ምዕራፍ 38 · 18 ደቂቃ ንባብ · 23 ደቂቃ ማዳመጥ
የመንፈስ ማደር፣ የአማኞች ሁሉ የጋራ መብት
ዮሐንስ 7:37–39 — «ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ ‹ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል› ብሎ ጮኸ። (ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ።»
የክርስቶስን መስቀል ከዚህ የበለጠ ከንቱ ያደረገው ነገር የለም፤ ለደካሞች አእምሮም ከዚህ የበለጠ እንቅፋትና የማሰናከያ ዓለት የሆነ ነገር የለም፤ ይኸውም አሁን በመካከላችን ተስፋፍቶ ያለው ግምት ነው፤ ግምቱም በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ውስጥ ያለው አብዛኛው ነገር የታሰበው ለጌታችን ለመጀመሪያዎቹና ለቅርብ ተከታዮቹ ብቻ ነው፤ ስለዚህም የተዘጋጀው ለአንድ ወይም ለሁለት መቶ ዓመታት ብቻ ነበር የሚል ነው። በዚህም የተነሣ ብዙዎች አሁን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት፣ መከራ፣ ሞትና ትንሣኤ የቄሣር «ማስታወሻዎች» ወይም የእስክንድር «ድሎች» በሚነበቡበት ዓይነት ያነቡታል፤ ይህም በእኛ ውስጥና በእኛ አማካይነት እንደ ገና እንዲፈጸሙ የታሰቡ ሳይሆኑ ይልቁን ለአሳብ ማብሰልሰያ ብቻ እንዲሆኑ የተሰጡ ነገሮች አድርገው ነው።
ይህ በጠቅላላ ስለ ወንጌል ትምህርቶች እውነት እንደ ሆነ ሁሉ፣ በተለይም የእግዚአብሔር መንፈስ በአማኞች ልብ ላይ ስለሚያደርገው አሠራር እውነት ነው፤ በቀድሞ ዘመን እንደ ነበረው በእነዚህ በመጨረሻዎቹ ቀናትም መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንደሚያስፈልገን ገና ስንጠቅስ፣ አንዳንዶች እንደ አክራሪዎችና እንደ እብዶች ይመለከቱናል፤ ሌሎች ደግሞ ሆን ብለን ሕዝቡን እንደምናታልልና የተመሠረተችውን ቤተ ክርስቲያን ሕገ ሥርዓት እንደምናናጋ አድርገው ይወነጅሉናል።
እንግዲህ እናንተው ፍረዱ፤ የዚህ ሰማያዊ ስጦታ ተካፋዮች የሆኑ የኢየሱስ እውነተኛ አገልጋዮች ድምፃቸውን እንደ መለከት የሚያነሡበት፣ ጌታ ኢየሱስ ክቡር ደሙን ያፈሰሰላቸው ነፍሳት እንዲጠፉ የማይወዱ ከሆነም፣ መንፈስ ቅዱስ በዘመናት ሁሉ ላሉ አማኞች ሁሉ የጋራ መብትና ዕድል ፈንታ እንደ ሆነ፣ እኛም እንደ መጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በእውነት የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ከመጠራታችን በፊት መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንዳለብን በሙሉ ድፍረት የሚያውጁበት ጊዜ አሁን አይደለምን?
ስለዚህ ምክንያት (ደግሞም ቤተ ክርስቲያናችን የአሁኑን በዓል [በዓለ ሃምሳን] ስትወስን የነበራትን ዓላማ እፈጽም ዘንድ) የዚህን ክፍል ቃላት መርጫለሁ።
እነዚህ ቃላት የተነገሩት ኢየሱስ ክርስቶስ በዳስ በዓል በነበረ ጊዜ ነው። ጌታችን በጠቅላላ በመቅደሱ አገልግሎት፣ በተለይም በአይሁድ ቤተ እምነት በዓላት ይገኝ ነበር። አሁን የተገኘበት በዓል የዳስ በዓል ነበረ፤ አይሁድም በድንኳን ይኖሩ የነበረበትን ዘመን ለማሰብ እግዚአብሔር እንደ ወሰነው ያከብሩት ነበር። በዚህ በዓል በመጨረሻው ቀን ብዙ ቀናተኛ ሰዎች ከአንድ የታወቀ ስፍራ ውኃ ቀድተው በራሳቸው ተሸክመው ማምጣት ልማዳቸው ነበረ፤ ይህንንም ከኢሳይያስ የተወሰደውን ይህን መዝሙር እየዘመሩ ያደርጉት ነበር፦ «ከመድኃኒት ምንጮች ውኃን በደስታ ትቀዳላችሁ።» ጌታችንም ይህን ተመልክቶ፣ ያገኘውን ነገር ሁሉ መንፈሳዊ ትርጉም መስጠት የዘወትር ልማዱ ስለ ነበረ፣ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦ «ማንም የተጠማ ቢኖር (ወደዚያ ምንጭ ሳይሆን) ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ (እግዚአብሔር ከደረቅ ዓለት ውኃ ያፈልቃል፣ እና የመሳሰሉት በተባሉበት ስፍራ) የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል።» አዳኛችን በዚህ በሕያው ውኃ ምን ማለቱ እንደ ሆነ እናውቅ ዘንድም ወንጌላዊው ወዲያውኑ እንዲህ ሲል ይጨምራል፦ «ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ።»
በሚቀጥለው ንግግሬ በዋናነት የማተኩረው በመጨረሻዎቹ ቃላት ላይ ነው፤ ደግሞም
በመጀመሪያ፣ «መንፈስ» በሚለው ቃል ምን እንደሚገለጽ ባጭሩ አሳያለሁ።
በሁለተኛ ደረጃ፣ ይህ መንፈስ የአማኞች ሁሉ የጋራ መብት እንደ ሆነ፤
በሦስተኛ ደረጃ፣ ይህ ትምህርት የተመሠረተበትን ምክንያት አሳያለሁ። ደግሞም
በመጨረሻ፣ መንፈስን ልንቀበል የምንችልበት ብቸኛ መንገድ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ እንድታምኑ በሚያሳስብ ጠቅላላ ምክር እደመድማለሁ።
በመጀመሪያ፣ «መንፈስ» በሚለው ቃል ምን እንደሚገለጽ ማሳየት አለብኝ።
«መንፈስ» ሲል በግልጽ የሚያመለክተው ዘላለም ብሩክ በሆነው በቅድስት ሥላሴ ውስጥ ሦስተኛው አካል የሆነውን፣ ከአብና ከወልድ ጋር በባሕርይ አንድ የሆነውንና በዘላለማዊነት የተካከለውን፣ ከሁለቱም የሚሠርፅ ሆኖ ሳለ ከሁለቱም ጋር እኩል የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ነው። ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ዕለት ሥርዓተ አምልኮ የምትጠቀምበትን ቃል ልጠቀምና፣ ስለ አብ ክብር የምናምነውን ያንኑ ስለ ወልድና ስለ መንፈስ ቅዱስም ያለ አንዳች ልዩነት ወይም አለመመጣጠን እናምናለን።
ስለዚህም ቅዱስ ዮሐንስ በመጀመሪያ መልእክቱ ምዕ. 5፣ ቁ. 7 እንዲህ ይላል፦ «በሰማይ የሚመሰክሩ ሦስት ናቸው፤ አብ፥ ቃልና መንፈስ ቅዱስ፤ እነዚህም ሦስቱ አንድ ናቸው።» ጌታችንም ሐዋርያቱን ሄደው አሕዛብን ሁሉ እንዲያስተምሩ ተልእኮ በሰጣቸው ጊዜ በአብና በወልድ ስም ብቻ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስም ስም እንዲያጠምቁ አዘዛቸው። ቅዱስ ጴጥሮስም በሐዋርያት ሥራ 5:3 ሐናንያን፦ «መንፈስ ቅዱስን ታታልል ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ?» አለው። በቁ. 4 ደግሞ፦ «እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም» ይላል። ከእነዚህ ክፍሎች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ እንደ አብና እንደ ወልድ በእውነትና በትክክል አምላክ እንደ ሆነ ግልጽ ነው። ይህ የማይነገር ምሥጢር ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የገለጠው ምሥጢር ነው፤ ስለዚህም በሙሉ ልባችን ልንቀበለው ይገባል፤ እግዚአብሔር ይዋሽ ዘንድ ሰው አይደለምና፥ ያታልልም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለምና። እንግዲህ እቀጥላለሁ፤
በሁለተኛ ደረጃ፣ መንፈስ ቅዱስ የአማኞች ሁሉ የጋራ መብት እንደ ሆነ ለማስረዳት።
ነገር ግን ተአምራትን እንድናደርግ ወይም ውጫዊ ምልክቶችንና ድንቆችን እንድናሳይ በሚያስችለን መንገድ መንፈስ ቅዱስን ስለ መቀበል የምናገር እንዳይመስላችሁ። በዚህ ትርጉም በመንፈስ ተነሣሥቻለሁ ብሎ መናገር ከተጻፈው በላይ ጠቢብ መሆን እንደ ሆነ ለተቃዋሚዎቻችን እቀበልላቸዋለሁ። እግዚአብሔር በዚህ ልዩ በሆነ መንገድ ጣልቃ የገባው፣ እንደ ሙሴ ሥርዓትና እንደ ወንጌል ሥርዓት የመጀመሪያ አመሠራረት ጊዜ፣ አዲስ መገለጥ በሚመሠረትበት ጊዜ ብቻ ካልሆነ በቀር በሌላ ጊዜ እንደ ሆነ ማስረዳት ምናልባት አይቻልም፤ እኔ በበኩሌም በዚህ ዘመን እንደነዚህ ያሉ ተአምራት እንዲደገሙ የሚያጸኑትን ሰዎች መንፈስ ከመጠርጠር ልመለስ አልችልም። ዓለም አሁን በስም ክርስቲያን ሆኗልና (ምንም እንኳ፣ እግዚአብሔር እንደሚያውቀው፣ ከኃይሉ በመካከላችን የቀረው ጥቂት ቢሆንም)፣ ኢየሱስ ወደ ዓለም ይመጣ ዘንድ ያለው መሲሕ እንደ ሆነ ለማስረዳት ውጫዊ ተአምራት አያስፈልጉም፤ የሚያስፈልገው ከቃሉ ጋር አብሮ የሚሠራው የመንፈስ ቅዱስ ውስጣዊ አሠራር ብቻ ነው።
ደግሞም፣ አንተ ሰው ሆይ፣ ተራሮችን እስክታፈልስ ወይም አጋንንትን እስክታወጣ ድረስ እምነት ቢኖርህ፣ ይልቁንም በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብትናገር፣ አዎን፣ ፀሐይንም በሰማይ መካከል እንድትቆም ብታዝዝ፣ የሚቀድሱት ጸጋዎቹ ተካፋይ ሳትሆን እነዚህ ሁሉ የመንፈስ ስጦታዎች ምን ይጠቅሙሃል? ሳኦል ሌላ ሰው እስኪሆን ድረስ ለጊዜው የአገዛዝ መንፈስ ነበረው፤ ቢሆንም ምናልባት የተጣለ ሆኖ ቀርቷል። በክርስቶስ ስም አጋንንትን ያወጡ ብዙዎችም በመጨረሻው ቀን እርሱ አላውቃችሁም ይላቸዋል። ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎች ሳይኖሩህ ስጦታዎቹ ብቻ ቢኖሩህ፣ ይበልጥ በታላቅ ግርማ ወደ ገሃነም እንድትወርድ ከማድረግ በቀር አይጠቅሙህም።
እንግዲህ በዚህ ነጥብ ከተቃዋሚዎቻችን ጋር እንስማማለን፤ እንደ ጌታችን የመጀመሪያ ሐዋርያት በዚህ ትርጉም በመንፈስ እንደማንነሣሣ በፈቃደኝነት እንቀበላለን። ነገር ግን ሰዎች የማያዩ ዓይኖችና የማይሰሙ ጆሮዎች ከሌሏቸው በቀር፣ የዚህን ክፍል የመጨረሻ ቃላት እንዴት አንብበው መንፈስ ቅዱስ በሌላ ትርጉም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የአማኞች ሁሉ የጋራ መብት እንደ ሆነ አይመሰክሩም? «ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ።» ልብ በሉ፤ ለአንድ ወይም ለሁለት ዘመን በእርሱ የሚያምኑ አላለም፤ በጠቅላላ በእርሱ የሚያምኑ፣ ማለትም በሁሉም ጊዜና በሁሉም ስፍራ የሚያምኑ ነው ያለው። ስለዚህ ቅዱስ ዮሐንስ እነዚህን ቃላት በጻፈ ጊዜ በማታለል ሥር እንደ ነበረ ማስረዳት ካልቻልን በቀር፣ በጌታ በኢየሱስ በሙሉ ልባችን ካመንን እኛም ደግሞ መንፈስ ቅዱስን እንደምንቀበል ማመን አለብን።
ደግሞም ጌታችን ከመራራ ሕማማቱ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ ስለ ተመረጠው ዓለም ኃጢአት ነፍሱን መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርብ በተዘጋጀ ጊዜ፣ ልቡ እጅግ በተከፈተበትና ለደቀ መዛሙርቱ ከሁሉ የሚበልጠውን ስጦታ እንደሚለምን ጥርጥር በሌለበት ሰዓት፣ እንዲህ ብሎ ይጸልያል፦ «ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፥ አባት ሆይ፥ አንተ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ እንዳለሁ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ እንዲሆኑ፥ እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ»፤ ይህም ማለት እውነተኛ ተከታዮቹ ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስና በአብ መካከል እንደ ነበረው ያለ እውነተኛ፣ ሕያውና ምሥጢራዊ በሆነ አንድነት በቅዱስ መንፈሱ ከእርሱ ጋር እንዲተባበሩ ነው። እውነተኛ ተከታዮቹ ሁሉ እላለሁ፤ ይህን ጸሎት ሲያቀርብ እኛንና አማኞችን ሁሉ በአሳቡ ይዞ እንደ ነበረ ከጌታችን ከራሱ ቃላት ግልጽ ነውና፦ «ስለ እነዚህም ብቻ አልለምንም፥ በእኔ ስለሚያምኑ ሁሉ ደግሞ እንጂ» — በቃላቸው አማካይነት ስለሚያምኑ፤ ስለዚህ ሊቃነ ካህናቱ እንዳደረጉት ጌታችንን እንደ ተሳዳቢ ካልቈጠርነው በቀር፣ በቃሉ ወይም በአገልጋዮቹ አገልግሎት በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች በመሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲተባበሩ መሆናቸውን ልንመሰክር ይገባናል።
በቅርቡ «ኤንቱዚያስት» (አክራሪ) በሚለው ቃል ዙሪያ ታላቅ ጩኸት ተነሥቷል፤ ቃሉም እንደ ስድብ መጠሪያ በወንጌል ሰባኪዎች ላይ ተወርውሯል፤ ነገር ግን ክርስቲያን ሁሉ በቃሉ ትክክለኛ ትርጉም ኤንቱዚያስት መሆን አለበት፤ ይህም ማለት በእግዚአብሔር መነሣሣት አለበት፣ ወይም እግዚአብሔርን በመንፈሱ በውስጡ ሊኖረው ይገባል ማለት ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች እንድንሆን የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋ ተሰጥቶናል» ይለናል፤ ጌታችንም፦ «አብና እርሱ አንድ እንደ ሆኑ እኛም አንድ እንድንሆን» ብሎ ይጸልያል፤ የገዛ ቤተ ክርስቲያናችንም ከእነዚህ የመጽሐፍ ቃላት ጋር ተስማምታ በግሩሙ የቍርባን ሥርዓቷ፣ ቍርባኑን በሚገባ የሚቀበሉ «በክርስቶስ እንደሚኖሩ፣ ክርስቶስም በእነርሱ እንደሚኖር፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ እንደ ሆኑ፣ ክርስቶስም ከእነርሱ ጋር አንድ እንደ ሆነ» ትነግረናለች። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ስማቸው እንደ ክፉ ነገር ሊጣል፣ በተለይም አገልጋዮች መንፈስ ቅዱስን በመቀበል በእውነት ከእግዚአብሔር ጋር መተባበር እንዳለብን ስለሚያረጋግጡ እንደ ሕዝብ አሳሳቾች ሊቈጠሩ ግድ ሆኗል። ሰማያት ሆይ፥ በዚህ ተደነቁ!
በእርግጥ የፊደል ብቻ ምሁራን የሆኑ ሰባኪዎቻችን ሁሉ ይህን ትምህርት በግልጽ ቃል ይክዱታል አልልም፤ ቢሆንም በተግባር ይክዱታል፤ በውስጥ የሚሰማን ስሜት በይፋ ይቃወማሉና፣ የእግዚአብሔርንም መንፈስ ሳይሰማን ሊኖረን ይችላል ይላሉ፤ ይህም በእውነቱ ነገሩን ራሱን መካድ ነው። የወንጌልን እድገት ለማሰናከልና የጨለማን መንግሥት ለማጽናት ብፈልግ ኖሮ፣ ለሰዎች የእግዚአብሔር መንፈስ ኖሮአቸው ሳይሰማቸው ሊቀር እንደሚችል እየነገርኋቸው እዞር ነበር።
ነገር ግን ወደ ጉዳዩ ልመለስ፤ ጌታችን ወደ አባቱና ወደ አባታችን፣ ወደ አምላኩና ወደ አምላካችን ሊያርግ በተዘጋጀ ጊዜ ለሐዋርያቱ ይህን ተልእኮ ሰጣቸው፦ «ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።» በዚህም ተልእኮ ሥልጣን መሠረት በዚህና በቤተ ክርስቲያን ዘመን ሁሉ እናስተምራለን፣ እናጠምቃለንም። ቃላቱንም «በስም እያጠመቃችኋቸው» ብለን ብንተረጕማቸውም፣ በጌታ ጸሎትና በሌሎች በብዙ ስፍራዎች የእግዚአብሔር ስም ባሕርዩን የሚያመለክት እንደ ሆነ፣ እንዲህ ተብለውም ሊተረጐሙ በተቻለ ነበር፦ «ወደ አብ ባሕርይ፣ ወደ ወልድ ባሕርይ፣ ወደ መንፈስ ቅዱስም ባሕርይ እያጠመቃችኋቸው።» ስለዚህ ጥምቀታችን ለመዳን የሚሠራ ከመሆኑ በፊት ሁላችን ወደ መንፈስ ቅዱስ ባሕርይ መጠመቅ ካለብን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት እናምናለን ለማለት ከመቻላችን በፊት ሁላችን በእርግጥ መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንዳለብን ግልጽ ነው። እንዲህ መንፈስ ቅዱስን የተቀበለ ካልሆነ በቀር ማንም ኢየሱስ ጌታዬ ነው ሊል አይችልምና።
ይህን ትምህርት፣ ቢቻል፣ ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ሌሎች ብዙ ጥቅሶችን መጥቀስ በተቻለ ነበር፤ ነገር ግን ራሳቸውን አባላት ብለው የሚጠሩ ማናቸውም፣ ይልቁንም በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ሰባኪዎች የሆኑ ብዙዎች፣ በዚህ ትምህርት ላይ ከንፈራቸውን እንኳ ለመክፈት እንዴት እንደሚደፍሩ እደነቃለሁ። ይሁን እንጂ — በኀዘን እናገረዋለሁ፣ እግዚአብሔር ፈራጄ ነው — የተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ከማናቸውም ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተለዩ ሰዎች ይልቅ በአብዛኛው ይህን የማያውቁ ይመስላሉ።
ነገር ግን የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ምን ስታደርጉ ኖራችኋል? የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓተ አምልኮ የምትቀበሉና የምትጠቀሙበት ሆናችሁ ሳለ መንፈስ ቅዱስ የአማኞች ሁሉ ዕድል ፈንታ መሆኑን የምትክዱ ከሆነ፣ ልባችሁ ከንፈራችሁን ስንት ጊዜ ሐሰተኛ አደረገው? ስንት ጊዜስ የሰነፎችን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረባችሁ፣ ጸሎታችሁም ወደ ኃጢአት ተለወጠ? በዕለታዊው የሥርየት ቃል አገልጋዩ ሕዝቡ «እግዚአብሔር ንስሐንና መንፈስ ቅዱሱን እንዲሰጣቸው» እንዲጸልዩ ይመክራል፤ በገና ዕለት ኮሌክት ጸሎት «በመንፈስ ቅዱሱ በየዕለቱ እንዲያድሰን» እግዚአብሔርን እንለምናለን፤ ባለፈው ሳምንት ኮሌክት ጸሎት «በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት ለዘላለም ደስ እንዲለን» ጸለይን፤ በየዕለቱም በምናቀርበው የመደምደሚያ ጸሎት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ሳይሆኑ «የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት» ለዘላለም ከሁላችን ጋር እንዲሆን እንጸልያለን።
ደግሞም ለአንዳንዶች የተቀደሰ ወቅት አሁን እየቀረበ ነው፤ የፋሲካን ቀናት ማለቴ ነው፤ በእነርሱም መጨረሻ ለዲቁና ማዕረግ የሚሾሙ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊትና በጉባኤው ፊት «ያን አገልግሎት በላያቸው ይወስዱ ዘንድ በውስጣቸው በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተነሣሡ እንደሚታመኑ» ይናገራሉ፤ ለክህነት ለሚሾሙትም ጳጳሱ እነዚህን የተቀደሱ ቃላት ይደግማል፦ «በእጃችን መጫን አሁን ለእነርሱ አደራ የተሰጠውን መንፈስ ቅዱስን አንተ ተቀበል።» ይሁን እንጂ — ምነው ይህን የምናገርበት ምክንያት ባልኖረኝ! — ሥርዓቶቻችንን የሚጠቀሙ ብዙዎችና ይህን መልካም ምስክርነት የመሰከሩ ብዙዎች፣ አሁን መንፈስ ቅዱስን መቀበል አስፈላጊ መሆኑን በመቃወም ለመነጋገርም ለመስበክም ይደፍራሉ፤ ይህ ብቻም ሳይሆን ይህን የሚያጸኑትን እንደ እብዶች፣ አክራሪዎች፣ መለያየት ፈጣሪዎችና የተመሠረተውን ሕገ ሥርዓት አናጊዎች አድርገው በእነርሱ ላይ ይጮኻሉ።
ነገር ግን መለያየት ፈጣሪዎቹ እናንተ ናችሁ፤ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን መቅሠፍት እናንተ ናችሁ፤ ሁልጊዜ «የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ» እያላችሁ ትጮኻላችሁ፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡን በሞተ ሥነ ምግባር ደረቅ አሰር ብቻ እየመገባችሁና የሰባውን ፊሪዳ — ማለቴ የተባረከውን የእግዚአብሔር መንፈስ አሠራር ትምህርቶች — ሳታቀርቡላቸው በራብ ከኅብረታችን እያስወጣችኋቸው ነው። ችግሩ ግን ይህ ነው፤ ብዙዎቻችን በመንፈስ ቅዱስ አንመራም፤ ስለዚህም ስለ እርሱ ከልብ በመነጨ ስሜት መናገር ባንችል አያስደንቅም፤ አንቀጾቻችንን እንፈርማለን፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሹመት የምንገባበት መክፈቻ እናደርጋቸዋለን፣ ከዚያም የፈረምንባቸውን እነዚያኑ አንቀጾች የሚቃረን እንሰብካለን። ቀሳውስትን ሁሉ በዚህ በሚያስጠላ ግብዝነት መክሰስ ከእኔ ይራቅ፤ አይደለም፤ እግዚአብሔር ይመስገን፣ የተሐድሶን ትምህርቶች ለመጠበቅና በኢየሱስ እንዳለ እውነትን ለመስበክ የሚደፍሩ አንዳንዶች በመካከላችን ቀርተዋል። ነገር ግን በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽም፤ አብዛኞቹ ቀሳውስት ከአንቀጾቻችን ወድቀዋል፤ ከእነርሱም ሆነ በመጻሕፍት ከተሰጠው ከጤናማ ቃል ምሳሌ ጋር በሚስማማ አይናገሩም፤ ዕውሮችን ለሚመሩ ለእንደነዚህ ያሉ ዕውሮች ወዮላቸው! «ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?» ከእግዚአብሔር ጽድቅ ፍርድ ሊጠብቃችሁ የሚችለው ትምህርታችሁ ሁሉ (በውሸት እውቀት የተባለው) አይደለም፤ ሹመታችሁ ሁሉም አይደለም። ገና ጥቂት ጊዜ ነው፤ ሁላችንም በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለን፤ በዚያ፣ በዚያ እገናኛችኋለሁ፤ በዚያ ታላቁ እረኛና የነፍሳት ጠባቂ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐሰተኞች ነቢያት እነማን እንደ ሆኑ፣ የበግ ለምድ የለበሱ ተኵላዎች እነማን እንደ ሆኑ ይወስናል፤ አሁን መንፈስ ቅዱስን መቀበልና መሰማት አለብን የሚሉት ናቸውን? ወይስ ይህን የአጋንንት ትምህርት ነው ብለው የሚጮኹበት?
ነገር ግን ከዚህ በላይ መናገር አልችልም፤ ማናቸውንም የሰዎች ወገን፣ በተለይም በአገልግሎት ያሉትን መንቀፍ ደስ የማያሰኝ ሥራ ነው፤ ከግድ በቀር ሌላ ምንም ሊያስተባብለው አይችልም፤ ያ ግድ ጌታችንን ራሱን በጸሐፍትና በፈሪሳውያን፣ በአይሁድ ቤተ እምነት የፊደል ብቻ ምሁራን በሆኑ አለቆችና አስተማሪዎች ላይ ብዙ ወዮታዎችን እንዲናገር ያስገደደው ነው፤ በእውነትም ሰዎች እውቀት በማጣት ሲጠፉ ማየትን ብችል፣ የእውነተኛውን እውቀት መክፈቻ ከእነርሱ ለሚከለክሉት ግን ዝም ብል፣ ድንጋዮቹ ራሳቸው ይጮኹ ነበር።
ቤተ ክርስቲያንን ወደ ቀድሞ ክብሯ ልንመልሳት ብንወድ፣ ብቸኛው መንገድ የክርስቶስን ትምህርትና የፈረምንባቸውን አንቀጾች መኖርና መስበክ ነው፤ ያን ጊዜ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተለዩ ሰዎች ቍጥር በየዕለቱ እየቀነሰ እንደሚሄድ፣ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያንም የምድር ሁሉ ደስታ እንደምትሆን እናገኛለን።
በሦስተኛ ደረጃ የዚህን ትምህርት ምክንያታዊነት ማሳየት አለብኝ።
የዚህ ትምህርት ምክንያታዊነት እላለሁ፤ ለፍጥረታዊ ሰው ሞኝነት ቢመስልም፣ መልካሙን የሕይወት ቃል ለቀመሱና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል ለተሰማቸው ግን በከፍተኛው ምክንያት ላይ የተመሠረተ ሆኖ ይታያቸዋልና፤ የሚያዩ ዓይኖች ላሏቸውም ማረጋገጫ እንኳ ሊቀርብለት ይችላል፤ ማረጋገጫ እላለሁ፤ የወደቅን ፍጥረታት መሆናችንን፣ ወይም የመጽሐፍን አነጋገር ልጠቀምና፣ «ሁላችን በአዳም መሞታችንን» በሚገልጸው ራሱን በራሱ በሚያስረዳ እውነት ላይ ቆሟልና።
በእርግጥ አሁን በመካከላችን የውርስ ኃጢአትን ትምህርት እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት መካድ ያልተለመደ ነገር እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ ነገር ግን የሚክዱት አስቀድመው የቅዱሳት መጻሕፍትን ሥልጣን ማስተባበል ይገባቸዋል፤ አንተ የማታምን ሆይ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ብለን የምንጠራው መጽሐፍ የእግዚአብሔርን ሕያዋን ቃሎች እንደማይዝ ማስረዳት ብትችል፣ የጥንት ቅዱሳን ሰዎች ይህን መጽሐፍ በውስጣቸው በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው እንዳልጻፉት ማሳየት ብትችል፣ ያን ጊዜ የውርስ ኃጢአትን ትምህርት እንተዋለን፤ ይህን ማድረግ ካልቻልክ ግን ሁላችንም በኃጢአት ተፀንሰን በኃጢአት እንደ ተወለድን አጥብቀን እንናገራለን፤ ሌላ ምክንያት ባይኖር እንኳ ስለዚህ አንድ ምክንያት፣ ሊዋሽ የማይችለው እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ነግሮናልና።
ነገር ግን ብርሃን ከጨለማ ጋር፣ ወይም የሠለጠኑ ከሓዲዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ምን ጕዳይ አላቸው? ወዮ! ለኃይሉ እንግዶች እንደ ሆኑ ሁሉ በአብዛኛው ለእግዚአብሔር ቃልም እንዲሁ ፍጹም እንግዶች ናቸው። ስለዚህ ልንሰብክላቸው ብንወድ ወደ ልብና ከልብ መስበክ አለብን፤ በመጽሐፍ ቋንቋ ለእነርሱ መናገር በማይታወቅ ልሳን እንደ መናገር ብቻ ነውና። እንግዲህ አንተ ሰው ሆይ፣ ማንም ብትሆን፣ የውርስ ኃጢአትን ትምህርት የምትክድ ሆይ፣ ሕሊናህ በጋለ ብረት እንደ ተጠበሰ ካልሆነ ንገረኝ! በተፈጥሮህ የአውሬና የዲያብሎስ ዝብርቅ ቅልቅል እንደ ሆንህ በራስህ ውስጥ አታገኝምን? ንገረኝ! እነዚህ ቃላት በልብህ ያለውን ፈሪሳዊነት ሁሉ እንደሚያነሣሡ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ሰይጣን ከዚህ ስፍራ እያጣደፈ አይውሰድህ፤ ጥቂት ቆም በልና እንዋቀስ፤ በተፈጥሮህ ወደ ትዕቢት ያዘነበልህ መሆንህን አታገኝምን? አለዚያማ አሁን ለምን ተቈጣህ? ደግሞም የክፋትን፣ የበቀልንና የፍቅር ማጣትን ሁሉ ዘር በራስህ ውስጥ አታገኝምን? እነዚህስ የዲያብሎስ ጠባዮች ራሳቸው ካልሆኑ ምንድር ናቸው? ደግሞም ሁላችን በተፈጥሮ ሥጋዊ ምኞቶቻችንን አንከተልምን? እንዲመሩንስ አንፈቅድላቸውምን? ሁልጊዜ ወደ ታች እያየን፣ በእርሱ ሕያዋን ሆነን ወደምንንቀሳቀስበትና ወደምንኖርበት አምላክ ወደ ላይ ፈጽሞ አንመለከትም። ይህስ የሚጠፉ እንስሶች ባሕርይ ራሱ ካልሆነ ምንድር ነው? ስለዚህ በመንፈስ የተነሣሣ አንድ ሐዋርያ ከብዙ ጊዜ በፊት የነገረንን፣ ማለትም «ዓለምም (በተፈጥሮ) በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ» ከገዛ ልብህ እንድትመሰክር አስገድድሃለሁ፤ ቅዱስ ይሁዳ «አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች» ብሎ ከሚጠራቸው አንበልጥም፤ ምድራውያን፣ ሥጋውያንና አጋንንታውያን መሆናችንን ፍጹም በሆነ ማረጋገጫ የሚያስረዱ ጠባዮች በተፈጥሮ በሁላችን ውስጥ አሉና።
ይህም በሚሰማ መንገድ የሚገለጥ የመንፈስ ቅዱስ አሠራር የሚባል ነገር ፈጽሞ የለም ብለው በሚክዱ በእነዚያ ሐሰተኛ ክርስቲያን ነን ባዮች ላይ፣ የተባረከው መንፈስ በአማኞች ልብ ላይ የሚያደርገው አሠራር እውነተኛ መሆኑን የሚያስረዳ ሌላ ማስረጃ ይሆናል። ዲያብሎስ በማይታዘዙ ልጆች ልብ እንደሚሠራ፣ ያውም እንዲሰማ አድርጎ እንደሚሠራ ከተቀበሉ (ሐዋርያውን ውሸታም ማድረግ ካልፈለጉ በቀር ይህን መቀበል ግድ ነው)፣ መልካሙ መንፈስ ለኢየሱስ ክርስቶስ እምነት በእውነት በሚታዘዙት ላይ ያንኑ ኃይል ቢኖረው ምኑ ያስደንቃል?
እንግዲህ ሁላችን ከውድቀት ወዲህ በተፈጥሮ የአውሬና የዲያብሎስ ቅልቅል መሆናችን እውነት ከሆነ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖርና በእርሱ ደስ ለመሰኘት ከመቻላችን በፊት ሁላችን መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንዳለብን ግልጽ ነው።
በወንጌል ያለው አባካኙ ልጅ ከእሪያዎች ጋር አሰር እስኪበላ ድረስ እንዴት ወደ ዝቅተኛ ሁኔታ እንደ ወረደ፣ ናቡከደነፆርም ከበሬዎች ጋር ሣር እንዲበላ እንዴት እንደ ተባረረ ስታነቡ፣ በዚያ በከፋው ሁኔታቸው እንደምታዝኑላቸው እርግጠኛ ነኝ። ኢየሱስ ክርስቶስም በመጨረሻው ቀን ከእግዚአብሔር ዳግመኛ ላልተወለዱ ሁሉ «እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ» እንደሚላቸው ስትሰሙ፣ ልባችሁ በስውር ድንጋጤ በውስጣችሁ አይኰማተርምን? በእኛ መጠን ብቻ በጎነት ያላቸው ፍጥረታት ባሕርያቸው በጣም ከምንዛመደው ከአውሬዎች ወይም ከአጋንንት ጋር የመኖርን አሳብ እንኳ መሸከም ካልቻሉ፣ ወሰን የሌለው በጎነትና ንጽሕና ራሱ የሆነው እግዚአብሔር የሁለቱም ባሕርይ ተካፋዮች ሆነን ሳለን ከእኛ ጋር እንዴት ሊኖር ይችላል ብለን እናስባለን? ይህ ሰማይንና ገሃነምን ለማስታረቅ እንደ ማሰብ ነው።
አዳም የተከለከለውን ፍሬ በበላ ጊዜ ሸሸ፤ ከእግዚአብሔርም ተሸሸገ፤ ለምን? ዕራቁቱን ስለ ነበረ ነው፤ ስለ አለመታዘዙ የሚገባው ቅጣት ሆኖ ከእግዚአብሔር ሕይወት ተለይቶ ነበር። እንግዲህ ሁላችን በተፈጥሮ በዚያን ጊዜ እርሱ እንደ ነበረ ዕራቁታችንንና ከእግዚአብሔር ባዶ ነን፤ ስለዚህም ተለውጠን፣ ታድሰንና እንደ ገና መለኮታዊ ባሕርይን ለብሰን እስክንገኝ ድረስ እኛም ከእግዚአብሔር መሸሽ ግድ ነው።
እንግዲህ የእግዚአብሔርን መንፈስ እንድንቀበል የመገደዳችን ምክንያታዊነት ከዚህ ይታያል። በውርስ ኃጢአት ትምህርት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ስለዚህም የመንፈስ ቅዱስን አሠራር መሰማት የሚቃወሙ ሰዎች በአዳም ስለ መውደቃችን እጅግ አልፎ አልፎ፣ ወይም ቢያንስ በቸልታ ብቻ እንደሚጠቅሱ ሁልጊዜ ታገኛላችሁ፤ ይልቁንም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ማያምኑ ሰዎች ርኵሰት የሰጠውን ዘገባ በጥንት ዘመን ለነበሩት ብቻ ያደርጉታል። በተቃራኒው ግን ሁላችን እንደ ሌሎቹ በመጀመሪያው ወላጃችን ኃጢአት በደልና ውጤት ሥር በእኩል መጠን የተካተትን መሆናችን ግልጽ ነው፤ የገዛ ቤተ ክርስቲያናችንንም አንቀጽ ቋንቋ ልጠቀምና፣ «ለእግዚአብሔር ቍጣና ለዘላለም ፍርድ የሚያጋልጠንን ርኵሰት ይዘን ወደ ዓለም እንመጣለን።»
ሌላ ትምህርት ብሰብክላችሁ የገዛ ነፍሴን እበድል ነበር፤ በእግዚአብሔርና በእናንተ ፊት ሐሰተኛ ምስክር ሆኜ እገኝ ነበር፤ ሌላ ትምህርት የሚሰብክም ሁሉ፣ ምንም ያህል የከበረና የታወቀ ቢሆን፣ ማንም ቢሆን፣ ቅጣቱን ይሸከማል።
እንግዲህ ከዚህ ግልጽ ምክንያት የተነሣ፣ እኛም እንደ መጀመሪያዎቹ ሐዋርያት፣ በዚህ ትርጉም የእግዚአብሔርን መንፈስ መቀበል ያለብን ለምን እንደ ሆነ አስፈላጊነቱ ይታያል።
ታላቁ የመቀደስ ሥራ፣ ማለትም ቅዱሳን የማድረጋችን ሥራ፣ በተለይ ለመንፈስ ቅዱስ የተተወ ነውና፤ ስለዚህ ጌታችን «ሰው ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም» ይላል።
ኢየሱስ ክርስቶስ የወረደው ከኃጢአት በደል ብቻ ሳይሆን ከኃጢአት ኃይልም ሊያድነን ነው፤ የእምነት መግለጫችንን ምንም ያህል ጊዜ ብንደግምና በመንፈስ ቅዱስ እንደምናምን ለእግዚአብሔር ብንነግረውም፣ በእርሱ አማካይነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በእውነት እስክንተባበር ድረስ በእርሱ ካላመንን፣ ቤልሆር ራሱ ካለው የበለጠ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መስማማት የለንም።
እንግዲህ ወንድሞቼ ሆይ፥ ከዚህ በላይ ምን እላለሁ? ንገሩኝ፤ ከእናንተ ብዙዎቹ እስካሁን በተነገረው አልተሰናከላችሁምን? አንዳንዶቻችሁ ምንም እንኳ በጎ አሳብ ቢኖረኝ ነጥቡን ትንሽ ከልክ በላይ የገፋሁት አይመስላችሁምን? ሌሎችስ፦ ይህ እውነት ከሆነ እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል? ብለው ለመጮኽ የተዘጋጁ አይደሉምን? ይህ ሰዎችን ወደ ተስፋ መቍረጥ መንዳት አይደለምን?
አዎን፣ በቅንነት እመሰክራለሁ፤ ነው፤ ነገር ግን ወደ ምን ዓይነት ተስፋ መቍረጥ? በክርስቶስ በኩል ካለው ምሕረት ተስፋ መቍረጥ ነውን? አይደለም፤ ይህ ከቶ አይሁን፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ሳይቀበሉ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ተስፋ መቍረጥ ነው። ዛሬ የምትሰሙኝ እናንተ ሁሉ ብቻ ሳትሆኑ ዓለም ሁሉ በዚህ ተስፋ መቍረጥ ቢሞላ ምነው ብዬ እግዚአብሔርን እለምናለሁ። እመኑኝ፤ ለሥጋችሁ ሐኪሞች በየዕለቱ እንዲያደርጉ ከምትፈቅዱላቸው የበለጠ ምንም አላደረግሁም፤ ቍስል ቢኖርባችሁና በእውነት መፈወስን ብትሹ ቀዶ ጠጋኙ ሐኪም እስከ ታችኛው ጥልቀቱ ድረስ እንዲመረምረው ታዝዙታላችሁ፤ የነፍሳችሁ ሐኪምስ ያንኑ ነጻነት ሊፈቀድለት አይገባውምን? አደጋችሁን አሳምኜ ፈውስ ለማግኘት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድትሄዱ ላነሣሣችሁ የተፈጥሮ ቍስሎቻችሁን ከመመርመር በቀር ምን አደረግሁ? በእርግጥ በተቻለኝ መጠን በርኅራኄ ያዝኋችሁ፤ አሁንም ካቈሰልኋችሁ በኋላ ልፈውሳችሁ እሞክራለሁ። እንግዲህ
በመጨረሻ ደረጃ እናንተ ሁላችሁ በእምነት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድትመጡ፣ በዚህም እናንተ ደግሞ፣ አዎን እናንተ ራሳችሁ፣ መንፈስ ቅዱስን እንድትቀበሉ ልመክራችሁ ይገባኛልና፤ «ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ።»
ልደርስበት የምናፍቀው ይህ ነው፣ ይህ ነው። እስከ አሁን ሕግን ብቻ ስሰብክ ነበር፤ ነገር ግን እነሆ፥ ታላቅ ደስታ የምሥራች አመጣላችኋለሁ። ካቈሰልኋችሁ አትፍሩ፤ እነሆ፥ አሁን ለቍስሎቻችሁ ሁሉ መድኃኒት አመጣለሁ። ምንም እንኳ ወደ አውሬና ወደ ዲያብሎስ ባሕርይ የሰጠማችሁ ብትሆኑ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ብታምኑ በዚህ ክፍል ተስፋ የተሰጠውን ሕይወት ሰጪውን መንፈስ ትቀበላላችሁ፤ ወደ እግዚአብሔር ልጆች ክቡር ነጻነትም ትመለሳላችሁ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ብታምኑ እላለሁ። «በእምነት ድነናልና፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።» አንዳንድ ሰዎችም በፍጡሩ ዘንድ ብቃት ያስፈልጋል፣ የክርስቶስን ጽድቅ ከመያዛችን በፊት የገዛ ራሳችን ጽድቅ ሊኖረን ይገባል ቢሉም፣ መጽሐፍን የምናምን ከሆነ ግን መዳን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ ነው፤ በእርሱም በሙሉ ልቡ የሚያምን ሁሉ ነፍሱ እንደ ገሃነም ራሱ ጥቁር ብትሆን እንኳ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ይቀበላል። እንግዲህ እነሆ፥ በዚህ በታላቁ የበዓል ቀን ቆሜ እጮኻለሁ፤ የተጠማ ሁሉ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ይምጣና ይጠጣ። «በእርሱ የሚያምን፣ (የምንጭ ፈሳሽ ብቻ ሳይሆን ሙሉ) የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል።» ይህን የምናገረው በኢየሱስ የሚያምኑ በእርግጥ ስለሚቀበሉት ስለ መንፈስ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነውና፤ እርሱ መንገድ፣ እውነት፣ ትንሣኤና ሕይወት ነው፤ «በእርሱ የሚያምን ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል።» በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ለሰው ፊት ማድላት የለም፤ ከፍተኛውና ዝቅተኛው፣ ባለ ጠጋውና ድሃው፣ አንዱ ከሌላው ጋር፣ በእምነት ከቀረቡ በትሑት መተማመን ወደ እርሱ ሊመጡ ይችላሉ፤ ከእርሱ ሁላችን በጸጋ ላይ ጸጋ ልንቀበል እንችላለን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋንና እውነትን የተሞላ ነውና፤ በእውነተኛ እምነት ወደ እርሱ የሚመለሱትን ሁሉ ፈጽሞ ሊያድን ዝግጁ ነው። በእርግጥ በአብዛኛው ወንጌልን የሚቀበሉ ድሆች ናቸው፤ «እግዚአብሔርም በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ የዚህን ዓለም ድሆች መረጠ።» ነገር ግን ብዙ ኀያላን፣ ብዙ ባላባቶች ባይጠሩም፣ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ የሚቀል ቢሆንም፣ እናንተ ባለ ጠጎች ራሳችሁን ብትክዱና እንደ ምስኪን ኃጢአተኞች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ብትመጡ፣ ለእናንተም እንኳ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳንን አሁን በነጻ አቀርብላችኋለሁ፤ እንደ ምስኪን ኃጢአተኞች እላለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት የመውረስ መብት እንዲኖራቸው የተባረኩት «በመንፈስ ድሆች» የሆኑት ብቻ ናቸውና። ኢየሱስ ክርስቶስም ጽድቁን ከሚጠሙትና በኃጢአታቸው ሸክም ደክመውና ሸክማቸው ከብዶባቸው ከሚሰማቸው በቀር ማንንም ወደ እርሱ አይጠራም። ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኛውን ያጸድቃል፤ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ሊጠራ አልመጣም።
እንግዲህ ብቁ አይደለንም አትበሉ፤ «ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ» የሚለው ቃል የታመነና እውነተኛ፣ ሁሉም እንዲቀበሉት የተገባ ነውና፤ እናንተም ከኃጢአተኞች ዋና ብትሆኑ፣ ራሳችሁንም እንዲህ ሆናችሁ ቢሰማችሁ፣ በእውነት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው በተለይ እናንተን ሊያድን ነው። ዮሴፍ ከወኅኒ ቤት ወደ ፈርዖን ቤተ መንግሥት በተጠራ ጊዜ ራሱን ለማዘጋጀት ለተወሰነ ጊዜ እንደ ቆየ ተነግሮናል፤ እናንተ ግን የወኅኒ ልብሳችሁን ሁሉ እንደ ለበሳችሁ ኑ፤ እንደ ሆናችሁ ድሆች፣ ምስኪኖች፣ ዕውሮችና ዕራቁታችሁን ኑ፤ እግዚአብሔር አብም ተመላሹን አባካኝ ልጅ እንደ ተቀበለው በተዘረጋ እጆች ይቀበላችኋል። ዕራቁትነታችሁን በውድ ልጁ ጽድቅ በሆነው በምርጡ ልብስ ይሸፍናል፤ በመንፈሱ ማኅተም ያትማችኋል፤ በሰባው ፊሪዳ፣ ማለትም በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት ይመግባችኋል። እንግዲህ ከእናንተ አንዳንዶቹ ስላመናችሁ በሰማይ ደስታ ይሁን፤ ወደ ጌታዬ ተመልሼ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነቴን አላመኑም እንድል አታድርጉኝ። ከእንግዲህ ልባችሁን አታደንድኑ፤ ነገር ግን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱት፣ የክብር ንጉሥም ይግባ፤ እመኑኝ፤ ስለ እናንተ ወደ ወኅኒም ሆነ ወደ ሞት ለመሄድ ፈቃደኛ ነኝ፤ ያለ እናንተ ግን ወደ ሰማይ ለመሄድ ፈቃደኛ አይደለሁም። የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ድምፄን እንደ መለከት ከፍ እንዳደርግ ግድ ይለኛል። ልቤ ሞልቶአል፤ ለክቡርና ለማይሞተው ነፍሳችሁ ካለኝ ፍቅር ብዛት የተነሣ አሁን አፌ ይናገራል፤ ንግግሬን እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ መቀጠል ብቻ ሳይሆን መናገር እስኪያቅተኝ ድረስ መናገር እችል ነበር። ስለ ማንስ ተስፋ እቈርጣለሁ? አይደለም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እኔ ያለውን ጐስቋላ እንደ ማረ ሳስብ ስለ ማንም ተስፋ ልቈርጥ አልችልም፤ የክርስቶስ ነጻ ጸጋ ግን ቀድሞ ደረሰልኝ፤ በደሜ ውስጥ አየኝ፤ በአጠገቤ አለፈ፤ በሕይወት ኑር አለኝ፤ ለእኔ የበቃኝ ያው ጸጋ ለእናንተም ይበቃችኋል፤ እነሆ፥ ያው የተባረከ መንፈስ እግዚአብሔር በላከው በኢየሱስ ክርስቶስ ብታምኑ በደረቁ አጥንቶቻችሁ ሁሉ ላይ እፍ ሊል ዝግጁ ነው፤ በእርግጥ ከዚህ የሚበልጥ ጌታ — ይበልጥ ኀያል ወይም ለማዳን ይበልጥ ፈቃደኛ የሆነ — ልታምኑበት ወይም ልታገለግሉት ፈጽሞ አትችሉም፤ ጌታ ክርስቶስ ቸር ነው፣ ቀንበሩ ልዝብ ነው፣ ሸክሙም እጅግ ቀሊል ነው ማለት እችላለሁ፤ ብዙ ዓመታት ካገለገላችሁት በኋላ እንደ ሕጉ ዘመን አገልጋዮች ሊያሰናብታችሁ ቢፈቅድ፣ ጌታችንን እንወደዋለን፣ ከእርሱም አንለይም ትሉ ነበር። እንግዲህ በደለኞች ወንድሞቼ ሆይ፥ ኑ፤ ኑና በክቡር ደሙ በዋጃችሁ ጌታ እመኑ፤ በእምነት ቀና ብላችሁ የወጋችሁትን እዩት፤ እየደማ፣ እያለከለከ፣ እየሞተ እነሆ እዩት! ሁላችሁንም ሊቀበላችሁ ዝግጁ ሆኖ እጆቹን ዘርግቶ እነሆ እዩት፤ ንስሐ የገባው ወንበዴ እንዳደረገው ወደ እርሱ ጩኹ፦ ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ ሳለህ አሁን አስበን፤ እርሱም ለነፍሳችሁ፦ ብዙም ሳይቆይ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናላችሁ ይላችኋል። ክርስቶስ ያጸደቃቸውን እነርሱን ደግሞ ያከብራቸዋልና፤ ዓለም ሳይፈጠር ከአብ ጋር በነበረው በዚያ ክብር እንኳ ያከብራቸዋል። መሬት ገዝቼአለሁ ወጥቼም ላየው በግድ ያስፈልገኛል፤ ወይም ጥምድ በሬዎች ገዝቼአለሁ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ፤ ወይም ሚስት አግብቼአለሁ፣ የዓይንን ምኞትና የሕይወትን ትዕቢት በትጋት በመከተል ተጠምጃለሁ፣ ስለዚህ ልመጣ አልችልም አትበሉ። ስማችሁ እንደ ክፉ ነገር እንዳይጣል ወይም ስለ ክርስቶስ ብላችሁ እንደ ሞኝ እንዳትቈጠሩ አትፍሩ፤ ገና ጥቂት ጊዜ ነው፤ እንደ ጠፈር ከዋክብትም ለዘላለም ታበራላችሁ። ብቻ እመኑ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ጥበብ፣ ጽድቅ፣ ቅድስናና የዘላለም ቤዛነት ይሆንላችኋል፤ ሥጋችሁ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል ይለወጣል፤ ነፍሳችሁም የእግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ተካፋይ ትሆናለች።
ለዚህም አምላክ ከወሰን የሌለው ምሕረቱ፣ ወዘተ።