ምዕራፍ 11 · 4 ደቂቃ ንባብ
የክርስቶስን ትእዛዛት መጠበቅ
«ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ» ዮሐንስ 13:17።
የእግዚአብሔር ቃል ብፅዕናና በረከት ሊታወቁ የሚችሉት እርሱን በማድረግ ብቻ ነው። ይህ ጉዳይ በክርስትና ሕይወት፣ ስለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን፣ እጅግ ታላቅ ጠቀሜታ ስላለው፣ እንደገና አንድ ጊዜ ወደ እርሱ እንድትመለስ ልለምንህ ግድ ነው። በዚህም ጊዜ ቃልን መጠበቅ ወይም ትእዛዛትን መጠበቅ የሚለውን አንዱን አገላለጽ ብቻ እንውሰድ። በመጀመሪያ በስንብት ንግግሩ ውስጥ እንመልከተው። ክፍሎቹን ታውቃቸው ይሆናል፤ ነገር ግን በአንድነት ብንመለከታቸው ይጠቅማል።
«ብትወዱኝ ትእዛዛቴን ትጠብቃላችሁ። እኔም አብን እለምናለሁ፥ ሌላ አጽናኝም ይሰጣችኋል» (ዮሐንስ 14:15, 16)።
«ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።» (ቁጥር 21)። «ኢየሱስም መለሰ አለውም። የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።» (ቁጥር 23)። «በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል።» (15:7)። «እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።» (15:10)። «እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ።» (15:14)።
ቃሎቹ ወደ ልብ ገብተው የክርስቶስን ትእዛዛት መጠበቅ ለእውነተኛ መንፈሳዊ በረከት ሁሉ የግድ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን የሚያረጋግጥ ጥልቅ እምነት እስኪያሳድሩ ድረስ እነዚህን ክፍሎች አጥናቸው፣ አነጻጽራቸውም። ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መምጣትና በእውነት በውስጣችን ለመኖሩ፣ በአብ ፍቅር ለመደሰት፣ ክርስቶስ በውስጥ ለመገለጡ፣ አብና ወልድ በልብ ውስጥ መኖሪያ ለማድረጋቸው፣ ለጸሎት ኃይል፣ በክርስቶስ ፍቅር ለመኖርና በወዳጅነቱ ለመደሰት የሚያስፈልገው አንዱ ነገር ትእዛዛትን መጠበቅ ነው።
እነዚህን በረከቶች ዕለት ዕለት በእምነት ለመጠየቅና ለመደሰት ለሚያስፈልገው ኃይል ደግሞ፣ በእርግጥ እንደምንጠብቃቸው የሚያውቅ የሕፃን ዓይነት ግንዛቤ የግድ አስፈላጊ ነው። ለፍሬያማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትም፣ እስከ መጨረሻው ድረስ ለመታዘዝ ዝግጁ መሆናችንን እርሱ ስለሚያውቅ ከእያንዳንዱ የእግዚአብሔር ቃል ጋር መለኮታዊ ብርሃንንና ብርታትን ለመጠበቅ የሚደፍር ጸጥ ያለ መተማመን ከዚህ ያላነሰ አስፈላጊ ነው።
ወደ አብ ልብ የምንደርስበት ብቸኛው መንገዳችን፣ እርሱም ወደ ልባችን የሚደርስበት ብቸኛው መንገዱ፣ ደስ በምንሰኝበትና በምናደርገው በእግዚአብሔር ፈቃድ በኩል ነው።
ትእዛዛትን ጠብቅ፤ ወደ በረከት ሁሉ የሚወስደው መንገድ ይህ ነው። ይህ ሁሉ በዮሐንስ የመጀመሪያ መልእክት ውስጥ በምናገኘው ቃል ምን ያህል በሚያስደንቅ ሁኔታ እንደሚጸና ተመልከት።
«ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን። አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም። ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል» (1ኛ ዮሐንስ 2:3-5)። ስለ እግዚአብሔር ያለን እውቀት እውነተኛ፣ ሕያውና የሚያድን መሆኑን የሚያረጋግጠው ብቸኛው ማስረጃ፤ በሃይማኖታችን ራሳችንን እንዳላታለልን የሚያረጋግጠው ብቸኛው ማስረጃ፤ የእግዚአብሔር ፍቅር ምናብ ሳይሆን በእጃችን ያለ ሀብት መሆኑን የሚያረጋግጠው ብቸኛው ማስረጃ ቃሉን መጠበቅ ነው።
«ልባችንስ ባይፈርድብን በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን፥ ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን። ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል» (3:21, 22 እና 24)። ትእዛዛትን መጠበቅ በእግዚአብሔር ፊት የድፍረትና ከእርሱ ጋር የእውነተኛ የቅርብ ኅብረት ምሥጢር ነው።
«ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና» (ቁጥር 3, 4)።
ከእግዚአብሔር በተወለደ ሕይወት ኃይል ትእዛዛቱን በመጠበቅ እውነትነቱ ካልተረጋገጠ በቀር፣ ፍቅር አለን ብለን መመስከራችን ከንቱ ነው። እግዚአብሔርን ማወቅ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ መፈጸሙ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት ማግኘት፣ በእርሱ መኖር፣ ከእርሱ መወለድና እርሱን መውደድ— ሁሉም በአንዱ ነገር ላይ የተመሠረተ ነው፦ ትእዛዛትን መጠበቅ።
ክርስቶስና መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ እውነት የሚሰጡትን ታላቅ ስፍራ ስንገነዘብ ብቻ ነው እኛም በሕይወታችን ያንኑ ስፍራ ልንሰጠው የምንማረው። ይህም ለእውነተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከቍልፎቹ አንዱ ይሆንልናል። የእግዚአብሔርንና የክርስቶስን ትእዛዝ ሁሉ ለመመርመርና ለመታዘዝ በናፍቆትና በቈረጠ ዓላማ መጽሐፍ ቅዱሱን የሚያነብ ሰው፣ ቃሉ ያመጣ ዘንድ የታሰበለትን በረከት ሁሉ ለመቀበል በትክክለኛው መንገድ ላይ ነው። በተለይ ሁለት ነገሮችን ይማራል፤ ወደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ እንዲመራው የመንፈስ ቅዱስን ትምህርት መጠበቅ ምን ያህል እንደሚያስፈልገው፤ ደግሞም የዕለት ተዕለት ተግባራትን ትክክል ስለሆኑ ወይም ደስ ስለሚያሰኙት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆኑ በመፈጸም ምን ያለ ብፅዕና እንዳለ። ክርስቶስ እንዳለው፦ «ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ» ሲል የዕለት ተዕለት ሕይወቱ ሁሉ እንዴት ከፍ እንደሚል ያገኛል። ቃሉ እርምጃዎቹ ሁሉ የሚቃኑበት ብርሃንና መሪ ይሆንለታል።
ሕይወቱ የቃሉ የሚቀድስ ኃይልና ማበረታቻው የሚረጋገጥበት የማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ይሆናል። እንዲሁም ትእዛዛትን መጠበቅ የመንፈሳዊ በረከት ሁሉ ቍልፍ ይሆናል።
ይህ የሙሉ መታዘዝ ሕይወት ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት በቍርጠኝነት ጥረት አድርግ። ከክርስቶስ ትእዛዛት እጅግ ግልጽ የሆኑትን አንዳንዶቹን ውሰድ፦ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፤ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል፤ እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ፤ የክርስቶስን የመሰለ ፍቅርና ትሕትናም ልትኖረው የሚገባህ ከተፈጥሮ በላይ የሆነው ሕይወት ሕግ አድርገህ ተቀበል። የውድቀት ወይም የአቅም ማጣት ስሜት ወደ ተስፋ መቍረጥ፣ ወይም ሊደረስበት ይችላል ብለህ በምታስበው ነገር ረክተህ ወደ መቀመጥ ከመምራት ይልቅ፣ በመንፈሱ መፈለግንም ማድረግንም በአንተ በሚሠራው በእርሱ ላይ ተስፋህን ይበልጥ ሙሉ በሙሉ እንድትጥል ብቻ ያበረታታህ።
እንደገናም እላለሁ፤ አንዱ ዓላማችን በኅሊናና በአካሄድ መካከል ፍጹም ስምምነት መሆን አለበት። እያንዳንዱ የኅሊና ማረጋገጫ ወደ ተግባር መለወጥ አለበት። የክርስቶስ ትእዛዛት የተሰጡት እንዲታዘዙ ነው። ይህ ካልተደረገ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት መከማቸት የሚያጨልምና የሚያደነድን ብቻ ይሆናል፤ እውቀትን በማግኘት በሚመጣው ደስታ የመርካትን ስሜትም ያመጣል፤ ይህም ለመንፈስ ቅዱስ ትምህርት ብቁ እንዳንሆን ያደርገናል።
ይህን የተባረከና የከበረ መልእክት ደጋግሜ በመናገሬ እንዳትሰለች እጸልያለሁ። ቀኑን ሙሉ የክርስቶስን ትእዛዛት ትጠብቅ እንደሆነ የሚለው ጥያቄ የሚወሰነው በውስጥ እልፍኝህ ውስጥ ነው። በሚመጣውም ሕይወትህ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅና ለማድረግ ፈጽሞ ራሱን የሰጠ ሰው ባሕርይ ይኖርህ እንደሆነ የሚወሰነውም በዚያው ነው።
ምዕራፍ 11 ተጠናቋል
የክርስቶስን ትእዛዛት መጠበቅ