የቄስ ቻርልስ ጂ. ፊኒ ማስታወሻዎች
በኦበርሊን የመጀመሪያዎቹ የአገልግሎት ዘመናት

ምዕራፍ 24 · 18 ደቂቃ ንባብ · 23 ደቂቃ ማዳመጥ

በኦበርሊን የመጀመሪያዎቹ የአገልግሎት ዘመናት

የሌን ሴሚናሪ ተማሪዎች ወደ ኦበርሊን መጡ፤ የኮሌጁ ባለአደራዎችም የሚያርፉበት «ሰፈር» ሠሩላቸው፤ ሌሎች ተማሪዎችም ከየአቅጣጫው ወደ እኛ ይጐርፉ ጀመር። ለመምጣት ከተስማማሁ በኋላ በኦበርሊን የነበሩት ወንድሞች፥ ሕዝቡን ሊያስተናግድ የሚበቃ ሰፊ ስፍራ በዚያ ስላልነበረ ስብሰባ የምናደርግበት ትልቅ ድንኳን ይዤ እንድመጣ ጠየቁኝ። ይህን ጥያቄ ለአንዳንድ ወንድሞቼ አሳወቅኋቸው፤ እነርሱም ሄጄ ድንኳን እንዳሠራ፥ ገንዘቡንም እነርሱ እንደሚሰጡ ነገሩኝ። ሄጄ ድንኳኑን አሠራሁ፤ ዋጋውን የምከፍልበትንም ገንዘብ ሰጡኝ። ድንኳኑ ክብ ሲሆን ዲያሜትሩ መቶ ጫማ ነበር፤ ለመትከልም የሚያስፈልጉት መሣሪያዎች ሁሉ ተሟልተውለት ነበር። ድንኳኑን ደግፎ በያዘው በመካከለኛው ምሰሶ ጫፍ ላይ ሰንደቅ ነበረ፤ በእርሱም ላይ በጣም በትልልቅ ፊደላት «ቅድስና ለእግዚአብሔር» ተብሎ ተጽፎ ነበር። ይህ ድንኳን እጅግ ጠቀመን። የአየሩ ሁኔታ በሚፈቅድበት ጊዜ በየሰንበቱ በአደባባዩ ላይ እንዘረጋውና ሕዝባዊ አምልኮ እናደርግበት ነበር፤ ከመጀመሪያዎቹ የምረቃ ሥነ ሥርዓቶቻችንም ብዙዎቹ የተካሄዱት በእርሱ ውስጥ ነበር። ደግሞም ፍላጎቱን ሊያሟሉ የሚችሉ ትልልቅ አብያተ ክርስቲያናት በሌሉባቸው በዙሪያው ባሉ ቦታዎች ተከታታይ ስብሰባ ለማድረግም በተወሰነ መጠን አገልግሎት ላይ ውሏል።

አርተር ታፓን፥ ከገንዘብ ችግር እስክንወጣ ድረስ መላ ገቢያቸውን ሰጥተው ገንዘብ እንደሚያቀርቡልን ቃል መግባታቸውን ቀደም ብዬ ጠቅሻለሁ። ከእርሳቸው ጋር በዚህ ስምምነት ላይ ተመሥርቼ ሥራውን ጀመርሁ። ነገር ግን ባለአደራዎቹ፥ እርሳቸው እንደ ፈለጉት ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የተቋሙን ችግሮችና ዓላማዎች በመላው አገር ማስታወቅ የሚገባቸውን ጥረት እንዳይተዉ፥ ቃል ኪዳናቸው ለእነርሱ እንዳይታወቅ በመካከላችን ተጨማሪ ስምምነት ነበረ። በዚህ ስምምነት መሠረት፥ በአንድ ታላቅ ጫካ እምብርት ውስጥ፥ በዚያን ጊዜም በብዙ መልኩ የማይመች በሆነ ስፍራ እንደ ነበርን ሲታሰብ፥ እዚህ ያለው ሥራ በተቻለ መጠን በፍጥነት ተገፋ።

ሕንጻዎቻችንን የመገንባቱን ሥራ ገና መጀመራችን ነበር፤ ብዙ ገንዘብ እንደሚያስፈልገንም አድርገን ዕቅድ አውጥተን ነበር፤ በዚህ ጊዜ ታላቁ የንግድ ውድቀት አቶ ታፓንን፥ ለመምህራኑ ደመወዝ ለሚውለው ገንዘብ የፈረሙትንም ሰዎች ከሞላ ጎደል ሁሉንም ጣላቸው። የንግዱ ውድቀት በመላው አገር ዐለፈ፤ አብዛኞቹን ሀብታሞችም ጣለ። ለመምህራኑ መደገፊያ ገንዘብ ሳይኖረን ብቻ ሳይሆን የሠላሳ ሺህ ዶላር ዕዳ ተሸክመን እንድንቀር አደረገን፤ ደግሞም ከኮሌጁ ወዳጆች በዚህ አገር ገንዘብ እናገኛለን የሚል ምንም ተስፋ አልታየንም። በዚህ ጊዜ አቶ ታፓን የገቡልኝን ቃል በግልጽ አምነው ተቀብለው፥ በመውደቃቸውና ቃላቸውን ለመፈጸም ፈጽሞ ባለመቻላቸው እጅግ ጥልቅ ሐዘን እንደ ተሰማቸው ጻፉልኝ። በዚያን ጊዜ ችግራችን ታላቅ ነበር፤ በሰው ዓይን ሲታይም ኮሌጁ መክሸፉ የማይቀር ይመስል ነበር።

አብዛኛው የኦሃዮ ሕዝብ ድርጅታችን ባርነትን የማስወገድ ባሕርይ ስለ ነበረው ፈጽሞ ይቃወመው ነበር። በዙሪያችን የነበሩት ከተሞች እንቅስቃሴያችንን በጠላትነት ይመለከቱ ነበር፤ በአንዳንድ ቦታዎችም መጥተው ሕንጻዎቻችንን እንደሚያፈርሱ ዛቱ። በዚያው ጊዜ የዴሞክራቲክ ፓርቲ የበላይነት የነበረው የግዛቱ ሕግ አውጪ ምክር ቤት ቻርተራችንን ለመሻር የሚያስችለውን አንዳች ምክንያት ሊያገኝብን ይጥር ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ በዚህ ስፍራ ባለው ሕዝብ መካከል ወደ እግዚአብሔር ታላቅ ጩኸት መኖሩ የታወቀ ነው።

በዚያው ጊዜ ስለ መነቃቃት ያስተማርኋቸው ትምህርቶች በእንግሊዝ በሰፊው ተሰራጭተው ነበር፤ የብሪታንያ ሕዝብ ዓላማዎቻችንን፥ ተስፋዎቻችንንና ያለንበትን ሁኔታ ቢያውቅ አጥብቆ እንደሚራራልን ተገንዝበን ነበር። ስለዚህ ከቄስ ጆን ኪፕና ከአቶ ዊልያም ዶውስ የተውጣጣ መልእክተኛ ቡድን ወደ እንግሊዝ ላክን፤ ከአገሪቱ ግንባር ቀደም የፀረ ባርነት ሰዎች መካከል ከአንዳንዶቹ የምክር ደብዳቤዎችንና በድርጅታችን ላይ ያላቸውን እምነት የሚገልጹ ቃላትን አስገኘንላቸው። እነርሱም ወደ እንግሊዝ ሄደው ዓላማዎቻችንንና ችግሮቻችንን በብሪታንያ ሕዝብ ፊት አቀረቡ። ሕዝቡም በልግስና ምላሽ ሰጠ፤ ስድስት ሺህ ፓውንድ ስተርሊንግም ሰጠን። ይህም ዕዳችንን ሊያስከፍል ምንም አልቀረውም ነበር።

ባርነት እንዲወገድ የሚታገሉና የመነቃቃት ወዳጆች የሆኑ፥ በሰሜናዊ ግዛቶች ሁሉ ተበትነው የሚኖሩ ወዳጆቻችን አቅማቸው በፈቀደ መጠን በልግስና ረዱን። ቢሆንም ለብዙ ዓመታት ከድህነትና ከብዙ መከራ ጋር መታገል ነበረብን። አንዳንድ ጊዜ ከቀን ወደ ቀን የሚያስፈልገን እንዴት እንደሚሟላልን አናውቅም ነበር። ነገር ግን በእግዚአብሔር በረከት በተቻለን መጠን ራሳችንን ረዳን።

በአንድ ወቅት ቤተሰቤን በብርድ ወቅት የማስተዳድርበት ምንም መንገድ አላየሁም። የምስጋና ቀን ደረሰ፤ በዚያን ጊዜ እጅግ ደኽይተን ስለ ነበር፥ ያጣሁትን ላም ለመተካት በወንጌል አገልግሎቴ ስጠቀምበት የነበረውን የመጓጓዣ ሣጥኔን ለመሸጥ ተገድጄ ነበር። በምስጋና ቀን ጠዋት ተነሣሁ፤ ችግራችንንም በጌታ ፊት ዘረጋሁ። በመጨረሻም፥ ርዳታ ካልመጣ ባይመጣ የተሻለ እንደ ሆነ እንደምቆጥር፥ ጌታ ጥበብ ነው ብሎ በሚያየው በማንኛውም መንገድ ፈጽሞ እንደምረካ በመናገር ጸሎቴን ደመደምሁ። ሄጄ ሰበክሁ፤ የራሴንም ስብከት ከመቼውም ጊዜ ባላነሰ ሁኔታ የተደሰትሁበት ይመስለኛል። ለነፍሴ የተባረከ ቀን ነበረኝ፤ ሕዝቡም እጅግ እንደ ተደሰተበት ማየት እችል ነበር።

ከስብሰባው በኋላ ከአንዳንድ ወንድሞች ጋር ስነጋገር ጥቂት ቈየሁ፤ ባለቤቴም ወደ ቤት ተመለሰች። በሩ ላይ ስደርስ እርሷ በተከፈተው በር ላይ ቆማ በእጇ ደብዳቤ ይዛ ነበር። ስቀርብም ፈገግ ብላ፦ «ውዴ ሆይ፥ መልሱ መጥቷል» አለችኝ፤ ከፕሮቪደንስ የአቶ ጆሳያ ቻፒንን የሁለት መቶ ዶላር ቼክ የያዘውን ደብዳቤ ሰጠችኝ። እርሳቸው ባለፈው በጋ ከባለቤታቸው ጋር እዚህ መጥተው ነበር። ስለ ችግሮቼ ምንም አልተናገርሁም ነበር፤ ምክንያቱም ለማንም ሰው የመናገር ልማድ ፈጽሞ አልነበረኝም። ነገር ግን ቼኩን በያዘው ደብዳቤ ውስጥ የመምህራን መደገፊያው ገንዘብ እንደ ከሸፈና እኔም ርዳታ እንደሚያስፈልገኝ እንደ ሰሙ ጻፉ። ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨማሪ ልጠብቅ እንደምችልም ፍንጭ ሰጡ። ለብዙ ዓመታትም በዓመት ስድስት መቶ ዶላር ይልኩልኝ ነበር፤ እኔም በዚህ ኑሮዬን ገፋሁ።

በኒው ዮርክ ባደረግሁት ስምምነት መሠረት፥ ለሁለት ወይም ለሦስት ዓመታት በጋውን በኦበርሊን፥ የብርዱን ወቅት ደግሞ በኒው ዮርክ እንዳሳለፍሁ መናገር ነበረብኝ። በዚያ ለመስበክ በተመለስሁ ቁጥር የተባረከ መነቃቃት ነበረን። እዚህም ያለማቋረጥ መነቃቃት ነበረን። በዚያን ጊዜ ወደዚህ የመጡ ተማሪዎች ሳይለወጡ የቀሩት በጣም ጥቂቶች ነበሩ። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ጤንነቴ ከእነዚህ ሁለት የአገልግሎት መስኮች አንዱን መተው እንዳለብኝ እስክረዳ ድረስ ተዳከመ። የኮሌጁ ጉዳዮች ግን ኮሌጁን እንድተው ፈጽሞ የማይፈቅዱ መሰሉ። ስለዚህ በኒው ዮርክ ካለው ቤተ ክርስቲያኔ ተሰናበትሁ፤ በኒው ዮርክ ላሳልፋቸው የነበሩትንም የብርድ ወራት የሃይማኖት መነቃቃትን ለማስፋፋት በልዩ ልዩ ስፍራዎች በማገልገል አሳለፍኋቸው።

ስለ ሃይማኖት መነቃቃት የሰጠኋቸው ትምህርቶች የተሰበኩት ገና በቻታም ስትሪት ቤተ ጸሎት የፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን እረኛ ሳለሁ ነበር። በተከታዮቹ ሁለት የብርድ ወቅቶች በብሮድዌይ ታበርናክል ለክርስቲያኖች ትምህርቶችን ሰጠሁ፤ እነዚህንም አቶ ሌቪት ዘግበው በኒው ዮርክ ኢቫንጀሊስት ጋዜጣ አሳተሟቸው። እነዚህም ደግሞ በዚህ አገርና በአውሮፓ በአንድ ጥራዝ ታትመዋል። እነዚያ ለክርስቲያኖች የተሰበኩ ስብከቶች በአብዛኛው በገዛ አእምሮዬ ውስጥ ይካሄድ የነበረው ጥልቅ ምርመራ ውጤት ነበሩ። ይህም ማለት የእግዚአብሔር መንፈስ ስለ መቀደስ ጥያቄ ብዙ ነገሮችን ያሳየኝ ነበር፤ እነዚያንም ስብከቶች ለክርስቲያኖች እንድሰብክ የመራኝ ይኸው ነው። ብዙ ክርስቲያኖች እነዚያን ትምህርቶች ከወንጌል ይልቅ የሕጉ ማሳያ አድርገው ቈጠሯቸው። እኔ ግን እንደዚያ አልቈጠርኋቸውም፤ አሁንም አልቈጥራቸውም። ለእኔ ሕግና ወንጌል አንድ የሕይወት መመሪያ ብቻ አላቸው፤ የሕጉን መንፈስ መተላለፍ ሁሉ የወንጌልንም መንፈስ መተላለፍ ነው። ነገር ግን ከፍተኛዎቹ የክርስቲያናዊ ልምምድ ደረጃዎች የሚገኙት የእግዚአብሔር ሕግ በሰው ሕሊናና ልብ ላይ እጅግ በሚያስፈራ ጥልቅ ምርመራ ሲተገበር ብቻ እንደ ሆነ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ተረድቻለሁ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ የደከምሁበት ውጤት የክርስቲያኖችን ታላቅ ድካም፥ ደግሞም የቤተ ክርስቲያን የቈዩ አባላት በአጠቃላይ በጸጋ እጅግ ጥቂት እድገት ብቻ እያሳዩ እንደ ነበሩ፥ ከዚያ ቀደም ካወቅሁት በበለጠ ግልጽ አድርጎ አሳየኝ። ከመነቃቃት ሁኔታ አዲስ ከተለወጡ ሰዎች እንኳ ቀድመው ወደ ኋላ እንደሚመለሱ አገኘሁ። እኔ ራሴ በተለወጥሁበት መነቃቃትም እንዲሁ ሆኖ ነበር። ይህም በመጀመሪያ በተማሩት ትምህርት ማለትም አዲስ የተለወጡ ሰዎች ሳሉ እንዲይዙት በተመሩት አመለካከት ምክንያት እንደ ሆነ በግልጽ አየሁ።

ደግሞም በእምነትና በፍቅር በኩል በራሴ ያለመጽናት ጉድለት እጅግ እንዳልረካ ተመራሁ። በግልጽነት እውነቱን ለመናገር፥ ለእግዚአብሔር ጸጋ ምስጋና ይሁንና፥ ብዙ ክርስቲያኖች በግልጽ ወደ ኋላ ባፈገፈጉበት መጠን እኔ ወደ ኋላ እንዳፈገፍግ አልፈቀደልኝም ማለት አለብኝ። ነገር ግን በፈተና ፊት ብዙ ጊዜ ራሴን ደካማ ሆኜ አገኘሁት፤ የሃይማኖት መነቃቃትን ለማስፋፋት በብቃት እንድሠራ የሚያስችለኝን ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ኅብረትና መለኮታዊውን ብርታት አጥብቆ መያዝን ለመጠበቅ፥ ብዙ ጊዜ የጾምና የጸሎት ቀናትን ማድረግና የራሴን ሃይማኖታዊ ሕይወት በመመርመር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ያስፈልገኝ ነበር።

በመነቃቃት አገልግሎቴ እንደ ተገለጠልኝ የክርስቲያን ቤተ ክርስቲያንን ሁኔታ ስመለከት፥ የክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ከምታውቀው የበለጠ ከፍ ያለና ይበልጥ የሚጸና ነገር ይኖር እንደ ሆነ፥ ክርስቲያኖች ፈጽሞ ከፍ ባለ የክርስቲያናዊ ሕይወት ደረጃ እንዲጸኑ በወንጌል የተሰጡ ተስፋዎችና መንገዶች ይኖሩ እንደ ሆነ አጥብቄ እንድጠይቅ ተመራሁ። የሜቶዲስት ወንድሞቻችን ስለ መቀደስ ያላቸውን አመለካከት በተወሰነ መጠን አውቅ ነበር። ነገር ግን ስለ መቀደስ ያላቸው ሐሳብ ከሞላ ጎደል ከስሜት ሁኔታዎች ጋር ብቻ የሚያያዝ መስሎ ስለ ታየኝ ትምህርታቸውን ልቀበል አልቻልሁም። ቢሆንም፥ ፈጽሞ ከፍ ያለና ይበልጥ የጸና የክርስቲያናዊ ሕይወት ደረጃ ሊደረስበት እንደሚችልና የክርስቲያኖች ሁሉ መብት እንደ ሆነ አእምሮዬ እስኪረካ ድረስ፥ መጻሕፍትን ለመመርመርና በዚህ ጉዳይ ላይ ያገኘሁትን ሁሉ ለማንበብ ራሴን በትጋት ሰጠሁ።

ይህም በብሮድዌይ ታበርናክል ስለ ክርስቲያናዊ ፍጽምና ሁለት ስብከቶችን እንድሰብክ መራኝ። እነዚያ ስብከቶች አሁን ለክርስቲያኖች በተሰበኩት ትምህርቶች ጥራዝ ውስጥ ተካትተዋል። በእነዚያ ስብከቶች ክርስቲያናዊ ፍጽምና ምን እንደ ሆነ ተረጐምሁ፤ በዚህ ሕይወት ሊደረስበት እንደሚችልና በምን ትርጉም ሊደረስበት እንደሚችልም ለማሳየት ጣርሁ። ነገር ግን በዚህ ጊዜ አካባቢ፥ የቃሉን አንቲኖሚያናዊ ትርጉም የያዘው የክርስቲያናዊ ፍጽምና ጥያቄ በኒው ሄቨን፥ በአልባኒና በተወሰነ መጠን በኒው ዮርክ ከተማ ብዙ ማከራከር ጀመረ። እነዚህን አመለካከቶች «ዘ ፐርፌክሽኒስት» በተባለው ወቅታዊ መጽሔት እንደ ታተሙ መረመርኋቸው። ነገር ግን ልቀበላቸው አልቻልሁም። ቢሆንም፥ በዚህ ሕይወት የመቀደስ ትምህርት፥ ደግሞም ክርስቲያኖች የሚያውቁትን ኃጢአት ሳይሠሩ መኖር መብታቸው ነው በሚል ትርጉም ፍጹም መቀደስ፥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርት እንደ ሆነና ያንንም ደረጃ ለማግኘት የተትረፈረፉ መንገዶች እንደ ተሰጡ ረክቼ ነበር።

በኒው ዮርክ ባሳለፍሁት የመጨረሻው የብርድ ወቅት፥ ጌታ ነፍሴን በታላቅ መታደስ ሊጐበኛት ወደደ። ከብዙ የልብ ምርመራ ጊዜ በኋላ፥ ብዙ ጊዜ እንዳደረገው ወደ ሰፊ ስፍራ አወጣኝ፤ ፕሬዚዳንት ኤድዋርድስ በራሳቸው ልምምድ እንዳገኙት የሚናገሩለትን መለኮታዊ ጣዕም በነፍሴ አብዝቶ ሰጠኝ። በዚያ የብርድ ወቅት ፈጽሞ ተሰበርሁ፤ ስለዚህም አንዳንድ ጊዜ ለረጅም ጊዜ ያህል ከራሴ ኃጢአቶችና በክርስቶስ ካለው የእግዚአብሔር ፍቅር የተነሣ ጮኼ ከማልቀስ ራሴን መግታት አልቻልሁም። በዚያ የብርድ ወቅት እንደዚህ ያሉ ጊዜያት ተደጋጋሚ ነበሩ፤ ውጤታቸውም የመንፈሳዊ ብርታቴ ታላቅ መታደስና ስለ ክርስቲያኖች መብቶችና ስለ እግዚአብሔር ጸጋ ብዛት የነበረኝ አመለካከት መስፋት ነበር።

ስለ መቀደስ ጥያቄ ያለኝ አመለካከት ብዙ ትችት እንደ ደረሰበት የታወቀ ነው። ለታሪክ ታማኝ ለመሆን፥ ያለዚያ በዝምታ የማልፋቸውን አንዳንድ ነገሮች መናገር አለብኝ። ኦበርሊን ኮሌጅን አቶ ሺፐርድ የመሠረቱት በሀድሰን የሚገኘውን ዌስተርን ሪዘርቭ ኮሌጅ በማሳደግ ረገድ ይበልጥ የሚመለከታቸው ሰዎች ስሜትና ፍላጎት በእጅጉ እየተቃወመ ነበር። የዚያ ኮሌጅ ዋና የገንዘብ ወኪል ይህን ኮሌጅ ለማጥፋት የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ እንደ ነገራቸው አቶ ሺፐርድ በአንድ ወቅት አጫወቱኝ። በሀድሰን ያሉት ሰዎች የሥነ መለኮት ፕሮፌሰር ሆኜ ወደ ኦበርሊን እንድመጣ ጥሪ እንደ ደረሰኝ እንደ ሰሙ፥ ባለአደራዎቹ በዌስተርን ሪዘርቭ ኮሌጅ «የእረኝነት ሥነ መለኮትና የቅዱስ ንግግር ጥበብ» ፕሮፌሰር አድርገው መረጡኝ፤ ስለዚህም ሁለቱንም ግብዣዎች በአንድ ጊዜ ይዤ ነበር። ለሁለቱም በጽሑፍ ቃል አልገባሁም፤ ነገር ግን ስፍራውን ለማየትና ከዚያም የግዴታዬን መንገድ ለመወሰን መጣሁ።

በዚያ ጸደይ የፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባውን በፒትስበርግ አደረገ። ክሊቭላንድ በደረስሁ ጊዜ፥ ከሀድሰን የመጡ ሁለት ፕሮፌሰሮች በማንኛውም ሁኔታ በመጀመሪያ ወደ ሀድሰን እንድሄድ ለማድረግ አስበው በክሊቭላንድ መምጣቴን ሲጠባበቁ እንደ ነበር ተነገረኝ። ነገር ግን በተቃራኒ ነፋሳት ምክንያት በኤሪ ሐይቅ ላይ ዘግይቼ ነበር፤ በክሊቭላንድ ሲጠብቁኝ የነበሩት ወንድሞችም በጠቅላላ ጉባኤው መክፈቻ ላይ ለመገኘት ሄደው ነበር፤ እንደ ደረስሁም ወዲያውኑ እንዲያገኘኝና በምንም ዓይነት ወደ ሀድሰን እንድሄድ እንዲያደርገኝ ለአንድ ወንድም መልእክት ትተው ነበር። ነገር ግን በክሊቭላንድ ከኒው ዮርክ ከአርተር ታፓን የተላከ ደብዳቤ ይጠብቀኝ ነበር። እርሳቸው ወደ ኦበርሊን ሳይሆን ወደ ሀድሰን እንድሄድ ለማግባባት ብርቱ ጥረት እየተደረገ እንደ ነበር በሆነ መንገድ አውቀው ነበር።

በዚያን ጊዜ በሀድሰን የነበረው ኮሌጅ ሕንጻዎቹና መሣሪያዎቹ፥ ዝናውና ተሰሚነቱ ነበሩት፤ አስቀድሞም የተደላደለ ኮሌጅ ነበር። ኦበርሊን ምንም አልነበረውም። ቋሚ ሕንጻዎች አልነበሩትም፤ በጫካ ውስጥ የሰፈረች፥ የራሳቸውን ቤቶች መሥራት፥ ሰፊውን ደን መመንጠርና ለኮሌጅ ስፍራ ማዘጋጀት ገና የጀመሩ ትንሽ የሰፋሪዎች ማኅበረሰብ ብቻ ነበረ። እርግጥ ቻርተሩና ምናልባትም መቶ የሚያህሉ ተማሪዎች በስፍራው ነበሩት፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር ገና መሠራት ነበረበት። ይህ የወንድም ታፓን ደብዳቤ የተጻፈው፥ በኦበርሊን ልናገኘው የምንፈልገውን በሀድሰን እንዲገኝ ለማድረግ መሣሪያ መሆን እችላለሁ ብዬ እንዳላስብ እንድጠነቀቅ ለማድረግ ነበር።

ቤተሰቤን በክሊቭላንድ ትቼ፥ ፈረስና ባለ አራት ጎማ ቀላል ጋሪ ተከራይቼ፥ ወደ ሀድሰን ሳልሄድ ወደ ኦበርሊን መጣሁ። ቢያንስ ኦበርሊንን አስቀድሜ ማየት አለብኝ ብዬ አሰብሁ። ኢሊሪያ በደረስሁ ጊዜ፥ በማዕከላዊ ኒው ዮርክ የማውቃቸውን አንዳንድ የቀድሞ ወዳጆች በዚያ አገኘሁ። እነርሱም የዌስተርን ሪዘርቭ ኮሌጅ ባለአደራዎች እኔን በሀድሰን እንድገኝ ማድረግ ከቻሉ ቢያንስ በአብዛኛው ኦበርሊንን እንደሚያሸንፉ እንዳሰቡ፥ በሀድሰንም አመለካከታቸውንና አካሄዳቸውን እንድቀበል ሊያስገድደኝ የሚችል በቂ ኃይል ያለው የአሮጌው ትምህርት ቤት ተጽዕኖ እንደ ነበረ ነገሩኝ። ይህም ከአቶ ታፓን ከደረሰኝ መረጃ ጋር ቃል በቃል የሚስማማ ነበር።

ወደ ኦበርሊን መጣሁ፤ በዚህ በምዕራብ ኮሌጅ በማቋቋም ረገድ ለሚገኝ ስኬት ሁሉ መሠረት ናቸው ብዬ ባሰብኋቸው መርሆች ላይ ብቻ ሳይሆን፥ የኦበርሊን ኮሌጅን የመደገፍና የማሳደግ ኃላፊነት የወሰዱት ሰዎች ልብ እንደሚወዳቸው በማውቃቸው የተሐድሶ መርሆች ላይ ኮሌጅ እንዳይገነባ የሚከለክል ምንም ነገር እንደሌለ አየሁ። በስፍራው የነበሩት ወንድሞች ሥር ነቀል በሆኑ የተሐድሶ መርሆች ላይ የተመሠረተ ትምህርት ቤት እንዲገነባ በሙሉ ልባቸው ይደግፉ ነበር። ስለዚህ ግብዣቸውን እንዳልተቀበልሁ ለሀድሰን ባለአደራዎች ጻፍሁላቸው፤ መኖሪያዬንም በኦበርሊን አደረግሁ። ስለ ሀድሰን የምናገረው ክፉ ነገር አልነበረኝም፤ በእርሱም ላይ የማውቀው ክፉ ነገር አልነበረም።

ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመት በኋላ የአንቲኖሚያን ፍጽምና ትምህርት የሚል ጩኸት ተሰማ፤ ይህም ክስ በእኛ ላይ ቀረበ። ደብዳቤዎች ተጻፉ፤ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች ተጐበኙ፤ እዚህ ያለውን አመለካከታችንን ፈጽሞ የኑፋቄ አድርጎ ለማቅረብ ብዙ ድካም ተደረገ። በአገሪቱ ርዝመትና ስፋት ሁሉ ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች እንደዚህ ያሉ ገለጻዎች ስለ ቀረቡ፥ ብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናትን ከኦበርሊን ሥነ መለኮት ተጽዕኖ የሚያስጠነቅቁ ውሳኔዎችን አሳለፉ። በእኛ ላይ የአገልጋዮች ተጽዕኖ በአጠቃላይ የተባበረ ይመስል ነበር። ይህን ያስጀመረው ምን እንደ ሆነና ይህ ሁሉ ግርግር በምን መንገድ እንደ ተነሣ እዚህ በሚገባ እናውቅ ነበር። እኛ ግን ምንም አልተናገርንም። በእኛ ላይ እንደዚህ ያለ ብርቱ የሕዝብ አስተያየት ለማስነሣት እንደሚደክሙ ከምናውቃቸው ከእነዚያ ወንድሞች ጋር ምንም ክርክር አልነበረንም። ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ልገባ አልችልም፤ ነገር ግን በዚህ መንገድ በእኛ ላይ የተሠሩት የጦር ዕቃዎች በተጠቀሙባቸው ሰዎች ላይ እጅግ በሚያጠፋ ሁኔታ ተመለሱ ማለት ይበቃል፤ በመጨረሻም በሀድሰን የባለአደራዎቹ ቦርድና የመምህራኑ አባላት ከሞላ ጎደል ሁሉም ተለወጡ፤ የኮሌጁ አጠቃላይ አስተዳደርም በሌሎች እጅ ገባ።

በዚያን ጊዜም ሆነ በየትኛውም ጊዜ በኦበርሊን በሃድሰን ላይ የተነገረ ነገር ከቶ ሰምቼ አላውቅም ማለት ይቻላል። እኛ የራሳችንን ሥራ እንሠራ ነበር፤ ከዚያ ወገን የሚመጣውን ተቃውሞ በተመለከተም ኃይላችን ዝም ብሎ መቀመጥ እንደ ሆነ ተሰማን፤ አልተሳሳትንምም። እግዚአብሔር እንዲህ ያለው ተቃውሞ እንዲያሸንፍ የመፍቀድ ዕቅድ እንደሌለው እርግጠኞች ነበርን። ይህን በግልጽ እንዲረዱልኝ እወዳለሁ፤ የዚያ ኮሌጅ የአሁኑ መሪዎችና አስተዳዳሪዎች በዚያን ጊዜ ለተደረገው ነገር ያደሉ ወይም በዚያን ጊዜ የተወሰደውን አካሄድ እንኳ የሚያውቁ መሆናቸውን ፈጽሞ አላውቅም።

በቅርብም በሩቅም ያሉ አገልጋዮች ተቃውሞአቸውን እጅግ ጽንፍ ድረስ አደረሱት። በዚያን ጊዜ የምዕራቡን ትምህርትና የምዕራቡን ኮሌጆች መደገፍ ጉዳይ ለመመርመር በክሊቭላንድ እንዲሰበሰብ ጉባኤ ተጠራ። ጥሪው የተጻፈበት መንገድ እንዲህ ያለ ስለ ነበረ፥ በጉባኤው ሂደት ተካፋይ እንሆናለን ብለን በመጠበቅ ከኦበርሊን ወጣን። እዚያ በደረስን ጊዜ ዶ/ር ቢቸርን በስፍራው አገኘናቸው፤ የኦበርሊንን ወንድሞችና ለኦበርሊን የሚያደሉትን ከጉባኤው ለማግለል የሚያስችል አካሄድ እየተዘጋጀ እንደ ነበረም ብዙም ሳንቆይ አየን። ስለዚህ በጉባኤው ውስጥ እንደ አባል መቀመጫ አልተፈቀደልኝም፤ ቢሆንም በብዙዎቹ ስብሰባዎቹ ላይ ተገኘሁ። እዚያ ከነበሩት በአካባቢው ካሉት አገልጋዮች አንዱ የኦበርሊንን ትምህርቶችና ተጽዕኖ ከሮማ ካቶሊካዊነት ትምህርቶችና ተጽዕኖ የከፋ አድርጎ እንደሚቈጥራቸው በግልጽ ሲናገር መስማቴን አስታውሳለሁ።

ያ ንግግር የብዙዎችን አሳብ የሚወክል ነበር፤ የዚያም ጉባኤ አመለካከት በግምት ይኸው ይመስል ነበር። ይህን ስል ሁሉም እንደዚህ ነበሩ ማለቴ በፍጹም አይደለም። በኦበርሊን የሥነ መለኮት ትምህርት የተማሩና ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደዚያ የመጡ አንዳንዶች ከአብያተ ክርስቲያናቱና ከጉባኤው ጋር እንዲህ ያለ ግንኙነት ስለ ነበራቸው መቀመጫ ተሰጣቸው።

እነዚህ ሰዎች የኦበርሊን መርሆችና ተግባሮች ጥያቄ ውስጥ በገቡበት መጠን ስለ እነርሱ በግልጽና በድፍረት ተናገሩ። የጉባኤው ዓላማ ኦበርሊንን ከየአቅጣጫው አጥሮ መያዝና ማናቸውንም ድጋፍ በሚከለክል የሕዝብ አስተያየት እኛን ማድቀቅ እንደ ነበረ ግልጽ ነው። ነገር ግን ይህን በግልጽ እንዲረዱልኝ እወዳለሁ፤ የዚያን ጉባኤ አባላት፥ ወይም ከጥቂቶቹ በቀር፥ በምንም ዓይነት አልወቅሳቸውም፤ ተሳስተው እንደ ተመሩና ስለ እውነታው ፈጽሞ በተሳሳተ ግንዛቤ እንደሚሠሩ አውቅ ነበርና። የዚያ ጉባኤ ዋና መሪ ዶ/ር ላይማን ቢቸር ነበሩ።

የተከተልነው መመሪያ ተቃውሞውን ዝም ብሎ መተው ነበር። የራሳችንን ሥራ እንሠራ ነበር፤ ሁልጊዜም ልንይዛቸው ከምንችለው በላይ ብዙ ተማሪዎች ነበሩን። እጆቻችን ሁልጊዜ በሥራ የተሞሉ ነበሩ፤ በጥረታችንም ሁልጊዜ እጅግ እንበረታታ ነበር።

ይህ ጉባኤ ከተሰበሰበ ከጥቂት ዓመታት በኋላ፥ እዚያ ከነበሩት ዋና ዋና አገልጋዮች አንዱ መጥቶ በቤታችን አንድ ሁለት ቀን አሳለፈ። ከተናገረኝም ነገሮች መካከል እንዲህ አለኝ፦ «ወንድም ፊኒ፥ ኦበርሊን ለእኛ ታላቅ ድንቅ ነው።» ደግሞም እንዲህ አለ፦ «እኔ ለብዙ ዓመታት ከአንድ ኮሌጅ ጋር ከመምህራኑ እንደ አንዱ ሆኜ ተያይዤ ኖሬአለሁ። የኮሌጅ ሕይወትና መርሆች፥ ኮሌጆችም የሚገነቡባቸው ሁኔታዎች ለእኔ በጣም የታወቁ ናቸው። ኮሌጆች በአገልጋዮች ካልተደገፉ ሊኖሩ አይችሉም ብለን ሁልጊዜ እናስብ ነበር» አለ። «ወደ ኮሌጅ ለመግባት የተዘጋጁ ወጣቶች የትኞቹን ኮሌጆች እንደሚመርጡ በአብዛኛው እረኞቻቸውን እንደሚያማክሩና በፍርዳቸውም እንደሚመሩ እናውቅ ነበር። አሁን ግን» አለ፥ «አገልጋዮቹ ከሞላ ጎደል ሁሉም በኦበርሊን ላይ ተሰለፉ። በፀረ ሕግ ፍጹምነት ጩኸትና ስለ ተሐድሶ ባላችሁ አመለካከት ተታለሉ፤ በቅርብም በሩቅም ያሉ የቤተ ክርስቲያን አካላትም፥ ኮንግሪጌሽናልም ፕሪስባይቴሪያንም የሁሉም ቤተ እምነቶችም፥ ተባበሩ። አብያተ ክርስቲያናቶቻቸውን ከእናንተ እንዲጠበቁ አስጠነቀቁ፤ ወጣቶችንም በሙሉ ወደ ኦበርሊን እንዳይመጡ ተስፋ አስቈረጡ፤ ያም ሆኖ ጌታ ገንብቷችኋል። በምዕራብ ካሉት ኮሌጆች ከሞላ ጎደል ከማናቸውም በተሻለ በገንዘብ ተደግፋችኋል፤ እጅግ የሚበልጡ ተማሪዎችም ነበሯችሁ፤ የእግዚአብሔርም በረከት በእናንተ ላይ ስለ ነበረ ስኬታችሁ አስደናቂ ሆኗል። እንግዲህ» አለ፥ «ይህ በኮሌጆች ታሪክ ውስጥ ፍጹም ያልተለመደ ነገር ነው። የኦበርሊን ተቃዋሚዎች ግራ ተጋብተዋል፤ እግዚአብሔርም በዚህ ተቃውሞ ሁሉ ውስጥ ከጎናችሁ ቆሞ ደግፏችኋል፤ ስለዚህም ተቃውሞው በጭራሽ አልተሰማችሁም ማለት ይቻላል።»

ይህን ኮሌጅ በመጀመሪያ ባቋቋምን ጊዜ የገጠመንን ተቃውሞ ሰዎች አሁን መገንዘብ ያስቸግራቸዋል። ለምሳሌና እንደ ወኪል ጉዳይ እንዲሆን፥ ስለምናገርበት ጊዜ አካባቢ የተፈጸመን አንድ የሚያስቅ ነገር እተርካለሁ። በሰንበት ለመስበክ ወደ አክሮን መሄድ ነበረብኝ። በፈረስና በትንሽ ጋሪ ሄድሁ። በመንገዴ ላይ ከመዲና መንደር ባሻገር፥ ከፊቴ በመንገዱ ላይ አንዲት ሴት ትንሽ እሽግ በእጅዋ ይዛ ስትሄድ አየሁ። ወደ እርስዋ በቀረብሁ ጊዜ በዕድሜ የገፉ፥ በሚያምር ሁኔታ የለበሱ ሴት እንደ ሆኑ፥ ነገር ግን እንደ መሰለኝ ከዕድሜያቸው የተነሣ በተወሰነ ችግር እንደሚሄዱ ተመለከትሁ። ወደ እርሳቸው ስደርስ የፈረሴን ልጓም ሳብሁና በዚያ መንገድ ምን ያህል እንደሚሄዱ ጠየቅኋቸው። ነገሩኝ፤ ከዚያም በጋሪዬ ውስጥ መቀመጫ ተቀብለው ቢሳፈሩ እንደሆነ ጠየቅኋቸው። «ኦ» ብለው መለሱ፥ «ብሳፈር በጣም አመሰግናለሁ፤ በጣም ረጅም የእግር ጉዞ እንደ ጀመርሁ ተረድቻለሁና።» ወደ ጋሪዬ እንዲወጡ ረዳኋቸውና ጉዞዬን ቀጠልሁ። በጣም አስተዋይ ሴት፥ በንግግራቸውም በጣም ነጻና እንደ ቤተሰብ የሚቀርቡ ሆነው አገኘኋቸው።

ጥቂት ርቀት ከተጓዝን በኋላ፥ «ለዚህ ጉዞ ውለታ ያለብኝ ለማን እንደ ሆነ ልጠይቅ እችላለሁ?» አሉ። ማን እንደ ሆንሁ ነገርኋቸው። ከዚያም ከወዴት እንደ መጣሁ ጠየቁ። ከኦበርሊን እንደ ሆንሁ ነገርኋቸው። ይህ ዜና አስደነገጣቸው። ከእኔ በተቻላቸው መጠን ርቀው ለመቀመጥ የፈለጉ ይመስል ተንቀሳቀሱ፤ ዞረውም ትኵር ብለው እያዩኝ፥ «ከኦበርሊን! እንዴ» አሉ፥ «የእኛ እረኛ እኮ ልጅን ወደ መንግሥት እስር ቤት መላክና ወደ ኦበርሊን መላክ ለእርሳቸው አንድ እንደ ሆነ ተናግረዋል!» በእርግጥ ፈገግ አልሁና ፍርሃት ካደረባቸው የአሮጊቷን ፍርሃት አረጋጋሁ፤ ከእኔም ምንም አደጋ እንደማይደርስባቸው አስረዳኋቸው። ይህን የምተርከው ይህ ኮሌጅ በመጀመሪያ በተቋቋመ ጊዜ እጅግ በሰፊው ሰፍኖ የነበረውን መንፈስ ለማሳየት ብቻ ነው። የተሳሳተ ወሬና የተሳሳተ ግንዛቤ በየአቅጣጫው በዝቶ ነበር፤ እነዚህ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችም ከሞላ ጎደል እስከ ዩናይትድ ስቴትስ ማእዘናት ሁሉ ደርሰው ነበር።

ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ሲታይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በዚህ ተቃውሞ የማይታመኑ እጅግ ብዙ ምእመናንና ቍጥራቸው ቀላል ያልሆነ አገልጋዮች ነበሩ፤ እነርሱም ለዓላማዎቻችን፥ ለአመለካከቶቻችንና ለጥረቶቻችን ያደሉ፥ በክፉም በደጉም ከጎናችን ጸንተው የቆሙ ነበሩ፤ በዚህም ተቃውሞ ምክንያት ለጊዜው የደረስንበትን ጭንቀት ያውቁ ስለ ነበሩ፥ ወደፊት እንድንገፋ ሊረዱን ገንዘባቸውንና ተጽዕኖአቸውን በልግስና ሰጡ።

የፕሮቪደንሱ አቶ ቻፒን ቤተሰቤን የምደግፍበትን በዓመት ስድስት መቶ ዶላር ለብዙ ዓመታት ይልኩልኝ እንደ ነበረ ተናግሬአለሁ። ይህን ማድረግ ግዴታቸው እንደ ሆነ እስካሰቡበት ጊዜ ድረስ ካደረጉት በኋላ፥ — በእርግጥም የገንዘብ ችግር ከዚያ በላይ እንዲያደርጉት እስኪያዳግታቸው ድረስ አደረጉት፤ — የቦስተኑ አቶ ዊላርድ ሲርስ ስፍራቸውን ወሰዱ፤ አቶ ቻፒን ይከፍሉት የነበረውን ያንኑ መጠን በየዓመቱ ከእርሳቸው እንድወስድ ለብዙ ዓመታት ፈቀዱልኝ። እስከዚያው ድረስ ሌሎቹን የመምህራን ጉባኤ አባላት ለመደገፍ ዘወትር ጥረት ይደረግ ነበር፤ በእግዚአብሔርም ጸጋ ማዕበሉን አልፈን ተሻገርን። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ድንጋጤው በተወሰነ መጠን በረደ።

ፕሬዚዳንት ማሃን፥ ፕሮፌሰር ካውልስ፥ ፕሮፌሰር ሞርጋንና እኔ ስለ መቀደስ ጉዳይ ጽሑፎች አሳተምን። «ዘ ኦበርሊን ኢቫንጀሊስት» የተባለ ወቅታዊ መጽሔት፥ በኋላም «ዘ ኦበርሊን ኳርተርሊ» የተባለውን አቋቋምን፤ በእነዚህም ውስጥ እውነተኛ አመለካከቶቻችን ምን እንደ ሆኑ በተመለከተ የሕዝቡን የተሳሳተ ግንዛቤ በአብዛኛው አቃናን። በ1846 ስለ ሥርዓታዊ ሥነ መለኮት ሁለት ጥራዞች አሳተምሁ፤ በዚህም ሥራ ስለ ሙሉ መቀደስ ጉዳይ በሰፊው ተወያየሁ። ይህ ሥራ ከታተመ በኋላ የኒው ዮርክ የትሮይ ፕሪስባይተሪ ኮሚቴ ገመገመው። ከዚያም የፕሪንስተኑ ዶ/ር ሆጅ በ«ቢብሊካል ሪፐርቶሪ» ላይ በሥነ መለኮቴ ላይ ረጅም ትችት አሳተሙ። ይህ ከአሮጌው ትምህርት ቤት አመለካከት የተጻፈ ነበር።

ከዚያም በዲትሮይት የሚኖሩት የአዲሱ ትምህርት ቤት ፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን አባል ዶ/ር ዳፊልድ ከአዲሱ ትምህርት ቤት አመለካከት ነኝ ብለው ገመገሙኝ፤ ግምገማቸው ግን ወጥ ከሆነው የአዲሱ ትምህርት ቤት አስተምህሮ እጅግ የራቀ ነበር። ለእነዚህ ለተለያዩ ግምገማዎች በወጡበት ጊዜ መልስ አሳተምሁ፤ እኔ እስከማውቀውም ድረስ ላለፉት ብዙ ዓመታት የእምነታችንን ትክክለኛነት ለመንቀፍ የሚፈልግ ዝንባሌ አልታየም።

እስካሁን ድረስ በኦበርሊን ካለው ትምህርት ቤት መቋቋምና ትግሎች ጋር የተያያዙትን ዋና ዋና እውነታዎች፥ እኔ በእነርሱ በተሳተፍሁበት መጠን ተረክሁ። የሥነ መለኮት መምህሩ እኔ ስለ ነበርሁም፥ የሥነ መለኮቱ ተቃውሞ በተፈጥሮ በዋናነት ወደ እኔ ያነጣጠረ ነበር፤ ይህም ከዚህ ሁሉ ጋር ስለ ነበረኝ ግንኙነት በሌላ ሁኔታ ከምናገረው በበለጠ በነጻነት እንድናገር የግድ አድርጎኛል። ነገር ግን አሳቤ እንዳይሳሳት እወዳለሁ። እንዲህ የተቃወሙን ወንድሞች በተቃውሞአቸው ክፉዎች ነበሩ ብዬ አልከራከርም። አብዛኞቹ በእውነት ተሳስተው እንደ ተመሩና በዚያን ጊዜ እንደ ተረዱት የትክክለኛውን ነገር አመለካከታቸውን ተከትለው እንደ ሠሩ ጥርጥር የለውም።

ለእግዚአብሔር ጸጋ ክብር ይህን ማለት አለብኝ፤ የገጠመን ተቃውሞ ሁሉ በዚህ ያለውን መንፈሳችንን አላናወጠውም፥ ወደ ክርክር መንፈስ ወይም ወደ ክፉ ስሜት እስኪገፋፋን ድረስም አላወከንም። እነዚህ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች እንዲፈጠሩ የተደረገውን ጥረት በሚገባ እናውቅ ነበር፤ በተጠቃንበት መንፈስና መንገድ የተቃወሙን እንዴት እንደ ሆነም በቀላሉ ልንረዳ እንችል ነበር።

በእነዚያ የጭስና የአቧራ፥ ከውጭ የሚመጣ የተሳሳተ ግንዛቤና ተቃውሞ በበዛባቸው ዓመታት፥ ጌታ በውስጥ አብዝቶ ይባርከን ነበር። እዚህ እንደ ቤተ ክርስቲያን በነፍሳችን የበለጸግን ብቻ ሳንሆን፥ የማያቋርጥ መነቃቃት ነበረን፥ ወይም በትክክል የመነቃቃት ሁኔታ ሊባል በሚችል ሁኔታ ውስጥ ነበርን። ተማሪዎቻችን በብዙ ደርዘኖች ተለወጡ፤ ጌታም ዘወትር በምሕረቱ ደመና ጋረደን። የመለኮታዊ ተጽዕኖ ነፋሳት ከዓመት ወደ ዓመት በላያችን ነፈሱ፤ የመንፈስንም ፍሬ፥ «ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት»ን በብዛት አፈሩ።

በዚህ በጎ ሥራ ውስጥ ያገኘነውን ስኬት ሁልጊዜ ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ጸጋ ሰጥቻለሁ። ይህን ስኬት ያስገኘው የእኛ ጥበብ ወይም ቸርነት አልነበረም። በፈተናዎቻችን ውስጥ የደገፈንና በጀመርነው ሥራ ውጤታማ ልንሆን በምንችልበት የአእምሮ ሁኔታ ያቆየን ማኅበረሰቡን ሁሉ ሞልቶ የሚኖረው የማያቋርጥ መለኮታዊ ተጽዕኖ ብቻ ነበር። ጌታ መንፈሱን ቢከለክል ምንም ዓይነት ውጫዊ ሁኔታ በእውነት የበለጸግን ሊያደርገን እንደማይችል ሁልጊዜ ተሰምቶናል።

በመካከላችንም ፈተናዎች ነበሩብን። ለሕዝብ ውይይት የሚቀርቡ ጉዳዮች በተደጋጋሚ ተነሥተዋል፤ አንድ ዓይነት አሳብ ባልነበረን በታላላቅ የግዴታና የተገቢነት ጥያቄዎች ላይ ስንወያይ አንዳንድ ጊዜ ቀናትን፥ እንዲያውም ሳምንታትን አሳልፈናል። ነገር ግን ከእነዚህ ጥያቄዎች አንዳቸውም በቋሚነት አልከፋፈሉንም። መርሓችን አንዳችን ለሌላው የግል ፍርድ መብትን መስጠት ነበር። በተለያየንባቸው ጉዳዮች ላይ በአብዛኛው በመሠረቱ ወደ መስማማት ደርሰናል፤ አንድ ዓይነት አመለካከት መያዝ እንዳልቻልን ባገኘን ጊዜም ጥቂቶቹ ለብዙኀኑ ፍርድ ራሳቸውን አስገዝተዋል፤ በአንዳንድ ነገሮች አንድ ዓይነት አመለካከት መያዝ ስላልቻልን ብቻ ቤተ ክርስቲያንን መከፋፈል የሚለው አሳብ ከቶ በእኛ ዘንድ አልታሰበም። «በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት» እጅግ በከፍተኛ መጠን ጠብቀናል፤ ምናልባትም ለዚህን ያህል ረጅም ጊዜ የኖረና እኛ ባለፍንባቸው ዓይነት ፈተናዎችና ለውጦች ያለፈ፥ በአጠቃላይ ሲታይ ከእኛ የሚበልጥ የስምምነት፥ የክርስቲያናዊ ትዕግሥትና የወንድማማች ፍቅር መንፈስ የጠበቀ ማኅበረሰብ አልነበረም።

የሙሉ መቀደስ ጥያቄ በመጀመሪያ እዚህ ለሕዝብ ውይይት በተነሣ ጊዜ፥ ጉዳዩም በመጀመሪያ የቤተ ክርስቲያኒቱን አጠቃላይ ትኩረት በሳበ ጊዜ፥ በብርቱ መነቃቃት መካከል ነበርን። መነቃቃቱ በተስፋ በሚካሄድበት ጊዜ አንድ ቀን ፕሬዚዳንት ማሃን ልብን የሚመረምር ስብከት ሰብከው ነበር። በስብከታቸው ሂደት ውስጥ፥ በዚያ አገባብ ውስጥ ለእኔ እጅግ አስፈላጊ መስሎ የታየኝን አንድ ነጥብ ሳይነኩት እንደ ተዉት አስተዋልሁ። ስብከታቸውን ሲጨርሱ የምሰጠው አስተያየት ካለኝ ብዙ ጊዜ ይጠይቁኝ ነበር፤ በዚህም አጋጣሚ እንዲሁ አደረጉ። ተነሥቼ እርሳቸው የተዉትን ነጥብ አጥብቄ አቀረብሁ። ይህም በምኞትና በፈቃድ መካከል ያለው ልዩነት ነበር። ካቀረቡት የአሳብ ሂደትና በዚያን ጊዜ ጉባኤው በነበረበት ሁኔታ ተነሥቼ፥ ያን ልዩነት ልክ በዚያ ነጥብ ላይ በሕዝቡ ላይ አጥብቆ ማቅረብ፥ በእውነት ክርስቲያኖች መሆን አለመሆናቸውን፥ በእውነት ራሳቸውን የቀደሱ ሰዎች መሆናቸውን፥ ወይም እግዚአብሔርን ለመታዘዝ በእርግጥ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ምኞት ብቻ ያላቸው መሆናቸውን በሚመለከተው ጥያቄ ላይ ብዙ ብርሃን እንደሚፈነጥቅ አየሁ፥ ወይም ያየሁ መሰለኝ።

ይህ ልዩነት ልክ በዚያ አገባብ ግልጽ በተደረገ ጊዜ፥ መንፈስ ቅዱስ እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ በጉባኤው ላይ እንደ ወረደ አስታውሳለሁ። እጅግ ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ደፉ፤ አንዳንዶቹም በቤቱ ሁሉ እንዲሰሙ ሆነው አቃሰቱ። የተታለሉትን የእምነት መስካሪዎች የሐሰት ተስፋ በየአቅጣጫው ቈራረጠው። ብዙዎች በዚያው ቦታ ተነሥተው ተታልለው እንደ ነበረና በምን እንደ ተታለሉ ማየት እንደሚችሉ ተናገሩ፤ ይህም እኔን እጅግ እስኪያስደንቀኝ ድረስ ሄደ፤ በእርግጥም በጉባኤው ውስጥ አጠቃላይ የመደነቅ ስሜት የፈጠረ ይመስለኛል።

ሥራው በኃይል ቀጠለ፤ የቆዩ የእምነት መስካሪዎች አዲስ ተስፋ አገኙ፥ ወይም እንደ ገና ተለወጡ፤ ቍጥራቸውም እጅግ ብዙ ስለ ነበረ በማኅበረሰቡ ሁሉ ላይ እጅግ ታላቅና አስፈላጊ ለውጥ መጣ። ፕሬዚዳንት ማሃን ከሌሎች መካከል ከአንዳንድ መምህሮቻችን ጋር እጅግ ተባረኩ። በዚያን ጊዜ ፈጽሞ አዲስ ወደ ሆነ የክርስቲያናዊ ልምምድ ዓይነት በግልጽ ገቡ።

ከዚህ ከጥቂት ቀናት በኋላ በአንድ ስብሰባ ላይ ከሥነ መለኮት ተማሪዎቻችን አንዱ ተነሥቶ እንዲህ ሲል ጠየቀ፦ ወንጌል ለክርስቲያኖች የጸና እምነትን፥ ተስፋንና ፍቅርን ሁኔታዎች ሁሉ አያዘጋጅላቸውምን? ክርስቲያኖች በአብዛኛው ከተለማመዱት የሚሻልና ከፍ ያለ ነገር የለምን? ባጭሩ፥ መቀደስ በዚህ ሕይወት ሊገኝ አይችልምን? ይህም ማለት ክርስቲያኖች ያልተቋረጠ ሰላም ሊኖራቸውና ወደ ኵነኔ እንዳይገቡ፥ ወይም የኵነኔ ስሜት ወይም የኃጢአት ንቃት እንዳይኖራቸው በሚያስችል ትርጕም ያለ መቀደስ። ወንድም ማሃንም ወዲያውኑ «አዎን» ብለው መለሱ። በዚህ ስብሰባ ላይ የሆነው ነገር የመቀደስን ጥያቄ እንደ ተግባራዊ ጥያቄ በጉልህ በፊታችን አመጣው። በጉዳዩ ላይ ምንም ንድፈ አሳብ፥ የምንሟገትለትም ፍልስፍና አልነበረንም፤ ዝም ብለን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ ተቀበልነው።

በዚህ መልክ፥ ወደ ሥነ መለኮታዊ ቀመር ልንቀንሰው ያልሞከርነው የልምምድ እውነት ሆኖ በመካከላችን ነበረ፤ ፍልስፍናውንም ለማብራራት ከብዙ ዓመታት በኋላ ድረስ አልሞከርንም። ነገር ግን የዚህ ጥያቄ ውይይት ለእኛና አሁን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተበተኑት ወይም ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሚስዮናውያን ሆነው ለሄዱት ለብዙ ተማሪዎቻችን ታላቅ በረከት ነበር።

ቀዳሚ ቀጣይ