የቄስ ቻርልስ ጂ. ፊኒ ማስታወሻዎች
በዌስተርንና በሮም የተደረጉ አገልግሎቶች፥ 1854-5

ምዕራፍ 31 · 8 ደቂቃ ንባብ · 10 ደቂቃ ማዳመጥ

በዌስተርንና በሮም የተደረጉ አገልግሎቶች፥ 1854-5

በሚቀጥለው የብርድ ወቅት፥ በገና ሰሞን፥ ቀደም ሲል እንደ ተረኩት በ1825 መጸው አገልግሎቴን ወደ ጀመርሁባት በኦናይዳ ካውንቲ ወደምትገኘው ወደ ዌስተርን እንደ ገና ሄድን። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ እንደ ገና ያለ እረኛ ነበሩ፤ እኛም በዚያ እጅግ አስደሳች በሆነ አገልግሎት ብዙ ሳምንታት አሳለፍን፥ እጅግ ጉልህ ፍሬም ታየ።

በዚህ ጊዜ በመነቃቃቱ ውስጥ ከተከሰቱት አስገራሚ ነገሮች መካከል የአንድን ወጣት ሰው ጉዳይ እጠቅሳለሁ። እርሱ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ወላጆች ልጅ ነበር፤ ለረጅም ጊዜም ሲጸለይለት ኖሯል። ወላጆቹ የቤተ ክርስቲያኑ ታዋቂ አባላት ነበሩ። እንዲያውም አባቱ ከቤተ ክርስቲያኑ ሽማግሌዎች አንዱ ነበሩ፤ እናቱም እግዚአብሔርን የምትፈራ፥ የምትጸልይ ሴት ነበረች። አገልግሎቴን በዚያ በጀመርሁ ጊዜ፥ ወላጆቹንና በአጠቃላይ ክርስቲያኑን ሕዝብ እጅግ እያስገረመና እያሳዘነ፥ በስብከቱ፥ በአጠቃላይ በስብሰባዎቹና መነቃቃቱን ለማስፋፋት በሚደረገው ነገር ሁሉ ላይ እጅግ መረረ። በፈቃዱ ኃይል ሁሉ ራሱን በዚህ ላይ አቆመ፤ እንደ ተነገረኝም፥ «ፊኒም ሆነ ሲኦል ሊለውጡኝ አይችሉም» ብሎ ተናገረ። ወላጆቹ እጅግ እስኪያዝኑ ድረስ ብዙ እጅግ የሚያስጠሉና ርኩስ ነገሮችን ተናገረ፤ ነገር ግን በአንዳች ውጫዊ ብልግና ተጠርጥሮ እንደ ነበር አላውቅም።

ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል መቋቋም እስኪያቅተው ድረስ ከቀን ወደ ቀን አጣበቀው። አንድ ቀን ጠዋት ወደ ክፍሌ መጣ። መልኩ በእውነት የሚያስደነግጥ ነበር። ልገልጸው አልችልም። የአእምሮው ሁኔታ በፊቱ ላይ እንዲህ ያለ ምልክት ያሳረፈበትን ሰው እምብዛም አይቼ አላውቅም። ሊያብድ የቀረበ ይመስል ነበር፤ ተቀምጦም ሳለ የክፍሉ ዕቃዎች በመንቀጥቀጡ በግልጽ እስኪናወጡ ድረስ ይንቀጠቀጥ ነበር። እጁን ስይዝ እጅግ ቀዝቃዛ መሆኑን አስተዋልሁ። ከንፈሮቹ ሰማያዊ ሆነው ነበር፤ መልኩም በሙሉ እጅግ የሚያስፈራ ነበር። እውነቱ፥ የኃጢአት ወቀሳውን ሊታገሠው እስከ ቻለ ድረስ ተቋቁሞት ነበር። ሲቀመጥ፥ «የምወድህ ወጣት ሆይ፥ ምን ሆነሃል?» አልሁት። እርሱም፥ «ወይኔ፥ የማይሰረየውን ኃጢአት ሠርቻለሁ» አለ። እኔም፥ «እንዲህ እንድትል ያደረገህ ምንድር ነው?» ብዬ መለስሁለት። እርሱም፥ «ወይኔ፥ እንደ ሠራሁት አውቃለሁ፤ ሆን ብዬም ነው ያደረግሁት» አለ።

ከዚያም ስለ ራሱ ይህን ሐቅ ተረከ። እንዲህ አለ፦ «ከብዙ ዓመታት በፊት ‹የባሕር ወንበዴው የራሱ መጽሐፍ› የሚባል መጽሐፍ እጄ ገባ። አነበብሁት፤ በአእምሮዬም ላይ እጅግ ያልተለመደ ውጤት አመጣ። ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ የባሕር ወንበዴ የመሆን አስፈሪና ገሃነማዊ የሆነ ምኞት አሳደረብኝ። ታሪካቸው ከተጻፈላቸው የመንገድ ዘራፊዎች፥ ሽፍቶችና የባሕር ወንበዴዎች ሁሉ በላይ አለቃ ለመሆን ቈረጥሁ። ነገር ግን» አለ፥ «ያደግሁበት ሃይማኖታዊ ትምህርት መንገዴን ዘጋብኝ። የወላጆቼ ትምህርትና ጸሎት በፊቴ የሚነሡ ይመስሉ ነበር፤ ስለዚህ ወደ ፊት መሄድ አልቻልሁም። ነገር ግን የእግዚአብሔርን መንፈስ አሳዝኖ ማራቅ፥ ዳግመኛም እንዳይሰማ አድርጎ አሠራሩን ማጥፋት እንደሚቻል ሰምቼ ነበር። ደግሞም ኅሊናዬ እንዳያስቸግረኝ ኅሊናዬን ማደንዘዝ እንደሚቻል አንብቤ ነበር፤ ውሳኔዬን ካደረግሁ በኋላም የመጀመሪያ ሥራዬ ያለ አንዳች የኅሊና ጸጸት ወደ ፊት ገፍቼ ማናቸውንም ዓይነት ዝርፊያና ግድያ መፈጸም እችል ዘንድ ሃይማኖታዊ ወቀሳዬን ማስወገድ ነበር። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስን ለመሳደብ ሆን ብዬ ተነሣሁ።» ከዚያም ይህን በምን ዓይነት ሁኔታ እንዳደረገውና ለመንፈስ ቅዱስ ምን እንዳለ ነገረኝ፤ ነገር ግን ደግሞ ለመናገር እጅግ የሚያስደፍር ስድብ ነበር።

እንዲህም ብሎ ቀጠለ፦ «ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ እንደሚለየኝ፥ ኅሊናዬም ከእንግዲህ እንደማያስቸግረኝ የግድ መሆን አለበት ብዬ ተሰማኝ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ወንጀል ፈጽሜ እንዴት እንደሚነካኝ ለማየት ወሰንሁ። ከቤታችን በመንገዱ ማዶ አንድ ትምህርት ቤት ነበረ፤ አንድ ቀን ማታ ሄጄ በእሳት አቃጠልሁት። ከዚያም ወደ ክፍሌ ሄጄ ተኛሁ። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ እሳቱ ታወቀ። ተነሥቼ እሳቱን ለማጥፋት ከተሰበሰበው ሕዝብ ጋር ተቀላቀልሁ፤ ነገር ግን ጥረቱ ሁሉ ከንቱ ሆነ፥ ሕንፃውም ተቃጥሎ ከመሬት ጋር ተደባለቀ።» ሕንፃን እንዲህ ማቃጠል በመንግሥት ወኅኒ ቤት የሚያስቀጣ ወንጀል ነበር። እርሱም ይህን ያውቅ ነበር። ከዚያ ወዲያ ሌላ ወንጀል ፈጽሞ እንደ ሆነ ጠየቅሁት። እርሱም፥ «የለም» ብሎ መለሰ። እንደ ጠበቀው ኅሊናው በዚህ ጉዳይ ዕረፍት እንዳላገኘ ጨምሮ የተናገረ ይመስለኛል። ያቃጠለው እርሱ እንደ ሆነ ተጠርጥሮ እንደ ሆነ ጠየቅሁት። እርሱ መጠርጠሩን እንደማያውቅ፥ ነገር ግን ሌሎች ወጣቶች እንደ ተጠረጠሩና ስለ እነርሱ እንደ ተወራ መለሰልኝ። ስለዚህ ጉዳይ ምን ለማድረግ እንዳሰበ ጠየቅሁት። ለመናዘዝ ወደ ትምህርት ቤቱ የአስተዳደር ቦርድ አባላት እንደሚሄድ መለሰ፤ ከእርሱም ጋር አብሬው እንድሄድ ለመነኝ።

በአቅራቢያ ይኖሩ ወደ ነበሩት ከቦርድ አባላቱ ወደ አንዱ ከእርሱ ጋር ሄድሁ፤ ወጣቱም ሐቁን እንድነግራቸው ለመነኝ። እንዲሁ አደረግሁ። የቦርዱ አባል መልካም ሰውና የዚህ ወጣት ወላጆች ታላቅ ወዳጅ ነበሩ። ዜናው በጥልቅ ነካቸው። ወጣቱ ዝም ብሎ በፊታቸው ቆመ። ከቦርዱ አባል ጋር ጥቂት ከተነጋገርሁ በኋላ፥ «ሄደን ሌሎቹን የቦርድ አባላት እናያለን» አልሁ። ሰውየውም፥ «የለም፥ መሄድ አያስፈልጋችሁም፤ እኔ ራሴ አይቻቸዋለሁ፤ ታሪኩንም በሙሉ እነግራቸዋለሁ» ብለው መለሱ። እርሳቸው ራሳቸው በፈቃደኝነት ይቅር እንደሚሉት ለወጣቱ አረጋገጡለት፤ ሌሎቹ የቦርድ አባላትና የከተማው ሕዝብም ይቅር እንደሚሉትና በእርሱም ሆነ በወላጆቹ ላይ በዚህ ጉዳይ አንዳች ወጪ እንደማይጥሉ እንደሚገምቱ ተናገሩ።

ከዚያም ወደ ክፍሌ ተመለስሁ፤ ወጣቱም ወደ ቤቱ ሄደ። ቢሆንም ገና ዕረፍት አላገኘም ነበር። ማታ ወደ ስብሰባ ስሄድ በበሩ ላይ አግኝቶኝ እንዲህ አለ፦ «በይፋ መናዘዝ አለብኝ። ብዙ ወጣቶች በዚህ ነገር ተጠርጥረዋል፤ እኔ እንዳደረግሁት፥ ተባባሪም እንዳልነበረኝ፥ ከእግዚአብሔርና ከእኔ በቀር ማንም እንዳላወቀው ሕዝቡ እንዲያውቅ እፈልጋለሁ።» ደግሞም ጨምሮ፦ «አቶ ፊኒ፥ ለሕዝቡ አይነግሩልኝም? እኔ እገኛለሁ፤ ማንም ጥያቄ ቢጠይቅ መናገር የሚያስፈልገውን ማናቸውንም ነገር እናገራለሁ፤ ነገር ግን አፌን መክፈት የምችል አይመስለኝም። እርስዎ ሁሉንም ሊነግሯቸው ይችላሉ» አለ።

ሕዝቡ በተሰበሰበ ጊዜ ተነሥቼ ሐቁን ተረክሁላቸው። ቤተሰቡ በማኅበረሰቡ ዘንድ እጅግ የታወቀና እጅግ የተወደደ ስለ ነበረ፥ የተነገረው ነገር ታላቅ ስሜት አሳደረ። በጉባኤው ሁሉ ሕዝቡ ተንሰቀሰቀ፥ አለቀሰም። ይህን የተሟላ ኑዛዜ ካደረገ በኋላ ሰላም አገኘ። ከዚያ ወዲህ ስላለው መንፈሳዊ ታሪኩ ብዙ አላውቅም። ይሁን እንጂ ክርስቶስን አጥብቆ እንደ ያዘና ወደ ኋላ የተመለሰ እንደማይመስል በቅርቡ ተረድቻለሁ። በዓመፁ ጊዜ ወደ ሠራዊቱ ገባ፤ በፎርት ፊሸር ጦርነትም ተገደለ።

እስካሁን የመነቃቃቶችን ታሪክ ስተርክ፥ ወደ እኔ መጥተው ምክር የጠየቁኝና ሐቁን የነገሩኝ ሰዎች የፈጸሟቸውን እጅግ ብዙ የወንጀል ጉዳዮች አልፌአቸዋለሁ። በእነዚህ መነቃቃቶች በብዙ አጋጣሚዎች፥ ገንዘቡን በቀጥታ በማጭበርበር ወይም በንግድ ግንኙነታቸው በአንዳች ራስ ወዳድ ብልጠት በማግኘታቸው ኅሊናቸው ያስጨነቃቸው ሰዎች፥ አንዳንድ ጊዜ እስከ ብዙ ሺህ ዶላሮች የሚደርስ ካሳ መለሱ።

በመጀመሪያ በቦስተን ያሳለፍሁት የብርድ ወቅት እንዲህ ያሉ እጅግ ብዙ ነገሮች እንዲገለጡ አደረገ። በዚያ በአንድ ሰንበት ጠዋት፥ «ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም» በሚለው ጥቅስ ላይ፥ ከሰዓት በኋላም በቀረው የቁጥሩ ክፍል፥ «የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል» በሚለው ላይ ሰብኬ ነበር። የእነዚያ ሁለት ስብከቶች ውጤት እጅግ ያልተለመደ እንደ ነበረ አስታውሳለሁ። ከዚያ በኋላ ለሳምንታት ያህል፥ በዕድሜ ከሞላ ጎደል ሁሉም ዓይነት የሆኑ ወንዶችና ሴቶች፥ መንፈሳዊ ምክር ለመጠየቅ ወደ እኔ መጡ፤ ልዩ ልዩ ማጭበርበሮችንና ከሞላ ጎደል ማናቸውንም ዓይነት ኃጢአቶች እንደ ፈጸሙ ገለጡልኝ። አንዳንድ ወጣቶች በንግድ ሥራ አሠሪዎቻቸውን አጭበርብረው ነበር፤ አንዳንድ ሴቶችም ሰዓቶችንና ከሞላ ጎደል የሴት አልባሳትን ሁሉ ሰርቀው ነበር። እንዲያውም በዚያን ጊዜ በዚያች ከተማ የጌታ ቃል የክፋትን ዋሻ እስኪገልጥ ድረስ በዚህ ዓይነት ኃይል ወደ ልብ የተላከ ይመስል ነበር። የፈጸሟቸው ሰዎች በተናዘዙት መሠረት በግል ያወቅኋቸውን ወንጀሎች ለመጥቀስ በእርግጥ ሰዓታት ይወስድብኛል። ነገር ግን በሁሉም አጋጣሚ ሰዎቹ ፈጽመው የተጸጸቱ ይመስሉ ነበር፤ በአቅማቸው እስከ መጨረሻው ድረስ ካሳ ለመመለስም ፈቃደኞች ነበሩ።

ነገር ግን ከዚህ ከወጣሁበት ርዕስ ወደ ዌስተርን ልመለስ። መነቃቃቱ እጅግ አስደሳች ባሕርይ ነበረው፤ ለእግዚአብሔር የተወለዱ ነፍሳትም በቁጥር ብዙ ነበሩ። በዚያ የአንዲት ወጣት ሴትን መለወጥ በታላቅ ትኩረት አስታውሳለሁ። እርሷ የመንደሩን ትምህርት ቤት ታስተምር ነበር። አባቷ ተጠራጣሪ ነበሩ ብዬ አምናለሁ፤ እንደ ተረዳሁትም እርሷ አንድ ብቻ ሴት ልጅና የአባቷ እጅግ የተወደደች ልጅ ነበረች። በትክክል ተነግሮኝ ከሆነ፥ አባቷ በከተማው ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ሰው ነበሩ፤ ነገር ግን ስብሰባዎቻችንን ፈጽሞ አይካፈሉም ነበር። የሚኖሩት ከመንደሩ ርቆ ባለ እርሻ ላይ ነበር። እንዲያውም መንደሩ እጅግ ትንሽ ነው፤ ነዋሪዎቹም በሞሃክ ሸለቆና በግራና በቀኝ ባሉት ኮረብቶች ላይ ተበታትነው ይኖራሉ፤ ስለዚህ አብዛኛው ነዋሪ ወደ ስብሰባ ለመምጣት ብዙ ርቀት መጓዝ አለበት። ይህች ወጣት ሴት ስብሰባዎቻችንን ብዙም እንደማትካፈልና ሥራውንም በከፍተኛ ደረጃ እንደምትቃወም ሰምቼ ነበር። አንድ ቀን በትምህርት ቤቱ በኩል ሳልፍ ላነጋግራት ገባሁ። መጀመሪያ ስገባ ስታየኝ የተገረመች ትመስል ነበር። ከእርሷ ጋር ተዋውቄ አላውቅም ነበር፤ በዚያ ስፍራ ባላገኛት ኖሮ ባላወቅኋትም ነበር። እርሷ ግን ታውቀኝ ነበር፤ መጀመሪያም ከፊቴ የምትሸሽ ትመስል ነበር። እጅግ በደግነት እጇን ይዤ ስለ ነፍሷ ላነጋግራት ጎራ እንዳልሁ ነገርኋት። «ልጄ ሆይ፥ ነገርሽ እንዴት ነው? ልብሽን ለእግዚአብሔር ሰጥተሻል?» አልኋት። ይህን ያልኋት እጇን ይዤ ሳለሁ ነበር። ራሷን ደፋች፤ እጇንም ለማስለቀቅ አንዳች ሙከራ አላደረገችም። የሚያስገዛ አንድ ኃይል እንደ መጣባት ወዲያው አየሁ፤ ኃይሉም እጅግ ጥልቅና አስገራሚ ስለ ነበረ፥ በዚያው ስፍራ ለእግዚአብሔር እንደምትገዛ ርግጠኛ ለመሆን ተቃርቤ ነበር።

ስገባ ከሁሉ አብልጬ የጠበቅሁት፥ እንድታስብበት ሊያነሣሷት ይችላሉ ብዬ ተስፋ ያደረግኋቸውን ጥቂት ቃላት ማነጋገርና በሰፊው የምንነጋገርበትን ጊዜ መቅጠር ነበር። ነገር ግን የተሰማት ስሜት ወዲያው እጅግ ግልጽ ሆነ፤ ልቧም በዚህ ያህል በቀላሉ የተሰበረ መሰለ፤ ስለዚህ በጸጥታና በለስላሳ ድምፅ በተነገሯት ጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ተቃውሞዋን የተወችና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመያዝ የተዘጋጀች መሰለች። ከዚያም ለተማሪዎቹ ጥቂት ቃላት እንድናገር ትፈቅድ እንደ ሆነ ጠየቅኋት፤ እርሷም፥ አዎን፥ ብናገር ደስ እንደሚላት ተናገረች። እንዲሁ አደረግሁ፤ ከዚያም እርሷንና ተማሪዎቿን በጸሎት ለእግዚአብሔር እንዳቀርብ ትፈቅድ እንደ ሆነ ጠየቅኋት። ባደርገው ደስ እንደሚላት ተናገረች፤ በትምህርት ቤቱም ፊት በጥልቅ ተነካች። ጸለይን፤ ጊዜውም እጅግ የተከበረና ልብን የሚያቀልጥ ነበር። ወጣቷ ሴት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የተገዛችና ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገረች ትመስል ነበር። ብዙም ሳትቆይ፥ ወደ ሰማይ እንደ ሄደች ተስፋ አደርጋለሁ፥ ከዚህ ዓለም ተለየች።

በዌስተርን የቆየሁባቸው እነዚህ ሁለት ወቅቶች በመካከላቸው ሠላሳ ዓመት ያህል ርቀት ነበራቸው። በዚያ ካገለገልሁበት የመጀመሪያው መነቃቃት ጊዜ በዚያ ይኖር ከነበረው ትውልድ ሌላ አዲስ ትውልድ በዚያ ስፍራ ለመኖር መጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ ከቀድሞዎቹ አባላት ጥቂቶቹን በዚያ አገኘሁ። ነገር ግን ጉባኤው በአብዛኛው አዲስ ሲሆን፥ በዋናነት ከመጀመሪያው መነቃቃት በኋላ ያደጉ ወጣቶችን የያዘ ነበር።

እንደ መጀመሪያው መነቃቃት ሁሉ በዚህኛውም፥ በሮም ያሉ ሰዎች በዌስተርን የሚሆነውን ሰሙ፤ ስብሰባዎቻችንንም ለመካፈል በብዙ ቁጥር ወደዚያ ወጡ። ይህም ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ሮም ወርጄ ጥቂት ጊዜ በዚያ እንዳሳልፍ ምክንያት ሆነ።

በዌስተርን ያለው የሃይማኖት ሁኔታ ከዚህ የመጨረሻ መነቃቃት ወዲህ እጅግ እንደ ተሻሻለ አምናለሁ። የወንጌል ሥርዓቶች ተጠብቀዋል፤ በትክክለኛውም አቅጣጫ ከፍተኛ እድገት እንደ ተደረገ አምናለሁ። ከአንድ ወንድ ልጅና ከቤተሰቡ በቀር የቢ—— ቤተሰብ ሁሉ ከዌስተርን ወጥተዋል። ያ ትልቅና አስደሳች ቤተሰብ ቀልጦ ጠፍቷል፤ አንዱ በዌስተርን፥ አንዱ በዩቲካ ቀርቷል፤ በዚያ በመጀመሪያው መነቃቃት የተለወጠውና ለብዙ ዓመታት አገልጋይ፥ በኒው ዮርክ ግዛት በዋተርታውን የሚገኘው የመጀመሪያው ፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን እረኛ የሆነው አንድ ወንድ ልጅም አለ።

በመጀመሪያ ጊዜ በሮም በነበርሁበት ጊዜና ከዚያም በኋላ ለብዙ ዓመታት ቤተ ክርስቲያኑ ኮንግሪጌሽናል ነበረ። ነገር ግን ለመጨረሻ ጊዜ በዚያ ከመገኘቴ ጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ወጣት የፕሪስባይቴሪያን አገልጋይ እረኛ አድርገው ሾመው ነበር፤ እርሱም ቤተ ክርስቲያኑ ከኮንግሪጌሽናል ይልቅ ፕሪስባይቴሪያን መሆን አለበት ብሎ ተሰማው። ይህንንም ለቤተ ክርስቲያኑ አቀረበና መከረ፤ ሊያስፈጽመውም ቻለ፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የነበሩ ብዙ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች እጅግ አልተደሰቱም። ይህም በሮም እጅግ የማይፈለግ ሁኔታ ፈጠረ፤ ከዌስተርን ወደዚያ በደረስሁ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ስለ ነበረው ስለዚያ እጅግ ከባድ የስሜት መከፋፈል ለመጀመሪያ ጊዜ ተገለጠልኝ። እረኛቸው ከቤተ ክርስቲያኑ እጅግ ተሰሚነት ያላቸው አባላት መካከል የብዙዎቹን እምነትና ፍቅር አጥቶ ነበር።

የነገሩን ሁኔታ ባወቅሁ ጊዜ፥ ያ ችግር ካልተፈወሰ በቀር አጠቃላይ መነቃቃትን ለማስፋፋት የሚቻለው እጅግ ጥቂት እንደ ሆነ ርግጠኛ ሆንሁ። ነገር ግን ጉዳዩ በብዙ ተወርቶበት ነበር፤ በመጀመሪያ የተሳተፉበት ሰዎችም በአቋማቸው እንዲህ ጸንተው ነበር፤ ስለዚህ እርቅ ለማምጣት የደከምሁት በከንቱ ሆነ። ነገሩ የሚሰበክበት አልነበረም፤ ነገር ግን በግል ውይይት ያን የምሬት ሥር ለመንቀል ሞከርሁ። ወገኖቹ ሐቁን በአንድ ዓይነት መንገድ እንደማያዩት አገኘሁ። ይሁን እንጂ መስበኬን ቀጠልሁ፤ የጌታም መንፈስ ፈሰሰ፤ ሰዎች በተደጋጋሚ ይለወጡ ነበር፤ ታላቅ መልካም ነገርም እንደ ተሠራ ተስፋ አደርጋለሁ።

ነገር ግን እግዚአብሔር የሚቀበለውን የስሜትና የጥረት አንድነት ለማስገኘት በከንቱ ከጣርሁ በኋላ፥ ትቻቸው ለመሄድ ወሰንሁ። ከዚያ ወዲህ፥ ቅር የተሰኙት አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት በሮም ያለውን ቤተ ክርስቲያን ፈጽመው ትተው ሄደው በዌስተርን ካለው ቤተ ክርስቲያን ጋር እንደ ተቀላቀሉ ሰምቻለሁ። እረኛው በዚያ ክርክር ውስጥ ግዴታዬ ነው ብሎ ያሰበውን እንዳደረገ እገምታለሁ፤ ነገር ግን ለዚያ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ፍቅር ስለ ነበረኝ፥ ከዚህ የተነሣ የመጡት መከፋፈሎች እጅግ አሳመሙኝ።

ጨርሰዋል፦ በዌስተርንና በሮም የተደረጉ አገልግሎቶች፥ 1854-5

ቀዳሚ ቀጣይ