ሕይወት፣ ተሞክሮና የወንጌል ድካም
የተስፋ ጸሎት

ምዕራፍ 5 · 1 ደቂቃ ንባብ · 1 ደቂቃ ማዳመጥ

የተስፋ ጸሎት

አምላኬ ሆይ! በሥጋዊም በመንፈሳዊም አደጋዎቼ ሁሉ በአንተ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አንተ ሁሉን የምትችል ኃይል ነህና ልትረዳኝ ትችላለህ፤ ወሰን የሌለህ ቸርነትም ነህና ልትደግፈኝ ዝግጁና ፈቃደኛ ነህ።

የውዱ ቤዛዬ ክቡር ደም ሆይ! የተሰቀለው መድኃኒቴ የተከፈቱ ቍስሎች ሆይ! ሰው የሆነውን የአምላክን መከራ እያሰላሰለ ተስፋውን ከፍ የማያደርግና በእርሱ የማይታመን ማን ነው? ሥጋዬ ፈርሶ ትቢያ ቢሆን፣ ያም ትቢያ በምድር ፊት ላይ ቢበተን ምን ይሆናል? ቤዛዬ ሕያው እንደ ሆነ፣ በመጨረሻውም ቀን እንደሚያስነሣኝ ያለ ጥርጥር አውቃለሁ። ብጽናናም ብተውም፣ ሰላም ባገኝም በፈተና ብጨነቅም፣ ጤናማ ብሆንም ብታመምም፣ የዚህ ሕይወት መልካም ነገሮች ቢረዱኝም ቢተዉኝም፣ አንተ ዋናውና ወሰን የሌለህ መልካም ነገሬ ሆይ፣ ሁልጊዜ በአንተ ተስፋ አደርጋለሁ።

በለስ ባታብብ፥ በወይንም ግንድ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራም ሥራ ቢጐድል፥ እርሻዎችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎችም ከበረት ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጥ ውስጥ ባይገኙ፥ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፥ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሴት አደርጋለሁ።

እዚህ ባዝንና ብጨነቅ፣ ለጊዜውም በዚህ ዓለም መከራ ሥር ባቃስት ምን ይሆናል? እንባዬ አንድ ቀን ወደ ደስታ እንደሚለወጥ፣ ያንንም ደስታ ማንም እንደማይወስድብኝ እርግጠኛ ነኝ። በዚህ ዓለም ታላላቅ ነገሮችን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እነርሱን ለማግኘት ይደክማል፤ ታዲያ ለዚያ ዘላለማዊ ርስት ካልተጋሁና ካልደከምሁ፣ የዘላለም ሕይወት ተስፋዬ እንዴት በጽኑ መሠረት ላይ ሊቆም ይችላል? እንዲህ ያለ ክቡር ደመወዝ ለመቀበል እየጠበቅሁ፣ እጅግ ዝቅተኛውን ድካም ፈጽሞ እንቢ አልልም፤ እንዲህ ያለ ዘላለማዊ ዋጋ ለማግኘት እየተጠባበቅሁ፣ በማንኛውም ጊዜያዊ ኪሳራ ፈጽሞ አላጕረመርምም። የተባረክህ ተስፋ ሆይ! በሕይወቴ ዋና ደስታዬ ሁን፤ ያን ጊዜም የምደላደል፣ የማልነቃነቅም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛልኝ እሆናለሁ። በሞት ሰዓትም መጽናናቴና ደጋፊዬ ሁን፤ ያን ጊዜም ከእስራቱ እንደ ተፈታ ምርኮኛ ይህን ዓለም በእርካታ እተዋለሁ።

ገጽ 1 / 1 · 1 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ