ከእናንተ ሳልለይ ወይም እናንተ ከዓለም ሳትለዩ ለራሳችንና ለእናንተ መዳን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይገባናል። በዓለም ያለው ሌላው ጉዳይ ሁሉ ከዚህ ጋር ሲነጻጸር እንደ መጫወቻና እንደ ሕልም ብቻ ነው። ነፍሳችሁ ምናልባትም አሁን እንኳ ወደ ቀረበው ሞትና ፍርድ እየቸኮለች ሳለ፣ የሙያችሁ ድካም የጭቃ ጎጆን ከመደገፍ አያልፍም። ስለዚህ በዚህ እጅግ በሚያስፈልግ ሥራ እርዳታ በማግኘታችሁ ደስ እንደሚላችሁ፣ የዓለም ከንቱ ነገሮች ከዚህ እጅግ በሚበልጥ ድካም ካልሆነ በቀር የማይገኙ ሲሆኑ ይህን ድካም ስላደረስሁባችሁ እንደማታማርሩ ተስፋ አደርጋለሁ።» ይህ ወይም ይህን የሚመስል ንግግር እናንተን ለመስማት፣ ትምህርትን ለመቀበል፣ ስለ እውቀታቸውና ስለ አኗኗራቸውም መግለጫ ሊሰጧችሁ ይበልጥ ፈቃደኞች እንዲሆኑ ሊረዳ ይችላል።
2. ሁሉንም እንዲህ ካነጋገራችኋቸው በኋላ አንድ በአንድ ውሰዷቸው፤ በተቻላችሁም መጠን ሌሎቹ በማይሰሙበት በግል አነጋግሯቸው። አንዳንዶች በሌሎች ፊት በነጻነት መናገር አይችሉምና፤ አንዳንዶችም ሌሎች መልሳቸውን ቢሰሙ ለኀፍረታቸው የሚሆን ስለሚመስላቸው በሌሎች ፊት መጠየቅን አይታገሡም፤ ራሳቸው የተሻለ መልስ መስጠት የሚችሉ አንዳንድ ሰዎችም ከሄዱ በኋላ የሰሙትን ለማውራትና እንደ እነርሱ አጥርተው መናገር የማይችሉትን ለማዋረድ ፈጣኖች ይሆናሉ፤ በዚህም ሰዎች ተስፋ ይቆርጣሉ፤ ለዚህ ልምምድ ዳተኞች የሆኑትም ለመተውና ለመራቅ ምክንያት ያገኛሉ፤ «መሣቂያና መዘባበቻ ልንሆን አንመጣም» ይላሉ። ስለዚህ እነዚህን ችግሮች ሁሉ ለመከላከል እጅግ ጥንቁቆች መሆን ይገባችኋል። ዋናው ምክንያት ግን በተሞክሮ እንዳገኘሁት፣ ሰዎች ስለ ኃጢአታቸው፣ ስለ ጐስቁልናቸውና ስለ ተግባራቸው የሚነገራቸውን ግልጽና ቀጥተኛ ንግግር በሌሎች ፊት ከሚቀበሉት ይልቅ ብቻቸውን ስታገኟቸው ይበልጥ ይቀበሉታል፤ እውነትን ወደ ልባቸው ለማድረስና ከሕሊናቸው ጋር በነጻነት ለመነጋገር አጋጣሚ ካላገኛችሁ ደግሞ ሁሉን ከንቱ ታደርጋላችሁ። ስለዚህ ምቹ ስፍራ ካላችሁ፣ ከእያንዳንዱ ሰው ጋር በሌላ ክፍል ለብቻው ስትነጋገሩ ሌሎቹ በአንድ ክፍል ይቆዩ፤ ብቻ ነቀፋን ለማስወገድ ሴቶችን ሌሎች ሰዎች ባሉበት ብቻ ልናነጋግራቸው ይገባናል፤ በዚህም አንዳች ጥቅም ብናጣ መፍትሔ የለውም። ለክፉዎች የመንቀፊያ ምክንያት ሰጥቶ ሥራውን ሁሉ ከማፍረስ እንዲህ ማድረግ ይሻላል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሌሎች ሰዎች በክፍሉ ውስጥ ቢኖሩም፣ እነርሱ ሊሰሙት የማይገባቸው ነገር እንዳይሰሙት በዝግታ ድምፅ እንዲነገር ማዘጋጀት እንችላለን፤ ስለዚህ በክፍሉ እጅግ ሩቅ በሆነው ወገን ሊቀመጡ ይችላሉ፤ ወይም ቢያንስ እርስ በርሳቸው ይበልጥ የሚቀራረቡና አንዱ ሌላውን ለመንቀፍ የማይቸኩሉ የአንድ ቤተሰብ አባላት ብቻ ይገኙ። ከዚያም ቀጥተኛ ንግግራችሁ ይበልጥ ግልጽ መሠረት እንዲኖረው፣ መስማቱም በቀጥታ ያልተነገራቸው የሚመስሉትን በዚያ ያሉትን እንዲያነቃ፣ እጅግ በሚያነቃቁ ምርመራዎቻችሁና ተግሣጾቻችሁ ይልቁንም አላዋቂዎችን፣ ግድ የለሾችንና ክፉ አድራጊዎችን አጥብቃችሁ ያዙ። እነዚህ ትናንሽ ነገሮች ትንሽ ላልሆነ ሥራ የሚያገለግሉ ስለ ሆኑ ትኩረት ይገባቸዋል፤ ትናንሽ ስሕተቶችም እጅግ ብዙ መልካም ነገርን ሊያደናቅፉ ይችላሉ።
3. ሥራችሁን ከትምህርተ ሃይማኖቱ መጽሐፍ ቃላት ምን ያህል እንደ ተማሩ በመመርመርና ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልሳቸውን በመቀበል ጀምሩ፤ ከእርሱም ጥቂት ብቻ ሊደግሙ ወይም ምንም ሊደግሙ ካልቻሉ የሃይማኖት መግለጫውንና ዐሥርቱን ትእዛዛት በቃል ሊናገሩ ይችሉ እንደ ሆነ ሞክሩ።
4. ከዚያም እጅግ ክብደት ካላቸው ነጥቦች አንዳንዶቹን ምረጡ፤ በተጨማሪ ጥያቄዎችም ምን ያህል እንደሚያስተውሏቸው ፈትኑ። በዚህም የሚከተሉትን ነገሮች ጠብቁ፦
(1) እምብዛም አስፈላጊ ባልሆኑ ነጥቦች ሳይሆን ራሳቸው በቅርብ እንደሚመለከቷቸው ሊገነዘቡ በሚችሉት ነጥቦች ጀምሩ። ለምሳሌ፦ «ሰዎች ሲሞቱ ምን የሚሆኑ ይመስላችኋል? ከዓለም መጨረሻ በኋላ እኛ ምን እንሆናለን? ኃጢአት እንዳለባችሁ፣ ወይም በኃጢአት እንደ ተወለዳችሁ ታምናላችሁን? እያንዳንዱ ኃጢአት ምን ይገባዋል? እግዚአብሔር ኃጢአተኞችንና ጐስቋሎችን ነፍሳት ለማዳን ምን መፍትሔ አዘጋጀ? ስለ ኃጢአታችን በእኛ ፋንታ መከራ የተቀበለ አለን? ወይስ እኛ ራሳችን ስለ እነርሱ መከራ መቀበል አለብን? እግዚአብሔር ይቅር የሚላቸው እነማን ናቸው? በክርስቶስ ደምስ የሚድኑት እነማን ናቸው? በሚድኑት ሁሉ ላይ ምን ለውጥ መደረግ አለበት? ይህስ ለውጥ እንዴት ይፈጸማል? ዋናው ደስታችን በምን ላይ ነው? ልባችንስ ከሁሉ አብልጦ ሊያርፍበት የሚገባው በምን ላይ ነው?» እነዚህንና የመሳሰሉትን ሌሎች ጥያቄዎች ጠይቁ።
(2) በራሳቸው እጅግ ክብደት ስላላቸው ጉዳዮች ቢሆኑም እንኳ ረቂቅ ወይም አላስፈላጊ ወይም አጠራጣሪ ወይም እጅግ አስቸጋሪ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ተጠበቁ። አንዳንድ በራሳቸው የሚመኩ ሰዎች ራሳቸው ሊመልሷቸው በማይችሏቸው እንደዚህ ባሉ ጥያቄዎች ይጠመዳሉ፤ ሊመልሷቸው የማይችሉትንም ምስኪኖች ሰዎች ሕይወትና ሞት በእነርሱ ላይ የተመሠረተ ይመስል አጥብቀው ይነቅፋሉ።
ምናልባት «እግዚአብሔር ምንድር ነው?» ብላችሁ ትጠይቋቸው ይሆናል፤ ራሳችሁስ የምትሰጡት መልስ ምን ያህል ጐደሎ ይሆናል! እርሱ ምን እንደ ሆነ ከመናገር ይልቅ ምን እንዳልሆነ ፈጥናችሁ ልትናገሩ ትችላላችሁ። «ንስሐ ምንድር ነው? እምነትስ ምንድር ነው? የኃጢአት ይቅርታስ ምንድር ነው?» ብላችሁ ብትጠይቁ፣ ትክክለኛ መልስ ከማግኘታችሁ በፊት ስንቱን አገልጋይ ልትጠይቁ ትችላላችሁ! አለዚያማ በዚህ ነጥብ እንዲህ ባልተለያዩ ነበር። ዳግመኛ መወለድ ምንድር ነው፣ መቀደስ ምንድር ነው ብላችሁ ብትጠይቋቸውም እንዲሁ ነው። ነገር ግን ምናልባት «ሰዎች እግዚአብሔር ምን እንደ ሆነ፣ ንስሐ፣ እምነት፣ መለወጥ፣ መጽደቅና መቀደስ ምን እንደ ሆኑ ካላወቁ እንዴት እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊሆኑና ሊድኑ ይችላሉ?» ትሉ ይሆናል። እኔም እንዲህ እመልሳለሁ፤ ምን እንደ ሆኑ በትክክል ማወቅ አንድ ነገር ነው፤ በአጠቃላይና ግልጽ ባልሆነ እውቀትም ቢሆን ባሕርያቸውንና ውጤታቸውን ማወቅ ደግሞ ሌላ ነገር ነው፤ ደግሞም ይህ ወይም ያ ምን እንደ ሆነ ማወቅ አንድ ነገር ነው፤ መናገር ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ስሙ ራሱ በተለመደው አጠቃቀም ያለ ትርጓሜ ነገሩን ያመለክታቸዋል፤ ከእነርሱም ያስገልጠዋል፤ ስሙንም በሌላ ቃል ሊነግሯችሁ ባይችሉም የሚያመለክተውን በከፊል ያስተውላሉ፤ ንስሐ መግባት፣ ማመን፣ ይቅር መባል ምን እንደ ሆነ እንደሚያውቁ ማለት ነው። በንግግር ልማድ እነዚህ ምን ማለት እንደ ሆኑ ያውቃሉ፤ ነገር ግን ሊተረጕሟቸው አይችሉም፤ ምናልባትም በገጠሬው መልስ «ንስሐ መግባት ንስሐ መግባት ነው፤ ይቅር መባልም ይቅር መባል ነው» ብለው ያልፏችኋል፤ «ምሕረት ማግኘት ነው» ማለት ቢችሉ ግን መልካም ነው። ሆኖም እንደዚህ ያሉትን ጥያቄዎች ፈጽሞ እንዳትጠቀሙ አልከለክላችሁም፤ ነገር ግን በዚህ ነጥብ፣ በተለይም ስለ እግዚአብሔር ራሱ፣ ከባድ አለማወቅ እንዳለባቸው ብትጠራጠሩ በጥንቃቄ አድርጉት።
(3) የምትፈልጉትን እንዲያስተውሉ፣ የምትጠብቁትም ረቂቅ ትርጓሜ ሳይሆን ቀላል መልስ ብቻ መሆኑን እንዲገነዘቡ ጥያቄዎቻችሁን አዘጋጁ፤ ከቃላት ይልቅ ቁም ነገሩን ተመልከቱ፤ እንዲያውም ቀላል አዎን ወይም አይደለም እንዲሉ፣ ወይም ራሳችሁ ካቀረባችኋቸው ሁለት መግለጫዎች አንዱን ብቻ እንዲመርጡ ተዉላቸው። ለምሳሌ፦ «እግዚአብሔር ምንድር ነው? እንደ እኛ ከሥጋና ከደም የተሠራ ነውን? ወይስ የማይታይ መንፈስ ነው? እርሱ ሰው ነውን ወይስ አይደለም? መጀመሪያ ነበረውን? ሊሞት ይችላልን? እምነት ምንድር ነው? የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ማመን ነውን? በክርስቶስ ማመን ምን ማለት ነው? እውነተኛ ክርስቲያን ከመሆን ጋር አንድ ነውን? ወይስ ክርስቶስ የኃጢአተኞች አዳኝ መሆኑን ማመንና ይቅር እንዲላችሁ፣ እንዲቀድሳችሁ፣ እንዲገዛችሁና እንዲያከብራችሁ እንደ አዳኛችሁ በእርሱ መታመን ነውን? ንስሐ ምንድር ነው? ስለ ኃጢአት ማዘን ብቻ ነውን? ወይስ ከኃጢአት ወደ እግዚአብሔር የአእምሮ መለወጥና ኃጢአትን መተው ነው? ወይስ ሁለቱንም ያጠቃልላል?»
(4) የጥያቄያችሁን ትርጉም እንዳላስተዋሉ ስትገነዘቡ፣ በተመሳሳይ ወይም በሚያብራራ ጥያቄ መልሳቸውን ማውጣት አለባችሁ፤ ይህም ካልሠራ መልሱን በጥያቄያችሁ ውስጥ አድርጋችሁ አዎን ወይም አይደለም ብቻ እንዲመልሱ ጠይቁ። ብዙ ጊዜ አንዳንድ እጅግ አላዋቂ ሰዎችን «ይህን ያህል ብዙና ታላቅ የሆነው ኃጢአታችሁ እንዴት ይቅር ሊባል የሚችል ይመስላችኋል?» ብዬ ጠይቄአቸዋለሁ። እነርሱም «ንስሐ በመግባታችንና ሕይወታችንን በማስተካከላችን» ይሉኛል፤ ኢየሱስ ክርስቶስንም ፈጽሞ አይጠቅሱም። ደግሞም «ነገር ግን መታረማችሁ ላለፈው ኃጢአት ለእግዚአብሔር ካሳ ወይም እርካታ ሊያስገኝ የሚችል ይመስላችኋልን?» ብዬ እጠይቃቸዋለሁ። እነርሱም «እንዲህ ተስፋ እናደርጋለን፤ አለዚያ ምን እንደሚያስገኝ አናውቅም» ብለው ይመልሳሉ። እንግዲህ አንድ ሰው እነዚህ ሰዎች ክርስቶስን ስለማይጠቅሱት ስለ እርሱ ፈጽሞ እውቀት የላቸውም ብሎ ያስባል፤ አንዳንዶቹንም በእርግጥ ስለ እርሱ ምንም እውቀት የሌላቸው ሆነው አገኛቸዋለሁ፤ የክርስቶስን ታሪክ፣ እርሱም ማን እንደ ሆነ፣ ምን እንዳደረገና ምን መከራ እንደ ተቀበለ ስነግራቸው እንደ እንግዳ ነገር ተደንቀው ይቆማሉ፤ አንዳንዶቹም በየጌታ ቀኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን ቢመጡም ይህን ያህል ከዚህ በፊት ሰምተው ወይም አውቀው እንደማያውቁ ይናገራሉ። ሌሎች ግን፣ እንደ ተገነዘብሁት፣ የጥያቄዬን ዓላማ ስላላስተዋሉ እንዲህ ያለ መልስ ይሰጣሉ፤ የክርስቶስን ሞት እንደ ታወቀ ነገር ወስጄ «ከክርስቶስ በታች የእናንተ ድርሻ ሆኖ ለእግዚአብሔር ካሳ የሚያስገኘው ምንድር ነው?» ብቻ ብዬ የምጠይቃቸው ይመስላቸዋል – ምንም እንኳ በዚህም አሳዛኝ አለማወቅን ቢገልጡም። «መልካም ሥራችሁ ከእግዚአብሔር ዘንድ አንዳች ነገር ሊያስገኝላችሁ ይችላልን?» ብዬ ስጠይቃቸው «አይችልም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እንደሚቀበለው ተስፋ እናደርጋለን» ብለው ይመልሳሉ። ደግሞም «ያለ ክርስቶስ ሞት ልትድኑ ትችላላችሁን?» ብዬ ብጠይቅ «አንችልም» ይላሉ። ደግሞም አብልጬ «እርሱ ስለ እናንተ ምን አደረገ? ምንስ መከራ ተቀበለ?» ብዬ ብጠይቅ «ስለ እኛ ሞተ፤ ወይም ስለ እኛ ደሙን አፈሰሰ» ይላሉ፤ ለመዳንም መታመናቸውን በዚያ ላይ እንዳደረጉ ይመሰክራሉ። ብዙ ሰዎች ለመነገር ገና ያልበሰለ ነገር በአእምሮአቸው አለ፤ ጐደሎ በሆነ አስተዳደግና ባለመለማመድ ምክንያት በተወሰነ መጠን የሚያስተውሏቸውን ነገሮች መግለጽ ለእነርሱ እንግዳ ነው። በዚህም አጋጣሚ፣ ለመማር ዝግጁና ታዛዦች ከሆኑ፣ መንገዶቹንም ለመጠቀም ፈቃደኞች ከሆኑ፣ ተራውን ሕዝብ በእውቀት ጉዳይና በአገላለጽ ጉድለት እጅግ በርኅራኄ ልትይዙት የሚገባችሁ ለምን እንደ ሆነ እዚህ ልታዩ ትችላላችሁ፤ ብዙዎች፣ ያረጁ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች እንኳ፣ ራሳቸውን በሚገባ ትክክለኛነት መግለጽ አይችሉምና፤ አገላለጾች በአፋቸው ሲደረጉላቸውም ሊማሯቸው አይችሉም። ከማውቃቸው እጅግ ቀናተኛ፣ ልምድ ያላቸውና የተመሰከረላቸው ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ (ሽማግሌዎች) የትምህርተ ሃይማኖቱን መጽሐፍ ቃላት መማር እንደማይችሉ በእንባ ያማርሩልኛል፤ ያገኙትንም ዕድል ሳስብ – ለአርባ፣ ለሃምሳ ወይም ለስድሳ ዓመታት ያለማቋረጥ በዘወትር ተግባርና በምርጥ ኅብረት እጅግ ግሩም የሆኑ እርዳታዎችን ማግኘታቸውን – ይህ እንዲህ ያለውን ኅብረትና ግንኙነት ለአንድ ዓመት ወይም ለአንድ ሳምንት እንኳ አግኝተው የማያውቁትን ምስኪን አላዋቂዎች ምን እንደምጠብቅባቸው ያስተምረኛል፤ አንዳንድ ግለኞችና ከልክ በላይ የወጡ ሃይማኖተኛ ነን ባዮች እንደሚፈልጉት ቶሎ እንዳንጥላቸውም ያስተምረኛል።
(5) ግራ እንደ ተጋቡና ጥያቄዎቻችሁን መመለስ እንዳልቻሉ ብታገኙ፣ ልታደናግሯቸውና ልታዋርዷቸው ብቻ እንደምታስቡ እንዳይገምቱ ጥያቄን በጥያቄ ላይ እያከታተላችሁ እጅግ አታጣድፏቸው፤ ብዙም አታቆዩአቸው፤ ነገር ግን መመለስ እንዳልቻሉ ስትገነዘቡ ራሳችሁ ጣልቃ ገብታችሁ ሸክሙን ከእነርሱ አንሡ፤ ጥያቄውንም ራሳችሁ መልሱ፤ በሚገባና በግልጽ አድርጉት፤ ከእነርሱም ሳትለዩ በትምህርታችሁ እንዲያስተውሉት እውነቱን ሁሉ በሙሉ አብራሩላቸው። በዚህም ጉዳዩን ከመጀመሪያው አንሥታችሁ በሥርዓት እያቀረባችሁ ወደ ተጠየቀው ነጥብ እስክትደርሱ ድረስ መሄድ ብዙ ጊዜ አስፈላጊ ነው።
5. እውቀታቸውን በመፈተን ረገድ ተገቢ ሆኖ ያያችሁትን ካደረጋችሁ በኋላ፣ ቀጥሎ ራሳችሁ ልታስተምሯቸው ተነሡ፤ ይህም እንደየአቅማቸው መሆን አለበት። የሃይማኖትን መሠረታውያን ትምህርቶች የሚያስተውል ሃይማኖተኛ ሰው ቢሆን፣ ይበልጥ እንደሚያስፈልገው ያስተዋላችሁትን ነገር ያዙ፤ ይኸውም አንዳንድ የወንጌልን ምሥጢራት አብልጣችሁ በማብራራት፣ ወይም ሊጠራጠረው የሚችለውን የአንድ ተግባር መሠረት በማስቀመጥ፣ ወይም ቸል የሚለውን ነገር አስፈላጊነት በማሳየት፣ ወይም ኃጢአቶቹንና ስሕተቶቹን በመጠቆም፣ ይበልጥ በሚያሳምነውና በሚያንጸው መንገድ አድርጉ። በሌላ በኩል ግን እጅግ አላዋቂ ሰው ቢሆን የክርስትናን ሃይማኖት ድምር በጥቂት ቃላት ግልጽና የተለመደ በሆነ አነጋገር ንገሩት፤ በትምህርተ ሃይማኖቱ መጽሐፍ ውስጥ ቀድሞውኑ ቢኖርም ይበልጥ የተለመደ አቀራረብ እንዲያስተውለው ይበልጥ ሊረዳው ይችላልና። እንዲህ፦ «ማወቅ ያለባችሁ ነገር፣ ከዘላለም ጀምሮ መጀመሪያ የሌለው መጨረሻም የማይኖረው አንድ አምላክ እንደ ነበረ ነው፤ እርሱም እንደ እኛ አካል ያለው ሳይሆን ሁሉን የሚያውቅ፣ ሁሉንም የሚችል፣ ቸርነትንና ብፅዕናንም ሁሉ በራሱ የያዘ እጅግ ንጹሕ መንፈሳዊ ህላዌ ነው። ይህ አምላክ አንድ ብቻ ነው፤ ነገር ግን ከማስተዋላችን በላይ በሆነ ሁኔታ ሦስት አካላት ነው፤ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ። ደግሞም ይህ አንድ አምላክ ዓለምን ሁሉ በቃሉ እንደ ፈጠረ ማወቅ አለባችሁ፤ ሰማያትን የክብሩ ስፍራ እንዲሆኑ፣ የቅዱሳን መላእክትንም ብዛት እንዲያገለግሉት ፈጠረ። ነገር ግን ከእነዚህ አንዳንዶቹ በትዕቢት ወይም በሌላ ኃጢአት ከከፍተኛ ማዕረጋቸው ወደቁ፤ አጋንንትም ሆኑ፤ ለዘላለምም ጐስቋሎች ይሆናሉ። ምድርን ከፈጠረ በኋላ በዚህ በታች ካሉት ፍጥረታቱ ሁሉ እጅግ የከበረ አድርጎ ሰውን ፈጠረ፤ ይኸውም አንድ ወንድና አንዲት ሴት፣ አዳምና ሔዋን ናቸው፤ ያለ አንዳች ኃጢአት ፍጹማን አድርጎ ፈጠራቸው፤ በዔድን ገነትም አኖራቸው፤ በገነቱም ካለው ከአንድ ዛፍ እንዳይበሉ ከለከላቸው፤ ከእርሱም ቢበሉ እንደሚሞቱ ነገራቸው። ነገር ግን ቀድሞ ራሱ የወደቀው ዲያብሎስ ኃጢአት እንዲሠሩ ፈተናቸው፤ እነርሱም ለፈተናው ተሸነፉ፤ በዚህም ከእግዚአብሔር ሕግ እርግማን በታች ወደቁ። ነገር ግን እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ጥበቡና ምሕረቱ የገዛ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛቸው እንዲሆን ላከ፤ እርሱም ዘመኑ በተፈጸመ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከድንግል ተወልዶ ሰው ሆነ፤ በምድርም በአይሁድ መካከል ሠላሳ ሦስት ዓመት ያህል ኖረ፤ በዚያም ዘመን ራሱ ወንጌልን ሰበከ፤ ትምህርቱንም ለማረጋገጥ ብዙ ተአምራትን አደረገ፤ አንካሶችን፣ ዕውሮችንና ድውያንን በመለኮታዊ ኃይሉ ፈወሰ፤ ሙታንንም አስነሣ፤ በመጨረሻም እኛ ልንሸከመው የሚገባንን ያንን እርግማን ይሸከም ዘንድ ስለ ኃጢአታችን መሥዋዕት ሆኖ በመስቀል ላይ ቀረበ።
«አሁንም ኃጢአተኞች በእርሱ ቢያምኑና ከኃጢአታቸው ንስሐ ቢገቡ ያለፈውን ሁሉ በነጻ ይቅር ይላቸዋል፤ የረከሰውንም ባሕርያቸውን ይቀድሳል፤ በመጨረሻም ወደ ሰማያዊ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ያመጣቸዋል። ኃጢአታቸውንና ምሕረቱን ቢያቃልሉ ግን በገሃነም ወደ ዘላለም ጐስቁልና ይፈርድባቸዋል። ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ከተነሣ በኋላ ይህን ወንጌል ለዓለም ሁሉ እንዲሰብኩ አገልጋዮቹን ሾመ፤ ይህንንም ለሐዋርያቱ ሁሉ አደራ ከሰጠ በኋላ በዓይናቸው ፊት ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በዚያም አሁን በእኛ ባሕርይ ከእግዚአብሔር አብ ጋር በክብር አለ። በዚህም ዓለም መጨረሻ በእኛ ባሕርይ ዳግመኛ ይመጣል፤ ሙታንንም ወደ ሕይወት ያስነሣል፤ ሁሉንም በፊቱ ያቀርባቸዋል፤ ይህም እያንዳንዱ ‹በሥጋው የተሠራውን›፣ ‹መልካም ቢሆን ወይም ክፉ›፣ ሁሉ መልስ ይሰጥበት ዘንድ ነው። ስለዚህ ልትድኑ ብትፈልጉ ከሚመጣው ቍጣ ብቸኛ አዳኝ እንደ ሆነ በክርስቶስ ማመን አለባችሁ፤ ከኃጢአታችሁ ንስሐ መግባት አለባችሁ፤ በአጭሩ ፈጽሞ አዲስ ፍጥረት መሆን አለባችሁ፤ አለዚያ መዳን አይኖርላችሁም።» ከሃይማኖት መሠረታውያን ትምህርቶች እንዲህ ያለ አጭር ማጠቃለያ፣ ልታስቡት በምትችሉት እጅግ በተለመደ አቀራረብ፣ በመጨረሻም በአጭር የተግባር ማሳሰቢያ፣ እጅግ አላዋቂ ከሆኑት ጋር ስትሠሩ አስፈላጊ ይሆናል። እንዳላስተዋሏችሁ ብትገነዘቡ ደግማችሁ አስረዷቸው፤ እንደ አስተዋሉትም ጠይቋቸው፤ በትዝታቸውም ውስጥ እንዲጸና ለማድረግ ሞክሩ።
6. ድንቁርናቸው የከፋ ይሁን አይሁን፣ ገና ያልተለወጡ መሆናቸውን ከጠረጠራችሁ፣ ቀጥሎ ስለ ሁኔታቸው በጥበብ ለመጠየቅ ሞክሩ። ይህን ለማድረግ ከሁሉ የተሻለውና አነስተኛ ቅሬታ የሚያስከትለው መንገድ፣ ልባቸውን የሚያለዝብና የጥያቄውን አስፈላጊነት የሚያሳምናቸው አንዳች ነገር በመናገር ለጥያቄው ማዘጋጀት፣ ከዚያም ከትምህርተ ሃይማኖቱ አንዱን አንቀጽ ምክንያት አድርጎ ሕሊናቸውን መንካት ነው። ለምሳሌ፦ «መንፈስ ቅዱስ በቃሉ አማካይነት የሰዎችን አእምሮ እንደሚያበራ፣ ልባቸውንም እንደሚያለሰልስና እንደሚከፍት፣ በክርስቶስ በማመንም ከሰይጣን ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር እንደሚመልሳቸው፣ ‹ገንዘቡ የሚሆንን ሕዝብ ለራሱ እንደሚያነጻቸው›፣ ከእነዚህም በቀር ማንም የዘላለም ሕይወት ተካፋይ እንደማይሆን ታያላችሁ። የማንንም ሰው ምሥጢር ያለ አስፈላጊነት ለመመርመር ፍላጎት ባይኖረኝም፣ በመዳን ጉዳይ ለሕዝባቸው ምክር መስጠት የመጋቢዎች ሥራ ስለ ሆነ፣ የዘላለም ሕይወትን ወይም የዘላለም ሞትን በሚመለከቱ ነጥቦች መሳሳትም እጅግ አደገኛ ነገር ስለ ሆነ፣ በቅንነት እንድትመላለሱ፣ ይህን ታላቅ ለውጥ በገዛ ልባችሁ ላይ አግኝታችሁት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነም እንድትነግሩኝ እለምናችኋለሁ። የእግዚአብሔር መንፈስ በቃሉ አማካይነት አዲስ ፍጥረት ካደረጋችሁ አዲስና ሰማያዊ ሕይወት ጋር ወደ ማስተዋላችሁ ሲገባ አግኝታችሁ ታውቃላችሁን? ልባችሁን የሚያየው ጌታ እንዲህ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ያውቃል፤ ስለዚህ እውነትን እንድትናገሩ እለምናችኋለሁ።» ተለውጦአል ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ – ሁሉም ኃጢአተኞች ናቸው – ነገር ግን ስለ ኃጢአቱ እንደሚያዝን፣ ወይም ይህን የመሰለ ነገር ቢነግራችሁ፣ ከእውነተኛ መለወጥ ግልጽ ምልክቶች አንዳንዶቹን በጥቂት ቃላት በዝርዝር ንገሩት፤ በዚህም ጥያቄውን አድሱ፤ አጽኑትም፤ እንዲህም በሉት፦ «መዳናችሁ ወይም ፍርዳችሁ በዚህ ላይ የተመሠረተ ስለ ሆነ፣ እንደዚህ ባለ ታላቅ ጉዳይ እንዳትሳሳቱ፣ ነገር ግን ጊዜው ሳይረፍድ እውነቱን እንድታገኙ በዚህ ነገር ጥቂት ልረዳችሁ እወዳለሁ፤ እግዚአብሔር ያለ አድልዎ እንደሚፈርድብን ሁሉ፣ ራሳችንን የምንፈርድበት ቃሉም በፊታችን አለ፤ ይህ ቃል ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚሄዱት እነማን፣ ወደ ሲኦልም የሚሄዱት እነማን እንደ ሆኑ በእርግጥ ይነግረናልና። እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ ያልተለወጠ ሰው ሁኔታ ይህ እንደ ሆነ ይነግረናል፦ ልቡን ከዚህ ከአሁኑ ዓለም ወደዚያ ሊስብ የሚችል ታላቅ ደስታ በሚመጣው ሕይወት በእግዚአብሔር ፍቅርና ኅብረት ውስጥ አያይም፤ ነገር ግን ለሥጋዊ ማንነቱ ወይም ለሥጋ ይኖራል፤ የሕይወቱም ዋነኛ ዝንባሌ በምድር ላይ መልካም እንዲሆንለት ነው፤ ያለውም ሃይማኖት ዓለምን ከዚህ በላይ መያዝ በማይችልበት ጊዜ እንዳይኰነን ብቻ በጎን የያዘው ጥቂት ነገር ነው፤ ስለዚህ ዓለምና ሥጋ በእርሱ ዘንድ ከሁሉ በላይ የተከበሩና ለልቡ የቀረቡ ናቸው፤ እግዚአብሔርና ክብርም ከእነርሱ በታች ናቸው፤ ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡትም አገልግሎት ሁሉ ዓለምና ሥጋ ሊያተርፉት የሚችሉትን ለእርሱ መስጠት ብቻ ነው። የማንኛውም ያልተለወጠ ሰው ሁኔታ ይህ ነው፤ በዚህ ሁኔታ ያሉ ሁሉ በጕስቍልና ውስጥ ናቸው። በእውነት የተለወጠ ሰው ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ነፍሱ የበራ ብርሃን አግኝቶአል፤ ይህ ብርሃን የኃጢአቱንና የጕስቍልናውን ታላቅነት አሳይቶታል፤ በነፍሱም ላይ ከባድ ሸክም አድርጎበታል፤ ክርስቶስ ማን እንደ ሆነ፣ ለኃጢአተኞችም ምን እንዳደረገ አሳይቶታል፤ በእርሱ ላይ የተገለጠውንም የእግዚአብሔርን የጸጋ ባለጠግነት እንዲያደንቅ አድርጎታል። ኦ፣ እንደ እርሱ ላሉ ለጠፉ ኃጢአተኞች ገና ተስፋ መኖሩ፣ ይህን ያህል ብዙና ታላላቅ ኃጢአቶች ይቅር ሊባሉ መቻላቸው፣ ይቅርታም ለሚቀበሉት ሁሉ መቅረቡ ለእርሱ እንዴት ያለ የምሥራች ነው! ይህን መልእክትና ይህን ግብዣ በምን ያህል ደስታ ይቀበላል! ከዚህም በኋላ ፈጽሞ የክርስቶስ ሊሆን፣ እርሱ ቃል ወደ ገባው ዘላለማዊ ክብር ለመድረስም በእርሱ ፈቃድ ሊመራ ራሱንና ያለውን ሁሉ ለክርስቶስ ያስረክባል። አሁን በክብር ያሉ ቅዱሳንን የተባረከ ሁኔታ እንዲህ አድርጎ ስለሚያይ፣ ከእርሱ ጋር ሲያነጻጽረው ይህን ዓለም ሁሉ እንደ ጉድፍና እንደ ፋንድያ ይንቀዋል፤ ደስታውንና ተስፋውን በዚያ ያከማቻል፤ የዚህንም ሕይወት ጉዳዮች ሁሉ ወደዚያ በሚወስደው መንገድ ላይ እንደ ረዳቶች ወይም እንደ እንቅፋቶች ብቻ ይቈጥራቸዋል፤ ስለዚህ የሕይወቱ ዋነኛ ጥንቃቄና ሥራ በሚመጣው ሕይወት ብፁዕ መሆን ነው። በእውነት የተለወጡና የሚድኑ ሁሉ ሁኔታ ይህ ነው። እንግዲህ የእናንተ ሁኔታ ይህ ነውን ወይስ አይደለም? እንደዚህ ያለውን ለውጥ በነፍሳችሁ ላይ ተመልክታችኋልን?»
ተለውጫለሁ ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ቢናገር፣ ወደ አንዳንድ ዝርዝር ነገሮች ውረዱ፤ እንዲህም በሉት፦ «እንግዲያው እነዚህን ሁለት ወይም ሦስት ጥያቄዎች እንድትመልሱልኝ እለምናችኋለሁ።
(1) ያለፈው ሕይወታችሁ የታወቁ ኃጢአቶች ሁሉ የልባችሁ ኀዘን እንደ ሆኑ፣ ስለ እነርሱም የዘላለም ጕስቍልና እንደሚገባችሁ እንደ ተሰማችሁ፣ ከዚህም ከባድ ሸክም የተነሣ የጠፋችሁ ሰው መሆናችሁ እንደ ተሰማችሁ፣ የአዳኝንም ዜና በደስታ እንደ ተቀበላችሁ፣ በደሙም ይቅርታን ለማግኘት ነፍሳችሁን በክርስቶስ ብቻ ላይ እንደ ጣላችሁ በእውነት ልትናገሩ ትችላላችሁን?
(2) ልባችሁ ከኃጢአት እስከዚህ ድረስ እንደ ተመለሰ፣ በአንድ ወቅት የወደዳችኋቸውን ኃጢአቶች እንደምትጠሉ፣ ቀድሞ ያልፈለጋችሁትንም ቅዱስ ሕይወት እንደምትወዱ፣ አሁንም በማንኛውም የታወቀ ኃጢአት ሆን ብላችሁ እንደማትኖሩ በእውነት ልትናገሩ ትችላላችሁን? ምንም ዋጋ ቢያስከፍላችሁ ከልባችሁ ልትተዉት የማትፈቅዱት ኃጢአት፣ ልትፈጽሙትም የማትፈቅዱት ተግባር የለምን?
(3) በእግዚአብሔር ለዘላለም መደሰትን ደስታችሁ አድርጋችሁ እስከዚህ ድረስ እንደ ተቀበላችሁ፣ ከልባችሁ፣ ከፍቅራችሁ፣ ከምኞታችሁና ከጥንቃቄያችሁ የሚበልጠውን ድርሻ እንደ ያዘ፣ እርሱን አደጋ ላይ ከመጣል ይልቅ በመለኮታዊ ጸጋ ኃይል በዓለም ያላችሁን ሁሉ ለመተው እንደ ቈረጣችሁ፣ እርሱንም መፈለግ የዕለት ተዕለትና ዋነኛ ሥራችሁ እንደ ሆነ በእውነት ልትናገሩ ትችላላችሁን? ድካምና ኃጢአት ቢኖርባችሁም፣ ዋነኛ ጥንቃቄያችሁና የመላ ሕይወታችሁ ዝንባሌ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘትና ለዘላለም በእርሱ መደሰት እንደ ሆነ፣ ለዓለም የእግዚአብሔርን ትርፍራፊ እንደምትሰጡ እንጂ ለእግዚአብሔር የዓለምን ትርፍራፊ እንደማትሰጡ፣ ዓለማዊ ሥራችሁም መንገደኛ በጕዞው ስንቅ እንደሚፈልግ ያለ ብቻ እንደ ሆነ፣ መንግሥተ ሰማያትም ቤታችሁ አድርጋችሁ የምትቈጥሩት ስፍራ እንደ ሆነ በእውነት ልትናገሩ ትችላላችሁን?»
ለእነዚህ ጥያቄዎች አዎን ብሎ ቢመልስ፣ የሰው ልብ ኃጢአቱን መጸየፉ፣ ደስታውንም ያለ ግብዝነት በሌላው ዓለም ማከማቸቱ፣ ከዓይን ለተሰወረው ለሌላው ዓለም ሲል በዚህ ዓለም መኖሩ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንደ ሆነ ንገሩት፤ ስለዚህም በእርግጥ እንዲሁ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ለምኑት። ከዚያም እርሱ ቸል ይላቸዋል ብላችሁ አብልጣችሁ የምትጠረጥሯቸውን ተግባራት ወደሚመለከቱ ወደ አንዳንዶቹ የትምህርተ ሃይማኖቱ አንቀጾች ተመለሱ፤ እንዲህ ያለውን ወይም እንዲያ ያለውን ተግባር ይፈጽም እንደ ሆነ ጠይቁት፤ ለምሳሌ በቤተሰቡ ውስጥ ወይም በግሉ መጸለዩን፣ የጌታንም ቀን በቅድስና ማሳለፉን።
ይሁን እንጂ ከምትመለከቷቸው ሰዎች በማንኛውም ላይ የችኰላ ወይም ፍጹም ፍርድ እንዳትሰጡ እጅግ እንድትጠነቀቁ እመክራችኋለሁ፤ ምክንያቱም ብዙዎች እንደሚያስቡት አንድ ሰው በእርግጥ ጸጋ የሌለው መሆኑን መለየት ቀላል ነገር አይደለም፤ በእጃችሁ ያለውንም ሥራ እንዲህ ባለ ፍጹም ድምዳሜ ልትሠሩት እንደምትችሉ ሁሉ ያለ እርሱም በሚገባ ልትሠሩት ትችላላችሁ።
7. ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የከፋ ድንቁርናው በመገለጡ፣ ወይም በእነዚህ በኋለኞቹ ስለ መንፈሳዊ ሁኔታው በተደረጉ ጥያቄዎች፣ ሰውዬው ገና ባልተለወጠ ሁኔታ ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ምልክት ካያችሁ፣ ቀጣዩ ሥራችሁ ልቡ ሁኔታውን እንዲገነዘብ ለማድረግ ችሎታችሁን ሁሉ መጠቀም ነው። ለምሳሌ፦ «ወዳጆቼ ሆይ፣ በእውነት ሁኔታችሁን ካለው የባሰ ለማድረግ ወይም ያለ ምክንያት ፍርሃትንና ጭንቀትን ላመጣባችሁ ፍላጎት እንደሌለኝ ጌታ ያውቃል፤ ነገር ግን ብሸነግላችሁና እውነቱን ባልነግራችሁ፣ ከዳተኛ ጠላት እንጂ ታማኝ መጋቢ እንዳልሆንሁ አድርጋችሁ እንደምትቈጥሩኝ እገምታለሁ። በሕመማችሁ ጊዜ ወደ ሐኪም ብትሄዱ፣ ከሁሉ የከፋ ቢሆንም እንኳ እውነቱን እንዲነግራችሁ ትፈልጋላችሁ። በዚህ ጉዳይማ ከዚያ እጅግ ይልቅ! በዚያ በሽታችሁን ማወቃችሁ ከፍርሃታችሁ የተነሣ ሊያባብሰው ይችላል፤ እዚህ ግን ልታውቁት ይገባል፤ ያለዚያ ፈጽሞ ልትፈወሱ አትችሉም። ገና ለክርስቲያናዊ ሕይወት እንግዳ እንደ ሆናችሁ እጅግ እፈራለሁ። በእርግጥ ክርስቲያን ብትሆኑና በእውነት ብትለወጡ ኖሮ፣ ልባችሁ ራሱ በእግዚአብሔርና በሚመጣው ሕይወት ላይ ባረፈ ነበር፤ ለዘላለማዊ ደስታ መዘጋጀትንም ዋነኛ ሥራችሁ ባደረጋችሁ ነበር፤ ሆን ተብሎ በሚደረግ በማንኛውም ኃጢአት ወይም የታወቀን ተግባር ቸል በማለት ለመኖር ባልደፈራችሁ፣ ባልፈቀዳችሁም ነበር።
«ወዮ! ምን አደረጋችሁ? እስከ አሁን ጊዜያችሁን እንዴት አሳለፋችሁ? የምትድን ወይም የምትጠፋ ነፍስ እንዳለቻችሁ፣ በመንግሥተ ሰማያት ወይም በሲኦል ለዘላለም መኖር እንዳለባችሁ፣ በዚህ ዓለም ሕይወታችሁንና ጊዜያችሁን ያገኛችሁት በዋነኛነት ለሌላው ዓለም ለመዘጋጀት እንደ ሆነ አታውቁም ነበርን? ወዮ! ሞት አሁን ቢያገኛችሁ እንዲህ ያላወቃችሁና ያልተዘጋጃችሁ ሆናችሁ የምትገኙት በዘመናችሁ ሁሉ ምን ስታደርጉ ነበር? ለምድር ያላችሁን ያህል ለመንግሥተ ሰማያት ሐሳብ ቢኖራችሁ ኖሮ፣ ካደረጋችሁት ይልቅ ስለ እርሱ የበለጠ ባወቃችሁ፣ ለእርሱም የበለጠ ባደረጋችሁ፣ በበለጠ ትጋትም በፈለጋችሁት ነበር። በዓለም ያለውን ሥራችሁን እንዴት እንደምትሠሩ መማር ትችላላችሁ፤ ታዲያ ብትከታተሉት ኖሮ ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ የበለጠ ለምን መማር ባልቻላችሁም ነበር? እንደ እናንተ በዓለም ብዙ ሥራ የነበራቸው፣ እንደ እናንተም ጥቂት ጊዜ የነበራቸው፣ ሆኖም የበለጠ መማር የቻሉ ጎረቤቶች አሏችሁ። መንግሥተ ሰማያት ድካማችሁ አይገባውም ብላችሁ ታስባላችሁን? ወይስ የዚህን ዓለም ጥቃቅን ነገሮች ያለ ጥንቃቄና ድካም ማግኘት ሳትችሉ፣ እግዚአብሔርም ‹አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ› ብሎ አዝዞአችሁ ሳለ፣ መንግሥተ ሰማያት ያለ አንዳች ጥንቃቄና ድካም ሊገኝ ይችላል ብላችሁ ታስባላችሁን? ወዮ! ወዳጆቼ ሆይ፣ ከዚህ ሰዓት በፊት ባልተለወጠ ሁኔታ ብትሞቱ ኖሮስ? ያን ጊዜ ምን በሆናችሁ ነበር? አሁንስ የት በነበራችሁ? ወዮ! ዘላለማዊ ሁኔታችሁን እስከ አሁን እንዳደረጋችሁት እንዲህ ተስፋ በሚያስቆርጥ ግዴለሽነት አደጋ ላይ እስክትጥሉት ድረስ በራሳችሁ ላይ ጨካኞች መሆናችሁ! ምን እያሰባችሁ ነበር? በቅርቡ እንደምትሞቱ፣ በዚያን ጊዜም በተገኛችሁበት ሁኔታ እንደምትፈረዱ በዚህ ሁሉ ጊዜ አታውቁም ነበርን? ከዘላለማዊ መዳናችሁ የሚበልጥ የምትሠሩት ሥራ ወይም የምታስቡበት ጉዳይ ነበራችሁን? በዚህ ዓለም ልታገኙት የምትችሉት ሁሉ በሞት ሰዓት የሚያጽናናችሁ፣ ወይም መዳናችሁን የሚገዛላችሁ፣ ወይም የሲኦልን ሥቃይ የሚያቀልላችሁ ይመስላችኋልን?»
እነዚህን ነገሮች በተለየ ትጋት ወደ ልቡ አስገቡ፤ ወደ ልብ ካልደረሳችሁ የምትሠሩት ጥቂት ነው ወይም ምንም አይደለም፤ ልብን የማይነካም ነገር ፈጥኖ ይረሳል።
8. ሁሉንም በተግባራዊ ምክር ደምድሙ፤ ይህ ምክር ሁለት ነገሮችን መያዝ አለበት፦ አንደኛ፣ በክርስቶስ የማመንን ግዴታ፤ ሁለተኛ፣ ከዚህ በኋላ የውጭ የጸጋ መንገዶችን የመጠቀምንና የቀድሞ ኃጢአቶችን የማስወገድን ግዴታ። ለምሳሌ፦ «ወዳጄ ሆይ፣ እንዲህ ባለ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ስላገኘኋችሁ ከልቤ አዝናለሁ፤ ነገር ግን በዚያው ውስጥ ብተዋችሁ ይበልጥ ባዘንሁ ነበር፤ ስለዚህ ስለ ጌታ ብላችሁ፣ ስለ ራሳችሁም ብላችሁ፣ ከዚህ በኋላ ስላለው ጊዜ የምነግራችሁን ልብ እንድትሉ ልለምናችሁ። ጌታ ባልተለወጠ ሁኔታችሁ ሳላችሁ ያልቈረጣችሁ መሆኑ፣ ገና ሕይወትና ጊዜ ያላችሁ መሆኑ፣ በክርስቶስ ደም መድኃኒት የተዘጋጀላችሁ መሆኑ፣ ይቅርታና ቅድስና የዘላለምም ሕይወት ለሌሎች እንደ ቀረበ ለእናንተም መቅረቡ ከታላቁ ምሕረቱ የተነሣ ነው። እግዚአብሔር ለአጋንንት እንዳደረገው ኃጢአተኛውን ሰው ለፍጹም ጥፋት አልተወውም፤ በይቅርታና በዘላለም ሕይወት ግብዣውም ከሌላ ከማንም ይልቅ እናንተን ለይቶ አላገለለም።
«ገና ስለ ኃጢአት የሚደማ ልብ ቢኖራችሁ፣ ለመታደስም በእምነት ወደ ክርስቶስ ብትመጡ፣ አዳኛችሁና ጌታችሁ እንዲሆን ራሳችሁን ለእርሱ ብታስረክቡ፣ ከዚህም በኋላ አዲስ ሰው ልትሆኑ ብትፈቅዱ፣ ጌታ ኃጢአታችሁን ይቅር በማለትና ነፍሳችሁን ለዘላለም በማዳን ይምራችኋል። ደግሞም እንዲህ ያለውን ልብ መስጠት የእግዚአብሔር ጸጋ ታላቅ ሥራ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ይቅር ሊላችሁና ሊያድናችሁ ካሰበ ይህን ለውጥ በእናንተ ላይ እንደሚያደርግ ልነግራችሁ ይገባኛል፤ ኃጢአታችሁ በዓለም ካሉ ሸክሞች ሁሉ እጅግ የከበደ ሸክም፣ በራሱ ከሁሉ ይልቅ የሚያስጸይፍ፣ ለቍጣውና ለመርገሙም ያጋለጣችሁ ነገር ሆኖ እንዲሰማችሁ ያደርጋል፤ የጠፋችሁ ሰው መሆናችሁን፣ በክርስቶስ ደም ይቅር ካልተባላችሁና በመንፈሱ ካልተቀደሳችሁም ከዘላለም ፍርድ በቀር ሌላ ዕጣ እንደሌላችሁ እንድታዩ ያደርጋል፤ ክርስቶስ ምን ያህል እንደሚያስፈልጋችሁ፣ ተስፋችሁና ሕይወታችሁ ሁሉ በእርሱ እንደ ሆነ እንድታዩ ያደርጋል፤ የዚህን ዓለምና ሊሰጣችሁ የሚችለውን ሁሉ ከንቱነት፣ ደስታችሁም ሁሉ ከቅዱሳንና ከመላእክት ጋር ክብሩን ልታዩበት፣ በፍቅሩ ልትኖሩበት፣ በምስጋናውም ልትሰማሩበት በምትችሉበት በዚያ በሰማይ ባለው የዘላለም ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር እንደ ሆነ እንድታዩ ያደርጋል። ይህ ሥራ በእናንተ ላይ እስኪፈጸም ድረስ ጐስቋላ ሰው እንደ ሆናችሁ ልንገራችሁ፤ ሳይፈጸምም ብትሞቱ ለዘላለም ጠፍታችኋል። አሁን ተስፋና ርዳታ በፊታችሁ አለ፤ ያን ጊዜ ግን ምንም አይኖርም።
«ስለዚህ ነፍሳችሁን የምትወዱ ከሆነ እለምናችኋለሁ፤ አንደኛ፣ አሁን ባላችሁበት ሁኔታ እንዳታርፉ። የሚያድን ለውጥ በልባችሁ እስኪደረግ ድረስ በአእምሮአችሁ አትረጋጉ። ጠዋት ስትነሡ እንዲህ ብላችሁ አስቡ፦ ኦ፣ ይህ ቀን የመጨረሻዬ ቢሆንስ፣ ሞትም ባልታደሰ ሁኔታ ቢያገኘኝስ? በሥራችሁ ላይ ሳላችሁ እንዲህ ብላችሁ አስቡ፦ ኦ፣ ነፍሴን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅና በመንፈሱ እንድትቀደስ ለማድረግ ገና የሚቀረኝ ሥራ ምን ያህል የሚበልጥ ነው! ስትበሉ ወይም ስትጠጡ ወይም በዓለም ያላችሁን ማንኛውንም ነገር ስትመለከቱ እንዲህ ብላችሁ አስቡ፦ የእግዚአብሔር ጠላት፣ ለክርስቶስና ለመንፈሱም እንግዳ ሆኜ ብኖርና ብሞት፣ እንዲሁም ለዘላለም ብጠፋ ይህ ሁሉ ምን ይጠቅመኛል? ነፍሳችሁ እስክትለወጥ ድረስ እነዚህ ሐሳቦች ቀንና ሌሊት በአእምሮአችሁ ይኑሩ። ሁለተኛ፣ ይህ ዓለም ምን ያህል ከንቱ እንደ ሆነ፣ ከእርሱ የተሻለ መዝገብ ባይኖራችሁ ምን ያህል ፈጥኖ ለቀዝቃዛ መቃብርና ለዘላለም ጕስቍልና አሳልፎ እንደሚሰጣችሁ በቍም ነገር እንድታስቡ እለምናችኋለሁ። በእግዚአብሔርም ፊት መኖር፣ ከክርስቶስ ጋር መንገሥ፣ እንደ መላእክትም መሆን ምን እንደ ሆነ አስቡ፤ ክርስቶስ ያስገኘላችሁ፣ እያዘጋጀላችሁ ያለውና ብትቀበሉት ብቻ የሚያቀርብላችሁ ሕይወት ይህ እንደ ሆነ አስቡ፤ ኦ፣ እንዲህ ያለውን ፍጻሜ የሌለው ክብር ማቃለልና እነዚህን ሥጋዊ ሕልሞችና ምድራዊ ጥላዎች ከእርሱ ማስበለጥ እብደት አይደለምን? ብላችሁ አስቡ። ብቻችሁን በሆናችሁ ጊዜ እንደነዚህ ያሉትን ሐሳቦች ልማድ አድርጉ፤ በአእምሮአችሁም ይኑሩ። ሦስተኛ፣ ያለ አንዳች መዘግየት አሁኑኑ ይህን ብፅዕናና ይህን አዳኝ እንድትቀበሉ እለምናችኋለሁ። ይህን የዘላለም ሕይወት ከሚያቀርብላችሁ ከጌታ ኢየሱስ ጋር ተጣበቁ፤ ብፁዓን ሊያደርጋችሁ የሚችል ብቸኛው መንገድ እንደ ሆነ አውቃችሁ ያቀረበላችሁን በደስታና በምስጋና ተቀበሉ፤ ያን ጊዜም ኃጢአታችሁ ሁሉ በእርሱ እንደሚደመሰስ ልታምኑ ትችላላችሁ። አራተኛ፣ በቀድሞ ኃጢአቶቻችሁ ላይ አሁኑኑ ቍረጡ፤ ልባችሁንና ሕይወታችሁን ያረከሰውን ፈልጋችሁ አግኙ፤ መርዝን ከሆዳችሁ እንደምታስወጡ ከእናንተ ጣሉት፤ ዳግመኛ መውሰዱን ማሰብ እንኳ ተጸየፉ።
«የመጨረሻው ልመናዬ ይህ ለውጥ እስኪደረግ ድረስ የጸጋ መንገዶችን በትጋት ለመጠቀም ራሳችሁን እንድትሰጡ፣ ከዚያም እስክትጸኑና በመጨረሻም ፍጹማን እስክትሆኑ ድረስ እነዚህን መንገዶች መጠቀማችሁን እንድትቀጥሉ ነው።
(1) ይህን ለውጥ በልባችሁና በሕይወታችሁ ላይ በራሳችሁ ልታመጡት ስለማትችሉ፣ በየዕለቱ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ ኃጢአታችሁን ሁሉ ይቅር እንዲል፣ ልባችሁን እንዲለውጥ፣ በክርስቶስ ያለውን የጸጋውን ባለጠግነትና የመንግሥቱን ክብር እንዲያሳያችሁ ስለ ሕይወታችሁ እንደምትለምኑ አድርጋችሁ አጥብቃችሁ ለምኑ። በእነዚህ ልመናዎች ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ተከተሉ።
(2) ከፈተናዎችና ለኃጢአት ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች ሽሹ፤ የቀድሞ ክፉ ጓደኞቻችሁን ተዉ፤ እግዚአብሔርን ከሚፈሩና በመንግሥተ ሰማያት መንገድ ከሚረዱአችሁ ሰዎች ጋር ተወዳጁ።
(3) የጌታን ቀን በጉባኤም ሆነ በግል በቅዱስ ተግባራት ለማሳለፍ በተለየ ሁኔታ ተጠንቀቁ፤ ከጊዜያችሁ ሁሉ የሩብ ሰዓት እንኳ አታባክኑ፤ በተለይም አእምሮአችሁን በእርሱ ላይ እንድታደርጉ፣ ከእርሱም እንድትማሩ፣ ለፍጻሜአችሁም ራሳችሁን እንድታዘጋጁ እግዚአብሔር ሆን ብሎ የሰጣችሁን ያን እጅግ ውድ ጊዜ አታባክኑ። ለእነዚህ ነገሮች ምን ትላላችሁ? ይህን አሁኑኑ፣ ወይም ቢያንስ የምትችሉትን ያህል ታደርጋላችሁን? ለዚህ ቃል ትገቡልኛላችሁን? ከዛሬ ጀምሮስ ያንን ቃል ለመጠበቅ ትተጋላችሁን?»
በዚህም ጊዜ ከተቻላችሁ ቃላቸውን መቀበላችሁንና እንዲታረሙ ማስማላችሁን እርግጠኛ ሁኑ፤ በተለይም የጸጋ መንገዶችን እንዲጠቀሙ፣ ጓደኞቻቸውን እንዲለውጡ፣ ኃጢአታቸውንም እንዲተዉ፤ እነዚህ ይበልጥ በአቅማቸው ውስጥ ያሉ ናቸውና፤ በዚህም መንገድ ገና ያልተደረገው ለውጥ እስኪፈጸም ድረስ ሊጠባበቁ ይችላሉ። ይህንንም ቃላቸውን የሚሰማውንና እንዲፈጽሙትም የሚጠብቀውን የእግዚአብሔርን መገኘት እያሳሰባችኋቸው በክብር አድርጉት፤ ከዚያም በኋላ አጋጣሚ ሲገኝላችሁ የገቡትን ቃል ልታሳስቧቸው ትችላላችሁ።
9. ስታሰናብቷቸው እነዚህን ሁለት ነገሮች አድርጉ፦
(1) ቅር እንዳይሰኙ በጥቂት ቃላት ልባቸውን እንደ ገና አለዝቡ። ለምሳሌ፦ «ይህን ድካም ስላደረስሁባችሁ ወይም በዚህ መንገድ በግልጽነት ስለ ተናገርኋችሁ እባካችሁ ቅር አይበላችሁ። ለእናንተ እንደ ሆነ ሁሉ ለእኔም ደስታ አይደለም። እነዚህ ነገሮች እውነትና አስፈላጊ መሆናቸውን ባላውቅ ኖሮ ይህን ድካም ለራሴም ለእናንተም በተውሁት ነበር፤ ነገር ግን በዚህ አብረን የምንቆየው ጥቂት ጊዜ ብቻ እንደ ሆነ አውቃለሁ፤ ወደሚመጣው ዓለም ቀድሞውኑ ልንደርስ ተቃርበናል፤ ስለዚህ ሁላችንም ዙሪያችንን የምንመለከትበትና እግዚአብሔር በሚጠራን ጊዜ ዝግጁ መሆናችንን የምናረጋግጥበት ጊዜ ነው።»
(2) እነዚያኑ ሰዎች ለማነጋገር ቶሎ አጋጣሚ ላታገኙ ስለምትችሉ፣ የጀመራችሁትን ወደ ፍጻሜ የሚያደርሱበትን መንገድ አሳዩአቸው። የእያንዳንዱ ቤተሰብ ራስ በየጌታ ቀኑ ቤተሰቡን ሁሉ ጠርቶ ከትምህርተ ሃይማኖቱ የተማሩትን እንዲያስደግማቸው፣ ሁሉም ፍጹም አድርገው እስኪያጠኑት ድረስ ይህን ልማድ እንዲቀጥል ቃል አስገቡት፤ ካጠኑትም በኋላ እንዳይረሱት አዘውትሮ በቃል ሲደግሙት መስማቱን እንዲቀጥል አድርጉ፤ እጅግ አስተዋዮች ለሆኑት እንኳ የክርስትና ሃይማኖት ማጠቃለያን በይዘቱ፣ በአደረጃጀቱና በቃላቱ በልብ መያዝ እጅግ ጥሩ ርዳታ ይሆናቸዋልና።
የቤተሰብ አስተዳዳሪዎችን ራሳቸውን፣ ወይም ሊረዱአቸው በማይፈቅዱ ጌቶች ሥር ያሉትን በተመለከተ፣ ከትምህርተ ሃይማኖቱ የተወሰነውን ብቻ ተምረው ከሆነ፣ የቀረውን ሲማሩ እንደ ገና ወደ እናንተ እንዲመጡ (ተራቸው ሳይደርስም ቢሆን)፣ አለዚያም ወደ አንድ ብቁና ልምድ ያለው ጎረቤት ሄደው እንዲደግሙለት ቃል አስገቧቸው፤ እናንተም ራሳችሁ ጊዜ በማታገኙበት ጊዜ የእንደዚህ ያሉ ሰዎችን ርዳታ ተቀበሉ።
10. የደብራችሁን ሰዎች ሁሉ ስም በመጽሐፍ ጽፋችሁ በአጠገባችሁ ያዙ፤ መጥተው ትምህርተ ሃይማኖቱን ሲደግሙ፣ የሚመጡትንና የማይመጡትን፣ ለጌታ እራትና ለሌላ ቅዱስ ኅብረት እስከማይበቁ ድረስ እጅግ ያልተማሩትንና ያልሆኑትንም በመጽሐፋችሁ መዝግቡ፤ የእያንዳንዳቸውንም ችግር እንዳስተዋላችሁ ከዚህ በኋላ እንዲሁ ያዙአቸው። ፈጽሞ እልኸኞች ሆነው ወደ እናንተ ለመምጣትም ሆነ ከእናንተ ለመማር የማይፈቅዱትን ግን፣ የሚያትሙና የሚያጸኑ ሥርዓቶችን በተመለከተ ትምህርትን በእልኸኝነት የሚንቁ ሰዎች ሊያዙ በሚገባው መንገድ ያዙአቸው፤ ይኸውም ከእነርሱ መራቅ፣ በጌታ እራትም ሆነ በሌሎች ሥርዓቶች ከእነርሱ ጋር ቅዱስ ወይም የቅርብ ኅብረት አለማድረግ ነው። አንዳንድ የተከበሩ ወንድሞች ልጆቻቸውን ለጥምቀት መቀበልን ቢደግፉም (ይህንንም በመቃወሜ በእኔ ቢከፉም)፣ እኔ ግን እንዲህ ማድረግ አልችልም፤ በአባቶቻቸው እምነት ሰበብ ወይም በእነዚህ ዓመፀኛ ወላጆች የአእምሮ ብቻ እምነት ሰበብ ይህን ለማድረግ አልደፍርም።
11. ከእነርሱ ጋር በምትነጋገሩበት ጊዜ ሁሉ፣ ይዘቱ ብቻ ሳይሆን አቀራረቡም ለዓላማው የሚስማማ መሆኑን አረጋግጡ።
አቀራረቡንም በተመለከተ እነዚህን ዝርዝር ነገሮች ጠብቁ፦
(1) እንደምታነጋግሯቸው ሰዎች ጠባይ ልዩነት አድርጉ። ለወጣቶች በሥጋዊ ተድላ ፍቅር ላይ የበለጠ ኀፍረት አሸክሙ፤ ሥጋን የመግደልን ምንነትና አስፈላጊነት አሳዩአቸው። ለሽማግሌዎች ይህን የአሁኑን ዓለም ይበልጥ አቃልሉባቸው፤ ከዚህ ዓለም የሚለዩበት ጊዜ ምን ያህል እንደ ቀረበ፣ በድንቁርና ወይም ንስሐ ሳይገቡ ቢኖሩና ቢሞቱ ኃጢአታቸው ምን ያህል እንደሚከብድ እንዲገነዘቡ አድርጉ። ከእናንተ በታች ለሆኑትና ለወጣቶች ይበልጥ ነጻ ሁኑ፤ ከእናንተ በላይ ለሆኑትና ለሽማግሌዎች ይበልጥ አክብሮት አሳዩ። ለባለጠጎች የዚህን ዓለም ከንቱነት፣ ራስን የመካድን ምንነትና አስፈላጊነት፣ የአሁኑን ሁኔታ ከሚመጣው ማስበለጥ ምን ያህል ለኵነኔ እንደሚያደርስ፣ እንዲሁም ለሌሎች መልካም በማድረግ መክሊታቸውን የማትረፍን አስፈላጊነት አሳዩአቸው። ለድሆች በወንጌል የቀረበላቸውን ታላቁን የክብር ባለጠግነት፣ የዘላለም ደስታ ሊገኝ ሲችል የአሁኑ ምቾት ቢቀር ምንም እንደማይጎዳ አሳዩአቸው። እያንዳንዱን ሰው ዕድሜው፣ ወይም ጾታው፣ ወይም ጠባዩ፣ ወይም በዓለም ያለው ሙያውና ሥራው ይበልጥ ወደሚያዘነብልበት ኃጢአት ላይ አብልጣችሁ አጽንዑ፤ ለምሳሌ በሴቶች ዘንድ ለፍላፊነት፣ ክፉ ንግግር፣ ቍጣ፣ ክፋትና ትዕቢት፤ በወንዶች ዘንድ ስካር፣ ሥልጣንን መመኘት፣ ወዘተ።
(2) የአእምሮ አቅማቸው ደካማ ከሆኑ ሰዎች ጋር በተቻለ መጠን ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ ቀረብ ብላችሁ በግልጽ ተናገሩ።
(3) የሚናገራቸው እናንተ ብቻ ሳትሆኑ እግዚአብሔር በእናንተ በኩል እንደ ሆነ እንዲያዩ ለምትሉት ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ስጧቸው።
(4) በሥራው ሁሉ፣ በተለይም ትምህርቱን ወደ ሕይወታቸው በምታዛምዱበት ጊዜ፣ የቻላችሁትን ያህል በቍም ነገር ሁኑ። አንዳንድ ግድ የለሽ መጋቢዎች ሥራውን በችልታ እንዳያልፉት፣ ሁሉንም በላይ በላዩና ያለ ሕይወት እንዳይሠሩት፣ ሌሎቹን ተግባራት ሁሉ እንደሚያጠፉት ይህንንም ወደ ባዶ ሥርዓት በመለወጥ እንዳያጠፉት ከመፍራት የሚበልጥ የምፈራው ነገር የለም ለማለት ይቻላል፤ ለሕዝባቸው ጥቂት ቀዝቃዛ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ፤ ራሳቸው አንዳች ሕይወትና ስሜት ሳይኖራቸው፣ በሰሚዎቹም ዘንድ ስሜት ሊያስነሣ የማይችል ሁለት ወይም ሦስት ቀዝቃዛ የምክር ቃላት ይሰጧቸዋል። ነገር ግን በእርግጥ ነፍሳትን የሚያከብርና በፊቱ ያለው አጋጣሚ ምን እንደ ሆነ የሚያውቅ ሰው ሥራውን በጥልቅ ቍም ነገር ይፈጽመዋል፤ ስለ ሕይወት ወይም ስለ ሞት እንደሚደረግ ያህልም ከእነርሱ ጋር አጥብቆ ይነጋገራል።
(5) ለዚህም ዓላማ ከሥራው በፊትም ሆነ በሥራው ውስጥ ሳለን የወንጌልን እውነትና የሚመጡትን የማይታዩ ክብርና ጕስቍልና ማመናችንን ለማነሣሣትና ለማጽናት ከገዛ ልባችን ጋር በተለየ ሁኔታ መድከማችን እጅግ አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ። ይህ ሥራ የእምነታችንን ብርታት እጅግ እንደሚፈትን እርግጠኛ ነኝ። በላይ በላዩ ብቻ ክርስቲያን የሆነ፣ ከሥሩም ጤናማ ያልሆነ ሰው፣ በተለይም ተግባሩ የተለመደ ነገር በሆነ ጊዜ፣ ሊያስተምርባቸው የሚገባውን ነገሮች ስለማያምን ቅንዓቱ ፈጽሞ ሲከዳው ሳይሰማው አይቀርም። በማስመሰል የሚደረግ የግብዝነት ግለት በዚህ ዓይነት ተግባራት ብዙ ጊዜ አይዘልቅም። ከድሆችና ካልተማሩ ነፍሳት ጋር ከሚደረግ ውይይት ይልቅ ምስባኩ ብዙውን ያገኘዋል። ምስባኩ የግብዝ መጋቢ የትዕይንት መድረክ ነውና፤ በዚያ፣ በኅትመትም፣ ለታይታ ስፍራ ባለባቸው በሌሎች የሕዝብ ተግባራትም ከሁሉ የተሻለውን፣ ምናልባትም ያለውን ሁሉ ታገኛላችሁ። በእጃችን ያለውን ይህን ሥራ በውጤት መሥራት ያለባቸው ሌላ ዓይነት ሰዎች ናቸው።
(6) ስለዚህ በስውር ጸሎት ራሳችንን ለእርሱ ማዘጋጀታችን እጅግ ተገቢ ነው፤ ጊዜም ቢፈቅድ፣ ብዙዎችም በአንድነት ቢገኙ፣ ከሕዝባችን ጋር በአጭር ጸሎት ብንጀምርና ብንፈጽም መልካም ነበር።
(7) ሁሉንም፣ እጅግ ጥብቅ የሆኑትን አነጋገሮች እንኳ፣ ለነፍሳቸው ያላችሁን ፍቅር በግልጽ እያሳያችሁ አከናውኑ፤ ከመዳናቸው በቀር ሌላ ዓላማ እንደሌላችሁ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እንዲሰማቸው አድርጉ። ሻካራና ተስፋ የሚያስቆርጥ አነጋገርን ሁሉ አስወግዱ።
(8) እዚህ እንደ ተመከረው ከእያንዳንዱ ሰው ጋር በሙላት ለመነጋገር ጊዜ ባይኖራችሁ፣ እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ክፍሎች አትተዉ። ወዳጆች የሆኑትንና አንዱ የሌላውን ድካም ለማውጣት የማይሹትን ብዙዎቹን በአንድነት ሰብስቡ፤ ሁሉንም የሚመለከተውንም ያህል በጋራ ንገሯቸው። ነገር ግን እውቀታቸውንና ሁኔታቸውን፣ ስለ ኃጢአትና ስለ ጕስቍልና ያላቸውንም ስሜት መመርመር፣ ለእነርሱ የሚሰጠውም የተለየ ምክር ለእያንዳንዱ ብቻውን መደረግ አለበት። ደግሞም ታማኝነት በጐደለው ስንፍና ወይም እውነተኛ ግድ ሳይኖር ከመጠን በላይ በማሳጠር ሥራውን በችኰላ እንዳታድበሰብሱት ተጠንቀቁ።
12. በመጨረሻም፣ እግዚአብሔር ቢያስችላችሁ፣ ከእናንተ ከመለየታቸው በፊት ለድሆቹ ልግስናችሁን ዘርጉ። ለችግራቸው መደገፊያና ከሥራቸው ለተወሰደው ጊዜ ምትክ የሆነ አንዳች ስጧቸው፤ ይልቁንም ከሁሉ የተሻለ ለሚያደርጉት ማበረታቻ ይሁን። ለሌሎቹም ትምህርተ ሃይማኖቱን በተማሩ ጊዜ ያንኑ ያህል እንደምትሰጧቸው ቃል ግቡላቸው። የሌላችሁን መስጠት እንደማትችሉ አውቃለሁ፤ የምናገረው ግን ለሚችሉት ነው። አሁንም፣ ወንድሞች ሆይ፣ ምክሬን ጨርሻለሁ፤ ተግባሩንም ለእናንተ እተዋለሁ። ትዕቢተኞች በንቀት፣ ራስ ወዳዶችና ሰነፎችም በመጸየፍ አልፎ ተርፎም በቍጣ ቢቀበሉት እንኳ፣ እግዚአብሔር የኃጢአትንና የሰይጣንን ተቃውሞ ሳይገድ ብዙ ባሪያዎቹን ወደ ተግባራቸው ለማንቃትና የእውነተኛውን ተሐድሶ ሥራ ለማስፋፋት እንደሚጠቀምበት አልጠራጠርም። በረከቱም ይህን አሁን የተያዘውን ሥራ እንደሚያጅበው፣ ለብዙ ነፍሳት መዳን፣ ለምትጀምሩትና ለምትፈጽሙት ለእናንተ ሰላም፣ በመላው አገር ያሉትን ባሪያዎቹን እናንተን እንዲደግፉ ለማነሣሣት፣ የአብያተ ክርስቲያናቱንም ንጽሕናና አንድነት ለመጨመር እንደሚሆን አልጠራጠርም። አሜን