በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች የተሰበኩ ስብከቶች
ስለ ቅንዓት

ምዕራፍ 93 · 15 ደቂቃ ንባብ · 19 ደቂቃ ማዳመጥ

ስለ ቅንዓት

ስብከት 92

ስለ ቅንዓት

«ሁልጊዜ ለመልካም ነገር መቅናት መልካም ነው።»

ገላትያ 4:18።

1. በሃይማኖት ክልል ሁሉ ውስጥ ከዚህ ጉዳይ የሚበልጥ አስፈላጊነት ያላቸው ርዕሶች ጥቂቶች ናቸው። ያለ ቅንዓት እኛ ራሳችን በሃይማኖት ጕልህ እድገት ማድረግ ወይም ለባልንጀራችን በምድራዊም ሆነ በመንፈሳዊ ነገር ጕልህ አገልግሎት መስጠት አይቻልምና። ይሁን እንጂ ለብዙ ዘመናት በአረማውያን፣ በመሐመዳውያንና በክርስቲያን ሕዝቦች መካከል ከሰፈነው የቅንዓት ዓይነት ይልቅ ሃይማኖትን የጐዳ ወይም በሰው ልጆች ላይ ጥፋት ያመጣ ምንም ነገር የለም። ስለዚህም ትዕቢት፣ ስስት፣ የሥልጣን ጥማትና በቀል በዓለም ሁሉ ሺዎችን ገደሉ፤ ቅንዓት ግን ዐሥር ሺዎችን ገደለ ቢባል እውነት ነው። የዚህም አስፈሪ ምሳሌዎች በጥንት ዘመን እጅግ በሠለጠኑት የአሕዛብ ሕዝቦች ዘንድ ተከስተዋል። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ኢሰብአዊ ስደት በዋናነት የተነሣው ከዚሁ ነበር፤ በኋለኞቹም ዘመናት የሮም ቤተ ክርስቲያን በፕሮቴስታንቶች ላይ ያደረሰችው ያላነሰ ኢሰብአዊ ስደት እንዲሁ። ደም አፍሳሿ ንግሥት ሜሪ በነገሠችበት ዘመን በአገራችን እሳትን ያነደደው ቅንዓት ነበር። ብዙም ሳይቆይ ብዙዎቹን የፈረንሳይ አውራጃዎች የደም ሜዳ ያደረጋቸው ቅንዓት ነበር። ፈጽሞ በማይረሳው የፓሪስ ጭፍጨፋ ምንም ያልተቃወሙትን ብዙ ሺህ ፕሮቴስታንቶች የገደለው ቅንዓት ነበር። ከዚያም ይበልጥ የሚዘገንነውን የአየርላንድ ጭፍጨፋ ያስከተለው ቅንዓት ነበር፤ በተገደሉት ሰዎች ብዛትም ሆነ ብዙዎቹ ግድያዎች በተፈጸሙባቸው አሰቃቂ ሁኔታዎች ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እንደ እርሱ ያለ ፈጽሞ ተከስቶ እንደማያውቅ በእውነት አምናለሁ። ስለ ቀሩት የአውሮፓ ክፍሎች ደግሞ አንድ ታዋቂ ጀርመናዊ ጸሐፊ ከተሐድሶ ወዲህ ስለ ፈሰሰው ደም በቂ እውቀት ለማግኘት በልዩ ልዩ ስፍራዎች የሚገኙትን መዛግብትና እጅግ ታማኝ የሆኑትን የታሪክ መጻሕፍት በብርቱ ድካም መርምሮአል፤ ከ1520 ዓመተ ምሕረት ጀምሮ በአርባ ዓመታት ውስጥ ከፊሉ በግል ስደት፣ ከፊሉም በሃይማኖታዊ ጦርነቶች ከአርባ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች እንደ ጠፉ ያሰላል!

2. ነገር ግን ትክክለኛውን ቅንዓት ከተሳሳተው መለየት አይቻልምን? ያለ ጥርጥር ይቻላል። ነገር ግን አስቸጋሪ ነው፤ የሰው ልብ ተንኰል እንዲህ ነውና፤ ስሜቶችም ራሳቸውን በዚህ ያህል ብልሃት ያጸድቃሉና። በዚህ ጉዳይ ላይ የተጻፉ መጻሕፍትም እጅግ ጥቂቶች ናቸው፤ ቢያንስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ። እስከ ዛሬ ድረስ ያየሁት ወይም የሰማሁት አንድ ስብከት ብቻ ነው፤ እርሱም ከመቶ ዓመት በላይ በፊት በዚያን ጊዜ የሮቸስተር ጳጳስ በነበሩት በዶ/ር ስፕራት የተጻፈ ነው፤ ስለዚህም አሁን እጅግ ብርቅ ሆኖአል።

3. እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት የሚሹ በጎ አሳብ ያላቸው ሰዎች እውነተኛውን ክርስቲያናዊ ቅንዓት ከልዩ ልዩ አስመሳዮቹ እንዲለዩ ለመርዳት፣ በእግዚአብሔር እርዳታ ይህን አስፈላጊ ጥያቄ ለማብራራት የእኔን ጥቂት ሳንቲም በደስታ ላበረክት እወዳለሁ። ይህም በዚህ ጊዜ ከብዙ ዓመታት ወዲህ ከነበረው ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ከስድሳ ዓመት በፊት በአገሪቱ ሃይማኖታዊ ቅንዓት የሚባል ነገር የቀረ አይመስልም ነበር። ሰዎች በአጠቃላይ ስለ ያቺ ተራ ነገር፥ ስለ ሃይማኖት በሚያስደንቅ ሁኔታ ቀዝቃዛና ግድ የለሾች ነበሩ። ከዚያ ወዲህ ግን እጅግ ጕልህ ለውጥ እንደ ተደረገ በቀላሉ ማየት ይቻላል። በአገሪቱ በሁሉም ክፍል ማለት ይቻላል ብዙ ሺዎች ነፍሳቸውን ለማዳን እውነተኛ ፍላጎት ተሰምቶአቸዋል። ዛሬም በእንግሊዝ ባለፈው መቶ ዓመት ከነበረው የሚበልጥ ሃይማኖታዊ ቅንዓት እንዳለ አምናለሁ።

4. ነገር ግን ይህ ቅንዓት ትክክለኛ ዓይነት ነውን ወይስ የተሳሳተ? ምናልባት ሁለቱም ነው። ከኋለኛው እንድንርቅ ከቀደመውም ጋር እንድንጣበቅ እነዚህን መለየት እንደምንችል እንይ። ለዚህም በመጀመሪያ እንዲህ ብዬ እጠይቃለሁ፦

I. የእውነተኛ ክርስቲያናዊ ቅንዓት ባሕርይ ምንድር ነው?

II. ጠባዮቹስ ምንድር ናቸው? እናም፦

III. አንዳንድ ተግባራዊ ትምህርቶችን አወጣለሁ።

I. እንግዲህ በመጀመሪያ፥ የቅንዓት ባሕርይ በአጠቃላይ፥ በተለይም የእውነተኛ ክርስቲያናዊ ቅንዓት ባሕርይ ምንድር ነው?

1. የመጀመሪያው ቃል በቀዳሚ ትርጕሙ ሙቀት ማለት ነው፤ እንደ ፈላ ውኃ ሙቀት ያለ። በምሳሌያዊ አነጋገር ለአእምሮ ሲሠራበት ማንኛውንም የሞቀ ስሜት ወይም ፍቅር ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ለምቀኝነት ይነገራል። በየሐዋርያት ሥራ 5:17 እንዲሁ ተርጕመነዋል፤ በዚያም «ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ምቀኝነት ሞላባቸው» እናነባለን፤ —ἐπλήσθησαν ζήλου፤ ምንም እንኳ ቅንዓት ሞላባቸው ተብሎ ሊተረጎም ቢችልም። አንዳንድ ጊዜ ለቍጣና ለብስጭት፥ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለብርቱ ምኞት ይነገራል። ከስሜቶቻችንም አንዱ በሃይማኖታዊ ምክንያት ለማንኛውም መልካም ነገር ወይም ክፉ ነው ብለን በምናስበው በማንኛውም ነገር ላይ በብርቱ ሲነሣሣ፥ ይህን ሃይማኖታዊ ቅንዓት እንለዋለን።

2. ነገር ግን ሃይማኖታዊ ቅንዓት የሚባለው ሁሉ ለዚያ ስም የሚገባ አይደለም። ከቸርነት ጋር ካልተጣመረ በትክክል ሃይማኖታዊ ወይም ክርስቲያናዊ ቅንዓት አይደለም። አንድ ድንቅ ጸሐፊ (ጳጳስ ስፕራት) ነገሩን ከዚህም አልፈው ያስኬዱታል። ያ ታላቅ ሰው እንዲህ ይላሉ፦ «ቸርነት ያልሆነ ቅንዓት ትክክል አይደለም ተብሎ ተነግሮአል፤ ነገር ግን በአብዛኛው ቸርነት ነው። ቸርነት ወይም ፍቅር በውሕዱ ውስጥ አንድ ንጥረ ነገር ብቻ ሳይሆን ዋናው ንጥረ ነገር ነው።» ከዚህም የበለጠ መሄድ አንችልምን? እውነተኛ ቅንዓት በአብዛኛው ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ቸርነት ነው ማለት አንችልምን? ይህም ቸርነትን በቅዱስ ጳውሎስ ትርጕም ፍቅር ብለን ብንወስደው ነው፤ ማለትም የእግዚአብሔርንና የባልንጀራችንን ፍቅር። ክርስቲያናዊ ቅንዓት ሁለመናው ፍቅር እንደ ሆነ እርግጠኛ እውነት ነውና (በዓለም ጥቂት ቢታወቅም)። ከዚህ ሌላ ምንም አይደለም። የእግዚአብሔርና የሰው ፍቅር ባሕርዩን ሁሉ ይሞላዋል።

3. ይሁን እንጂ ይህ ስም የሚሰጠው ለየትኛውም የዚያ ፍቅር መጠን አይደለም። ቅንዓት በሌለበት ስፍራ አንዳች ፍቅር፥ ትንሽ መጠን ያለው ፍቅር ሊኖር ይችላል። ቅንዓት ግን በትክክል ሲነገር ከፍ ያለ መጠን ያለው ፍቅር ነው። የሚነድ ፍቅር ነው። እውነተኛ ክርስቲያናዊ ቅንዓት የፍቅር ነበልባል እንጂ ሌላ አይደለም። ባሕርዩ፥ ውስጣዊ ማንነቱም ይህ ነው።

II. 1. ከዚህም የፍቅር ጠባዮች የቅንዓትም ጠባዮች እንደ ሆኑ ይከተላል። ከፍቅር ዋና ዋና ጠባዮች አንዱ ትሕትና ነው፤ «ፍቅር … አይታበይም»። በዚሁ መሠረት ይህ የእውነተኛ ቅንዓት ጠባይ ነው፤ ትሕትና ከእርሱ አይለይም። የቅንዓት መጠን እንደ ሆነ የትሕትናም መጠን እንዲሁ ነው፤ አብረው ይነሣሉ፥ አብረውም ይወድቃሉ። ሰውን ለእግዚአብሔር በቅንዓት የሚሞላው ያው ፍቅር በገዛ ዓይኖቹ ታናሽ፥ ድሀና የተናቀ ያደርገዋል።

2. ሌላው የፍቅር ጠባይ የዋህነት ነው፤ ስለዚህም ከቅንዓት ጠባዮች አንዱ ነው። ትሑታን ብቻ ሳይሆን የዋሆችም እንድንሆን፥ ከቍጣም ሆነ ከትዕቢት በእኩል ከፍ እንድንል ያስተምረናል። ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ በዚህ ቅዱስ ነበልባል ፊት የሚያውኩ ስሜቶች ሁሉ ቀልጠው ይጠፋሉ፤ ነፍስንም ያልተረበሸችና ጸጥ ያለች አድርገው ይተዋታል።

3. ደግሞም ሌላው የፍቅር፥ ስለዚህም የቅንዓት ጠባይ የማይደክም ትዕግሥት ነው፤ «ፍቅር … በሁሉ ይጸናል»ና። ነፍስን ለመለኮታዊ መግቦት ውሳኔዎች ሁሉ በሙሉ በመገዛት ያስታጥቃታል፤ በሚደርስብንም ነገር ሁሉ «እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ በፊቱ መልካም የመሰለውን ያድርግ» እንድንል ያስተምረናል። በማንኛውም ሁኔታ የምንኖርበት ኑሮ እንዲበቃን፥ በምንም ነገር እንዳንማረር፥ በምንም ነገር እንዳናጕረመርም፥ ይልቁንም «በነገር ሁሉ» እንድናመሰግን ያስችለናል።

4. በተለይ ሊታሰብበት የሚገባው አራተኛ የክርስቲያናዊ ቅንዓት ጠባይ አለ። ይህንም ከሐዋርያው ቃላት እንማራለን፦ «ሁልጊዜ መቅናት መልካም ነው» (የቅንዓት ጊዜያዊ ንክኪ ማግኘት ሳይሆን የጸና ሥር የሰደደ ዝንባሌ መያዝ) «ለመልካም ነገር»፤ መልካም ለሆነው ነገር፤ የቅንዓት ትክክለኛ ዒላማ በአጠቃላይ መልካም የሆነው ነው፤ ማለትም በእግዚአብሔር ፊት በእውነት መልካም የሆነው ነገር ሁሉ።

5. ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነው ምንድር ነው? እግዚአብሔር ሁልጊዜ ደስ የሚሰኝበት ያ ሃይማኖት ምንድር ነው? ክፍሎቹ እንዴት አንዱ ከሌላው በላይ ከፍ ይላሉ? የእያንዳንዳቸውስ አንጻራዊ ዋጋ ምንድር ነው?

ይህ እጅግ ጥቂት የታሰበበት፥ ስለዚህም ጥቂት የተረዳ ነጥብ ነው። ብዙዎች ስለ አዎንታዊ መለኮታዊ ትምህርት አንዳች እውቀት አላቸው። ስለ አንጻራዊ መለኮታዊ ትምህርት ግን አንዳች የሚያውቁ ጥቂቶች ናቸው። በዚህ ርዕስ ላይ ከአንድ ጽሑፍ በቀር ያየሁት የለም፤ የእርሱንም አጭር ንድፍ ማከል ይጠቅም ይሆናል።

በክርስቲያን አማኝ ዘንድ ፍቅር በነፍስ ውስጠኛ ክፍል በተተከለው ዙፋን ላይ ተቀምጦአል፤ ማለትም ልብን ሁሉ የሚሞላና ያለ ተቀናቃኝ የሚነግሥ የእግዚአብሔርና የሰው ፍቅር። ከዙፋኑ አጠገብ ባለው ክበብ ቅዱሳት ጠባያት ሁሉ አሉ፤ ቻይነት፣ ገርነት፣ የዋህነት፣ ታማኝነት፣ ራስን መግዛት፤ ደግሞም «በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ» በሚለው ውስጥ የተካተተ ሌላ ቢኖር። በውጨኛው ክበብ የሰዎችን ነፍሳት ወይም ሥጋ የሚመለከቱ የምሕረት ሥራዎች ሁሉ አሉ። በእነዚህ ቅዱሳት ጠባያትን ሁሉ እንለማመዳለን፤ በእነዚህ ያለማቋረጥ እናሳድጋቸዋለን፤ ስለዚህም ይህ በብዛት ባይታሰብበትም እነዚህ ሁሉ እውነተኛ የጸጋ መንገዶች ናቸው። ከእነዚህ ቀጥሎ በተለምዶ የአምልኮ ሥራዎች የሚባሉት አሉ፤ ቃሉን ማንበብና መስማት፥ የሕዝብ፣ የቤተሰብና የግል ጸሎት፥ የጌታን እራት መቀበል፥ ጾም ወይም መከልከል። በመጨረሻም ተከታዮቹ እርስ በርሳቸው ለፍቅር፥ ለቅዱሳት ጠባያትና ለመልካም ሥራ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲነቃቁ፥ የተባረከው ጌታችን በምድር ሁሉ በተበተነ በአንድ አካል፥ በቤተ ክርስቲያን አንድ አድርጎአቸዋል፤ የዚችም የዓለም አቀፍዋ ቤተ ክርስቲያን ትንሽ ምሳሌ በእያንዳንዱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አለን።

6. በበዓለ ኀምሳ ቀን መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ጊዜ ጀምሮ ጌታችን በምድር ላይ የመሠረተው ሃይማኖት ይህ ነው። ሙሉውና እርስ በርሱ የተያያዘው የክርስትና ሥርዓት ይህ ነው፤ ክፍሎቹም ከዝቅተኛው ነጥብ፥ በአንድነት ከመሰብሰባችን፥ እስከ ከፍተኛው፥ በልብ ውስጥ እስከ ነገሠው ፍቅር ድረስ አንዱ ከሌላው በላይ እንዲህ ከፍ ይላሉ። ከዚህም የእያንዳንዱን የሃይማኖት ቅርንጫፍ አንጻራዊ ዋጋ መማር ቀላል ነው። ከዚህም ደግሞ አምስተኛውን የእውነተኛ ቅንዓት ጠባይ እንማራለን። ይኸውም ሁልጊዜ ἐν καλῷ፥ መልካም በሆነው ነገር እንደሚሠራ፥ እንዲሁ ሁልጊዜ ለዚያ መልካም ነገር፥ በዒላማው ውስጥ ላለው የመልካምነት መጠን ተመጣጣኝ መሆኑ ነው።

7. ለምሳሌ፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን ያለ ጥርጥር ለቤተ ክርስቲያን ቀናተኛ ሊሆን፥ ብርቱ ፍቅር ሊኖረው፥ ብልጽግናዋንና መስፋፋቷንም በትጋት ሊመኝ ይገባዋል። ስለ ዓለም አቀፍዋ ቤተ ክርስቲያን ያለማቋረጥ በመጸለይ ለእርሷ እንዲህ ቀናተኛ ሊሆን ይገባዋል፤ በተለይም እርሱ ራሱ አባል ለሆነባት ለዚያች ለተለየች ቤተ ክርስቲያን ወይም የክርስቲያን ማኅበር። ስለዚህች በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር ሊታገል ይገባዋል፤ በዚያው ጊዜም ድንበሯን ለማስፋትና ወንድሞቹ የመድኃኒታችንን የእግዚአብሔርን ትምህርት ያስጌጡ ዘንድ እነርሱን ለማበርታት በአቅሙ ያለውን መንገድ ሁሉ ይጠቀም።

8. ነገር ግን ከቤተ ክርስቲያን ራሷ ይልቅ ለክርስቶስ ሥርዓቶች ይበልጥ ቀናተኛ ሊሆን ይገባዋል፤ ለሕዝብና ለግል ጸሎት፥ ለጌታ እራት፥ ቃሉን ለማንበብ፣ ለመስማትና ለማሰላሰል፥ እጅግም ቸል ለተባለው የጾም ተግባር። እነዚህን አስቀድሞ በምሳሌነቱ፥ ከዚያም አጋጣሚ በተገኘ ቍጥር በምክር፣ በማስረጃ፣ በማሳመንና በማሳሰቢያ በትጋት ሊያስተዋውቃቸው ይገባዋል።

9. ለአምልኮ ሥራዎች ቅንዓቱን እንዲህ ሊያሳይ ይገባዋል፤ ለምሕረት ሥራዎች ግን ከዚህ እጅግ ይበልጥ፤ እግዚአብሔር «ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም» ብሎአልና፤ ይህም ከመሥዋዕት ይልቅ ማለት ነው። ስለዚህ አንዱ ከሌላው ጋር በተጋጨ ቍጥር የምሕረት ሥራዎች ሊመረጡ ይገባቸዋል። የባልንጀራችንን ሥጋዊ ወይም ነፍሳዊ ጭንቀት እንድናቃልል በተጠራን ጊዜ፥ «ሁሉን ቻዩ የፍቅር ጥሪ ሲመጣ» ማንበብ፥ መስማትና ጸሎት እንኳ ሊቀሩ ወይም ሊዘገዩ ይገባቸዋል።

10. ነገር ግን ለመልካም ሥራዎች ሁሉ የቱንም ያህል ቀናተኞች ብንሆን፥ ለቅዱሳት ጠባያት ከዚያ ይበልጥ ቀናተኞች ልንሆን ይገባናል፤ በራሳችን ነፍስም ሆነ ግንኙነት ባለን ሰዎች ሁሉ ዘንድ የአእምሮ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ገርነትን፣ ቻይነትን፣ ባለን መርካትን፣ ለእግዚአብሔር ፈቃድ መገዛትን፣ ለዓለምና ለዓለም ነገሮች መሞትን ለመትከልና ለማሳደግ፤ ይህ ለእግዚአብሔር በእውነት ሕያው የምንሆንበት ብቸኛው መንገድ ነውና። ለእነዚህ የሕያው እምነት ማስረጃዎችና ፍሬዎች ከልክ በላይ ልንቀና አንችልም። እነርሱን «በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም» ልንናገራቸው ይገባናል። ከማንኛውም ውጫዊ ሥራ እጅግ የሚበልጡ በመሆናቸው ዘወትር የጸሎት ጉዳይ ልናደርጋቸው ይገባናል፤ እነዚያ ሥጋ ሲወድቅ ያልፋሉና፥ እነዚህ ግን ወደ ዘላለም አብረውን ይሄዳሉ።

11. ነገር ግን እጅግ የተመረጠው ቅንዓታችን ለፍቅር ራሱ ሊጠበቅ ይገባዋል፤ ለትእዛዝ ፍጻሜ፥ ለሕግ ፍጻሜ። ቤተ ክርስቲያን፥ ሥርዓቶች፥ ማንኛውም ዓይነት ውጫዊ ሥራ፥ አዎን፥ ሌሎቹ ቅዱሳት ጠባያት ሁሉ ከዚህ ያንሳሉ፤ ዋጋቸውም ከፍ የሚለው ይበልጥ ወደ እርሱ በቀረቡ መጠን ብቻ ነው። እንግዲህ የክርስቲያናዊ ቅንዓት ታላቁ ዒላማ ይህ ነው። በክርስቶስ የሚያምን እውነተኛ አማኝ ሁሉ ልቡ ለእግዚአብሔርና ለሰው ልጆች ሁሉ ባለው ፍቅር ይበልጥ እየሰፋ እንዲሄድ በመንፈስ በሙሉ ትጋት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይቅረብ። ይህን አንድ ነገር ያድርግ፤ «በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ» ያገኝ ዘንድ ወደ ምልክቱ ይፍጠን።

III. ከላይ ከተመለከትናቸው ነገሮች አንዳንድ ተግባራዊ ትምህርቶችን ማውጣት ብቻ ይቀራል።

1. እንግዲህ በመጀመሪያ፥ ቅንዓት፥ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ቅንዓት ከፍቅር ነበልባል በቀር ሌላ ካልሆነ፥ በማንኛውም ዓይነትና መጠን ያለ ጥላቻ፥ በሚቃወሙንም ላይ ያለ ማንኛውም ዓይነት መራርነት የቅንዓትን ስም ለመቀበል የሚገባ ከመሆን እጅግ የራቀ ነው፤ እንዲያውም ቀጥተኛ ተቃራኒው ነው። ቅንዓት የሚነድ ፍቅር ብቻ ከሆነ፥ «ፍቅር … በደልን አይቆጥርም»ና ከጭፍን ጥላቻ፥ ከቅናትና ከክፉ ጥርጣሬ እጅግ የራቀ ነው። እንግዲያስ ማንኛውም ዓይነት ጭፍን ወገንተኝነት፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ የማሳደድ መንፈስ ከእርሱ ጋር ፈጽሞ አይስማሙም። ስለዚህ ከእነዚህ ያልተቀደሱ ጠባያት አንዳቸውም በዚያ ቅዱስ ስም ሥር አይሸሸጉ። እነዚህ ሁሉ የዲያብሎስ ሥራዎች እንደ መሆናቸው በራሳቸው መልክ ይታዩ፤ ከእንግዲህም በዚያ አሳሳች ጭንብል ሥር ሆነው ጥንቃቄ የጐደላቸውን የእግዚአብሔር ልጆች አያታልሉ።

2. ሁለተኛ፥ ትሕትና የቅንዓት ጠባይ ከሆነ ትዕቢት ከእርሱ ጋር አይስማማም። የእግዚአብሔር ፍቅር በልብ ውስጥ ከፈሰሰ በኋላ አንዳች መጠን ያለው ትዕቢት ሊቀር እንደሚችል እውነት ነው፤ እግዚአብሔር ሁሉን አዲስ በሚያደርግበት ጊዜ ተነቅሎ ከሚወጡት የመጨረሻዎቹ ክፋቶች አንዱ ነውና፤ ነገር ግን የሚነድ ፍቅር በሚገኝበት ስፍራ ሊነግሥ ወይም ጕልህ ኃይል ይዞ ሊቆይ አይችልም። አዎን፥ ጥቂት እንኳ ብንፈቅድለት ያንን ቅዱስ ትጋት ያቀዘቅዘዋል፤ ወዲያውም ወደ ክርስቶስ ተመልሰን ባንሸሽ፥ መንፈስን ፈጽሞ ያጠፋዋል።

3. ሦስተኛ፥ የዋህነት ከቅንዓት የማይለይ ጠባይ ከሆነ ቍጣቸውን በዚያ ስም ስለሚጠሩት ሰዎች ምን እንላለን? እንግዲህ እውነትን ፈጽመው እንደሚስቱ፥ በሙሉ ትርጕሙም ጨለማውን ብርሃን፥ ብርሃኑንም ጨለማ እንደሚያደርጉ ነው። ከዚህ ማታለል ከልክ በላይ ልንጠነቀቅ አንችልም፤ በክርስቲያን ዓለም ሁሉ ላይ ተዘርግቶአልና። በሁሉም ስፍራ ማለት ይቻላል ቅንዓትና ቍጣ እንደ ተመሳሳይ ቃላት ይቈጠራሉ፤ በመካከላቸውም አንዳች ልዩነት እንዳለ ያመኑ ሰዎች እጅግ ጥቂቶች ናቸው። «ይህ ሰው ምን ያህል ቀናተኛ እንደ ሆነ እዩ!» ሲባል ምን ያህል ጊዜ እንሰማለን! የለም፥ ቀናተኛ ሊሆን አይችልም፤ ይህ የማይቻል ነው፤ በቍጣ ተይዞአልና፤ ቍጣም ብርሃን ከጨለማ፥ ሰማይም ከገሃነም ጋር እንደማይስማማ እንዲሁ ከቅንዓት ጋር አይስማማም!

ይህ ነጥብ በሚገባ ቢታወቅ መልካም ነበር። ጥቂት ይበልጥ እንመልከተው። የሃይማኖተኛ ሰው ስም ያለውን አንድ ሰው በባልንጀራው ላይ በብርቱ ሲቈጣ ብዙ ጊዜ እናያለን። ምናልባት ወንድሙን ራቃ፥ ወይም ደንቆሮ ይለው ይሆናል። የስድብ ክስ ያመጣበታል። ስለ ብስጭቱ በለዘብታ ትገሥጸዋላችሁ። እርሱም «ቅንዓቴ ነው!» ብሎ ይመልሳል። አይደለም፤ ኃጢአትህ ነው፤ ንስሐም ካልገባህበት ከመቃብር በታች ያሰጥምሃል። እንዲህ ያለ ቅንዓት በጥልቁ ጕድጓድ ውስጥ ብዙ አለ። የዚህ ዓይነት ቅንዓት ሁሉ የሚመጣው ከዚያ ነው፤ ወደዚያም ይሄዳል፤ ከዚህ ዓለም ከመሄድህ በፊት ከእርሱ ካልዳንህ አንተም ከእርሱ ጋር ትሄዳለህ!

4. አራተኛ፥ ትዕግሥት፥ ባለው መርካትና መገዛት የቅንዓት ጠባዮች ከሆኑ ማጕረምረም፥ መነጫነጭ፥ አለመርካትና ትዕግሥት ማጣት ከእርሱ ጋር ፈጽሞ አይስማሙም። ይሁን እንጂ የሰው ልጆች ይህን ምን ያህል አያውቁም! ሰዎች በኃጢአተኞች ላይ ሲበሳጩ፥ ወይም በዚህ ወይም በዚያ ነገር ትዕግሥታቸው እንዳለቀ ሲነግሯችሁ፥ ይህንንም ሁሉ ቅንዓታቸው ብለው ሲጠሩት ምን ያህል ጊዜ እናያለን! ኦ፥ ከስሕተታቸው ለመመለስ ምንም ድካም አትቈጥቡ! ቢቻላችሁ ቅንዓት ምን እንደ ሆነ አሳዩአቸው፤ በኃጢአት ላይ ማጕረምረም ወይም መበሳጨት ሁሉ የኃጢአት ዓይነት እንደ ሆነና ከእውነተኛው የወንጌል ቅንዓት ጋር አንዳች መመሳሰል ወይም ግንኙነት እንደሌለው አሳምኑአቸው።

5. አምስተኛ፥ የቅንዓት ዒላማ መልካም የሆነው ነገር ከሆነ ለማንኛውም ክፉ ነገር መትጋት ክርስቲያናዊ ቅንዓት አይደለም። ለምሳሌ ጣዖት አምልኮን፥ መላእክትን፥ ቅዱሳንን፥ ምስሎችንና መስቀልን ማምለክን እጠቅሳለሁ። ስለዚህ አንድ ሰው ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ከመከልከል ይልቅ «ሥጋውን ለእሳት መቃጠል አሳልፎ» እስኪሰጥ ድረስ በዚያ ላይ በብርቱ ቢጣበቅ፥ ብትፈልጉ ይህን ጭፍን ወገንተኝነት ወይም አጉል እምነት ብላችሁ ጥሩት፤ ቅንዓት ግን አትበሉት፤ ያ ፈጽሞ ሌላ ነገር ነው።

ከዚያው መነሻ ደግሞ ለግድ የለሽ ነገሮች መትጋት ክርስቲያናዊ ቅንዓት እንዳልሆነ ይከተላል። ነገር ግን ይህም ስሕተት እንዴት እጅግ የተለመደ ነው! በእርግጥ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች እንዲህ ላለ ድካም የተጋለጡ ሊሆኑ አይችሉም ብሎ ሰው ያስብ ይሆናል። ነገር ግን ወዮ! የዘመናት ሁሉ ታሪክ ተቃራኒውን ያረጋግጣል። ከጳጳስ ሪድሊና ከጳጳስ ሁፐር የበለጠ ብርቱ ማስተዋል የነበራቸው ሰዎች እነማን ነበሩ? እነዚህና ሌሎችም የዚያ ዘመን ታላላቅ ሰዎች ስለ ክህነት አልባሳት ምን ያህል በብርቱ ተከራከሩ! ቀሚሰ ተክህኖን ስለ መልበስና ስላለመልበስ ለመቶ ዓመት ያህል የተደረገው ፍጥጫ ምን ያህል ብርቱ ነበር! ኦ፥ ለሰው እፍረት ነው! ስለ ገለባ ወይም ስለ ገብስ ቅንጣት ብከራከር ይሻለኝ ነበር። ይህም በእርግጥ ቅንዓት ተብሎ ይጠራል! ታዲያ ይልቁንስ ጥበብ ወይም ቅድስና ለምን አልተባለም?

6. ከዚያው መነሻ ደግሞ ለአስተያየቶች መትጋት ክርስቲያናዊ ቅንዓት እንዳልሆነ ይከተላል። ነገር ግን ይህን የሚገነዘቡ ምን ያህል ጥቂቶች ናቸው! ይህ የሐሰተኛ ቅንዓት ዓይነት እንኳ በክርስቲያን ዓለም ውስጥ ያስከተላቸው ጥፋቶች ምን ያህል ስፍር ቍጥር የሌላቸው ናቸው! ለሮማ ካቶሊክ አስተያየቶች በቀኑ ሰዎች ስንት ሺህ ሕይወት ተጣለ! ስለ ኅብስቱና ወይኑ ወደ ሥጋና ደም መለወጥ ስለሚለው ትርጕም የለሽ አስተያየት በቀናተኞች እጅ ከምድር ምርጦች ስንቶቹ ተቈረጡ! ነገር ግን ይህ ቅንዓት «የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው»፥ ሐዋርያው በዚህ ስፍራ ከሚመክረው ቅንዓትም ጋር እጅግ ተቃራኒ እንደ ሆነ ጭፍን ጥላቻ የሌለው ሰው ሁሉ አያይምን?

እንግዲያስ ታላቁ ገጣሚያችን «በመጨረሻው ቀን ላይ የተጻፈ ግጥም» በተባለው ሥራው በሰማይ ስለ መገናኘት ሲናገር የገለጸው ፍቅር ምንኛ ከልክ ያለፈ ነው፦

እርስ በርሳቸው በተወጋጉት ቍስል የሞቱትን፥

ለየራሳቸው እምነት በነደደ ቅንዓት የተቃጠሉትን! በእርግጥ ቅንዓት! እርስ በርሳቸው አንገት እንዲቈራረጡ የመራቸው ይህ ምን ዓይነት ቅንዓት ነበር? በዚህ መንፈስ የተቃጠሉና በእርሱም የሞቱ ያለ ጥርጥር ዕድል ፈንታቸው በሰማይ ሳይሆን (በዚያ ፍቅር ብቻ አለና) «በማይጠፋ እሳት» ውስጥ ይሆናል።

7. በመጨረሻ፥ እውነተኛ ቅንዓት ሁልጊዜ በዒላማው ውስጥ ላለው የመልካምነት መጠን ተመጣጣኝ ከሆነ፥ ከላይ በተጠቀሰው መሰላል መሠረት፥ በልዩ ልዩ የሃይማኖት ክፍሎች አንጻራዊ ዋጋ መሠረት፥ ይበልጥ እየጨመረ ከፍ ሊል ይገባዋል። ለምሳሌ፥ እግዚአብሔርን በእውነት የሚፈሩ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን ቀናተኞች ሊሆኑ ይገባቸዋል፤ ለሁሉን አቀፍዋ ወይም ለዓለም አቀፍዋ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ አባላት ለሆኑባት ለዚያች ክፍሏ። ይህ የሰው ሳይሆን የእግዚአብሔር ሥርዓት ነው። በዚህም ትርጕም እንኳ «ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም» ብሎ አየ፤ ይልቁንም የልጆቹ አካል ሁሉ «በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ» እንዲጸና ነው። በዚያው ጊዜ ለእግዚአብሔር ሥርዓቶች ይበልጥ ቀናተኞች ሊሆኑ ይገባቸዋል፤ ለሕዝብና ለግል ጸሎት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማትና ለማንበብ፥ ለጾምና ለጌታ እራት። ነገር ግን ለአምልኮ ሥራዎች እንኳ ከሚኖራቸው ይልቅ ለምሕረት ሥራዎች ይበልጥ ቀናተኞች ሊሆኑ ይገባቸዋል። ደግሞም ለቅዱሳት ጠባያት ሁሉ፥ ለትሕትና፣ ለየዋህነትና ለመገዛት ከዚያም ይበልጥ ቀናተኞች ሊሆኑ ይገባቸዋል፤ ከሁሉ በላይ ግን የሃይማኖት ድምርና ፍጽምና ለሆነው ለእግዚአብሔርና ለሰው ፍቅር እጅግ ቀናተኞች ይሁኑ።

8. እነዚህን ነገሮች በራሳችን ነፍስ ላይ በቅርበትና በቅንነት መተግበር ብቻ ይቀራል። «ሁልጊዜ ለመልካም ነገር መቅናት መልካም ነው» የሚለውን አጠቃላይ እውነት ሁላችን እናውቃለን። አሁንም እያንዳንዳችን በተለይ በገዛ ነፍሳችን ላይ እንተግብረው።

9. በእርግጥ አሁንም በበደልና በኃጢአት ሙታን የሆኑ በዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የላቸውም፤ እንደ ስካር፥ ሰንበትን መሻር ወይም ርኩስ መሐላ ባለ በማንኛውም ግልጽ ኃጢአት የሚኖሩትም እንዲሁ። እነዚህ ከቅንዓት ጋር አንዳች ግንኙነት የላቸውም፤ ቃሉን በአፋቸው ለማንሣት እንኳ ምንም ጉዳይ የላቸውም። ማንም የዲያብሎስን ሥራ እየሠራ ስለ እግዚአብሔር ቅንዓት መናገሩ ፍጹም ስንፍናና ድፍረት ነው። ነገር ግን ዲያብሎስንና ሥራዎቹን ሁሉ ክዳችሁ፥ በልባችሁም «ለጌታ ለአምላኬ እሰግዳለሁ፥ እርሱንም ብቻ አመልካለሁ» ብላችሁ ከቈረጣችሁ፥ እንግዲያስ በራድም ትኩስም እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ፤ እንግዲያስ ለእግዚአብሔር ቅኑ። ከዝቅተኛው ደረጃ ልትጀምሩ ትችላላችሁ። ለቤተ ክርስቲያን ቅኑ፤ ይልቁንም ዕጣችሁ ለወደቀባት ለዚያች ለተለየች ቅርንጫፏ። ደኅንነቷን አጥኑ፤ ስለ ሕሊናም ሥርዓቶቿን ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቁ። ነገር ግን በዚያው ጊዜ ከእግዚአብሔር ሥርዓቶች አንዱንም ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ ቤተ ክርስቲያን ራሷ በአብዛኛው የተመሠረተችው ለእነርሱ ሲባል ነውና፤ ስለዚህም ለእነርሱ ይበልጥ ቀናተኞች ሳትሆኑ ስለ ቤተ ክርስቲያን ቅንዓት መናገር እጅግ የማይመስል ነገር ነው። ነገር ግን ለአምልኮ ሥራዎች እንኳ ከምትቀኑት ይልቅ ለምሕረት ሥራዎች ይበልጥ ትቀናላችሁን? እናንተ የጌታችሁን ምሳሌ ትከተላላችሁን? ምሕረትንም ከመሥዋዕት እንኳ ታስቀድማላችሁን? የተራቡትን በማብላት፥ የተራቈቱትን በማልበስ፥ የታመሙትንና በወኅኒ ያሉትን በመጠየቅ ትጋትን ሁሉ ታደርጋላችሁን? ከሁሉም በላይ ደግሞ ነፍሳትን ከሞት ለማዳን በአቅማችሁ ያለውን መንገድ ሁሉ ትጠቀማላችሁን? ጊዜ ባገኛችሁ መጠን «ለሰው ሁሉ» መልካም ብታደርጉ፥ «ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች»፥ ለቤተ ክርስቲያን ያላችሁ ቅንዓት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛል፤ ካልሆነ ግን፥ «በመልካም ሥራ በጥንቃቄ» ካልጸናችሁ፥ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ምን ጉዳይ አላችሁ? «ባልንጀሮቻችሁ የሆኑትን ባሪያዎች» ካልማራችሁ፥ ጌታችሁም እናንተን አይምራችሁም። «ከንቱ መባ ደግሞ አታምጡ።» አገልግሎታችሁ ሁሉ «በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው።»

10. እግዚአብሔር ያጣመረውን ላለመለየት፥ የአምልኮ ሥራዎችን ከምሕረት ሥራዎች ላለመነጠል የተሻለ ትምህርት አግኝታችኋልን? ለሁለቱም በእኩል ትቀናላችሁን? እንግዲያስ እስከዚያ ድረስ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ባለው ሁኔታ ትመላለሳላችሁ፤ ይህም እግዚአብሔር «ልብንና ኵላሊትን የሚመረምር» እንደ ሆነ፥ «እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል» የሚለውን፥ ስለዚህም ማንም ሰው ያለ እነርሱ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ስፍራ ሊኖረው ከማይችልባቸው ከቅዱሳት ጠባያት ካልመነጩ በቀር ማንኛውም ውጫዊ ሥራ በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ዘወትር ብታስቡ ነው።

11. ነገር ግን ከቅዱሳት ጠባያት ሁሉ፥ ከሌሎቹም ሁሉ በላይ ለፍቅር እጅግ ቀናተኞች እንድትሆኑ ተጠንቀቁ። ከዚህ ጋር ሲነጻጸር ሁሉን እንደ ጉዳት ቍጠሩ፤ የእግዚአብሔርንና የሰው ልጆችን ሁሉ ፍቅር። ድሆችን ለመመገብ ያላችሁን ሁሉ ብታካፍሉ፥ አዎን፥ ሥጋችሁንም ለእሳት መቃጠል አሳልፋችሁ ብትሰጡ፥ ትሑት፥ ገርና ታጋሽ ፍቅር ግን ከሌላችሁ ምንም እንደማይጠቅማችሁ እጅግ እርግጥ ነው። ኦ፥ ይህ በልባችሁ ላይ በጥልቅ ይቀረጽ፦ «ያለ ፍቅር ሁሉም ከንቱ ነው!»

12. እንግዲያስ እግዚአብሔር በቃሉ እንደ ገለጠው ሃይማኖትን በሙሉ አንድ ላይ ውሰዱ፤ ለእያንዳንዱም ክፍሉ እንደ መልካምነቱ መጠን በእኩል ቀናተኞች ሁኑ። ቅንዓታችሁን ሁሉ በአንዱ መሠረት ላይ፥ «በኢየሱስ ክርስቶስ እርሱም እንደተሰቀለ» በሚለው ላይ መሥርቱ፤ «አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው» የሚለውን አንድ መርሕ አጥብቃችሁ ያዙ፤ ቅንዓታችሁንም ለዒላማው ዋጋ ተመጣጣኝ አድርጉ። ስለዚህ በመጀመሪያ ለቤተ ክርስቲያን በእርጋታ ቅኑ፤ «በምድር ላይ የምትጋደለው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ሁኔታ»፤ በተለይም ይበልጥ በቀጥታ ለተያያዛችሁባት ለዚያች ቅርንጫፏ። የተባረከው ጌታችን እስከ ዓለም ፍጻሜ በእርሷ ውስጥ እንዲኖሩ ለሠራቸው ለእነዚያ ሥርዓቶች ሁሉ ይበልጥ ቅኑ። ለእነዚያ የምሕረት ሥራዎች፥ ለእነዚያ «እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኙ መሥዋዕቶች»፥ የእስራኤል እረኛ በመጨረሻው ቀን በጎቹን ለሚያውቅባቸው ለእነዚያ ምልክቶች ይበልጥ ቅኑ። ለቅዱሳት ጠባያት፥ ለቻይነት፣ ለገርነት፣ ለየዋህነት፣ ለትሕትናና ለመገዛት ከዚያም ይበልጥ ቅኑ፤ ከሁሉ በላይ ግን የጸጋዎች ሁሉ ንግሥት ለሆነው፥ በምድርም ሆነ በሰማይ ከፍተኛ ፍጽምና ለሆነው፥ በታች ባሉ ሰዎችም በላይ ባሉ መላእክትም ዘንድ የማይታየው አምላክ ትክክለኛ ምስል ለሆነው ለፍቅር እጅግ ቅኑ። «እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል»ና።

ቀዳሚ ቀጣይ