ምዕራፍ 35 · 18 ደቂቃ ንባብ · 24 ደቂቃ ማዳመጥ
በእንግሊዝና በስኮትላንድ የተደረጉ አገልግሎቶች
በዚህ ጊዜ በለንደን ሳለሁ፥ በስኮትላንድ የሚገኘውን ኤድንበርግን እንድጎበኝ አጥብቄ ተጋበዝሁ፤ በኦገስት አጋማሽ ገደማም ለንደንን ትተን በእንፋሎት መርከብ በጠረፉ በኩል ሽቅብ በጀርመን ባሕር አቋርጠን ወደ ኤድንበርግ ተጓዝን። ወደዚያ እንድሄድ ያጥብቁብኝ የነበሩት የኤድንበርጉ ቄስ ዶ/ር ከርክ ሲሆኑ፥ እርሳቸውም በስኮትላንድ የወንጌላዊ ኅብረት ቤተ ክርስቲያን ተብሎ የሚጠራው የቤተ ክርስቲያን ክፍል አባል ነበሩ። የእነርሱ ዋና የሥነ መለኮት ሊቅ በግላስጎው የሥነ መለኮት ትምህርት ቤትን የሚመሩ አቶ ሞሪሰን የተባሉ ሰው ነበሩ። አቶ ከርክን ቀናተኛ ሰውና የመነቃቃትን ሥራ እጅግ የሚወዱ ሆነው አገኘኋቸው። ይህ የወንጌላዊ ኅብረት፥ ወይም እነርሱ እንደሚሉት ኢ. ዩ. ቤተ ክርስቲያን፥ የተገኘው የመነቃቃት ትምህርቶቼ በዚያች አገር ለመጀመሪያ ጊዜ በታተሙበት ወቅት በስኮትላንድ ከተደረገ የመነቃቃት ጥረት ነበር። ቍጥራቸው ቀላል ያልሆነ የስኮትላንድ አገልጋዮችና ከእነርሱ እጅግ የሚበልጡ ምእመናን በብርቱ ተነሣሥተው ብዙ የተሳኩ የመነቃቃት ጥረቶችን አድርገው ነበር፤ ነገር ግን የስኮትላንድ ፕሪስባይቴሪያኖች ከሚያራምዱት ጽንፈኛ ካልቪናዊ አመለካከት ጋር በሚደረግ ክርክር ኃይላቸውን እጅግ አባክነው ነበር።
በኤድንበርግ ሦስት ወር ቆየሁ፤ በአብዛኛው የምሰብከው በኤድንበርግ ካሉት ትልልቅ የአምልኮ ስፍራዎች አንዱ በሆነው በአቶ ከርክ ቤተ ክርስቲያን ነበር። በዚያ ስፍራ እጅግ አስደሳች የሆነ መነቃቃት ሆነ፤ ብዙ ነፍሳትም ተለወጡ። የቤተ ክርስቲያን አባላት እጅግ ተባረኩ፤ የአቶ ከርክ እጆችም ቀንና ሌሊት በጠያቂዎች መካከል በሚሠሩት ሥራ የተሞሉ ነበሩ። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በጭፍን ጥላቻ ግንብ እንደ ተከበቡ ተረዳሁ። የፕሪስባይቴሪያን አብያተ ክርስቲያናት ይህን የኢ. ዩ. የቤተ ክርስቲያን ቅርንጫፍ አጥብቀው ይቃወሙት ነበር፤ እኔም በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የመሥራት በር እንዳይከፈትልኝ ታጥሬ አገኘሁት።
አቶ ከርክ በዚያን ጊዜ እረኛ ብቻ ሳይሆኑ በግላስጎው በሚገኝ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት መምህርም ነበሩ፤ ከዚህም በተጨማሪ በግላስጎው ይታተም የነበረው «ክሪስቺያን ኒውስ» የተባለው ጋዜጣ አዘጋጅ ነበሩ። በዚያ ጋዜጣ ላይ የሥነ መለኮት አመለካከቴ ከሥነ መለኮት ትምህርት ቤታቸውና ከቤተ ክርስቲያናቸው አመለካከት ጋር አንድ እንደ ሆነ አልፎ አልፎ ይገልጹ ነበር። እኔ ግን በአንዳንድ ነጥቦች ከእነርሱ በእጅጉ እንደምለይ አገኘሁ። እምነትን እንዲያው የአእምሮ ሁኔታ ብቻ አድርገው የሚያዩበትን አመለካከታቸውን ልቀበል አልቻልሁም። የምርጫን ትምህርት ለእኔ ፈጽሞ በማይገባኝ መንገድ አጣመው ያስተባብሉት ነበር፤ በልዩ ልዩ ሌሎች ነጥቦችም እንደማልስማማቸው አገኘሁ። ይሁን እንጂ አቶ ከርክ አመለካከቴን ስሰብከው እንደ ሰሙት ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበሉትና ያም የኢ. ዩ. ቤተ ክርስቲያን አመለካከት እንደ ሆነ አጥብቀው ይናገሩ ነበር። በዚህም አመለካከቴ ከእነርሱ ጋር አንድ እንደ ሆነ አጥብቀው በመናገራቸው፥ ሳያስቡት የሌሎቹን መስበኪያ መድረኮች በሮች በእኔ ላይ ዘጉ፤ ያለ ጥርጥርም አለበለዚያ መጥተው ሊሰሙኝ ይችሉ የነበሩ እጅግ ብዙ ሰዎችን ከስብሰባዎቻችን አራቁ።
ወይዘሮ ፊኒ በዚህ ስፍራ የሠሩት ሥራ እጅግ ተባረከ። የእረኛው ሚስት ወይዘሮ ከርክ እጅግ ቀናተኛ ክርስቲያን ሴት ነበሩ፤ ከባለቤቴ ጋርም በሙሉ ኃይላቸው ተባበሩ። የሴቶች የጸሎት ስብሰባ አቋቋሙ፤ ይህም ስብሰባ እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል፤ ስለ እርሱም በየዓመቱ በ«ክሪስቺያን ኒውስ» ላይ ዘገባዎች ቀርበዋል፤ ወይዘሮ ከርክም የዚያን ስብሰባ አመሠራረትና እድገት የሚተርክ አንድ ትንሽ መጽሐፍ አሳትመዋል። በዚያ የተሰጡት የጸሎት መልሶች እጅግ አስደናቂ ነበሩ። ለልዩ ልዩ ስፍራዎች፥ ሰዎችና ጉዳዮች እንዲጸልዩ ከተለያዩ የስኮትላንድ ክፍሎች ልመናዎች ተልከውላቸዋል። የዚያ ስብሰባ ታሪክ ያልተለመደ ብርታት የሚሰጥ ሆኗል። ከዚያም በተለያዩ የስኮትላንድ ክፍሎች ተመሳሳይ ስብሰባዎች ተነሡ፤ እነዚህም በሃይማኖታዊ መነቃቃቶች ውስጥ የግል ጥረት ከማድረግ አንጻር የስኮትላንድን ሴቶች እጅግ በአዲስ ቦታ ላይ አስቀምጠዋቸዋል።
በኤድንበርግ ሦስት ወር ቆይተን በዚያ የተባረከ የጸጋ ሥራ ካየን በኋላ፥ ወደ አበርዲን እንድንሄድ የቀረበልንን ግብዣ ተቀበልን፤ በኖቬምበርም በስኮትላንድ ሰሜናዊ ጫፍ አቅራቢያ በምትገኘው በዚያች ከተማ ተገኘን። ወደዚያ የጋበዙን ደግሞ የኢ. ዩ. ቤተ ክርስቲያን አገልጋይና የአቶ ከርክ የቅርብ ወዳጅ የሆኑት አቶ ፈርገሰን የተባሉ ሰው ነበሩ። ከፕሪስባይቴሪያንና ከኮንግሪጌሽናል አብያተ ክርስቲያናት ባጋጠማቸው ተቃውሞ እጅግ ተበሳጭተው ነበር፤ እኛ በደረስንበት ጊዜም እንደዚሁ ነበሩ። የእርሳቸው ጉባኤ ከአቶ ከርክ ጉባኤ ይልቅ ይበልጥ በጭፍን ጥላቻ የታጠረ ነበር። ቀናተኛ ክርስቲያን ሰው ነበሩ፤ ነገር ግን እንደ ግንብ በከበባቸው ተቃውሞ እጅግ ተቈጥተው ነበር። መጀመሪያ ላይ ከራሳቸው ሕዝብ በቀር የሚሰማኝ ላገኝ አልቻልሁም፤ እኔም እጅግ ተስፋ ቈረጥሁ፤ ወንድም ፈርገሰንም ራሳቸው እንዲሁ ተስፋ ቈረጡ።
በዚህ ተስፋ መቍረጥ ወቅት፥ በላንካሻየር የቦልተን ኮንግሪጌሽናል አገልጋይ የሆኑት አቶ ዴቪሰን መጥቼ ከእርሳቸው ጋር እንድሠራ እጅግ አጥብቀው የሚለምኑ ደብዳቤ ጻፉልኝ። በአበርዲን የነበረው ሁኔታ እጅግ ተስፋ የሚያስቈርጥ ስለ ነበረ እንደምሄድ ተስፋ ሰጠኋቸው። ነገር ግን በዚያው መካከል በአበርዲን ያለው ፍላጎት እጅግ ጨመረ፤ ሌሎች አገልጋዮችና አብያተ ክርስቲያናትም በዚያ እየሆነ ያለውን ነገር ተጽዕኖ ይሰማቸው ጀመር። የኮንግሪጌሽናሉ አገልጋይ በአንድ ሰንበት በቤተ ክርስቲያናቸው እንድሰብክ ጋበዙኝ፤ እኔም ሰበክሁ። ከፕሪስባይቴሪያን አብያተ ክርስቲያናት በአንዱ የሚያገለግሉ አቶ ብራውን የተባሉ ሰውም እንድሰብክ ጋበዙኝ፤ ነገር ግን በሌላ ጊዜ ልሰብክላቸው ባስብም በዚያን ጊዜ እጆቼ እጅግ የተሞሉ ስለ ነበሩ ግብዣቸውን ልቀበል አልቻልሁም። ከዚህ በፊት መናገር የነበረብኝ ነገር፥ በአቶ ፈርገሰን ጉባኤ ውስጥ ሥራው ጀምሮ እጅግ አስደሳች ወደ ሆነ ሁኔታ እየገባ ነበር። ብዙዎች ተለውጠው ነበር፤ በጉባኤያቸውና በዚያች ከተማ ላይም እጅግ አስደሳች ለውጥ በግልጽ እየመጣ ነበር። ነገር ግን በዚያው መካከል ወደ ቦልተን ለመሄድ ራሴን በጣም አስሬ ስለ ነበር መሄድ እንዳለብኝ አገኘሁ፤ ስለዚህ የገና በዓላት ጥቂት ቀደም ብለን አበርዲንን ትተን ወደ ቦልተን ሄድን።
በአበርዲን ከአቶ ፈርገሰን ጋር ሳለሁ፥ በግላስጎው ከኢ. ዩ. አብያተ ክርስቲያናት በአንዱ ላይ እረኛ ሆኖ የተሾመው ልጃቸው ለጥቂት ጊዜ ከእርሱ ጋር እንድሠራ አጥብቆ ለመነኝ። ይህ ኤድንበርግን ከመልቀቄ በፊትም ተጠይቄበት ነበር። እኔ ግን ከዚያ ቤተ እምነት ጋር ሥራዬን ከዚህ በላይ ለመቀጠል አልፈለግሁም። ይህም ደጋግ ሰዎችና ለእግዚአብሔር ቀናተኛ ሠራተኞች ስላልነበሩ አይደለም፤ ነገር ግን ክርክሮቻቸው ከአካባቢያቸው አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲህ ስላበላሹት፥ የእነርሱን ልዩ አመለካከት ከሚጋሩት በቀር ከሌሎች ሁሉ ጋር ከመተሳሰብና ከመተባበር ያገልሉኝ ነበር። በዚህች አገር ከፕሪስባይቴሪያኖችና ከኮንግሪጌሽናሊስቶች ጋር በነጻነት መሥራትን ለምጄ ነበር፤ በስኮትላንድ ፕሪስባይቴሪያኖችና ኮንግሪጌሽናሊስቶች መካከልም ለመደመጥ እጅግ ተመኘሁ። ነገር ግን ከኢ. ዩ. አብያተ ክርስቲያናት ጋር ስሠራ ራሴን በተሳሳተ ቦታ ላይ አገኘሁት። በ«ክሪስቺያን ኒውስ» የተባለው ነገርና በዚያ ቤተ እምነት ውስጥ እሠራ የነበረ መሆኔ፥ በእውነቱ ባልስማማቸውም፥ በልዩ አመለካከታቸው እንደምስማማቸው እንዲገመት አደረገ።
በዚህ የተሳሳተ ቦታ ላይ ከዚህ በላይ መቆየት ግዴታዬ እንዳልሆነ አሰብሁ። ስለዚህ ወደ ግላስጎው ለመሄድ እንቢ አልሁ። የጋበዘኝን ወንድም ከሰዎች ሁሉ እጅግ ደግ ከሆኑት እንደ አንዱ፥ ቤተ ክርስቲያኑንም እግዚአብሔርን የሚፈራና የሚጸልይ ሕዝብ አድርጌ ብቈጥርም፥ በግላስጎው ሌሎች እግዚአብሔርን የሚፈሩና የሚጸልዩ ሰዎች ነበሩ፤ ቍጥራቸውም በኢ. ዩ. ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊገኙ ከሚችሉት እጅግ የሚበልጥ ነበር። ራሴን በተሳሳተ መንገድ ሊያስረዳ በሚችል ቦታ ላይ በመሆኔ አልተመቸኝም። ከእነዚያ ወንድሞች ጋር እስከ ተዋወቅኋቸው ድረስ ጽኑ ፍቅር ቢኖረኝም፥ ሥራዬን በዚያ ቤተ እምነት ብቻ ብወስነው የራሴን ጠቃሚነት እጅግ እንደምገድብ ተሰማኝ። ስለዚህ አበርዲንን ትተን በባቡር ወደ ቦልተን ሄድን፤ በ1859 የገና ዋዜማም ደረስን።
ቦልተን ሠላሳ ሺህ ገደማ ነዋሪዎች ያሏት፥ ከማንቸስተር ጥቂት ማይሎች ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት። የምትገኘውም በእንግሊዝ ታላቁ የኢንዱስትሪ አውራጃ እምብርት ውስጥ ነው። ማንቸስተርን ማእከል አድርጎ ወደ ሁሉም አቅጣጫ በተዘረጋው በዚያ እጅግ ብዙ ሕዝብ ክልል ውስጥ ትገኛለች። በማንቸስተር ዙሪያ በስድሳ ማይል ክልል ውስጥ ቢያንስ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች እንደሚኖሩ ይገመታል። በዚህ ስፍራ የጌታ ሥራ ወዲያውኑ ጀመረ። በእንግድነት የተቀበሉን አቶ ጄ—— ቢ—— ነበሩ። እርሳቸው የሜቶዲስት ቤተ እምነት አባል ነበሩ፤ እውነተኛ የሆነ እግዚአብሔርን መምሰል ያላቸው፥ በአመለካከታቸውና በስሜታቸውም ከቡድንተኝነት እጅግ የራቁ ሰው ነበሩ። በደረስን በማግሥቱ ምሽት ለሃይማኖታዊ ውይይትና ለጸሎት ጥቂት ወዳጆችን ጋበዙ፤ ከእነርሱም መካከል ለተወሰነ ጊዜ በጠያቂነት የአእምሮ ሁኔታ ውስጥ የቆየች አንዲት ሴት ነበረች። ጥቂት ከተወያየን በኋላ የጸሎት ጊዜ እንዲኖረን ወሰንን። ባለቤቴ ስለ እርሷ በተናገርኋት በዚህች ሴት አጠገብ ተንበረከከች፤ በጸሎቱም ጊዜ ሴትየዋ በጥልቅ እንደ ተነካች አስተዋለች። ከተንበረከክንበት በተነሣን ጊዜ ወይዘሮ ፊኒ እጇን ያዙና መጥቼ እንዳነጋግራት በክፍሉ ማዶ ሆነው በምልክት ጠሩኝ። ሴትየዋ፥ በኋላ እንደ ተረዳሁት፥ ኩዌከር ሆና ያደገች ነበረች፤ ነገር ግን ሜቶዲስት የሆነ ሰው አግብታ ነበር። ስለ ነፍሷ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ስትጨነቅ ቆይታለች፤ ነገር ግን የአሁኑንና የቅጽበቱን መገዛት ጥያቄ ፊት ለፊት ተጋፍጣ አታውቅም ነበር።
የባለቤቴን ጥሪ ተቀብዬ ክፍሉን አቋርጬ ሄጄ አነጋገርኋት። የአእምሮዋ ጭንቀት ጥልቅ እንደ ሆነ ወዲያውኑ አየሁ። ስለዚህ ለግል ውይይት ለጥቂት ጊዜ ልታገኘኝ ትፈቅድ እንደ ሆነ ጠየቅኋት። እርሷም በፈቃደኝነት ተስማማች፤ መተላለፊያውን አቋርጠን ወደ ሌላ ክፍል ገባን፤ ከዚያም ወዲያውኑ ቅጽበታዊ የመገዛትንና ክርስቶስን የመቀበልን ጥያቄ ፊት ለፊት አቀረብሁላት። በዚያኑ ጊዜና በዚያኑ ስፍራ ራሷንና ሌላውን ነገር ሁሉ ክዳ ልቧን ለክርስቶስ ትሰጥ እንደ ሆነ ጠየቅኋት። እርሷም፦ «አንድ ቀን ማድረጌ አይቀርም፤ ስለዚህ አሁኑኑ ባደርገው ይሻላል» ብላ መለሰች። ወዲያውኑ ተንበረከክን፤ የሰው ዕውቀት እስከሚደርስበት ድረስም በእውነት ለእግዚአብሔር ተገዛች። ከተገዛች በኋላ ወደ እንግዳ መቀበያው ክፍል ተመለስን፤ በእርሷና በባሏ መካከል የሆነው ትዕይንትም እጅግ ልብ የሚነካ ነበር። ወደ ክፍሉ እንደ ገባች በፊቷ ላይ የተገለጠውን ያን የመሰለ ለውጥ አየ፤ ሁለቱም ሳያስቡት እርስ በርሳቸው የተቃቀፉ መሰሉ፤ በጌታም ፊት ተንበረከኩ።
ገና ከመቀመጣችን የአቶ ቢ—— ልጅ ወደ እንግዳ መቀበያው ክፍል ገብቶ ከአገልጋዮቹ አንዷ በጥልቅ እንደ ተነካች አስታወቀ። በጣም በአጭር ጊዜም እርሷ ደግሞ ለክርስቶስ እንደ ተገዛች ማስረጃ አሳየች። ከዚያም ሌላዋ በማእድ ቤት እያለቀሰች እንደ ሆነች ሰማሁ፤ ወዲያውኑም ወደ እርሷ ሄድሁ፤ ከጥቂት ውይይትና ትምህርት በኋላ እርሷም ልቧን ለእግዚአብሔር የሰጠች መሰለች። በዚህ ዓይነት ሥራው ጀመረ። ወይዘሮ ቢ—— ራሳቸው ለዓመታት በጥርጣሬና በተስፋ መቍረጥ የአእምሮ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ፤ እርሳቸውም ደግሞ ቀልጠው ወዲያውኑ ማለት ይቻላል ወደ ሌላ የአእምሮ ሁኔታ የገቡ መሰሉ። ጌታ እያደረገ ያለው ነገር ወሬ ብዙም ሳይቆይ በየቦታው ተሰራጨ፤ ሰዎችም ለውይይት በየቀኑ፥ በየሰዓቱም ማለት ይቻላል ይመጡ ነበር። የጃንዋሪ የመጀመሪያው ሳምንት የጸሎት ሳምንት ሆኖ እንዲከበር ተወስኖ ነበር፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በየዓመቱ እንዲሁ ሲከበር ቆይቷል፤ የተለያዩ ቤተ እምነቶችም በሳምንቱ ውስጥ የኅብረት ስብሰባዎችን ለማድረግ ተስማሙ።
የመጀመሪያው ስብሰባችን የተደረገው ወደ ቦልተን እንድመጣ ልከው ባስጠሩኝ በአቶ ዴቪሰን የጸሎት ቤት ነበር። እርሳቸው ኢንዲፔንደንት ነበሩ፤ ይህም እኛ በዚህች አገር ኮንግሪጌሽናሊስት የምንለው ነው። በመጀመሪያው ምሽት የጸሎት ቤታቸው ሞላ። ስብሰባውን የከፈቱት አንድ የሜቶዲስት አገልጋይ ነበሩ፤ እርሳቸውም በታላቅ ትጋትና በነጻነት ጸለዩ፤ ይህም የእግዚአብሔር መንፈስ በጉባኤው ላይ እንዳለና ብርቱ ስብሰባ እንደሚኖረን በግልጽ አመለከተኝ። ከእርሳቸው ቀጥዬ አንዳንድ ነገሮችን እንድናገር ተጋበዝሁ። እንዲሁም አደረግሁ፤ ስለ ጸሎት ጉዳይ በመናገር ጥቂት ጊዜ ወሰድሁ። ማሰናከያዎቹን ከመንገድ አስወግደው የእምነት ጸሎትን ቢያቀርቡ ጸሎት ወዲያውኑ እንደሚመለስ እንደ እውነታ በልባቸው ላይ ለማሳደር ሞከርሁ። ቃሉ በክርስቲያኖች ልብ ውስጥ የሚያንቀጠቅጥ ይመስል ነበር። በእርግጥም ከጸሎት ርዕስ የበለጠ ብርቱና ጠቃሚ ውጤት ያስገኘ በሚመስል በማናቸውም ርዕስ ላይ ጉባኤዎችን የተናገርሁበት ጊዜ እምብዛም ነው። በየትም ቦታ እንዲሁ ሆኖ አገኘዋለሁ። የሚጸልዩ ሰዎች ለበረከት እግዚአብሔርን አጥብቀው እንዲይዙ በእርሱ ወዲያውኑ ይነሣሣሉ። በዚህም ስፍራ እንዲሁ ሆኑ። ያ ብርቱ ስብሰባ ነበር።
በዚያ ሳምንት ሁሉ የጸሎት መንፈስ እየጨመረ የሄደ ይመስል ነበር፤ ስብሰባዎቻችንም የበለጠና የበለጠ ኃይል ነበራቸው። ስብሰባዎቻችን በጀመሩ በሦስተኛው ወይም በአራተኛው ቀን ገደማ፥ እንደማስበው፥ በቦልተን ሌላው የኮንግሪጌሽናል አገልጋይ የሆኑት አቶ ቤስት የተባሉ ሰው በጸሎት ቤታቸው ስብሰባውን የማድረግ ተራ ደረሳቸው። በዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ ጠያቂዎችን ጠራሁ። ወደዚያ ነጥብ ለማድረስ በተዘጋጀ መንፈስ ጉባኤውን ለተወሰነ ጊዜ ካነጋገርሁ በኋላ ጠያቂዎችን ጠራሁ፤ የቤተ ክርስቲያኑ ተጓዳኝ ክፍልም በእነርሱ ተጨናነቀ። ከእነርሱ ጋር ልብ የሚነካ ስብሰባ አደረግን፤ ከእነርሱም ብዙዎቹ ለእግዚአብሔር እንደ ተገዙ ተስፋ አደርጋለሁ።
በከተማዋ ውስጥ ከጸሎት ቤቶቹ ከማናቸውም የበለጠ ብዙ ሰዎችን የሚያስተናግድ የአልኮል መጠጥ ተቃዋሚዎች ማኅበር አዳራሽ ነበር። ከዚህ የጸሎት ሳምንት በኋላ ወንድሞች አዳራሹን ለስብከት አገኙት፤ እኔም በዚያ በሰንበት ሁለት ጊዜ፥ በሳምንቱ ውስጥም አራት ምሽቶች መስበክ ጀመርሁ። ብዙም ሳይቆይ ፍላጎቱ እጅግ አጠቃላይ ሆነ። አዳራሹ በየምሽቱ ይጨናነቅ ነበር፤ ስለዚህም አንድም ሰው እንኳ ወደ በሩ ውስጥ ሊገባ አይችልም ነበር። የእግዚአብሔር መንፈስ በብዛት ፈሰሰ።
ከዚያም ወንድሞች ከተማዋን ሁሉ እንዲያዳርሱ፥ ሁለት ሁለት ሆነው እንዲሄዱና እያንዳንዱን ቤት እንዲጎበኙ፥ ከተፈቀደላቸውም በከተማዋ ባለ እያንዳንዱ ቤት እንዲጸልዩ መከርኋቸው። ይህን ሥራ ለመፈጸም ወዲያውኑ በድፍረት ተሰለፉ። እጅግ ብዙ ማስታወቂያዎችን፥ በራሪ ጽሑፎችን፥ ለግድግዳ የሚለጠፉ ማስታወቂያዎችንና ሁሉንም ዓይነት የግብዣ ጽሑፎች አሳትመው ቤት ለቤት የማዳረሱን ሥራ ጀመሩ። ኮንግሪጌሽናሊስቶቹና ሜቶዲስቶቹ ሥራውን በታላቅ ትጋት ያዙት።
ሜቶዲስቶች በቦልተን እጅግ ጠንካሮች ናቸው፤ ከዌስሊ ዘመን ጀምሮም ሁልጊዜ እንዲሁ ነበሩ። ቦልተን ዌስሊ ከሚወዳቸው የሥራ መስኮች አንዱ ነበረ፤ በዚያም ሁልጊዜ ብቁ አገልጋዮችና ጠንካራ አብያተ ክርስቲያናት ነበሯቸው። በዚያ ያላቸው ተጽዕኖ ከሌሎች ሃይማኖታዊ ቤተ እምነቶች ሁሉ እጅግ የላቀ ነበር። በመካከላቸውም እጅግ ግሩምና ቀናተኛ የክርስቶስ ሠራተኞች የሆኑ አገልጋዮችንም ምእመናንንም አገኘሁ። ነገር ግን ኮንግሪጌሽናሊስቶቹም በታላቅ መንፈስና ብርታት ወደ ሥራው ገቡ፤ ቢያንስ እኔ በዚያ እስከ ቆየሁበት ጊዜ ድረስ ቡድንተኝነት ሁሉ የተቀበረ ይመስል ነበር። ከተማዋን በሚገባ አዳረሷት፤ ቤት ለቤት የሚያዳርሱትም ሰዎች ዘገባዎቻቸውን ለማቅረብና ሥራውን ወደ ፊት ለመግፋት ተጨማሪ ዝግጅቶችን ለማሰብ በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ይሰበሰቡ ነበር። አንድ ሜቶዲስትና አንድ ኮንግሪጌሽናሊስት እጅ ለእጅ ተያይዘው፥ በልብም አንድ ሆነው፥ በራሪ ጽሑፎችን ይዘው ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ፥ በተፈቀደላቸውም ቦታ ሁሉ በእያንዳንዱ ቤት ሲጸልዩ፥ ሰዎችንም ከሚመጣው ቍጣ እንዲሸሹ ሲያስጠነቅቁና ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ ሲያጥብቁባቸው ማየት እጅግ የተለመደ ነበር።
እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሥራው ባልተለወጡት ሰዎች መካከል በፍጥነት መስፋፋቱ የታወቀ ነው። የሁሉም ዓይነት ሰዎች፥ ከፍተኞችና ዝቅተኞች፥ ሀብታሞችና ድሆች፥ ወንዶችና ሴቶች ፍላጎት አደረባቸው። በሰበክሁበት ምሽት ሁሉ ጠያቂዎችን ወደ ፊት መጥተው ከመድረኩ ፊት ለፊት ባሉት መቀመጫዎች እንዲቀመጡ መጥራት ልማዴ ነበር። እጅግ ብዙዎች በቻሉት መጠን የቤቱን ጓዳና ጐድጓዳ ሁሉ በሞሉት ጥቅጥቅ ያሉ ሕዝቦች መካከል እየተጋፉ ወደ ፊት ይመጡ ነበር። አዳራሹ በምድር ቤቱ ሰፊ ብቻ ሳይሆን፥ ሁልጊዜ የሚጨናነቅ ላይኛው ሰገነትም ነበረው። ጠያቂዎቹ ወደ ፊት ከመጡ በኋላ የጸሎት ስብሰባ አደረግን፤ ጠያቂዎቹ በጌታ ፊት ተንበርክከው ሳሉ ብዙ ጸሎቶች በተከታታይ ይቀርቡ ነበር።
የሜቶዲስት ወንድሞች በሥራው እጅግ ተጠምደው ነበር፤ ኃጢአተኞች ወደ ፊት በመጡ ጊዜም ለተወሰነ ጊዜ በጸሎታቸው እጅግ ጩኸትና ስሜት የተሞሉ ነበሩ። ከእኔ እንዲርቁና መንፈስን እንዲያሳዝኑ እንዳላደርጋቸው ብዬ ለተወሰነ ጊዜ ስለዚህ ነገር ምንም አልተናገርሁም። ስሜቱ በበዛ መጠን ሥራው ይበልጥ በፍጥነት ወደ ፊት እንደሚሄድ ያስቡ እንደ ነበር አየሁ። ስለዚህ አግዳሚ ወንበሮቹን ይደበድቡ፥ እጅግ ጮኸው ይጸልዩ፥ አንዳንድ ጊዜም ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች በአንድ ጊዜ ይጸልዩ ነበር። ይህ ጠያቂዎቹን እንደሚያደናግርና በእውነት እንዳይለወጡ እንደሚከለክላቸው ተረድቼ ነበር፤ የጠያቂዎቹም ቍጥር ብዙና ሁልጊዜም እየጨመረ የሚሄድ ቢሆንም፥ የጠያቂዎቹ ቍጥር እጅግ ባነሰበት ስፍራ እንኳ ማየት በለመድሁት ፍጥነት የተለወጡት ሰዎች ቍጥር አልበዛም ነበር።
የሜቶዲስት ወንድሞች እኔን፥ እኔም እነርሱን እስክናውቅ ድረስ ነገሮች ለሁለት ወይም ለሦስት ሳምንታት እንዲሁ እንዲያልፉ ከተውሁ በኋላ፥ አንድ ምሽት ጠያቂዎቹን ወደ ፊት ስጠራ የተለየ መንገድ እንድንከተል ሐሳብ አቀረብሁ። ይህን ያህል ጩኸት በሚኖርበት ጊዜ ከሚያገኙት የበለጠ ለማሰብ ዕድል ጠያቂዎቹ እንደሚያስፈልጋቸው፥ ትምህርት እንደሚያስፈልጋቸውና በጸሎት በአንድ ድምፅ መመራት እንደሚያስፈልጋቸው፥ እንዲያደምጡና በማስተዋል እንዲለወጡ የምንጠብቅ ከሆነም ምንም ዓይነት ግርግር ወይም ወደ ግርግር የሚጠጋ ማናቸውም ነገር መኖር እንደሌለበት ነገርኋቸው። በዚህ ረገድ ምክሬን ለአጭር ጊዜ ለመከተል ሞክረው ውጤቱ ምን እንደሚሆን ያዩ እንደ ሆነ ጠየቅኋቸው። እንዲሁም አደረጉ፤ መጀመሪያ ላይ ለመጸለይ ሲሞክሩ ጥቂት እንደ ታሰሩና ብርቱ ስብሰባን የሚያስገኘው ምን እንደ ሆነ ከነበራቸው አስተሳሰብ ጋር ስለ ተቃረነባቸው ጥቂት ተስፋ እንደ ቈረጡ አየሁ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆዩ ከዚህ ያገገሙ መሰሉ፤ ምክንያቱም በጸሎት ስብሰባዎቻችን ውስጥ የሚታየው ስሜት ቢቀንስም፥ ከምሽት ወደ ምሽት የሚለወጡት ሰዎች ግን እጅግ እንደ በዙ እንዳመኑ አስባለሁ።
የዚህ ሥራ ዝና በየአቅጣጫው ተሰማ፤ ብዙም ሳይቆይ ሰዎች ስብሰባዎቻችንን ለመካፈል ከማንቸስተር ወደ ቦልተን በብዛት መምጣት ጀመሩ፤ ይህም ሁልጊዜ እንደሚሆነው በዚያች ከተማ ከፍተኛ መነሣሣትን ፈጠረ፤ በተቻለኝ ፍጥነትም ወደዚያ እንድመጣ ፍላጎት አሳደረ። ይሁን እንጂ በቦልተን ሦስት ወር ያህል፥ ምናልባትም ከዚያ በላይ የቆየሁ ይመስለኛል። ሥራው እጅግ ብርቱ ከመሆኑ የተነሣ በሁሉም መደቦችና በሁሉም ዓይነት ሰዎች መካከል ሰብሮ ገባ።
ወንድም ቢ—— በቦልተን ሰፊ የጥጥ ፋብሪካ ነበራቸው፤ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ሠራተኞችንም ቀጥረው ያሠሩ ነበር። ከእርሳቸው ጋር አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ወደ ፋብሪካቸው ወርጄ ከሠራተኞቻቸው ጋር ስብሰባዎችን አደረግሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ በሄድን ዕለት ብርቱ ስብሰባ ሆነ። እጅግ እስክደክም ድረስ ከእነርሱ ጋር ቆየሁ፤ ከዚያም ወንድም ቢ—— ከእነርሱ ጋር እንዲጸልዩና እንዲያስተምሯቸው ትቼአቸው ወደ ቤት ተመለስሁ። ወደ ቤት በመጡ ጊዜ በዚያች ምሽት ከገዛ ሠራተኞቻቸው መካከል ከስድሳ የማያንሱ ሰዎች በግልጽ የተለወጡ እንደሚመስሉ ነገሩኝ። እነዚህ ስብሰባዎች ሠራተኞቻቸው ሁሉ ማለት ይቻላል በክርስቶስ ተስፋ እንዳገኙ እስኪመሰክሩ ድረስ ቀጠሉ።
በዚያን ጊዜ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ብዙ የኃጢአት ወቀሳና የመለወጥ ሁኔታዎች ነበሩ። እኔ ራሴ ረጋ ብዬ፥ ሕዝቡም ትምህርትን የሚያዳምጡበትንና በሚያደርጉት ነገር ሁሉ በማስተዋል የሚሠሩበትን ሁኔታ ይዘው እንዲቆዩ ብጥርም፥ በአንዳንድ ሁኔታዎች ግን ሰዎች ለጥቂት ቀናት ለአእምሮአቸው ጤናማ አሠራር ከሚገባው በላይ ተነሣሥተው ነበር፤ ሆኖም እውነተኛ የአእምሮ መታወክ የደረሰበትን አንድም ሰው አላስታውስም።
አንድ ምሽት መድረኩ ላይ ቆሜ እየሰበክሁ ሳለሁ፥ በጉባኤው ውስጥ የነበረ አንድ ሰው ተነሥቶ ሰዎችን እየገፋ ወደ መድረኩ ወጣና ለጉባኤው፦ «ዝርፊያ ፈጽሜአለሁ» አለ። እየሰበክሁ ሳለሁ አቋርጦኝ መናዘዝ ጀመረ። ከልክ በላይ እንደ ተነሣሣ አየሁ፤ በመድረኩ ላይ ተቀምጠው የነበሩት ወንድም ዴቪሰንም ወደ እርሱ ቀርበው በጆሮው አንሾካሾኩለት፤ ወደ አንድ የጎን ክፍልም ወስደው አነጋገሩት። በግዞት ሊላክበት የሚችል ወንጀል እንደ ፈጸመ ደረሱበት። ምክር ሰጡት፤ በዚያች ምሽት ስለ ጉዳዩ ከዚያ በላይ አልሰማሁም። በኋላ ግን ሁኔታው በይበልጥ ታወቀኝ። ይሁን እንጂ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሰውዬው ተስፋ አገኘ።
አንድ ምሽት ስለ መናዘዝና ስለ ካሣ መመለስ ሰበክሁ፤ ይህም በነጋዴዎች መካከል እጅግ ታላቅ እንቅስቃሴ ፈጠረ። አንድ ሰው በማግሥቱ፥ ባልንጀራውን እንደ ራሱ በመውደድ መርሕ እንዳልሠራ ባሰበበት አንድ ጉዳይ፥ ሄዶ ካሣ እንደ መለሰ ነገረኝ፤ መጠኑም አንድ ሺህ አምስት መቶ ፓውንድ እንደ ነበረ አስባለሁ። በእንዲህ ያለ ሁኔታ የሰዎች ሕሊና እጅግ ስሱ ይሆናል። አሁን የጠቀስሁት ይህ ሰው አንድ የሚወደው ወዳጁ ሞቶ ንብረቱን እንዲያስተዳድር ትቶለት እንደ ነበረ ነገረኝ። እርሱም ይህን ፈጽሞ ስለ ድካሙና ስላወጣው ወጪ ሕጉ የሰጠውን ብቻ ተቀብሎ ነበር። ነገር ግን ያን ስብከት ሲሰማ፥ ቤተሰቡ የሕግ ክፍያውን ሊፈቅዱለት ከሚችሉት ይልቅ፥ እርሱ እንደ ወዳጅና እንደ ክርስቲያን ወንድም ምንም ሳያስከፍል ያን ንብረት ቢያስተዳድር እንደሚቀልለት ወደ አእምሮው መጣ። በእርሱ ላይ የነበረው የእግዚአብሔር መንፈስ ይህን እጅግ አጥብቆ እንዲሰማው ስላደረገው ወዲያውኑ ሄዶ ገንዘቡን መለሰ።
በኒው ዮርክ ግዛት በምትገኘው በሮቼስተር የተፈጸመ፥ ልጠቅሰው የረሳሁት ነገር ግን በዚህ ስፍራ ቢጠቀስ የሚስማማ፥ ተመሳሳይ ዓይነት አንድ ጉዳይ ነበር። እጅግ ስሱ የሆነ ሕሊና አንድን ሰው ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን በመውደድና ሰዎች ሊያደርጉልን የምንወደውን ለእነርሱ በማድረግ መርሕ ስለ መሥራት ጉዳይ አጥብቆ እንዲያይና እንዲሰማው አደረገው። እኔ በሠራሁባቸው በሮቼስተር ከነበሩት መነቃቃቶች በአንዱ ብዙ ሀብት የነበረው አንድ ሰው ተለወጠ፤ እርሱም ከሮቼስተር ብዙ በማይርቅ መንደር ለምትኖር አንዲት ባልቴት ሴት አንድ ጉዳይ ሲያስፈጽምላት ቆይቶ ነበር። ጉዳዩም የአንዳንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ዝውውር ሲሆን ስለ አገልግሎቱ አንድ ሺህ አምስት መቶ ወይም አንድ ሺህ ስድስት መቶ ዶላር ያህል ተከፍሎት ነበር። እንደ ተለወጠ ወዲያውኑ ይህ ጉዳይ ትዝ አለው፤ ቢያስብበትም፥ እርሱ ቢሞት ሌላ ሰው ለባልቴት ሚስቱና አባት ለሌላቸው ልጆቹ እንዲያደርግላቸው የሚወደውን ያህል ለዚያች ባልቴትና አባት ለሌላቸው ለእነዚያ ልጆች እንዳላደረገ ተሰማው። ስለዚህ ሊያያት ሄደ፤ ጉዳዩንም በአእምሮው እንደ ታየው አድርጎ አስረዳት። እርስዋም ጉዳዩን ፈጽሞ እንደዚያ እንዳላየችው መለሰችለት፤ የምትጠይቀውንና የምትጠብቀውን ሁሉ እንድታገኝ አድርጎ ጉዳይዋን ስላስፈጸመላት ራስዋን ለእርሱ እጅግ ባለ ውለታ አድርጋ ትቆጥር እንደ ነበረ ነገረችው። ስለዚህ ሊመልስላት ያቀረበውን ገንዘብ አልቀበልም አለች።
ጥቂት ካሰበበት በኋላ ልቡ እንዳላረፈ ነገራት፤ ከጎረቤቶችዋም እጅግ የሚታመኑትን አንዳንዶቹን እንድትጠራና ጥያቄውን በፊታቸው እንዲያቀርቡ ፈለገ። እርስዋም እንዲሁ አደረገች፤ አንዳንድ ክርስቲያን ወዳጆችን፥ የንግድ ሰዎችን ጠራች፤ ጉዳዩንም በሙሉ በፊታቸው አቀረቡ። እነርሱም ጉዳዩ የንግድ ግብይት እንደ ሆነ፥ እርሱም ጉዳዩን ቤተሰቡ በሚቀበሉትና ለጥቅማቸው በሆነ መንገድ እንዳስፈጸመ ግልጽ መሆኑን ተናገሩ፤ ገንዘቡን የሚመልስበት ምንም ምክንያት እንዳላዩም ገለጹ። የሚሉትን ሰማ፤ ነገር ግን ከከተማይቱ ከመውጣቱ በፊት ዳግመኛ ወደ ሴትዮዋ ሄዶ፦ «አእምሮዬ አላረፈም። እኔ ብሞትና ሚስቴን ባልቴት፥ ልጆቼንም አባት የሌላቸው አድርጌ ብተዋቸው፥ አንድ ወዳጄም እንዲህ ያለውን ጉዳይ ቢያስፈጽምላቸው፥ ለባልቴትና አባት ለሌላቸው ልጆች የተደረገ ስለ ሆነ ያለ ክፍያ ሊያደርገው እንደሚገባ ይሰማኛል» አላት። ደግሞም፦ «ከዚህ ሌላ ሊታየኝ አይችልም» አለ። ከዚያም ገንዘቡን በጠረጴዛዋ ላይ አኑሮ ሄደ።
ሰዎች ልባቸው ለእርሱ ተጽዕኖ ክፍት በሆነ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በአእምሮአቸው የሚሠራበትን መንገድ የሚያሳይ ሌላ ጉዳይ አሁን ትዝ አለኝ። በአንድ ወቅት ከታላላቅ ከተሞች በአንዲቱ ስሰብክ፥ በንግድ ውስጥ ስላሉት የማታለል ሥራዎችና ሰዎች ሌሎችን አታልለው ለመጠቀም ስለሚያወጡአቸው ዕቅዶች፥ ወርቃማውን ሕግ በመጣሳቸውም ራሳቸውን እንዴት እንደሚያጸድቁ አብራርቼ እናገር ነበር። ስብከቴን ሳልጨርስ፥ በአዳራሹ መካከል አንድ ሰው ተነሥቶ ጥያቄ ማቅረብ ይችል እንደ ሆነ ጠየቀኝ። ከዚያም አንድ ሁኔታ በምሳሌነት አቀረበ፤ ካስረዳውም በኋላ ያ ሁኔታ እኔ ባቀረብሁት ሕግ ሥር ይወድቅ እንደ ሆነ ጠየቀኝ። እኔም፦ «አዎን፥ በግልጽ የሚወድቅ ይመስለኛል» አልሁት። እርሱም ተቀመጠ፤ ከዚያ በላይም ምንም አልተናገረም፤ ነገር ግን በኋላ ሄዶ እስከ ሠላሳ ሺህ ዶላር የሚደርስ ካሣ እንደ መለሰ ሰማሁ። ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ብርቱና መርማሪ ተጽዕኖ ሥር በተመሳሳይ መንገድ እንዲሠሩ የተመሩባቸውን እጅግ ብዙ ሁኔታዎች ልተርክ እችላለሁ።
ነገር ግን ከወጣሁበት ርዕስ ልመለስ፤ ከተማይቱን በየቤቱ የማዳረሱን እንቅስቃሴ ሲመሩ ከነበሩት አገልጋዮች አንዱ፥ መነቃቃቱ በከተማይቱ ያለውን ቤተሰብ ሁሉ እንደ ደረሰ፥ እያንዳንዱም ቤተሰብ እንደ ተጎበኘ ማግኘታቸውን በይፋ እስኪናገሩ ድረስ፥ ሥራው በቦልተን እየቀጠለና እየተስፋፋ ሄደ።
በቂ ስፋት ያለው የአምልኮ ስፍራ ቢኖረን ኖሮ፥ ምናልባት ከምሽት ወደ ምሽት በጉባኤዎቹ ውስጥ አሥር ሺህ ሰዎች ይኖሩን ነበር። ማድረግ የቻልነው ሁሉ አዳራሹን ሊይዝ የሚችለውን ያህል በሰው መሙላትና፥ ከዚያም በሌሎች የአምልኮ ስፍራዎች የነበሩትን ብዙ ሕዝብ ለመድረስ የምንችለውን ሌላ መንገድ ሁሉ መጠቀም ነበር።
በዚያ ከነበሩት ታላላቅ የፋብሪካ ባለቤቶች መካከል የተፈጸመ አንድ አስደናቂ የመለወጥ ሁኔታ ትዝ ይለኛል። ከእነርሱ አንዱ እጅግ ንፉግ ሰው እንደ ሆነ ተነግሮኝ ነበር። ለባለጠግነት ታላቅ ጥማት ነበረው፤ ተስፋ የሌለው ሰው እንደ ሆነም ይወራለት ነበር። መነቃቃቱ ከዚያ ዓይነት ሰዎች ብዙዎቹን ደርሶ ነበር፤ ይህ ሰው ግን ተቋቁሞ የቆመ ይመስል ነበር፤ ዓለማዊ አስተሳሰቡና የንፉግነት መንፈሱም የበላው ይመስል ነበር። ነገር ግን እኔም ሆንሁ ሌሎች ከጠበቅነው በተቃራኒ፥ እርሱ በተራው ሊያየኝ መጣ። ወደ ክፍሌ ጋበዝሁት፤ ከእርሱም ጋር እጅግ ከባድ ውይይት አደረግሁ። ታላቅ ንፉግ እንደ ነበረ፥ አንድ ጊዜም እግዚአብሔር ሌላ መቶ ሺህ ፓውንድ ቢሰጠው ለዘላለም ቢፈረድበት እንኳ እንደማይጠላ ለእግዚአብሔር እንደ ተናገረ አመነልኝ። በዚህ እጅግ ደነገጥሁ፤ ነገር ግን በዚያ የአእምሮ ሁኔታ ኃጢአተኛነት በአስፈሪ ሁኔታ እንደ ተወቀሰ በግልጽ ማየት ቻልሁ።
ከዚያም ክርስቶስ ሰዎችን በምድር ላይ መዝገብ ከመሰብሰብ የሚያስጠነቅቅበትንና በሰማይ መዝገብ እንዲሰበስቡ የሚመክርበትን የማቴዎስ ስድስተኛውን ምዕራፍ ከፊል አሰማሁት። በመጨረሻም ወደዚህ ቁጥር ደረስሁ፦ «ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።» እርሱም ወደ እኔ ዘንበል ብሎ፥ ሁሉ ነገር ለእርሱ አዲስ የሆነ ያህል እጅግ ትኩረት የሰጠ መሰለ። ይህን ቁጥር ባሰማሁት ጊዜ በታላቅ ልባዊነት፦ «ይህን ታምናለህ?» አለኝ። እኔም፦ «በእርግጥ አምናለሁ። የእግዚአብሔር ቃል ነው» አልሁት። እርሱም፦ «እንግዲያውስ እገባበታለሁ» አለ፤ በታላቅ መነሣሣትም ብድግ ብሎ ቆመ። «ይህ እውነት ከሆነ ሁሉን ነገር አሁኑኑ ለክርስቶስ እሰጣለሁ» አለ። ወዲያውም ተንበረከክን፤ እኔም ጉዳዩን በጸሎት ለእግዚአብሔር አቀረብሁ፤ እርሱም እንደ ሕፃን ልጅ የተሰበረ መሰለ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እጅግ የተለየ ሰው ሆኖ ታየ። የንፉግነት ስሜቱ ሁሉ የቀለጠ መሰለ። ሥራውን ከልቡ እንደ ቆረጠ ሰው ያዘ፤ ሄዶም በገዛ ወጪው አንድ የከተማ ሚስዮናዊ ቀጠረና ነፍሳትን ለክርስቶስ እንዲማርክ ወደ ሥራ አሰማራው።
በዚህም ስፍራ ደግሞ የወይዘሮ ፊኒ ስብሰባዎች እጅግ ብዙ ሰዎች ይገኙባቸው ነበር። እርስዋም ሁልጊዜ እንደምታደርገው በቀን ታደርጋቸው ነበር፤ አንዳንድ ጊዜም በሴቶች ስብሰባዋ ቴምፐራንስ ሆል ሊሞላ ተቃርቦ እንደ ነበረ ይነገረኝ ነበር። የልዩ ልዩ ቤተ እምነቶች ክርስቲያን ሴቶች ከእርስዋ ጋር ተባብረው አበረታቷት፤ በእነዚያ የሴቶች ስብሰባዎች አማካይነትም ታላቅ መልካም ነገር እንደ ተሠራ እተማመናለሁ።
እኔና ባለቤቴ ሁለታችንም በእነዚህ ድካሞች እጅግ ዝለን ነበር። ቢሆንም በኤፕሪል ወደ ማንቸስተር ሄድን። በማንቸስተር፥ እንደ ተነገረኝ፥ የኮንግሪጌሽናል ወገን ከሌሎቹ ቤተ እምነቶች ይልቅ በልጦ ይገኛል። በሰፊው እንደሚታወቀው፥ የኢንዱስትሪ አውራጃዎች ከሌሎቹ የእንግሊዝ ክፍሎች ይልቅ ብርቱ የዲሞክራሲ ዝንባሌ አላቸው። ስለዚህ ኮንግሪጌሽናሊዝም ከጎበኘኋቸው ከተሞች ሁሉ ይልቅ በማንቸስተር ይበልጥ ተስፋፍቶአል። ይሁን እንጂ በዚያ ብዙ ሳልቆይ በወንድሞች መካከል ታላቅ የእርስ በርስ መተማመን ጒድለት እንዳለ አየሁ። በመሪዎቹ መካከል አለመግባባት እንዳለ አስተዋልሁ፤ ብዙ ጊዜም በሥራው ውስጥ እውነተኛ የልብ አንድነት እንደሌለ የሚያመለክቱ አነጋገሮችን እያዘንሁ ሰማሁ። ይህ ሊሸነፍ የሚገባው ታላቅ መሰናክል እንደ ሆነ፥ ሊሸነፍ ካልቻለም ሥራው በቦልተን እንደ ነበረው በዚያ ፈጽሞ ሊስፋፋ እንደማይችል ብዙም ሳይቆይ ተረዳሁ። ብዙም ሳይቆይ ሥራውን እንዲመሩና አጠቃላዩን እንቅስቃሴ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን እንዲያዘጋጁ በተመረጡት አንዳንድ ሰዎች ላይ ቅሬታ ታየ።
ይህም መንፈስን አሳዘነ፤ ሥራውንም አሽመደመደ። ከመጀመሪያው ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ ከቃሉ ጋር የነበረ ቢሆንም፥ ሥራው ግን በቦልተን እንዳደረገው በከተማይቱ ሁሉ ሊስፋፋ በሚችልበት ደረጃ የወንድሞችን አጠቃላይ የቡድንተኝነት ስሜትና አለመግባባት ፈጽሞ አላሸነፈም። ወደዚያች ከተማ ስሄድ የሜቶዲስትና የኮንግሪጌሽናል ወንድሞች በቦልተን እንዳደረጉት ተስማምተው አብረው ይሠራሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፤ በዚህ ግን ተሳስቼ ተገኘሁ። በሜቶዲስቶችና በኮንግሪጌሽናሊስቶች መካከል የልብ ቅንነትና መተሳሰብ ጒድለት ብቻ ሳይሆን፥ በኮንግሪጌሽናሊስቶች በራሳቸው መካከልም ታላቅ የመተማመንና የመተሳሰብ ጒድለት ነበር። ይሁን እንጂ ስብሰባዎቻችን እጅግ ትኩረት የሚስቡ ነበሩ፤ በየአቅጣጫውም እጅግ ብዙ ጠያቂዎች ይገኙ ነበር፤ ለጠያቂዎች ስብሰባ በተቀጠረ ጊዜ ሁሉ ብዙ ሰዎች ይገኙ ነበር። ቢሆንም እኔ ለማየት የናፈቅሁት በቦልተን እንዳየነው በማንቸስተርም የመንፈስ ተጽዕኖዎች አጠቃላይ ጐርፍ ነበር። ችግሩ በዚያን ጊዜ በእንቅስቃሴው ውስጥ በነበሩት መሪ ሰዎች ዘንድ መልካም መንፈስ አለመታየቱ ነበር። ምክንያቱን አላወቅሁም — ምናልባት በእኔ ራሴ ውስጥ ያለ አንድ ነገር ሊሆን ይችላል። እጅግ ብዙ ሰዎች እንደ ተለወጡ እርግጠኛ ብሆንም — በብርቱ የተወቀሱና በሁሉ መልኩ የተለወጡ የሚመስሉ እጅግ ብዙ ሰዎችን እኔ ራሴ አይቻለሁና አነጋግሬአለሁና — መሰናክሎቹ ግን የጌታ ቃልና የጌታ መንፈስ በሕዝቡ መካከል ያለ ዕንቅፋት እንዲሮጡ በሚያስችል ሁኔታ አልፈረሱም።
ከዚያ ስንለይ፥ በእነዚያ ስብሰባዎች ወቅት በተለየ ሁኔታ ለተባረኩት ሰዎች ስብሰባ ተጠራ፤ የተገኙትም ሰዎች ቍጥር አገልጋዮቹ ራሳቸው ከጠበቁት እጅግ የበለጠ እንደ ነበረ አምናለሁ። በተገኙት ሰዎች ብዛትና በስብሰባው መንፈስ እንደ ተደነቁ እርግጠኛ ነኝ። በእርግጥም በዚያ ከነበሩት አገልጋዮች መካከል የሥራውን ስፋት የተገነዘበ አንድም እንደ ነበረ አላስብም፤ ምክንያቱም በአብዛኛው በስብሰባዎቻችን አይገኙም ነበር። ስብሰባዎቹን ከስፍራ ወደ ስፍራ አይከተሉም ነበር፤ በጠያቂዎች ስብሰባዎችም አልፎ አልፎ ብቻ ይታዩ ነበር። እስከ ኦገስት መጀመሪያ ገደማ ድረስ በማንቸስተር ቆየን፤ መነቃቃቱም እስከዚያ ጊዜ ድረስ እየጨመረና እየተስፋፋ ቀጠለ።
ነገር ግን የእኔም የባለቤቴም ጉልበት ተሟጦ ነበር፤ አንዳንድ መሪ ወንድሞችም ድካማችንን አቋርጠን ወደ ዌልስ ወርደን ለጥቂት ሳምንታት እንድናርፍ፥ ከዚያም ወደ ማንቸስተር ተመልሰን ሥራችንን እንድንቀጥል ሐሳብ አቀረቡልን። ያቀረቡትም ሐሳብ አንድ ትልቅ አዳራሽ በመያዝ ስብሰባዎቻችንን ከማንም ሳንወግን እንድንቀጥል ነበር። ከአንድ የተወሰነ ጉባኤ ጋር ከመሥራት ይልቅ በዚያ መንገድ የበለጠ መልካም ነገር እንደምናስገኝ እነርሱ አሰቡ፤ እኔም ራሴ እንዲሁ አሰብሁ። በዚያች አገር የቤተ እምነቶች ድንበሮች በዚህች አገር ካሉት ይልቅ እጅግ ጐልተው የተሰመሩ ናቸው። የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን በተለዩ ወገኖች የአምልኮ ስፍራ እንዲገኙ ማድረግ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ሜቶዲስቶች በአብዛኛው ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር በነጻነት አብረው አያመልኩም። በእርግጥም ይኸው በእንግሊዝና በስኮትላንድ ስላሉት ቤተ እምነቶች ሁሉ እውነት ነው። የቡድንተኝነት ድንበሮች ከዚህች አገር ይልቅ እጅግ በግልጽ የተሰመሩ ናቸው፤ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት አባላትም ከዚህች አገር ይልቅ በድንበሮቻቸው ውስጥ አጥብቀው ይቆያሉ። በዚያ ለመነቃቃት እንቅስቃሴ የሚሠራበት እውነተኛው መንገድ ከየትኛውም የተለየ ቤተ እምነት ጋር የተለየ ግንኙነት አለማድረግ፥ ነገር ግን እውነተኛውን ወንጌል መስበክና የቤተ እምነት ስሜቶችና ልዩ ጠባዮች የእግዚአብሔርን መንፈስ ተጽዕኖዎች ሊያጠብቡ በማይችሉባቸው አዳራሾች፥ የአየሩ ሁኔታ ሲፈቅድም በመንገዶች ላይ እንኳ፥ ጸንቶ መቆም እንደ ሆነ ተረድቻለሁ።
ኦገስት ሁለት ቀን 1860 ከማንቸስተር ተነሥተን ወደ ሊቨርፑል ወረድን። ከወዳጆቻችን ብዙዎቹ ከእኛ ጋር ወርደው እዚያው አደሩ። በሦስተኛው ቀን ጠዋት «ፐርሺያ» በምትባለው መርከብ ወደ ኒው ዮርክ ተነሣን። ሊሰናበቱን ከልዩ ልዩ የእንግሊዝ ክፍሎች እጅግ ብዙ ወዳጆቻችን ተሰብስበው አገኘን። በፍቅርና ልብ በሚነካ ሁኔታ ተሰናበትናቸው፤ ያቺም የከበረች አሮጌ የእንፋሎት መርከብ እየተምዘገዘገች ወደ ባሕር ወጣች፤ እኛም ወደ አገራችን ጉዞ ጀመርን።