ምዕራፍ 15 · 37 ደቂቃ ንባብ · 47 ደቂቃ ማዳመጥ
ትምህርት 13. አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችን እንዴት ሊረዱ ይችላሉ
ትምህርት 13.
አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችን እንዴት ሊረዱ ይችላሉ።
ጥቅስ።—ሙሴም እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ያሸንፍ ነበር፤ እጁንም ባወረደ ጊዜ አማሌቅ ያሸንፍ ነበር። የሙሴ እጆች ግን ከብደው ነበር፤ ድንጋይም ወስደው ከበታቹ አኖሩለት፥ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በዚህ አንዱም በዚያ ሆነው እጆቹን ደገፉ፤ እጆቹም ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ጸንተው ቆሙ። ኢያሱም አማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ።—ዘጸአት 17፥11-13።
መጽሐፍ ቅዱሳችሁን የምታነብቡ እናንተ እነዚህ ቁጥሮች የሚገኙበትን ዐውድ ታስታውሳላችሁ። የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶቻቸውን ሲያስገዙ ከአማሌቃውያን ጋር ለመዋጋት መጡ፤ እነዚህም ነገሮች ተፈጸሙ። አነጋገሩ የጸሎትን አቋም እንደሚያመለክት ካልተረዳን በቀር ሙሴ እጆቹን ማንሣቱ ለምን እንዲህ ያለ ትኩረት እንደ ተሰጠው መረዳት አስቸጋሪ ነው። እንግዲህ እጆቹን ማንሣቱና ከዚያ ጋር የሆነው ድል ከእግዚአብሔር ጠላቶች ጋር በምናደርገው ትግል ሁሉ ርዳታውን ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ምን ያህል አስፈላጊ እንደ ሆነ ያስተምረናል። የአሮንና የሖር ትብብርና ድጋፍ በአጠቃላይ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችን በሥራቸው የመደገፍና የመርዳት ግዴታ እንዳለባቸው፥ ይህም ትብብር ለተሰበከው ወንጌል ስኬት ምን ያህል አስፈላጊ እንደ ሆነ የሚያመለክት ተደርጎ ተረድቷል። እኔም ዛሬ በዚሁ መንገድ እጠቀምበታለሁ። አገልጋዮች ለመነቃቃት የመድከም ግዴታቸውን ተናግሬአለሁና አሁን የምመለከተው፦
መነቃቃትን በማስገኘትና በማስቀጠል የቤተ ክርስቲያን ትብብር ያለውን አስፈላጊነት ነው።
መነቃቃትን በማስፋፋት ረገድ አብያተ ክርስቲያናትና አገልጋዮች በሚገባ ያላጤኑአቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤ እነዚህ ካልተጠበቁ መነቃቃቶች እንዲስፋፉ፥ እንዲያውም ለረጅም ጊዜ እንዲቀጥሉ ማድረግ የማይቻል ይሆናል። ባለፉት ሁለት ትምህርቶቼ ስለ አገልጋዮች ግዴታዎች ሳወራ ቈይቻለሁ፤ ምክንያቱም ስለ መነቃቃት ተከታታይ ትምህርቶችን ስሰጥ ወደዚያ የመንገዶች ክፍል ይብዛም ይነስም ሳልገባ መስበክ አይቻለኝም ነበርና። ያንን የርእሱን ክፍል ገና አልጨረስሁም፤ ነገር ግን እዚህ ላይ ፈቀቅ ብዬ ቤተ ክርስቲያን መነቃቃትን ልታገኝ ብትጠብቅ አገልጋይዋን ልትደግፍና ልትረዳው የሚገባባቸውን አንዳንድ ነጥቦች መወያየት አስፈላጊ መስሎ ታይቶኛል። ርእሱን ስወያይ እንዲህ ለማድረግ አስባለሁ፦
I. ክርስቲያኖች አገልጋዮችን ሊደግፉ ቢወዱ ሊርቋቸው የሚገቡትን አንዳንድ ነገሮች መጥቀስ።
II. ልብ ሊሉአቸው የሚገቡትን አንዳንድ ነገሮች።
I. ሊርቁ የሚገቡትን አንዳንድ ነገሮች እጠቅሳለሁ።
1. በምንም ዓይነት አገልጋዩ ብቻውን መነቃቃትን ማስፋፋት አለበት ከሚለው አሳብ በንድፈ ሐሳብም በተግባርም ራቁ። ብዙ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ተቀባይ ብቻ ሆነው የሚያደርጉት ነገር እንደሌለ ይሰማቸዋል። በትምህርትና በመጽናናት እንዲመግባቸው አገልጋይ ቀጥረው ከፍለውታል፤ አሁን እርሱ የሚሰጣቸውን ምግብ ተቀምጠው ከመዋጥ በቀር የሚያደርጉት ነገር የለም። ደመወዙን ይከፍላሉ፥ ስብከቱንም ይሰማሉ፤ ይህም ብዙ እንደ ማድረግ ይቈጥሩታል። እርሱም በበኩሉ እንዲያጠነክራቸውና እንዲያጽናናቸው መልካም፥ ጤናማና የሚያጽናና ትምህርት እንዲሰብክ ይጠበቅበታል፤ እንዲህም ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደሚሄዱ ይጠብቃሉ። እላችኋለሁ፥ ሃይማኖታቸው ይህ ከሆነ ወደ ገሃነም ይሄዳሉ። ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚወስደው መንገድ ይህ አይደለም።
ይህ መንፈስ በቤተ ክርስቲያን በሚገዛበት ስፍራ አገልጋዩ የቱንም ያህል መልካም ቢሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ መነቃቃትን የሚከለክለውን መንገድ እንደ ያዘች እርግጠኞች ሁኑ። የቱንም ያህል ታማኝ፥ የቱንም ያህል በሥራው የተጠመደ፥ የቱንም ያህል ተሰጥኦ ያለውና አንደበተ ርቱዕ ቢሆን ራሱን ሊያደክም፥ ምናልባትም ሕይወቱን ሊያጠፋ ይችላል፤ ነገር ግን መነቃቃትን ጥቂት ወይም ምንም አያይም።
ቤተ ክርስቲያን በሌለችበት ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጣም ጥቂት አባላት ባሉበት ስፍራ ያለ ቤተ ክርስቲያን የተደራጀ ጥረት መነቃቃት ሊስፋፋ ይችላል፤ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን በዚያ የለችም፤ በእንዲህ ያለው ሁኔታም ሐዋርያት ወንጌልን በዓለም ለመትከል ብቻቸውን በወጡ ጊዜ እንዳደረገው እግዚአብሔር ጸጋውን ከሁኔታው ጋር ያስማማዋል። እንዲህ በሆነባቸው ስፍራዎች የኃይለኛ መነቃቃት ምሳሌዎችን አይቻለሁ። ነገር ግን መንገዶች ባሉበት ስፍራ እግዚአብሔር ሥራ ላይ እንዲውሉ ይፈልጋል። የማትሠራ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ስፍራ መነቃቃትን ለማስፋፋት ከምሞክር በስፍራው ምንም ቤተ ክርስቲያን ባይኖር እመርጣለሁ። እግዚአብሔር በረከትን እንዲሰጥ በሕዝቡ ሊለመን ይወዳል። የማትሠራ ቤተ ክርስቲያን የምታሳድረው ተቃራኒ ተጽዕኖ ከክሕደት የከፋ ነው። አንዳንድ ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ገለልተኞች እንደ ሆኑ ቢያስቡም ስለ መነቃቃት ገለልተኛ ስፍራ መያዝ ፈጽሞ አይቻልም። ሃይማኖተኛ ነኝ የሚል ሰው ራሱን ለሥራው ካልሰጠ ይቃወመዋል። እንዲህ ያለው ሰው መካከለኛ ስፍራ ለመያዝ ቢሞክርና ነገሩ እንዴት እንደሚሆን ቈይቼ አያለሁ ቢል—ይህ ዲያብሎስ እንዲይዘው የሚፈልገው ስፍራ ራሱ ነው። ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ በዚህ መንገድ ሥራውን በግልጽ ከመቃወም ይልቅ እጅግ አጥብቀው ሊሠሩለት ይችላሉ። በግልጽ ቢቃወሙ ሁሉም ሃይማኖት የላቸውም ይላል። በዚህ መካከለኛ መንገድ ግን ተጽዕኖአቸውን ይዘው ይቈያሉ፤ እንዲህም የዲያብሎስን ሥራ አጥብቀው ይሠራሉ።
ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ስትቀጥር በክርስቶስ ዓላማ ወደ ተግባር የሚመራቸውን መሪ ብቻ እንደ ቀጠሩ ማስታወስ አለባቸው። አንድ ሰው የጦር አዛዥን ደግፈን ብቻውን እንዲዋጋ እንልቀቀው ቢል ሰዎች እንግዳ ነገር አድርገው ያዩታል! አገልጋይ ብቻውን ወደ ፊት ለመሄድ መሞከሩም ከዚህ ያላነሰ ሞኝነትና ጥፋት ነው። ቤተ ክርስቲያን አገልጋይዋን ብቻውን እንዲሠራ ብትተወው የአገልግሎትን ዓላማ በስሕተት ተረድታለች። ስብከቶቹን መስማታቸው ብቻ በቂ አይደለም። ያ ቤተ ክርስቲያን ልትከተለው የሚገባት የትእዛዝ ቃል ብቻ ነው።
2. ግዴታችሁን የማትፈጽሙ ከሆናችሁ መነቃቃት ስለሌለ አገልጋያችሁን አታማርሩ። ግዴታችሁን የማትፈጽሙ ከሆናችሁ መነቃቃት የለም ብሎ ማማረር ምንም ጥቅም የለውም። መነቃቃት እንዳይኖር ያ ብቻውን በቂ ምክንያት ነው። ቤተ ክርስቲያን ራሷ በከባድ እንቅልፍ ተኝታ ሳለች በአገልጋይዋ ላይ ማማረሯ እጅግ ጨካኝና አስጸያፊ ነገር ነው። ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ በአገልጋዮቻቸው ላይ በማማረር ራሳቸውን ማመስገንና ሕሊናቸውን ማረጋጋት በጣም የተለመደ ነው። አገልጋዮች ነቅተው መኖራቸው ያለው አስፈላጊነት ሲነገር እንዲህ ያሉ ሰዎች፥ እንዲህ ያለ አገልጋይ እያለን ፈጽሞ መነቃቃት አናገኝም ለማለት ፈጣኖች ናቸው፤ እውነታው ግን አገልጋያቸው ከእነርሱ እጅግ የበለጠ ነቅቶ መኖሩ ነው።
በዚህ ነጥብ ረገድ እውነትና ሊታወቅ የሚገባው ሌላም ነገር አለ። ቤተ ክርስቲያን ወደ ዝቅተኛ ሁኔታ ስትወርድ ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ በቤተ ክርስቲያንና በመካከላቸው ባለው የሃይማኖት ዝቅተኛ ሁኔታ ላይ ለማማረር ፈጣኖች ናቸው። ያ የማይዳሰስና ተጠያቂነት የሌለበት አካል፥ «ቤተ ክርስቲያን»፥ ተኝታለች ተብሎ በእነርሱ እጅግ ይወቀሳል። ቤተ ክርስቲያን ከግለሰቦች የተሠራች መሆኗን፥ እያንዳንዱም የራሱን ጉዳይ በእጁ እስኪይዝ፥ በራሱ ላይ እስኪያማርር፥ በእግዚአብሔርም ፊት ራሱን እስኪያዋርድ፥ ንስሐ እስኪገባና እስኪነቃ ድረስ ቤተ ክርስቲያን ውጤታማ ልትሆን እንደማትችልና መነቃቃትም ፈጽሞ ሊኖር እንደማይችል ሳይገነዘቡ ስለ ሃይማኖት ዝቅተኛ ሁኔታና ስለ ቤተ ክርስቲያን ወይም ስለ አገልጋዩ ቀዝቃዛነት በሐዘን ያማርራሉ። በአገልጋያችሁ ወይም በቤተ ክርስቲያን ላይ ከማማረር ይልቅ እያንዳንዳችሁ ብትነቁ፥ ከሰውም ሁሉ ደም ንጹሕ እንደ ሆናችሁና ኃጢአተኞችን ለማዳን ግዴታችሁን እንደምትፈጽሙ እስክትሉ ድረስ በእርሱ ወይም በእነርሱ ላይ ባታማርሩ፥ እርሱ የማማረራችሁን ትክክለኛነት ሊሰማው ይችላል፤ እርሱ ባይሰማው እንኳ እግዚአብሔር ይሰማዋል፥ ወይ ያነቃዋል ወይ ያስወግደዋል።
3. እናንተ ልትረዱት እምቢ እያላችሁ አገልጋያችሁ ሥራውን ብቻውን ለመሸከም በመሞከር ራሱን እንዲገድል አትፍቀዱ። አንዳንድ ጊዜ አገልጋይ ኃይሉን ሁሉ ካላፈሰሰ በቀር የጌታ ታቦት እንደማይንቀሳቀስ ያገኛል፤ መነቃቃትንም እጅግ ስለ ተመኘ ይህን አድርጎ ሞቷል። ስለ እርሱም ሊሞት ፈቃደኛ ነበረ። በዚህ ክፍለ ሀገር ቤተ ክርስቲያን ከሥራው ወደ ኋላ ባለችበት ስፍራ መነቃቃትን ለማስፋፋት በደከሙት ድካም ምክንያት፥ ያለ ጥርጥር፥ አገልጋዮች የሞቱባቸውን አንዳንድ ጉዳዮች መጥቀስ እችል ነበር።
አንድ ጉዳይ እጠቅሳለሁ። ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ አገልጋይ መነቃቃት ባለበት ስፍራ ይሠራ ነበር፤ በርቀት ከምትገኝ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሽማግሌ መጥቶ ወደዚያ ሄዶ እንዲሰብክ ፈለገ። በዚያ መነቃቃት አልነበረም፥ ከቶም ኖሮ አያውቅም፤ ሽማግሌውም ስለ ሁኔታቸው አማረረ፤ ሁለት ግሩም አገልጋዮች እንደ ነበሩአቸው፥ አንዱ ፈጽሞ ደክሞ እንደ ሞተ፥ ሌላውም ራሱን አድክሞ ተስፋ ቈርጦ እንደ ተዋቸው፥ እነርሱም ድሆችና ደካሞች ቤተ ክርስቲያን እንደ ሆኑ፥ መነቃቃት ካላገኙም ተስፋቸው እጅግ የጨለመ እንደ ሆነ ተናገረ፤ ስለዚህም ይህ አገልጋይ መጥቶ እንዲረዳቸው ለመነው። እጅግ ያዘነ ይመስል ነበር፤ አገልጋዩም ልቅሶውን ሰምቶ በመጨረሻ፥ ለምን ከቶ መነቃቃት አላገኛችሁም? ብሎ በመጠየቅ መለሰ። አላውቅም አለ ሽማግሌው። አገልጋያችን እጅግ ደከመ፥ ቤተ ክርስቲያን ግን የነቃች አትመስልም ነበር፤ በሆነ ምክንያትም መነቃቃት የነበረ አይመስልም። አገልጋዩም እንዲህ አለ፦ «እንግዲህ፥ የምትፈልጉትን አያለሁ፤ ከእግዚአብሔር አገልጋዮች አንዱን ገደላችሁ፥ ሌላውንም ሰበራችሁት ትቶአችሁም ሄደ፤ አሁን ደግሞ ሌላ አምጥታችሁ ልትገድሉት ትፈልጋላችሁ፤ ዲያብሎስም አልጋችሁን እንድወዘውዝላችሁ ልታስሄዱኝ ወደዚህ ልኮሃል። የሚሰብክላችሁ አንድ መልካም አገልጋይ ነበራችሁ፥ እናንተ ግን መተኛታችሁን ቀጠላችሁ፤ እርሱም በሥራው ላይ ፈጽሞ እስኪሞት ድረስ ራሱን አደከመ። ከዚያም ጌታ ሌላ ሰጣችሁ፤ አሁንም ተኝታችሁ ቀራችሁ፥ ለግዴታችሁም አልነቃችሁም። አሁን ደግሞ ተስፋ ቈርጣችሁ ወደዚህ መጥታችሁ ሌላ አገልጋይ ትፈልጋላችሁ፥ አይደለም? እንዳደረጋችሁት እያደረጋችሁ ሳላችሁ ሌላ እንዳታገኙ እግዚአብሔር ይከልክል። ቤተ ክርስቲያን ለግዴታዋ እስክትነቃ ድረስ አገልጋይ እንዳታገኙ እግዚአብሔር ይከልክል።» ሽማግሌው ልቡ ተነካ፥ መልካም ሰው ነበርና። እንባ ከዓይኖቹ ፈሰሰ፤ የሚገባቸውም ይህ እንደ ሆነ ተናገረ። አገልጋዩም፥ «አሁንስ፥ ታማኝ ትሆናለህን? ወደ ቤትህ ሄደህ የምለውን ለቤተ ክርስቲያን ትነግራለህን? ብትነግርና እነርሱም ታማኞች ሆነው ለግዴታቸው ቢነቁ፥ አገልጋይ ያገኛሉ፤ ይህን ዋስ ሆኜ አረጋግጥላቸዋለሁ» አለ። ሽማግሌውም እንደሚነግር ተናገረ፤ ለቃሉም ታማኝ ሆነ፤ ወደ ቤቱ ሄዶ ካልነቁ በቀር ሌላ አገልጋይ ወደ መካከላቸው እንዲመጣ መለመናቸው ምን ያህል ጨካኝ እንደ ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ነገራቸው። ተሰማቸው፥ ኃጢአታቸውንም ተናዘዙ፥ ለግዴታቸውም ነቁ፤ አገልጋይም ተላከላቸው፤ ውድና ኃይለኛ መነቃቃትም ተከተለ።
አብያተ ክርስቲያናት ቀዝቃዛነታቸውና ዳተኛነታቸው ስንት ጊዜ የአገልጋዮች ሞት ትክክለኛ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አይገነዘቡም። የሕዝቡና የኃጢአተኞች ሁኔታ በአእምሮአቸው ላይ ይከብዳል፤ ሌሊትና ቀን በነፍሳቸው ይምጣሉ፤ በጊዜውም አለጊዜውም ሰብዓዊ ሰውነት ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ይደክማሉ፤ እስኪያልቁና እስኪሞቱ ድረስ። አገልጋይ ስለ ነፍሳት ሲምጥ፥ ቤተ ክርስቲያንም እንድትረዳ ሊያነቃት ሲደክም፥ አሁንም በሞት እንቅልፍ ተኝታ ሲያያት የልቡን ጭንቀት ቤተ ክርስቲያን አታውቅም። ምናልባት አንዳንድ ጊዜ ለጥቂት ቀናት ተነሥተው ድንገተኛ ጥረት ያደርጋሉ፤ ከዚያም ሁሉ እንደ ገና ይቀዘቅዛል። እንዲሁም ብዙ ታማኝ አገልጋይ ራሱን አድክሞ ይሞታል፤ ከዚያም እነዚህ ልብ የሌላቸው ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ይህን ያህል ብዙ በማድረጉ ለመውቀስ የመጀመሪያዎቹ ናቸው።
መነቃቃት ወደ ነበረበት ስፍራ የሄደና በዚያም ሳለ ለአገልጋዮች የተነገረ ቀጥተኛ ስብከት የሰማ አንድ መልካም አገልጋይ አስታውሳለሁ። እንደ እግዚአብሔር ሰው ተቀበለው፤ በእግዚአብሔር እውነት ላይ አላመፀም፥ ነገር ግን በሕዝቡ መካከል መነቃቃትን እስኪያይ ድረስ ፈጽሞ እንደማያርፍ ለእግዚአብሔር ተሳለ። ወደ ቤቱ ተመልሶ ሥራ ጀመረ፤ ከጥቂት አባላት በቀር ቤተ ክርስቲያን አልነቃችም፤ ጌታም እነርሱን ባረካቸው፥ መንፈሱንም አፈሰሰ፤ አገልጋዩ ግን በመነቃቃቱ መካከል በአልጋው ላይ ተኝቶ ሞተ።
4. ተግሣጹ በራሳችሁ ላይ ሲያርፍ እንኳ ግልጽና ቀጥተኛ በሆነ ስብከት ላይ ከማማረር ተጠንቀቁ። አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ ተጠያቂ የሆነው ለእግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ይረሳሉ። እንዳይመለከታቸው አገልጋዩ የሚሰብክበትን ሕግ ሊያወጡለት ይፈልጋሉ። በቤተ ክርስቲያን ላይ አጥብቆ ቢናገርና በመካከላቸው የሰፈኑትን ኃጢአቶች ቢገልጥ፥ ግላዊ ጥቃት ብለው ይጠሩታል፥ በእውነትም ላይ ያምፃሉ። ወይም፥ በዓለም ፊት ለቤተ ክርስቲያን እንዲህ በግልጽ መስበክ አይገባውም፤ ሃይማኖትን ያጋልጣል ይላሉ፤ ለብቻቸው ወስዶ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሊሰብክ እንጂ ክርስቲያኖች ምን ያህል ክፉ እንደ ሆኑ ለኃጢአተኞች ሊነግር አይገባውም ይላሉ። ነገር ግን አገልጋይ ለያዕቆብ ቤት ኃጢአታቸውን ከማሳየት ያነሰ ሊያደርግ የማይችልባቸው ጉዳዮች አሉ። ለምን ብቻችንን ስንሆን አታደርገውም? ብትሉ፥ ኃጢአተኞች ክፉ እንደምታደርጉ የማያውቁ ይመስል! እላለሁ። ለኃጢአት ብቻችሁን ስትሰበሰቡ እኔም ስለ ኃጢአታችሁ ብቻችሁን እሰብክላችኋለሁ። ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በዓለም ፊት ብትበድሉ በዓለም ፊት ትገሠጻላችሁ። ኃጢአተኞች እንዴት እንደምትኖሩ እንደሚያውቁና በእናንተ ተሰናክለው ወደ ገሃነም እንደሚወድቁ እውነት አይደለምን? እንግዲያስ አገልጋዮች ቤተ ክርስቲያንን በግልጽ በዓለም ፊት መገሠጽ ግዴታቸው እንደ ሆነ ሲያዩ አትውቀሱአቸው። ይህን መታገሥ እስከማትችሉ ድረስ ትዕቢተኞች ከሆናችሁ መነቃቃትን አትጠብቁ። የቤተ ክርስቲያንን ጕድለት ስለሚገልጥ ስብከትን እጅግ ግልጽ ነው አትበሉ። እጅግ ግልጽ የሆነ ስብከት የሚባል ነገር የለም።
5. አንዳንድ ጊዜ ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ አገልጋዩ በግልጽ ስብከቱ ኃጢአተኞችን እንዳያስቀይም ይሰጋሉ። እርሱንም ስለዚህ ማስጠንቀቅ ይጀምራሉ፥ ላለማስቀየም ትንሽ ቢለውጥ አይሻልምን? እያሉ ይጠይቁታል። ይህ ፍርሃት በተለይ ከጉባኤው መካከል ሀብታምና ተጽዕኖ ያላቸው አንዳንዶች ቢቀየሙ፥ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን ድጋፍ እንዳያቋርጡ፥ የአገልጋዩንም ደመወዝ ለመክፈል ገንዘባቸውን መስጠት እንዳያቆሙና ሸክሙም በቤተ ክርስቲያን ላይ እንዳይከብድ ይነሣሣል። በእንዲህ ያለች ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ መነቃቃት ሊኖር አይችልም። እንዴ፥ ቤተ ክርስቲያን ከሁሉ በላይ እውነት በኃጢአተኞች ላይ እንደ እሳት እንዲመጣ መጸለይ አለባት። ቢቀየሙስ ምን ይሆናል? ክርስቶስ ያለ ገንዘባቸው በደኅና ሊሄድ ይችላል። አገልጋያችሁን አትውቀሱ፥ ኃጢአተኞችን ደስ ለማሰኘትና ለማባበል የስብከቱን ስልት እንዲለውጥም አትለምኑት። አገልጋይ እውነትን ሊሰብክላቸው ካልቻለ ንስሐ ላልገቡ መስበኩ ምንም አይጠቅምም። እንዲመረመሩና እንዲድኑ ተደርጎ ካልተሰበከላቸውም ለወንጌል ድጋፍ መክፈላቸው ምንም አይጠቅማቸውም።
አንዳንድ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን አባላት ኃጢአተኞች ስለ ተከፉ ስለ አገልጋዩ ጥንቃቄ ማጣት በመካከላቸው ይነጋገራሉ፥ ወገንም ያቋቁማሉ፥ እጅግ የተሳሳተ መንፈስም ውስጥ ይገባሉ። ኃይለኛ መነቃቃትና ታላቅ ተቃውሞ የነበረበት አንድ ስፍራ ነበረ። አገልጋዩ ግልጽነቱንና ቀጥተኛነቱን ካልቀነሰ ንስሐ ካልገቡት አንዳንዶቹ ሄደው ሌላ ጉባኤ ይቀላቀላሉ ብለው ቤተ ክርስቲያን ፈሩ። ከቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ሰዎች አንዱ ወደ አገልጋዩ ሄዶ እንዲህ አጥብቆ እንዳይሰብክ እንዲለምነው ተመደበ፤ እንዲህ ማድረጉን ቢቀጥል እገሌና እገሌ ጉባኤውን ይተዋሉና። አገልጋዩም፥ ስብከቱ እውነት አይደለምን? ብሎ ጠየቀ። «አዎን።» እግዚአብሔርስ አይባርከውምን? «አዎን።» በዚህ ስፍራ እንዲህ ያለውን ሥራ ከዚህ በፊት አይተህ ታውቃለህን? «አይ፥ ከቶ አላየሁም።» «ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ ዲያብሎስ በዚህ ጕዳይ ወደዚህ ልኮሃል፤ እግዚአብሔር ስብከቱን እንደሚባርክ፥ ሥራው እንደሚቀጥል፥ ኃጢአተኞችም በየቀኑ እንደሚለወጡ ታያለህ፤ አሁን ደግሞ የኃጢአተኞችን አእምሮ ለማሳረፍ የስብከቱን ቃና እንዳወርድ ልታደርገኝ መጣህ።» ሰውዬው ተግሣጹ ተሰማው፥ እንደ ክርስቲያንም ተቀበለው፤ ስሕተቱን አይቶ ተገዛ፥ ዳግመኛም በስብከት ግልጽነት ላይ ሲነቅፍ ከቶ አልተሰማም።
መነቃቃት በነበረበት በሌላ ከተማ ተጽዕኖ የነበራት አንዲት ሴት (ሃይማኖተኛ ያልነበረች)፥ እርሷ እንደምትለው ግልጽ፥ ቀጥተኛና ግላዊ በሆነ ስብከት ላይ እጅግ አማረረች። ብዙም ሳይቈይ ግን እርሷ ራሷ የሥራው ፍሬ ሆነች። ከዚያ በኋላ ንስሐ ያልገቡ አንዳንድ ወዳጆቿ «እንዲህ አቃጥሎ ስለሚሰብክ» በሰባኪው ላይ ትናገረው የነበረውን አስታወሷት። እርሷም አሁን አመለካከቷ እንደ ተለወጠ፥ እውነት እንደ ፍም ቀልቶ ቢሰበክ እንኳ ምን ያህል ቢያቃጥል ግድ እንደማይሰጣት ተናገረች።
6. በምንም መንገድ ከኃጢአተኞች ጋር አትወግኑ። ብታደርጉት እጃቸውን ታበረታላችሁ። ኃጢአተኞች አገልጋዩን ጥንቃቄ የጐደለው ወይም ግላዊ ጥቃት የሚያደርስ ብለው ቢከሱት፥ የቤተ ክርስቲያን አባላትም አገልጋዩ እንዲህ እንደሚያደርግ ባይቀበሉም ግላዊ ስብከት ስሕተት ነው ብለው ብቻ ቢቀበሉና ስለ ግላዊ ስብከት ተገቢ አለመሆን ቢያወሩ፥ ኃጢአተኞች በእንዲህ ያለው አነጋገር እንደ ተበረቱ ይሰማቸዋል። ከቶ ከእነርሱ ጋር አትተባበሩ፤ በአገልጋያቸው ላይ እናንተን ከጐናቸው እንዳገኙ ይሰማቸዋልና። መርሖአቸውን ትቀበላላችሁ፥ ቋንቋቸውንም ትጠቀማላችሁ፥ ከእነርሱም ጋር እንደምትራሩ ትቈጠራላችሁ። ግላዊ ስብከት ምንድን ነው? እርሱን እንደሚመለከት እንዲሰማው ካልተደረገ በቀር ማንም ግለሰብ በስብከት አይጠቀምም። እንግዲህ እንዲህ ያለ ስብከት ሁልጊዜ ግላዊ ነው። ብዙ ጊዜ ለክፉ ሰዎች እጅግ ግላዊ ስለሚመስላቸው በጉባኤው ፊት በስማቸው ሊጠሩ የቀረቡ ያህል ይሰማቸዋል። አንድ አገልጋይ በአንድ ወቅት ለጉባኤ ይሰብክ ነበር፤ አንዳንድ ጠባዮችንም ሲገልጽ፥ «ሁሉን አዋቂ ብሆን ኖሮ ከዚህ ሥዕል ጋር የሚስማሙትን ሰዎች በስማቸው መጥራት በቻልሁ ነበር» አለ። አንድ ሰው፥ «እኔን ጥራኝ!» ብሎ ጮኸ፤ ወደ መሬትም ሊሰጥም ያለ ይመስል ነበር። ከዚያ በኋላ ጮኾ ለመናገር ምንም አሳብ እንዳልነበረው፥ ነገር ግን አገልጋዩ እርሱን ፍጹም አድርጎ ስለ ገለጸው በስሙ ሊጠራው እንደ ሆነ በእውነት እንዳሰበ ተናገረ። አገልጋዩ እንዲህ ያለ ሰው በዓለም መኖሩን አያውቅም ነበር። ሰዎች የራሳቸው ምግባር እንደ ተገለጸ ማሰባቸው የተለመደ ነው፤ «ስለ እኔ ማን ነገረው? አንድ ሰው ስለ እኔ አውርቶለት በእኔ ላይ እንዲሰብክ አድርጎታል» እያሉም ያማርራሉ። እንዲህ ያሉ አምስት መቶ ወይም አንድ ሺህ ጉዳዮች ሰምቻለሁ ብዬ እገምታለሁ። እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን አባላት አገልጋይ በስብከቱ ማንንም ማመልከቱ ስሕተት ነው ብለው ቢቀበሉ፥ እንዴት ምንም መልካም ነገር ሊያደርግ ይችላል? አገልጋያችሁ ማንንም እንዲያመለክት ወይም ለማንም እንዲሰብክ ፈቃደኞች ካልሆናችሁ ብታሰናብቱት ይሻላችኋል። በፊቱ ላሉት ሰዎች፥ ለግለሰቦቹ ካልሆነ ለማን ይሰብካል? እነርሱንስ ሳያመለክት እንዴት ሊሰብክላቸው ይችላል?
7. መነቃቃትን ለማስፋፋት ከአገልጋያችሁ ጎን ለመቆም ብትፈልጉ ስብከቱን በሕይወታችሁ አትቃረኑ። ኃጢአተኞች ወደ ገሃነም እየሄዱ ናቸው ብሎ ቢሰብክ እናንተ በቀላልነታችሁና በግድየለሽነታችሁ ቃሉን ውሸት አታድርጉት፤ በፈገግታም ሁሉን አታቃልሉት። ልብን በሚመረምር ከባድ ስብከት በኋላ የክርስቲያኖች ቀላልነት በአእምሮአቸው ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ኃጢአተኞች ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እነርሱ ይረጋሉ፥ ልባቸውም ይለሰልሳል፥ ስለ ሁኔታቸውም መደንገጥ ይጀምራሉ፤ እነዚህ ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ግን በእነርሱ ላይ ከማልቀስ ይልቅ ቀለው ተዝናንተው ያዩአቸዋል፤ ይህም እንዲህ እንደ ማለት ነው፤ «ኃጢአተኞች ሆይ፥ አትፍሩ፤ ነገሩ ያን ያህል የከፋ አይደለም፤ ተረጋጉ፥ ደኅና ትሆናላችሁ፤ እናንተ እንዲህ በፍጥነት ወደ ገሃነም የምትሄዱ ቢሆን እኛ የምንስቅና የምንቀልድ ይመስላችኋል? ቤታችሁ ብቻ በእሳት ቢያያዝ እንኳ አንስቅም ነበር፤ እናንተ በውስጡ ስትቃጠሉ ብናይማ ከቶ አንስቅም።» እንዲህ ባለ ሁኔታ አገልጋይ ለኃጢአተኞች ቢሰብክ ምን ይጠቅማል?
8. ያለ አስፈላጊ ምክንያት የአገልጋያችሁን ጊዜ አትውሰዱ። አስፈላጊ የሚነጋገሩበት ነገርም ሆነ የተለየ ጉዳይ ሳይኖራቸው ለወሬ ብቻ በሚጎበኙአቸው ሰዎች ምክንያት አገልጋዮች ብዙ ጊዜ ያጣሉ። አገልጋዩ ወዳጆቹን በማየቱ ይደሰታል፤ ሕዝቡንም ስለሚወድድና ስለሚያከብር ከእነርሱ ጋር በመነጋገር ጊዜውን ለማሳለፍ ብዙ ጊዜ ከመጠን በላይ ፈቃደኛ ነው። ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ የአገልጋይ ጊዜ ከወርቅ እንደሚበልጥ ማስታወስ አለባቸው፤ ወርቅ ሊገዛው በማይችለው ነገር ላይ ሊውል ይችላልና። እነርሱ በእርሱ ጨዋታ ለመደሰት ብለው አገልጋዩን ከጉልበቱ፥ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱሱ፥ ወይም ከጥናቱ ቢያስቀሩት ታላቅ ጉዳት ያደርሳሉ። በቂ ምክንያት ሲኖራችሁ እርሱን ለመጎብኘት ከቶ ወደ ኋላ ማለት የለባችሁም፤ የሚያስፈልገውንም ጊዜ ሁሉ ብትወስዱ ችግር የለውም። ነገር ግን የምትናገሩት የተለየ አስፈላጊ ነገር ከሌለ ራቁ። በአንዱ ከተሞቻችን ሥራ የሌለው አንድ ሰው አውቃለሁ፤ እርሱም የአገልጋዩን የወራት ጊዜ ይወስድ ነበር። ሌላ የሚሠራው ነገር ስላልነበረው ወደ ጥናት ክፍሉ መጥቶ በአንድ ጊዜ ሦስት ሰዓት ተቀምጦ ያወራ ነበር፤ በመጨረሻም አገልጋዩ በግልጽ ሊገሥጸውና ምን ያህል ኃጢአት እየሠራ እንደ ሆነ ሊነግረው ግድ ሆነበት።
9. የሕዝብን ትኩረት ከሃይማኖት ጉዳይ ሊያዘናጋ የሚችልን ማንኛውንም ነገር ፈጽሞ አትደግፉ። ብዙ ጊዜ የሥራ ወቅት ሲደርስ፥ ምሽቶች ረዣዥም ሲሆኑ፥ ንግድም ሲቀል፥ ይህም ልዩ ጥረት የሚደረግበት ትክክለኛ ጊዜ ሲሆን፥ በዚያው ሰዓት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ ሰው ግብዣ ያዘጋጃል፤ ግብዣውም ሃይማኖታዊ እንዲሆን አንዳንድ ክርስቲያን ወዳጆችን ይጋብዛል። ከዚያም ውለታውን ለመመለስ ሌላ ቤተ ሰብ እንዲሁ ማድረግ አለበት። ከዚያም ሌላው፥ ደግሞም ሌላው፥ ይህ ሁሉ ክረምቱን በሙሉ የሚበላ የተደራጀ የግብዣ ሥርዓት እስኪሆን ድረስ ይቀጥላል። እንዴት ያለ ርኩሰት ነው! ይህ የዲያብሎስ ታላቅ ተንኮል ነው፤ በጎ ስሜትን ለማሳደግና ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ይበልጥ እንዲተዋወቁ የሚረዳ ስለሚመስል እጅግ ንጹሕና ተገቢ ሆኖ ይታያልና። በዚህም ከጸሎት ስብሰባዎች ይልቅ እነዚህን ግብዣዎች ያደርጋሉ።
የእነዚህ ግብዣዎች ክፋት እጅግ ታላቅ ነው። ብዙ ጊዜ በታላቅ ወጪ ይዘጋጃሉ፥ በውስጣቸውም እጅግ አስጸያፊ ሆዳምነት ይፈጸማል። ወጪው ከአንድ መቶ እስከ ሁለት ሺህ ዶላር ይደርሳል ይባላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ታላላቅ ግብዣዎችንና ታላላቅ ድግሶችን አድርገው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ገንዘብ የፈጸሙትን ይህን ኃጢአተኛ ብክነት ድግሱ ካለቀ በኋላ የተረፈውን ለድሆች! በመስጠት እንደ ሰበብ እንዳቀረቡት ተነግሮኛል። በዚህም ድሆችን እንጠቅማለን በሚል ሰበብ በእግዚአብሔር መግቦት በረከቶች እስከ መጥገብ ድረስ መፈንጠዝንና መደሰትን በጎ ምግባር ያደርጉታል። ይህ በመሠረቱ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአንዲት ጎረቤት ከተማ ከተደረገው ከአንድ ግሩም የዳንስ ድግስ ጋር አንድ ነው። ያ የዳንስ ድግስ ለድሆች ጥቅም ተብሎ የተዘጋጀ ነበር፤ እያንዳንዱ ጨዋ ሰው የተወሰነ ገንዘብ ይከፍል ነበር፤ ድግሱም ካለቀ በኋላ ከተሰበሰበው ገንዘብ የተረፈው ሁሉ ለድሆች ይሰጥ ነበር። በእውነት ይህ እንግዳ ምጽዋት ነው፤ ይበላሉ፥ ይጠጣሉ፥ ይጨፍራሉ፤ ከዚያም ከወዲያ በኋላ መደሰት እስኪሳናቸው ድረስ ከፈነጠዙና ከተመገቡ በኋላ ከማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ለድሆች ያድላሉ። እንዲህ ያለው የዳንስ ድግስ እንደነዚህ ያሉ የክርስቲያን ግብዣዎችን ያህል ለምን መንፈሳዊ እንደማይሆን አይገባኝም። የዳንስ ድግሶች ክፋት በጭፈራው ብቻ አይደለም፤ ከእነርሱ ጋር በተያያዙት ብልግና፥ ጥጋብና ፈተናዎች ውስጥ ነው።
ነገር ግን እነዚህ የክርስቲያን ግብዣዎች ናቸው፤ የሚገኙባቸውም ሁሉም ወይም ሁሉም ማለት ይቻላል ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ናቸው ይባላል። ደግሞም ብዙ ጊዜ በጸሎት ይፈጸማሉ ይባላል። እኔ ግን ይህን ከክፉ ገጽታዎቻቸው አንዱ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፤ ጊዜና ገንዘብ ከባከነ በኋላ፥ በመብልና በመጠጥ ከተሰለጠነ በኋላ፥ እንዲህ ያለው ወቅት በሚሞላበት ከንቱ ወሬና ስም በሌላቸው ሞኝነቶች ሁሉ በኋላ፥ በጸሎት በመደምደም ሊቀድሱትና በእግዚአብሔር ላይ ሊያላክኩት መሞከራቸው ነው። የፈለጋችሁትን ተናገሩ፤ የዳንስ ድግስን፥ ወይም ቲያትርን፥ ወይም የካርታ ጨዋታ ስብሰባን በጸሎት መዝጋት ከዚህ የበለጠ ሞኝነት ወይም አለመስማማት ወይም ርኩሰት አይሆንም።
የዓለምን መዳን እንመኛለን የሚሉ ሃይማኖተኛ ነን ባዮች፥ ወንጌልን እንዲልኩ፥ መጻሕፍት ቅዱሳትን፥ ትራክቶችንና ሚስዮናውያንን እንዲያቀርቡ፥ ዓለምንም ከሞት እንዲያድኑ ከአራቱ የሰማይ ነፋሳት እንዲህ ያለ ጥሪ ሲቀርብላቸው፥ በአንድ ምሽት በመቶ የሚቈጠሩ ዶላሮችን አውጥተው ከዚያም ወደ ወርሃዊው የጸሎት ስብሰባ ሄደው ስለ አሕዛብ ይጸልዩ ዘንድ ነገሩ እዚህ ደርሶአልን!
በአንዳንድ ሁኔታዎች አገልጋያቸው በግብዣዎቻቸው ላይ ስለሚገኝ ለሕሊናቸው መጽናኛ እንደሚያገኙ ተነግሮኛል። ይህ በእርግጥ ለእንዲህ ያለው ምሳሌ ክብደት ይሰጠዋል፤ አንድ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚል ግብዣ አድርጎ አገልጋዩን ከጋበዘ ሌሎችም እንዲሁ ማድረግ አለባቸው። የሚወስዱት ቀጣዩ እርምጃ ደግሞ እያንዳንዳቸው የዳንስ ድግስ አዘጋጅተው አገልጋያቸውን አስተባባሪ አድርገው መሾም ሊሆን ይችላል! ለምን አይሆንም? ምናልባትም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ክራር እንዲጫወትላቸው ውለታ ይውልላቸው ይሆናል። በእኔ ግምት ሄዶ እንዲህ ያለውን ግብዣ በጸሎት ከመዝጋት ይህን ቢያደርግ ልዩነት የለውም።
በሮቼስተር—በዚያ በጌታ እጅግ በተባረከው ስፍራ—የግብዣዎች ዙር እንደ ተካሄደ በኀዘን ሰምቻለሁ፤ እስከ ምን ድረስ እንደ ሆነ ግን አላውቅም። በማን ተጽዕኖ እንደ ተዘጋጁ፥ ወይም በየትኞቹ ሰዎች እንደ ተደገፉና እንደ ተገኙባቸው አላውቅም። ነገር ግን የግብዣዎችን ዙር ለማድረግ ያቀደ ማንኛውም ጉባኤ በዚያው ጊዜ አገልጋዩን እንዲያሰናብተው እመክራለሁ፤ ሕዝቡ ቃሉን ለመቀበልና ለመጠቀም ዝግጁ ወደ ሆነበት ስፍራ ሄዶ ይስበክ፤ እነርሱ በልባቸውም በእጃቸውም በዲያብሎስ አገልግሎት ተጠምደው ሳሉ በመካከላቸው ሃይማኖትን ለማስፋፋት ሲሞክር እንዲጨነቅ፥ እንዲያዝንና እንዲገደል በዚያ እንዲቆይ አያድርጉት።
ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ሰዎች አስቀድመው ከአገልጋያቸው ጋር ሳይመካከሩና የልዩ ጸሎት ጉዳይ ሳያደርጉት የሕዝብን ትኩረት ከሃይማኖት ሊያዘናጋ የሚችልን ማንኛውንም ነገር ከቶ ማዘጋጀት የለባቸውም። ይህን ውጤት እንደሚያስከትል ካወቁ ደግሞ ፈጽሞ ሊያደርጉት አይገባም። ይህን ዝንባሌ ያላቸው ጉዳዮች ብዙ ጊዜ በሕዝብ ፊት ይቀርባሉ፤ ለምሳሌ ተከታታይ ንግግሮች፥ ወይም ትርዒት፥ ወይም እንዲህ ያለ ነገር። ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ጥበበኞች ሊሆኑና የሚያደርጉትን ሊያስተውሉ ይገባቸዋል፤ የሚያመጣውን ተጽዕኖና መነቃቃትን ያደናቅፍ እንደ ሆነ እስኪያዩ ድረስ ለእንዲህ ያለው ነገር ድጋፍ መስጠት የለባቸውም። ያን የሚያደርግ ከሆነ ምንም አይነካካቸው። እንዲህ ያለው ነገር ሁሉ በክርስቶስ መንግሥት ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ መመዘን አለበት።
ግብዣዎችን በተመለከተ ንጹሕ መዝናኛ ናቸው ብላችሁ የፈለጋችሁትን ተናገሩ፤ እኔ ግን በእነርሱ ላይ የተገኛችሁትን ማንኛችሁንም እጠይቃለሁ፤ ለጸሎት ያዘጋጁአችኋልን? መንፈሳዊነታችሁንስ ይጨምራሉን? ወይስ ኃጢአተኞች በእነርሱ ውስጥ ተለውጠው ያውቃሉን? ወይስ ክርስቲያኖች ስለ ነፍሳት በጸሎት እንዲቃትቱ ተደርገው ያውቃሉን?
II. አብያተ ክርስቲያናት መነቃቃትን ለማስፋፋትና አገልጋያቸውን ለመርዳት ቢፈልጉ ሊያደርጓቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮችን እጠቅሳለሁ።
1. ለምድራዊ ፍላጎቶቹ ትኩረት መስጠት አለባቸው። ራሱን ሙሉ በሙሉ ለሥራው የሰጠ አገልጋይ በዓለማዊ ሥራ ሊሰማራ አይችልም፤ ስለዚህም ቤተ ሰቡን መደገፍን ጨምሮ ለምድራዊ ፍላጎቶቹ ሙሉ በሙሉ በሕዝቡ ላይ ጥገኛ ነው። ይህን ሁላችሁ በሚገባ ስለምታውቁት እዚህ መከራከር አያስፈልገኝም። «ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል።» ይህ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው። አሁን ግን ዙሪያችሁን ተመልከቱ፥ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ጉዳይ እንዴት እንደሚያደርጉም እዩ። ለምሳሌ አገልጋይ ሲፈልጉ በምን ያህል ርካሽ ሊያገኙት እንደሚችሉ ያሰላሉ። ጨዉ ምን ያህል እንደሚያስወጣው፥ ዱቄቱም ምን ያህል እንደሚያስወጣው እስከ መጨረሻዋ ሳንቲም ድረስ ያሰላሉ፤ ከዚያም ደመወዙን በጣም ዝቅ አድርገው ስለሚወስኑ ኑሮውን ለመግፋትና ቤተ ሰቡን ለማስተዳደር ከፍተኛ ችግር ላይ ይወድቃል። አገልጋይ በውጤት ለማጥናትና ለመሥራት አእምሮው የተረጋጋ መሆን አለበት፤ ዋጋ በማስቀነስ፥ በመከራከርና የሚያስፈልገውን በርካሽ ለመግዛት የተሻለ አጋጣሚ በመፈለግ ሊጠመድ አይችልም። ይህን ለማድረግ ቢገደድ አእምሮው ይታወካል። ሐሳቡ ከእነርሱ እንዲላቀቅ ምድራዊ ፍላጎቶቹ ካልተሟሉለት ተግባሩን እንዴት ሊፈጽም ይችላል?
2. ከአገልጋያችሁ ጋር ታማኞች ሁኑ።
በምን ያህል ጨውና በምን ያህል ቁና እህል ሊኖር እንደሚችል አትስፈሩና አታስሉ። የምትገናኙት ከክርስቶስ ጋር መሆኑን አስታውሱ። እርሱም አገልጋዮቹን በተለመደው ጥንቃቄ ብቻ ምድራዊ ችግር ፈጽሞ እንዳይደርስባቸው በሆነ ሁኔታ እንድታኖሩአቸው ይጠራችኋል።
3. ለእርሱ በሰዓቱ ክፈሉ።
አንዳንድ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ ሊሾሙ ሲሉ ደመወዝ በመስጠት ረገድ ታላቅ ኩራት ያሳያሉ፤ የመዋጮ ዝርዝርም አዘጋጅተው ፈጽሞ የማይከፍሉትን፥ ምናልባትም ሊከፍሉት ያላሰቡትን መጠን ያስመዘግባሉ። በዚህም ከአንድ፥ ከሁለት፥ ከሦስት ወይም ከአራት ዓመት በኋላ ማኅበሩ የአገልጋዩን ሦስት ወይም አራት መቶ ዶላር ውዝፍ ይይዛል፤ ከዚያም እርሱ ይተውልናል ብለው ይጠብቃሉ። በዚህ ሁሉ ጊዜም መነቃቃት ለምን እንደሌለ ይደነቃሉ! ምክንያቱ ራሱ ይህ ሊሆን ይችላል፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዋሽታለችና፤ ይህን ያህል ለመክፈል በታማኝነት ቃል ገብተው አላደረጉትም። እግዚአብሔር በእንዲህ ያለች ቤተ ክርስቲያን ላይ መንፈሱን ማፍሰስ ከባሕርዩ ጋር አይስማማም።
4. ሳይጠይቃችሁ ደመወዙን ክፈሉት።
ለአገልጋይ ደመወዙን ለማግኘት ሕዝቡን ደጋግሞ ለመጠየቅ እንደ መገደድ የሚያሳፍረው ብዙ ጊዜ ምንም ነገር የለም። ገንዘቡን ለማግኘት ደጋግሞ ደጋግሞ ለመጠየቅ በመገደዱ፥ ከዚያም እንደ ገቡለት ቃል ባለማግኘቱ ብዙ ጊዜ ጠላቶችን ያፈራል፥ ሰዎችንም ያስቀይማል። ክብራቸው አደጋ ላይ ቢሆን ኖሮ በከፈሉት ነበር፤ የሚጠየቀው ግን ሕሊና እና የእግዚአብሔር በረከት ብቻ ሲሆን ይተዉታል። ከእነርሱ አንዱ በባንክ የሚከፈል የዕዳ ሰነድ ቢኖረው ከቀኑ ሦስት ሰዓት በፊት በስፍራው ለመገኘት ጠንቃቃና ፈጣን ሆኖ ታዩት ነበር። ይህ ሰነዱ ተቃውሞ ስለሚመዘገብበትና ስማቸውን ስለሚያጡ ነው። አገልጋዩ ግን ለደመወዙ እንደማይከሳቸው ያውቃሉ፤ ስለዚህ ቸል ብለው ይተዉታል፤ እርሱም ችግሩን መሸከም ግድ ይሆንበታል። ይህ በከተማ ውስጥ እንደ ገጠር የተለመደ አይደለም። በገጠር ግን የሚገባውን ነገር በመከልከል በጉባኤዎች ቸልተኝነትና ጭካኔ የተነሣ የደረሱ ልብ የሚሰብሩ የጭንቀትና የመከራ ሁኔታዎችን አውቃለሁ። አብያተ ክርስቲያናት በልማዳዊ ውሸትና ማጭበርበር ይኖራሉ፤ ከዚያም መነቃቃት ለምን እንደሌላቸው ይደነቃሉ። እንዴት ሊደነቁ ይችላሉ?
5. ስለ አገልጋያችሁ ጸልዩ።
በዚህ አንድ ነገር ማለቴ ነው። ምን ማለቴ ይመስላችኋል? ሐዋርያት እንኳ አብያተ ክርስቲያናትን ስለ እነርሱ እንዲጸልዩ ያሳስቡ ነበር። ይህ ከምታስቡት በላይ አስፈላጊ ነው። አገልጋዮች ሰዎች ስለ እነርሱ እንዲጸልዩ የሚጠይቁት እንደ ተራ ሰዎች ብቻ አይደለም፤ ወይም የግል ደስታቸውን ለማሳደግ ብቻ በመንፈስ ተጽዕኖ ብዛት እንዲሞሉ አይደለም። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በአገልጋይ ድካም ላይ በረከትን አጥብቃ ካልተመኘች እርሱ በረከቱን መጠበቁ እግዚአብሔርን መፈታተን እንደ ሆነ ያውቃሉ። አገልጋይ ስንት ጊዜ ልቡ ለእግዚአብሔር በረከት ሊሰበር እንደ ደረሰ እየተሰማው ወደ መድረኩ ይወጣል፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደምትመኘው የሚያምንበት ምክንያት ስለሌለ በረከቱን የሚጠብቅበት ስፍራ እንደሌለ ይሰማዋል! ምናልባት ሁለት ሰዓት በጉልበቱ ሆኖ ሲማልድ ቆይቶ ይሆናል፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ በረከትን ስለማትመኝ ቃሎቹ ተመልሰው ፊቱን የሚመቱ ያህል ይሰማዋል።
አገልጋዩ ወደ መድረኩ ሲወጣ አእምሮው በደመና እንዳይሸፈን፥ ወይም ልቡ እንዳይቀዘቅዝ፥ ወይም ቅባት እንዳይጎድለውና በረከቱ እንዳይመጣ በመፍራት በጭንቅ የሚሆኑ ክርስቲያኖችን አይቻለሁ። እንዲህ ካለ አንድ ሰው ጋር አብሬ ሠርቻለሁ። እግዚአብሔር በስብከቴ ከእኔ ጋር እንደሚሆን በአእምሮው ማረጋገጫ እስኪያገኝ ድረስ ይጸልይ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜም እስኪታመም ድረስ ይጸልይ ነበር። ሕዝቡ እየተሰበሰቡ ሳለ ለጊዜው በጨለማ ውስጥ ሆኖ፥ አእምሮውም በጭንቀት ተሞልቶ፥ ደጋግሞ ለመጸለይ የሚሄድበት ጊዜ አውቃለሁ፤ በመጨረሻም በተረጋጋ ፊት ወደ ክፍሉ ገብቶ «ጌታ መጥቶአል፥ ከእኛም ጋር ይሆናል» ይል ነበር። ተሳስቶ ያገኘሁበትም ጊዜ እንዳለ አላውቅም።
አንዲት ቤተ ክርስቲያን አገልጋያቸውን ከቀን ወደ ቀን በጸሎት በክንዶቻቸው ሲሸከሙትና በድካሙ መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ጋር እንዲሆን በማይነገር ጭንቀት ሲተጉ አውቃለሁ! እንዲህ ሲሰማቸውና እንዲህ ሲጸልዩ፥ ኦ፥ በጉባኤው ውስጥ እንዴት ያሉ ስሜቶችና እንዴት ያሉ ፊቶች ይገለጣሉ! ቃሉ በኃይል እንዲመጣና እንዲሠራ በማይነገር ጭንቀት ተመኝተዋል፤ ጸሎታቸው እንደ ተመለሰ ሲያዩ፥ አንድ ቃል ወይም አንድ ዓረፍተ ነገር ከልብ በሙቀት ወጥቶ በሕዝቡ መካከል ሲሠራ ሲሰሙ፥ ነፍሳቸው ሁሉ በዓይኖቻቸው ውስጥ ስትመለከት ታያላችሁ። ቤተ ክርስቲያን አገልጋዩ ስለሚጸልይ እነርሱ መጸለይ አያስፈልጋቸውም ብለው በሚያስቡበት ስፍራ ግን ሁኔታው እንዴት የተለየ ነው! ተሳስተዋል። ቤተ ክርስቲያን በረከትን መመኘትና ስለ እርሱ መጸለይ አለባት። እግዚአብሔር በእስራኤል ቤት እንዲለመን ይናገራል። ለዚህ ምትክ ሊኖር እንደማይችል እንዲሰማችሁ እወዳለሁ።
በመነቃቃቶች ውስጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ በጸሎት ረገድ ወደ ኋላ ተገፍታ፥ ከሌላ ስፍራ የመጡ ሰዎች በስብሰባዎቹ ሁሉ እንዲጸልዩ የተጠሩባቸውን ሁኔታዎች አይቻለሁ። መነቃቃት ቢኖር እንኳ ይህ ሁልጊዜ አሳዛኝ ነው፤ መነቃቃቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ባለው ተጽዕኖ ያነሰ ኃይልና ያነሰ ጥቅም ይኖረዋልና። ከሌላ ስፍራ የመጡትን ሳይሆን የዚያን ስፍራ ቤተ ክርስቲያን አባላት ለጸሎት ደጋግሜ በመጥራቴ ከሌላ ስፍራ የመጡ ክርስቲያኖችንና አገልጋዮችን አንዳንድ ጊዜ አስቀይሜ ይሆናል። ይህም ለእነርሱ ካለኝ ንቀት አልነበረም፤ ዋናው ጉዳይ የሚመለከታት ያቺ ቤተ ክርስቲያን በረከትን እንድትመኝ፥ እንድትጸልይና እንድትቃትት ማድረግ አላማው ስለ ነበረ ነው።
በአንድ ስፍራ የተራዘመ ስብሰባ ተካሂዶ ምንም መልካም ውጤት አላመጣም፤ ይልቁንም ታላቅ ክፋት አስከተለ። ምክንያቱን እንድመረምር ተመራሁ። እንዲህም ሆኖ ተገኘ፤ በስብሰባዎቻቸው ሁሉ ከራሳቸው ቤተ ክርስቲያን አንድም አባል እንዲጸልይ አልተጠራም፤ ጸሎቶቹ ሁሉ ከሌላ ስፍራ በመጡ ሰዎች ተደርገው ነበር። ምንም መልካም ነገር ባይሠራ አያስደንቅም። ቤተ ክርስቲያኒቱ ግድ አልነበራትም። የስብሰባው መሪ በጎ አስቦ ነበር፤ ነገር ግን በዚያ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ወደ ሥራው ሳያስገባ መነቃቃትን ለማስፋፋት ሞከረ። ሰነፍ ቤተ ክርስቲያን ምንም ሳታደርግ ዝም ብላ እንድትተኛ ተዋት፤ ስለዚህም ምንም መልካም ነገር ሊሆን አልቻለም።
አብያተ ክርስቲያናት ኃጢአተኞችን በእውነት ቃል የሚሰብሩ ፈጻሚዎች እንደ መሆናቸው ስለ አገልጋዮች መጸለይ አለባቸው። ስለ አገልጋይ የሚቀርብ ጸሎት ብዙ ጊዜ በተለመደና በደረቀ ሥርዓት ይደረጋል፤ በጸሎት ስብሰባዎችም ብቻ ይወሰናል። ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት በአሮጌው መንገድ ጸሎታቸውን ይደግማሉ፤ «ጌታ ሆይ፥ በዚህ በጽዮን ቅጥር ክፍል ላይ ያቆምከውን አገልጋይህን ባርከው» ይላሉ፤ ወዘተ፤ ልብ ስለሌለበትም ምንም አይጠቅምም። ማስረጃውም ብዙ ጊዜ ስለ እርሱ በስውር ለመጸለይ ፈጽሞ አለማሰባቸው፥ በድካሙ ላይ በረከት እንዲወርድ በጸሎት ክፍላቸው ከቶ አለመቃተታቸው ነው። በስብሰባዎቻቸው ውስጥ ፈጽሞ አይተዉት ይሆናል። ያንንም ቢተዉ ስለ አገልጋያቸው ድካም እጅግ ጥቂት ብቻ ግድ እንደሚላቸው ግልጽ ነው። ነገር ግን ያ ዋናው ስፍራ አይደለም። ስለ አገልጋያችሁ የሚሠራ ጸሎት የምታቀርቡበት መንገድ ጉዳዩን ወደ ጸሎት ክፍላችሁ መውሰድ ነው፤ በስውርም ሳላችሁ ድካሙ እንዲሳካ ከእግዚአብሔር ጋር ታገሉ።
በሕመም ላይ የነበረ አንድ አገልጋይ አውቃለሁ፤ ተስፋ ቈርጦ በአእምሮው ተዋረደ፥ እጅግም በጨለማ ውስጥ ሆነ፤ ከዚህም የተነሣ ከእንግዲህ መስበክ የሚችል መስሎ አልተሰማውም። ከቤተ ክርስቲያኒቱ አንድ ሰው ለአገልጋዩ ሁኔታ እንዲያዝንና በስብከቱ መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ጋር እንዲሆን እንዲጸልይ ተነቃቃ። በአንድ የሰንበት ጠዋት የዚህ ሰው አእምሮ እጅግ ተጨነቀ፤ ገና ሲነጋም መጸለይ ጀመረ፤ በዚያን ቀን በረከት እንዲመጣም ደጋግሞ ጸለየ። ጌታም በሆነ መንገድ አገልጋዩን ጸሎቱ በሚሰማበት ስፍራ መራው። ሰውየው ስለ አገልጋዩ ሁኔታና ስለ አእምሮው ሁኔታ ያሰበውን ልክ ለጌታ እየነገረ፥ እንቢ እንደማይባል ሰው ሆኖ በረከትን ይማልድ ነበር። አገልጋዩ ወደ መድረኩ ወጥቶ ሰበከ፤ ብርሃንም በላዩ በራ፥ ቃሉም በኃይል ሆነ፤ በዚያው ቀን መነቃቃት ጀመረ።
6. አገልጋይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሊደገፍ፥ ኑሮውም ከኃጢአተኞች ነጻ በሆነ መንገድ ሊረጋገጥለት ይገባል። አለዚያ ቤተ ሰቡን በራብ ለመቅጣት፥ ወይም ኃጢአተኞችን እንዳያስቀይም የእውነትን ክፍል ለመደበቅ ይገደድ ይሆናል። እውነትን ሙሉ በሙሉ ለመግለጥ እንደሚፈራ ያገኘሁትን አንድ አገልጋይ በአንድ ወቅት ገሠጽሁት። በአንዳንድ ነጥቦች ላይ አጥብቆ አለመናገሩ እንዳስደነቀኝ ነገርሁት። እርሱም በዚያ ነጥብ የሚነኩ አንዳንድ ሰዎችን ማስደሰት ግድ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ነገረኝ። በዋናነት ይደግፉት የነበሩት ኃጢአተኞቹ ነበሩ፤ ይህም ጥገኛና አድርባይ አደረገው። ሆኖም ምናልባት አገልጋያቸውን ለእንጀራው በኃጢአተኞች ላይ ጥገኛ አድርጋ የተወችው ያቺው ቤተ ክርስቲያን በእምነት ማጣቱና ሰውን በመፍራቱ ዞራ ትሰድበው ይሆናል። ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ አገልጋይዋን እንዲህ ልትለው ይገባል፤ «እኛ እንደግፍሃለን፤ ወደ ሥራ ሂድ፤ እውነትን በሕዝቡ ላይ አዝንበው፤ እኛም ከጎንህ እንቆማለን።»
7. ሰዎች በስብሰባ ውስጥ ተመችቶአቸው እንዲቀመጡ ሁሉም ነገር መዘጋጀቱን አረጋግጡ። ሰዎች ተመችቶአቸው ካልተቀመጡ ትኩረታቸውን መሳብም ሆነ መያዝ አስቸጋሪ ነው። በትኩረት ካልሰሙ ደግሞ ሊለወጡ አይችሉም። የመጡት ስለ ሕይወታቸው ሊሰሙ ነው፤ በነፍሳቸው ሁሉ ሊሰሙ በሚችሉበትና በአካል አቀማመጣቸው ትኩረታቸውን የሚስብ ምንም ነገር በሌለበት ሁኔታ ሊቀመጡ ይገባቸዋል። የመሰብሰቢያው ስፍራ ምቹ እንዲሆን ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደ ሆነ አብያተ ክርስቲያናት አይገነዘቡም። ያጌጠ ማለቴ አይደለም። የውድ ባለ ብዙ መብራት ቀንዲሎቻችሁ፥ የውድ ምንጣፎቻችሁና የግሩም መድረኮቻችሁ ብልጭልጭና ክብር ሁሉ ሌላው ጽንፍ ነው፤ ትኩረትንም እንዲሁ ክፉኛ ይወስዳል፤ ኃጢአተኛ ወደ ስብሰባ የሚመጣበትንም ዓላማ ሁሉ ያከሽፋል። በዚያ መነቃቃትን መጠበቅ አያስፈልጋችሁም።
8. የእግዚአብሔር ቤት ንጹሕ ሆኖ እንዲጠበቅ አረጋግጡ። የእግዚአብሔር ቤት የራሳችሁ ቤት እንዲጠበቅ የምትፈልጉትን ያህል ንጹሕ ሆኖ መጠበቅ አለበት። አብያተ ክርስቲያናት ብዙ ጊዜ ከመጠን በላይ ቆሽሸው ይኖራሉ። ሰዎች ብዙ ትንባሆ የሚጠቀሙባቸውንና ስለ ንጽሕና እጅግ ጥቂት ግድ የሚላቸውን አብያተ ክርስቲያናት አይቻለሁ፤ በዚያም በምቾት መስበክ የማይቻል ነበር። በአንድ ወቅት በተራዘመ ስብሰባ ጉዳዩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ተከሰሰ፤ እነርሱም ለሚስዮን ሥራ ከሚሰጡት ይልቅ ለትንባሆ ብዙ ገንዘብ እንደሚከፍሉ ማመን ግድ ሆነባቸው። ቤቱ እጅግ ቆሻሻ ስለ ነበረና የትንባሆ ፈሳሽ በወለሉ ላይ ሁሉ ስለሚፈስስ፥ በመቀመጫዎቻቸው መንበርከክ አልቻሉም፤ ሴቶችም ሁልጊዜ ልብሳቸውን ሳይጠብቁ መቀመጥ አልቻሉም፤ የሚረግጡበትንም መጠንቀቅ ነበረባቸው። ሰዎች በሚያስጸይፍ እይታና ሽታ ሳይረበሹ ሊሰሙበትና በጸሎት ሊንበረከኩበት ወደሚችሉበት ስፍራ መሄድ ካልቻሉ የተራዘመ ስብሰባ ምን ይጠቅማል? በእነዚህ ነገሮች ውስጥ ያልተገነዘበ አስፈላጊነት አለ። ያንን ሰው እዩ! ምን እያደረገ ነው? እኔ ስለ ዘላለም ሕይወት እሰብክለታለሁ፤ እርሱ ግን ስለ ቆሻሻው መቀመጫ ያስባል። ያቺ ሴትም እግሮቿን ከትንባሆ ፈሳሽ ለማራቅ የእግር ማሳረፊያ ትጠይቃለች። ነውር ነው!
9. ቤቱ በልኩ ሞቃት እንጂ ከመጠን በላይ ሞቃት እንዳይሆን አስፈላጊ ነው። አንድ አገልጋይ ወደ አንድ ቤት ገብቶ ቀዝቃዛ ሆኖ አገኘው እንበል፤ እንደ ገባ ወዲያው ቤቱ ቢቀመጥ ይሻለው እንደ ነበር ያያል፤ ሕዝቡ ይንቀጠቀጣሉ፥ እግሮቻቸው ቀዝቅዘዋል፥ ጉንፋን የሚይዛቸው ይመስላቸዋል፥ አይመቻቸውም፤ እርሱም ምንም ሊያደርግ እንደማይችል ስለሚያውቅ ቤቱ ቢሆን ይመኛል፤ ነገር ግን መስበክ አለበት፤ አለዚያ ያዝናሉ።
ወይም ቤቱን ከመጠን በላይ ሞቃት ሆኖ ያገኘው ይሆናል፤ ሕዝቡም እውነትን ከመስማት ይልቅ ራሳቸውን ያራግባሉ፥ ትንፋሽ ያጥራቸዋል፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንዲት ሴት ራስዋን ስታ ትወድቃለች፥ ሁካታም ትፈጥራለች፤ የሐሳብና የስሜት ሰንሰለቱ ሁሉ ይጠፋል፤ በዚህም አንድ ስብከት ሙሉ ያለ ጥቅም ይባክናል። እነዚህ ጥቃቅን ነገሮች የሰዎችን ትኩረት ከዘላለም ሕይወት ቃሎች ይወስዳሉ። ብዙ ጊዜም በክርክሩ ሰንሰለት ውስጥ አንዲት ቀለበት ብትጥሉ ሁሉን ታጣላችሁ፤ ሕዝቡም ይፈረድባቸዋል፤ ይህም ቸልተኛዋ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ጥቃቅን ጉዳዮች በአግባቡ ስለማታስተካክል ብቻ ነው።
10. ቤቱ በሚገባ አየር የሚገባበት መሆን አለበት። ከቤቶች ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ፍጹም በሆነ ሁኔታ አየር የሚገባባት መሆን አለባት። አየሩ ካልተለወጠ በብዙ ሳንባዎች ውስጥ ስለሚያልፍ ይበላሻል፥ ሕይወት ሰጪነቱም ያልቃል፤ ሕዝቡም ለምን እንደ ሆነ ሳያውቁ ትንፋሽ ያጥራቸዋል፥ ሊቋቋሙት የማይቻል የእንቅልፍ ፍላጎትም ይሰማቸዋል፤ አገልጋዩም በከንቱ ይሰብካል። ስብከቱ ይጠፋል፥ ከመጥፋትም የከፋ ይሆናል። ይህ ጉዳይ እጅግ ጥቂት መታሰቡ ብዙ ጊዜ አስደንቆኛል። ሕዝቡ በአየር እጦት ሊሞቱ ጥቂት ሲቀራቸው፥ አገልጋዩም ክፍሉ አየሩ እንደ ተመጠጠ ዕቃ በሆነበት ስፍራ በመስበክ ጉልበቱን ሲያባክን፥ ሽማግሌዎችና ባለ አደራዎች ስብከቱን ሙሉ ተቀምጠው ይሰማሉ፤ ነገሩን ለማስተካከል አንዳች ለማድረግ ከቶ ሳያስቡ በዚያው ይቀመጣሉ። ይህ በትክክል እንዲስተካከል፥ ቤቱ በልኩ ሞቃት እንዲሆንና አየሩ ንጹሕ ሆኖ እንዲጠበቅ ኃላፊነቱን ራሳቸው ሊወስዱ ይገባቸዋል። አገልጋዩ በተሻለ ውጤት እንዲደክም፥ ሕዝቡም ነፍሳቸውን ለሚያድነው እውነት ያልተከፋፈለ ትኩረታቸውን እንዲሰጡ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ጉዳይ ንቁ መሆንዋ ምንኛ አስፈላጊ ነው።
ነገሮች ሲበላሹ ሁሉንም በቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ላይ ማላከክ በጣም የተለመደ ነው። ይህ እንዲህ አይደለም። ብዙ ጊዜ ጠባቂው ተጠያቂ አይደለም። ቤቱ ቀዝቃዛና የማይመች ከሆነ ብዙ ጊዜ ማገዶው ጥሩ ስላልሆነ፥ ወይም ምድጃዎቹ ተስማሚ ስላልሆኑ፥ ወይም ቤቱ እጅግ ክፍት ስለ ሆነ ሊሞቅ ስለማይችል ነው። ከመጠን በላይ ሞቃት ከሆነ ደግሞ ምናልባት እርሱ በሌለበት ሰዓት አንድ ሰው ጣልቃ ገብቶ ያለ ማስተዋል ማገዶ ከምሮበት ይሆናል። ወይም ጠባቂው ጥፋተኛ ከሆነ ምናልባት ቤተ ክርስቲያኒቱ ለአገልግሎቱ በቂ ክፍያ ስለማትከፍለው፥ ቤቱን በሥርዓት ለመጠበቅ የሚያስፈልገውን ትኩረት መስጠት ስለማይችል ይሆናል። አብያተ ክርስቲያናት አንዳንድ ጊዜ የጠባቂውን ደመወዝ እስከ ዝቅተኛው ደረጃ ስለሚያወርዱት ሥራውን ቸል ለማለት ይገደዳል። ወይም በርካሽ ለማግኘት ብለው ብቃት የሌለውን ይመርጣሉ፤ ከዚያም ሥራው አይሠራም። ጥፋቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ነው። ለሥራው በቂ ክፍያ ይስጡ፤ ሥራውም ይሠራል፥ በታማኝነትም ይሠራል። አንዱ ጠባቂ በትክክል ባይሠራ ሌላው ይሠራል፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም በትክክል መሠራቱን የማረጋገጥ ግዴታ አለባት፤ አለዚያ አገልጋያቸውን ያሰናብቱት፤ ሌሎቹን ነገሮች ድካሙ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ በተዘበራረቀ ሁኔታ እያቆዩ እርሱን አያቆዩት። እንዴት ያለ ቁጠባ ነው! የአገልጋዩን ደመወዝ ይከፍላሉ፤ ከዚያም በጠባቂው ደመወዝ ላይ በሚጨመር ሃምሳ ዶላር እጦት ሁሉም ነገር እጅግ ስለሚዘበራረቅ የአገልጋዩ ድካም ሁሉ ይጠፋል፥ ነፍሳት ይጠፋሉ፥ ልጆቻችሁና ጎረቤቶቻችሁም ወደ ገሃነም ይወርዳሉ!
አንዳንድ ጊዜ ይህ ቆሻሻነት፥ ቸልተኝነትና ዝብርቅርቅ በአገልጋዩ ላይ የሚቈጠር ነው። ምናልባት እርሱ ራሱ ትንባሆ ይጠቀማል፥ የእግዚአብሔርንም ቤት የማርከስ ምሳሌ ይሆናል። ምናልባት መድረኩ ከቤቱ ሁሉ እጅግ የቆሸሸው ስፍራ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሊቆሙባቸው የማይገባ እጅግ አስጸያፊ በሆኑ መድረኮች ላይ ቆሜአለሁ። አገልጋይ ከዚህ የበለጠ ቅድስናና ጨዋነት ከሌለው በጉባኤው ውስጥ ነገሮች ቢዘበራረቁ አያስደንቅም። በአብዛኛውም እንዲሁ ነው።
11. ሰዎች ውሾቻቸውንና በጣም ትንንሽ ልጆቻቸውን ቤት ሊተዉ ይገባቸዋል። በአገልግሎቱ ውስጥ የስብሰባውን ውጤት በከፍተኛ ደረጃ በሚያጠፋው በዚያው ወቅት ውሾች ሲጣሉና ልጆች ሲያለቅሱ ብዙ ጊዜ አውቃለሁ። ልጆች ተገኝተው ቢያለቅሱ ወዲያውኑ መወሰድ አለባቸው። የልጁ ለቅሶ የጉባኤውን ሁሉ ትኩረት እየሳበ ሳለ እናት ወይም ሞግዚት ተቀምጣ ልጁን ስታወዛውዝ አንዳንድ ጊዜ አውቃለሁ። ይህ ጭካኔ ነው። ውሾችን በተመለከተ ደግሞ ትኩረትን ከእግዚአብሔር ቃል ከሚያዘናጉ ቢሞቱ እጅግ በጣም ይሻላል። ያንን ዲያቆን እዩ፤ ምናልባት ውሻው በዚህ መንገድ ዲያቆኑ ለማዳን መሣሪያ ሊሆን ከሚችለው የበለጡ ነፍሳትን አጥፍቶ ይሆናል።
12. የቤተ ክርስቲያን አባላት ከቤት ወደ ቤት በመጎብኘትና ነፍሳትን ለማዳን በመሞከር አገልጋዩን መርዳት አለባቸው። ይህን ሁሉ ለአገልጋዩ አትተዉት። ጊዜውን ሁሉ ቢሰጥና ጥናቱንና የጸሎት ክፍሉን ቸል ቢል እንኳ ይህን ማድረግ አይቻለውም። የቤተ ክርስቲያን አባላት በዚህ ሥራ ጠቃሚዎች እንዲሆኑ ጥረት አድርገው ራሳቸውን ለዚህ ግዴታ ማብቃት አለባቸው።
13. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክፍሎችን ማካሄድ አለባቸው። ወጣቶችን ለማስተማር፥ በስብከቱ የነቁ ወይም የተነኩ ሰዎችም የሚቀበሉበትና የሚለወጡበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክፍሎችን የሚያካሂዱ ተስማሚ ሰዎች መመረጥ አለባቸው። ማንም እንደ ተነካ ሲታይ ወዲያውኑ በአግባቡ ወደሚያዙበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክፍል እንዲቀላቀል ይጋበዝ፤ ምናልባትም ይለወጣል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዚህ አገልግሎት ምርጥ ሰዎችን መምረጥ አለባት፤ ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክፍሎችን ለመሙላት ንቁዎች መሆን አለባቸው። ይህ በዚህ ጉባኤ ተደርጎአል፤ ሰዎች ልባቸው ሲነካ አንድ ሰው አይቶአቸው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክፍል እንዲቀላቀሉ መጋበዙ፥ እነርሱም መቀላቀላቸውና በዚያ መለወጣቸው በጣም የተለመደ ነገር ነው። በዚህ መንገድ ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ወይም ልናደርግ የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው ማለቴ አይደለም። እንዲህ ያሉትን ክፍሎች ለመምራት የሚችሉና ፈቃደኞች የሆኑ ተጨማሪ አስተማሪዎች ያስፈልጉናል።
14. አብያተ ክርስቲያናት የሰንበት ትምህርት ቤቶችን መደገፍ አለባቸው፤ በዚህም መንገድ አገልጋዮቻቸውን ነፍሳትን በማዳን መርዳት አለባቸው። አገልጋይ ይህንም እያከናወነ እንዴት ሊሰብክ ይችላል? ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ኃላፊነቶች፥ ጭንቀቶችና ድካሞች ካልተረከበች እርሱ ወይ ቸል ሊላቸው ወይ ሊደቀቅ ግድ ነው። ቤተ ክርስቲያን ፍጹም ንቁ ትሁን፤ ትጠብቅ፥ ልጆችንም ወደ ትምህርት ቤቱ ታምጣ፥ በታማኝነትም ታስተምራቸው፥ በትምህርት ቤቱም መነቃቃትን ለማስፋፋት ራስዋን ትስጥ።
15. የቤተ ክርስቲያንን አባላት መጠበቅ አለባቸው። እርስ በርሳቸው ለመነቃቃት፥ አንዱ የሌላውን መንፈሳዊ ሁኔታ ለማወቅና ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እርስ በርስ ለመነሣሣት መጎብኘት አለባቸው። አገልጋዩ ይህን ማድረግ አይችልም፤ ጊዜ የለውም፤ እያጠናና ስብከቶችን እያዘጋጀ በዚያው ጊዜ ወደ ፊት እንዲገፉ ለማድረግ እንደሚያስፈልገው እያንዳንዱን የቤተ ክርስቲያን አባል ደጋግሞ መጎብኘት አይቻለውም። ቤተ ክርስቲያን ይህን የማድረግ ግዴታ አለባት። አንዱ የሌላውን መንፈሳዊ ደኅንነት ለመጠበቅ በመሐላ ሥር ናቸው። ነገር ግን ይህ እንዴት ይደረጋል? ብዙዎቹ እርስ በርሳቸው አይተዋወቁም። እንደ እንግዶች ይገናኛሉ፥ ይተላለፋሉም፤ ስለ መንፈሳዊ ሁኔታቸውም ከቶ አይጠያየቁም። ስለ አንዱ ክፉ ነገር ከሰሙ ግን ሄደው ለሌሎች ይነግራሉ። ለበጎ ነገር እርስ በርሳቸው ከመጠባበቅ ይልቅ መሰናከላቸውን ይጠባበቃሉ። እርስ በርሳቸው እንኳ ሳይተዋወቁ ለበጎ እንዴት ሊጠባበቁ ይችላሉ?
16. ቤተ ክርስቲያን የስብከትን ውጤት መከታተል አለባት። ለተሰበከው ቃል መሳካት የሚጸልዩ ከሆኑ በእርግጥ ውጤቱን ይከታተላሉ። ንቁዎች ሊሆኑ ይገባቸዋል፤ በጉባኤው ውስጥ ማንም የእግዚአብሔር ቃል እንደ ያዘው ምልክት ሲያሳይ ሊከታተሉት ይገባቸዋል። የስሜት መገለጫ በታየበት ስፍራ ሁሉ እነዚያ ሰዎች ወዲያውኑ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፤ የተሰማቸው ስሜት እስኪጠፋም ድረስ መተው የለባቸውም። ሊያነጋግሩአቸው፥ ወይም እንዲጎበኙ ሊያደርጉ፥ ወይም ወደ የጭንቀት ስብሰባ፥ ወይም ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክፍል ሊያስገቡአቸው፥ ወይም ወደ አገልጋዩ ሊያመጡአቸው ይገባል። የቤተ ክርስቲያን አባላት ይህን ካላደረጉ ግዴታቸውን ቸል ይላሉ። ቢያደርጉት ግን ሊቈጠር የማይችል መልካም ነገር ሊሠሩ ይችላሉ።
እጅግ ቀዝቃዛና ክፉ በሆነ ስፍራ የምትኖር አንዲት በእግዚአብሔር የምትፈራ ወጣት ሴት ነበረች። የጸሎት መንፈስ የነበራት እርሷ ብቻ ነበረች፤ በቃሉም ላይ በረከት እንዲወርድ ስትጸልይ ቆይታ ነበር። በመጨረሻም በጉባኤው ውስጥ በስብከቱ የተነካ የሚመስል አንድ ሰው አየች፤ አገልጋዩም ከመድረኩ እንደ ወረደ ተረብሻና እየተንቀጠቀጠች ወደ ፊት መጥታ ሄዶ ያንን ሰው ወዲያውኑ እንዲያነጋግረው ለመነችው። እርሱም እንዲሁ አደረገ፤ ሰውየውም ብዙም ሳይቆይ ተለወጠ፤ መነቃቃትም ተከተለ። እንግዲህ ከእናንተ ደንታ ቢስ ሃይማኖተኛ ነን ባዮች አንዱ ያንን የነቃውን ሰው ባላየው ነበር፤ ስድስት የሚያህሉትንም ሳያስተውል ይሰናከልባቸውና ወደ ገሃነም እንዲሄዱ ይተዋቸው ነበር። ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ እያንዳንዱን ስብከት መከታተልና ጉባኤውን እንዴት እንደሚነካ ማየት አለባቸው። አንገታቸውን እየዘረጉ በቤቱ ውስጥ ዙሪያውን ማፍጠጥ አለባቸው ማለቴ አይደለም፤ ነገር ግን በተቻላቸው መጠን ሊያስተውሉ ይገባቸዋል፤ በስብከቱ የተነካ ሰው ካገኙም በመንገዱ ተገኝተው ወደ መድኃኒቱ ሊመሩት ይገባቸዋል።
17. ተጠንቀቁ፤ ስብከቱን ሁሉ ለሌሎች አትስጡ። ድርሻችሁን ካልወሰዳችሁ በራብ ትሞታላችሁ፥ እንደ መንፈሳዊ አጽሞችም ትሆናላችሁ። ክርስቲያኖች ድርሻቸውን ለራሳቸው መውሰድ አለባቸው። ቃሉ እነርሱን በጣም የሚመረምር ቢሆን በቅንነት በራሳቸው ላይ ሊተገብሩት፥ ከልባቸው ጋር ሊያስተያዩት፥ ሊፈጽሙትና በእርሱ ሊኖሩ ይገባቸዋል። አለዚያ ስብከት ለእነርሱ ምንም አይጠቅማቸውም።
18. አገልጋያችሁ መልካም ነገርን ለማድረግ ያቀደውን እንዲፈጽም ለመርዳት ዝግጁ ሁኑ። አገልጋዩ ለጥቅም የሚሆኑ ዕቅዶችን ለማውጣት ጥበበኛ ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያኒቱም ለመፈጸም ዝግጁ ስትሆን ሁሉን ማሸነፍ ይችላሉ። ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን በግድ እስኪጎተቱ ድረስ ከማንኛውም ተግባር ወደ ኋላ ስትል፥ ገንዘብ ስለሚያስወጣ እያንዳንዱን ሐሳብ ስትቃወም በአገልጋዩ ላይ የሞተ ሸክም ናት። ምድጃዎች ቢያስፈልጉ፥ ኧረ አይሆንም፥ ገንዘብ ያስወጣሉ ይላሉ። በጨለማ ከመስበክ ለመዳን መብራቶች ቢጠየቁ፥ ኧረ አይሆንም፥ ገንዘብ ያስወጣሉ ይላሉ። ስለዚህ በምሰሶዎቹ ላይ ሻማዎችን ይለጥፋሉ፥ ወይም የምሽት ስብሰባዎችን ፈጽሞ ይተዋሉ። ሻማዎችን ቢለጥፉ ብዙም ሳይቆይ ወይ ብርሃን አይሰጡም፥ ወይ አንድ ሰው እየዞረ ክሩን መቁረጥ አለበት። በዚህም ጉባኤው ሁሉ በሻማ ቈራጩ ይረበሻል፥ ትኩረታቸው ይወሰዳል፥ ስብከቱም ይጠፋል።
በአንድ ወቅት ቤቱ መብራት ስላልነበረው በተቸገርንበት የተራዘመ ስብሰባ ላይ ነበርሁ። ሕዝቡ መብራቶችን እንዲያመጡ አሳሰብኋቸው፤ እነርሱ ግን በጣም ውድ እንደሚሆን አሰቡ። ከዚያም እኔ ራሴ ላመጣቸው ሐሳብ አቀረብሁ፤ ላደርገውም ተቃርቤ ነበር፤ ነገር ግን እንደሚያስቀይም ስላወቅሁ ያለ መብራት ቀጠልን። በረከቱ ግን በብዛት አልመጣም። እንዴት ሊመጣ ይችላል? ቤተ ክርስቲያኒቱ ምን ያህል እንደሚያስወጣ እስከ መጨረሻዋ ሳንቲም በማስላት ጀመረች፤ ነፍሳትንም ከገሃነም ለማዳን ከዚያ አልፋ አልሄደችም።
እንዲሁም አገልጋይ ስብሰባ ሲጠራ እንዲህ ያሉ ሰዎች ገንዘብ ስለሚያስወጣ ሊያደርጉት አይችሉም። ምንም የማያስወጣቸውን ለጌታ ማቅረብ ከቻሉ ያደርጉታል። ምስኪን ረዳቶች ናቸው! እንዲህ ያለች ቤተ ክርስቲያን መነቃቃት ሊኖራት አይችልም። እንዲህ ያለች ቤተ ክርስቲያን ከመኖርዋ በአንገቱ ላይ የወፍጮ ድንጋይ ቢኖር ለአገልጋዩ ልዩነት የለውም። የተሻለ ነገር ሊያስተምራቸው ካልቻለ ትቶአቸው እንዲህ ወደማይታሰርበት ስፍራ ቢሄድ ይሻለዋል።
19. የቤተ ክርስቲያን አባላት በጸሎት ስብሰባዎች ላይ መገኘትን ግዴታቸው ሊያደርጉ ይገባል፤ ደግሞም በሰዓቱ ሊገኙ ይገባል። አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባላት በስብከት ላይ ሁልጊዜ ይገኛሉ፤ ምክንያቱም በዚያ ተቀምጦ ከመስማትና ከመደሰት በቀር የሚያደርጉት ነገር የለም፤ በጸሎት ስብሰባዎች ላይ ግን አንድ ነገር እንዲያደርጉ እንዳይጠየቁ ፈርተው አይገኙም። እንደነዚህ ያሉ አባላት የአገልጋዩን እጆች ያስራሉ፤ ልቡንም ያደክማሉ። አገልጋይን የሚቀጥሩት ለምንድን ነው? በስብከት እንዲያዝናናቸው ነውን? ወይስ እንዲፈጽሙት የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲያስተምራቸው ነው?
20. የቤተ ክርስቲያን አባላት ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሊያጠኑና ሊጠይቁ፥ ከዚያም ሊያደርጉት ይገባል። ክርስቲያኖች እንደ ወታደሮች ጭፍራ መሠልጠን አለባቸው። ለጥቅም እንዲበቁ ማሠልጠን፥ ማስተማርና መምራት፥ እጅግ የላቀውን የሞራል ተጽዕኖ በሚያስገኝ መንገድ ወደ ፊት መምራት የአገልጋይ ግዴታና ሹመት ነው። ከዚያም እነርሱ በስፍራቸው ጸንተው ግዴታቸውን መፈጸም አለባቸው፤ አለዚያ በትክክል መንገድ ላይ ቆመው እንቅፋት ይሆናሉ።
ያስታወስኳቸውና ልነካቸው ያሰብኳቸው ሌሎች ብዙ ነጥቦች አሉ፤ ነገር ግን ጊዜ የለም። ሊጠበቁ የሚገባቸውን ልዩ ልዩ ዝርዝሮች ብተነትን የዚህን መጽሐፍ ቅዱስ ያህል ትልቅ መጽሐፍ ልጽፍ እችል ነበር። ስለዚህ በሚከተሉት ጥቂት ማሳሰቢያዎች ልደምድም፤
ማሳሰቢያዎች።
1. የአገልጋይ ፍሬ ማጣት ሙሉ በሙሉ በሹመቱ አፈጻጸም የጥበብ ጉድለት ምክንያት ላይሆን እንደሚችል ታያላችሁ። ቸልተኛ ለሆኑ አገልጋዮች ልከራከርላቸው አይደለም። አገልጋዮችን ከግልጽ እውነት ፈጽሞ አላድናቸውም፤ ለሰዎችም የሽንገላ ማዕረግ አልሰጥም። ተወቃሾች ከሆኑ ይወቀሱ። ቃሉ ምንም ፍሬ ባያፈራ ምንም ጥርጥር የለውም፥ ሁልጊዜ በመጠኑም ቢሆን ተወቃሾች ናቸው። ነገር ግን ሁልጊዜ ዋነኞቹ ተወቃሾች እነርሱ ናቸው ማለት ከእውነት እጅግ የራቀ ነው። አንዳንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ከአገልጋዩ እጅግ የበለጠ ተወቃሽ ናት፤ ሐዋርያ ወይም ከሰማይ የመጣ መልአክ እንኳ ቢሰብክ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ መነቃቃትን ሊያመጣ አይችልም። ምናልባት ለአገልጋያቸው ታማኞች አይደሉም፥ ወይም ስስታሞች ናቸው፥ ወይም ስለ ሕዝባዊ አምልኮ ምቾት ግድ የላቸውም። ወዮ! ብዙ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ናቸው፤ በመቶ ዶላር እጦት ሁሉ ነገር የማይመችና የማያስደስት ይሆናል፥ የሰባኪውም ድካም ይጠፋል። እነርሱ ራሳቸው በተሸፈኑ ቤቶች ይኖራሉ፤ የእግዚአብሔርን ቤት ግን ፈርሶ ይተዉታል። ወይም ቤተ ክርስቲያን በኃጢአተኛ ኑሮዋ የስብከቱን ተጽዕኖ ሁሉ ታፈርሳለች። ወይም ምናልባት በዚህ ከተማ እንዳሉት እንደ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ግብዣዎቻቸውና ዓለማዊ ትርኢታቸው የወንጌልን ተጽዕኖ ያጠፋሉ።
2. አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይን ቀጥረው በሥራው ባይረዱት እጅግ በደለኞች እንደሆኑ ሊያስቡ ይገባል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ከክፉ መንገዳቸው እንዲመልስ ወደ እነርሱ መልእክተኛ ልኳል፤ እርሱም ቤተ ክርስቲያን ግዴታዋን ለመፈጸም እምቢ ስላለች በተላከበት ጉዳይ ይወድቃል። መልእክቱን ከማመስገንና ልመናውን ከመደገፍ፥ በሚገባው መንገድ ሁሉ እጆቹን ከፍ አድርጎ ከመያዝ ይልቅ በትክክል መንገድ ላይ ቆመው መልእክቱን ይቃወማሉ፥ ተጽዕኖውንም ያፈርሳሉ፤ ነፍሳትም ይጠፋሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ባሉ አብዛኞቹ ጉባኤዎች አገልጋዩ እጅግ ስለሚደናቀፍ፥ ሥራ በሌላትና በደነዘዘች ቤተ ክርስቲያን ራስ ላይ በላይ መስበክ ሲገባው፥ ስብከቱ ኃጢአተኞችን በመለወጥ ካለው ውጤት አንጻር ብዙውን ጊዜ በዚያ ከመሆን ይልቅ በውጭ አገር ተልእኮ ላይ ቢሆን ልዩነት እንደሌለው ምንም ጥርጥር የለውም።
ሆኖም እነዚሁ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋያቸው የተራዘመ ስብሰባ ለመሳተፍ ለጥቂት ቀናት እንዲሄድ አይፈቅዱም። «ልንለቀው አንችልም፤ ለምን አገልጋያችን ነው፤ አገልጋያችንም እዚህ እንዲሆን እንወዳለን» ይላሉ፤ በዚያው ጊዜ ግን የሚችለውን ሁሉ ያደናቅፋሉ። ቢችል ኖሮ ራሱን ነቅሎ አገልጋይ ወደሌለበትና ሕዝቡ ወንጌልን ለመቀበል ፈቃደኛ ወደሆነበት ስፍራ ይሄድ ነበር። ነገር ግን በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ለሦስት ወር የሚቆይ መነቃቃት እንዲኖራት ቤተ ክርስቲያንን ማዘጋጀት ባይችልም በዚያ መቆየት አለበት። ለቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲህ ቢል መልካም ሳይሆን አይቀርም፤ «ከእነዚህ ረጅም እንቅልፎች አንዱን ለመተኛት በወሰናችሁ ጊዜ፥ እንደገና ለመንቃት እስክትዘጋጁ ድረስ በዚያ መካከል ወደ ሌላ ስፍራ ሄጄ እንድሠራ እባካችሁ አሳውቁኝ።»
3. ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በመነቃቃት ሊባረኩ አይችሉም፤ ምክንያቱም አገልጋያቸውን ራሳቸው በበቂ ሁኔታ መደገፍ እየቻሉ ለደመወዙ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናትና ከጌታ ግምጃ ቤት ጥገኛ ሆነው እየመጠጡ ነው። ምናልባት ለወንጌል ሲሉ ምንም ራስን መካድ ሳያደርጉ በሀገር ውስጥ ሚሲዮናዊ ማኅበር ወይም በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ላይ ይደገፋሉ። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት እንዴት እንደሚኖሩ ሳይ ተደንቄአለሁ። የማውቃት አንዲት ቤተ ክርስቲያን ለሚሲዮን ከሚሰጡት ይልቅ ለትንባሆ ብዙ ገንዘብ እንደሚያወጡ በእርግጥ ተናዘዙ። ሆኖም አገልጋይን ለመደገፍ ስለማይችሉ አገልጋይ አልነበራቸውም። አሁንም የላቸውም። ሆኖም በዚያች ቤተ ክርስቲያን አገልጋይን ሊደግፍ የሚችል አንድ ሰው አለ። አሁንም አገልጋይ የላቸውም፤ ስብከትም የላቸውም።
አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ጉዳይ ስላለባቸው ግዴታ አልተማሩም። ባለፈው በጋ ስብከት በሌለበት አንድ ስፍራ ቆምኩ። ለምን እንደዚያ እንደሆነ አንድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሽማግሌ ጠየቅሁት፤ እርሱም እጅግ ድሆች ስለሆኑ ነው አለ። ምን ያህል ሀብት እንዳለው ጠየቅሁት። ቀጥተኛ መልስ አልሰጠኝም፤ ነገር ግን የሌላው ሽማግሌ ገቢ በዓመት $5,000 ገደማ እንደሆነ ተናገረ፤ በመጨረሻም የዚህም ሰው ገቢ ያንኑ ያህል እንደሆነ አወቅሁ። እንዲህ አልኩ፤ እነሆ ሁለት ሽማግሌዎች ናችሁ፤ ከእናንተ እያንዳንዳችሁ አገልጋይን መደገፍ ትችላላችሁ፤ ከውጭ እርዳታ ማግኘት ስላልቻላችሁ ስብከት የላችሁም። ለምን፥ ስብከት ቢኖራችሁም እንኳ እንዲህ ከጌታ ግምጃ ቤት እየመጠጣችሁ ሳላችሁ አይባረክም ነበር። በመጨረሻም አገልጋይን መደገፍ እንደሚችል ተናዘዘ፤ ሁለቱም በአንድነት ሊያደርጉት ተስማሙ።
አብያተ ክርስቲያናት በእርግጥ ምንም እርዳታ ሳያስፈልጋቸው፥ የራሳቸውንም አገልጋይ ቢደግፉ እጅግ ሲሻላቸው እርዳታ መጠየቃቸው የተለመደ ነው። ራሳቸው ሊያሰባስቡት የሚገባውን ገንዘብ ከሀገር ውስጥ ሚሲዮናዊ ማኅበር ቢወስዱ የጌታን እርግማን በላያቸው ሊጠብቁ ይችላሉ፤ ይህም ወንጌል ከበረከት ይልቅ እርግማን የሚሆንባቸው በቂ ምክንያት ይሆናል። ስንቶቹ አብያተ ክርስቲያናት «እናንተ፥ ይህች ቤተ ክርስቲያን ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ሰርቃችኋል» ሊባልላቸው ይቻላል!
አገልጋይን ለግማሽ ጊዜ ብቻ የቀጠረችና ለዚያም እንኳ ደመወዙን መክፈል እንደማትችል የተሰማትን አንዲት ቤተ ክርስቲያን አውቃለሁ። በአጎራባች ከተማ ያለ አንድ የሴቶች የሥራ ማኅበር ገንዘቡን ለዚህ ዓላማ መድቦ ይህችን ቤተ ክርስቲያን የአገልጋይዋን ደመወዝ በመክፈል ረዳት። ውጤቱ እንደሚጠበቀው ሆነ። እርሱ ጥቂት ወይም ምንም መልካም ነገር አላደረገላቸውም። በስብከቱ ሥር መነቃቃት አልነበራቸውም፤ በእንዲህ ያለ መርሕ እየተመሩ ሳሉም ሊጠብቁ አይችሉም። በዚያ ጉባኤ ውስጥ አገልጋይን ሙሉ ጊዜ ሊደግፍ የሚችል አንድ ሰው ነበረ። የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ሀብታቸው ሁለት መቶ ሺህ ዶላር እንደሚሆን ይገመት እንደነበር አንድ አባል ነገረኝ። ይህ እውነት ከሆነ፥ እነሆ በሰባት በመቶ ወለድ በዓመት $14,000 ገቢ ያላት ቤተ ክርስቲያን፥ ግማሽ ጊዜ የሚሰብክ አገልጋይን ለመደገፍ $200 ለመክፈል እጅግ ድሆች እንደሆኑ ተሰማቸው፤ ይህንንም ገንዘብ እንዲከፍሉ የአጎራባቿ ከተማ ሴቶች በገዛ እጃቸው እንዲሠሩ ፈቀዱ። ከዚህች ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መካከል ብዙዎቹ ትንባሆ እንደሚጠቀሙ አገኘሁ፤ አብረው የሚኖሩ ሁለቱም በመጽሐፍ ቅዱሳቸው ባዶ ገጽ ላይ በተጻፈ ቃል ኪዳን ያንን ኃጢአት ለዘላለም ለመተው ቃል ገብተው ፈረሙ።
ይህች ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለውን መንገድ የተከተለችው በአብዛኛው ትክክለኛ ትምህርት በማጣቷ ነበር። ጉዳዩ በተነሣና ግዴታቸው በፊታቸው በቀረበ ጊዜ፥ የምናገርለት ባለ ጠጋ ሰው ጉባኤው ቅር ተሰኝቶ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበዛል ብሎ ባያስብ ኖሮ ደመወዙን በሙሉ ራሱ እንደሚከፍል ተናገረ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ አምጥታ ከደመወዙ ከፊሉን ብታሰባስብ ቀሪውን እርሱ እንደሚሸፍን ተናገረ። አሁን አገልጋይን ለግማሽ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ጊዜ መደገፍና ደመወዙን ራሳቸው መክፈል ይችላሉ። ይህንንም ማድረጋቸው መልካምና ጠቃሚ ሆኖ ያገኙታል።
በመነቃቃቶች ውስጥ እየሠራሁ ከስፍራ ወደ ስፍራ ስሄድ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ልግስናቸው መጠን እንደተባረኩ ሁልጊዜ አግኝቻለሁ። ወንጌልን ለመደገፍና ሀብታቸውን በልግስና ወደ ጌታ ግምጃ ቤት ለማፍሰስ ፈቃደኝነት ባሳዩበት ስፍራ በመንፈሳዊም በምድራዊም ነገር ተባርከዋል። ነገር ግን ንፉጎች በሆኑበትና አገልጋዩ በጥቂት ወይም ያለ ምንም ዋጋ እንዲሰብክላቸው በተዉበት ስፍራ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ከመባረክ ይልቅ ተረግመዋል። በአጠቃላይም በሃይማኖታዊ መነቃቃቶች ውስጥ፥ አዳዲስ አማኞች ወንጌልን ለመደገፍ በሚያደርጉት ጥረት እጅግ ለጋስ ወደሆኑት አብያተ ክርስቲያናት ለመቀላቀል ይበልጥ እንደሚያዘነብሉ እውነት ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ጉዳይ እጅግ በጨለማ ውስጥ ናቸው። ግዴታቸውን አልተማሩም። ጉዳዩ በፊታቸው በቀረበ ጊዜ ለማድረግ እጅግ ዝግጁነት በብዙ አጋጣሚዎች አግኝቻለሁ። ቤተ ክርስቲያኒቱ ድሀ ስለሆነች ለግማሽ ጊዜ አገልጋይ ስለ ማግኘት ይናገር የነበረ፥ የገዛ ገቢው ግን ብዙ የነበረ አንድ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ አውቅ ነበር። የእርሱ ገቢ ብቻውን አገልጋይን ሙሉ ጊዜ ለመደገፍ አይበቃምን ብዬ ጠየቅሁት። ይበቃል አለ። በእጁ ያለውን የጌታን ገንዘብ በገዛ ከተማው አገልጋይን ለግማሽ ሳይሆን ሙሉ ጊዜ ከመቅጠር ይልቅ ለክርስቶስ መንግሥት ጥቅም ይበልጥ በሚጠቅም በምን ሌላ መንገድ ሊጠቀምበት እንደሚችል በተጠየቀ ጊዜ፥ ራሱ ጉዳዩን ለመያዝ ወሰነ። በዚህም መሠረት አገልጋይ ተገኝቷል፤ ሙሉ ደመወዙንም ለመክፈል ምንም ችግር እንደማያገኙ አምናለሁ።
እውነቱ፥ አገልጋይ ግማሽ ጊዜ ብቻ በመስበክ ጥቂት ብቻ ሊያደርግ ይችላል። በአንድ ሰንበት ስሜት ቢፈጠር፥ ሁለት ሳምንት ሳይሞላ ይጠፋል። ለቁጠባ ሲባል እንኳ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ሙሉ ጊዜ ለመደገፍ ራሷን ልትሰጥ ይገባል። ትክክለኛውን ዓይነት አገልጋይ አግኝተው ያለማቋረጥ በሥራ ቢያቆዩት መነቃቃት ሊኖራቸው ይችላል፤ እንዲሁም ኃጢአተኞች ተለውጠው ገብተው ይረዷቸዋል። በዚህም በአንድ ዓመት ውስጥ በኃይላቸው ላይ ታላቅ ጭማሪ ሊኖራቸው ይችላል። ነገር ግን አገልጋይን ለግማሽ ጊዜ ብቻ ቢቀጥሩ፥ ኃጢአተኞች ወደ ሲኦል እየሄዱ ሳሉ ዓመት ከዓመት ሊያልፍ ይችላል፤ ከኃጢአተኞችም ሰልፍ በኃይላቸው ላይ ምንም ጭማሪ አይደረግም።
እውነቱ፥ ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ያላቸው ሀብት ሁሉ የጌታ እንደሆነ እንዲሰማቸው አልተደረገም። ስለዚህ ለወንጌል ድጋፍ ንብረታቸውን ስለ መስጠት ይናገራሉ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማኝ እንደሆነና እነርሱም ወንጌሉን እንደ ምጽዋት እንዲደግፉ የተጠሩ ይመስል! በዚህ ክፍለ ሀገር ካሉ ከተሞች በአንዱ የሚኖር አንድ ነጋዴ የአገልጋዩን ደመወዝ ትልቁን ክፍል ይከፍል ነበር። ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት አንዱ ይህንን ከውጭ ለመጣ አገልጋይ እየነገረ ይህ ነጋዴ ስለሚከፍለው መሥዋዕትነት ይናገር ነበር። በዚያን ጊዜ ነጋዴው ገባ። አገልጋዩም እንዲህ አለ፤ «ወንድሜ ሆይ፥ አንተ ነጋዴ ነህ። ዕቃ የሚሸጥ ጸሐፊና ልጆችህን የሚያስተምር መምህር ብትቀጥር፥ ጸሐፊህን ለመምህሩ ስለ ማስተማሩ አገልግሎት ከሱቁ ይህን ያህል እንዲከፍለው ብታዝዘው፥ አሁን ጸሐፊህ እርሱ ለዚህ መምህር ደመወዙን መክፈል እንዳለበት ቢያወራ፥ ይህንንም ለማድረግ እርሱ ስለሚከፍለው መሥዋዕትነት ቢናገር፥ ስለዚህ ምን ትላለህ?» ነጋዴውም «ለምን፥ የሚያስቅ ነው እላለሁ» አለ። አገልጋዩም እንዲህ አለ፤ «እንግዲህ እግዚአብሔር እንደ ጸሐፊው ዕቃ እንድትሸጥ አንተን ቀጥሮሃል፤ አገልጋይህንም ልጆቹን እንዲያስተምር ቀጥሮታል፤ ደመወዙንም ከሱቁ ገቢ እንድትከፍለው ያዝሃል። አሁን ይህን መሥዋዕትነትህ ትለዋለህን? የዚህን አገልጋይ ደመወዝ ለመክፈል ታላቅ መሥዋዕትነት እከፍላለሁ ትላለህን? አይደለም፤ እርሱ ለእግዚአብሔር ሊሰብክ እንደሚገደድ አንተም ለእግዚአብሔር ዕቃ ልትሸጥ እንዲሁ ትገደዳለህ። እርሱ ለዚያው ዓላማ ወንጌልን ለመስበክ መብት እንደሌለው፥ አንተም ገንዘብ ለማከማቸት ዓላማ ዕቃ ለመሸጥ መብት የለህም። እርሱ ወንጌልን በመስበክ እንደሆነ፥ አንተም ዕቃ በመሸጥ እንዲሁ ቅዱስ ልትሆንና በአንድ ልብ የእግዚአብሔርን ክብር ልታልም ትገደዳለህ። ስለዚህ እርሱ እንደሚያደርገው አንተም ጊዜህን ሁሉ ለእግዚአብሔር አገልግሎት ፈጽመህ ልትሰጥ ይገባሃል። አንተና ቤተሰብህ ከዚህ ሱቅ ትርፍ በሕጋዊ መንገድ ልትኖሩ ትችላላችሁ፤ አገልጋዩና ቤተሰቡም እንዲሁ በሕጋዊ መንገድ ሊኖሩ ይችላሉ። በእነዚህ ዓላማዎች ዕቃ ብትሸጥ ዕቃ መሸጥ እንደ መስበክ እግዚአብሔርን ማገልገል ነው። በእነዚህ መርሖች ዕቃ የሚሸጥና በእነርሱ የሚመላለስ ሰው፥ ወንጌልን እንደሚሰብክ ሰው ያህል ቅዱስ ነው፤ እንደ እርሱም ያህል በእግዚአብሔር አገልግሎት ውስጥ ነው። ሰው ሁሉ እግዚአብሔርን በሙያው ሊያገለግል ይገደዳል፤ አገልጋዩ በማስተማር፥ ነጋዴው ዕቃ በመሸጥ፥ ገበሬው እርሻውን በማረስ፥ ጠበቃውና ሐኪሙ የሙያቸውን ተግባር በመፈጸም።»
«ከእነዚህ ማናቸውም ለሚጠፋ መብል መሥራት እኩል ያልተፈቀደ ነው። የሚያደርጉት ሁሉ ለእግዚአብሔር ሊሆን ይገባል፤ ቤተሰቦቻቸውን በምቾት ከደገፉ በኋላ የሚያገኙት ሁሉ ለወንጌል መስፋፋትና ለዓለም መዳን ሊሰጥ ይገባል።»
አገልጋዮች ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ ቅዱሳን መሆን እንዳለባቸው፥ እነርሱ ዓለምን መውደድ እንደሌለባቸው፥ እነርሱ ለእግዚአብሔር መሥራት እንዳለባቸው፥ በተቻለ መጠን በቁጠባ መኖር እንዳለባቸውና የኢየሱስ ክርስቶስን መንግሥት ለመገንባት ጊዜያቸውን፥ ጤናቸውን፥ ኃይላቸውንና ሕይወታቸውን ሁሉ ማዋል እንዳለባቸው ለረጅም ጊዜ ሲታሰብ ቆይቷል። ይህ እውነት ነው። ነገር ግን ሌሎች ሰዎች በዚያው መስክ እንዲሠሩና ጊዜያቸውን ለሕዝባዊ ትምህርት እንዲሰጡ ባይጠሩም፥ ጊዜያቸውን ሁሉ የእግዚአብሔር አድርገው ሊቆጥሩ ፈጽመው እንዲሁ ይገደዳሉ፤ ዓለምን ለመውደድ፥ ወይም ሀብት ለማከማቸት፥ ወይም ለልጆቻቸው ለማስቀመጥ፥ ወይም ለምኞታቸው ለማባከን ከአገልጋዮች የበለጠ መብት የላቸውም።
ቤተ ክርስቲያን እነዚህን መርሖች የምታውቅበት ጊዜ አሁን ነው፤ የሀገር ውስጥ ሚሲዮናዊ ማኅበር ሕዝቡን ለመለወጥ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ሊደክም ይችላል፤ አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ረገድ ያለባቸውን ግዴታ እስኪያስተውሉና እስኪሰማቸው ድረስ ግን ፈጽሞ አይሳካለትም። ለምን፥ ራሳቸው አገልጋያቸውን መደገፍ እየቻሉ ከሀገር ውስጥ ሚሲዮናዊ ማኅበር ለዚሁ እርዳታ መጠየቃቸውና መቀበላቸው፥ ድካሙ በመካከላቸው ይበልጥ ያልተባረከበት ዋነኛ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።
የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ሚሲዮናዊ ማኅበር ራሳቸውን መርዳት የማይችሉትን ደካማ አብያተ ክርስቲያናት ለመርዳት አሁን ካለው መቶ እጥፍ ሀብት ቢኖረው እወድ ነበር። ነገር ግን መቻል እየቻሉ ወንጌልን ለመደገፍ ፈቃደኞች ላልሆኑት ገንዘቡን መስጠት ቁጠባም ቅድስናም አይደለም። መቻል እየቻሉ ራሳቸውን ለመርዳት ፈቃደኞች ካልሆኑ እነርሱን ለመርዳት መሞከር ከንቱ ነውና።
ሚሲዮናዊ ማኅበሩ አንድ ቶን ወርቅ ቢኖረው እንኳ ለእንዲህ ያለች ቤተ ክርስቲያን መስጠት ምጽዋት አይሆንም። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን አሥራቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጎተራ ታምጣ፤ እግዚአብሔርም የሰማይን መስኮቶች ይከፍታል፥ በረከትንም ያፈስሳል። ነገር ግን አብያተ ክርስቲያናት እስከ አቅማቸው ድረስ ራሳቸውን ለመርዳት ፈቃደኞች ካልሆኑ፥ በአገልጋዮቻቸው ድካም ላይ እንዲህ ያለ ጥቂት ፍሬ ለምን እንደሚታይ እንደሚያውቁ በእርግጥ ይወቁ። እነሆ ድጎማቸውን ከጌታ ግምጃ ቤት እየመጠጡ ነው። ስንቶቹ አብያተ ክርስቲያናት ገንዘባቸውን ለሻይና ለቡና ለትንባሆም አውጥተው ከዚያም መጥተው ከሀገር ውስጥ ሚሲዮናዊ ማኅበር እርዳታ ይጠይቃሉ! ሻይና ትንባሆ የሚጠቀሙትን፥ ያለ ትንሹ ራስን መካድ የሚኖሩትንና ምንም የማያስከፍላቸውን ብቻ ለእግዚአብሔር ማቅረብ የሚፈልጉትን ቤተ ክርስቲያን መርዳትን እቃወማለሁ።
በመጨረሻም—ሊባረኩ ካሰቡ ግዴታቸውን ይፈጽሙ፤ ግዴታቸውን ሁሉ ይፈጽሙ፤ ትከሻቸውን ከመንኰራኵሩ ጋር ያስጠጉ፤ የወንጌልን የጦር ዕቃ ይታጠቁ፤ ወደ ሥራውም ይውጡ። ያን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን በሜዳው ላይ ከሆነች፥ ሲኦል ሁሉ ቢቃወምም የመዳን ሰረገላ ወደ ፊት ይገሰግሳል፤ ኃጢአተኞችም ተለውጠው ይድናሉ። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ድካሙን ሁሉ ለአገልጋዩ ትታ እርሱ ሲደክም ተቀምጣ ብትመለከት፥ ራሳቸውም እርሱን ከማማረር በቀር ምንም ባያደርጉ፥ ሃይማኖታዊ መነቃቃትን ማጣት ብቻ ሳይሆን፥ በስንፍናና በፈራጅነት ቢቀጥሉ በክርስቶስ አገልግሎት ስላላቸው አለመታዘዝና የማይጠቅም ስለ መሆናቸው ውሎ አድሮ ራሳቸውን በሲኦል ያገኛሉ።