ምዕራፍ 11 · 7 ደቂቃ ንባብ · 9 ደቂቃ ማዳመጥ
የዋህነትና ዕረፍት
የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና።—ማቴዎስ 5:5
የሰውን ዘር ለማያውቀው ሰው ስለ እርሱ በትክክል የቀረበ መግለጫ ለመስጠት፣ ብፅዕናዎቹን ወስዶ ውስጣቸውን ወደ ውጭ ገልብጦ፦ «የሰው ዘር ይኸውልህ» ማለት በቂ ሳይሆን አይቀርም። በብፅዕናዎቹ ውስጥ ካሉት በጎ ምግባሮች ፍጹም ተቃራኒ የሆኑት የሰውን ሕይወትና አካሄድ የሚለዩት ጠባዮች ራሳቸው ናቸውና።
በሰዎች ዓለም ውስጥ ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከት መክፈቻ ቃላት ወደ ተናገራቸው በጎ ምግባሮች የሚቀርብ ምንም ነገር አናገኝም። ከመንፈስ ድህነት ይልቅ እጅግ የከፋውን ትዕቢት እናገኛለን፤ ከሚያዝኑ ይልቅ ተድላን የሚያሳድዱ እናገኛለን፤ ከየዋህነት ይልቅ ትምክህትን፤ ጽድቅን ከመራብ ይልቅ ሰዎች፦ «ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም» ሲሉ እንሰማለን፤ ከምሕረት ይልቅ ጭካኔን እናገኛለን፤ ከልብ ንጽሕና ይልቅ የረከሰ ምናብን፤ ከሚያስተራርቁ ይልቅ ጠበኞችና ቂመኞች ሰዎችን እናገኛለን፤ በመገፋት ደስ ከመሰኘት ይልቅ በእጃቸው ባለ መሣሪያ ሁሉ መልሰው ሲዋጉ እናገኛቸዋለን።
የሠለጠነው ማኅበረሰብ የተሠራው ከእንዲህ ያለው የሞራል ጥሬ ዕቃ ነው። አየሩ በእርሱ የተሞላ ነው፤ በእያንዳንዱ እስትንፋሳችን እንተነፍሰዋለን፤ ከእናታችንም ጡት ወተት ጋር እንጠጣዋለን። ባህልና ትምህርት እነዚህን ነገሮች ጥቂት ያለሰልሷቸዋል እንጂ በመሠረቱ ሳይነኩ ይተዋቸዋል። ይህን ዓይነቱን ሕይወት ብቸኛው መደበኛ ሕይወት አድርጎ ለማጽደቅ አንድ ሙሉ የሥነ ጽሑፍ ዓለም ተፈጥሯል። ይህም ይበልጥ የሚያስደንቀው፣ ሕይወትን ለሁላችንም እንዲህ ያለ መራራ ትግል የሚያደርጉት እነዚሁ ክፋቶች መሆናቸውን ስናስብ ነው። የልባችን ሕመም ሁሉና ብዙዎቹ የሥጋ ደዌዎቻችን በቀጥታ ከኃጢአታችን ይመነጫሉ። ትዕቢት፣ ትምክህት፣ ቂመኝነት፣ ክፉ ምናብ፣ ተንኰል፣ ስግብግብነት—እነዚህ ሟች ሥጋን ካሠቃዩት ደዌዎች ሁሉ ይልቅ ለሰው ልጅ ሥቃይ ምንጭ ናቸው።
እንዲህ ወዳለው ዓለም የኢየሱስ ቃላት ድምፅ ድንቅና እንግዳ ሆኖ፣ ከላይ እንደ መጣ ጕብኝት ይደርሳል። እርሱ መናገሩ መልካም ነው፤ ሌላ ማንም እንደ እርሱ አድርጎ ሊናገር አይችልምና፤ እኛም ብንሰማ መልካም ነው። ቃላቱ የእውነት ፍሬ ነገር ናቸው። እርሱ አስተያየት እያቀረበ አይደለም፤ ኢየሱስ ፈጽሞ አስተያየት ተናግሮ አያውቅም። ፈጽሞ በግምት አልተናገረም፤ ያውቅ ነበር፤ አሁንም ያውቃል። ቃላቱ እንደ ሰሎሞን ቃላት የጤናማ ጥበብ ድምር ወይም የጥልቅ ምልከታ ውጤት አይደሉም። እርሱ ከመለኮቱ ሙላት ተናገረ፤ ቃላቱም እውነት ራሱ ናቸው። «ብፁዓን» ብሎ በፍጹም ሥልጣን ሊናገር የሚችል እርሱ ብቻ ነው፤ ለሰው ልጆች ብፅዕናን ለመስጠት ከላይኛው ዓለም የመጣ ብፁዕ እርሱ ነውና። ቃላቱም በዚህ ምድር ላይ ሌላ ማንም ሰው ካደረገው ከማንኛውም ሥራ በሚበልጡ ሥራዎች የተደገፉ ነበሩ። መስማት ለእኛ ጥበብ ነው።
ብዙ ጊዜ ኢየሱስ እንደሚያደርገው፣ ይህን «የዋህ» የሚለውን ቃል በአጭርና በቍርጥ ዓረፍተ ነገር ተጠቀመበት፤ ሊያብራራውም የቀጠለው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነበር። በዚያው በማቴዎስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ተጨማሪ ይነግረናል፤ በሕይወታችንም ላይ ይተገብረዋል፦ «እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።» እዚህ እርስ በርሳቸው ተቃራኒ ሆነው የቆሙ ሁለት ነገሮች አሉን፤ ሸክምና ዕረፍት። ሸክሙ ለእነዚያ ለመጀመሪያዎቹ ሰሚዎች ብቻ የተለየ የአካባቢ ሸክም አይደለም፤ መላው የሰው ዘር የሚሸከመው ሸክም እንጂ። የፖለቲካ ጭቈና ወይም ድህነት ወይም ከባድ ሥራ አይደለም። ከዚያ እጅግ የጠለቀ ነው። ሀብትም ሆነ ሥራ ፈትነት ፈጽሞ ሊያድኑን የማይችሉት ነገር ስለ ሆነ፣ ድሆች እንደሚሰማቸው ሁሉ ሀብታሞችም ይሰማቸዋል።
የሰው ልጆች የሚሸከሙት ሸክም ከባድና የሚያደቅቅ ነገር ነው። ኢየሱስ የተጠቀመበት ቃል እስከ መዛል ድረስ የተሸከሙትን ጭነት ወይም የደከሙትን ድካም ማለት ነው። ዕረፍት በቀላሉ ከዚያ ሸክም መፈታት ነው። እኛ የምናደርገው ነገር አይደለም፤ ማድረግ ስናቆም ወደ እኛ የሚመጣ ነው። የእርሱ የራሱ የዋህነት—ዕረፍቱ ያ ነው።
ሸክማችንን እንመርምር። ሙሉ በሙሉ ውስጣዊ ሸክም ነው። ልብንና አእምሮን ያጠቃል፤ ወደ ሥጋም የሚደርሰው ከውስጥ ብቻ ነው። በመጀመሪያ የትዕቢት ሸክም አለ። የራስ ፍቅር ድካም በእውነት ከባድ ነው። ብዙው ሐዘንህ አንድ ሰው አቃልሎ ስለ አንተ በመናገሩ የተነሣ የመጣ አለመሆኑን ለራስህ አስብ። ታማኝ ልትሆንለት የሚገባህ ትንሽ አምላክ አድርገህ ራስህን እስካቆምህ ድረስ፣ ጣዖትህን በመዳፈር ደስ የሚላቸው ሰዎች ይኖራሉ። ታዲያ ውስጣዊ ሰላም እንዴት ታገኛለህ ብለህ ተስፋ ልታደርግ ትችላለህ? ልብ ራሱን ከማናቸውም ንቀት ለመጠበቅ፣ በቀላሉ የሚነካውን ክብሩን ከወዳጅና ከጠላት ክፉ አመለካከት ለመከለል የሚያደርገው ብርቱ ጥረት አእምሮን ከቶ አያሳርፈውም። ይህን ትግል ለዓመታት ቀጥል፤ ሸክሙም የማይቻል ይሆናል። ሆኖም የምድር ልጆች ይህን ሸክም ያለማቋረጥ ይሸከማሉ፤ በእነርሱ ላይ የተነገረውን ቃል ሁሉ ይሞግታሉ፣ ከእያንዳንዱ ትችት በታች ይኰማተራሉ፣ በታሰበ ንቀት ሁሉ ይቈስላሉ፣ ሌላው ከእነርሱ ቢመረጥ እንቅልፍ አጥተው ይገላበጣሉ።
እንዲህ ያለውን ሸክም መሸከም አስፈላጊ አይደለም። ኢየሱስ ወደ ዕረፍቱ ይጠራናል፤ የዋህነትም ዘዴው ነው። የዋህ ሰው ከእርሱ የሚበልጥ ማን እንደ ሆነ ፈጽሞ ግድ አይሰጠውም፤ የዓለም አክብሮት ጥረት የሚገባው አለመሆኑን ከብዙ ጊዜ በፊት ወስኗልና። ለራሱ ደግ የሆነ የቀልድ ስሜት ያዳብራል፤ እንዲህም ማለትን ይማራል፦ «ኦ፣ ለካ ተዘንግተሃል? ሌላ ሰው ከአንተ አስቀድመዋል? ለካስ አንተ ከንቱ ትንሽ ነገር ነህ ብለው ተንሾካሹከዋል? አሁንስ ስለ ራስህ ስትናገረው የነበረውን ያንኑ ነገር ዓለም ስለ አንተ ስለሚናገር ተጐዳሁ ብለህ ይሰማሃል? ገና ትናንት ለእግዚአብሔር ምንም እንዳልሆንህ፣ ተራ የአፈር ትል እንደ ሆንህ ትነግረው ነበር። ታዲያ ወጥነትህ የት አለ? ና፣ ራስህን አዋርድ፤ ሰዎች ስለሚያስቡት ግድ መስጠትንም ተው።»
የዋህ ሰው በራሱ ዝቅተኛነት ስሜት የተጠቃ የሰው አይጥ አይደለም። ይልቁንም በሥነ ምግባር ሕይወቱ እንደ አንበሳ ደፋር፣ እንደ ሶምሶንም ብርቱ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ስለ ራሱ መታለልን አቁሟል። እግዚአብሔር ስለ ሕይወቱ የሰጠውን ግምት ተቀብሏል። እግዚአብሔር እንዳወጀው ደካማና ረዳት የሌለው መሆኑን ያውቃል፤ ይሁን እንጂ በሚያስገርም ተቃርኖ፣ በዚያው ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ከመላእክት የበለጠ ዋጋ እንዳለው ያውቃል። በራሱ ምንም፤ በእግዚአብሔር ሁሉም ነገር። ይህ መሪ ቃሉ ነው። ዓለም እግዚአብሔር እንደሚያየው አድርጎ ፈጽሞ እንደማያየው በሚገባ ያውቃል፤ ግድ መስጠቱንም ትቷል። እግዚአብሔር የራሱን ዋጋ እንዲሰጥ በመፍቀድ ፍጹም ረክቶ ያርፋል። ሁሉም ነገር የራሱን የዋጋ መለያ የሚያገኝበትንና እውነተኛ ዋጋ ወደ ትክክለኛ ስፍራው የሚመለስበትን ቀን በትዕግሥት ይጠብቃል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት ይበራሉ። ያንን ቀን ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነው።
እስከዚያው ድረስ የነፍስ ዕረፍት ስፍራ ላይ ደርሷል። በየዋህነት እየተመላለሰ ሳለ እግዚአብሔር እንዲከላከልለት በመፍቀድ ደስ ይለዋል። ራሱን የመከላከል የቀድሞው ትግል አብቅቷል። የዋህነት የሚያመጣውን ሰላም አግኝቷል።
ደግሞም ከማስመሰል ሸክም ነጻ ይወጣል። በዚህ ግብዝነትን ማለቴ አይደለም፤ ይልቁንም መልካም ገጽታችንን ብቻ አስቀድመን እውነተኛውን ውስጣዊ ድህነታችንን ከዓለም ለመደበቅ ያለውን የተለመደ ሰብአዊ ምኞት ነው። ኃጢአት ብዙ ክፉ ተንኰል ሠርቶብናልና፤ ከእነርሱም አንዱ የሐሰት የእፍረት ስሜትን በውስጣችን ማስረጹ ነው። ሌሎች ስለ እርሱ ያላቸውን ግንዛቤ ሳያሳምር እንዳለ ሆኖ ለመታየት የሚደፍር ወንድ ወይም ሴት እምብዛም የለም። የመጋለጥ ፍርሃት በልባቸው ውስጥ እንደ አይጥ ይቦረቡራል። የሠለጠነው ሰው አንድ ቀን ከእርሱ ይበልጥ የሠለጠነ ሰው ያገኛል የሚል ፍርሃት ያሳድደዋል። የተማረው ሰው ከእርሱ ይበልጥ የተማረ ሰው ለማግኘት ይፈራል። ሀብታሙ ሰው ልብሱ ወይም መኪናው ወይም ቤቱ አንድ ቀን ከሌላ ሀብታም ሰው ንብረት ጋር ሲነጻጸር ርካሽ መስሎ ይታያል በሚል ፍርሃት ያልበዋል። «ከፍተኛው ማኅበረሰብ» የሚባለው ከዚህ ባልበለጠ ግፊት ይንቀሳቀሳል፤ ድሆቹ መደቦችም በራሳቸው ደረጃ ብዙም የተሻሉ አይደሉም።
ማንም ይህን በፈገግታ አያሳልፈው። እነዚህ ሸክሞች እውነተኛ ናቸው፤ ቀስ በቀስም የዚህን ክፉና ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ የሕይወት ዘይቤ ሰለባዎች ይገድላሉ። ለዓመታት በዚህ ዓይነት ነገር የተፈጠረው አስተሳሰብም እውነተኛውን የዋህነት እንደ ሕልም የማይጨበጥ፣ እንደ ኮከብም የራቀ አስመስሎ ያሳያል። ለዚህ ለሚቦረቡረው ደዌ ሰለባዎች ሁሉ ኢየሱስ፦ «እንደ ሕፃናት መሆን አለባችሁ» ይላል። ሕፃናት አያወዳድሩምና፤ ያላቸውን ከሌላ ነገር ወይም ከሌላ ሰው ጋር ሳያዛምዱ በቀጥታ ይደሰቱበታል። ቅናትና ምቀኝነት የሚታዩት ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድና ኃጢአት በልባቸው ውስጥ መንቀሳቀስ ሲጀምር ብቻ ነው። ያን ጊዜ ሌላው ሰው የበለጠ ትልቅ ወይም የተሻለ ነገር ካለው ባላቸው መደሰት አይችሉም። በዚያ በለጋ ዕድሜ ነው የሚያቈስለው ሸክም በለስላሳ ነፍሳቸው ላይ የሚወርደው፤ ኢየሱስም ነጻ እስኪያወጣቸው ድረስ ፈጽሞ አይለቃቸውም።
ሌላው የሸክም ምንጭ ሰው ሠራሽነት ነው። ብዙ ሰዎች አንድ ቀን ቸልተኛ ሆነው በአጋጣሚ ጠላት ወይም ወዳጅ ወደ ምስኪንና ባዶ ነፍሳቸው እንዲያጮልቅ ይፈቀድለታል ብለው በስውር ፍርሃት እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነኝ። ስለዚህ ፈጽሞ ዘና አይሉም። ብልህ ሰዎች ተራ ወይም የሞኝ ነገር እንዲናገሩ ተጠምደው እንዳይያዙ በመፍራት ውጥረትና ንቃት ላይ ናቸው። ብዙ የተጓዙ ሰዎች እነርሱ ፈጽሞ ያልሄዱበትን ሩቅ ስፍራ ሊገልጽ የሚችል አንድ ማርኮ ፖሎ እንዳያገኙ ይፈራሉ።
ይህ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ሁኔታ የኃጢአት አሳዛኝ ውርሳችን አንዱ ክፍል ነው፤ በዘመናችን ግን በመላው የሕይወት ዘይቤአችን ተባብሷል። ማስታወቂያ በአብዛኛው የተመሠረተው በዚሁ የማስመሰል ልማድ ላይ ነው። በዚህ ወይም በዚያ የሰው ዕውቀት መስክ «ኮርሶች» ይቀርባሉ፤ በግልጽም የሚማጸኑት ሰለባው በግብዣ ላይ ጎልቶ የመታየት ምኞቱን ነው። እኛ ያልሆንነውን መስለን የመታየትን ይህን ምኞት ያለማቋረጥ በመነካካት መጻሕፍት ይሸጣሉ፣ ልብሶችና መዋቢያዎችም ይቸረቸራሉ። ሰው ሠራሽነት በኢየሱስ እግር ሥር በተንበረከክንና ራሳችንን ለየዋህነቱ በሰጠን ቅጽበት የሚወድቅ እርግማን ነው። ያን ጊዜ እግዚአብሔር ደስ እስካለው ድረስ ሰዎች ስለ እኛ የሚያስቡት ግድ አይሰጠንም። ያን ጊዜ እውነተኛ ማንነታችን ሁሉም ነገር ይሆናል፤ መስለን የምንታየው ግን በምንሰጠው ትኵረት መለኪያ እጅግ ዝቅ ብሎ ስፍራውን ይይዛል። ከኃጢአት በቀር የምናፍርበት ምንም ነገር የለንም። ካለን ማንነት ሌላ መስለን እንድንታይ የሚያደርገን ጎልቶ የመታየት ክፉ ምኞት ብቻ ነው።
የዓለም ልብ በዚህ የትዕቢትና የማስመሰል ጭነት ሥር እየተሰበረ ነው። ከክርስቶስ የዋህነት በቀር ከሸክማችን ምንም መፈታት የለም። መልካም ጥልቅ አመክንዮ ጥቂት ሊረዳ ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ክፉ ጠባይ እጅግ ብርቱ ከመሆኑ የተነሣ በአንድ ስፍራ ብንጫነው በሌላ ስፍራ ብቅ ይላል። በየስፍራው ላሉ ወንዶችና ሴቶች ኢየሱስ፦ «ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ» ይላል። እርሱ የሚሰጠው ዕረፍት የየዋህነት ዕረፍት ነው፤ ራሳችንን እንዳለን ተቀብለን ማስመሰልን ስናቆም የሚመጣው የተባረከ እፎይታ ነው። በመጀመሪያ ጥቂት ድፍረት ይጠይቃል፤ ነገር ግን ይህን አዲስና ልዝብ ቀንበር ከብርቱው የእግዚአብሔር ልጅ ከራሱ ጋር እየተጋራን መሆናችንን ስንማር የሚያስፈልገው ጸጋ ይመጣል። እርሱ «ቀንበሬ» ይለዋል፤ እርሱ በአንዱ ጫፍ ይሄዳል፣ እኛም በሌላው ጫፍ እንሄዳለን።
ጌታ ሆይ፣ እንደ ሕፃን አድርገኝ። ለስፍራ ወይም ለክብር ወይም ለማዕረግ ከሌላው ጋር ከመፎካከር ፍላጎት አድነኝ። እንደ ትንሽ ሕፃን ቀላልና ተንኰል የሌለኝ መሆን እወዳለሁ። ከአጕል አቀማመጥና ከማስመሰል አድነኝ። ስለ ራሴ በማሰቤ ይቅር በለኝ። ራሴን እንድረሳና አንተን በማየት እውነተኛ ሰላሜን እንዳገኝ እርዳኝ። ይህን ጸሎት ትመልስልኝ ዘንድ በፊትህ ራሴን አዋርዳለሁ። በእርሱ ዕረፍት አገኝ ዘንድ ራስን የመርሳትን ልዝብ ቀንበርህን በላዬ ጫን። አሜን።