በጸሎት ያለ ታላቅ ኃይል
የቁራዎች ጩኸት

ምዕራፍ 13 · 22 ደቂቃ ንባብ · 29 ደቂቃ ማዳመጥ

የቁራዎች ጩኸት

«ለእንስሳት ምግባቸውን የሚሰጥ፣ የቁራ ጫጩቶችም ሲጮኹ የሚመግብ።» መዝሙር 147:9።

ይህን ስብከት በአንድ ጥቅስ እጀምራለሁ። ካሪል ስለ ቍራዎች የጻፈውን ማብራሪያ በራሱ ቃላት ልሰጣችሁ ይገባኛል። «የተፈጥሮ ተመራማሪዎች እንዲህ ይነግሩናል፤ ቍራ ጫጩቶቹን ላባቸው በሚገባ እስኪበቅልና ወጥተው መብረር እስኪችሉ ድረስ በጎጆው ውስጥ ከመገባቸው በኋላ፣ ከጎጆው ገፍቶ ያስወጣቸዋል፤ በዚያም እንዲቆዩ አይፈቅድላቸውም፤ ነገር ግን የራሳቸውን ምግብ እንዲፈልጉ ያባርራቸዋል። እንግዲህ እነዚህ ጫጩቶች ከጎጆአቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በሚበርሩበትና ራሳቸውን የሚመግቡበትን መንገድ ገና በደንብ በማያውቁበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር ምግብ ያዘጋጅላቸዋል።

«ታማኝ ምስክሮች እንደሚናገሩት፣ ቍራ በዚህ ነገር እጅግ ጥብቅና ጨካኝ ነው፤ ጫጩቶቹ ራሳቸውን መመገብ እንደ ቻሉ ከዚያ ወዲያ ምግብ አያመጣላቸውም። አንዳንዶች ደግሞ አሮጌዎቹ ቍራዎች ጫጩቶቹ በተፈለፈሉበት አገር እንዲቀመጡ እንኳ አይፈቅዱላቸውም ይላሉ፤ ይህ እውነት ከሆነም መንከራተታቸው ግድ ነው። እኛ በምሳሌ ‹ችግር አሮጊቷን ያሯሩጣታል› እንላለን፤ ‹ወጣቶቹንም እንዲሁ› ማለት እንችላለን።»

አንዳንድ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ እንዲህ ያደርጉ ነበር፤ ምናልባትም አሁንም ያደርጉ ይሆናል፤ ልጆቹ ራሳቸውን መቻል እንደ ጀመሩና እንጀራቸውን በመጠኑም ቢሆን ማግኘት እንደ ቻሉ፣ ቍራ ጫጩቶቹን ከጎጆ እንደሚያስወጣ እነርሱም ከቤት ያስወጡአቸዋል። እንግዲህ እግዚአብሔር በዚህ ቃል እንዲህ አለ፤ የቍራ ጫጩቶች በዚህ ጭንቅ ውስጥ ሲሆኑ፣ ሲባረሩና ምግብ አጥተው ሲንከራተቱ፣ የሚመግባቸው ማን ነው? «እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? አሮጌውን ቍራ የምመግብ እኔ፣ ጫጩቶቹንም በጎጆ ሳሉም ሆነ ምግብ አጥተው ሲንከራተቱ የምመግባቸው እኔ አይደለሁምን?»

ሰሎሞን ታካቹን ወደ ገብረ ጕንዳን ላከው፤ እርሱም ራሱ ከሽኮኮዎች፣ ከግራጫ ውሾችና ከሸረሪቶች ትምህርት ተማረ! እኛም ከእግዚአብሔር ፍጥረታት ከማናቸውም ለመማር ፈቃደኞች እንሁን፤ ዛሬ ማታም በትምህርት ቤት እንዳለ ሰው ለመማር ወደ ቍራዎች ጎጆ እንሂድ። ለንጹሖች ርኩስ የሆነ ምንም የለም፤ ለጠቢባንም ተራ የሆነ ምንም የለም። አጉል እምነት ያላቸው ቍራን እንደ መጥፎ ገድ ወፍ ይፍሩት፤ ግድ የለሾችም በእርሱ የሚያብረቀርቅ ጥቁር ክንፍ ያለው ፍጡር እንጂ ሌላ ነገር አይዩ፤ እኛ ግን ከዚያ የበለጠ ለማየት ፈቃደኞች ነን፤ ለመማርም ዝግጁ ብቻ ከሆንን ያለ ዋጋ እንደማንቀር አያጠራጥርም።

የኖኅ ቍራ የወይራ ቅርንጫፍ ይዞለት አልተመለሰም፤ የእኛ ግን ሊያመጣልን ይችላል! እንዲያውም ጥንት ኤልያስን በኮራት ፈፋ አጠገብ እንደ መገቡት፣ ዛሬ ማታም ቍራዎች ምግብ ያመጡልን ይሆናል። ብፁዕ ጌታችን በአንድ ወቅት ከቍራዎች እጅግ ብርቱ የሆነ ማስረጃ አቅርቦ ነበር፤ ይህም ስለ ምድራዊ ኑሮአቸው በማያስፈልግ ጭንቀት የተዋጡትን ባሪያዎቹን ለማጽናናትና ለማበረታታት የታሰበ ማስረጃ ነበር። ለእነዚህም እንዲህ አላቸው፦ «ቁራዎችን አስቡ። አይዘሩም፤ አያጭዱም። ጓዳም ጎተራም የላቸውም። ሆኖም እግዚአብሔር ይመግባቸዋል። እናንተ ደግሞ ከወፎች እጅግ የበለጠ ዋጋ አላችሁ!»

የመምህሩን አመክንዮ ተከትዬ — በንግግሩ እንደማይዋሽ ሁሉ በአስተሳሰቡም ፈጽሞ ስሕተት ስላልነበረበት ትክክል እንደ ነበረ ሁላችሁም ትስማማላችሁ — ዛሬ ማታ እንዲህ ብዬ እከራከራለሁ፦ ቍራዎችን ሲጮኹ አስቡ! በሻካራ፣ ትርጕም በሌለውና በሚያንቋርር ድምፅ ፍላጎታቸውን ያስታውቃሉ፤ የሰማዩ አባታችሁም ጸሎታቸውን ሰምቶ ምግብ ይልክላቸዋል! እናንተም ደግሞ መጸለይና ሞገሱን መፈለግ ጀምራችኋል፤ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? እግዚአብሔር ስለ ቍራዎች ይገደዋልን፤ ስለ እናንተስ አይገደውምን? ላባ ያላበቀሉ የቍራ ጫጩቶች በጎጆአቸው ውስጥ ተርበው እንዲመግባቸው ወደ እርሱ ሲጮኹ ጩኸታቸውን አይሰማምን?

እላችኋለሁ፣ ለጩኸታቸው መልስ ሰጥቶ ይመግባቸዋልን? እናንተንስ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ፊቱንና ሞገሱን የምትፈልጉ የምትንቀጠቀጡ ምስኪን የሰው ልጆች ሆይ፣ አይመልስላችሁምን? የዚህ ምሽት ሥራ በሙሉ ያንን አንድ አሳብ ማብራራት ብቻ ይሆናል። ዛሬ ማታ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት፣ ምሕረትን ለማግኘት ሲጸልዩ ኖረው ገና ላልተቀበሉት — ምናልባትም ለወራት በአንድ እጅግ ታላቅና መራራ ጩኸት በጕልበታቸው ለቆዩ፣ ነገር ግን የሰላምን መንገድ ገና ላላወቁ — አንድ ነገር ለመናገር አስባለሁ።

ኃጢአታቸው አሁንም እንደ ወፍጮ ድንጋይ በአንገታቸው ላይ ተንጠልጥሎአል። በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ ተቀምጠዋል። ምንም ብርሃን አልወጣላቸውም፤ እጃቸውን እያሹ እንዲህ እያሉ ያቃስታሉ፦ «እግዚአብሔር ምሕረት ማድረግን ረሳን? የሚፈልጉትን ነፍሳት ጸሎት ጆሮውን ዘጋን? ከእንግዲህ የኃጢአተኞችን አሳዛኝ ጩኸት አያስብምን? የንስሐ ገቢዎች እንባ በምድር ላይ እየወረደ ከእንግዲህ ርኅራኄውን አያነሣሣምን?» ውድ ወዳጆች፣ አሁን በዚህ ዓይነት የአእምሮ ሁኔታ ውስጥ ላላችሁት ሰይጣንም እግዚአብሔር ፈጽሞ እንደማይሰማችሁ ይነግራችኋል። እስክትሞቱ ድረስ እንድትጮኹ እንደሚተዋችሁ! ሕይወታችሁን በትካዜና በእንባ ጨርሳችሁ በመጨረሻ ወደ እሳት ባሕር እንደምትጣሉ!

ዛሬ ማታ ጥቂት መጽናናትና መበረታታት ልሰጣችሁ እናፍቃለሁ። ከዚህ በበለጠ አጥብቃችሁ እንድትጮኹ ላሳስባችሁ እወዳለሁ! ወደ መስቀሉ ኑ፤ ያዙትም፤ ነፍሳችሁ የምትመኘውን ስጦታ እስክታገኙ ድረስ ከጥላው ፈጽሞ እንዳትለዩ ተሳሉ። መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ቢረዳኝ፣ እንደ ንግሥት አስቴር በልባችሁ «ወደ ንጉሡ እሄዳለሁ። ብጠፋም እጠፋለሁ» እንድትሉ ላነሣሣችሁ እወዳለሁ። በዚያም ላይ የያዕቆብን ስእለት «ካልባረከኝ አልለቅህም» ብላችሁ ጨምሩ። እንግዲህ የያዝነው ጥያቄ ይህ ነው፦ እግዚአብሔር የቍራ ጫጩቶችን ይሰማል፤ እናንተንስ አይሰማችሁምን?

1. በመጀመሪያ፣ የተናቀውን የቍራ ጩኸት እንደሚሰማ፣ እናንተም በአንድ መልኩ ከቍራ እጅግ እንደምትበልጡ ሳስብ፣ እንደሚሰማችሁ እከራከራለሁ። ቍራ ድንገት ቢሞት በፍጥረት ውስጥ ምንም ዓይነት አሳዛኝ ክፍተት የማይተው ምስኪን ርኩስ ወፍ ብቻ ነው። ነገ በሺዎች የሚቈጠሩ ቍራዎች አንገታቸው ቢጠመዘዝ፣ በዓለሙ ሁሉ ስለ እነርሱ ታላቅ ኀዘንና ልቅሶ ይሆናል ብዬ አላስብም! የሞቱ ብዙ ምስኪን ወፎች ብቻ ይሆናሉ፤ ያም ብቻ ነው።

እናንተ ግን የማትሞት ነፍስ ናችሁ! ቍራ ሕይወቱ ሲያልቅ ይጠፋል፤ ከዚያ በኋላ ቍራ የለም። እናንተ ግን የአሁኑ ሕይወታችሁ ሲያልፍ ህልውናችሁ አያከትምም፤ ገና ወደ ሕይወት ባሕር ተገፋችሁ እንጂ፤ ለዘላለም መኖር ገና ጀመራችሁ እንጂ። የማይሞተው መንፈሳችሁ ከማለፉ በፊት የምድር ጥንታውያን ተራሮች ፈራርሰው እንደ ኢምንት ሲሆኑ ታያላችሁ! ጨረቃ ደካማ ብርሃንዋ ይደበዝዛል፣ የፀሐይም ታላቅ እሳት በዘላለም ጨለማ ይጠፋል፤ መንፈሳችሁ ግን አሁንም በዘላለማዊ ጕዞው ወደ ፊት ይገሠግሣል — እግዚአብሔር ጩኸታችሁን ካልሰማ በቀር የሰቆቃ ዘላለማዊ ጕዞ —

«ኦ፣ ያ ታላቅ እውነት፤ ይህ ሟች አለመሞትን ይለብሳል! የአእምሮ ትርታ ፈጽሞ አያቋርጥም፤ በእግዚአብሔር ተቀስቅሶ ለዘላለም ይመታል፤ እንደ ራሱ ዘላለማዊነት ዘላለማዊ ሆኖ! ከመላእክት በላይ ወይም ከአጋንንት በታች፤ በክብር ለመውጣት ወይም በኀፍረት ለመውረድ — የሰው ልጅ በማይገታ ዕጣ ተወስኖአል።» እንግዲህ እግዚአብሔር ያለውንና የሌለውን — ለቅጽበት እዚህ ኖሮ ከህልውና የሚደመሰሰውን — ምስኪን ወፍ ይሰማል፤ እናንተን ግን፣ ዘመናችሁ ከራሱ ዘመን ጋር እኩል የሚሆን የማትሞት ነፍስ የሆናችሁትን አይሰማችሁም ብላችሁ ታስባላችሁን? የሚሞተውን ቍራ የሚሰማ ከሆነ የማይሞተውንም ሰው በእርግጥ እንደሚሰማ ይህ ሊገለጥላችሁ ይገባል ብዬ አስባለሁ። የጥንት ሰዎች ስለ ጁፒተር ጥቃቅን ነገሮችን የሚያስብበት ጊዜ የለውም ይሉ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ከፍጥረታቱ ለታናሹ እንኳ ለማሰብ ራሱን ዝቅ ያደርጋል፤ ወደ ወፎች ጎጆ እንኳ ይመለከታል! ታዲያ የአስፈሪ ዘላለማዊነት ወራሾች ለሆኑት መናፍስት በምሕረት አያስብላቸውምን?

ደግሞም ቍራዎች በእግዚአብሔር መልክ እንደ ተፈጠሩ ፈጽሞ ሰምቼ አላውቅም! ዘራችን የረከሰ፣ የተበላሸና የወረደ ቢሆንም፣ በመጀመሪያ ግን እግዚአብሔር «ሰውን በመልካችን፣ እኛን እንዲመስል እንሥራ» እንዳለ አገኛለሁ። በሰው ውስጥ በታችኞቹ ፍጥረታት የማይገኝ አንድ ነገር አለ፤ ከእነርሱ መካከል እጅግ የተሻሉትና የከበሩት እንኳ ከአዳም ልጆች እጅግ ከተናቀው በማይለካ መጠን ያንሳሉ። ስለ ሰው አፈጣጠር ምክር ተደረገ፤ በአእምሮውም፣ ሰውነቱም አእምሮውን እንዲረዳ በተዘጋጀበት ሁኔታ እንኳ፣ የልዑሉ ጥበብ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተገልጦአል።

ከሰው ዘር እጅግ የተበላሸውን፣ የተናቀውንና ክፉውን ወደዚህ አምጡ፤ ምንም እንኳ የሰውን ተፈጥሮ በሥነ ምግባር ረገድ ለማሞካሸት ባልደፍርም፣ ሰው በመሆን እውነታ ውስጥ በምድር አራዊት ሁሉ — ምንም ቢሆኑ — የማይገኝ ክብር አለ። ብሄሞትና ሌዋታን ከሰው እግር በታች ተገዝተዋል። ንስር የሰው ነፍስ እንደምትወጣ ያህል ከፍ ብሎ ሊበር አይችልም፤ አንበሳም የሰው መንፈስ እንደሚራበው ያለ ንጉሣዊ መብል አይበላም። ታዲያ እግዚአብሔር እንደ ቍራ ያለውን እጅግ ዝቅተኛና የተናቀ ፍጡር ሰምቶ፣ እናንተን ግን በመልኩ ከተፈጠረው ዘር አንዱ ስትሆኑ አይሰማችሁም ብላችሁ ታስባላችሁን?

ኦ፣ መንገዱ ሁልጊዜ ቅን ስለ ሆነው ስለ እርሱ እንዲህ ያለ ጨካኝና የሞኝነት አሳብ አታስቡ! ይህን ለራሳችሁ አቀርባለሁ። ተፈጥሮ ራሱ ሰው ከሰማይ ወፎች በላይ ሊታሰብለት እንደሚገባ አያስተምርምን? የቍራ ጫጩቶችን ጩኸት ብትሰሙ፣ እንዴት እንደምትመግቧቸው ብታውቁ ምግብ እስክትሰጡአቸው ድረስ ለእነዚያ ወፎች ልትራሩ ትችሉ ይሆናል። ነገር ግን ከእናንተ ማንም ወፎቹን እየረዳ፣ በጨካኝ ቸልተኝነት ከተጣለበት ስፍራ ጩኸቱን የምትሰሙትን የሚጠፋ ሕፃን ለማዳን በርኅራኄ ክንፍ አይበርርም ብዬ ማመን አልችልም! በሌሊት ጸጥታ ውስጥ፣ በበሽታ ሊሞት የተቃረበና የሚራራለት የሌለው ሰው በመንገድ ላይ ሲያቃስት ብትሰሙ፣ ተነሥታችሁ አትረዱትምን?

ቍራን የምትረዱ ሰዎች ከሆናችሁ እንደምትረዱት እርግጠኛ ነኝ። ለቍራ ርኅራኄ ካላችሁ፣ ለሰውማ እጅግ አብልጣችሁ እንደምትራሩ የታወቀ ነው! ቤት ለሌላቸው ወንዶችና ሴቶች ይልቅ ቤት ለሌላቸው ውሾች የሚያስቡ አንዳንድ ሞኞች እንዳሉ በሹክሹክታ እንደሚወራ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ለውሾች የሚራሩት እነዚያው ለሰዎችም እጅግ በርኅራኄ የሚያስቡ መሆናቸው የበለጠ የሚመስል ነው። ያም ሆነ ይህ፣ እርዳታ ቢያስፈልገኝ ስለ እነርሱ መልካም ግምት ይኖረኛል። ታዲያ ሁሉን የሚያውቅ ጥበበኛው እግዚአብሔር እነዚህን ላባ ያላበቀሉ ጫጩቶች በጎጆ ውስጥ የሚጠብቅ ከሆነ እናንተንም በእርግጥ እንደሚጠብቃችሁ አታስቡምን?

ልባችሁ «አዎን» ይላል። እንግዲህ ከአሁን ጀምሮ የልባችሁን አለማመን በራሱ ትክክለኛ አመክንዮ በማዞር መልሱለት። ነገር ግን እንዲህ ስትሉ እሰማችኋለሁ፦ «አሃ፣ ቍራ ግን እንደ እኔ ኃጢአተኛ አይደለም! ርኩስ ወፍ ይሆናል፤ ነገር ግን በሥነ ምግባር እንደ እኔ ርኩስ ሊሆን አይችልም። በቀለሙ ጥቁር ይሆናል፤ እኔ ግን በኃጢአት ጠቍሬአለሁ! ቍራ ሰንበትን ሊሽር፣ ሊሳደብ፣ ሊያመነዝር አይችልም! ቍራ ሰካራም ሊሆን አይችልም! እኔ በረከስሁባቸው በእንደዚህ ያሉ ርኵሰቶች ራሱን ሊያረክስ አይችልም።»

ወዳጆቼ ሆይ፣ ያን ሁሉ አውቃለሁ፤ ጕዳያችሁን ይበልጥ ተስፋ ቢስ የሚያደርገው ይመስላችሁ ይሆናል፤ ነገር ግን በእውነቱ እንዲህ የሚያደርግ አይመስለኝም። ለአንድ ደቂቃ እስኪ አስቡበት። ይህ ምን ያረጋግጣል? ኃጢአት መሥራት የምትችሉ ፍጡራን እንደ ሆናችሁ፣ ስለዚህም ቍራ በማይኖርበት መንገድ የምትኖሩ አስተዋይ መናፍስት እንደ ሆናችሁ ነው። እናንተ በመንፈሳዊው ዓለም የምትንቀሳቀሱ ፍጡራን ናችሁ! ቍራ ምንም ድርሻ በሌለበት በነፍሳት ዓለም ውስጥ ትገኛላችሁ። ቍራ መንፈስ፣ ነፍስ ስለሌለው ኃጢአት ሊሠራ አይችልም። እናንተ ግን የተሻለው ክፍላችሁ ነፍሳችሁ የሆነ አስተዋይ ፍጡራን ናችሁ። እንግዲህ ነፍስ ከሥጋ ወሰን በሌለው መጠን የከበረች እንደ ሆነች! ቍራም — አሁን በተራ አነጋገር ነው የምናገረው — ከሥጋ በቀር ምንም ስላልሆነ፣ እናንተ ግን ከሥጋ በተጨማሪ ነፍስም እንደ ሆናችሁ ግልጥ ስለ ሆነ — አለዚያ ኃጢአት መሥራት ባልቻላችሁ ነበር — በዚያ ጥቁርና ተስፋ በሚያስቆርጥ አሳብ ውስጥ እንኳ የብርሃን ፍንጣቂ አያለሁ!

እግዚአብሔር ስለ ሥጋና ደም፣ ስለ አጥንትና ስለ ጥቁር ላባ ይገደዋልን? ስለ ማስተዋላችሁ፣ ስለ ፈቃዳችሁ፣ ስለ ፍርዳችሁ፣ ስለ ሕሊናችሁ፣ ስለማትሞተው ነፍሳችሁስ አይገደውምን? ኦ፣ ብታስቡበት ብቻ፣ የቍራ ጩኸት በመለኮታዊ ቸርነት ጆሮ ዘንድ ተሰሚነትን አግኝቶ፣ የእናንተ ጸሎት ግን በልዑሉ ዘንድ የተናቀና ቸል የተባለ ሊሆን እንደማይቻል ማየት አለባችሁ —

«በደካማ ክንፎቹ በአንዲት የበጋ ጨረር ላይ የሚወነጨፈው ነፍሳት፤ የፀደይ እስትንፋስ ለግማሽ ቀን ሕይወት የሚቀሰቅሰው አበባ፤ እጅግ ትንሿ ብናኝ፣ እጅግ ለስላሳዋ ጠጕር፣ ሁሉም የሰማዩን አባታችንን ጥበቃ ይቀምሳሉ።» እንግዲያስ በእርግጥ የትሑታንን ጩኸት ይመለከታል፤ ጸሎታቸውንም እምቢ አይልም!

ይህን ነጥብ ከመተዌ በፊት፣ የቍራ መጠቀሱ ኃጢአተኛን ሊያበረታታ እንደሚገባ ሳልናገር ማለፍ አልችልም። አንድ የጥንት ጸሐፊ እንደ ጻፈው፦ «ከወፎች መካከል በመሳፍንት ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆኑትንና የሚመገቡትን ጭልፊትንና ጭላትን አልጠቀሰም። ነገር ግን ሰው ሊያስቸግረው የሚችለውን በድን ከመብላቱ በቀር ማንም ዋጋ የማይሰጠውን ያን የተጠላና ክፉ ወፍ፣ የሚያንቋርረውን ቍራ መረጠ። እንግዲህ እዩ፤ የእግዚአብሔርንም መግቦትና ቸርነት አድንቁ፤ ይህን ያህል የሚያስፈራ መልክና ይህን ያህል የማይጣፍጥ ድምፅ ላለው፣ ለብዙ ሰዎች ለሚያስጠላና ለአንዳንዶችም መጥፎ ገድ ለሆነው ፍጡር ለቍራ ምግብ ያዘጋጃል። በበጋ ምግብዋን ለምትሰበስበው ለገብረ ጕንዳን በማዘጋጀቱ የእግዚአብሔር ታላቅ መግቦት ይታያል፤ ራሱን ለመመገብ ቢረሳ ወይም ግድ ባይለው እንኳ እግዚአብሔር በሚያዘጋጅለትና በሚያከማችለት በቍራ ግን የበለጠ ይታያል።»

አንድ ሰው እግዚአብሔር ስለ ቍራዎች «ራሳቸውን ይቻሉ ወይም ይጥፉ» ማለት የሚገባው ይመስለው ይሆናል! አይደለም፤ ጌታ እግዚአብሔር ከእጁ ሥራ ማንኛውንም አይንቅም። ቍራ ህልውናውን ያገኘው ከእግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህም ቍራ በእርሱ ይመገባል። ውቢቱ ንጹሕ ርግብ ብቻ ሳትሆን አስቀያሚው ቍራም ምግቡን ከእግዚአብሔር ያገኛል። ይህም እናንተ ቍራ የመሰላችሁ ጥቁር ኃጢአተኞች ሆይ፣ በእናንተ ዘንድ የመልካምነት መጕደል ጩኸታችሁ በሰማይ እንዳይሰማ እንደማይከለክል በግልጥ ያሳያል! አለመገባትን የኢየሱስ ደም ያስወግደዋል፤ ርኵሰትንም እርሱ ፈጽሞ ያነጻዋል። በኢየሱስ ብቻ እመኑ፤ ሰላምንም ታገኛላችሁ!

2. እንግዲህ በሚቀጥለው ደረጃ፣ በእናንተ ጩኸትና በቍራ ጩኸት መካከል ታላቅ ልዩነት አለ። የቍራ ጫጩቶች ሲጮኹ የሚፈልጉትን ነገር እምብዛም አያውቁም ብዬ እገምታለሁ። ለምግብ እንዲጮኹ የሚያደርጋቸው የተፈጥሮ ስሜት አላቸው፤ ጩኸታቸው ግን በራሱ ፍላጎታቸውን አይገልጥም። ምግብ መፈለጋቸውን ብዙም ሳትቆዩ ትረዱ ይሆናል፤ ነገር ግን ግልጥ ንግግር የላቸውም፤ አንዲት ቃል እንኳ አይናገሩም! የማያቋርጥ፣ የሚያንቋርርና የሚለምን ጩኸት ብቻ ነው፤ ያም ብቻ ነው።

እናንተ ግን የሚያስፈልጋችሁን ታውቃላችሁ፤ ቃላችሁ ጥቂት ቢሆንም ልባችሁ የራሱን ምሬትና ከባድ ጭንቀት ያውቃል። ትካዜአችሁና መቃተታችሁ ግልጥ ትርጕም አላቸው። ማስተዋላችሁ በተራበው ልባችሁ ቀኝ አለ። ሰላምና ይቅርታ እንደምትሹ ታውቃላችሁ። ኢየሱስ፣ ክቡር ደሙና ፍጹም ጽድቁ እንደሚያስፈልጋችሁ ታውቃላችሁ። እንግዲህ፣

እግዚአብሔር እንደ ቍራ ያለውን እንግዳ፣ የሚንጫጫና ግልጥ ያልሆነ ጩኸት የሚሰማ ከሆነ፣ «እግዚአብሔር ሆይ፣ ለእኔ ለኃጢአተኛው ራራልኝ» እያለ ወደ እርሱ የሚጮኸውን የምስኪን፣ የችግረኛና የበደለኛ ነፍስ አስተዋይና ትርጕም ያለው ጸሎትም እንደሚሰማ አታስቡምን? ማስተዋላችሁ በእርግጥ ይህን ይነግራችኋል!

ደግሞም የቍራ ጫጩቶች ማስተዋል ስለሌላቸው ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም። እናንተ እንደምትሉት ሊሉ አይችሉም —

«ከአምላኬ ጋር ለመታገል የምይዘውን ማስረጃ ያውቃል፤ ስለ ራሱ ምሕረት ብዬ እማልዳለሁ፤ ስለ መድኃኒትም ደም።»

አንድ ማስረጃ ብቻ አላቸው፤ ይኸውም ጩኸታቸውን ከእነርሱ የሚያስወጣው ጽኑ ችግራቸው ነው፤ ከዚህ በላይ ግን መሄድ አይችሉም። ይህንንም እንኳ በሥርዓት ሊያቀርቡት ወይም በቋንቋ ሊገልጡት አይችሉም። እናንተ ግን በእጃችሁ የተዘጋጁ ብዙ ማስረጃዎች አሏችሁ፤ እነርሱንም በሰልፍ አሰልፋችሁ የጸጋውን ዙፋን ለመክበብ የምታዘጋጁበት ማስተዋል አላችሁ። ያልተነገረው የቍራ ችግር ብቻ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያሸንፍ ከሆነ፣ እናንተማ ጕዳያችሁን በፊቱ ብትሟገቱና ማስረጃን በአፋችሁ ይዛችሁ ወደ እርሱ ብትቀርቡ በልዑሉ ዘንድ እጅግ አብልጣችሁ ታሸንፋላችሁ! ተስፋ የቈረጣችሁ ሆይ፣ ኑ፤ ጌታዬን ሞክሩት! አሁን እለምናችኋለሁ፤ ያ የሐዘን እንጕርጕሮ ወደ ምሕረት ጆሮ ይውጣ! ቃላት ከአቅማችሁ በላይ ከሆኑ ያን ሊፈነዳ የደረሰውን ልብ ክፈቱት፤ በእንባም ያውጣው!

ነገር ግን እፈራለሁ፣ ቍራ እግዚአብሔርን በጸሎት ከሚፈልጉ አንዳንድ ኃጢአተኞች ይልቅ አንዳንድ ጊዜ ታላቅ ብልጫ አለው፤ ይኸውም በዚህ ነው፦ የቍራ ጫጩቶች አንዳንዶች ስለ ነፍሳቸው ከሚተጉት ይልቅ ስለ ምግባቸው ይበልጥ ይተጋሉ። ይህ ግን እናንተን የሚያስቆርጥ አይደለም፤ ይልቁንም ከበፊቱ ይበልጥ እንድትተጉ ምክንያት ነው። ቍራዎች ምግብ ሲያስፈልጋቸው እስኪያገኙ ድረስ ጩኸታቸውን አያቋርጡም። የተራበን የቍራ ጫጩት አፉ እስኪሞላ ድረስ ዝም ማሰኘት አይቻልም፤ በእውነት የሚተጋን ኃጢአተኛም ልቡ በመለኮታዊ ምሕረት እስኪሞላ ድረስ ዝም ማሰኘት አይቻልም። ከእናንተ አንዳንዶች አጥብቃችሁ ብትጸልዩ ምነው! «መንግሥተ ሰማያት ጥቃት እየደረሰባት ነው፤ ዓመፀኞችም ሊነጥቋት ይሞክራሉ።»

አንድ የጥንት ፒዩሪታን እንዲህ አለ፦ «ጸሎት የሰማይን በሮች በኃይል ለመክፈት በሰማይ ደጅ ላይ የተደቀነ መድፍ ነው።» ከተማይቱን ማግኘት ከፈለጋችሁ በጦርነት መያዝ አለባችሁ! በላባ ፍራሽ ላይ ተኝታችሁ ወደ ሰማይ አትጓዙም። ጕዞ መሄድ አለባችሁ፤ በከባድ እንቅልፍ ተኝታችሁ ወደ ክብር አገር መሄድ የለም፤ የሚያልሙ ታካቾች በሲኦል ውስጥ ይነቃሉ! እግዚአብሔር በነፍሳችሁ የመዳንን አስፈላጊነት እንዲሰማችሁ ካደረገ፣ እንደ ነቃና ሕያው እንደ ሆነ ሰው ጩኹ! ትጉ! በታላቅ ድምፅ ጩኹ! አትቈጥቡ! ከዚያም ማስረጃዬ ፍጹም ትክክል እንደ ሆነ ታገኛላችሁ ብዬ አስባለሁ፤ በሁሉ ረገድ አስተዋይ፣ ማስረጃ ያለውና ትርጕም ያለው ጸሎት ከቍራ ተራ ጩኸትና ጫጫታ ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ የማሸነፍ ዕድሉ ይበልጣል፤ እንደ ቍራ ያለውን ጩኸት የሚሰማ ከሆነም የእናንተን እንደሚሰማ እጅግ የተረጋገጠ ነው።

3. የጸሎታችሁ ጕዳይ ቍራ ለምግብ ከሚጮኸው ጩኸት ይልቅ ለእግዚአብሔር ጆሮ ይበልጥ የሚስማማ መሆኑን አስቡ። የቍራ ጫጩቶች የሚጠሩት ምግብን ብቻ ነው፤ ጥቂት በድን ስጡአቸው፤ ይበቃቸዋል። የእናንተ ጩኸት ግን በውድ ልጁ ደም በኩል ይቅርታን ስለምትለምኑ ለእግዚአብሔር ጆሮ እጅግ የሚያስደስት መሆን አለበት። ለልዑሉ ሥጋዊ ስጦታን ከመስጠት ይልቅ መንፈሳዊ ስጦታን መስጠት የከበረ ሥራ ነው። የመለኮታዊ ጸጋ ጅረቶች ከላይኞቹ ምንጮች ይፈስሳሉ። እርሱ እጅግ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ስለ ሆነ በቍራ ጫጩት አፍ ውስጥ ምግብ ሲጥል እንኳ ራሱን እንደማያዋርድ አውቃለሁ፤ ቢሆንም ለሰው ልጆች ሰላምን፣ ይቅርታንና መታረቅን በመስጠት ሥራ ውስጥ የበለጠ ክብር አለ።

ዘላለማዊ ፍቅር ከዓለም መፈጠር በፊት የምሕረትን መንገድ ወሰነ፤ ወሰን የሌለው ጥበብም መለኮታዊውን ዕቅድ ለመፈጸም ወሰን ከሌለው ኃይል ጋር ተሰልፎአል። በእርግጥ ጌታ የሰውን ልጆች በማዳን እጅግ ደስ ሊሰኝ ይገባዋል! እግዚአብሔር የምድርን አራዊት በመመገብ ደስ የሚሰኝ ከሆነ፣ የራሱን ልጆች በመመገብ እጅግ አብልጦ ደስ እንደሚሰኝ አታስቡምን? በሬያችሁን ከመቀለብ ወይም በጎተራ ደጅ ላይ ለዶሮዎች ገብስ ከመበተን ይልቅ የገዛ ልጆቻችሁን በማስተማር የሚስማማ ሥራ የምታገኙ ይመስለኛል፤ ምክንያቱም በመጀመሪያው ሥራ ውስጥ ኃይላችሁን ሁሉ ይበልጥ የሚጠራና ውስጣዊ ማንነታችሁን የሚያወጣ የከበረ ነገር አለና።

እዚህ ለመገመት አልተተውሁም። «በጽኑ ፍቅር ደስ ይለዋል» ተብሎ ተጽፎአል። እግዚአብሔር ኃይሉን ሲጠቀም ሊያዝን አይችልም፤ ብፁዕ አምላክ ነውና። ነገር ግን ወሰን የሌለው አምላክ በአንድ ጊዜ ከሌላው ጊዜ ይልቅ ይበልጥ ደስ ሊሰኝ የሚቻል ቢሆን፣ ይህ የሚሆነው በኢየሱስ ክቡር ደም በኩል ኃጢአተኞችን ይቅር በሚልበት ጊዜ ነው። አሃ፣ ኃጢአተኛ ሆይ፣ ወደ እግዚአብሔር ስትጮኽ ከሁሉ ይልቅ ሊያደርገው የሚወድደውን ነገር እንዲያደርግ ዕድል ትሰጠዋለህ! ይቅር ማለትን፣ ኤፍሬሙን በእቅፉ ማስጠጋትን፣ ስለ አባካኙ ልጁም «ጠፍቶ ነበር፤ አሁን ግን ተገኝቷል»፣ «ሞቶ ነበርና፤ አሁን ግን እንደ ገና ሕያው ሆኗል» ማለትን ይወድዳል። ይህ ለአባቱ ልብ የሰባውን ፊሪዳ ከመቀለብ ወይም በሺህ ኮረብቶች ላይ ያሉትን ከብቶች ከመጠበቅ ይልቅ የሚያስደስት ነው።

እንግዲህ ውድ ወዳጆች ሆይ፣ ለቍራዎች ምግብን ከመስጠት ይልቅ መስጠቱ እግዚአብሔርን እጅግ የሚያከብረውን ነገር ስለምትለምኑ፣ ዛሬ ማታ አለማመናችሁን ሰባብሮ ለመጣል ከማስረጃዬ መዶሻ እጅግ ብርቱ ምት የሚወርድ ይመስለኛል! እውነተኛው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር በእናንተ ውስጥ በኃይል ይሥራ! በእርግጥ ለቍራዎች ምግብ የሚሰጥ አምላክ ለሚፈልጉት ኃጢአተኞች ሰላምንና ይቅርታን አይከለክልም። ሞክሩት! በዚህች ቅጽበት ሞክሩት! አይደለም፣ ከቦታችሁ አትነሡ! አሁኑኑ ሞክሩት!

4. ጕዳዩ ሁሉ እጅግ ሰፊ ስለ ሆነ በአንድ ነጥብ ላይ መቆየት የለብንም። ለእናንተ ሌላ የመጽናኛ ምንጭ አለ፤ ይኸውም ቍራዎች እንዲጮኹ የትም ቦታ አልታዘዙም። ሲጮኹ ልመናቸው ከመለኮታዊ አፍ በወጣ በምንም የተለየ ምክር የተደገፈ አይደለም። እናንተ ግን በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ለመቅረብ ከመለኮታዊ ምክሮች የተገኘ ፈቃድ አላችሁ!

አንድ ባለ ጠጋ ሰው ላልተጋበዙት ቤቱን ቢከፍት፣ የተጋበዙትን በእርግጥ ይቀበላል። ቍራዎች ሳይጠሩ ይመጣሉ፤ ቢሆንም ባዶአቸውን አይሰደዱም! እናንተ እንደ ተጋበዘ እንግዳ እንድትመጡ ታዝዛችኋል፤ እንዴት ትከለከላላችሁ? እንድትመጡ ያልተጠራችሁ ይመስላችኋልን? ይህን ስሙ፦ «የጌታን ስም የሚጠሩ ሁሉ ይድናሉ።» «መከራም ሲመጣ ወደ እኔ ጩኽ፤ ነጻ አወጣሃለሁ፤ አንተም ታከብረኛለህ።» «ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱና ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ አውጁ። ያመነና የተጠመቀ ሁሉ ይድናል፤ ለማመን እምቢ ያለ ግን ይፈረድበታል።» «በጌታ በኢየሱስ እመን»፣ ትድናለህም። «ንስሓ ግቡ»፤ «እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ»።

እነዚህ ስለ ሰዎች ጠባይ ምንም ገደብ ሳይደረግ የተሰጡ ምክሮች ናቸው። በነጻ ይጋብዟችኋል፤ አይደለም፣ እንድትመጡ ያዝዟችኋል። ታዲያ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ይጥላችኋል ብላችሁ ታስባላችሁን? መስኮቱ ተከፍቶአል፤ ቍራ በርሮ ይገባል፤ የምሕረት አምላክም አያባርረውም! በሩ ተከፍቶአል፤ የተስፋ ቃልም እንድትመጡ ይጠራችኋል፤ ይከለክላችኋል ብላችሁ አታስቡ፤ ይልቁንም «በቸርነት እንደሚቀበላችሁና በነጻ እንደሚወድዳችሁ» እመኑ፤ ከዚያም «በወይፈኖች ፋንታ ከንፈሮቻችሁን ታቀርቡለታላችሁ»። ያም ሆነ ይህ ሞክሩት! አሁኑኑ እንኳ ሞክሩት!

5. ደግሞም ሌላ፣ እጅግ የበረታ ማስረጃ ገና አለ። የቍራ ጫጩት ጩኸት የአንድ ፍጡር የተፈጥሮ ጩኸት ብቻ ነው፤ የእናንተ ጩኸት ግን ቅን ከሆነ በልባችሁ ውስጥ የመለኮታዊ ጸጋ ሥራ ፍሬ ነው። ቍራ ወደ ሰማይ ሲጮኽ የሚጮኸው የቍራው ራሱ ብቻ ነው፤ እናንተ ግን «እግዚአብሔር ሆይ፣ ለእኔ ለኃጢአተኛው ራራልኝ» ብላችሁ ስትጮኹ በእናንተ ውስጥ የሚጮኸው መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው!

ከታላቁ መገኛው ጋር ኅብረትና ግንኙነት እንዲኖረው ወደ መጣበት ምንጭ የሚጮኸው እግዚአብሔር የሰጣችሁ አዲሱ ሕይወት ነው። ሰውን በቅንነትና በእውነት እንዲጸልይ ለማድረግ እግዚአብሔር ራሱ ያስፈልጋል! ብናስብበት ልጆቻችንን «ጸሎታቸውን እንዲያነበንቡ» ማስተማር እንችላለን፤ ነገር ግን «እንዲጸልዩ» ልናስተምራቸው አንችልም። «የጸሎት መጽሐፍ» ልታዘጋጁ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት «ጸሎት» በመጽሐፍ ውስጥ ልታስገቡ አትችሉም፤ በገጾች መካከል ለመታሸግ እጅግ መንፈሳዊ ነገር ነውና። ከእናንተ አንዳንዶች ምናልባት በቤተ ሰብ ውስጥ «ጸሎቶችን ታነባላችሁ» ይሆናል። ልማዱን አላወግዝም፤ ነገር ግን ስለ እርሱ ይህን ያህል እላለሁ — እነዚያን «ጸሎቶች» ሰባ ዓመት ልታነቡ ትችላላችሁ፤ ቢሆንም አንድ ጊዜ እንኳ ሳትጸልዩ ትቀሩ ይሆናል፤ ጸሎት ከተራ ቃላት ፈጽሞ የተለየ ነገር ነውና።

እውነተኛ ጸሎት የልብ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያደርገው ንግድ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር በሸራዎቹ ውስጥ ነፋስን እስኪያስገባና መርከቢቱን ወደ ወደብዋ እስኪያፋጥን ድረስም ልብ ከሰማይ ወደቦች ጋር መንፈሳዊ ንግድ ፈጽሞ አይገባም። «ከላይ መወለድ አለባችሁ።» በልባችሁ ውስጥ እውነተኛ ጸሎት ካለ፣ ምሥጢሩን ባታውቁትም መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር በዚያ አለ! እንግዲህ ከራሱ ያልወጡትን ጩኸቶች የሚሰማ ከሆነ ከራሱ የወጡትንማ እንዴት አብልጦ ይሰማቸዋል! ምናልባት ጩኸታችሁ ተፈጥሮአዊ ወይስ መንፈሳዊ እንደ ሆነ ለማወቅ ራሳችሁን ስታስጨንቁ ኖራችሁ ይሆናል። ይህ እጅግ አስፈላጊ ሊመስል ይችላል፤ እንደዚያም መሆኑ አያጠራጥርም — ነገር ግን ጩኸታችሁ ከሁለቱ የትኛውም ቢሆን፣ ጌታን መፈለጋችሁን ቀጥሉ!

ምናልባት ተፈጥሮአዊ ጩኸቶች በእግዚአብሔር ዘንድ ይሰሙ እንደ ሆነ ትጠራጠሩ ይሆናል። እንደሚሰሙ ላረጋግጥላችሁ። በአንድ ወቅት በአንድ ጽንፈኛ ካልቪናዊ የአምልኮ ስፍራ ስለዚህ ጕዳይ አንድ ነገር እንደ ተናገርሁ አስታውሳለሁ። በዚያን ጊዜ ለልጆች እየሰበክሁ እንዲጸልዩ እመክራቸው ነበር። ማንኛውም እውነተኛ መለወጥ ከመሆኑ እጅግ አስቀድሞ ለተራ ምሕረቶች እጸልይ እንደ ነበረና እግዚአብሔርም ጸሎቴን እንደ ሰማ በአጋጣሚ ተናገርሁ። ይህ ራሳቸውን እጅግ የጠሩ አድርገው የሚቈጥሩትን ደጋግ ወንድሞቼን አላስደሰታቸውም! ከዚያም በኋላ ሁሉም ምን ማለቴ እንደ ሆነ ለማወቅ ነው ብለው በዙሪያዬ ተሰበሰቡ፤ በእውነቱ ግን እንደ ጠባያቸውና ልማዳቸው ለመንቀፍና ለመተቸት ነበር።

«እንደ ንብ መንጋ መጡብኝ። አዎን፥ እንደ ንብ መንጋ መጡብኝ!» ትንሽ ቆይተው፥ እንደ ጠበቅሁትም፥ ሰዎችን በስም የመሰየም የተለመደ ጨዋታቸውን ጀመሩ። ይህ ምን ያለ የከፋ የአርሚኒያን ትምህርት ነው! ይሉ ጀመር። ሊያከብሩኝ የወደዱበት ሌላው አነጋገር ደግሞ «ፉለራዊ» የሚለው ስም ነበር፤ ይህ ስም ግን በነገራችን ላይ እጅግ የተከበረ በመሆኑ በተናገርሁት ነገር ላይ ስላያያዙልኝ ከልቤ ላመሰግናቸው በቻልሁ ነበር! ነገር ግን እግዚአብሔር የተፈጥሮ ሰዎችን ጸሎት ይሰማል ማለት ለእነርሱ ከአርሚኒያን ትምህርት የከፋ ነገር ነበር፤ በእርግጥ ከዚያ የሚከፋ ነገር ሊኖር የሚችል ከሆነ! ያን የሐሰት ጥቅስ፥ «እግዚአብሔር የክፉዎችን ጸሎት ይጸየፋል» የሚለውን ጠቀሱ፤ እኔም ያንን ጥቅስ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ፈልገው ያሳዩኝ እንደ ሆነ በመጠየቅ ፈጥኜ መለስሁላቸው፤ የዚያ አባባል ደራሲ ዲያብሎስ ነው፥ በመጽሐፍ ቅዱስም ውስጥ ፈጽሞ የለም ብዬ ለመናገር ደፍሬ ነበርና።

«እግዚአብሔር የክፉዎችን መሥዋዕት ይጸየፋል» የሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ፤ ነገር ግን ይህ ከ«የክፉዎች ጸሎት» እጅግ የተለየ ነገር ነው። ደግሞም በዚያ ስፍራ «ክፉዎች» በሚለው ቃል በተፈለገው ሰውና እኛ በምንከራከርበት በተፈጥሮ ሰው መካከል ግልጥ ልዩነት አለ። በማናቸውም መልኩ መጸለይ የሚጀምር ሰው ሰሎሞን ካሰባቸው «ክፉዎች» መካከል ሙሉ በሙሉ እንደ ተቈጠረ ሊታይ ይችላል ብዬ አላስብም፤ ሕግን ከመስማት ጆሮአቸውን ከሚመልሱት፥ ጸሎታቸው አስጸያፊ እንደ ሆነ ከተጻፈላቸው ሰዎች መካከልም በእርግጥ አይደለም።

እነርሱም፦ «መልካም፥ ነገር ግን እግዚአብሔር የተፈጥሮን ጸሎት እንዴት ሊሰማ ይችላል?» አሉ። እኔም ለጥቂት ጊዜ ዝም ብዬ ሳለሁ፥ ቀይ ካባ የለበሰች አንዲት አሮጊት በዙሪያዬ በነበረው በትንሹ ክበብ መካከል ተጋፍታ ገባችና፥ በእርግጥም በእስራኤል እንዳለች እናት፥ እጅግ በኃይለ ቃል እንዲህ አለቻቸው፦ «እግዚአብሔር ራሱ የተናገረውን ረስታችሁ ይህን ጥያቄ ለምን ታነሣላችሁ! እግዚአብሔር የተፈጥሮን ጸሎት አይሰማም የምትሉት ይህ ምንድር ነው? የቁራ ጫጩቶች ወደ እርሱ ሲጮኹ አይሰማቸውምን? እነርሱስ መንፈሳዊ ጸሎት የሚያቀርቡ ይመስላችኋልን?»

ወዲያውም እነዚያ የጦር ሰዎች እግሬ አውጪኝ ብለው ሸሹ፤ ከዚያ የበለጠ ፍጹም ሽንፈት አልነበረም፤ በሕይወታቸውም ለአንድ ጊዜ እንኳ ሊሳሳቱ እንደሚችሉ ሳይሰማቸው አልቀረም! ወንድሞች ሆይ፥ በእርግጥ ይህ ሊያበረታታችሁና ሊያጽናናችሁ ይችላል! ጸሎታችሁ የተፈጥሮ ወይም መንፈሳዊ መሆኑን፥ ከእግዚአብሔር መንፈስ የሚመጣ ወይም የማይመጣ መሆኑን እንድትመረምሩ አሁን ይህን ሥራ አልሰጣችሁም፤ ይህ ምናልባት ተስፋ ሊያስቆርጣችሁ ይችላልና። ጸሎቱ ከልባችሁ ጥልቅ የሚወጣ ከሆነ፥ እናንተ ባታውቁትም እንኳ እኛ ወደዚያ እንዴት እንደ ገባ እናውቃለን። እግዚአብሔር ቁራዎችን ይሰማል፤ እናንተንም እንደሚሰማችሁ በእውነት አምናለሁ፤ ደግሞም አሁን በልባችሁ ውስጥ ጥያቄውን ማንሣት ባልፈልግም፥ ጸሎታችሁን እንደሚሰማ አምናለሁ፤ ምክንያቱም፥ ምንም እንኳ ባታውቁት፥ መጸለይን የሚያስተምራችሁ የእግዚአብሔር መንፈስ የሆነ ስውር ሥራ በውስጣችሁ እየተሠራ ነውና።

6. ነገር ግን የበለጡ ብርቱና ወደ ዒላማው የቀረቡ ማስረጃዎች አሉኝ። የቁራ ጫጩቶች ሲጮኹ ብቻቸውን ይጮኻሉ። እናንተ ስትጸልዩ ግን ከእናንተ የሚበልጥ ብርቱ የሆነ አንድ ከእናንተ ጋር ይጸልያል! ያ ኃጢአተኛ፦ «እግዚአብሔር ሆይ፣ ለእኔ ለኃጢአተኛው ራራልኝ» ብሎ ሲጮኽ ትሰሙታላችሁን? ስሙ! ከእርሱ ጩኸት ጋር አብሮ ወደ ላይ የሚወጣውን ያን ሌላ ጩኸት ትሰማላችሁን? አይደለም፥ ጆሮአችሁ የደነዘዘና የከበደ ስለ ሆነ አትሰሙትም፤ እግዚአብሔር ግን ይሰማዋል። ከመጀመሪያው እጅግ የሚጮኽና የሚጣፍጥ፥ እጅግም የሚያሸንፍ ሌላ ድምፅ በዚያው ቅጽበት ወደ ላይ እየወጣ፦ «አባት ሆይ፥ በክቡር ደሜ ይቅር በላቸው» እያለ ይማልዳል።

ለኃጢአተኛው ሹክሹክታ የሚመለሰው ማሚቶ እንደ ነጐድጓድ ድምፅ ግርማ ያለው ነው! ክርስቶስ በዚያው ጊዜ ሳይጸልይ ኃጢአተኛ በእውነት የሚጸልይበት ጊዜ ፈጽሞ የለም! ልታዩትም ልትሰሙትም አትችሉም፤ ነገር ግን ኢየሱስ በመንፈሱ የነፍሳችሁን ጥልቀት ሲያነቃቃ የራሱ ነፍስ ደግሞ ሳትነቃቃ ፈጽሞ አይቀርም። ኃጢአተኛ ሆይ፥ ጸሎትህ በእግዚአብሔር ፊት በሚደርስበት ጊዜ ከአንተ ሲወጣ ከነበረው እጅግ የተለየ ነገር ነው!

አንዳንድ ጊዜ ድሆች ወደ አንድ ድርጅት ወይም ወደ አንድ ታላቅ ባለሥልጣን ሊልኩት የሚፈልጉትን አቤቱታ ይዘው ወደ እኛ ይመጣሉ። አቤቱታውን አምጥተው እንድናቀርብላቸው ይለምኑናል። ፊደሉ እጅግ የተበላሸ፥ አጻጻፉም እጅግ እንግዳ ነው፤ ምን ማለታቸው እንደ ሆነም በጭንቅ ብቻ እንረዳለን። ቢሆንም የሚያስፈልጋቸውን እንድናውቅ የሚበቃ ነገር አለበት። በመጀመሪያ ንጹሕ ቅጅ እናዘጋጅላቸዋለን፤ ከዚያም ጉዳያቸውን ካስረዳን በኋላ የራሳችንን ስም ከታች እንጽፋለን። ተሰሚነትም ካለን፥ በአቤቱታው ግርጌ በተፈረመው ስም ኃይል የሚመኙትን እንደሚያገኙ የታወቀ ነው።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምስኪን ጸሎታችን የሚያደርገው ልክ ይህንኑ ነው! ንጹሕ ቅጅ ያዘጋጅለታል፤ በራሱ የማስተሰረያ ደም ማኅተም ያትመዋል፤ የራሱን ስም በግርጌው ያኖራል፤ እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ይወጣል። ጸሎቱ የእናንተ ነው፤ ነገር ግን ኦ፥ የእርሱም ጸሎት ነው! እንዲያሸንፍ የሚያደርገውም የእርሱ ጸሎት መሆኑ ነው። እንግዲህ ይህ እንደ መዶሻ የሚመታ ማስረጃ ነው፤ ቁራዎች ብቻቸውን ሲጮኹ የሚያሸንፉ ከሆነ፥ ምስኪኑ ጩኸታቸው በራሱ የሚያስፈልጋቸውን የሚያስገኝላቸው ከሆነ፥ «ስለ ኢየሱስ ብለህ» ማለት የሚችለው፥ ማስረጃዎቹንም ሁሉ፦ «ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይገባዋል! ጌታ ሆይ፥ ስለ እርሱ ብለህ ስጠኝ» በሚለው ብፁዕ ልመና የሚያጸናው የምስኪኑ የሚንቀጠቀጥ ኃጢአተኛ ሐዘን የሞላበት ልመና እንዴት አብልጦ ያሸንፍ ይሆን?

ስናገራቸው የነበሩት እነዚህ ፈላጊዎች፥ ለረጅም ጊዜ ሲጮኹ የኖሩትና ፈጽሞ እንደማይሰሙ የሚፈሩት፥ ከዚህ በላይ ብዙ መጠበቅ ሳያስፈልጋቸው በቶሎ የሰላም ቸር መልስ እንዲያገኙ በእውነት ተስፋ አደርጋለሁ! የልባቸውን ምኞት አሁኑኑ ባያገኙም እንኳ፥ የጸጋ ቀን እስኪነጋ ድረስ እንዲጸኑ እንዲበረታቱ ተስፋ አደርጋለሁ። ቁራዎች የሌላቸው የተስፋ ቃል አላችሁ፤ ጊዜ በዚህ ላይ እንድንቆይ ቢፈቅድልን ይህ ሌላ ማስረጃ ሊሆን ይችል ነበር። የምትንቀጠቀጥ ሆይ፥ የምትማጸንበት የተስፋ ቃል ስላለህ በጸጋው ዙፋን ፊት እንደምትሰማ ፈጽሞ አትጠራጠር!

አሁንም በመደምደሚያዬ ለኃጢአተኛው እንዲህ ልበል፦ ጮኻችሁ ሳይሳካላችሁ ቢቀር፥ አሁንም መጮኻችሁን ቀጥሉ። «ሰባት ጊዜ፦ ‹ተመለስ›»፤ አዎን፥ «እስከ ሰባ ሰባት ጊዜ»! በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የእግዚአብሔር ምሕረት ብቸኛ ተስፋችሁ መሆኑን አስቡ!

እንግዲህ የሚሰጥም ሰው በእጁ ሊደርስ የሚችለውን ብቸኛ ገመድ አጥብቆ እንደሚይዝ እናንተም አጥብቃችሁ ያዙት። በክቡሩ ደም በኩል ምሕረትን እየለመናችሁ ብትጠፉ፥ እንዲህ ሆኖ ከጠፉት የመጀመሪያዎቹ ትሆናላችሁ! ጩኹ! መጮኻችሁን ብቻ ቀጥሉ! ነገር ግን ኦ፥ ደግሞ እመኑ! ማመን የአጥቢያ ኮከብንና የንጋትን ብርሃን ያመጣልና።

የጆን ራይላንድ ሚስት ቤቲ በሞት አልጋ ላይ በነበረች ጊዜ፥ ለብዙ ዓመታት ክርስቲያን የነበረች ብትሆንም፥ በታላቅ የአእምሮ ጭንቀት ውስጥ ነበረች። ባልዋም እንግዳ በሆነው ነገር ግን ጥበብ ባለበት በራሱ መንገድ፦ «መልካም፥ ቤቲ፥ ምን ሆንሽ?» አላት። «ኦ ጆን፥ እየሞትሁ ነው፤ ተስፋም የለኝም፥ ጆን!» «ታዲያ ውዴ ሆይ፥ ወዴት ትሄጃለሽ?» «ወደ ሲኦል እሄዳለሁ!» ብላ መለሰች። እርሱም ጥልቅ ጭንቀቱን በተለመደው ቀልዱ እየሸፈነ፥ ነገሩን በትክክል የሚመታና ጥርጣሬዋን ፈጥኖ የሚያባርር ምት ለመምታት አስቦ፦ «መልካም፥ እዚያ ስትደርሺ ምን ልታደርጊ አስበሻል፥ ቤቲ?» አላት። ደጓ ሴት መልስ መስጠት አልቻለችም፤ ሚስተር ራይላንድም፦ «እዚያ ስትደርሺ የምትጸልዪ ይመስልሻልን?» ሲል ቀጠለ።

እርስዋም፦ «ኦ ጆን፥ የትም ቦታ ብሆን እጸልያለሁ። ከመጸለይ ልከለከል አልችልም!» አለች። እርሱም፦ «መልካም እንግዲያስ፥ ‹ቤቲ ራይላንድ እዚህ ትጸልያለች። አስወጡአት! እዚህ የሚጸልይ ማንንም አንፈልግም! አስወጡአት!› ይላሉ» አላት። ይህ እንግዳ የአነጋገር መንገድ ለነፍስዋ ብርሃን አመጣላት፤ ክርስቶስን በእውነት የምትፈልግ ነፍስ ከፊቱ ለዘላለም ትጣላለች ብሎ መጠርጠር እንኳ ምን ያህል የማይመስል ነገር እንደ ሆነ ወዲያውኑ አየች! ነፍስ ሆይ፥ ጩኺ! መጮኽሽን ቀጥዪ! ሕፃን መጮኽ እስከ ቻለ ድረስ በሕይወት አለ። እናንተም የምሕረትን ዙፋን መከበብ እስከ ቻላችሁ ድረስ ተስፋ አላችሁ! ነገር ግን ከመጮኽ ጋር ስሙ፥ የምትሰሙትንም እመኑ፤ ሰላም የሚገኘው በማመን ነውና።

ነገር ግን ጥቂት ቆዩ፤ የምናገረው ሌላ ነገር አለኝ። የምትጮኹለትን በረከት ምናልባት አስቀድማችሁ አግኝታችሁት ሊሆን ይችላልን? «ኦ፥ አስቀድሜ ያገኘሁትን ነገር አልለምንም! እንዳገኘሁት ባውቅ መጮኼን ትቼ እግዚአብሔርን ማመስገንና መባረክ እጀምር ነበር» ትላላችሁ። እንግዲህ እናንተ ፈላጊዎች ሁላችሁ እንዲህ ባለ አስተማማኝ ሁኔታ ውስጥ እንዳላችሁ አላውቅም፤ ነገር ግን የሚለምኑትን ምሕረት የተቀበሉ አንዳንድ ፈላጊ ነፍሳት እንዳሉ ተረድቻለሁ። ጌታ ዛሬ ማታ ለእነርሱ «ፊቴን ፈልጉ» ከማለት ይልቅ እንዲህ ይላቸዋል፦ «ለምን ወደ እኔ ትጮኻለህ? በሞገሴ ጊዜ መለስኩልህ፤ በመዳን ቀን ደረስኩልህ። ዓመፅህን እንደ ደመና አጠፋሁ፤ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ። አድኜሃለሁ። አንተ የእኔ ነህ። ከኃጢአትህ ሁሉ አንጽቼሃለሁ። መንገድህን ሂድ፥ ደስም ይበልህ።»

እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ከሚያስጨንቅ ጸሎት ይልቅ በእምነት የሚቀርብ ምስጋና ይገባል። «ኦ፥ ነገር ግን ገና እየፈለግሁት ሳለሁ ምሕረትን አግኝቼ ይሆናል ማለት የሚመስል አይደለም» ትላላችሁ። መልካም፥ እኔ አላውቅም። ምሕረትን የምትፈልግ ነፍስ አንዳንድ ጊዜ ከበሩ ውጭ ራስዋን ስታ ትወድቃለች። ራስዋን ስታ ሳለች ወደ ውስጥ ልትገባ፥ በዚያም ጊዜ ሁሉ አሁንም ከውጭ እንዳለች ልታስብ አይቻልምን? ውሻው ገና ሲጮኽ ትሰማለች፤ ነገር ግን አቤት፥ ምስኪን ነፍስ፥ ስትነቃ ከትንሿ በር ውስጥ እንዳለችና በሰላም እንዳለች ታገኛለች!

እንዲሁ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ ወደ ክርስቶስ ልትመጡ ስትሉ በተስፋ መቍረጥ ራሳችሁን ስታችሁ ወድቃችሁ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ከሆነ ሉዓላዊው ጸጋ ይመልሳችሁ፤ ምናልባትም ዛሬ ማታ ለዚህ መሣሪያ እሆን ይሆናል። የምትፈልጉት ምንድር ነው? ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ የሚያበሩ ራእዮችን ለማየት ትጠብቃላችሁ፤ ነገር ግን ይህ ምኞታችሁ ፈጽሞ እንዳይፈጸም ተስፋ አደርጋለሁ፤ ሺህ ራእዮች አንድ ሳንቲም እንኳ አያወጡምና። ከተአምራት ዘመን ወዲህ በዓለም ያሉ ራእዮች ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰቡ ከሁሉም በኋላ ተራ ሕልሞች ብቻ ናቸው፤ ሕልሞችም ከከንቱነት በቀር ሌላ አይደሉም! ሰዎች በእራት ጊዜ ከልክ በላይ ይበሉና ከዚያም ያልማሉ፤ ይህ የምግብ አለመፈጨት ወይም የአንጎል ጤናማ ያልሆነ እንቅስቃሴ ነው፤ ያ ብቻ ነው! የመለወጣችሁ ማስረጃ ይህ ብቻ ከሆነ ብትጠራጠሩት መልካም ታደርጋላችሁ። በዚህ ፈጽሞ እንዳትረኩ እለምናችኋለሁ፤ የዘላለም ተስፋችሁን የምትሠሩበት ከንቱ ጥራጊ ነው።

ምናልባት እጅግ እንግዳ የሆኑ ስሜቶችን ትጠብቁ ይሆናል፤ የኤሌክትሪክ ንዝረት ባይሆንም እጅግ ልዩና ያልተለመደ ነገር። እመኑኝ፥ እጅግ የምታከብሩአቸውን እነዚያን እንግዳ እንቅስቃሴዎች ፈጽሞ ሊሰማችሁ አያስፈልግም። አንዳንድ ሰዎች ከመለወጥ ጋር አያይዘው የሚናገሩአቸው እነዚያ እንግዳ ስሜቶች ሁሉ ለእነርሱ ጥቅም ሊኖራቸውም ላይኖራቸውም ይችላል፤ ነገር ግን ለመለወጥ አስፈላጊ እስከ መሆን ድረስ ከመለወጥ ጋር በእውነት ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው እርግጠኛ ነኝ!

አንድ ወይም ሁለት ጥያቄ ላቅርብላችሁ። ራሳችሁን ኃጢአተኞች እንደ ሆናችሁ ታምናላችሁን? «አዎን» ትላላችሁ። ነገር ግን «ኃጢአተኛ» የሚለውን ቃል ባስቀረውስ? የእግዚአብሔርን ሕግ እንደ ጣሳችሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ የበደላችሁ ከንቱዎች እንደ ሆናችሁ ታምናላችሁ ማለት ነውን? ቢያንስ በልባችሁ ትእዛዛትን ሁሉ እንደ ጣሳችሁና በዚሁ መሠረት ቅጣት እንደሚገባችሁ ታምናላችሁን? «አዎን፥ ይህን የማምነው ብቻ አይደለም፤ ይሰማኛልም! በየዕለቱ የምሸከመው ሸክም ነው» ትላላችሁ።

አሁን ደግሞ ሌላ ነገር፦ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ኃጢአታችሁን ሁሉ ሊያስወግድ እንደሚችል ታምናላችሁን? አዎን፥ ይህን ታምናላችሁ። እንግዲያስ እንዲያድናችሁ በእርሱ ልትታመኑ ትችላላችሁን? መዳን ያስፈልጋችኋል። ራሳችሁን ማዳን አትችሉም። እንዲያድናችሁ በእርሱ ልትታመኑ ትችላላችሁን? «አዎን፥ ይህንማ አስቀድሜ አደርገዋለሁ» ትላላችሁ። መልካም፥ ውድ ወዳጄ ሆይ፥ በእውነት በኢየሱስ የምትታመን ከሆንህ የዳንህ መሆንህ እርግጥ ነው፤ ከማናችንም ጋር ዘወትር የሚኖረው ብቸኛው የመዳን ማስረጃ አለህና! እንደ ቅድስናና እንደ መንፈስ ጸጋዎች ያሉ ከዚያ በኋላ የሚከተሉ ሌሎች ማስረጃዎች አሉ፤ ነገር ግን በሕይወት ካሉት ሰዎች ከሚበልጡት ጋር ዘወትር የሚኖረው ብቸኛ ማስረጃ ይህ ነው፦

«ምንም በእጄ ይዤ አልመጣም፥
መስቀልህን ብቻ አጥብቄ ይዣለሁ።»

የጉልት ነጋዴውን የጃክን ስንኝ ልትጠቀሙበት ትችላላችሁን?

«እኔ ምስኪን ኃጢአተኛ ነኝ፥ ምንም አይደለሁም፥
ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሁሉ በሁሉ ነው።»?

ከጊዜ በኋላ በአንዳንድ ነገሮች በተሞክሮ ከዚህ እጅግ አብልጣችሁ እንድትሄዱ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን የማስረጃችሁን መሠረትና የተስፋችሁን ምክንያት በተመለከተ ከዚህ አንዲት ስንዝር እንኳ እንድትራመዱ አልፈልግም። እዚያው ቁሙ፤ አሁን በውስጣችሁም ሆነ በውጭአችሁ ካለው ነገር ሁሉ ዓይናችሁን አንሥታችሁ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ብትመለከቱ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀባይነት የምታገኙበት መሠረት አድርጋችሁ በቀራንዮ በተቀበለው መከራና በሙሉ የማስተሰረያ ሥራው ብትታመኑ፥ ድናችኋል! ከዚህ የበለጠ ምንም አያስፈልጋችሁም! ከሞት ወደ ሕይወት ተሻግራችኋል። «በእርሱ የሚያምን አይኮነንም»። «የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው።»

ከበሬ ወጥቼ ወደ ልብስ መለወጫ ክፍሌ ስሄድ በዚያ መተላለፊያ ላይ አሁን አንድ መልአክ ብገናኝና፦ «ቻርልስ ስፐርጀን፥ ኃጢአትህ ይቅር እንደ ተባለልህ ልነግርህ ከሰማይ መጥቻለሁ» ቢለኝ፥ እኔ፦ «እንዲህ ያለውን ነገር ምንም ሳትነግረኝ ይህን አውቃለሁ! ከአንተ እጅግ በሚበልጥ ሥልጣን አውቀዋለሁ» እለዋለሁ። እንዴት እንዳወቅሁት ቢጠይቀኝም፦ «የእግዚአብሔር ቃል ከመልአክ ቃል ይልቅ ለእኔ ይበልጣል፤ እርሱም፦ ‹በእርሱ የሚያምን አይኮነንም› ብሎ ተናግሮአል። እኔ በእርሱ አምናለሁ፤ ስለዚህ አልኮነንም፤ ይህንንም የሚነግረኝ መልአክ ሳያስፈልገኝ አውቀዋለሁ» ብዬ እመልስለታለሁ።

እናንተ የተጨነቃችሁ፥ መላእክትንና ምልክቶችን፥ ማስረጃዎችንና ተአምራትን አትፈልጉ። በፍጹሙ የኢየሱስ ሥራ ላይ ብታርፉ በዓለም ላይ ካሉት ሁሉ የሚበልጠው የመዳናችሁ ማስረጃ አስቀድሞ አላችሁ! ለዚህ የእግዚአብሔር ቃል አላችሁ፤ ከዚህ በላይ ምን ያስፈልጋል? የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል አትችሉምን? የአባታችሁን ቃል ትቀበላላችሁ። የእናታችሁን ቃል ትቀበላላችሁ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ለምን መቀበል አትችሉም? ኦ፥ እግዚአብሔርን ራሱን ለመጠርጠር ምን ያህል ወራዳ ልብ ሊኖረን ይገባል!

ምናልባት እንዲህ ያለውን ነገር አናደርግም ትሉ ይሆናል። ኦ፥ ነገር ግን በክርስቶስ የማትታመኑ ከሆነ እግዚአብሔርን ትጠራጠራላችሁ፤ «እግዚአብሔርን የማያምን» እርሱን «ሐሰተኛ አድርጎታል»ና። በክርስቶስ የማትታመኑ ከሆነ በውጤቱ እግዚአብሔር ሐሰተኛ ነው እያላችሁ ነው! ይህን ማለት አትፈልጉም፤ አይደለምን? ኦ፥ የእግዚአብሔርን እውነተኛነት እመኑ! የእግዚአብሔር መንፈስ የአብን ምሕረት፥ የወልድን ደም ኃይል፥ የመንፈስ ቅዱስንም ኃጢአተኞችን ወደ ራሱ ለማምጣት ፈቃደኛነት እንድታምኑ ያስገድዳችሁ!

ውድ አድማጮቼ ሆይ፥ ኑ፥ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በኢየሱስ እንድታዩ በመለኮታዊ ጸጋ እንድትመሩ በሚለው ጸሎት ከእኔ ጋር ተባበሩ፦

«ጸሎት የፍጡር ብርታቱ፥ እስትንፋሱና ሕልውናው ነው።
ጸሎት የምሕረትን ትንሽ በር የሚከፍት የወርቅ መክፈቻ ነው።
ጸሎት ዕጣ ፈንታን፦ ይሁን የሚለው ድንቅ ድምፅ ነው።
ጸሎት የሁሉን ቻዩን ጡንቻዎች የሚያንቀሳቅስ ቀጭን ጅማት ነው፤
ስለዚህ፥ ፍጡር ሆይ፥ ጸልይ፤ ፍላጎቶችህ ብዙና ታላቅ ናቸውና።
አእምሮህ፥ ሕሊናህና ሕልውናህ፥ ፍላጎቶችህ ወደ ጸሎት ያደርሱሃል፤
የጭንቀት ሁሉ ፈውስ፥ ለሕመም ሁሉ ታላቅ መድኃኒት፥
የጥርጣሬ አጥፊ፥ የጥፋት መፍትሔ፥ የሥጋት ሁሉ ማርከሻ ነው።»

ቀዳሚ