ምዕራፍ 117 · 14 ደቂቃ ንባብ · 18 ደቂቃ ማዳመጥ
ክርስትና ውጤት ያላስገኘባቸው ምክንያቶች
ስብከት 116
ክርስትና ውጤት ያላስገኘባቸው ምክንያቶች
«በገለዓድ የሚቀባ መድኃኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን? እንግዲህ የሕዝቤ ሴት ልጅ ጤና ስለ ምን አልተመለሰም?»
ኤርምያስ 8:22
1. ይህ ጥያቄ ነቢዩ እዚህ እንዳቀረበው፥ የሚመለከተው አንድን ሕዝብ ብቻ ነው፤ — የእስራኤልን ልጆች። እኔ ግን እዚህ ላይ በጠቅላላ ትርጉሙ፥ የሰውን ዘር ሁሉ በሚመለከት ልመረምረው እወዳለሁ። ክርስትና በዓለም ላይ ይህን ያህል ጥቂት መልካም ነገር ያደረገው ስለ ምንድር ነው? ብዬ በቁም ነገር መጠየቅ እወዳለሁ። ታላቁ ሐኪም የሰዎችን መንፈሳዊ ጤና ይመልስ ዘንድ የሰጣቸው የሚቀባ መድኃኒት፥ ውጫዊው መንገድ፥ እርሱ አይደለምን? ታዲያ ጤናቸው ስለ ምን አልተመለሰም? እናንተ፦ ከሰው ተፈጥሮ ጥልቅና ሁሉን አቀፍ ርኩሰት የተነሣ ነው ትላላችሁ። እጅግ እውነት ነው፤ ነገር ግን ችግሩ ራሱ ያለው እዚህ ላይ ነው። ሁሉን በሚያውቀውና ሁሉን በሚችለው ፈጣሪያችን ለዚያ ርኩሰት መድኃኒት እንዲሆን የታሰበ አልነበረምን? ለሁሉን አቀፍ ክፋት ሁሉን አቀፍ መድኃኒት? ነገር ግን ይህን ዓላማ አልፈጸመም፤ ፈጽሞም አያውቅም፤ ዛሬም አይፈጽመውም። ደዌው አሁንም በሙሉ ኃይሉ እንዳለ ነው፤ ዓይነቱ ብዙ የሆነ ኃጢአት፥ ውስጣዊና ውጫዊ ብልግና በዓይነቱ ሁሉ አሁንም የምድርን ፊት እንደ ሸፈነ ነው።
2. ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ «አንተ ጻድቅ ነህ! ነገር ግን ከአንተ ጋር እንከራከር።» ይህ እንዴት ነው? ለራስህ ክብር የፈጠርኸውን፥ የሠራኸውን ዓለም ረሳኸውን? የእጅህን ሥራ፥ በልጅህ ደም የተገዛውን ልትንቅ ትችላለህን? ደዌያችንን የሚፈውስ መድኃኒት ሰጥተኸናል፤ ደዌያችን ግን አልተፈወሰም። አሁንም ጨለማ ምድርን፥ ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ አዎን፥
«አጋንንት የሚሰማቸው ዓይነት ጨለማ፥
ከገሃነም ጕድጓድ እየወጣ።»
3. ክርስትና በዓለም ላይ ይህን ያህል ጥቂት መልካም ነገር ማድረጉ እንዴት ያለ ምሥጢር ነው! ለዚህ አንዳች ማብራሪያ ሊሰጥ ይቻላልን? ለዚህስ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይቻላልን? ይህን ያህል ጥቂት መልካም ነገር ካደረገበት ምክንያቶች አንዱ ይህ አይመስልምን፥ — ይህን ያህል ጥቂት ስለሚታወቅ? በማይታወቅበት ስፍራ አንዳች መልካም ነገር ሊያደርግ እንደማይችል በእርግጥ ነው። ነገር ግን ዛሬ በምድር ከሚኖሩት እጅግ ብዙዎቹ አያውቁትም። ባለፈው ምዕተ ዓመት፥ ብልሁና ትጉሁ የአገራችን ሰው አቶ ብሬርውድ፥ ክርስቲያኖች ከአረማውያንና ከመሐመዳውያን ጋር ሲነጻጸሩ ምን ያህል ድርሻ እንዳላቸው በተቻለ መጠን ለመመርመር ብሎ የታወቀውን ዓለም ብዙውን ክፍል ተዘዋወረ። እንደ እርሱም ስሌት (ምናልባት እስከ ዛሬ ከተደረገው ሁሉ እጅግ ትክክለኛው ይህ ነው)፥ የሰውን ዘር በሠላሳ ክፍሎች ብንከፍለው፥ ከእነዚህ ውስጥ አሥራ ዘጠኙ ክፍሎች አሁንም ገሃድ አረማውያን ናቸው እላለሁ፤ ስለ ክርስትና ከሚጠፉ እንስሶች የበለጠ እውቀት የላቸውም። በዚህም ላይ በዚህ ምዕተ ዓመት የተገኙትን ብዙ ሕዝቦች ልንጨምር እንችላለን። የመሐመድን ሃይማኖት የሚከተሉትንና ክርስትናን ፈጽመው የሚንቁትን ደግሞ ጨምሩባቸው፤ ከሰው ዘር ከሠላሳው ክፍል ሀያ አምስቱ በስም እንኳ ክርስቲያኖች አይደሉም። እንግዲህ ከሰው ዘር ከስድስቱ ክፍል አምስቱ ስለ ክርስትና ፈጽሞ አያውቁም። ስለዚህ ከሰው ዘር ከስድስቱ አምስቱ፥ ምናልባትም ከአሥሩ ዘጠኙ፥ ከእርሱ አንዳች ጥቅም ባያገኙ የሚያስደንቅ አይደለም።
4. ነገር ግን ክርስቲያን በሆነው ዓለም ከእርሱ የሚገኘው ጥቅም ይህን ያህል ጥቂት የሆነው ለምንድር ነው? ክርስቲያኖች ከሌሎች ሰዎች በምንም ይሻላሉን? ከመሐመዳውያን ወይም ከአረማውያን ይሻላሉን? እውነቱን ለመናገር፥ ከእነርሱ የባሱ ባይሆኑ መልካም ነው፤ ከመሐመዳውያንም ሆነ ከአረማውያን የባሱ። በብዙ ረገድ እጅግ የባሱ ናቸው፤ ነገር ግን እነርሱ በትክክለኛው ትርጉም ክርስቲያኖች አይደሉም። አብዛኞቹ የክርስቲያንን ስም ቢሰሙም፥ ክርስትና ምን እንደ ሆነ አያውቁም። ግሪክኛን ወይም ዕብራይስጥን እንደማያስተውሉ ሁሉ እርሱንም አያስተውሉትም፤ ስለዚህ በእርሱ ምንም ሊሻሉ አይችሉም። በቱርክ ግዛቶች ሁሉ ተበትነው የሚኖሩት፥ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች የሚባሉት፥ ስለ እውነተኛ ክርስትና ምን ያውቃሉ? የሞሬያ፥ የሰርካሲያ፥ የሚንግሬሊያ፥ የጆርጂያ ሰዎችስ? እነርሱ የሰው ዘር ግርጌ አይደሉምን? የደቡቡ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች፥ በሐበሻ የሚኖሩት፥ «እግዚአብሔርን በመንፈስና በእውነት ስለ ማምለክ» ከእነዚያ የበለጠ ግንዛቤ አላቸው ብለን የምናስብበት ምክንያት አለንን? ወደ ቤታችን ቀረብ ብለን እንመልከት። የሰሜኑን አብያተ ክርስቲያናት፥ ከሞስኮው ፓትርያርክ በታች ያሉትን እዩ። ስለ ውጫዊውም ሆነ ስለ ውስጣዊው ክርስትና የሚያውቁት እንዴት እጅግ ጥቂት ነው! ከእነዚያ ምስኪን አረመኔዎች ስንት ሺዎች፥ አዎን፥ ስንት እልፍ አእላፋት ከክርስትና ከስሙ በቀር ምንም አያውቁም! በአንድ በኩል ካሉት አረማውያን ታታሮች፥ በሌላ በኩልም ካሉት አረማውያን ቻይናውያን የሚያውቁት እንዴት ጥቂት ብቻ ይበልጣል!
5. ነገር ግን ክርስትና ቢያንስ በምዕራቡ ዓለም ለሚኖሩት ሁሉ በሚገባ የታወቀ አይደለምን? ብዙው ክፍሉ በተለየ ሁኔታ ሕዝበ ክርስቲያን፥ ወይም የክርስቲያኖች ምድር ተብሎ ይጠራልና። ከእነዚህ ከፊሎቹ አሁንም የሮም ቤተ ክርስቲያን አባላት ናቸው፤ ከፊሎቹ ፕሮቴስታንቶች ይባላሉ። ስለ ቀደሞቹ፥ ስለ ፖርቱጋላውያን፥ ስለ ስፔናውያን፥ ስለ ጣሊያናውያን፥ ስለ ፈረንሳውያንና ስለ ጀርመናውያን፥ አብዛኞቹ ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና ምን ያውቃሉ? ከእነዚህ ከብዙዎቹ ጋር በአገር ውስጥም በውጭም ለመነጋገር ብዙ ጊዜ አጋጣሚ ስላገኘሁ፥ በጠቅላላው የክርስትናን ትምህርትም ሆነ ተግባር ፈጽመው እንደማያውቁ በድፍረት አረጋግጣለሁ፤ ስለዚህም በሺህ የሚቈጠሩት «እውቀት ከማጣታቸው የተነሣ» — የክርስትናን የመጀመሪያ መሠረታዊ ትምህርቶች እንኳ ባለማወቃቸው — «እየጠፉ» ናቸው።
6. «ነገር ግን በእርግጥ ይህ በፈረንሳይ፥ በስዊዘርላንድ፥ በጀርመንና በሆላንድ ባሉ ፕሮቴስታንቶች ዘንድ ሊሆን አይችልም፤ በዴንማርክና በስዊድንማ ከቶ አይሆንም።» በእርግጥ ሙሉ በሙሉ እንደዚያ እንዳልሆነ ተስፋ አደርጋለሁ። በመካከላቸው ብዙ የሚያውቁ ክርስቲያኖች እንዳሉ አምናለሁ፤ ነገር ግን ከአሥሩ አንዱ፥ ከአምሳውም አንዱ እንኳ ቢሆን፥ ከዚህ ቍጥር ነው ብለን ማሰብ እንደሌለብን እፈራለሁ፤ በታላቋ ብሪታንያና በአየርላንድ በምናገኛቸው ሰዎች ልክ ስለ እነርሱ የምንፈርድ ከሆነ፥ በእርግጥ አይደለም። በገዛ ደጃችን ነገሩ እንዴት እንደ ሆነ እንመልከት። የእንግሊዝ ሕዝብ በጠቅላላው (ከፍተኞቹ ወይም ዝቅተኞቹ አይደሉም፤ እነዚህ በአብዛኛው ስለ ጉዳዩ ምንም አያውቁምና፤ ነገር ግን መካከለኛው ደረጃ ያሉት ሰዎች) ክርስትናን ያስተውላሉን? ምን እንደ ሆነ ይገነዘባሉን? ስለ ሐሳባዊውም ሆነ ስለ ተግባራዊው ክፍሉ የሚያስተውል ማብራሪያ ሊሰጡ ይችላሉን? ስለ መሠረታዊ ትምህርቶቹ፥ — ስለ እግዚአብሔር ተፈጥሮአዊና ሥነ ምግባራዊ ባሕርያት፥ ስለ ልዩ መግቦቱ፥ ስለ ሰው ቤዛነት፥ ስለ ክርስቶስ ሹመቶች፥ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥራዎች፥ ስለ መጽደቅ፥ ስለ አዲስ ልደት፥ ስለ ውስጣዊና ውጫዊ መቀደስ ምን ያውቃሉ? ከእነዚህ ነገሮች ስለ አንዱ አብራችሁ ላላችሁት የመጀመሪያዎቹ አሥር ሰዎች ተናገሩ፤ ከአሥሩ ዘጠኙ ስለ ጉዳዩ ሁሉ የማያውቁ ሆነው አታገኙአቸውምን? በስኮትላንድ ደጋማ ግዛቶች የሚኖሩት አብዛኞቹ እንደ እነዚህ ፈጽመው የማያውቁ አይደሉምን? አዎን፥ በአየርላንድ ያለው ተራው ሕዝብስ? (እኔ የምለው አሁን ስለ እነርሱ ብቻ የምንናገርላቸውን ፕሮቴስታንቶችን ነው።) በገጠር ጎጆዎች ብቻ ሳይሆን በኮርክ፥ በዎተርፎርድ፥ በሊመሪክ ከተሞች፥ አዎን፥ በደብሊን ራሱ ቅን ምርመራ አድርጉ። ክርስትና ምን ማለት እንደ ሆነ የሚያውቁት እንዴት ጥቂቶች ናቸው! ስለ እምነት ስምምነት፥ እርስ በርሳቸው ስለ ተያያዙት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ሰንሰለትና አንዱ ከሌላው ጋር ስላላቸው ግንኙነት፥ — ይኸውም ስለ ሰው ተፈጥሮአዊ ርኩሰት፥ በእምነት ስለ መጽደቅ፥ ስለ አዲስ ልደት፥ ስለ ውስጣዊና ውጫዊ ቅድስና — አንዳች ግንዛቤ ያላቸው የምታገኙት እንዴት ጥቂት ቍጥር ነው! በእነዚህ መንግሥታት ውስጥ ከባልንጀሮቻቸው ጋር በነጻነት የሚነጋገሩ ብቁ ፈራጆች ሁሉ፥ ከእነርሱ እጅግ ብዙዎቹ ስለ እነዚህ ነገሮች ዕብራይስጥን ወይም ዐረብኛን ከሚያውቁት የበለጠ እንደማያውቁ ሊያምኑ ይገባቸዋል። ክርስትናን ፈጽመው ለማያውቁ ለእነዚህ ታዲያ ክርስትና ምን መልካም ነገር ሊያደርግላቸው ይችላል?
7. ይሁን እንጂ በእንግሊዝም በአየርላንድም በአንዳንድ ክፍሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና በሚገባ ይታወቃል፤ በተለይም በለንደን፥ በብሪስቶል፥ በደብሊንና በሁለቱም መንግሥታት ባሉት በብዙ ሕዝብ በሚኖርባቸው ታላላቅ ከተሞችና መንደሮች ሁሉ ማለት ይቻላል። በእነዚህ ስፍራዎች የክርስትና ቅርንጫፍ ሁሉ በግልጥና በሰፊው ይሰበካል፤ በሺህ የሚቈጠሩ ሰዎችም ደግሞ በሺህ እየተጨመሩ ዘወትር «እውነት በኢየሱስ እንዳለ» ይሰማሉ፥ ይቀበሉማል። ታዲያ በእነዚህ ስፍራዎች እንኳ ክርስትና ይህን ያህል ጥቂት ውጤት ያስገኘው ስለ ምንድር ነው? በእነዚህ ስፍራዎች ሁሉ ያለው አብዛኛው ሕዝብ በጠባዩም ሆነ በኑሮው ከአፍሪካ ወይም ከአሜሪካ አረማውያን ሳይሻል አሁንም አረማውያን የሆነው ስለ ምንድር ነው? ይህ ታዲያ እንዴት ይብራራል? እኔ እንዲህ እገነዘባለሁ፦ በጥንቲቱ ቤተ ክርስቲያን በክርስቲያኖች መካከል «ነፍስና ሥጋ ሰውን ያደርጋሉ፤ መንፈስና ሥርዓት ክርስቲያንን ያደርጋሉ» የሚል የተለመደ አባባል ነበረ፤ ይህም ያለ ክርስቲያናዊ ሥርዓት እርዳታ ማንም እውነተኛ ክርስቲያን ሊሆን እንደማይችል የሚያመለክት ነው። ነገር ግን ይህ እንዲህ ከሆነ፥ ጥቂት ክርስቲያኖችን ብቻ ብናገኝ የሚያስደንቅ ነውን? ክርስቲያናዊ ሥርዓት የት አለና? በእንግሊዝ በየትኛው ክፍል (ከዚህ ሳንርቅ) ነው ክርስቲያናዊ ሥርዓት በክርስቲያናዊ ትምህርት ላይ የተጨመረው? እንግዲህ የትኛውም ትምህርት ቢሰበክ፥ ሥርዓት በሌለበት ስፍራ በሰሚዎቹ ላይ ሙሉ ውጤቱን ሊያስገኝ አይችልም።
8. ነገሩን ይበልጥ ወደ እኛ ለማቅረብ፦ በተለምዶ ሜቶዲስቶች በሚባሉት ሰዎች መካከል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና አይሰበክምን? በጠቅላላውስ አይታወቅምን? አድልዎ የሌለባቸው ሰዎች ይታወቃል ብለው ይቀበላሉ። ክርስቲያናዊ ሥርዓትስ ደግሞ በሁሉም አስፈላጊ ቅርንጫፎቹ በመደበኛነትና ያለማቋረጥ ሲሠራበት በእነርሱ ዘንድ የለምን? ከእርሱ አንዳች አስፈላጊ ክፍል ጐድሎአል ብለው የሚያስቡ ያሳዩት፤ ለረጅም ጊዜም አይጐድልም። ታዲያ ክርስቲያናዊ ትምህርትም ክርስቲያናዊ ሥርዓትም ያላቸው እነዚህ ፈጽመው ክርስቲያኖች ያልሆኑት ስለ ምንድር ነው? ሜቶዲስቶች የሚባሉት ሰዎች መንፈሳዊ ጤና ያልተመለሰው ስለ ምንድር ነው? «በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ» ሁሉ «በእኛ ዘንድ» ያልሆነው ስለ ምንድር ነው? የመጀመሪያውን ትምህርታችንን፥ የዋህና በልብ ትሑት መሆንን ከእርሱ ያልተማርነው ስለ ምንድር ነው? በሕይወት ሁኔታዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር፦ «አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን። ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ መጥቻለሁ» ማለትን ያልተማርነው ስለ ምንድር ነው? «ዓለም ለእኛ የተሰቀለበት እኛም ለዓለም የተሰቀልንበት» ያልሆንነው፥ — ለ«የሥጋ ምኞት፥ ለዓይን አምሮትና ለኑሮ ትዕቢት» የሞትን ያልሆንነው ስለ ምንድር ነው? ሁላችንም «በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር የተሰወረውን ሕይወት» የማንኖረው ስለ ምንድር ነው? ኦ! የሚቻለው እርዳታ ሁሉ ያለን እኛ «ክርስቶስ እንደ ተመላለሰ» የማንመላለሰው ስለ ምንድር ነው? ፍለጋውን እንድንከተል ምሳሌ ትቶልን አይደለምን? እኛ ግን ምሳሌውን ወይም ትእዛዙን እንመለከታለንን? በአንድ ነጥብ ብቻ ምሳሌ ለመስጠት፦ «በምድር ላይ ለእናንተ መዝገብ አትሰብስቡ» የሚለውን የተከበረ ቃል የሚመለከት ማን ነው? «የዓመፃ ገንዘብ» በሚለው ስብከት በዚህ ርእስ ላይ ከተሰጡት ሦስት ሕግጋት የመጀመሪያውን ሕግ፥ ማለትም «የቻላችሁትን ሁሉ አትርፉ» የሚለውን የሚጠብቁ ብዙዎችን ልታገኙ ትችላላችሁ። ሁለተኛውን፥ «የቻላችሁትን ሁሉ ቈጥቡ» የሚለውን የሚጠብቁ ጥቂቶችን ልታገኙ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ሦስተኛውን ሕግ፥ «የቻላችሁትን ሁሉ ስጡ» የሚለውን የሚጠብቁ ስንቶችን አግኝታችኋል? ከአምሳ ሺህ ሜቶዲስቶች መካከል ከእነዚህ አምስት መቶ ይገኛሉ ብላችሁ የምታምኑበት ምክንያት አላችሁን? ሆኖም ያለ ሦስተኛው ሕግ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ሕግጋት የሚጠብቁ ሁሉ ከቀድሞው ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሱ የገሃነም ልጆች እንደሚሆኑ ከዚህ የበለጠ ግልጥ የሆነ ነገር የለም።
9. ኦ! ከዚህ ሳልሄድና ሳልታይ፥ የቻሉትን ሁሉ ለሚያተርፉና ለሚቈጥቡ፥ ነገር ግን የቻሉትን ሁሉ ለማይሰጡ ሰዎች ድምፄን እንደ መለከት አንሥቼ እንድናገር እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ደግሞ ቢያስችለኝ! የእግዚአብሔርን ቅዱስ መንፈስ ዘወትር የምታሳዝኑት፥ የጸጋውንም ሥራ በጉባኤዎቻችን ላይ እንዳይወርድ በብዙ መጠን የምትከለክሉት እናንተ ናችሁ፤ ከእነዚያ ሰዎች ዋነኞቹ እናንተ ናችሁ። በእግዚአብሔር የተወደዱ ብዙ ወንድሞቻችሁ የሚበሉት ምግብ የላቸውም፤ የሚለብሱት ልብስ የላቸውም፤ ራሳቸውን የሚያስጠጉበት ስፍራ የላቸውም። ታዲያ እንዲህ የተጨነቁት ስለ ምንድር ነው? እናንተ የእናንተና የእነርሱ ጌታ የእነርሱን ችግር እንድታሟሉበት ብሎ በእናንተ እጅ ያኖረውን ያለ ፈሪሀ እግዚአብሔር፥ ያለ ፍትሕና በጭካኔ ስለምትከለክሉአቸው ነው! ያን በራብ የተጐዳውን፥ በብርድ የሚንቀጠቀጠውን፥ ግማሽ ራቍቱን የሆነውን ምስኪን የክርስቶስ ብልት እዩ! በዚያው ጊዜ እናንተ የዚህ ዓለም ብዙ ሀብት፥ — ምግብና መጠጥ ልብስም — አላችሁ። በእግዚአብሔር ስም እጠይቃችኋለሁ፥ ምን እያደረጋችሁ ነው? እግዚአብሔርን አትፈሩምን? ሰውንስ አታፍሩምን? እንጀራችሁን ለተራበ የማትቈርሱትና የተራቈተውን ልብስ የማታለብሱት ስለ ምንድር ነው? እነዚህን ሁለቱን ዓላማዎች ሊፈጽም የሚችለውን ዋጋው ለከበረ ለገዛ ልብሳችሁ አውጥታችሁታልን? እግዚአብሔር እንዲህ እንድታደርጉ አዘዛችሁን? እንዲህ ስላደረጋችሁስ ያመሰግናችኋልን? የእርሱን ሀብት (የእናንተን አይደለም) ለዚህ ዓላማ በአደራ ሰጣችሁን? አሁንስ፦ «የእግዚአብሔር ባሪያ ሆይ፥ መልካም አደረግህ» ይላልን? እንደማይል በሚገባ ታውቃላችሁ። ይህ ከንቱ ወጪ በእግዚአብሔር ዘንድም ሆነ በገዛ ሕሊናችሁ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። እናንተ ግን አቅም አለን ትላላችሁ! ኦ! እንዲህ ያለውን ምስኪን ከንቱ ንግግር በአፋችሁ ለማውጣት እፈሩ! እንዲህ ያለውን የሞኝነት ዲስኩር፥ እንዲህ ያለውን ግልጥ ቂልነት ከቶ ደግማችሁ አትናገሩ! አንድ መጋቢ ፍጹም ወስላታ ለመሆን፥ የጌታውን ሀብት ለማባከን አቅም ሊኖረው ይችላልን? አንድ ባሪያ ጌታው ካዘዘው ሌላ በሆነ መንገድ የጌታውን ገንዘብ ለማውጣት አቅም ሊኖረው ይችላልን? ከዚህ እጅግ የራቀ ነው፤ ይህን የሚያደርግ ሁሉ ከክርስቲያን ማኅበር ሊገለል ይገባዋል።
10. «ነገር ግን በማኅበራችን ያሉትን ድሆች ሁሉ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማሟላት ይቻላልን?» ይህን ማድረግ ከዚህ በሚበልጥ ማኅበር በአንድ ወቅት ተችሎ ነበር። በኢየሩሳሌም በነበረችው በመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን «በመካከላቸው አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረም፤ ነገር ግን ማናቸውም እንደሚፈልግ መጠን ለእያንዳንዱ ያካፍሉት ነበር።» አሁንም ደግሞ እንዲህ ሊሆን እንደሚችል ሙሉ ማስረጃ አለን። ኩዌከሮች በሚባሉት ሰዎች ዘንድ እንዲሁ ነው። አዎን፥ ሞራቪያውያን በሚባሉትም ዘንድ። ታዲያ በእኛ ዘንድ እንዲሁ የማይሆነው ስለ ምንድር ነው? «እነርሱ ከእኛ አሥር እጥፍ ሀብታሞች ስለ ሆኑ ነው።» ምናልባት አምሳ እጥፍ፤ ሆኖም እኩል ፈቃደኞች ብንሆን ይህን ለማድረግ በቂ አቅም አለን።
አንድ ጨዋ ሰው (ሜቶዲስት የሆነ) ከጥቂት ዓመታት በፊት፦ «ለልጆቼ አርባ ሺህ ፓውንድ ትቼ እሄዳለሁ» አለኝ። እንግዲህ ሀያ ሺህ ብቻ ትቶላቸው ሌላውን ሀያ ሺህ ለእግዚአብሔርና ለድሆች ቢሰጥ ኖሮ፥ እግዚአብሔር፦ «አንተ ሰነፍ» ይለው ነበርን? ይህም ማኅበሩን ሁሉ ከችግር እጅግ ከፍ ያደርገው ነበር።
11. ነገር ግን ሀብታችሁን እኩሌታ ለእግዚአብሔር ስለ መስጠት ወይም ስለ መተው አልናገርም። ይህ ለመንግሥተ ሰማያት እጅግ ውድ ዋጋ ነው ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ወደ ዝቅተኛ ሁኔታዎች እወርዳለሁ። በመካከላችሁ መቶ ፓውንድ ሊሰጡ የሚችሉ ጥቂቶች፥ ምናልባትም ሺህ ፓውንድ ሊሰጡ የሚችሉ አንዳንዶች፥ ሆኖም ለልጆቻቸው የራሳቸውን መዳን እንዲፈጽሙ የሚረዳቸውን ያህል ሊተዉላቸው የሚችሉ የሉምን? በሁለት ሺህ ፓውንድ፥ ከዚያም ብዙ ባነሰ፥ የድሆቻችንን ሁሉ የአሁኑን ችግር ልናሟላ፥ ወደ ፊትም የራሳቸውን ችግር የሚያሟሉበትን መንገድ ልናዘጋጅላቸው እንችላለን። እንግዲህ ይህ ሊደረግ ይቻላል ብንል፥ ሳይደረግ ሳለ በእግዚአብሔር ፊት ንጹሓን ነንን? ይህን ቸል ማለታችሁ በእናንተ ዘንድ ብዙዎች፥ በነፍስም በሥጋም፥ አሁንም የታመሙና የደከሙ ከሆኑበት ምክንያቶች አንዱ አይደለምን? የዓለምን ፋሽን ከእግዚአብሔር ትእዛዛት በማስበለጥ አሁንም መንፈስ ቅዱስን የሚያሳዝኑበትስ? እኛ ሰባኪዎችም በተወሰነ መጠን የኃጢአታቸው ተካፋዮች እንዳልሆንን ብዙ ጊዜ እጠራጠራለሁ። አንድ ዓይነት አድልዎ እንዳይሆን እጠራጠራለሁ። እነርሱን በማኅበራችን ማኖራችን ታላቅ ኃጢአት እንዳይሆን እጠራጠራለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን በመቃወም መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ በማበረታታት ነፍሳቸውን ሊጐዳ አይችልምን? በተወሰነ መጠንስ የተባረከው መንፈስ በማኅበረሰቡ ሁሉ ላይ የሚያሳድረውን ጠቃሚ ሥራ ሊያግድ አይችልምን?
12. ተጨንቄአለሁ። ምን እንደማደርግ አላውቅም። በአንድ ወቅት ማድረግ የምችለውን አያለሁ። በቁርጥና በግልጥ እንዲህ ማለት እችል ነበር፦ «እነሆኝ፤ እኔና መጽሐፍ ቅዱሴ። ከዚህ መጽሐፍ በታላቅም ሆነ በትንሽ ነገር አልወጣም፥ ለመውጣትም አልደፍርም። በውስጡ ካለው አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ለመተው ሥልጣን የለኝም። የመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን ለመሆን ቈርጬአለሁ፤ ጥቂት የቀረኝ ሳይሆን ፈጽሞ። በዚህ መሠረት ላይ ከእኔ ጋር የሚቆም ማን ነው? በዚህ ላይ ተባበሩኝ፤ አለዚያ ከቶ አትተባበሩኝ።» በተለይም በአለባበስ ረገድ፥ ኩዌከሮች እንደሚባሉት ሰዎች ወይም እንደ ሞራቪያ ወንድሞች ጸንቼ መቆም እችል ነበር (አሁንም እጅግ የተሻለ ይሆን እንደ ነበረ አያለሁ)፤ — እንዲህ ማለት እችል ነበር፦ «መጽሐፍ ቅዱሳዊም ምክንያታዊም እንደ ሆነ የምናውቀው አለባበሳችን ይህ ነው። ከእኛ ጋር ብትተባበሩ፥ እኛ እንደምንለብስ ልትለብሱ ይገባችኋል፤ ነገር ግን ካልወደዳችሁ ከእኛ ጋር መተባበር የለባችሁም።» ነገር ግን ወዮ! ጊዜው አሁን አልፎአል፤ አሁን ምን ማድረግ እንደምችል መናገር አልችልም።
13. ነገር ግን ወደ ዋናው ጥያቄ ልመለስ። ክርስትና በእኛ መካከል እንኳ ይህን ያህል ጥቂት መልካም ነገር ያደረገው ስለ ምንድር ነው? በሜቶዲስቶች መካከል፥ — ክርስቲያናዊውን ትምህርት ሁሉ በሚሰሙትና በሚቀበሉት፥ በዚያም ላይ በእጅግ አስፈላጊ ክፍሎቹ ክርስቲያናዊ ሥርዓት በተጨመረላቸው መካከል? በግልጥ፥ የጌታችንን፦ «በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ» የሚለውን የተከበረ ቃል ስለ ረሳን፥ ወይም ቢያንስ በሚገባ ስላልተጠነቀቅንበት ነው። ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ ቅዱስ ሰው፦ «በክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይህን ያህል የእግዚአብሔር ኃይል በመካከሉ ያለውና ይህን ያህል ጥቂት ራስን መካድ ያለው ሕዝብ ከዚህ በፊት ከቶ አልነበረም» ብሎ ተናግሮ ነበር። በእርግጥ ይህ ዋና ጕድለት ቢኖርም የእግዚአብሔር ሥራ በሚያስደንቅ ሁኔታ ወደ ፊት ይሄዳል፤ ነገር ግን ይህ ባይኖር ኖሮ በሚሄድበት መጠን ሊሄድ አይችልም፤ ሰሚዎቹም «ራሳቸውን ካልካዱና መስቀላቸውን ዕለት ዕለት ካልተሸከሙ» የእግዚአብሔር ቃል ሙሉ ውጤቱን ሊያስገኝ አይችልም።
14. ሜቶዲስቶች በጠቅላላው ክርስቲያናዊ ራስን መካድን በመለማመድ በስንት ረገድ በሚያሳዝን ሁኔታ ጐዶሎ እንደ ሆኑ ማሳየት ቀላል ነው፤ በእርግጥም ከዚህ በአንቲኖሚያኖች የሞኝነት ጩኸት ዘወትር እንዲሸሹ ተደርገዋል። በአንድ ብቻ ምሳሌ ለመስጠት፦ በኦክስፎርድ በነበርን ጊዜ የእያንዳንዱ ሜቶዲስት ሕግ (በሕመም ጊዜ ካልሆነ በቀር) ከፍ ያለ አክብሮት ያላቸውን የጥንቲቱን ቤተ ክርስቲያን በመምሰል በዓመቱ ውስጥ በየረቡዑና በየዓርቡ መጾም ነበር። እንግዲህ ይህ የጥንቲቱ ቤተ ክርስቲያን ልማድ መሆኑን ሁሉም ይቀበላሉ። የጥንት ጸሐፊ የሆነው ኤጲፋንዮስ፦ «የሳምንቱ የአራተኛውና የስድስተኛው ቀን ጾም» (ረቡዕና ዓርብ) «በዓለም ሁሉ በክርስቲያኖች እንደሚጠበቅ የማያውቅ ማን ነው?» ይላል። ሜቶዲስቶችም ለብዙ ዓመታት እንዲሁ ይጠብቁአቸው ነበር፤ ሁሉም ያለ አንዳች ልዩነት፤ በኋላ ግን በለንደን አንዳንዶች ይህን ከልክ በላይ አድርገው ጤናቸውን እስኪጐዱ ድረስ ጾሙ። ሌሎችም ይህን ምክንያት አድርገው ከቶ ላለመጾም ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። አሁንም በእንግሊዝም በአየርላንድም ይህንኑ ክፉ ምሳሌ በመከተል መጾምን ፈጽመው የተዉ፥ ሜቶዲስቶች የሚባሉ በሺህ የሚቈጠሩ እንዳሉ እፈራለሁ፤ እነርሱም (ጥብቆቹ ፈሪሳውያን ሁሉ እንዳደረጉት) በሳምንት ሁለት ጊዜ ከመጾም እጅግ ርቀው በወር ሁለት ጊዜ እንኳ አይጾሙም። አዎን፥ ከእናንተ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ መጨረሻው አንድ ቀን እንኳ የማትጾሙ አንዳንዶች የሉምን? ነገር ግን ለዚህ ምን ምክንያት ሊኖር ይችላል? የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አባላት ነን ለሚሉት ብቻ አልልም፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነ እናምናለን ለሚሉ ሁሉ። እንደ እርሱ ከሆነ፥ ከቶ የማይጾም ሰው ከቶ ከማይጸልይ ሰው የበለጠ በመንግሥተ ሰማያት መንገድ ላይ አይደለምና።
15. ነገር ግን የስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን አባላት ዘወትር፥ በተለይም በቅዱስ ቍርባን ወቅቶቻቸው እንደሚጾሙ ማንም ሊክድ ይችላልን? በአንዳንድ ደብሮች እነዚህ ወቅቶች በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ይመጣሉ፤ በሌሎች ግን፥ ለምሳሌ በታላላቅ ከተሞች፥ በዓመት ሁለት ጊዜ ወይም ሦስት ጊዜ እንኳ ይሆናሉ። እንግዲህ የጌታ እራት ከመሰጠቱ በፊት ባለው ሳምንት ሁልጊዜ የጾም ቀን እንዳለ በሚገባ ይታወቃል። ነገር ግን በአንድ አጋጣሚ በአንዱ የቤተ ክርስቲያናቸው ዕቃ ቤት የሂሳብ መዝገብ ስመለከት፥ በጾሙ ቀን ለአገልጋዮቹ ምሳ ይህን ያህል ገንዘብ ተመዝግቦ አየሁ፤ በሁሉም መዝገቦች ይኸው ዓይነት ሂሳብ እንዳለ ተነግሮኛል። ሕዝቡስ ልክ አገልጋዮቻቸው በሚጾሙበት ሁኔታ እንደሚጾሙ ጥርጥር አለን? ነገር ግን ይህ እንዴት ያለ ፌዝ ነው! በግልጥ ክርስቲያናዊ ግዴታ ላይ እንዴት ያለ ምስኪን ቀልድ ነው! ኦ! ጠቅላላ ጉባኤው ለአገሩ ክብር ቢጠነቀቅ! ግዴታውን በማስፈጸም ወይም ያንን ሂሳብ ከመዝገቦቻቸው በማስወገድ ይህን አሳፋሪ ነቀፋ ከእርሱ ያንከባልሉለት። ከእንግዲህ ወዲያ ከቶ በዚያ አይታይ! ለዘላለም ይጥፋ
16. ነገር ግን በጠቅላላው ራስን መካድ በአሁኑ ጊዜ በሜቶዲስቶች መካከል ይህን ያህል ጥቂት የሚተገበረው ስለ ምንድር ነው? እጅግ በቆዩትና በታላላቆቹ ማኅበራት እንኳ ከእርሱ እጅግ ጥቂት ብቻ የሚገኘው ስለ ምንድር ነው? ነገሮችን ይበልጥ ባስተዋልሁና ባሰብሁ ቍጥር፥ በለንደን፥ በብሪስቶል፥ በበርሚንግሃም፥ በማንችስተር፥ በሊድስ፥ በደብሊን፥ በኮርክ የዚህ ምክንያት ምን እንደ ሆነ ይበልጥ ግልጥ ሆኖ ይታየኛል። ሜቶዲስቶች እየበለጸጉ ስለሚሄዱ ይበልጥና ይበልጥ ለራሳቸው ምቾት ያደላሉ። ብዙዎቹ አሁንም በሚያሳዝን ሁኔታ ድሆች ቢሆኑም («በጋት አታውሩት፤ በአስቀሎና ጎዳናዎች አታውጁት!»)፥ ሌሎች ብዙዎች ግን በሀያ፥ በሠላሳ ወይም በአርባ ዓመታት ውስጥ መጀመሪያ ወደ ማኅበሩ ሲገቡ ከነበሩበት ሀያ፥ ሠላሳ፥ አዎን፥ መቶ እጥፍ ሀብታሞች ሆነዋል። ከእነዚህም ከአሥሩ ዘጠኙ በሀብት በጨመሩበት መጠን በጸጋ መቀነሳቸው ጥቂት ልዩነቶች ብቻ ያሉት ምልከታ ነው። በእርግጥም እንደ ሀብት ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ፥ ሌላ እንዲሆን ልንጠብቅ አንችልም።
17. ነገር ግን ይህ እንዴት የሚያስደንቅ ነገር ነው! እንዴትስ ልናስተውለው እንችላለን? ክርስትና፥ እውነተኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና፥ ከጊዜ ብዛት ራሱን የመሸርሸርና የማጥፋት ዝንባሌ ያለው አይመስልምን (ይህ ግን ሊሆን አይችልም)? እውነተኛ ክርስትና በሚስፋፋበት ስፍራ ሁሉ ትጋትንና ቍጠባን ማስገኘቱ የግድ ነውና፤ እነዚህም በተፈጥሮአዊው የነገሮች አካሄድ ሀብትን መውለዳቸው የግድ ነው! ሀብትም በተፈጥሮው ትዕቢትን፥ የዓለምን ፍቅርንና ክርስትናን የሚያጠፋውን ጠባይ ሁሉ ይወልዳል። እንግዲህ ይህን የምንከላከልበት መንገድ ከሌለ፥ ክርስትና ከራሱ ጋር የማይስማማ ነው፤ በዚህም ምክንያት በየትኛውም ሕዝብ መካከል ሊቆም፥ ለረጅም ጊዜም ሊቀጥል አይችልም፤ በጠቅላላው በሚሰፍንበት ስፍራ ሁሉ የገዛ መሠረቱን ይንዳልና።
18. ነገር ግን ይህን የምንከላከልበት መንገድ የለምን? — ክርስትናን በአንድ ሕዝብ መካከል የምናስቀጥልበት? ትጋትና ቍጠባ ሀብትን ማስገኘታቸው የግድ ነው ብንቀበል እንኳ፥ ሀብት ባለ ሀብቶቹን ሃይማኖት እንዳያጠፋ የምንከለክልበት አንዳች መንገድ የለምን? እኔ የማየው አንድ የሚቻል መንገድ ብቻ ነው፤ የሚችል ሌላ ያግኝ። የቻላችሁትን ሁሉ ታተርፋላችሁን? የቻላችሁትንስ ሁሉ ትቈጥባላችሁን? እንግዲያስ በነገሮች ተፈጥሮ መበልጸጋችሁ የግድ ነው። ታዲያ ከገሃነም ፍርድ ለማምለጥ አንዳች ፍላጎት ካላችሁ፥ የቻላችሁትን ሁሉ ስጡ፤ አለዚያ ስለ እናንተ መዳን ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ መዳን ካለኝ የበለጠ ተስፋ ሊኖረኝ አይችልም።
19. ከምመክረው በላይ እንደማላደርግ እግዚአብሔርን በነፍሴ ላይ ምስክር አድርጌ እጠራለሁ። እግዚአብሔር ይመስገን፥ የቻልሁትን ሁሉ አተርፋለሁ፥ እቈጥባለሁ፥ እሰጣለሁም። የእግዚአብሔርም እስትንፋስ በአፍንጫዬ እስካለ ድረስ እንዲሁ እንደማደርግ በእግዚአብሔር እታመናለሁ። ታዲያ ምን ይሁን? ስለ ጌታዬ ስለ ኢየሱስ ከሁሉ ስለሚበልጥ እውቀት ሁሉን እንደ ጉዳት እቈጥራለሁ! አሁንም፥
«ሌላውን ልመና ሁሉ እተዋለሁ፥ —
ጌታ ሆይ፥ እኔ የተፈረደብኝ ነኝ! አንተ ግን ሞተሃል!»
ደብሊን፥ ጁላይ 2 ቀን 1789።