ምዕራፍ 6 · 8 ደቂቃ ንባብ · 10 ደቂቃ ማዳመጥ
ቅድስናና ቤዛነት
አምስተኛ ቀን።
«በኵርን ሁሉ ቀድስልኝ፤ ለእኔ ይሁኑ።» —ዘጸ. 13:2።
«በኵር ሁሉ የእኔ ነው፤ በግብፅ ምድር በኵርን ሁሉ በመታሁበት ቀን በእስራኤል ያለውን በኵር ሁሉ ቀደስሁ፥ ለራሴ ለየሁት፤ የእኔ ይሆናሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።» —ዘኍ. 3:13፤ 8:17።
«አምላክ እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ ስለዚህ ቅዱሳን ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ ነኝና።» —ዘሌ. 11:45።
«ተቤዥቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ።» —ኢሳ. 43:1።
በኮሬብ፥ በወደቀው ሰው ታሪክ ውስጥ ቅዱስ የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ መጠቀሱ በእግዚአብሔር መገለጥ ውስጥ ከሚጀምረው አዲስ ዘመን፥ ማለትም ከቤዛነት ዘመን ጋር እንዴት እንደ ተያያዘ አይተናል። በፋሲካ ቤዛነት ምን እንደ ሆነ የሚያሳየውን የመጀመሪያውን መገለጥ እናገኛለን፤ ከዚህም ጀምሮ ቅዱስ የሚለው ቃል ይበልጥ ደጋግሞ መነገር ይጀምራል። በቂጣ በዓል፥ በደም የሆነው ቤዛነት የሚያደርስበትን የአሮጌውን ማስወገድና የአዲሱን መልበስ የሚያመለክት ምሳሌ አለን። ስለ ሰባቱ ቀኖች እንዲህ እናነባለን፤ «በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፥ በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤» የተቤዠው ሕዝብ መዳኑን ለማሰብ መሰብሰቡ ቅዱስ ጉባኤ ነው፤ በታዳጊያቸው፥ በቅዱሱ ጥላ ሥር ይሰበሰባሉ። ሕዝቡ ከግብፅ እንደ ተቤዠ ወዲያው እግዚአብሔር ለእነርሱ የተናገረው የመጀመሪያው ቃል «በኵርን ሁሉ ቀድስልኝ —ለእኔ ቅዱስ አድርግልኝ፤ የእኔ ነው» የሚል ነበር። (ዘጸ. 13:2 ተመልከት።) ይህ ቃል ባለቤትነት በቤዛነትም በመቀደስም ውስጥ ካሉት ዋና ሐሳቦች አንዱ፥ ሁለቱንም አንድ ላይ የሚያስተሳስራቸው ማሰሪያ እንደ ሆነ ይገልጣል። ቃሉ እዚህ የተነገረው ስለ በኵሮች ብቻ ቢሆንም፥ እነርሱ የሕዝቡ ሁሉ ምሳሌ ሆነው ተቈጥረዋል። እድገትና አደረጃጀት ሁሉ ከአንድ ማእከል እንደሚጀምር፥ ከዚያም የሕያው አካሉ ሕይወት እየሰፉ በሚሄዱ ክበቦች እንደሚዘረጋ እናውቃለን። በሰው ዘር ውስጥ ያለው ቅድስና እውነተኛና ትክክለኛ፥ እንደ እግዚአብሔርም ቅድስና ነጻ እንዲሆን ከተፈለገ፥ ሰው ራሱ ተቀብሎ የራሱ በሚያደርገው እድገት የሚገኝ ፍሬ መሆን አለበት። ስለዚህ በኵሮች ይቀደሳሉ፥ ከዚያም በኋላ በእነርሱ ፋንታ ካህናቱ ይቀደሳሉ፤ ይህም ሕዝቡ ሁሉ በአሕዛብ መካከል የእግዚአብሔር በኵር፥ የእርሱ የተለየ ርስት፥ «ቅዱስ ሕዝብ» ሆኖ ምን ሊሆን እንዳለው የሚያሳይ ምሳሌ ነው። ከቤዛነትና ከመቀደስ ጋር የተያያዘው ይህ የባለቤትነት ሐሳብ እግዚአብሔር ካህናቱን በበኵሮች ፋንታ ስለ መለወጡ ሲናገር (ዘኍ. 3:12, 13፤ 8:16, 17) በተለየ ግልጥነት ይታያል፤ «ሌዋውያን ፈጽመው ለእኔ የተሰጡ ናቸው፤ በበኵሮች ፋንታ ለእኔ ወስጃቸዋለሁ፤ በኵር ሁሉ የእኔ ነውና፤ በግብፅ ምድር በኵርን ሁሉ በመታሁበት ቀን ለራሴ ቀደስኋቸው።»
በቤዛነትና በቅድስና መካከል ያለውን ዝምድና ለመረዳት እንሞክር። በገነት እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን መቀደሱ ምን እንደ ሆነ አይተናል፤ የራሱ አደረገው፥ ባረከው፥ በእርሱም ዐረፈና ተዝናና። እግዚአብሔር ገብቶ በሚያርፍበት ስፍራ ቅድስና አለ፤ ነገሩ እርሱ እንዲገባበትና እንዲያድርበት ይበልጥ ፍጹም ሆኖ በተዘጋጀ መጠን ቅድስናውም ይበልጥ ፍጹም ይሆናል። ሰባተኛው ቀን የሰው መቀደስ ዘመን ሆኖ ተቀደሰ። ነገር ግን እግዚአብሔር ሰውን ወደ ቅድስናው ሊመራው በወሰደው በመጀመሪያው እርምጃ —ከዛፉ እንዳይበላ በሰጠው ትእዛዝ— ሰው ወደቀ። እግዚአብሔር ዕቅዱን አልተወም፤ ነገር ግን አሁን ሌላ፥ ይበልጥ የዘገየ መንገድ መከተል ነበረበት። ሀያ አምስት ምዕተ ዓመታት በዝግታ ግን በሚያስፈልግ ዝግጅት ካለፉ በኋላ፥ አሁን ራሱን እንደ ታዳጊ ይገልጣል። ለራሱ የመረጠውንና ያበጀውን ሕዝብ፥ ልባቸው ታዳጊን እንዲናፍቅና እንዲቀበል ይዘጋጅ ዘንድ፥ ለጭቈናና ለባርነት አሳልፎ ይሰጣል። በተከታታይ ታላላቅ ተአምራት የጠላቶቻቸው አሸናፊ መሆኑን ያረጋግጣል፤ ከዚያም በደጃፋቸው ላይ በተቀባው በፋሲካው በግ ደም ቤዛነት ምን እንደ ሆነ ያስተምራቸዋል፤ ይህም በዚህ ምድር ካለ ግፈኛ ጨቋኝ ብቻ ሳይሆን ኃጢአታቸው ከሚገባው ከጽድቅ ፍርድ መዳን ነበር። ፋሲካ ከሚታየውና ጊዜያዊ ከሆነው ወደማይታየውና መንፈሳዊ ወደ ሆነው መሻገሪያ ይሆናቸዋል፤ እግዚአብሔርን ኃያል ብቻ ሳይሆን ቅዱስም መሆኑን ይገልጥላቸዋል፤ ከባርነት ቤትም ብቻ ሳይሆን ከአጥፊው መልአክም ነጻ ያወጣቸዋል።
እንዲህም ከተቤዣቸው በኋላ አሁን የራሱ መሆናቸውን ይነግራቸዋል። በሲና በቈዩበትና በምድረ በዳ በተጓዙበት ዘመን ሁሉ፥ እግዚአብሔር በክንዱ ብርታት የራሱ ያደረጋቸው የጌታ ሕዝብ መሆናቸውንና ይህንም ያደረገው እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ ለራሱ ቅዱሳን ያደርጋቸው ዘንድ መሆኑን ይህ ሐሳብ ዘወትር ይነገራቸው ነበር። የቤዛነት ዓላማ ባለቤትነት ነው፤ የባለቤትነትም ዓላማ ታዳጊና ባለቤት የሆነውን እርሱን መምሰል ነው፤ ይኸውም ቅድስና ነው።
ስለዚህ ቅድስናና ከቤዛነት የተነሣ ስለሚገኝበት መንገድ፥ የበኵሮች መቀደስ የሚያስተምረን ከአንድ በላይ ትምህርት አለ።
በመጀመሪያ፥ ቤዛነትና ቅድስና ምን ያህል የማይለያዩ እንደ ሆኑ መረዳት ያስፈልገናል። አንዱ ያለ ሌላው ሊኖር አይችልም። ወደ ቅድስና የሚያደርሰው ቤዛነት ብቻ ነው። ቅድስናን የምፈልግ ከሆንሁ፥ የተቤዠሁ መሆኔን፥ ስለዚህም የእግዚአብሔር ገንዘብና ርስት መሆኔን በግልጥና በሙላት በመለማመድ መኖር አለብኝ። ቤዛነት ብዙ ጊዜ ከአሉታዊ ጎኑ ብቻ፥ ከአንድ ነገር መዳን ተደርጎ ይታያል፤ እውነተኛ ክብሩ ግን ለእርሱ ለራሱ መቤዠት የሚለው አዎንታዊ ክፍሉ ነው። ቤትን ሙሉ በሙሉ መያዝ ማለት በውስጡ መኖር ማለት ነው፤ ቤት ኖሮኝ ባልኖርበት የርኵሰትና የክፋት ሁሉ መኖሪያ ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር እኔን ፈጽሞ ለመያዝ ብሎ ተቤዠኝ፥ የራሱም አደረገኝ። ስለ ነፍሴ «የእኔ ናት» ይላል፤ የባለቤትነት መብቱም እንዲታወቅና ፈጽሞ እንዲገለጥ ይሻል። እግዚአብሔር ገብቶ ፈጽሞና ሙሉ በሙሉ በያዘበት በዚያ ፍጹም ቅድስና ይሆናል። በእኔ ላይ መብትንና ኃይልን ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ቤዛነት ነው፤ አሁን እግዚአብሔር እንዲይዘኝና እንዲባርከኝ ነጻ የሚያወጣኝ ቤዛነት ነው፤ ኃይሉ በእኔ የሚሠራውን ሁሉ ማረጋገጫና ልምምድ የሚያመጣልኝ፥ የተረዳሁትና ነፍሴን የሞላው ቤዛነት ነው። በእግዚአብሔር ዘንድ ቤዛነትና መቀደስ አንድ ናቸው፤ ቤዛነት መለኮታዊ እውነት ሆኖ በያዘኝ መጠን፥ ከታዳጊው አምላክ፥ ከቅዱሱ ጋር ይበልጥ እተሳሰራለሁ።
እንዲሁም ደግሞ፥ የቤዛነትን ማረጋገጫና ደስታ የሚያመጣው ቅድስና ብቻ ነው። ቤዛነትን ከዚህ ባነሰ ደረጃ አጥብቄ ለመያዝ ብፈልግ ልታለል እችላለሁ። ትጋቴን ብተውና ግድ የለሽ ብሆን፥ ዓላማው ከሆነው ከቅድስና ለይቼ በቤዛነት የመታመንን ሐሳብ እንኳ ልፈራው ይገባኛል። እግዚአብሔር ለእስራኤል «ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፤ ስለዚህ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ» ብሎ ተናገረ። የራሱ ያደረገን፥ እኛንም ቅዱሳን እንድንሆን የሚጠራን ታዳጊው እግዚአብሔር ነው፤ ቅድስና ከቤዛነት ሁሉ እጅግ አስፈላጊና እጅግ ውድ ክፍል ይሁንልን፤ ይኸውም የራሱ አድርጎ ለወሰደን፥ ፈጽሞም የራሱ ሊያደርገን ለተነሣው ለእርሱ ራሳችንን መስጠት ነው።
ሁለተኛው የምናገኘው ትምህርት በመቀደስ ውስጥ በእግዚአብሔርና በሰው ሥራ መካከል ያለው ግንኙነት ነው። እግዚአብሔር ሙሴን «በኵርን ሁሉ ቀድስልኝ» አለው። ከዚያም በኋላ «በኵርን ሁሉ ለራሴ ቀደስሁ» ይላል። እግዚአብሔር የሚያደርገውን የሚያደርገው በእኛ በኩል እንዲፈጸምና የራሳችን እንዲሆን ነው። በክርስቶስ ኢየሱስ እንደ ተቀደስን፥ የእርሱ ቅዱሳን እንደ ሆንን ሲነግረን፥ የሚናገረው ስለ ዓላማው ብቻ ሳይሆን በእውነት ስላደረገው ነገር ነው፤ በክርስቶስ በአንዱ መሥዋዕትና በእርሱ አዲስ ፍጥረት በመሆናችን ተቀድሰናል። ነገር ግን ይህ ሥራ የሰው ጎን አለው። ቅዱሳን እንድንሆን፥ ቅድስናን እንድንከተል፥ ቅድስናን ፍጹም እንድናደርግ ጥሪው ወደ እኛ ይመጣል። እግዚአብሔር የራሱ አደረገን፤ የእርሱ መሆናችንንም እንድንናገር ይፈቅድልናል፤ አሁን ግን ሁሉን በሙላቱ ይሞላ ዘንድ ወደ ውስጣዊ ማንነታችን ምሥጢራዊ ክፍሎች ሰፋ ያለ መግቢያ እንድንሰጠው ይጠብቀናል። ቅድስና ወደ እግዚአብሔር የምናመጣው ወይም ለእርሱ የምናደርገው ነገር አይደለም። ቅድስና በእኛ ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር ነገር ነው። እግዚአብሔር በመቀደስ ራሱን የእኛ ያደርግ ዘንድ በቤዛነት የራሱ አደረገን። ቅዱሳን በመሆን ረገድ የእኛ ሥራም ሕይወታችንን ሁሉ፥ እያንዳንዱንም ክፍሉን ለዚህ ቅዱስ አምላክ አገዛዝ ማስገዛት፥ ብልታችንን ሁሉና ኃይላችንን ሁሉ በመሠዊያው ላይ ማኖር ነው።
ይህም በመቀደስ ውስጥ ድንገተኛው ነገርና ቀስ በቀስ የሚሆነው ነገር እንዴት እንደሚገናኙ ለሚለው ጥያቄ መልሱን ያስተምረናል፤ ማለትም መቀደስ አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተጠናቀቀ ሆኖ ሳለ፥ ገና ያልተፈጸመና ፍጹም መሆን የሚያስፈልገው እንዴት ነው? እግዚአብሔር የሚቀድሰው ነገር እንደ ስጦታው በመለኮታዊና በፍጹም ቅድስና ቅዱስ ነው፤ ሰው ግን እግዚአብሔር በቀደሰው ነገር ረገድ ያንን ቅድስና በማወቅ፥ በመጠበቅና በሥራ በመግለጥ ሊቀድስ ይገባዋል። እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ቀደሰ፤ ሰው ሊቀድሰው፥ ማለትም ቅዱስ አድርጎ ሊጠብቀው ይገባዋል። እግዚአብሔር በኵሮችን የራሱ አድርጎ ቀደሳቸው፤ እስራኤል ሊቀድሳቸው፥ እንደ ቅዱሳን ሊይዛቸውና ለእግዚአብሔር ሊሰጣቸው ይገባ ነበር። እግዚአብሔር ቅዱስ ነው፤ እኛ ያንን ቅድስና በማወቅ፥ በማምለክና በማክበር እርሱን ልንቀድሰው ይገባናል። እግዚአብሔር ታላቅ ስሙን ቀደሰ፤ ስሙ ቅዱስ ነው፤ እኛም ስሙን በመፍራት፥ በእርሱ በመታመንና የቅድስናው መገለጫ አድርገን በመጠቀም ያንን ስም እንቀድሳለን። እግዚአብሔር ክርስቶስን ቀደሰው፤ ክርስቶስም እግዚአብሔር በቀደሰው ቅድስና በግል ፈቃዱና በሥራው ፍጹም በመስማማት ራሱን ቀደሰ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ቀድሶናል፤ እኛም ለዚያ ቅድስና ኃይል ራሳችንን በማስገዛት፥ በሥራ በመግለጥና በሕይወታችንና በአካሄዳችን ሁሉ በማሳየት ቅዱሳን ልንሆን ይገባናል። አንድ ጊዜ ፈጽሞና ሙሉ በሙሉ የተሰጠው ውጫዊው መለኮታዊ ስጦታ በግል ውስጣዊ ርስት ሆኖ የራሳችን ሊሆን ይገባዋል፤ ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ራሳችንን ልናነጻ ይገባናል። ለቅድስና ተቤዠን፤ ሁለቱ ሐሳቦች በእግዚአብሔር አሳብና ሥራ እንደ ተያያዙ፥ በልባችንና በሕይወታችንም ሊያያዙ ይገባቸዋል።
ኢሳይያስ ሁለተኛውን፥ እውነተኛውን ቤዛነት ባወጀ ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን ስም «ታዳጊው፥ የእስራኤል ቅዱስ» ብሎ ከሙሴ ይልቅ በግልጥና በሙላት እንዲገልጥ ተሰጠው። ይህን ስም ባጠናነው፥ በቀደስነውና እግዚአብሔርን በእርሱ ባመለክነው መጠን ቃላቱ ይበልጥ የማይለያዩ ሆነው ይተሳሰራሉ፤ ታዳጊው ቅዱስ እንደ ሆነ የተቤዡትም ደግሞ ቅዱሳን እንደ ሆኑ እናያለን። ኢሳይያስ ስለ «የቅድስና መንገድ» ሲናገር «የተቤዡት በዚያ ይሄዳሉ» ይላል። ከእግዚአብሔር ቅድስና የሚወጣው ቤዛነት ወደ ቅድስናው መልሶ ሊያደርስ ይገባዋል። በክርስቶስ መቤዠት በክርስቶስ ቅዱስ መሆን እንደ ሆነ እንረዳለን፤ የታዳጊው አምላካችንም ጥሪ አዲስ ትርጕም ያገኛል፤ «እኔ ቅዱስ ነኝ፤ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።»
እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ።
አቤቱ ጌታ አምላክ! የእስራኤል ቅዱስና ታዳጊው ሆይ! በጥልቅ ትሕትና በፊትህ እሰግዳለሁ። ከቅዱስነትህ ይልቅ ታዳጊነትህን አስቀድሜ ለረጅም ጊዜ እንደ ፈለግሁህ በኀፍረት እናዘዛለሁ። የተቤዠኸኝ ቅዱስ ሆነህ እንደ ሆነ፥ ቤዛነት የቅድስናህ ውጤትና ፍሬ እንደ ሆነ፥ ከቅድስናህም ተካፋይ መሆን ብቸኛ ዓላማውና ከፍተኛ ውበቱ እንደ ሆነ አላወቅሁም ነበር። ያሰብሁት ከባርነትና ከሞት ስለ መቤዠት ብቻ ነበር፤ እንደ እስራኤል፥ ከአንተ ጋር ያለ ኅብረትና አንተን ያለ መምሰል ቤዛነት ዋጋውን እንደሚያጣ አላስተዋልሁም።
እጅግ ቅዱስ አምላክ ሆይ! የተቤዠሃቸውን ሰዎች ራስ ወዳድነትና ዝግታ በምትታገሥበት ትዕግሥት አመሰግንሃለሁ። ቅዱሳንህን፥ እኔንም ጭምር እየመራ፥ ለቤዛነት ዋጋ የሚሰጠው ቅድስናህና ከእርሱ ተካፋዮች እንድንሆን የቀረበልን ጥሪ እንደ ሆነ፥ የተቤዠነውም ለአንተ ለቅዱሱ፥ የአንተ እንድንሆን፥ በአንተ እንድንያዝና እንድንቀደስ እንደ ሆነ እንድናይ ስለሚያስተምረን ስለ ቅድስናህ መንፈስ አመሰግንሃለሁ።
አምላኬ ሆይ! በማይነገር ፍቅርና ደስታና ምስጋና፥ ከአንተ ዘንድ መቀደስና ቤዛነት ስለ ሆነልን ስለ ክርስቶስ አመሰግንሃለሁ። በእርሱ አንተ ታዳጊዬ፥ ቅዱሴ ነህ። በእርሱ እኔ የተቤዠኸኝ ሰውህ፥ ቅዱስህ ነኝ። አምላክ ሆይ! ይህን ያደረገልንን ከእውቀት የሚያልፈውን ፍቅር ለማምለክ፥ ደግሞም አሁን በክርስቶስ ቅዱስ ሆኖ በፊትህ በቆመው በእኔ እንደ ኃይልህ ታላቅነት ክቡር ዓላማህን ሁሉ እንደምትፈጽም ለማመን በማይነገር ስግደት እወድቃለሁ። አሜን።
1. «በደሙ የተደረገ ቤዛነት።» ደሙን በቅድስና መንገድ መግቢያ ደጃፍ ላይ እናገኘዋለን። የእግዚአብሔር እሳት የበላው፥ ነገር ግን ሊበላው ያልቻለው የመሥዋዕቱ ደም ነውና። ያ ደም እንዲህ ያለ የቅድስና ኃይል ስላለው «በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ» ብለን እናነባለን። ስለ ቅድስና ስታስብ ወይም ስለ እርሱ ስትጸልይ ሁልጊዜ በደም እንደ ተቤዠ ሰው ሁን። ዕለት ዕለት በሚያነጻው ኃይሉ በደሙ ጥላ ሥር ኑር።
2. የእግዚአብሔርን ቅድስና እንደ እሳት ስናውቅና ለጽድቅ ፍርዱ ስንሰግድ ብቻ የደሙን ክቡርነት ወይም የቤዛነቱን እውነተኛነት ልናደንቅ እንችላለን። የእግዚአብሔርን ፍቅር እንደ ቸርነት ብቻ እስካሰብን ድረስ ጥሩ ለመሆን ልንጥር እንችላለን፤ በሚቤዠው አምላክ ማመን ግን በክርስቶስ ቅዱሳን የመሆንን ፍላጎትና ደስታ በውስጣችን ያነቃቃል።
3. እግዚአብሔር በተቤዠው ነገር ላይ ያለውን የባለቤትነት መብት ተረድተሃልን? የእኔ። አንተ የእኔ ነህ። የሚል ድምፅ ሰምተሃልን? ለአንተ እንዲናገረው እግዚአብሔርን በታላቅ ትሕትና ለምነው። በእርጋታም አድምጠው።
4. የፍጡር ቅድስና መነሻው በመለኮታዊ ፈቃድ፥ በመለኮታዊ ምርጫ፥ ቤዛነትና ባለቤትነት ውስጥ ነው። ለዚህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ራስህን አሳልፈህ ስጥ፤ በእርሱም ደስ ይበልህ።
5. እግዚአብሔር እንደ ፈጠረ እንዲሁ ለመቀደስ ተቤዠ። ለዚህ በእርሱ ታላቅ እምነት ይኑርህ።
6. እግዚአብሔር አንተን ፈጽሞ እንዲይዝህና እንደ ፈቃዱ እንዲያዝብህ ፍቀድለት። ቅድስና የእርሱ ነው፤ የእኛ ቅድስና እርሱ፥ ቅዱሱ፥ ሁሉ እንዲሆን መፍቀድ ነው።