በክርስቶስ ቅዱሳን
ቅድስናና እውነት

ምዕራፍ 17 · 7 ደቂቃ ንባብ · 9 ደቂቃ ማዳመጥ

ቅድስናና እውነት


አሥራ ስድስተኛ ቀን።

«በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።»—ዮሐንስ 17፥17።

«እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ እውነትንም በማመን ለመዳን እንደ በኵራት መርጦአችኋል።»—2ኛ ተሰሎንቄ 2፥12።

እግዚአብሔር የሚጠቀምበት ዋናው የመቀደሻ መንገድ ቃሉ ነው። ሆኖም ሰዎችን ቅዱሳን በማድረግ ረገድ ምንም ውጤት የማያስገኝ ስንት የቃሉ ንባብና ጥናት፥ ስንት የቃሉ ትምህርትና ስብከት አለ። የሚቀድሰው ቃሉ አይደለም፤ ሊቀድስ የሚችል እግዚአብሔር ራሱ ብቻ ነው። እርሱም ይህን የሚያደርገው በቃሉ ብቻ ሳይሆን በቃሉ ውስጥ ባለው እውነት ነው። ቃሉ እንደ መሣሪያ እግዚአብሔር ቢጠቀምበት፥ እውነትን እንደሚይዝ ዕቃ ሆኖ ሊነገር የማይችል ዋጋ አለው፤ እንደ መሣሪያ እግዚአብሔር ባይጠቀምበት ግን ምንም ዋጋ የለውም። የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቃል ከቅዱሱ አምላክ ራሱ ጋር ለማያያዝ እንትጋ። እግዚአብሔር በቃሉ በኩል በእውነት ይቀድሳል።

ኢየሱስ ገና፥ «የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁ» ብሎ ነበር። ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ ለመረዳት እንሞክር። ያንን በዘላለም የተፈጸመውን ታላቅ ነገር አስብ፤ እግዚአብሔር ብለን የምንጠራው ወሰን የሌለው አካል ቃሉን ለልጁ ሲሰጥ፤ በቃሉ ልቡን ሲከፍት፥ ሐሳቡንና ፈቃዱን ሲያካፍል፥ ራሱንና ዓላማውን ሁሉ ፍቅሩንም ሲገልጥ። ከአእምሮ በላይ በሆነ መለኮታዊ ኃይልና እውነታ እግዚአብሔር ቃሉን ለክርስቶስ ሰጠ። በዚያው ሕያው ኃይል ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ መቀበል በቻሉት መጠንም በልባቸው እንዲሠሩ በመለኮታዊ ሕይወትና ጉልበት የተሞሉ ነበሩ። በምድር ባለ ሰው ቃል በእርሱ ያለውን ጥበብ ወይም ቸርነት ሁሉ እንደምናገኝ፥ እንዲሁ የሦስት ጊዜ ቅዱሱ ቃል በእግዚአብሔር ቅድስና ሕያው ነው። የሚቃጠለው ቅንዓቱና የሚቃጠለው ፍቅሩ ቅዱስ እሳት ሁሉ በቃሉ ውስጥ ያድራል።

ሆኖም ሰዎች እነዚህን ቃላት ሊይዙ፥ ሊያጠኑአቸውና ሊናገሩአቸው፥ ደግሞም ለቅድስናቸው ወይም ለመቀደስ ኃይላቸው ፈጽመው እንግዶች ሊሆኑ ይችላሉ። በቃሉ በኩል ሊቀድስ የሚገባው ቅዱሱ እግዚአብሔር ራሱ ነው። የዛፍ ሕይወት የሚገኝበት እያንዳንዱ ዘር ውስጣዊ ሕይወቱን የሚጠብቅና የሚሰውር ቅርፊት ወይም ልባስ አለው። ዘሩ ተስማሚ መሬት ሲያገኝና ቅርፊቱ ተሰንጥቆ ሲወገድ ብቻ ዘሩ ሊበቅልና ሊያድግ ይችላል። እንዲሁም ቃሉ በእርግጥ የሚቀድሰው ከእግዚአብሔር ቅድስና ጋር የሚስማማ፥ የሚናፍቀውና ራሱን የሚሰጠው ልብ ባለበት ብቻ ነው። እውነትን፥ በእርሱም ራሱን የሚገልጥለት በቃሉ ያልረካ፥ ነገር ግን በቃሉ ውስጥ ሕያውና ቅዱስ የሆነውን የሚፈልግ ልብ ነው። ሕይወታችንን እንዲገዛና እንዲሞላ፥ እግዚአብሔር ለክርስቶስ እንደ ሰጠው በክርስቶስ የተሰጠን፥ እርሱም እንደ ተቀበለው በእኛ የተቀበልነው ቃል ለመቀደስ ኃይል አለው።

ነገር ግን መድኃኒታችን በቃሉ ሳይሆን በእውነት ቀድሳቸው ማለቱን በተለይ ልናስተውል ይገባናል። በሰው ሥጋ፥ ነፍስና መንፈስ እንዳለ እንዲሁ በእውነትም አለ። በመጀመሪያ የቃል እውነት አለ፤ ሰው የያዘውን እውነት በእርግጥ ሳይረዳ ትክክለኛ የቃላት አቀማመጥ ሊኖረው ይችላል። ከዚያም የሐሳብ እውነት አለ፤ የእውነትን ኃይል ሳይለማመዱ በአእምሮ ግልጽ ማስተዋል ሊኖር ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እውነት እንደ ሕያው እውነታ ይናገራል፤ ይህም የምንመሰክረው እውነት መንፈስ ራሱ ገብቶ ውስጣዊ ሁለንተናችንን የያዘበት የሕይወት እውነት ነው። ክርስቶስ ራሱን እውነት ብሎ ይጠራል፤ ጸጋንና እውነትንም የተሞላ እንደ ሆነ ተነግሮለታል። መለኮታዊ ሕይወትና ጸጋ በእርሱ እንደ ተጨባጭ ህላዌና እውነታ አሉ። በሐሳብና በምክንያት በእኛ ላይ የሚሠራ ብቻ ሳይሆን ከአብ ያመጣልንን የዘላለም ሕይወት እውነታ አድርጎ ያካፍላል። መንፈስ ቅዱስ የእውነት መንፈስ ይባላል፤ የሚያካፍለው ሁሉ እውነተኛና ተጨባጭ፥ የማይታዩት ነገሮች ራሳቸው ናቸው፤ ወደ እውነት ይመራል፥ ወደ ሐሳብ እውነት ወይም ወደ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ወደ ሕይወት እውነት፥ በኢየሱስ እንዳለው እውነትን በግል ወደ መያዝ ይመራል። የእውነት መንፈስ እንደ መሆኑ የቅድስና መንፈስ ነው፤ ቅድስናው የሆነውን የእግዚአብሔርን ሕይወት እንደ ተጨባጭ ርስት ያመጣልናል።

ኢየሱስ «በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።» ያለው የዘር ሕይወት በቅርፊቱ እንደሚያድር በቃሉ ስለሚያድረው ስለዚህ ሕያው እውነት ነው። በቃሉና በእውነት መካከል ያለውን የቅርብ ግንኙነትና ሰፊ ልዩነትም እንድናስተውል ይወድዳል። ግንኙነቱ እግዚአብሔር የፈቀደውና የማይለያይ እንዲሆን የታሰበ ነው። «ቃልህ እውነት ነው፤» በእግዚአብሔር ዘንድ ሁለቱ አንድ ናቸው። በሰው ዘንድ ግን አይደሉም። ከኢየሱስ ጋር በቅርብ የተገናኙና ዘወትር የተነጋገሩ፥ እርሱ ግን ሰው ብቻ እንጂ ከዚያ ያለፈ ያልሆነላቸው ሰዎች እንደ ነበሩ፥ እንዲሁ ቃሉን የሚያውቁና የሚያስተውሉ፥ ነገር ግን ለእውነተኛው መንፈሳዊ ኃይሉ እንግዶች የሆኑ ክርስቲያኖች አሉ። ፊደሉ አላቸው መንፈሱ ግን የላቸውም፤ እውነት በቃል እንጂ በኃይል አይመጣላቸውም። በመንፈስና በእውነት ስለማይይዙት ቃሉ አይቀድሳቸውም። በአንጻሩ ግን እውነትን ከፍቅሩ ጋር መቀበል ምን እንደ ሆነ ለሚያውቁ፥ ከቃሉ ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ሁሉ በቃሉና በእነርሱም ውስጥ ለሚያድረው ለእውነት መንፈስ ራሳቸውን ለሚሰጡ ለሌሎች፥ ቃሉ በእርግጥ እንደ እውነት፥ እንደ መለኮታዊ እውነታ፥ የሚናገረውን እያካፈለና እየሠራ ይመጣል። መድኃኒታችንም «በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።» ያለው ስለዚህ ዓይነቱ የቃሉ አጠቃቀም ነው። እግዚአብሔር የሰጠው ቃል ሁሉ በእግዚአብሔር የዘላለም ሕይወትና ፍቅር ፈቃድም ኃይል፥ የአብ ዓላማ መገለጥና ማካፈል እንደ ነበረ፥ የእግዚአብሔር ቃል ለእርሱና በእርሱ እውነት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ በእኛ ሊሆን ይችላል። እንዲህም ስንቀበለው በእውነት እንቀደሳለን።

እንግዲህ በቅድስና መንገድ እዚህ የምንማራቸው ትምህርቶች ምንድር ናቸው? የመጀመሪያው ይህ ነው፤ ከተባረከው የእግዚአብሔር ቃል ጋር በምናደርገው ግንኙነት ሁሉ እንደ እግዚአብሔር እውነት፥ እንደ መንፈስና እንደ ኃይል ከመለማመድ ባነሰ ነገር እንዳንረካ እንጠንቀቅ። ኢየሱስ «በቃሌ ብትኖሩ… እውነትንም ታውቃላችሁ» አለ። ማንም ትንተና የዘርን ሕይወት ሊያገኝ ወይም ሊያረጋግጥ አይችልም፤ በተገቢው መሬት ትከለው፥ እድገቱም ስለ ሕይወቱ ይመሰክራል። የእግዚአብሔርን ቃል ከፍቅሩ ጋር ስንቀበለው፥ በእኛም ሲያድግና ሲሠራ ብቻ እውነቱን፥ የእግዚአብሔር እውነት እንደ ሆነም ልናውቅ እንችላለን። በኢየሱስ ቃላት በፍቅርና በመታዘዝ ስንኖር፥ ስንጠብቃቸውና ስናደርጋቸው፥ ከሰማይ የሆነው እውነት፥ በእነርሱ ያለው የመለኮታዊ ሕይወት ኃይል ይገለጥልናል። ክርስቶስ እውነት ነው፤ በእርሱ ፍቅርና ጸጋ፥ የእግዚአብሔር ሕይወት ራሱ፥ እንደ ተጨባጭ ህላዌ፥ እንደ ሕያውና ብርቱ ኃይል፥ ከዚህ በፊት በምድር ያልነበረ አዲስ ነገር ሆኖ ወደ ምድር መጥቶአል (ዮሐንስ 1፥17)፤ እንደ ሕያው እውነት እንዲይዘንና እንዲገዛን ለሕያው ክርስቶስ ራሳችንን እንስጥ፤ ያን ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ለእኛና በእኛ እውነት ይሆናል።

የክርስቶስ መንፈስ የእውነት መንፈስ ነው፤ በክርስቶስ ያለው ያ ተጨባጭ ሰማያዊ የመለኮታዊ ሕይወትና ፍቅር እውነታ፥ እውነቱ፥ ሊያካፍለውና ሊሰጠው የሚመጣ መንፈስ አለው። ቃሉ በጥንት በእርሱ የተነገረበት ያ መንፈስ ሳይኖር የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት ወይም ለማስተዋል ወይም ለመያዝ ከመሞከር እንጠንቀቅ፤ ቅርፊቱን ብቻ፥ የሐሳብና የስሜት እውነትን፥ ምናልባት እጅግ ውብ የሆነውን ነገር ግን እኛን ለመቀደስ ኃይል የሌለውን ብቻ እናገኛለን። የእውነት መንፈስ በውስጣችን ሊኖረን ይገባል። እርሱ ወደ እውነት ይመራናል፤ በእውነት ስንሆን እግዚአብሔር በእርሱና በእርሱ በኩል ይቀድሰናል። እውነት በእኛ፥ እኛም በእውነት መሆን አለብን። እግዚአብሔር በውስጥ እውነትን ይወድዳል፤ ክርስቶስ «ከእውነት ብትሆኑ»፥ «ከእውነት የሆነ ያውቀኛል» ብሎ ከሚናገርላቸው ሰዎች ልንሆን ይገባናል። በዕለት ተዕለት ኑሮና ጠባይ፥ በሐሳብና በሥራ በታችኛው ክፍል ለእውነት ጽኑ ፍቅርና ስለ እርሱ ሁሉን ለመሠዋት ፈቃደኝነት ሊኖር ይገባል፤ በመንፈሳዊ ሕይወትም ሃይማኖታችን ሁሉ በየዕለቱና በየቅጽበቱ ፈጽሞ በእግዚአብሔር እውነት እንዲቆም ጥልቅ ረሃብ ሊኖር ይገባል። የቃሉ እውነት የሚከፈተውና የሚገለጠው ለቀላል፥ ለትሑትና ለሕፃን መሰል መንፈስ ነው። በእንደነዚህ ያሉት የእውነት መንፈስ ሊያድር ይመጣል። እንደነዚህ ያሉት በየዕለቱ በዝምታና በባዶነት፥ በአክብሮትና በቅዱስ ፍርሃት በቅዱሱ ፊት ሲጠብቁ፥ መንፈስ ቅዱሱ በእነርሱ ይሠራል እውነትንም በውስጣቸው ይሰጣል። በቃሉ የተገለጠውን ክርስቶስን በመለኮታዊ ሕይወቱና ፍቅሩ የራሳቸው ሕይወት አድርጎ በዚህ መንገድ በማካፈል፥ በክርስቶስ ቅድስና ቅዱሳን ያደርጋቸዋል።

ሌላም ትምህርት አለ። ያንን ጸሎት አድምጥ፤ እርሱ ለዘላለም በሕይወት ኖሮ የሚጸልየው ጸሎት ምድራዊ ማስተጋቢያ ነው፤ «ቅዱስ አባት ሆይ! በእውነትህ ቀድሳቸው።» የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፥ ቅዱስ መሆን ትወድዳለህን? ዘወትር ወደ አብ እቅፍ ወደሚፈስሰውና ወደሚደርሰው ወደዚያ ብርቱ የምልጃ ጅረት ራስህን ጣል። ለሰው ንግግር እጅግ ጥልቅና ብርቱ በሆነ በማይነገር መቃተት ነፍስህ ሁሉ «ቅዱስ አባት ሆይ! በእውነትህ ቀድሰኝ» ብላ እስክትጮኽ ድረስ ይሸከምህ። ክርስቶስን እንደ እውነት፥ የምትናፍቀው እውነታ አድርገህ፥ ሁሉን በሚያሸንፈው ምልጃውም ስትታመን፥ በውስጥህ ያለውን መንፈስ የእውነት መንፈስ አድርገህ ስትጠብቅ፥ ወደ አብ ቀና ብለህ ተመልከት፥ እንዲቀድስህም የራሱን ቀጥተኛና ሁሉን ቻይ ሥራ ጠብቅ። የቅድስና ምሥጢር የሥላሴ ምሥጢር ነው። ወደ ቅዱስ ሕይወት ይበልጥ ጠልቆ መግባት በሦስቱ በአንዱ ኅብረት ላይ ያርፋል። በክርስቶስ የሚያጸናን፥ በየዕለቱ በአዲስ ስጦታ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጠን አብ ነው፤ ነፍስ «በእውነትህ ቀድሰኝ» በሚለው ጸሎት ዘወትር ቀና ብላ የምትመለከተው ወደ አብ፥ ወደ ቅዱሱ አባት ነው።

በሊቀ ካህናቱ ጸሎት ውስጥ ዋናው ሐሳብ ቅዱስ የሚለው ቃል እንደ ሆነ በሚገባ ተነግሮአል። እንደ አብ ባሕርይ (ዮሐንስ 17፥11)፥ እንደ ወልድ ስለ ራሱና ስለ እኛ ሥራ (ቁጥር 19)፥ እንደ አብ በመንፈስ በኩል ቀጥተኛ ሥራ (ቁጥር 17፥ 20)፥ የእግዚአብሔር ክብር በራሱና በእኛ መገለጥ ነው። ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንግባ፥ ከታላቁ ሊቀ ካህናታችን ጋር ስንሰግድም ስለ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ሁሉ «ቅዱስ አባት ሆይ! በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።» የሚል ጥልቅና የማያቋርጥ ጩኸት ይውጣ። እግዚአብሔር የሚቀድስበት ቃል በዚህ ይጠቃለላል፤ በክርስቶስ ቅዱሳን። እግዚአብሔር ይህን በእኛ እውነት ያድርገው!

እኔ ቅዱስ እንደ ሆንሁ እናንተ ቅዱሳን ሁኑ።

የተባረክህ አባት ሆይ! ለእስራኤል፥ እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝ እቀድሳለሁም ብለሃል። ነገር ግን እኛን የሚቀድሰው የቅድስናህ ሙሉ ክብር የተገለጠው በተወደደው ልጅህ ብቻ ነው። አንተ በእውነትህ የምትቀድሰን ቅዱስ አባታችን ነህ።

ልጅህ የሰጠኸውን ቃል ስለ ሰጠን፥ እርሱም ከአንተ በሕይወትና በኃይል እንደ ተቀበለው እኛም ደግሞ እንድንቀበለው ስለ ተቻለን እናመሰግንሃለን። አባት ሆይ! በፍጹም ልባችን እንቀበለዋለን፤ መንፈስ በውስጣችን እውነትና ሕይወት ያድርገው። እንዲሁ ኃጢአትን የምትበላ፥ ኃጢአተኛውን የምታድስ ቅዱስ እንደ ሆንህ እናውቅሃለን።

ከሁሉ በላይ እውነት ስለሚያድርበት ሕያው ቃል፥ ስለ እግዚአብሔር ቅዱስ፥ ስለ ተባረከው ልጅህ እንባርክሃለን። በማያቋርጠው ምልጃው «አባት ሆይ፥ በእውነትህ ቀድሳቸው» የሚለው ጩኸት ዘወትር ወደ አንተ ስለሚደርስ፥ መልሱም ከክብርህ ዘወትር ስለሚፈስስ እናመሰግንሃለን። ቅዱስ አባት ሆይ! በእውነትህ፥ እውነት በሆነው በእርሱ ራስህን በገለጥህበት ድንቅ መገለጥ ቀድሰን። እኛ በእውነት የተቀደስን እንድንሆን ስለ እኛ ራሱን የሚቀድሰው ቅዱሱ ልጅህ ኢየሱስ መንገድና እውነት ሕይወትም እንዲሆንልን መንፈስ ቅዱስህ በልባችን እንዲሁ ይግዛ። በፊትህ በእርሱ እንዳለን፥ እንድትቀድሰን ለምናቀርበው ጸሎት የምትመልሰው አንዱ ቃልህም—በክርስቶስ ቅዱሳን—እንደ ሆነ እንወቅ። አሜን።

1. እግዚአብሔር የእውነት አምላክ ነው—በመናገር እውነት ብቻ ወይም በትምህርት እውነት ብቻ ሳይሆን—የህላዌ እውነት፥ ማለትም በመለኮታዊ እውነታው ያለ ሕይወት። ክርስቶስም እውነት ነው፤ የዚህ መለኮታዊ ሕይወት ተጨባጭ መገለጫ ነው። ክርስቶስ ንጉሥ የሆነበት የእውነት፥ የመለኮታዊ መንፈሳዊ እውነታዎች መንግሥትም አለ። በክርስቶስ ያለው የዚህ የእግዚአብሔር እውነት ሁሉ ዋና ማንነት መንፈስ ነው። እርሱ የእውነት መንፈስ ነው፤ ከእውነት እንድንሆንና በእርሱ እንድንመላለስ ወደ እርሱ ይመራናል። ከእውነት፥ በእግዚአብሔር ካለው እውነታ፥ ቅድስና ጥልቁ ሥር ነው፤ የእውነት መንፈስ ቅዱስ መንፈስ ነው።

2. በእውነት መቀደሳችን የአብ ሥራ ነው፤ «ቅዱስ አባት ሆይ! በእውነትህ ቀድሰን» የሚለውን ጸሎት ስንተነፍስ በሕፃን መሰል መታመን እጅግ ዝቅ ብለን እንስገድ። እርሱ ያደርገዋል።

3. ይህን በረከት የሚለምነውና የሚያገኘው የወልድ ምልጃ ነው፤ በእርሱ ስፍራችንን እንያዝ፥ መልስ እንደሚገኝ በማረጋገጥም ደስ ይበለን።

4. እኛ በእውነት፥ እውነትም በእኛ እንዲያድር አብ ይህን ሥራ የሚሠራው በእውነት መንፈስ ነው። ወልድ እንደሚጸልይ አብ በእውነት እንዲቀድሰን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በምናደርገው ግንኙነት ለመንፈስ አመራር እጅግ በነጻነትና እጅግ በሙላት ራሳችንን እንስጥ።

5. ከዚህ ከሦስቱ አንዱ ሥራ ብርሃን የተነሣ ቃሉን በዚህ ዓላማ ብቻ እናንብብ፤ በእግዚአብሔር በእውነት እንድንቀደስ።

ጨርሰዋል፦ ቅድስናና እውነት

ቀዳሚ ቀጣይ