ማለዳ ማለዳ
የኦክቶበር ወር

ምዕራፍ 10 · 36 ደቂቃ ንባብ · 47 ደቂቃ ማዳመጥ

የኦክቶበር ወር

ኦክቶበር 1

«ውዴ ሆይ፥ ለአንተ ያኖርሁትን አዲሱንና አሮጌውን ያማረ ፍሬ ሁሉ።» (መኃልየ መኃልይ 7:13)

ሙሽሪት የምታፈራውን ሁሉ ለኢየሱስ ልትሰጥ ትመኛለች። ልባችን «ያማረ ፍሬ ሁሉ» አለው፤ «አዲሱም አሮጌውም» አለ፤ ለውዳችንም ተከማችቶአል። በዚህ የበለጸገ የመከር ወራት የፍሬ ጊዜ፥ ጎተራዎቻችንን እንመርምር። አዲስ ፍሬዎች አሉን። አዲስ ሕይወት፥ አዲስ ደስታ፥ አዲስ ምስጋና ሊሰማን እንሻለን፤ አዲስ ውሳኔዎችን ልናደርግና በአዲስ ድካም ልንፈጽማቸው እንወዳለን፤ ልባችን በአዲስ ጸሎቶች ያብባል፤ ነፍሳችንም ለአዲስ ጥረት ራስዋን ቃል ታስገባለች። ነገር ግን አንዳንድ አሮጌ ፍሬዎችም አሉን። የመጀመሪያው ፍቅራችን አለ፤ ምንኛ የተመረጠ ፍሬ ነው! ኢየሱስም በእርሱ ደስ ይለዋል። የመጀመሪያው እምነታችን አለ፤ ምንም ሳይኖረን ሁሉን ገንዘብ ያደረግንበት ያ ቀላል እምነት። ጌታን መጀመሪያ ባወቅነው ጊዜ የነበረን ደስታ አለ፤ እናድሰው። የተስፋ ቃሎቹን የቀድሞ ትዝታዎቻችንን ይዘናል። እግዚአብሔር ምንኛ ታማኝ ሆኖአል! በሕመም ጊዜ አልጋችንን ምንኛ አለሰለሰልን! በጥልቅ ውኆች ውስጥ ምንኛ በጸጥታ ደግፎ አንሣን! በሚነድደው እቶን ውስጥ ምንኛ በጸጋ አዳነን። በእውነት አሮጌ ፍሬዎች ናቸው! ምሕረቶቹ ከራሳችን ጠጕር በልጠዋልና ብዙዎች አሉን። ስለ አሮጌ ኃጢአቶች ልንጸጸት ይገባናል፤ ነገር ግን እርሱ የሰጠን ንስሐዎች ነበሩን፤ በእነርሱም እያለቀስን ወደ መስቀሉ ደረስን፥ የደሙንም ዋጋ ተማርን። በዚህ ማለዳ አዲስም አሮጌም ፍሬዎች አሉን፤ ዋናው ነገር ግን ይህ ነው፤ ሁሉም ለኢየሱስ ተከማችተዋል። በእውነት ከሁሉ የሚሻሉና የሚወደዱ አገልግሎቶች ኢየሱስ ብቻ የነፍስ ዓላማ የሆነበት፥ ምንም ሳይቀላቀልበትም ክብሩ የጥረታችን ሁሉ ፍጻሜ የሆነበት ናቸው። ብዙ ፍሬዎቻችን ለውዳችን ብቻ ይከማቹ፤ እርሱ ከእኛ ጋር ሲሆን እናሳያቸው እንጂ በሰዎች ፊት አናውጣቸው። ኢየሱስ ሆይ፥ የአትክልታችንን በር እንቈልፋለን፤ በደም ላብህ ካጠጣኸው መሬት አንዲትን መልካም ፍሬ እንኳ ሊሰርቅብህ ማንም አይገባም። ኢየሱስ ሆይ፥ ውዳችን ሆይ፥ ያለን ሁሉ ያንተ ይሆናል፥ ያንተ ብቻ!

ኦክቶበር 2

«በሰማያት ስለ ተዘጋጀላችሁ ተስፋ።» (ቆላስይስ 1:5)

ስለሚመጣው ዘመን በክርስቶስ ያለን ተስፋ በዚህ ዓለም ያለው ደስታችን ዋና ምንጭና ዋና ምሰሶ ነው። ልንመኘው የምንችለው ሁሉ በዚያ ተሰጥቶናልና ስለ ሰማይ ዘወትር ማሰብ ልባችንን ያነቃቃል። በዚህ ደክመናል በድካምም ዝለናል፤ በዚያ ግን የድካም ላብ የሠራተኛውን ግንባር ከእንግዲህ የማያርስበት፥ ድካምም ለዘላለም የሚባረርበት የዕረፍት ምድር አለ። ለደከሙና ለዛሉ ሰዎች «ዕረፍት» የሚለው ቃል ሰማይን የተሞላ ነው። ዘወትር በጦር ሜዳ ላይ ነን፤ በውስጥ እጅግ እንፈተናለን፥ በውጭም በጠላቶች እጅግ እንታወካለን፤ ስለዚህ ሰላማችን ጥቂት ነው ወይም ምንም የለም፤ በሰማይ ግን ዓላማው በድል ከፍ ብሎ ሲውለበለብ፥ ሰይፍም ወደ ሰገባው ሲመለስ፥ የመዳናችን ራስ «መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ» ሲል ስንሰማ ድልን እንደሰታለን። ሐዘን በሐዘን ላይ ደርሶብናል፤ ነገር ግን መቃብር ወደማይታወቅበት ወደ ሟች ያልሆኑት ምድር እንሄዳለን። በዚህ ኃጢአት ዘወትር ያሳዝነናል፤ በዚያ ግን ፍጹማን ቅዱሳን እንሆናለን፤ የሚያረክስ ነገር ሁሉ ወደዚያ መንግሥት ፈጽሞ አይገባምና። መርዘኛ አረም በሰማያዊው እርሻ ትልሞች ውስጥ አይበቅልም። ኦ! ለዘላለም በስደት እንዳትኖር፥ በዚህ ምድረ በዳ ለዘላለም እንዳትቀመጥ፥ ነገር ግን ፈጥነህ ከነዓንን እንድትወርስ ደስታ አይደለምን? ቢሆንም ስለ ወደ ፊቱ እያለምን የአሁኑን እንረሳለን ተብሎ ከቶ አይነገርብን፤ ወደ ፊቱ የሚመጣው የአሁኑን ለከፍተኛ ጥቅም ይቀድሰው። በእግዚአብሔር መንፈስ የሰማይ ተስፋ በጎነትን ለማፍራት ከሁሉ የበረታ ኃይል ነው፤ የደስተኛ ጥረት ምንጭ ነው፤ የደስተኛ ቅድስናም የማዕዘን ራስ ድንጋይ ነው። ይህ ተስፋ በውስጡ ያለው ሰው የጌታ ደስታ ኃይሉ ነውና ሥራውን በብርታት ያከናውናል። የሚመጣው ዓለም ተስፋ የባላጋራውን የሚነድዱ ፍላጾች ያስመልሳልና ፈተናን በቅንዓት ይዋጋል። በሚመጣው ዓለም ዋጋን ይጠባበቃልና ያለ አሁን ዋጋ ሊደክም ይችላል።

ኦክቶበር 3

«ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?» (ዕብራውያን 1:14)

መላእክት የእግዚአብሔር ቅዱሳን የማይታዩ አገልጋዮች ናቸው፤ እግራችን በድንጋይ እንዳይሰናከል በእጆቻቸው ያነሡናል። ለጌታቸው ያላቸው ታማኝነት በፍቅሩ ልጆች ላይ ጥልቅ አሳብ እንዲያሳድሩ ያደርጋቸዋል፤ የጠፋው ልጅ በምድር ወዳለው ወደ አባቱ ቤት በመመለሱ ደስ ይላቸዋል፤ አማኙም በላይ ወዳለው ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ሲደርስ ይቀበሉታል። በቀድሞ ዘመን የእግዚአብሔር ልጆች በሚታይ መልክ ሲገለጡላቸው ይታደሉ ነበር፤ ዛሬም ምንም ባናያቸው፥ ሰማይ አሁንም ተከፍቶአል፤ የእግዚአብሔርም መላእክት መዳንን የሚወርሱትን ይጐበኙ ዘንድ በሰው ልጅ ላይ ይወጣሉ ይወርዱማል። ሱራፌል እጅግ የተወደዱትን ሰዎች ከንፈር ይዳስሱ ዘንድ ከመሠዊያው በተወሰደ የፍም ፍንጣሪ አሁንም ይበርራሉ። ዓይኖቻችን ቢከፈቱ በጌታ ባሪያዎች ዙሪያ የእሳት ፈረሶችንና የእሳት ሰረገሎችን ባየን ነበር፤ የንጉሣዊውን ዘር የሚጠብቁና የሚከላከሉ ወደ ሆኑት ወደ አእላፋት መላእክት ደርሰናልና። የስፔንሰር ስንኝ የቅኔ ፈጠራ አይደለም፤ እንዲህ ሲል ይዘምራል፤

«ስንት ጊዜ በወርቃማ ክንፎቻቸው

የሚያልፈውን ሰማይ እንደ ፈጣን መልእክተኛ ይሰነጥቃሉ፤

በርኩሳን አጋንንት ላይ የምንዋጋውን እኛን ሊረዱ!»

የሰማይ ብሩሃን ባለሟሎች በፈቃዳቸው አገልጋዮቻቸው ሲሆኑ፥ የተመረጡት ወደ ምን ያለ ክብር ከፍ ይላሉ! እንከን ከሌለባቸው ሰማያውያን ጋር ኅብረት ስላለን ወደ ምን ያለ ኅብረት ተነሥተናል! የእግዚአብሔር ሰረገሎች ሁሉ፥ ሀያ ሺው ሁሉ፥ ለመዳናችን ስለ ታጠቁ ምንኛ በሚገባ ተጠብቀናል! ይህን ሁሉ ለማን ባለ ዕዳ ነን? ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም በእኛ ዘንድ የተወደደ ይሁን፤ በእርሱ ከአለቅነትና ከሥልጣን ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ እንድንቀመጥ ተደርገናልና። ሰፈሩ በሚፈሩት ዙሪያ የሆነ እርሱ ነው፤ እግሩ በዘንዶው ላይ ያለ እውነተኛው ሚካኤል እርሱ ነው። ኢየሱስ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን! የእግዚአብሔር የፊቱ መልአክ ሆይ፥ ይህ ቤተ ሰብ የማለዳ ስእለቱን ለአንተ ያቀርባል።

ኦክቶበር 4

«በማታ ጊዜ ብርሃን ይሆናል።» (ዘካርያስ 14:7)

ብዙ ጊዜ በማታ ጊዜ ብርሃን እንደሚሆን ረስተን ወደ እርጅና ዘመን በፍርሃት እንመለከታለን። ለብዙ ቅዱሳን እርጅና በሕይወታቸው ከሁሉ የተመረጠ ወቅት ነው። መርከበኛው ወደ ዘላለማዊነት ዳርቻ ሲቀርብ ለስላሳ አየር ጉንጩን ያራግባል፤ ባሕሩን የሚያናውጡ ማዕበሎች ይቀንሳሉ፤ ጥልቅ፥ ጸጥ ያለና የተከበረ ጸጥታ ይነግሣል። ከእርጅና መሠዊያ ላይ የወጣትነት እሳት ብልጭታዎች አልፈዋል፤ ይበልጥ እውነተኛው የልባዊ ስሜት ነበልባል ግን ይቀራል። ተጓዦቹ የሰማይ ቀናት በምድር ላይ እንዳሉ የሆኑበት ወደዚያ ደስተኛ አገር ወደ ቡላ ምድር ደርሰዋል። መላእክት ይጐበኙታል፤ ሰማያዊ ነፋሳት ይነፍሱበታል፤ የገነት አበቦች ይበቅሉበታል፤ አየሩም በሱራፌል ዝማሬ ተሞልቶአል። አንዳንዶች በዚያ ለዓመታት ይኖራሉ፤ ሌሎች ከመሄዳቸው ጥቂት ሰዓታት ብቻ በፊት ይደርሱበታል፤ ነገር ግን በምድር ላይ ያለ ኤደን ነው። በጥላው ዱሮች ውስጥ የምንደገፍበትንና የፍጻሜው ጊዜ እስኪመጣ ድረስ በተስፋ የምንረካበትን ጊዜ ብንናፍቅ ይገባናል። የምትጠልቀው ፀሐይ በሰማይ ከፍ ብላ ከነበረችበት ይልቅ ትልቅ ትመስላለች፤ የክብር ግርማም በመጥለቅዋ ዙሪያ ያሉትን ደመናዎች ሁሉ ያቀልማል። በድካም የሚፈጸም ኃይል በትዕግሥት ሁሉን ስለሚሸከም፥ ሕመም የእርጅናን ጣፋጭ የምሽት ብርሃን ጸጥታ አያፈርስም። የተመረጠ ልምምድ የበሰሉ ፍሬዎች የሕይወት ምሽት ብርቅ ማዕድ ሆነው ይለቀማሉ፤ ነፍስም ለዕረፍት ራስዋን ታዘጋጃለች።

የጌታ ሕዝብ ደግሞ በሞት ሰዓት ብርሃንን ይደሰታሉ። አለማመን ያለቅሳል፤ ጥላዎች ይወድቃሉ፥ ሌሊቱ እየመጣ ነው፥ ሕልውና እያለቀ ነው ይላል። እምነት ግን፥ አይደለም፥ ሌሊቱ አልፎአል፥ እውነተኛው ቀን ቀርቦአል ብላ ትጮኻለች። ብርሃን መጥቶአል፤ የዘላለማዊነት ብርሃን፥ የአባት ፊት ብርሃን። እግርህን በአልጋው ላይ ሰብስብ፤ የሚጠባበቁትን የመናፍስት ጭፍሮች እይ! መላእክት ይዘውህ ይሄዳሉ። የተወደድህ ሆይ፥ ደኅና ሁን፤ ሄደሃል፤ እጅህን ታውለበልባለህ። አሁን ብርሃን ነው። የዕንቍ በሮች ተከፍተዋል፤ የወርቅ መንገዶች በኢያስጲድ ብርሃን ያበራሉ። እኛ ዓይኖቻችንን እንሸፍናለን፤ አንተ ግን የማይታየውን ታያለህ፤ ወንድም ሆይ፥ ደኅና ሁን፤ እኛ ገና ያላገኘነውን የምሽት ብርሃን አገኘህ።

ኦክቶበር 5

«ተነሥቶም በላ ጠጣም፥ በዚያም መብል ኃይል አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ።» (1ኛ ነገሥት 19:8)

ቸሩ አምላካችን የሚሰጠን ብርታት ሁሉ ለአገልግሎት እንጂ ለቅንጦት ወይም ለትምክህት አይደለም። ነቢዩ ኤልያስ ከክትክታው በታች ተኝቶ ሳለ በፍም ላይ የተጋገረውን እንጐቻና በራስጌው የተቀመጠውን የውኃ ማሰሮ ባገኘ ጊዜ፥ ተዘርግቶ በምቾት ይዝናና ዘንድ በጣፋጭ ምግብ የሚደሰት ጨዋ ሰው አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ በዚያ ኃይል ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ኮሬብ እየተጓዘ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እንዲሄድ ታዘዘ። ጌታ ደቀ መዛሙርቱን ከእርሱ ጋር «ኑ፥ ምሳ ብሉ» ብሎ በጠራቸው ጊዜ፥ ግብዣው ካለቀ በኋላ ጴጥሮስን «በጎቼን አሰማራ» አለው፤ ደግሞም «ተከተለኝ» ብሎ ጨመረ። ለእኛም እንዲሁ ነው፤ ብርታታችንን በጌታ አገልግሎት እናውል ዘንድ የሰማይን እንጀራ እንበላለን። ወደ ፋሲካ እንመጣለን፤ ረኃባችንን ካረካን በኋላ ወዲያው እንድንነሣ ወገባችንን ታጥቀን በትራችንንም በእጃችን ይዘን የፋሲካውን በግ እንበላለን። አንዳንድ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ለመኖር ይሻሉ፤ ነገር ግን ለክርስቶስ ለመኖር ያን ያህል አይጓጉም። ምድር ለሰማይ መዘጋጃ ልትሆን ይገባታል፤ ሰማይም ቅዱሳን ከሁሉ ይበልጥ የሚመገቡበትና ከሁሉ ይበልጥ የሚሠሩበት ስፍራ ነው። በጌታችን ማዕድ ይቀመጣሉ፤ በመቅደሱም ቀንና ሌሊት ያገለግሉታል። ሰማያዊ ምግብ ይበላሉ፤ ፍጹም አገልግሎትም ያቀርባሉ። አማኝ ሆይ፥ ከክርስቶስ በየዕለቱ በምታገኘው ብርታት ለእርሱ ሥራ። አንዳንዶቻችን ጌታችን ጸጋውን የሰጠን ስለ ምን ዓላማ እንደ ሆነ ገና ብዙ ልንማር ይገባናል። የግብጽ በድን ስንዴን ለዘመናት እንዲያድግ ዕድል ሳይሰጠው እንደ ያዘ፥ የከበሩትን የእውነት ፍሬዎች ይዘን ልንቀመጥ አይገባንም፤ ልንዘራቸውና ልናጠጣቸው ይገባናል። ጌታ በተጠማችው ምድር ላይ ዝናብን የሚያወርደው፥ ሞቃቱንም የፀሐይ ብርሃን የሚሰጠው ስለ ምንድር ነው? እነዚህ ሁሉ የምድር ፍሬዎች ለሰው ምግብ እንዲሰጡ እንዲረዱ አይደለምን? እንዲሁም ጌታ የታደሰውን ብርታታችንን ከዚያ በኋላ ለክብሩ መስፋፋት እንድናውለው ነፍሳችንን ይመግባል ያድሳልም።

ኦክቶበር 6

«እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም።» (ዮሐንስ 4:14)

በኢየሱስ የሚያምን ሰው አሁን የሚያጠግበውና ለዘላለምም የሚያረካው በጌታው ውስጥ ያገኛል። አማኝ ቀኖቹ ከመጽናናት እጦት የተነሣ የሚያደክሙት፥ ሌሊቶቹም ልብን የሚያበረታ አሳብ በማጣት የሚረዝሙበት ሰው አይደለም፤ በሃይማኖቱ እንዲህ ያለ የደስታ ምንጭ፥ እንዲህ ያለ የመጽናናት ፏፏቴ ያገኛልና ይረካል ደስተኛም ነው። በወህኒ ቤት ብታኖረው መልካም ጓደኝነትን ያገኛል፤ በምድረ በዳ ብታስቀምጠው የሰማይን እንጀራ ይበላል፤ ከወዳጅነት ብታባርረው «ከወንድም ይልቅ የሚጠጋ ወዳጅን» ያገኛል። ቅሎቹን ሁሉ አድርቅ፤ ከዘመናት ዓለት በታች ጥላን ያገኛል፤ የምድራዊ ተስፋዎቹን መሠረት ናድ፤ ልቡ ግን በእግዚአብሔር እየታመነ ጸንቶ ይኖራል። ኢየሱስ እስኪገባበት ድረስ ልብ እንደ መቃብር የማይጠግብ ነው፤ ከዚያ በኋላ ግን ሞልቶ የሚፈስ ጽዋ ይሆናል። በክርስቶስ እንዲህ ያለ ሙላት ስላለ እርሱ ብቻውን የአማኙ ሁሉ ነገር ነው። እውነተኛው ቅዱስ በኢየሱስ ሁሉን ቻይነት ፈጽሞ ስለሚረካ ከእንግዲህ አይጠማም፤ ከሕያው ምንጭ ይበልጥ ጠልቆ ለመጠጣት ካልሆነ በቀር። አማኝ ሆይ፥ በዚያ ጣፋጭ መንገድ ትጠማለህ፤ የፍቅር ናፍቆት እንጂ የሕመም ጥም አይሆንም፤ የኢየሱስን ፍቅር ይበልጥ ሙሉ በሙሉ ለመደሰት መናፈቅ ጣፋጭ ነገር ሆኖ ታገኘዋለህ። በቀድሞ ዘመን አንድ ሰው እንዲህ አለ፤ «ባልዲዬን ወደ ጕድጓዱ ብዙ ጊዜ አውርጃለሁ፤ አሁን ግን ኢየሱስን መጠማቴ እጅግ የማይጠግብ ስለ ሆነ፥ ጕድጓዱን ራሱን ወደ ከንፈሮቼ አስጠግቼ ያለማቋረጥ ልጠጣ እናፍቃለሁ።» አማኝ ሆይ፥ ይህ አሁን የልብህ ስሜት ነውን? ምኞቶችህ ሁሉ በኢየሱስ እንደ ረኩ፥ ስለ እርሱ ይበልጥ ከማወቅና ከእርሱ ጋር ይበልጥ የቀረበ ኅብረት ከማድረግ በቀር አሁን ሌላ ፍላጎት እንደሌለህ ይሰማሃልን? እንግዲያስ ዘወትር ወደ ምንጩ ና፤ የሕይወትንም ውኃ በነጻ ውሰድ። ኢየሱስ ከመጠን በላይ እንደምትወስድ ከቶ አያስብም፤ ነገር ግን «ወዳጆች ሆይ፥ ጠጡ፥ እስክትረኩም ድረስ ጠጡ» እያለ ሁልጊዜ ይቀበልሃል።

ኦክቶበር 7

«ባሪያህን ስለ ምን አስጨነቅኸው?» (ዘኍልቍ 11:11)

የሰማዩ አባታችን እምነታችንን ሊፈትን ብዙ ጊዜ መከራን ይልክብናል። እምነታችን አንዳች ዋጋ ያለው ቢሆን ፈተናውን ይቋቋማል። ወርቅ የተቀባ ነገር እሳትን ይፈራል፤ ወርቅ ግን አይፈራም፤ የሐሰት ዕንቍ በአልማዝ መነካትን ይፈራል፤ እውነተኛው ዕንቍ ግን ማንኛውንም ፈተና አይፈራም። ወዳጆች ታማኞች ሲሆኑ፥ ሥጋ በጤና ሲሞላ፥ ንግድም ትርፍ ሲያስገኝ ብቻ በእግዚአብሔር ሊታመን የሚችል እምነት ደካማ እምነት ነው፤ ነገር ግን ወዳጆች ሲሄዱ፥ ሥጋ ሲታመም፥ መንፈስ ሲደቅቅ፥ የአባታችንም ፊት ብርሃን ሲሰወር፥ የጌታን ታማኝነት የሚይዝ እምነት እውነተኛ እምነት ነው። በከፋው መከራ ውስጥ «ቢገድለኝም እንኳ በእርሱ እታመናለሁ» ሊል የሚችል እምነት ከሰማይ የተወለደ እምነት ነው። ጌታ ባሪያዎቹን የሚያስጨንቃቸው ራሱን ሊያከብር ነው፤ የገዛ እጁ ሥራ በሆኑት በሕዝቡ ጸጋዎች እጅግ ይከብራልና። «መከራ ትዕግሥትን፥ ትዕግሥትም ፈተናን፥ ፈተናም ተስፋን» ሲያደርግ፥ ጌታ በእነዚህ በሚያድጉ በጎነቶች ይከብራል። አውታሮቹ ሳይነኩ ቢቀሩ የበገናን ዜማ ፈጽሞ ባላወቅን ነበር፤ የወይን ፍሬ በመጭመቂያው ባይረገጥ ጭማቂውን ባልተደሰትን ነበር፤ ቀረፋ ባይጨመቅና ባይወቀጥ ጣፋጭ መዓዛውን ባላገኘን ነበር፤ ፍሙ ፈጽሞ ባይቃጠል የእሳትን ሙቀት ባልተሰማን ነበር። የታላቁ ሠራተኛ ጥበብና ኃይል የምሕረቱ ዕቃዎች እንዲያልፉባቸው በተፈቀዱላቸው ፈተናዎች ይገለጣሉ። የአሁኑ መከራዎች ደግሞ የወደ ፊቱን ደስታ ያበዛሉ። የብርሃኑን ውበት ለማውጣት በሥዕሉ ውስጥ ጥላዎች ሊኖሩ ይገባል። የኃጢአትን እርግማንና የምድርን ኀዘን ባናውቅ ኖሮ በሰማይ እንዲህ እጅግ ብፁዓን ልንሆን እንችል ነበርን? ሰላም ከግጭት በኋላ፥ ዕረፍትም ከድካም በኋላ ይበልጥ አይጣፍጥምን? ያለፉት መከራዎች ትዝታ የከበሩትን ሰዎች ብፅዕና አያበዛምን? አጭሩን ማሰላሰላችንን በጀመርንበት ጥያቄ ላይ ሌሎች ብዙ የሚያጽናኑ መልሶች አሉ፤ ቀኑን ሁሉ በእርሱ ላይ እናሰላስል።

ኦክቶበር 8

«ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ።» (ሉቃስ 5:4)

ከዚህ ታሪክ የሰውን መሣሪያነት አስፈላጊነት እንማራለን። የዓሣው ማጥመድ ተአምራዊ ነበረ፤ ሆኖም ዓሣ አጥማጁም ሆነ ታንኳው ወይም የማጥመጃ መሣሪያው አልተናቁም፤ ነገር ግን ዓሣዎቹን ለመያዝ ሁሉም ተጠቀመባቸው። እንዲሁም ነፍሳትን በማዳን እግዚአብሔር በመሣሪያዎች ይሠራል፤ የአሁኑ የጸጋ ሥርዓት እስካለ ድረስ እግዚአብሔር የሚያምኑትን በስብከት ሞኝነት ሊያድን ደስ ይለዋል። እግዚአብሔር ያለ መሣሪያ ሲሠራ በእርግጥ ይከብራል፤ ነገር ግን በምድር ላይ ከሁሉ ይበልጥ የሚከብርበት መንገድ እንደ ሆነ የመሣሪያነትን ዕቅድ ራሱ መርጦአል። መሣሪያዎች በራሳቸው ፈጽሞ ዋጋ ቢሶች ናቸው። «አቤቱ፥ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም።» የዚህ ምክንያቱ ምን ነበረ? የራሳቸውን ሙያ የሚሠሩ ዓሣ አጥማጆች አልነበሩምን? በእውነት ጀማሪዎች አልነበሩም፤ ሥራውን ያውቁ ነበር። ድካሙን ያለ ብልሃት ሠርተውት ነበርን? አይደለም። ትጋት ጐድሎአቸው ነበርን? አይደለም፤ ደክመዋል። ጽናት ጐድሎአቸው ነበርን? አይደለም፤ ሌሊቱን ሁሉ ደክመዋል። በባሕሩ ውስጥ ዓሣ አንሶ ነበርን? በእርግጥ አይደለም፤ ጌታ እንደ መጣ በመንጋ ወደ መረቡ ዋኝተው መጥተዋልና። እንግዲያስ ምክንያቱ ምንድር ነው? ከኢየሱስ መገኘት ተለይተው መሣሪያዎች በራሳቸው ኃይል ስለሌላቸው አይደለምን? «ያለ እርሱ ምንም ልናደርግ አንችልም።» ከክርስቶስ ጋር ግን ሁሉን ልናደርግ እንችላለን። የክርስቶስ መገኘት ስኬትን ይሰጣል። ኢየሱስ በጴጥሮስ ታንኳ ውስጥ ተቀመጠ፤ ፈቃዱም በምሥጢራዊ ኃይል ዓሣውን ወደ መረቡ ሳበው። ኢየሱስ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከፍ ከፍ ሲል፥ መገኘቱ የቤተ ክርስቲያን ኃይል ነው፤ የንጉሥ እልልታ በመካከልዋ አለ። «እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።» በዚህ ማለዳ ወደ ላይ በእምነት፥ በዙሪያችንም በጽኑ ጭንቀት እየተመለከትን ነፍሳትን ወደ ማጥመድ ሥራችን እንውጣ። ሌሊት እስኪመጣ ድረስ እንድከም፤ በከንቱም አንደክምም፤ መረቡን እንድንጥል የሚያዝዘን እርሱ በዓሣ ይሞላዋልና።

ኦክቶበር 9

«ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ ለሚችለው።» (ይሁዳ 24)

በአንድ በኩል ወደ ሰማይ የሚወስደው መንገድ እጅግ አስተማማኝ ነው፤ በሌላ በኩል ግን እንደ እርሱ አደገኛ የሆነ መንገድ የለም። በችግሮች የተከበበ ነው። አንዲት የተሳሳተች እርምጃ (ጸጋ ከሌለ እርስዋን መውሰድ ምንኛ ቀላል ነው!)፥ እኛም ወደ ታች እንወድቃለን። አንዳንዶቻችን የምንረግጠው መንገድ ምንኛ የሚያንሸራትት ነው! ከዘማሪው ጋር «እግሮቼ ሊሰናከሉ ጥቂት ቀረ፥ አረማመዴም ሊንሸራተት ጥቂት ቀረ» ብለን ስንት ጊዜ ልንጮኽ ይገባናል! ብርቱዎችና እግራቸው የማይንሸራተት ተራራ ወጪዎች ብንሆን ይህ ያን ያህል ባልከፋ ነበር፤ ነገር ግን በራሳችን ምንኛ ደካሞች ነን! በተሻሉት መንገዶች ፈጥነን እንደናቀፋለን፤ በለሰለሱት ጎዳናዎችም ቶሎ እንሰናከላለን። እነዚህ የደከሙ ጕልበቶቻችን የሚንገዳገደውን ክብደታችንን ሊሸከሙ በጭንቅ ይችላሉ። ገለባ ሊጥለን ይችላል፤ ጠጠርም ሊያቈስለን ይችላል፤ በእምነት ጉዞ የመጀመሪያ እርምጃዎቻችንን እየተንቀጠቀጥን የምንወስድ ሕፃናት ብቻ ነን፤ የሰማዩ አባታችን በክንዳችን ይይዘናል፤ አለዚያ ፈጥነን በወደቅን ነበር። ኦ፥ ከመውደቅ ከተጠበቅን፥ በየዕለቱ የሚጠብቀንን ታጋሽ ኃይል ምንኛ ልንባርክ ይገባናል! ወደ ኃጢአት ምንኛ ያዘነበልን፥ አደጋን ለመምረጥ ምንኛ የፈጠንን፥ ራሳችንን ወደ ታች ለመጣል ያለን ዝንባሌ ምንኛ የበረታ እንደ ሆነ አስብ፤ እነዚህ አሳቦችም ከቶ ከዘመርነው ይልቅ አጣፍጠን «ከመሰናከል ሊጠብቀን ለሚችለው ክብር ይሁን» ብለን እንድንዘምር ያደርጉናል። ሊገፉን የሚሞክሩ ብዙ ጠላቶች አሉን። መንገዱ ሸካራ ነው፤ እኛም ደካሞች ነን፤ ከዚህም በላይ ጠላቶች በድብቅ ያደባሉ፤ ባልጠበቅናቸው ጊዜ እየሮጡ ወጥተው ሊያደናቅፉን ወይም በአቅራቢያው ካለው ገደል ሊወረውሩን ይጣጣራሉ። ሊያጠፉን ከሚሹት ከእነዚህ የማይታዩ ጠላቶች ሊጠብቀን የሚችል ሁሉን የሚችለው ክንድ ብቻ ነው። እንዲህ ያለው ክንድ ስለ መከላከያችን ተሰልፎአል። ተስፋ የሰጠው የታመነ ነው፤ ከመሰናከልም ሊጠብቀን ይችላል፤ ስለዚህ የገዛ ድካማችንን በጥልቅ እያወቅን፥ በፍጹም ደኅንነታችን ጽኑ እምነትን ልንይዝና በደስታ በመተማመን እንዲህ ልንል እንችላለን፤

«ምድርና ሲኦል በእኔ ላይ ቢተባበሩ፥

መለኮታዊ ኃይል ግን ከጎኔ አለ፤

ኢየሱስ ሁሉ ነው፥ እርሱም የእኔ ነው!»

ኦክቶበር 10

«በክብሩም ፊት ነውር የሌላችሁ አድርጎ።» (ይሁዳ 24)

«ነውር የሌላችሁ!» የሚለውን ያንን ድንቅ ቃል በአእምሮህ አውጣና አውርድ። አሁን ከእርሱ እጅግ ርቀናል፤ ነገር ግን ጌታችን በፍቅር ሥራው ከፍጽምና በታች ከቶ ስለማይቆም፥ አንድ ቀን እንደርስበታለን። ሕዝቡን እስከ መጨረሻ የሚጠብቃቸው አዳኝ፥ በመጨረሻ «እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር የሌለባት ቅድስትና ያለ ነውር የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን» አድርጎ ለራሱ ያቀርባቸዋል። በአዳኙ ዘውድ ያሉት ዕንቍዎች ሁሉ ከሁሉ የላቀ ጥራት ያላቸውና አንዲት እንከን የሌለባቸው ናቸው። የበጉን ሚስት የሚያጅቡት የክብር ደንገጡሮች ሁሉ እድፈትና ጉድፍ የሌለባቸው ንጹሓት ደናግል ናቸው። ነገር ግን ኢየሱስ እንዴት ነውር የሌለን ያደርገናል? ከእግዚአብሔር ንጹሕ መልአክ የሚያህል ነጭና ውብ እስክንሆን ድረስ በገዛ ደሙ ከኃጢአታችን ያጥበናል፤ በጽድቁም እንለብሳለን፤ የሚለብሰውን ቅዱስ በእርግጥ ነውር የሌለበት በሚያደርገው በዚያ ጽድቅ፤ አዎን፥ በእግዚአብሔር ፊት ፍጹም። በእርሱ ዓይን እንኳ የማንወቀስና የማንነቀፍ እንሆናለን። ሕጉ በእኛ ላይ ክስ የሌለው ብቻ አይሆንም፤ ነገር ግን በእኛ ይከብራል። ከዚህም በላይ በውስጣችን ያለው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ፈጽሞ ይፈጸማል። ወደ ኃጢአት የሚቀር ምንም ዝንባሌ እንዳይኖረን እጅግ ፍጹማን ቅዱሳን ያደርገናል። ማስተዋል፥ ትዝታ፥ ፈቃድ፥ ኃይልና ስሜት ሁሉ ከክፋት ባርነት ነጻ ይወጣሉ። እግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆነ እኛም ቅዱሳን እንሆናለን፤ በፊቱም ለዘላለም እንኖራለን። ቅዱሳን በሰማይ ከስፍራቸው ውጭ አይሆኑም፤ ውበታቸው ለእነርሱ እንደ ተዘጋጀው ስፍራ ውበት ታላቅ ይሆናል። የዘላለም ደጆች ከፍ በሚሉበትና እኛም ለርስቱ የበቃን ሆነን ከቅዱሳን ጋር በብርሃን በምንኖርበት በዚያ ሰዓት ያለው ፍሥሓ ምንኛ ነው! ኃጢአት ሄዶአል፥ ሰይጣን ተዘግቶበታል፥ ፈተና ለዘላለም አልፎአል፥ እኛም በእግዚአብሔር ፊት «ነውር የሌለን» ሆነናል፤ ይህ በእውነት ሰማይ ይሆናል! በደም ከታጠቡት ሠራዊት ሁሉ በሙሉ ዝማሬ ፈጥኖ የሚፈስሰውን የዘላለም ምስጋና መዝሙር አሁን እየተለማመድን ደስ ይበለን፤ በዙፋኑ ፊት ለሚሆነው ፍሥሓችን መቅድም አድርገን ዳዊት በታቦቱ ፊት ያደረገውን ደስታ እንምሰል።

ኦክቶበር 11

«ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማያት ወዳለው ወደ እግዚአብሔር እናንሣ።» (ሰቆቃው ኤርምያስ 3:41)

የጸሎት ተግባር ብቁ አለመሆናችንን ያስተምረናል፤ ይህም እንደ እኛ ላሉ ትዕቢተኞች ፍጡራን እጅግ ጤናማ ትምህርት ነው። እግዚአብሔር ስለ እነርሱ እንድንጸልይ ሳያስገድደን ሞገሱን ቢሰጠን፥ ምን ያህል ድሆች እንደ ሆንን ከቶ ባላወቅን ነበር፤ እውነተኛ ጸሎት ግን የጕድለቶች ዝርዝር፥ የፍላጎቶች መዝገብ፥ የተሰወረ ድህነት መገለጥ ነው። ወደ መለኮታዊ ባለ ጠግነት የሚቀርብ ልመና ሆኖ ሳለ፥ የሰውን ባዶነት የሚናዘዝ ነው። የክርስቲያን ከሁሉ ጤናማ ሁኔታ ሁልጊዜ በራሱ ባዶ ሆኖ ለሚያስፈልገው ዘወትር በጌታ መደገፍ ነው፤ ሁልጊዜ በራሱ ድሀ በኢየሱስ ግን ባለ ጠጋ መሆን፤ በግሉ እንደ ውኃ ደካማ፥ በእግዚአብሔር ግን ታላላቅ ሥራዎችን ለማድረግ ብርቱ መሆን ነው፤ ስለዚህም የጸሎት ጥቅም ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን እያመለከ ፍጡሩን በሚገባው ስፍራ፥ በትቢያ ውስጥ ያኖረዋልና። ጸሎት ከሚያመጣው መልስ ተለይቶ በራሱ ለክርስቲያን ታላቅ ጥቅም ነው። ሯጭ በየዕለቱ ልምምድ ለሩጫው ብርታትን እንደሚያገኝ፥ እንዲሁ ለታላቁ የሕይወት ሩጫ በቅዱሱ የጸሎት ድካም ኃይልን እናገኛለን። ጸሎት ከደመናት በላይ መውጣትን ይማሩ ዘንድ የእግዚአብሔርን ንስር ጫጩቶች ክንፍ ያለብሳል። ጸሎት የእግዚአብሔርን ጦረኞች ወገብ ያስታጥቃል፤ ጅማታቸው የጠነከረና ጡንቻቸው የጸና ሆኖ ወደ ውጊያ ይልካቸዋል። ልባዊ ተማጣኝ ፀሐይ ከምሥራቅ እልፍኝ እንደሚወጣ፥ እንደ ኃያል ሰው በሩጫው ደስ እያለው ከእልፍኙ ይወጣል። ጸሎት ከኢያሱ ሰይፍ ይልቅ አማሌቃውያንን የሚያሸንፈው ያ የሙሴ ከፍ ያለ እጅ ነው፤ ለሶርያውያን ሽንፈትን የሚያበስር ከነቢዩ እልፍኝ የተወረወረው ፍላጻ ነው። ጸሎት የሰውን ድካም በመለኮታዊ ኃይል ያስታጥቃል፤ የሰውን ስንፍና ወደ ሰማያዊ ጥበብ ይለውጣል፤ ለተጨነቁ ሟቾችም የእግዚአብሔርን ሰላም ይሰጣል። ጸሎት የማያደርገውን ምን እንደ ሆነ አናውቅም! ታላቅ አምላክ ሆይ፥ ስለ ምሕረት ዙፋን እናመሰግንሃለን፤ እርሱ የድንቅ ቸርነትህ የተመረጠ ማስረጃ ነው። በዚህ ቀን ሁሉ በሚገባ እንድንጠቀምበት እርዳን!

ኦክቶበር 12

«በትእዛዝህ አሰላስላለሁ።» (መዝሙር 119:15)

ብቸኝነት ከጓደኝነት፥ ዝምታም ከንግግር የሚሻልበት ጊዜ አለ። ብቻችንን ብንሆን፥ እግዚአብሔርን ብንጠብቅ፥ በቃሉም ላይ በማሰላሰል ለአገልግሎቱ ድካም መንፈሳዊ ብርታትን ብንሰበስብ የተሻልን ክርስቲያኖች በሆንን ነበር። በእግዚአብሔር ነገሮች ላይ ልናሰላስል ይገባናል፤ እንዲህ በማድረግ እውነተኛውን ምግብ ከእነርሱ እናገኛለንና። እውነት የወይን ዘለላ ይመስላል፤ ከእርሱ የወይን ጠጅ ብንሻ ልንጨፈልቀው ይገባናል፤ ብዙ ጊዜ ልንጨምቀውና ልንጭመቀው ይገባናል። የረጋጩ እግሮች በደስታ በዘለላዎቹ ላይ ሊወርዱ ይገባል፤ አለዚያ ጭማቂው አይፈስስም፤ ወይኑንም በሚገባ ሊረግጡት ይገባል፤ አለዚያ ከከበረው ፈሳሽ ብዙው ይባክናል። እንዲሁም ከእውነት ዘለላዎች የመጽናናትን ወይን ጠጅ ብናገኝ፥ በማሰላሰል ልንረግጣቸው ይገባናል። ሰውነታችን የሚደገፈው ምግብን ወደ አፍ በማስገባት ብቻ አይደለም፤ ጡንቻውን፥ ነርቩን፥ ጅማቱንና አጥንቱን በእውነት የሚመግበው ሂደት የመፈጨት ሂደት ነው። የውጭው ምግብ ከውስጣዊው ሕይወት ጋር የሚዋሐደው በመፈጨት ነው። ነፍሳችን የምትመገበው ለጥቂት ጊዜ ይህን፥ ከዚያም ያን፥ ከዚያም ሌላውን የመለኮታዊ እውነት ክፍል በመስማት ብቻ አይደለም። መስማት፥ ማንበብ፥ ማስተዋልና መማር ጥቅማቸው ይፈጸም ዘንድ ሁሉም በውስጥ መፈጨትን ይሻሉ፤ የእውነትም ውስጣዊ መፈጨት በአብዛኛው በእርሱ ላይ በማሰላሰል ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ብዙ ስብከቶችን ቢሰሙም በመለኮታዊው ሕይወት የሚያደርጉት እድገት ዝግ ያለ የሆነው ስለ ምንድር ነው? የጸሎት እልፍኛቸውን ስለሚተዉና በእግዚአብሔር ቃል ላይ በአሳብ ስለማያሰላስሉ ነው። ስንዴውን ይወዳሉ፤ ነገር ግን አይፈጩትም፤ እህሉን ይሻሉ፤ ነገር ግን ሊሰበስቡት ወደ እርሻ አይወጡም፤ ፍሬው በዛፉ ላይ ተንጠልጥሎአል፤ ነገር ግን አይለቅሙትም፤ ውኃው በእግራቸው ሥር ይፈስሳል፤ ነገር ግን ሊጠጡት አያጎነብሱም። አቤቱ፥ ከእንዲህ ያለ ስንፍና አድነን፤ በዚህ ማለዳም ውሳኔያችን ይህ ይሁን፤ «በትእዛዝህ አሰላስላለሁ።»

ኦክቶበር 13

«እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን … ንስሐ ያደርጋልና።» (2ኛ ቆሮንቶስ 7:10)

ስለ ኃጢአት የሚሆን እውነተኛ መንፈሳዊ ልቅሶ የእግዚአብሔር መንፈስ ሥራ ነው። ንስሐ በተፈጥሮ አትክልት ውስጥ ለማደግ እጅግ የተመረጠች አበባ ናት። ዕንቍ በተፈጥሮ በዛጎሎች ውስጥ ይበቅላል፤ ንስሐ ግን መለኮታዊ ጸጋ በውስጣቸው ካልሠራው በቀር በኃጢአተኞች ዘንድ ከቶ አይገለጥም። ለኃጢአት እውነተኛ ጥላቻ አንዲት ቅንጣት እንኳ ቢኖርህ፥ እግዚአብሔር ሰጥቶህ መሆን አለበት፤ የሰው ተፈጥሮ እሾኽ አንዲት በለስ እንኳ ከቶ አላፈራምና። «ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው።»

እውነተኛ ንስሐ ከአዳኙ ጋር ግልጽ ግንኙነት አለው። ስለ ኃጢአት ንስሐ ስንገባ አንድ ዓይናችንን በኃጢአት ላይ ሌላውንም በመስቀሉ ላይ ልናደርግ ይገባናል፤ ወይም ሁለቱንም ዓይኖቻችንን በክርስቶስ ላይ ብናደርግና መተላለፋችንን በፍቅሩ ብርሃን ብቻ ብናይ ይበልጥ ይሻላል።

ስለ ኃጢአት የሚሆን እውነተኛ ኀዘን እጅግ ተግባራዊ ነው። በኃጢአት እየኖረ ማንም ኃጢአትን እጠላለሁ ሊል አይችልም። ንስሐ የኃጢአትን ክፋት በንድፈ አሳብ ብቻ ሳይሆን በልምምድ እንድናይ ያደርገናል፤ የተቃጠለ ሕፃን እሳትን እንደሚፈራ። በቅርቡ ተይዞ የተዘረፈ ሰው በአውራ ጎዳና ላይ ያለውን ሌባ እንደሚፈራ እንዲሁ እንፈራዋለን፤ እንሸሸዋለንም፤ በነገር ሁሉ እንሸሸዋለን፤ ሰዎች ትላልቅ እባቦችን ብቻ ሳይሆን ትናንሽ እፉኝቶችንም እንደሚሸሹ፥ በታላላቅ ነገሮች ብቻ ሳይሆን በትናንሽ ነገሮችም። ስለ ኃጢአት የሚሆን እውነተኛ ልቅሶ ክፉ ቃል እንዳይናገር ስለ አንደበታችን እጅግ እንድንቀና ያደርገናል፤ በአንዳች እንዳንበድል በየዕለቱ ሥራችን ላይ እጅግ ንቁዎች እንሆናለን፤ በየሌሊቱም ቀኑን ስለ ጕድለታችን በሚያሠቃይ ኑዛዜ እንዘጋለን፤ በየማለዳውም እንዳንበድለው እግዚአብሔር በዚህ ቀን እንዲደግፈን በጭንቀት ጸሎት እንነቃለን።

ቅን ንስሐ የማያቋርጥ ነው። አማኞች እስከሚሞቱበት ቀን ድረስ ንስሐ ይገባሉ። ይህ የሚንጠባጠብ ምንጭ የሚቋረጥ አይደለም። ሌላው ኀዘን ሁሉ ለጊዜ ይሸነፋል፤ ይህ ውድ ኀዘን ግን ከእድገታችን ጋር ያድጋል፤ እንዲህ ያለ ጣፋጭ መራራ ስለ ሆነም ወደ ዘላለም ዕረፍታችን እስክንገባ ድረስ እንድንደሰትበትና እንድንቀበለው ስለ ተፈቀደልን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን።

ኦክቶበር 14

«ስለ ጌታዬ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ከሁሉ ስለሚበልጥ እውቀት ሁሉን እንደ ጉዳት እቈጥራለሁ።» (ፊልጵስዩስ 3:8)

የክርስቶስ መንፈሳዊ እውቀት የግል እውቀት ይሆናል። ሌላ ሰው ከእርሱ ጋር ባለው ትውውቅ ኢየሱስን ላውቀው አልችልም። አይደለም፤ እኔ ራሴ ላውቀው ይገባኛል፤ በገዛ ራሴ ላውቀው ይገባኛል። የማስተዋል እውቀት ይሆናል፤ ባለ ራእይ እንደሚያልመው ሳይሆን ቃሉ እንደሚገልጠው እርሱን ላውቀው ይገባኛል። መለኮታዊና ሰብአዊ ባሕርያቱን ላውቅ ይገባኛል። ሹመቶቹን፥ ባሕርያቱን፥ ሥራዎቹን፥ ውርደቱን፥ ክብሩን ላውቅ ይገባኛል። «ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር እስካስተውል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር እስካውቅ» ድረስ በእርሱ ላይ ላሰላስል ይገባኛል። ስለ እርሱ የፍቅር እውቀት ይሆናል፤ በእርግጥ ጨርሶ ካወቅሁት ልወደው ይገባኛል። አንዲት ቅንጣት የልብ እውቀት ከአንድ ቶን የራስ ትምህርት ይበልጣል። ስለ እርሱ ያለን እውቀት የሚያረካ እውቀት ይሆናል። አዳኜን ሳውቅ አእምሮዬ እስከ አፉ ይሞላል፤ መንፈሴ የናፈቀውን እንዳገኘሁ ይሰማኛል። «ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው።» በዚያው ጊዜ የሚያነሣሣ እውቀት ይሆናል፤ ስለ ውዴ ይበልጥ ባወቅሁ መጠን ይበልጥ ለማወቅ እሻለሁ። ከፍ ብዬ በወጣሁ መጠን የሚጓጉትን እርምጃዎቼን የሚጋብዙ ጫፎች ይበልጥ ከፍ ያሉ ይሆናሉ። ይበልጥ ባገኘሁ መጠን ይበልጥ እሻለሁ። እንደ ንፉግ ሰው ሀብት ወርቄ ይበልጥ እንድመኝ ያደርገኛል። ለመደምደም፥ ይህ የክርስቶስ ኢየሱስ እውቀት እጅግ ደስ የሚያሰኝ ይሆናል፤ በእርግጥ እጅግ ከፍ የሚያደርግ ስለ ሆነ አንዳንድ ጊዜ ከመከራዎችና ከጥርጣሬዎች ከኀዘኖችም ሁሉ በላይ ፈጽሞ ያነሣኛል፤ በእርሱም እየተደሰትሁ ሳለ «ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን አጭር ነው፥ መከራም የሞላበት ነው» ከሚባለው ሰው የሚበልጥ ያደርገኛል፤ ለዘላለም የሚኖረውን የአዳኙን ዘላለማዊነት በዙሪያዬ ይጥላልና፥ በዘላለም ደስታውም የወርቅ መታጠቂያ ያስታጥቀኛልና። ነፍሴ ሆይ፥ ነዪ፥ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀመጪ፤ ቀኑን ሁሉ ይህን ሁሉ ከእርሱ ተማሪ።

ኦክቶበር 15

«ነገር ግን የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው?» (ሚልክያስ 3:2)

የመጀመሪያው መምጣቱ ያለ ውጫዊ ግርማና ያለ ኃይል መግለጫ ነበረ፤ ሆኖም በእውነት የሚፈትነውን ኃይሉን ሊቋቋሙ የቻሉት ጥቂቶች ነበሩ። ሄሮድስና ከእርሱ ጋር ኢየሩሳሌም ሁሉ ስለ ድንቁ ልደት በሰሙት ዜና ታወኩ። እርሱን እንጠባበቃለን ብለው ያሰቡት ሰዎች በመጣ ጊዜ በመናቃቸው የሃይማኖት ምስክርነታቸውን ሐሰትነት ገለጡ። በምድር ላይ ሕይወቱ ታላቁን የሃይማኖት መግለጫ ክምር የፈተነ መንሽ ነበረ፤ ሂደቱንም የተቋቋሙት እጅግ ጥቂቶች ነበሩ። ዳግም ምጽአቱ ግን ምን ይሆን? ስለ እርሱ ማሰብን ሊታገሥ የሚችል ኃጢአተኛ ማን ነው? «ምድርን በአፉ በትር ይመታል፥ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉውን ይገድላል።» በውርደቱ ጊዜ ለወታደሮቹ «እኔ ነኝ» ብቻ ባለ ጊዜ ወደ ኋላ ወደቁ፤ ራሱን «እኔ ነኝ» ብሎ ይበልጥ ሙሉ በሙሉ ሲገልጥ የጠላቶቹ ድንጋጤ ምን ይሆን? ሞቱ ምድርን አናወጠ ሰማይንም አጨለመ፤ ሕያው አዳኝ ሆኖ ሕያዋንንና ሙታንን በፊቱ የሚጠራበት የዚያ ቀን የሚያስፈራ ግርማ ምን ይሆን? ኦ፥ የጌታ ግርማ ሰዎችን ኃጢአታቸውን እንዲተዉ፥ እንዳይቈጣም ልጁን እንዲስሙ ቢያሳምናቸው! በግ ቢሆንም፥ ንጥቂያውን የሚቦጭቅ የይሁዳ ነገድ አንበሳ ነው፤ የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ ባይሰብርም፥ ጠላቶቹን በብረት በትር ይሰብራቸዋል፥ እንደ ሸክላ ሠሪም ዕቃ ያደቅቃቸዋል። ከጠላቶቹ አንዱ እንኳ በቍጣው ዐውሎ ነፋስ ፊት አይቆምም፤ ወይም ከሚጠርገው የመዓቱ በረዶ ራሱን አይሰውርም፤ በደም የታጠቁ የተወደዱ ሕዝቡ ግን መገለጡን በደስታ ይጠባበቃሉ፤ ያለ ፍርሃትም ሊታገሡት ተስፋ ያደርጋሉ፤ ለእነርሱ አሁንም እንደ አንጥረኛ ተቀምጦአል፤ ከፈተናቸውም በኋላ እንደ ወርቅ ይወጣሉ። የጌታ መምጣት በአእምሮአችን የጨለማ ፍርሃት እንዳያመጣ፥ በዚህ ማለዳ ራሳችንን እንመርምር፤ መጠራታችንንና መመረጣችንንም እናጽና። ኦ፥ ግብዝነትን ሁሉ እንድንጥልና በመገለጡ ቀን ቅኖችና ያለ ነቀፋ ሆነን እንድንገኝ ጸጋ ቢሰጠን!

ኦክቶበር 16

«ኢየሱስም። ኑ፥ ምሳ ብሉ አላቸው።» (ዮሐንስ 21:12)

በእነዚህ ቃላት አማኙ ወደ ኢየሱስ ቅዱስ ቅርበት ተጋብዞአል። «ኑ፥ ምሳ ብሉ» ማለት አንድ ማዕድና አንድ መብል ማለት ነው፤ አዎን፥ አንዳንድ ጊዜም ጎን ለጎን መቀመጥና ራሳችንን በአዳኙ ደረት ላይ ማስደገፍ ማለት ነው። የሚቤዥ ፍቅር ዓላማ በሚውለበለብበት ወደ ግብዣው ቤት መግባት ነው። «ኑ፥ ምሳ ብሉ» ከኢየሱስ ጋር ያለን አንድነት ራእይ ይሰጠናል፤ ከኢየሱስ ጋር ስንመገብ ልንበላው የምንችለው ብቸኛ ምግብ እርሱ ራሱ ነውና። ኦ፥ ይህ ምን ያለ አንድነት ነው! እንዲህ ኢየሱስን መመገባችን አእምሮ ሊመረምረው የማይችል ጥልቀት ነው። «ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።» ደግሞም ከቅዱሳን ጋር ኅብረትን እንድንደሰት የተደረገ ግብዣ ነው። ክርስቲያኖች በብዙ ነጥቦች ሊለያዩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሁሉም አንድ መንፈሳዊ ፍላጎት አላቸው፤ ሁላችንም አንድ ዓይነት ስሜት ባይኖረን፥ ከሰማይ በወረደው የሕይወት እንጀራ ሁላችንም አንድ ዓይነት መብል እንመገባለን። ከኢየሱስ ጋር ባለው የኅብረት ማዕድ አንድ እንጀራና አንድ ጽዋ ነን። የፍቅር ጽዋ ሲዞር በእርሱ እርስ በርሳችን ከልብ እንጠጣለን። ወደ ኢየሱስ ቅረብ፤ በዚያው ሰማያዊ መና ከሚደገፉት እንደ አንተ ካሉት ሁሉ ጋር በመንፈስ ይበልጥ እየተቈራኘህ ራስህን ታገኛለህ። ወደ ኢየሱስ ይበልጥ ብንቀርብ እርስ በርሳችን ይበልጥ በተቀራረብን ነበር። ደግሞም በእነዚህ ቃላት ለክርስቲያን ሁሉ የብርታት ምንጭ እናያለን። ወደ ክርስቶስ መመልከት ሕይወት ነው፤ ነገር ግን እርሱን ለማገልገል ብርታትን ለማግኘት «ኑ፥ ምሳ ብሉ» የሚለውን ልትቀበል ይገባሃል። የጌታን ይህን ትእዛዝ ቸል በማለታችን ብዙ አላስፈላጊ ድካም ይጫነናል። ከእኛ ማንም ራሱን በጥቂት ምግብ ላይ ሊያኖር አያስፈልገውም፤ በተቃራኒው በወንጌል ቅልጥምና ስብ ልንወፍር ይገባናል፤ ይህም በእርሱ ብርታትን እንድናከማችና በጌታ አገልግሎት ኃይልን ሁሉ እስከ ሙሉ ጥንካሬው እንድንገፋፋ ነው። እንግዲህ ከኢየሱስ ጋር ቅርበትን፥ ከኢየሱስ ጋር አንድነትን፥ ለሕዝቡ ፍቅርን፥ ከኢየሱስም ብርታትን ብትሻ፥ በእምነት ከእርሱ ጋር «ኑ፥ ምሳ ብሉ» የሚለውን ተቀበል።

ኦክቶበር 17

«ዳዊትም በልቡ። አሁን አንድ ቀን በሳኦል እጅ እጠፋለሁ አለ።» (1ኛ ሳሙኤል 27:1)

በዚያን ጊዜ የዳዊት ልብ ያሰበው አሳብ ሐሰተኛ አሳብ ነበረ፤ እግዚአብሔር በሳሙኤል በኩል የቀባው ባዶና ትርጉም የሌለው ሥራ ሆኖ እንዲቀር ታስቦ ነበር ብሎ የሚያስብበት ምንም ምክንያት በእርግጥ አልነበረውምና። ጌታ ባሪያውን አንድ ጊዜ ስንኳ አልተወውም ነበር፤ ብዙ ጊዜ በአደገኛ ስፍራ ተቀምጦ ነበር፤ ነገር ግን መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ያላዳነበት አንድም አጋጣሚ አልነበረም። የደረሱበት መከራዎች ልዩ ልዩ ነበሩ፤ አንድ መልክ ብቻ ሳይሆን ብዙ መልክ ይዘው ነበር፤ ነገር ግን በሁሉም ሁኔታ መከራውን የላከው እርሱ መውጫ መንገድንም በቸርነቱ አዘጋጅቶ ነበር። ዳዊት በማስታወሻ ደብተሩ ውስጥ ያለውን አንድ ጽሑፍ በጣቱ ጠቍሞ፥ «ጌታ እንደሚተወኝ ማስረጃው ይኸው» ሊል አልቻለም፤ ያለፈው ሕይወቱ ሁሉ ፍጹም ተቃራኒውን አረጋግጦአልና። እግዚአብሔር ስለ እርሱ ካደረገው ተነሥቶ እግዚአብሔር አሁንም ጠባቂው እንደሚሆን ማመዛዘን ይገባው ነበር። ነገር ግን እኛስ የእግዚአብሔርን እርዳታ የምንጠራጠረው በዚሁ መንገድ አይደለምን? ያለ ምክንያት አለመታመን አይደለምን? የአባታችንን በጎነት ለመጠራጠር የምክንያት ጥላ ስንኳ ኖሮን ያውቃልን? ቸርነቱ ድንቅ አልሆነምን? መታመናችንን አንድ ጊዜ ስንኳ አሳፍሮአልን? አይደለም! አምላካችን በምንም ጊዜ አልተወንም። ጨለማ ሌሊቶችን አሳልፈናል፤ ነገር ግን የፍቅር ኮከብ በጨለማው መካከል አብርቶአል፤ በብርቱ ሰልፍ ውስጥ ነበርን፤ ነገር ግን እርሱ የመከላከያችንን ጋሻ ከራሳችን በላይ ከፍ አድርጎ ይዞአል። በብዙ መከራዎች አልፈናል፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ለጥቅማችን እንጂ ለጉዳታችን ከቶ አልነበረም፤ ካለፈው ተሞክሮአችንም የምንደርስበት መደምደሚያ ይህ ነው፤ በስድስት መከራ ከእኛ ጋር የነበረው በሰባተኛው አይተወንም። ስለ ታማኙ አምላካችን ያወቅነው እስከ መጨረሻ እንደሚጠብቀን ያረጋግጣል። እንግዲያስ ከማስረጃው በተቃራኒ አናመዛዝን። አምላካችንን እስክንጠራጠር ድረስ እንዴት ንፉጋን ልንሆን እንችላለን? ጌታ ሆይ፥ የአለማመናችንን ኤልዛቤል ጣላት፥ ውሾችም ይብሉአት።

ኦክቶበር 18

«ጎዳናዎችህ ስብን ያንጠባጥባሉ።» (መዝሙር 65:11)

«ስብን የሚያንጠባጥቡ» «የእግዚአብሔር ጎዳናዎች» ብዙ ናቸው፤ ነገር ግን ከሁሉ የተለየው የጸሎት ጎዳና ነው። በእልፍኙ ብዙ ጊዜ የሚያሳልፍ አማኝ «ክሳቴ፥ ክሳቴ፥ ወዮልኝ» ብሎ መጮኽ አያስፈልገውም። የተራቡ ነፍሳት ከምሕረት ዙፋን ርቀው ይኖራሉ፥ በድርቅ ዘመንም እንደ ደረቀ እርሻ ይሆናሉ። በሚታገል ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ማሸነፍ አማኙን ደስተኛ ባያደርገው እንኳ ብርቱ ማድረጉ አይቀርም። ለሰማይ ደጅ ከሁሉ የሚቀርበው ስፍራ የሰማያዊው ጸጋ ዙፋን ነው። ብዙ ጊዜ ለብቻህ ብትሆን ብዙ መረጋገጥ ይኖርሃል፤ ከኢየሱስ ጋር ለብቻህ የምትሆንበት ጊዜ ጥቂት ቢሆን ግን ሃይማኖትህ ጥልቀት የሌለው፥ በብዙ ጥርጣሬና ፍርሃት የረከሰ፥ በጌታም ደስታ የማያንጸባርቅ ይሆናል። ነፍስን የሚያበለጽገው የጸሎት ጎዳና ከሁሉ ለደከመው ቅዱስ እንኳ የተከፈተ ስለ ሆነ፥ ከፍ ያለ ደረጃ ስለማይጠየቅ፥ የላቀ ቅዱስ ስለ ሆንህ እንድትመጣ የታዘዝህ ሳይሆን ቅዱስ ብቻ ብትሆን በነጻ ስለ ተጋበዝህ፥ የተወደድህ አንባቢ ሆይ፥ ዘወትር በግል የአምልኮ መንገድ ላይ እንድትገኝ ተጠንቀቅ። ብዙ ጊዜ ተንበርከክ፤ ኤልያስ እንዲሁ በተራበው በእስራኤል እርሻ ላይ ዝናብን አውርዶአልና።

ለሚሄዱበት ስብን የሚያንጠባጥብ ሌላም የተለየ ጎዳና አለ፤ እርሱም የኅብረት ስውር አካሄድ ነው። ኦ! ከኢየሱስ ጋር ያለው የኅብረት ደስታ! በኢየሱስ ደረት ላይ የተደገፈችውን ነፍስ ቅዱስ ጸጥታ የሚገልጥ ቃል ምድር የላትም። ጥቂት ክርስቲያኖች ብቻ ይረዱታል፤ በቈላው ይኖራሉ፥ ወደ ናባው ራስ እምብዛም አይወጡም፤ በውጭው አደባባይ ይኖራሉ፥ ወደ ቅድስቱ አይገቡም፥ የክህነትንም መብት አይይዙም። መሥዋዕቱን ከሩቅ ያዩታል፥ ነገር ግን ከእርሱ ሊበሉና በሚቃጠለው መሥዋዕት ስብ ሊደሰቱ ከካህኑ ጋር አይቀመጡም። አንተ ግን አንባቢ ሆይ፥ ዘወትር በኢየሱስ ጥላ ሥር ተቀመጥ፤ ወደዚያ ዘንባባ ውጣ፥ ቅርንጫፎቹንም ያዝ፤ ውድህ በዱር ዛፎች መካከል እንዳለ እንኮይ ይሁንልህ፥ እንደ ቅልጥምና እንደ ስብም ትጠግባለህ። ኢየሱስ ሆይ፥ በማዳንህ ጎብኘን!

ኦክቶበር 19

«በክርስቶስ ሕፃናት።» (1ኛ ቆሮንቶስ 3:1)

አማኝ ሆይ፥ በመለኮታዊ ሕይወት እጅግ ደካማ ስለ ሆንህ፥ እምነትህ እጅግ ትንሽ፥ ፍቅርህም እጅግ ደካማ ስለ ሆነ ታዝናለህን? አይዞህ፤ የምታመሰግንበት ምክንያት አለህና። በአንዳንድ ነገሮች ከሁሉ ታላቅ ከሆነውና ፍጹም ካደገው ክርስቲያን ጋር እኩል እንደ ሆንህ አስብ። እርሱ በደም እንደ ተገዛ አንተም እንዲሁ በደም ተገዝተሃል። እንደ ማንኛውም አማኝ አንተም የእግዚአብሔር የማደጎ ልጅ ነህ። ሙሉ ሰው የወላጆቹ ልጅ እንደ ሆነ ሕፃንም እንዲሁ በእውነት የወላጆቹ ልጅ ነው። አንተም ፈጽመህ ጸድቀሃል፤ መጽደቅህ ደረጃ ያለው ነገር አይደለምና፤ ትንሹ እምነትህ ሁለንተናህን ንጹሕ አድርጎሃል። ከሁሉ የላቁ አማኞች ያላቸውን ያህል በኪዳኑ ክቡር ነገሮች ላይ መብት አለህ፤ በኪዳኑ ምሕረቶች ላይ ያለህ መብት በእድገትህ ሳይሆን በኪዳኑ ራሱ ላይ ነውና፤ በኢየሱስ ያለህ እምነትም በእርሱ ያለህ ርስት መለኪያ ሳይሆን ምልክቱ ነው። በደስታ ባይሆን እንኳ በእውነተኛ ይዞታ እንደ ባለ ጠጎች ሁሉ ባለ ጠጋ ነህ። ከሚያበሩት ከዋክብት ሁሉ ትንሹ በሰማይ ተተክሎአል፤ ከብርሃን ጨረሮች ሁሉ ደካማው ከታላቁ የቀን ብርሃን ጋር ዝምድና አለው። በክብር የቤተ ሰብ መዝገብ ታናናሾቹና ታላላቆቹ በአንድ ብዕር ተጽፈዋል። በቤተ ሰቡ ውስጥ እንዳለ ታላቅ ሁሉ አንተም ለአባትህ ልብ የተወደድህ ነህ። ኢየሱስ ለአንተ እጅግ ርኅሩኅ ነው። አንተ የሚጤስ የጥዋፍ ክር ትመስላለህ፤ ሻካራ መንፈስ ያለው «ያን የሚጤስ ክር አጥፉት፤ ቤቱን በሚያስጠላ ሽታ ይሞላል!» ይል ነበር፤ እርሱ ግን የሚጤሰውን ክር አያጠፋም። የተቀጠቀጠ ሸምበቆ ትመስላለህ፤ ከዋናው መዘምር እጅ ያነሰ ርኅራኄ ያለው ማንኛውም እጅ ይረግጥህ ወይም ይጥልህ ነበር፤ እርሱ ግን የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ ከቶ አይሰብርም። ባለህበት ሁኔታ ምክንያት ከማዘን ይልቅ በክርስቶስ ድል ልትነሣ ይገባሃል። በእስራኤል መካከል ታናሽ ብቻ ነኝን? ነገር ግን በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ እንድቀመጥ ተደርጌአለሁ። በእምነት ድሀ ነኝን? ሆኖም በኢየሱስ የሁሉ ነገር ወራሽ ነኝ። «ከምንም ያነሰ ነኝ፥ የምመካበትም የለኝ፤ ከንቱነቴንም እናዘዛለሁ» ብልም፥ የነገሩ ሥር በእኔ ውስጥ ቢኖር በጌታ ደስ ይለኛል፥ በመድኃኒቴም አምላክ እመካለሁ።

ኦክቶበር 20

«በነገር ሁሉ ወደ እርሱ እንደግ።» (ኤፌሶን 4:15)

ብዙ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ነገር ቀንጭረውና ድንክ ሆነው ይኖራሉ፤ ዓመት ከዓመት ያው መልክ ይታይባቸዋል። የላቀና የጠራ ስሜት ሲበቅልባቸው አይታይም። ይኖራሉ እንጂ «በነገር ሁሉ ወደ እርሱ አያድጉም።» ነገር ግን ወደ «ዛላው» ልንሻገር፥ በመጨረሻም «በዛላው ፍጹም ሰብል» ሆነን ልንበስል ስንችል በ«ቡቃያው» ደረጃ መርካት ይገባናልን? በክርስቶስ አምነን «ድኛለሁ» በማለት፥ በእርሱ ያለውን ሙላት በራሳችን ተሞክሮ ይበልጥ ለማወቅ ሳንመኝ መርካት ይገባናልን? እንዲህ መሆን የለበትም፤ በሰማይ ገበያ እንደ መልካም ነጋዴዎች በኢየሱስ እውቀት ለመበልጸግ መመኘት ይገባናል። የሌሎችን ሰዎች የወይን ቦታ መጠበቅ መልካም ነው፤ ነገር ግን የራሳችንን መንፈሳዊ እድገትና መብሰል ቸል ማለት የለብንም። በልባችን ውስጥ ሁልጊዜ ክረምት ለምን ይሆናል? የዘር ጊዜ ሊኖረን ግድ ነው፥ እውነት ነው፤ ነገር ግን ኦ፥ የጸደይ ጊዜ ቢኖረን—አዎን፥ የቀደመ መከርን ተስፋ የሚሰጥ የበጋ ወራት! በጸጋ ልንበስል ብንወድ ወደ ኢየሱስ ቀርበን—በፊቱ—በፈገግታው ፀሐይ እየበሰልን መኖር አለብን። ከእርሱ ጋር ጣፋጭ ኅብረት ልናደርግ ይገባናል። ፊቱን ከሩቅ ማየትን ትተን እንደ ዮሐንስ ቀርበን ራሳችንን በደረቱ ላይ ልናስደግፍ ይገባናል፤ ያን ጊዜ በቅድስና፥ በፍቅር፥ በእምነት፥ በተስፋ—አዎን፥ በክቡር ስጦታ ሁሉ ስናድግ ራሳችንን እናገኛለን። ፀሐይ በመጀመሪያ በተራሮች ራስ ላይ ወጥታ በብርሃንዋ እንደምታስጌጣቸውና ለመንገደኛው ዓይን እጅግ ከሚያምሩ ትዕይንቶች አንዱን እንደምታሳይ፥ እንዲሁም እንደ ሳኦል ከባልንጀሮቹ በላይ በመንፈሳዊ ቁመት ባደገው በአንድ ቅዱስ ራስ ላይ የመንፈስ ብርሃን ሲያንጸባርቅ መመልከት በዓለም ካሉት እጅግ አስደሳች ማሰላሰሎች አንዱ ነው፤ እርሱም በበረዶ እንደ ተከናነበ እንደ ታላቅ የአልፕስ ተራራ ከተመረጡት መካከል በመጀመሪያ የጽድቅን ፀሐይ ጨረሮች ያንጸባርቃል፥ ሁሉም እንዲያዩትና አይተውም በሰማያት ያለውን አባቱን እንዲያከብሩ የክብሩን ነጸብራቅ ከፍ አድርጎ ይሸከማል።

ኦክቶበር 21

«የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና።» (2ኛ ቆሮንቶስ 5:14)

ለጌታዬ ምን ያህል ዕዳ አለብህ? ለአንተ አንዳች ነገር አድርጎልህ ያውቃልን? ኃጢአትህን ይቅር ብሎልሃልን? በጽድቅ ልብስ አልብሶሃልን? እግርህን በዓለት ላይ አቁሞአልን? አረማመድህን አጽንቶአልን? ሰማይን አዘጋጅቶልሃልን? አንተንስ ለሰማይ አዘጋጅቶሃልን? ስምህን በሕይወት መጽሐፉ ጽፎአልን? ቍጥር የሌለው በረከት ሰጥቶሃልን? ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው የምሕረት ክምችት አከማችቶልሃልን? እንግዲያስ ለፍቅሩ የሚገባ አንድ ነገር ለኢየሱስ አድርግ። ለሚሞተው ቤዛ የቃል ብቻ መባ አትስጥ። ጌታህ ሲመጣ ለእርሱ አንዳች እንዳላደረግህ፥ ነገር ግን ወደ ድሆቹም ሆነ ወደ ሥራው ሳይፈስስ እንደ ረጋ ኩሬ ፍቅርህን ዘግተህ እንደ ያዝህ ልትናዘዝ ብትገደድ ምን ይሰማሃል? እንዲህ ያለው ፍቅር ይጥፋ! በሥራ ራሱን ከቶ የማይገልጥ ፍቅርን ሰዎች ምን ያስቡታል? «የተገለጠ ተግሣጽ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል» ይላሉ። አንዲት የራስን መካድ፥ የለጋስነት፥ የጀግንነት ወይም የቅንዓት ሥራ እንድትሠራ የማያንቀሳቅስህን ያህል ደካማ ፍቅር ማን ይቀበላል! እርሱ እንዴት እንደ ወደደህና ስለ አንተ ራሱን እንደ ሰጠ አስብ! የዚያን ፍቅር ኃይል ታውቃለህን? እንግዲያስ የዓለማዊነትህን ደመና ጠርጎ የኃጢአትንም ጭጋግ ለማስወገድ ለነፍስህ እንደ ዓውሎ ነፋስ ይሁን። «ስለ ክርስቶስ» — ይህ በአንተ ላይ የሚቀመጥ የእሳት ልሳን ይሁን፤ «ስለ ክርስቶስ» — ይህ መለኮታዊ ተመስጦ፥ ከምድር ከፍ አድርጎ የሚያወጣህ ሰማያዊ እስትንፋስ፥ በጌታህ አገልግሎት እንደ አንበሳ ደፋር እንደ ንስርም ፈጣን የሚያደርግህ መለኮታዊ መንፈስ ይሁን። ፍቅር ለአገልግሎት እግሮች ክንፍን፥ ለድካም ክንዶችም ብርታትን ሊሰጥ ይገባዋል። በማይናወጥ ጽናት በእግዚአብሔር ላይ ተተክለን፥ ወደ ኋላ በማይመለስ ቍርጥ አሳብ እርሱን ለማክበር ወስነን፥ ከቶ በማይደክም ትጋትም ወደ ፊት እየገሠገሥን፥ ለኢየሱስ ያለንን የፍቅር ግዴታ እንግለጥ። መለኮታዊው ማግኔት ወደ ራሱ ወደ ሰማይ ይሳበን።

ኦክቶበር 22

«በነጻ እወድዳቸዋለሁ።» (ሆሴዕ 14:4)

ይህ ዓረፍተ ነገር በጥቂቱ የተጠቃለለ ሙሉ የሥነ መለኮት ትምህርት ነው። ትርጉሙን የሚያስተውል የሥነ መለኮት ሊቅ ነው፤ ወደ ሙላቱም ጠልቆ ሊገባ የሚችል በእውነት የእስራኤል መምህር ነው። በቤዛችን በክርስቶስ ኢየሱስ የተሰጠን የክቡሩ የመዳን መልእክት ማጠቃለያ ነው። ትርጉሙ «በነጻ» በሚለው ቃል ላይ የተንጠለጠለ ነው። ፍቅር ከሰማይ ወደ ምድር የሚፈስስበት ክቡር፥ ተገቢ፥ መለኮታዊ መንገድ ይህ ነው፤ ላልተገባቸው፥ ላልገዙትና ላልፈለጉት የሚፈስስ ከራሱ የሚመነጭ ፍቅር። በእርግጥም እግዚአብሔር እንደ እኛ ያሉትን ሊወድ የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ይህ ነው። ይህ ጥቅስ ለማንኛውም ዓይነት ብቃት የሞት ምት ነው፤ «በነጻ እወድዳቸዋለሁ።» በእኛ ዘንድ ብቃት የሚያስፈልግ ቢሆን ኖሮ በነጻ ባልወደደን ነበር፤ ቢያንስ ይህ የነጻነቱን ማቃለያና ጉድለት በሆነ ነበር። ነገር ግን «በነጻ እወድዳችኋለሁ» ተብሎ ጸንቶ ይኖራል። እኛ «ጌታ ሆይ፥ ልቤ እጅግ ደንዳና ነው» ብለን እናማርራለን። «በነጻ እወድዳችኋለሁ።» «ነገር ግን እንደምመኘው ክርስቶስን መፈለጌ አይሰማኝም።» «ፍላጎታችሁ ስለ ተሰማችሁ አልወድዳችሁም፤ በነጻ እወድዳችኋለሁ።» «ነገር ግን የምመኘው የመንፈስ ልስላሴ አይሰማኝም።» አስታውስ፥ የመንፈስ ልስላሴ ቅድመ ሁኔታ አይደለም፤ ቅድመ ሁኔታዎች የሉምና፤ የጸጋ ኪዳን ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ የለበትም፤ ስለዚህ እኛ ያለ ምንም ብቃት እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ በሰጠን ተስፋ ላይ ልንደፍር እንችላለን፤ እርሱ «በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም» ብሎአልና። የእግዚአብሔር ጸጋ ያለ ዝግጅት፥ ያለ ብቃት፥ ያለ ገንዘብና ያለ ዋጋ በማንኛውም ጊዜ ለእኛ ነጻ መሆኑን ማወቅ የተባረከ ነው! «በነጻ እወድዳቸዋለሁ።» እነዚህ ቃሎች ያፈገፈጉትን እንዲመለሱ ይጋብዛሉ፤ በእርግጥም ጥቅሱ በተለይ ለእነርሱ ተጽፎአል፤ «ከዳተኝነታቸውን እፈውሳለሁ፤ በነጻ እወድዳቸዋለሁ።» አንተ ያፈገፈግህ ሆይ! የተስፋው ለጋስነት ልብህን ወዲያው እንደሚሰብረው፥ እንደምትመለስና የበደልኸውን የአባትህን ፊት እንደምትፈልግ የታወቀ ነው።

ኦክቶበር 23

«እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን?» (ዮሐንስ 6:67)

ብዙዎች ክርስቶስን ትተዋል፥ ከዚያም ወዲያ ከእርሱ ጋር አልሄዱም፤ አንተ ግን ለመለወጥ ምን ምክንያት አለህ? ባለፈው ጊዜ ለዚህ ምክንያት ነበረን? ኢየሱስ ሁሉን የሚበቃ መሆኑን አላሳየምን? በዚህ ማለዳ «ለእናንተ ምድረ በዳ ሆንሁን?» ብሎ ይጠይቅሃል። ነፍስህ በቀላሉ በኢየሱስ በታመነች ጊዜ ከቶ አፍረህ ታውቃለህን? እስከ አሁን ድረስ ጌታህን ርኅሩኅና ለጋስ ወዳጅ ሆኖ አላገኘኸውምን? በእርሱ ያለህ ቀላል እምነትስ መንፈስህ ሊመኘው የሚችለውን ሰላም ሁሉ አልሰጠህምን? ለአንተ ከሆነው የሚሻል ወዳጅ በሕልምህ ስንኳ ልታስብ ትችላለህን? እንግዲያስ አሮጌውንና የተፈተነውን በአዲስና በሐሰተኛ አትለውጥ። ስለ አሁኑ ጊዜ ደግሞ፥ እርሱ ክርስቶስን እንድትተው ሊያስገድድህ ይችላልን? በዚህ ዓለም ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉት በጠነከሩ መከራዎች በብርቱ በተከበብን ጊዜ ራሳችንን በአዳኛችን ደረት ላይ ማስደገፍ እጅግ የተባረከ ነገር ሆኖ እናገኘዋለን። በእርሱ መዳናችን ዛሬ ያለን ደስታ ይህ ነው፤ ይህ ደስታ የሚያረካ ከሆነ ስለ መለወጥ ለምን እናስባለን? ወርቅን በዝገት የሚለውጥ ማን ነው? የሚሻል ብርሃን እስክናገኝ ድረስ ፀሐይን አንክድም፤ የሚበልጥ ወዳጅ እስኪገለጥ ድረስ ጌታችንን አንተውም፤ ይህ ደግሞ ከቶ ሊሆን ስለማይችል በማይሞት እጅ አጥብቀን እንይዘዋለን፥ ስሙንም እንደ ማኅተም በክንዳችን ላይ እናስረዋለን። ስለሚመጣው ጊዜ ደግሞ፥ እንድታምፅ ወይም አሮጌውን ሰንደቅ ትተህ በሌላ አለቃ ሥር እንድታገለግል የሚያስገድድ የሚነሣ ነገር ልታስብ ትችላለህን? አይመስለንም። ሕይወት ረጅም ቢሆን—እርሱ አይለወጥም። ድሆች ብንሆን ባለ ጠጎች ሊያደርገን የሚችል ክርስቶስን ከማግኘት የሚሻል ምን አለ? ስንታመም በበሽታችን አልጋችንን የሚያነጥፍልን ከኢየሱስ ሌላ ምን እንፈልጋለን? ስንሞት «ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል» ተብሎ አልተጻፈምን! ከጴጥሮስ ጋር «ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን?» እንላለን።

ኦክቶበር 24

«የእግዚአብሔር ዛፎች ጭማቂ ሞልቶባቸዋል።» (መዝሙር 104:16)

ዛፍ ያለ ጭማቂ ሊለመልም ቀርቶ ሊኖርም አይችልም። ሕያውነት ለክርስቲያን አስፈላጊ ነው። ሕይወት ሊኖር ይገባል—እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ያፈሰሰው ሕያው መሠረት፤ አለዚያ የእግዚአብሔር ዛፎች ልንሆን አንችልም። ክርስቲያን የመባል ስም ብቻ የሞተ ነገር ነው፤ በመለኮታዊ ሕይወት መንፈስ ልንሞላ ይገባናል። ይህ ሕይወት ምሥጢራዊ ነው። የጭማቂውን ዝውውር፥ በምን ኃይል እንደሚወጣ፥ በምን ኃይልም ተመልሶ እንደሚወርድ አናስተውልም። እንዲሁም በውስጣችን ያለው ሕይወት ቅዱስ ምሥጢር ነው። ዳግም ልደት የሚፈጸመው መንፈስ ቅዱስ ወደ ሰው ገብቶ የሰው ሕይወት በመሆኑ ነው፤ በአማኝ ውስጥ ያለው ይህ መለኮታዊ ሕይወት ከዚያ በኋላ የክርስቶስን ሥጋና ደም ይመገባል፥ በዚህም በመለኮታዊ ምግብ ይጸናል፤ ነገር ግን ከወዴት እንደሚመጣ ወዴትም እንደሚሄድ ማን ይገልጥልናል? ጭማቂው እንዴት ያለ ስውር ነገር ነው! ሥሮቹ በጥቃቅን ጫፎቻቸው አፈሩን እየመረመሩ ይሄዳሉ፤ ነገር ግን ልዩ ልዩ ጋዞችን ሲስቡ ወይም ማዕድኑን ወደ ተክል ሲለውጡ ልናያቸው አንችልም፤ ይህ ሥራ በጨለማ ውስጥ ይሠራል። የእኛ ሥር ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፥ ሕይወታችንም በእርሱ ተሰውሮአል፤ ይህ የጌታ ምሥጢር ነው። የክርስቲያን ሕይወት መሠረት እንደ ሕይወቱ ራሱ ስውር ነው። በዝግባው ውስጥ ያለው ጭማቂ እንዴት ዘወትር የሚሠራ ነው! በክርስቲያን ውስጥ መለኮታዊው ሕይወት ሁልጊዜ በኃይል የተሞላ ነው—ሁልጊዜ ፍሬ በማፍራት ባይሆንም በውስጣዊ አሠራር። የአማኙ ጸጋዎች ሁሉ ዘወትር በእንቅስቃሴ ላይ አይደሉም፤ ነገር ግን ሕይወቱ በውስጡ መምታቱን ከቶ አያቆምም። ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር አይሠራም፤ ነገር ግን ልቡ ሁልጊዜ በእርሱ ይኖራል። ጭማቂው የዛፉን ቅጠልና ፍሬ በማስገኘት ራሱን እንደሚገልጥ፥ እንዲሁ በእውነት ጤናማ በሆነ ክርስቲያን ጸጋው በአካሄዱና በንግግሩ በውጭ ይገለጣል። ከእርሱ ጋር ብትነጋገር ስለ ኢየሱስ ከመናገር ሊቆጠብ አይችልም። ሥራውን ብትመለከት ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበረ ታያለህ። ምግባሩንና ንግግሩን በሕይወት ሊሞላው ግድ እስኪሆን ድረስ በውስጡ ብዙ ጭማቂ አለ።

ኦክቶበር 25

«በእኛ ስለሚኖርና ለዘላለም ከእኛ ጋር ስለሚሆን ስለ እውነት።» (2ኛ ዮሐንስ 2)

የእግዚአብሔር እውነት አንድ ጊዜ ወደ ሰው ልብ መግቢያ አግኝቶ ሰውን ሁሉ ለራሱ ካስገዛ በኋላ ሊያፈናቅለው የሚችል ሰዋዊም ሆነ ሲኦላዊ ኃይል የለም። እንደ እንግዳ ሳይሆን እንደ ቤቱ ጌታ እንቀበለዋለን—ይህ ለክርስቲያን የግድ አስፈላጊ ነገር ነው፤ እንዲህ የማያምን ክርስቲያን አይደለም። የወንጌልን ሕያው ኃይል የሚሰማቸው፥ መንፈስ ቅዱስም የጌታን ቃል ሲከፍት፥ በልብ ላይ ሲያሳርፍና ሲያትም ብርታቱን የሚያውቁ፥ ከመዳናቸው ወንጌል ከሚነጠሉ ይልቅ ቢቈራረጡ ይመርጣሉ። እውነት ለዘላለም ከእኛ ጋር እንደሚሆን በሚሰጠው ማረጋገጫ ውስጥ ስንት ሺህ ምሕረቶች ተጠቅልለዋል፤ በሕይወታችን ደጋፊያችን፥ በሞታችን መጽናናታችን፥ በትንሣኤያችን መዝሙራችን፥ የዘላለም ክብራችንም ይሆናል፤ ይህ የክርስቲያን መብት ነው፤ ያለ እርሱ እምነታችን ጥቂት ዋጋ ብቻ በኖረው ነበር። አንዳንድ እውነቶችን አድገን እንተዋቸዋለን፤ ለጀማሪዎች የሚሆኑ የመጀመሪያ ትምህርቶችና ልምምዶች ብቻ ናቸውና፤ ነገር ግን መለኮታዊውን እውነት እንዲህ ልናደርገው አንችልም፤ ለሕፃናት ጣፋጭ ምግብ ቢሆንም፥ በከፍተኛው ትርጉም ለሙሉ ሰዎች ጠንካራ ምግብ ነውና። ኃጢአተኞች ነን የሚለው እውነት ትሑታንና ንቁዎች ያደርገን ዘንድ በሚያሠቃይ ሁኔታ ከእኛ ጋር ነው፤ በጌታ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ይድናል የሚለው ይበልጥ የተባረከው እውነት ደግሞ ተስፋችንና ደስታችን ሆኖ ከእኛ ጋር ይኖራል። ተሞክሮ የጸጋን ትምህርቶች መያዛችንን ከማላላት ይልቅ ይበልጥ ይበልጥ አጥብቆ አስተሳስሮናል፤ የምናምንበት መሠረትና ምክንያት ከመቼውም ይልቅ አሁን የበረታና የበዛ ነው፤ በሞትም አዳኙን በእቅፋችን እስክንይዘው ድረስ እንዲሁ እንደሚሆን የምንጠብቅበት ምክንያት አለን።

ይህ ጸንቶ የሚኖር የእውነት ፍቅር በተገኘበት ስፍራ ሁሉ ፍቅራችንን ልናሳይ ግድ አለብን። ጠባብ ክበብ የጸጋ ርኅራኄያችንን ሊይዝ አይችልም፤ የልባችን ኅብረት እንደ ጸጋ ምርጫ ሰፊ ሊሆን ይገባዋል። ከተቀበልነው እውነት ጋር ብዙ ስሕተት ተቀላቅሎ ሊሆን ይችላል፤ ስሕተቱን እንዋጋ፥ ነገር ግን በወንድማችን ላይ ስለምናየው የእውነት መጠን አሁንም እንውደደው፤ ከሁሉም በላይ እኛ ራሳችን እውነትን እንውደድ፥ እናስፋፋውም።

ኦክቶበር 26

«ብዙ ተመኛችሁ፥ እነሆም፥ ጥቂት ሆነ፤ ወደ ቤትም ባገባችሁት ጊዜ እፍ አልሁበት። ይህ ስለ ምንድር ነው? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ቤቴ ፈርሶ ሳለ እናንተ እያንዳንዳችሁ ወደ ገዛ ቤታችሁ ትሮጣላችሁና።» (ሐጌ 1:9)

ንፉግ ነፍሳት ለአገልግሎትና ለሚስዮናዊ ሥራ የሚሰጡትን ያሳንሳሉ፥ ይህንንም መልካም ቍጠባ ብለው ይጠሩታል፤ በዚህ ራሳቸውን እያደኸዩ እንዳሉ በሕልማቸውም አያስቡም። ማመካኛቸው ለገዛ ቤተ ሰባቸው ሊያስቡ ግድ ነው የሚል ነው፤ የእግዚአብሔርን ቤት ቸል ማለት በገዛ ቤታቸው ላይ ጥፋትን የሚያመጣ እርግጠኛ መንገድ እንደ ሆነ ይረሳሉ። አምላካችን በመግቦቱ ጥረታችንን ከምንጠብቀው በላይ የሚያሳካበት ወይም ዕቅዳችንን ለኀፍረታችንና ለድንጋጤአችን የሚያፈርስበት መንገድ አለው፤ እጁን በመመለስ መርከባችንን ወደ ትርፋማ መተላለፊያ ሊመራ ወይም በድህነትና በኪሳራ ላይ እንድትወድቅ ሊያደርጋት ይችላል። ጌታ ለጋሶችን እንደሚያበለጽግ፥ ንፉጋንንም መከልከል ወደ ድህነት እንደሚያደርስ ራሳቸው እንዲያውቁ እንደሚተዋቸው የመጽሐፍ ትምህርት ነው። በጣም ሰፊ በሆነ የመመልከቻ መስክ፥ ከማውቃቸው ክርስቲያኖች መካከል እጅግ ለጋሶቹ ሁልጊዜ እጅግ ደስተኞች፥ ከሞላ ጎደልም ዘወትር እጅግ የበለጸጉ እንደ ነበሩ አስተውያለሁ። ለጋስ ሰጪ በሕልሙ ስንኳ ወዳላሰበው ሀብት ሲወጣ አይቻለሁ፤ ንፉግና ስስታም ሰው ደግሞ ሊነሣበት ባሰበበት ስስት ወደ ድህነት ሲወርድ እንዲሁ ብዙ ጊዜ አይቻለሁ። ሰዎች መልካም መጋቢዎችን በብዙና በብዙ ገንዘብ ያምኑአቸዋል፤ ከጌታም ጋር ብዙ ጊዜ እንዲሁ ነው፤ በቍና ለሚሰጡት በጋሪ ይሰጣል። ሀብት በማይሰጥበትም ስፍራ፥ አሥራቱ ለጌታ በተቀደሰለት ድርሻ የተቀደሰ ልብ በሚሰማው እርካታ ጌታ ጥቂቱን ብዙ ያደርጋል። ራስ ወዳድነት በመጀመሪያ ወደ ቤቱ ይመለከታል፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን አስቀድሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ይፈልጋል፤ ሆኖም በረጅም ጊዜ ራስ ወዳድነት ኪሳራ ነው፥ እግዚአብሔርን መምሰል ግን ታላቅ ትርፍ ነው። ወደ አምላካችን በተዘረጋ እጅ ለመሥራት እምነት ያስፈልጋል፤ ነገር ግን በእርግጥ ይህ ከእኛ ይገባዋል፤ የምናደርገውም ሁሉ ለቸርነቱ ላለብን አስደናቂ ዕዳ እጅግ ደካማ እውቅና ብቻ ነው።

ኦክቶበር 27

«ቃሉ የታመነ ነው።» (2ኛ ጢሞቴዎስ 2:11)

ጳውሎስ እነዚህ አራት «የታመኑ ቃሎች» አሉት። የመጀመሪያው በ1ኛ ጢሞቴዎስ 1:15 ይገኛል፤ «ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው።» ቀጣዩ በ1ኛ ጢሞቴዎስ 4:6 ነው፤ «እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል። ይህ ቃል የታመነ ሁሉም እንዲቀበሉት የተገባ ነው።» ሦስተኛው በ2ኛ ጢሞቴዎስ 2:12 ነው፤ «ቃሉ የታመነ ነው—ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን»፤ አራተኛውም በቲቶ 3:3 ነው፤ «ቃሉ የታመነ ነው። እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ።» በእነዚህ የታመኑ ቃሎች መካከል ያለውን ትስስር ልንከተል እንችላለን። የመጀመሪያው በታላቁ ቤዛ መላክ እንደ ተገለጠልን የዘላለም መዳናችንን መሠረት በእግዚአብሔር ነጻ ጸጋ ላይ ይጥላል። ቀጣዩ በዚህ መዳን የምናገኘውን ድርብ ብፅዕና ያረጋግጣል—የላይኛውና የታችኛው ምንጮች በረከቶች—የዘመንና የዘላለም። ሦስተኛው የተመረጡት ሕዝብ ከተጠሩባቸው ግዴታዎች አንዱን ያሳያል፤ «ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን» በሚለው ተስፋ ለክርስቶስ መከራ እንድንቀበል ተሹመናል። የመጨረሻው መልካም ሥራን በትጋት እንድንጠብቅ በማዘዝ የክርስቲያንን አገልግሎት ተግባራዊ መልክ ያቀርባል። እንዲሁም የመዳን ሥር በነጻ ጸጋ ውስጥ አለን፤ ቀጥሎም በአሁኑና በሚመጣው ሕይወት የዚያ መዳን መብቶች አሉን፤ ደግሞም ከክርስቶስ ጋር መከራ መቀበልና ከክርስቶስ ጋር ማገልገል የተባሉ፥ በመንፈስ ፍሬዎች የተጫኑ ሁለት ታላላቅ ቅርንጫፎች አሉን። እነዚህን የታመኑ ቃሎች እንደ መዝገብ አስቀምጡ። የሕይወታችን፥ የመጽናናታችንና የትምህርታችን መሪዎች ይሁኑ። የአሕዛብ ሐዋርያ የታመኑ መሆናቸውን አረጋግጦአል፤ አሁንም የታመኑ ናቸው፤ አንድ ቃል ስንኳ በምድር ላይ አይወድቅም፤ ሁሉ እንዲቀበሉአቸው የተገቡ ናቸው፤ አሁን እንቀበላቸው፥ ታማኝነታቸውንም እንፈትን። እነዚህ አራት የታመኑ ቃሎች በቤቴ በአራቱ ማዕዘን ላይ ይጻፉ።

ኦክቶበር 28

«እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ።» (ዮሐንስ 15:19)

ልዩ የሚያደርግ ጸጋና የሚለይ ፍቅር ይህ ነው፤ አንዳንዶች የመለኮታዊ ፍቅር ልዩ ተቀባዮች ተደርገዋልና። በዚህ ከፍ ባለ የምርጫ ትምህርት ላይ ለማሰላሰል አትፍራ። አእምሮህ እጅግ በከበደና በተጨነቀ ጊዜ እጅግ የበለጸገ የሚያበረታ መጠጥ የተሞላ ጠርሙስ ሆኖ ታገኘዋለህ። የጸጋን ትምህርቶች የሚጠራጠሩ ወይም ወደ ጥላ የሚገፉአቸው የኤሽኮልን እጅግ የበለጸጉ ዘለላዎች ያጣሉ፤ በአምቡላ ላይ የቆየውንና የጠራውን የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላበትን የሰባ ነገር ያጣሉ። በገለዓድ ከእርሱ ጋር የሚወዳደር በለሳን የለም። በዮናታን ዱር ያለው ማር በተነካ ጊዜ ዓይኖችን ካበራ፥ ይህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢራት እንድትወድድና እንድትማር ልብህን የሚያበራ ማር ነው። ብላ፥ መጥገብንም አትፍራ፤ በዚህ ምርጥ ጣፋጭ ምግብ ኑር፥ እጅግ የቀመሰ ምግብ ይሆናል ብለህም አትፍራ። ከንጉሡ ማዕድ የሚገኝ ምግብ ከአሽከሮቹ አንዱንም አይጎዳም። የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ፥ ለዘላለም የሚኖር፥ የሚለይ ፍቅር ይበልጥ ይበልጥ እንድትረዳ አእምሮህ እንዲሰፋ ተመኝ። እስከ ምርጫ ከፍታ በወጣህ ጊዜ በእኅቱ ተራራ በጸጋ ኪዳን ላይ ቆይ። የኪዳን ቃል ኪዳኖች ከኋላቸው ተመሽገን የምንተኛባቸው የግዙፍ ዓለት ምሽጎች ናቸው፤ ከዋሱ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር የተደረጉ የኪዳን ቃል ኪዳኖች ለሚንቀጠቀጡ መናፍስት ጸጥ ያሉ ማረፊያዎች ናቸው።

«መሐላው፥ ኪዳኑ፥ ደሙ፥

በሚናወጥ ጎርፍ ውስጥ ይደግፉኛል፤

ምድራዊ ምርኩዝ ሁሉ ሲወድቅ፥

ይህ ዘወትር ኃይሌና መደገፊያዬ ነው።»

ኢየሱስ ወደ ክብር ሊያመጣኝ ኃላፊነት ከወሰደ፥ አብም ለነፍሱ ጭንቅ ማለቂያ የሌለው ዋጋ አንድ ክፍል እንድሆን ለወልድ እንደሚሰጠኝ ተስፋ ከሰጠ፥ እንግዲያስ ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔር ራሱ ታማኝ እስካልሆነ ድረስ፥ ኢየሱስም እውነት መሆኑን እስኪያቆም ድረስ፥ አንቺ በደኅና ነሽ። ዳዊት በታቦቱ ፊት በዘፈነ ጊዜ እንዲህ እንዲያደርግ ያደረገው ምርጫ እንደ ሆነ ለሜልኮል ነገራት። ነፍሴ ሆይ፥ ነዪ፥ በጸጋ አምላክ ፊት ሐሤት አድርጊ፥ ከልብሽም ደስታ የተነሣ ዝለዪ።

ኦክቶበር 29

«እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ። በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ ወዘተ።» (ማቴዎስ 6:9)

ይህ ጸሎት እውነተኛ ጸሎት ሁሉ ሊጀመርበት በሚገባው ስፍራ፥ በልጅነት መንፈስ፥ «አባታችን» በማለት ይጀምራል። «ተነሥቼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ» እስክንል ድረስ ተቀባይነት ያለው ጸሎት የለም። ይህ የሕፃንነት መንፈስ «በሰማያት» ያለውን የአባቱን ግርማ ፈጥኖ ይገነዘባል፥ ወደ ቅን ስግደትም ይወጣል፤ «ስምህ ይቀደስ።» «አባ፥ አባት» ብሎ የሚንተባተበው ልጅ «ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ» ወደሚለው ኪሩብ ያድጋል። ከሐሤት አምልኮ ወደሚንበለበለው የሚስዮናዊ መንፈስ አንድ እርምጃ ብቻ ነው፤ ይህም የልጅነት ፍቅርና የአክብሮት ስግደት እርግጠኛ ፍሬ ነው፤ «መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን።» ቀጥሎም በእግዚአብሔር ላይ መደገፍን የሚገልጥ ከልብ የሆነ ቃል ይከተላል፤ «የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን።» በመንፈስ ይበልጥ ሲበራ፥ ጥገኛ ብቻ ሳይሆን ኃጢአተኛ መሆኑን ያስተውላል፤ ስለዚህ ምሕረትን ይለምናል፤ «እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤» ይቅርታን አግኝቶ፥ የክርስቶስ ጽድቅ ተቈጥሮለት፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ አውቆ፥ በትሕትና ቅዱስ መጽናትን ይማልዳል፤ «ወደ ፈተና አታግባን።» በእውነት ይቅር የተባለ ሰው ዳግመኛ ላለመበደል ይጨነቃል፤ መጽደቅን ማግኘት ለመቀደስ ወደ ብርቱ ምኞት ይመራል። «በደላችንን ይቅር በለን»፥ ይህ መጽደቅ ነው፤ «ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን»፥ ይህ በአሉታዊና በአዎንታዊ መልኩ መቀደስ ነው። የዚህ ሁሉ ውጤት ሆኖ የድል የምስጋና መግለጫ ይከተላል፤ «መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን።» የእኛ ንጉሥ በመግቦት እንደሚነግሥ በጸጋም እንደሚነግሥ፥ ከወንዝ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ፥ ለግዛቱም መጨረሻ እንደሌለው ደስ ይለናል። እንዲሁ ይህ አጭር የጸሎት ምሳሌ ነፍስን ከልጅነት ስሜት ጀምሮ ከሚነግሠው ጌታችን ጋር እስከ ኅብረት ድረስ ይመራታል። ጌታ ሆይ፥ እንዲህ መጸለይን አስተምረን።

ኦክቶበር 30

«አቤቱ፥ አመሰግንሃለሁ።» (መዝሙር 9:1)

ምስጋና ዘወትር የተመለሰን ጸሎት ሊከተል ይገባዋል፤ የሰማይ ፍቅር ፀሐይ ምድርን ሲያሞቅ የምድር የምስጋና ጭጋግ እንደሚወጣ። ጌታ ለአንተ ቸር ሆኖአልን? ወደ ልመናህም ድምፅ ጆሮውን አዘንብሎአልን? እንግዲያስ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ አመስግነው። የበሰለው ፍሬ ሕይወቱን ወደ ሳበበት ለም አፈር ይውደቅ። ጸሎትህን ለመለሰውና የልብህን ምኞት ለሰጠህ መዝሙርን አትከልክለው። ስለ እግዚአብሔር ምሕረቶች ዝም ማለት የውለታ ቢስነትን በደል መሸከም ነው፤ ከለምጻቸው ከነጹ በኋላ ፈዋሹን ጌታ ለማመስገን እንዳልተመለሱት እንደ ዘጠኙ ለምጻሞች በክፋት መሥራት ነው። እግዚአብሔርን ማመስገን መርሳት ራሳችንን ለመጥቀም እምቢ ማለት ነው፤ ምስጋና እንደ ጸሎት የመንፈሳዊ ሕይወትን እድገት ከሚያበረታቱ ታላላቅ መንገዶች አንዱ ነውና። ሸክማችንን ለማስወገድ፥ ተስፋችንን ለማነሣሣት፥ እምነታችንን ለመጨመር ይረዳል። የአማኙን የልብ ትርታ የሚያፋጥን፥ በጌታውም አገልግሎት ለአዲስ ተግባር የሚያበረታው ጤናማና ኃይል ሰጪ ልምምድ ነው። ስለ ተቀበልነው ምሕረት እግዚአብሔርን መባረክ ደግሞ ባልንጀሮቻችንን የምንጠቅምበት መንገድ ነው፤ «ትሑታን ይህን ሰምተው ደስ ይላቸዋል።» በተመሳሳይ ሁኔታ የነበሩ ሌሎች፥ «ኦ! ከእኔ ጋር እግዚአብሔርን ታላቅ አድርጉት፤ በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ፤ ይህ ችግረኛ ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው» ማለት ብንችል ይጽናናሉ። ደካሞች ልቦች ይበረታሉ፥ የዛሉ ቅዱሳንም «የመዳን ዝማሬያችንን» ሲሰሙ ይነቃቃሉ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችን ስንማማርና ስንገሣሥ ጥርጣሬአቸውና ፍርሃታቸው ይገሠጻል። እነርሱም ቅዱስ ስሙን ታላቅ ስናደርግ ሲሰሙ «በእግዚአብሔር መንገድ ይዘምራሉ።» ምስጋና ከክርስቲያን ግዴታዎች ሁሉ እጅግ ሰማያዊ ነው። መላእክት አይጸልዩም፤ ነገር ግን ቀንና ሌሊት ማመስገንን አያቆሙም፤ ነጭ ልብስ የለበሱ፥ የዘንባባ ዝንጣፊዎችንም በእጃቸው የያዙ የተዋጁት «የታረደው በግ ይገባዋል» የሚለውን አዲስ መዝሙር ከመዘመር ከቶ አይታክቱም።

ኦክቶበር 31

«የቀናውን መንፈስ በውስጤ አድስ።» (መዝሙር 51:10)

ያፈገፈገ ሰው በውስጡ የሕይወት ብልጭታ ቢቀር ወደ መታደስ ይቃትታል። በዚህ መታደስ በመለወጣችን ጊዜ እንደ ነበረው ያው የጸጋ አሠራር ያስፈልጋል። ያን ጊዜ ንስሐ አስፈልጎን ነበር፤ አሁንም በእርግጥ ያስፈልገናል። በመጀመሪያ ወደ ክርስቶስ እንድንመጣ እምነት ያስፈልገን ነበር፤ አሁንም ወደ ኢየሱስ ሊያመጣን የሚችለው ያው ጸጋ ብቻ ነው። ያን ጊዜ ፍርሃታችንን ለማስቆም ከልዑል ቃል፥ ከተወዳጁ አፍ ቃል ያስፈልገን ነበር፤ የአሁኑ ኃጢአት ስሜት በያዘን ጊዜ አሁንም እንደሚያስፈልገን ፈጥነን እናውቃለን። ማንም ሰው በመጀመሪያ እንደ ተሰማው ያህል እውነተኛና ትክክለኛ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል መገለጥ ሳይኖር ሊታደስ አይችልም፤ ሥራው እንዲሁ ታላቅ ነውና፥ ሥጋና ደምም እንደ ቀድሞው ሁሉ አሁንም መንገድ ላይ ቆመዋልና። ክርስቲያን ሆይ፥ የግል ድካምህ ወደ አምላክህ እርዳታ ለማግኘት አጥብቀህ እንድትጸልይ የሚያደርግ ምክንያት ይሁንልህ። አስታውስ፥ ዳዊት አቅም እንደሌለው በተሰማው ጊዜ እጆቹን አላጣጠፈም፥ ከንፈሮቹንም አልዘጋም፤ ነገር ግን «የቀናውን መንፈስ በውስጤ አድስ» እያለ ወደ ምሕረት ዙፋን ፈጠነ። ያለ እርዳታ ምንም ማድረግ አትችልም የሚለው ትምህርት እንድታንቀላፋ አያድርግህ፤ ነገር ግን በሚያስፈራ ትጋት ወደ እስራኤል ብርቱ ረዳት የሚነዳህ በጎንህ ያለ መውጊያ ይሁን። ኦ፥ ስለ ሕይወትህ ራሱ እንደምትማልድ ሆነህ በእግዚአብሔር ፊት ለመማለድ ጸጋ ቢኖርህ! «ጌታ ሆይ፥ የቀናውን መንፈስ በውስጤ አድስ።» ይህን እንዲያደርግ ወደ እግዚአብሔር በቅንነት የሚጸልይ እግዚአብሔር የሚሠራባቸውን መንገዶች በመጠቀም ቅንነቱን ያረጋግጣል። ብዙ ጊዜ በጸሎት ሁን፤ በእግዚአብሔር ቃል ብዙ ኑር፤ ጌታህን ከአንተ ያባረሩትን ምኞቶች ግደል፤ ወደ ፊት የሚነሡትን የኃጢአት መነሣሣቶች ለመጠበቅ ተጠንቀቅ። ጌታ የራሱ የተወሰኑ መንገዶች አሉት፤ በመንገድ ዳር ተቀመጥ፥ በሚያልፍበትም ጊዜ ዝግጁ ትሆናለህ። እየሞቱ ያሉትን ጸጋዎችህን በሚያሳድጉና በሚመግቡ በእነዚያ የተባረኩ ሥርዓቶች ሁሉ ጽና፤ ኃይል ሁሉ ከእርሱ ሊወጣ እንደሚገባ አውቀህም፥ «የቀናውን መንፈስ በውስጤ አድስ» ብለህ መጮኽን አታቋርጥ።

ጨርሰዋል፦ የኦክቶበር ወር

ቀዳሚ ቀጣይ