ሃይማኖታዊ የልብ ዝንባሌዎች
II. የልብ ዝንባሌዎች በሰውነት ላይ ታላቅ ውጤት ማስከተላቸው የእውነተኛ ሃይማኖት ባሕርይ እንዳላቸው ወይም እንደሌላቸው ምልክት አይደለም

ምዕራፍ 4 · 6 ደቂቃ ንባብ · 7 ደቂቃ ማዳመጥ

II. የልብ ዝንባሌዎች በሰውነት ላይ ታላቅ ውጤት ማስከተላቸው የእውነተኛ ሃይማኖት ባሕርይ እንዳላቸው ወይም እንደሌላቸው ምልክት አይደለም

II. የልብ ዝንባሌዎች በሰውነት ላይ ታላቅ ውጤት ማስከተላቸው የእውነተኛ ሃይማኖት ባሕርይ እንዳላቸው ወይም እንደሌላቸው ምልክት አይደለም።

ማናቸውም የልብ ዝንባሌ ሁሉ በሆነ መንገድ ወይም መጠን በሰውነት ላይ ውጤት አለው። ቀደም ብሎ እንደ ተመለከትነው፣ ተፈጥሮአችን እንዲህ ነው፣ የነፍስና የሥጋ አንድነት ሕጎችም እንዲህ ናቸው፤ ስለዚህ አእምሮ በሰውነት ላይ አንዳች ውጤት ሳያስከትል ሕያው ወይም ብርቱ እንቅስቃሴ ሊኖረው አይችልም። ሰውነት ለአእምሮ እጅግ የተገዛ ነው፤ ፈሳሾቹም፣ በተለይም እንስሳዊ መናፍስት የሚባሉት፣ የአእምሮን እንቅስቃሴዎችና ተግባራት እጅግ አጥብቀው ይከተላሉ፤ ስለዚህ በእነርሱ ላይ ውጤት የሌለው አንድ የጠለቀ ሐሳብ እንኳ ሊኖር አይችልም። እንዲያውም በሥጋ የተለበሰች ነፍስ በሰውነት በአንድ ክፍል ውስጥ ባሉት ፈሳሾች ላይ በተወሰነ መጠን የሚመጣጠን እንቅስቃሴ ወይም የእንቅስቃሴ ለውጥ ሳይኖር አንዲት ሐሳብ እንኳ ታስብ ወይም ማናቸውም ዓይነት እንቅስቃሴ ይኖራት እንደሆነ አጠያያቂ ነው። ነገር ግን የልብ ዝንባሌዎች እንቅስቃሴ በተለየ ሁኔታ በሰውነት ላይ በግልጥ የሚሰማ ውጤት የማስከተል አዝማሚያ እንዳለው የሰው ሁሉ ተሞክሮ ያሳያል። የልብ ዝንባሌዎች ሁሉ በሰውነት ላይ አንዳች ውጤት ያላቸው ከሆነ ደግሞ፣ የልብ ዝንባሌዎቹ በበዙና እንቅስቃሴአቸው በበረታ መጠን (ሌሎቹ ሁኔታዎች እኩል ሲሆኑ) በሰውነት ላይ የሚያስከትሉት ውጤትም የዚያኑ ያህል ይበልጣል ብለን በሚገባ ልናስብ እንችላለን። ስለዚህ እጅግ ታላላቅና ብርቱ የልብ ዝንባሌ እንቅስቃሴዎች በሰውነት ላይ ታላቅ ውጤት ቢያስከትሉ የሚያስደንቅ አይደለም። ስለዚህም ተራም መንፈሳዊም የሆኑ እጅግ ታላላቅ የልብ ዝንባሌዎች ስላሉ፣ ከእነዚህ ከሁለቱም ዓይነት የልብ ዝንባሌዎች በሰውነት ላይ ታላቅ ውጤት ቢመጣ የሚያስደንቅ አይደለም። ስለሆነም እነዚህ ውጤቶች የመጡባቸው የልብ ዝንባሌዎች ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ዓይነት ስለ መሆናቸው ምልክቶች አይደሉም።

በሰውነት ላይ የሚታዩ ታላላቅ ውጤቶች የልብ ዝንባሌዎች መንፈሳዊ ስለ መሆናቸው በእርግጥ አስተማማኝ ማስረጃዎች አይደሉም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉ ውጤቶች ብዙ ጊዜ ስለ ጊዜያዊ ነገሮች ካሉ ታላላቅ የልብ ዝንባሌዎች፣ ሃይማኖትም በእነርሱ ውስጥ በምንም መንገድ ሳይገባ፣ እንደሚመጡ እናያለንና። ፍጹም ተፈጥሮአዊ የሆኑ ስለ ዓለማዊ ነገሮች ያሉ ታላላቅ የልብ ዝንባሌዎች እነዚህን ውጤቶች ሊያስከትሉ የሚችሉ ከሆነ፣ እንደዚሁ ከተፈጥሮ የሚመነጩ ስለ ሃይማኖታዊ ነገሮች ያሉ ከፍተኛ የልብ ዝንባሌዎች ተመሳሳይ ውጤት ሊያስከትሉ አይችሉም ብለን በምን መመሪያ እንደምንወስን አላውቅም።

በሌላ በኩልም፣ የጸጋና ቅዱስ የልብ ዝንባሌዎች እንደ ማናቸውም ተፈጥሮአዊ የልብ ዝንባሌዎች ከፍ ብለው ሲነሡና እኩል ብርቱና ኃይለኛ እንቅስቃሴ ሲኖራቸው በሰውነት ላይ ታላቅ ውጤት ሊያስከትሉ አይችሉም ብሎ ለመወሰን ማንም ያለውን አንዳች መመሪያ አላውቅም። እንዲህ ያለ መመሪያ ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ሊወጣ አይችልም፤ የሰሎሞንን ክብር በማየት መነካት ሰውነትን እንደሚያዝለው ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ክብር በማየት መነካትም ሰውነትን የማያዝለው ለምን እንደሆነ ምንም ምክንያት አላውቅም። እንዲህ ያለ መመሪያም እስከ አሁን ድረስ ከመጽሐፍ ቅዱስ አልቀረበም፤ በዚህ ዓይነት ነገሮች ዙሪያ በቅርቡ በተደረጉት ክርክሮች ሁሉ ውስጥ አንድም አልተገኘም። በመንፈሳዊ የልብ ዝንባሌዎች ውስጥ ታላቅ ኃይል አለ፤ በክርስቲያኖች ውስጥ ስለሚሠራው ኃይል፣22 ኤፌሶን 3:7። የእግዚአብሔርም መንፈስ የኃይል መንፈስ ሆኖ በእነርሱ ውስጥ ስለ መኖሩ፣33 2ኛ ጢሞቴዎስ 1:7። በእነርሱም ውስጥ ስለሚሠራው ስለ ኃይሉ አሠራር እናነባለን።44 ኤፌሶን 3:7፣ 20። ነገር ግን የሰው ተፈጥሮ ደካማ ነው፤ ሥጋና ደም በመጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ደካማ ሆነው ተገልጠዋል፤ በተለይም ለታላላቅ መንፈሳዊና ሰማያዊ አሠራሮችና እንቅስቃሴዎች ብቁ ካለመሆኑ አንጻር፤ ማቴዎስ 26:41፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 15:43 እና 50። የምንመለከተው ጥቅስ ስለ «ሊነገር ስለማይቻልና ክብር ስለ ሞላበት ደስታ» ይናገራል። የሰው ተፈጥሮ ምን እንደሆነ፣ የልብ ዝንባሌዎችም ባሕርይ ምን እንደሆነ የሚያስብ ማንም ሰው፣ እንዲህ ያሉ ሊነገሩ የማይችሉና የከበሩ ደስታዎች ለደካማው አፈርና አመድ እጅግ ታላላቅና ኃያላን ሆነው በብዙ ሊያሸንፉት እንደሚችሉ በምክንያት ሊጠራጠር ይችላልን? እውነተኛ መለኮታዊ መገለጦች ወይም የእግዚአብሔር ክብር ሐሳቦች በታላቅ መጠን ሲሰጡ አእምሮን በመንካት ሰውነትን የማሸነፍ አዝማሚያ እንዳላቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ግልጥ ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ሐሳቦች ወይም ራእዮች በሰማይ በሚሰጡበት መጠን ቢሰጡ ደካማው የሰውነት አቋም ከሥራቸው ሊጸና እንደማይችል፣ ማንም ሰው በዚያ ሁኔታ እግዚአብሔርን አይቶ በሕይወት ሊኖር እንደማይችል መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ያስተምረናል። ቅዱሳን በዚህ ዓለም ስለ እግዚአብሔር ውበትና ክብር ያላቸው እውቀትና ከእርሱ የሚመነጩት ቅዱስ የልብ ዝንባሌዎች ቅዱሳን በሰማይ ከሚቀበሉት ጋር አንድ ባሕርይና አንድ ዓይነት ናቸው፤ የሚለያዩት በመጠንና በሁኔታ ብቻ ነው፤ እግዚአብሔር እዚህ የሚሰጣቸው የሰማያዊ ደስታ ቅምሻና የሚመጣው ርስታቸው መያዣ ነው። እግዚአብሔርን ይህን መያዣ በመስጠቱ ማን ይገድበዋል? ወይስ፦ ከርስቱ ይህን ያህል ብቻ፣ ከሚመጣው ዋጋ ይህን ያህል ክፍል ብቻ ለሁሉ መያዣ አድርጎ ይሰጣል፣ ከዚያ አይበልጥም ብሎ ማን ይናገራል? እግዚአብሔርም ሙሉው ዋጋ ሰውነትን በአንድ ጊዜ የሚያጠፋ እንደሆነ በቃሉ አስተምሮናል፤ ታዲያ እግዚአብሔር ራሱን በየትም ስፍራ እንዲህ ሳይወስን ሳለ፣ የዚህን ዋጋ መያዣ በዚህ ዓለም ሲሰጥ የሰውነትን ብርታት በጥቂቱ እንኳ እስኪያደክም ድረስ ከእርሱ ፈጽሞ አይሰጥም ብለን ለሉዓላዊው አምላክ እንዲህ ድንበር ማበጀታችን እጅግ የድፍረት ነገር አይደለምን?

መዝሙረኛው ስለ ነበሩት ብርቱ ሃይማኖታዊ የልብ ዝንባሌዎች ሲናገር፣ በነፍሱ ውስጥ ከነበረው ሌላ በሥጋው ወይም በሰውነቱ ላይ ስለ ደረሰ ውጤት ይናገራል፤ አንዱንም ከሌላው ደጋግሞ በግልጥ ይለያል፤ መዝሙር 84:2፦ «ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትናፍቃለች፣ እጅግም ትዝላለች፤ ልቤና ሥጋዬ ወደ ሕያው አምላክ ይጮኻሉ።» ልብና ሥጋ እያንዳንዳቸው እንደ ተነኩ በመካከላቸው ግልጥ ልዩነት እዚህ አለ። እንዲሁም መዝሙር 63:1፦ «ውኃ በሌለበት በደረቅና በተጠማ ምድር ነፍሴ አንተን ተጠማች፣ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች።» እዚህም ደግሞ በነፍስና በሥጋ መካከል ሆን ተብሎ የተደረገ ግልጥ ልዩነት አለ።

ነቢዩ ዕንባቆም ሰውነቱ በእግዚአብሔር ግርማ ስሜት እንደ ተሸነፈ ይናገራል፤ ዕንባቆም 3:16፦ «በሰማሁ ጊዜ ሆዴ ተንቀጠቀጠ፤ ከድምፁ የተነሣ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ፤ ብስባሽ ወደ አጥንቶቼ ገባ፤ በውስጤም ተንቀጠቀጥሁ።» እንዲሁም መዝሙረኛው ሥጋው እንደ ተንቀጠቀጠ በግልጥ ይናገራል፤ መዝሙር 119:120፦ «ሥጋዬ አንተን ከመፍራት የተነሣ ይንቀጠቀጣል።»

በዚህ ዓለም አንዳንድ ጊዜ የሚሰጡት እንዲህ ያሉ የእግዚአብሔር ክብር ሐሳቦች ሰውነትን የማሸነፍ አዝማሚያ እንዳላቸው ግልጥ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለዚያው ዓላማ፣ ማለትም የእግዚአብሔርን ግርማና ክብር ሐሳብ ሊሰጣቸው፣ ለአንዳንድ ቅዱሳን ያደረጋቸው እነዚያ የራሱ ውጫዊ መገለጦች አንዳንድ ጊዜ በእርግጥ ይህን ውጤት እንዳስከተሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። እንዲህ ያሉ ምሳሌዎች በነቢዩ ዳንኤልና በሐዋርያው ዮሐንስ ዘንድ አሉን። ዳንኤል የክርስቶስን ክብር ውጫዊ መግለጫ ሲተርክ እንዲህ ይላል፤ ዳንኤል 10:8፦ «ኃይልም አልቀረልኝም፤ ውበቴም ወደ ብልሽት ተለወጠ፤ ምንም ኃይል አላገኘሁም።» ሐዋርያው ዮሐንስም ለእርሱ የተደረገውን መገለጥ ሲተርክ እንዲህ ይላል፤ ራእይ 1:17፦ «ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ።» እዚህ ላይ፦ እነዚህ ቅዱሳን ያዩአቸው የክርስቶስ ክብር ውጫዊ መገለጦች ወይም ምሳሌዎች ብቻ ነበሩ ማለት ከንቱ ነው፤ ምክንያቱም በሥጋ ዓይኖቻቸው ያዩአቸው የክርስቶስ ክብር ውጫዊ መግለጫዎች እንደ ነበሩ እውነት ቢሆንም፣ የእነዚህ ውጫዊ ምሳሌዎች ወይም መግለጫዎች ዓላማና ጥቅም ለእነዚህ ነቢያት የተገለጸውን ነገር ሐሳብ መስጠት ነበር፤ ያም እውነተኛው የክርስቶስ መለኮታዊ ክብርና ግርማ፣ ማለትም መንፈሳዊ ክብሩ ነበር፤ እነርሱም ጥቅም ላይ የዋሉት የዚህ መንፈሳዊ ክብር ማመልከቻዎች ሆነው ብቻ ነበር፤ ቅዱሳኑም ያለ ጥርጥር እንዲሁ ተቀበሏቸው፣ ተጠቀሙባቸውም፣ በእነርሱም ተነኩ። እግዚአብሔር እነዚህን ውጫዊ ምልክቶች ባሰበበት ዓላማ መሠረት፣ በእነርሱ አማካይነት እነርሱ ምልክቶቹ የሆኑለትን የእግዚአብሔርን ባሕርይ እውነተኛ ክብርና ግርማ ታላቅና ሕያው በሆነ መረዳት ተረዱ፤ በዚህም እጅግ ተነኩ፣ ነፍሶቻቸው ተዋጡ፣ ሰውነታቸውም ተሸነፈ። እግዚአብሔር እንዲህ ያለ ውጫዊ ጥላ ጣልቃ ሳይገባ የዚያኑ የባሕርዩን እውነተኛ ክብርና ግርማ ተመሳሳይ ግልጥና ልብን የሚነካ ሐሳብና መረዳት ለማናቸውም ቅዱሳኑ ሊሰጥ አይችልም ወይም አይሰጥም የሚሉ እጅግ ደፋሮችና ተዳፋሪዎች ናቸው ብዬ አስባለሁ።

ይህን ርዕስ ከመተዉ በፊት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱስና የመንፈሳዊ የልብ ዝንባሌዎችን ብርታት ለመግለጽ የሰውነት ውጤቶችን ብዙ ጊዜ እንደሚጠቀም ግልጥ መሆኑን ደግሞ ልጠቁም እወዳለሁ፤ እነርሱም መንቀጥቀጥ፣55 መዝሙር 119:120። ዕዝራ 9:4። ኢሳይያስ 66:2፣ 5። ዕንባቆም 3:16። መቃተት፣66 ሮሜ 8:26። መታመም፣77 መኃልየ መኃልይ 2:5 እና 5:8። መጮኽ፣88 መዝሙር 84:2። ቁና ቁና መተንፈስ፣99 መዝሙር 38:10፣ 42:1 እና 119:131። መዛልም ናቸው።1010 መዝሙር 84:2 እና 119:81። እንግዲህ እነዚህ የልብ ዝንባሌን መጠን ለመግለጽ የተነገሩ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ብቻ ናቸው ቢባል እንኳ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ሊገልጻቸው የሚጠቀምባቸውን የእነዚያን መንፈሳዊ የልብ ዝንባሌዎች ከፍተኛ መጠን ለመግለጽ ተስማሚና የሚገቡ ምሳሌዎች እንደሆኑ ሁሉም እንደሚቀበሉ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን እነዚያ መንፈሳዊ የልብ ዝንባሌዎች ምንም ያህል ከፍተኛ መጠን ላይ ቢደርሱ ወደ እንደዚህ ያሉ ነገሮች አንዳች አዝማሚያ የሌላቸው ቢሆኑ፣ ይልቁንም በተቃራኒው እነዚህ ነገሮች የሐሰተኛ የልብ ዝንባሌዎችና የዲያብሎስ ማታለል ትክክለኛ ውጤቶችና አሳዛኝ ምልክቶች ቢሆኑ፣ እንዴት ተስማሚ ምሳሌዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ አይታየኝም። እግዚአብሔር ከመንፈሳዊ የልብ ዝንባሌዎች እጅግ የራቁትን፣ የሰይጣን እጅ ጉልህ ምልክቶች የሆኑትንና የጥልቁ ጉድጓድ ብርቱ ሽታ የሚሸቱትን ነገሮች የቅዱስና የሰማያዊ የልብ ዝንባሌዎችን ከፍተኛ መጠን ለመግለጽ እንደ ውብ ምሳሌዎች አዘውትሮ ይጠቀምባቸዋል ብዬ ማሰብ አልችልም።

ቀዳሚ ቀጣይ