በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች የተሰበኩ ስብከቶች
የሚቅበዘበዙ አሳቦች

ምዕራፍ 42 · 13 ደቂቃ ንባብ · 17 ደቂቃ ማዳመጥ

የሚቅበዘበዙ አሳቦች

ስብከት 41

የሚቅበዘበዙ አሳቦች

«ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን።»

2ኛ ቆሮንቶስ 10:5።

1. ነገር ግን ገና በሥጋ ሳለን እንኳ አንድም የሚቅበዘበዝ አሳብ በአእምሮአችን ውስጥ ስፍራ እስኪያጣ ድረስ እግዚአብሔር «አሳብን ሁሉ ለክርስቶስ ለመታዘዝ» ይማርካልን? አንዳንዶች እንዲህ ብለው አጥብቀው ተከራክረዋል፤ አዎን፣ በማስተዋል ረገድ የሚቅበዘበዙ አሳቦች ሁሉ እስኪወገዱ ድረስ ፍጹማን ካልሆኑ በቀር፣ ማለትም እያንዳንዱ ስሜትና ዝንባሌ ቅዱስ፣ ጻድቅና በጎ ብቻ ሳይሆን በአእምሮ ውስጥ የሚነሣው እያንዳንዱ አሳብ ጥበበኛና ሥርዓት ያለው ካልሆነ በቀር፣ ማንም በፍቅር ፍጹም አልሆነም ብለው አረጋግጠዋል።

2. ይህ ቀላል ግምት የሚሰጠው ጥያቄ አይደለም። እግዚአብሔርን ከሚፈሩት፣ አዎን፣ ምናልባትም በፍጹም ልባቸው ከሚወድዱት መካከል ስንቶቹ በዚህ ምክንያት እጅግ ተጨንቀዋል! ስንቶቹስ ነገሩን በትክክል ባለማስተዋላቸው መጨነቅ ብቻ ሳይሆን በነፍሳቸው እጅግ ተጐድተዋል፤ — ወደ እግዚአብሔር የሚያደርጉትን ጕዞ ወደሚያዘገዩና በፊታቸው የተዘጋጀውን ሩጫ ሲሮጡ ወደሚያደክሟቸው ወደማይጠቅሙ፣ አዎን፣ ወደሚጐዱ የአእምሮ ክርክሮች ተጥለዋል! ከዚህም አልፎ ብዙዎች በዚሁ ነገር ላይ በተሳሳተ ግንዛቤ ምክንያት የእግዚአብሔርን ክቡር ስጦታ ጥለዋል። በመጀመሪያ እግዚአብሔር በነፍሳቸው የሠራውን ሥራ እንዲጠራጠሩ፣ ከዚያም እንዲክዱ ተገፋፍተዋል፤ በዚህም የእግዚአብሔርን መንፈስ አሳዝነዋል፤ እርሱም ተለይቶ በፍጹም ጨለማ እስኪተዋቸው ድረስ!

3. እንግዲያስ በቅርቡ በሁሉም ጉዳዮች ማለት ይቻላል ከታተሙት ከብዙ መጻሕፍት መካከል ስለ ሚቅበዘበዙ አሳቦች አንድም የሌለን እንዴት ነው? ቢያንስ የረጋንና ቁም ነገረኛን አእምሮ በምንም መንገድ የሚያረካ አንድም የለንም? ይህን በተወሰነ መጠን ለማድረግ የሚከተሉትን ለመመርመር አስባለሁ፦

I. የሚቅበዘበዙ አሳቦች የተለያዩ ዓይነቶች ምንድር ናቸው?

II. በአጠቃላይ የሚነሡባቸው ምክንያቶች ምንድር ናቸው?

III. ከእነርሱ ኃጢአት የሆኑት የትኞቹ ናቸው? ኃጢአት ያልሆኑትስ የትኞቹ ናቸው?

IV. ከየትኞቹ ለመዳን ልንጠብቅና ልንጸልይ እንችላለን?

I. 1. በመጀመሪያ፣ የሚቅበዘበዙ አሳቦች የተለያዩ ዓይነቶች ምንድር ናቸው? የሚለውን ልመረምር አስባለሁ። ዝርዝር ዓይነቶቻቸው ስፍር ቍጥር የላቸውም፤ በአጠቃላይ ግን ሁለት ዓይነት ናቸው፦ ከእግዚአብሔር የሚቅበዘበዙ አሳቦችና በእጃችን ካለው ከተወሰነው ነጥብ የሚቅበዘበዙ አሳቦች።

2. የመጀመሪያዎቹን በተመለከተ፣ አሳቦቻችን ሁሉ በተፈጥሮአቸው እንዲህ ያሉ ናቸው፤ ያለማቋረጥ ከእግዚአብሔር ይቅበዘበዛሉና፤ ስለ እርሱ ምንም አናስብም፤ እግዚአብሔር በአሳባችን ሁሉ ውስጥ የለም፤ ሐዋርያው እንደሚለው፣ ሁላችንም አንድ በአንድ «በዓለም ያለ እግዚአብሔር» ነን። የምንወድደውን እናስባለን፤ እግዚአብሔርን ግን አንወድደውም፤ ስለዚህ ስለ እርሱ አናስብም። ወይም አልፎ አልፎ ለጥቂት ጊዜ ስለ እርሱ እንድናስብ ብንገደድ እንኳ፣ በዚያ ደስታ ስለሌለን፣ ይልቁንም እነዚህ አሳቦች ጣዕም የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ የሚያስጠሉንና የሚያሰለቹን ስለ ሆኑ፣ በተቻለን ፍጥነት እናባርራቸዋለን፤ ማሰብ ወደምንወድደውም ነገር እንመለሳለን። ስለዚህ ዓለምና በዓለም ያሉ ነገሮች፣ — ምን እንበላለን፣ ምን እንጠጣለን፣ ምን እንለብሳለን፣ — ምን እናያለን፣ ምን እንሰማለን፣ ምን እናተርፋለን፣ — ስሜቶቻችንን ወይም ምናባችንን እንዴት ደስ እናሰኛለን የሚለው፣ — ጊዜያችንን ሁሉ ይወስዳል፤ አሳባችንንም ሁሉ ይቈጣጠራል። ስለዚህ ዓለምን እስከ ወደድን ድረስ፣ ማለትም በፍጥረታዊ ሁኔታችን እስካለን ድረስ፣ ከጥዋት እስከ ማታ፣ ከማታም እስከ ጥዋት ያሉት አሳቦቻችን ሁሉ የሚቅበዘበዙ አሳቦች እንጂ ሌላ አይደሉም።

3. ነገር ግን ብዙ ጊዜ «በዓለም ያለ እግዚአብሔር» ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ጋር የምንዋጋም ነን፤ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ በተፈጥሮው «በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል» የሆነ «ስለ ሥጋ ማሰብ» አለና። ስለዚህ ሰዎች በአለማመን አሳቦች ቢሞሉ ምንም አያስደንቅም፤ በልባቸው «እግዚአብሔር የለም» ይላሉ፤ ወይም ኃይሉን ወይም ጥበቡን፣ ምሕረቱን ወይም ፍትሑን ወይም ቅድስናውን ባይክዱ እንኳ ይጠራጠራሉ። ስለ መግቦቱ፣ ቢያንስ ወደ ኩነቶች ሁሉ መድረሱን ብዙ ጊዜ ቢጠራጠሩ፣ ወይም ቢቀበሉት እንኳ የማጕረምረምና የማማረር አሳቦችን ቢያስተናግዱ አያስደንቅም። ከእነዚህ ጋር በቅርብ የተዛመዱና ብዙ ጊዜም አብረዋቸው የሚገኙ የትዕቢትና የከንቱነት ምናቦች ናቸው። ደግሞም፦ አንዳንድ ጊዜ በቍጣ፣ በክፋት ወይም በበቀል አሳቦች ይያዛሉ፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ የስሜትም ሆነ የምናብ በሆኑ ከንቱ የተድላ ቅዠቶች፤ በዚህም ምድራዊውና ሥጋዊው አእምሮ ይበልጥ ምድራዊና ሥጋዊ ይሆናል። እንግዲህ በእነዚህ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ግልጽ ጦርነት ይገጥማሉ፤ እነዚህ እጅግ የከፉት የሚቅበዘበዙ አሳቦች ናቸው።

4. ከእነዚህ እጅግ የተለዩ ሌሎቹ ዓይነት የሚቅበዘበዙ አሳቦች ናቸው፤ በእነርሱ ልብ ከእግዚአብሔር አይቅበዘበዝም፤ ማስተዋል ግን በዚያን ጊዜ ከያዘው ከተወሰነው ነጥብ ይቅበዘበዛል። ለምሳሌ፦ ከጽሑፉ በፊት ባለው ቍጥር ውስጥ ያሉትን «የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ … በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው» የሚሉትን ቃላት ለማሰላሰል እቀመጣለሁ። እንዲህም አስባለሁ፦ «ክርስቲያኖች ከሚባሉት ሁሉ ጋር ነገሩ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል። ነገር ግን ምንኛ ተቃራኒ ሆኖአል! ክርስቲያናዊው ዓለም ተብሎ የሚጠራውን ክፍል ሁሉ ማለት ይቻላል ዙሪያውን ተመልከቱ። እነዚህ ምን ዓይነት የጦር ዕቃ ይጠቀማሉ? በምን ዓይነትስ ጦርነት ተሰማርተዋል፤

ሰዎች እንደ አጋንንት እርስ በርሳቸው ሲበጫጨቁ፣

በገሃነማዊው የጦርነት ቍጣ ሁሉ?

እስቲ እነዚህ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚዋደዱ ተመልከቱ! ከቱርኮችና ከአረማውያን በምን ይሻላሉ? በመሐመዳውያን ወይም በአሕዛብ መካከል የሚገኝ፣ በክርስቲያኖች መካከል ግን የማይገኝ ምን ርኵሰት አለ?» እንዲህም አእምሮዬ ሳላውቀው ከአንዱ ጉዳይ ወደ ሌላው ይሮጣል። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ በአንድ መልኩ የሚቅበዘበዙ አሳቦች ናቸው፤ ከእግዚአብሔር ባይቅበዘበዙም፣ ይልቁንም ከእርሱ ጋር ባይዋጉም፣ ከያዝሁት ከተወሰነው ነጥብ ግን ይቅበዘበዛሉና።

II. የሚቅበዘበዙ አሳቦች ባሕርይ እንዲህ ነው፤ ዓይነቶቻቸውም (በፍልስፍና ሳይሆን ይልቁን በሚጠቅም መንገድ ለመናገር) እንዲህ ናቸው። ነገር ግን በአጠቃላይ የሚነሡባቸው ምክንያቶች ምንድር ናቸው? ይህን በሁለተኛ ደረጃ እንመረምራለን።

1. እግዚአብሔርን የሚቃወሙ ወይም ከእርሱ የሚቅበዘበዙ የመጀመሪያዎቹ ዓይነት አሳቦች ምክንያት በአጠቃላይ ኃጢአተኛ ዝንባሌዎች እንደ ሆኑ ማስተዋል ቀላል ነው። ለምሳሌ፦ እግዚአብሔር በፍጥረታዊ ሰው አሳብ ሁሉ ውስጥ፣ በየትኛውም አሳቡ ውስጥ የሌለው ስለ ምንድር ነው? ምክንያቱ ግልጽ ነው፦ ባለ ጠጋ ይሁን ድሃ፣ የተማረ ይሁን ያልተማረ፣ እርሱ አምላክ የለሽ ነው፤ (በተራው አነጋገር እንዲህ ባይባልም፤) እግዚአብሔርን አያውቀውም፣ አይወድደውምም። አሳቡ ዘወትር ዓለምን እየተከተለ የሚቅበዘበዘው ስለ ምንድር ነው? ጣዖት አምላኪ ስለ ሆነ ነው። እርግጥ ነው፣ ምስልን አያመልክም፤ ለዛፍ ግንድም አይሰግድም፤ ቢሆንም እኩል ወደሚያስኰንን የጣዖት አምልኮ ሰጥሟል፦ ዓለምን ይወድዳል፣ ማለትም ያመልካል። ደስታን በሚታዩ ነገሮች፣ ሲጠቀሙባቸው በሚጠፉ ተድላዎች ይፈልጋል። አሳቡ ከሕልውናው ዋና ዓላማ፣ ማለትም እግዚአብሔርን በክርስቶስ ከማወቅ ዘወትር የሚቅበዘበዘው ስለ ምንድር ነው? የማያምን ስለ ሆነ ነው፤ እምነት ስለሌለው ነው፤ ወይም ቢያንስ ከዲያብሎስ የሚበልጥ እምነት ስለሌለው ነው። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ የሚቅበዘበዙ አሳቦች ከዚያ ክፉ የአለማመን ሥር በቀላሉና በተፈጥሮ ይበቅላሉ።

2. በሌሎችም ሁኔታዎች ነገሩ እንዲሁ ነው፦ ትዕቢት፣ ቍጣ፣ በቀል፣ ከንቱነት፣ ምኞት፣ መጐምጀት፣ እያንዳንዳቸው ከራሳቸው ባሕርይ ጋር የሚስማሙ አሳቦችን ያስነሣሉ። የሰው አእምሮ ሊኖረው የሚችለው እያንዳንዱ ኃጢአተኛ ዝንባሌም እንዲሁ ያደርጋል። ዝርዝሮቹን መቍጠር የሚቻል አይደለም፤ የሚያስፈልግም አይደለም፤ በየትኛውም ነፍስ ውስጥ ምን ያህል ክፉ ዝንባሌዎች ስፍራ ቢያገኙ፣ ያቺ ነፍስ በከፋው ዓይነት የሚቅበዘበዙ አሳቦች በዚያው ልክ በብዙ መንገድ ከእግዚአብሔር እንደምትርቅ ማስተዋል ይበቃል።

3. የኋለኞቹ ዓይነት የሚቅበዘበዙ አሳቦች ምክንያቶች እጅግ የተለያዩ ናቸው። እጅግ ብዙዎቹ የሚነሡት በነፍስና በሥጋ መካከል ባለው ተፈጥሮአዊ አንድነት ነው። ማስተዋል በታመመ ሥጋ ምንኛ በቅጽበትና ምንኛ በጥልቀት ይነካል! ደሙ በአንጐል ውስጥ ያለ ሥርዓት ይንቀሳቀስ እንጂ፣ ሥርዓት ያለው አስተሳሰብ ሁሉ ያከትማል። ኃይለኛ እብደት ይከተላል፤ ከዚያም የተስተካከለ አሳብ ሁሉ ደኅና ሰንብት ይባላል። አዎን፣ የሕይወት ኃይላት እስከ ተወሰነ ደረጃ ብቻ ቢቻኰሉ ወይም ቢናወጡ፣ ጊዜያዊ እብደት፣ ማለትም ቅዠት፣ የረጋን አሳብ ሁሉ ይከለክላል። ይኸው የአሳብ መዛባትስ በተወሰነ መጠን በማንኛውም የነርቭ መታወክ አይመጣምን? እንዲሁ «የሚበሰብሰው ሥጋ ነፍስን ያከብዳታል፥ ስለ ብዙ ነገርም እንድታሰላስል ያደርጋታል።»

4. ነገር ግን ይህን የሚያደርገው በሕመም ወይም ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ መታወክ ጊዜ ብቻ ነውን? አይደለም፤ ብዙም ይሁን ጥቂት በሁሉም ጊዜ፣ ፍጹም ጤንነት ባለበት ሁኔታ እንኳ ያደርገዋል። አንድ ሰው የቱንም ያህል ጤነኛ ቢሆን፣ በየሃያ አራት ሰዓቱ ብዙም ይሁን ጥቂት ይቃዣል። አይተኛምን? ሲተኛስ ሕልም ለማየት የተጋለጠ አይደለምን? ታዲያ በዚያን ጊዜ የገዛ አሳቡ ጌታ የሆነ ወይም ሥርዓታቸውንና ተያያዥነታቸውን ሊጠብቅ የሚችል ማን ነው? በዚያን ጊዜ በአንድ ነጥብ ላይ ጸንተው እንዲቆሙ ሊያደርጋቸው ወይም ከዋልታ ወደ ዋልታ እንዳይቅበዘበዙ ሊከለክላቸው የሚችል ማን ነው?

5. ነገር ግን ነቅተናል እንበል፤ አሳባችንን በጽናት ልንገዛ በምንችልበት መጠን ሁልጊዜ ነቅተናልን? በዚሁ በሥጋ መሣሪያ ባሕርይ ምክንያት ሳንወድ በግድ ለተቃራኒ ጽንፎች የተጋለጥን አይደለንምን? አንዳንድ ጊዜ ማንኛውንም የአሳብ ሰንሰለት ለመከተል እጅግ የከበድን፣ እጅግ የደነዘዝንና የዛልን ነን። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በተቃራኒው እጅግ የተነቃቃን ነን። ምናብ ያለ ፈቃድ ወዲያና ወዲህ ይዘልላል፤ ብንፈልግም ባንፈልግም ወዲያና ወዲህ ይወስደናል፤ ይህም ሁሉ ከሕይወት ኃይላት ተራ ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴ ወይም ከነርቮች ንዝረት ብቻ የሚመጣ ነው።

6. ደግሞም፦ ፈጽሞ ሳናውቅና ከምርጫችን ነጻ ሆነው ከሚፈጠሩት ከተለያዩ የሐሳቦቻችን ትስስሮች ስንት የአሳብ መቅበዝበዝ ሊነሣ ይችላል? እነዚህ ትስስሮች እንዴት እንደሚፈጠሩ ልንናገር አንችልም፤ ነገር ግን በሺህ የተለያዩ መንገዶች ይፈጠራሉ። እነዚህን ትስስሮች መበጠስ ወይም የእነርሱ የግድ ውጤትና የዕለት ዕለት ምልከታ የሆነውን መከልከል ከሰዎች ሁሉ እጅግ ጥበበኛ ወይም እጅግ ቅዱስ ለሆነው እንኳ የሚቻል አይደለም። እሳቱ የባሩዱን መስመር አንዱን ጫፍ ብቻ ይንካ እንጂ፣ ወዲያውኑ እስከ ሌላው ጫፍ ይሮጣል።

7. ደግሞም፦ በማንኛውም ጉዳይ ላይ የቻልነውን ያህል በትጋት ትኵረታችንን እናድርግ፤ ቢሆንም ደስታ ወይም ሥቃይ ቢነሣ፣ በተለይም ብርቱ ቢሆን፣ ወዲያውኑ ትኵረታችንን ይጠይቃል፤ አሳባችንንም ወደ ራሱ ይስባል። እጅግ የጸናውን ማሰላሰል ያቋርጣል፤ አእምሮንም ከሚወድደው ጉዳይ ያስቀይሳል።

8. እነዚህ የሚቅበዘበዙ አሳቦች ምክንያቶች በውስጣችን ያሉ ናቸው፤ በራሱ በተፈጥሮአችን ውስጥ የተሸመኑ ናቸው። ነገር ግን ከውጫዊ ነገሮች ልዩ ልዩ ግፊትም እንዲሁ በተፈጥሮና በግድ ይነሣሉ። የስሜት ሕዋስን፣ ዓይንን ወይም ጆሮን፣ የሚመታ ማንኛውም ነገር በአእምሮ ውስጥ ግንዛቤን ያስነሣል። በዚሁ መሠረት የምናየውም ሆነ የምንሰማው ሁሉ ቀድሞ የነበረንን የአሳብ ሰንሰለት ጥሶ ይገባል። ስለዚህ በፊታችን ማንኛውንም ነገር የሚያደርግ ወይም በጆሮአችን ማንኛውንም ነገር የሚናገር ሰው ሁሉ አእምሮአችን ቀድሞ ያስብበት ከነበረው ነጥብ ብዙም ይሁን ጥቂት እንዲቅበዘበዝ ያደርገዋል።

9. ዘወትር የሚውጡትን የሚፈልጉ እነዚያ ክፉ መናፍስት አእምሮአችንን ለማቻኰልና ለመበታተን ከላይ የተጠቀሱትን ምክንያቶች ሁሉ እንደሚጠቀሙባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። አንዳንድ ጊዜ በአንዱ፣ አንዳንድ ጊዜ በሌላው በእነዚህ መንገዶች ያስጨንቁናል፤ ግራም ያጋቡናል፤ እግዚአብሔርም እስከሚፈቅድላቸው ድረስ አሳባችንን ያቋርጣሉ፤ በተለይም አሳባችን በበጎ ጉዳዮች ላይ በተሰማራ ጊዜ። ይህም ፈጽሞ የሚያስገርም አይደለም፤ የአሳብን ምንጮች ራሳቸውን ያስተውላሉና፤ ምናብ፣ ማስተዋልና ሌላው የአእምሮ ችሎታ ሁሉ ይበልጥ በቀጥታ በየትኞቹ የአካል ክፍሎች ላይ እንደሚመረኰዙ ያውቃሉ። በዚህም እነዚያን የአካል ክፍሎች በመንካት በእነርሱ ላይ የተመረኰዙትን ሥራዎች እንዴት እንደሚነኩ ያውቃሉ። በዚህ ላይ ደግሞ ከላይ ከተጠቀሱት መንገዶች አንዳቸውም ሳያስፈልጓቸው ሺህ አሳቦችን ሊያስገቡ እንደሚችሉ ጨምሩ፤ ቍስ በቍስ ላይ እንደሚሠራ ሁሉ መንፈስም በመንፈስ ላይ መሥራቱ ተፈጥሮአዊ ነውና። እነዚህ ነገሮች ሲታሰቡ፣ አሳባችን ከያዝነው ከማንኛውም ነጥብ ብዙ ጊዜ መቅበዝበዙ ሊያስደንቀን አይገባም።

III. 1. ከሚቅበዘበዙ አሳቦች ኃጢአት የሆኑት ምን ዓይነቶቹ እንደ ሆኑ፣ ኃጢአት ያልሆኑትስ ምን ዓይነቶቹ እንደ ሆኑ የምንመረምረው ሦስተኛው ነገር ነው። በመጀመሪያ፣ ከእግዚአብሔር የሚቅበዘበዙ፣ በአእምሮአችን ውስጥ ለእርሱ ስፍራ የማይተዉ አሳቦች ሁሉ ያለ ጥርጥር ኃጢአት ናቸው። እነዚህ ሁሉ በተግባር የሚገለጥ እግዚአብሔር የለም ባይነትን ያመለክታሉና፤ በእነዚህም በዓለም ያለ እግዚአብሔር ነን። ለእግዚአብሔር ተቃራኒ የሆኑት፣ በእርሱ ላይ ተቃውሞን ወይም ጥልን የሚያመለክቱት ሁሉ ደግሞ ከዚህ እጅግ በበለጠ ኃጢአት ናቸው። እንደ እነዚህ ያሉት በውጤቱ «በላያችን ልትነግሥ አንወድም» የሚሉ የማጕረምረምና ያለመርካት አሳቦች ሁሉ ናቸው፤ — ሕልውናውን፣ ባሕርያቱን ወይም መግቦቱን በተመለከተ የአለማመን አሳቦች ሁሉ። መግቦቱ ስል በጽንፈ ዓለም ውስጥ ባሉ ሰዎች ሁሉ ላይ ብቻ ሳይሆን በነገሮች ሁሉ ላይ ያለውን ልዩ መግቦቱን ማለቴ ነው፤ ያለ እርሱ «አንዲት ድንቢጥ እንኳ በምድር ላይ አትወድቅም»፤ በእርሱም «የራሳችን ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል»፤ ከልዩው መግቦት ተለይቶ የሚነገረው አጠቃላይ መግቦት (በተራ አነጋገር እንደሚጠራው) ግን ምንም ትርጉም የሌለው ጨዋና ጆሮ የሚያስደስት ቃል ብቻ ነውና።

2. ደግሞም፦ ከኃጢአተኛ ዝንባሌዎች የሚመነጩ አሳቦች ሁሉ ያለ ጥርጥር ኃጢአት ናቸው። ለምሳሌ፣ ከበቀለኛ ዝንባሌ፣ ከትዕቢት፣ ወይም ከምኞት፣ ወይም ከከንቱነት የሚመነጩት እንደ እነዚህ ያሉ ናቸው። «ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም»፤ ስለዚህ ዛፉ ክፉ ከሆነ ፍሬውም እንዲሁ ክፉ መሆን አለበት።

3. ማንኛውንም ኃጢአተኛ ዝንባሌ የሚያስገኙ ወይም የሚመግቡ አሳቦችም እንዲሁ መሆን አለባቸው፤ ትዕቢትን ወይም ከንቱነትን፣ ቍጣን ወይም የዓለምን ፍቅር የሚያስነሡ፣ ወይም እነዚህን ወይም ሌላ ማንኛውንም ያልተቀደሰ ዝንባሌ፣ ምኞት ወይም ስሜት የሚያጸኑና የሚያበዙ። ከክፉ የሚፈልቅ ማንኛውም ነገር ክፉ ብቻ ሳይሆን ወደ ክፉ የሚመራ ማንኛውም ነገርም ክፉ ነውና፤ ነፍስን ከእግዚአብሔር የሚያርቅ፣ የምድር፣ የሥጋና የአጋንንት የሚያደርጋት ወይም እንዲሁ የሚያስቀራት ማንኛውም ነገር።

4. ስለዚህ በድካም ወይም በሕመም፣ በሥጋ ተፈጥሮአዊ አሠራር ወይም በሕይወት አንድነት ሕግጋት የሚነሡ አሳቦች እንኳ፣ በራሳቸው የቱንም ያህል ንጹሐን ቢሆኑ፣ በውስጣችን ማንኛውንም ኃጢአተኛ ዝንባሌ፣ ለምሳሌ የሥጋ ምኞትን፣ የዓይን ምኞትን ወይም የሕይወትን ትዕቢት፣ ሲያስገኙ ወይም ሲንከባከቡና ሲያበዙ ኃጢአት ይሆናሉ። በተመሳሳይ መንገድ፣ በሌሎች ሰዎች ቃል ወይም ድርጊት የሚነሡ የሚቅበዘበዙ አሳቦች ማንኛውንም የተሳሳተ ዝንባሌ ቢያስነሡ ወይም ቢመግቡ፣ ያን ጊዜ ኃጢአት መሆን ይጀምራሉ። በዲያብሎስ የሚጠቈሙትን ወይም የሚገቡትንም በተመለከተ እንዲሁ ልናስተውል እንችላለን። ማንኛውንም ምድራዊ ወይም ዲያብሎሳዊ ዝንባሌ ሲያገለግሉ፣ (ይህንንም ለእነርሱ ስፍራ በሰጠናቸውና በዚህም የራሳችን ባደረግናቸው ጊዜ ሁሉ ያደርጉታል፤) ያን ጊዜ ከሚያገለግሏቸው ዝንባሌዎች ጋር እኩል ኃጢአት ናቸው።

5. ነገር ግን ከእነዚህ ሁኔታዎች ውጭ ስናያቸው፣ በኋለኛው የቃሉ ትርጉም የሚቅበዘበዙ አሳቦች፣ ማለትም ማስተዋላችን ከያዘው ነጥብ የሚቅበዘበዝባቸው አሳቦች፣ በደም ሥሮቻችን ውስጥ ካለው የደም እንቅስቃሴ ወይም በአንጐላችን ውስጥ ካለው የሕይወት ኃይላት እንቅስቃሴ የበለጠ ኃጢአት አይደሉም። ከደካማ የሰውነት አቋም ወይም ከአንዳች ድንገተኛ ድካም ወይም ሕመም ቢነሡ፣ ደካማ የሰውነት አቋም ወይም የታመመ ሥጋ መያዝ ንጹሕ እንደ ሆነ ሁሉ እነርሱም እንዲሁ ንጹሐን ናቸው። በእርግጥም የነርቭ መታወክ፣ ማንኛውም ዓይነት ትኩሳት፣ ጊዜያዊም ሆነ ዘላቂ ቅዠት ከፍጹም ንጽሕና ጋር አብሮ ሊኖር እንደሚችል ማንም አይጠራጠርም። ጤናማ ከሆነ ሥጋ ጋር በተዋሐደች ነፍስ ውስጥም ቢነሡ፣ በሥጋና በነፍስ መካከል ካለው ተፈጥሮአዊ አንድነት ወይም አሳብን በሚያገለግሉት በእነዚያ የአካል ክፍሎች ውስጥ ሊከሰቱ ከሚችሉ ከአሥር ሺህ ለውጦች ከአንዱም ቢሆን፤ — ከእነዚህ በማንኛውም ሁኔታ ልክ እንደሚመነጩባቸው ምክንያቶች ፍጹም ንጹሐን ናቸው። ከሐሳቦቻችን ድንገተኛና ያለ ፈቃድ ከሚመጡ ትስስሮች ሲመነጩም እንዲሁ ናቸው።

6. ሌሎች ሰዎች ስሜቶቻችንን በልዩ ልዩ መንገድ በመንካታቸው አሳቦቻችን ከያዝነው ነጥብ ቢቅበዘበዙ፣ አሁንም እኩል ንጹሐን ናቸው፤ የማየውንና የምሰማውን፣ በብዙ ሁኔታዎችም ከማየት፣ ከመስማትና ከማስተዋል ልከለከል የማልችለውን ማስተዋል ዓይንና ጆሮ ከመያዝ የበለጠ ኃጢአት አይደለምና። «ነገር ግን ዲያብሎስ የሚቅበዘበዙ አሳቦችን ቢያስገባ፣ እነዚያ አሳቦች ክፉ አይደሉምን?» አስጨናቂዎች ናቸው፤ በዚያም መልኩ ክፉ ናቸው፤ ኃጢአት ግን አይደሉም። ዲያብሎስ ለጌታችን በሚሰማ ድምፅ እንደ ተናገረው አላውቅም፤ ምናልባት «ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ» ባለው ጊዜ ለልቡ ብቻ ተናግሮ ይሆናል። ነገር ግን በውስጥም ተናገረ በውጭ፣ ጌታችን ያለውን ያለ ጥርጥር አስተውሏል። ስለዚህ ከእነዚያ ቃላት ጋር የሚመሳሰል አሳብ ነበረው። ነገር ግን ኃጢአተኛ አሳብ ነበርን? እንዳልነበረ እናውቃለን። በእርሱ በድርጊትም ሆነ በቃል ወይም በአሳብ ምንም ኃጢአት አልነበረም። ሰይጣን በማንኛውም የጌታችን ተከታይ ውስጥ በሚያስገባቸው በተመሳሳይ ዓይነት ሺህ አሳቦችም ውስጥ ምንም ኃጢአት የለም።

7. ከዚህም የሚከተለው (ጥንቃቄ የጐደላቸው ሰዎች ምንም ቢያረጋግጡና በዚህም ጌታ ያላሳዘናቸውን ቢያሳዝኑ) ከእነዚህ የሚቅበዘበዙ አሳቦች አንዳቸውም ከፍጹም ፍቅር ጋር የማይስማሙ አለመሆናቸው ነው። በእርግጥ የማይስማሙ ቢሆኑ ኖሮ፣ ብርቱ ሥቃይ ብቻ ሳይሆን እንቅልፍ ራሱ እንኳ ከእርሱ ጋር የማይስማማ በሆነ ነበር፤ — ብርቱ ሥቃይ፦ ይህ በመጣ ጊዜ ሁሉ፣ ከዚያ በፊት ስለ ምንም ስናስብ ብንቆይ፣ አስተሳሰባችንን ያቋርጣልና፤ በዚህም አሳባችንን ወደ ሌላ መስመር ይስባል፤ — አዎን፣ እንቅልፍም ራሱ፦ የስሜት አልባነትና የድንዛዜ ሁኔታ ስለ ሆነ፤ በአብዛኛውም በምድር ላይ ከሚቅበዘበዙ፣ ልቅ፣ ዱርና የማይያያዙ አሳቦች ጋር የተቀላቀለ ስለ ሆነ። ቢሆንም እነዚህ ከፍጹም ፍቅር ጋር እንደሚስማሙ እርግጥ ነው፤ እንግዲያስ የዚህ ዓይነቱ የሚቅበዘበዙ አሳቦች ሁሉ ደግሞ ይስማማሉ።

IV. 1. ከተመለከትነው ነገር ለመጨረሻው ጥያቄ ግልጽ መልስ መስጠት ቀላል ነው፤ — ከየትኞቹ ዓይነት የሚቅበዘበዙ አሳቦች ለመዳን ልንጠብቅና ልንጸልይ እንችላለን?

ከመጀመሪያዎቹ ዓይነት የሚቅበዘበዙ አሳቦች፣ — ልብ ከእግዚአብሔር ከሚቅበዘበዝባቸው፣ ከፈቃዱ ተቃራኒ ከሆኑት ሁሉ ወይም በዓለም ያለ እግዚአብሔር ከሚያስቀሩን ሁሉ፣ — በፍቅር ፍጹም የሆነ ሁሉ ያለ ጥርጥር ድኗል። ስለዚህ ይህን መዳን ልንጠብቅ እንችላለን፤ ስለዚህ ልንጸልይ እንችላለን፣ ልንጸልይም ይገባናል። የዚህ ዓይነቱ የሚቅበዘበዙ አሳቦች ለእግዚአብሔር ጥልን ባያመለክቱ እንኳ አለማመንን ያመለክታሉ፤ እርሱ ግን ሁለቱንም ያጠፋል፣ ፈጽሞም ያከትማቸዋል። በእርግጥም ከኃጢአተኛ የሚቅበዘበዙ አሳቦች ሁሉ ፈጽመን እንድናለን። በፍቅር ፍጹማን የሆኑ ሁሉ ከእነዚህ ድነዋል፤ አለዚያ ከኃጢአት አልዳኑም ነበር። ሰዎችና አጋንንት በሁሉ ዓይነት መንገድ ይፈትኗቸዋል፤ ነገር ግን ሊያሸንፏቸው አይችሉም።

2. የኋለኞቹን ዓይነት የሚቅበዘበዙ አሳቦች በተመለከተ ግን ነገሩ እጅግ የተለየ ነው። ምክንያቱ እስኪወገድ ድረስ ውጤቱ እንዲቋረጥ በአእምሮ ልንጠብቅ አንችልም። የእነዚህ መንስኤዎች ወይም ምክንያቶች ግን በሥጋ እስካለን ድረስ ይኖራሉ። ስለዚህ እስከዚያው ድረስ ውጤቶቹም እንደሚኖሩ ለማመን በቂ ምክንያት አለን።

3. ይበልጥ በዝርዝር ለመናገር፦ አንዲት ነፍስ የቱንም ያህል ቅድስት ብትሆን በታመመ ሥጋ ውስጥ ትኖራለች እንበል፤ ኃይለኛ እብደት እስኪከተል ድረስ አንጐሉ ፈጽሞ ተዛብቷል እንበል፤ ያ መዛባት እስካለ ድረስ አሳቦች ሁሉ ዱርና የማይያያዙ አይሆኑምን? ትኩሳት ቅዠት ብለን የምንጠራውን ያን ጊዜያዊ እብደት ያስከትላል እንበል፤ ያ ቅዠት እስኪወገድ ድረስ ትክክለኛ የአሳብ ትስስር ሊኖር ይችላልን? አዎን፣ የነርቭ መታወክ የሚባለው ቢያንስ ከፊል እብደትን እስከሚያስከትል ድረስ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል እንበል፤ ሺህ የሚቅበዘበዙ አሳቦች አይኖሩምን? እነዚህስ ሥርዓት የለሽ አሳቦች የሚያስከትላቸው መታወክ እስካለ ድረስ መቀጠላቸው የግድ አይደለምን?

4. ከብርቱ ሥቃይ በግድ የሚነሡትን አሳቦች በተመለከተስ ነገሩ እንዲሁ አይሆንምን? ያ ሥቃይ እስካለ ድረስ በማይጣሰው የተፈጥሮ ሥርዓት ብዙም ይሁን ጥቂት ይቀጥላሉ። ይህ ሥርዓት ደግሞ ከሥጋ ተፈጥሮአዊ አቋም በሚመነጭ የግንዛቤ፣ የፍርድ ወይም የምናብ ጕድለት አሳቦች በሚታወኩበት፣ በሚሰበሩበት ወይም በሚቋረጡበት ስፍራ ሁሉ ይሠራል። ከሐሳቦቻችን ሊገለጽ ከማይችልና ያለ ፈቃድ ከሚመጣ ትስስርስ ስንት መቋረጦች ሊመነጩ ይችላሉ! እንግዲህ እነዚህ ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመጡት አእምሮን በሚያከብደው በሚበሰብሰው ሥጋ ነው። ስለዚህ «ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ» እንጂ ከዚያ በፊት እንዲወገዱ ልንጠብቅ አንችልም።

5. በምናያቸውና በምንሰማቸው ነገሮች፣ አሁን በዙሪያችን ባሉት ሰዎች መካከል ከሚነሡት የሚቅበዘበዙ አሳቦች የምንድነው በዚያን ጊዜ ብቻ፣ በትቢያ ውስጥ ስንተኛ ነው። ከእነዚህ ለመራቅ ከዓለም መውጣት አለብን፤ በውስጡ እስካለን ድረስ፣ በዙሪያችን ወንዶችና ሴቶች እስካሉ ድረስ፣ የሚያዩ ዓይኖችና የሚሰሙ ጆሮዎች እስካሉን ድረስ፣ በየዕለቱ የምናያቸውና የምንሰማቸው ነገሮች አእምሮአችንን በእርግጥ ይነካሉ፤ ቀድሞ የነበሩንን አሳቦችም ብዙም ይሁን ጥቂት ጥሰው ገብተው ያቋርጣሉና።

6. ክፉ መናፍስትም በተጐሳቈለና በተዘበራረቀ ዓለም ውስጥ ወዲያና ወዲህ እስከ ተመላለሱ ድረስ፣ እስከዚያው ድረስ (ማሸነፍ ቢችሉም ባይችሉም) ሥጋና ደም የለበሰውን ነዋሪ ሁሉ ያጠቃሉ። ሊያጠፏቸው የማይችሉትን እንኳ ያውካሉ፤ ማሸነፍ ባይችሉም ያጠቃሉ። ከእነዚህ እረፍት ከሌላቸው፣ ከማይደክሙ ጠላቶቻችን ጥቃቶችም «ክፉዎች ማወካቸውን ወደሚተዉበት፥ የደከሙም ወደሚያርፉበት» ስፍራ እስክንገባ ድረስ ፍጹም መዳንን መጠበቅ የለብንም።

7. ሁሉንም ለማጠቃለል፦ በክፉ መናፍስት ከሚነሡ የሚቅበዘበዙ አሳቦች መዳንን መጠበቅ ዲያብሎስ እንዲሞት ወይም እንዲያንቀላፋ፣ ወይም ቢያንስ ከእንግዲህ እንደሚያገሣ አንበሳ እንዳይዞር መጠበቅ ነው። በሌሎች ሰዎች ከሚነሡት መዳንን መጠበቅ ሰዎች ከምድር እንዲጠፉ፣ ወይም እኛ ፈጽመን ከእነርሱ እንድንገለል፣ ከእነርሱም ጋር ምንም ግንኙነት እንዳይኖረን፣ ወይም ዓይኖች እያሉን እንዳናይ፣ በጆሮአችንም እንዳንሰማ፣ ነገር ግን እንደ ግንድ ወይም እንደ ድንጋይ ስሜት አልባ እንድንሆን መጠበቅ ነው። በሥጋ ከሚነሡት መዳንን ብሎ መጸለይ ደግሞ በውጤቱ ከሥጋ እንድንለይ መጸለይ ነው፤ አለዚያ የማይቻሉና የማይረቡ ነገሮችን መጸለይ ነው፤ ከሚበሰብስ ሥጋ ጋር ያለንን አንድነት ያለዚያ አንድነት ተፈጥሮአዊና የግድ ውጤቶች በማስቀጠል እግዚአብሔር እርስ በርስ የሚቃረኑ ነገሮችን እንዲያስታርቅ መጸለይ ነው። ይህም በአንድ ጊዜ መላእክትም ሰዎችም፣ ሟቾችም የማንሞትም እንድንሆን የመጸለይ ያህል ነው። አይደለም! — ነገር ግን የማይሞተው በመጣ ጊዜ ሟችነት ይሻራል።

8. ይልቁንም እነዚህ ነገሮች ሁሉ ለበጎአችን አብረው እንዲሠሩ በመንፈስም በአእምሮም እንጸልይ፤ የተፈጥሮአችንን ድካሞች ሁሉ፣ የሰዎችን መቋረጦች ሁሉ፣ የክፉ መናፍስትን ጥቃቶችና ጥቆማዎች ሁሉ እንድንታገሥ፣ በሁሉም «ከአሸናፊዎች እንድንበልጥ»። ከኃጢአት ሁሉ እንድንድን እንጸልይ፤ ሥሩም ቅርንጫፉም እንዲጠፉ፤ «ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ»፣ ከክፉ ዝንባሌ፣ ከቃልና ከሥራ ሁሉ እንድንነጻ፤ «ጌታ አምላካችንን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም አሳባችን፣ በፍጹም ነፍሳችንና በፍጹም ኃይላችን» እንድንወድድ፤ የመንፈስ ፍሬ ሁሉ በእኛ ውስጥ እንዲገኝ፣ — ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም ብቻ ሳይሆን «ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የዋህነት፥ ራስን መግዛት» ደግሞ። ወደ ዘላለሙ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት እስኪሰጣችሁ ድረስ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እንዲያብቡና እንዲትረፈረፉ፣ በእናንተም ውስጥ ይበልጥ እየበዙ እንዲሄዱ ጸልዩ!

ቀዳሚ ቀጣይ