በክርስቶስ ቅዱሳን
ቅድስናና ፍጥረት

ምዕራፍ 4 · 7 ደቂቃ ንባብ · 9 ደቂቃ ማዳመጥ

ቅድስናና ፍጥረት


ሦስተኛ ቀን።

«እግዚአብሔርም የሰንበትን ቀን ባረከ፥ ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ፈጥሮ ከሠራው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና።»—ዘፍ. 2፡3።

በዘፍጥረት የመጀመሪያዎች መጽሐፍ አለን። የሰው ጥበብ ፈጽሞ መልስ ሊያገኝላቸው ባልቻለ በብዙ ጥያቄዎች ላይ ለሚያበራው መለኮታዊ ብርሃን በተለይ ለመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕራፎቹ ባለ ዕዳዎች ነን። ቅድስናን በምንፈልግበትም ጊዜ ወደዚያው እንመራለን። በዘፍጥረት መጽሐፍ ሁሉ ቅዱስ የሚለው ቃል አንድ ጊዜ ብቻ ይገኛል። ያም አንድ ጊዜ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ሰማያዊ በረከት የሚያስተምረንና የሚሰጠን ሁሉ የሚፈልቅበትን ስውር ምንጭ በሚገልጥልን ሁኔታ ነው። ልንረዳው የምንሻው የዚያ ክቡር ቃል፥ ልንወርሰውም የምንሻው የዚያ ዋጋ የማይወጣለት በረከት፥ ማለትም የ«በክርስቶስ የተቀደሱ» ሙሉ ትርጉም፥ እግዚአብሔር የፍጥረት ሥራውን የፈጸመበትንና ያ ሥራ እንዴት በሚያስደንቅ ሁኔታ እንደሚቀጥልና ፍጹም እንደሚሆን የገለጠበትን ያንን ድንቅ ሥራ በተመለከተ እዚህ ከተጻፈው ይመነጫል። እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ሲባርከውና ሲቀድሰው፥ ከሌሎቹ ቀኖች በላይ ከፍ አደረገው፤ ከዚያ በፊት የነበረውን ሁሉ በክብር ለሚበልጥ ሥራና ለራሱ መገለጥ ለየው። በዚህ ቀላል አነጋገር መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ባሕርይ እንደ ቅዱሱ፥ የሚቀድስ አምላክ አድርጎ ይገልጥልናል፤ የሚቀድስበትንም መንገድ፥ ይኸውም ገብቶ በማረፍ መሆኑን፥ የእግዚአብሔርን መቀደስ ሁልጊዜ የሚያጅበውን የበረከት ኃይልም ይገልጥልናል። ቅድስናን ለማግኘት በምናደርገው ፍለጋ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ሁሉ ሥር የሆኑትን መሠረታዊ እውነቶች የያዙ በመሆናቸው እነዚህን ሦስት ትምህርቶች በሚገባ ማጥናት እጅግ አስፈላጊ ሆኖ እናገኘዋለን።

1. እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ቀደሰ። ሰማይና ምድር ወደ ሕልውና ከተጠሩበት ጀምሮ ሰው እስከ ተሠራበት ድረስ የስድስቱ ቀኖች ቁልፍ ቃል እግዚአብሔር ፈጠረ የሚለው ነበር። በድንገት አዲስ ቃልና አዲስ የእግዚአብሔር ሥራ ገባ፤ እግዚአብሔር ቀደሰ። ከፍጥረት የሚበልጥ፥ ፍጥረት የተገኘበት ዓላማ የሆነ ነገር አሁን ሊገለጥ ነው፤ ሁሉን የሚችል አምላክ አሁን እጅግ ቅዱስ አምላክ ሆኖ ሊታወቅ ነው። የፍጥረት ሥራ ኃይሉ ሳይጠቀስ ኃይሉን እንደሚያሳይ፥ እንዲሁ ሰባተኛውን ቀን መቀደሱ ቅዱሱ መሆኑን ባሕርዩን ይገልጣል። ሁሉን ቻይነት ከተፈጥሮአዊ ባሕርያቱ ዋናው እንደ ሆነ፥ ቅድስናም ከግብረ ገባዊ ባሕርያቱ የመጀመሪያው ነው። እርሱ ብቻውን ፈጣሪ እንደ ሆነ፥ እንዲሁ እርሱ ብቻውን ቀዳሽ ነው፤ መፍጠር ሥራው እንደ ሆነ ሁሉ መቀደስም በእውነት የእርሱ ብቻ ሥራ ነው። ይህን በእውነትና በሙላት የሚያምን የእግዚአብሔር ልጅ ብፁዕ ነው!

እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ቀደሰ። ይህ ቃል እግዚአብሔር ሲቀድስ የሚሠራው ሥራ ምን ዓይነት እንደ ሆነ ሊያስተምረን ይችላል። በገነት የነበረው መቀደስ በቤዛነት ከሚሆነው መቀደስ በመሠረቱ ሊለይ አይችልም። እግዚአብሔር ሥራዎቹን ሁሉ፥ ከእነርሱም ዋና የሆነውን ሰውን፥ እጅግ መልካም ብሎ ተናግሮ ነበር። ቢሆንም ቅዱሳን አልነበሩም። የስድስቱ ቀኖች ሥራ ምንም ርኵሰት ወይም ኃጢአት አልነበረበትም፤ ቢሆንም ቅዱስ አልነበረም። አስቀድሞ እጅግ መልካም የነበረውን ሰው የመቀደሱ ታላቅ ሥራ ይፈጸም ዘንድ ሰባተኛው ቀን በተለየ ሁኔታ መቀደስ አስፈለገው። በዘፀአት እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን የቀደሰው ሰውን ለመቀደስ ብሎ እንደ ሆነ በግልጥ ይናገራል፤ «የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ።» መልካምነት፥ የዋህነት፥ ንጽሕና፥ ከኃጢአት ነጻ መሆን ቅድስና አይደለም። መልካምነት የሁሉን ቻይነት ሥራ ነው፤ እግዚአብሔር እንደ ፈጠረው የተፈጥሮ ባሕርይ ነው፤ ቅድስና ግን ወሰን በሌለው ሁኔታ እጅግ ከፍ ያለ ነገር ነው። የእግዚአብሔርን ቅድስና ወሰን የሌለው ግብረ ገባዊ ፍጽምናው ብለን እንናገራለን፤ የሰው ግብረ ገባዊ ፍጽምና ግን ሊመጣ የሚችለው ፈቃዱን በመጠቀም፥ በነጻነት ለእግዚአብሔር ፈቃድ በመስማማትና በእርሱ በመኖር ብቻ ነበር። በዚህ ብቻ ቅዱስ ሊሆን ይችል ነበር። እግዚአብሔር ሰውን እንደሚቀድሰው መያዣ እንዲሆን ሰባተኛውን ቀን ቀደሰው። ከሰባተኛው ቀን በፊት በነበሩት ዘመናት፥ በፍጥረት ዘመን፥ የእግዚአብሔር ኃይል፥ ጥበብና መልካምነት ተገልጦ ነበር። የሚመጣው ዘመን፥ የሰባተኛው ቀን ዘመን፥ የቅድስና ዘመን ይሆናል፤ እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ቀደሰ።

2. እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ቀደሰ፥ ከሥራው ሁሉ በእርሱ ስላረፈ። ይህ ዕረፍት እውነተኛ ነገር ነበር። በፍጥረት እግዚአብሔር አዲስ ነገርን ለማስገኘት ከራሱ ወጥቶ እንደ ነበረ ነው፤ ሲያርፍ ግን በፈጠረው ሰው ላይ በፍቅሩ ደስ ሊሰኝና ራሱን ለእርሱ ሊያካፍል ከፈጠረው ሥራ ወደ ራሱ ይመለሳል። ይህ እግዚአብሔር የሚቀድስበትን መንገድ ይከፍትልናል። በማረፍና በመቀደስ መካከል ያለው ግንኙነት በዘፈቀደ የሆነ አልነበረም፤ መቀደሱም የኋላ ሐሳብ አልነበረም፤ በነገሩ ባሕርይ ሌላ ሊሆን አይችልም ነበር፤ የቀደሰው በእርሱ ስላረፈ ነው፤ በማረፍ ቀደሰ። የተፈጸመውን ሥራውን፥ በተለይም ሰውን፥ ሲመለከትና ደስ ሲሰኝበት፥ በዘፀአትም እንደ ተጻፈ «ሲዝናና»፥ ይህ የመለኮታዊ ዕረፍቱ ዘመን የጀመረውን ወደ ፍጻሜ የሚያደርስበት፥ በመልኩም የተፈጠረውን ሰው በእውነት የከፍተኛው ክብሩ፥ የቅድስናው፥ ተካፋይ የሚያደርግበት ዘመን ነው።

እግዚአብሔር በደስታና በፍቅር በሚያርፍበት ስፍራ ይቀድሳል። የሚገለጠው፥ የሚገባውና የሚይዘው የእግዚአብሔር መገኘት እውነተኛውን ቅድስና የሚያስገኘው ነው። ቅድስና ምን እንደ ሆነ በዘመናት ሂደት እየተገለጠ የሄደበትን ስናጠና ይህ እውነት ዘወትር ያጋጥመናል። እግዚአብሔር በሰማይ በማደሩ፥ በምድር ባለው መቅደሱ፥ በተወደደው ልጁ፥ በመንፈስ ቅዱስም በአማኙ ሰውነት ውስጥ፥ ቅድስና ሰው የሆነው ወይም የሚያደርገው ነገር ሳይሆን እግዚአብሔር በሚመጣበት ሁሉ የሚመጣ መሆኑን በየስፍራው እናገኛለን። በቃሉ ጥልቅ ትርጉም፥ እግዚአብሔር ሊያርፍ በሚገባበት ስፍራ በዚያ ይቀድሳል። ቅዱሳን የምንሆንበትን መንገድ በተመለከተ የአዲስ ኪዳንን መገለጥ ስናጠናም፥ ይህ ከቀደሙትና ከጥልቅ ትምህርቶቻችን አንዱ ሆኖ እናገኘዋለን። የቅድስናው ተካፋዮች የምንሆነው ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት ስንገባ ነው። «እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን»፤ «ወደ ዕረፍቱ የገባ፥ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፥ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና።» ነፍስ ከራሷ ጥረት ስታቆምና ሁሉን ስለ እኛ በፈጸመው፥ በእኛም ውስጥ ሁሉን በሚፈጽመው በእርሱ ስታርፍ፥ በእውነተኛ እምነት ጸጥ ባለ መታመን በእግዚአብሔር ለማረፍ ራሷን ስትሰጥ፥ ያን ጊዜ እውነተኛ ቅድስና ምን እንደ ሆነ ታውቃለች። ነፍስ ወደ ፍጹም መታመን ሰንበታዊ ጸጥታ በምትገባበት ስፍራ እግዚአብሔር ሰንበቱን ቅዱስ አድርጎ ሊጠብቅ ይመጣል፤ የሚያርፍባትንም ነፍስ ይቀድሳታል። ስለ ራሱ ቀን «ቀደሰው» ብንል፥ ወይም ስለ ራሱ ሕዝብ «በክርስቶስ የተቀደሱ» ብንል፥ የቅድስና ምሥጢር ሁልጊዜ አንድ ነው፤ «ስላረፈ ቀደሰ።»

3. ቀጥሎም «ባረከው፥ ቀደሰውም» ብለን እናነባለን። በመጀመሪያው ምዕራፍና በዘፍጥረት መጽሐፍ ሁሉ ውስጥ እንደ ተሠራበት «እግዚአብሔር ባረከ» የሚለው ቃል ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። «ብዙ፥ ተባዙ» የሚለው ለአዳም እንደ ሆነ እንዲሁ በኋላ ለኖኅና ለአብርሃም የትርጉሙ መለኮታዊ ማብራሪያ ነበር። እግዚአብሔር አዳምንና ኖኅን አብርሃምንም የባረከበት በረከት የፍሬያማነትና የብዛት፥ የመዋለድና የመባዛት ኃይል ነበር። እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ሲባርከው በቅድስናው ሕያው ኃይል ሞላው፤ ይኸውም እንደ እርሱ ወደ ዕረፍቱ ሊገቡና ሊቀድሱት በሚሹት ውስጥ ያ ቅድስና እንዲበዛና ራሱን እንዲያባዛ ነው። ሰባተኛው ቀን አሁንም የምንኖርበት ቀን ነው። ስለ እያንዳንዱ የፍጥረት ቀን እስከ መጨረሻው ድረስ «ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን» ተብሎ ተጽፎአል። ስለ ሰባተኛው ግን መዝገቡ ገና አልተጻፈም፤ እኛ አሁን በእርሱ ውስጥ እንኖራለን፤ የእግዚአብሔር የራሱ የዕረፍት፥ የቅድስናና የበረከት ቀን ነው። በተለየ ሁኔታ ገብቶ በመያዝ፥ በፍጥረቱ ደስ የሚሰኝበትና እርሱንም በመቀደስ የፍቅሩን ሙላት የሚገልጥበት ጊዜ አድርጎ፥ አሁን የምንኖርበትን ዘመን የመለኮታዊና የኃያል በረከት ዘመን አደረገው። በዚያው ጊዜም በረከቱ ምን እንደ ሆነ አስተማረን። ቅድስና ብፅዕና ነው። በቅዱስ ዕረፍቱ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ ብፅዕና ነው። በክርስቶስ ያሉት የእግዚአብሔር በረከቶች ሁሉ አንድ ምንጭ ብቻ፥ ይኸውም የእግዚአብሔርን ቅድስና፥ እንዳላቸው፥ እንዲሁ ሁሉም አንድ ዓላማ ብቻ አላቸው፤ ይኸውም የዚያ ቅድስና ተካፋዮች እንድንሆን ማድረግ ነው። እግዚአብሔር ፈጠረ፥ ባረከም፤ በፍጥረት በረከት። እግዚአብሔር ቀደሰ፥ ባረከም፤ በዕረፍቱ የሰንበት በረከት። የመልካምነት፥ የፍሬያማነትና የግዛት የሆነው የፍጥረት በረከት፥ በእግዚአብሔር በማረፍና ከእርሱ ጋር በኅብረት በመቀደስ በሆነው የሰንበት በረከት ዘውድ ሊደፋ ነው።

እግዚአብሔር የፈጸመው የፍጥረት ሥራ በኃጢአት ተበላሸ፤ በቅዱስ ዕረፍቱ በረከት ከእርሱ ጋር የነበረን ኅብረትም ተቋረጠ። የተፈጸመው የቤዛነት ሥራ ግን ይበልጥ እውነተኛ የሆነ ዕረፍትንና ወደ እግዚአብሔር ቅድስና ይበልጥ የጸና መግቢያን ከፈተልን። በቅዱሱ ቀን እንዳረፈ፥ እንዲሁ አሁን በቅዱሱ ልጁ ያርፋል። በእርሱም አሁን ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት በሙላት ልንገባ እንችላለን። «በክርስቶስ የተቀደስን» ስለ ሆንን በእርሱ እንረፍ። እግዚአብሔር በታላቅ ኃይሉ የፍጥረት ሥራውን በሚያስደንቅ ሁኔታ እንደ ፈጸመ፥ እንዲሁ የመቀደስ ሥራውን እንደሚፈጽምና ፍጹም እንደሚያደርግ ስለምናይ እንረፍ። እርሱ ባረፈበት እንድናርፍ፥ በራሱ ቅድስና እንድንቀደስ፥ በእግዚአብሔርም የራሱ በረከት እንድንባረክ ራሳችንን በክርስቶስ ለእግዚአብሔር እንስጥ። ቀዳሽ እግዚአብሔር የሚለው ስም አሁን በፈጣሪው እግዚአብሔር ዙፋን ላይ ተቀርጾአል። በሰው ልጅ ታሪክ መግቢያ ላይ ይህ ወሰን የሌለው የተስፋና የመታመን ቃል ያበራል፤ «እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም፥ በእርሱ ዐርፎአልና።»

እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ።

የተባረክህ ጌታ አምላክ ሆይ! በትሕትና እየሰገድሁ በፊትህ እወድቃለሁ። ፈጣሪ አምላክና ቀዳሽ አምላክ ብዬ አመልክሃለሁ። ራስህን ሁሉን የሚችል አምላክና እጅግ ቅዱስ አምላክ አድርገህ ገለጥህ። እንዲህ ያለ አምላክ መሆንህን እንዳውቅህና እንድታመንብህ አስተምረኝ ብዬ እለምንሃለሁ።

የሰንበትን ቀን በመቀደስህ የገለጥሃቸውን ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶች እንድማርና አጥብቄ እንድይዛቸው ጸጋን በትሕትና እለምንሃለሁ። ሰውን የፈጠርህበት ዓላማህ ቅድስናህን ለመግለጥና እርሱንም የቅድስናህ ተካፋይ ለማድረግ ነው። አቤቱ፥ ፈጣሪዬና ቀዳሼ አምላክ አድርጌ በአንተ እንዳምን አስተምረኝ፤ የስድስተኛውን ቀን የፍጥረት በረከት የሰጠው ያው ሁሉን የሚችል ኃይል የሰባተኛውን ቀን የመቀደስ በረከት እንደሚያረጋግጥልን በፍጹም ልቤ እንዳምን አስተምረኝ። ፈቃድህ መቀደሳችን ነው።

ጌታ ሆይ፥ ይህ በረከት እንዴት እንደሚመጣ ይበልጥ እንዳስተውል ደግሞ አስተምረኝ። የምትቀድሰው ልታርፍ፥ ልትዝናናና ራስህን ልትገልጥ በምትገባበት ስፍራ ነው። አምላኬ ሆይ! ልቤ የማረፊያ ስፍራህ ይሁን። በሚያሳርፍ እምነት ጸጥታና መታመን በአንተ ማረፍ እወዳለሁ፤ ሁሉን በእኔ ውስጥ የምትሠራው አንተ እንደ ሆንህ አምናለሁ። ከአንተ፥ ከፍቅርህና ከፈቃድህ ጋር እንዲህ ያለው ኅብረት የቅድስና ሕይወት ምሥጢር ይሁንልኝ። በእርሱ በቀደስኸን በጌታችን በኢየሱስ ስም እለምንሃለሁ። አሜን።

1. ፈጣሪው እግዚአብሔር ቀዳሹ እግዚአብሔር ነው። የመጀመሪያውን ሥራ የሠራው ሁሉን ቻይነት ሁለተኛውንም ደግሞ ይሠራል። ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሚያደርገኝ ልታመንበት እችላለሁ። እግዚአብሔር ቅዱስ ነው፤ እግዚአብሔር ሁሉ ነገሬ ከሆነ፥ መገኘቱ ቅድስናዬ ይሆናል።

2. ዕረፍት ከሥራ ማቆም ነው፤ ዳግመኛ ላለመሥራት ሳይሆን አዲስ ሥራ ለመጀመር ነው። እግዚአብሔር ያርፋል፤ ወዲያውም የሚያርፍበትን ሊቀድስ ይጀምራል። በኃይሉ ቃል ፈጠረ፤ በፍቅሩ ያርፋል። ፍጥረት የመቅደሱ መሠራት ነበር፤ መቀደስ ወደ ውስጥ መግባትና መያዝ ነው። ኦ፥ ወደ ሰው ባሕርይ የሆነው ያ ድንቅ መግባት!

3. እግዚአብሔር የሚያርፈው ባረፈና ፈጽሞ ለእርሱ በተሰጠ ነገር ብቻ ነው። ቀዳሹን እግዚአብሔርን መመልከት ያለብን በእምነት ዕረፍት ነው፤ እርሱ ወደ ዐረፈች ነፍስ ገብቶ ቅዱስ ሰንበቱን በእርሷ ይጠብቃል። እኛ በእግዚአብሔር ዕረፍት እናርፋለን፤ እግዚአብሔር በእኛ ዕረፍት ያርፋል።

4. በፈጠረው ሰው የሚያርፍ፥ በማረፉም የሚቀድስ፥ በመቀደሱም የሚባርክ አምላክ፥ እርሱ አምላካችን ነው፤ አመስግኑት፥ አምልኩትም። ሥራውንም እንዲሠራ ታመኑበት።

5. ዕረፍት! እንዴት ያለ ቀላል ቃል ነው። የእግዚአብሔር ዕረፍት! በዚያ ቃል ውስጥ እንዴት ያለ ሊታሰብ የማይችል የሕይወትና የፍቅር ሙላት አለ። እስኪጋርደንና ወደ እርሱ፥ ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት፥ እስክንገባ ድረስ በእርሱ ላይ እናሰላስል፤ በፊቱም እንስገድ። ዕረፍት የእግዚአብሔር ነው፤ የራሱን ዕረፍት እንድንካፈል በማድረግ ሊሰጠው የሚችል እርሱ ብቻ ነው።


ጨርሰዋል፦ ቅድስናና ፍጥረት

ቀዳሚ ቀጣይ