የቄስ ቻርልስ ጂ. ፊኒ ማስታወሻዎች
ስለ አገልጋዮች ትምህርት የተሰጡ አስተያየቶች

ምዕራፍ 7 · 14 ደቂቃ ንባብ · 19 ደቂቃ ማዳመጥ

ስለ አገልጋዮች ትምህርት የተሰጡ አስተያየቶች

በዚህ ጉዳይ ላይ የምናገረውን ሁሉ ወንድሞቼ ከፍተኛውን ጥቅም እንዲሰጡ ከመመኘት ከሚመነጭ ደግና በጎ አሳቢነት ሌላ በሆነ ዓላማ እንዳይተረጕሙብኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ትችቶቻቸውን ሁልጊዜ በበጎ ተቀብያለሁ፤ በጎ ዓላማ እንዳላቸውም አምኜላቸዋለሁ። አሁን ሽማግሌ ሰው ነኝ፤ የአመለካከቶቼና የዘዴዎቼ ብዙ ፍሬዎችም በሕዝብ ዘንድ የታወቁ ናቸው። ታዲያ በዚህ ጉዳይ ለአገልጋዮች በግልጽ መናገሬ ከእኔ የማይጠበቅ ነገር ይሆናልን? ለተቃውሞዎቻቸው መልስ ስሰጥ፥ የጠቅላይ ፍርድ ቤት አንድ ዳኛ በዚሁ ጉዳይ ላይ የነገረኝን አንዳንድ ጊዜ እነግራቸው ነበር። እንዲህ አለ፦ «አገልጋዮች ሕዝቡን ሲያነጋግሩ ጤናማ ማስተዋልን አይጠቀሙም። መደጋገምን ይፈራሉ። ተራው ሕዝብ በሚገባ የማይረዳውን ቋንቋ ይጠቀማሉ። ምሳሌዎቻቸውም ከተለመደው የሕይወት ሥራ የተወሰዱ አይደሉም። እጅግ ከፍ ባለ ዘይቤ ይጽፋሉ፤ ሳይደጋግሙም ያነብባሉ፤ ሕዝቡም አይረዳቸውም። እንግዲህ» አለ፥ «ጠበቆች እንዲህ ያለውን መንገድ ቢከተሉ ራሳቸውንም ጉዳያቸውንም ያጠፉ ነበር።» ቀጥሎም እንዲህ አለ፦ «በጥብቅና ሙያ በነበርሁ ጊዜ፥ ከፊቴ የተከበሩ ሰዎች ያሉበት የሕዝብ ዳኞች ሸንጎ ሲቀመጥ፥ ዋና ዋና ነጥቦቼን በሸንጎው መቀመጫ ውስጥ ባሉት ሰዎች ቍጥር ያህል ጊዜ መደጋገም እንደሚኖርብኝ እንደ ተረጋገጠ ነገር እቈጥረው ነበር። ይህን ካላደረግሁ፥ ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች — የሕጉንና የማስረጃውን ዋና ዋና ነጥቦች — በምሳሌ ካላብራራሁ፥ ካልደጋገምሁና ደጋግሜ ካላገላበጥሁ ጉዳዬን እንደምረታ ተማርሁ። ለሸንጎ ስንናገር» አለ፥ «ዓላማችን ከሸንጎው መቀመጫ ከመውጣታቸው በፊት አእምሮአቸው እንዲረጋ ማድረግ ነው፤ በከፊል ብቻ በሚረዱት ቋንቋ ንግግር ማድረግ አይደለም፤ ከማስተዋላቸው ፈጽሞ በላይ በሆኑ ምሳሌዎች ራሳችንን መልቀቅ አይደለም፤ የንግግር ችሎታችንን አሳይተን ዝም ብለን ማሰናበት አይደለም። የቈረጥነው ብይን ለማግኘት ነው። ስለዚህ እንድንገባቸው ቈርጠናል። ልናሳምናቸው እንፈልጋለን፤ ስለ ሕጉም ጥርጣሬ ካላቸው እንዲረዱት እናደርጋለን፥ በአእምሮአቸውም ውስጥ እንቸነክረዋለን። ባጭሩ፥ ብይን እንደምናገኝ፥ ያውም በዚያው ቅጽበት እንደምናገኘው እንጠብቃለን፤ ስለዚህ ወደ ክፍላቸው ሲገቡ እንደ ተረዱንና በእውነታዎቹና በክርክሮቹ እንደ ተረቱ ይገኛል። እያንዳንዱን ሐሳብ፥ እያንዳንዱን ቃልና እያንዳንዱን ነጥብ በዚህ ሁኔታ ተግተን ወደ ልባቸው በማድረስ በእምነታቸው ውስጥ እንዲተከል ካላደረግን ጉዳያችንን እንደምንረታ የተረጋገጠ ነው። ጭፍን አስተሳሰባቸውን ማሸነፍ አለብን፤ አለማወቃቸውን ማሸነፍ አለብን፤ በደንበኛችን ላይ የሚጻረር ጥቅም ካላቸውም ያንን እንኳ ለማሸነፍ መጣር አለብን። እንግዲህ» አለ፥ «አገልጋዮች ይህን ቢያደርጉ የስብከታቸው ውጤት ካሁኑ በማይነገር ሁኔታ የተለየ ይሆን ነበር። ወደ ጥናት ክፍላቸው ገብተው ስብከት ይጽፋሉ፤ ወደ መድረካቸው ወጥተው ያነብቡታል፤ የሚሰሙትም በጥቂቱ ብቻ ይረዱታል። ከተጠቀሙባቸው ቃላት ብዙዎቹን ወደ ቤታቸው ሄደው መዝገበ ቃላታቸውን እስኪያዩ ድረስ አይረዷቸውም። ሕዝቡን ሊያሳምኑትና በዚያው ቅጽበት ለክርስቶስ የሚደግፍ ብይኑን ሊያገኙ ጠብቀው አይናገሩትም። እንዲህ ያለውን ዓላማ አይሹም። ይልቁንም ያማሩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ለማዘጋጀትና ታላቅ የንግግር ችሎታንና ያጌጠ የቋንቋ አጠቃቀምን ለማሳየት ያለሙ ይመስላሉ።» እርግጥ ነው፥ ይህን ያህል ጊዜ ካለፈ በኋላ ዳኛው የተጠቀመበትን ትክክለኛ ቃል እሰጣለሁ አልልም፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ለእኔ እንደ ተናገረው የንግግሩን ፍሬ ሐሳብ ሰጥቻለሁ።

ወንድሞቼ ብዙ ጊዜ በሻካራነት ቢያስተናግዱኝም፥ በእነርሱ ላይ ትንሽ እንኳ ቅሬታ አድሮብኝ አያውቅም። መልካም እንዳደርግ እጅግ እንደሚጓጉ አውቅ ነበር፤ አመለካከታቸውን ብቀበል እጅግ የበለጠ መልካም፥ እጅግ ያነሰም ክፉ እንደማደርግ በእውነት ያስቡ ነበር። እኔ ግን የተለየ አስተያየት ነበረኝ። የአገልጋዮችን አመለካከትና አንዳንድ ጊዜ ያስተናግዱኝ የነበረበትን ሁኔታ የሚያሳዩ ብዙ እውነታዎችን መጥቀስ እችል ነበር። ለምሳሌ በፊላዴልፊያ እሰብክ በነበርሁ ጊዜ፥ ከኮነቲከት የመጣው ስካርን በመቃወም የሚያስተምረው ዝነኛው ተናጋሪ ዶ/ር — ወደዚያ መጥቶ ስሰብክ ሰማኝ። የመድረኩን ክብር ዝቅ ባደረግሁበት ሁኔታ እጅግ ተቈጣ። ይሁን እንጂ ዋና ንግግሩን ያደረገው በዚያን ጊዜ አብሬው እሠራ ከነበረው ከአቶ ፓተርሰን ጋር ነበር። የአገልጋይነት ትምህርት እስካገኝ ድረስ እንድሰብክ ሊፈቀድልኝ እንደማይገባ፥ ስብከቴን አቁሜ ወደ ፕሪንስተን ሄጄ ሥነ መለኮትን እንድማርና ወንጌል ሊሰበክ የሚገባበትን መንገድ በተሻለ እንድረዳ አጥብቆ ተናገረ።

በዚህ ጉዳይ ላይ የምናገረው ማንኛውም ነገር አመለካከቶቼ ወይም ዘዴዎቼ ፍጹም እንደ ሆኑ አስብ እንደ ነበር የሚል ስሜት በማንም አእምሮ ውስጥ አያሳድር፤ እንዲህ ያለ ሐሳብ አልነበረኝምና። ገና ሕፃን መሆኔን አውቅ ነበር። የከፍተኛ ትምህርት ቤቶችን ዕድል አላገኘሁም ነበር፤ በተለይ በአገልጋዮች ዘንድ፥ ደግሞም — እንደ ፈራሁት — በትልልቅ ስፍራዎች ባለው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሚያሰጡኝ ብቃቶች እንደሚጐድሉኝ ከመጀመሪያው ጀምሮ እጅግ ተገንዝቤ ስለ ነበር፥ ወደ አዳዲስ ሰፈሮችና ወንጌልን ወደማያገኙ ስፍራዎች ከመሄድ የበለጠ ምኞት ወይም ዓላማ ፈጽሞ አልነበረኝም። እንዲያውም በስብከቴ የመጀመሪያ ዓመታት ስብከቴ እጅግ ለተማሩት ወገኖች እንኳ ይህን ያህል የሚያንጽና ተቀባይነት ያለው ሆኖ ሳገኘው ብዙ ጊዜ እኔ ራሴ እደነቅ ነበር። ይህ ከጠበቅሁት በላይ፥ ወንድሞቼ ከጠበቁት እጅግ በላይ፥ እኔ ራሴም ተስፋ ለማድረግ ከደፈርሁት በላይ ነበር። ተሳስቼ ባገኘሁበት ነገር ሁሉ ለመሻሻል ሁልጊዜ እጥር ነበር። ነገር ግን ብዙ በሰበክሁ ቍጥር፥ ስሕተቴ አገልጋይ ወንድሞቼ ባሰቡት አቅጣጫ ነው ብዬ የማስብበት ምክንያት እያነሰ ሄደ።

ልምዴ በበዛ ቍጥር፥ የስብከቴን ዘዴ ውጤቶች ባየሁ ቍጥር፥ ከከፍተኛውም ከዝቅተኛውም፥ ከተማሩትም ካልተማሩትም ከሁሉም ወገኖች ጋር በተነጋገርሁ ቍጥር፥ እግዚአብሔር እንደ መራኝ፥ እንዳስተማረኝ፥ ነፍሳትን ለመማረክ ስለሚሻለው መንገድ ትክክለኛ ግንዛቤ እንደ ሰጠኝ ይበልጥ እየተረጋገጠልኝ ሄደ። እግዚአብሔር አስተማረኝ እላለሁ፤ እንዲህም መሆን እንደ ነበረበት አውቃለሁ፤ እነዚህን ሐሳቦች በእርግጥ ከሰው አላገኘኋቸውምና። ጳውሎስ እንዳለው፥ ወንጌልን የተማርሁት ከሰው ሳይሆን ከራሱ ከክርስቶስ መንፈስ ነው ብዬ በፍጹም እውነት ልናገር እንደምችል ብዙ ጊዜ አስቤአለሁ። በጌታም መንፈስ እጅግ ግልጽና ብርቱ በሆነ መንገድ ስለ ተማርሁት፥ አገልጋይ ወንድሞቼ ይህን ያህል ብዙ ጊዜና ለረጅም ዘመን ደጋግመው ያቀርቡልኝ የነበረው ማንኛውም ክርክር በእኔ ላይ ትንሽ እንኳ ክብደት አልነበረውም።

ይህን የምጠቅሰው እንደ ግዴታ ነው። ትምህርት ቤቶቹ አገልጋዮችን በብዙ መጠን እያበላሿቸው ነው የሚለው እምነት አሁንም በጥልቅ ይሰማኛልና። በዚህ ዘመን ያሉ አገልጋዮች በማናቸውም የሥነ መለኮት ጥያቄ ላይ መረጃ ለማግኘት ታላቅ ምቹ ሁኔታ አላቸው፤ ከሥነ መለኮት፥ ከታሪክና ከመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት አንጻር ሲታዩም በዓለም ታሪክ በማናቸውም ዘመን ከነበሩት ምናልባት እጅግ የበለጠ የተማሩ ናቸው። ሆኖም በዚህ ሁሉ ትምህርታቸው እንዴት እንደሚጠቀሙበት አያውቁም። ከሁሉም በኋላ፥ በብዙ መጠን የሳኦልን የጦር ልብስ እንደ ለበሰው እንደ ዳዊት ናቸው። ሰው በመስበክ ካልሆነ በቀር መስበክን ፈጽሞ ሊማር አይችልም።

ነገር ግን አገልጋዮች ከሁሉም በላይ የሚያስፈልጋቸው አንድ ታላቅ ነገር አለ፤ እርሱም ያልተከፋፈለ ዓይን ነው። ሊያስጠብቁትና ሊንከባከቡት የሚፈልጉት ዝና ካላቸው የሚያደርጉት መልካም ነገር ጥቂት ይሆናል። ከብዙ ዓመታት በፊት የማውቀው አንድ የተወደደ እረኛ ለጤንነቱ ሲል ከቤቱ ወጣ፤ በሌለበትም ጊዜ መድረኩን እንዲሸፍን ከሥነ መለኮት ትምህርት ቤት ገና የወጣ አንድ ወጣት ቀጠረ። ይህ ወጣት የቻለውን ያህል ያማሩ ስብከቶችን ጽፎ ሰበከ። በመጨረሻም የእረኛው ሚስት ደፍራ እንዲህ አለችው፦ «ከሕዝባችን ራስ በላይ ትሰብካለህ። ቋንቋህንም ሆነ ምሳሌዎችህን አይረዱም። ትምህርትህን በብዛት ወደ መድረክ ታመጣለህ።» እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰ፦ «እኔ ወጣት ነኝ። ዘይቤ እያዳበርሁ ነው። መድረክ ይዤ በዙሪያዬ የሠለጠነ ጉባኤ እንዲኖረኝ ራሴን ለማዘጋጀት ዓላማ አድርጌአለሁ። ወደ ሕዝባችሁ ደረጃ ዝቅ ማለት አልችልም። ከፍ ያለ ዘይቤ ማዳበር አለብኝ።» ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሐሳቤንና ዓይኔን በዚህ ሰው ላይ አድርጌአለሁ። እስካሁን መሞቱን አላውቅም፤ ነገር ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከዓመት ወደ ዓመት ባገኘናቸው ታላላቅ መነቃቃቶች ሁሉ መካከል ስሙ ከአንድም መነቃቃት ጋር ተያይዞ አይቼው አላውቅም፤ አመለካከቱ ከሥሩ ካልተለወጠና ሕዝቡን ፈጽሞ ከተለየ አቋምና ፈጽሞ ከተለየ ዓላማ ተነሥቶ ካልተናገረ በቀር፥ እንዲህ ያለውን አያለሁ ብዬም አልጠብቅም።

መጀመሪያ መስበክ በጀመርሁ ጊዜ በመድረኩ ላይ ክብሬን የማልጠብቅ ስለ ነበርሁ፥ እንዲህ ያለ ተራ ቋንቋ ስለ ተጠቀምሁ፥ ሕዝቡን እንዲህ ፊት ለፊት ስለ ተናገርሁ፥ ጌጥን ወይም የመድረኩን ክብር መጠበቅን ፈጽሞ ዓላማ ስላላደረግሁ እጅግ ያፍሩብኝ የነበሩ፥ እንደ እኔው ሽማግሌዎች የሆኑ፥ ገና በሕይወት ያሉ አገልጋዮችን በስም መጥቀስ እችላለሁ።

የተወደዱ ወንድሞች ነበሩ፤ እኔም ሁልጊዜ በእጅግ ደግ ስሜት አስባቸው ነበር፤ በተናገሩትም ነገር በአንድም ጊዜ እንኳ እንደ ተበሳጨሁ ወይም እንደ ተቈጣሁ አላውቅም። ይህ ተቃውሞ እንደሚገጥመኝ፥ በእኔና በሌሎች አገልጋዮች መካከል በአመለካከታችን ይህ ሰፊ ገደል እንዳለ፥ በተግባርም እንደሚኖር ከመጀመሪያው አውቅ ነበር። ከእነርሱ አንዱ እንደ ሆንሁ ወይም በእውነት የወንድማማችነታቸው አባል አድርገው እንደሚቈጥሩኝ የተሰማኝ እምብዛም ነው። ያደግሁት ለጥብቅና ሙያ ተዘጋጅቼ ነበር። በቀጥታ ከጠበቃ ቢሮ ወደ መድረክ መጣሁ፤ ለሕዝብ ዳኞች ሸንጎ እንደምናገረው አድርጌም ለሕዝቡ ተናገርሁ።

በስብከቴ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት፥ እኔ በአገልግሎት ብሳካ ትምህርት ቤቶቹን እንደሚያስነቅፍ፥ ሰዎችም አንድ ሰው ያለ እነርሱ የተሳካለት ሰባኪ ሆኖ ተቀባይነት ማግኘት ከቻለ በገንዘባቸው ሊደግፏቸው ብዙም እንደማይገባ ማሰብ እንደሚጀምሩ በመካከላቸው መስማማት በአገልጋዮች ዘንድ እጅግ የተለመደ እንደ ነበረ ሰማሁ። እኔ ግን በኮሌጆች ወይም በሥነ መለኮት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠውን ትምህርት ለማቃለል ፈጽሞ አስቤ አላውቅም፤ ምንም እንኳ በአንዳንድ ረገድ ተማሪዎቻቸውን በሚያሠለጥኑበት መንገድ እጅግ ተሳስተዋል ብዬ ያሰብሁ፥ አሁንም የማስብ ቢሆንም። ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ጊዜ ለሕዝቡ እንዲናገሩና በአካባቢው ባሉ ገጠሮች ለሚኖረው ሕዝብ ያለ ጽሑፍ የመናገርን ልማድ እንዲለምዱ አያበረታቷቸውም። ሰዎች ያለ ልምምድ በጥናት ብቻ መስበክን ሊማሩ አይችሉም። ተማሪዎቹ ክፍት ወደ ሆኑላቸው ስፍራዎች ሁሉ እየወጡ በልባዊ ንግግር ክርስቶስን ለሕዝቡ ከፍ አድርገው በማቅረብ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ስጦታና ጥሪ እንዲለማመዱ፥ እንዲፈትኑና እንዲያሻሽሉ መበረታታት አለባቸው። መስበክን መማር ያለባቸው በዚህ መንገድ ነው። ከዚህ ይልቅ ተማሪዎቹ ስብከት ብለው የሚጠሩትን እንዲጽፉና ለትችት እንዲያቀርቡ፥ ማለትም ለክፍሉና ለፕሮፌሰሩ እንዲሰብኩ፥ ይኸውም እንዲያነብቡላቸው ይጠየቃሉ። በዚህ መንገድ በስብከት ይጫወታሉ። ማንም ሰው በዚህ ሁኔታ ሊሰብክ አይችልም። እነዚህ ስብከት የሚባሉት ነገሮች በሚደርስባቸው ትችት የተነሣ በእርግጥ ወደ ሥነ ጽሑፋዊ ድርሰቶች ዝቅ ይላሉ። ሕዝቡ ለእንዲህ ያሉ ስብከቶች እንደ ስብከት ምንም አክብሮት የለውም። ይህ ያማሩ ሥነ ጽሑፋዊ ድርሰቶችን ማንበብ ለእነርሱ ስብከት አይደለም። የሥነ ጽሑፍ ጣዕምን ያረካል እንጂ በመንፈስ አያንጽም። የነፍስን ፍላጎት አያሟላም። ነፍሳትን ወደ ክርስቶስ ለመማረክ የተዘጋጀ አይደለም። ተማሪዎቹ ያማረና ከፍ ያለ የአጻጻፍ ዘይቤ እንዲያዳብሩ ይማራሉ። እውነተኛውን የንግግር ኃይል በተመለከተ ግን — ነፍሱ በርዕሱ በእሳት ከተቀጣጠለችና ልቡን ለሚጠባበቅና ልባዊ ለሆነ ሕዝብ ለማፍሰስ ነጻ ከሆነ ከተማረ ሰው በተፈጥሮ የሚፈልቀውን ያንን እንደ ምንጭ የሚፈስስ፥ ልብ የሚነካና የሚያሳምን ንግግር — ከዚያ ምንም የላቸውም።

አስተዋይ አእምሮ ያለው ሰው በዘላለም ሞት አፋፍ ላይ ለተንጠለጠሉ ሕያዋን ነፍሳት በመድረክ ላይ እንዲህ ያሉትን የትምህርትና የንግግር ጥበብ ናሙናዎች ማቅረብ ፍጹም ከቦታው ውጭ እንደ ሆነ ይሰማዋል። ሰዎች በእውነት ልባዊ በሆኑበት በማናቸውም ጉዳይ እንዲህ እንደማያደርጉ ያውቃሉ። ከተማ በእሳት ሲቃጠል የእሳት አደጋ ቡድን አለቃ ለቡድኑ እየጮኸ እንቅስቃሴአቸውን ሲመራ ድርሰት አያነብብላቸውም፤ ወይም ያማረ የንግግር ጥበብ ናሙና አያሳይም። ጉዳዩ አስቸኳይ ነው፤ እያንዳንዱ ቃልም እንዲገባቸው ያስባል። ከእነርሱ ጋር ፈጽሞ ልባዊ ነው፤ እነርሱም በሚጠቀምበት ቋንቋ ላይ መተቸት ከቦታው ውጭ እንደ ሆነ ይሰማቸዋል።

ሰዎች ፈጽሞ ልባዊ በሆኑ ጊዜ ሁልጊዜ እንዲሁ ነው። ቋንቋቸው ከነጥቡ ጋር የሚስማማ፥ ቀጥተኛና ቀላል ነው። ዓረፍተ ነገሮቻቸው አጭሮች፥ አሳማኞችና ብርቱዎች ናቸው። ጥሪው በቀጥታ ለተግባር ይቀርባል፤ ስለዚህም እንዲህ ያሉ ንግግሮች ሁሉ ውጤት ያመጣሉ። ቀድሞ ያልተማሩት የሜቶዲስት ሰባኪዎችና ልባዊዎቹ የባፕቲስት ሰባኪዎች ከእኛ እጅግ ከተማሩት የሥነ መለኮት ሊቃውንትና መምህራን እጅግ የበለጠ ውጤት ያመጡበት ምክንያት ይህ ነው። አሁንም እንዲሁ ያደርጋሉ። የአንድ ተራ ምክር ሰጪ የጋለ ንግግር ብዙ ጊዜ እነዚያ ያማሩ የንግግር ጥበብ ትርኢቶች ሊያደርጉት ከሚችሉት ሁሉ እጅግ በላይ ጉባኤን ያንቀሳቅሳል። ታላላቅ ስብከቶች ሕዝቡ ሰባኪውን እንዲያወድስ ያደርጋሉ። መልካም ስብከት ግን ሕዝቡ አዳኙን እንዲያወድስ ያደርጋል።

የሥነ መለኮት ትምህርት ቤቶቻችን እጅግ የበለጠ ተግባራዊ ቢሆኑ ኖሮ ካሁኑ እጅግ የበለጠ ዋጋ ይኖራቸው ነበር። አንድ የሥነ መለኮት መምህር ያለ ጽሑፍ የመስበክን አስፈላጊነት የሚመለከት ስብከት ሲያነብብ ሰማሁ። በዚያ ጉዳይ ላይ የነበረው አመለካከት ትክክል ነበር፤ ተግባሩ ግን ፈጽሞ ይቃረነው ነበር። ጉዳዩን ያጠናና እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራዊ አመለካከቶች ላይ የደረሰ ይመስል ነበር። ሆኖም ከተማሪዎቹ አንዱ እንኳ እነዚያን አመለካከቶች በተግባር ሲቀበል አይቼ አላውቅም። እንደ ሰባኪ ሕይወቱን እንደ ገና ቢጀምር አሁን ባለው አመለካከቱ መሠረት እንደሚሠራ፥ በዚህ ረገድ ትምህርቱ የተሳሳተ በመሆኑና በዚህም ምክንያት ተግባሩ የተሳሳተ ሆኖ በመቈየቱ እንደሚያዝን እንደሚናገር ሰምቻለሁ።

በኦበርሊን በሚገኘው ትምህርት ቤታችን ተማሪዎቻችን ስብከታቸውን መጻፍ እንዳለባቸው እንዲያስቡ ተመርተዋል — ይህን ያደረግሁት እኔ እንዳልሆንሁ መናገር ይገባኛል፤ እኔም ልነግራቸው የቻልሁትን ሁሉ ብናገርም፥ ከእነርሱ ደፍረው የሚገቡና ራሳቸውን ያለ ጽሑፍ ለመስበክ አሳልፈው የሚሰጡ እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ደጋግሞ እንዲህ ተብለዋል፦ «ፊኒን ለመምሰል አታስቡ። ፊኒዎች መሆን አትችሉም።»

አገልጋዮች ተነሥተው በቻሉት መጠን ለሕዝቡ መናገርንና ለሕዝቡ የመናገርን ልማድ ወዲያውኑ ራሳቸውን ማስለመድን አይወዱም። መስበክ አለባቸው፤ በተለመደው የቃሉ ትርጕም መስበክ ካለባቸውም መጻፍ አለባቸው። ስለዚህ በዚያ አመለካከት መሠረት እኔ ፈጽሞ ሰብኬ አላውቅም። እንዲያውም ሰዎች ብዙ ጊዜ እንዲህ ብለውኛል፦ «ምነው፥ አንተ አትሰብክም እኮ። ለሕዝቡ ታወራለህ እንጂ።» በለንደን አንድ ሰው ከስብሰባዎቻችን ከአንዱ እጅግ በኃጢአት ተወቅሶ ወደ ቤቱ ሄደ። ተጠራጣሪ ነበር፤ ሚስቱም እጅግ ተረብሾ ባየችው ጊዜ፦ «ባሌ ሆይ፥ ፊኒ ሲሰብክ ልትሰማ ሄደህ ነበርን?» አለችው። እርሱም፦ «ወደ ፊኒ ስብሰባ ሄጄ ነበር። እርሱ አይሰብክም፤ ሌሎች ሰዎች የሚሰብኩትን ያብራራል እንጂ» ብሎ መለሰላት። ይህን በፍሬ ሐሳቡ ደጋግሜ ሰምቻለሁ። «ምነው!» ይላሉ፥ «አንተ እንደምትሰብከው ማንም ሊሰብክ ይችላል። ዝም ብለህ ለሕዝቡ ታወራለህ። በእንግዳ መቀበያ ክፍል እንደ ተቀመጠ ሰው ልክ በቤትህ እንዳለህ ሆነህ ትናገራለህ።» ሌሎች ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ «ምነው፥ ስብከት አይመስልም፤ ነገር ግን ፊኒ ለብቻዬ ወስዶኝ ፊት ለፊት የሚያነጋግረኝ ይመስላል።»

አገልጋዮች በአጠቃላይ በፊታቸው ያለው ሕዝብ በተለይ ለእርሱ እንደ ተነገረ አድርጎ የሚረዳውን ከመስበክ ይርቃሉ። ሕዝቡን ፊት ለፊት በማነጋገር፦ «በእነዚህ ኃጢአቶች በደለኞች ናችሁ፤» እንዲሁም «ጌታ ይህን ከእናንተ ይፈልጋል» ከማለት ይልቅ ስለ ሌሎች ሰዎችና ስለ ሌሎች ሰዎች ኃጢአት ይሰብኩላቸዋል። ብዙ ጊዜ ወንጌልን ከመስበክ ይልቅ ስለ ወንጌል ይሰብካሉ። ብዙ ጊዜ ለኃጢአተኞች ከመስበክ ይልቅ ስለ ኃጢአተኞች ይሰብካሉ። በዚያ ባለ በማንም ላይ የተነገረለት ሰው እርሱ ራሱ እንደ ሆነ የሚል ስሜት በማሳደር ረገድ የግል ከመሆን በጥንቃቄ ይርቃሉ። እኔ ግን የተለየ መንገድ መከተል ግዴታዬ እንደ ሆነ አስቤአለሁ፤ ሁልጊዜም የተለየ መንገድ ተከትያለሁ። ብዙ ጊዜ፦ «ስለ ሌላ ሰው የምናገር አይምሰላችሁ፤ የምለው አንተን፥ አንተንም፥ አንተንም ነው» ብያለሁ።

አገልጋዮች መጀመሪያ ላይ ሰዎች ይህን ፈጽሞ እንደማይታገሡ፥ ተነሥተው እንደሚወጡና ዳግመኛ ሊሰሙኝ ፈጽሞ እንደማይመጡ ነገሩኝ። ነገር ግን ይህ ሁሉ ስሕተት ነው። በዚህ እንደ ሌላው ነገር ሁሉ፥ ብዙው የተመካው ነገሩ በተነገረበት መንፈስ ላይ ነው። ሕዝቡ ነገሩ በፍቅር መንፈስ፥ መልካም ሊያደርግላቸው ባለው ጥልቅ ናፍቆት እንደ ተነገረ ካዩ፤ የግል ጥላቻ ገንፍሎ የወጣ ነው ሊሉት ካልቻሉ፥ ይልቁንም በፍቅር እውነትን መናገር እንደ ሆነ ካዩና ሊክዱት ካልቻሉ፤ እያንዳንዳቸውን ለማዳን በቀጥታ ወደ ልባቸው እንደሚደርስ ካዩ፥ ቂም ይዘው የሚቀጥሉ እጅግ ጥቂቶች ናቸው። በዚያን ጊዜ እንደ ተጠቈሙና እንደ ተገሠጹ ቢሰማቸውም፥ ይህ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያምኑበት እምነት ያድርባቸዋል፤ በመጨረሻም በእርግጥ ታላቅ መልካም ነገር ያደርግላቸዋል።

ሰዎች እንደ ተቀየሙ ሳይ ብዙ ጊዜ እንዲህ ብያቸዋለሁ፦ «እንግዲህ ይህን ትቀየማላችሁ፤ ሄዳችሁም ዳግመኛ አንመጣም ትላላችሁ፤ ነገር ግን ትመጣላችሁ። የገዛ ሕሊናችሁ ከእኔ ጋር ነው። የምነግራችሁ እውነት እንደ ሆነ፥ የምነግራችሁም ለራሳችሁ መልካም እንደ ሆነ፥ ቂም ይዛችሁ ልትቀጥሉም እንደማትችሉ ታውቃላችሁ።» ይህም እውነት ሆኖ ሁልጊዜ አግኝቼዋለሁ።

ልምዴ እንደሚያሳየው፥ በግል ተወዳጅነት ረገድ እንኳ ለአገልጋይ «ቅንነት ከሁሉ የሚበልጥ ብልሃት ነው»፤ የማንኛውንም ሕዝብ መተማመን፥ አክብሮትና ፍቅር ይዞ ለመቈየት ካሰበ ለነፍሳቸው ታማኝ መሆን አለበት። ተወዳጅነትን ለማትረፍ ብሎ እንደማይለማመጣቸው፥ ነገር ግን ነፍሳቸውን ለማዳን እየጣረ እንደ ሆነ እንዲያዩ ማድረግ አለበት። ሰዎች ሞኞች አይደሉም። ወደ መድረክ ወጥቶ የሚለሰልሱ ነገሮችን ለሚሰብክ ሰው ጽኑ አክብሮት የላቸውም። በውስጣዊ ነፍሳቸው ይህን ፈጽመው ይንቁታል። ማንም ሰው የክርስቶስ መልእክተኛ ሆኖ ከነፍሳቸው ጋር በታማኝነት ካልተያያዘ በቀር ዘላቂ አክብሮት እንደሚያገኝ፥ በሕዝቡም ዘንድ ለዘለቄታ እንደሚከበር አያስብ።

የወንጌልን ስብከት በተመለከተ የነበረኝን አመለካከት የሚቃወመው ታላቁ ክርክር፥ ስብከቶቼን ብጽፍ ኖሮ ልሰጥ የምችለውን ያህል ትምህርት ለሕዝቡ እንደማልሰጥ፥ ያውም ወደዚያ እንኳ እንደማልቀርብ ነበር። እንደማላጠና ይናገሩ ነበር፤ ስለዚህ በአንድ ስፍራ ጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት ብቻ በምሠራበት ሁኔታ እንደ ወንጌላዊ ብሳካ እንኳ፥ ለእረኛ ያለ ጽሑፍ መስበክ ፈጽሞ እንደማይሆን ይናገሩ ነበር።

እኔ ግን የተጻፉ ስብከቶችን የሚሰብኩ ሰባኪዎች ለሕዝባቸው የሚሰጡት ትምህርት እነርሱ እንደሚያስቡት ያህል እንዳልሆነ ለማመን ከሁሉ የተሻለ ምክንያት አለኝ። ሕዝቡ ስብከቶቻቸውን አያስታውሱም። በብዙ አጋጣሚዎች ሰዎች እንዲህ ብለው ሲያማርሩ ሰምቻለሁ፦ «ከመድረኩ ከምሰማው ምንም ነገር ይዤ ወደ ቤቴ መሄድ አልችልም።» በመቶዎች በሚቈጠሩ አጋጣሚዎችም እንዲህ ብለውኛል፦ «አንተ ስትሰብክ የሰማነውን ሁልጊዜ እናስታውሳለን። ጥቅስህንና ያብራራህበትን መንገድ እናስታውሳለን፤ የተጻፉ ስብከቶችን ግን ልናስታውሳቸው አንችልም።»

አሁን ለብዙ ዓመታት እረኛ ሆኛለሁ — እንዲያውም ከ1832 ጀምሮ፤ ሕዝቡን አላስተማረም የሚል ማጕረምረም ግን ፈጽሞ ሰምቼ አላውቅም። ከመድረክ ትምህርት አንጻር፥ ሕዝቤ የተጻፉ ስብከቶችን የሚሰሙ ሰዎች በተማሩት ያህል በሚገባ አልተማሩም ማለት እውነት ነው ብዬ አላምንም። ሰው ያለ ብዙ ጥናት ወይም ሐሳብ ያለ ጽሑፍ ሊሰብክ እንደሚችል እውነት እንደ ሆነ ሁሉ፥ ብዙ ሳያጠና ስብከቶቹን ሊጽፍ እንደሚችልም እውነት ነው። የሰማኋቸው ብዙ የተጻፉ ስብከቶች ጥልቅና ትክክለኛ ሐሳብን ፈጽሞ አላሳዩም።

ልማዴ ሁልጊዜ ወንጌልንና የሚሻለውን አተገባበሩን ዘወትር ማጥናት ነው። ስብከቶቼን በምጽፍባቸው ሰዓታትና ቀናት ብቻ ራሴን አልወስንም፤ ነገር ግን አእምሮዬ የወንጌልን እውነቶችና እነርሱን የምጠቀምባቸውን የተሻሉ መንገዶች ሁልጊዜ ያሰላስላል። ወደ ሕዝቡ መካከል እሄዳለሁ፤ ፍላጎቶቻቸውንም እረዳለሁ። ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን የአሁኑን ችግራቸውን ያሟላል ብዬ የማስበውን ርዕስ እወስዳለሁ። ለምሳሌ በሰንበት ጠዋት በርዕሱ ላይ በብርቱ አስባለሁ፥ ስለ ርዕሱም ብዙ እጸልያለሁ፤ አእምሮዬንም በእርሱ እሞላለሁ፤ ከዚያም ሄጄ ለሕዝቡ አፈስሰዋለሁ። በተጻፈ ስብከት ላይ ያለው አንድ ታላቅ ችግር ግን፥ ሰው ከጻፈው በኋላ ስለ ርዕሱ ብዙ ማሰብ የማያስፈልገው መሆኑ ነው። ብዙ መጸለይም አያስፈልገውም። ምናልባት ቅዳሜ ማታ ወይም ሰንበት ጠዋት የእጅ ጽሑፉን ያነብበው ይሆናል፤ ነገር ግን አፉ እንዲከፈትና በክርክሮች እንዲሞላ፥ ከሞላ ልብም ለመስበክ እንዲችል በብርቱ መቀባት እንደሚያስፈልገው አይሰማውም። እርሱ ፍጹም ተዝናንቷል። ዓይኑንና ድምፁን ብቻ መጠቀም ይበቃዋል፤ በራሱ መንገድም መስበክ ይችላል። ለዓመታት የተጻፈ ስብከት ሊሆን ይችላል፤ ወይም በዚያው ሳምንት ውስጥ እያንዳንዱን ቃል የጻፈው ስብከት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በሰንበት ቀን ምንም ትኩስነት የለበትም። ከእግዚአብሔር ወደ ልቡ፥ በልቡም በኩል ወደ ሕዝቡ የተላከ የተቀባ መልእክት ሆኖ የግድ አዲስና ትኩስ ሆኖ አይመጣም።

ስብከቶቼን ባለመጻፌ ምክንያት ይበልጥ እንዳጠናሁ አስባለሁ ብዬ እጅግ በጥብቅ ለመናገር ዝግጁ ነኝ። የምሰብክባቸውን ርዕሶች ከሐሳቤ ጋር እንዲዋሐዱ ማድረግ፥ አእምሮዬን በእነርሱ መሙላት፥ ከዚያም ሄጄ ለሕዝቡ መናገር ግድ ሆኖብኝ ነበር። ላብራራቸው የምፈልጋቸውን አርእስት በተቻለ መጠን በአጭሩ፥ ምናልባትም በስብከቱ ጊዜ አንድም ቃሉን በማልጠቀምበት ቋንቋ እጽፋለሁ። የሐሳቦቼን ቅደም ተከተልና ልይዛቸው ያሰብኋቸውን አቋሞች ብቻ እመዘግባለሁ፤ ባጭሩም የምደመድምባቸውን አስተያየቶችና የሚወጡትን ትምህርቶች ንድፍ አወጣለሁ።

ነገር ግን ሰዎች ካልሞከሩት፥ ልባቸውን በእውነትና በመንፈስ ቅዱስ ሞልተው በቻሉት መጠን ለሕዝቡ መናገር ካልጀመሩ በቀር፥ ያለ ጽሑፍ የሚሰብኩ ሰባኪዎች ፈጽሞ አይሆኑም። ንግግሩ የሚወጋ፥ ቀጥተኛ፥ ልባዊና ምክንያታዊ ከሆነ፥ ከሳምንት ወደ ሳምንት ለሕዝቡ የሚደረግ የግማሽ ሰዓት ልባዊ ንግግር፥ የሚጽፉ ሰዎች በሰንበት ለሕዝባቸው ከሚያቀርቧቸው ሁለት በድካም ከተዘጋጁ ስብከቶች ይልቅ በእውነት የበለጠ ያስተምራቸዋል ብዬ አምናለሁ። ሕዝቡ ከእነዚያ በድካም ከተዘጋጁ የተጻፉ ስብከቶች ከሚያገኙት ይልቅ የተነገረውን እጅግ የበለጠ እንደሚያስታውሱ፥ የበለጠ እንደሚሳቡበት፥ ሊያሰላስሉትም ይዘውት እንደሚሄዱ አምናለሁ።

በቅርብ ዓመታት ለመድረክ የምዘጋጅበትን መንገድ ተናግሬአለሁ። መጀመሪያ መስበክ በጀመርሁ ጊዜና በአገልግሎቴ የመጀመሪያዎቹ አሥራ ሁለት ዓመታት ገደማ አንድም ቃል አልጻፍሁም፤ ብዙውን ጊዜም በጸሎት ካገኘሁት በቀር ምንም ዓይነት ዝግጅት ሳላደርግ ለመስበክ እገደድ ነበር። ብዙ ጊዜ በየትኛው ጥቅስ እንደምናገር ወይም የምናገረውን አንድ ቃል እንኳ ሳላውቅ ወደ መድረክ እወጣ ነበር። ጥቅሱን እንዲያመለክቱኝና ርዕሱን በሙሉ ለአእምሮዬ እንዲከፍቱልኝ በሁኔታውና በመንፈስ ቅዱስ እታመን ነበር፤ በእርግጥም በአገልግሎቴ በማናቸውም ክፍል ከዚያ በበለጠ ስኬትና ኃይል ሰብኬ አላውቅም። በመንፈስ ተነሣሥቼ ካልሰበክሁ እንዴት እንደ ሰበክሁ አላውቅም። ርዕሱ እኔን ራሴን በሚያስደንቅ ሁኔታ ለአእምሮዬ መከፈቱ የተለመደ ልምዴ ነበር፤ በአገልግሎት ሕይወቴም ሁሉ እንዲሁ ሆኗል። መናገር ያለብኝን በውስጣዊ ግልጽነት በቀጥታ ማየት የምችል ይመስለኝ ነበር፤ የሐሳቦች፥ የቃላትና የምሳሌዎች ሙሉ ሰልፎች ልናገራቸው በምችልበት ፍጥነት ወደ እኔ ይመጡ ነበር። መጀመሪያ «አጽሞችን» ማዘጋጀት በጀመርሁ ጊዜ፥ ያዘጋጀኋቸው ከሰበክሁ በኋላ እንጂ ከመስበኬ በፊት አልነበረም። ይህን ያደረግሁት አሁን በጠቀስኋቸው ዓይነት አጋጣሚዎች የተሰጠኝን የሐሳብ ንድፍ ለመጠበቅ ነበር። የእግዚአብሔር መንፈስ ስለ አንድ ርዕስ እጅግ ግልጽ የሆነ እይታ በሰጠኝ ጊዜ፥ የሐሳቦቹን ንድፍ ካልጻፍሁ በቀር በሌላ አጋጣሚ ለመጠቀም ልይዘው እንደማልችል አገኘሁ። ነገር ግን ከሁሉም በኋላ፥ አሮጌ አጽሞችን ሳላሻሽላቸውና በመንፈስ ቅዱስ ስለ ርዕሱ አዲስና ትኩስ እይታ ሳይሰጠኝ በስብከት ውስጥ በማናቸውም ጕልህ መጠን ልጠቀምባቸው እንደምችል ራሴን ፈጽሞ አላገኘሁትም። ርዕሶቼን ሁልጊዜ ማለት ይቻላል የማገኘው በጕልበቴ ተንበርክኬ በጸሎት ነው፤ ከመንፈስ ቅዱስ ርዕስ በተቀበልሁ ጊዜ፥ በአእምሮዬ ላይ እጅግ ብርቱ ስሜት በማሳደር እንድንቀጠቀጥ፥ በችግርም ብቻ መጻፍ እንድችል ማድረጉ የተለመደ ልምዴ ሆኖ ቈይቷል። በሥጋዬም በነፍሴም ውስጥ የሚያልፉ የሚመስሉ ርዕሶች እንዲህ ሲሰጡኝ፥ በመንፈስ የቀረበውን እይታ ለመያዝ የሚያስችለኝን አጽም በጥቂት ደቂቃዎች ማዘጋጀት እችላለሁ፤ እንዲህ ያሉ ስብከቶችም ሁልጊዜ በሕዝቡ ላይ በታላቅ ኃይል እንደሚሠሩ አገኛለሁ።

በኦበርሊን ከሰበክኋቸው እጅግ ውጤታማ ስብከቶች አንዳንዶቹን በዚህ ሁኔታ የተቀበልኋቸው ደወሉ ለቤተ ክርስቲያን ከተደወለ በኋላ ነው፤ እጅግ አጭር ከሆነው አጽም በላይ ሳልጽፍ፥ ያውም አንዳንድ ጊዜ በስብከቴ የሸፈንሁትን ግማሽ እንኳ የማይሸፍን አጽም ብቻ ይዤ፥ ሄጄ ከሞላው ልቤ ለማፍሰስ ተገድጄ ነበር።

ይህን የምናገረው በትምክህት ሳይሆን እውነት ስለ ሆነና ምስጋናውን ለራሴ ለማናቸውም ችሎታ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ለመስጠት ነው።

እጅግ ኃይለኛ የተባሉት እነዚያ ስብከቶች ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ የራሴ አእምሮ ወይም የራሴ ልብ ፍሬዎች እንደ ሆኑ ማንም አያስብ። የእኔ አልነበሩም፤ በእኔ ውስጥ ካለው ከመንፈስ ቅዱስ ነበሩ እንጂ።

ይህም ለአገልጋዮች ከተሰጠው ተስፋ ወይም አገልጋዮች ሊጠብቁት መብት ካላቸው የሚበልጥ መነሣሣትን መጠየቅ ነው ብሎ ማንም አይበል። በክርስቶስ ወንጌልን ለመስበክ የተጠሩ አገልጋዮች ሁሉ «ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን» ይሰብኩ ዘንድ በዚህ ዓይነት ትርጕም በመንፈስ ሊነሣሡ እንደሚገባቸውና እንደሚችሉም አምናለሁና። ክርስቶስ፦ «ሂዱና አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ እነሆም፥ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ» ባለ ጊዜ ሌላ ምን ማለቱ ነበር? ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር፦ «ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል፤» «የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል» ባለ ጊዜ ምን ማለቱ ነበር? «በእኔ የሚያምን፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል» ባለ ጊዜ ምን ማለቱ ነበር? «ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ።» የሚሰሟቸው ሁሉ «እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው» የሚል እምነት እንዲያድርባቸው፥ አገልጋዮች ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሊሞሉ ይችላሉ፤ ደግሞም ይገባቸዋል።

ማስታወሻ። — እዚህ ላይ ፊኒ ከተዋቸው በመቶዎች ከሚቈጠሩት «አጽሞች» መካከል በዘፈቀደ የተወሰደውን የአንዱን ትክክለኛ ቅጂ እናቀርባለን። — አዘጋጁ።

ጨርሰዋል፦ ስለ አገልጋዮች ትምህርት የተሰጡ አስተያየቶች

ቀዳሚ ቀጣይ