ምዕራፍ 76 · 14 ደቂቃ ንባብ · 18 ደቂቃ ማዳመጥ
ስለ መለያየት
ስብከት 75
ስለ መለያየት
«በአካል መለያየት እንዳይሆን።»
1ኛ ቆሮንቶስ 12:25።
1. በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትርጉሙ እንደ «ቤተ ክርስቲያን» ቃል አሻሚና ያልተወሰነ የሆነ ቃል ቢኖር፣ እርሱ ከእርሱ ጋር እጅግ የተቀራረበው ቃል — «መለያየት» የሚለው ቃል ነው። ይህ ቃል ለብዙ መቶ ዓመታት ቍጥር ለሌላቸው ክርክሮች ምክንያት ሆኖአል፤ በክርስቲያኑ ዓለም በየትኛውም ክፍል ስለ እርሱ ቍጥር የሌላቸው የሚያሰኙ መጻሕፍት ተጽፈዋል። ከእነዚህም እጅግ ብዙው ክፍል በአገራችን ታትሞአል፤ በተለይም ባለፈው መቶ ዓመትና በአሁኑ መቶ ዓመት መጀመሪያ። እጅግ ብርቱ ማስተዋል ያላቸውና ፍጹም የተማሩ ሰዎችም በንግግርም በጽሑፍም ኃይላቸውን ሁሉ በዚህ ጥያቄ ላይ ጨርሰዋል። የተሐድሶ ቤተ ክርስቲያን ከሮማ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መገንጠል ከተገነጠለች ወዲህ ይህ ከምንጊዜውም ይልቅ አስፈላጊ መስሎ ታይቶአል። የዚያች ቤተ ክርስቲያን አባሎች ከእርሷ በሚገነጠሉት ሁሉ ላይ ይህን ክስ ከማቅረብ ፈጽሞ አይቦዝኑም፤ ስለዚህም ይህ ክስ በሁለቱም ወገን ያሉትን እጅግ ብቁ ተከራካሪዎች አሳብና ብዕር ሲያሠራ ኖሮአል። የየወገኑ ሰዎችም ወደ ክርክሩ ሜዳ በገቡ ጊዜ ብዙውን ጊዜ ድሉ የእነርሱ እንደ ሆነ ተማምነው ነበር፤ የክርክራቸው ኃይል እጅግ ታላቅ በመሆኑ አስተዋዮች ሰዎች ሊቋቋሙት እንደማይችሉ አስበው ነበርና።
2. ነገር ግን በእነዚህ ሁሉ ክርክሮች እጅግ ጥቂት መልካም ነገር ብቻ እንደ ተደረገ ልብ ማለት ይቻላል። ከጋለ ስሜት ያላቸውና ብቁ ከሆኑት ተከራካሪዎች ተቃዋሚዎቻቸውን ለማሳመን የቻሉት እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ሊባል የሚቻለው ሁሉ ከተባለ በኋላ የጳጳሱ ተከታዮች አሁንም የጳጳሱ ተከታዮች፣ ፕሮቴስታንቶችም አሁንም ፕሮቴስታንቶች ናቸው። ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ስለ መገንጠል እጅግ አጥብቀው የተከራከሩትንም ያው ውጤት ገጥሞአቸዋል። ከእርሷ የተገነጠሉት በመለያየት በብርቱ ተከሰሱ፤ እነርሱም ክሱን በዚያው ብርታት ካዱ፤ በአንዱም ሆነ በሌላው ወገን ተቃዋሚዎቻቸውን ማሳመን የቻሉ ከቶ አልነበሩም ማለት ይቻላል።
3. ይህ ክርክር እንዲህ ፍሬ ቢስ የሆነበት፣ ከሁለቱም ወገን ያመኑት እጅግ ጥቂቶች የሆኑበት አንድ ታላቅ ምክንያት ይህ ነው፦ ስለሚከራከሩበት ቃል ትርጉም እምብዛም አይስማሙም ነበር፤ የዚህንም ትርጉም ካልወሰኑ፣ ስለ ቃሉ መከራከር ከመጀመራቸው በፊት ፍቺውን ካላስቀመጡ፣ አንድ እርምጃ እንኳ ወደ ፊት ሳይራመዱ፣ መጀመሪያ ከተነሡበት ጊዜ ይልቅ አንዳቸው ወደ ሌላው ቅንጣት ታህል ሳይቀርቡ ክርክሩን እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ሊቀጥሉ ይችላሉ።
4. ቢሆንም ይህ ጉዳይ ታላቅ ክብደት ያለው መሆን አለበት፤ አለዚያማ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እርሱ እንዲህ በቁም ነገር ባልተናገረ ነበር። ስለዚህ የሚከተሉትን ማሰብ እጅግ አስፈላጊ ነው፦
I. የመለያየትን ምንነት፣ እና ፣
II. የመለያየትን ክፋት።
I. 1. ይህን ማድረግ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው በዚህ ርዕስ ላይ በሮማ ካቶሊክ ተከታዮችም በፕሮቴስታንቶችም ከተጻፉት ስፍር ቍጥር ከሌላቸው መጻሕፍት መካከል መለያየትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መንገድ የሚፈታ አንድም ማግኘት አስቸጋሪ ስለ ሆነ ነው። የሮማ ካቶሊኮች ሁሉ መለያየትን «ከሮም ቤተ ክርስቲያን መገንጠል» ብለው ይፈቱታል፤ የእኛ ጸሐፊዎችም ሁሉ ማለት ይቻላል «ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን መገንጠል» ብለው ይፈቱታል። በዚህም ሁለቱም ገና ከመነሻቸው ተሳስተዋል፤ በመግቢያው ደጃፍ ላይ ተሰናክለዋል። «መለያየት» የሚለው ቃል የሚገኝባቸውን ልዩ ልዩ ጥቅሶች በእርጋታ ለሚመረምር ሰው ይህ በቀላሉ ይገለጥለታል፤ ከአጠቃላይ መንፈሳቸው መለያየት ከማናቸውም ቤተ ክርስቲያን (አጠቃላይም ሆነች የተወሰነች፣ ሁሉን አቀፊቱም ሆነች ማናቸውም ብሔራዊ ቤተ ክርስቲያን) መገንጠል ሳይሆን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጠር መለያየት መሆኑ ግልጥ ነውና።
2. ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ቃል ከተጠቀመበት ከመጀመሪያው ቁጥር እንጀምር። ይህም ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው በመጀመሪያው መልእክቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ ያለው አሥረኛው ቁጥር ነው። ቃሉም እንዲህ ይላል፦ «ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ» «መለያየት» (የመጀመሪያው ቃል σχίσματα ነው) «በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።» እዚህ የተነገረላቸው መለያየቶች ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መገንጠሎች ሳይሆኑ በውስጧ የተፈጠሩ መከፋፈሎች እንደ ነበሩ ከዚህ የበለጠ ግልጥ ሊሆን የሚችል ነገር አለን? በዚህም መሠረት ቀጥሎ «በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ» ይላል። በልብና በአሳብ አንድ መሆን የቆሮንቶስ መለያየት ቀጥተኛ ተቃራኒ እንደ ነበረ እዚህ ታያላችሁ። ስለዚህ ይህ መለያየት በቆሮንቶስ ካለችው ቤተ ክርስቲያን ወይም ክርስቲያናዊ ማኅበር መገንጠል አልነበረም፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተፈጠረ መለያየት ነበር፤ ይህም ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ እንደ ቀድሞው በውጭ ተባብረው በቀጠሉት ሰዎች መካከል የተፈጠረ የልብና የአሳብ (ምናልባትም የፍቅር) አለመስማማት ነው።
3. በቆሮንቶስ የነበረው ይህ መለያየት ምን ዓይነት እንደ ነበረ ወዲያው ቀጥለው በሚመጡት ቃላት (ከዚህ የበለጠ ግልጥ የሆነ ነገር ሊኖር ከቻለ) ይበልጥ ግልጥ ሆኖ ተወስኖአል፦ «ይህንም እላለሁ» — የምናገርለት መለያየት ይህ ነው፤ እናንተ በተለያዩ ወገኖች ተከፋፍላችኋል፤ ከእናንተ አንዳንዶቹ ለአንዱ ሰባኪ፣ ሌሎቹም ለሌላው ሰባኪ ታደላላችሁ — «እያንዳንዳችሁ» (ቁ. 12) «እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፥ እኔ ግን የኬፋ ነኝ» ትላላችሁ፤ ኬፋ ማለት ጴጥሮስ ነው። እንግዲህ ሐዋርያው እዚህ ቆሮንቶስ ሰዎችን የሚገሥጽበት መለያየት፣ ለአንዱ ወይም ለሌላው ሰባኪ ቅድሚያ በመስጠታቸው በተለያዩ ወገኖች መከፋፈል እንጂ ከዚህ ያልበለጠም ያላነሰም መሆኑን የማያይ ማን ነው? ይህን ዓይነቱን መለያየት ደግሞ በማናቸውም ሃይማኖታዊ ማኅበር ውስጥ መጠንቀቅ የሚያስፈልግበት ጊዜ ይኖራል።
4. ሐዋርያው ይህን ቃል የሚጠቀምበት ሁለተኛው ስፍራ በዚሁ መልእክት በአሥራ አንደኛው ምዕራፍ በአሥራ ስምንተኛው ቁጥር ነው፦ «ወደ ማኅበር ስትሰበሰቡ» — ማለትም ወደ ክርስቲያኖች ጉባኤ — «በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ እሰማለሁ» (የመጀመሪያው ቃል እዚህም σχίσματα፣ ማለትም መለያየቶች ነው)። ነገር ግን እነዚህ መለያየቶች ምን ነበሩ? ሐዋርያው ወዲያው ይነግራችኋል፦ (ቁ. 20) «አብራችሁ ስትሰበሰቡ»፣ ዓላማችሁ «የጌታን እራት መብላት» እንደ ሆነ እየተናገራችሁ፣ «እያንዳንዳችሁ የራሳችሁን እራት ከሌላው አስቀድማችሁ ትወስዳላችሁ»፤ የተለመደ ማዕድ ይመስል። እንግዲያስ መለያየቱ ምን ነበር? ይህን በማድረጋቸው፣ በዚያ በተቀደሰ ጊዜ እንኳ አንዳቸው በሌላው ላይ ቍጣንና ቂምን በሚያሳድሩ ትንንሽ ወገኖች ተከፋፍለው የነበረ ይመስላል።
5. (በዚህ ጉዳይ ላይ አላስፈላጊ በሆነ የኅሊና መጠራጠር ለሚታወኩ ሰዎች ስል ትንሽ ከርዕሱ ወጣ ብዬ) ሐዋርያው በዚህ ምዕራፍ በቆሮንቶስ ቍርባን ተቀባዮች ላይ የሚከሳቸው ኃጢአት ብዙውን ጊዜ ፈጽሞ በስሕተት እንደሚረዳ ልብ ማለት አይቻልምን? ኃጢአቱ በትክክል ይህ ነበር፤ ከዚህም ሌላ ምንም አልነበረም፦ «እያንዳንዱ ከሌላው አስቀድሞ የራሱን እራት መውሰዱ»፤ ይህም «አንዱም ይራባል አንዱ ግን ይሰክራል» እስኪባል ድረስ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ነበር። ይህን በማድረጋችሁ፣ ይላል፣ «ትበላላችሁ፥ ትጠጣላችሁም»፤ («ፍዳን» አይደለም፤ ይህ የቃሉ እጅግ ክፉ የተሳሳተ አተረጓጐም ነው፤ ነገር ግን) ፍርድን፣ ጊዜያዊ ፍርድን፣ «ለራሳችሁ»፤ ይህም አንዳንድ ጊዜ ዕድሜያቸውን ያሳጥር ነበር። «ስለዚህ» — በዚህ ክፉ ሁኔታ ኃጢአት ስለ ሠሩ — «በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ»። እዚህ ሁለት ነገሮችን ልብ በሉ፦ በመጀመሪያ፣ የቆሮንቶስ ሰዎች ኃጢአት ምን ነበር? በደንብ አስተውሉት፤ አስታውሱትም። ኃጢአቱ እያንዳንዱ ከሌላው አስቀድሞ የራሱን እራት መውሰዱ ነበር፤ ስለዚህም አንዱ ይራብ፣ ሌላው ይሰክር ነበር። ሁለተኛ፣ ቅጣቱ ምን ነበር? የሰውነት መድከምና ሕመም ነበር፤ ይህም ንስሐ ካልገቡ በሞት ሊፈጸም ይችል ነበር። ነገር ግን ይህ ለእናንተ ምን ያደርጋል? እናንተ የእነርሱን ኃጢአት ልትሠሩ አትችሉም፤ ስለዚህ የእነርሱን ቅጣት ልትቀበሉ አትችሉም።
6. ነገር ግን ወደ ርዕሳችን እንመለስ። ሐዋርያው በዚህ ምዕራፍ «ኑፋቄዎች» የሚለውን ቃል «መለያየቶች» ከሚለው ቃል ጋር ፍጹም አቻ አድርጎ እንደሚጠቀምበት በቁም ነገር ሊታሰብበት ይገባዋል። (ቁ. 18) «በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ እሰማለሁና፥ በአንድ በኩልም አምናለሁ» ይላል፤ ከዚያም (ቁ. 19) «በመካከላችሁ ወገኖች ደግሞ ሊሆኑ ግድ ነውና» ብሎ ይጨምራል፤ በዚህም «ወገኖች»፣ ማለትም ኑፋቄዎች (ይህም ለዚያው ነገር ሌላ ስም ነው)፣ ሊሆኑ ግድ የሆነው «በእናንተ ዘንድ የተፈተኑት እንዲገለጡ» ነው። ይህም፦ «የእግዚአብሔር ጥበብ ለዚህ ዓላማ፣ ማለትም ልባቸው ከእርሱ ጋር የቀና የሆኑት ግልጥ ሆነው እንዲገለጡ፣ ይህ እንዲሆን ይፈቅዳል» እንዳለ ነው። ስለዚህ ይህ ቃል (ኑፋቄ)፣ ለብዙ መቶ ዓመታት የተሳሳቱ አመለካከቶችን፣ ማለትም «ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ» ከተሰጠው ሃይማኖት ጋር የሚቃረኑ አመለካከቶችን የሚያመለክት ይመስል እጅግ በሚያስገርም ሁኔታ የተጣመመው ቃል — ከተሞችን ለማጥፋት፣ አገሮችን ሰው አልባ ለማድረግና የንጹሓንን ደም እንደ ባሕር ለማፍሰስ ሰበብ የተደረገው ቃል — ትክክለኞችም ሆኑ የተሳሳቱ ከአመለካከቶች ጋር ቅንጣት ታህል ግንኙነት የለውም። በመጽሐፍ ቅዱስ በተገኘበት ስፍራ ሁሉ ትርጉሙ በቀላሉ በሃይማኖታዊ ማኅበር ውስጥ ያሉ መከፋፈሎች ወይም ወገኖች ማለት ብቻ ነው።
7. ሐዋርያው በዚህ መልእክት ይህን ቃል የሚጠቀምበት ሦስተኛውና ብቸኛው የቀረው ስፍራ የአሥራ ሁለተኛው ምዕራፍ ሃያ አምስተኛው ቁጥር ነው፤ በዚያም ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲናገር (ዓለም አቀፋዊቱን ቤተ ክርስቲያን፣ ማለትም የክርስቶስን አካል ሁሉ ማለቱ ይመስላል) እንዲህ ይላል፦ «እግዚአብሔር ግን ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር ሰጥቶ አካልን አገጣጠመው፤ ይህም በአካል መለያየት እንዳይሆን ነው» (ቁ. 24፣ 25)። የራሱን ቃላት ትርጉም ወዲያው ይወስናል፦ «ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በአንድነት እንዲተሳሰቡ ነው። አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።» እዚህ «መለያየት» የሚለው ቃል የዚህ እርስ በርስ የመተሳሰብ ርኅራኄ መጓደል ማለት እንደ ሆነ በቀላሉ ልብ ልንል እንችላለን። ያለ ጥርጥር ከእነርሱ ማንኛቸውም በወንድሞቻቸው ላይ የሚኖራቸውን የፍቅር መራቅ ማለት ነው፤ የልብ መከፋፈልንና ከእርሱም የሚወጡትን ወገኖች ማለት ነው፤ ምንም እንኳ በውጭ አሁንም በአንድነት የተባበሩ ቢሆኑ፣ ምንም እንኳ የዚያው የውጭ ማኅበር አባሎች ሆነው ቢቀጥሉም።
8. ነገር ግን ኑፋቄና መለያየት አንድ ነገር ማለት ናቸው ብሎ በመገመት ላይ አንድ ከባድ ተቃውሞ ያለ ይመስላል። ቅዱስ ጴጥሮስ በሁለተኛው መልእክቱ በሁለተኛው ምዕራፍ «ኑፋቄዎች» የሚለውን ቃል በፍጹም በተለየ ትርጉም ይወስደዋል ይባላል። ቃሉም (ቁ. 1) እንዲህ ነው፦ «በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው» «የሚያኰንን»፣ ወይም አጥፊ፣ «ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ።» ቅዱስ ጴጥሮስ እዚህ «ኑፋቄዎች» የሚለውን ቃል ቅዱስ ጳውሎስ ከሚወስደው በተለየ ትርጉም እንደሚወስደው በምንም መንገድ አይታይም። በዚህ ክፍል እንኳ መልካምም ሆኑ ክፉ ከአመለካከቶች ጋር ግንኙነት ያለው አይመስልም። ይልቁንም ትርጉሙ፦ አጥፊ ወገኖችን ወይም ክፍልፋዮችን «አሹልከው ያገባሉ» ወይም ያስነሣሉ ማለት ነው (በተለመደው የፈረንሳይኛ ትርጉም እንዲህ ተብሎ ተተርጕሞአል)፤ እነዚህም «የዋጃቸውን ጌታ» የሚክዱ ናቸው። እንደ እነዚህ ያሉት ክፍልፋዮች አሁን በክርስቲያኑ ዓለም ሁሉ ተርመስምሰዋል።
9. በመንፈስ መሪነት በተጻፉት መጻሕፍት ውስጥ ይህ «መለያየት» የሚለው ቃል የሚገኝበትን ሌላ ስፍራ ለሚያሳየኝ ሰው ሁሉ አመስጋኝ እሆናለሁ። እኔ የማስታውሰው እነዚህን ሦስቱን ብቻ ነው። በእነዚህም በአንዳቸውም ቢሆን ምክንያት ኖሮም ሆነ ሳይኖር ከማናቸውም ቤተ ክርስቲያን ወይም የክርስቲያኖች አካል መገንጠል ማለት እንዳልሆነ ለማንኛውም ከአድልዎ ነጻ ለሆነ አንባቢ ግልጥ ነው። ስለዚህ የጳጳሱ ተከታዮችም ፕሮቴስታንቶችም መለያየትን ከሮም ቤተ ክርስቲያንም ይሁን ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን እንደ መገንጠል አድርገው በመቃወም ሙሉ መጻሕፍትን ሲጽፉ፣ ኃይላቸውን ሁሉ እያፈሰሱና ትምህርታቸውን ሁሉ እያቀረቡ የደከሙበት እጅግ ብዙ ድካም ለእጅግ ጥቂት ጥቅም ብቻ ውሏል። ራሳቸው ካስነሡት ጥላ ጋር ሲዋጉ ኖረዋል፤ ከራሳቸው ምናብ በቀር ህልውና ከሌለው ኃጢአት ጋር በኃይል ሲታገሉ ኖረዋል፤ ይህም ኃጢአት በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን አንድ ጊዜ እንኳ ያልተከለከለ፣ አይደለም፣ አንድ ጊዜ እንኳ ያልተጠቀሰ ነው።
10. «ታዲያ ብዙ የተማሩና የሃይማኖት ሰዎች የሆኑ ጸሐፊዎች ‹መለያየት› ብለው የጠሩትን የሚመስል፣ የሃይማኖታዊ ማኅበራት አባሎችም ሁሉ በጥንቃቄ ሊጠበቁበት የሚገባ ምንም ኃጢአት የለምን?» እንዳለ አልጠራጠርም፤ ይህም ደግሞ በሩቅ ትርጉም «መለያየት» ተብሎ ሊጠራ የማይችል መሆኑን እርግጠኛ አይደለሁም፤ ይህም ማለት፦ «ከሕያዋን ክርስቲያኖች አካል ያለ ምክንያት መገንጠል» ማለቴ ነው። ቃሉን በዚህ ትርጉም መውሰድ ምንም እንኳ በጥብቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባይሆን ምንም ሞኝነት የለበትም። የክርስቲያን ማኅበራት አባሎች ሁሉ በጥንቃቄ ከእርሱ ሊጠበቁ እንደሚገባቸው እርግጥ ነው። ምክንያቱም ምንም ያህል ትንሽ ነገር ቢመስል፣ ምንም ያህልም ነውር የሌለበት ተደርጎ ቢቆጠር፣ መለያየት በዚህ ትርጉም እንኳ በራሱ ክፉ ነው፤ ክፉ ውጤቶችንም ያስከትላል።
11. በራሱ ክፉ ነው። ቀድሞ ከእነርሱ ጋር አንድ ከነበርንበት ከሕያዋን ክርስቲያኖች አካል ራሳችንን መገንጠል የፍቅርን ሕግ እጅግ በከባድ ሁኔታ መተላለፍ ነው። እኛን በአንድነት ማስተሳሰር የፍቅር ባሕርይ ነው፤ ፍቅሩ በበለጠ መጠን አንድነቱም ይበልጥ የጠበቀ ይሆናል። ፍቅር በብርታቱ እስከ ቀጠለ ድረስ ፍቅር ያስተባበራቸውን ምንም ሊለያቸው አይችልም። ከወንድሞቻችን ስለ መገንጠል ልናስብ የምንችለው ፍቅራችን ሲቀዘቅዝ ብቻ ነው። ይህም ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው በፈቃዳቸው በሚገነጠሉ ሁሉ ላይ በእርግጥ የሚሆን ነገር ነው። ለመገንጠል የሚቀርቡት ሰበቦች ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፤ እውነተኛው ምክንያት ግን ሁልጊዜ የፍቅር ማጣት ነው፤ አለዚያማ አሁንም «በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት» በጠበቁ ነበር። ስለዚህ ይህ የወንድማማች መዋደድ ከታዘዘባቸው የእግዚአብሔር ትእዛዛት ሁሉ ጋር ይቃረናል፤ ቅዱስ ጳውሎስ፦ «የወንድማማች መዋደድ ጸንቶ ይኑር» ካለው፤ — ቅዱስ ዮሐንስ፦ «የተወደዳችሁ ልጆቼ ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ» ካለው፤ — በተለይም ብሩክ ጌታችን፦ «እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት» ካለው ጋር ይቃረናል። እንዲያውም፦ «እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ» ይላል።
12፣ እንዲህ ያለው መገንጠል የወንድማማች መዋደድን መተላለፍ በመሆኑ በራሱ ክፉ እንደ ሆነ ሁሉ፣ እንዲሁ ክፉ ፍሬን ያፈራል፤ በባሕርዩ እጅግ ጎጂ የሆኑ ውጤቶችን ያስከትላል። በራሳችንም በሌሎችም ውስጥ ለደግነት የጎደላቸው ዝንባሌዎች ሁሉ በር ይከፍታል። በቀጥታ ወደ ክፉ ጥርጣሬዎች ሰልፍ ሁሉ፣ አንዱ ሌላውን ወደ መጨከንና ፍቅር የሌለበት ፍርድ ወደ መፍረድ ይመራል። ለመሰናከል፣ ለቍጣና ለቂም ምክንያት ይሰጣል፤ ምናልባትም በወንድሞቻችን ብቻ ሳይሆን በራሳችንም ውስጥ፤ ይህም ወዲያው ካልተገታ ወደ ምሬት፣ ወደ ክፋትና ወደ ጸና ጥላቻ ሊያደርስ ይችላል፤ በተገኙበትም ስፍራ ሁሉ ለዘላለማዊ ገሃነም መቅድም ሆኖ የአሁን ገሃነምን ይፈጥራል።
13. ነገር ግን የዚህ ዓይነቱ መለያየት እንኳ ክፉ ውጤቶች በልብ ውስጥ ብቻ አያበቁም። ክፉ ዝንባሌዎች ውጫዊ ፍሬን ሳያፈሩ ለረጅም ጊዜ በውስጥ ሊቆዩ አይችሉም። በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራል። ልቡ በፍቅር የተሞላ ሰው አፉን በጥበብ እንደሚከፍት፣ በከንፈሮቹም የቸርነት ሕግ እንዳለ፣ እንዲሁ ልቡ በጭፍን ጥላቻ፣ በቍጣ፣ በጥርጣሬ ወይም በማናቸውም ደግነት የጎደለው ዝንባሌ የተሞላ ሰው በእርግጥ ከአእምሮው ዝንባሌ ጋር በሚስማማ መንገድ አፉን ይከፍታል። ከዚህም የተነሣ ውሸትና ስም ማጥፋት ባይሆን እንኳ (እነዚህም ቢሆኑ ከቶ ሊቀሩ አይችሉም)፣ መራራ ቃላት፣ ወሬ ማቀበል፣ ሐሜትና ማናቸውም ዓይነት ክፉ መናገር ይነሣሉ።
14. ከክፉ ቃላት፣ ከወሬ ማቀበል፣ ከሐሜትና ከክፉ መናገር ስንት ክፉ ሥራዎች በተፈጥሮ ይፈስሳሉ! ቍጣ፣ ቅንዓት፣ ምቀኝነትና ማናቸውም ዓይነት የተሳሳቱ ዝንባሌዎች በቃላት ብቻ አይገለጡም፤ ይልቁንም ሰዎችን ወደ ማናቸውም ዓይነት እግዚአብሔርን ወደማይፈሩና ወደ ዓመፀኛ ተግባራት ዘወትር ይገፋሉ። ከዚህ ምንጭ የጨለማ ሥራዎች ሁሉ የተትረፈረፈ መከር ይበቅላል ተብሎ ሊጠበቅ ይችላል፤ በዚህም በመጨረሻ በሺህ የሚቈጠሩ ነፍሳት፣ ከእነርሱም በአንድ ወቅት በእግዚአብሔር ፊት ብርሃን የተመላለሱ ጥቂት ያልሆኑ ሰዎች፣ ከሰላም መንገድ ተመልሰው በመጨረሻ በዘላለማዊ ጥፋት ውስጥ ሊሰጥሙ ይችላሉ።
15. ብሩክ ጌታችን፦ «ወዮ ለዓለም ስለ ማሰናከያ» ማለቱ ተገቢ ነው፤ ሆኖም «ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና»። እንዲያውም በማናቸውም ሃይማኖታዊ ማኅበር ውስጥ እንዲህ ያለ ስብራት በተፈጠረ ጊዜ ብዙ ማሰናከያዎች ግድ ይነሣሉ፤ ማኅበሩን ትተው የሚወጡት ሰዎች የተገነጠሉባቸውን በመንቀፍ ራሳቸውን ለማጽደቅ ይጥራሉ፤ እነዚያ ደግሞ በበኩላቸው ክሱን መልሰው በእነርሱ ላይ ይጥላሉ፤ ነቀፋውንም በእነርሱ ላይ ለማድረግ ይተጋሉ። ነገር ግን ይህ ሁሉ ጭቅጭቅ ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ እንዴት እጅግ ያሳዝናል! በአንዱም በሌላውም ነፍስ ውስጥ የሚሠራውን የዋህና ለስላሳ ሥራውን እንዴት ያደናቅፋል! ይዋል ይደር እንጂ ኑፋቄዎችና መለያየቶች (በእነዚህ ቃላት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም) ውጤቱ ይሆናሉ፤ በአንዱም በሌላውም ወገን ክፍልፋዮች ይፈጠራሉ፤ በዚህም የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። የጽድቅ ረሃብና ጥማት፣ የእግዚአብሔርን ሞገስ ወይም የእግዚአብሔርን ሙሉ መልክ የመራብና የመጠማት ጉጕት፣ ከዚያም ጋር ብዙዎች ተሞልተውበት የነበረው በወንድሞቻቸው ነፍስ ውስጥ የእግዚአብሔርን ሥራ የማስፋፋት ናፍቆት፣ ይዝላሉ፤ ማሰናከያዎችም እየበዙ ሲሄዱ ቀስ በቀስ እየከሰሙ ይጠፋሉ። «የመንፈስ ፍሬ» እየደረቀ ሲሄድ ደግሞ «የሥጋ ሥራ» እንደ ገና ያይላል፤ ይህም በመጀመሪያ የሃይማኖትን ኃይል፣ ከዚያም የሃይማኖትን መልክ እንኳ ፈጽሞ እስኪያጠፋ ድረስ ነው። እነዚህ ውጤቶች የምናብ ውጤቶች አይደሉም፤ በግምት ብቻ ላይ የተመሠረቱም አይደሉም፤ ነገር ግን ግልጥ በሆነ እውነታ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ባለፉት ሠላሳ ወይም አርባ ዓመታት ውስጥ ደጋግሞ እንዲህ ሆኖአል፤ እንደዚህ ያለውን መገንጠል ተከትለው ሲመጡ ደጋግመን ያየናቸው ፍሬዎች እነዚህ ናቸው።
16. እነዚህም ነገሮች በውጭ ላሉት፣ ከሃይማኖት ለራቁት፣ የእግዚአብሔርን መምሰል መልክም ኃይልም ለሌላቸው እንዴት ያለ ከባድ ማሰናከያ ይሆኑባቸዋል! በእነዚህ በአንድ ወቅት ታዋቂ በነበሩ ክርስቲያኖች ላይ እንዴት ይዘብቱባቸዋል! «እነዚህ ከእኛ በምን ይሻላሉ?» ብለው እንዴት በድፍረት ይጠይቃሉ! በእውነት ላይ ልባቸውን ይበልጥ እንዴት ያደነድናሉ፤ በክፋታቸውም ራሳቸውን እንዴት ይባርካሉ! ክርስቲያኖቹ በአካሄዳቸው ነቀፋ የሌለባቸው ሆነው ቢቀጥሉ ኖሮ፣ ምናልባት የእነርሱ ምሳሌ ከዚህ ክፋት መልሶአቸው ነበር። ከክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ወይም ማኅበር የሚገነጠሉ ሰዎች በራሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በዚያ ማኅበር ሁሉ ላይና በአጠቃላይ በዓለም ሁሉ ላይ የሚያደርሱት የተወሳሰበ ጉዳት እንዲህ ያለ ነው።
17. ነገር ግን ምናልባት እንደነዚህ ያሉት ሰዎች እንዲህ ይሉ ይሆናል፦ «ይህን ያደረግነው በፈቃዳችን አይደለም፤ ከዚያ ማኅበር በንጹሕ ሕሊና በውስጡ ልንቀጥል ስላልቻልን ለመገንጠል ተገደድን፤ ያለ ኃጢአት ልንቀጥል አልቻልንም። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሳልተላለፍ በውስጡ እንድቀጥል አልተፈቀደልኝም።» ነገሩ እንዲህ ከሆነ ከዚያ ማኅበር በመገንጠላችሁ ልትነቀፉ አትችሉም። ለምሳሌ የሮም ቤተ ክርስቲያን አባል ብትሆኑና ጣዖትን ሳታመልኩ፣ ምስሎችም ይሁኑ ቅዱሳንና መላእክት ጣዖታትን ሳትሰግዱ በውስጧ መቆየት ባትችሉ፣ ያን ጊዜ ያንን ማኅበር መተው፣ ፈጽሞም ከእርሱ መገንጠል የግድ የሆነባችሁ ግዴታ ይሆናል። የእግዚአብሔር ቃል የሚከለክለውን አንድ ነገር ሳታደርጉ ወይም የእግዚአብሔር ቃል በግልጥ የሚያዝዘውን አንድ ነገር ሳትተዉ በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን መቆየት ባትችሉ፣ ነገሩ እንዲህ ቢሆን (ነገር ግን እግዚአብሔር ይመስገን፣ እንዲህ አይደለም)፣ ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን መገንጠል ይገባችኋል። ጉዳዩን የራሴ ጉዳይ አድርጌ ልናገር፦ እኔ አሁን የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አባልና አገልጋይ ነኝ፤ ከወጣትነቴም ጀምሮ እንዲሁ ነበርሁ፤ ነፍሴ ከሥጋዬ እስክትለይ ድረስ ከእርሷ የመገንጠል ፍላጎትም ሆነ ዓላማ የለኝም። ሆኖም እግዚአብሔር እንዳደርገው የሚፈልግብኝን ሳልተው በውስጧ እንድቆይ ባልተፈቀደልኝ፣ ያን ጊዜ ሳልዘገይ ከእርሷ መገንጠል ተገቢና ትክክል፣ የግድ የሆነብኝም ግዴታ ይሆናል። ይበልጥ በዝርዝር ልናገር፦ እግዚአብሔር የወንጌልን መጋቢነት በአደራ እንደ ሰጠኝ አውቃለሁ፤ አዎን፣ የራሴም መዳን በመስበኩ ላይ የተመሠረተ ነው፤ «ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ።» እንግዲህ ይህን ሳልተው፣ ወንጌልን ከመስበክ ሳልቆጠብ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መቆየት ባልችል፣ ከእርሷ ለመገንጠል ወይም የገዛ ነፍሴን ለማጣት እገደድ ነበር። እንደዚሁም ኃጢአትን ሳልሠራ፣ ያለ ውሸትና ያለ ግብዝነት፣ እኔ ራሴ የማላምንባቸውን ትምህርቶች ለሌሎች ሳልሰብክ ከማናቸውም ትንሽ ማኅበር፣ ቤተ ክርስቲያን ወይም የክርስቲያኖች አካል ጋር አንድ ሆኜ መቀጠል ባልችል፣ ከዚያ ማኅበር ለመገንጠል ፍጹም የግድ ይሆንብኝ ነበር። በእነዚህም ሁሉ ሁኔታዎች የመገንጠሉ ኃጢአት ከእርሱም የሚከተሉት ክፉ ነገሮች ሁሉ በእኔ ላይ አይወድቁም ነበር፤ ነገር ግን በሕሊና ልስማማባቸው የማልችላቸውን የኅብረት ቅድመ ሁኔታዎች በእኔ ላይ በመጫን ያንን መገንጠል እንዳደርግ ባስገደዱኝ ላይ ይወድቃሉ። ነገር ግን ይህን ሁኔታ ወደ ጎን ትተን፣ አሁን አንድ የሆንሁባት ቤተ ክርስቲያን ወይም ማኅበር መጽሐፍ ቅዱስ የሚከለክለውን ማናቸውንም ነገር እንዳደርግ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዝዘውን ማናቸውንም ነገር እንድተው የማትጠይቀኝ ብትሆን፣ በውስጧ መቀጠል የማይቀር ግዴታዬ ነው። እንደዚህ ያለ ግድ ሳይኖር ከእርሷ ብገነጠል ደግሞ (አስቀድሜ ባያቸውም ባላያቸውም) ከዚያ መገንጠል በሚከተሉት ክፉ ነገሮች ሁሉ በትክክል ተጠያቂ እሆናለሁ።
18. በዚህ ነጥብ ላይ ይበልጥ በግልጥ የተናገርሁት እምብዛም ስለማይታወቅ ነው፤ ብዙ ሃይማኖትን የሚናገሩ፣ አዎን፣ በእውነትም በተወሰነ መጠን ሃይማኖትን የሚደሰቱበት ብዙ ሰዎች ስለዚህ ጉዳይ ቅንጣት ታህል ግንዛቤ ስለሌላቸው፣ እንዲህ ያለውም መገንጠል በፍጹም ኃጢአት እንደ ሆነ ስለማያስቡ ነው። ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል እንደሚወጡ ያህል ግድ ሳይሰጣቸው ክርስቲያናዊ ማኅበርን ይተዋሉ። ለዚህ ሁሉ የተወሳሰበ ጉዳት ምክንያት ይሆናሉ፤ ከዚያም አፋቸውን ያብሳሉ፤ ምንም ክፉ አላደረግንም ይላሉ! በእውነቱ ግን በእግዚአብሔርና በሰው ፊት በራሱ ክፉ በሆነ ድርጊትም፣ በራሳቸውም፣ በወንድሞቻቸውም፣ በዓለምም ላይ ይከተላሉ ተብለው በሚጠበቁት ክፉ ውጤቶች ሁሉም በትክክል ተጠያቂዎች ናቸው።
19. ስለዚህ፣ ወንድሞቼ ሆይ፣ እግዚአብሔርን የምትፈሩ፣ እርሱንም ደስ ለማሰኘት የምትሹ ሁሉ፣ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ነውር የሌለባት ሕሊና እንዲኖራችሁ የምትመኙ ሁሉ፣ እለምናችኋለሁ፤ ይህን ጉዳይ አቅልላችሁ አትመልከቱት፤ ነገር ግን በእርጋታ አስቡበት። ከማናቸውም ክርስቲያናዊ ማኅበር ጋር የሚያስተሳስሯችሁን የተቀደሱ ማሰሪያዎች በችኮላ አትበጥሱ። ይህ በእርግጥ ለአንተ፣ በስም ብቻ ክርስቲያን ለሆንኸው፣ ያን ያህል ብዙ ክብደት የለውም። አሁን ከክርስቶስ ብልቶች ከአንዳቸውም ጋር ሕያው በሆነ አንድነት አልተጣመርህምና። ክርስቲያን ተብለህ ብትጠራም በእውነት የማናቸውም ክርስቲያናዊ ቤተ ክርስቲያን አባል አይደለህም። ነገር ግን ሕያው ብልት ከሆንህ፣ በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር የተሰወረውን ሕይወት የምትኖር ከሆንህ፣ ከወንድሞችህ በመገንጠል የክርስቶስን አካል እንዳትቀድድ ተጠንቀቅ። ይህ በራሱ ክፉ ነገር ነው። በውጤቱም ከባድ ክፋት ነው። ኦ፣ ለራስህ እዘን! ለወንድሞችህ እዘን። እግዚአብሔርን ለማይፈሩት ዓለምም እንኳ እዘን! ክርስቶስ በሞተላቸው በእነዚህ መንገድ ላይ ተጨማሪ ማሰናከያዎችን አታኑር።
20. ነገር ግን ያለ አግባብ «መለያየት» ተብሎ የሚጠራውን መለያየት ብትፈራ፣ ይህም ያለ ምክንያት ባይሆንም፣ ሕሊናህ ርኅሩኅ ከሆነ በትክክለኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉሙ መለያየትን እንዴት ይበልጥ ትፈራ! ኦ፣ ተጠንቀቅ፤ በክርስቲያናዊ ማኅበር ውስጥ ማናቸውንም ክፍልፋዮች ከመመሥረት አልልም፣ ነገር ግን ከመደገፍ ወይም ከማበረታታት ተጠንቀቅ! በቃልም ሆነ በድርጊት በውስጡ ማናቸውንም መከፋፈል ፈጽሞ አታበረታታ፤ ይልቁንም አታስነሣ። በነገሮች ባሕርይ «በመካከላችሁ ወገኖች ደግሞ ሊሆኑ ግድ ነውና»፣ ማለትም መከፋፈሎች፤ አንተ ግን ራስህን በንጽሕና ጠብቅ። ጠብ ሳይነሣ ክርክርን ተው፤ የጭቅጭቅን መጀመሪያ እንኳ ሽሽ። ለክርክር ከተሰጡት፣ ጠብን ከሚወዱ ሰዎች ጋር አትተባበር። «መከራከርን የሚወድ እግዚአብሔርን አይወድም» የሚለው አስተያየት ሲሳሳት አይቼ አላውቅም። ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተል፤ ያለ እርሱ ቅድስናን በብቃት መከታተል አትችልምና። «ሰላምን ይሻ ይከተለውም» እንደ ተባለ ሰላምን መሻት ብቻ ሳይሆን ተከተለውም፤ ከአንተ የሚሸሽ ቢመስልም ቢሆን አሳደደው። «ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።»
21. በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያስታርቅ ሰው የሚለውን መልካም ስም የሚያገኝ ሰው ብፁዕ ነው። አንተ ለዚህ የማትደክመው ስለ ምንድን ነው? ጠብን ባለማስነሣት ብቻ አትርካ፤ ነገር ግን የጠቡን የመጀመሪያ ብልጭታ እንኳ ለመከላከል ወይም ለማጥፋት በአንተ የሚቻለውን ሁሉ አድርግ። በእርግጥ ነበልባሉ ከተነሣ በኋላ ከማጥፋት ይልቅ እንዳይነሣ መከላከል እጅግ ይቀላል። ሆኖም ይህንም እንኳ ለመሞከር አትፍራ፤ የሰላም አምላክ ከአንተ ጋር ነው። እርሱ ተቀባይነት ያላቸውን ቃላት ይሰጥሃል፤ ወደ ሰሚዎችም ልብ ይልካቸዋል። አንድ የሃይማኖት ሰው፦ «ኖሊ ዲፊዴሬ፤ ኖሊ ዲስኬዴሬ» ይላል፤ «ፋክ ኩዎድ ኢን ቴ ኤስት፤ ኤት ዴውስ አዴሪት ቦናኤ ቱአኤ ቮሉንታቲ»፤ ይህም፦ «ሥልጣን ሁሉ ያለውን፣ የሰዎችንም ሁሉ ልብ በእጁ የያዘውን አትጠራጠረው። በአንተ የሚቻለውን አድርግ፤ እግዚአብሔርም ይገኛል፤ መልካሙንም ምኞትህን ለመልካም ፍጻሜ ያደርሰዋል» ማለት ነው። መልካም ሥራን ለመሥራት ፈጽሞ አትታክት። ባትዝል በጊዜው ታጭዳለህ።