የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ኢየሱስ ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገ

ምዕራፍ 104 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ኢየሱስ ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገ

ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ዳር ለሰባቱ ደቀ መዛሙርት ከተገለጠ ብዙ ሳይቈይ፥ በኢየሱስ ያመኑ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ እንዲሰበሰቡ ባዘዛቸው በገሊላ ባለው ተራራ ላይ ታላቅ ጉባኤ አደረጉ። በዚህ ጉባኤ የኢየሱስ ተከታዮች የሆኑ ከአምስት መቶ የሚበልጡ ሰዎች በአንድ ስፍራ እንደ ተሰበሰቡ ይነገራል። በዚያም ኢየሱስ ለጉባኤው ሁሉ ራሱን ገለጠ። ባዩትም ጊዜ በፊቱ እስከ ምድር ድረስ ሰገዱለት፤ ነገር ግን ያን ጊዜም እንኳ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ጌታን በእውነት አይተው እንደ ሆነ ተጠራጠሩ።

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ወደዚህ ጉባኤ ቀርቦ እንዲህ አላቸው፦

«የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መሆኔ፥ በሰማይና በምድርም የእግዚአብሔር መንግሥት ንጉሥ እንደ መሆኔ፥ ሥልጣን ሁሉ ከአባቴ ተሰጥቶኛል። ስለዚህ ሄዳችሁ ለዓለም ሁሉ ወንጌልን እንድትሰብኩ፥ አሕዛብንም ሁሉ በምድር ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንድታደርጉ አዝዛችኋለሁ። በእኔ የሚያምኑትን በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስም ስም አጥምቋቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው። በእኔ መድኃኒቱ አድርጎ የሚያምን ሁሉ ከኃጢአቱ ይድናል፤ የማያምን ግን የኃጢአቱን ፍርድ ይሸከማል። ለሚያምኑትም ይህ ኃይል ይሰጣቸዋል፤ በስሜ ክፉ መናፍስትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ልሳኖች ይናገራሉ፤ መርዘኛ እባቦችን በእጃቸው ይይዛሉ፥ አንዳችም አይጐዳቸውም፤ የሚገድል ነገር ቢጠጡ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ፥ እነርሱም ይድናሉ። እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።»

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ለያዕቆብ ዘጠነኛ ጊዜ ተገለጠ፤ ይህ የዮሐንስ ወንድም ያዕቆብ አይደለም፤ የዮሴፍና የማርያም ልጅ፥ የኢየሱስም ታናሽ ወንድም የሆነው ሌላው ያዕቆብ ነው። በዚያ መገለጥ የተነገረው ምን እንደ ሆነ አልተጻፈም፤ ነገር ግን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያዕቆብ ከኢየሱስ ተከታዮች ዋነኞቹ አንዱ ሆነ፤ ለብዙ ዓመታትም በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን መሪ ነበረ። ከዚህም ብዙ ዘመን በኋላ ያዕቆብ በአዲስ ኪዳን ካሉት መጻሕፍት አንዱን፥ የያዕቆብን መልእክት ጻፈ።

ኢየሱስ በአርባ ቀን ውስጥ አልፎ አልፎ ለደቀ መዛሙርቱና ለተከታዮቹ ታየ። ኢየሱስ የተገለጠባቸውን ዐሥር ጊዜያት እናውቃለን፤ ነገር ግን በወንጌሎች ወይም በሌሎቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ያልተጠቀሱ ሌሎች ጊዜያትም ሊኖሩ ይችላሉ። እኛ እንደምናውቀው ዐሥረኛውና የመጨረሻው መገለጡ ከመቃብሩ ከተነሣ ከአርባ ቀን በኋላ በኢየሩሳሌም በሰገነቱ ላይ ባለው ቤት ሳይሆን አይቀርም። በዚያን ጊዜ እንዲህ አለ፦

«ከእናንተ ጋር ሳለሁ፥ በሙሴ መጻሕፍትና በመዝሙራት በነቢያትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ሊፈጸም እንዲገባው ነገርኋችሁ።»

ከዚያም በብሉይ ኪዳን የተጻፈውን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው።

እንዲህም አለ፦ «የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ መከራ ሊቀበል፥ ሊሞትም፥ በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ እንዲገባው ተጽፎአል፤ ይህም እንደ ተፈጸመ አያችሁ። አሁንም ሰዎች በየስፍራው ሁሉ ከኃጢአታቸው ተመልሰው ወደ እግዚአብሔር እንዲዞሩ፥ በተሰጠኝም ኃይል ኃጢአታቸው እንዲሰረይላቸው ልትሰብኩ ትሄዳላችሁ። ስብከታችሁንም እዚሁ በኢየሩሳሌም፥ እኔ በተሰቀልሁበት በዚሁ ስፍራ ትጀምራላችሁ። አባቴ የሰጠውን ተስፋ፥ መንፈስ ቅዱስን፥ በቅርቡ በላያችሁ እልካለሁ። ነገር ግን ከላይ ኃይል እስኪመጣባችሁ ድረስ በዚች ከተማ ቈዩ።»

ከዚያም ከሙታን የተነሣው ክርስቶስ ከከተማ ወደ ደብረ ዘይት አወጣቸው። ከሌሎች ሰዎች ሁሉ የተሰወረ ነበርና በእርሱ ካመኑት በቀር ማንም ሊያየው አልቻለም። ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ እጆቹን አንሥቶ ተከታዮቹን ባረካቸው። እነርሱም ሲመለከቱት፥ እጆቹም ተዘርግተው ሳሉ፥ ወደ ላይ ከፍ ከፍ እያለ ወደ አየር ወጣ፤ ከጥቂት ጊዜም በኋላ ደመና ከዓይናቸው ሰወረው፤ የክብር ጌታ ኢየሱስም ከዚያ ወዲያ አልታየም።

ወደ ላይ ሲመለከቱ ሳሉ፥ የሚያንጸባርቅ ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች፥ የእግዚአብሔር መላእክት፥ በአጠገባቸው ቆመው ታዩ። እነዚህ መላእክት የኢየሱስን ተከታዮች እንዲህ አሉአቸው፦

«የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን በዚህ ቆማችኋል? ከእናንተ የተወሰደው ይህ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲወጣ እንዳያችሁት እንዲሁ ደግሞ ወደ ምድር ይመጣል።»

እንዲሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በዚያም በእግዚአብሔር ቀኝ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ። ወደ ምድር የሚመለስበት ቀን እስኪደርስ ድረስ ሕዝቡን እየጠበቀ አሁንም በዚያ ተቀምጦአል።


ቀዳሚ