የዕለት ተዕለት ጉዟችን
ሴፕቴምበር

ምዕራፍ 9 · 42 ደቂቃ ንባብ · 54 ደቂቃ ማዳመጥ

ሴፕቴምበር

ሴፕቴምበር 1

ራስን መጠበቅ!

«ጠብቅ (ተከላከል) ልብህን ከምትጠብቀው ሁሉ አብልጠህ፤ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።»— ምሳሌ 4:23

ጴጥሮስ ጌታችንን፦ «ስለምትናገረው ስለዚህ ሞት ራስህን ራራለት፤ ይህ መራራ መከራና ጭንቀት ከቶ አይደርስብህም!» አለው።

እነዚህ ቃላት ዛሬም ያለማቋረጥ ይነገራሉ፤ ራሳችንን እንድንራራለት የሚያዝዙን ድምፆችም ብዙ ናቸው፤ የሚወዱን የወዳጆቻችን ድምፆች፣ የጥንቃቄና የዓለማዊ ጥበብ ድምፆች፣ የገዛ ዐመፀኛ ልባችን ድምፆች።

ራስህን በመፍረድ ራስህን አትራራለት። በሌሎች ላይ ብታየው አንተ ቀድመህ የምትኰንነውን ነገር ራስህ እንድታደርግ ከቶ አትፍቀድ። በባልንጀራህ ላይ በምንም ሁኔታ የማትታገሠውን በደል አንተ እንድትፈጽም የሚያበቁ ምክንያቶች እንዳሉ ከቶ አታስብ።

ኃጢአትህንና ስሕተትህን በመናዘዝ ራስህን አትራራለት። መናዘዝ የክቡር ልብ መፈተኛ አንዱ ነው። ለእግዚአብሔር ለመናዘዝ ፈቃደኞች ሆነው ለሰዎች ለመናዘዝ ፈጽሞ የማይሞክሩ ጥቂቶች አይደሉም። በደለኛውን አምላኩን ይቅርታ እንደሚለምን ሁሉ ባልንጀራውንም ይቅርታ እንዲጠይቅ የማያደርገው የኃጢአት ኀዘን እውነተኛና ጥልቅ መሆኑ አጠያያቂ ነው። ወንድማችን በእኛ ላይ አንዳች እንዳለው ባሰብን ጊዜ ሁሉ መባችንን በመሠዊያው ፊት ትተን አስቀድመን ከእርሱ ጋር ለመታረቅ እንድንሄድ፣ ከዚያም በኋላ መሥዋዕታችንን ለእግዚአብሔር እንድናቀርብ ከሚለው ከክርስቶስ ቃል የበለጠ ግልጽ ነገር የለም።

የመልካምነት ዋነኛው መፈተኛ በባሕርያችንና በአኗኗራችን ታላላቅ ሳይሆን ጥቃቅን በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ነው፤ በሕዝብ ፊት በደማቅ ብርሃን ስንመረመር ምን እንደ ሆንን ሳይሆን፣ ወደ ቤታችን የእሳት ምድጃ ብልጭታ ስንደርስ ምን እንደ ሆንን ነው፤ ለሕይወትና ለነጻነት እንድንዋጋ የሚጠራ የመለከት ድምፅ በአየር ላይ ሲያስተጋባ ምን እንደ ሆንን ሳይሆን፣ የጥበቃው እሳት እየከሰመ ሳለ በግራጫው ማለዳ ዘብ እንድንቆም ስንጠራ የምናሳየው ዝንባሌ ነው። ባሕርይ በዕለት ተዕለት አለመጣጣም፣ በታማኝነት ማጣትና በሚከብብ ኃጢአት ተበልቶና ዝጎ ከሆነ በታላቁ ሰዓት በተሻለ ሁኔታችን መገኘት አይቻልም።

ራስህን ሳትሰጥ ሰዎችን በእውነት ልትረዳ አትችልም። ፍሬ የሚያፈራ ብቸኛው ሥራ አንዳች የሚያስከፍልህ ነው። ወርቅ፣ ብርና የከበሩ ድንጋዮች ከገዛ ሕይወትህ ጎተራ ልታወጣቸው ፈቃደኛ ካልሆንህ በቀር በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ሕንጻ ውስጥ ከቶ ሊገቡ አይችሉም።

ጸሎት

እጅግ አፍቃሪ አባት ሆይ፥ ፍቅር ልቤን ይሙላው፤ ይግዛውም። ያን ጊዜ በአንተና በእኔ መካከል የባሕርይ መመሳሰልና የፈቃድ አንድነት ይበቅላል፤ ይጠበቃልም፤ ስለዚህም አንተ የምትመርጠውን እመርጣለሁ፤ አንተ የምትጥለውንም እጥላለሁ። አሜን።

ሴፕቴምበር 2

ስለ ነፍሳት መትጋት

«ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። ... ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው።»— ቆላስይስ 1:27, 28።

«ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።»— የሐዋርያት ሥራ 20:31

የማስጠንቀቅ አገልግሎት የቤተ ክርስቲያንና የእያንዳንዱ አባልዋ ሥራ እንደ ሆነ የታወቀ ክፍል ሊሆን ይገባዋል። የጭጋግ ጥሩምባ መርከቢቱን ከገዳዮቹ አለቶች ያስጠነቅቃል፤ ቀዩ መብራት ባቡሩን ከቀረበ አደጋ ያስጠነቅቃል፤ በቸነፈር ዘመን ሰዎች በሽታው ከገባባቸው ስፍራዎች እንዲርቁ ይጠነቀቁ ነበር፤ እንግዲያስ ክርስቶስን እምቢ በሚሉት ላይ የሚኖረውን የእግዚአብሔርን ቍጣ የምናውቅ እኛማ የማስጠንቀቂያ ድምፃችንን ልናሰማ እንዴት አብልጦ ይገባናል! ይህንንም ሆን ብለን፣ በትጋት፣ በትዕግሥትና ቃላችን ምንም ያህል ቢያስቆጣ ክፉውን ከመንገዱ ስሕተት የሚያቆም፣ በተከለከሉ ጎዳናዎች የመጀመሪያ እርምጃቸውን የሚወስዱትንም እንዳይገፉበት የሚመልስ መሣሪያ እንዲያደርገው በእግዚአብሔር መንፈስ በመታመን ልናደርገው ይገባል (ሕዝቅኤል 33:7, 8, 9)።

እግዚአብሔር ማስጠንቀቂያዎቹንና ልመናዎቹን እንዲያደርሱ መላእክትን አለማዘዙ እንዴት ድንቅ ነው! ይልቁንም መላእክት ሊያደርጉት የሚወድዱት ሥራ ለሰዎች ዐደራ ተሰጥቷል። በዚህ ረገድ ያሉንን አጋጣሚዎች ቸል ብንል ለራሳችን አደጋ ነው። ብዙ የባቡር ሐዲዶች በሚገናኙበት ወይም በሚለያዩበት ስፍራ የተመደበ የምልክት ሰጪ በሥራ ቦታው ቢተኛ ወይም ተግባሩን ቸል ቢል በሰው መግደል ወንጀል ሊከሰስ ይችላል፤ እኛም በቅርብ የተጽዕኖአችን ክበብ ውስጥ ያሉ ሰዎች አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ደኅንነታቸውን የማጥፋት አደጋ ላይ እንዳሉ ካወቅን የማስጠንቀቂያ ድምፅ ልናሰማ ግዴታ አለብን። በወንዝ ላይኛው ክፍል በሰዎች የተሞላች ጀልባ አደጋውን ሳታስተውል ወደ ፏፏቴው ስትጣደፍ ብናይ፣ ስለ ጥፋታቸው የሚያስጠነቅቃቸውን አንዳች ነገር ማድረግ ቢሳነን በእርግጥ በጥፋታቸው ተባባሪ በመሆን በደለኞች እንሆን ነበር።

ከማስጠንቀቂያ ቃላችን ጋር የእግዚአብሔር ፍቅር በግልጽ ደጋግሞ ሊነገር ይገባል። እርሱ የኃጢአተኛውን ሞት አይወድድም፤ ይልቁንም ከክፋቱ ተመልሶ በሕይወት እንዲኖር ይወድዳል። ሰዎችን የተሳሳተውን መንገድ ከመያዝ ለመከልከል መሞከር ብቻ አይበቃም፤ ደስ የሚያሰኙትን የጽድቅና የሰላም መንገዶች እንዲይዙ ልንማጸናቸውና ልንስባቸው ይገባናል። ሁሉም በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ተካትተዋል። ኃጢአት እንኳ ፍቅሩን ሊመልሰው አይችልም፤ ፍቅሩ በአባካኙ ልጅ ምሳሌ ወይም በ1ኛ ቆሮንቶስ 13:1-13 እንደ ተገለጸው ነውና።

ጸሎት

አምላክ ሆይ፥ ልናደርጋቸው የሚገቡንን ብዙ ነገሮች ሳናደርግ ቀርተናል። ለእርዳታ የተዘረጉ እጆች ነበሩ፤ እኛ ግን አልረዳናቸውም፤ ርኅራኄ ፍለጋ ወደ እኛ የዞሩ ልቦች ነበሩ፤ እኛ ግን አልባረክናቸውም። እንለምንሃለን፥ ይቅር በለን፤ የቱንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍለን ክርስቶስን በቤዛነት ዓላማው እንከተለው። አሜን።

ሴፕቴምበር 3

ሳይዘጋጁ የመገኘት ሞኝነት

«ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ።» — ማቴዎስ 25:10።

ሰነፎቹ ቈነጃጅት አምስት ታላላቅ ስሕተቶችን ሠሩ።

(1)ብርሃናቸው እንዲቀጥል ምንም ዝግጅት አላደረጉም። መብራቱን መያዝ ብቻ አይበቃም፤ እሳቱ የሚመገበው ነገር ስላለ መብራቱ ሊበራና ሊጠበቅ ይገባዋል። በሃይማኖታዊ ሕይወታቸው የመጀመሪያ ደረጃ በእሳት የነደዱና የተጉ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የተቀጣጠለውን ነበልባል ለማቆየት ምንም ዝግጅት ያላደረጉ ስንት ናቸው! መብራቶች አሏቸው፤ ዘይት መያዝን ግን ቸል ብለዋል። ዘይቱ ከጌታ ኢየሱስ ጋር ያለውን ኅብረት፣ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ፣ የዕለት ተዕለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን፣ ከክርስቲያን ወንድሞችና እኅቶች ጋር ልብን የሚያቀጣጥለውን የአምልኮ ኅብረት ያመለክታል።

(2)ተኙ። በሰነፎቹና በልባሞቹ እንቅልፍ መካከል ልዩነት ነበር። ሁለት ዓይነት እንቅልፍ አለ። አንዱ ከደኅንነት ስሜትና ከመታመን ይመነጫል። ዝግጅት ሁሉ ተደርጓል፤ ሊደረግ የሚቻለውም ሁሉ ተደርጓል፤ እኛም ሆን ብለን ራሳችንን ለእግዚአብሔር ጥበቃ እንሰጣለን። ጴጥሮስ መልአኩ ሊያድነው ከመምጣቱ በፊት በወኅኒ ውስጥ እንዲሁ ተኝቶ ነበር። ነገር ግን ሌላ ዓይነት እንቅልፍም አለ። ጠላት በመተላለፊያው ሾልኮ ሲወጣ የዘበኛው እንቅልፍ፤ መርከቢቱ ወደ አለቶቹ የተደረደሩ ጥርሶች ስታመራ የመርከብ መሪው እንቅልፍ፤ የበሽተኛው ሕይወት በሚዛን ላይ ሲንቀጠቀጥ የአስታማሚዋ እንቅልፍ። እነዚህ ሰነፎች ሙሽራውን ለመቀበል ፈጽሞ ሳይዘጋጁ ሳሉ የመተኛት መብት አልነበራቸውም። ነገሮችን እንደ ተረጋገጡ አድርገን መቍጠር ወይም «ሰላም ሳይኖር፦ ሰላም፥ ሰላም!» ማለት የለብንም።

(3) ከልባሞቹ ዘይት ማግኘት እንደሚችሉ አሰቡ። ነገር ግን ልመናው ከንቱ ሆነ። እያንዳንዱ በእግዚአብሔር ፊት የኃላፊነቱን ሸክም ራሱ ሊሸከም ይገባዋል። «ያለ ገንዘብና ያለ ዋጋ» ልንገዛ እንችላለን፤ ነገር ግን እያንዳንዱ የኢየሱስን ሕያው ጸጋና ኃይል ለራሱ ገንዘብ ሊያደርግ ይገባዋል።

(4)መግባት እንደሚችሉ አሰቡ፤ «ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን!» ነገር ግን ደጁ ፈጽሞ በማይከፈትበት ሁኔታ ተዘግቶ ነበር! «እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን?»

(5)ሙሽራው እንደሚያውቃቸው አሰቡ። እርሱ ግን፦ «አላውቃችሁም» አለ። እያንዳንዱ ራሱን፦ «ኢየሱስ ያውቀኛልን? በመጨረሻ ያውቀኝ ይሆን?» ብሎ ይጠይቅ። እርግጠኛ ለመሆን ብቸኛው መንገድ በመንፈስ ቅዱስ እስኪያትመንና፦ «ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ» እስኪለን ድረስ በመስቀሉ እግር ሥር መንበርከክ ነው።

ጸሎት

ጌታ ሆይ፥ ሕይወታችን አንተ ዘይት የምትሰጣቸው መብራቶች እንዲሆኑ እንለምንሃለን። ለዚህ ጨለማ ዓለም የሚነዱና የሚያበሩ መብራቶች እንድንሆን እርዳን። አሜን።

ሴፕቴምበር 4

ስንዴና እንክርዳድ

«ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ።»— ማቴዎስ 13:25።

ጌታችን የሰይጣንን አካላዊ ማንነት እንዴት በግልጽ አስተማረ! ይህን ምሳሌ ሲተረጕም፦ «የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው» ብሎ በግልጽ ተናገረ። በልብ ሁሉ ውስጥ፣ በዓለም እንዳለ ሁሉ በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ፣ የእግዚአብሔር መንግሥትና የሰው ደስታ ታላቁ ጠላት እንክርዳድን እየዘራ ዘወትር እንደሚሠራ ያውቅ ነበር። ዘሩ እጅግ ትንሽ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በአንድ ሌሊት ብቻ የማይጠገን ጉዳት ሊደርስ ይችላል።

የምንቀበለውን ዘር እንደምንመስል አስተውሉ፤ የስንዴውን ዘር የሚቀበሉ ስንዴ ይሆናሉ፤ የእንክርዳዱን ዘር የሚቀበሉ እንክርዳድ ይሆናሉ። «ሰው በልቡ እንደሚያስብ እንዲሁ ነው።» በምናነባቸው መጻሕፍት፣ በምንመሠርተው ጓደኝነትና ወዳጅነት፣ በምንሳተፍባቸውም መዝናኛዎች ምንኛ ልንጠነቀቅ ይገባናል! ባሕርያችን የሚቀረጽባቸው ሂደቶች ከእነዚህ መካከል ናቸው። የማናስብና ግድ የለሾች ከሆንን ወደ አረምና ቆሻሻ የሚበቅለውን የእንክርዳድ ዘር ለመቀበል ራሳችንን እናጋልጣለን። እርግጥ ነው፣ አስፈላጊ ተግባሮቻችን ክፋት ወደ በዛባቸው ስፍራዎች ቢወስዱን የክርስቶስን የመጠበቅ ኃይል ልንጠይቅና ራሳችንን በእርሱ ውስጥ ልንሰውር እንችላለን። ሐኪም ወይም አስታማሚ ቸነፈር ወይም ትኵሳት ወደ ገባበት ቤት ሲጠሩ ራሳቸውን በበሽታ ማጥፊያ መድኃኒት እንደሚያጠግቡ፣ እንዲሁ ነፍሳችንን በእርሱ ውስጥ ልናጥብ የምንችለው መንፈስ ቅዱስ እንደ ፀረ ተሕዋስ መድኃኒት ይሆናል፤ ከፈተና ጀርሞችም ያድነናል (ገላትያ 5:16, 17)።

በዕድገት መጀመሪያ ደረጃዎች በስንዴና በእንክርዳድ መካከል ብዙም ልዩነት እንደሌለ ይነገራል፤ ልዩነቱ በግልጽ የሚለይ መከሩ ሲደርስ ብቻ ነው። እንዲሁም በቤተ ክርስቲያንና በዓለም ብዙ ሐሰተኞች አሉ፤ ደጎችና እውነተኞች የሚመስሉ ሰዎች፣ ነገር ግን የሚመስሉትን ያልሆኑ፣ በሒሳብ ቀንም እንደ ቆሻሻ ተነቅለው የሚጣሉ። በመጨረሻ የሚጣሉት ሁለቱ ወገኖች «እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን» ናቸው (ማቴዎስ 13:41, የተሻሻለው ትርጉም)። ምናልባት ግልጽ በሆነ በየትኛውም ዓይነት ዓመፃን ከሚያደርጉት መካከል አትሆን ይሆናል፤ ነገር ግን በማይጣጣም ጠባይህ ወይም በዓለማዊነትህ ሌሎችን እያሰናከልህ ነውን? እያንዳንዳችን ራሳችንን በጥንቃቄ እንመርምር፤ ጌታ ኢየሱስ በቃሉ ሊተክለው የሚጠብቀውንም የማይጠፋውን ዘር ከእጁ ለመቀበል ልባችንን እንክፈት።

ጸሎት

ጌታ ሆይ፥ በማንኛውም ስሕተት እንዳንታለልና እንዳንወሰድ የቃልህን ንጹሕ ፍርድና እውነተኛ ማስተዋል ስጠን፤ ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እንድናድግ ስጠን። አሜን።

ሴፕቴምበር 5

የሚያበሩ ብርሃናት

«ያለ ነቀፋና ያለ ተንኰል እንድትሆኑ፥ በጠማማና በተጣመመ ትውልድ መካከል ነውር የሌለባችሁ የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ፥ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ።»— ፊልጵስዩስ 2:15, 16 (የተሻሻለው ትርጉም)።

ጠቢቡ ሰው እንደሚለው፣ የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ነው (ምሳሌ 20:27)። በተፈጥሮአችን እንዳልበሩ ብዙ መብራቶችና ሻማዎች ነን። ክሩ ለነበልባሉ የተዘጋጀ ቢሆንም እስኪቀጣጠል ድረስ ጨለማና ቀዝቃዛ ሆኖ እንደሚቆም፣ እንዲሁ እኛም «ብርሃን የሆነውና ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የሌለው» ከእርሱ ዘላለማዊ ባሕርይ ባሕርያችን እስኪቀጣጠል ድረስ ምንም ብርሃን ልንሰጥ አንችልም። የሕይወትህ ሻማ የጽድቅ ፀሐይ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር በመገናኘት በርቷልን?

ጌታችን፦ «ብርሃናችሁ ... በሰው ፊት ይብራ» ይላል። መብራትን አብርቶ በዕንቅብ ሥር በማስቀመጥ ጨረሩን መሰወር ምን ያህል ከንቱ እንደ ሆነ ያሳያል። ብርሃኑ ከተሸፈነ የማብራቱ ዓላማ ይከሽፋል። ወዮ! ስንቶቻችን ለእግዚአብሔር በምንሰጠው ምስክርነት ብርሃን ላይ ዕንቅብ እንደፋለን፤ የፍቅር የጐደለው ንግግር ዕንቅብ! የቍጡ ጠባይ ዕንቅብ! የማያመሰግንና የሚያጕረመርም መንፈስ ዕንቅብ! እነዚህም ይበልጥ ጎልተው ከሚታዩ ጕድለቶች ጋር በጨለማ ዓለም ውስጥ እንደ ብርሃን እንዳናበራ ይከለክሉናል። ነበልባሉን ማቀጣጠል ወይም ዘይቱን ማቅረብ የእኛ ድርሻ አይደለም። እኛ ማድረግ ያለብን መብራቶቻችንን ንጹሕና ብሩህ አድርጎ መጠበቅ፣ የእግዚአብሔር ፍቅርና ሕይወት በነፍስ በኩል እንዳያበራ ሊያግድ ከሚችል ነገር ሁሉ መጠንቀቅ ብቻ ነው። የምስክርነታችንን ውጤት ሊያደናቅፍና ተጽዕኖአችንን ሊያበላሽ የሚችል ነገር ሁሉ መወገዱን በጥንቃቄ ብናረጋግጥ፣ ብርሃናችን የዓላማውን ሙሉ መጠን እንዲፈጽም ክርስቶስ ራሱ ይጠነቀቅበታል።

ከዕንቅቡ በተቃራኒ መቆሚያው ወይም መቅረዙ አለ። የቤቱ ጌታ እጅግ ትንሽ በሆነ ጨለማ ማዕዘን፣ እጅግ ዝቅ ባለ መቆሚያም ላይ ሊያኖርህ ይችላል፤ ነገር ግን አንድ ቀን በዚያ ሲያልፍ፣ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን ሲወጣ እርምጃዎቹን ታበራለታለህ። መቆሚያህ ምንድር ነው? በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለህ ስፍራ፣ በቤት ውስጥ ያለህ ቦታ፣ በአንድ የንግድ ድርጅት፣ ፋብሪካ ወይም ትምህርት ቤት ያለህ ሥራ ነውን? የትም ቢሆን ግድ የለውም፤ ብርሃንህ የተረጋጋና ጥርት ያለ ሆኖ እያበራ፣ ወንዶችንና ሴቶችን እያስጠነቀቀና በሕይወት መንገድ እየመራ እስካለ ድረስ በቂ ነው።

ጸሎት

ክርስቶስ ሆይ፥ የመለኮታዊ ፍቅርህ እሳት ዕንቅቦቻችንን ያቃጥል፤ በዚህ ጨለማ ዓለም ውስጥ እንደ ብርሃን እንድናበራ እርዳን። አሜን።

ሴፕቴምበር 6

ለአጭር እይታ የሚሆን መድኃኒት

«እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና፤ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል።»— 2ኛ ጴጥሮስ 1:8,9 (የተሻሻለው ትርጉም)።

እኛ ልንጨምራቸው የሚገቡን የክርስቲያን በጎ ባሕርያት በሐዋርያው አእምሮ ፊት በእምነት የሚጀምርና በፍቅር የሚፈጸም የሰንሰለት ወይም የአንገት ጌጥ የወርቅ ቀለበቶች ሆነው ይታያሉ፤ ስለዚህም እምነትና ፍቅር በመካከል ይያያዛሉ (2ኛ ጴጥሮስ 1:5, 6, 7)።

«ጨምሩ» ተብሎ ከተተረጐመው ቃል ጋር እዚህ በልግስና ገንዘብን የማውጣት ሐሳብ ተያይዟል (2ኛ ጴጥሮስ 1:5, 6, 7, 8, 9, 10, 11)። ከጥንት የግሪክ ልማዶች መካከል ታላላቅ ዜጎች ለበጎ አድራጊዎች ወይም ከጦርነት በድል ለሚመለሱ የጦር አለቆች ክብር ሕዝባዊ ግብዣዎችንና ትርኢቶችን በማዘጋጀት ለኅብረተሰቡ በጎ ፈቃዳቸውን የሚገልጹበት ልማድ ነበር። በዘመናችን ሰዎች ለሆስፒታሎችና ለቤተ መጻሕፍት ገንዘብ እንደሚለግሱ፣ ባለ ጠጎችም ወጪውን ለመሸፈን ፈቃድ ይለምኑ ነበር።

ስለዚህ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፦ «እነዚህን ነገሮች» በክብር በማዘጋጀት ምንም ወጪ እንዳትቈጥቡ ተጠንቀቁ፤ እነዚህ የክርስቲያን በጎ ባሕርያት በእናንተ ውስጥ ሆነው እስኪበዙ ድረስ ሐሳብንም ድካምንም አትቈጥቡ። ያን ጊዜ ለእናንተም የሰማያዊ አቀባበል የተትረፈረፈ ልግስና ይጠብቃችኋል። ወደ ሰማያዊቱ ከተማ ሳትታወቁና ብቻችሁን አትገቡም። በዝማሬና በሰልፍ የሚደረግ አቀባበል የእናንተ ይሆናል። ውኃ እንደ ሞላባት መርከብ ሳይሆን ሰንደቃላማ እያውለበለበና ሸራዎቹ ሁሉ ተዘርግተው ወደ ወደቡ ትገባላችሁ! (2ኛ ጴጥሮስ 1:11።)

የእነዚህን በጎ ባሕርያት ቅደም ተከተል አስተውሉ። እያንዳንዳቸው በውስጣቸው የሚገጥሙ ብዙ ትናንሽ ሣጥኖችን እንደሚይዙት እንደ እነዚያ የቻይና ሣጥኖች አንዱ በሌላው ውስጥ ነው። «እምነት» የሚል ምልክት ያለበትን ስትከፍቱ የወንድነት ድፍረት ሊገኝ ይገባል፤ ድፍረትን ስትከፍቱ እውቀት ሊገለጥ ይገባል፤ ከእውቀት ወደ ራስን መግዛት ልንደርስ ይገባል፤ በራስን መግዛት ውስጥ ትዕግሥት ሊኖር ይገባል፤ በሰዎች ፊት በምናሳየው ትዕግሥት ውስጥ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር የሚሆን እግዚአብሔርን መምሰል ሊኖር ይገባል፤ ከዚያም የወንድማማች መዋደድን እናገኛለን፤ በመጨረሻም ወደ ፍቅር እንደርሳለን!

ሐዋርያው «እነዚህ ነገሮች» የሌሉአቸው አጭር እይታ ያላቸው እንደ ሆኑ ይናገራል፤ የዚህን ዓለም ነገሮች ብቻ ያያሉ እንጂ የዘላለምን እውነተኛ ነገሮች አያዩም። አሥረኛው ቍጥር እነዚህን ነገሮች በልብ ውስጥ በጥንቃቄ ማልማት በውጫዊ ሕይወት መሰናከልን እንደሚከላከል ያስጠነቅቀናል (ይሁዳ 1:20-24)። ብዙ ሰዎች መልካምነትን ከማድረጋቸው በፊት መልካም ስሜት እስኪሰማቸው ይጠብቃሉ። መለኮታዊው መንገድ ግን አስፈላጊውን ጸጋ እንደሚሰጥ በማመን ለክርስቶስ በመታዘዝ ጎዳና ላይ ወደ ፊት መራመድ ነው።

ጸሎት

እጅግ መሐሪ አባት ሆይ፥ ራሳችንን፣ ሥጋችንን፣ ነፍሳችንንና መንፈሳችንን ለአንተ የምናቀርብበትን ይህን የታደሰ መሰጠት ተቀበል። እንደ ኢየሱስ ንጹሓንና ያልረከሱ፣ የዋሆችና ገሮች፣ ሰላማውያን፣ ታጋሾች፣ ረኪዎችና አመስጋኞች እንድንሆን ስጠን። አሜን።

ሴፕቴምበር 7

በመርከቡ ፊት ቁም!

«በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ ... ምልክትን እፈጥናለሁ።»— ፊልጵስዩስ 3:13, 14

ሁልጊዜ በመርከቡ ፊት ቁም! ወደ ኋላ የሚመለከተውን የመርከቡን ጀርባ ትተህ ወደ ፊቱ ሂድ። ያለፉትን ኃጢአቶችና ውድቀቶች በኀዘን በመከለስ ጊዜን ማሳለፍ በተሻለ መንገድ መጠቀም አይደለም። ተናዘዛቸው፤ ስለ ውዱ ክርስቶስ ብለውም ፈጽመው ይቅር እንደ ተባሉ እመን! ውድቀት ብዙ ጊዜ ለስኬት መሣሪያ ይሆናል፤ የሞቱት የቀድሞ ማንነቶቻችንም ወደ ተሻሉ ነገሮች የሚያደርሱ መረማመጃ ድንጋዮች ሊሆኑ ይችላሉ። ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን፦ «እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም» አላላቸውምን? ያለፈው ሊጠገን አይችልም፤ ነገር ግን ወዲያውኑ፦ «ተነሡ፥ እንሂድ!» ብሎ ጨመረ፤ መጪው ጊዜ በእጃችን ነው። ስለዚህ ወደ ኋላ የሚመለከተውን የመርከቡን ጀርባ ትተህ ወደ ፊቱ ሂድ።

እርግጥ ነው፣ በፊታችን ያለው ሰማይ በማዕበል ደመናዎች ሊጨልም ይችላል። የአየር ጠባይ ነቢያት ዓለም የቀድሞ መሠረቶቿን በተሻሉ ሳትተካ እየጣለች እንደ ሆነች፣ ሰባት ሥልጣኔዎች አስቀድመው እንዳለፉና የስምንተኛውን ሞት ልናይ እንደ ሆነ ይናገራሉ። ይሁን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚናወጡትን ውኆች በእጁ ጕድጓድ እንደሚይዝ፣ ኢየሱስም ወዳጆቹን ለመርዳት በሚያስፈራሩ ማዕበሎች ላይ እንደ ተራመደ ይረሳሉ። ምድር ቅርጽ የሌላትና ባዶ በነበረች ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በትርምሱና በጨለማው ላይ እንደ ሰፈፈ፣ ሰማያትንና ምድርንም እንደ ፈጠረ ይረሳሉ። የፈጣሪውን፦ «እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ!» የሚለውን ድምፅ መለየት አይችሉም። ከትርምስ ሥርዓት ያለው ዓለም ይወለዳል። እያንዳንዱ ዘመን በምጥ ይፈጸማል፤ ከዚያም አዲስ ዘመን ይወለዳል።

ወደ ሰፊው የአድማስ ክበብ ተመልከት፤ ለሚመረመሩት አዳዲስ አገሮች፣ ለሚጠብቁን ድንቅ ግኝቶች፣ በመጪው ጊዜ ውስጥ ተሰውረው ሊፈጸሙ ለሚጠባበቁት ታላላቅ ተልእኮዎች ተዘጋጅ። ደመናዎቹ እንደሚገፈፉ ከቶ አትጠራጠር። ክፋት እንደሚያሸንፍ ከቶ አታስብ። ራስህን እግዚአብሔር የተወው ወይም የረሳው አድርገህ ከቶ አትቍጠር። ጌታ ምንም ሳያስተውልና ግድ ሳይለው በትራሱ ላይ የተኛ ሊመስል ይችላል፤ እጁ ግን በመሪው ላይ ነው። አካሄድህን ይመራል። ማዕበሎችን ይገዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል።

ጸሎት

ዐውሎ ነፋሱን ጸጥታ ያደርጋል፤ ማዕበሎቹም ጸጥ ይላሉ። ጸጥ በማለታቸውም ደስ ይላቸዋል፤ ወደሚፈልጉትም ወደብ ያደርሳቸዋል። ሰዎች ስለ ቸርነቱ እግዚአብሔርን ቢያመሰግኑት ምንኛ መልካም ነበር! አሜን።

ሴፕቴምበር 8

መጽሐፍ ቅዱስን ለአምልኮ መጠቀም

«ቃልህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴም ብርሃን ነው።» — መዝሙር 119:105።

በመዝሙር 119 በእያንዳንዱ ቍጥር ውስጥ፣ ከአንዱ በቀር፣ መዝሙረኛው ቅዱሳት መጻሕፍትን ይጠቅሳል፤ ጌታችንና ሐዋርያቱም ብሉይ ኪዳንን ዘወትር መጥቀሳቸው በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ከጻፉትና ከተናገሩት ካለፉት ዘመናት ቅዱሳን ሰዎች ጋር የፍቅርና የአክብሮት ኅብረት እንደ ነበራቸው የተትረፈረፈ ማስረጃ ይሰጣል። ጌታ ኢየሱስ በፈተናው፣ በትምህርቱ ሁሉና በመስቀሉ ጣር ውስጥ በብሉይ ኪዳን ቅዱሳን በኩል ለተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ልዩ ሥልጣን ዘወትር መመስከሩ በተለይ የሚደንቅ ነው።

መዝሙረኛው እንደሚለው፣ እግዚአብሔርን በሦስት ዓይነት መገለጥ ልናውቀው እንችላለን። ሰማያት የሚሰማ ድምፅ ወይም ቋንቋ ባይኖራቸውም የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ እልፍ አእላፋት ከዋክብት ያጌጡት የጠፈር ጠፈርም የእጁን ሥራ ያወራል። ንግግር ባይኖራቸውም ቃላቸው እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለእርሱ ይመሰክራል።

የዚህ ታላቅ መዝሙር የመጨረሻው ክፍል እግዚአብሔር በሥነ ምግባራዊ ተፈጥሮአችን አሠራርና አመራር ውስጥ ያለውን የእጁን ሥራ ይገልጣል። በእነዚህ የወርቅ ማያያዣዎች መካከል መዝሙረኛው ቅዱሳት መጻሕፍትን በአሥር አስደናቂ ምሳሌዎች ያወድሳል፤ ከእነርሱም በአንዱ ክልል ውስጥ የማይገባ ጠባይ በእውነት ያልተለመደ መሆን አለበት። መታደስ የሚያስፈልጋት ነፍስ፣ ጠቢብ ለመሆን የሚሻ አላዋቂ፣ ደስ ሊለው የሚሻ ያዘነ ልብ፣ ሊበሩ የሚሹ ዓይኖች፣ የእውነትን ወርቅ የምትናፍቅ ነፍስ፣ የቅንነትና የእውነተኛነት ፍላጎት፣ የማስተዋልና የጽድቅ ፍለጋ፤ እነዚህ ሁሉና ሌሎችም ብዙ ፍላጎቶች ቅዱሱን መጽሐፍ በአምልኮ መንፈስ በማንበብ ይሟላሉ።

ለረጅም ዘመናት ትኩስና መዓዛማ ሆነው የቆዩ ታላላቅ አገልግሎቶች ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰወረውን የማያልቅ ትምህርትና መነሣሣት ብልጽግና አረጋግጠዋል። እያንዳንዳችን ወደ ጸሎት ከመዞራችን በፊት ራሳችንን በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ለመዘፈቅ እንወስን፤ የውኃ መሳቢያውን ቈዳ ለማርጠብ የሚፈስስ ውኃ ውኃውን ወደ ላይ ለመሳብ እንደሚረዳ ነውና።

ጸሎት

የመነሣሣት ብፁዕ መንፈስ ሆይ፥ ለበጎ ሥራ ሁሉ ፈጽመን እንድንዘጋጅ፣ ሌሎችንም ወደ ተሰወሩት ሀብቶቹ እውነተኛ ማስተዋልና ፍቅር ለመምራት እንድንችል ቃሎችህን እንድናነብ፣ እንድናስተውል፣ እንድንማርና በውስጣችን እንድናጣጥም አስተምረን። አሜን።

ሴፕቴምበር 9

ባርኩ!

«በክፉዎች ምክር ያልሄደ ... ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ የሚለው ሰው ብፁዕ ነው።»— መዝሙር 1:1, 2።

የዚህ የመጀመሪያው መዝሙር ጭብጥ የእግዚአብሔር አእምሮና ፈቃድ ቅጂ የሆነውን «ሕጉን» የመጠበቅ ብፅዕና ነው። ዳዊት እርሱን ከማወደስ ፈጽሞ አልደከመም፦ «ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ መጫወቻዬ ነው!»

ዛሬ ሁላችንም የሚያስፈልገን ለእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዛት የጋለ ፍቅር ነው። ለመማር ልበ ገርነትና ለመፈጸም እምነት ልባችን ንጹሕና እንደ ሕፃን ሆኖ የሚጠበቅባቸው፣ መጽሐፍ ቅዱስንም፣ ተፈጥሮንም፣ የሰውንም ሕይወት የምናስተውልባቸው ሁለቱ ባሕርያት ናቸው። ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝን በውስጡ የያዘው የመዝሙር መጽሐፍ በ«ብፁዕ» መጀመሩና በ«ሃሌ ሉያ» መፈጸሙ ተገቢ ነው!

እዚህ በመጀመሪያ የታማኝና የእውነተኛ ነፍስ «አይሆንም» ባዮች አሉ። በክፉዎች ምክር ለመሄድ እምቢ ካልን በፌዘኞች ወንበር ከቶ አንቀመጥም። ነገር ግን ቅጥር ከኋላው የሚያድገውን ተክል እንደሚጠብቅ፣ እነዚህ አሉታዊ ነገሮች በዋናነት የሚጠቅሙት ለአዎንታዊው በማገዛቸው ነው። የዛፉ ሥሮች ከወንዙ ለመጠጣት ከአፈሩ በታች እንደሚሳቡ፣ ሃይማኖታዊ ሕይወታችንም ከተሰወሩ ምንጮች ሊመገብ ይገባዋል (መዝሙር 1:3)። እንዲህ ያለው ሕይወት ፍሬያማና ውብ ይሆናል። በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ ስለሚኖርም የተከናወነ ነው። በክፉ ነገር በእውነት ሊጐዳ አይችልም፤ በጥልቁ ትርጕምም እግዚአብሔር የላከበትን ዓላማ ይፈጽማል።

ለእግዚአብሔር ፈቃድ አክብሮትንና መታዘዝን እምቢ የሚል ሕይወት ሁሉ በሚያበጥረው ነፋስ የሚበተነውን ሥር የሌለውን፣ ፍሬ የሌለውንና ሕይወት የሌለውን ገለባ መምሰሉ አይቀርም።

ሕይወትህ የቱን ዓይነት ይመስላል? ውበትንና ፍሬን ለብዙዎችም መጠለያን የሚሰጥ በጥልቅ ሥር የሰደደ ዛፍ ነህን? ወይስ ሕይወትህ እንደ ከንቱ ገለባ እየባከነ ነው?

ጸሎት

የእውነት መንፈስ ሆይ፥ ነፍሴ ዘወትር እንድትበለጽግ፣ ለክብርህና ለምስጋናህም በበጎ ቃልና ሥራ ሁሉ እንድበዛ የቃልህን ሀብቶች ክፈትልኝ፤ እለምንሃለሁ። አሜን።

ሴፕቴምበር 10

የክርስቶስ ሰብአዊነት የሚስበው ኃይል

«ብዙ ሕዝብም ተከተሉት።»— ማቴዎስ 19:2።

«ሁሉ ይፈልጉሃል!»— ማርቆስ 1:37።

በአንድ ጊዜ በሮማውያን ቲያትር ቤት ተነግሮ በነጐድጓድ ጭብጨባ የተቀበለው አንድ ዓረፍተ ነገር ስለ ሰው ልጅ በተትረፈረፈ ሁኔታ እውነት ነበር፦ «እኔ ሰው ነኝ፤ ሰብአዊነትን የሚነካ ማንኛውም ነገር ለእኔ ባዕድ አይደለም።» ይህ በምድራዊ ሕይወቱ ዘመን እውነት ነበር፤ ዘወትርም እውነት ነው፤ ለዚህም በወንጌል ታሪክ ውስጥ በቂ ምሳሌ አለን።

ጌታችን ባልና ሚስትን በቅዱስ ጋብቻ ሲኖሩ ይባርካቸዋል፤ ልጆቻቸውን በእቅፉ ይይዛል፤ ወጣት ወንዶችንና ሴቶችን ከፍ ባሉ ዓላማዎች ያነሣሣል፤ ሰዎችን ስለ ሀብትና ሥልጣን ክፉ አጠቃቀም ያስጠነቅቃል፤ ስለ እርሱ ብለው የቤት ሕይወትን፣ የወላጆችንና የልጆችን ደስታ ራሳቸውን እየካዱ በዚህ ሕይወት ለማለፍ ፈቃደኞች ለሆኑት ወሰን በሌለው ሁኔታ እንደሚካሱ ተስፋ ይሰጣል።

ኢየሱስ ሊካፈለው ፈቃደኛ ያልሆነው የሰው ሕይወት ገጽታ የለም፤ በግንኙነቶችና በሁኔታዎች ሁሉ ውስጥ የፍጹም ፍቅርን መዓዛ ሊተነፍስ ይጠብቃል። ይህ ሁላችንም የሚያስፈልገን፣ ነገር ግን ብዙዎች የሚያጡት በረከት አይደለምን? ብዙ ትዳሮች ለምን ይበላሻሉ? ብዙ ጊዜ እያንዳንዱ ከመስጠት ይልቅ ለማግኘት፣ ከማገልገል ይልቅ ለመገልገል ስለሚሻ አይደለምን? እያንዳንዱ ሌላውን የሐሳቡ፣ የእንክብካቤውና የርኅራኄው ማዕከል በሚያደርግ ፍቅር ቢነሣሣ፣ የሰርጉ ደወሎች በሚያልፉት ዓመታት ሁሉ መደወላቸውን ይቀጥሉ ነበር።

የክርስቶስ ፍቅር እጅግ የሚስብ ስለ ሆነ እርሱ በትክክል ሲቀርብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች አበቦች ወደ ፀሐይ እንደሚዞሩ ወደ እርሱ ይዞራሉ። ወዮ! በክፉ ምሳሌአችንና በውድቀታችን ብዙ ጊዜ እንከለክላቸዋለን። ለፍቅሩ ያለን አድናቆትና ምላሽ ምንኛ ደካማ ነው! የሥነ ምግባራዊና የተከበረ ሕይወት ትእዛዛትን ስለሚስማማንና ደስ ስለሚያሰኘን ለመጠበቅ ፈቃደኞች ነን፤ እርሱን ወደ መከተልና ስለ ውድ ስሙ ሀብትን፣ ማዕረግንና ራስን ማስደሰትን ወደ መተው ሲደርስ ግን ወደ ኋላ እንመለሳለን! ዓላማዎቹንና ትምህርቱን እናደንቃለን፤ ነገር ግን ከእርሱ ይልቅ ራሳችንን በእውነት ስለምንወድድ ብዙ ጊዜ እያዘንን እንሄዳለን!

ጸሎት

ከሰማየ ሰማያት ከፍ ያለው፣

ከጥልቁ ባሕር የጠለቀው፣

ጌታ ሆይ፥ ፍቅርህ በመጨረሻ አሸንፏል፤

አሁን የነፍሴን ልመና ስጠኝ፦

ከራሴ ምንም፣ ከአንተ ግን ሁሉ። አሜን።

ሴፕቴምበር 11

መለያው መስመር

«ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም?»— ማቴዎስ 25:44።

ጌታችን በሥጋ በነበረበት ዘመን ሰዎች ከገንዘባቸው እንዳገለገሉት እኛ ዛሬ ልናገለግለው አንችልም። ነገር ግን ወኪሎቹን ትቶልናል፤ ለእነርሱ የምናደርገውንም ሁሉ ለራሱ እንደ ተደረገ አድርጎ ይቀበለዋል። ስለዚህ ለሰዎች ሁሉ ባለ ዕዳዎች ነን፤ ለሰው ልጅ ካለብን ወሰን የሌለው ዕዳ የተወሰነውን ድርሻ ለእያንዳንዱ የሰው ዘር አባል መክፈል ይገባናል (ማቴዎስ 1:14)።

ከዚህ በኋላ የሚለየው መስመር የእምነት መግለጫ መስመር አይሆንም፤ «ምን ያህል ታምናለህ?» አይደለም። የአምልኮ መስመርም አይሆንም፤ «ምን ያህል ጸለይህ?» አይደለም። ይልቁንም የተግባር መስመር ነው፤ «ምን አደረግህ?» ነው። ሐዋርያው ያዕቆብ እምነታችን በሥራችን እንደሚገለጥ ያሳያል (ያዕቆብ 2:14-20)። «ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ» ማለት ብቻ በቂ አይደለም። ባልንጀሮቻችንን በመውደድ የጌታችንን መንፈስ ማሳየት አለብን፤ አለዚያ በመጨረሻው ቀን እንጣላለን።

የጌታ ወንድሞች በዓለም ሁሉ ተሰራጭተዋል። የተራበውንና የተጠማውን፣ እንግዳውንና ቤት አልባውን፣ የታመመውን ወይም የታሰረውን ነፍስ ባገኘን ቁጥር እርሱ «ወንድሜ» ወይም «እኅቴ» ብሎ የሚጠራውን ሰው እናገኛለን፤ ከእነዚህ አንዱን መርዳትም በአዳኛችን ነፍስ ውስጥ የደስታ ስሜት እንዲያልፍ ማድረግ ነው። ጌታችን የሚለብሳቸውን ብዙ ዓይነት መሸፈኛዎች ዘልቀው የሚያዩ ፈጣን የፍቅር ዓይኖች ሊኖሩን ይገባል። ቅዱስ ፍራንሲስ በአንድ ሜዳ ላይ በፈረስ እየሄደ ሳለ በመንገድ ዳር ቆሞ ምጽዋት የሚለምን አንድ ለምጻም አየ ይባላል። ከፈረሱም ወርዶ ምጽዋት መስጠት ብቻ ሳይሆን ጉንጩን ሳመው። ሲሄድም ወደ ኋላ ዞር ብሎ ሲመለከት ለማኙ በቆመበት ስፍራ ክርስቶስ ራሱ ቆሞ አየ፤ ጌታውን ለመሳም እንደ ተፈቀደለትም አወቀ።

ቅዱሳን በአብዛኛው ለክርስቶስ በቀጥታ አንዳች እንዳደረጉ እንደማይገነዘቡ አስተውሉ፤ «ጌታ ሆይ፥ መቼ አየንህ?» ይላሉ። የልጅነት ውበት ራሱን አለማወቁ እንደ ሆነ፣ የበጎነትም ውበት ትሕትናውና ራሱን አለማሳየቱ ነው። ደግሞም በክርስቶስ ዓይን አለማድረግ ወንጀል መሆኑን አስተውሉ። ሙሴ ክፉ ማድረግ ስሕተት ነው ይላል፤ ኢየሱስ ግን መልካም አለማድረግ ስሕተት ነው ይላል። አንዳንዶች ሰዎች እንክርዳድን እንደሚጥሉ የተጣሉት አሥርቱን ትእዛዛት ስለ ጣሱ ሳይሆን የፍቅርን ሕግ ስላልፈጸሙ ነው።

ስለ ወደደንና ራሱን ስለ እኛ አሳልፎ ስለ ሰጠው ስለ እርሱ ብለን ራሳችንን ለወንዶች፣ ለሴቶችና ለልጆች አገልግሎት እንቀድስ።

ጸሎት

ውድ ጌታ ሆይ፥ የሌሎችን ችግር እንድናገለግል፣ ድሆችንና ችግረኞችን፣ ምንም የሌላቸውንና የተገለሉትን እንድንንከባከብ፣ ከወንድሞችህ ለሚያንሱት በምናሳየው ርኅራኄና እርዳታ ለአንተ ያለንን ፍቅር እንድንገልጥ እርዳን። አሜን።

ሴፕቴምበር 12

የተሰወሩ ጣዖታት

«ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና፦ ‹አንድ ነገር ጐደለህ፤ … ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ … መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ› አለው። … ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ።»— ማርቆስ 10:21፣ 22።

ግዴታቸው ምን እንደ ሆነ በልባቸው እያወቁ የተከለከለ ነገር ስለ ሸሸጉ የማይፈጽሙት ስንቶች ናቸው! በስውር በአሸዋ ቋጥኝ ላይ መልሕቅ ስለ ጣሉ አጠገባቸው በሚያልፈው ፈሳሽ ላይ ለመንሳፈፍ እምቢ ይላሉ፤ የዘላለምን ሕይወት በቅንነት የሚፈልጉ መስለው ከአንዱ አስተማሪ ወደ ሌላው ይሄዳሉ፤ ነገር ግን የተሰወረ ጣዖታቸውን ለመተው ስለማይፈቅዱ ፍለጋቸው ከንቱ ሆኖ ይቀራል።

በዚህ ወጣት ሁኔታ ጣዖቱ የገንዘብ ፍቅር ነበር። «ብዙ ንብረት ነበረውና።» በገንዘብ ምንም ጉዳት የለም። እግዚአብሔር ለሰዎች ከሰጣቸው ስጦታዎች አንዱ ነው፤ ነገር ግን መጋቢዎች ብቻ መሆናችንን ከመገንዘብ ይልቅ እንደ ራስ ገንዘብ ወደ መቍጠር ሳይደርሱ ገንዘብን መያዝ ከባድ ነው። ጌታችን ይህን ከሁሉ የላቀ ፈተና ያቀረበው በዚህ ምክንያት ነበር። የአሲሲው ቅዱስ ፍራንሲስ እነዚህ ቃላት በሁሉ ላይ ይሠራሉ ብሎ አሰበ፤ ስለዚህም በድህነት ለመኖር ቃል የገባውን የፍራንሲስካውያንን ማኅበር መሠረተ። ነገር ግን ይህ እውነትን ለሚፈልገው ለዚህ ሰው ራሱን ለራሱ እንዲገልጥለት የቀረበ ልዩ ፈተና ነበር ብሎ ማመን ከወንጌል መንፈስ ጋር ይበልጥ የሚስማማ ይመስላል።

የፍቅር ሕግ አሉታዊ ብቻ ሳይሆን አዎንታዊም ነው። ለእያንዳንዳችን ከሁሉ የሚያስፈልገው ቅድመ ሁኔታ በዚያ ዘመን ይኖር እንደ ነበረው እንደ ሌላው ወጣት «ክርስቶስን አተርፍ ዘንድ በእርሱም እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕዳት ለመቍጠር» ፈቃደኛ መሆን ነው (ፊልጵስዩስ 3:8)። ክርስቶስን ልትከተል ብትወድና ስለ ፍቅር ብለህ ሁሉን ለመተው ብትዘጋጅ፣ ምናልባት ብዙ እጥፍ አደራ ይሰጥሃል፤ ክርስቶስ በምጽዋት አከፋፋይነት ሊሾምህ እንደሚችል ያውቃልና፤ ገንዘቡ በእጅህ ሲያልፍ የወርቅ ብናኝ በመዳፍህ ላይ ይጣበቃል ብሎ አይፈራም።

ከገንዘብና ከንብረት ጣዖት እንጠንቀቅ። ብዙ በሮችን የሚከፍት ባለ ጠግነት ወደ ሰማይ የሚያስገባ ቍልፍ አይሰጥም። ሁልጊዜ የእግዚአብሔር ንብረት መጋቢዎች ሆነን እንድንሠራ እንጠንቀቅ፤ ነገር ግን ይህ የሚቻለው ከጌታችን ጋር ዘወትር በኅብረት የምንኖር ከሆነ ብቻ ነው፤ እርሱ ሀብታም ሲሆን እኛ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች እንሆን ዘንድ ስለ እኛ ድሀ ሆነ፤ ለእኛም ደግሞ «መስቀሉን ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ» ይለናል።

ጸሎት

ያወቅሁት እጅግ የምወደው ጣዖት፣ ያ ጣዖት ምንም ቢሆን፣ ከዙፋንህ ላይ ነቅዬ እንድጥለው፣ አንተን ብቻም እንዳመልክ እርዳኝ። አሜን

ሴፕቴምበር 13

ሰዎችን አጥማጆች

«ኢየሱስ … ሁለት ወንድማማች … መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። እርሱም፦ ‹በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ› አላቸው።»— ማቴዎስ 4:18፣ 19።

ክርስቶስ ራሱን ከአእምሮና ከልብ ጋር የሚያስማማው እንዲህ ነው። እነዚህን ዓሣ አጥማጆች ለእነርሱ በሚስማማ መጥመጃ ያዛቸው። እነዚህን ሁለት ወንድማማቾች ሰዎችን አጥማጆች እንደሚያደርጋቸው የሰጠውን ተስፋ ያለ አንዳች ጥርጥር እርግጠኛነት አስተውሉ፤ መረባቸውን የሚጥሉት በገሊላ ባሕር ውኃ ውስጥ ሳይሆን በታላቁ የሰው ልጆች ውቅያኖስ ውስጥ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስን በአራት ዓመት ውስጥ ሦስት ሺህ ነፍሳትን የሚያጠምድበትን ታላቅ አደን እንደሚያደርግ ማሳመን እንዴት የማይቻል በሆነ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 2:41)። አቤት፥ የጌታን ጥሪ ታዘን እርሱን ለመከተል ሁሉን በምንተውበት ጊዜ ምን እንደሚጠብቀን ከቶ አናውቅም!

«ተከተለኝ!» ጌታችን ይህን ጥሪ ዘወትር ያቀርባል (ዮሐንስ 21:19፣ 20፣ 21፣ 22)። ይህ መስቀልን መሸከም ማለት ነው፤ ነገር ግን እንደ እርሱ በምድር ላይ ወድቀን እስክንሞት ድረስ ክርስቶስን ለመከተል ፈቃደኞች መሆን አለብን፤ እግዚአብሔር በእኛ በኩል እንዲሠራ መንገድ እንድንለቅለት ለራሳችን ምኞት፣ ለሥልጣንና ለተሰሚነት ፍቅራችን፣ ለራሳችን ብርታትና ስጦታ እንሞታለን። ራሳችንን ወደ ፊት ማውጣትን ሳይሆን ተሰውረን መኖርን መማር አለብን። ለተሳካ ዓሣ ማጥመድ የመጀመሪያው፣ ሁለተኛውና ሦስተኛው ቅድመ ሁኔታ ከዓይን መሰወር ነው። ሰዎችን ለማጥመድ ከሁሉ የተሻሉት ገመድና መጥመጃ ሰብአዊው ነገር ከዓይን የተሰወረበትና አንድ ዓላማችንም የክርስቶስን ፈቃድ ማገልገልና እርሱን ማክበር የሆነበት ነው።

መረባችንንና ጀልባዎቻችንን፣ እንዲያውም ለእኛ እጅግ ቅርብና ውድ የሆኑትን እንኳ መተው ያስፈልጋል (ማቴዎስ 4:20፣ 21፣ 23)። እነዚህ ወንድማማቾች መረባቸውንና ዓሣ ማጥመዳቸውን ትተው ክርስቶስን ለመከተል መለየታቸው ቀላል አልነበረም። ነገር ግን የማንነቱ ማራኪነት አሸነፈ። ዋጋዋ እጅግ የበዛውን ዕንቁ ታላቅ ዋጋ ልትገልጥላቸው ብትችል፣ ሰዎችን ዝቅተኛውንና አነስተኛውን ነገር እንዲተዉ ማሳመን አያስቸግርም። ያን ጊዜ እርሷን ለመግዛት ያላቸውን ሁሉ በደስታ ይሸጣሉ።

ጸሎት

ኢየሱስ ይጠራናል፤ በምሕረትህ፣

አዳኝ ሆይ፥ ጥሪህን እንድንሰማ አድርገን።

ልባችንን ለመታዘዝህ ስጠው፣

ከሁሉ በላይ እንድናገለግልህና እንድንወድህ። አሜን።

ሴፕቴምበር 14

የፍቅር ግድ ማለት

«ቤቴ እንዲሞላ ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣና ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው።»— ሉቃስ 14:23።

እግዚአብሔር ለሰዎች ነፍስ ያለውን የናፍቆት ፍቅር ከቶ ልንለካው አንችልም። በእርሻና በኢንዱስትሪ፣ በንግድና በተድላ፣ በቤታችንና በቤተሰብ ሕይወታችን ተውጠን ያየናል፤ እነዚህም ሁሉ የዘላለም የመጀመሪያው ንክኪ ሲደርስ እንደ ሕልም እንደሚያልፉ ያውቃል። በሚኖር ደስታ በእውነት እንድንረካ በጽኑ ፍቅር ይመኛል።

እርሱ የሚያዘጋጀው ግብዣ የተትረፈረፈና የተዘጋጀ ነው (ኢሳይያስ 25:6፤ ኢሳይያስ 55:1፣ 2)። ግብዣ ደስታ የሚያመጣ ጊዜ ነው። እንግዶቹ አብረው ሲቀመጡ የሚያብለጨልጭ ጨዋታ፣ የሣቅ ብልጭታ፣ በቀረቡት መልካም ነገሮች መደሰት፣ የወዳጅነትና የኅብረት መለዋወጥ ይኖራል። ግብዣ የሚወክለውን ሁሉ እግዚአብሔር ሊሰጠን ይጠብቃል። «ደስ እንዲለን ሁሉን አትርፎ ይሰጠናል።» ሰዎች በክፉው እየተዘበቱ እግዚአብሔር በዘረጋላቸው የግብዣ ማዕድ ላይ ያላቸውን ስፍራ እንዲያጡ መታለላቸው እንዴት የሚያስደንቅ ነው!

መጀመሪያ የተጠሩት የአይሁድ ሕዝብ ነበሩ፤ ነገር ግን ለዚያ ቸር ጥሪ መልስ ለመስጠት በምድራዊ ነገሮች እጅግ ተጠምደው ነበር። ያቀረቧቸው ምክንያቶች ጥልቀት የሌላቸውና ሞኝነት ነበሩ፤ እውነተኛው ምክንያት ግን በጣም ጠልቆ ይገኛል፤ ይኸውም ነፍስ እውነተኛ ሕይወት የሆነውን ሕይወት ለመያዝ ራሷን ለማንቃት አለመፈለጓ ነው! ነገር ግን የእግዚአብሔር የፍቅር ዓላማ ሊሸነፍ አይችልም (ሉቃስ 13:28፣ 29፣ 30፤ የሐዋርያት ሥራ 13:45፣ 46፣ 47፣ 48)።

«ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣ።» እንደ ባሪያዎቹ ሥራችን ይህ ነው! ዋና ዋና መንገዶች የንግድና የተድላ፣ የሰርግና የቀብር፣ የመንግሥት ሰዎችና የነጋዴዎች፣ የወጣት ወንዶችና ሴቶች፣ የቤት እመቤቶችና የልጆች ጅረቶች ዘወትር የሚያልፉባቸው ናቸው! ቅጥሮቹ ደግሞ አንዳንዴ በጸደይ አበቦች፣ አንዳንዴም በመከር ቀለማት የተሸፈኑ ጸጥ ያሉና ገለል ያሉ የገጠር መንገዶች ናቸው። ዘመናዊው መኪናም ሆነ ቀስ ብሎ የሚጓዘው የገጠር ጋሪ የተለያዩ የሕይወት ዓይነቶች ምልክቶች ናቸው፤ ነገር ግን የሚጠቀሙባቸው ነፍሳት ሁሉ እኩል የምሥራቹን መልእክት ይፈልጋሉ። የጌታችን ቤት እንዲሞላ እንውጣና ይገቡ ዘንድ ግድ እንበላቸው!

ጸሎት

ብፁዕ ጌታ ሆይ፥ የፍቅርህን ጥሪ የሚቃወሙትን ማራቸው! ድንቁርናን፣ የልብ ድንዳኔንና ቃልህን መናቅን ሁሉ ከእኛ አርቅ፤ ውድ ጌታ ሆይ፥ እንድንድንና በታላቁ የነፍሳት እረኛ ሥር አንድ መንጋ እንድንሆን እንዲሁ ወደ መንጋህ ወደ ቤት መልሰን። አሜን።

ሴፕቴምበር 15

ፈቃድ ካለ መንገድ አለ!

«ስለ ሕዝቡም ብዛት እንዴት አድርገው እንዲያገቡት ሲያቅታቸው፥ ወደ ሰገነቱ ወጡ የጣራውንም ጡብ አሳልፈው በመካከል በኢየሱስ ፊት ከነአልጋው አወረዱት።»— ሉቃስ 5:19።

ይህ እንዴት ያለ ደስ የሚል ሰብአዊ ታሪክ ነው! ጌታችን ሲያስተምር በዙሪያው የተሰበሰበው ሕዝብ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሣ ፈሪሳውያንና ሊቃውንት ተቀምጠውበት የነበረውን እርሱ ያረፈበትን ቤት መሙላቱ ብቻ ሳይሆን በደጁ አደባባይ ላይ ታላቅ ሕዝብ ሆኖ ተትረፍርፎ ነበር። ጌታ በውስጥም በውጭም ያለውን ሕዝብ ለማዳረስ እንዲችል ባለ ሁለት ፎቅ ቤት በረንዳ ላይ ቆሞ ሊሆን ይችላል።

እያስተማረም ሳለ አራት ሰዎች በመካከላቸው በተንጠለጠለ የገመድ አልጋ ላይ አንድ ሽባ ሰው ተሸክመው ቀረቡ። ወጣቶች እንደ ነበሩ በግልጽ ቃል አልተነገረንም፤ ነገር ግን ትጋታቸውና ብልሃታቸው አንድ ሰው ወደዚህ ሐሳብ እንዲያዘነብል ያደርጋል። ምናልባት አብረው የተማሩ የትምህርት ቤት ባልንጀሮች ነበሩ፤ ሲያድጉም ወደ ክፉ መንገድ ገብተው «የወጣትነት ስንፍናቸውን» አብረው ዘርተው ይሆናል፤ ከእነርሱም አንዱ ውጤቱን እየተቀበለ ይሆናል፤ ጌታችን የኃጢአቱን ይቅርታ ከሰውነቱ ፈውስ አስቀድሞ በግልጽ አስቀምጧልና። አራቱ ባልንጀሮቹ ክርስቶስን ሲሰብክ ሰምተው ተከታዮቹ ሆነው ይሆናል፤ ይህን የመዳንና የፈውስ ተአምር ያደረገው «እምነታቸውንም አይቶ» ነበርና። በማንኛውም መንገድ ቢሆን ወዳጃቸውን ወደ ክርስቶስ ቸር ፊት ለማምጣት ተስማሙ። በሕዝቡ መካከል ማለፍ ባቃታቸው ጊዜ ተስፋ አልቈረጡም፤ ይልቁንም ወደ ጣራው ላይ ወጡ፤ ታሪኩም «የጣራውንም ጡብ አሳልፈው … አወረዱት» ይላል። በብርቱ እጆች በአራቱ ገመዶቹ የወረደው የገመድ አልጋ በጌታ እግር ሥር ተንጠለጠለ፤ የዚህ ምስኪን ሰው በተስፋና በልመና የተሞሉ ዓይኖች ከተሸካሚዎቹ ግልጽ እምነት የበለጠ ለእርዳታ የሚጮኽ ልመና ሊያቀርቡ አይችሉም ነበር።

ጌታችን ሰላምታ ያቀረበለት ቃላት እጅግ ርኅሩኅና ቸር ነበሩ፦ «አንተ ሰው፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ!» ለሥጋ ጤንነት ከሚሆኑ እርግጠኛ መንገዶች አንዱ የመንፈስ መንጻትና ይቅርታ ማረጋገጫ ማግኘት ነው (ያዕቆብ 5:14፣ 15፣ 16)። ሁላችንም ወዳጆቻችንን ወደ ክርስቶስ ለማምጣት እንዲሁ በተጨነቅን! አራት ሰዎች ስለ አምስተኛው ቢስማሙና እርሱ ወይም እርሷ ወደ ኢየሱስ እስኪመጡ ድረስ ፈጽሞ ባያርፉ፣ እንዴት ያለ መነቃቃት ይፈነዳ ነበር (ዮሐንስ 4:28፣ 29፣ 30)!

ጸሎት

ሁሉን ተስፋ እንድናደርግ፣ በሁሉ እንድንጸና፣ ለሰዎችም ችግርና ድካም የፈዋሽ ምሕረትህ መልእክተኞች እንድንሆን ነፍሳችንን በመለኮታዊ ፍቅር አስፋት። አሜን።

ሴፕቴምበር 16

ወደ ኋላ መመልከት

«አምላክህ እግዚአብሔር በእነዚህ አርባ ዓመታት የመራህን መንገድ ሁሉ አስብ።»— ዘዳግም 8:2።

የዚህ ምዕራፍ ዋና ቃል «አስብ!» የሚለው ነው። እምነት ከውጭ የሚመጣና ተጨባጭ የሆነ እርግጠኛ ማስረጃ ሳይኖረው ይጀምራል፤ ሕይወት እየገፋ ሲሄድ ግን አንዱ ቀን ከሌላው በኋላ የማይካድ ምስክርነቱን ክብደት ይጨምራል። በዙሪያችን በሁሉ አቅጣጫ የሚከበን ዘላለማዊና መንፈሳዊ ዓለም አለ በሚለው ሐሳብ ላይ ተመሥርተን ብንራመድ፣ ስለ እርሱ እጅግ ግልጽና የጠራ ማረጋገጫ ላይ እንደርሳለን፤ ስለዚህም የራሳችንን መኖር መጠራጠር ይቀልልናል። ወደ ኋላ ተመልክቶ መንገዱን ማየት መልካም ነው፤ የመለኮታዊው ዓላማ ክር የሕይወታችንን ብዙ ቀለም ያላቸውን ቀለበቶች በአንድነት እያሰካ እንዳለ በተቻለ መጠን እርግጠኛ ነው።

በዘዳግም 8:15፣ ዘዳግም 8:16 ያለውን የቃላት ስምምነት አስተውሉ፦ «የመራህ»፤ «የመገበህ»። እግዚአብሔር በሚመራበት ስፍራ ይመግባል! ያለፈውን ወደ ኋላ ተመልከት፤ የእግዚአብሔር ምሪት እርግጠኛ እንደ ነበረ ጥበቃውም እንዲሁ እንደ ነበረ እይ። በራሱ ጎዳና እንዲመራቸው ለሚፈቅዱለት ምንም አይጐድልባቸውም።

ያለፈውን ወደ ኋላ ተመልከት! ኃጢአቶቹንና ኋላ መመለሶቹን ለዘላለም ወደ ኋላ ትተህ በአዲስ ሕይወት ተነሣ። ተግሣጹን ተመልከት፤ ሊገሥጸንና ሊያበረታን የታሰበ ነው። መከራዎቹን ተመልከት፤ እርሱን እናከብረው ዘንድ እግዚአብሔር በመከራ ሰዓት ለማዳን ያለውን ኃይል ሊገልጡ የታሰቡ ናቸው። የብቸኝነት አስፈሪ ምድረ በዳ፣ የፈተና እሳታም እባቦች፣ ከቶ ያልጐደለው መና፣ ዓለቱ ሁልጊዜ የሰጠው ውኃ። ዘዳግም 8:17፣18 የትሕትናን ትምህርት ያስተምሩናል። በሆነ ምክንያት በሀብት፣ በክብር ወይም በተሰሚነት ስፍራ ላይ ብትቀመጥ አትታበይ፤ ምስጋናውም ለችሎታህ ወይም ለብቃትህ የሚገባ አይምሰልህ። እግዚአብሔርን አመስግን፤ ሀብትን ወይም ክብርን የማግኘት ኃይል የሚሰጥ እርሱ እንደ ሆነ፣ ይህንም እጅግ በተወሰነ ዓላማ እንደሚያደርገው አስብ! እርሱን ለማገልገልና ለማምለክ ቃል አትገባምን? የኮረብታውን ጫፍ ወጥተህ በፊትህ በጭጋግ የተሸፈነውን ነገር ሳታውቅ ወደ ሜዳው መውረድ ስትጀምር አትፍራ፤ ወገብህን ታጠቅ፤ እጅህን በእጁ ውስጥ አድርግ፤ የሰዎችን ዓለም ለመባረክ መሣሪያው ትሆን ዘንድ ከእርሱ ጋር ተመላለስ።

ጸሎት

የሠራዊት አምላክ ጌታ ሆይ፥ አሁንም ከእኛ ጋር ሁን፤

እንዳንረሳ፥ እንዳንረሳ! አሜን።

ሴፕቴምበር 17

ንጉሣዊው የድል ጉዞ

«እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል። … ሕዝቡም፦ ‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም› እያሉ ይጮኹ ነበር።»— ማቴዎስ 21:5፣ 6፣ 7፣ 8፣ 9፤ የመሲሐዊውን ትንቢት ፍጻሜ ከዘካርያስ 9:9 ጋር አነጻጽሩ።

የክብር

ንጉሥ (መዝሙር 24:7፣ 8፣ 9፣ 10) ወደ ቅድስቲቱ ከተማ የቀረበው በብዙ ጌጥ በተሸፈነ የጦር ፈረስ ላይ ተቀምጦ ወይም በሚያብረቀርቅ የወታደሮች ጭፍራ ታጅቦ ሳይሆን፣ በትሑት አህያ ላይ ተቀምጦና እጅግ ብዙ የገጠር ተሳላሚዎች አጅበውት ነበር! የተቀበሉትም አገረ ገዢው ጲላጦስ ወይም ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ሳይሆኑ ልጆች፣ ድሆች፣ የፈወሳቸውም ዕውሮችና አንካሶች ነበሩ። ማደሪያው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ያለው ባዶ መሬት ነበር፤ ቢያንስ በአንድ ወቅት ከበለስ ቅጠል ፍሬ እስኪፈልግ ድረስ ተርቦ ነበር።

ሆኖም የመቅደሱን አደባባዮች በጩኸትና በርኩሰት የሞሉት ሕዝብ ተባርረው የወጡበት፣ የካህናት አለቆችና ጻፎችም ስለ ሥልጣኑ በጠየቁት ጊዜ ሊቀበሉት ግድ የሆነባቸው ምሥጢራዊ ኃይል በእርሱ ነበረ (ማቴዎስ 21:23፣ ከማቴዎስ 7:28፣ 29 ጋር አነጻጽሩ)። ሥልጣኑ የእውነት፣ የንጽሕናና የእግዚአብሔር ሥልጣን ነበር። ከባሕርያዊ ግርማው የወጣች አንዲት የብርሃን ጨረር ነበረች። እርሱን በቅርብ የሚያውቀው አንዱ እንዲህ አለ፦ «አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን (ዮሐንስ 1:18፣ 3:16፣ 18፣ 1ኛ ዮሐንስ 4:9)፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ ነበር» (ዮሐንስ 1:14፤ ከዮሐንስ 1:16፣ 2ኛ ቆሮንቶስ 12:9፣ 2ኛ ጢሞቴዎስ 2:1፣ ራእይ 22:21 ጋር አነጻጽሩ፤ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ቍጥር ነው!)።

የሰው ነፍስ ሆይ፥ ንጉሥሽ ወደ አንቺም ይመጣል! የልብሽ በሮች መዝጊያዎቻቸውን ያንሡ፤ ያስገቡትም! መጀመሪያ ላይ መምጣቱ የሚያመለክተውን ለውጥ ትፈሪ ይሆናል፤ ነገር ግን ለልዑሉ ለአማኑኤል የሰው ነፍስ ከተማን ቍልፎች ሁሉ ለመስጠት ፍጠኚ። በልብሽ ውስጥ አንግሺው! እርሱ ንጉሥና ወራሽ ነው፤ ከራሱም ጋር አብረሽ ወራሽ ያደርግሻል (ሮሜ 8:17)። የሕይወታችሁ መንግሥት የእግዚአብሔርና የክርስቶሱ መንግሥት ትሁን (ዮሐንስ 3:3)። አሳብ ሁሉ ለእርሱ ይገዛ (2ኛ ቆሮንቶስ 10:3፣ 4፣ 5)። ነገር ግን በሌላ በኩል የሕይወትን ቤት ያለ እርሱ ለመሥራት ብትረኩ (ማቴዎስ 7:24፣ 25ን ከማቴዎስ 7:26፣ 27 ጋር አነጻጽሩ)፣ ለሕንጻው አስፈላጊውን ጽናትና ውበት ብቻውን ሊሰጥ የሚችለውን አንዱን የማዕዘን ራስ ድንጋይ እየናቃችሁ እንደ ሆነ እጅግ እርግጠኞች ሁኑ (መዝሙር 118:22፣ ኢሳይያስ 8:14፣ 15፣ 28:16፣ ማቴዎስ 21:42፣ የሐዋርያት ሥራ 4:11፣ ኤፌሶን 2:20፣ 1ኛ ጴጥሮስ 2:6 — «ክርስቶስ ዓለታችን» የሚለውን ጥናት ይመልከቱ)። ያን ማጣት የሕይወት ኃይላችሁን ሁሉ ያፈሰሳችሁበትን ሕንጻ ፈጽሞ መፍረስ ያስከትላል (ማቴዎስ 7:27)። (አንዳንድ ጥቅሶች ተጨምረዋል)

ጸሎት

ነገር ግን ከሁሉ አስቀድሞ በነጻው ልባችን፣

ዘላለማዊ ሆይ፥ መንፈስህ እንዲያርፍ እዘዝ፤

የውስጥ ነፍሳችንንም አድርጋት፣

ንጹሕና ለአንተ የሚገባ መቅደስ።

ሆሣዕና በአርያም! አሜን።

ሴፕቴምበር 18

የእግዚአብሔርን ሀልዎት መለማመድ

«ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕርም መጨረሻ ብኖር፥ በዚያ ደግሞ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች።»— መዝሙር 139:7፣ 9፣ 10።

ይህን አባባል ዘወትር ይጠቀምበት የነበረው መነኩሴ ታሪክ ለብዙ ሰዎች የታወቀ ነው። በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን፣ በአንድ የክረምት ቀን ወንድም ሎረንስ በጫካ ውስጥ ሲራመድ ቅጠሉ ከረገፈ ዛፍ ሥር ቆሞ ራሱን አገኘው። ያው ዛፍ ብዙም ሳይቆይ በጸደይ ቅጠሎችና ክብር እንደሚሸፈን የሚል ሐሳብ ድንገት በአእምሮው ብልጭ አለ። «እንግዲያስ እግዚአብሔር እዚህ መሆን አለበት» ብሎ ለራሱ አለ፤ መላ ሰውነቱም በፍርሃትና በአክብሮት ተውጦ በእግዚአብሔር ሐሳብ ተሞላ። ያ ስሜት በቀረው ዕድሜው ሁሉ ከእርሱ ጋር ኖረ፤ በቅዱስ ቍርባን ፊት ተንበርክኮ ከነበረበት ጊዜ ይልቅ ለወንድሞቹ መነኮሳት ምግብ በሚያዘጋጅበት በማዕድ ቤት ውስጥ የእግዚአብሔርን ሀልዎት በእውነት በጥልቅ እንደሚሰማው ተናግሯል።

ነፍስ በዚህ የእግዚአብሔር ግንዛቤ ውስጥ ስትኖር፣ በእርሱ ሕያዋን ሆነን ስንንቀሳቀስና ስንኖር፣ የንጋትን ክንፍ ወስደን ከፀሐይ ጋር ወደ ምዕራቡ ባሕር ብንጓዝም ሆነ ወደ ሞት ጥላ ሸለቆ ብንወርድም፣ ይህ የተባረከ ተሞክሮ ነው። ጌታችን «እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ» (ማቴዎስ 28:20) እንዳለ እያሰብን ይህን መዝሙር (መዝሙር 139:1-23) እንደ ገና እናንብብ።

የእግዚአብሔርን ሀልዎት የመለማመድ ልማድ በተለይ የሚገኘው ከመለኮታዊው ሀብት ለመቅዳት ራሳችንን ስናለማምድ ነው። ሁለት ጎልተው የሚታዩ ምሳሌዎችን ልናስታውስ እንችላለን፤ አንዱ በአብርሃም ታማኝ አገልጋይ፣ ሌላውም በነህምያ የተሰጠ ነው። በመጀመሪያው መንገደኛው ለጌታው ልጅ ሚስት ስለ መምረጥ ምሪትን ለማግኘት ልቡን ወደ እግዚአብሔር አነሣ፤ ሁለተኛው ደግሞ ንጉሡ የኀዘኑን ምክንያት በጠየቀውና እርሱ በመለሰለት መካከል ተገቢውን መልስ ለማግኘት ፈጣን ጩኸት ወደ እግዚአብሔር እንዳቀረበ፣ መልሱም እንደ ተሰጠው ይነግረናል። ታዲያ እኛ በማንኛውም የጥርጣሬና የግራ መጋባት ጊዜ፣ ፈታኙ በሚቀርብበትም ጊዜ የእግዚአብሔርን ቸር እርዳታ ወዲያውኑ ለምን አንጠይቅም?

ጸሎት

ቸር መንፈስ ሆይ፥ ቀኑን ሙሉ በእግዚአብሔር ፍርሃት እንድንኖር በጸጋህ አስችለን፤ የዕለት ተዕለት ኑሮአችን ችግሮችና ፈተናዎች እያንዳንዱን እርምጃ በእግዚአብሔር ሀልዎት ግንዛቤ እንድንራመድ ይምሩን። አሜን።

ሴፕቴምበር 19

በሰማይ የተሞላች ምድር

«የሠራዊት ጌታ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ ነው፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች።»— ኢሳይያስ 6:3።

የንጉሥ ዖዝያን ዘመነ መንግሥት ብልጽግና የሕዝቡን ጠባይ ያደከመ ይመስላል፤ ሥር የሰደደ ብልሽት ውስጣዊ ሕይወቱን እየበላ ነበር። ለአምሳ ዓመት ያልተቋረጠው የብልጽግናና የሀብት በጋ የነቢዩን ልብ በድንጋጤ የሞላ የሥነ ምግባር ውድቀት አስከትሎ ነበር። ኢሳይያስ ወደ መቅደስ የገባው በዚህ በተጨነቀ የአእምሮ ሁኔታ ነበር፤ በዚያም የካህናቱና የሌዋውያኑ ሥርዓት፣ የመሥዋዕቱ መቅረብ፣ የመዘምራኑ ተቀባብሎ መዘመር መንፈሱን ይበልጥ ያነቃቁት ይመስላል።

ራእዩ (ኢሳይያስ 6:1፣ 2፣ 3፣ 4)። የምድራዊው ሕንጻ ወሰን ከዓይኑ ጠፋ፤ የሱራፌልንም አምልኮ ተገነዘበ፤ ፊታቸው በመለኮታዊው ግርማ ፊት ተሸፍኖ፣ አካላቸው በትሕትና ተሸፍኖ፣ የቀሩት ክንፎቻቸውም ለፈጣን መታዘዝ ተዘጋጅተው ነበር። እርስ በርሳቸው ይበልጥ ዝቅ ወዳለ አክብሮትና ይበልጥ ወደ ተመሰጠ ውዳሴ እየተቀሳቀሱ ተቀባብለው ይዘምሩ ነበር።

ለእኛ እንዴት ያለ ትምህርት ቀርቧል! ይህ ከደካማው አምልኮአችንና ብዙ ጊዜ ከሚዘገየው መታዘዛችን ጋር እንዴት ያለ ተቃርኖ ነው! ይህ ታላቅ አምላክ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አባታችን ነው፤ ነገር ግን ከልጅነት መታመናችን ጋር በቂ አክብሮትን እናዋሕዳለንን? በጸሎታችን ብዙ ጊዜ ለፍላፊዎች አይደለንምን? በፊቱ ስንንበረከክ የንጹሕ ልብንና የንጹሕ እጅን አስፈላጊነት እንገነዘባለንን?

ጥሪው (ኢሳይያስ 6:5፣ 6፣ 7፣ 8)። ትሑቱ የኃጢአት ኑዛዜ የእኛም መሆን አለበት። ሱራፌል አንድ መልስ ብቻ እንዳለ ያውቁ ነበር። የመሠዊያው ፍም የመሥዋዕቱን ደም መጥጦ አሁን በነጭ ሙቀት እየነደደ ነበር። ለመንጻትና ለመነሣሣት ያገለግል ነበር፤ ይህም በተፈጸመ ጊዜ የአገልግሎቱን ጥሪ የሚያዘገይ ምንም ነገር አልቀረም።

ተልእኮው (ኢሳይያስ 6:9፣ 10፣ 11፣ 12፣ 13)። ነቢዩ ተስፋ መቍረጥ አልነበረበትም። በጨለማው ውስጥ የብርሃን ብልጭታዎች ብቻ ቢኖሩም እንኳ በመልእክቱ መጽናት ነበረበት።

ጸሎት

ታላቅና ቅዱስ አምላክ ሆይ፥ ለቅዱስ አገልግሎትህ የተገባን እንድንሆን በቀራንዮ በፈሰሰው ደምና በመንፈስህ እሳት በልባችን፣ በንግግራችንና በተግባራችን አንጻን። አንጻን፣ ጥራን፣ ላከንም! አሜን።

ሴፕቴምበር 20

የመጨረሻ መልሕቃችን!

«እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ … እንደግ።»— ኤፌሶን 4:14፣ 15።

«በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል።»— 1ኛ ዮሐንስ 3:3።

መድረሻችን ሊኖር ከሚችለው ሁሉ የላቀ ነው፤ «እርሱን እንድንመስል» ነው። እርሱ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔርን ልጅ መልክ እንድንመስል ለዚህ ተፈጠርን፣ ተዋጀን፣ ተቀደስንም (ሮሜ 8:29)።

ሐዋርያው ይህ ተስፋ ያላቸው ራሳቸውን እንደሚያነጹ ይናገራል። አንዲት ወጣት ወዳጄ በሩቅ ምዕራብ ባለ አንድ ክፍለ ግዛት ውስጥ ባቡሬ በአንዲት የመንገድ ዳር ጣቢያ ላይ በቆመ ጊዜ እጮኛዋን ለማግኘት እንድሞክር በአንድ ወቅት ጠየቀችኝ። ስንደርስ ጨለማ ሌሊት ነበር፤ በታላቁ የፑልማን ሠረገላ ደረጃዎች ላይ የችኰላ ውይይት ተደረገ። ይህ ወጣት በከብት አርቢ ሕይወት ብዙ ፈተናዎች መካከል ንጽሕናንና እውነትን አጥብቆ እንደ ያዘ ተረዳሁ። በማንኛውም የሃይማኖት አገልግሎት ላይ ለመገኘት እጅግ አልፎ አልፎ ብቻ አጋጣሚ እንደሚያገኝ፣ ነገር ግን ከትውልድ አገሩ የሚመጡለት ደብዳቤዎች የመጨረሻ መልሕቁ እንደ ሆኑለት ነገረኝ። ምን ማለቱ እንደ ሆነ ገባኝ። የሁኔታዎችን ብርቱ ጅረት ተገንዝቦ ነበር፤ ነገር ግን የማያቋርጥ ጸሎቷ ዓላማ ባደረገችው በአንዲት ጣፋጭና ንጹሕ ልጃገረድ መወደዱና የሚያበረታቱ ደብዳቤዎቿን መቀበሉ እንደ አየር ከከበበው ክፉ ነገር ጋር ከመስማማት ጠበቀው፤ ብዙም ሳይቆይ ሙሽራው አድርጎ ሊወስዳት እንደሚችል ማሰቡ ሕይወቱን እንዲያነጻና እንዲያጸና ረዳው። እንዲሁም ስሙን ለምንሸከም ለእኛ ከክርስቶስ ጋር የመሆንና እርሱን የመምሰል ተስፋ የመጨረሻ መልሕቅ ሊሆንልን ይገባል።

ክርስቶስን ፊት ለፊት ማየት፣ ባልተቋረጠ ኅብረት ከእርሱ ጋር መሆንና እርሱን መምሰል፤ ይህ የእያንዳንዱ ክርስቲያን ነፍስ ሦስት እጥፍ መድረሻ ነው። ነገር ግን የወደፊቱን ሕይወታችንን ምን ያህል ጥቂት ልናስበው እንችላለን! የትንሣኤ አካል ምን እንደሚመስል፣ ከቅዱሳን ፍጡራን ጋር ያለው ንግግር ምን እንደሚሆን፣ ምን አገልግሎት እንደሚሰጠን ለማወቅ ጥቅጥቅ ያለውን የጭጋግ መጋረጃ ዘልቀን ለማየት በከንቱ እንታገላለን፤ ምን እንደምንሆን አናውቅም፤ ነገር ግን «እርሱን እንድንመስል እናውቃለን»፤ ይህም ይበቃል! ያለምነውና ተስፋ ያደረግነው ሁሉ በዚያ በደስታው የበጋ ወራት አበባውንና ፍሬውን ያገኛል።

ጸሎት

አምላክ ሆይ፥ በሕይወት መኖር ብቻ ሳይሆን ማደግም የልቤ ጽኑ ምኞት ነው፤ በጸጋና በጌታዬና በአዳኜ በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ማደግ። በትዕግሥትና በነፍስ ጥንካሬ፣ በትሕትናና በቅንዓት፣ በመንፈሳዊነትና በሰማያዊ የአእምሮ ዝንባሌ እንዳድግ አድርገኝ። አሜን።

ሴፕቴምበር 21

የእግዚአብሔር ሀብት

«በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?»— ዘፍጥረት 18:14

«አቤቱ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እነሆ፥ ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኃይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጠርህ፤ ለአንተም የሚሳንህ ነገር የለም።»— ኤርምያስ 32:17

በአብርሃም ድንኳን ደጃፍ ፊት በድንገት የተገለጡት እነዚህ ሦስት እንግዶች እነማን እንደ ሆኑ ምንም ጥርጥር የለም። «እግዚአብሔር ተገለጠለት» ተብሎ በግልጽ ተነግሮናል። ጌታችን ሥጋ መልበሱን አስቀድሞ ያሳየው በዚህ መንገድ ነበር። ማንነቱን ሰውሮ መጣ፤ «ደስታዬም ከሰው ልጆች ጋር ነበረ» (ምሳሌ 8:31)። በምድር ላይ በኖረበት ዘመን የሰዎችን ቤቶች ይወድ ነበር፤ ከጴጥሮስና ከዘኬዎስ ጋር አደረ፤ ማርያም በምትወድበትና ማርታ በምታገለግልበት በዚያ ውድ ቤትም ተቀመጠ። ከትንሣኤውም በኋላ ከሁለቱ ጋር በመንደሩ የእንግዳ ማረፊያ ቈየ። እንዲሁም ወደ አንተ ልብና ወደ እኔ ልብ ይመጣል። ምንም እንኳ ዘላለምን የሚኖር ከፍ ያለውና ልዑሉ ቢሆን፣ ከእኛ ጋር እራት ሊበላ እኛም ከእርሱ ጋር ልንበላ እንድናስገባው ይማጠናል (ራእይ 3:20)። ነገር ግን ብዙ ጊዜ የተራበና የተጠማ መንገደኛ መስሎ ተሰውሮ ይመጣል። ማቴዎስ 25:40ን እያሰብን «እርሱን ለመቀበል እንሩጥ»።

እግዚአብሔር የማንም ባለ ዕዳ አይደለም፤ ሁልጊዜ የማደሪያውን ዋጋ ይከፍላል፤ ለሣራ የሰጠው ተስፋም ከዚህ የተነሣ ነው! እርስዋ ባለማመን ሳቀች፤ ነገር ግን በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? ይህ ማንም ሊመልሰው ከማይችል የእግዚአብሔር ጥያቄዎች አንዱ ነው። በዘመናት ሁሉ የሰውን ሕሊና ሲሞግት ኖሮአል። ተፈጥሮ ከምታስከትላቸው ችግሮች ዓይናችንን አንሥተን ውቅያኖሶችን ሁሉን በሚችል እጁ መዳፍ ወደሚይዘው ወደ እርሱ እንመልከት። ያን ጊዜ በተራራው ጥግ ከእርሱ ጋር ቆመን ስለ ሰዶም ልንማልድ እንችላለን፤ ያን ጊዜ እግዚአብሔር ራሱ አብልጠንና ደግሞም አብልጠን እንድንለምን ይስበናል፤ እምነታችንም ባለቀ ጊዜ ከለመንነውና ካሰብነው ሁሉ እጅግ የሚበልጥ ነገር ያደርጋል።

ጸሎት

እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው፥ ለእርሱ በቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኢየሱስ እስከ ትውልዶች ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።

ሴፕቴምበር 22

የክርስቲያናዊ ንግግር ጸጋ

«ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል።»— 1ኛ ጴጥሮስ 3:10

«ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን።» — ቆላስይስ 4:6

የክርስቲያናዊ ንግግር መለኪያ ሐዋርያው ለቆላስይስ ሰዎች በተናገረው ቃል ተሰጥቶአል። ንግግራችን ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ መሆን አለበት፤ ጸጋ ደግሞ ርኅራኄን፣ ፍቅርን፣ የሌላውን ቃልና ተግባር በተሻለ መንገድ ለመተርጐም ፈቃደኛ መሆንን ያመለክታል። ምቀኝነትን፣ ቅናትን ወይም ክፉ ስሜትን ለመቋቋም ከንፈሮቻችን ክርስቶስ በሚፈልገው መንገድ እንዲናገሩ ማስገደድ ታላቅ እርዳታ ነው። በሌላ ሰው ብትቀና፣ ፈተናው ክፉ ወይም የሚያንቋሽሽ ነገር መናገር ነው፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ብንኖር፣ እንዲህ ያሉትን ቃላት እንድንገታና በእኛም በሌሎችም በኩል ደግ አሳቢነትን በሚያሳዩ ቃላት እንድንተካቸው ያስችለናል። ሊነገር የሚችለውን መልካም ነገር ሁሉ ለመናገር ትጋ፤ ክፉውን ግን ምንም አትናገር። ስለምንበሳጭባቸው ሰዎች በደግነት ለመናገር ጥረት ስናደርግ መላው ውስጣዊ ስሜታችን ተለውጦ የድምፃችንን ቃና መያዙ የሚያስደንቅ ነው።

በንግግራችን ውስጥ ጨው ሊኖር ይገባል፤ ይህም ንጹሕ፣ ከመበስበስ የሚጠብቅና እንደ ምሳሌ መጽሐፍ የሚያንጸባርቅ ነው። ተጫዋች ቀልድና ብሩህ ፈጣን መልስ ከሐዋርያው መለኪያ ጋር አይቃረኑም፤ ነገር ግን ከሰዎች ጋር በምንጨዋወትበት ጊዜ ሁሉ፣ በክፋት የተሞላ ሐሜትን ወይም ጸያፍ ቀልድን እንዳይናገሩ የሚያደርግ አንድ ነገር በእኛ ውስጥ እንዳለ ሊገነዘቡ ይገባቸዋል።

እግዚአብሔር የቃልን በር እንዲከፍትልን፣ ስለ አዳኛችንም የተሰወረ ውበትና ክብር እንድንናገር በጸሎት መጽናት አለብን። አንዳንድ ጊዜም ለአስቸጋሪ ጥያቄዎች እንዴት እንደምንመልስ ለማወቅ በተጨነቅን ጊዜ፣ እንዴት መናገር እንዳለብን በዚያች ሰዓት ይሰጠናል፤ መንፈስ ቅዱስም በከንፈሮቻችን አማካይነት የሚናገረውን ቃል እንዳገኘ እንረዳለን (ሉቃስ 12:12፤ 1ኛ ጴጥሮስ 3:15)።

ጌታችን በፍርድ ሂደቱ ጊዜ ለጲላጦስም ሆነ ለሄሮድስ አንዲት ቃል እንዳልተናገረ፣ ነገር ግን ወደ መስቀሉ እንደ ደረሰ እንደ አማላጃቸው ሆኖ፦ «አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!» እያለ ልቡን እንዳፈሰሰ ተጽፎአል። ከሚሰድቡህና ከሚያስፈራሩህ ሰዎች ይልቅ ለእግዚአብሔር አብልጠህ ተናገር። እርሱ የከንፈሮቻችንን በር ሊጠብቅ እንደሚችል መገንዘብ የተባረከ ነው፤ ከባሕርያችን ክፍሎች ሁሉ ከዚህ ይበልጥ የእርሱን ጠባቂ ኃይል የሚያስፈልገው ምናልባት የለምና።

ጸሎት

ብፁዕ ጌታ ሆይ፥ ሕይወታችን የርዳታና የብፅዕና ወንጌሎች ይሆኑ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስህ በእኛ ውስጥ ኑር። የስንፍና ንግግርና መጎምጀት ሁሉ፣ መራርነትና ንዴት ቍጣም ከክፋት ሁሉ ጋር ከእኛ ዘንድ ይወገድ። አሜን።

ሴፕቴምበር 23

የዕረፍት ጊዜ መንፈስ

«እናንት ራሳችሁ ብቻችሁን ኑና ጥቂት ዕረፉ፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ።»— ማርቆስ 6:31

በደማችን ውስጥ በተወሰኑ ጊዜያት ዕረፍትንና ለውጥን የሚናፍቅ አንድ ነገር አለ። ቤታችንን፣ ሥራችንን፣ በዚህ የዕለት ተዕለት ድካም በሞላበት ዓለም ውስጥ ድርሻችንን የምንወጣበትንም ዕድል ልንወድ እንችላለን፤ ነገር ግን በጋ ሲመጣ ከተጨናነቀችው ከተማና ከአድካሚው ሥራ ለማምለጥ እንናፍቃለን፤ ፋታንና ዕረፍትንም እንጓጓለን። የተፈጥሮ ፍቅር ከእግዚአብሔር ፍቅር የተገኘ ቅዱስ ውርስ ነው፤ እንዲህ ብሎ የሚጠራንም የእርሱ ድምፅ ነው፦ «ልጆቼ ሆይ፥ ኑ፤ ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ፤ በክሎቨር ማሳዎች፣ በእሾኻማ ቍጥቋጦና በሄዘር መካከል ሲያልፍ ያጣፈጥሁትን መዓዛ ያለውን አየር ተንፍሱ፤ በዱሮችና በአበቦች፣ በወርቃማው የጀንበር መጥለቅና በሐምራዊ ተራሮች፣ በውቅያኖስ ክብርና በባሕሩ ዳርቻ ደስ ይበላችሁ።»

ነገር ግን የዕረፍት ጊዜያችንን በእውነት ልንደሰትበት ብንወድ ራስ ወዳዶች መሆን የለብንም። በሌሎች ኪሳራ እንኳ ቢሆን ለገንዘባችን የተቻለውን ያህል የተሻለ ዋጋ፣ እንዲያውም ከዚያ ትንሽ የሚበልጥ ለማግኘት የሚመጣውን ፈተና መቋቋም አስቸጋሪ ነው። ሁልጊዜ ስለ ሌላ ሰው አስብ—ከትከሻህ በላይ ማየት ስለማይችለው አጭሩ ዘኬዎስ! በሠረገላው መስኮት ወደ ውጭ መመልከት ስለሚወደው ሕፃን፤ ነፋሱን መቋቋም ስለማይችለው በሽተኛ! ዕረፍት ከሌላቸው ልጆች ጋር ስለ ደከመችው እናት! የጌታ ኢየሱስን ገርነት፣ ጣፋጭነትና ራስ ወዳድ አለመሆን ለማሳየት የዕለት ዕለት ዕድሎችን ፈልግ።

አንዳንድ ጊዜ ብቻህን ለመሆን ጊዜ መድብ። ሁልጊዜ በሌላ ሰው ፊት መሆን ስሕተት ነው። ነፍስ ዝም ማለትና ጸጥ ማለት አለባት። በእግዚአብሔር ድምፅ ውስጥ እጅግ ጥልቅና ጸጥ ያሉ ቃናዎች ስላሉ የባልንጀራ እስትንፋስ እንኳ እንዳይሰሙ ሊያደርጋቸው ይችላል። ነገር ግን ጣፋጭ ኅብረት የምታደርግበት የተመረጠ ወዳጅና ባልንጀራ ማግኘት ደስ የሚያሰኝ ነው፤ «ከወንድምም ይልቅ አብልጦ የሚጠጋ ወዳጅ አለ»። እርሱ ይቀርባል፤ ከአንተም ጋር ይመላለሳል፤ በመንገድም ከአንተ ጋር ሲነጋገር ልባችሁ በውስጣችሁ ይቃጠላል።

በድህነት፣ በሕመምና በችግር ያሉትን አስቡ፤ በራሳችሁም ደስታና ሐሤት መካከል ምንም ላልተዘጋጀላቸው ዕድል ፈንታቸውን ስደዱላቸው (ነህምያ 8:10፣ 11፣ 12)።

ጸሎት

ስላደረገልኝ ቸርነት ሁሉ ለእግዚአብሔር ምን እመልሳለሁ?

በሕይወቴ ዘመን ሁሉ አመሰግንሃለሁ፣ እባርክሃለሁ፣ ምስጋናም አቀርብልሃለሁ። ጌታ ሆይ፥ ክብርንና ውዳሴን ኃይልንም ልትቀበል ይገባሃል። አሜን።

ሴፕቴምበር 24

እንጀራ ፍለጋ!

«እርሱም መልሶ፦ ‹ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል› አለ።» «ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።»— ማቴዎስ 4:4፤ ማቴዎስ 6:33።

ሰይጣን ጌታችንን የጠየቀው ጥያቄ በእያንዳንዱ ሕይወት ውስጥ እልባት ማግኘት አለበት። እንጀራና እንጀራ ማግኘት ቦታቸው የት ነው? የመጀመሪያው ጉዳያችን ሊሆን ይገባዋልን ወይስ የመጨረሻው? ሰይጣን ሕይወትን በሚመለከትበት መንገድ የእንጀራ ጉዳይ ከሁሉ የላቀ ነው፤ ክርስቶስ እንደሚለው ግን ሁለተኛ ደረጃ ነው። ከሁለቱ መርሖች የአንተ የትኛው እንደ ሆነ፣ በታላቅ የፈተና ወቅትም መምረጥ ቢኖርብህ ምን እንደምታደርግ በቁም ነገር አስበህ ታውቃለህን? ወደ ጌታችን የመጣው ይህ ፈተና ወደ ሁላችንም ይመጣል፤ ይዋል ይደር እንጂ፣ በብቸኛው የተራራ ጥግም ሆነ በተጨናነቁት የሕይወት አውራ ጎዳናዎች፣ ዲያብሎስ መኖር አለብን፣ በመጨረሻም እንጀራችንን መሥራት ወይም ማግኘት አለብን የሚል ሐሳብ ይዞ ይመጣል፤ የንጽሕናን፣ የእውነትን፣ የእግዚአብሔርን ክብርና የዘላለምን ጉዳዮች ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ እንዲይዙ ይተዋቸዋል!

በውስጣዊ ሕይወት ታሪክ ውስጥ በእያንዳንዱ አስፈላጊ መታጠፊያ እነዚህ ሁለት መንገዶች ይቀርባሉ፦ ሰይጣን «እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል» ይላል፤ ክርስቶስ ደግሞ «ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም» ይላል። ከእግዚአብሔርና ከገንዘብ መካከል መምረጥ አለብን። በተለያዩ የባሕርያችን ክፍሎች ረሃብ ሊያጠቃን ይችላል፦ ለምግብ ስንራብ ሰይጣን ነጥቀን እንድንወስደው ያዘናል፤ ለፍቅር ስንራብ ከእግዚአብሔር ተለይተን ልናረካው እንፈተናለን፤ ለእውቀት ስንራብ በዘላለማዊ እውነት ብርሃን ባልበሩ መንገዶች ልንፈልገው እንቃጣለን።

እነዚህን ብርቱ ፍላጎቶችና ምኞቶች የሰጠን እግዚአብሔር ምግብ እንደሚያስፈልገን ያውቃል። ሰውነት ከመብል ይበልጣል፤ አንዱን ከሰጠ ሌላውን ማሟላት የእርሱ ኃላፊነት ነው። የእርዳታው ብፁዓን መላእክት አሁን እንኳ ወደ አንተ በመንገድ ላይ ናቸው፤ በሕይወትህ ላለው ፍላጎት ሁሉ የሚሆነውን አቅርቦት ይዘው እንዲመጡ ታዘዋል። ሕይወትህን ከእግዚአብሔር እጅ ወስደህ በስሜት ትእዛዝ አትመላለስ! ኃላፊነቱን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣል፤ እርሱን የሚጠባበቁ አያፍሩምና። በምድረ በዳ ለኤልያስ ምግብ ያዘጋጀውን መልአክ፣ ጌታችንም ራሱ ለደከሙትና ለተራቡት ወዳጆቹ ያዘጋጀውን ቍርስ አስብ። በአንተና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ብቻ ቢቀርም እንኳ እርሱን ለመታመንና ለመጠበቅ ብትደፍር፣ እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር የሚያስፈልግህን ሁሉ ይሞላልሃል። «በእግዚአብሔር ታመን፥ መልካምንም አድርግ፤ በምድርም ትኖራለህ፥ በእውነትም ትመገባለህ።»

ጸሎት

ሌላው ሁሉ እንደሚጨመርልን በጽኑና በእርግጠኛ እምነት አስቀድመን መንግሥትህንና ጽድቅዋን እንድንፈልግ ጸጋን ስጠን። አሜን።

ሴፕቴምበር 25

የሰልፍ ቀዳሚ

«እነሆ፥ ለሕዝቦች ምስክር፥ ለሕዝቦችም መሪና አዛዥ አድርጌ ሰጠሁት።»— ኢሳይያስ 55:4።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጌታችን አራት ጊዜ ራስ ወይም አለቃ ተብሎ ተጠርቶአል።

ቃሉ በመጀመሪያ ትርጉሙ የሰዎች ሰልፍ ቀዳሚ ማለት ነው፤ ስለዚህም አለቃቸው ወይም አዛዣቸው ማለት ነው (የሐዋርያት ሥራ 3:15፤ የሐዋርያት ሥራ 5:31፤ ዕብራውያን 2:10፤ ዕብራውያን 12:2 ተመልከት)።

ክርስቶስ ከሞት ወደ ሕይወት ይመራል። ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ቆመው ሳሉ የደረቀውን የዮርዳኖስን ወለል መጀመሪያ የተሻገረው ምናልባት ኢያሱ ሳይሆን አይቀርም፤ ነገር ግን ይህ ቢያንስ እውነት ነው፦ አዳኛችን በሞት ውኃ በኩል ቀድሞን አልፎአል፤ የተቤዡትም እያንዳንዳቸው «ፈጽመው እስኪሻገሩ» ድረስ ውኃውን ያቆመዋል (ኢያሱ 3:17)።

ክርስቶስ ተከታዮቹን ወደ ድል ይመራል። ጌታችን ወደ ኃይል ቀኝ ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ፣ ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል ብዙ ሕዝብ በዘመናት ሁሉ የሚረግጡትን ጎዳና ከፈተ። እርሱ እንዳሸነፈ እኛም ልናሸንፍ እንችላለን፤ እርሱ በአለቅነትና በሥልጣን ሁሉ ላይ እንደሚነግሥ፣ እንዲሁ ሰይጣንን ከእግራችን በታች እንደሚቀጠቅጠውና ከአሸናፊዎች እንድንበልጥ እንደሚያደርገን እናምናለን።

ክርስቶስ መከራ የሚቀበሉትን ወደ ፍጹምነት ይመራል። የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም፣ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ መከራንም ለወጠው፤ ማጣሪያ ዕቃ፣ የሚያነጻ እቶን፣ የተግሣጽ፣ የብርታትና የመከበር መንገድ እንደ ሆነም አሳየ። ወደሚነድደው የእሳት እቶን ብንጣል የእግዚአብሔር ልጅ በጎናችን ሲመላለስ እናገኘዋለን፤ ከእስራታችንም ተፈትተን፣ የእሳትም ሽታ ሳይኖርብን እንወጣለን። ኢየሱስ የረጅም የሰማዕታትና የመከራ ተቀባዮች ሰልፍ መሪ ነው። እርሱ አስቀድሞ ካለፈባቸው የበለጡ ጨለማ ክፍሎች በኩል አይመራንም፤ ምን ያህል መሸከም እንደምንችል በትክክል ያውቃል፤ ከአቅማችንም በላይ አይፈትነንም። እርሱ «ሁልጊዜ» ከእኛ ጋር ነው፤ ፍለጋውንም ስንከተል መታዘዝን፣ እምነትንና ተስፋን እንድንማር ይረዳናል።

ጸሎት

መንገዱ ፍጹም የሆነ ጌታ ሆይ፥ ከአንተ ጋር እየተመላለስንና በፍጹም ቅንነት እየተከተልንህ ጸጥ ያለና የረካ አእምሮ እንድናገኝ፣ አንተም ስለ እኛ ታስባለህና የሚያስጨንቀንን ሁሉ በአንተ ላይ እንድንጥል ሁልጊዜ በቸርነትህ እንድንታመን እርዳን። አሜን።

ሴፕቴምበር 26

ያማሩ ልብሶች

«ንቂ፥ ንቂ፤ ኃይልሽን ልበሺ፤ ያማረ ልብስሽን ልበሺ።»— ኢሳይያስ 52:1

«ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን ደርሶአል፤ እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ።»— ሮሜ 13:11፣ 12

ኃይልን ልበሱ። ኃይልን መግዛት ወይም በጸሎትና በውሳኔ ማመንጨት የለብንም፤ ዝም ብለን መልበስ ብቻ ነው። በማለዳ ሰዓት ስንነቃና ብዙ ጊዜ ውድቀትንና ሽንፈትን ወዳየው የሕይወት መድረክ መውጣት ሲኖርብን፣ የሕያው ክርስቶስን ብርታትና ኃይል እንልበስ። እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን በኃይል ሁሉ ሊያበረታን ይጠብቃል (ኤፌሶን 3:16)። እንዲጠብቅህና እንዲረዳህ ብቻ አትጸልይ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበስ። «እግዚአብሔር የሕይወቴ ኃይል ነው፤ ማንን እደነግጣለሁ?» (መዝሙር 27:1)

ያማረ ልብስን ልበሱ። የክርስቲያን ነፍስ ሕይወት ምሳሌ በጌጣጌጥ የተሸለሙ ሙሽራ ወይም ሙሽሪት ነው (ራእይ 19:7)፤ ወይም ውብ አበቦች የሞሉበት አትክልት ስፍራ ነው (ኢሳይያስ 61:10፣ 11)። ትክክለኛ ነገሮችን ማድረግ ብቻ ሳይሆን በውበት ልናደርጋቸው ይገባል፤ እውነትን መናገር ብቻ ሳይሆን በፍቅር ልንናገረው ይገባል (ኤፌሶን 4:15)፤ ርዳታችንን ለሚሹ መስጠት ብቻ ሳይሆን በቸርነትና በደስታ ልንሰጥ ይገባል። ከርኅራኄ፣ ከቸርነት፣ ከትሕትና፣ ከየዋህነትና ከለጋስነት የተሠራውን የነፍስን ውበት ልናሳድግ ይገባል (ቆላስይስ 3:12)። የአምላካችን የእግዚአብሔር ውበት በእኛ ላይ ሊሆን ይገባል።

እነዚህን ያማሩ ልብሶች ልንሸምናቸው ወይም ከራሳችን ባሕርይ ልናበጃቸው አንችልም፤ ነገር ግን ሁሉም በክርስቶስ ተዘጋጅተውልናል፤ እርሱ «ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም ሆነልን።» (1ኛ ቆሮንቶስ 1:30) ከእንቅልፍ እንንቃ (ኤፌሶን 5:12)፤ የጨለማን ሥራ እናውጣ (ሮሜ 13:13)፤ የብርሃንም ጋሻ ጦር የሆነውን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንልበስ። (ሮሜ 13:14)

ጸሎት

የኃይልና የፍቅር ጌታ ሆይ! በሁሉን ቻይ ብርታትህና ወሰን በሌለው ቸርነትህ ታምኜ፣ በራሴ የጎደለኝን፣ ይኸውም አንተ እንድሆንና እንዳደርግ የምትወደውን እንድሆንና እንዳደርግ የሚረዳኝን ጸጋ ከአንተ ለመለመን እመጣለሁ። የዘላለም ብርታት ባለህ በአንተ እታመናለሁ። ከራሴ ብርታት በላይ የምትሸከመኝና የማስበውን፣ የምናገረውንና የማደርገውን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊትህ ተቀባይነት ያለው የምታደርገው ረዳቴ ሁን። አሜን።

ሴፕቴምበር 27

የዘመናችን ተአምራት

«ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው፦ ‹ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ› አሉ። በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።»— ዮሐንስ 10:41፣ 42።

ሕዝቡ መጥምቁ ዮሐንስ ተአምር ስላላደረገ ሕይወቱን የማቃለል ዝንባሌ ነበራቸው። ነገር ግን በእርግጥ ሕይወቱ ሁሉ ተአምር ነበር፤ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በመለኮታዊ ኃይል ይንቀጠቀጥ ነበር። ይህ ዛሬም የሰዎች ስሕተት ነው። የተአምራት ዘመን አልፎአል ይላሉ። እንዲህ ያሉ ድንቆች ምናልባት በአንድ ወቅት ተፈጽመው ሊሆን እንደሚችል ቢቀበሉ እንኳ፣ ዓለም ከእነርሱ አልፎ እንዳደገ፣ የሰው ልጅም በብስለቱ እንደ ሕፃንነት ነገሮች እንደ ተዋቸው አጥብቀው ይናገራሉ!

ተአምራት የሉም! ነገር ግን ባለፈው በጋ እግዚአብሔር አምስቱን የገብስ እንጀራ ከአምስት ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች እንዲበቃ እንዳደረገ፣ እንዲሁ ገበሬዎች በእርሻቸው ላይ የበተኑትን ዕፍኝ እህል የዓለምን ሕዝቦች ሁሉ ለመመገብ እንዲበቃ በቀላሉ አደረገ! ተአምራት የሉም! ነገር ግን ባለፈው መከር የሌሊቱን ጠልና የማለዳውን ካፊያ የሰውን ልብ ደስ ወደሚያሰኙ ፍሬዎች ለወጠ፤ ልክ በአንድ ወቅት በቃና ከድንጋይ ጋኖች የተቀዳውን ውኃ ወደ ቀላው የወይን ጠጅ እንደ ለወጠው! ተአምራት የሉም! ነገር ግን በሚመጣው ጸደይ ከጥቃቅን ዘሮችና የሞቱ ከሚመስሉ የአበባ ሥሮች ዓለምን በውበት፣ በቀለምና በመዓዛ ያለብሳታል።

እነዚህን መስመሮች ከሚያነቡት ብዙዎቹ ተአምራትን ለመሥራት አቅም የሌላቸው ይመስላሉ። ለእነርሱ የተራ ነገሮች ድግግሞሽና ምንም አዲስ ነገር የሌለበት የዕለት ተዕለት ኑሮ ግራጫ ሰማይ አስቀድሞ የተወሰነላቸው ዕድል ፈንታ ይመስላል። ነገር ግን እንደነዚህ ያሉት ሁሉ ይጽናኑ! በእግዚአብሔር ጸጋ ሊጠይቁት ብቻ ቢፈቅዱ የሕይወት እውነተኛ ታላቅነት በእጃቸው የሚደረስበት ነው። ታላቅ ነገር ለማድረግ አትሞክር፤ አለዚያ ፈጽሞ ላይመጣ የሚችለውን ዕድል በመጠባበቅ ሕይወትህን ሁሉ ልታባክን ትችላለህ። ነገር ግን ትናንሽ ነገሮች ሁልጊዜ ትኩረትህን ስለሚሹ፣ ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰዎች መልካም ለማድረግ ከታላቅ ዓላማ ተነሥተህ እንደ መጡ አድርጋቸው። እንዲህ ያለ ማንኛውም ተግባር ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን ከክርስቶስ ፈጣን እውቅናና የመጨረሻ ብድራት አይቀርበትም። ሕይወት ሁሉ እጅግ የሚማርክ ነው፤ ነገር ግን የሚያዩ ዓይኖችና የሚያስተውሉ ልቦች ያስፈልጉናል! ራስህን ለመሆን ድፈር—ቀላል፣ ትሑትና ቅን የኢየሱስ ተከታይ ሁን፤ ስለ አንተም እንዲህ ሊባል ይችላል፦ «እርሱ ወይም እርስዋ አንድ ተአምር እንኳ አላደረጉም፤ ነገር ግን በሕይወትና በቃል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ነገሮችን ተናገሩ፤ እኛም በራሳችን ፈትነናቸዋል። በእርግጥም እኛ ራሳችን በክርስቶስ እንድናምን መሩን።»

ጸሎት

አምላኬና ንጉሤ ሆይ፥ አስተምረኝ፥

በነገር ሁሉ አንተን እንዳይ፥

በማንኛውም የማደርገውን፥

ለአንተ እንደሚደረግ እንዳደርገው።

ይህን ቃል የያዘ አገልጋይ

አድካሚውን ሥራ መለኮታዊ ያደርጋል!

ስለ ሕግህ ብሎ ክፍልን የሚጠርግ፥

ክፍሉንም ተግባሩንም ያማረ ያደርጋል። አሜን።

ሴፕቴምበር 28

መታዘዝ

«በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።»— ዮሐንስ 12:46። (ከመዝሙር 119:130፣ ዮሐንስ 1:9፣ 1:4፣ 3:19፣ 20፣ 21፣ 8:12፣ 9:5፣ 2ኛ ጢሞቴዎስ 1:10፣ ኢሳይያስ 9:2፣ ሚልክያስ 4:2 ጋር አነጻጽሩ)

የክርስቶስ ብርሃን ሁልጊዜ ተለይቶ ይታወቃል፤ ስለ ትክክለኛው ነገር ጥልቅ የሆነውን መረዳት፣ ስለ እግዚአብሔርም ፈቃድ ግልጽ የሆነውን እርግጠኝነት ያመለክታልና። በየስፍራው ሰዎች ክርስቶስን እንዴት ሊያውቁት እንደሚችሉ ይጠይቃሉ፤ መልሱም አንድ ብቻ ነው፦ እንደሚወድህ፣ ሊያድንህ በመስቀል ላይ እንደ ሞተ፣ ለተሻለና ለቅዱስ ሕይወት የሚሰማህን እያንዳንዱን መረዳትና ናፍቆት እንድትከተል በመንፈሱ እየገፋፋህ እንዳለ እመን።

ይህ ትምህርት በዙሪያችን ካለው ዓለም ትምህርት እንዴት የተለየ ነው! በዚያ የቱንም ያህል ያማረ ንግግርና ተስፋ ቢኖረው ሕይወታችንን ለማንኛውም መሪ አሳልፈን ለመስጠት ከመድፈራችን በፊት እንድናውቅ እንታዘዛለን፤ ክርስቶስ ግን በእኛ ላይ የሚበራውን የመጀመሪያውን የብርሃን ጭላንጭል እንድንታዘዝ ያዘናል፤ እንዲህ ብናደርግም በጨለማ እንደማንመላለስ ዋስ ይሆናል። አለመታዘዝ እንደ ቅርፊት ክርስቶስን ከእኛ ይሰውራል፤ መታዘዝ ግን ወደ ራሱ ፊት ያደርሰናል (ከዮሐንስ 7:17፣ 1ኛ ሳሙኤል 15:22፣ 23 ጋር አነጻጽሩ)። ራሳችንን ስንክድ (ማርቆስ 8:34፤ ሉቃስ 9:23 «ዕለት ዕለት» የሚለውን ይጨምራል!) እውነት፣ ንጹሕ፣ ጽድቅ፣ ተወዳጅና መልካም ወሬ ያለበትን ሁሉ ለመከተል (ፊልጵስዩስ 4:8)፣ ፍርዳችን ሁልጊዜ ትክክል፣ ራእያችንም ግልጽ ይሆናል።

ምናልባት እነዚህን መስመሮች በምታነብበት ጊዜ የምትሸሸው አንድ ግዴታ፣ ለማንሣት እምቢ የምትለው አንድ መስቀል፣ ወደ ኋላ የምትልበት አንድ ተግባር ይኖር ይሆናል። ምንም እንኳ በቀጥታ ከክርስቶስ ጋር አያይዘኸው ባታውቅም፣ ለአንተ ፈቃዱ እንደ ሆነና በማድረግህም ደስ እንደሚሰኝ ልትጠራጠር አትችልም (2ኛ ቆሮንቶስ 5:9)። ያ የቀረበው የመታዘዝ ተግባር እስኪፈጸም ድረስ እርሱን ለማወቅ መሞከር ከንቱ ነው። ሰዎች የተፈጥሮን ሕጎች በጥቃቅኑ ዝርዝር ሁሉ ለመታዘዝ ራሳቸውን እስኪያዘጋጁ ድረስ ብርቱ ኃይሎቿ ምን እንደሚያደርጉላቸው ሊያውቁ አይችሉም። ከክርስቶስና ከመንፈሳዊው ዓለም ሕጎች ጋር ባለው ግንኙነትም እንዲሁ ነው። የጌታችን እናት በቃና ለአገልጋዮቹ፦ «የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ!» ባለቻቸው ጊዜ የተናገረችው ቃል እውነተኛ ቃል ነበር (ዮሐንስ 2:5)። ይህን ትምህርት በናዝሬት በነበሩት በእነዚያ ረጅም፣ ጸጥ ያሉና የተባረኩ ዓመታት ሳትማረው አልቀረችም። እርሱን ቃል በቃል ከመታዘዝ የተሻለ እርሱን የማወቂያ መንገድ እንደሌለ ታውቅ ነበር፤ የልምምዷንም ፍሬ ለሁላችን አስተላለፈች።

«ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤» (ዮሐንስ 12:35) እንዲህም ብርሃኑን ታውቃላችሁ፤ በጌታም ብርሃን ትሆናላችሁ። (ኤፌሶን 5:8)

ጸሎት

ልጄ ሆይ፥ ራስህን ተው፤ እኔንም ታገኛለህ። ጌታ ሆይ፥ ራሴን ስንት ጊዜ አሳልፌ ልስጥ? ራሴንስ በምን ልተው? ሁልጊዜ፥ አዎን በየሰዓቱ፥ በትንሹም ነገር በታላቁም። አሜን።

ሴፕቴምበር 29

የዓመታት ተረት

«ዘመናችን ሁሉ በቍጣህ አልፎአልና፤ ዓመታችንን እንደ ተነገረ ተረት እንፈጽማለን።»— መዝሙር 90:9።

ይህ መዝሙር (መዝሙር 90) በግርማው ተወዳዳሪ የለውም ማለት ይቻላል፤ «የእግዚአብሔር ሰው» የሆነው የሙሴ በመንፈስ የተቃኘ ብልህነት የሚገባው መታሰቢያ ነው። የምድረ በዳውን ጕዞ መንከራተትና ልምምዶች ያንጸባርቃል፦ የበዳዊ ሌባ ሰርጎ እንዳይገባ ወይም የዱር አውሬ እንዳያደባ በሌሊት የሚደረገውን ጥበቃ፤ በኃይለኛ ዝናብ ምክንያት የሚመጣውን፣ ነገር ግን በአሸዋማው መሬት ላይ ፈጥኖ የሚጠፋውን የጎርፍ ግፊት፤ በሲሮኮ ነፋስ የሚለበለበውን የማለዳ ሣር፤ የሰፈሩ ሰላዮች ያመጡትንና ፈጥኖ ያለቀውን ወሬ፤ የማራን ምንጮች ያስከተሉትን ቅሬታ፤ ኤሊምን መልቀቅ የግድ መሆኑን! የረጅሙን አድካሚ የጕዞ ቀናት፣ እናቲቱንና ሕፃኑን፣ አረጋውያንንና ትናንሽ ልጆችን፣ በምድረ በዳው መንገድ ላይ ያለውን ደካማ፤ ዘወትር ድንኳን መትከሉንና መንቀሉን—እነዚህ ሁሉ የሕይወትን ድካምና ፈተና ከባድ ልምምዶች የሚያሳዩ የአላፊነት ምሳሌዎች ናቸው። የተሰወሩ ኃጢአቶችና በደሎች፤ ስለ መተላለፍ የተመለሰው የእግዚአብሔር ፊት፤ በሰማንያ ዓመቱ የሽማግሌው ሞት፣ እንደ ደካማ አበባም የተቈረጠው የሕፃኑ ሞት። አዎን! ነገር ግን ይህ ሁሉ ቢሆንም፣ እግዚአብሔር ለሚተካካው ትውልድ እንደ ሆነ ሁሉ ለእያንዳንዲቱ ነፍስ መኖሪያና ቤት ነው።

የዚህን መዝሙር የመደምደሚያ ልመናዎች የራሳችን አናደርጋቸውምን? እኛም በምድረ በዳው ባድማ አቋርጠን ወደ ዘላለማዊው ቤት የምንጓዝ ተሳላሚዎች ነንና። እየቀነሰ የሚሄደውን ቍጥራቸውን እየተመለከትን፣ የቀሩትንም በሚገባ ለመጠቀም በጥንቃቄ በመትጋት ስለ ቀኖቻችን ይበልጥ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። የማይደርቁ የሐሤትና የደስታ ምንጮች እንዲኖሩን በየማለዳው በእግዚአብሔር ምሕረት መጥገብና መሞላት ያስፈልገናል። የክፋትን ኃይል በመገልበጥ ለመርዳት እንናፍቃለን፤ እያረጀን ስንሄድም የአምላካችን የእግዚአብሔር ውበት በእኛ ላይ እንዲሆን እንጸልያለን፤ የእጃችንንም ሥራ እንዳጸናልን ይሰማን።

ጸሎት

ውድ ጌታ ሆይ፥ ሞትን ስለ ሻርህና ሕይወትንና የማይጠፋውን ሕይወት ወደ ብርሃን ስላወጣህ እንዴት አድርገን በበቂ እናመሰግንሃለን? በሕይወታችን ዘመን ሁሉ እንድንከተልህ ጸጋን ስጠን፤ ለመሻገር ጥሪው ወደ እኛ በሚመጣበት ጊዜም የወንዙ ውኃ እጅግ የጐደለ ይሁን። አሜን።

ሴፕቴምበር 30

የድል ቁልፍ

«በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።»— ሮሜ 8:37።

ከክርስቶስ ፍቅር አንዳች ሊለየኝ ይችላልን? ቅዱስ ጳውሎስ ሊያስብበት የሚገባ አድርጎ የቈጠረው ብቸኛ ጥያቄ ይህ ነበር። በዚህ ክፍል የሕልውናን ጽንፎች ወስዶ በጥንቃቄ ይመረምራቸዋል፤ በመካከላቸው ያለውን ሁሉ እንደሚያጠቃልሉ ያውቃልና። በመጀመሪያ ሕልውናን ይጠይቃል—«ሞትና ሕይወት»፤ ቀጥሎ የተፈጠሩ አእምሮዎችን—«መላእክት፣ ግዛትና ኃይላት»፤ ቀጥሎ የጊዜን ጽንፎች—«ያለውና የሚመጣው»፤ ቀጥሎ የስፍራን—«ከፍታና ዝቅታ»፤ በመጨረሻም የተፈጠረውን ዓለም ሁሉ—«ልዩ ፍጥረት»። እያንዳንዳቸው እነዚህ ጽንፎች አንድ በአንድ ይመረመራሉ። ከጥልቁ በላይ ሊወዛወዝበት ያለውን የሰንሰለት ቀለበት ሁሉ እንደሚፈትን ሰው ነው። ሁሉንም በጥንቃቄና በትጋት ፈትኖአል፤ ከእነርሱም አንዳቸውም ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊቈርጡት እንደማይችሉ ተረድቶ ረክቶአል።

የአባታችንን የእግዚአብሔርን ፍቅር በሚገርም ሁኔታ በተሳሳተ መንገድ እንፈርዳለን፤ እንጠራጠረውማለን፤ ጭንቀታችንና መከራችን፣ ኃጢአታችንና ውድቀታችን ያነሰ እንዲወደን የሚያደርጉት ይመስለናል። ነገር ግን በቤት ውስጥ የእናትን እንክብካቤ አብልጦ የሚይዘው የጠንካሮቹ ልጆች መንጋ ሳይሆን፣ ራሱን መርዳትና ፍቅሯን መመለስ ሳይችል በአልጋው ላይ የተኛው ደካማና ሰላላ ሕይወት ነው። በዓለምም እንዲሁ ሞትና ሥቃይ፣ በሽታና ሐዘን፣ ኃጢአትና ውድቀት ከእግዚአብሔር ፍቅር ከመለየት ይልቅ አጥብቀው ያቀራርቡናል።

የተባረክህ ፍቅር ሆይ! ከኢየሱስ ልብ ወደ እኛ የሚወርድ፣ የእግዚአብሔር የዘላለም ፍቅር ዋና ባሕርይ—አንዳች ሊገታው፣ ሊያደርቀው ወይም ሊያቋርጠው አይችልም። ለእርሱ ያለን ፍቅራችን ሳይሆን ለእኛ ያለው የእርሱ ፍቅር ነው፤ ከእግዚአብሔር ፍቅር አንዳች ሊለየን ስለማይችል ለዘላለም መውደዱን ይቀጥላል፤ የሕይወቱንና የክብሩን ሙላት ሁሉ በእኛ ውስጥ ያፈስሳል። ችግሮቻችን ምንም ቢሆኑ፣ ድካማችንና ደዌያችን ምንም ቢሆን፣ የምንደላደል፣ የማንነቃነቅ፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛልን ሆነን እንጠበቃለን፤ በጉዳታችን እናተርፋለን፣ በውድቀታችን እንሳካለን፣ በሽንፈታችን ድል እንነሣለን፣ በወደደንም በእርሱ ሁልጊዜ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።

ጸሎት

አዎን፥ በሕይወት፥ በሐዘንና በኃጢአት ውስጥ እርሱ ይበቃኛል፤ በቅቶኛልና፤ ክርስቶስ መጨረሻ ነው፤ ክርስቶስ መጀመሪያ ነበርና፤ ክርስቶስ መጀመሪያ ነው፤ መጨረሻው ክርስቶስ ነውና።

ቀዳሚ ቀጣይ