ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈው የቀሌምንጦስ የመጀመሪያ መልእክት
የሁከት አነሣሾችን ሳይሆን እግዚአብሔርን እንታዘዝ

ምዕራፍ 21 · 1 ደቂቃ ንባብ · 1 ደቂቃ ማዳመጥ

የሁከት አነሣሾችን ሳይሆን እግዚአብሔርን እንታዘዝ

ወዳጆች ሆይ፥ ብዙ ቸርነቱ ለሁላችንም ፍርድ እንዳይሆንብን ተጠንቀቁ። ለእርሱ የሚገባ ሆነን ካልተመላለስን፣ በፊቱም መልካምና ደስ የሚያሰኘውን ነገር በአንድ ልብ ካላደረግን [እንዲህ መሆኑ አይቀርም]። [መጽሐፍ] በአንድ ስፍራ፦ «የጌታ መንፈስ የሆድን ስውር ክፍሎች የሚመረምር መብራት ነው» ይላልና። እርሱ ምን ያህል ቅርብ እንደ ሆነ፣ ከምናስባቸውም ሐሳቦችና ከምናመዛዝናቸው ምክንያቶች አንዳቸውም ከእርሱ የተሰወሩ እንዳልሆኑ እናስብ። ስለዚህ ፈቃዱ ከመደበልን ስፍራ ልንለቅ አይገባንም። እግዚአብሔርን [ከማስቀየም] ይልቅ ሰነፎችን፣ የማያስተውሉትንና የታበዩትን፣ በንግግራቸውም ትዕቢት የሚመኩትን ሰዎች ብናስቀይም ይሻላል። ደሙ ስለ እኛ የተሰጠውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንፍራ፤ የሚመሩንን እናክብር፤ በመካከላችን ያሉትን ሽማግሌዎች እናክብር፤ ጐበዞችን በእግዚአብሔር ፍርሃት እናሳድግ፤ ሚስቶቻችንን ወደ መልካም ነገር እንምራ። [በአካሄዳቸው ሁሉ] ውብ የሆነውን የንጽሕና ጠባይ ያሳዩ፤ ቅን የሆነውን የየዋህነት መንፈስ ይግለጡ፤ በአነጋገራቸውም ምላሳቸውን እንደሚገዙ ያስታውቁ፤ ፍቅራቸውንም አንዱን ከሌላው በማስበለጥ ሳይሆን እግዚአብሔርን በቅድስና ለሚፈሩት ሁሉ እኩል ፍቅር በማሳየት ይግለጡ። ልጆቻችሁ እውነተኛውን የክርስቲያን ትምህርት ይካፈሉ፤ ትሕትና በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል ኃይል እንዳለው፣ ንጹሕ ፍቅር በእርሱ ዘንድ ምን ያህል እንደሚችል፣ መፈራቱ ምን ያህል መልካምና ታላቅ እንደ ሆነ፣ በንጹሕ ልብም በእርሱ የሚመላለሱትን ሁሉ እንዴት እንደሚያድን ይማሩ። እርሱ የ[ልብ] ሐሳብና ምኞት መርማሪ ነውና፤ እስትንፋሱ በእኛ ውስጥ ነው፤ በወደደም ጊዜ ይወስዳታል።

ገጽ 1 / 1 · 1 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ