ምዕራፍ 17 · 44 ደቂቃ ንባብ · 57 ደቂቃ ማዳመጥ
ትምህርት 15. የመነቃቃት እንቅፋቶች
ትምህርት 15.
የመነቃቃት እንቅፋቶች።
ጥቅስ፦ «ታላቅ ሥራ እሠራለሁ፥ ስለዚህ ልወርድ አልችልም፤ ሥራውን ትቼ ወደ እናንተ ስወርድ ሥራው ለምን ይቆማል?»—ነህምያ 6፡3።
ይህ የእግዚአብሔር ባሪያ መቅደሱን እንደ ገና ሊሠራና የእግዚአብሔርን አምልኮ የአባቶቹ መቃብሮች ባሉባት ከተማ በኢየሩሳሌም እንደ ገና ሊያቆም ከባቢሎን ወጥቶ ነበር። የጽዮንን ፍርስራሽ ለረጅም ጊዜ ሲደሰቱበት የነበሩት ሰንባላጥና አጋሮቹ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች መቅደሱና ቅድስቲቱ ከተማ አሁን እንደ ገና ሊሠሩ መሆናቸውን ባወቁ ጊዜ ታላቅ ተቃውሞ አስነሡ። ሰንባላጥና ሌሎቹ መሪዎች ነህምያንና ወዳጆቹን ከሥራቸው ለማዘናጋትና ወደ ፊት እንዳይሄዱ ለማገድ በብዙ መንገድ ሞከሩ፤ አንድ ጊዜ አስፈራሩአቸው፤ ከዚያም በንጉሡ ላይ ሊያምፁ ነው ብለው ከሰሱአቸው። ደግሞም ዓላማቸው ሃይማኖታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው ብለው ተከራከሩ፤ ነህምያም በቀላልና በፈጣን ክህደት እንዲህ ሲል መለሰ፦ «እንደምትለው ያለ ነገር አልተደረገም፤ ነገር ግን ከልብህ ፈጥረኸዋል።» በመጨረሻም ሰንባላጥ ጉዳዩን ሁሉ በሰላም እንዲወያዩበትና ችግሩን እንዲያስተካክሉ በኦኖ ሜዳ እንዲገናኘው ወደ ነህምያ መልእክት ላከ፤ ዓላማው ግን ክፉ ሊያደርግበት ነበር። ነህምያን ሊያስፈሩት እንዳልቻሉ አውቀው ነበር፤ አሁን ደግሞ በተንኰልና በማታለል ሊከቡት፥ ሥራውንም በብርቱ ከመቀጠል ሊያዘናጉት ፈለጉ። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ «ታላቅ ሥራ እሠራለሁ፥ ስለዚህ ልወርድ አልችልም፤ ወደ እናንተ ስወርድ ሥራው ለምን ይቆማል?»
የእግዚአብሔር ባሪያዎች ለዓላማው አንዳች ነገር ሲያደርጉና ይሳካላቸዋል የሚመስል ተስፋ ሲታይ፥ ሰይጣን በወኪሎቹ አማካይነት አእምሮአቸውን ለማዘናጋትና ድካማቸውን ከንቱ ለማድረግ ዘወትር ይሞክራል፤ ይህ ሁልጊዜ የሆነ ነው። በምድሪቱ ርዝመትና ስፋት ሁሉ እንዲህ ያሉ አስደናቂ መነቃቃቶች በሆኑባቸው ባለፉት አሥር ዓመታትም እንዲሁ ሆኗል። እነዚህ መነቃቃቶች እጅግ ታላላቅ፥ ኃይለኞችና ሰፊዎች ነበሩ። በዚያ ጊዜ ውስጥ ከሁለት መቶ ሺህ ያላነሱ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንደ ተለወጡ ተገምቷል።
ዲያብሎስም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማዘናጋትና ለመበታተን፥ ታላቁን የመዳን ሥራ ወደ ፊት ከመግፋትም ኃይላቸውን ለማስቀየስ በተንኰሎቹ ተጠምዶ ቆይቷል። ስለዚህ ጉዳይ ስናገር የሚከተሉትን ለማሳየት አስባለሁ።
I. የሃይማኖት መነቃቃት ታላቅ ሥራ እንደ ሆነ።
II. ሊያስቆሙት የሚችሉትን አያሌ ነገሮች መጥቀስ።
III. ይህ ታላቅ መነቃቃት እንዲቀጥል ምን መደረግ እንዳለበት ለማሳየት መሞከር።
I. የሃይማኖት መነቃቃት ታላቅ ሥራ እንደ ሆነ ማሳየት አለብኝ።
ታላቅ ሥራ ነው፤ ምክንያቱም ታላላቅ ጥቅሞች ተያይዘውበታል። በሃይማኖት መነቃቃት ውስጥ የዚህን ዓለም አገዛዝ በሚመለከት የእግዚአብሔር ክብርና የሰዎች መዳን ሁለቱም ተያይዘዋል። ወሰን የሌለው አስፈላጊነት ያላቸው ሁለት ነገሮች በእርሱ ውስጥ አሉ። የአንድ ሥራ ታላቅነት የሚለካው በእርሱ ላይ በተመሠረቱት ውጤቶች ታላቅነት ነው። የአስፈላጊነቱም መለኪያ ይኸው ነው።
II. መነቃቃትን ሊያስቆሙ የሚችሉትን አያሌ ነገሮች መጥቀስ አለብኝ።
አንዳንዶች በዚህ ጉዳይ ላይ እውነተኛውን መነቃቃት ምንም ነገር ሊጎዳው እንደማይችል አድርገው በጣም በሞኝነት ተናግረዋል። «መነቃቃታችሁ የእግዚአብሔር ሥራ ከሆነ ሊቆም አይችልም፤ የተፈጠረ ፍጡር እግዚአብሔርን ሊያስቆም ይችላልን?» ይላሉ። እንግዲህ ይህ ማስተዋል ነውን? ብዬ እጠይቃለሁ። ቀድሞ መነቃቃት የእግዚአብሔር ሥራ ስለ ሆነ ሊቆም አይችልም የሚል የጸና እምነት ነበር። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሆነ ከውጭ ሊያግዱት ምንም ቢደረግ ይቀጥላል ብለው አሰቡ። ነገር ግን ገበሬውም እንዲሁ ሊያስብ፥ እህልን የሚያበቅል እግዚአብሔር ስለ ሆነ ሄዶ ስንዴውን ቢያጭድ አዝመራውን አይጎዳም ብሎ ሊያስብ ይችል ነበር። መነቃቃት የእግዚአብሔር ሥራ ነው፤ የስንዴ አዝመራም እንዲሁ ነው፤ እግዚአብሔርም በሁለቱም ላይ መንገዶችን በመጠቀም ላይ እኩል ይመረኰዛል። ስለዚህ መነቃቃት ልክ እንደ ስንዴ እርሻ ሊጎዳ ይችላል።
1. ቤተ ክርስቲያን መነቃቃቱ ሊቆም ነው ብላ ባመነች ጊዜ ሁሉ መነቃቃቱ ይቆማል። ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ይህን ሥራ የሚሠራባት መሣሪያ ናት፤ በሥራውም በፈቃዳቸውና በልባቸው ሊሠሩ ይገባቸዋል። ወዳጆቹ መነቃቃቱ ሊቆም ነው ብለው ከመተንበይ የበለጠ ለመነቃቃት የሚገድል ነገር የለም። የሥራው ጠላቶች ሁሉ ነገር አልቆ ከንቱ ይሆናል ብለው ቢተነብዩ ወይም መሰል ነገር ቢናገሩ ግድ የለውም። በዚህ መንገድ ሊያስቆሙት አይችሉም፤ ወዳጆቹ ግን ሥራውን ለማስቀጠል በእምነት መድከምና መጸለይ አለባቸው። ሥራውን ለማስቀጠል በእምነት እንደሚደክሙና እንደሚጸልዩ እያሉ ሊቆም ነው ብለው ማመናቸው እርስ በርሱ የሚቃረን ነው። እምነታቸውን ካጡ መቆሙ አይቀርም። የመነቃቃቶች ወዳጆች መነቃቃቱ ሊቆም ነው ብለው መተንበይ በጀመሩ ጊዜ ሁሉ በጌታ ስም ወዲያውኑ ሊገሠጹ ይገባል። ይህ ሐሳብ አንድ ጊዜ መስፋፋት ከጀመረና ልትቃወሙትና ከሥሩ ልትነቅሉት ካልቻላችሁ፥ መነቃቃቱ ያለ ጥርጥር ይቆማል፤ ክርስቲያኖች መነቃቃቱን ለማስፋፋት በእምነት መድከምና መጸለያቸው ለሥራው የግድ አስፈላጊ ነውና፤ ሊቆም ነው ብለው እያመኑ እንዲቀጥል በእምነት ሊደክሙ ይችላሉ ማለት እርስ በርሱ የሚቃረን ነው።
2. ክርስቲያኖች መነቃቃቱ እንዲቆም በተስማሙ ጊዜ ይቆማል። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች መነቃቃቱ የመቆም አደጋ ላይ እንዳለ፥ ውጤታማ የሆነ ነገር ካልተደረገም እንደሚቆም ያያሉ። ይህ ሁኔታ ቢያስጨንቃቸውና ወደ ጸሎትና ወደ አዲስ ጥረት ቢገፋፋቸው ሥራው አይቆምም። ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ሥራና የነፍሳትን መዳን እጅግ ከመውደዳቸው የተነሣ የመቀዝቀዝ ስጋት ብቻ ቢያስጨንቃቸው፥ ወደ ጸሎትና ወደ ጥረት ምጥ ይገፋፋቸዋል። መቆሙን ለመከላከል ወደ ምጥና ጥረት ካልገፋፋቸው፥ አደጋውን አይተው ሊያስወግዱት ወይም ሥራውን ሊያድሱ ካልሞከሩ፥ እንዲቆም ተስማምተዋል። በዚህ ጊዜ በአገሩ ሁሉ መነቃቃቶች ሲቀዘቅዙና ፈጽሞ የመቆም ታላቅ አደጋ ላይ እንዳሉ የሚያዩ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ሆኖም የሚያሳዩት ጭንቀት ጥቂት ነው፥ ስለ ጉዳዩም ብዙም ግድ የሰጣቸው አይመስሉም። አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ሁኔታቸውን ያያሉ፤ መንቃት ካልመጣ ምን እንደሚመጣ ያያሉ፤ ሆኖም ተደላድለው ተቀምጠዋል፤ እግዚአብሔር ሥራውን እንዲያነቃቃ በጸሎት አያቃስቱም፥ አይጣጣሩምም። አንዳንዶች እንዲያውም በዋይትፊልድና በኤድዋርድስ ዘመን በኋላ እንደ ሆነው አሁን ታላቅ ኋላ ቀር ምላሽና ታላቅ ድርቅ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሊመጣ ነው ብለው ይተነብያሉ። ሆኖም በራሳቸው ትንቢት አይደነግጡም፤ ስለ ጉዳዩ ቀዝቃዛዎች ናቸው፤ ወዲያውኑ ፊታቸውን ወደ ሌሎች ነገሮች ያዞራሉ። እንዲቆም ተስማምተዋል። በእግዚአብሔር ምርጦች ሰልፍ መካከል ፍርሃትን እንዲበትኑ የተላኩ የዲያብሎስ መለከት ነፊዎች ይመስላሉ።
3. ክርስቲያኖች መነቃቃቱን ለማስፋፋት በሚያደርጉት ሙከራ እንደ ማሽን በሆኑ ጊዜ ሁሉ መነቃቃቱ ይቆማል። እምነታቸው ብርቱ፥ ልባቸው ሞቅ ያለና ለስላሳ፥ ጸሎታቸው በቅዱስ ስሜት የተሞላ፥ ቃላቸውም በኃይል የሆነ ሲሆን ሥራው ይቀጥላል። ጸሎታቸው መቀዝቀዝና ስሜት ማጣት ሲጀምር፥ ጥልቅ ስሜታቸው ሲጠፋ፥ እንደ ማሽን መድከምና ያለ ስሜት ቃላትን መጠቀም ሲጀምሩ ግን መነቃቃቱ ይቆማል።
4. ክርስቲያኖች ሥራው ያለ እነርሱ እርዳታ ይቀጥላል የሚል ሐሳብ በያዙ ጊዜ ሁሉ መነቃቃቱ ይቆማል። ቤተ ክርስቲያን መነቃቃትን በማስፋፋት ከእግዚአብሔር ጋር አብረው የሚሠሩ ናቸው፤ ሥራውም ቤተ ክርስቲያን ልታስኬደው እስከምትፈቅደው ድረስ ብቻ እንጂ ከዚያ አልፎ አይሄድም። እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ወደ ሥራው ለማስገባት አንድ ሺህ ስምንት መቶ ዓመት ሲሞክር ኖሯል። እንዲይዙት ሲጠራ፥ ሲያሳስብ፥ ሲያዝ፥ ሲለምን፥ ሲያጣድፍና ሲያበረታታ ቆይቷል። በዚህ ሁሉ ጊዜ ሥራውን ከእነርሱ ጋር ለማስኬድ ክንዱን ሊገልጥ ተዘጋጅቶ ቆሟል። ቤተ ክርስቲያን ግን የራሷን ድርሻ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነችም። ዓለምን መለወጥን ለእግዚአብሔር ብቻ ለመተው የቈረጡ ይመስላሉ፤ «ዓለም እንዲለወጥ ከፈለገ እርሱ ያድርገው» ይላሉ። ይህ የማይቻል መሆኑን ሊያውቁ ይገባቸዋል። እኛ እስከምናውቀው ድረስ እግዚአብሔርም ሆነ ሰው ያለ ቤተ ክርስቲያን ተባባሪነት ዓለምን ሊለውጡ አይችሉም። ኃጢአተኞች ያለ ራሳቸው ተሳትፎ ሊለወጡ አይችሉም፤ መለወጥ በፈቃዳቸው ወደ እግዚአብሔር መመለሳቸው ነውና። ኃጢአተኞችም እነርሱን የሚመልሱ ተገቢ የሥነ ምግባር ተጽእኖዎች ሳይኖሩ፥ ማለትም በቀጥታ መገለጥ ወይም በሰዎች አማካይነት እውነትና የነገሮች እውነታ በአእምሮአቸው ፊት በሙላት ሳይቀርብ ሊለወጡ አይችሉም። እግዚአብሔር ዓለምን በአካላዊ ሁሉን ቻይነት ሊለውጥ አይችልም፤ ይልቁንም በቤተ ክርስቲያን የሥነ ምግባር ተጽእኖ ላይ ይመረኰዛል።
5. ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጉዳይ ይልቅ የራሷን ጉዳይ መከታተል በመረጠች ጊዜ ሥራው ይቆማል። ሰዎች በትክክል የራሳቸው የሆነ ጉዳይ አላቸው ብዬ አልቀበልም፤ እነርሱ ግን እንዲህ ያስባሉ፤ በእርግጥም ለእግዚአብሔር ከመሥራት ይልቅ የራሳቸው ብለው የሚቆጥሩትን ይመርጣሉ። ከዓለማዊ ሥራቸው መነቃቃትን ለማስኬድ የሚበቃ ጊዜ ሊሰጡ አይችሉም ብለው ማሰብ ይጀምራሉ። ሃይማኖትን መከታተል ለማቆም እንደ ተገደዱ ያስመስላሉ፤ ልባቸውንም እንደ ገና ወደ ዓለም ይለቁታል። ሥራውም መቆሙ አይቀርም።
6. ክርስቲያኖች በታላቁ መነቃቃታቸው ሲታበዩ ይቆማል። ይህንንም ስል ቀደም ብለው መነቃቃቱን በማስፋፋት መሣሪያ የነበሩትን ክርስቲያኖች ማለቴ ነው። በመነቃቃት ጊዜ የቤተ ክርስቲያን አንድ ክፍል በሥራው ምንም ተሳትፎ ለማድረግ እጅግ ትዕቢተኛ ወይም እጅግ ዓለማዊ መሆኑ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል የሚሆን ነገር ነው። ራሳቸውን አግልለው ምን እንደሚሆን፥ እንዴትስ እንደሚያልቅ ለማየት ለመጠበቅ ቈርጠዋል። የዚህ የቤተ ክርስቲያን ክፍል ትዕቢት መነቃቃቱን ሊያስቆም አይችልም፤ መነቃቃቱ በእነርሱ ላይ ከቶ አልተመሠረተምና። ያለ እነርሱ ጀመረ፥ ያለ እነርሱም ሊቀጥል ይችላል። እጃቸውን አጣጥፈው ከመመልከትና ከመንቀፍ በቀር ምንም ላያደርጉ ይችላሉ፤ ሥራው ግን አሁንም ሊቀጥል ይችላል። ነገር ግን የሚሠራው የቤተ ክርስቲያን ክፍል ምን ያህል ታላቅ መነቃቃት እንዳገኙ፥ እንዴት እንደ ደከሙና እንደ ጸለዩ፥ ምን ያህል ደፋሮችና ቀናተኞች እንደ ነበሩ፥ ምን ያህልም መልካም እንዳደረጉ ማሰብ ሲጀምር ሥራው ሊቀዘቅዝ ይቀርባል። ምናልባት በቤተ ክርስቲያኒቱ ምን ዓይነት መነቃቃት እንደ ነበረ፥ አባላቱም ምን ያህል እንደ ተጉ በጋዜጦች ታትሞ ይሆናል፤ እንዲህ ያለ ታላቅ መነቃቃት ስላገኙም በአገሩ ሁሉ ባሉ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ግምት ምን ያህል ከፍ ብለው እንደሚቆሙ ያስባሉ። ስለዚህ ይታበያሉ፥ ከንቱም ይሆናሉ፤ ከዚያም የእግዚአብሔርን ሀልዎት ሊያጣጥሙ አይችሉም፤ መንፈስም ከእነርሱ ይርቃል፤ መነቃቃቱም ይቆማል።
7. ቤተ ክርስቲያን በድካም በዛለች ጊዜ መነቃቃቱ ይቆማል። ብዙ ክርስቲያኖች በመነቃቃት ጊዜ በዚህ ረገድ ታላቅ ስሕተት ይሠራሉ። እጅግ ግድየለሾችና ማስተዋላቸውም እጅግ ጥቂት ስለ ሆነ የአኗኗር ልማዳቸውን ሁሉ ያፈርሳሉ፤ በተገቢው ሰዓት መብላትንና መተኛትን ቸል ይላሉ፤ መነሣሣቱም ይዞአቸው እንዲሄድ ይፈቅዳሉ፤ ስለዚህ ሰውነታቸውን ከአቅም በላይ ያደክማሉ፤ እጅግ ጥንቃቄ የጐደላቸውም ስለ ሆኑ ብዙም ሳይቆዩ ይዝላሉ፤ በሥራውም መቀጠል አይቻላቸውም። መነቃቃቶችን የሚያስኬዱ ሰዎች በዚህ ረገድ ቸልተኞችና ጥንቃቄ የጐደላቸው በመሆናቸው ብዙ ጊዜ መነቃቃቶች ይቆማሉ፤ ውድቀትም ይከተላል።
8. ቤተ ክርስቲያን ከተግባር ጋር ምንም ግንኙነት ስለሌላቸው ረቂቅ ትምህርቶች መላምት ማውጣት ስትጀምር መነቃቃቱ ይቆማል። ቤተ ክርስቲያን ትኩረቷን ከመዳን ነገሮች አዙራ ረቂቅ ነጥቦችን ወደ ማጥናት ወይም ወደ መከራከር ብትሄድ መነቃቃቱ መቆሙ አይቀርም።
9. ክርስቲያኖች ተከታይ ማፍራት ሲጀምሩ። ባፕቲስቶች ፕሬስቢቴሪያኖችን፥ ወይም ፕሬስቢቴሪያኖች ባፕቲስቶችን፥ ወይም ሁለቱም ሜቶዲስቶችን፥ ወይም ኤጲስቆጶሳውያን ሌሎቹን እጅግ ሲቃወሙና አዳዲስ አማኞችን ወደ ራሳቸው ቤተ ክርስቲያን ለማስገባት ጥረት ማድረግ ሲጀምሩ፥ ብዙም ሳይቆዩ የመነቃቃቱን መጨረሻ ታያላችሁ። ምናልባት መነቃቃት ለጊዜው ይቀጥላል፥ የወገንተኝነት ችግሮችም ሁሉ ይወገዳሉ፤ ይህም አንድ ሰው ተከታዮችን ለማፍራት በስውር መጽሐፍ እስኪያሰራጭ ድረስ ነው። ምናልባት አንድ ከልክ በላይ ቀናተኛ ዲያቆን፥ ወይም አንዲት ጠብ አጫሪ ሴት፥ ወይም ተከታይ የሚያሳድድ አገልጋይ ከዚያ በላይ ዝም ማለት አቅቶት ተከታዮችን ለማፍራት በመሞከር የዲያብሎስን ሥራ መሥራት ይጀምራል፤ እንዲሁም መራርነትን ያነሣሣል፥ የራስ ወዳድነትንም ክርክር አስነሥቶ መንፈስን አሳዝኖ ያርቃል፥ ክርስቲያኖችንም ሁሉ ወደ ወገኖች ይከፋፍላል። ከዚያ በኋላ በዚያ መነቃቃት የለም።
10. ክርስቲያኖች እንደ ተቀበሉት ጥቅም መጠን ለጌታ ለመመለስ እንቢ ሲሉ። ይህ የሃይማኖታዊ ውድቀቶች ፍሬያማ ምንጭ ነው። እግዚአብሔር ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን የሰማይን መስኮቶች ከፍቶ በረከትን አፍስሶላታል፤ ከዚያም ዐሥራቱን ወደ ጎተራው እንዲያመጡ፥ ለጽዮንም የልግስና ነገር እንዲያስቡና እንዲፈጽሙ በትክክል ይጠብቃል፤ እነሆም፥ እንቢ ብለዋል፤ የክርስቶስን ዓላማ ለማስፋፋት በዚያ መጠን ራሳቸውን አልሰጡም፤ ስለዚህ መንፈስ አዝኗል፥ በረከቱም ተወስዷል፤ እግዚአብሔር እጅግ ቸር ሆኖ ሳለ ቤተ ክርስቲያን ለጋስ ለመሆን ስላልፈለገች በአንዳንድ ሁኔታዎችም ታላቅ ኋላ ቀር ምላሽ ሆኗል። ስለ እንዲህ ያለ አካሄድ በመካንነት የተረገሙ የሚመስሉ አብያተ ክርስቲያናትን አውቃለሁ። የከበረ መነቃቃት አግኝተው ነበር፤ ከዚያም በኋላ ምናልባት የመሰብሰቢያ ቤታቸው ጥገና አስፈልጎት ወይም ጥቂት ገንዘብ የሚያስወጣ ሌላ ነገር አስፈልጎ ነበር፤ እነርሱም ሊያደርጉት እንቢ አሉ፤ ስለዚህ ስለ ንፉግ መንፈሳቸው እግዚአብሔር ተዋቸው።
11. ቤተ ክርስቲያን በማንኛውም መንገድ መንፈስ ቅዱስን ስታሳዝን።
(1.) በመንፈስ ላይ መመረኰዛቸው ሳይሰማቸው ሲቀር። ክርስቲያኖች በራሳቸው ብርታት በበረቱ ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር በረከታቸውን ይረግማል። በብዙ ሁኔታዎች ክርስቲያኖች በስኬታቸው ስለሚታበዩ፥ ምስጋናውንም ለራሳቸው ወስደው ክብሩን ሁሉ ለእግዚአብሔር ስለማይሰጡ በራሳቸው ምሕረት ላይ ኃጢአት ይሠራሉ። እርሱ እንዲህ ይላል፦ «ባትሰሙ፥ ለስሜም ክብርን ትሰጡ ዘንድ በልባችሁ ባታኖሩት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እርግማንን እሰድድባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማለሁ፤ በልባችሁም ስላላኖራችሁት አሁን ረግሜዋለሁ።» በዚህ አገር እንዲህ ያለው ነገር ያለ ጥርጥር ብዙ ሆኗል። በጋዜጦች ውስጥ ይህን የሚመስሉ ብዙ ነገሮች አይቻለሁ፤ በዚያም ሰዎች መነቃቃቶችን በማስፋፋት ለተገኘው ስኬት ምስጋናውን ለራሳቸው የመውሰድ ዝንባሌ ያላቸው ይመስሉ ነበር። ለዚህ ታላቅ ፈተና እንዳለ ጥርጥር የለውም፤ አገልጋዮችና አብያተ ክርስቲያናትም ከእርሱ እንዲጠበቁ፥ በሰዎችም በከንቱ በመመካት መንፈስን አሳዝነው እንዳያርቁት እጅግ ትጋት ያስፈልጋቸዋል።
(2.) መንፈስ በመነቃቃቱ በመመካት መንፈስ ሊያዝን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ መነቃቃት እንደ ጀመረ በጋዜጦች ላይ ሲለፈፍ ታያላችሁ። ብዙውን ጊዜ ይህ መነቃቃቱን ይገድለዋል። በአጎራባች ክፍለ ሀገር መነቃቃት የጀመረበትና ወዲያውኑ መነቃቃት እንዳለው የሚገልጽ ከመጋቢው ደብዳቤ የወጣበት ሁኔታ ነበር። ደብዳቤውን አይቼ በልቤ፦ ስለዚህ መነቃቃት የምንሰማው ይህ የመጨረሻው ነው አልሁ። እንዲሁም ሆነ። በጥቂት ቀናት ውስጥ ሥራው ፈጽሞ ቆመ። እንዲህ ያሉ ነገሮችም ያልተለመዱ አይደሉም። ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን የሚያስታብዩ፥ ለመነቃቃቱም ከዚያ በኋላ ጥቂት ወይም ምንም ሊደረግ እስከማይችል ድረስ እጅግ የሚያስመኩ ነገሮችን ያሳተሙባቸውን ሁኔታዎችና ስፍራዎች ልጠቅስ እችላለሁ።
አንዳንዶች ለእግዚአብሔር ምስጋናና ክብር ነገሮችን እናሳትማለን በማለት ራሳቸውን ከፍ የማድረግ ዝንባሌ በብርቱ የሚሸትባቸውን ነገሮች አሳትመዋል፤ የራሳቸውንም ተሳትፎ እጅግ ጎልቶ እንዲታይ አድርገዋል፤ ይህም መጥፎ ስሜት እንደሚፈጥር ግልጽ ነበር። ካለፈው ዓመት በፊት ባለው በልግ በዚህች ቤተ ክርስቲያን በተደረገው የተራዘመ ስብሰባ ስማቸውንና የሚኖሩበትን ስፍራ የምናውቃቸው አምስት መቶ ሰዎች በተስፋ ተለወጡ። ከእነርሱ ብዙዎቹ ወደዚህች ቤተ ክርስቲያን ተቀላቀሉ። ብዙዎቹም ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ተባበሩ። ስለዚህ በጋዜጦች ምንም አልተባለም። በዚህ ጉዳይ ለምን ዝም እንዳልን ብዙ ጊዜ ተጠይቄአለሁ። በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ራስን ከፍ የማድረግ ዝንባሌ እጅግ ስለ ነበረ በጉዳዩ ላይ አንዳች ነገር ለማሳተም እንደ ፈራሁ ብቻ መመለስ ቻልሁ። ምናልባት ተሳስቼ ይሆናል። ነገር ግን ያለ ጊዜው በሚወጡ ጽሑፎች ጉዳት ሲደርስ ብዙ ጊዜ ስላየሁ ስለ እርሱ ምንም አለመናገር የተሻለ መስሎ ታየኝ። ከአራት ዓመት በፊት በዚህች ከተማ በሆነው መነቃቃት ራስን ከፍ የማድረግ የሚመስል ብዙ ነገር በጋዜጦች ስለ ተነገረ ለማሳተም ፈራሁ። የመነቃቃቶችን ዘገባ የማሳተምን ልማድ በራሱ እየተቃወምሁ አይደለም። ነገር ግን የሚደረግበት መንገድ እጅግ አስፈላጊ ነው። ከንቱ ውዳሴን በሚያነሣሣ መንገድ ከተደረገ ለመነቃቃቱ ሁልጊዜ ገዳይ ነው።
(3.) እንዲሁም የእግዚአብሔርን ሥራ ለማቃለል የሚያዘነብሉ ነገሮችን በመናገር ወይም በማሳተም መንፈስ ያዝናል። የተባረከ የእግዚአብሔር ሥራ በቀላሉ ሲነገርለትና ለስሙ የሚገባው ክብር ለእግዚአብሔር ሳይሰጥ ሲቀር መንፈስ ያዝናል። ስለ መነቃቃት አንዳች ነገር ቢነገር፣ ግልጽና ያልተሸፈኑ እውነታዎችን ብቻ እንዳሉ ስጡ፤ በሚገባቸውም ዋጋ ይታዩ።
12. ክርስቲያኖች የወንድማማች ፍቅር መንፈስን ሲያጡ መነቃቃት ይቋረጣል ተብሎ ሊጠበቅ ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች የወንድማማች ፍቅርን በተግባር እስከ ቀጠሉ ድረስ ብቻ እንጂ ከዚያ በላይ በመነቃቃት ከእነርሱ ጋር አይቀጥልም። ክርስቲያኖች በመነቃቃት መንፈስ ሲሆኑ ይህ ፍቅር ይሰማቸዋል፤ ያን ጊዜም እጅግ በፍቅር እርስ በርሳቸው ወንድሜ፣ እኅቴ ሲባባሉ ትሰማላችሁ። ነገር ግን መቀዝቀዝ ሲጀምሩ ይህን የእርስ በርስ የፍቅር ሙቀትና ግለት ያጣሉ፤ ያን ጊዜም ወንድሜ፣ እኅቴ መባባሉ የሞኝነትና የሚናቅ ነገር መስሎ ይታያቸዋል፤ ይተዉታልም። በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ፈጽሞ እንዲህ አይባባሉም፤ ነገር ግን መነቃቃት ባለበት ስፍራ ክርስቲያኖች በተፈጥሮ ያደርጉታል። እንዲህ ያላደረጉበትን መነቃቃት ፈጽሞ አይቼ አላውቅም፤ ምናልባትም እንዲህ ያለ መነቃቃት ከቶ አልነበረም። ነገር ግን ይህ መቅረት እንደ ጀመረ የእግዚአብሔር መንፈስ ያዝናል፤ ከመካከላቸውም ይሄዳል።
13. ክርስቲያኖች ደጋግመው እንደ ገና ካልተለወጡ መነቃቃት ይደክማል፤ ይቋረጣልም። ይህን ስል ክርስቲያኖች በመነቃቃት መንፈስ ለመጽናት በአብዛኛው ደጋግመው በኃጢአት መወቀስ፣ መዋረድ፣ በእግዚአብሔር ፊት መሰበርና እንደ ገና መለወጥ ያስፈልጋቸዋል ማለቴ ነው። ስለ ክርስቲያን እንደ ገና መለወጥ ስንናገር ብዙዎች የማይረዱት ነገር ነው። እውነታው ግን በመነቃቃት ጊዜ የክርስቲያን ልብ ቅርፊት ሊለብስና ለመለኮታዊ ነገሮች የነበረውን ጥልቅ ጣዕም ሊያጣ ይችላል፤ በጸሎቱ የነበረው ቅባትና የማሸነፍ ኃይሉ ይቀንሳል፤ ያን ጊዜም እንደ ገና መለወጥ ያስፈልገዋል። በጥቂት ቀናት ልዩነት በእንዲህ ያለ ሂደት ካላለፈ ሥራውን እንዳይጎዳ አድርጎ በዚያ ሁኔታ ማቆየት አይቻልም። በሥራው ጸንቶ የሚቆይና መነቃቃትን ዘወትር ለመምራት ብቁ የሆነ፣ ሆኖም በሁለት ወይም በሦስት ሳምንት አንድ ጊዜ በዚህ የመሰበር ሂደት የማያልፍ ሰው ጋር በመነቃቃቶች ውስጥ አብሬ ሠርቼ አላውቅም። መነቃቃቶች በአብዛኛው የሚደክሙት ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ፊት እንድትሰበር በደሏንና ጥገኝነቷን እንድታስተውል ማድረግ የማይቻል ሆኖ ስለሚገኝ ነው። አገልጋዮች ይህን ማስተዋላቸው፣ ቤተ ክርስቲያንን እንዴት እንደሚሰብሩና ሲያስፈልጋቸውም ራሳቸውን እንዴት እንደሚሰብሩ መማራቸው አስፈላጊ ነው፤ አለዚያ ክርስቲያኖች በቶሎ በሥራቸው እንደ ማሽን ይሆናሉ፤ ግለታቸውንና በእግዚአብሔር ዘንድ የማሸነፍ ኃይላቸውን ያጣሉ። ጴጥሮስ አዳኙን በካደ ጊዜ ያለፈበት ሂደት ይህ ነበር፤ ጌታም በዚህ መሰበር በበዓለ ሃምሳ ቀን ለነበረው ታላቅ ሥራ አዘጋጀው። ከጥቂት ዓመታት በፊት «መሰበር» የሚለው ቃል ለአንዳንድ አገልጋዮችና ሃይማኖተኛ ነን ለሚሉ ሰዎች ማሰናከያ ሆኖ ሳገኘው ተደነቅሁ። ለኒቆዲሞስ የተሰጠውን «አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?» የሚለውን ተግሣጽ በራሳቸው ላይ አመጡ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ «መሰበር» ምን እንደ ሆነ እስኪያውቁ ድረስ ለመነቃቃት ጉዳይ ከዚህ የበለጠ ብዙ እንደማያደርጉ እርግጠኛ ነኝ።
14. ክርስቲያኖች ራስን መካድን ለመለማመድ እንቢ ሲሉ መነቃቃት ሊቀጥል አይችልም። ቤተ ክርስቲያን በመነቃቃት ደስ ተሰኝታ በእርሱ መወፈር ስትጀምርና ራስን ወደ ማስደሰት ስትገባ መነቃቃቱ ቶሎ ይቋረጣል። ኃጢአተኞችን ለማዳን ሁሉን ከተወው ከእግዚአብሔር ልጅ ጋር ካልተራሩ፣ ቅንጦታቸውንና ምቾታቸውን ለመተው፣ ራሳቸውንም ለሥራው ለመስጠት ፈቃደኞች ካልሆኑ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በላያቸው እንዲፈስስ ሊጠብቁ አይገባቸውም። ይህ ያለ ጥርጥር የግል መንፈሳዊ ውድቀት ዋና ምክንያቶች አንዱ ነው። በመነቃቃት ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ራስን ከመካድ ወደ ኋላ የማለትና አንዱን የራስ ማስደሰት ዓይነት ከሌላው በኋላ የመቀበል ዝንባሌ ሾልኮ ሲገባባቸው መጀመሪያ ባስተዋሉት ጊዜ ይጠንቀቁ! ይህ ከእግዚአብሔር ሥራ ሊያባብላቸው፣ ደንዛዞች፣ ሥጋውያን፣ ሰነፎች፣ ፈሪዎች፣ የማይጠቅሙና ፍትወተኞች ሊያደርጋቸው፣ መንፈስንም አባርሮ መነቃቃቱን ሊያጠፋ የሚጠቀምበት የሰይጣን ተንኰል ነው።
15. ስለ አዳዲስ ዘዴዎች በሚነሡ ክርክሮች መነቃቃት ይቆማል። መነቃቃትን ከዚህ የበለጠ በእርግጥ የሚገለብጥ ነገር የለም። ነገር ግን ያለፈው ትምህርቴ ስለ አዳዲስ ዘዴዎች ስለ ነበረ አሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ረዥም ጊዜ መቆየት አያስፈልገኝም።
16. የአሮጌው ወገን የማያቋርጥ ተቃውሞ ከአዲሱ ወገን ክፉ መንፈስ ጋር ሲጣመር መነቃቃቶች ሊጨፈለቁ ይችላሉ። መነቃቃትን ለማስፋፋት ምንም የማያደርጉ ተቃውሞአቸውን ቢቀጥሉ፣ እርሱን ለማስፋፋት የሚደክሙትም ትዕግሥት አጥተው ወደ ክፉ መንፈስ እንዲገቡ ራሳቸውን ቢፈቅዱ መነቃቃቱ ይቋረጣል። የአሮጌው ወገን ሰዎች በመነቃቃቶች ወይም በመነቃቃት ሰዎች ላይ በጋዜጦች ደብዳቤ ሲጽፉ፣ የአዲሱ ወገን ሰዎችም በቁጣ፣ በጠብና በምሬት መንፈስ መልሰው ሲጽፉባቸውና ወደ ጭቅጭቅ ክርክር ሲገቡ መነቃቃቶች ይቋረጣሉ። በሥራቸው ይጽኑ፤ ስለ ተቃውሞውም አይናገሩ፣ አይስበኩ፣ አያሳትሙም። ሌሎች ዘለፋቸውንና ከንቱ ነገራቸውን ማሳተም ቢመርጡ፣ የጌታ አገልጋዮች በሥራቸው ይጽኑ፤ በመነቃቃቱ የተሰማሩት ጉዳያቸውን እያሰቡ በሥራቸው እስከ ጸኑ ድረስ ጽሑፎቹና ሐሜቱ ሁሉ መነቃቃቱን አያስቆሙትም። ይህ በተግባር ምን ያህል እውነት ሆኖ እንደሚገኝ የሚያስደንቅ ነው።
መነቃቃት በነበረበት በአንድ ስፍራ አንዳንድ አገልጋዮች በቤተ ክርስቲያኒቱ እረኛ ላይ ተማማሉ፤ እርሱንም ለማጥፋት ዕቅድ ተነደፈ፤ በእውነትም በፕሬስቢተሪው ፊት አስከሰሱት፤ በመነቃቃቱ መካከል ስድስት ሳምንት የፈጀ ችሎት ሆነ፤ ሥራው ግን አሁንም ቀጠለ። የቤተ ክርስቲያኒቱ የሚጸልዩ አባላት ራሳቸውን ለሥራው እንዲህ ሰጡ፤ ስለዚህም በዚያ ሁሉ ትዕይንት ውስጥ በድል ቀጠለ። እረኛው ችሎቱን ለመከታተል ተጠራ፤ ነገር ግን በሕዝቡ መካከል የሚሠራ ሌላ አገልጋይ ነበረ፤ አባላቱም በአብዛኛው ወደ ችሎቱ እንኳ አልሄዱም፤ ይልቁንም ስለ ነፍሳት መጸለይና መድከም ቀጠሉ፤ መነቃቃቱም ማዕበሉን አልፎ ጸና። በሌሎች ብዙ ስፍራዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቃውሞ ተነሥቷል፤ ነገር ግን ጥቂት ትሑታን ነፍሳት በሥራቸው ጸንተዋል፤ ቸሩ እግዚአብሔርም የተገለጠ ክንዱን ዘርግቶ ተቃውሞው ሁሉ ቢኖርም መነቃቃቱ ወደ ፊት እንዲሄድ አደረገ።
ነገር ግን መነቃቃትን በማስፋፋት በትጋት የተሰማሩት በተቃውሞው ምክንያት የለሽነትና ግትርነት ሲበሳጩ፣ ሊታገሡት እንደማይችሉ ሲሰማቸው፣ ትዕግሥታቸውን ሲያጡ፣ ክርክራቸውን መመለስና ሐሜታቸውን ማስተባበል እንዳለባቸው ሲሰማቸው፣ ያን ጊዜ ወደ ኦኖ ሜዳ ይወርዳሉ፤ ሥራውም መቋረጡ አይቀርም።
17. የሕዝብን አሳብ የሚያዘናጋ ማንኛውም ነገር መነቃቃትን ያደናቅፋል። የሕዝብን ትኩረት በማዘናጋት የሚሳካለት ማንኛውም ነገር መነቃቃትን ያስቆማል። በጠቀስሁት ሁኔታ፣ አገልጋዩ በፕሬስቢተሪው ፊት ለፍርድ በቀረበበት፣ መነቃቃቱ ያልጠፋበት ምክንያት የቤተ ክርስቲያኒቱ የሚጸልዩ አባላት ራሳቸውን እንዲዘናጉ ስላልፈቀዱ ነው። ችሎቱን እንኳ አልተከታተሉም፤ ይልቁንም ስለ ነፍሳት መጸለይና መድከም ቀጠሉ፤ ስለዚህም የዲያብሎስ ጥረት ሁሉ ቢኖርም የሕዝብ ትኩረት በጉዳዩ ላይ ጸና።
ነገር ግን በሌላ በማንኛውም ጉዳይ የሕዝብን ትኩረት መዋጥ በተሳካለት ጊዜ ሁሉ መነቃቃቱን ያስቆመዋል። ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን ለውጥ የለውም። ከሰማይ መልአክ ወርዶ ቢሰብክ ወይም በጎዳናዎች ቢዘዋወር፣ ለመነቃቃት በዓለም ላይ ካሉ ነገሮች ሁሉ የከፋው ሊሆን ይችላል፤ ኃጢአተኞችን ከራሳቸው ኃጢአት፣ ቤተ ክርስቲያንንም ስለ ነፍሳት ከመጸለይ ፈጽሞ መልሶ ይህን የከበረ ፍጡር እንዲከተሉና እንዲመለከቱት ያደርጋቸዋልና፤ መነቃቃቱም ይቋረጣል።
18. የልከኝነትን ተሐድሶ መቃወም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መነቃቃቶችን ያስቆማል። ቤተ ክርስቲያን ከዚህ የከበረ ተሐድሶ ርቃ መቆምዋ ከእንግዲህ ከበደል ነጻ ሊሆን የማይችልበት ጊዜ ደርሷል። ይህ ባለማወቅ ሊደረግ የሚችልበት ጊዜ ነበረ። በመካከላቸው የሚያሰክር መጠጥ ይጠጣ የነበረ ቢሆንም አገልጋዮችና ክርስቲያኖች በመነቃቃት ደስ ሊሰኙ የሚችሉበት ጊዜ ነበረ። ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ብርሃን ከፈነጠቀና መጠጡ ጉዳት ብቻ እንደ ሆነ ከተገኘ ወዲህ፣ ማንም የቤተ ክርስቲያን አባል ወይም አገልጋይ በዚህ ጉዳይ ገለልተኛ ሆኖ ንጹሕ ሊሆን አይችልም። በግልጽ መናገርና ወገን መያዝ አለባቸው። በአንዱ ወገን አቋም ካልያዙ ተጽዕኖአቸው በሌላው ወገን ነው። የልከኝነትን ተሐድሶ ተቃውሞ አቋም የያዘና መነቃቃት ያገኘ አንድ አገልጋይ አሳዩኝ። አሁን ከእርሱ ርቆ የቆመና መነቃቃት ያለው አንድ አሳዩኝ። አሁን በዚህ ነጥብ ላይ የሚያመቻምች፣ ወጥቶም ለልከኝነት የማይቆም፣ ሆኖም መነቃቃት ያለው አንድ አሳዩኝ? ቀድሞ እንዲህ አልነበረም። አሁን ግን ጉዳዩ ተነሥቷል፣ ተመክሮበታል፣ ተረድቷልም፤ ማንም ሰው ዓይኑን ከእውነት ሊጨፍን አይችልም። ከልከኝነት ጉዳይ ርቆ የሚቆም ሰው እጆቹ በደም የቀሉ ናቸው። ታዲያ መነቃቃት ሊያገኝ ይችላልን?
19. አገልጋዮችና አብያተ ክርስቲያናት የሰውን መብት በሚመለከት በማንኛውም ጥያቄ የተሳሳተ አቋም ሲይዙ መነቃቃቶች ይደናቀፋሉ። ለምሳሌ የባርነትን ጉዳይ ውሰዱ። ይህ ጉዳይ በሕዝብ አሳብ ፊት ያልነበረበት ጊዜ ነበረ። ጆን ኒውተን ከተለወጠ በኋላ በባሪያ ንግድ ቀጥሎ ነበር። አእምሮው እንዲህ ተጣምሞ፣ ሕሊናውም በዚህ እጅግ ክፉ ንግድ ረገድ እንዲህ ፈጽሞ ደንዝዞ ስለ ነበረ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንጂ ኃጢአትነቱ ወደ አሳቡ ፈጽሞ አልመጣም ነበር። ከመለወጡ በፊት በአእምሮው ላይ ብርሃን ፈስሶ ቢሆን ኖሮ ይህን ኃጢአት አስቀድሞ ሳይተው ፈጽሞ ሊለወጥ ባልቻለ ነበር። ከተለወጠም በኋላ ክፋቱን ባመነ ጊዜ ኃጢአቱን ለዘላለም ሳይተው በእግዚአብሔር ፊት ደስ ሊሰኝ አልቻለም። እንዲሁም በዚህ ርኩሰት ቢካፈሉም ኃጢአትነቱ ለአእምሮአቸው ግልጽ ስላልነበረ በገዛ አገራችን ብዙ የባሪያ ነጋዴዎችና ባሪያ ገዢዎች ያለ ጥርጥር ተለውጠዋል። እንዲሁም በምድሪቱ ሁሉ አገልጋዮችና አብያተ ክርስቲያናት በብዙ መጠን ዝም ብለዋል፤ በቤተ ክርስቲያንና በሕዝቡ ውስጥ ባለው በዚህ አስጸያፊ ርኩሰት ላይ ምንም ምስክርነት አልሰጡም። ነገር ግን በቅርቡ ጉዳዩ ለውይይት ተነሥቷል፤ የእግዚአብሔርም መግቦት በሰዎች ሁሉ ዓይን ፊት በግልጽ አቅርቦታል። በልከኝነት ጉዳይ ላይ እንደ ሆነው አሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ብርሃን ፈንጥቋል። እውነታዎች ቀርበዋል፤ መርሆች ጸንተዋል፤ በሰዎች አእምሮ ላይ ብርሃን በርቷል፤ ይህም ጭራቅ ከአስፈሪው ዋሻው ተጎትቶ ወጥቶ በቤተ ክርስቲያን ፊት ቀርቧል፤ እነርሱም «ይህ ኃጢአት ነውን?» ተብለው ይጠየቃሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ምስክርነታቸውን መስጠት አለባቸው። እነርሱ የእግዚአብሔር ምስክሮች ናቸው። «እውነቱን፣ ሙሉውን እውነት፣ ከእውነትም በቀር ሌላ ምንም» ሊናገሩ ምለዋል። ምስክርነታቸው በአንዱ ወገን ወይም በሌላው ሳይሰጥ መቅረቱ የማይቻል ነው። ዝምታቸው ከእንግዲህ ባለማወቅ ወይም ትኩረታቸው ወደ ጉዳዩ ከቶ ስላልተመለሰ ነው ተብሎ ሊገለጽ አይችልም። ስለዚህ ክርስቲያኖች በዚህ ጉዳይ ላይ ዝም ማለታቸው ባርነትን እንደ ኃጢአት እንደማይቆጥሩት በተግባር መናገር ነው። እውነቱ ይህ ነው፤ ያለ በደል ዝም ሊሉበት የማይችሉት ጉዳይ ነው። በእግዚአብሔር መግቦት፣ ከደቡብ የሚነፍሰው ነፋስ ሁሉ በልቅሶ፣ በዋይታና በወዮታ ጩኸት ተጭኖ የሚመጣበት ጊዜ ደርሷል። በገዛ አገራችን የተዋረዱ ሁለት ሚሊዮን አሕዛብ በሰንሰለት የታሰሩና የሚደሙ እጆቻቸውን ዘርግተው ወደ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን የሥቃይ የእርዳታ ጩኸት ይልካሉ። ታዲያ ቤተ ክርስቲያን ዓለምን ለመመለስና ለማዳን በምታደርገው ጥረት ለዚህ የሥቃይና የተስፋ መቁረጥ ድምፅ ጆሮዋን ትደፍናለችን? አይሁን። ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ጥያቄ ፊቷን ልታዞር አትችልም። ቤተ ክርስቲያንና ሕዝቡ ሊወስኑበት የሚገባ ጥያቄ ነው፤ እግዚአብሔርም ወደ ውሳኔ ያደርሰዋል።
አብያተ ክርስቲያናት መከፋፈልን፣ ጠብንና ክርክርን በመፍራት ይህን መቃወማቸው ከንቱ ነው። ይህን የጭንቅ ጩኸት ከመስማት ጆሮን መመለስ እንደ እግዚአብሔርን የመፍራት ተግባር መቁጠር ከንቱ ነው።
ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጉዳይ ላይ መመስከር አለባት፤ «እውነቱን፣ ሙሉውን እውነት፣ ከእውነትም በቀር ሌላ ምንም» መመስከር አለባት፤ አለዚያ በሐሰት የማለች ትሆናለች፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ ከእርስዋ ይለያል። ለመመስከር በመሐላ ሥር ናት፤ ኃጢአት ነው ብለው የማይናገሩ አገልጋዮችና አብያተ ክርስቲያናትም ለእግዚአብሔር የሐሰት ምስክርነት ይሰጣሉ። በአሁኑ ጊዜ ሃይማኖት በዝቅተኛ ሁኔታ ላይ ከሚገኝበት ምክንያቶች አንዱ፣ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በባርነት ጉዳይ የተሳሳተውን ወገን መያዛቸው፣ ጭፍን አመለካከት በመርሆ ላይ እንዲያሸንፍ መፍቀዳቸውና ይህን ርኩሰት በእውነተኛ ስሙ ለመጥራት መፍራታቸው መሆኑ ያለ ጥርጥር እውነት ነው።
20. መነቃቃቶችን የሚያደናቅፍ ሌላው ነገር የሚስዮንን ጥሪዎች ቸል ማለት ነው። ክርስቲያኖች ለአሕዛብ ባይራሩ፣ ወርሃዊውን የጸሎት ስብሰባ ቸል ቢሉ፣ ትኩረታቸውንም በራሳቸው ቤተ ክርስቲያን ብቻ ቢወስኑ፣ ሚሽነሪ ሄራልድ የተባለውን መጽሔት እንኳ ባያነቡ ወይም ስለ ዓለም ጥሪዎች ራሳቸውን የሚያሳውቁበት ሌላ ማንኛውንም መንገድ ባይጠቀሙ፣ እግዚአብሔር በፊታቸው የሚያበራውን ብርሃን ቢጥሉ፣ በዚህም ጉዳይ እግዚአብሔር እንዲያደርጉ የሚጠራቸውን ባያደርጉ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ከእነርሱ ይለያል።
21. ቤተ ክርስቲያን ወጣቶችን ለአገልግሎት እንድታስተምር እግዚአብሔር የሚያቀርብላትን ጥሪ ስትጥል መነቃቃትን ታደናቅፋለች፤ ታጠፋለችም። የፕሬስቢቴሪያንን ቤተ ክርስቲያን ተመልከቱ፤ በአሥር ዓመት ውስጥ የተለወጡትን 200,000 ነፍሳት፣ ዓለምን በአገልጋዮች ለመሙላት የሚበቃ ሀብትም ተመልከቱ፤ ሆኖም አገልግሎቱ እንደ ገዛ አገራችን የሕዝብ ቍጥር ፈጥኖ እየጨመረ አይደለም፤ አገልጋዮችን ለማዘጋጀት ከዚህ የበለጠ ነገር ካልተደረገ እኛ ራሳችን አሕዛብ እንሆናለን። አብያተ ክርስቲያናት ወደ አገልግሎት የመግባትን ግዴታ በወጣቶች ላይ አጥብቀው አያቀርቡም። እግዚአብሔር መንፈሱን በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ያፈስሳል፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ነፍሳትንም ይለውጣል፤ ታዲያ ሠራተኞቹ ወደ መከሩ ካልወጡ፣ የእግዚአብሔር እርግማን በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ከመምጣቱ፣ መንፈሱ ከመወሰዱና መነቃቃቶች ከመቋረጣቸው በቀር ምን ሊጠበቅ ይችላል? በዚህ ጉዳይ ማንም አገልጋይ፣ ማንም ቤተ ክርስቲያን ዝም ወይም ሥራ ፈት ሊሆን አይገባውም።
22. መነቃቃቶችን ማማት ብዙ ጊዜ ያጠፋቸዋል። በፕሬዚዳንት ኤድዋርድስ ዘመን የነበረው ታላቅ መነቃቃት በዚህ ረገድ በቤተ ክርስቲያን ጠባይ እጅግ ተጎዳ። የእግዚአብሔር ጠላቶች መነቃቃቶችን እንዲሰድቡ፣ እንዲያጣምሙና እንዲያሙ የሚጠበቅ ነው። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ራስዋ በዚህ ሥራ ስትሰማራ፣ ከአባሎችዋም እጅግ ተጽዕኖ ያላቸው ብዙዎቹ የከበረውን የእግዚአብሔር ሥራ በማማትና በማጣመም ሲረዱና ሲያበረታቱ፣ መንፈስ አዝኖ ቢሄድ ተገቢ ነው። ይህ እጅግ በሚያሳዝንና እግዚአብሔርን በሚያዋርድ መጠን መደረጉ ሊካድ አይችልም። ይህ መነቃቃት ከጀመረ ወዲህ በአንድ ዓመት ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ መቶ ሺህ ነፍሳት ወደ እግዚአብሔር እንደ ተለወጡ ተገምቷል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ ከተለወጡት ሁሉ ይህ ያለ ጥርጥር ታላቁ ቍጥር ነበረ። ይህ በ1831 ነበረ። ከዚያ ወዲህ ይበልጥ ሰፊ መነቃቃቶች ሆነዋል። በ1857-8 በዩናይትድ ስቴትስ ሰሜናዊ ክፍል ለስድስት ወይም ለስምንት ሳምንታት በተከታታይ በየሳምንቱ 50,000 ሰዎች እንደ ተለወጡ ተገምቷል። በዚህ መጠን ባለ መነሣሣት፣ በሰዎች መካከል፣ የሚያስቆጭ ምንም ነገር እንዳይኖር መጠበቅ አይቻልም ነበር። እንዲህ ባለ፣ በዚህ መጠን ባለና በሰው መሣሪያነት በሚካሄድ ሥራ ፍጽምናን መጠበቅ ፈጽሞ ምክንያታዊ ያልሆነና የማይረባ ነው። ክፉ ነገሮች ያለ ጥርጥር ነበሩ፤ አሁንም አሉ። በእርግጥ የሚጠበቁ ነበሩ፤ በተቻለም መጠን ሊጠነቀቁባቸው ይገባ ነበር። በመጠንና በተጽዕኖ ወደዚህ የሚቀርብ መነቃቃት በዚህ ያህል ጥቂት ክፉ ነገሮችና በቅንነት ሊያስቆጩ በሚችሉ በዚህ ያህል ጥቂት ነገሮች የታጀበበትን አንድ ምሳሌ የዓለም ታሪክ ሊያቀርብ ይችላል ብዬ አላምንም።
ነገር ግን ይህ የተባረከ የእግዚአብሔር ሥራ እንዴት ተስተናገደ? የሚወቀሱት ክፉ ነገሮች ሁሉ እውነተኛ ናቸው ብንል እንኳ፣ ይህ ደግሞ ከእውነት እጅግ የራቀ ነው፣ በከበረው ፀሐይ ገጽ ላይ እንዳሉ ነጠብጣቦች ብቻ በሆኑ ነበር፤ ከሥራው ወሰን የሌለው ታላቅነትና ብልጫ ጋር ሲነጻጸሩ ሊታሰቡ እንኳ የማይገባቸው ነገሮች ናቸው። ሆኖም የፕሬስቢቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ክፍል ይህን የተባረከ የእግዚአብሔር ሥራ እንዴት ተቀበለውና አስተናገደው? በዚህ ታላቅ ሥራ መካከል የፕሬስቢቴሪያንን ቤተ ክርስቲያን በሚወክለው በዚያ የተከበሩ ሰዎች ስብስብ በሆነው ጠቅላላ ጉባኤ፣ የምስጋና ቀን ከመወሰን ይልቅ፣ ስለ ሥራውም ታላቅነት እግዚአብሔርን ከማመስገንና ከማክበር ይልቅ፣ ከእነርሱ የምንሰማው የተግሣጽ ድምፅ ነው። እዚያ ስለ ተደረጉት ንግግሮች ከቀረቡት ዘገባዎች እንደሚታየው አዳራሹ በማጉረምረም ተሞልቶ ነበር። ሥራውን ወደ ፊት የሚያራምዱ ዘዴዎችን ከመቀየስ ይልቅ ትኩረታቸው ከሥራው ጋር አብረው በሚመጡ በአንጻሩ ጥቃቅን በሆኑ ክፉ ነገሮች የተያዘ ይመስል ነበር። ከብዙ ማጉረምረምም በኋላ ኮሚቴ እስከ መሾም ደረሱ፤ ጥርጣሬን የሚያነሣሣ፣ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ቅንዓት የሚያጠፋ፣ ስለ በረከቱ ታላቅነት ለእግዚአብሔር ክብር ከመስጠት መልሶ ስለ ክፉ ነገሮች ወደ መንቀፍና ወደ መነዝነዝ የሚያዞራቸው «የእረኝነት ደብዳቤ» ወደ አብያተ ክርስቲያናት ላኩ። በዚያ ጠቅላላ ጉባኤ የተደረገውን በሰማሁ ጊዜ፣ ንግግሮቻቸውን ባነበብሁ ጊዜ፣ የእረኝነት ደብዳቤአቸውን ባየሁ ጊዜ ነፍሴ ታመመች፤ የማይነገር የጭንቅ ስሜት በአእምሮዬ ላይ መጣ፤ እግዚአብሔርም የፕሬስቢቴሪያንን ቤተ ክርስቲያን ስለዚህ ዓይነቱ ድርጊት «እንደሚጎበኛት» ተሰማኝ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክብሩ እየለቀቀ ሄዷል፤ መነቃቃቶችም እያነሱና እያነሱ—ኃይላቸውም እየቀነሰና እየቀነሰ መጥቷል። እንደ ዶክተር ላይማን ቢቸርና አቶ ኔትልተን ያሉ ሰዎች እንግዳ ተቃውሞ ይህን ተቃውሞ በማነሣሣትና በመደገፍ ረገድ ብዙ ድርሻ ነበረው።
አሁንም በጠቅላላ ጉባኤው መድረክ ላይ ያንን ማጉረምረም ያፈሰሱትና ያንን የእረኝነት ደብዳቤ በማዘጋጀት ተሳታፊ የነበሩት አገልጋዮች ከዚያ ወዲህ ሃይማኖታዊ መነቃቃትን በማስፋፋት ተባርከው እንደ ሆነ—የእግዚአብሔር መንፈስ በላያቸው እንደ ሆነ፣ አብያተ ክርስቲያኖቻቸውም ከቅዱሱ ቅባት እንዳላቸው ሊመሰክሩ ይችሉ እንደ ሆነ ቢታወቅ ደስ ባለኝ።
23. የቤተ ክህነት ውዝግቦች መንፈስን አሳዝነው የሚያርቁና መነቃቃቶችን የሚያጠፉ ናቸው። የአገልጋዮችን ትኩረት ከጌታ ሥራ ወደ ክርክሮችና ወደ ቤተ ክህነት ሙግቶች ማዞር ሁልጊዜ የዲያብሎስ ስልት ሆኖ ኖሯል። ፕሬዚዳንት ኤድዋርድስ በቤተ ክህነት ጉባኤዎች ፊት በክርክሮች ለረዥም ጊዜ ለመያዝ ተገድዶ ነበር፤ በእኛም ዘመን፣ በእነዚህ ታላላቅ ሃይማኖታዊ መነቃቃቶች መካከል፣ እነዚህ ውዝግቦች በሚያስደነግጥና በሚያሳፍር ሁኔታ በዝተዋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እጅግ ውጤታማ ከሆኑት አገልጋዮች አንዳንዶቹ ነፍሳትን ለክርስቶስ ለመማረክ ከሚያደርጉት ቀጥተኛ ጥረት ተጠርተው፣ በእነርሱ ላይ ወይም በአገልግሎት ባልደረቦቻቸው ላይ የቀረቡትንና ፈጽሞ ሊጸኑ የማይችሉትን ክሶች ለመከታተል ቀን በቀን፣ በአንዳንድ ሁኔታም ሳምንት በሳምንት ተገድደዋል።
ፊላደልፊያን ተመልከቱ፤ ማብቂያ የሌላቸውና አሳፋሪ ጭቅጭቆች በዚያች ከተማ፣ በምድሪቱም ርዝመትና ስፋት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል አወኩ፣ አሳዘኑም። በፕሬስቢቴሪያን ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይም እነዚህ የቤተ ክህነት ውዝግቦች ፍጥረትን የሚያስለቅስ በቂ ክፋት አስከትለዋል። ወንድም ቢማን መነቃቃቶችን ከማስፋፋት በአሳፋሪና በክፉ ሁኔታ ተጠርቶ፣ እውነት ቢሆኑ እንኳ አብዛኞቹ የሚያስቁ በሆኑና ፈጽሞ ሊጸኑ በማይችሉ ክሶች በገዛ ፕሬስቢተሪው ፊት ችሎት እንዲከታተል ተደረገ። ከዚያን ጊዜ ወዲህም፣ የግድ ይመስላል፣ ከጊዜው ታላቅ ክፍል የቤተ ክህነት ውዝግቦችን በማስተካከል ተይዟል። የካርላይሉ ወንድም ዳፊልድ፣ የፊላደልፊያው ወንድም ባርንስና ሌሎችም እጅግ የተሳካላቸው የእግዚአብሔር አገልጋዮች ለዓመታት በእነዚህ ውዝግቦች ከጊዜአቸው ብዙውን ተስተጓጉለዋል። በጌት አትንገሩ! ራሳቸው ጥቂት ወይም ምንም የማያደርጉ እነዚያ አገልጋዮችና ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ሌሎችን ተዉ ብለው ለእግዚአብሔር እንዲሠሩ የሚፈቅዱላቸው መቼ ነው?
24. መነቃቃቶች ሊደናቀፉ የሚችሉበት ሌላው ነገር በሁለቱም ወገን፣ በተለይም መነቃቃትን ወደ ፊት በማራመድ በተሰማሩት ዘንድ ያለ ፈራጅነት ነው። የሥራው ተቃዋሚዎች የወዳጆቹን መሰናከል እንደሚጠባበቁ፣ ስሕተት ስለ ሆነው ሁሉ፣ ብዙ ጊዜም በጠባያቸው ትክክል ስለ ሆነው እንደሚነቅፏቸው የሚጠበቅ ነው። በተለይም ሥራውን በማስፋፋት ረገድ ታዋቂ መሣሪያዎች በሆኑት ላይ ብዙ ፈራጅና ክርስቲያናዊ ያልሆኑ አስተያየቶች እንደሚሰነዘሩ የሚጠበቅ ነው። ይሁን እንጂ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ይሁኑ ከውጭ፣ በሥራው ተቃዋሚዎች በኩል ያለው ይህ ፈራጅነት በራሱ መነቃቃቱን አያስቆመውም። አስፋፊዎቹ በትሕትናና በጸሎት መንፈስ እስከ ጸኑ ድረስ፣ አጸፋ ሳይመልሱ ነፍሳቸውን በትዕግሥት እስከ ያዙ ድረስ፣ እንዲዘናጉ፣ እንዲወነጅሉና የጸሎትን መንፈስ አሳዝነው እንዲያርቁ ራሳቸውን እስካልፈቀዱ ድረስ ሥራው ወደ ፊት ይሄዳል፤ በመነቃቃት መካከል አገልጋዩ ለስድስት ሳምንት ለፍርድ በቀረበበት በተጠቀሰው ሁኔታ እንደ ሆነው። በዚያ ሕዝቡ በትቢያ ውስጥ ጸንተው ጸለዩ፤ ስለ አገልጋያቸው ብዙም አይደለም፤ እርሱን ለእግዚአብሔር ትተውት ነበርና፤ ነገር ግን በብርቱ ጩኸትና በእንባ ስለ ኃጢአተኞች እግዚአብሔርን ተማጸኑ። እግዚአብሔርም ሰማቸው፣ ባረካቸውም፤ ሥራውም ቀጠለ። ሥራውን በሚቃወሙት ዘንድ ያለ ፈራጅነት ብዙም የሚያስፈራ አይደለም፤ መንፈስ የላቸውምና፣ በእነርሱም ላይ የተመሠረተ ምንም ነገር የለምና፤ ሥራውን ሊያደናቅፉ የሚችሉት ራሳቸው በግል ተጽዕኖ እስካላቸው መጠን ብቻ ነው። ሌሎቹ ግን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል አላቸው፤ ሥራውም በትክክለኛ መንፈስ በመጽናታቸው ላይ የተመሠረተ ነው። ቢሳሳቱና መንፈስን አሳዝነው ቢያርቁ ምንም ረዳት የለም፤ ሥራው መቋረጡ አይቀርም። ስለዚህ የዚህ የተባረከ ሥራ አስፋፊዎች ምንም ዓይነት ማበሳጨት ቢደርስባቸው፣ ሥራው ቢቋረጥ ኃላፊነቱ የእነርሱ ይሆናል። በዚህ ጉዳይ ረገድ እጅግ ከሚያስደነግጡ እውነታዎች አንዱ ደግሞ ሥራውን ወደ ፊት በማራመድ የተሰማሩት በብዙ ሁኔታዎች መንፈስን ያጡ መምሰላቸው ነው። እየተዘናጉ ናቸው፤ ተቃውሞው ከእንግዲህ ሊታገሡት የማይገባ እንደ ሆነ፣ ወጥተውም ተቃዋሚዎቹ ለሚሉት በጋዜጦች መልስ መስጠት እንዳለባቸው ማሰብ ጀምረዋል። የዚህ ከመነቃቃቶች ሁሉ ታላቅ የሆነው ወዳጆችና አስፋፊዎች ራሳቸውን ለመከላከልና በእነርሱ ላይ ለሚጽፉት መልስ ለመስጠት ወደ ጋዜጣ ጭቅጭቅ እንዲጠሩ በፈቀዱ ጊዜ ሁሉ የጸሎት መንፈስ ፈጽሞ አዝኖ እንደሚርቅና ሥራው እንደሚቋረጥ ሊታወቅና በሁሉ ዘንድ ሊታመን ይገባል። አስፋፊዎቹ ተቃውሞውን ሰምተው መልስ መስጠት ከመጀመራቸው የበለጠ ለሃይማኖታዊ መነቃቃቶች የሚጎዳ ነገር የለም፤ ሁልጊዜም እንዲሁ ሆኖ ተገኝቷል። ስለ መነቃቃቶች የጻፈውን መጽሐፉን የምታውቁ እንደምታስተውሉት ይህ በፕሬዚዳንት ኤድዋርድስ ዘመን እውነት ሆኖ ተገኝቷል።
III. ላለፉት አሥር ዓመታት ሲካሄድ የነበረውን ይህን ታላቅና የከበረ ሃይማኖታዊ መነቃቃት ለማስቀጠል ሊደረጉ የሚገባቸውን አንዳንድ ነገሮች ወደ መጥቀስ እሄዳለሁ።
1. በአገልጋዮች በኩል ታላቅና ጥልቅ ንስሐ ሊኖር ይገባል። ወንድሞቼ ሆይ፣ እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን ማዋረድ አለብን። ሕዝቡን ወደ ንስሐ መጥራት ብቻ በቂ ነው ብለን ማሰብ አይሆንልንም። እኛ ንስሐ መግባት አለብን፤ በንስሐ ቀዳሚ መሆን አለብን፤ ከዚያም አብያተ ክርስቲያናት እንዲከተሉ መጥራት አለብን።
በተለይም ስለ መነቃቃቶች የተቃውሞና የአለመተማመን ስሜትን በማስነሣት ቀዳሚ የነበሩት ንስሐ መግባት አለባቸው። አንዳንድ አገልጋዮች በመነቃቃቶችና በመነቃቃት ዘዴዎች ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በገዛ ጉባኤዎቻቸው ብቻ ወስነዋል፤ ሥራው በመካከላቸው እንዳይስፋፋና እንዳያሸንፍ በገዛ ሕዝባቸው መካከል እንዲህ ያለ ጥርጣሬ ፈጥረዋል። እንዲህ ያሉ አገልጋዮች ፕሬዚዳንት ኤድዋርድስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠውን አስተያየት ቢያስቡበት መልካም ነው።
«አገልጋዮች ምንም ያህል መልካም ትምህርት ቢሰብኩ፣ በሥራቸውም ምንም ያህል ቢደክሙና ቢተጉ፣ እንደዚህ ባለ ዘመን ለዚህ ሥራ በጎ አመለካከት እንደሌላቸው፣ ይልቁንም እጅግ እንደሚጠራጠሩትና እንደማይተማመኑበት ለሕዝባቸው ቢያሳዩ፣ ከመልካም ይልቅ በሕዝባቸው ላይ እጅግ የበዛ ጉዳት ማድረሳቸው አይቀርም፤ ሕዝባቸው የእግዚአብሔር ሥራ እንደ ሆነ እንዲያምኑ ቢፈቀድላቸው ኖሮ፣ የእንዲህ ያለው ታላቅና ልዩ የእግዚአብሔር ሥራ ዝና ራሱ፣ የሌሎች ከተሞች ምሳሌም፣ አልፎ አልፎ ከሚሰሙት ስብከት ጋር፣ ሕዝባቸውን በሃይማኖት ለማንቃትና ለማነቃቃት በአእምሮአቸው ላይ ከድካማቸው ሁሉ እጅግ የበለጠ ተጽዕኖ ይኖረው ነበርና፤ ከዚህም በላይ የአገልጋያቸው አስተያየት በውጭ ስለሚሰሙት ሥራ ጥርጣሬን ይወልድባቸዋል፤ በዚህም በእርሱ የሚገለጠው ኃያሉ የእግዚአብሔር እጅ በአእምሮአቸው ላይ ተጽዕኖውን ያጣል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው በሚገለጠው ተመሳሳይ ባሕርይ ባለው ነገር ሁሉ ላይ፣ በምድሪቱ ላይ እንደ ወረርሽኝ የተስፋፋው ያው በሽታ እንደ ሆነ አድርገው፣ ጥርጣሬን ይፈጥራል፤ ይህም በውጤቱ በሕያው ሃይማኖት ሁሉ ላይ ጥርጣሬን መፍጠር ነው፤ በተገለጠበትም ስፍራ ሁሉ ሕዝቡ እንዲቃወመውና እንዲያሰናክሉት፣ እንደ ተነሣም ወዲያው ራሱን እንዲመቱት ማድረግ ነው። አገልጋዮች የሆንነው እኛም ከዓመት ወደ ዓመት ይህን ሥራ በቅር በተሰኘ ፊት ብንመለከት፣ እንደ እረኞች በመመገብ ድርሻችንን ከመወጣት ይልቅ በጎቹን ከመሰማሪያቸው በእርግጥ እናግዳቸዋለን፤ ሕዝባችንም እንደዚህ ባለ ዘመን ምንም ቋሚ አገልጋይ ባይኖራቸው እጅግ በተሻላቸው ነበር።»
ሌሎች ይበልጥ በይፋ ሠርተዋል፤ ሰፊ ተጽዕኖ ለማሳደርም አልመዋል። አንዳንዶቹ ለሕዝብ ጋዜጦች ጽሑፎችን ጽፈዋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍ ያለ ማዕረግ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች ፈጽሞ ያልታተሙ ደብዳቤዎችን አሰራጭተዋል። ሌሎች ደብዳቤዎቻቸውን አሳትመው አሰራጭተዋል። በአገሩ ሁሉ አለመተማመንን ለመፍጠር የታለመ የደብዳቤ አጻጻፍ ሥርዓት የነበረ ይመስላል። በፕሬዚዳንት ኤድዋርድስ ዘመን በመሠረቱ ያው አካሄድ ተከትሎ ነበር፤ ይህንም በማየት ስለ መነቃቃቶች በጻፈው ሥራው እንዲህ ይላል፦
«ማተሚያው ለዚህ ሥራ ጥቅም ተቃራኒ ለሆነ ዓላማ እንዳይውል ታላቅ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። እግዚአብሔር ለተጨቆነችው ቤተ ክርስቲያኑ መዳን ሲሳራን በተዋጋ ጊዜ የጸሓፊን በትር የሚይዙ በዚያ ጉዳይ ጌታን ለመርዳት እንደ መጡ እናነባለን።—መሳፍንት 5፥14። የታሰቡት በእስራኤል ውስጥ ምንም ዓይነት ሰዎች ቢሆኑ፣ ቃሉ የተጻፈው እስከ ዓለም ፍጻሜ ያሉትን ድርጊቶች ሁሉ ፍጹም አድርጎ በሚያይ መንፈስ ስለ ሆነ፣ በዚህም መዝሙር የእስራኤል ይህ መዳን ምሳሌ ወደ ሆነለት በኋለኛው ዘመን ወደሚሆነው ወደዚያ ታላቅ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን መዳን በተለየ ዓይን ስለ ተመለከተ፣ በብዕራቸው የሰይጣንን መንግሥት የሚዋጉትን ጸሓፊዎች ማመልከቱ የማይመስል አይደለም። ስለዚህ በዚህ ሥራ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በጥርጣሬ ሥር የሚጥሉት፣ የሚያሰናክሉት ወይም የሚያደናቅፉት በራሪ ጽሑፎችን የሚያሳትሙ ሰዎች፣ ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ሥራ እንዳልሆነ፣ ከሆነም እግዚአብሔር በመንገዱ የሚቆሙትን ሁሉ ሊበላ እንደ እሳት እንደማይወጣና እነዚያን በራሪ ጽሑፎች እንደማያቃጥል፣ በእነርሱም ውስጥ የተቀጣጠለው እሳት ጸሓፊዎቹን እንዳያቃጥል አደጋ እንደሌለ በሚገባ ቢያስቡበት መልካም ነው።»
እነዚህ ሁሉ ንስሐ መግባት አለባቸው። ንስሐ እስኪገቡ ድረስ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይቅር አይላቸውም፤ በስብከታቸውም ላይ በረከቱን ፈጽሞ አያገኙም፤ በመነቃቃቶችም ለመሥራት አይከበሩም። ፕሬዚዳንት ኤድዋርድስ ይህን ግዴታ በዘመኑ በነበሩት አገልጋዮች ላይ እጅግ በብርቱ ቃላት አጥብቆ አቀረበ። ያን ጊዜ እንደ ነበሩ አሁንም በሁለቱም ወገን ስሕተቶች ያለ ጥርጥር ነበሩ። ጥልቅ ንስሐና በሁለቱም ወገን እርስ በርስ ስሕተትን መናዘዝ ሊኖር ይገባል።
«በሁለቱም ወገን ስሕተትን በመናዘዝ ብዙ ነገር ሊደረግ ይገባል፤ በቅርቡ በነበሩት ጭቅጭቆችና ሁከቶች፣ በብርሃንና በጨለማ መደባለቅም የተፈጸሙት ስሕተቶች ያለ ጥርጥር ብዙዎችና ታላላቆች ናቸውና። ከተበላሸው ዝንባሌአችን ይበልጥ የሚቃረንና የሰውን ትዕቢት ይበልጥ የሚገድል ግዴታ ከቶ የለም፤ ነገር ግን መደረግ አለበት። መጥምቁ ዮሐንስ ከሰበከው እንደሚታየው፣ መንግሥተ ሰማያት በቀረበች ጊዜ፣ ወይም በተለይ እንድትመጣ በምንጠብቅበት ወይም በምንመኝበት ጊዜ፣ ከስሕተት ንስሐ መግባት ልዩ በሆነ መንገድ ተገቢ ግዴታ ነው። እግዚአብሔርም አሁን ንስሐ እንድንገባ በታላቅ ድምፅ የሚጠራን ከሆነ፣ ንስሐችንን በተገቢው ሁኔታ እንድንገልጥም ይጠራናል። ይህን ሥራ በግልጽ የተቃወሙ ወይም ከጊዜ ወደ ጊዜ በቀላሉ የተናገሩበት፣ በተለይ አገልጋዮች ከሆኑ፣ በዚህ ረገድ ስሕተታቸውን በግልጽ ሳይናዘዙ በእግዚአብሔር ፊት ሊያመልጡ እንደማይችሉ ተረድቻለሁ። በማንኛውም መንገድ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ ሥራውን ከተቃወሙ ወይም በሕዝብ ፊት ባደረጉት አገልግሎት ወይም በግል ንግግራቸው የሕዝባቸውን አእምሮ በሥራው ላይ እንዲያጣምም አድርገው ከተመላለሱ፣ ከዚህ በኋላ የተቃወሙት ነገር መልካምነትና መለኮታዊነት ቢገለጥላቸው፣ ጉዳዩን ማቃለል፣ ራሳቸውን ማመካኘት፣ ሁልጊዜ እንዲህ ያስቡ እንደ ነበረና የተቃወሙት እንዲህና እንዲህ ያሉትን አለማስተዋሎች ብቻ እንደ ሆነ ማስመሰል ፈጽሞ አይገባቸውም፤ ይልቁንም እምነታቸውን በግልጽ ማወጅና ስላደረጉት ነገር ራሳቸውን መኮነን ይገባቸዋል፤ ይህን ሥራ በማቃለልና ሌሎችን በእርሱ ላይ በማጣመም የተናገሩበት ክርስቶስን ነውና፤ እንዲያውም ከዚያ የከፋ፣ መንፈስ ቅዱስን ነው። ባለማወቅና ባለማመን ቢያደርጉትም እንኳ፣ የተቃወሙት ማን እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ እግዚአብሔር በይፋ እንዲናዘዙት ያለ ጥርጥር ይጠይቃቸዋል።
በሌላው ወገን ደግሞ፣ ሥራውን ለማስፋፋት የቀኑት ከላይ በተጠቀሱት በማናቸውም ሁኔታዎች በግልጽ ከመንገድ እጅግ ወጥተው፣ ከክርስቲያናዊ ሥርዓት ተቃራኒ የሆነውን አድርገው፣ በዚህም ሌሎችን በግልጽ ጎድተው ወይም መልካም ሥርዓትን እጅግ ጥሰው፣ ሃይማኖትንም የሚያቆስል ነገር ሠርተው ከሆነ፣ ድንጋዮቹን ለቅመው የእግዚአብሔርን ሕዝብ መንገድ እንደሚያዘጋጁ፣ በይፋ ሊናዘዙትና ራሳቸውን ሊያዋርዱ ይገባቸዋል። በግልጽ መተላለፋቸው በሌሎች መንገድ ላይ ታላላቅ ማሰናከያዎችን ያኖሩ በግልጽ ንስሐቸው ሊያስወግዷቸው ግዴታ አለባቸው።»
በዘመናችን አገልጋዮች አሉ፤ ይህን የምለው በክፋት ሳይሆን በታማኝነት ነው፤ ስናገረውም ሁሉም እዚህ በፊቴ ቢሆኑ በወደድሁ ነበር፤ ለዓመታት ከጊዜአቸው ብዙውን በመነቃቃቶች ላይ ጥርጣሬ በሚፈጥር መንገድ ከመሥራት፣ ከመናገርና ከመጻፍ በቀር ሌላ ጥቂት ነገር ብቻ ያደረጉ የሚመስሉ። ፕሬዚዳንት ኤድዋርድስ እንዳለው፣ ንስሐ ገብተው በረከቱን መልሰው ካላገኙ በቀር አብያተ ክርስቲያኖቻቸው ምንም አገልጋይ ባይኖራቸው እንደሚሻላቸው ልጠራጠር አልችልም።
2. መነቃቃቶችን የተቃወሙ አብያተ ክርስቲያናት ራሳቸውን ማዋረድና ንስሐ መግባት አለባቸው። ከሥራው ርቀው የቆሙ ወይም ያደናቀፉት አብያተ ክርስቲያናት ከኃጢአታቸው ንስሐ መግባት አለባቸው፤ አለዚያ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር አይሄድም። በመነቃቃቶች ላይ ጥርጣሬ ሲጥሉ የነበሩትን እነዚያን አብያተ ክርስቲያናት አሁን ተመልከቱ። በመነቃቃቶች ደስ ይሰኛሉን? እነርሱን ለማስፋትና ለማነጽ መንፈስ ቅዱስ በላያቸው ይወርዳልን? በዚህች ከተማ ከሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት በአንዲቱ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች ጉባኤ መነቃቃቶችን ለማስፋፋት በተሳካ ሁኔታ በሚደክሙ ብዙ አገልጋዮች ላይ ምክንያት የሌለውና መሠረተ ቢስ ጥርጣሬን ለማነሣሣት የታለመውን «ድንጋጌና ምስክርነት» ብለው የሚጠሩትን በጋዜጦች ሲያሳትሙ ቆይተዋል። ታዲያ የዚያች ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ምንድን ነው? መነቃቃት አግኝተዋልን? ለጠቅላላ ጉባኤው ከቀረበው ይፋዊ ዘገባ እንደሚታየው በአንድ ዓመት ውስጥ በሃያ ሰባት በመቶ አንሳለች። እንዲህ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ንስሐ ገብተው መነቃቃት ካላገኙ በቀር ሌላ ሊደረግ የሚችል ነገር ሁሉ ቢደረግም ማነሳቸውን ይቀጥላሉ። እጅግ መንፈሳውያንና ለእግዚአብሔር ክብር ቀናተኞች መስለው ሊታዩ ይችላሉ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ቅኖች እንደ ሆኑ አያምንም። መንፈሱንም ባለማፍሰስ ቁጣውን ይገልጣል። በቂ የሆነ ታላቅ ድምፅ ቢኖረኝ፣ መነቃቃቶችን ያሙትን እነዚህን አብያተ ክርስቲያናትና አገልጋዮች ሁሉ እያንዳንዳቸውን እንዲሰሙኝ ባደረግሁ ነበር፤ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሞትን መጋረጃ በማምጣት እንደ ረዱ፣ የእግዚአብሔርም እርግማን አሁንም በላያቸው እንዳለ፣ ንስሐ ካልገቡም እንደሚኖር እንደማምን እላቸው ነበር። እግዚአብሔር አሁንም በነፍሶቻቸው ላይ ክሳትን ልኳል፤ ብዙዎቹም ያውቁታል።
3. ሥራውን በማስፋፋት የተሳተፉትም ንስሐ መግባት አለባቸው። ያደረጉት ስሕተት ሁሉ ንስሐ ሊገባበት ይገባል፤ አለዚያ መነቃቃቶች እንደ ቀድሞው ዘመን አይመለሱም። የተሳሳተ መንፈስ በተገለጠበት ጊዜ ሁሉ፥ ወይም በተቃውሞው ተበሳጭተውና ተቆጥተው ትዕግሥታቸውን ባጡ ጊዜ፥ ወይም ክርስቲያናዊ ታማኝነትን ከክፉ ቃልና ከተሳሳተ መንፈስ ጋር ባምታቱ ጊዜ ንስሐ መግባት አለባቸው። ተቃዋሚዎች ብቻቸውን መነቃቃትን ፈጽሞ ሊያቆሙት አይችሉም፥ የሚያስፋፉት ራሳቸው ካልተሳሳቱ በቀር። ስለዚህ የፈራጅነት፥ የትዕቢት፥ የዕብሪት ወይም የጭካኔ ቃል ተናግረን ከሆነ ንስሐ መግባት አለብን። እንዲህ ያለው ጊዜ ራሳችንን እያጸደቅን የምንቆምበት ጊዜ አይደለም። የመጀመሪያው ጥሪያችን ንስሐ መግባት ነው። እያንዳንዱ ስለ ራሱ ኃጢአት ንስሐ ይግባ፤ ማን የበለጠ ጥፋተኛ እንደ ሆነም አይጣሉ፥ አይከራከሩም።
4. ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካ ረገድ ትክክለኛ አቋም መያዝ አለባት። አሁን የፖለቲካ ስብከት ልሰብክ ነው፥ ወይም ተባብራችሁ በፖለቲካ ውስጥ የክርስቲያን ፓርቲ እንድታቋቁሙ እፈልጋለሁ ብላችሁ አታስቡ። አይደለም፤ በዚያ አላምንም። ነገር ግን ክርስቲያኖች ለታማኝ ሰዎች የሚመርጡበትና በፖለቲካ ወጥ የሆነ አቋም የሚይዙበት ጊዜ ደርሷል፤ አለዚያ ጌታ ይረግማቸዋል። እነርሱ ራሳቸው ታማኝ ሰዎች መሆን አለባቸው፤ አንድን ሰው የፓርቲያቸው አባል ስለ ሆነ ብቻ፥ የባንኩ ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ፥ የጃክሰን ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ ስለ ሆነ ብቻ ከመምረጥ ይልቅ ታማኝና ቅን፥ ለመታመንም የሚገባ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው። ቤተ ክርስቲያን ወስላታ፥ ወይም አመንዝራ፥ ወይም ሰንበትን የሚሽር፥ ወይም ቁማርተኛ፥ ወይም ሰካራም መሆኑ የታወቀን ማንንም ሰው በሥልጣን ላይ እንደማትደግፍ ዓለም እንዲያይ ማድረግ አለባቸው። በአገራችን የዕውቀት መስፋፋትና የመገናኛ ቅለት እንዲህ ያለ በመሆኑ እያንዳንዱ ሰው ድምፁን ለማን እንደሚሰጥ ሊያውቅ ይችላል። ድምፁንም ለታማኝ ሰዎች ብቻ ቢሰጥ አገሪቱ ቅን ገዢዎች እንዲኖሩአት ትገደዳለች። ፓርቲዎች ሁሉ ታማኝ ሰዎችን ዕጩ አድርገው ለማቅረብ ይገደዳሉ። ክርስቲያኖች በዚህ ጉዳይ እጅግ በደለኞች ሆነዋል። ነገር ግን በተለየ መንገድ የሚሠሩበት ጊዜ ደርሷል፤ አለዚያ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይረግማል፥ መንፈሱንም ይመልሳል። በባርነትና በልከኝነት ጉዳይ እንደ ሆነው ሁሉ በዚህም ጉዳይ ቤተ ክርስቲያን በትክክል መሥራት አለባት፤ አለዚያ አገሪቱ ትጠፋለች። ቤተ ክርስቲያን ትክክለኛ አቋም ካልያዘች በቀር እግዚአብሔር የምንወዳትንና የምንጸልይላትን ይህችን ነፃና የተባረከች አገር ሊደግፋት አይችልም። እንደዚህች ባለ አገር ፖለቲካ የሃይማኖት አንድ ክፍል ነው፤ ክርስቲያኖችም ለአገሪቱ ያለባቸውን ግዴታ ለእግዚአብሔር ያለባቸው ግዴታ ክፍል አድርገው መፈጸም አለባቸው። አንዳንድ ጊዜ የሕዝቡ መሠረቶች እየበሰበሱ ያሉ ይመስላል፤ ክርስቲያኖችም በፖለቲካ የሚያደርጉትን እግዚአብሔር የማያይ መስሎ እንደ ታያቸው ሆነው ይሠራሉ። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ እርሱ ያያል፤ እንደሚይዙትም አካሄድ ይህን ሕዝብ ይባርካል ወይም ይረግማል።
5. አብያተ ክርስቲያናት በባርነት ጉዳይ ትክክለኛ አቋም መያዝ አለባቸው። እዚህም ትክክለኛው አቋም ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ይነሣል። በመጀመሪያም ሊወገዱ የሚገባቸውን አንዳንድ ነገሮች እገልጻለሁ።
(1.) ከሁሉ በፊት ክፉ መንፈስ ሊወገድ ይገባል። ክርስቲያኖች በዚህ ጉዳይ በቁጣ ክርክር ውስጥ ከመግባታቸው የበለጠ ሃይማኖትንም ባሪያዎቹንም ራሳቸውን የሚጎዳ ነገር የለም። ይህ በክርስቲያኖች መካከል የቁጣ ክርክር የማያስፈልግበት ጉዳይ ነው። ባሪያ ያላቸው ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ፥ አረቄ እንደሚሸጡ ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ሁሉ፥ ራሳቸውን ለማጽደቅ ይጥሩ ይሆናል፤ ሕሊናቸውን በሚወጉና ኃጢአታቸውን እንዲተዉ በሚጠሩአቸውም ላይ ይቆጡ ይሆናል። አንድን ሰው በጥቁር ቆዳው የሚወቅሱ ወይም ጥቁር ቆዳ መኖር ነውር ነው ብለው የሚያስቡ እነዚያ ትዕቢተኞች ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ጭፍን ጥላቻቸው ጆሮአቸውን እስኪደፍኑና ጉዳዩን በሚያቀርቡላቸው ላይ እስኪጣሉ ድረስ እንዲያይል ይፈቅዱለት ይሆናል። ነገር ግን እደግመዋለሁ፥ የባርነት ጉዳይ ክርስቲያኖች፥ የሚጸልዩ ሰዎች፥ ሊለያዩበት የማያስፈልጋቸው የማይገባቸውም ጉዳይ ነው።
(2.) ሊወገድ የሚገባው ሌላው ነገር በዚህ ጉዳይ ገለልተኛ አቋም ለመያዝ መሞከር ነው። ጉዳዩ ለውይይት ከቀረበ ወዲህ ክርስቲያኖች ሰንበትን ስለ መቀደስ ጉዳይ ገለልተኛ አቋም መያዝ እንደማይችሉ ሁሉ በዚህም ጉዳይ ገለልተኛ አቋም መያዝ አይችሉም። ይህ ታላቅ የሕዝብ ኃጢአት ነው። የቤተ ክርስቲያን ኃጢአት ነው። አብያተ ክርስቲያናት በዝምታቸውና ባሪያ ያላቸው ሰዎች የኅብረታቸው አባላት እንዲሆኑ በመፍቀዳቸው ተስማምተውበታል። ኩዌከሮች በቅርብ ዓመታት እጃቸውን ከእርሱ ቢታጠቡም ቤተ እምነቶች ሁሉ ከፍም ዝቅም ብለው በደለኞች ሆነዋል። አብያተ ክርስቲያናት ይህ የፖለቲካ ኃጢአት ብቻ ነው ብለው ማስመሰላቸው ከንቱ ነው። እደግመዋለሁ፥ ይህ ቤተ እምነቶች ሁሉ የተስማሙበት የቤተ ክርስቲያን ኃጢአት ነው። በተግባር ሕጋዊ ነው ብለው አውጀዋል። ባሪያ ያላቸው ሰዎች በአብያተ ክርስቲያናቶቻቸው ውስጥ በመልካም አቋም በጸጥታ እንዲኖሩ መፍቀዳቸው ራሱ ኃጢአት አይደለም የሚለውን አመለካከታቸውን የሚገልጽ እጅግ ጠንካራና ግልጽ መግለጫ ነው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጉዳይ ገለልተኛ አቋም እይዛለሁ ብላ ማስመሰሏ ፍጹም ሞኝነት ነው። እውነቱ ግን ፈጽሞ ገለልተኛ ስፍራ ላይ አለመሆኗ ነው። ባሪያ ያላቸውን ሰዎች በኅብረቷ ውስጥ እስከ ታገሠች ድረስ ልማዱን ራሷ ታጸድቃለች። ይህም የእግዚአብሔር ጠላት የሆነ ሰው የትኛው ወገን ይበልጥ ተወዳጅ እንደሚሆን ስላላወቀ ቅዱስም ኃጢአተኛም አይደለሁም፥ ገለልተኛ አቋም እይዛለሁ ብሎ በማስመሰል «መልካም ጌታ፥ መልካም ዲያብሎስም» ብሎ ቢጸልይ እንደሚሆነው ያለ ነው።
(3.) በሁለቱም ወገን ያለውን የፈራጅነት መንፈስ ለማስወገድ ታላቅ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። ይህ ጥያቄውን ለመፍታት የተሻለው መንገድ ምን እንደ ሆነ በክርስቲያኖች መካከል የሐሳብ ልዩነት የነበረበትና ምናልባትም ለተወሰነ ጊዜ የሚኖርበት ጉዳይ ነው። ስለዚህ በሁለቱም ወገን በታላቅ ትዕግሥት ሊያዝ ይገባዋል። እርስ በርስ ዓላማን የሚከስ የውግዘት መንፈስ ክርስቲያናዊ አይደለም፤ የእግዚአብሔርን መንፈስ ያሳዝናል፥ መነቃቃቶችንም ያጠፋል፤ ለቤተ ክርስቲያንም ለባሪያዎቹም ራሳቸው እኩል ጎጂ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ፥ በእኔ አስተያየት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጉዳይ እንድታደርጋቸው አጥብቃ የተጠራችባቸውን በርካታ ነገሮች እጠቅሳለሁ፦
(1.) የሁሉም ቤተ እምነት ክርስቲያኖች ጭፍን ጥላቻን ትተው ያለ አንዳች መዘግየት በዚህ ጉዳይ ራሳቸውን ማሳወቅ አለባቸው። እጅግ ብዙ ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ሰዎች ጭፍን ጥላቻን እስከዚህ ድረስ ስላስተናገዱ ለማንበብና ለመስማት፥ ጉዳዩንም በትክክል ለመረዳት ፈቃደኞች አይደሉም። ነገር ግን ክርስቲያኖች በዚህ የአእምሮ ሁኔታ ሊጸልዩ አይችሉም። ይህን ወይም ሌላ ማንኛውንም የግዴታ ጥያቄ ለመመርመር እጅግ በጭፍን ጥላቻ ተይዞ ሳለ የጸሎት መንፈስ ያለው ማንም ቢኖር እንዲያሳየኝ እሞግታለሁ። ብርሃኑ ባያበራ ኖሮ ክርስቲያኖች በዚህ ነጥብ በጨለማ ውስጥ ሆነው የጸሎት መንፈስ ሊኖራቸው ይችል ነበር። ነገር ግን ወደ ብርሃን ለመምጣት እምቢ ካሉ ሊጸልዩ አይችሉም። እንግዲህ በዚህ የተገኛችሁትን፥ ለመመርመር ፈቃደኞች ስላልነበራችሁ ይህን ጉዳይ ያልመረመራችሁትን ሁሉ የጸሎት መንፈስ እንዳላችሁ ወይም እንደሌላችሁ እንድትናገሩ እጠራችኋለሁ። እውነቱ እጅግ በሰፊው ተሰራጭቶ በሕዝብ ፊት ባለበት በአሁኑ ጊዜ አገልጋዮች፥ ግለሰብ ክርስቲያኖች ወይም ሙሉ አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ነጥብ እውነትን የሚቃወሙ ከሆነ ሃይማኖታዊ መነቃቃትን ያገኛሉ ወይም ሊያገኙ ይችላሉ ብዬ አላምንም።
(2.) በዚህ ጉዳይ ላይ ሚዛናዊና አስተዋይ ውይይቶችን የያዙ ጽሑፎች፥ በሕዝብ ፊት ያሉትም የእውነታዎች መግለጫዎች በጸጥታና በሰፊው ሊሰራጩ፥ በመላዋ ቤተ ክርስቲያንም በጥንቃቄና በጸሎት ሊመረመሩ ይገባል። በዚህ የቤተ ክርስቲያን ትኩረት በመካከሏ ያሉትን ነፍሳት የማዳንን ዋና ጥያቄ እስክትዘነጋ ድረስ በዚህ ይዋጥ ማለቴ አይደለም። የክርስቲያኑን ማኅበረሰብ የሚያስደነግጡና በሁከት ውስጥ የሚጥሉ ያለጊዜያቸው የሆኑ እንቅስቃሴዎች በዚህ ጉዳይ ይደረጉ ማለቴም አይደለም፤ ነገር ግን የሚጸልዩ ሰዎች በማስተዋል እንዲሠሩ፥ በቂ መረጃም በማኅበረሰቡ ውስጥ እንደ ተሰራጨ አብያተ ክርስቲያናት በየዋህነት ነገር ግን በጽናት በዚህ ጉዳይ ቁርጥ ያለ አቋም እንዲይዙ፥ በመላው ሕዝብና በዓለም ፊትም ለዚህ ኃጢአት ያላቸውን ጥላቻ እንዲገልጹ ማለቴ ነው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበረው የፀረ ፍሪሜሰን መነሣሣት በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እጅግ ጥፋት አድርሶ፥ በአገልጋዮችና በሕዝቡ መካከል ለጊዜው ብዙ የስሜት መራራቅንና ክፉ ፈቃድን አስከትሎ ስለ ነበር፥ የዚህም ጉዳይ የመጀመሪያ መነሣት እንዲህ ያለ ሁከት ስላስከተለ፥ ራሳቸው ባርነትን ፈጽመው የሚቃወሙ ብዙ መልካም አገልጋዮች አብያተ ክርስቲያናቶቻቸው ጉዳዩን ተቀብለው በእርጋታ ለማጤንና በወንጌል መንፈስ ለመወሰን የሚበቃ ሃይማኖት የላቸውም ብለው በመፍራት ጉዳዩን በሕዝባቸው መካከል ማንሣትን ይፈራሉ። የዚህ አደጋ እንዳለ አውቃለሁ። ቢሆንም ጉዳዩ ለአብያተ ክርስቲያናት መቅረብ አለበት። በጥንቃቄና በብዙ ጸሎትም ቢቀርብ፥ መነቃቃቶችን ካገኙና በአሁኑ ጊዜ ለመነቃቃት መንፈስ ቅርብ ከሆኑ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በዚህ ጉዳይ እውነትን እንዲቀበሉ ሊደረጉ የማይችሉት እጅግ ጥቂቶች ናቸው። በዚህ ስሕተት አይኑር። ዊልያም ሞርጋን ስለ ፍሪሜሰንነት ያወጣው ማጋለጫ በ1826 ታተመ። ተከትሎ የመጣው መነሣሣትና ክርክር እስከ 1830 ቀጠለ። በዚህ መካከል አብያተ ክርስቲያናት በአጠቃላይ በፍሪሜሰንነት ላይ ምስክርነታቸውን ሰጥተው፥ በፍሪሜሰንነት ከጸኑ ሰዎች ጋር ኅብረት ማድረግ እንደማይችሉ ወሰኑ። በዚህም ምክንያት የፍሪሜሰን ማኅበራት በአብዛኛው ተበተኑ፥ የምሥረታ ፈቃዶቻቸውንም መለሱ። ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በብዛት ከማኅበራቱ ሸሹ። ይህ መንገዱን አዘጋጀ፤ በ1830ም ዓለም እስከዚያ ጊዜ አይቶት የማያውቀው ታላቁ መነቃቃት በፀረ ፍሪሜሰን አካባቢው ማእከል ተጀመረ፥ ቤተ ክርስቲያን እርምጃ በወሰደችበት አካባቢ ሁሉ ተስፋፋ፥ አዳዲስ አማኞቹም 100,000 ነፍሳት እስኪደርሱ ድረስ ቀጠለ።
በዚህች አገር ከዚህች ቤተ ክርስቲያን የበለጠ በዚህ ጉዳይ ከባድ ፈተና የደረሰባት ቤተ ክርስቲያን ምናልባት የለችም። ወጣቶችና በአብዛኛው ልምድ የሌላቸው ክርስቲያኖች ያሉባት ቤተ ክርስቲያን ነበረች። እኔ በሌለሁበትም ጊዜ በመካከላቸው ግራ መጋባትንና የተሳሳተ ስሜትን ለማምጣት ብዙ ሁኔታዎች ተባበሩ። ነገር ግን በዚህች ቤተ ክርስቲያን ስላለው ስሜት አሁን እስከማውቀው ድረስ በዚህ ጉዳይ በመካከላቸው ምንም ክፉ ፈቃድ አላውቅም። ጌታ ባርኮናል፥ መንፈስም በላያችን ተንጠባጥቧል፤ ከተመለስሁም ወዲህ በየወሩ በቁጥር ብዙ ሰዎች ወደ ኅብረታችን ተጨምረዋል። በዚህች ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጉዳይ በእጅግ የተለያየ መጠን የሚሰማቸው ሰዎች መኖራቸው አያጠራጥርም። ሆኖም በመካከላቸው በአመለካከት ትንሽ እንኳ ልዩነት እንዳለ እንደማላውቅ በቅንነት መናገር እችላለሁ። ወደ ውጭ አገር ጉዞዬ ከመሄዴ በፊት ጀምሮ፥ ከመጀመሪያው በልከኝነት ጉዳይ የያዝነውን ያንኑ አቋም በባርነት ጉዳይም ይዘናል። ባሪያ ያላቸውንና በዚህ ንግድ የተሳተፉትን ሁሉ ከኅብረታችን አግልለናል። ከዚህች ቤተ ክርስቲያን ውጭ ያሉ አንዳንዶች ይህን አካሄድ ተገቢ ያልሆነና ፍቅር የጎደለው ብለው ነቅፈውታል፤ እኔም የራሴን ፍርድ ወይም የዚህችን ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ለሌሎች አገልጋዮችና አብያተ ክርስቲያናት መተዳደሪያ ደንብ በምንም ዓይነት አላደርገውም። ቢሆንም አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ኃጢአት ላይ ያላቸውን ጥላቻ በመግለጽ የሚተባበሩበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ በሕሊናዬ አምናለሁ። ባርነትን በለስላሳና በክርስቲያናዊ ስም ካላጠመቅሁት፥ ኃጢአት ብዬ ከጠራሁት፥ ኃጢአቱ እስከ ቀጠለ ድረስ ፈጻሚዎቹ ለክርስቲያናዊ ኅብረትና አንድነት የሚገቡ ሊሆኑ አይችሉም ወደሚለው የማይቀር መደምደሚያ ወጥነትም ሕሊናም ይመሩኛል።
በዚህ ላይ በፕሬስቢቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሪያ ያላቸው ብዙ አገልጋዮች አሉ የሚል ተቃውሞ ይቀርባል። ባሪያ ያለውን ሰው ወደ ኅብረታችን እንዲመጣ ለመፍቀድ እምቢ እያልን ከእነርሱ ጋር ግን በአንድ ቤተ ክርስቲያን መሆናችን፥ በቤተ ክህነት ጉባኤዎች ከእነርሱ ጋር መቀመጣችን፥ እንደ አገልጋዮችም መቀበላችን እጅግ የማይጣጣም ነው ይባላል። ለዚህም፥ እነዚያን አገልጋዮች የምዳኝበት ሥልጣን እንደሌለኝ፥ አንዳንድ አገልጋዮቿ ወይም አባሎቿ ባሪያ ያላቸው ስለ ሆኑም ከቤተ ክርስቲያን መለየት እንደማይገባኝ እመልሳለሁ። ዲያብሎስ እንኳ አባል ቢሆንባት የእኔ ግዴታ የቤተ ክርስቲያን አባል መሆን ነው። ሥልጣን ባለኝ ስፍራ ባሪያ ያላቸውን ከኅብረቱ አገልላለሁ፤ በሕይወት እስካለሁም ድረስ ሁልጊዜ እንዲሁ አደርጋለሁ። ሥልጣን በሌለኝ ስፍራ ግን የክርስቶስ ማዕድ ከተዘረጋ፥ ሌላ ማንም ቢቀመጥ ወይም ቢቀር፥ ለትእዛዙ በመታዘዝ በእርሱ ላይ እቀመጣለሁ።
እነዚያን ባሪያ ያላቸውን አገልጋዮችና ሃይማኖተኛ ነን የሚሉትን ሁሉ ግብዞች ብዬ ለማውገዝና ክርስቲያኖች አይደሉም ለማለት በምንም ዓይነት አልፈልግም። ነገር ግን ይህን እላለሁ፤ በዚያ አቋም እስከ ቀጠሉ ድረስ፥ በሌሎች ሰዎች ኃጢአት ተካፋዮች ለመሆን ካላሰብን በቀር፥ የክርስቶስና የሰው ልጅ ጉዳይ እንደ ክርስቲያኖች እንዳይቈጠሩ ይጠይቃል። ባሪያ ያላቸውን ሰዎች የፕሬስቢቴሪያን ቤተ ክርስቲያን አባላት ቢሆኑም ማግለል አስካሪ መጠጥ የሚጠጡትን ወይም የሚሸጡትን ሰዎች ከማግለል የበለጠ የማይጣጣም አይደለም። በፕሬስቢቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አባላት የሆኑ እጅግ ብዙ አረቄ ሻጮች አሉና።
ጊዜው ደርሷል ብዬ አምናለሁ፤ ነቢይ ባልሆንም እንደ ደረሰ እንደሚገኝ አምናለሁ፤ ይኸውም በዩናይትድ ስቴትስ ያለው መነቃቃት የሚቀጥለውና የሚያሸንፈው ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጉዳይ ትክክለኛ አቋም በምትይዝበት መጠንና ፍጥነት ብቻ ነው። ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ምስክሮች ናት። እውነቱ ባርነት ከሁሉ በላይ የቤተ ክርስቲያን ኃጢአት መሆኑ ነው። በኃጢአተኞች ዓይን ይህን ርኩሰት ሁሉ የሚቀድሰው የተለያዩ ቤተ እምነቶች አገልጋዮችና ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ሰዎች ባሪያዎች መያዛቸው ራሱ ነው። በልከኝነት ጉዳይ በአገሩ ያለ ሰካራም ሁሉ አረቄ ከሚሸጥ ዲያቆን ወይም የወይን ጠጅ ከሚጠጣ አገልጋይ ጀርባ እንደሚደበቅ የማያውቅ ማን ነው? ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ሰዎች ያደርጉታል የሚለው ከመጠን በላይ ለሚጠጡና በልክ ለሚጠጡ ሰዎች እጅግ የተለመደ ተቃውሞና መሸሸጊያ ነው። አስካሪ መጠጥ የሚነግዱትንና አረቄ የሚጠጡትን ከኅብረቱ የማግለልን አስገዳጅ አስፈላጊነት የሚፈጥረው ይህ ነው። የሁሉም ቤተ እምነት አብያተ ክርስቲያናት በልከኝነት ጉዳይ ገልጠው ይናገሩ፤ ከዚህ ሞት ከሚያመጣ ርኩሰት ጋር ምንም ግንኙነት ባላቸው ሁሉ ላይ በሮቻቸውን ይዝጉ፤ የልከኝነትም ዓላማ ድል ይነሣል። ጥቂት ዓመታት ንግዱን ያጠፉታል። በባርነትም እንዲሁ ነው።
ይህን ኃጢአት በዋናነት የምትደግፈው ቤተ ክርስቲያን ናት። በዚህ ጉዳይ የምትሰጠው የተባበረ ምስክርነት ጥያቄውን ይፈታዋል። የሁሉም ቤተ እምነት ክርስቲያኖች በየዋህነት ነገር ግን በጽናት ወጥተው ፍርዳቸውን ያውጁ፤ ኅብረቶቻቸውን ያጥሩ፥ ከዚህም ነገር እጃቸውን ይታጠቡ፤ በዚህ ታላቅ ርኩሰት ራስና ፊት ላይ ኃጢአት! ብለው ያውጁ፥ ይጻፉም፤ በሦስት ዓመትም ሁሉን ጠራርጎ የሚወስድ የሕዝብ አስተያየት ይፈጠራል፤ በዚህችም አገር በሰንሰለት የታሰረ አንድ ባሪያ ወይም የተቈጣና ጨካኝ ባሪያ ነጂ አይገኝም።
ቢሆንም በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ይህ ጉዳይ ግራ መጋባትንና ክፉ ፈቃድን ሳይፈጥር ሊቀርብ አይችልም ሊባል ይችላል። ይህ ሊሆን ይችላል። በልከኝነት ጉዳይም እንዲሁ ነበር፤ በመነቃቃቶች ጉዳይም እንዲሁ። በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ልከኝነትም ሆነ መነቃቃቶች መከፋፈልን ሳያስከትሉ ሊቀርቡ አይችሉም። የሰንበት ትምህርት ቤቶች፥ የሚስዮን ሥራዎች፥ እንዲህ ያለውም ነገር ሁሉ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል፤ በብዙ አብያተ ክርስቲያናትም መከፋፈልን አስከትለዋል። ነገር ግን ይህ እነዚህን ጉዳዮች ለማግለል በቂ ምክንያት ነውን? ክርክርን በመፍራት እነዚህን ጉዳዮች ያገለሉ አብያተ ክርስቲያናትስ በመነቃቃቶች ተባርከዋልን? እንዳልተባረኩ ሁሉም ያውቃል። ነገር ግን አብያተ ክርስቲያናት በእነዚህ ጉዳዮች ጽኑ አቋም በያዙበት ስፍራ፥ ግለሰቦችና አንዳንድ ጊዜም ብዙዎች ቢቃወሙም፥ በመነቃቃቶች ተባርከዋል። ከእነዚህ ጉዳዮች ማናቸውም በጥንቃቄና በጸሎት በሚቀርቡበት፥ በትክክለኛ መንፈስ በሚቀርቡበትና ለእያንዳንዳቸው እውነተኛው አንጻራዊ ክብደት በሚሰጥበት ስፍራ፥ በእንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሁከት የሚፈጥሩና የሚቃወሙ ቢኖሩ ወቀሳው በሚገባው ላይ ይውደቅ። ይህን ጉዳይ ለመጣላት ራሳቸው የተዘጋጁ፥ «እነዚህን ነገሮች ወደ ቤተ ክርስቲያን አታግቡ፤ ተቃውሞ ይፈጥራሉ» ብለው ለመጮኽ ሁልጊዜ ዝግጁ የሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች አሉ። አገልጋዩና የሚጸልዩ ሰዎችም ጉዳዩን ማቅረብ ግዴታቸው እንደ ሆነ ቢሰማቸው፥ እነርሱ ራሳቸው ሁከት ይፈጥሩና ከዚያም «አያችሁ፥ ነግሬአችሁ ነበር፤ ይህን ጉዳይ ማቅረባችሁ ያደረገውን አሁን እዩ፤ ቤተ ክርስቲያንን ቁርጥራጭ አድርጎ ይበጣጥሳታል» ይላሉ። እነርሱ ራሳቸው መከፋፈልን ለመፍጠር የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ሳሉ መከፋፈሉን በራሳቸው ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ያላክካሉ። በብዙ አብያተ ክርስቲያናቶቻችን እንዲህ ያሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ። የሰንበት ትምህርት ቤቶችም፥ ሚስዮኖችም፥ መነቃቃቶችም፥ ፀረ ባርነትም፥ ወይም እግዚአብሔርን የሚያከብርና የሰዎችን ነፍሳት የሚጠቅም ሌላ ማንኛውም ነገር፥ እነዚህ ጠንቃቃ ነፍሳት ሳይሰናከሉበት በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አይፈጸምም።
ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በብዙ፥ በሌሎቹም በጥቂት ተቃውሞ፥ በአንዳንዶቹም ምናልባት ምንም ተቃውሞ ሳይኖር አንድ በአንድ ቀርበው ተቀባይነት አግኝተዋል። እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን አምላክ መሆኑ እውነት እንደ ሆነ፥ ዓለምም መለወጥ እንዳለበት እርግጥ እንደ ሆነ፥ ይህ ጉዳይ በቤተ ክርስቲያን መታየትና ኃጢአት ተብሎ መታወጅ አለበት። ቤተ ክርስቲያን እንደ ባርነት ባለ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ገለልተኛ ሆና ለመቆየት ከምትሞክር ወይም የሐሰት ምስክርነት ከምትሰጥ ይልቅ በዓለም ላይ ምንም ቤተ ክርስቲያን ባይኖር እጅግ እጅግ በተሻለ ነበር፤ በተለይም ጉዳዩ ከተነሣ ወዲህ፥ ከነገሩም ባሕርይ የተነሣ ምስክርነቷ በአንዱ ወይም በሌላው ወገን ሚዛን ላይ አለመውደቁ የማይቻል ስለ ሆነ።
«ምን ይደረግ? በመካከላችን ካሉት ነፍሳት መዳን ከሚለው እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ትኩረትን እያዞርን ሁሉን የሚውጥ የንግግር ርዕስ እናድርገውን?» ብላችሁ ትጠይቃላችሁን? እኔም አይደለም ብዬ እመልሳለሁ። ቤተ ክርስቲያን በጉዳዩ ላይ አስተያየቷን ትግለጽ፥ በሰላምም ትኑር። እኔ እስከማውቀው ድረስ እኛ በዚህ ጉዳይ ፍጹም ሰላም አለን። አስተያየታችንን ገልጸናል፤ ኅብረታችንን ባሪያ ባላቸው ሰዎች ላይ ዘግተናል፤ ሌሎች ነገሮችንም እየተከታተልን ነው። በዚህ ጉዳይ በመካከላችን ጤናማ ያልሆነ ትንሽ መነሣሣት እንኳ እንዳለ አላውቅም። በአንድ ስፍራ ሁሉን የሚውጥ የንግግር ርዕስ በሆነበትም ቦታ፥ በአብዛኛው ጉዳዩ እንዲሰማ እንኳ እንዳይፈቀድ የተቃወሙ ጥቂት ግለሰቦች ባሳዩት ግትርና ምክንያት የለሽ ተቃውሞ የተነሣ እንደ ሆነ አምናለሁ።
6. ቤተ ክርስቲያን መነቃቃቶችን ማስፋፋት ከፈለገች ሰንበትን መቀደስ አለባት። በአገሩ ውስጥ እጅግ ብዙ ሰንበትን መሻር አለ። ነጋዴዎች ይሽሩታል፥ መንገደኞች ይሽሩታል፥ መንግሥትም ይሽረዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት በዚህ ክፍለ ግዛት ምዕራባዊ ክፍል ሰንበትን የሚያከብሩ የጀልባዎችና የመጓጓዣ ሠረገሎች መሥመር ለማቋቋምና ለማስቀጠል ሙከራ ተደርጎ ነበር። ነገር ግን ይህን ሥራ ቤተ ክርስቲያን እንደማትደግፈው ታወቀ። ብዙ ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ሰዎች በእነዚህ ሠረገሎች አይጓዙም፥ በሰንበትም ከመጓዝ በሚቆሙ የቦይ ጀልባዎች ዕቃቸው እንዲላክ አይፈልጉም ነበር። በአንድ ወቅት ክርስቲያኖች የሰንበትን የደብዳቤ መላክ እንዲያቆም ለኮንግረስ አቤቱታ በማቅረብ እጅግ ተጠምደው ነበር፤ አሁን ግን በዚህ የሚያፍሩ ይመስላሉ። ነገር ግን አንድ ነገር እጅግ እርግጥ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ሰንበትን መቀደስን እንድታስፋፋ አንድ ነገር ካልተደረገ፥ በፍጥነትና በውጤታማነትም ካልተደረገ፥ ሰንበት ይጠፋል፤ በሰንበትም ደብዳቤዎቻችን ሲጓዙና ፖስታ ቤቶች ክፍት ሲሆኑ ብቻ ሳይሆን፥ ከጊዜ በኋላ ፍርድ ቤቶቻችንና የሕግ አውጪ አዳራሾቻችንም በሰንበት ክፍት ይሆናሉ። ታዲያ ቤተ ክርስቲያን ምን ማድረግ ትችላለች? ይህስ ሕዝብ ያለ አንዳች ሰንበት ምን ያደርጋል?
7. ቤተ ክርስቲያን በልከኝነትና በግብረ ገብ ተሐድሶ ጉዳይ፥ ከጊዜ ወደ ጊዜም ውሳኔ ለማግኘት በሚቀርቡ የተግባራዊ ሥነ ምግባር ጉዳዮች ሁሉ ትክክለኛ አቋም መያዝ አለባት።
በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከግብረ ገብ ተሐድሶ ጉዳይ ራቅ ብለው የቆሙ፥ በመድረክ ላይም ዝሙትን የሚቃወም ማንኛውም ነገር እንዲነገር የሚፈሩ አሉ። ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጉዳይ ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ ይፈቀድላታል ብላ መጠበቅ የለባትም። በእግዚአብሔር መግቦት ጉዳዩ ለውይይት ቀርቧል። ክፋቶቹ ተገልጠዋል፥ የተሐድሶም ጥሪ ቀርቧል። የሰውን ልጅ የሚያድሰው ከእውነት በቀር ምንድን ነው? እውነትንስ ቤተ ክርስቲያንና አገልግሎት ካልሆኑ ማን ያቀርበዋል? ክርስቲያኖች ገለልተኛ ሆነው ዝም ብለው ሳሉ የእግዚአብሔርን ሞገስና በረከት ሊያገኙ ይችላሉ የሚለው ሐሳብ ይወገድ።
በእንዲህ ያሉ ጉዳዮች ሁሉ ዝም የሚል አገልጋይ ከተቃራኒው ወገን ጋር ይቈጠራል። በመነቃቃት ጊዜ እንዲህ እንደ ሆነ ሁሉም ያውቃል። አንድ ሰው በሥራው ላይ መሳደብ አያስፈልገውም። ዝም ቢልና ገለልተኛ አቋም ቢይዝ ብቻ የመነቃቃቱ ጠላቶች ሁሉ ከእነርሱ ወገን እንደ ሆነ ይቈጥሩታል። በልከኝነት ጉዳይም እንዲሁ ነው። አንድ ሰው ከሰካራሞችና በልክ ከሚጠጡ ሰዎች ጋር በጣም መልካም ግንኙነት እንዲኖረው በቀዝቃዛ ውኃ ማኅበር ላይ መሳደብ አያስፈልገውም። የወይን ጠጅን በልክ መጠጣት እንዲደረግ ብቻ ይሟገት፥ እንደ ምቾት ነገርም መጠጣቱን ብቻ ይቀጥል፤ ሰካራሞች ሁሉ ከእነርሱ ወገን እንደ ሆነ ይቈጥሩታል። ተጽእኖውን ለልከኝነት ዓላማ ለመስጠት እምቢ ቢል በእርግጥ ሌላው ወገን ወዳጁ አድርጎ ይወስደዋል። በእነዚህ ጉዳዮች ሁሉ፥ በሚነሡበት ጊዜ፥ አብያተ ክርስቲያናትና አገልጋዮች በመነቃቃቶች የእግዚአብሔርን በረከት ለማግኘት የሚጠብቁ ከሆነ ትክክለኛውን አቋም መያዝ፥ በግልጽም መያዝ፥ በእርሱም መጽናትና እስከ መጨረሻ ማድረስ አለባቸው። በላያቸው የበራውን ብርሃን ንቀው አስካሪ መጠጥ መጠጣትን ወይም መነገድን የሚቀጥሉትን አባላት ከኅብረታቸው ማውጣት አለባቸው።
8. ለክርስቲያናዊ በጎ አድራጎት ታላላቅ ዓላማዎች ሁሉ የበለጠ መደረግ አለበት። ለሚስዮን ሥራ፥ ለትምህርት፥ ለመጽሐፍ ቅዱስ፥ ለሌሎችም የሃይማኖት ሥራ ቅርንጫፎች ሁሉ እጅግ የበለጠ ጥረት መደረግ አለበት፤ አለዚያ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን ታስከፋለች። ተመልከቱት። የተቀበልነውን ምሕረት፥ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት፥ ቁጥርና ብልጽግና አስቡ። ቤተ ክርስቲያን ለጋስ እንደ ሆነች፥ ገንዘቧንም ለመስጠትና ለእግዚአብሔር ለመሥራት ፈቃደኛ እንደ ሆነች ለማሳየት እንደ ተቀበልነው ጥቅም መጠን ለእግዚአብሔር መልሰናልን? አይደለም። ከዚያ እጅግ የራቀ ነው። ቤተ ክርስቲያን በጨመረችበት መጠን መንገዶቻችንን አብዝተናል፥ ዕቅዶቻችንንም አስፋፍተናልን? እግዚአብሔር በተደረገው ረክቷልን? ወይስ ሊረካበት ምክንያት አለውን? ባለፉት አሥር ዓመታት የአሜሪካ አብያተ ክርስቲያናት ያገኙት እንዲህ ያለ መነቃቃት! ለሚስዮኖች፥ ለመጽሐፍ ቅዱሶች፥ ለትምህርት፥ ለትራክቶች፥ ለነፃ አብያተ ክርስቲያናት፥ ሃይማኖትን ለማስፋፋትና ነፍሳትን ለማዳን በተዘጋጁ መንገዶች ሁሉ ካደረግነው አሥር እጥፍ ማድረግ በተገባን ነበር። አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ጉዳይ ካልነቁና ራሳቸውን በሰፊ መጠን ካልሰጡ በዩናይትድ ስቴትስ ያለው መነቃቃት እንደሚቆም ሊጠብቁ ይችላሉ።
9. በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ክርስቲያኖች ዓለም እስኪለወጥ ድረስ መነቃቃቶች እንዲስፋፉና እንዲያሸንፉ የሚጠብቁ ከሆነ በመነቃቃቶች ረገድ ጥርጣሬንና ቅናትን የሚያነሣሡ ደብዳቤዎችን መጻፍንና ጽሑፎችን ማሳተምን መተው፥ ራሳቸውም ሥራውን መያዝ አለባቸው። መላዋ ቤተ ክርስቲያን በአንድነት ከአሥር ዓመት በፊት ወደ ሥራ ገብታ ስማቸውን ልጠራ የምችላቸው ጥቂት ግለሰቦች እንዳደረጉት ብትቀጥልበት ኖሮ አሁን በአገሩ ውስጥ ንስሐ ያልገባ አንድ ኃጢአተኛ እንኳ ባልተገኘ ነበር። የሺው ዓመት መንግሥት ከዛሬ በፊት በዩናይትድ ስቴትስ ሙሉ በሙሉ በመጣ ነበር። እየተሳሳትን ነው ብለው የሚያስቡ አገልጋዮች ዝም ብለው ቆመው ከበርክሻየር ደብዳቤ ከመጻፍ ይልቅ ትጥቃቸውን ታጥቀው ወደ ፊት ይገስግሱ፥ ከሁሉ የሚበልጠውንም መንገድ ያሳዩን። በምሳሌያቸው እንዴት የተሻለ ማድረግ እንደምንችል ያስተምሩን። ስሕተቶችን እንደ ሠራን፥ ጥፋቶችንም እንደ ፈጸምን አልክድም። በመነቃቃቶች ውስጥ በአንዳንድ ሰዎች የሚደረጉ ብዙ የተሳሳቱ ነገሮች እንዳሉ አልክድም። ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፥ እነርሱን የምናርምበት መንገድ ይህ ነውን? ጳውሎስ እንዲህ አላደረገም። ወንድሞቹን ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ እንደሚያሳያቸው በደግነት በመንገር አረማቸው። ወንድሞቻችን ሥራውን ይያዙ፥ ወደ ፊትም ይገስግሱ። ከመድረኮቻቸው ሁሉ ጩኸቱን እንስማ። ወደ ሥራ! ጌታ ከእነርሱ ጋር በሚሄድበትና ክንዱን በሚገልጥበት ስፍራ ይምሩ፤ እኔም በበኩሌ እከተላለሁ። ብቻ ወደ ፊት ይሂዱ፤ ዩናይትድ ስቴትስም ወደ እግዚአብሔር ስትመለስ እንይ፤ ጥቃቅን ጥያቄዎችም ሁሉ ይቁሙ።
ይህ ካልሆነና በዚህች አገር መነቃቃቶች ቢቆሙ፥ አገልጋዮችና አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ምክንያት ወደ ሲኦል በሚሄዱት ነፍሳት ሁሉ ደም በደለኞች ይሆናሉ። ሥራው የሚቆምበት ምንም ምክንያት የለም። ቤተ ክርስቲያን ግዴታዋን ሁሉ ብትፈጽም የሺው ዓመት መንግሥት በሦስት ዓመት ውስጥ በዚህች አገር ሊመጣ ይችላል። ነገር ግን ይህ ደብዳቤ መጻፍ አገሩን በጥርጣሬና በቅናት እየሞላ የሚቀጥል ከሆነ፥ በመነቃቃት ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ሁለት ሦስተኛው ወደ ኋላ እያፈገፈገ ከመንቀፍ በቀር ምንም ሳያደርግ ሁልጊዜ እንዲሁ የሚኖር ከሆነ፥ የእግዚአብሔር እርግማን በዚህ ሕዝብ ላይ ይሆናል፤ ይህም ብዙ ሳይቆይ ነው።
ማሳሰቢያዎች።
1. በክርስቲያኖችና በአገልጋዮች መካከል ታላቅ የልብ ምርመራ የሚደረግበት ጊዜ እጅግ ደርሷል። ወንድሞች ሆይ፥ ይህ እውነትን የምንቃወምበት፥ ወይም እውነት በግልጽ ስለ ተነገረ የምንከራከርበትና የምንነቅፍበት ጊዜ አይደለም። እርስ በርስ የምንካሰስበት ወይም የምንጣላበት ጊዜ አይደለም፤ ነገር ግን የራሳችንን ልብ መመርመርና በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን ማዋረድ አለብን።
2. ንስሐ ገብተን ኃጢአታችንን መተው፥ መንገዳችንንና ሥራችንንም ማቅናት አለብን፤ አለዚያ መነቃቃቱ ይቆማል። የቤተ ክህነት ውዝግቦቻችን መቆም አለባቸው፤ የሃይማኖትን ታላላቅ ጉዳዮች ለማስፋፋት እንድንተባበርም ጥቃቅን ልዩነቶች ሁሉ ወደ ጎን ተደርገው መተው አለባቸው። ይህ ካልሆነ መነቃቃቶች ከመካከላችን ይቋረጣሉ፤ የጠፉት የሚሊዮኖች ደምም በልብሳችን ዘርፍ ላይ ይገኛል።
ቤተ ክርስቲያን ግዴታዋን ሁሉ ብትፈጽም የሃይማኖትን ድል በዓለም ላይ በቅርቡ ታጠናቅቃለች። ነገር ግን ይህ የአዋጅና የምስክርነት ሰነድ ጦርነት፥ ይህም የስለላ፥ የአሽሙርና የውግዘት ሥርዓት የሚቀጥል ከሆነ፥ መነቃቃቶች የሚቆሙ ብቻ አይደሉም፤ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ድንጋጤ ከማገገሟ በፊት ወደ ሲኦል የሚሄዱት የሚሊዮኖች ደም ይህን አስከፊ ክርክር ባስነሡትና ባስቀጠሉት ሰዎች ልብስ ዘርፍ ላይ ይገኛል።
4. በመነቃቃቶች ላይ የሐሜት ወሬ ያሰራጩ ንስሐ መግባት አለባቸው። ስለ ኑፋቄ፥ አንዳንድ ሰዎችም የመንፈስን ሥራ ይክዳሉ ስለ መባሉ ብዙ ተብሏል፤ ይህ ግን ፈጽሞ መሠረት የሌለውና ከምንም የተፈጠረ ነው። ወሬዎቹን የፈጠሩትም፥ በወንድሞቻቸውም ላይ ያሰራጩአቸው ንስሐ ገብተው ይቅርታውን እንዲያገኙ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ አለባቸው።
5. በክርስቲያኖች ዘንድ ወደ መድከምና ወደ ኋላ ወደ መመለስ ያለውን የማያቋርጥ ዝንባሌ እናያለን። ይህ በመነቃቃቶች ሁሉ በተለወጡ አዲስ አማኞች ሁሉ ዘንድ እውነት ነው። በፕሬዚዳንት ኤድዋርድስ ዘመን የነበረውን መነቃቃት ተመልከቱ። ሥራው 30,000 ነፍሳት እስኪለወጡ ድረስ ቀጠለ፤ በዚህ ጊዜም ብዙ አገልጋዮችና ክርስቲያኖች በአንዱም በሌላውም ወገን መጻሕፍትንና በራሪ ጽሑፎችን በመጻፍ እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ገቡ፤ ሁሉንም አጠፉ፥ መነቃቃቱም ቆመ። ሥራውን የተቃወሙት እልከኞችና ኃይለኞች ሆኑ፤ ያስፋፉትም የዋህነታቸውን አጥተው ቁጡዎች ሆኑ፤ ከዚያም በሐሰት በተከሰሱባቸው በእነዚያው ክፋቶች ውስጥ ተገፍተው ገቡ።
እንግዲህ አሁን ምን እናድርግ? ይህ ታላቅና ክቡር የእግዚአብሔር ሥራ የማሽቆልቆል ምልክት የሚያሳይ ይመስላል። መነቃቃቱ አልሞተም፤ ለዚህም እግዚአብሔር ይመስገን፤ አልሞተም! አይደለም፤ ክርስቲያኖች በዚህ ጉዳይ እያነበቡና ስለ መነቃቃቱ እየጠየቁ እንደ ሆኑ ከአገሩ ክፍሎች ሁሉ እንሰማለን። በአንዳንድ ስፍራዎች አሁን ብርቱ መነቃቃቶች አሉ። ታዲያ ዓርማውን ከፍ ለማድረግ፥ ይህን መላውን ሕዝብ ለማንቀሳቀስና ይህን ሁሉ ታላቅ ሕዝብ ወደ ጌታ ለመመለስ ምን እናድርግ? ትክክል ማድረግ አለብን። ሁላችንም የተሻለ መንፈስ ሊኖረን፥ በትቢያ ውስጥ ዝቅ ልንል፥ በአንድነት ልንሠራ፥ ይህንም ታላቅ ሥራ በሙሉ ልባችን ልንይዝ ይገባናል፤ ከዚያም እግዚአብሔር ይባርከናል፥ ሥራውም ይቀጥላል።
የዚህ ሕዝብ ሁኔታ ምንድን ነው? እግዚአብሔር የጦርነትን በትር በዚህ ሕዝብ ራስ ላይ እንደ ያዘ አያጠራጥርም። ፍርዶቹን ከመልቀቁ በፊት ቤተ ክርስቲያን ትክክል ታደርግ እንደ ሆነ ለማየት እየጠበቀ ነው። ቤተ ክርስቲያን በመነቃቃቶች ረገድ እንዲህ ባለ ሁኔታ ስለ ተመላለሰች ሕዝቡ በእርሱ ቁጣ ሥር ነው። እንግዲህ ጦርነት ቢመጣ መነቃቃቶቻችን የት ይሆኑ ነበር? ጦርነት የመነቃቃትን መንፈስ እንዴት በፍጥነት በዋጠው ነበር! የጦርነት መንፈስ ከመነቃቃቶች መንፈስ ፈጽሞ የራቀ ነው። የሕዝቡ አእምሮ ሁሉን በሚውጠው የጦርነት ጉዳይ በተያዘ ጊዜ የሃይማኖትን ጥያቄዎች ማን ይከታተላል? ይህ ሕዝብ እንዴት በድንገት ወደ ጦርነት አፋፍ እንደ ቀረበ አሁን እዩ። እግዚአብሔር የሚንበለበል ሰይፉን በራሳችን ላይ ይወዘውዛል። ቤተ ክርስቲያን ንስሐ ትገባለችን? እግዚአብሔር በዋናነት የሚመለከተው ቤተ ክርስቲያንን ነው። የጦርነትን እርግማን እንዴት እናመልጣለን? በቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ብቻ። ጦርነትን እንዲያስቀሩ ወደ ፖለቲከኞች መመልከት ከንቱ ነው። ምናልባት በአብዛኛው ጦርነትን ይደግፉ ይሆናል። ለማስቀረት የሚያደርጓቸው ነገሮች በቀጥታ ወደ እርሱ ሊያስገቡን ይችላሉ። ቤተ ክርስቲያን የማይሰማት፥ የማትነቃ፥ የማትሠራ ከሆነ፥ እርዳታ ከየት እንጠብቃለን? ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ የማትንቀሳቀስ፥ በራሳችን ላይ በተንጠለጠሉት በእግዚአብሔር ጽድቅ ፍርዶች ፊት የማትንቀጠቀጥ ከሆነ፥ እንደ ሕዝብ በእርግጥ ለመረገም ቀርበናል።
6. የሚደረገው ማንኛውም ነገር በፍጥነት መደረግ አለበት። ሚዛኑ በእኩል ተንጠልጥሏል። ወደ ፊት ካልሄድን ወደ ኋላ መመለሳችን አይቀርም። ነገሮች እንዳሉ ሊቆዩ አይችሉም። ቤተ ክርስቲያን ካልተነሣች፥ እስካሁን ካገኘነው የበለጠ ብርቱ መነቃቃት ካላገኘን በጣም በቅርቡ ምንም መነቃቃት አይኖረንም። እንዲህ ያለ ታላቅ መነቃቃት ስላገኘን አሁን ትናንሽ መነቃቃቶች የሕዝቡን አእምሮ አይስቡም። እንደ ግለሰቦች መሥራት አለባችሁ። የራሳችሁን ግዴታ ፈጽሙ። ኃላፊነት አለባችሁ። ፈጥናችሁ ንስሐ ግቡ። ሌላ ዓመት አትጠብቁ። ነገሮች ያለ ታላቅና አጠቃላይ ሃይማኖታዊ መነቃቃት ለሌላ ዓመት ቢቀጥሉ የእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ሁኔታ ምን እንደሚሆን ከእግዚአብሔር በቀር ማን ያውቃል?
7. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነገሮች ሁሉ ሲበላሹ እያንዳንዱ ሰው የራሱን የወቀሳ ድርሻ ችላ ብሎ ቤተ ክርስቲያንንና ወንድሞቹን መንቀፍ የተለመደ ነው። ማንም «ቤተ ክርስቲያን» በሚባለው ረቂቅ ነገር ላይ ስሕተት በመፈለግ ጊዜውን አያጥፋ። ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ግለሰብ አባል ይሥራ፥ በትክክልም ይሥራ፥ በትቢያ ውስጥ ዝቅ ይበል፥ በትዕቢትም ሆነ በፈራጅነት ፈጽሞ አይናገር። ወደ ፊት ሂዱ። እንዲህ ያለውን ሥራ ትቶ ደብዳቤ ወደ መጻፍ የሚሄድ፥ እነዚህ ሁሉ ጥቃቅን ክርክሮች ሊስተካከሉ ይችሉ እንደ ሆነ ለማየት ወደ ኦኖ ሜዳ የሚወርድ፥ ሥራውንም የሚያስቆም ማን ነው? ሥራችንን እናስብ፥ የቀረውንም ጌታ ይጠብቀው። ግዴታችንን እንፈጽም፥ ውጤቱንም ለእግዚአብሔር እንተው።
እነዚህ ትምህርቶች ከተሰጡ ወዲህ በዚህች አገር በበጎ አድራጎት ሥራዎች ሁሉ ታላቅ እድገት ተደርጓል። በፕሬስቢቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እጅግ ብዙ የተሳሳተ ተቃውሞ የተነሣባቸው የእነዚያ መነቃቃቶች ንጽሕናና ሊተመን የማይችል ዋጋ ጥያቄ በጊዜ ተፈትቷል። ተቃዋሚዎች የተነበዩት ታላቅና አጥፊ የኋሊት ምላሽ እንዳልታየ አሁን ታውቋል። የእነዚያ መነቃቃቶች አዳዲስ አማኞች የአብያተ ክርስቲያናት ብርታት እንደ ነበሩ፥ ክርስቲያናዊ ተጽእኖአቸውም በመላው አገር እንደ ተሰማ አሁን መቀበል ግድ ነው። እንዲህ ያለ የተቃውሞ ማዕበል ከተነሣበት ከዚያ ታላቅና የተባረከ የእግዚአብሔር ሥራ የበለጠ ኃይሉና ንጽሕናው በጊዜና በተሞክሮ የተረጋገጠ መነቃቃት ከቶ አልነበረም። ተቃውሞው ግልጽ የሆነ ታላቅ ስሕተት ነበር። ተቃውሞው ከሥራው ጋር በነበሩ ታላላቅ ክፋቶች የተነሣ አስፈላጊ ነበር፥ እነዚያም ክፋቶችና ስሕተቶች በተቃውሞው ተገትተው ታርመዋል አይባል። እውነቱ ለተቃውሞው ምክንያት የተደረጉት ስሕተቶችና ክፋቶች ተብለው የታሰቡት ነገሮች ማስደንገጥንም ሆነ ተቃውሞን የሚያጸድቅ መጠን ፈጽሞ አልነበራቸውም። ጥያቄውን ይበልጥ በሰፊው የመረመርሁበትን የእነዚያን መነቃቃቶች ታሪክ ጽፌአለሁ። አብያተ ክርስቲያናት የተጠነቀቁባቸውን እነዚያን ክፋቶች ለማስቀረት እስኪበቃ ድረስ ልከኝነትንና ሌሎችንም የተሐድሶ ቅርንጫፎች በእርግጥ ያዙ። በባርነት ጥያቄ ግን ቤተ ክርስቲያን ጦርነቱን ለማስቀረት በምስክርነቷ ዘገየች። ነገር ግን የመነቃቃት ተጽእኖ በተሰማበት በዚያ ሰሜናዊ አካባቢ ሁሉ በተቋማቸው ላይ እየጨመረ በመጣው ተቃውሞ ባሪያ ያላቸው ሰዎች እጅግ ደነገጡ፥ ተበሳጩም። ርኩሰቱን ለመከላከልና ለማስቀጠል መሣሪያ አነሡ፤ ይህንም በማድረጋቸው አስወገዱት።