ጸሎት — የሕይወት ትርታ
በመንፈስ መጸለይ

ምዕራፍ 4 · 4 ደቂቃ ንባብ

በመንፈስ መጸለይ

እኛ ከዚህ ዓለም አይደለንም፤ ስለዚህ በመመዘኛዎቹ አንመላለስም። ስለዚህ የዜግነታችንን ቋንቋ፥ ማለትም የመንፈስን ቋንቋ እንናገር።

በመጀመሪያ፥ ሰው በዋነኛነት ነፍስ ያለው፣ በሥጋዊ አካል ውስጥ የሚኖር መንፈስ ነው። አንድ ሰው ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፉ ሲመሰክርና እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልቡ ሲያምን፥ ያ ሰው ይድናል (ሮሜ 10:8-9)። ይህ ሰው ከዚያ በኋላ ከሌሎቹ ይለያል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5:17 እንዲህ ይላል፦ «ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።» አዲስ ፍጥረት ይሆናል፤ ልዕለ ሰው፣ የእግዚአብሔር ሕይወት ያለው ሰው፣ በሕይወት ፈጽሞ ሊጎዳ የማይችል ሰው ይሆናል። በዚህም አሁን በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ነው፤ የሚገባበትም ስፍራ ያ ነው። ስለዚህ በመንግሥቱ ውስጥ የሚሆነውን ነገር ሁሉ እንዲያውቅ ሊረዳው ስለሚችል፥ የመጣበትን ስፍራ ቋንቋ ማወቅ ለእርሱ (ለእርስዋ) እጅግ ወሳኝ ይሆናል።

ያንን ቋንቋ አንድ ሰው እንዴት ሊያውቀው ወይም ሊማረው ይችላል? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

ለዚህ አዲስ ፍጥረት፣ ለዚህ ልዕለ ሰው፣ የታደሰው መንፈስ ቋንቋ ተሰጥቶታል። ይህም በሌሎች ልሳኖች መናገር ነው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተለየ መንገድ ያስቀምጡትና የመላእክት ቋንቋ ነው ይላሉ። ይህ ቋንቋ በሰዎች የሚማር ሳይሆን በእግዚአብሔር የሚሰጥ ነው፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ቋንቋ ስለ ሆነ ተራ ሰዎች ሊረዱት አይችሉም። እግዚአብሔር አብጠርጥሮ የሚያውቀውን፥ ሰይጣን እንኳ አንዲት ቃል ሊረዳው የማይችለውን ቋንቋ መናገር ያማረ አይደለምን? በመንፈስ መጸለይ ይህ ነው። እንዴት ግሩም ነው!

ደግሞ ይህን ቋንቋ መናገር፣ በሌሎች ልሳኖች መናገር እንዴት ልጀምር እችላለሁ? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ለዚህ ከሚሰጡት መልሶች አንዱ በልሳኖች መናገር መለያው የሆነውን የመንፈስ ቅዱስን ሙላት እግዚአብሔርን በጸሎት መለመን፣ ይህንንም በማድረግ እንደ መለሰልህ ማመንና በሌሎች ልሳኖች መናገር መጀመር ነው። ቀደም ብለን እንደ ጠቀስነው፥ አትጠራጠር። ሌላው መልስ ደግሞ በሐዋርያት ሥራ 19:6 እንደምናየው እጅ በመጫን ነው፦ «ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው በልሳኖችም ተናገሩ፥ ትንቢትም ተናገሩ።»

ሌላም ጥያቄ ሊመጣ ይችላል፦ «እያንዳንዱ አማኝ በልሳኖች መናገር አለበት ወይስ ለተመረጡት ብቻ ነው? በልሳኖች ባንጸልይ ምን ይሆናል? በልሳኖች ካልጸለይን መንፈስ ቅዱስ የለንም ማለት ነው? በልሳኖች መጸለይ ምን ጥቅም አለው?» እንግዲያውስ በቀጥታ ወደ ዝርዝሩ እንግባ፤ እሺ?

አማኞች ሁሉ በልሳኖች መናገር አለባቸውን?

ይህ ጥያቄ አንድ ሰው ምግብ መብላት አለበትን ብሎ እንደ መጠየቅ ነው። አንድ ሰው ሊበላ ወይም ላይበላ ይችላል፤ ነገር ግን ለረጅም ጊዜ ምግብ አለመብላት በሰውነት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዲህ አለ፦ «ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፥ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ።» ማርቆስ 16:17። ይህ ማለት በልሳኖች መናገር ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተገደበ አይደለም፤ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ ነው። ማንም ሊኮንነው ወይም ለተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ ነው ሊል አይገባም። አንተ መንፈስ ስለ ሆንህ እግዚአብሔርም ደግሞ መንፈስ ስለ ሆነ፥ የመንፈስን ቋንቋ መናገር ቅድሚያ ልትሰጠው የሚገባ ነገር ነው።

በልሳኖች መናገር አንድ ሰው በመንፈስ እንደ ተሞላ የሚያሳይ ምልክት ነው፦ ደቀ መዛሙርቱ በበዓለ ኀምሳ ቀን መንፈስ ቅዱስን ይጠብቁ ነበር። በአንድ ልብ ነበሩ።

እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች በእያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጡ። የሐዋርያት ሥራ 2:4ን ተመልከት፦ «በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።»

በብሉይ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ ሥራውን እንዲፈጽሙና የእግዚአብሔርን ሕዝብ እንዲያስተምሩ በነገሥታት፣ በካህናትና በመሳፍንት ላይ ይወርድ ነበር። ስለዚህ በመጀመሪያ እንደ እሳት ልሳኖች በላያቸው ተቀመጠ። ከዚያ በኋላ ሞላቸው። በአዲስ ኪዳን ግን መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ ይኖራል፤ ቤተ መቅደሱም ያደርገናል። ሊሞላህ በአንተ ላይ ይመጣል። በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተሞላህ የሚያሳየው ማስረጃ በልሳኖች የመናገር ምልክት ነው። ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መሆንና በመንፈስ ቅዱስ መሞላት አንድ ዓይነት ነገር አይደሉም። በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ በሌሎች ልሳኖች ይናገራሉ። ስለዚህ በልሳኖች መናገር ለፓስተሮች፣ ለጳጳሳትና ለወንጌላውያን ብቻ የታሰበ አይደለም፤ ለሁሉም ነው።

ታዲያ በልሳኖች ለምን መናገር አለብህ?

1. ያንጽሃል፦ «በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ማኅበሩን ያንጻል።» 1ኛ ቆሮንቶስ 14:4። ማነጽ ማለት መገንባት፣ መሥራትና ማጽናት ማለት ነው። ይሁዳ 1:20 እንዲህ ይላል፦ «እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ።» ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ እየጸለይን በተቀደሰው ሃይማኖታችን ራሳችንን እንድናንጽ ይነግረናል። በልሳኖች መጸለይ ያን ያህል አስፈላጊ ነው። በልሳኖች ስትናገር ትታነጻለህ፤ ከሚገጥሙህም ሁኔታዎች ትበልጣለህ። ያማረ ነው፤ አይደለም እንዴ?

መፍትሔ የሌለው የሚመስል ፈተና ወይም ሁኔታ ገጥሞሃል? ስለ ጤናህ፣ ስለ ቤተሰብህ፣ ስለ ማኅበረሰብህ ወይም ስለ አገሪቱ ነው? አንተን በሚመለከት ነገር ሁሉ ላይ ለውጥ የማምጣት ኃይል አለህ። በልሳኖች ተናገር፤ በልሳኖች መናገርህን ቀጥል፤ ለውጥም ይመጣል።

ሃሌ ሉያ!

2. በልሳኖች መናገር ኃይል ይሞላሃል፦ በዚያው በ1ኛ ቆሮንቶስ መጽሐፍ ውስጥ፥ በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል። ይህ ቃል ኃይል መሙላት ማለትም ነው። በሌሎች ልሳኖች ስትናገር ኃይልና ብርታት እያመነጨህ ነው።

ጠዋት ኃይል ሞልተሃል? ወደ ክፍል ስትሄድ ኃይል ሙላ። ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመሄድህ በፊት ኃይል ሙላ። ማጥናት ስትጀምር ኃይል ስለ ሞላህ በሚገባ ትሠራለህ። ጌታ ይመስገን!

4. በሌሎች ልሳኖች መናገር ያድስሃል፦ እንደ ክርስቲያን፥ መረጋጋት እንደሚያስፈልግህ በተሰማህ ጊዜ ሁሉ፥ ምናልባት አእምሮህ በማንኛውም ነገር፣ በማንኛውም ጉዳይ በተጨናነቀ ጊዜ፥ በልሳኖች መናገር ያድስሃል። በእነዚያ ጊዜያት እግዚአብሔር ሊናገርህ፣ ሊመራህና ሰላም ሊሰጥህ ይችላል። «እግዚአብሔር በባዕድ ከንፈርና በልዩ ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል» ኢሳይያስ 28:11።

5. በልሳኖች መናገር ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ኅብረት እንድናደርግ ያስችለናል፦ በልሳኖች ስንናገር የመንፈስ ቅዱስን ቋንቋ እየተናገርን ነው። ከእርሱ ጋር የምንገናኝበትና ጥበቡን፣ ድፍረቱንና ግልጥነቱን የምንቀበልበት መንገድ ነው። ሁሉም በልሳኖች መናገር ያለበት ለዚህ ነው። በልሳኖች አዘውትረህ ስትናገር ፈጽሞ አትሸነፍም። ምን ማድረግ እንዳለብህ ታውቃለህ፤ በሰማይና በምድር አምላክም ትመራለህ፤ ይህም በትክክለኛው መንገድ ላይ እንድትጸና ያደርግሃል። ሃሌ ሉያ!

ገጽ 1 / 1 · 4 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል