ምዕራፍ 12 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ
አንቀጽ 2
ከሥራው አስቸጋሪነት የሚመነጩ ማነሣሻዎች
ከሥራው ጥቅሞች የተወሰዱትን የመጀመሪያዎቹን ዓይነት ምክንያቶች ካቀረብሁላችሁ በኋላ፣ ከአስቸጋሪነቱ ወደ ተወሰዱት ወደ ሁለተኛዎቹ ዓይነት እመጣለሁ። እነዚህ ብቻቸውን ቢወሰዱ ኖሮ ከማነሣሣት ይልቅ ተስፋ የሚያስቈርጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ እመሰክራለሁ፤ ከእነርሱ በፊት ካሉትና ከሚከተሉት ጋር አብረን ስንወስዳቸው ግን ነገሩ ፈጽሞ ሌላ ነው፤ በአስፈላጊ ሥራ ውስጥ ያሉ ችግሮች ወደ የበለጠ ትጋት ሊያነሣሡ ይገባቸዋልና።
በራሳችንም ሆነ በሕዝባችን ዘንድ ብዙ ችግሮችን እናገኛለን፤ ነገር ግን ልምዳችሁ እንድትጠራጠሩባቸው ምንም ስፍራ የማይተውላችሁ እጅግ ግልጽ ነገሮች ስለ ሆኑ፣ በጥቂት ቃላት አልፋቸዋለሁ።
1. በራሳችን ያሉትን ችግሮች ልጥቀስ።
(1) በራሳችን ውስጥ ብዙ ድንዛዜና ስንፍና አለ፤ ስለዚህም እንዲህ ባለ ከባድ ሥራ ታማኞች እንድንሆን ማድረግ ቀላል አይሆንም። መነሣት እንዳለበት እያወቀ እንደሚዘገይና የቻለውን ያህል ተጋድሞ መቆየት እንደሚፈልግ በአልጋው ላይ እንዳለ ታካች፣ እኛም የረከሰው ተፈጥሮአችን በሚጠላቸው ተግባራት ላይ እንዲሁ እናደርጋለን። ይህ ኃይላችንን ሁሉ እንድንጠቀም ያስገድደናል። ስንፍና ብቻውን የብዙዎችን እጅ ያስራል።
(2) ሰውን ለማስደሰት የሚሻ የተዋረደ ጠባይ አለን፤ ይህም ፍቅራቸውን እንዳናጣ ሰዎች እንዲጠፉ፣ መዳናቸውን በመፈለጋችን እንዳናስቈጣቸው በጸጥታ ወደ ሲኦል እንዲሄዱ እንድንተዋቸው ያደርገናል፤ የሕዝባችንን ጥላቻ በራሳችን ላይ ከምናመጣ ይልቅ የእግዚአብሔርን ቍጣ ለመድፈርና የሕዝባችንን የዘላለም መከራ አደጋ ላይ ለመጣል ዝግጁዎች ነን። ይህን ደዌ በትጋት ልንቃወመው ይገባል።
(3) ብዙዎቻችን ደግሞ ከእነርሱ ጋር ለመጀመርና በግልጽ ለመናገር ወደ ኋላ የሚያደርገን የሞኝነት ዓይናፋርነት አለብን። እኛ እጅግ ጨዋዎች ነን፣ እንደሚባለው፤ ስለዚህም ለክርስቶስ ለመናገር፣ ወይም ዲያብሎስን ለመቃወም፣ ወይም ነፍስን ለማዳን ፊታችን በኀፍረት ይቀላል፤ በዚያው ጊዜ ግን በአሳፋሪ ሥራዎች የምናፍረው ያነሰ ነው።
(4) እጅግ ሥጋውያን ከመሆናችን የተነሣ፣ ገቢያችንን እንዳንቀንስ፣ ወይም በራሳችን ላይ ችግር እንዳናመጣ፣ ወይም ሕዝቡን በእኛ ላይ እንዳናነሣሣ፣ ወይም ይህን በመሳሰለ ምክንያት፣ ሥጋዊ ጥቅማችን በክርስቶስ ሥራ ታማኞች እንዳንሆን ይስበናል። እነዚህን ሁሉ ለመቃወም ትጋት ያስፈልጋል።
(5) በእምነት እጅግ ደካሞች ነን፤ ይህም ከሁሉ የሚበልጠው እንቅፋት ነው። ስለዚህም አንድን ሰው እንዲለወጥ በሙሉ ኃይላችን ልንቀርበው በሚገባን ጊዜ፣ መንግሥተ ሰማያትና ሲኦል መኖራቸውን የሚጠራጠር የአለማመን እንቅስቃሴ በውስጣችን ባይኖር እንኳ፣ ቢያንስ በእነርሱ ያለን እምነት እጅግ የደከመ ስለ ሆነ ልባዊ፣ ቈራጥና የማያቋርጥ ቅንዓትን በውስጣችን ሊያነሣሣ ጭራሽ አይችልም፤ የእምነት ምንጭ እጅግ ደካማ ስለ ሆነ እንቅስቃሴያችን ሁሉ ደካማ ብቻ ይሆናል። ስለዚህ መጋቢዎች ስለ ራሳቸውና ስለ ሥራቸው ሲሉ እምነታቸውን በሚገባ ይጠብቁ ዘንድ፣ በተለይም ስለሚመጣው ሕይወት ደስታና ሥቃይ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሚቀበሉበት እምነታቸው ጤናማና ሕያው ይሆን ዘንድ እንዴት ያለ ታላቅ ፍላጎት አላቸው!
(6) በመጨረሻም፣ ለዚህ ሥራ ብዙውን ጊዜ ታላቅ የክህሎትና የብቃት ማጣት አለብን። ወዮ! አላዋቂና ዓለማዊ የሆነን ሰው እንዲለወጥ እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚያውቁ እንዴት ጥቂቶች ናቸው! ወደ ውስጡ ዘልቆ መግባትና ልቡን ማሸነፍ፤ ንግግራችንን ለሁኔታውና ለጠባዩ ማስማማት፤ እጅግ ተገቢ የሆኑ ርእሶችን መምረጥና በቅዱስ የቁም ነገር፣ የማስፈራራት፣ የፍቅር፣ የየዋህነትና የወንጌላዊ ማባበያዎች ቅልቅል መከታተል — ኦ! እንዲህ ላለው ነገር ብቁ የሆነ ማን ነው? ከእንዲህ ያለ ሥጋዊ ሰው ጋር እንዲለወጥ በትክክል መነጋገር፣ እንደ ልማዳችን የምንሰብካቸውን ዓይነት ስብከቶች የመስበክን ያህል ከባድ ነገር፣ ምናልባትም ከዚያ እጅግ የሚበልጥ ሆኖ በልምዴ እንደሚታየኝ በቁም ነገር እመሰክራለሁ። እነዚህ በራሳችን ያሉ ችግሮች ሁሉ እንዳያሸንፉንና ከሥራው ወይም በሥራው ውስጥ እንዳያሰናክሉን ወደ ቅዱስ ቍርጠኝነት፣ ዝግጅትና ትጋት ሊያነቁን ይገባል።
2. እነዚህን በራሳችን ያሉ ችግሮች ከተመለከትሁ በኋላ፣ አሁን በሕዝባችን ዘንድ የምናገኛቸውን አንዳንዶቹን እጠቅሳለሁ።
(1) ብዙዎቹ ለመማር በእልከኝነት ፈቃደኞች አይሆኑም፤ ትምህርተ ሃይማኖትን በግል ለመማር እጅግ የተሻሉ ወይም ለመማር እጅግ ያረጁ እንደ ሆኑ አድርገው ወደ እኛ ለመምጣት ይንቃሉ፤ ይህም የሚሆነው በአደባባይም በግልም በጥበብ ካልያዝናቸውና ጠማማነታቸውን በምክንያት ኃይልና በፍቅር ብርታት ለማሸነፍ ካልተጋን ነው።
(2) ፈቃደኞች የሆኑት ብዙዎቹም እጅግ ደንዳኖች ከመሆናቸው የተነሣ በረጅም ጊዜ ውስጥ የትምህርተ ሃይማኖትን መጽሐፍ አንድ ገጽ እንኳ ለመማር ይቸገራሉ፤ ስለዚህም እነርሱን ለማበረታታት ጥበበኞችና ትጉዎች ካልሆንን በአላዋቂነታቸው አፍረው ይርቃሉ።
(3) በመጡም ጊዜ የብዙዎቹ አላዋቂነትና የማስተዋል ድክመት እጅግ ታላቅ ስለ ሆነ እናንተን እንዲያስተውሉ ማድረግ እጅግ ከባድ ነገር ሆኖ ታገኙታላችሁ፤ ስለዚህም ነገሮችን ግልጽ የማድረግ የተባረከ ጥበብ ከሌላችሁ እንደ ቀድሞው አላዋቂዎች አድርጋችሁ ትተዋቸዋላችሁ።
(4) ነገሮችን በልባቸው ላይ እንዲሠሩ ማድረግና የእኛ ታላቅ ግብ የሆነውን፣ ያለ እርሱም ድካማችን ከንቱ የሚሆነውን ያን የሚያድን ለውጥ እስኪያስገኙ ድረስ ወደ ሕሊናቸው ጠልቀው እንዲገቡ ማድረግ ደግሞ ከዚያ የበለጠ ከባድ ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኦ፣ የደነደነ ሥጋዊ ልብ እንዴት ያለ ግንድ፣ እንዴት ያለ ዓለት ነው! እጅግ ብርቱ የሆኑትን ማግባባቶች እንዴት አጥብቆ ይቃወማል! ስለ ዘላለም ሕይወት ወይም ሞት እንደ ከንቱ ነገር ይሰማል! ስለዚህ ታላቅ የቁም ነገር ስሜት፣ ትኩስ ትጋት፣ ብርቱ ይዘትና ተገቢ አገላለጽ ከሌላችሁ ምን መልካም ነገር ልትጠብቁ ትችላላችሁ? ሁሉን ካደረጋችሁ በኋላም ሥራውን መሥራት ያለበት የጸጋ መንፈስ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔርና ሰዎች ብዙውን ጊዜ ለሥራው ወይም ለግቡ ባሕርይ የሚስማሙ መሣሪያዎችን እንደሚመርጡ፣ እንዲሁ የጥበብ፣ የሕይወትና የቅድስና መንፈስ ብዙውን ጊዜ በሞኞች፣ በሙታንና በሥጋውያን መሣሪያዎች አይሠራም፤ ነገር ግን ራሱንና በእነርሱ የሚሠራውን ሥራ እጅግ በሚመስሉ የብርሃን፣ የሕይወትና የንጽሕና ማግባባቶች ይሠራል።
(5) በመጨረሻም፣ በልባቸው ላይ መልካም የሆነ ስሜት ካሳደራችሁ በኋላ ካልተከታተላችኋቸውና ልዩ ጥንቃቄ ካላደረጋችሁላቸው፣ ልባቸው ቶሎ ወደ ቀድሞ ድንዳኔው ይመለሳል፤ የቀድሞ ጓደኞቻቸውና ፈተናዎቻቸውም ሁሉን እንደገና ያጠፋሉ። በአጭሩ፣ ሕዝባችሁን የምታስተዋውቋቸው የመለወጥ ሥራ ችግሮች ሁሉ በአሁኑ ሥራችን ውስጥ በፊታችን አሉ።