ምዕራፍ 28 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ
አባሪ ለ፦ እውነትን መረዳት
እግዚአብሔር አቶ ሙለርን በ1829 በቲንማውዝ ሳለ ያሳየው የጀመራቸው አንዳንድ ነጥቦች፦
1. የእግዚአብሔር ቃል ብቻ በመንፈሳዊ ነገሮች የፍርዳችን መለኪያ መሆኑን፤ ሊተረጐም የሚችለውም በመንፈስ ቅዱስ ብቻ መሆኑን፤ በቀድሞ ዘመን እንደ ነበረውም በእኛም ዘመን እርሱ የሕዝቡ አስተማሪ መሆኑን። ከዚያ ጊዜ በፊት የመንፈስ ቅዱስን ሥራ በተሞክሮ አላስተዋልሁም ነበር። እንዲያውም በተለምዶ ሥላሴ ተብሎ በሚጠራው ውስጥ ካሉት ከተባረኩት አካላት የእያንዳንዳቸውን ሥራ በተሞክሮ አልተረዳሁም ነበር። አብ ዓለም ሳይፈጠር እንደ መረጠን፣ ያ አስደናቂ የቤዛነታችን ዕቅድ ከእርሱ እንደ መነጨ፣ የሚፈጸምበትንም መንገድ ሁሉ እርሱ ራሱ እንደ ወሰነ ከዚያ በፊት ከቅዱሳት መጻሕፍት አላየሁም ነበር። እንዲሁም ወልድ እኛን ለማዳን የሕጉን ፍላጎት፣ ከእርሱም ጋር የእግዚአብሔርን ቅድስና ለማርካት ሕጉን እንደ ፈጸመ፤ ለኃጢአታችን የሚገባውን ቅጣት እንደ ተሸከመ፣ በዚህም የእግዚአብሔርን ፍትሕ እንዳረካ አላየሁም ነበር። ደግሞም በተፈጥሮ ያለንበትን ሁኔታ ሊያስተምረን፣ የአዳኝን አስፈላጊነት ሊያሳየን፣ በክርስቶስ እንድናምን ሊያስችለን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሊተረጕምልን፣ በስብከትም ሊረዳን፣ ወዘተ. የሚችል መንፈስ ቅዱስ ብቻ እንደ ሆነ አላስተዋልሁም ነበር። በእኔ ላይ ታላቅ ውጤት ያመጣው በተለይ ይህን የመጨረሻውን ነጥብ ማስተዋል መጀመሬ ነበር፤ ጌታ የማብራሪያ መጻሕፍትንና ሌሎቹን መጻሕፍት ሁሉ ማለት ይቻላል ወደ ጎን አድርጌ የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ በማንበብና በማጥናት ይህን በተሞክሮ እንድፈትነው አስችሎኛልና። የዚህም ውጤት፣ ለጸሎትና በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ለማሰላሰል ራሴን ለመስጠት በክፍሌ ውስጥ ራሴን በዘጋሁበት በመጀመሪያው ምሽት፣ ቀደም ሲል በብዙ ወራት ውስጥ ከተማርሁት ይልቅ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የበለጠ መማሬ ነበር። ዋናው ልዩነት ግን እንዲህ በማድረጌ ለነፍሴ እውነተኛ ብርታት መቀበሌ ነበር። አሁንም የተማርኋቸውንና ያየኋቸውን ነገሮች በቅዱሳት መጻሕፍት መፈተን ጀመርሁ፤ በፈተናውም የጸኑት መርሆዎች ብቻ በእርግጥ ዋጋ ያላቸው መሆናቸውን አገኘሁ።
2. ከዚህ ጊዜ በፊት የምርጫን፣ የተወሰነ ቤዛነትን፣ እስከ መጨረሻም የሚያጸና ጸጋን ትምህርቶች እጅግ እቃወም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ቲንማውዝ ከደረስሁ ከጥቂት ቀናት በኋላ ምርጫን የዲያብሎስ ትምህርት ብዬ ጠራሁት። ራሴን ወደ ጌታ እንዳመጣሁ አላምንም ነበር፤ ይህ በግልጥ ሐሰት ነበርና፤ ሆኖም እስከ መጨረሻ ልቃወም እችል ነበር ብዬ አምን ነበር። ደግሞም ስለ እግዚአብሔር ሕዝብ መመረጥ ምንም አላውቅም ነበር፤ የእግዚአብሔር ልጅ አንድ ጊዜ ልጅ ከሆነ በኋላ ለዘላለም በደኅንነት እንደሚኖርም አላምንም ነበር። በሥጋዊ አእምሮዬ፦ ለዘላለም የእግዚአብሔር ልጅ መሆኔን አንድ ጊዜ ማረጋገጥ ብችል፣ ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት ወደ ዓለም ተመልሼ፣ ከዚያም ወደ ጌታ ተመልሼ በመጨረሻ ልድን እችላለሁ ብዬ ደጋግሜ ተናግሬ ነበር። አሁን ግን እነዚህን የከበሩ እውነቶች በእግዚአብሔር ቃል እንድመረምር ተደረግሁ። በኃጢአተኞች መመለስ ውስጥ ለራሴ ምንም ክብር እንዳይኖረኝና ራሴን እንደ መሣሪያ ብቻ እንድቆጥር ፈቃደኛ ተደርጌ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚሉትንም ለመቀበል ፈቃደኛ ተደርጌ፣ እነዚህን እውነቶች በተለይ በማሰብ አዲስ ኪዳንን ከመጀመሪያው እያነበብሁ ወደ ቃሉ ሄድሁ። ስለ ምርጫና ስለሚያጸና ጸጋ በግልጥ የሚናገሩት ክፍሎች እነዚህን እውነቶች የሚቃወሙ ከሚመስሉት በአራት እጥፍ ያህል እንደሚበልጡ ሳገኝ እጅግ ተደነቅሁ፤ እነዚያም ጥቂቶቹ እንኳ ብዙም ሳይቆይ መርምሬ ባስተዋልኋቸው ጊዜ ከላይ በተጠቀሱት ትምህርቶች እንድጸና አገለገሉኝ። እነዚህን ትምህርቶች ማመኔ በእኔ ላይ ስላሳደረው ውጤት ለእግዚአብሔር ክብር ይህን ለመናገር ተገድጃለሁ፤ ምንም እንኳ አሁንም እጅግ ደካማ ብሆን፣ ልሆን እንደምችለውና እንደሚገባኝም ለሥጋ ምኞትና ለዓይን አምሮት ለገንዘብም ትዕቢት ፈጽሞ የሞትሁ ባልሆንም፣ በእግዚአብሔር ጸጋ ግን ከዚያ ጊዜ ወዲህ ከእርሱ ጋር ይበልጥ ተቀራርቤ ተመላልሻለሁ። ሕይወቴ እንደ ቀድሞው ተለዋዋጭ አልሆነም፤ ከቀድሞው ይልቅ ለእግዚአብሔር እጅግ አብልጬ ኖሬአለሁ ማለት እችላለሁ። ለዚህም ጌታ በብዙ መጠን በእነዚህ እውነቶች አማካይነት አበርትቶኛል። በፈተና ጊዜ፦ እንዲህ ልበድልን? ለጊዜው በነፍሴ ላይ መከራን አመጣለሁ፣ እግዚአብሔርንም አዋርዳለሁ፤ ለዘላለም የእግዚአብሔር ልጅ ስለ ሆንሁ፣ በከባድ ተግሣጽ ቢሆንም እንኳ፣ እንደ ገና መመለሴ አይቀርም ብዬ ለመናገር ደጋግሜ ተመርቻለሁና። ስለዚህ፣ እላለሁ፣ በክርስቶስ ያለው የእግዚአብሔር የምርጫ ፍቅር (ልገነዘበው በቻልሁበት ጊዜ) ወደ ኃጢአት ከመምራት ይልቅ ቅድስናን የሚያስገኝ መንገድ ብዙ ጊዜ ሆኖልኛል። አደገኛ የሆነው እንዲህ ያሉትን እውነቶች በሐሳብ ብቻ ማወቅ፣ በአእምሮ ውስጥ ሳሉ በልብ ውስጥ አለመኖራቸው ነው።
3. በተወሰነ መጠን የተመራሁበት ሌላው እውነት የጌታን መምጣት የሚመለከት ነበር። እስከዚያ ጊዜ ድረስ በዚህ ነጥብ ላይ የነበረኝ አመለካከት ፈጽሞ ግልጽ ያልሆነና ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር የማይስማማ ነበር። ሌሎች የነገሩኝን በቃሉ ሳልፈትን አምን ነበር። ነገሮች እየተሻሻሉ እንደሚሄዱና ብዙም ሳይቆይ ዓለም ሁሉ እንደሚመለስ አስብ ነበር። አሁን ግን ከጌታችን መመለስ በፊት የዓለምን መመለስ እንድንጠብቅ ቅዱሳት መጻሕፍት ቅንጣት ታህል ማረጋገጫ እንደማይሰጡን በቃሉ አገኘሁ። የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ለቅዱሳን ያልተቋረጠ ደስታን የሚያስገባው የጌታ ኢየሱስ መመለስ እንደ ሆነ፣ እስከዚያም ድረስ ነገሮች ይብዛም ይነስም በሁከት ውስጥ እንደሚሆኑ በቅዱሳት መጻሕፍት አገኘሁ። የሐዋርያት ዘመን ክርስቲያኖች ተስፋ ሞት ሳይሆን የኢየሱስ መመለስ እንደ ነበረ፣ ስለዚህም መገለጡን መጠባበቅ እንደሚገባኝ በቃሉ አገኘሁ። ይህም እውነት በልቤ እጅግ ስለ ገባ፣ ወደ ለንደን ዳግመኛ እመለሳለሁ ብዬ እምብዛም ሳልጠብቅ እጅግ ደክሜ ወደ ዴቨንሻየር ብሄድም፣ ይህን እውነት ባየሁ ጊዜ ወዲያውኑ ሞትን ከመጠባበቅ ተላቅቄ የጌታን መመለስ እንድጠባበቅ ተደረግሁ። ይህን እውነት ካየሁ በኋላ ጌታ ቢያንስ በተወሰነ መጠን በራሴ ልብ ላይ እንድሠራበትና፦ ጌታ በቅርቡ ሊመጣ ስለሚችል፣ ከመመለሱ በፊት ለጌታ ምን ላደርግ እችላለሁ? የሚለውን ከባድ ጥያቄ ለራሴ እንዳቀርብ በቸርነቱ አስቻለኝ።
4. ከእነዚህ እውነቶች በተጨማሪ፣ ከዚያ በፊት ካየሁት የላቀ የመሰጠትን መለኪያ እንዳይ ጌታ ሊመራኝ ወደደ። በዚህ ዓለም ያለኝ እውነተኛ ክብር ምን እንደ ሆነ፣ ይኸውም ከክርስቶስ ጋር መናቅ፣ ድሀና ዝቅተኛ መሆን እንደ ሆነ፣ በተወሰነ መጠን እንዳይ መራኝ። ጌታው ድሀ፣ ዝቅተኛና የተናቀ በነበረበት በዚያ ዓለም ባሪያው ባለጠጋ፣ ታላቅና የተከበረ ለመሆን መሻቱ እንደማይገባው በዚያን ጊዜ በተወሰነ መጠን አየሁ፤ ከዚያ ወዲህ ግን ይበልጥ በሙላት አይቼዋለሁ።