ምዕራፍ 19 · 10 ደቂቃ ንባብ · 13 ደቂቃ ማዳመጥ
4.2 ንስሐ
«እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው።» ሐዋ 11፥18።
ንስሐ ለመዋጥ መራራ ኪኒን ይመስላል፤ ነገር ግን የኃጢአትን ክፉ ፈሳሽ የሚያስወግድ ነው። አንዳንድ የአንቲኖሚያን መንፈስ ያላቸው ሰዎች የሕግ ትምህርት ነው ብለው ያጣጥሉታል፤ ነገር ግን ክርስቶስ ራሱ ሰበከው። «ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ፦ ንስሐ ግቡ ብሎ ይሰብክ ጀመር»፥ ወዘተ። ማቴ 4፥17። ወደ ሰማይ ሲያርግ በመጨረሻው የስንብት ቃሉ «በስሙም ንስሐ ይሰበካል» ብሎ አዘዘ። ሉቃ 24፥47። ንስሐ ንጹሕ የወንጌል ጸጋ ነው። የሥራ ኪዳን ንስሐን አይቀበልም ነበር፤ ፍጹምና የግል መታዘዝን መፈጸም ያልቻሉትን ሁሉ ይረግም ነበር። ገላ 3፥10። ንስሐ የሚመጣው በወንጌል ነው፤ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች እንዲድኑ መሆኑ ክርስቶስ የገዛው ፍሬ ነው። የተሰቀለውን ክርስቶስን በዓይኖቻችን ፊት በሚያቀርብበት ጊዜ በወንጌል አገልግሎት ይሠራል። እንደ ፈቃዳችን የሚተው ሳይሆን የግድ አስፈላጊ ነው፤ ያለ እርሱ መዳን የለም። «ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ።» ሉቃ 13፥3። መርከባችን ከተሰበረ በኋላ ይህን ሳንቃ ስለ ተወልን እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባናል።
I. በመጀመሪያ የንስሐን አስመሳዮች አሳያለሁ።
[1] ተፈጥሮአዊ የመንፈስ ልስላሴና ርኅራኄ። አንዳንዶች ከተፈጥሮ ጠባያቸው የሚመነጭ ርኅሩኅ ስሜት አላቸው፤ በዚህም የሚያሳዝን ነገር ባዩ ጊዜ ለማልቀስና ለመራራት ፈጣኖች ናቸው። እነዚህ የንስሐ እንባዎች አይደሉም፤ ብዙዎች የሌላውን መከራ አይተው ያለቅሳሉ፥ በራሳቸው ኃጢአት ግን ማልቀስ አይችሉም።
[2] የሕግ ፍርሃቶች። በኃጢአት ጎዳና የኖረ ሰው በመጨረሻ ይሰማዋል፤ ሲኦል ሊውጠው ተዘጋጅቶ ያያል፥ በጭንቀትና በድንጋጤም ይሞላል፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የሕሊናው ማዕበል አልፎ ጸጥ ይላል። ከዚያም በኃጢአት ውስጥ መራራነትን ስለ ቀመሰ እውነተኛ ንስሐ ገቢ ነኝ ብሎ ይደመድማል፤ ይህ ግን ንስሐ አይደለም። ይሁዳ የተወሰነ የአእምሮ ጭንቀት ነበረው። ጭንቀትና መታወክ ለንስሐ በቂ ቢሆኑ ኖሮ የተኰነኑት ከሁሉ ይበልጥ ንስሐ ገቢዎች በሆኑ ነበር፤ ከሁሉ ይበልጥ በአእምሮ ጭንቀት ውስጥ ናቸውና። በእግዚአብሔር ላይ ስለ ተደረገው በደል ኀዘን በሌለበት የአእምሮ መታወክ ሊኖር ይችላል።
[3] ጥቂትና ላይ ላዩን የሆነ ኀዘን። የእግዚአብሔር እጅ በሰው ላይ ስትከብድ፥ ለምሳሌ ሲታመም ወይም ሲያነክስ፥ ይተነፍስ ወይም እንባ ያፈስስ ይሆናል፥ «ጌታ ሆይ፥ ማረኝ» ይልም ይሆናል፤ ይህ ግን እውነተኛ ንስሐ አይደለም። አክዓብ ከዚህ ሁሉ የበለጠ አድርጓል። «ልብሱን ቀደደ፥ ጾመም፥ በማቅም ላይ ተኛ፥ በዝግታም ሄደ።» 1ነገ 21፥27። ልብሱ ተቀደደ፥ ልቡ ግን አልተቀደደም። ዓይን እንባ ሞልቶበት ልብ እንደ ባልጩት ሊሆን ይችላል። አፕሪኮት ውጭው ለስላሳ ሊሆን ይችላል፥ ውስጡ ግን ጠንካራ ፍሬ አለው።
[4] በልብ ውስጥ የሚነሡ መልካም መነሣሣቶች። እያንዳንዱ መልካም መነሣሣት ንስሐ አይደለም። አንዳንዶች ኃጢአታቸውን ለመተውና ሃይማኖተኞች ለመሆን በልባቸው መነሣሣት ቢኖራቸው ንስሐ እንደ ሆነ ያስባሉ። ዲያብሎስ በጻድቃን ውስጥ ክፉ መነሣሣቶችን ሊያነሣሣ እንደሚችል፥ እንዲሁ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃጥአን ውስጥ መልካም መነሣሣቶችን ሊያነሣሣ ይችላል። ሄሮድስ በመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት ብዙ መልካም ሐሳቦችና ዝንባሌዎች ተነሣሥተውበት ነበር፤ ሆኖም በዘመድ ርኩሰት ይኖር ስለ ነበር በእውነት ንስሐ አልገባም።
[5] ስእለቶችና ቍርጥ ውሳኔዎች። አንዳንዶች በሕመማቸው ጊዜ እግዚአብሔር ቢፈውሳቸው አዲስ ሰዎች እንደሚሆኑ ምን ያህል ስእለትና የተከበረ ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፤ በኋላ ግን እንደ ቀድሞው ክፉዎች ይሆናሉ! «አንቺም፦ አልተላለፍም አልሽ»፤ ይህ ቍርጥ ውሳኔ ነበር፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ጣዖቶቿን ተከትላ ሮጠች። «በለመለመም ዛፍ ሁሉ በታች ተቅበዝብዘሽ ገለሞትሽ።» ኤር 2፥20።
[6] አንዳንድ ከባድ ኃጢአትን መተው። (1) ሰው አንዳንድ ኃጢአቶችን ትቶ ሌሎችን ሊይዝ ይችላል። ሄሮድስ የተበላሹትን ብዙ ነገሮች አስተካከለ፥ ሄሮድያዳን ግን ያዘ። (2) አዲስ ኃጢአትን ለማስተናገድ አሮጌ ኃጢአት ሊተው ይችላል። ሰው ፈንጠዝያንና አባካኝነትን ትቶ ስስታም ሊሆን ይችላል፤ ይህም አንዱን ኃጢአት በሌላው መለወጥ ብቻ ነው።
እነዚህ የንስሐ አስመሳዮች ናቸው። እንግዲህ ንስሐችሁ አስመሳይ እንደ ሆነና በትክክል ንስሐ እንዳልገባችሁ ካገኛችሁ፥ ያጠፋችሁትን አስተካክሉ። በሰውነት ውስጥ አጥንት በተሳሳተ ሁኔታ ቢገጠም ወጌሻው እንደ ገና ሰብሮ በትክክል ከመግጠም በቀር ሌላ መንገድ እንደሌለው፥ እንዲሁ በንስሐ ማድረግ አለባችሁ፤ በትክክል ንስሐ ካልገባችሁ ልባችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ገና ሊሰበር፥ ስለ ኃጢአትም ከቀድሞው ይልቅ ጠልቃችሁ ልታዝኑ ይገባችኋል።
II. ይህ ንስሐ በምን እንደሚገኝ ወደ ማሳየት ያመጣኛል። በሁለት ነገሮች ይገኛል፤ በመዋረድና በመለወጥ።
[1] መዋረድ። «ያልተገረዘ ልባቸው ቢዋረድ።» ዘሌ 26፥41። የትምህርት ቤት ሊቃውንት እንደሚሉት፥ ሁለት ዓይነት መዋረድ ወይም የልብ መሰበር አለ። (1) መፈርፈር፤ ዓለት ተሰባብሮ ሲፈረፈር እንደሚሆነው። ይህ የሚደረገው ልብን የሚሰብር መዶሻ በሆነው በሕግ ነው። (2) መቅለጥ፤ በረዶ ቀልጦ ውሃ ሲሆን እንደሚሆነው። ይህ የሚደረገው «ልብን እንደሚያቀልጥ» እሳት በሆነው በወንጌል ነው። ኤር 23፥9። የተናቀ ቸርነት መታሰቡ ልብን ያቀልጣል።
[2] መለወጥ ወይም ለውጥ። «በልባችሁ መታደስ ተለወጡ።» ሮሜ 12፥2። ንስሐ በሰው ሁለንተና ላይ ለውጥ ያመጣል። የወይን ጠጅ በውሃ ብርጭቆ ውስጥ ሲጨመር ወደ ውሃው ክፍል ሁሉ እንደሚሰራጭና ቀለሙንና ጣዕሙን እንደሚለውጥ፥ እንዲሁ እውነተኛ ንስሐ በአንድ ክፍል ብቻ አያርፍም፤ ነገር ግን ወደ ክፍል ሁሉ ይዘረጋል፥ ይሰራጫልም።
(1) ንስሐ በአእምሮ ላይ ለውጥን ያመጣል። ቀድሞ ሰው ኃጢአትን ይወድ ነበር፤ ስለ እርሱም ሲከራከር እንደ ዮናስ «ብቈጣ መልካም አደርጋለሁ» ይል ነበር፤ ምዕ 4፥9፤ ወይም መማሌና ሰንበትን መሻሬ መልካም ነበር ይል ነበር። ንስሐ ገቢ ሲሆን ግን ፍርዱ ይለወጣል፤ ኃጢአትን ከሁሉ የሚበልጥ ክፉ ነገር አድርጎ ይመለከተዋል። ንስሐ የሚለው የግሪክ ቃል የኋላ ጥበብ ማለት ነው፤ ይህም ኃጢአት ምን ያህል የተበላሸና የሚያስኰንን ነገር እንደ ሆነ አይተን ሐሳባችንን ስንለውጥ ነው። ጳውሎስ ከመመለሱ በፊት የኢየሱስን ስም የሚቃወም ብዙ ነገር ሊያደርግ እንደሚገባው በእርግጥ ያስብ ነበር (ሐዋ 26፥9)፤ ንስሐ ገቢ በሆነ ጊዜ ግን ሌላ ሐሳብ ያዘ። «ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጠው ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ እውቀት ሁሉን እንደ ጉዳት እቈጥራለሁ።» ፊልጵ 3፥8። ንስሐ የፍርድ ለውጥን ያመጣል።
(2) ንስሐ በስሜቶች ላይ ለውጥን ያመጣል፤ ስሜቶች ዋና አዛዥ ከሆነው ፈቃድ በታች ይንቀሳቀሳሉ። ስሜቶችን ፈጽሞ ይለውጣል። በኃጢአት ደስ መሰኘትን ስለ ኃጢአት ወደ ማዘን ይለውጣል፤ በኃጢአት መድፈርን ወደ ቅዱስ እፍረት ይለውጣል፤ የኃጢአትን ፍቅር ወደ ጥላቻ ይለውጣል። አምኖን ትዕማርን ከወደዳት ይልቅ እጅግ አብልጦ እንደ ጠላት (2ሳሙ 13፥15)፥ እንዲሁ እውነተኛ ንስሐ ገቢ ኃጢአትን ከወደደው ይልቅ አብልጦ ይጠላዋል። «የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።» መዝ 119፥104።
(3) ንስሐ በሕይወት ላይ ለውጥን ያመጣል። ንስሐ ከልብ ቢጀምርም በዚያ አያርፍም፥ ወደ ሕይወትም ይገባል። ከልብ ይጀምራል። «ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ልብሽን እጠቢ።» ኤር 4፥14። ምንጩ ቢበላሽ ንጹሕ ጅረት ከእርሱ ሊፈስ አይችልም። ንስሐ ከልብ ቢጀምርም በዚያ አያርፍም፥ ሕይወትንም ይለውጣል። ንስሐ በጳውሎስ ላይ ምንኛ ለውጥ አደረገ! አሳዳጁን ሰባኪ አደረገው። በወኅኒ ቤቱ ጠባቂ ላይ ምንኛ ለውጥ አደረገ! ሐዋ 16፥33። ጳውሎስንና ሲላስን ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፥ ማዕድም አቀረበላቸው። በመግደላዊት ማርያም ላይ ምንኛ ለውጥ አደረገ! ቀድሞ ወዳጆቿን በልቅ እቅፍ ትስም የነበረችው አሁን የክርስቶስን እግር ትስማለች፤ ጠጕሯን ትጠቀልልና በውድ ዕንቍዎች ታስጌጠው የነበረችው አሁን የክርስቶስን እግር የምታብስበት ፎጣ ታደርገዋለች፤ በምኞት ያበሩና በርኩስ እይታ ወዳጆቿን ያማልሉ የነበሩት ዓይኖቿ አሁን የመድኃኒቷን እግር የሚያጥቡ የእንባ ምንጮች ሆኑ፤ በከንቱና በልቅ ይናገር የነበረው አንደበቷ አሁን እግዚአብሔርን ለማመስገን የተቃኘ መሣሪያ ሆነ። ይህ የሕይወት ለውጥ ሁለት ነገሮች አሉበት፦ —
[1] terminus a quo [መነሻው]፥ ኃጢአትን መተው። «ኃጢአትህን በጽድቅ አስወግድ።» ዳን 4፥27። ይህ ኃጢአትን መተው ሦስት ባሕርያት ሊኖሩት ይገባል። (1) ሁሉን አቀፍ ሊሆን ይገባዋል፤ ኃጢአትን ሁሉ መተው። አንድ በሽታ እንደ ብዙዎቹ ሊገድል ይችላል። የሚኖሩበት አንድ ኃጢአት እንደ ብዙዎቹ ሊያስኰንን ይችላል። እውነተኛው ንስሐ ገቢ የተሰወሩትን፥ ትርፍ የሚያስገኙትንና የለመዳቸውን ኃጢአቶች ይተዋል፤ የሥጋን ምኞት የመግደልን የመሥዋዕት ቢላዋ ወስዶ በሚወዳቸው ምኞቶቹ ልብ ውስጥ ይሰድደዋል። (2) ኃጢአትን መተው ቅን ሊሆን ይገባዋል፤ ከፍርሃት ሳይሆን በመንፈሳዊ ምክንያት፥ ማለትም ከመጥላትና ከመጸየፍ እንዲሁም እግዚአብሔርን ከመውደድ መርሕ ሊሆን ይገባዋል። ኃጢአት እንዲህ ያሉ ክፉ ውጤቶች ባይኖሩት እንኳ እውነተኛ ንስሐ ገቢ እግዚአብሔርን ስለሚወድ ይተወዋል። በአንድነት የቀዘቀዙትን ነገሮች ለመለያየት የተሻለው መንገድ በእሳት ነው። ኃጢአትና ልብ በአንድነት ሲቀዘቅዙ እነርሱን ለመለያየት የተሻለው መንገድ በፍቅር እሳት ነው። በቸሩ አባት ላይ ኃጢአት ልሥራን? ይቅር የሚለኝንስ ፍቅር ላቃልልን? (3) ኃጢአትን መተው ዘላቂ ሊሆን ይገባዋል፤ ዳግመኛ ከኃጢአት ጋር ምንም ጕዳይ እንዳይኖር። «ከጣዖታት ጋር ደግሞ ምን አለኝ?» ሆሴ 14፥8። ንስሐ እስከ ሞት ድረስ ሊጸና የሚገባው መንፈሳዊ ፍቺ ነው።
[2] የሕይወት ለውጥ terminus ad quem [መድረሻውን]፥ ማለትም ወደ ጌታ መመለስን ይዟል። «ወደ እግዚአብሔር ንስሐ መግባት» ተብሏል። ሐዋ 20፥21። ንስሐ ስንገባ አሮጌ ኃጢአቶችን መተው ብቻ በቂ አይደለም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር አገልግሎት መሰማራት ይገባናል፤ ነፋስ ምዕራብን ሲለቅ ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ እንደሚዞር። ንስሐ የገባው አባካኙ ልጅ ጋለሞቶቹን መተው ብቻ ሳይሆን ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ። ሉቃ 15፥18። በእውነተኛ ንስሐ ልብ፥ መርፌ ወደ ሰሜን ዋልታ እንደሚያመለክት፥ በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር ያመለክታል።
ትግበራ። ሁላችንም ይህን ታላቅ የንስሐ ሥራ እንጀምር፤ በቅንነትና በፍጥነት ንስሐ እንግባ፤ ከኃጢአቶቻችን ሁሉ፥ ከትዕቢታችን፥ ከችኩል ቍጣችንና ከአለማመናችን ንስሐ እንግባ። «ያለ ንስሐ ስርየት የለም።» ኃጢአተኛ በዓመፅ ተግባር ላይ ሳለ ይቅር ማለት ከእግዚአብሔር ባሕርይ ቅድስና ጋር አይስማማም። ኦ፥ እግዚአብሔርን በጦር መሣሪያ ሳይሆን በዓይኖቻችሁ እንባ ተገናኙት። ወደ ቀለጠ የንስሐ ልብ ሁኔታ እንድትነሣሡ፦ —
(1) በተግባር ትቀጥሉበት ዘንድ በኃጢአት ውስጥ ምን እንዳለ አስቡ። «እርም የሆነ ነገር» ነው። ኢያ 7፥11። የተጣራ የክፋት መንፈስ ነው። የነፍስን ክብር ያረክሳል፤ በውበት ላይ እንዳለ እድፍ ነው። ከመቅሠፍት ቍስል ጋር ተመስሏል። 1ነገ 8፥38። እንደ ኃጢአት የሰውን ክብር ወደ እፍረት የሚለውጥ ምንም ነገር የለም። ያለ ንስሐ ኃጢአት ወደ መጨረሻ ኵነኔ ይመራል። Peccatum transit actu, manet reatu [የኃጢአቱ ቅጽበት ያልፋል፥ በደሉ ግን ይቀራል]። ኃጢአት በመጀመሪያ በብርጭቆ ውስጥ ቀለሙን ያሳያል፤ በኋላ ግን እንደ እባብ ይነድፋል። በራእ 9፥7 ያሉት አንበጦች የኃጢአት ምሳሌ ናቸው፤ «በራሳቸውም ላይ ወርቅ እንደሚመስሉ አክሊሎች ነበሩአቸው፥ የሴቶችን ጠጕር የሚመስል ጠጕር ነበራቸው፥ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ፥ በጅራታቸውም መውጊያ አለ።» ንስሐ ያልተገባበት ኃጢአት በአሳዛኝ ፍጻሜ ይደመደማል። ዲያብሎስ አባቱ፥ እፍረት ጓደኛው፥ ሞትም ደመወዙ ነው። ሮሜ 6፥23። እንግዲያስ ሰዎች በኃጢአት ይጸኑ ዘንድ በእርሱ ውስጥ ምን አለ? ጣፋጭ ነው አትበሉ። የሚገድልን ደስታ ማን ይመኛል?
(2) ንስሐ እግዚአብሔርን እጅግ ደስ ያሰኛል። እንደ ተሰበረ ልብ ያለ መሥዋዕት የለም። «አቤቱ፥ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።» መዝ 51፥17። አውግስጢኖስ በታመመ ጊዜ ይህ ቃል በአልጋው በላይ እንዲጻፍ አደረገ። መበለቲቱ ባዶ ዕቃዎችን ወደ ኤልሳዕ ባመጣች ጊዜ ዘይቱ በውስጣቸው ፈሰሰ። 2ነገ 4፥6። የተዋረደ ልብን የተሰበረ ዕቃ ወደ እግዚአብሔር አምጡ፥ እርሱም የምሕረትን ዘይት ያፈስስበታል። የንስሐ እንባዎች የእግዚአብሔርና የመላእክት ደስታ ናቸው። ሉቃ 15፥7። ርግቦች በውሃ አጠገብ መሆንን ይወዳሉ፤ በእርግጥም አንድ ጊዜ በርግብ አምሳል የወረደው የእግዚአብሔር መንፈስ በንስሐ ውሃ እጅግ ደስ ይሰኛል። ማርያም እያለቀሰች በኢየሱስ እግር አጠገብ ቆመች። ሉቃ 7፥38። ወደ ክርስቶስ ሁለት ነገሮችን አመጣች፤ እንባና ሽቱ፤ ነገር ግን እንባዋ ከሽቱዋ ይልቅ በክርስቶስ ዘንድ የከበረ ነበረ።
(3) ንስሐ ይቅርታን ያስከትላል። ስለዚህ ሁለቱ በአንድነት ተጣምረዋል። «ንስሐና የኃጢአት ስርየት።» ሉቃ 24፥47። የኃጢአት ይቅርታ ከሁሉ የሚበልጥ በረከት ነው፤ የታመመን ሰው ለመፈወስ በቂ ነው። «በዚያም የሚቀመጥ፦ ታምሜአለሁ አይልም፤ በእርሷ የሚኖሩ ሕዝብ በደላቸው ይሰረይላቸዋል።» ኢሳ 33፥24። ይቅርታ ይበልጥ ባለ ጠጋ የሆነውን የተስፋ ቃሎች ሰነድ ያጸናልናል። ይቅር ባይ ምሕረት ሌሎችን ምሕረቶች ሁሉ ይበልጥ እንዲጣፍጡ የሚያደርግ ቅመም ነው፤ ጤናችንን፥ ባለ ጠግነታችንንና ክብራችንን ያጣፍጣል። ዳዊት በራሱ ላይ የጥሩ ወርቅ ዘውድ ተደርጎለት ነበር። መዝ 21፥3። ዳዊት እግዚአብሔርን አብልጦ የባረከው በራሱ ላይ የወርቅ ዘውድ ስላደረገለት ሳይሆን የምሕረት ዘውድ ስላደረገለት ነበር። «ምሕረትን የሚያቀዳጅህ።» መዝ 103፥4። ይህ የምሕረት ዘውድ ምን ነበር? በቁ 3 ታያላችሁ፤ «ኃጢአትህን ሁሉ ይቅር የሚል።» ዳዊት የጥሩ ወርቅ ዘውድ ከመልበሱ ይልቅ በይቅርታ በመቀዳጀቱ እጅግ ደስ አለው። እንግዲህ ለኃጢአት ይቅርታ መንገድ የሚያዘጋጀው ከንስሐ በቀር ምንድር ነው? የዳዊት ነፍስ በተዋረደችና በተሰበረች ጊዜ ነቢዩ ናታን የምሥራች አመጣለት። «እግዚአብሔርም ኃጢአትህን አርቆልሃል።» 2ሳሙ 12፥13።
ነገር ግን ኃጢአቶቼ እጅግ ታላቅ ስለ ሆኑ ንስሐ ብገባ እንኳ እግዚአብሔር ይቅር አይላቸውም!
እግዚአብሔር ከተስፋ ቃሉ አይመለስም። «ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ፥ ተመለሺ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔ መሐሪ ነኝና ቍጣዬን በእናንተ ላይ አላወርድም።» ኤር 3፥12። ኃጢአቶችህ እንደ ዓለቶች ቢሆኑ እንኳ ንስሐ ብትገባ የእግዚአብሔር የምሕረት ባሕር ሊያሰጥማቸው ይችላል። «ታጠቡ፥ ንጹሐንም ሁኑ።» ኢሳ 1፥16። በንስሐ መታጠቢያ ታጠቡ። «ኑ፥ እንዋቀስ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ቢሆን እንደ በረዶ ነጭ ይሆናል»፤ ቁ 18። ምናሴ እንደ ደም የቀላ ኃጢአተኛ ነበረ፤ ነገር ግን ራሱን እጅግ ባዋረደ ጊዜ የምሕረት የወርቅ በትረ መንግሥት ተዘረጋለት። ራሱ ስለ ኃጢአት የሚያለቅስ ምንጭ በሆነ ጊዜ የክርስቶስ ጎን ኃጢአትን የሚያጥብ ምንጭ ሆነ። የሚያጠፋው የኃጢአት ታላቅነት ሳይሆን ንስሐ አለመግባት ነው። ክርስቶስን በመስቀል እጃቸው የነበረበት አይሁድ ንስሐ ሲገቡ ያፈሰሱት ደም እነርሱን የሚፈውስ ታላቅ መድኃኒት ሆኖ አገኙት። አባካኙ ልጅ ወደ አባቱ ቤት በመጣ ጊዜ ልብሱና ቀለበቱ ተደረገለት፥ «አባቱም ሳመው።» ሉቃ 15፥20, 22። ኃጢአቶቻችሁን ብትተዉ እግዚአብሔር ወዳጃችሁ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር ያለው ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ኃይሉ ሊረዳችሁ የእናንተ ይሆናል፤ ጥበቡ ሊመክራችሁ የእናንተ ይሆናል፤ መንፈሱ ሊቀድሳችሁ የእናንተ ይሆናል፤ የተስፋ ቃሎቹ ሊያጽናኑአችሁ የእናንተ ይሆናሉ፤ መላእክቱ ሊጠብቁአችሁ የእናንተ ይሆናሉ፤ ምሕረቱ ሊያድናችሁ የእናንተ ይሆናል።
(4) በንስሐ እንባ ውስጥ ብዙ ጣፋጭነት አለ። ነፍስ ስለ ኃጢአት በርኅራኄ ልትቀልጥ ከምትችልበት ጊዜ ይልቅ ይበልጥ የምትሰፋበትና በውስጧ ደስ የምትሰኝበት ጊዜ የለም። የልቅሶ ቀናት የበዓል ቀናት ናቸው። ንስሐ መግባት የሚለው የዕብራይስጥ ቃል nicham፥ consolari፥ «መጽናናትን መቀበል» ማለት ነው። «ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።» ዮሐ 16፥20። ክርስቶስ የእንባን ውሃ ወደ ወይን ጠጅ ይለውጣል። በእስራኤል ታላቁ አልቃሽ የነበረው ዳዊት ጣፋጩ ዘማሪ ነበረ። እውነተኛ ንስሐ ገቢ የሚያገኘው ደስታ የገነት ደስታ ቅድመ መባና ቅድመ ቅምሻ ነው። የኃጥእ ደስታ ወደ ኀዘን ይለወጣል፤ የንስሐ ገቢው ኀዘን ወደ ደስታ ይለወጣል። ንስሐ በመጀመሪያ እሾሃማና መራራ ቢመስልም ክርስቲያን ከዚህ እሾህ ወይን ይለቅማል። እነዚህ ሁሉ ሐሳቦች ስለ ኃጢአት እንድናለቅስና ከእርሱም እንድንመለስ በነፍሳችን ውስጥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነውን የኀዘን ምንጭ ሊከፍቱ ይችላሉ። እግዚአብሔር መጽናናትን የሚመልስ ከሆነ ለሚያለቅሱለት ነው። ኢሳ 57፥18። ካለቀስን በኋላ ይቅርታን ለማግኘት ወደ ክርስቶስ ደም ቀና ብለን እንመልከት። እንደዚያ ቅዱስ ሰው lava, Domine, lacrimas meas፤ «ጌታ ሆይ፥ እንባዬን በደምህ እጠብ» በሉ። ከእንባችን ጋር ኃጢአትን እናንጠባጥባለን፤ እንባችንንም ለማጠብ የክርስቶስ ደም ያስፈልገናል። ይህ ንስሐ ቶሎ እንደሚያልፍ ለወዳጅ እንደሚደረግ ልቅሶ ለጥቂት ቀናት ብቻ መሆን የለበትም፤ ነገር ግን የሕይወታችን ሥራ መሆን አለበት፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነው የኀዘን ፈሳሽ እስከ ሞት ድረስ መቆም የለበትም። ኃጢአት ይቅር ከተባለ በኋላም ንስሐ መግባት አለብን። ዕዳችንን እንደ ገና እናበዛለን፤ «ዕለት ዕለት ኃጢአት እንሠራለን፥ ስለዚህ ዕለት ዕለት ንስሐ መግባት አለብን።» አንዳንዶች ስለ ኃጢአት ጥቂት እንባ ያፈስሳሉ፤ እንደ መበለቲቱ ዘይት ለጥቂት ጊዜ ከፈሰሱ በኋላ ይቆማሉ። ብዙዎች የንስሐ መለጠፊያ ጥቂት ማቃጠል ቢጀምር ይነቅሉታል፤ የንስሐ መለጠፊያ ግን እስከ ሞት ድረስ ተለጥፎ ሊቆይ እንጂ ሊነቀል አይገባውም፤ በዚያን ጊዜ እንደ ሌሎቹ እንባዎች ሁሉ እነዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ያሉ የኀዘን እንባዎችም ይታበሳሉ።
የንስሐ ልብ ሁኔታን ለማግኘት ምን እናድርግ?
ስለ እርሱ እግዚአብሔርን ለምኑ። «የሥጋ ልብ» ሊሰጥ (ሕዝ 36፥26)፥ የልቅሶንም መንፈስ በእኛ ላይ ሊያፈስስ የገባው ተስፋ ቃሉ ነው። ዘካ 12፥10። የእግዚአብሔርን «መንፈስ ቅዱስ» ለምኑ። «ነፋሱን ያነፍሳል፥ ውኆችም ይፈስሳሉ።» መዝ 147፥18። የእግዚአብሔር መንፈስ ነፋስ በእኛ ላይ ሲነፍስ የንስሐ እንባ ውኆች ከእኛ ይፈስሳሉ።