ምዕራፍ 15 · 16 ደቂቃ ንባብ · 21 ደቂቃ ማዳመጥ
ቃል በቃል የሆነ ሲኦል አለን?
«የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል።» — ማቴዎስ 5:22።
ርእሴ «እውነተኛ ሲኦል አለን?» የሚል ነው። ልሰብካችሁ ያሰብኋቸው ነገሮች እውነት ባይሆኑ በወደድሁ ነበር። እግዚአብሔርም ይህንኑ ይወዳል፤ ጌታ «ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል» (2ኛ ጴጥሮስ 3:9)። ነገር ግን እግዚአብሔር በራሱ መልክ፣ የሞራል ባሕርይ፣ ራሳችንን የመወሰን ችሎታና የመምረጥ ኃይል ያለን አድርጎ ፈጥሮናል፤ ሰዎችም ቢፈልጉ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ሊመርጡ ይችላሉ። የእግዚአብሔርን አዳኝ ፍቅር ከእግራቸው በታች ለመርገጥ ሊመርጡ ይችላሉ። ስለ መተላለፋቸው የቈሰለውን፣ ስለ በደላቸውም የደቀቀውን፣ የደኅንነታቸውም ተግሣጽ በእርሱ ላይ የነበረውን እርሱን ለመቃወም ሊመርጡ ይችላሉ፤ አንዳንዶችም እንዲሁ ይመርጣሉ። እንዲህ በማድረጋቸው አዝናለሁ። እነርሱን ለማዳን ብሞት እንኳ ፈቃደኛ ነኝ። ጌታ ኢየሱስም እነርሱን ለማዳን በእርግጥ ሞቷል። እነርሱ ግን ይንቁታል። ስለዚህ ዛሬ ምሽት የምናገራቸው እነዚህ ነገሮች እውነት ናቸው፤ እኔም የምሰብካቸው እንድታውቋቸውና እርግጠኞች እንድትሆኑባቸው ነው። ስለ ሲኦል የምሰብከው ከእናንተ የቻልሁትን ያህል ብዙዎቻችሁን ወደዚያ ከመሄድ ለመጠበቅ ነው።
እውነተኛ ሲኦል አለን? ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ የሚያምኑ አስተዋዮች ሁሉ ማለት ይቻላል፣ በአሁኑ ሕይወት ኃጢአት የሚሠሩና ንስሐ ሳይገቡና ሳይድኑ የሚሞቱ ወንዶችና ሴቶች በሚመጣው ሕይወት ቢያንስ በተወሰነ መጠን እንደሚቀጡ ያምናሉ። ኃጢአት የሚሠራ ሁሉ መሠቃየት እንዳለበት፣ ኃጢአት የሚያመጣውም ሥቃይ በዚህ በአሁኑ ሕይወት ብቻ እንደማይወሰን ያምናሉ። ነገር ግን ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ የሚያምኑ አስተዋዮች ሁሉ ማለት ይቻላል አንድ ዓይነት የወደፊት ቅጣት እንዳለ ቢያምኑም፣ በእውነተኛ ሲኦል፣ ማለትም አስፈሪና ሊነገር የማይችል ሥቃይ ባለበት ስፍራ የማያምኑ ብዙዎች አሉ። ሲኦል አለን? ንስሐ ያልገቡ ወንዶችና ሴቶች ከሞት በኋላ በሆነ ጊዜ የሚሄዱበትና በዚህ ምድር ማንም ከሚቀበለው እጅግ የሚበልጥ ጭንቀት የሚቀበሉበት ስፍራ አለን? አንዳንዶች «አዎን» ሲኦል አለ ይላሉ። ብዙዎች፣ ትክክለኛውን ትምህርት ይዘዋል የሚባሉ ጥቂት የማይባሉ ሰባኪዎችም ጭምር፣ «የለም፤ ያለው ብቸኛ ሲኦል በሰው ልብ ውስጥ ያለው ውስጣዊ ሲኦል ነው» ይላሉ። ይህን ጥያቄ እንዴት እንፍታው? ማን ትክክል እንደ ሆነ እንዴት እንወስን? አንዳንዶች ሊፈቱት እንደሚሞክሩት «አፍንጫ በመቍጠር» ልንፈታው አንችልም። ብዙኃኑ ሁልጊዜ ትክክል አይደሉም። በተለይም በሳይንስ፣ በፍልስፍናና በሥነ መለኮት ብዙኃኑ ሁልጊዜ ትክክል አለመሆናቸው እውነት ነው። ከአንድ መቶ ዓመት በፊት አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች አጥብቀው ያመኑበትን ነገር ዛሬ አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች ይስቁበታል። አብዛኞቹ ፈላስፎች በአንድ ወቅት ያመኑበትን ዛሬ አብዛኞቹ ፈላስፎች እንደ መሳቂያ ይቈጥሩታል። ስለዚህ ብዙኃኑ ሁልጊዜ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህም ብዙኃኑ የሚያምኑት ምንድን ነው ብለን በመጠየቅ ይህን ጥያቄ ልንፈታው አንችልም።
እግዚአብሔርን የመሰለ አካል ምን ማድረግ አለበት ብለን በማመዛዘንም ጥያቄውን ልንፈታው አንችልም፤ ውሱንና ሞኝ የሆነ ሰው ወሰን የሌለው ቅዱስና ወሰን የሌለው ጠቢብ የሆነ አምላክ ምን እንደሚያደርግ እንዴት ሊፈርድ ይችላል? ሰው ወሰን የሌለው አምላክ ምን ማድረግ እንዳለበት በማመዛዘን ለማውጣት ከሚሞክርበት ጊዜ ይበልጥ ሞኝ ሆኖ የሚታይበት ጊዜ የለም። እግዚአብሔር ምን ማድረግ አለበት ወይም ምን ማድረግ የለበትም ብሎ በማመዛዘን ስለ ሲኦል የሚቀርቡት እነዚህ ክርክሮች ሁሉ ሞኝነት ናቸው። የሰባት ዓመት ልጅ ጠቢብና መልካም የሆነ የሃምሳ ዓመት ሰው ምን እንደሚያደርግ ያለ ስሕተት ሊያመዛዝን አይችልም፤ ይልቁንም ከትቢያ የተገኘን ደካሞች ፍጥረታት (እንደ እናንተና እንደ እኔ፣ እጅግ የተማሩ ፈላስፎችና የሥነ መለኮት ሊቃውንትም እንደ ሆኑት) ወሰን የሌለው ጠቢብና ወሰን የሌለው ቅዱስ የሆነ አምላክ ምን ማድረግ እንዳለበት ያለ ስሕተት ልናመዛዝን አንችልም። ይሁን እንጂ ከንጹሕ ማመዛዘን አንጻር በእውነተኛ ሲኦል፣ ደግሞም በዘላለማዊ ሲኦል ማመን ከሦስት ዓመት ተኩል በፊት ከነበረው ይልቅ ዛሬ እጅግ ይቀላል። ቢሆንም፣ እውነተኛ ሲኦል አለ ወይስ የለም የሚለውን ጥያቄ ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔርን የመሰለ አካል ምን ማድረግ አለበት ብለን በማመዛዘን ልንፈታው አንችልም።
ይህን ጥያቄ በትክክል የምንፈታበት አንድ መንገድ ብቻ አለ፤ እርሱም ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ሄደን የሚለውን ማወቅና ያለ ማመንታት በዚያ ላይ አጥብቀን መቆም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ቅን ሰው ሊጠራጠረው በማይችል ሁኔታ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ባለፉት ሦስት የእሁድ ምሽቶች አይተናል፤ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይም ሆነ በሌላ በማንኛውም ጉዳይ የሚናገረው ሁሉ እውነትና እርግጥ ነው። በተለይም ስለ ወደፊት ቅጣትና ስለ ወደፊት ብፅዕና ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ሄደን የሚለውን ማወቅ እንዳለብን እውነት ነው። ስለ ወደፊቱ የምናውቀው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረንን ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከሚነግረን ውጭ ስለ ወደፊቱ የሚደረግ ማመዛዘን ሁሉ ተራ ግምት ነው፤ ጊዜ ማባከንም ነው። ስለ መንግሥተ ሰማያት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚነግረን በቀር ምንም አናውቅም፤ ስለ ሲኦልም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚነግረን በቀር ምንም አናውቅም። እንዲህ ባለው ጉዳይ አንዲት ቍንጣሪ የእግዚአብሔር መገለጥ ከሺህ ቶን የሰው ግምት ትበልጣለች። ጥያቄው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሲኦል ምን ይላል? የሚለው ነው። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመካን ብንሆንም፣ መጽሐፍ ቅዱስ ልናውቀው የሚያስፈልገንን ሁሉ በግልጥ ይገልጣል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንግሥተ ሰማያት ብዙ ይነግረናል፤ ስለ ሲኦል ደግሞ ከዚያም የበለጠ ይነግረናል፤ የሚያስገርመውም፣ የቀረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን የማይቀበሉ ብዙዎች ሥልጣኑን ለመቀበል ዝግጁ የሆኑለት ጌታ ኢየሱስ ራሱ ስለ ሲኦል አብልጦ፣ ደግሞም አብልጦ በግልጥ የሚነግረን መሆኑ ነው። በእርግጥም የማሳያችሁ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ጌታ ኢየሱስ ራሱ የሚለውን ነው።
1. ሲኦልና ሐዴስ አንድ አይደሉም
በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ የሚለውን ለማጥናት መንገዱን ለመጥረግ፣ ሲኦልና ሐዴስ አንድ አለመሆናቸውን ላሳስባችሁ። በእንግሊዝኛው «የተፈቀደ ትርጉም» «ሲኦል» የሚለው ቃል የሚገኝባቸው፣ በ«ተከለሰው ትርጉም» ግን ያ ቃል የማይገኝባቸውና በ«ሲኦል» ፈንታ «ሐዴስ» የሚለው ቃል የገባባቸው ብዙ ስፍራዎች አሉ። የግሪክ ቋንቋ ሊቅ ሁሉ እንደሚያውቀው፣ «የተከለሰው ትርጉም» በዚህ ነጥብ ትክክል ነው። ሐዴስ ሲኦል አይደለም። «ሐዴስ» የብሉይ ኪዳኑ የዕብራይስጥ ቃል «ሺኦል» የግሪክ አቻ ነው። ይህ «ሺኦል» የሚለው የዕብራይስጥ ቃል በእንግሊዝኛው «የተፈቀደ ትርጉም» ብሉይ ኪዳን ብዙ ጊዜ «መቃብር» በሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ተተርጕሟል። ፈጽሞ እንዲህ መተርጐም አልነበረበትም፤ «መቃብር» ማለት ፈጽሞ አይደለምና። ይህ የዕብራይስጥ ቃል የተጠቀሰበትን እያንዳንዱን ክፍል በትጋት መርምሬአለሁ፤ በአንድም ስፍራ «መቃብር» ማለት አይደለም። በዚያ መንገድ በትክክል ሊተረጐም የሚችል ፈጽሞ የተለየ የዕብራይስጥ ቃል አለ። «ሺኦል»፣ ወይም የአዲስ ኪዳኑ «ሐዴስ»፣ የሙታን መናፍስት የሚሄዱበት ስፍራ ማለት ነው። ሺኦል (ወይም ሐዴስ) ከጌታችን መምጣት፣ ሕይወት፣ ሞት፣ ትንሣኤና ዕርገት በፊት መልካሞችም ክፉዎችም የሙታን መናፍስት ሁሉ የሚሄዱበት ስፍራ ነበር። ከክርስቶስ ዕርገት በፊት በሐዴስ ውስጥ የተባረኩ ሙታን ስፍራ የሆነችው ገነትና የክፉ ሙታን ስፍራ የሆነው ታርታሮስ ነበሩ። ክርስቶስ ባረገ ጊዜ በሐዴስ የነበረችውን ገነት ባዶ አድርጎ ከእርሱ ጋር ወደ ሰማይ ወሰዳት፤ በኤፌሶን 4:8 «ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ» ብለን እንደምናነበው። ክርስቶስ ከማረጉ በፊት ገነት በታች ነበረች፤ አሁን ግን በላይ ናት። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ንስሐ ለገባው ወንበዴ «እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ» አለው፤ ኢየሱስ ራሱም ወደ «ምድር ልብ» እንደሚወርድ አስተምሮናል (ማቴዎስ 12:40)፤ የሚሞተውም ወንበዴ ከእርሱ ጋር ወደዚህ ከምድር በታች ወዳለችው ገነት ወረደ። ኢየሱስ ራሱ የጠፉ መናፍስት ወደሚገኙበት የሐዴስ ክፍልም የሄደ ይመስለኛል (1ኛ ጴጥሮስ 3:18-20)፤ ይህ ግን በኋላ የምንመለከተው ሌላ ታሪክ ነው። አሁን አስፈላጊው ይህ ብቻ ነው፤ ንስሐ የገባው የሚሞተው ወንበዴ ወደ ገነት ወረደ፤ ከጌታ ዕርገት በኋላ ግን ጳውሎስ ወደ ገነት በሄደ ጊዜ «እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ»፣ «ወደ ገነት ተነጠቀ» (2ኛ ቆሮንቶስ 12:2-4)። አሁን በሐዴስ የቀሩ የተባረኩ ሙታን የሉም፤ በመጨረሻም «ሞት» እና «ሐዴስ»፣ ማለትም ገና ያልተነሡ ወይም ወደ ሰማያዊቱ ገነት ያልተነጠቁ ሙታን ሁሉ፣ አሁንም በሐዴስ ያሉ ሁሉ፣ «በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ» ተብሎ እንደ ተጻፈው ይጣላሉ (ራእይ 20:14)። ሞትና ሐዴስ የሚጣሉበት ይህ «የእሳት ባሕር» እውነተኛውና የመጨረሻው ሲኦል ነው።
2. እውነተኛ ሲኦል ይኖራል
ሲኦልና ሐዴስ አንድ ናቸው የሚለውን በዛሬው ዘመን በሰዎች አእምሮ ውስጥ የተለመደውን የተሳሳተ ግንዛቤ በማስወገድ መንገዱን ከጠረግን በኋላ፣ አሁን በመቀጠል ሲኦል እንደሚኖር እንናገር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ ኢየሱስ በማቴዎስ 5:22 እንዲህ ይላል፦ «እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል።» በዚያው ምዕራፍ በቍጥር 29 ጌታ ኢየሱስ እንዲህ ይላል፦ «ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና።» በቍጥር 30 ደግሞ እንዲህ ይላል፦ «ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና።» ጌታችን ኢየሱስ በማርቆስ 9:45-48 የተናገረውንም ደግሞ እናነባለን፦ «እግርህም ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጣት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል፤ በዚያ ትላቸው አይሞትም እሳቱም አይጠፋም።» አንድ ሰው እነዚህ የጌታችን ቃሎች ምሳሌያዊ ናቸው ይል ይሆናል። ምሳሌያዊ መሆናቸውን የሚጠቍም ትንሽ ፍንጭ እንኳ የለም። ዐውዱ ሁሉ ምሳሌያዊ ሆነው እንዳይወሰዱ ይቃወማል። ምሳሌያዊ አነጋገርን ቃል በቃል እንደ ሆነ አድርጎ መተርጐም በእርግጥ ስሕተት ነው፤ ነገር ግን ቃል በቃል የሆነን አነጋገር ምሳሌያዊ እንደ ሆነ አድርጎ መተርጐምም እንዲሁ መሠረት የሌለውና እንዲሁ ስሕተት ነው። እርግጥ ነው፣ «ሲኦል» ተብሎ የሚተረጐመው «ገሃነም» የሚለው ቃል ከሄኖም ሸለቆ የተገኘ ነው፤ በዚያም በጥንት ዘመን ሰዎች ይሠዉ ነበር፤ ነገር ግን የቃሉ ምንጭ ምሳሌያዊ ቢሆንም፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሁሉ አጠቃቀሙ ቃል በቃል ነው፤ ምሳሌያዊ የሆነው ምንጩ ብቻ ነው። በምንጫቸው ምሳሌያዊ የሆኑ ብዙ ቃላት በአጠቃቀማቸው ቃል በቃል ናቸው፤ የቃላትም ትርጉም ፈጽሞ የሚወሰነው በአጠቃቀም እንጂ በምንጭ አይደለም። ለምሳሌ «ግርዶሽ» ተብሎ የሚተረጐመው የእንግሊዝኛው «ኢክሊፕስ» የሚለው ቃል ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። በምሳሌው መሠረት፣ የተጋረደው የትኛውም ቢሆን፣ የጨረቃ ወይም የፀሐይ መተው፣ መጕደል ወይም መዛል ማለት ነው። ምንጩ ምሳሌያዊ ቢሆንም የተለመደው አጠቃቀሙ ግን ቃል በቃል ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ «ገሃነም» ወይም «ሲኦል» የሚለው ቃል የሚሠራበት በየትም ስፍራ ቃል በቃል ነው። እዚህ «ሲኦል» ተብሎ የተተረጐመው ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ አሥራ ሁለት ጊዜ ይገኛል፤ ከእነዚህ ከአሥራ ሁለቱ አሥራ አንዱን ጊዜ የተጠቀመበት ጌታችን ኢየሱስ ራሱ ነው፤ እርሱም አሁን ባነበብኋቸው ክፍሎች እንደሚታየው፣ ዘወትር ስለ እውነተኛ ሲኦል ይጠቀምበታል። እውነተኛ ሲኦል ከሌለ፣ ጌታችን ኢየሱስ ወይ ሞኝ ወይ አታላይ ነበር። እውነተኛ ሲኦል እንዳለ የሚያሳይ ስሜት ሊሰጥ እንዳሰበ ምንም ጥርጥር የለውም። ወደ ቃሎቹ ሄደን ተፈጥሮአዊ ትርጉማቸው ምን እንደ ሆነ ብንመረምር በዚህ ላይ ምንም ጥርጥር ሊኖር አይችልም። እውነተኛ ሲኦል ከሌለ፣ ወይ ኢየሱስ ሳይኖር ያለ መስሎት ነበር፣ እንዲህ ከሆነ ሞኝ ነበር፤ ወይም እንደሌለ እያወቀ ሰዎች እንዳለ እንዲያስቡ ለማድረግ ሞከረ፣ እንዲህ ከሆነ አታላይ ነበር። እውነተኛ ሲኦል እንዳለ ከማመን፣ ወይም የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ ጌታችንና መድኃኒታችን፣ ሞኝ ወይም አታላይ ነበር ብሎ ከማመን በቀር ሌላ አማራጭ የለም። ኢየሱስ ሞኝ እንዳልነበረ አውቃለሁ። እርሱ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እንደ ሆነ፣ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት እንደሚኖርበት፣ እርሱና አብ አንድ እንደ ሆኑ፣ ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ እንደሚገባ አውቃለሁ። የእግዚአብሔርን ቃል ራሱን እንደ ተናገረ አውቃለሁ፤ ስለዚህ እውነተኛ ሲኦል እንዳለ አውቃለሁ፤ እርሱ እንዲህ ብሎአልና። ደግሞም ዛሬ ምሽት ያነበብኋችሁ እነዚህ ስለ ሲኦል የተነገሩ ቃሎች አብዛኞቹ ከተራራው ስብከት የተወሰዱ መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባዋል፤ ይህም ሰዎች ሁሉ ማለት ይቻላል እናምነዋለን የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ እርግጠኞች አይደለንም፣ የተራራውን ስብከት ግን እንቀበላለን የሚሉ ብዙዎች አሉ። እንግዲህ እነዚህ ክፍሎች በአብዛኛው ከተራራው ስብከት የተወሰዱ ናቸው። ወይ ይህን የተራራውን ስብከት ክፍል ተቀበሉ፣ ወይም ሁሉንም የሞኝ ወይም የአታላይ ንግግር አድርጋችሁ ጣሉት። ነገሮችን እስከ መጨረሻ ለማሰብ ፈቃደኛ ለሆነ ሰው ሁሉ ሌላ ሊቆምበት የሚችል መሠረት የለም።
3. የሲኦል እሳት እውነተኛ እሳት ነውን?
ቀጥሎ የሚገጥመን ጥያቄ፣ ካነበብናቸው ክፍሎች በአንዳንዶቹ የተጠቀሰው የሲኦል እሳት እውነተኛ እሳት ነውን? የሚለው ነው። ይህ ጥያቄ እውነተኛ ሲኦል አለን? እንደሚለው ጥያቄ ወሳኝ አይደለም፤ ቢሆንም አስፈላጊ ጥያቄ ነው፤ ጥያቄውም በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ደግሞም በኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በግልጥ የተመለሰ ይመስለኛል። ቀደም ብለን ወደ ጠቀስነው ክፍል፣ ወደ ማቴዎስ 5:22 እንደገና ስንመለስ እንዲህ እናነባለን፦ «እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል።» እነዚህ የክርስቶስ የራሱ ቃሎች ናቸው። እርሱ ስለ ሲኦል ብቻ ሳይሆን ስለ «ገሃነመ እሳት» ይናገራል፤ ይህም ደግሞ ከተራራው ስብከት የተወሰደ ነው። በማቴዎስ 18:9 ጌታ ኢየሱስ እንደገና እንዲህ ይላል፦ «ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።» ደግሞም ከጥቂት ጊዜ በፊት ባነበብነው ክፍል፣ በማርቆስ 9:43-49 እንዲህ እናነባለን፦ «እጅህም ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከምትሄድ ይልቅ ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። እግርህም ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጣት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል፤ በዚያ ትላቸው አይሞትም እሳቱም አይጠፋም።» እዚህም እንደገና አንዳንዶች እሳቱ ምሳሌያዊ ነው ይሉ ይሆናል። ወደ ማቴዎስ 13:30፣ 41፣ 42 ዞር በሉ፤ እነዚህን ቃሎች እናነባለን፦ «እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን። እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ»። እንግዲህ ይህ ምሳሌ ነው፤ በውስጡም ምሳሌያዊ ነገሮች አሉ፤ ያለን ይህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ በቍጥሩ ውስጥ ያሉ ሌሎች ነገሮች ምሳሌያዊ እንደ ሆኑ እሳቱም ምሳሌያዊ ነው ለማለት ምክንያት በኖረ ነበር፤ ነገር ግን በዚያው ምዕራፍ በቍጥር 41ና 42 እንዲህ እናነባለን፦ «የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።» እዚህ የምሳሌው ትርጓሜ አለን። እንግዲህ ቀደም ብለን እንደ ተናገርነው፣ በምሳሌዎች ውስጥ ምሳሌያዊ ነገሮች አሉ፤ በምሳሌዎች ትርጓሜ ውስጥ ግን ምሳሌያዊ ነገሮቹ የሚወክሏቸው ቃል በቃል የሆኑ እውነታዎች አሉ፤ እዚህም በምሳሌው ውስጥ ብቻ ሳይሆን በትርጓሜውም ውስጥ እሳት እንዳለ በግልጥ እናያለን። በምሳሌው ውስጥ ያለው ሌላው ነገር ሁሉ ተብራርቷል፤ ከእሳቱ በቀር በምሳሌው ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ነገር ተብራርቷል፤ እሳቱ ግን በምሳሌው ውስጥ እንደ ሆነ ሁሉ በምሳሌው ትርጓሜ ውስጥም እሳት ሆኖ ይቀራል። በቍጥር 47 እስከ 50 ባለው በሌላው ምሳሌ፣ ወደ ባሕር በተጣለው መረብ ምሳሌ ውስጥም ይህንኑ እናገኛለን። እዚህም ደግሞ በምሳሌው ውስጥ እንደ ሆነ ሁሉ በምሳሌው ትርጓሜ ውስጥም እሳት አለን። የምሳሌው ሌላው ምሳሌያዊ ነገር ሁሉ በሚወክለው ቃል በቃል በሆነ እውነታ ተብራርቷል፤ በምሳሌው ትርጓሜ ውስጥ ግን «እሳት» አለን። ከእነዚህ እውነታዎች አንጻር፣ ምክንያታዊ የሆነውን የትርጓሜ ሕግ ሁሉ ሳንጥስ የሲኦልን እውነተኛ እሳት ልንክድ አንችልም። ከዚህም በላይ፣ በራእይ 20:15 በታላቁ ነጭ ዙፋን ፍርድ ጊዜ «በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ» ብለን እናነባለን። በዐውዱ ሁሉ ውስጥ ምሳሌያዊ አነጋገርን የሚጠቍም ምንም ነገር የለም። በምዕራፍ 21 ቍጥር 8 ደግሞ እንዲህ እናነባለን፦ «ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው።»
ደግሞም በዘላለማዊው ዓለም ያሉ ክፉዎች ሥጋ የሌላቸው መናፍስት ብቻ እንዳልሆኑ አስታውሱ። ይህ ከብሉይ ኪዳንም ከአዲስ ኪዳንም ግልጥ ነው። በዳንኤል 12:2 እንዲህ እናነባለን፦ «በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎቹ ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፣ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና።» እንግዲህ ይህ «በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት» ይላል። ነፍስ ወደ ሐዴስ ትሄዳለች። ፈርሶ ትቢያ የሚሆነው ሥጋ ነው፤ የሚነሣውም ሥጋ ነው። በአዲስ ኪዳን፣ በዮሐንስ 5:28፣ 29 ጌታችን እንዲህ እንዳለ ተጽፏል፦ «በዚህ አታድንቁ፤ በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።» እንግዲህ በመቃብር ያሉት የሰዎች ነፍሳት አይደሉም፤ የሰዎች ሥጋ ነው፤ ይህም ክፍል የመልካሞችንም የክፉዎችንም የሥጋ ትንሣኤ ያስተምራል። በ1ኛ ቆሮንቶስ 15:22 «ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና» ብለን እናነባለን። ጳውሎስ በዚህ ምዕራፍ ሁሉ የሚናገረው ስለ ነፍስ አለመሞት ብቻ ሳይሆን ስለ ሥጋ ትንሣኤ ነው፤ እዚህም እያንዳንዱ የአዳም ልጅ በክርስቶስ የሥጋውን ትንሣኤ እንደሚያገኝ በግልጥ ተነግሮናል።
ከዚህም በላይ፣ በማቴዎስ 5:30 ኢየሱስ እንዲህ ይላል፦ «ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና።» እዚህ ሥጋ ወደ ሲኦል እንደሚሄድ በተቻለ መጠን ግልጥ በሆነ ቃል ተነግሯል፤ በተመሳሳይ መንገድም በማቴዎስ 10:28 ጌታ ኢየሱስ እንዲህ ይላል፦ «ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።» ከእነዚህ ግልጥና ቍርጥ ከሆኑ የጌታችን ቃሎች፣ በሚመጣው ሕይወት ሥጋ እንደሚኖረን፣ የጠፉትም ሰዎች ሥጋ በእውነተኛና በሥጋዊ የእሳት ሲኦል ውስጥ ስፍራ እንደሚኖረው እንደ ቀን ብርሃን ግልጥ ነው። የሲኦል እሳት ሥጋዊ ሥቃይ የሲኦል እጅግ አስፈሪው ገጽታ ባይሆንም፣ የአእምሮ ጭንቀት፣ የጸጸት ጭንቀት፣ የእፍረት ጭንቀትና የተስፋ መቍረጥ ጭንቀት የከፋ፣ ሊለካ በማይችል መጠን የከፋ ቢሆንም፣ ቢሆንም ሥጋዊ ሥቃይ፣ በምድር ላይ ያለ የትኛውም ሕመም ከእርሱ ጋር ሲነጻጸር ምንም የማይሆንበት ሥጋዊ ሥቃይ፣ የሲኦል አንዱ ገጽታ ነው።
4. የእሳቱ ባሕር የነቃ ሥቃይ ስፍራ ነውን፣ ወይስ የመደምሰስ፣ ማለትም ያለ መኖር ስፍራ፣ ወይስ ያለ ንቃት የመኖር ስፍራ ነው?
ገና መልስ የሚያስፈልገው አንድ ሌላ ጥያቄ ቀርቶአል፤ እርሱም፦ የእሳት ባሕር በንቃተ ህሊና የሚሠቃዩበት ስፍራ ነውን? ወይስ ፈጽሞ የሚጠፉበት፣ ማለትም ሕልውና የሌለበት ስፍራ ነው? ወይስ ንቃተ ህሊና በሌለበት ሁኔታ የሚኖሩበት ስፍራ ነው? የሚል ነው። ቃል በቃል ሲኦል እንዳለ የሚያምኑ፣ ነገር ግን ወደዚያ የሚጣሉት ለረጅም ጊዜ በንቃተ ህሊና እንደሚሠቃዩ የማያምኑ ሰዎች አሉ። እነርሱ ወደ ሲኦል የሚላኩት ፈጽሞ ይጠፋሉ፣ አለዚያም ንቃተ ህሊና በሌለበት ሁኔታ በዚያ ይኖራሉ ብለው ያስተምራሉ። በእርግጥ ይህም ዘላለማዊ ሲኦልና ዘላለማዊ ቅጣት ይሆናል፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ሲኦል ይህ ነውን? የእሳት ባሕር የማያቋርጥ፣ በንቃተ ህሊና የሚደርስ ሥቃይ ስፍራ ነውን? ወይስ ንቃተ ህሊና የሌለበት ሕልውና ስፍራ ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ እንዲሆን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የኃጥኣን ቅጣት በአብዛኛው «ሞት» እና «ጥፋት» ተብሎ እንደሚጠራ ልብ እንድትሉ እወዳለሁ። እነዚህ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም ምን ማለት ናቸው?
1. በመጀመሪያ «ሞት» የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደ ተሠራበት እንመልከት። ብዙዎች ሞት ማለት ሕልውና ማጣት፣ ወይም ቢያንስ ንቃተ ህሊና የሌለው ሕልውና ማለት እንደ ሆነ ደጋግመው ይነግሩናል፤ ስለዚህም ንስሐ ለማይገቡ ሰዎች የሚመጣው ቅጣት ተብሎ በተጠቀሰባቸው ክፍሎችም ትርጉሙ ይኸው መሆን አለበት ይላሉ። ነገር ግን «ሞት» በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም ንቃተ ህሊና የሌለው ሕልውና ወይም ፈጽሞ መጥፋት ማለት ነውን? በመጀመሪያ 1ኛ ጢሞቴዎስ 5:6ን ተመልከቱ፤ በዚያም «ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት» እናነባለን። እዚህ ሞት በእርግጥ ሕልውና ማጣትንም ሆነ ንቃተ ህሊና የሌለውን ሕልውና አያመለክትም። በቅምጥልነት የምትኖረው ሴት አሁንም በሕይወት አለች፤ በንቃተ ህሊናም እንደምትኖር የታወቀ ነው፤ ቢሆንም «የሞተች» ናት። ሞት ማለት ሕልውና ማጣት ሳይሆን የተሳሳተ ሕልውና ማለት ነው። ሞት የሕይወት ፍጹም ተቃራኒ ነው፤ ሕይወት ደግሞ በአዲስ ኪዳን አጠቃቀም ዝም ብሎ መኖር ማለት አይደለም፤ ትክክለኛ ሕልውና፣ እግዚአብሔርን የሚመስል ሕልውና፣ ቅዱስ ሕልውና ማለት ነው። ሕይወት የሕልውና መክበር፣ መወደስና መለኮታዊ ባሕርይ መካፈል ማለት ነው፤ ሞት ደግሞ ፍጹም ተቃራኒው ነው፤ የተሳሳተ ሕልውና፣ የረከሰ ሕልውና፣ የሕልውና መፍረስ፣ እፍረት፣ ውርደትና ተስፋ መቍረጥ ማለት ነው። በተመሳሳይ መንገድ በኤፌሶን 2:1 ሰዎች በእግዚአብሔር ኃይል ሕያዋን እስኪሆኑ ድረስ «በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን» እንደ ሆኑ ተነግሮናል። እንግዲህ ሞት ሕልውና ማጣትን ወይም ንቃተ ህሊና የሌለውን ሕልውና እንደማያመለክት ፍጹም ግልጽ ነው። ከዚህም የበለጠ ቍርጥ የሆነው ግን እግዚአብሔር ራሱ በራእይ 21:8 ሞትን እጅግ በትክክልና በሙላት መግለጹ ነው፦ «ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው።» እዚህ በግልጽ ቃል የምንማረው፣ በኃጢአትና ባለማመን የመጽናት የመጨረሻ ውጤት የሆነው «ሞት» በሥቃይ ስፍራ፣ ማለትም በእሳት ባሕር ውስጥ ዕድል ፈንታ መሆኑን ነው። ይህ የእሳት ባሕር በንቃተ ህሊና የሚሠቃዩበት ስፍራ እንደ ሆነ ደግሞ ከዚህ በፊት ባለው ምዕራፍ በራእይ 20:10 ተገልጦአል፤ በዚያም «ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ» ተብሎ ተነግሮናል። ዲያብሎስ ወደ እሳት ባሕር በተጣለ ጊዜ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ በዚያ ሺህ ዓመት ቆይተው ነበር፤ እነርሱም ያለ ዕረፍት በንቃተ ህሊና ይሠቃዩ ነበር።
2. አሁን ደግሞ «ጥፋት» በአዲስ ኪዳን ምን ማለት እንደ ሆነ እንመልከት። አንድ የሃይማኖት አስተሳሰብ ወገን «ጥፋት» ማለት ጥፋት ነው ይለናል። አዎን፣ «ጥፋት» ማለት ጥፋት ነው፤ ነገር ግን ጥፋት ምን ማለት ነው? እነርሱ ፈጽሞ መጥፋት ወይም መኖር ማቆም ማለት ነው ይላሉ፤ ነገር ግን እንዲህ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ፈጽሞ ይህን ትርጉም አይሰጥም። በዛሬው ጊዜ ካሉት የአዲስ ኪዳን የግሪክኛ-እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ሁሉ የሚበልጠው፣ የግሪም ታላቅ ሥራ የታየር ትርጉም፣ አንድ ነገር «ጠፋ» ሲባል (በብዛት «ጥፋት» እና «ፍዳ» ተብሎ የሚተረጎመው ስም የተገኘበት ግስ «መጥፋት» ተብሎ የሚተረጎመው ነው) መኖሩ አቆመ ማለት ሳይሆን «ለተሠራበት ዓላማ ከእንግዲህ ወዲህ እስከማይጠቅም ድረስ ተበላሸ» ማለት እንደ ሆነ ይነግረናል። ከዚህም በላይ፣ በዚህም ቦታ እግዚአብሔር ቃላቱን ለመፍታት ተጠንቅቆአል። እርሱ ራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ የ«ጥፋት»ን ትርጉም ሰጥቶናል። በራእይ 17:8፣ 11 እንዲህ እናነባለን፦ «ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፥ አሁንም የለም፥ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ … በምድር የሚኖሩ … ያደንቃሉ። … የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው ከሰባቱም አንዱ ነው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል።» እዚህ አውሬው ወደ «ጥፋት» እንደሚሄድ ተነግሮናል። በዚህ ስፍራ በእንግሊዝኛው ትርጉም «ፍዳ» ተብሎ የተተረጎመው ቃል በሌሎች ስፍራዎች «ጥፋት» ተብሎ ከተተረጎመው ቃል ጋር ፍጹም አንድ ነው፤ እዚህም እንዲሁ «ጥፋት» ተብሎ መተርጎም ይገባው ነበር፤ አለዚያም በሌሎቹ ስፍራዎች እንደዚህኛው «ፍዳ» ተብሎ መተርጎም ይገባው ነበር። እንግዲህ አውሬው ወዴት እንደሚሄድ ማወቅ ከቻልን «ጥፋት» ምን ማለት እንደ ሆነ በትክክል እናውቃለን፤ እርሱ «ወደ ጥፋት» እንደሚሄድ ተነግሮናልና። በራእይ 19ኛው ምዕራፍ፣ በ20ኛው ቁጥር አውሬው ወዴት እንደሚሄድ በትክክል ተነግሮናል፦ «አውሬውም ተያዘ በእርሱም ፊት ተአምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ።» ቀጥሎ ወዳለው ምዕራፍ፣ ቀደም ብዬ ወደ ጠቀስሁት ወደ 10ኛው ቁጥር ስንሄድ እንዲህ እናነባለን፦ «ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ።» እነዚህን ክፍሎች አንድ ላይ ስናገናኛቸው አውሬው ወደ «ጥፋት» እንደሚሄድ፣ የሚሄድበትም ጥፋት በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ውስጥ ያለ ስፍራ እንደ ሆነ እናያለን፤ በዚያም ለሺህ ዓመት በንቃተ ህሊና ይሠቃያል፤ ሺሁ ዓመት ካለፈም በኋላ አሁንም በዚያው አለ፤ አሁንም ይሠቃያል። እንግዲህ «ጥፋት» በአዲስ ኪዳን «ሞት» በተፈታበት በዚያው መንገድ፣ በንቃተ ህሊና የሚሠቃዩበት ስፍራ ያሉ ፍጡራን ሁኔታ ተብሎ በግልጽ ተፈትቶአል።
ደግሞም በራእይ 14:10፣ 11 ለአውሬውና ለምስሉ ስለሚሰግዱትና ምልክቱን በግንባራቸው ወይም በእጃቸው ስለሚቀበሉት እንዲህ እናነባለን፦ «እርሱ ደግሞ በቍጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፥ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሳቀያል። የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፥ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት የሚቀበል ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።» ለበጉ በሆነው በሕይወት መጽሐፍ «ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም» የሚጣልበት የእሳት ባሕር የማያቋርጥ፣ በንቃተ ህሊና የሚደርስ ሥቃይ ስፍራ እንደ ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ ሊያስረዳ በሚችለው መጠን ግልጽ አድርጎታል። መጽሐፍ ቅዱሳችንን ጥለን የሐዋርያትንና የኢየሱስ ክርስቶስን የራሱን ትምህርት ካላቃለልን በቀር ከዚህ ግልጽ የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ማምለጥ አንችልም።
በሚቀጥለው እሑድ ምሽት «የኃጥኣን ቅጣት ዘላለማዊ ነውን?» የሚለውን ጥያቄ እንመለከታለን፤ ዛሬ ምሽት ግን እዚህ ላይ ማቆም አለብን። ሸርማን «ጦርነት ሲኦል ነው» ብሎአል። ሸርማን ባሰበው መንገድ ይህ እውነት እንደ ሆነ የታወቀ ነው። ይህ ደግሞ ከእርስ በርስ ጦርነታችን እጅግ የከፉና ፈጽሞ ይቅርታ የማይገባቸው ገጽታዎች ይልቅ — ለምሳሌ ከደቡብ ወገን ሊቢና አንደርሰንቪል፣ ከሰሜን ወገን ደግሞ በጆርጂያ በኩል የተደረገው ጉዞ — በዛሬው ጦርነት እጅግ የበለጠ እውነት ነው። ነገር ግን ጀርመን በሚያስደነግጥ ጭካኔዋ ሁሉ የምታካሂደው የዛሬው ጦርነት እንኳ ሲኦል አይደለም። ሲኦል አሁን በአውሮፓ ከሚፋፋመው ጦርነት በማይነጻጸር ሁኔታ እጅግ የሚያስፈራ ነው፤ ዛሬ ምሽት ያጠናነው ይህ አስፈሪ ሲኦል ደግሞ ፈጥናችሁ ንስሐ ገብታችሁ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ካልተቀበላችሁ በቀር፣ በዚህ ክፍል ውስጥ ካላችሁት ለአንዳንዶቻችሁ ዕጣ ፈንታችሁ ነው። ስለ ሲኦል ሌሎች አስደንጋጭ እውነቶችን በሚቀጥለው እሑድ ምሽት እንመለከታለን፤ ነገር ግን ማንኛውም እውነተኛ ክርስቲያን ሌሎችን ከዚህ አስፈሪ ሲኦል ለማዳን በሙሉ ኃይሉ ለመሥራት እንዲወስን የሚያደርግ በቂ ነገር አይተናል። ደግሞም ዛሬ ምሽት እዚህ ያለ ማንኛውም ቅንና አስተዋይ ሰው ምንም ዋጋ ቢያስከፍለው ከዚህ አስፈሪ ሲኦል ለማምለጥ እንዲወስን የሚያደርግ በቂ ነገር አይተናል።