ምዕራፍ 1 · 2 ደቂቃ ንባብ
የጸሎት መግቢያ
ጸሎት ምን እንደ ሆነ አስቀድመህ ካወቅህ ብቻ ነው እንዴት መጸለይ እንዳለብህ ልታውቅ የምትችለው!
ጸሎት ምንድን ነው፣ ሰዎች ለምን ይጸልያሉ፣ ወይም አንዳንዶች በሕይወታቸው ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ነገር እንደ ሆነ አድርገው ሁልጊዜ የሚጸልዩት ለምንድን ነው ብለህ አስበህ ታውቃለህ? እንዲህ ከሆነ ይህ መጽሐፍ ለአንተ ነው! ብዙ ሰዎች ስለ ጸሎት ተምረዋል፤ በተማሩትም ነገር ተባርከዋል። ሆኖም አንዳንዶች አሁንም ስለ ጸሎት ጥያቄዎች አሏቸው። ይህ መጽሐፍ ስለ ጸሎት ያሉትን ጥያቄዎች ሁሉ ባይሆን እንኳ አብዛኞቹን እንደሚመልስ አምናለሁ። እንግዲያውስ ለምን እንጠብቃለን? በቀጥታ እንግባ!
ጸሎት ምንድን ነው?
1. ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የማድረግና ከእርሱ ጋር አንድ የመሆን ክብርና መብት ነው። እዚህ ላይ አንድ መሆን ማለት አንድ ሰው በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ያለውን ማወቅና እግዚአብሔር የሚነግረውን ማድረግ መቻል ማለት ነው። በዚህ አንድነት የክርስቶስን ልብ ልታውቅ፣ እንደ ክርስቶስ ልትኖር፣ እንደ እርሱ ልታስብ፣ እርሱም ፍጹም እንደ ሆነ ፍጹም ልትሆን ትችላለህ። ጸሎት የሚያደርገው ይህንኑ ነው፤ በሕይወት ውስጥ በሚገጥምህ በማንኛውም ሁኔታ ምን ማድረግ እንዳለብህ ልታውቅ በምትችልበት በዚያ ኅብረት፣ ከእግዚአብሔር ጋር በዚያ አንድነት እንድትኖር ይረዳሃል። ይህ እንዴት ድንቅ ነው!
2. ጸሎት ባለ ሁለት መስመር መገናኛ ነው። እግዚአብሔር ይናገረናል፤ እኛም ደግሞ እርሱን የማናገር መብት ተሰጥቶናል።
ስለዚህ ጸሎት ጸልየን ትተን የምንሄድበት የአንድ ወገን መስመር ተደርጎ ፈጽሞ አይቆጠርም፤ ሊቆጠርም አይገባም። በፍጹም! እግዚአብሔርም ይናገራል፤ የጸሎት ብቸኛው ዓላማም ይኸው ነው፦ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር፣ እርሱን ይበልጥ ማወቅና ፈቃዱ ምን እንደ ሆነ መረዳት። በጸሎት ጊዜህ እግዚአብሔርም እንዲናገርህ ሆን ብለህ ቦታ ስጠው። ልቡንና ፈቃዱን የምታውቀው በዚህ መንገድ ነው።
ሃሌ ሉያ!
3. ጸሎት ደግሞ የግድ አስፈላጊ ነገር ነው። ሉቃስ 18:1 «ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው» ይላል። ይህ ልመና እንዳልሆነ ግልጥ ነው። መጽሐፉ ሰዎች ይጸልዩ ይሆናል፣ ሊጸልዩ ይፈቀድላቸዋል፣ ሊጸልዩ ይችላሉ ወይም ምናልባት ይጸልዩ ይሆናል አይልም። ይልቁንም ሳይታክቱ ሊጸልዩ እንዲገባቸው ይናገራል። ይህ ማለት ጸሎት የዕለት ተዕለት ኑሮህ ክፍል መሆን አለበት ማለት ነው፤ የጸሎት ጊዜያትም በቀንህ ውስጥ እጅግ አስደሳች ጊዜያት ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ልክ ባይሰማህም እንኳ እንደምትበላው ሁሉ ጸሎትም የአኗኗርህ መንገድ ይሁን።
ፍጹም ምሳሌ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ቢያውቅም፣ ኢየሱስ ለመጸለይ የሚያበቃ ትሕትና ነበረው። ይህንንም በሉቃስ 6:12 እናያለን፦ «በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ።»
ወዳጄ ሆይ፥ ለመጸለይ ፈጽሞ ሥራ አይብዛብህ፤ ከእንግዲህ መጸለይ የማያስፈልግህ ጊዜ እንዳለም ፈጽሞ አታስብ።
ጸሎት የአማኝ ሁሉ የሕይወት ትርታ ነው። ያለ ጸሎት ኢየሱስ እንዳደረገው ከእግዚአብሔር ጋር ልትነጋገር አትችልም። ያለ ጸሎት አብ ለሕይወትህ ያለው ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ላታውቅ ትችላለህ። ያለ ጸሎት በክርስቶስ ያለህን ሥልጣን ልትጠቀምበት የማይቻል ሊሆንብህ ይችላል። ይህ ማለት ሥልጣንን ይዞ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት ነገሮች እንዲፈጸሙ ማድረግ ማለት ነው። ደግሞም በሕይወትህ ያለውን የእግዚአብሔርን መገኘት ለማንቃትና ያንንም በመገንዘብ ለመመላለስ ልትቸገር ትችላለህ፤ በሚቀጥሉት ምዕራፎቻችን የምናብራራቸውም ሌሎች ብዙ ገጽታዎች አሉ።
ምዕራፍ 1 ተጠናቋል
የጸሎት መግቢያ