ምዕራፍ 20 · 28 ደቂቃ ንባብ · 37 ደቂቃ ማዳመጥ
ትምህርት 18. ለኃጢአተኞች የሚሰጡ መመሪያዎች
ትምህርት 18.
ለኃጢአተኞች የሚሰጡ መመሪያዎች።
ጥቅስ።—እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?—የሐዋርያት ሥራ 16፥30።
እነዚህ ቃላት በፊልጵስዩስ የነበረው የወኅኒ ጠባቂ ቃላት ናቸው፤ በዚያን ጊዜ በእጁ እስረኞች ሆነው ለነበሩት ለጳውሎስና ለሲላስ ያቀረበው ጥያቄ ነው። ሰይጣን እነዚህን የእግዚአብሔር ባሪያዎች ወንጌልን በመስበክ ሥራቸው በብዙ መንገድ ተቃውሞአቸው ነበር፤ ያን ያህል ጊዜም ተሸንፎና ተዋርዶ ነበር። እዚህ በፊልጵስዩስ ግን ድካማቸውን የሚያከሽፍበት አዲስና ለየት ያለ ዘዴ ቀየሰ። በፊልጵስዩስ የጥንቈላ መንፈስ፥ በሌላ አነጋገር የዲያብሎስ መንፈስ ያደረባት አንዲት ሴት ነበረች፤ በሟርቷም ለጌቶችዋ ብዙ ትርፍ ታመጣላቸው ነበር። ዲያብሎስ ይህችን ሴት ጳውሎስንና ሲላስን በየመንገዱ እንድትከተላቸው አደረገ፤ የሕዝቡንም ትኩረት መሳብ እንደ ጀመሩ ገብታ፦ «የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው» እያለች ትጮኽ ነበር። ይህም ማለት የሰባኪዎቹን ምክር ለመደገፍ ተነሣች፤ ለትምህርታቸው ተጨማሪ ክብደት የምትሰጥ መስላም ምስክርነቷን ጨመረች። ውጤቱም ሰይጣን የፈለገው ዓይነት ሆነ። ሕዝቡ ሁሉ ይህች ሴት ክፉና ወራዳ መሆኗን ያውቁ ነበር፤ ይህን አዲስ ስብከት ልታመሰግን ስትሞክር በሰሙ ጊዜ ተጸየፉ፥ ሁሉም አንድ ዓይነት ነው ብለውም ደመደሙ። እንዲህ ያለችውን ሰው የሐዋርያትን ስብከት እንድትቃወም ወይም በእርሱ ላይ እንድትናገር ማድረግ ምንም እንደማይጠቅመው፥ ይልቁንም ዓላማቸውን እንደሚረዳ ዲያብሎስ ያውቅ ነበር። ያ ዘዴ የሚሳካበት ጊዜ አልፎ ነበር። ስለዚህ በሌላ በኩል ዞሮ ተቃራኒውን አቋም ያዘ፤ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች እንድታመሰግናቸውና ለትምህርታቸው የረከሰ ምስክርነቷን እንድትሰጥ በማድረግ ሐዋርያት እንደ እርሷ ያሉ ሰዎች እንደ ሆኑና የእርሷም መንፈስ እንዳላቸው ሕዝቡ እንዲያስብ አደረገ፤ በዚህም ድካማቸው ሁሉ ከንቱ ሆነ። ጳውሎስም ነገሮች እንዲህ ቢቀጥሉ ፈጽሞ እንደሚሰናከልና በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያንን ሊመሠርት እንደማይችል አየ። ወደ እርሷም ዞሮ ርኩሱን መንፈስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከእርሷ እንዲወጣ አዘዘው። ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ጠፋ ባዩ ጊዜ ታላቅ ስደት አስነሡ፥ ጳውሎስንና ሲላስን ያዙ፥ ታላቅ ሁከትም አደረጉ፥ ወደ ገዢዎችም አመጡአቸው፤ ገዢዎቹም ወኅኒ እስኪያስገቡአቸውና እግሮቻቸውን በግንድ እስኪያጣብቁ ድረስ ታላቅ ጩኸት አሰሙ።
እንዲህም መነሣሣቱን ያበረዱት መሰላቸው። ነገር ግን በእኩለ ሌሊት ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ በዝማሬ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር። ለረጅም ዘመን በስድብና በመሐላ ድምፅ ሲያስተጋባ የኖረው ያ አሮጌ ወኅኒ አሁን በእግዚአብሔር ምስጋና ተሞላ፤ ያን ያህል ጸንተው የቆሙት እነዚያ ግንቦችም አሁን በጸሎት ኃይል ተናወጡ። ግንዱ ተፈታ፥ በሮቹ ተከፈቱ፥ የሁሉም እስራት ተበጠሰ። የወኅኒ ጠባቂውም ከእንቅልፉ ነቃ፤ የወኅኒውን ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ እስረኞቹ ቢያመልጡ በሕይወቱ እንደሚከፍል ያውቅ ነበርና ሰይፉን መዝዞ ራሱን ሊገድል ነበር። ጳውሎስ ግን በስውር የማምለጥ ሐሳብ አልነበረውምና ወዲያው ጮኾ እንዲህ አለው። «ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ።» የወኅኒ ጠባቂውም መብራት ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጦ ገባ፥ እየተንቀጠቀጠም መጥቶ በእስረኞቹ በጳውሎስና በሲላስ ፊት ወደቀ፤ ወደ ውጭም አውጥቶ፦ «ጌቶች ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?» አላቸው።
ባለፈው ትምህርቴ በኃጢአት ወቀሳ ሥር ላሉ ኃጢአተኞች ስለሚሰጡ የሐሰት መመሪያዎች፥ ብዙ ጊዜም ስለሚሰጣቸው የሐሰት መጽናናትና እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ስለሚቀበሉት የተሳሳተ ትምህርት በሰፊው ተናግሬአለሁ። ዛሬ ማታ ዓላማዬ የተጨነቁ ኃጢአተኞች በፍጥነትና በእውነት እንዲለወጡ ምን ዓይነት መመሪያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ማሳየት ነው። በሌላ አነጋገር፥ «እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?» ብለው ለሚጠይቁ ምን መልስ ሊሰጥ እንደሚገባ ላስረዳችሁ ነው። ይህንም ሳደርግ እንዲህ ለማድረግ አስባለሁ፦
I. ኃጢአተኞች በጥቅሱ ያለውን ጥያቄ ሲጠይቁ ሊሰጣቸው የማይገባውን መመሪያ ማሳየት።
II. ለጥያቄው ተገቢ የሆነውን መልስ ማሳየት። እንዲሁም፥
III. የተጨነቁ ኃጢአተኞች በቀላሉ የሚወድቁባቸውን በርካታ ስሕተቶች መጥቀስ።
I. ለተጨነቁ ኃጢአተኞች ሊሰጡ የማይገባቸውን መመሪያዎች ላሳይ ነው።
«እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?» ከሚለው የበለጠ አስፈላጊ ጥያቄ ከቶ ተጠይቆ አያውቅም። የሰው ልጆች «ምን እበላለሁ? ምንስ እጠጣለሁ?» ብለው ለመጠየቅ የፈጠኑ ናቸው፤ ያም ጥያቄ ያለ ብዙ አደጋ በተለያየ መንገድ ሊመለስ ይችላል። ኃጢአተኛ ግን ከልቡ «እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?» ብሎ ሲጠይቅ ትክክለኛውን መልስ መቀበሉ ወሰን የሌለው ጠቀሜታ አለው። ዛሬ ማታ ፍላጎቴ፥ እናንተ ሃይማኖተኛ ነን የምትሉ፥ ለዚህ ጥያቄ ምን መመለስ እንዳለባችሁ ልነግራችሁ፥ እናንተ ኃጢአተኞች የሆናችሁም ለመዳን ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ልነግራችሁ ነው።
1. ለኃጢአተኛ አሁንም በመራራ መርዝ በዓመፅም እስራት የሚተውን ምንም መመሪያ መስጠት አይገባም። ቢፈጽመውና በቀጣዩ ቅጽበት ቢሞት ወደ መንግሥተ ሰማያት የማያስገባውን ምንም መልስ መስጠት ተገቢ አይደለም።
2. የልብ መለወጥን፥ ወይም ቅን ልብን፥ ወይም ለክርስቶስ ከልብ መታዘዝን የማያካትት ምንም መመሪያ መስጠት አይገባም። በሌላ አነጋገር፥ በእርግጥ ክርስቲያን መሆንን የማያመለክት ምንም ነገር ተገቢ አይደለም። ከዚህ የሚያንስ ማንኛውም መመሪያ ምንም አይጠቅምም። ወደ መንግሥቱ ምንም አያቀርበውም፥ ምንም መልካም ነገር አያደርግም፤ ይልቁንም ለመዳን ሊያደርገው የሚገባውን ያንኑ ነገር እንዲያዘገይ ብቻ ያደርገዋል። ኃጢአተኛው ወዲያውኑ በግልጽ ምን ማድረግ እንዳለበት ወይም እንደሚሞት ሊነገረው ይገባል፤ ቅን የልብ ሁኔታን የማያካትት ምንም ነገር ሊነገረው አይገባም። ኃጢአተኛ ሆይ፥ ቅን ልብን የማያካትት የምታደርገው ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው። በዓመፅ እስካለህ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ብታነብም ባታነብም ኃጢአት ነው። ወደ ስብሰባ ብትሄድም ብትቀርም፥ ብትጸልይም ባትጸልይም በየቅጽበቱ ዓመፅ እንጂ ሌላ አይደለም። ኃጢአተኛ ሲጸልይና መጽሐፍ ቅዱሱን ሲያነብ እግዚአብሔርን የሚያገለግል መስሎ ራሱን መቍጠሩ ያስደንቃል። በዚህ መንግሥት ላይ ያመፀ ሰው በዓመፁ እየቀጠለና የመታዘዝ ምንም ሐሳብ ሳይኖረው የሕግ መጽሐፉን ቢያነብ፥ የመቋቋምና የጦርነት መሣሪያዎቹን አጥብቆ ይዞ ምሕረትን ቢለምን፥ ለአገሩ አገልግሎት እንደሚሰጥና ሞገስ እንዲያሳዩት ግዴታ እንደሚጥልባቸው ታስባላችሁን? አይደለም፤ ንባቡና ልመናው ሁሉ የሕግ ሰጪውንም የሕጉንም ግርማ መስደብ ብቻ ነው ትላላችሁ። እንዲሁ አንተ ኃጢአተኛ ሆይ፥ ንስሐ ሳትገባ እስካለህ ድረስ ቃሉን ብታነብና ብትጸልይም ብትተወውም እግዚአብሔርን ትሰድባለህ፥ ትዳፈረውማለህ። ሰውነትህ በየትኛውም ስፍራ ወይም አቋም ቢሆን፥ በጕልበትህ ብትሆን ወይም በእግዚአብሔር ቤት ብትሆን፥ ልብህ ቅን እስካልሆነ ድረስ፥ መንፈስ ቅዱስን እስከተቃወምህና ክርስቶስን እስከ ናቅህ ድረስ በፈጣሪህ ላይ ያመፅህ ነህ።
II. ለዚህ ጥያቄ ተገቢ የሆነውን መልስ ላሳይ ነው። «እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?»
በአጠቃላይ ቅን ልብን የሚያካትት ማንኛውንም መመሪያ ለኃጢአተኛው ልትሰጡት ወይም ማንኛውንም ነገር እንዲያደርግ ልትነግሩት ትችላላችሁ፤ እንዲረዳውና እንዲያደርገው ብታደርጉ ይድናል። የእግዚአብሔር መንፈስ ከኃጢአተኞች ጋር ሲታገል ትግሉን ባገኛቸው የአእምሮ ሁኔታ ልክ ያስማማዋል። ከእነርሱ ጋር የሚታገልበት ታላቅ ዓላማው ከመሸሸጊያቸው አስወጥቶ ወዲያውኑ ለእግዚአብሔር እንዲገዙ ማድረግ ነው። እነዚህ ተቃውሞዎች፥ ችግሮችና የአእምሮ ሁኔታዎች እንደ ሰው ልጆች ሁኔታ የተለያዩ ናቸው፤ እንደ ግለሰቦቹም ብዛት ብዙ ናቸው። የግለሰቦች ጠባይ ማለቂያ የሌለው ልዩነት አለው። በእያንዳንዱ ምን መደረግ እንዳለበትና እንዴት እንደሚለወጥ በራሱ ልዩ ስሕተቶች ላይ የተመሠረተ ነው። ስሕተቶቹን ማወቅ፥ ምን እንደሚረዳና ምን ይበልጥ በፍጹም ሊማር እንደሚያስፈልገው መረዳት፥ የእግዚአብሔር መንፈስ በሕሊናው ላይ የሚጫንበትን ነጥብ ማየትና እነዚያኑ ነገሮች በመጫን ወደ ክርስቶስ ማምጣት አስፈላጊ ነው። በብዛት የሚሰጡት መመሪያዎች የሚከተሉት ናቸው፦
1. በአጠቃላይ ኃጢአተኛን ንስሐ ግባ ብሎ መንገር ተገቢ፥ የማያሰጋና የሚስማማ መመሪያ ነው። በአጠቃላይ እላለሁ። አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ የኃጢአተኛውን ትኩረት ወደ ራሱ ኃጢአቶች ሳይሆን ወደ ሌላ ነገር የሚመራ ይመስላልና። በሐዋርያት ዘመን የሕዝቡ አእምሮ በዋነኝነት ኢየሱስ እውነተኛው መሲሕ ነውን በሚለው ጥያቄ የታወከ ይመስላል። ስለዚህ ሐዋርያት እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ለማስረዳት አብዛኛውን ትምህርታቸውን ወደዚህ ነጥብ አቀኑ። የተጨነቁ ኃጢአተኞች ምን ማድረግ እንዳለባቸው በጠየቁአቸው ጊዜ ሁሉ አብዛኛውን ጊዜ «በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን» ብለው ይመክሩአቸው ነበር። በዚህ ነጥብ ላይ አጥብቀው ጫኑ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ከእነርሱ ጋር የሚታገለው በዚህ ነበርና፥ በተለይ የሰዎችን አእምሮ ያናወጠው ርእስ ይህ ነበርና፤ ስለዚህም ሰው ለእግዚአብሔር ሲገዛ የሚያደርገው የመጀመሪያው ነገር ይህ ሳይሆን አይቀርም። በዚያ ዘመን በእግዚአብሔርና በአይሁድና በአሕዛብ መካከል የነበረው ታላቁ የክርክር ነጥብ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነውን የሚለው ነበር። የሙግቱ ነጥብ ይህ ነበር። ኃጢአተኛውን በዚህ አከራካሪ ጥያቄ እንዲገዛ ማድረግ እርሱን ለማዋረድ ከሁሉ ይበልጥ ውጤታማ መንገድ ነበር።
በሌላ ጊዜ ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ ከኃጢአተኞች ጋር የሚሠራው በዋናነት ከራሳቸው ኃጢአቶች ጋር በተያያዘ ሆኖ ይገኛል። አንዳንድ ጊዜ እንደ ጸሎት፥ ምናልባትም እንደ ቤተ ሰብ ጸሎት ባለ በአንድ ልዩ ግዴታ ይሠራባቸዋል። ኃጢአተኛው መጸለይ ይገባው እንደ ሆነ ወይም በቤተ ሰቡ ውስጥ ሊጸልይ ይገባው እንደ ሆነ በዚያ ነጥብ ከእግዚአብሔር ጋር ሲሟገት ይገኛል። ግለሰቡ በዚህ ነጥብ ሲታገል የነበረባቸውን እንዲህ ያሉ አስደናቂ ሁኔታዎች አውቃለሁ፤ ሊጸልይ በጕልበቱ እንደ ተንበረከከም ልቡን አስገዛ፤ ይህም የእግዚአብሔር መንፈስ ይሟገትበት የነበረው ነጥብ ይኸው እንደ ሆነና ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ክርክር ሁሉ የተንጠለጠለበት ማጠፊያ እርሱ እንደ ነበረ አሳየ። ያ መለወጥ ነበር።
ንስሐ ግባ የሚለው መመሪያ ሁልጊዜ ተገቢ ነው፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ውጤታማ አይሆንም፤ ኃጢአተኛው ሊነገረው የሚያስፈልገው ሌላ ነገር ሊኖር ይችላልና። ተገቢ መመሪያ በሆነበትም ስፍራ ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ መነገር ብቻ ሳይሆን ንስሐ ምን እንደ ሆነ ሊብራራላቸው ያስፈልጋል። በዚህ ርእስ ዙሪያ ብዙ ምሥጢራዊነት፥ የሐሰት ፍልስፍናና የሐሰት ሥነ መለኮት ስለ ተከመረ ለኃጢአተኞች በንስሐ ምን ማለታችሁ እንደ ሆነ ብቻ ሳይሆን ምን ማለታችሁ እንዳልሆነ መንገር አስፈላጊ ሆኗል። ቀድሞ ግልጽና በቀላሉ የሚገቡ የነበሩ ቃላት አሁን እጅግ ስለ ተጣመሙ ለኃጢአተኞች ሊብራሩ ያስፈልጋል፤ ያለዚያ ብዙ ጊዜ በአእምሮአቸው የተሳሳተ ስሜት ይፈጥራሉ። ንስሐ የሚለው ቃልም እንዲሁ ነው። ብዙዎች የሕሊና ስቃይ፥ ወይም የበደለኛነት ስሜት ንስሐ እንደ ሆነ ያስባሉ። እንግዲያስ ሲኦል በንስሐ የተሞላ ነው፤ በማይነገርና በዘላለማዊ የሕሊና ስቃይ ተሞልቷልና። ሌሎች እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጋቸው ቍጭት ይሰማቸዋል፤ ያንንም ከእርሱ ንስሐ መግባት ብለው ይጠሩታል። ነገር ግን ኃጢአትን ስለሚጸየፉ ሳይሆን በሚያስከትለው ውጤት ምክንያት ብቻ በመበደላቸው ይቈጫሉ። ይህ ንስሐ አይደለም። ሌሎች የኃጢአት ወቀሳና ብርቱ የሲኦል ፍርሃት ንስሐ እንደ ሆኑ ያስባሉ። ሌሎች የሕሊናን ተግሣጽ እንደ ንስሐ ይቈጥራሉ፤ «ምንም ክፉ ነገር ሳደርግ ንስሐ ሳልገባ አላልፍም፤ በማድረጌ ሁልጊዜ አዝናለሁ» ይላሉ። ሌሎች ንስሐን ስለ ኃጢአት የሚሰማ የሐዘን ስሜት አድርገው ይመለከቱታል። ንስሐ ግን በየትኛውም ዓይነት ወይም መጠን ያለፈቃድ የሚመጣ ስሜት አይደለም። እነዚህ ሁሉ ንስሐ እንዳልሆኑ ለኃጢአተኞች ሊገለጽላቸው ይገባል። ከከፋው ክፋት ጋር አብረው ሊኖሩ ይችላሉ ብቻ ሳይሆን ዲያብሎስ ሁሉንም ሊኖሩት ይችላል፤ ያለ ጥርጥርም ሁሉም አሉት፤ ቢሆንም ዲያብሎስ ሆኖ ይኖራል። ንስሐ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ኃጢአት ራሱ የአእምሮ መለወጥ ነው። የአመለካከት መለወጥ ብቻ ሳይሆን የነፍስ የመጨረሻ ምርጫ መለወጥ ነው። በፈቃድ የሚሆን መለወጥ ነው፤ በዚህም ምክንያት የስሜትና በእግዚአብሔርና በኃጢአት ላይ የተግባር መለወጥን ያካትታል። በማንኛውም ትኩረት የሚሻና አስፈላጊ ርእስ ላይ የአእምሮ መለወጥ ሲባል በተፈጥሮ የሚረዳው ይኸው ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው በባርነት መሻር ጉዳይ ሐሳቡን እንደ ለወጠ፥ ወይም በፖለቲካ አመለካከቱን እንደ ለወጠ እንሰማለን። በአመለካከቱ፥ በስሜቱና በምግባሩ መለወጥ እንዳደረገ ሁሉም ይረዳል። ይህ በዚያ ርእስ ላይ ንስሐ ነው፤ የአእምሮ መለወጥ ነው፤ ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር አይደለም። የወንጌል ንስሐ ከእግዚአብሔር አንጻር የፈቃድ፥ የስሜትና የሕይወት መለወጥ ነው።
ንስሐ ሁልጊዜ ኃጢአትን መጸየፍን ያመለክታል። ስለ ኃጢአት እግዚአብሔር እንደሚፈልግና እንደሚሰማው መፈለግና መሰማት ነው። በእርግጥ የእግዚአብሔርን ፍቅርና ኃጢአትን መጸየፍን ያካትታል። ሁልጊዜ ኃጢአትን መተውን ያመለክታል። ኃጢአተኞች ይህን እንዲረዱ ሊደረግ ይገባል። ንስሐ የሚገባ ኃጢአተኛ ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኞች ሃይማኖተኛ ቢሆኑ ኃጢአታቸውን ሲተዉ ሊሰማቸው ይገባል ብለው እንደሚያስቡት አይሰማውም። ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኞች ሃይማኖትን እንዲህ አድርገው ይመለከቱታል፤ መንፈሳውያን ቢሆኑ ከዳንስና ከግብዣ እንዲርቁ፥ ቲያትርን ወይም ቁማርን ወይም አሁን የሚደሰቱባቸውን ሌሎች ነገሮች እንዲተዉ ይገደዳሉ። ከእነዚያ ነገሮች ሁሉ ቢለዩ እንዴት ሊደሰቱ እንደሚችሉ አይታያቸውም። ነገር ግን ይህ ስለ ጉዳዩ ትክክለኛ አመለካከት ከመሆን እጅግ የራቀ ነው። ሃይማኖት ከሚደሰቱባቸው ነገሮች በመለየት ደስታ አያሳጣቸውም፤ በእርሱ የመጀመሪያው እርምጃ ንስሐ መግባት፥ ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ አእምሮአቸውን መለወጥ ነውና። ንስሐ የገባ ሰው ለእነዚህ ነገሮች ምንም ዝንባሌ እንደሌለው፥ እንደ ተዋቸውና አእምሮውን ከእነርሱ እንደ መለሰ የተገነዘቡ አይመስሉም። ኃጢአተኞች ልክ አሁን እንደሚፈልጉት እንደዚያ ዓይነት ስፍራዎች ለመሄድና በእንደዚያ ያሉ ትዕይንቶች ለመቀላቀል እንደሚመኙ፥ ይህም ደስታ የሚያሳጣቸው የማያቋርጥ መሥዋዕት እንደሚሆን ይሰማቸዋል። ይህ ታላቅ ስሕተት ነው።
ዝናቸውን ማጣትን ወይም እንዲህ ያለውን ነገር በመፍራት ባይገደዱ ኖሮ ወደ ቀድሞ ልማዳቸው በደስታ የሚመለሱ አንዳንድ ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ እንዳሉ አውቃለሁ። እንግዲህ ልብ በሉ። እንዲህ ከተሰማቸው ሃይማኖት ስለሌላቸው ነው፤ ኃጢአትን አይጠሉም። የቀድሞ መንገዳቸውን ቢመኙ ሃይማኖት የላቸውም፤ ንስሐም ከቶ አልገቡም፤ ንስሐ ሁልጊዜ የምርጫ፥ የአመለካከትና የስሜት መለወጥ ነውና። በእውነት ቢለወጡ ኖሮ እንዲህ ያሉትን ነገሮች ከመምረጥ ይልቅ በመጸየፍ ከእነርሱ ይመለሱ ነበር። የግብፅን የሥጋ ምንቸቶች ከመመኘትና ወደ ቀድሞ ማኅበራቸው፥ ግብዣቸው፥ ዳንሳቸውና ወደ መሰሉት ለመሄድ ከመሻት ይልቅ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ታላቅ ደስታቸውን ያገኛሉ።
2. ኃጢአተኞች ወንጌልን እንዲያምኑ ሊነገራቸው ይገባል። እዚህም ደግሞ ሊብራራላቸውና እምነት ምን እንዳልሆነ፥ ምንስ እንደ ሆነ ሊነገራቸው ያስፈልጋል። ኃጢአተኛ ወንጌልን እመን ሲባል «አምናለሁ እኮ» ከማለት የበለጠ የተለመደ ነገር የለም። እውነቱ ግን፥ ወንጌል እውነት መሆኑን አምኖ እንዲቀበል አድጓል እንጂ አያምነውም፤ ስለ ማስረጃው ምንም አያውቅም፤ እምነቱም ሁሉ ያለ ማስረጃ የሆነ ተራ መቀበል ነው። በአንድ ዓይነት ልል፥ ግልጽ ባልሆነ ትርጕም እውነት እንደ ሆነ ይቀበለዋል፤ ስለዚህም ሁልጊዜ «መጽሐፍ ቅዱስን አምናለሁ እኮ» ለማለት ዝግጁ ነው። በእርግጥ በሚያምኑአቸው ነገሮች እንደሚያደርጉት በእነዚህ እውነቶች ላይ ከቶ እንዳልሠሩ ሊያዩ ይገባቸዋልና ያምናሉ ብለው በማሰባቸው መታለላቸውን አለማየታቸው ያስገርማል። ቢሆንም እንደማያምኑ ማሳመን ብዙ ጊዜ እጅግ አስቸጋሪ ነው።
እውነቱ ግን ግድየለሹ ኃጢአተኛ ወንጌልን ፈጽሞ አያምንም። ግድየለሹ ኃጢአተኛ በአእምሮ የሚያምን ነው የሚለው ሐሳብ ከንቱ ነው። ዲያብሎስ በአእምሮ የሚያምን ነው፤ እንዲንቀጠቀጥ የሚያደርገውም ያ ነው። ኃጢአተኛውን የሚያስጨንቀው በአእምሮ ማመን መጀመሩ ነው፤ ያም እንዲሰማው ያደርገዋል። በሰማይ፥ በምድር ወይም በሲኦል ያለ ማንም ፍጡር የወንጌልን እውነቶች በአእምሮ አምኖ ስለ ርእሱ ሳይሰማው ሊኖር አይችልም። የተጨነቀው ኃጢአተኛ ከአጋንንት ጋር አንድ ዓይነት እምነት አለው፤ ነገር ግን የእርሱ ያን ያህል አይበዛም፤ ስለዚህም ያን ያህል አይሰማውም። በሃይማኖት ጉዳይ ምንም የማይሰማውና ምንም የማያደርግ ሰው ምንም ቢናገር ከሓዲ ነው። ምንም የማይሰማውና ምንም የማያደርግ ምንም አያምንም። ይህ ፍልስፍናዊ እውነታ ነው።
እምነት ክርስቶስ በተለይ ለአንተ እንደ ሞተ በአእምሮ በማመን ወይም ክርስቲያን እንደ ሆንህ ወይም እንደምትሆን ወይም ኃጢአትህ እንደ ተሰረየልህ በማመን አይደለም። እምነት ግን በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ላይ ያለ፥ በእኛ ላይ ባለው ግንኙነቱ ሁሉ ነፍስን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ አሳልፎ የሚሰጥ መታመን ወይም መተማመን ነው። በእርሱ አካል፥ በእውነተኛነቱና በቃሉ ላይ በፈቃድ የሚደረግ መታመን ነው። የአብርሃም እምነት ይህ ነበር። እግዚአብሔር በተናገረው ላይ እውነት እንደ ሆነ አድርጎ እንዲሠራ የሚያደርገው መተማመን ነበረው። ሐዋርያው በዕብራውያን አሥራ አንደኛው ምዕራፍ የሚያብራራው በዚህ መንገድ ነው። «እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።» በተለያዩ ምሳሌዎችም ሊያብራራው ይቀጥላል። «ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ በእምነት እናስተውላለን»፤ ይህም ማለት ይህን እናምናለን፥ እንደዚያም እንሠራለን። የኖኅን ጉዳይ ውሰዱ። ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ከእግዚአብሔር ማስጠንቀቂያ ተቀበለ፤ ይህም ማለት እግዚአብሔር ዓለምን በውኃ ሊያሰጥም እንደ ሆነ ተረዳ፥ አመነውም፥ እንደዚያም ሠራ፤ ቤተ ሰቡን ለማዳን መርከብን አዘጋጀ፤ ይህንም በማድረጉ ያላመነውን ዓለም ኰነነ፤ ሥራውም ቅን መሆኑን አስመሰከረ። አብርሃምም ደግሞ በእርሱ እንደሚጠቀም ተስፋ ተሰጥቶት አገሩን እንዲለቅ በእግዚአብሔር ተጠራ፤ ታዘዘም፥ ወዴት እንደሚሄድም ሳያውቅ ወጣ። ምዕራፉን ሁሉ አንብቡ፥ ብዙ እንደዚህ ያሉ ምሳሌዎችንም ታገኛላችሁ። የምዕራፉ ዓላማ ሁሉ የእምነትን ባሕርይ ማብራራትና ሁልጊዜ ወደ ተግባር እንደሚያደርስ ማሳየት ነው። ወንጌል የሚጠይቀው እምነት በክርስቶስ ላይ ያለ፥ እርሱ በሚናገረው ላይ እንደ እርግጠኛ እውነት እንዲሠራ የሚያደርገው መተማመን መሆኑ ለኃጢአተኛው ሊብራራለትና እንዲያየው ሊደረግ ይገባል። በክርስቶስ ማመን ይህ ነው፥
3. ለኃጢአተኛው ሊሰጥ የሚገባው ሌላው መመሪያ ልቡን ለእግዚአብሔር እንዲሰጥ ነው። እግዚአብሔር «ልጄ ሆይ፥ ልብህን ስጠኝ» ይላል። ነገር ግን እዚህም ደግሞ ምን ማለት እንደ ሆነ እንዲረዳ ማብራሪያ ያስፈልገዋል። በዚህ ነገር ላይ ጨለማ መኖሩ እጅግ ያስደንቃል። ይህ በሁሉ ሰው አፍ ያለ የዕለት ተዕለት ሕይወት ቋንቋ ነው፤ ስለ ሌላ ማንኛውም ነገር ስንጠቀምበትም ሁሉም ምን ማለት እንደ ሆነ በትክክል ይረዳል። ወደ ሃይማኖት ሲመጣ ግን ሁሉም በጨለማ ያሉ ይመስላሉ። ዕድሜውም ሆነ ትምህርቱ ምንም ይሁን ምን አንድን ኃጢአተኛ ልብን ለእግዚአብሔር መስጠት ምን ማለት እንደ ሆነ ጠይቀው፤ የሚያስገርም ቢመስልም መልስ ያጣል። አንዲትን ሴት ልቧን ለባሏ መስጠት ምን እንደ ሆነ፥ ወይም አንድን ሰው ልቡን ለሚስቱ መስጠት ምን እንደ ሆነ ጠይቅ፤ ይረዱታል። ልባቸውን ለእግዚአብሔር ስለ መስጠት ግን ፈጽመው ዕውሮች ናቸው። ይህን ጥያቄ ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ የተጨነቁ ኃጢአተኞች ሳልጠይቅ አልቀርም። ልባቸውን ለእግዚአብሔር መስጠት እንዳለባቸው ስነግራቸው ሁልጊዜ ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች እንደ ሆኑ፥ አንዳንድ ጊዜም ለማድረግ እንደሚጓጉ ይነግሩኝ ነበር፤ እንዲያውም ስለዚሁ በምኞት ጣር ውስጥ ያሉ ይመስሉ ነበር። ከዚያም ይህን ለማድረግ እንዲህ ፈቃደኞች ከሆኑ ልብን ለእግዚአብሔር መስጠት ምን እንደ ሆነ እንደሚረዱ ጠየቅኋቸው። በማንኛውም ዕድሜ ካለ ኃጢአተኛ ትክክለኛ ወይም ምክንያታዊ መልስ ያገኘሁት እጅግ አልፎ አልፎ ነው። አንዳንድ ጊዜ ሊታሰቡ የሚችሉትን እጅግ እንግዳ መልሶች አግኝቻለሁ፤ ሊሉት ከሚገባቸው በቀር ሁሉንም። እንግዲህ ልብህን ለእግዚአብሔር መስጠት ልብህን ለሌላ ለማንም ከመስጠት ጋር አንድ ነው፤ አንዲት ሴት ልቧን ለባሏ ከምትሰጥበት ጋር አንድ ነው። ያችን ሴት ይህን ትረዳ እንደ ሆነ ጠይቃት። «አዎን፥ ይህማ ግልጽ ነው፤ ፍቅሬን በእርሱ ላይ ማድረግና በሁሉ ነገር ደስ ላሰኘው መጣር ነው።» መልካም፥ ፍቅርህን በእግዚአብሔር ላይ አድርግ፥ በሁሉ ነገርም ደስ ልታሰኘው ጣር። ነገር ግን ወዮ፥ ወደ ሃይማኖት ጉዳይ ሲመጡ ሰዎች በውስጡ አንድ አስደናቂ ምሥጢር ያለ ይመስላቸዋል። አንዳንዶች በደረታቸው ያለውን ይህን የጡንቻ ጥቅል ወይም የሥጋ ብልት አውጥተው ለእግዚአብሔር መስጠት እንደ ሆነ የሚያስቡ ይመስል ይናገራሉ። ኃጢአተኛ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ከሁሉ በላይ እንድትወድደው ነው።
3. ለእግዚአብሔር ተገዙ የሚለውም ለተጨነቁ ኃጢአተኞች ተገቢ መመሪያ ነው። ወይ፥ ኃጢአተኞች በዚህም ላይ እንዴት በጨለማ ናቸው! ለእግዚአብሔር ለመገዛት ፈቃደኛ ነኝ የማይል ኃጢአተኛ ማግኘት ያዳግታል። ነገር ግን አይረዱትም። እውነተኛ መገዛት ምን እንደ ሆነ ሊነገራቸው ያስፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ ለመኰነን ፈቃደኞች መሆን ማለት ይመስላቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን በዚህ አቋም ላይ አድርገው መገዛት ብለው ይጠሩታል፤ የተመረጡ ከሆኑ ይድናሉ፥ ካልሆኑ ደግሞ ይኰነናሉ ይላሉ። ይህ መገዛት አይደለም። እውነተኛ መገዛት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ነው። በመንግሥት ላይ መሣሪያ ያነሣ አንድ ዓመፀኛ እንዲገዛ ቢጠራ ምን የሚረዳ ይመስልሃል? ክርክሩን መተው፥ መሣሪያውን ማስቀመጥና ሕጎቹን መታዘዝ እንዳለበት ነው። ኃጢአተኛ ለእግዚአብሔር መገዛት ማለትም ይህ ነው። ከፈጣሪው ጋር የሚያደርገውን ትግልና ግጭት ትቶ፥ እግዚአብሔር የሚጠይቀውን ሁሉ ለመሆንና ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ የታዛዥ ልጅ አቋም መያዝ አለበት። «ጌታ ሆይ፥ እነሆ አለሁ፤ ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?»
አንድ የወታደሮች ጭፍራ ዐመፀ እንበል፤ መንግሥትም እነርሱን የሚያስገዛ ሠራዊት ኖሮት ስንቅ ወደጨረሱበትና የሚያመልጡበት መንገድ ወደሌለበት ምሽግ ገፍቶ አስገባቸው፤ እነርሱም የሚያደርጉትን አጡ እንበል። ዓመፀኞቹ በዚህ ጭንቅ ውስጥ ምን መደረግ እንዳለበት ለመመካከር ተሰበሰቡ እንበል፤ አንዱም ተነሥቶ እንዲህ አለ፤ «ጓደኞቼ ሆይ፥ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሁላችንም እንደ ተሳሳትን አምኛለሁ፤ አሁንም የሥራችን ዋጋ ሊደርስብን ነው፥ ማምለጥም አንችልም፤ እዚህ ቆይቼ ለመሞት ደግሞ አልወስንም። ራሴን ለዋናው አዛዥ ምሕረት አሳልፌ ልሰጥ ነው።» ያ ሰው ተገዛ። ወደዚህ ውሳኔ በደረሰበት ቅጽበት ከዚያች ሰዓት ጀምሮ በልቡ ዓመፀኛ መሆኑን ያቆማል። ኃጢአተኛውም ክርክሩን ትቶ እግዚአብሔር የሚጠይቀውን ሁሉ ለማድረግና ለመሆን በልቡ ሲስማማ እንዲሁ ነው። ኃጢአተኛው ምን እንደሚያደርግ ሊጠራጠር ይችላል፤ ራሱን በእግዚአብሔር እጅ ቢጥል እግዚአብሔር እንደሚገባው ምናልባት ወደ ገሃነም ይልከው ይሆናል ብሎ በማሰብ ሊፈራ ይችላል። ነገር ግን የእርሱ ድርሻ ያን ጥያቄ ሁሉ ለእግዚአብሔር መተውና ከእንግዲህ ፈጣሪውን አለመቃወም ነው፤ ሁሉን ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት፥ ምንም ቅድመ ሁኔታ አለማስቀመጥ፥ የሚደረገውን ነገርና የወደፊት ሁኔታውን የመወሰኑን ጉዳይ ፈጽሞ ለእግዚአብሔር በጎነትና ጥበብ መተው ነው። ኃጢአተኛ ሆይ፥ ይህን እስክታደርግ ድረስ የሚጠቅም አንዳች ነገር አላደረግህም።
5. ለኃጢአተኞች ሊሰጥ የሚገባው ሌላው መመሪያ ኃጢአታችሁን ተናዘዙ፥ ተዉትም የሚለው ነው። ይህም ኃጢአታቸውን መናዘዝም መተውም አለባቸው ማለት ነው። በእግዚአብሔር ላይ የሠሩትን ኃጢአት ለእግዚአብሔር፥ በሰዎች ላይ የሠሩትንም ኃጢአት ለሰዎች መናዘዝ፥ ሁሉንም መተው አለባቸው። ሰው በአቅሙ ያለውን ካሳ ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ኃጢአቱን አልተወም። ገንዘብ ሰርቆ ወይም ባልንጀራውን ንብረቱን አጭበርብሮ ከሆነ ከእንግዲህ ላለመስረቅ ወይም ዳግመኛ ላለማታለል በመወሰን ብቻ ኃጢአቱን አልተወም፤ በአቅሙ ልክ ካሳ መክፈል አለበት። እንዲሁም ማንንም አማቶ ከሆነ ዳግመኛ እንዲህ አላደርግም በማለት ብቻ ኃጢአቱን አልተወም። ካሳ መክፈል አለበት። በተመሳሳይም ኃጢአተኞች ሁሉ እንዳደረጉት እግዚአብሔርን ዘርፎ ከሆነ በአቅሙ እስከ ቻለ ድረስ ካሳ መክፈል አለበት። አንድ ሰው በእግዚአብሔር ላይ እያመፀ ገንዘብ አፍርቷል እንበል፤ ጊዜውን፥ ችሎታውንና አገልግሎቱን ከእርሱ ከልክሏል፥ በመግቦቱ በረከቶች ላይ ኖሯል፥ ተንደላቅቋልም፥ ራሱንም ለዓለም መዳን ለማዋል እንቢ ብሏል፤ እርሱ እግዚአብሔርን ዘርፏል። እንግዲህ ይህ ገንዘብ የራሱ እንደ ሆነ እየተሰማው ቢሞትና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሳይጠይቅ ለወራሾቹ ቢተወው፥ እንግዲያስ እንደ መንገድ ቀማኛ ወደ ገሃነም መሄዱ የተረጋገጠ ነው። ለእግዚአብሔር ምንም ካሳ አልከፈለም። በዚያ ሁሉ ማልቀሱና መንፈሳዊ ወሬው የገዛ ኃጢአቱን ለእግዚአብሔር ፈጽሞ አልተናዘዘም፥ ኃጢአቱንም አልተወም፤ ራሱን የእግዚአብሔር መጋቢ አድርጎ ፈጽሞ አልተሰማውም፥ አላመነምና። በእጁ ያለውን ንብረት እንደ እግዚአብሔር መጋቢ ለመያዝ እንቢ ቢል፥ የራሱ አድርጎ ቢቆጥረውና እንደዚያም ለልጆቹ ቢሰጠው፥ በተግባር እግዚአብሔርን እንዲህ ይላል፤ «ያ ንብረት የአንተ አይደለም፤ የእኔ ነው፤ ለልጆቼም እሰጠዋለሁ።» እግዚአብሔርን ዘርፎ የወሰደውን ነገር ባለቤትነት ስለማይተው በኃጢአቱ መጽናቱን ቀጥሏል።
አንድ ነጋዴ ተቀጥሮ የሚሠራ ጸሐፊው ዋና ገንዘቡን ሁሉ ወስዶ የራሱን ሱቅ ቢከፍትና ገንዘቡ በእጁ እንዳለ ቢሞት ምን ያስባል? እንዲህ ያለ ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት ይሄዳልን? እያንዳንዳችሁ «አይሄድም፤ እንዲህ ያለ ሰው ወደ ገሃነም ካልሄደ ገሃነም ባይኖር ይሻላል» ትላላችሁ። እንዲህ ያለውን ሰው ሳይቀጣ ቢተወው እግዚአብሔር ፍጹም ፍትሕ የጎደለው መሆኑን ያሳይ ነበር። እንግዲያስ ዕድሜውን ሁሉ እግዚአብሔርን ስለ ዘረፈ ሰው ምን እንላለን? እግዚአብሔር ጸሐፊው አድርጎ ከጉዳዮቹ አንዳንዱን እንዲያስተዳድር አስቀመጠው፤ እርሱ ግን ሄዶ ገንዘቡን ሁሉ ሰረቀ፥ የእኔ ነው ይላል፥ ይይዘዋል፥ ይሞታል፥ ሁሉም የራሱ ሕጋዊ ንብረት እንደ ሆነ አድርጎ ለልጆቹ ይሰጠዋል። ያ ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት ይሄዳልን? ያ ሰው ኃጢአትን ትቷልን? አይደለም እላችኋለሁ። ራሱንና ያለውን ሁሉ ለእግዚአብሔር አሳልፎ ካልሰጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት በሚወስደው መንገድ የመጀመሪያውን እርምጃ አልወሰደም።
6. ለኃጢአተኞች ሊሰጥ የሚገባው ሌላው መመሪያ «የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ» የሚለው ነው። በብሉይ ኪዳን ዘመን ይህ ወይም ከዚህ ጋር የሚመጣጠን ነገር እጅግ የተለመደ መመሪያ ነበር። እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ድረስ ሰዎችን በክርስቶስ እንዲያምኑ መጥራት የተለመደ አልነበረም። እርሱ ወደ እርሱ የመጡትን የንስሐ ጥምቀት አጠመቃቸው፥ ከእርሱም በኋላ በሚመጣው እንዲያምኑ አዘዛቸው። በኢያሱ ዘመን የተሰጠው ቃል ሕዝቡ ሁሉ ገና በሩቅ ባለው መሲሕ እንዲያምኑ ከሚደረግ ጥሪ ይልቅ በቀላሉ የሚረዱት ነገር ነበር፤ እርሱም «የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ» የሚል ነበር። በሌላ ጊዜ ሙሴ እንዲህ አላቸው፤ «ሕይወትንና ሞትን፥ በረከትንና መርገምን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በእናንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ።» መመሪያው ከሕዝቡ እውቀት ጋር የሚስማማ ነበር። ያኔም እንደ ነበረ ዛሬም መልካም ነው። ኃጢአተኞች እንዲመርጡ ተጠርተዋል፤ ምንን? እግዚአብሔርን ወይስ ዓለምን እንደሚያገለግሉ፥ ቅድስናን ወይስ ኃጢአትን እንደሚከተሉ። መምረጥ ምን ማለት እንደ ሆነና የሚመረጠው ምን እንደ ሆነ እንዲረዱ ይደረግ፤ ከዚያም ነገሩ ከልብ ከተደረገ ይድናሉ።
ከእነዚህ መመሪያዎች ማንኛቸውም ቢፈጸሙ እውነተኛ መለወጥ ይሆናሉ። የተለየው የልብ እንቅስቃሴ በተለያዩ ሁኔታዎች ሊለያይ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ በመለወጥ ውስጥ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ ለእግዚአብሔር መገዛት ነው፤ አንዳንድ ጊዜ ንስሐ፥ አንዳንድ ጊዜ እምነት፥ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔርንና አገልግሎቱን መምረጥ ነው፤ ባጭሩ በዚያን ጊዜ ሐሳባቸውን የያዘው ማንኛውም ነገር ነው። በዚያች ቅጽበት ሐሳባቸው ወደ ክርስቶስ ከተመራ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ እምነት ይሆናል። ወደ ኃጢአት ከሆነ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ ንስሐ ይሆናል። ወደ ወደፊቱ የሕይወት አካሄዳቸው ከሆነ የእግዚአብሔርን አገልግሎት መምረጥ ነው። ወደ መለኮታዊው መንግሥት ከሆነ መገዛት ነው። በዚያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ኃጢአተኛውን በየትኛው ነጥብ ላይ እየወተወተው እንደ ሆነ በትክክል ማወቅና ያንኑ ነጥብ ለመግፋት መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው። ስለ ክርስቶስ ከሆነ ያንን አጥብቀህ አቅርብ፤ ስለ ወደፊቱ የሕይወት አካሄዱ ከሆነ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ ወዲያውኑ እንዲመርጥ ግፋው።
በመለወጥ ውስጥ አንድ የተለየ እንቅስቃሴ ሁልጊዜ ቀዳሚ እንደ ሆነ፥ ወይም እያንዳንዱ ኃጢአተኛ መጀመሪያ እምነት ወይም መጀመሪያ መገዛት ሊኖረው እንደሚገባ ማሰብ ታላቅ ስሕተት ነው። ይህ በፍልስፍናም ሆነ በእውነታ እውነት አይደለም። በሰዎች የልብ እንቅስቃሴ ውስጥ ታላቅ ልዩነት አለ። በእግዚአብሔርና በኃጢአተኛው መካከል የተያዘው ነጥብ ምንም ይሁን ምን ኃጢአተኛው ያንን ሲተው ተለውጧል። የተለየው እንቅስቃሴ ምንም ይሁን ምን በማንኛውም ነጥብ ላይ ለእግዚአብሔር የልብ መታዘዝን የሚያካትት ከሆነ እውነተኛ መለወጥ ነው። አንድን ነጥብ ለእግዚአብሔር ሥልጣን ሲተው ሁሉን ለመተው ዝግጁ ነው። ሐሳቡን ለውጦ በአንድ ነገር የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ሆነ ሲታዘዝ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆናቸውን እስካየ ድረስ በሌሎች ነገሮችም ይታዘዛል። እንግዲህ ይህ ትክክለኛ ምርጫ ባለበት አእምሮ ወደ ማንኛውም የግዴታ ነጥብ በተመራ ቁጥር ለመከተል ዝግጁ ነው። ግልጽ ብቻ ከተደረገና ለእግዚአብሔር የመታዘዝ መፈተኛ ሆኖ እንዲያገለግል ወደ ነጥቡ ከሆነ ከእነዚህ መመሪያዎች የትኛው ቢሰጥ ብዙም ለውጥ የለውም። የእግዚአብሔር መንፈስ ከኃጢአተኛው አእምሮ ጋር በሚከራከርበት ነጥብ ላይ ከሆነ፥ ከመንፈሱ ሥራ ጋር እንዲስማማና የኃጢአተኛውን ትኩረት ከክርክሩ ዋና ነጥብ እንዳያስቀይስ ፍጹም ግልጽ ይደረግ፤ ከዚያም ኃጢአተኛው እስኪተው ድረስ አጥብቆ ይቅረብለት፤ እርሱም ይድናል።
III. የተጨነቁ ኃጢአተኞች ስለዚህ ታላቅ ጥያቄ ሊወድቁባቸው የሚቀናቸውን አንዳንድ ስሕተቶች እጠቅሳለሁ።
1. የመጀመሪያው ስሕተት ራሳቸውን ማሻሻል ወይም ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው፥ በዚህም በሆነ መንገድ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ምሕረት ማቅረብ እንዳለባቸው ማሰብ ነው። ኃጢአተኞች ማድረግ ያለባቸው ሁሉ በእጃቸው ተዘጋጅቶ የቀረበላቸውን መዳን ከእግዚአብሔር መቀበል ብቻ እንደ ሆነ አለመረዳታቸው ያስደንቃል። ነገር ግን የተማሩም ያልተማሩም ሁሉ በመጀመሪያ እፎይታ ለማግኘት ወደ ሕግ መንገድ ይዞራሉ። ጉዳዩን ማሰብ እንደ ጀመሩ ወዲያውኑ ክርስቲያኖች የማይሆኑበት አንዱ ዋና ምክንያት ይህ ነው። ለመምጣት በሆነ መንገድ መዘጋጀት እንዳለባቸው ያስባሉ። ልብሳቸውን መለወጥና ራሳቸውን ትንሽ ማሳመር አለባቸው፤ ባሉበት ሁኔታ በጨርቃቸውና በድህነታቸው ለመምጣት ፈቃደኞች አይደሉም። ወደ እግዚአብሔር ከመቅረባቸው በፊት ሌላ ነገር መልበስ አለባቸው። እግዚአብሔር የሚጠይቀውን እስኪያደርጉ ድረስ የተሻሉ መሆን እንደማይችሉ ወዲያውኑ ሊገለጽላቸው ይገባል። እግዚአብሔር እንደ መጀመሪያ ተግባር የሚጠይቅባቸውን ያንኑ ነገር እስካላደረጉ ድረስ በእግዚአብሔር ላይ በዓመፅ ጸንተው ስለ ቆሙ፥ በሚመታው በእያንዳንዱ ትርታ፥ በሚተነፍሱት በእያንዳንዱ እስትንፋስ እየባሱ ይሄዳሉ።
2. ሌላው ስሕተት በትክክል ወደ ክርስቶስ ለመምጣት ከመዘጋጀታቸው በፊት እንደ አንድ ዓይነት ቅጣት ለረጅም ጊዜ በኃጢአት ወቀሳ ሥር መሠቃየት እንዳለባቸው ማሰብ ነው። ስለዚህ ለወቀሳ ይጸልያሉ። በቂ ጊዜ በጭንቀት እስከ ምድር ድረስ ቢደቀቁ እግዚአብሔር እጅግ ጎስቋሎች ሆነው ሲያያቸው ይራራላቸዋል፥ ሊረዳቸውም ይበልጥ ዝግጁ ይሆናል ብለው ያስባሉ። እንዲህ ደስታ የራቃቸውና ጎስቋሎች የሆኑት እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን እፎይታ ለመቀበል እንቢ በማለታቸው ብቻ እንደ ሆነ በግልጽ እንዲረዱ ሊደረጉ ይገባል። ወላጁ በበትር በላዩ የቆመበትን፥ የሚንቀጠቀጥና የሚጮኽን እልኸኛ ልጅ እንመልከት። ያ ልጅ በጣሩ አንዳች የሚያተርፍ ሊመስለው ይገባልን? ጭንቀቱ ከወቀሳው የሚመነጭ ነው፤ ታዲያ ለተጨማሪ ወቀሳ ይጸልይን? ይህ አንዳች ያሻሽለዋልን? እምቢ ብሎ ስለ ቆመ አባቱ ይበልጥ ይራራለታልን? ሁልጊዜ እየባሰ መሄዱን የማያይ ማን ነው?
3. አንዳንድ ጊዜ ኃጢአተኞች ለእግዚአብሔር ከመገዛታቸው በፊት የተለየ ስሜት መጠበቅ እንዳለባቸው ያስባሉ። «ክርስቶስን ለመቀበል ገና ትክክለኛ ስሜት ያለኝ አይመስለኝም፤ ለመለወጥ ገና የተዘጋጀሁ አይመስለኝም» ይላሉ። እግዚአብሔር ከእነርሱ የሚጠይቀው ትክክለኛውን መፍቀድ እንደ ሆነ እንዲያዩ ሊደረጉ ይገባል። በፈቃዳቸው ቢታዘዙና ቢገዙ ስሜቶቹ በጊዜው ራሳቸውን ያስተካክላሉ። ጥያቄው የስሜት አይደለም፤ የመፍቀድና የማድረግ ነው።
ስሜቶች ያለ ፈቃድ የሚመጡ ናቸው፤ ከሚተባበሩት ከፈቃድ ድርጊት ከሚያገኙት በቀር የራሳቸው የሆነ ሥነ ምግባራዊ ባሕርይ የላቸውም። ፈቃድ ትክክል ከመሆኑ በፊት ስሜቶች እንደማይስተካከሉ የታወቀ ነው። ኃጢአተኛው ክርስቶስን ወዲያውኑ በመቀበል ወደ እርሱ መምጣት አለበት፤ ይህንም ማድረግ ያለበት ለስሜቱ በመታዘዝ ሳይሆን ለሕሊናው በመታዘዝ ነው። ታዘዝ፥ ተገዛ፥ ታመን። ሁሉን ወዲያውኑ ተው፤ ስሜትህም ይስተካከላል። የተሻለ ስሜትን አትጠብቅ፤ ይልቁንም ሁለንተናህን ወዲያውኑ ለእግዚአብሔር አሳልፈህ ስጥ፤ ይህም ብዙም ሳይቆይ የምትጠብቀውን ስሜት ያመጣል። እግዚአብሔር ከአንተ የሚጠይቀው ከኃጢአት ወደ ቅድስና፥ ከሰይጣን አገልግሎት ወደ ሕያው እግዚአብሔር አገልግሎት የሚመለስ የአሁኑን የአእምሮህን ድርጊት ነው።
4. ሌላው የኃጢአተኞች ስሕተት ልባቸው እስኪለወጥ ድረስ መጠበቅ እንዳለባቸው ማሰብ ነው። «ምን?» ይላሉ፤ «ልቤ ሳይለወጥ በክርስቶስ ማመን አለብኝን? ልቤ ሳይለወጥ ንስሐ መግባት አለብኝ ማለትህ ነውን?» እንግዲህ ለዚህ ሁሉ ቀላሉ መልስ የልብ መለወጥ ራሱ በጥያቄ ላይ ያለው ነገር ነው የሚል ነው። እግዚአብሔር ኃጢአተኞች እንዲወድዱት ይጠይቃል። ይህ ማለት ልባቸውን መለወጥ ነው። እግዚአብሔር ኃጢአተኛው በወንጌል እንዲያምን ይጠይቃል። ይህ ማለት ልቡን መለወጥ ነው። እግዚአብሔር ንስሐ እንዲገባ ይጠይቃል። ይህ ማለት ልቡን መለወጥ ነው። እግዚአብሔር ልቡ እስኪለወጥ ድረስ እንዲጠብቅ፥ ከዚያም ንስሐ እንዲገባና እንዲያምን፥ እግዚአብሔርንም እንዲወድድ አይነግረውም። ንስሐ የሚለው ቃል ራሱ የአእምሮ ወይም የልብ መለወጥን ያመለክታል። ከእነዚህ ነገሮች ማንኛውንም ማድረግ ልክ እግዚአብሔር እንደሚጠይቀው ልብህን መለወጥና ለራስህ አዲስ ልብ ማድረግ ነው።
5. ኃጢአተኞች ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር የሚጠይቀውን ለማድረግ ፍጹም ፈቃደኞች እንደ ሆኑ ያስባሉ። ይህን ወይም ያንን አድርጉ፥ ንስሐ ግቡ፥ ወይም እመኑ፥ ወይም ልባችሁን ለእግዚአብሔር ስጡ በላቸው፤ እነርሱም «አዎን፥ ያንን ለማድረግ ፍጹም ፈቃደኛ ነኝ፤ ባደርገው ደስ ባለኝ፤ ማድረግ ብችል ማንኛውንም ነገር እሰጥ ነበር» ይላሉ። በእውነት ፈቃደኛ መሆን ማድረግ እንደ ሆነ፥ ነገር ግን በመፍቀድና በመመኘት መካከል ልዩነት እንዳለ ሊረዱ ይገባል። ሰዎች ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች ለመሆን ፈጽመው ፈቃደኞች ሳይሆኑ ለመሆን ይመኛሉ። መልካም መስሎ የሚታየንን ነገር ስናይ እንድንመኘው ሆነን ተፈጥረናል። በአእምሯችን ፊት ሲሆን የግድ እንመኘዋለን። መልካምነቱ በአእምሯችን ፊት በቀረበ መጠን ከመመኘት ልንቆጠብ አንችልም። ሆኖም በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ለማግኘት ፈቃደኞች ላንሆን እንችላለን። በአጠቃላይ አሁን ያለው ባለቤት ይዞት እንዲቀጥል እንመርጥ ይሆናል። ወይም ከእኛ ይልቅ ወዳጃችን ወይም ልጃችን እንዲያገኘው እንመርጥ ይሆናል። አንድ ሰው በብዙ ምክንያቶች ወደ ፊላዴልፊያ ለመሄድ ሊመኝ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ይበልጥ ከባድ በሆኑ ምክንያቶች ወደዚያ ላለመሄድ ይመርጣል። እንዲሁም ኃጢአተኛው ክርስቲያን ለመሆን ሊመኝ ይችላል። ክርስቲያን በመሆን ብዙ መልካም ነገሮችን ሊያይ ይችላል። ክርስቲያን ቢሆን እጅግ ይበልጥ ደስተኛ እንደሚሆን፥ ሲሞትም ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደሚሄድ ሊያይ ይችላል፤ ሆኖም ክርስቲያን ለመሆን ፈቃደኛ አይደለም። ክርስቶስን ለመታዘዝ ፈቃደኛ መሆን ክርስቲያን መሆን ነው። አንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመታዘዝ በእርግጥ ሲመርጥ ክርስቲያን ነው። ነገር ግን በእውነተኛ ምርጫ የማይደመደሙ እንዲህ ያሉ ምኞቶች ሁሉ ከንቱ ናቸው።
6. ኃጢአተኛው አንዳንድ ጊዜ ልቡን ለእግዚአብሔር ለመስጠት እንደሚያቀርብ፥ እግዚአብሔር ግን ፈቃደኛ እንዳልሆነ በተዘዋዋሪ ይናገራል። ይህ ግን ከንቱ ነገር ነው። እግዚአብሔር የሚጠይቀው ምንድን ነው? እንድትወድደው ነው። እንግዲህ ልብህን ለእግዚአብሔር ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ፥ እግዚአብሔር ግን ፈቃደኛ አይደለም ማለት፥ እግዚአብሔርን ለመውደድ ፈቃደኛ ነኝ፥ እግዚአብሔር ግን በእኔ ለመወደድ ፈቃደኛ አይደለም፥ እንድወድደውም አይፈቅድልኝም እንደ ማለት ነው። እውነት ሊደርስበት የማይችልበትና የሚያርፍበት ጨለማና ምሥጢራዊ ማዕዘን እንዳይኖረው እነዚህን ነጥቦች ሁሉ በኃጢአተኛው አእምሮ ውስጥ ማጥራት አስፈላጊ ነው።
7. ኃጢአተኞች በኃጢአታቸው የተወቀሱ ብቻ ሆነው ሳሉ አንዳንድ ጊዜ ንስሐ እንደ ገቡ ይመስላቸዋል። ኃጢአተኛው በማንኛውም ውሸት ላይ ሲያርፍ በተገኘ ጊዜ ሁሉ ምንም ያህል ቢያሠቃየውና ቢያስጨንቀው እውነት ጠራርጎ ያስወግደው። እንዲህ ያለ ስሕተት ካለበት ወደ ገሃነም ጥልቅ እንዲሰናከል ካልፈለጋችሁ ከእርሱ ነቅላችሁ ልታስወግዱት ይገባችኋል።
8. ኃጢአተኞች በእግዚአብሔር ፊት የሚያስመሰግናቸውን አንድ ነገር፥ አንድ ዓይነት ስሜትን፥ በዚያ ማግኘት ይችሉ እንደ ሆነ ለማየት ብዙ ጊዜ ራሳቸውን በመመልከት ፈጽመው ይያዛሉ። ተገቢ ትምህርት በማጣቱ ዴቪድ ብሬነርድ በእግዚአብሔር ፊት የሚያስመሰግኑትን ስሜቶች እየፈለገ ስለ አእምሮው ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ተይዞ እንደ ነበረ ግልጽ ነው። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለ ስሜት እንዳለው አስቦ አሁን ምሕረቱን ለመቀበል እንደሚገባው እንደ ተሰማው በጸሎት ለእግዚአብሔር ይነግረው ነበር፤ ከዚያም ፈጽሞ ተሳስቶ እንደ ነበረ አይቶ ትክክለኛ ስሜት እንዳለው ለእግዚአብሔር በመናገሩ ያፍር ነበር። በዚህ ሁኔታ ምስኪኑ ሰው ትክክለኛ ትምህርት በማጣቱ ወደ ተስፋ መቁረጥ ሊደርስ ጥቂት ቀረው፤ በዚህ ነጥብ ላይ በተቀበለው የተሳሳተ ፍልስፍና በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ክርስቲያናዊ የልብ እንቅስቃሴዎቹ እጅግ እንደ ተለወጡ፥ መጽናናቱና ጥቅሙም እጅግ እንደ ተጎዱ ማየት ቀላል ነው። ኃጢአተኛውን ከራሱ ዞር አድርጋችሁ ወደ ሌላ ነገር ልትመልሱት ይገባል። ወደ ተስፋ መቁረጥ እስኪገባ ድረስ ራሱን መመርመሩን ቢቀጥል እንበል። ያን ጊዜ ትክክለኛው መንገድ ትኩረቱን ራሱን ከመመልከት ማዞርና መፈጸም ያለበትን አንድ ግዴታ እንዲመለከት ወይም ክርስቶስን እንዲመለከት ማድረግ ነው፤ ምናልባትም ሳያውቀው ለእግዚአብሔር እንደ ተገዛ ያገኛል። ትኩረቱ ከራሱ ተዘዋውሮ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ምክንያታዊነት ወይም የክርስቶስን ማስተሰረያ በቂነት ወይም እንዲህ ያለውን ነገር ወደ ማሰላሰል ሄደ፤ በዚያም ላይ ሲያሰላስል ልቡን ዝም ብሎ አሳልፎ ሰጠ፤ ጣሩም አለቀ።
ማሳሰቢያዎች።
1. ለኃጢአተኞች በተሰጡ የተሳሳቱ ትምህርቶች የአገልጋዮች ድካም እጅግ ጨምሯል፤ በመዳን መንገድ ላይ ያሉ ችግሮችም እጅግ በዝተዋል። ውጤቱም ቀድሞ ግልጽ የነበሩ መመሪያዎች አሁን የተድበሰበሱ መሆናቸው ነው። ሰዎች በመለወጥ ውስጥ እጅግ ምሥጢራዊና የማይገባ ነገር እንዳለ ለረጅም ጊዜ ስለ ተማሩ ሊረዱት እንኳ አይሞክሩም። ኃጢአተኞች እነዚህን የተሳሳቱ አሳቦች ተምረዋል፤ አሁንም በየስፍራው እንደ «ንስሐ መግባት አልችልም»፥ «እግዚአብሔርን መጠበቅ አለብኝ» እና እንደ እነዚህ ባሉ አሳቦች በስተ ኋላ መሽገዋል። ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደምንማረው ቀድሞ ኃጢአተኞችን ንስሐ እንዲገቡ ወይም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ መንገር በቂ ነበር። አሁን ግን እምነት እንደ ድርጊት ሳይሆን እንደ መሠረተ ባሕርይ፥ ንስሐም እንደ አእምሮ እንቅስቃሴ ሳይሆን በአእምሮ ውስጥ እንደሚቀመጥ ነገር ተነግሮለታል፤ ኃጢአተኞችም ግራ ተጋብተዋል። እምነት መሠረተ ባሕርይ ሳይሆን እንቅስቃሴ እንደ ሆነ፥ ኃጢአትም የሰው ተፈጥሮ ክፍል ሳይሆን ድርጊት እንደ ሆነ ለማስተማር ስለ ደፈሩ አገልጋዮች ኑፋቄን ይሰብካሉ ተብለው ይከሰሳሉ። ኃጢአተኞችም በዚህ ዓይነት ውስብስብ አስተሳሰብ እጅግ ከመሠልጠናቸው የተነሣ ማለት የፈለጋችሁትን ብቻ ሳይሆን ማለት ያልፈለጋችሁትንም ለማብራራት እጅግ መድከም ይኖርባችኋል፤ አለዚያ በእርግጥ ሊሳሳቱአችሁ ይችላሉ፤ ወይ ግዴታቸውን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል ከጭንቀታቸው የሐሰት እፎይታ ያገኛሉ፥ ወይም ለመዳናቸው የሚያስፈልገውን ማድረግ የማይቻል መስሏቸው ወደ ተስፋ መቁረጥ ይገባሉ። ከተታለሉባቸው ከእነዚህ ሥነ መለኮታዊ ጥልፍልፎችና ውስብስብ መንገዶች አውጥቶ ቀጥተኛውንና ቀላሉን የወንጌል መንገድ እንዲከተሉ መምራት ብዙ ጊዜ እጅግ ከባድ ነገር ነው። የሰዎችን አእምሮ ለማደናገርና ኃጢአተኛን በማያልቅ ጨለማ ውስጥ ሊያስገባ የተዘጋጀ እጅግ ረቂቅ የሆነ የሐሰት ሥነ መለኮት ድር ለመሥራት ታላቅ ብልሃት የተሠራበት ይመስላል።
በመነቃቃቶች ውስጥ የነበረ ማን ነው የተሰበኩትን የማያልቁትን የሞኝነት ነገሮች ያላጋጠመው? ይህም እንደ ሀ ሁ ግልጽ መሆን አስፈላጊ እስኪሆንና እጅግ የተማሩት እንኳ ልክ እንደ ልጆች ሊነገራቸው እስኪገባ ድረስ ነው። እጅግ ግልጽ በሆኑ ነገሮች የሰዎችን አእምሮ ለማደናገርና ለማሞኘት እጅግ ብዙ ተሠርቷል። ኃጢአተኛን እመን በለው፤ እርሱም ወደ አንተ ዞሮ አፍጥጦ ያይሃል፤ «ምን ትላለህ? እምነት በነፍስ ውስጥ የተተከለ መሠረተ ባሕርይ አይደለምን? ይህን መሠረተ ባሕርይ እስካገኝ ድረስ እንዴት ማመን እችላለሁ?» እንዲሁም አገልጋይ በበዓለ ኀምሳ ቀን በነበረው ታላቅ መነቃቃት ሐዋርያት የተጠቀሙበትን ያንኑ ቃል ለኃጢአተኛ፥ «እያንዳንዳችሁ ንስሐ ግቡ፥ ተመለሱም» ቢለው፥ እነርሱም እንደ ተማሩት እንዲህ ብለው ይመልሳሉ፤ «ኧረ፥ አርሚኒያን ሳትሆን አትቀርም፤ የአንተን የአርሚኒያን ትምህርት አልፈልግም፤ የመንፈስን አሠራር አትክድምን?» ብዙ ትውልዶች ወደ ገሃነም እስኪራገፉ ድረስ በወንጌል ግልጽ መመሪያዎች ዙሪያ የተጣለውን ጭጋግና ጨለማ ማየት የሰውን ልጅ ሊያስለቅስ ይበቃል።
2. ለኃጢአተኞች የሚሰጡ እነዚህ የተሳሳቱ ትምህርቶች ምንም ከሌለ እጅግ የከፉ ናቸው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝቡ የተሳሳተ የሥነ መለኮት አሳባቸውን እንዲተዉ ማድረግን ከማንኛውም ነገር ይበልጥ አስቸጋሪ ሆኖ አገኘው። እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁድ ዘንድ ያለው ታላቅ ችግር ይህ ነው፤ የተሳሳተ የሥነ መለኮት አሳብ ተቀብለዋል፥ በአንዳንድ ነጥቦች ላይ እውነትን አጣመዋል፥ በወንጌል ውስጥ እጅግ ግልጽ የሆኑትን ነጥቦች እንኳ እንዲረዱ ልታደርጋቸው አትችልም። ከኃጢአተኞችም ጋር እንዲሁ ነው፤ ሊደረግ ከሚገባው እጅግ አስቸጋሪው ነገር ከሐሰተኛ ሥነ መለኮት ያገኙአቸውን እነዚህን የሐሰት መጠጊያዎች ማስወገድ ነው። እነዚህ መጠጊያዎች ኦርቶዶክሳዊ ስለሚባሉና ኃጢአተኛውን ነጻ አድርገው እግዚአብሔርን ስለሚኰንኑ አጥብቀው ሊይዟቸው እጅግ ይወዳሉ፤ ስለዚህም እነርሱን ማባረር የአገልጋይ ድካም እጅግ ግራ የሚያጋባ፥ አስቸጋሪና ተስፋ የሚያስቆርጥ ክፍል ሆኖ ይገኛል።
3. በእነዚህ እንግዳ ዶግማዎች እንዲህ ተጭኖ ሳለ ወንጌል እንዲህ ጥቂት ውጤት ማስገኘቱ አያስደንቅም። እውነቱ፥ በእነዚህ መቶ ዘመናት በሐሰተኛ ሥነ መለኮት ሳይታነቅና ሳይድበሰበስ ወደ ዓለም የወጣው ወንጌል እጅግ ጥቂት ነው። ሰዎች ንስሐ መግባት እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል፤ በዚያው ትንፋሽም እውነት ራሱ ከስሕተት ጋር ፈጽሞ ተደባልቆ ከስሕተት ጋር አንድ ዓይነት ተግባራዊ ውጤት እስኪያመጣ ድረስ ንስሐ መግባት እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል፤ የሚሰበከውም ወንጌል ሌላ ወንጌል ወይም ፈጽሞ ወንጌል ያልሆነ ሆኗል።
4. የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሴት ልጅ ቍስል በቀላሉ መፈወስ ምን ማለት እንደ ሆነና የማድረጉንም አደጋ መረዳት ትችላላችሁ። ኃጢአተኞች በወቀሳ ሥር ሲሆኑ ጉዳዩን የሚያለሰልስና ጭንቀታቸውን የሚያቀል ነገር መናገር እጅግ ቀላል ነው፤ ይህም ወይ የሐሰት ተስፋ እንዲያገኙ፥ ወይም አመለካከታቸው እጅግ ተድበስብሶ እንዲለወጡ ያደርጋል፤ ስለዚህም ሁልጊዜ ምስኪኖች፥ ደካሞች፥ ወላዋዮች፥ ተጠራጣሪዎችና ፍሬ ቢሶች ክርስቲያኖች ይሆናሉ።
5. አንድ ሰው በወቀሳ ሥር ሳለ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚያዝ ብዙ ነገር ይወሰናል። በወቀሳ ሥር ሳለ የወንጌል መመሪያዎች በምን ያህል ግልጽነት፥ ብርታትና ጽናት እንደሚሰጡት የወደፊቱ መጽናናቱና ጥቅሙ በብዙ ይወሰናል። የሚይዙት ሰዎች መመርመሪያውን በሚገባ ለመጠቀም ቢፈሩ ሁልጊዜ ምስኪን፥ በሽተኛና ተጠራጣሪ ክርስቲያን ይሆናል። ጨርሶ ቢለወጥ እንኳ ብዙ መልካም ነገር ፈጽሞ አያደርግም። ትክክለኛው መንገድ ከኃጢአተኛ ጋር በጥልቀትና በግልጽ መነጋገር፥ ሊያዘጋጀው የሚችለውን እያንዳንዱን ሰበብ ነቅሎ መጣልና ምን እንደ ሆነና ምን ሊሆን እንደሚገባው በግልጽ ማሳየት ነው፤ እርሱም ለነፍሱ እንዲህ ታማኞች ከሆኑ ሰዎች ጋር በመገናኘቱ እስከ ዘላለም እግዚአብሔርን ይባርካል። እንዲህ ያለ ጥልቅና መርማሪ አያያዝ በማጣት ብዙዎች ሞተው የተወለዱ የሚመስሉ ሆነው ይለወጣሉ። ምክንያቱም ከቶ በታማኝነት አልተያዙም። ክርስቲያኖች እንደ ሆኑ በፍቅር ተስፋ ልናደርግ እንችላለን፤ ሆኖም ነገሩ እርግጠኛ ያልሆነና አጠራጣሪ ነው። መለወጣቸው የልብ መለወጥ ሳይሆን የአስተያየት መለወጥ ይመስላል። ነገር ግን ኃጢአተኛ በወቀሳ ሥር ሲሆን እውነትን ብታፈስሱበት፥ መመርመሪያውን ብታስገቡ፥ የድሮውን መሠረት ብታፈርሱ፥ የሐሰት መጠጊያዎቹንም ጠራርጋችሁ ብታስወግዱ፥ የእግዚአብሔርንም ቃል እንደ እሳትና እንደ መዶሻ ብትጠቀሙበት፥ በግልጽ አመለካከት፥ በብርቱ እምነትና በጽኑ መሠረተ ሐሳብ እንደሚወጡ ታገኛላችሁ፤ ተጠራጣሪዎች፥ አንካሶችና ቆራጥነት የጎደላቸው ክርስቲያኖች ሳይሆኑ ጌታን በፍጹም የሚከተሉ ይሆናሉ። ብርቱ ክርስቲያኖችን የማፍራት መንገድ ይህ ነው። በዘመናችን በብዙ መነቃቃቶች ይህ በጉልህ ሆኗል። አረጋውያን ክርስቲያኖች ስለ አዳዲስ አማኞች እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ፤ «እነዚህ አዳዲስ አማኞች ሙሉ ሰው ሆነው የተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ናቸው፤ ከቶ ሕፃናት አልነበሩም፤ ይልቁንም ከመጀመሪያው የአረጋውያን ክርስቲያኖችን ግልጽ አመለካከትና የእምነት ብርታት ሁሉ ይዘዋል። የሃይማኖትን ትምህርቶች የሚረዱ ይመስላሉ፤ መነቃቃትን ለማስፋፋት ምን እንደሚያደርጉና እንዴት እንደሚጀምሩ በቤተ ክርስቲያን ካሉት ከአሮጌዎቹ አባላት ከመቶው አንዱ ከሚያውቀው ይበልጥ ያውቃሉ።»
በአንድ ወቅት ከቤቱ ርቆ ሳለ የተለወጠ አንድ ወጣት አውቅ ነበር። ይኖርበት የነበረው ስፍራ አገልጋይም፥ ስብከትም፥ ሃይማኖትም አልነበረውም። ከተለወጠ በሦስት ቀን ውስጥ ወደ ቤቱ ሄዶ ወዲያውኑ ለመነቃቃት ለመድከም ሥራ ጀመረ። በሰፈሩ ስብሰባዎችን አቋቋመ፥ ጸለየም፥ ደከመም፤ መነቃቃትም ተቀሰቀሰ፤ በዚያ ብርቱ ሥራ ውስጥ ዋናው መሪ እርሱ ነበር፤ ሥራውም የስፍራውን ታላላቅ ሰዎች አብዛኞቹን ለወጠ። እውነቱ፥ ምን እየሠራ እንዳለ እንዲያውቅ ሆኖ ተይዞ ነበር። ጉዳዩን ተረድቶ ነበር፤ ራሱም የት እንደ ቆመ ያውቅ ነበር። ራሱ ክርስቲያን መሆን አለመሆኑን በመጠራጠር ሁልጊዜ አይታወክም ነበር። እግዚአብሔርን እያገለገለ እንደ ሆነና እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር እንደ ሆነ ያውቅ ነበር፤ ስለዚህም በድፍረትና በቆራጥነት ወደ ዓላማው ገፋ። ነገር ግን ስሕተቶቻቸውን ሁሉ ሳትቈርጡና የሐሰት ተስፋቸውን ሳትነቅሉ አዳዲስ አማኞችን ለማፍራት ብትሞክሩ ብዙ ግብዞችን፥ ወይም ሁልጊዜ የሚጠራጠሩ፥ ከመነቃቃት መንፈስ በቀላሉ ወደ ኋላ የሚመለሱና ምንም የማይጠቅሙ ደካሞችና ድንክዬ ክርስቲያኖችን ልታፈሩ ትችላላችሁ። መንገዱ ቀጥ አድርጎ ወደ ብርሃን ማውጣት ነው። ሰው በዚህ መንገድ ሲለወጥ ልትተማመኑበትና የት እንደምታገኙት ልታውቁ ትችላላችሁ።
7. የተራዘመ የወቀሳ ወቅት ብዙውን ጊዜ ከጎደሎ ትምህርት የሚመነጭ ነው። ለኃጢአተኞች ግልጽና ታማኝ ትምህርት በሚሰጥበት ሁሉ ወቀሳዎች ጥልቅና ወጊ፥ ነገር ግን አጭር እንደ ሆኑ በአብዛኛው ታገኛላችሁ።
8. ለተወቀሱ ኃጢአተኞች ግልጽና ለይቶ የሚያሳይ ትምህርት በሚሰጥበት ስፍራ፥ ቶሎ ካልተገዙ ወቀሳቸው በአብዛኛው ይለቃቸዋል። በእንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች ወቀሳዎች ብዙውን ጊዜ አጭር ናቸው። ኃጢአተኞች በሐሰት አመለካከት በሚታለሉበት ስፍራ ለሳምንታት፥ ምናልባትም ለወራት፥ አንዳንድ ጊዜም ለዓመታት በዛለ ሁኔታ ሊቆዩ ይችላሉ፤ በመጨረሻም ምናልባት ተገፍተው ወደ መንግሥቱ ገብተው ይድኑ ይሆናል። ነገር ግን እውነት በኃጢአተኛው አእምሮ ፍጹም ግልጽ በሆነበትና ስሕተቶቹ ሁሉ በተነቀሉበት ስፍራ፥ ቶሎ ካልተገዛ ጉዳዩ ተስፋ ቢስ ነው። እውነት በአእምሮው ላይ በሚሠራበትና እርሱ የሚለውጠውን ያንኑ እውነት በቀጥታ በሚቃወምበት ስፍራ ከዚህ በላይ የሚደረግ ነገር የለም። መንፈስ የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች ራሳቸው ስለ ተቃወሙ መንፈስ ቶሎ ይተወዋል። ትምህርቶች ግልጽ ባልሆኑበትና ከስሕተቶች ጋር በተደባለቁበት ስፍራ ኃጢአተኞችን ከሐሰተኛ ትምህርት ጭጋግ ለማሳለፍ መንፈስ በታላቅ ምሕረት ለዓመታት እንኳ ሊታገል ይችላል። ግዴታቸው በግልጽ በተብራራላቸው፥ ወዲያውኑ ወደ መገዛት ብቸኛ ነጥብ ቀጥ ብለው በቀረቡበት፥ የሐሰት ሰበቦቻቸው ሁሉ በተጋለጡበትና የግዴታ መንገድ ፍጹም ግልጽ በተደረገበት ስፍራ ግን እንዲህ አይደለም። ያን ጊዜ ካልተገዙ የእግዚአብሔር መንፈስ ይተዋቸዋል፤ ሁኔታቸውም ተስፋ ቢስ ሊሆን ጥቂት ይቀረዋል።
በዚህ ቤት ውስጥ ኃጢአተኞች ካሉና ግዴታችሁን በግልጽ ካያችሁ፥ ከመዘግየት እጅግ ተጠንቀቁ። ካልተገዛችሁ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደሚተዋችሁ ልትጠብቁ ትችላላችሁ፤ እናንተም ጠፍታችኋል።
8. ለተጨነቁ ኃጢአተኞች ከሚሰጠው መመሪያ እጅግ ብዙው ከጳጳሳዊው የምሕረት ሰነድ (ኢንዱልጀንስ) ትምህርት የማይተናነስ ነው። ጳጳሱ ኃጢአት ለመሥራት የሚፈቅዱ የምሕረት ሰነዶችን ይሸጥ ነበር፤ ይህም በሉተር ዘመን ወደ ተደረገው ተሐድሶ መራ። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ ኃጢአት ለመሥራት፥ ወይም አንድን የተለየ ኃጢአት ወይም በርካታ ኃጢአቶችን ለመሥራት የምሕረት ሰነድ ይገዙ ነበር። እንግዲህ በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከዚያው ነገር የማይተናነስ እጅግ ብዙ ነገር አለ። ኃጢአተኛን ጠብቅ ማለት ከዚህ በምን ይለያል? ፍሬ ነገሩ እግዚአብሔር እስኪለውጠው ሲጠብቅ ጥቂት ጊዜ ተጨማሪ በኃጢአት እንዲቀጥል መንገር ነው። ይህስ ኃጢአት ለመሥራት ከሚሰጥ ፈቃድ በቀር ምንድን ነው? ኃጢአተኞችን እግዚአብሔርን ወዲያውኑ እንዲታዘዙ የማይጠይቅ ማንኛውም መመሪያ ኃጢአት ለመሥራት የሚሰጥ ፈቃድ ነው። በተግባር በእግዚአብሔር ላይ በኃጢአት እንዲቀጥሉ ነጻነት መስጠት ነው። እንዲህ ያሉ መመሪያዎች ክፉዎች ብቻ ሳይሆኑ አጥፊዎችና ጨካኞችም ናቸው። ያለ ጥርጥር ብዙ ጊዜ እንደሚያደርጉት ነፍስን ባያጠፉ እንኳ ኃጢአተኛው በእግዚአብሔርና በክርስቶስ የሚያገኘውን ደስታ በማንኛውም ሁኔታ ያዘገዩታል፤ እርሱም እንዲህ ያሉትን ትምህርቶች ሲሰማ ለዘላለም የመጥፋት ታላቅ ዕድል አለው። ወይ፥ ልቡን ለእግዚአብሔር ከመስጠቱ በፊት አንዲት ቅጽበት እንኳ ሊጠብቅ እንደሚችል እንዲያስብ ለኃጢአተኛ ምክንያት መስጠት እንዴት አደገኛ ነው!
9. ለመመልከት ዕድል እስካገኘሁ ድረስ እጅግ ድንገተኛ የሆኑት መለወጦች ብዙውን ጊዜ ምርጥ ክርስቲያኖች ሆነው ተገኝተዋል። የዚህ ተቃራኒው ብዙ ጊዜ እንደ ተያዘና እንደ ተከራከሩለት አውቃለሁ። ነገር ግን ብዙዎች አሁንም እንኳ አንድ ሰው እጅግ በድንገት ከተለወጠ እንደ አጠራጣሪ ነገር ቢቆጥሩትም ለዚህ ምንም ምክንያት እንደሌለ ረክቻለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለዚህ አሳብ ምንም ድጋፍ አይሰጥም። በመጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ውስጥ አንድም የተራዘመ ወቀሳ ታሪክ አልተመዘገበም። በዚያ የተመዘገቡት መለወጦች ሁሉ ድንገተኛ መለወጦች ናቸው። ዓለምን አልችልም ባይነት በሞሉት በእነዚያ የሥነ መለኮት ጥመቶች ባይሆን ኖሮ፥ ይህን ያህል ብዙ አሰልቺ ወቀሳዎች፥ በመጨረሻም ብዙ ጊዜ ወደ ምንም የሚያልቁ፥ ፈጽሞ ባልኖሩ ነበር ብዬ አምናለሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ኃጢአተኞችን ንስሐ ግቡ ይሏቸው ነበር፤ እነርሱም ያን ጊዜውኑ ያደርጉት ነበር። አልችልም ባይነት በዚያ ዘመን ገና አልተነሣም ነበር። ብዙዎች የሚያልፉበትን የተራዘመ ጭንቅና ጣር ሁሉ፥ ምናልባትም ጥፋትን፥ መሠረት የሚጥለው ይህ ኃጢአተኞች እግዚአብሔርን መታዘዝ አይችሉም የሚለው ግምታዊ አሳብ ነው። ኃጢአተኛ ማድረግ ያለበትን እንዲያይ ሲደረግና ወዲያውኑ አቋሙን ወስዶ ሲያደርገው፥ ብዙውን ጊዜ ከዚያ በኋላም እንዲሁ ያደርጋል፤ እንዲህ ያለውም ሰው እስከ መጨረሻ እንደሚጸናና ቆራጥ ባሕርይ እንዳለው በአብዛኛው ታገኛላችሁ። እንደ መርከብ ከነፋስና ከማዕበል ጋር ተቃርኖ ሁልጊዜ ወደ ግዴታ መጎተት ካለባቸው ሰዎች አንዱ ሆኖ አታገኙትም። በግዴታ ሁልጊዜ ወደ ፊት መጎተት ያለባቸውን ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ሰዎች ተመልከቱ፤ ሲለወጡ ግልጽና ወጥ የሆነ መመሪያ እንዳልነበራቸው በአብዛኛው ታገኛላችሁ፤ ምናልባትም «እነዚህን ድንገተኛ መለወጦች እጅግ እንፈራለን» ይላሉ።
ድንገተኛ መለወጦችን መፍራት! ከማውቃቸው ምርጥ ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ተወቅሰው ተለውጠዋል። እኔ ከተናገርሁበት ጊዜ በአራተኛው እጅ ውስጥ ብዙዎቹ ነቅተው ወዲያውኑ ወደ ጌታ ወገን ወጥተዋል፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም በቤተ ክርስቲያን የሚያበሩ ብርሃኖች ሆነዋል፤ በመጀመሪያ ወጥተው በጌታ ወገን አቋም በወሰዱ ጊዜ ያሳዩትን ያንኑ በሃይማኖት ውስጥ ያለ የባሕርይ ቆራጥነት በአብዛኛው አሳይተዋል።