ምዕራፍ 20 · 9 ደቂቃ ንባብ · 12 ደቂቃ ማዳመጥ
4.3 የእግዚአብሔር ቃል
ከእግዚአብሔር ቍጣና እርግማን የምናመልጥበትና በክርስቶስ የሆነውን የቤዛነት ጥቅም የምናገኝበት ሦስተኛው መንገድ የእግዚአብሔርን ሥርዓቶች በትጋት መጠቀም ነው፤ በተለይም «ቃሉን፥ ምሥጢራትንና ጸሎትን»።
ከእነዚህ ሥርዓቶች እጅግ በሚበልጠው እጀምራለሁ።
«በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል»። 1ተሰ 2፥13።
ቃሉ በሥራ ይሠራል ማለት ምን ማለት ነው?
የእግዚአብሔር ቃል በሥራ ይሠራል የሚባለው እግዚአብሔር ለእርሱ የወሰነውን መልካም ውጤት በእኛ ላይ ሲያመጣ ነው፤ ይኸውም ብርቱ ብርሃንንና ፍጹም መታደስን ሲያደርግ ነው። «ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸው ዘንድ።» ሐዋ 26፥18። ዓይናቸው መከፈቱ ብርሃንን ያመለክታል፤ ከሰይጣን ወደ እግዚአብሔር መመለሳቸውም መታደስን ያመለክታል።
ቃሉ ለመዳን በሥራ እንዲሠራ እንዴት ልናነበውና ልንሰማው ይገባል?
ይህ ጥያቄ ሁለት ቅርንጫፎች አሉት።
ቃሉን በሥራ እንዲሠራ እንዴት እናንብበው?
ቃሉን ለመዳናችን በሥራ በሚጠቅም መንገድ እናነብ ዘንድ፥
(1) ለቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል ሁሉ የአክብሮት ግምት ይኑረን። «ከወርቅ ይልቅ የሚወደዱ ናቸው።» መዝ 19፥10። የእግዚአብሔርን መጽሐፍ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ በላይ አክብሩት። ይህ በመንፈስ ቅዱስ የተጻፈና ከሰማይ የተላከልን የወርቅ መልእክት ነው። ግምታችንን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ነፍሳችንን የምናስጌጥበት መንፈሳዊ መስተዋት ነው። በተፈጥሮ ሕሊና ብርሃን ከምናየው የበለጠ ያሳየናል። ሕሊና ግዙፍ ኃጢአቶችን ሊገልጥ ይችላል፤ የቃሉ መስተዋት ግን የልብ ኃጢአቶችን፥ ከንቱ ሐሳቦችን፥ አለማመንንና የመሳሰሉትን ያሳየናል። እድፋችንን ማሳየት ብቻ ሳይሆን ያጥበዋልም። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን ለመዋጋት መንፈሳዊ የጦር መሣሪያ የምናወጣበት ግምጃ ቤት ነው። መድኃኒታችን በዲያብሎስ በተፈተነ ጊዜ ጋሻውንና መሣሪያውን ከመጻሕፍት አወጣ፤ «ተብሎ ተጽፎአል» አለ። ማቴ 4፥4, 7። ቅዱሱ መጽሐፍ ለነፍስ የሁሉ ፈውስ መድኃኒት ነው፤ ለልብ መደንዘዝ፥ መዝ 119፥50፤ ለትዕቢት፥ 1ጴጥ 5፥5፤ ለአለማመንም፥ ዮሐ 3፥36 መድኃኒት ያዝዛል። የኃጢአትን መርዝ የሚያስወጣ ቅጠልና ማርከሻ የምንለቅምበት የመድኃኒት አትክልት ቦታ ነው። የመጻሕፍት ቅጠሎች እንደ ሕይወት ዛፍ ቅጠሎች «ለሕዝብ መፈወሻ» ናቸው። ራእ 22፥2። ይህ ለቃሉ የአክብሮት ግምት ሊያሳድርብን አይገባምን?
(2) የተጻፈው ቃል በነፍሳችን ላይ እንዲሠራ ከፈለግን «በሙሉ ልብ ትኵረት» እናንብበው። «መጻሕፍትን መርምሩ።» ዮሐ 5፥39። ኤሩናቴ (ereunate) የሚለው የግሪክ ቃል «የብር ሥር» እንደሚፈለግ መፈለግ ማለት ነው። የቤርያ ሰዎች «ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ» ነበር። ሐዋ 17፥11። አናክሪኖንቴስ (anakrinontes) የሚለው ቃል በጥንቃቄና በጥልቀት መመርመር ማለት ነው። አጵሎስ በመጻሕፍት የበረታ ነበር። ሐዋ 18፥24። አንዳንዶች አንድን ምዕራፍ በችኰላ ይሽቀዳደሙበታል፤ ምንም ጥቅምም አያገኙበትም። ቃሉ በሥራ እንዲሠራና እንዲያድን ከፈለግን የመጻሕፍትን ክፍል ሁሉ ልብ ብለን ልንመለከት ይገባናል። መጻሕፍትን በትጋት እናነብ ዘንድ፥ የተጻፈው ቃል ኖርማ ኩልቱስ (norma cultus) [ብቸኛው የአኗኗር መለኪያ]፥ ሕይወታችንን የምናቃናበት ደንብና ንድፍ እንደ ሆነ እናስብ። ለመዳን የሚያስፈልገውን ሁሉ ይዟል፤ ምን ተግባሮችን እንድናደርግና ከምን ኃጢአቶች እንድንርቅ ይነግረናል። መዝ 19፥7። እግዚአብሔር ለሙሴ ማደሪያው እንዴት እንዲሠራ እንደሚፈልግ ምሳሌ ሰጠው፤ እርሱም ልክ እንደ ምሳሌው ሊሠራ ይገባው ነበር። ዘጸ 25፥9። ቃሉ ሕይወታችንን እንድንቀርጽበት እግዚአብሔር በጽሑፍ የሰጠን ምሳሌ ነው። ስለዚህ ይህን ምሳሌ በመከተልና በመመልከት ምንኛ ልንጠነቀቅ ይገባናል!
የተጻፈው ቃል ምሳሌያችን እንደ ሆነ እንዲሁ ፈራጃችንም ይሆናል። «እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል።» ዮሐ 12፥48። መጻሕፍት እንደ ተከፈቱ እናነባለን። ራእ 20፥12። እግዚአብሔር ከሚከፍታቸው መጻሕፍት አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ነው፤ በእርሱም ሰዎችን ይፈርዳል። «በዚህ ቃል ደንብ መሠረት ኖራችኋልን?» ይላቸዋል። ቃሉ ሁለት ሥራ አለው፤ ማስተማርና መፍረድ።
(3) የተጻፈው ቃል በሥራ እንዲሠራ ከፈለግን በምናነብበት ጊዜ እምነትን ይዘን እንቅረብ፤ የዘላለማዊው ያህዌ ቃል መሆኑን እናምን። በሥልጣን ይመጣል፤ ከሰማይ የተሰጠውንም ተልእኮ ያሳያል። «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።» በእግዚአብሔር መንፈስ የተነፈሰ ነው። 2ጢሞ 3፥16። የመጻሕፍት ቃል ከሰማይ ከሚመጣ ድምፅ ይልቅ በእኛ ዘንድ የጸና ሊሆን ይገባል። 2ጴጥ 1፥18, 19። አለማመን የመጻሕፍትን ኃይል ያደክማል፤ ፍሬ ቢስም ያደርገዋል። ሰዎች አስቀድመው የመጻሕፍትን እውነት ይጠራጠራሉ፤ ከዚያም ከእርሱ ይርቃሉ።
(4) የተጻፈው ቃል ለመዳን በሥራ እንዲሠራ ከፈለግን እንደ መንፈሳዊ ብርታት ሰጪ መጠጥ ደስ ልንሰኝበት ይገባል። «ቃልህ ተገኘ፥ በላሁትም፤ ቃልህም ለልቤ ደስታና ሐሤት ሆነልኝ።» ኤር 15፥16። እውነተኛና ጽኑ መጽናናት ሁሉ የሚገኘው ከቃሉ ነው። ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚለው ቃሉ መንፈሳዊ አትክልት ቦታ ነው፤ የተስፋ ቃላቱም በዚህ አትክልት ቦታ ያሉ መዓዛቸው የሚጣፍጥ አበቦችና ሽቱዎች ናቸው። በእነዚህ የሽቱ መደቦች መካከል ስንመላለስ ምንኛ ደስ ሊለን ይገባል! በሚያጠራጥርና በሚያስጨንቅ ጉዳይ ሁሉ የሚመክረን መካሪ ማግኘት መጽናናት አይደለምን? «ምስክሮችህ መካሪዎቼ ናቸው።» መዝ 119፥24። ወደ ሰማይ የመግባታችንን ማስረጃ ማግኘትስ መጽናናት አይደለምን? ከቃሉስ በቀር ከየት እናገኘዋለን? 1ተሰ 1፥4, 5። የተጻፈው ቃል በጭንቅ ሰዓት ኃያል መድኃኒትና መጽናኛ ነው። «ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና ይህች በመከራዬ መጽናኛዬ ናት።» መዝ 119፥50። «ውኃውን የወይን ጠጅ» እንደሚለወጥ መከራችንን ሁሉ ሊለውጥ ይችላል። በቃሉ እንዴት እጅግ ልንደሰትና ልንረካ ይገባናል! በደስታ ወደ ቃሉ የሚመጡ ብቻ በበረከት ይመለሳሉ።
(5) መጽሐፍ ቅዱስ በሥራ እንዲሠራና እንዲያድን ከፈለግን ቃሉን ካነበብን በኋላ በልባችን ልንሰውረው ይገባል። «ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።» መዝ 119፥11። በልብ ውስጥ የተቈለፈ ቃል ከኃጢአት ይጠብቃል። ዳዊት ቃሉን በልቡ የሰወረው ስለ ምንድር ነው? «አንተን እንዳልበድል።» ሰው ወደ ተበከለ ስፍራ ሲቀርብ ማርከሻ ይዞ እንደሚሄድ፥ ዳዊትም ከኃጢአት ብክለት ይጠብቀው ዘንድ ቃሉን እንደ ቅዱስ ማርከሻ በልቡ ይዞ ነበር። ልምላሜ በሥሩ ሲሰወር ቅርንጫፎቹን ፍሬያማ ያደርጋል፤ ዘርም በመሬት ሲሰወር እህሉ ይበቅላል፤ እንዲሁም ቃሉ በልብ ሲሰወር መልካም ፍሬ ያፈራል።
(6) የተጻፈው ቃል በሥራ እንዲሠራ ከፈለግን ብርሃኑ በራሳችን ብቻ ሳይሆን ኃይሉ በልባችን እንዲሆን እንትጋ። ቃሉ ተገልብጦ በልባችን ለሁለተኛ ጊዜ እንዲጻፍ እንጣጣር። «የአምላኩ ሕግ በልቡ ነው።» መዝ 37፥31። ቃሉ «ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ» ይላል። 1ጴጥ 5፥5። እንግዲህ በራሳችን ዓይን ዝቅተኞችና ትሑታን እንሁን። ቃሉ ቅድስናን ይጠይቃል። ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድንሆንና ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ ነገር በውስጣችን እንዲፀነስ እንትጋ። 2ጴጥ 1፥4። ቃሉ እንዲህ በልባችን ሲገለበጥና እኛም ወደ መልኩ ስንለወጥ፥ በእኛ ላይ በሥራ ይሠራል፤ የሕይወት መዓዛም ይሆንልናል።
(7) ቅዱሳት መጻሕፍትን በምናነብበት ጊዜ በረከትን ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር እንመልከት። «የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር» እናይ ዘንድ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንለምን። ኤፌ 1፥17፤ 1ቆሮ 2፥10። መጻሕፍትን የጻፈው ያው መንፈስ እንድናስተውላቸው እንዲያስችለን እግዚአብሔርን ለምኑ። በምናነበው ቃል ጣፋጭነትን እንድናጣጥም «የእውቀቱን ሽታ» እንዲሰጠን ጸልዩ። 2ቆሮ 2፥14። ዳዊት ቃሉን «ከማርና ከማር ወለላ ይልቅ ጣፋጭ» ሆኖ ቀመሰው። መዝ 19፥10። እግዚአብሔር ቃሉን የቅድስና ደንብ አድርጎ ብቻ ሳይሆን ጸጋውንም የቅድስና መሠረት አድርጎ እንዲሰጠን እንጸልይ።
ቃሉ በሥራ እንዲሠራና ነፍሳችንን እንዲያድን እንዴት ልንሰማው ይገባል?
(1) ለተሰበከው ቃል ታላቅ ትኵረት ስጡ። አንዳች ነገር ልብ ሳትሉት እንዲያልፍ አትፍቀዱ። «ሕዝቡ ሁሉ ሲሰሙት ተንጠልጥለውበት ነበርና።» ሉቃ 19፥48። ከአፉ በሚወጣው ቃል ላይ ተንጠልጥለው ነበር። «ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።» ሐዋ 16፥14። የሕይወትና የሞት ጉዳይ እንደ ሆነ ለቃሉ ትኵረት ስጡ። ለዚህም ዓላማ የሚበታትኗችሁንና ከያዛችሁት ሥራ የሚያዘናጉአችሁን ከንቱና የማይገቡ ሐሳቦችን ለማባረር ተጠንቀቁ። እነዚህ አሞሮች ወደ መሥዋዕቱ ይመጣሉ፤ ስለዚህ ልናባርራቸው ይገባናል። ዘፍ 15፥11። ቀስተኛ በትክክል ሊያነጣጥር ይችላል፤ ነገር ግን አንድ ሰው በክርኑ አጠገብ ቆሞ ሊወረውር ሲል ቢገፋው ዒላማውን አይመታም። ክርስቲያኖችም በመስማት መልካም ዓላማ ሊኖራቸው ይችላል፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር አገልግሎት የሚገፏችሁንና የሚያደናቅፏችሁን የማይገቡ ሐሳቦችን ተጠንቀቁ። ድንዛዜን አባርሩ። ዲያብሎስ ለብዙ ሰሚዎች የእንቅልፍ ጕርሻ ይሰጣቸዋል፤ ስለዚህም በስብከት ጊዜ ዓይናቸውን ገልጠው መቆየት አይችሉም። በጌታ ቀን እጅግ ስለሚበሉ ከቤተ መቅደስ ይልቅ ለትራስና ለአልጋ ይገባሉ። በስብከት ጊዜ ዘወትር እንደ ልማድ ማንቀላፋት ለሥርዓቱ ታላቅ ንቀትና አለማክበር እንዳለ ያሳያል። ለሌሎች ክፉ ምሳሌ ይሆናል፤ ቅንነታችሁን ያስጠረጥራል፤ የዲያብሎስ የዘር ወቅት ነው። «ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ።» ማቴ 13፥25 ጳውሎስ እፉኝቱን እንዳራገፈ ማንቀላፋትን አራግፉ! ቃሉን በመስማት ቍም ነገረኞችና ትኵረት ሰጪዎች ሁኑ። «ይህ ለእናንተ ከንቱ ነገር አይደለምና፥ ሕይወታችሁ ነው።» ዘዳ 32፥47። ሰዎች እግዚአብሔር በቃሉ የሚነግራቸውን ልብ ካላሉ፥ እግዚአብሔርም በጸሎት የሚሉትን እንዲሁ ጥቂት ልብ ይላል።
(2) የተሰበከው ቃል በሥራ እንዲሠራ ከፈለጋችሁ ቅዱስ ምኞትን ይዛችሁ ወደ ቃሉ ኑ። 1ጴጥ 2፥2። የተጠማች ነፍስ የምትለመልም ነፍስ ናት። በተፈጥሮ ሰው የምግብ ፍላጎት ኖሮት ማንሸራሸር ሊያቅተው ይችላል፤ በሃይማኖት ግን እንዲህ አይደለም። ለቃሉ ታላቅ ፍላጎት ባለበት በአብዛኛው መልካም መፈጨትም አለ። ቃሉ ደስ ብቻ ሳያሰኛችሁ እንዲጠቅማችሁም በነፍስ ረሃብ ተመኙትና ኑ። ከምግቡ ይልቅ የሳህኑን ጌጥ አትመልከቱ፤ ማለትም ከጽኑ ቍም ነገር ይልቅ አንደበተ ርቱዕነትንና የንግግር ውበትን። ከጤናማ ምግብ ይልቅ በሰላጣና በጣፋጭ ቍርስ መመገብ ቅምጥል ምላስንና የጠገበ ሆድን ያሳያል።
(3) የቃሉ ስብከት በሥራ እንዲሠራ ከፈለጋችሁ ልባችሁ ገር ሆኖ ኑ። «ልብህ ገር ስለ ሆነ።» 1ዜና 22፥5። ለደንዳና ልብ መስበክ የናስ ግንብ ላይ እንደ መተኰስ ነው፤ ቃሉ አይገባም። በዕብነ በረድ ላይ የወርቅ ማኅተም እንደ ማኖር ነው፤ ምንም ምልክት አይቀበልም። ወይ! በቀለጠ ልብ ወደ ተሰበከው ቃል ኑ! የማኅተሙን ምልክት የሚቀበለው የቀለጠ ሰም ነው፤ እንዲሁም ልብ በቀለጠ ሁኔታ ሲሆን የተሰበከውን ቃል ምልክት በተሻለ ይቀበላል። የጳውሎስ ልብ ስለ ኃጢአት በቀለጠና በተሰበረ ጊዜ «ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?» ብሎ ጮኸ። ሐዋ 9፥6። በደንዳና ልብ ወደዚህ አትምጡ። ዘሩ በጭንጫ መሬት ላይ ሲበቅል አዝመራን ማን ሊጠብቅ ይችላል?
(4) ቃሉ በሥራ እንዲሠራ ከፈለጋችሁ በየዋህነት ተቀበሉት። «በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ።» ያዕ 1፥21። የዋህነት ለቃሉ የሚገዛ የልብ ሁኔታ ነው፤ የቃሉን ምክርና ተግሣጽ ለመስማት ፈቃደኛ መሆን ነው። የዚህ የዋህነት ተቃራኒ ሰዎች በቃሉ ላይ በቍጣ ለመነሣት የሚዘጋጁበት የመንፈስ ጭካኔ ነው። ትዕቢተኞችና በደለኞች ሰዎች ስለ ስሕተታቸው መስማትን አይታገሡም። ትዕቢተኛው ሄሮድስ ዮሐንስን በወኅኒ አሳሰረው። ማር 6፥17። በደለኞቹ አይሁድ ክርስቶስን እንደ ሰቀሉ በተነገራቸው ጊዜ እስጢፋኖስን ወገሩት። ሐዋ 7፥59። ለሰዎች ስለ ኃጢአታቸው መንገር የራሱን ፊት ማየት ለማይታገሥ መልከ ጥፉ ሰው መስተዋት እንደ መያዝ ነው። የየዋህነት ተቃራኒም ቃሉ የፈለገውን ቢናገር ሰዎች ኃጢአታቸውን አጥብቀው ለመያዝ የሚወስኑበት የልብ እልከኝነት ነው። «ለሰማይ ንግሥት እናጥናለን።» ኤር 44፥17። ወይ! ከዚህ ተጠንቀቁ! የተሰበከው ቃል በሥራ እንዲሠራ ከፈለጋችሁ ጭካኔንና እልከኝነትን አስወግዱ፤ ቃሉንም በየዋህነት ተቀበሉ። የተሰበከው ቃል የሚተከለው በየዋህነት ነው። መልካም ቀንበጥ በክፉ ግንድ ላይ ሲከተብ የፍሬውን ባሕርይ እንደሚለውጥና እንደሚያጣፍጠው፥ እንዲሁ ቃሉ በነፍስ ውስጥ ሲተከል ይቀድሳታል፤ የጽድቅንም ጣፋጭ ፍሬ እንድታፈራ ያደርጋታል።
(5) የተሰበከውን ቃል ከእምነት ጋር አዋሕዱት። «የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም።» ዕብ 4፥2። በመድኃኒት ውስጥ ዋናውን ንጥረ ነገር ብትተዉ ሥራውን ያደናቅፋል፤ የእምነትን ንጥረ ነገር አትተዉ። ቃሉን እመኑ፤ ደግሞም ለራሳችሁ እስክታደርጉት ድረስ እመኑት። ክርስቶስ ሲሰበክ ስትሰሙ ለራሳችሁ ውሰዱት። ይህ ጌታን ኢየሱስን መልበስ ነው። ሮሜ 13፥14። የተስፋ ቃል ሲነገር ስትሰሙ ለራሳችሁ ውሰዱት። ይህ የተስፋውን ቃል አበባ መምጠጥና ወደ ማር መለወጥ ነው።
(6) በመስማት ጊዜ ትኵረት ሰጪዎች ብቻ ሳይሆን ከሰማችሁም በኋላ የምትይዙ ሁኑ። «ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል፤» ውኃ ከወንፊት እንደሚፈስ እንዳይፈስብን። ዕብ 2፥1። መሬት የተዘራበትን ዘር ካልያዘ መልካም አዝመራ አይገኝም። አንዳንዶች እንደሚያፈስሱ ዕቃዎች ያለ የማስታወስ ችሎታ አላቸው፤ የሚሰሙት ስብከት ወዲያው ይጠፋል፤ ምንም መልካም ነገርም አይደረግም። ምግብ በሆድ ውስጥ ቆይቶ ካልተፈጨ አይመግብም። ሰይጣን ቃሉን ከአእምሮ ለመስረቅ ይተጋል። «በሰሙት ጊዜም ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል ይወስዳል።» ማር 4፥15። የማስታወስ ችሎታችን ሕጉ እንደ ተቀመጠበት እንደ ታቦቱ ሣጥን ሊሆን ይገባዋል።
(7) የሰማችሁትን ወደ ተግባር ለውጡት። በምትሰሙት ስብከት ኑሩ። «ትእዛዛትህንም አደረግሁ።» መዝ 119፥166። ራሔል ውብ በመሆኗ አልረካችም፤ ምኞቷ ፍሬያማ መሆን ነበር። ፍሬያማ ልብ የሌለው አዋቂ ራስ ምንድር ነው? «በጽድቅ ፍሬ ተሞልታችሁ።» ፊልጵ 1፥11። መስማትን የሚያቀዳጀው መታዘዝ ነው። ሕይወትን የማያድስ መስማት ነፍስን ከቶ አያድናትም።
(8) እግዚአብሔር ቃሉን በመገኘቱና በበረከቱ እንዲያጅበው ለምኑት። ሁሉን በሥራ እንዲሠራ የሚያደርገው መንፈስ ነው። አገልጋዮች መድኃኒት ሊያዝዙ ይችላሉ፤ እንዲሠራ የሚያደርገው ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ነው። «ነፍሳትን የሚመልሰው እርሱ መድረኩ በሰማይ ነው።» አውግስጢኖስ። «ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።» ሐዋ 10፥44። ኬሚስቱ ከብረት ዘይት ሊያወጣ ይችላል ይባላል። የእግዚአብሔር መንፈስ እጅግ በደነደነ ልብ ውስጥ ጸጋን ሊያስገኝ ይችላል።
(9) ቃሉ ለመዳናችሁ በሥራ እንዲሠራ ከፈለጋችሁ የለመዳችሁት አድርጉት። ወደ ቤት ስትመለሱ ስለ ሰማችሁት ተነጋገሩ። «አንደበቴ ቃልህን ይናገራል።» መዝ 119፥172። አንዳንድ ሰዎች ከሚሰሙት ብዙ ጥቅም የማያገኙበት አንዱ ምክንያት ስለ ሰሙት ነገር እርስ በርሳቸው ፈጽሞ አለመነጋገራቸው ነው፤ ስብከቶች ዳግመኛ ሊነገሩ የማይገባቸው ምሥጢሮች እንደ ሆኑ፥ ወይም ስለ መዳን ጉዳይ መናገር ነውር እንደ ሆነ። «እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ... የመታሰቢያም መጽሐፍ ተጻፈ።» ሚል 3፥16።
የመጀመሪያው ትግበራ። ነፍሳችሁን የምትወዱ ከሆነ ቃሉ በእናንተ ላይ ፍሬ ቢስ እንዳይሆን ተጠንቀቁ። የተሰበከው ቃል የማይሠራባቸው አንዳንዶች አሉ። (1) ቃሉን የሚነቅፉ፤ ራሳቸውን በመፍረድ ፈንታ ቃሉን የሚፈርዱ። (2) ቃሉን በመቃወም የሚኖሩ። ኢሳ 30፥9። (3) በቃሉ ይበልጥ የሚደነድኑ። «ልባቸውን እንደ አልማዝ ድንጋይ አደረጉ።» ዘካ 7፥12። ሰዎችም ልባቸውን ሆን ብለው ሲያደነድኑ እግዚአብሔር በፍርድ ያደነድናቸዋል። «ጆሮአቸውንም አደንቍር።» ኢሳ 6፥10። ቃሉ ለእነዚህ ፍሬ ቢስ ነው። የሰው ምግብ ባይመግበው፥ ይልቁንም መርዝ ቢሆንበት አያሳዝንምን? ወይ! የተሰበከው ቃል ፍሬ ቢስና ከንቱ እንዳይሆንባችሁ ተጠንቀቁ!
ሁለተኛው ትግበራ። ሦስት ነገሮችን አስቡ፦
(1) የተሰበከው ቃል ካልጠቀመን የምንድንበት ሌላ መንገድ የለም። ይህ የእግዚአብሔር ሥርዓት ነው፤ ነፍሳትን ለመመለስ የሚጠቀምበትም ዋናው መሣሪያ ነው። «ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው።» ሉቃ 16፥31። አንድ መልአክ ከሰማይ ወደ እናንተ መጥቶ ስለ ክቡሩ ሁኔታ ብልጫና ስለ ሰማይ ደስታ እጅግ ልብ በሚነካ መንገድ ቢሰብክ፥ የተሰበከው ቃል ካላሳመናችሁ በዚህ ከሰማይ በመጣ ንግግርም አትለወጡም ነበር። የተኰነነ መንፈስ ከሲኦል መጥቶ በነበልባል ውስጥ ሆኖ ቢሰብክላችሁ፥ ሲኦል ምን ዓይነት ስፍራ እንደ ሆነ ቢነግራችሁ፥ የተኰነኑትንም ሥቃይ በጩኸት ቢገልጥላችሁ፥ ሊያንቀጠቅጣችሁ ይችል ይሆናል፤ የቃሉ ስብከት ካልመለሳችሁ ግን አይመልሳችሁም።
(2) ወደ ቃሉ መጥቶ ለመዳን አለመለወጥ ዲያብሎስን ደስ የሚያሰኘው ነገር ነው። በሥራ እስካልሆነ ድረስ ዘወትር ብትሰሙ ግድ የለውም፤ እርሱ የመስማት ጠላት አይደለም፤ የመጠቀም እንጂ። አገልጋዩ የሥርዓቶቹን ጡቶች ቢዘረጋላችሁ፥ ቅን የሆነውን የቃሉን ወተት እስካልጠባችሁ ድረስ አያሳስበውም። የስብከት ኪኒኖች በሕሊናችሁ ላይ እስካልሠሩ ድረስ ስንቱን ብትውጡ ዲያብሎስ ግድ የለውም።
(3) የተሰበከው ቃል ለሰዎች መመለስ ካልሠራ ለፍርዳቸው ይሠራል። ቃሉ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ መሥራቱ አይቀርም፤ ልባችሁን ካላሻሻለ ሰንሰለታችሁን ያከብዳል። የተሰበከው ቃል የሌላቸውን እናዝንላቸዋለን፤ በቃሉ ያልተቀደሱት ግን የባሰ ይሆንባቸዋል። ስብከቶችን ተሸክመው ወደ ሲኦል የሚሄዱ ሰዎች ሁኔታ የሚያስፈራ ነው። ነገር ግን ከሐዋርያው ጋር «አብልጦ የሚሻለውና ለመዳን የሚሆነው» እንዲሆንላችሁ ተረድቻለሁ ብዬ እደመድማለሁ። ዕብ 6፥9።