ምዕራፍ 18 · 26 ደቂቃ ንባብ · 34 ደቂቃ ማዳመጥ
በዊልሚንግተንና በፊላዴልፊያ የተደረጉ መነቃቃቶች
ባለፈው በጋ በኒው ሌባኖን እየሠራሁ ሳለ፥ አባታቸው በኒው ሌባኖን ይኖሩ የነበሩት የዴላዌሩ የዊልሚንግተን ቄስ አቶ ጊልበርት ሊጠይቁ ወደዚያ መጡ። አቶ ጊልበርት በሥነ መለኮት አመለካከታቸው እጅግ የአሮጌው ትምህርት ቤት ሰው ነበሩ፤ ቢሆንም ደግና ቅን ሰው ነበሩ። ለነፍሳት የነበራቸው ፍቅር በእርሳቸውና በእኔ መካከል በነበሩት ረቂቅ የሥነ መለኮት ልዩነት ጥያቄዎች ላይ የነበረውን ችግር ሁሉ አሸነፈው። በኒው ሌባኖን ስሰብክ ሰሙኝ፤ ፍሬውንም አዩ፤ ወደ ዊልሚንግተን መጥቼ እንዳግዛቸውም እጅግ አጥብቀው ለመኑኝ።
ስለዚህ ስቲቨንታውንን ለቅቄ ለመሄድ መንገዱ እንደ ተከፈተልኝ ባየሁ ጊዜ ወደ ዊልሚንግተን ሄድሁ፤ ከአቶ ጊልበርትም ጋር በሥራ ተሰማራሁ። ብዙም ሳይቆይ ትምህርታቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን አመለካከታቸው እስኪታረም ድረስ በመካከላቸው መነቃቃትን ማስፋፋት የማይቻልበት ሁኔታ ላይ እንዳስቀመጣት ተረዳሁ።
ሥራውን ከእግዚአብሔር እጅ እንዳይወስዱ በመፍራት ምንም ጥረት ለማድረግ የሚፈሩ ይመስሉ ነበር። ከአሮጌው ትምህርት ቤት የትምህርተ እምነት አመለካከቶች እጅግ አሮጌውን ይዘው ነበር፤ ስለዚህም ንድፈ ሐሳባቸው፥ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በራሱ ጊዜ ይለውጣቸዋል፤ ስለዚህም ፈጥነው ንስሐ እንዲገቡ ማሳሰብ፥ ባጭሩም መነቃቃትን ለማስፋፋት መሞከር፥ ሰዎችን በሰው ወኪልነትና በሰው ኃይል ክርስቲያኖች ለማድረግ መሞከር ነው፤ በዚህም ሥራውን ከእጁ በመውሰድ እግዚአብሔርን ማዋረድ ነው የሚል ነበር። ደግሞም በጸሎታቸው ውስጥ መንፈስ ፈጥኖ እንዲፈስስ የሚያሳስብ ጉጉት እንዳልነበረ፥ ይህም ሁሉ ካደጉበት አመለካከት ጋር የሚስማማ እንደ ሆነ አስተዋልሁ።
የአቶ ጊልበርት አመለካከት በዚህ ጉዳይ ላይ ካልተለወጠ በቀር ምንም ሊደረግ እንደማይችል ግልጽ ነበር። ስለዚህ ስለ ልዩ አመለካከታቸው ከእርሳቸው ጋር እየተነጋገርሁ በየቀኑ ሰዓታትን አሳለፍሁ። ጉዳዩን ሁሉ በወንድማዊ መንገድ ተወያየንበት፤ በዚህ መንገድ ከእርሳቸው ጋር ለሁለት ወይም ለሦስት ሳምንታት ከደከምሁ በኋላ፥ የራሴ አመለካከት በሕዝባቸው ፊት እንዲቀርብ አእምሮአቸው እንደ ተዘጋጀ አየሁ። በሚቀጥለው ሰንበት፦ «አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ለራሳችሁ አድርጉ፤ ስለ ምን ትሞታላችሁ?» የሚለውን ጥቅስ ለስብከቴ ወሰድሁ። ስለ ኃጢአተኛው ኃላፊነት በጥልቀት ገባሁበት፤ አዲስ ልብ ምን እንዳልሆነና ምን እንደ ሆነም አሳየሁ። ሁለት ሰዓት ያህል ሰበክሁ፤ በዚያም የጊዜ ርዝመት እጅግ ፈጣን አነጋገር በሚፈቅድልኝ መጠን ጉዳዩን ሁሉ በሚገባ እስክዳስሰው ድረስ አልተቀመጥሁም።
ጉባኤው እጅግ በብርቱ ተማረከ፤ በቤቱ ክፍል ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ተነሥተው በእግራቸው ቆሙ። ቤቱ ፈጽሞ ሞልቶ ነበር፤ በጉባኤውም ውስጥ እንግዳ የሆኑ ፊቶች ይታዩ ነበር። አንዳንዶቹ የተጨነቁና የተቈጡ ይመስሉ ነበር፤ ሌሎቹ እጅግ ተማርከው ነበር። በራሴ አመለካከትና እነርሱ በተማሩበት አመለካከት መካከል ያለውን ልዩነት አጥብቄ ባወጣሁ ጊዜ፥ ብዙ ጊዜ አንዳንዶቹ ይስቁ፥ አንዳንዶቹ ያለቅሱ፥ አንዳንዶቹም በግልጽ ይቈጡ ነበር፤ ነገር ግን ከቤቱ ወጥቶ የሄደ ሰው እንደ ነበረ አላስታውስም። እንግዳ የሆነ መናወጥ ነበር።
በዚህ መካከል አቶ ጊልበርት ከኋላዬ በመድረኩ ላይ ከሶፋው አንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ ይንቀሳቀሱ ነበር። ሲተነፍሱና ሲቃትቱ እሰማቸው ነበር፤ እርሳቸውም ራሳቸው በታላቅ ጭንቀት ውስጥ እንደ ነበሩ ከማስተዋል ልቈጠብ አልቻልሁም። ቢሆንም በኅሊናቸው እንደ ያዝኋቸው አውቅ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝባቸው የሚሉትን ለመቋቋም ቍርጥ ውሳኔ ያደርጉ እንደ ሆነ አላውቅም ነበር። እኔ ግን የምሰብከው ጌታን ደስ ለማሰኘት እንጂ ሰውን አልነበረም። ምናልባት በዚያ የምሰብከው የመጨረሻ ጊዜ ሊሆን ይችላል ብዬ አሰብሁ፤ ነገር ግን ውጤቱ ምንም ቢሆን፥ በምንም ሁኔታ በዚያ ጉዳይ ላይ እውነትን፥ እውነትንም ሁሉ ልነግራቸው ቈረጥሁ።
ሰው አመለካከታቸው እንደሚያቀርበው ያህል አቅመ ቢስ ቢሆን፥ በኃጢአቱ ተወቃሽ እንዳልሆነ ለማሳየት ጣርሁ። በአዳም ውስጥ የመታዘዝን ኃይል ሁሉ አጥቶ መታዘዝ የማይቻል ቢሆንበት፥ ይህም በራሱ ድርጊት ወይም ፈቃድ ሳይሆን በአዳም ድርጊት ቢሆን፥ ሊያስወግደው ባልቻለው ነገር ይወቀሳል ማለት ከንቱ ንግግር ብቻ ነው። ደግሞም እንደዚያ ከሆነ ማስተሰረያው ጸጋ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር የሰውን ልጆች እንዲህ ባለ አሳዛኝና ክፉ ዕድል ባለው ሁኔታ ውስጥ ስላስቀመጣቸው በእርሱ በኩል ለእነርሱ የሚገባ ዕዳ እንደ ሆነ ለማሳየት ጣርሁ። በእርግጥም ጌታ የአሮጌውን ትምህርት ቤት ልዩ ቀኖናዎችና የማይቀሩ ውጤቶቻቸውን ሊቋቋሙት በማይቻል ግልጽነት እንዳጋልጥ ረዳኝ ብዬ አስባለሁ።
በጨረስሁ ጊዜ አቶ ጊልበርትን እንዲጸልዩ አልጠራኋቸውም፤ ለማድረግ አልደፈርሁምና፤ ነገር ግን ጌታ ቃሉን ወደ ልብ እንዲያደርስ፥ እንዲያስረዳውም፥ የተነገረውንም ለመመዘን፥ እውነትን ለመቀበልና ስሕተት ሊሆን የሚችለውንም ለመጣል ቅን አእምሮ እንዲሰጥ ራሴ ጸለይሁ። ከዚያም ጉባኤውን አሰናበትሁ፤ አቶ ጊልበርትም ተከትለውኝ ከመድረኩ ደረጃዎች ወረድሁ። ጉባኤው እጅግ ቀስ ብሎ ወጣ፤ ብዙዎችም በቤቱ ክፍል ሁሉ ማለት ይቻላል ቆመው አንድ ነገር የሚጠብቁ ይመስሉ ነበር። መተላለፊያዎቹ በአብዛኛው ጸዱ፤ የቀረውም ጉባኤ የተነገረውን በተመለከተ ከአቶ ጊልበርት የሚሰሙ መስሏቸው በመጠባበቅ ሁኔታ የቆዩ ይመስሉ ነበር። ወይዘሮ ጊልበርት ግን ወዲያውኑ ወጡ።
ከመድረኩ ደረጃዎች ስወርድ፥ ልናልፍበት በሚገባን መተላለፊያ በግራ በኩል ተቀምጠው የነበሩ፥ ከዚህ ቀደም የተዋወቅኋቸውና የአቶ ጊልበርት የቅርብ ወዳጆችና ደጋፊዎች እንደ ሆኑ የማውቃቸው ሁለት ሴቶች አስተዋልሁ። በከፊል ያዘኑ፥ በከፊልም የተቈጡ፥ እጅግም የተደነቁ እንደሚመስሉ አየሁ። መጀመሪያ የደረስንባት፥ ከመድረኩ ደረጃዎች አጠገብ የነበረችው፥ አቶ ጊልበርት ከኋላዬ ሲከተሉ ያዘቻቸውና፦ «አቶ ጊልበርት፥ ስለዚህ ምን ያስባሉ?» አለቻቸው። በከፍተኛ ሹክሹክታ ተናገረች። እርሳቸውም በዚያው ዓይነት፦ «አምስት መቶ ዶላር ያወጣል» ብለው መለሱላት። ይህ እጅግ አስደሰተኝ፤ በጣምም ነካኝ። እርሷም፦ «እንግዲያስ ወንጌልን ፈጽሞ ሰብከው አያውቁም ማለት ነው» ብላ መለሰች። እርሳቸውም፦ «እንግዲህ፥ ፈጽሞ ሰብኬ አላውቅም ለማለት አዝናለሁ» አሉ። ወደ ፊት አለፍን፤ ከዚያም ሌላዪቱ ሴት ተመሳሳይ ነገር ነገረቻቸው፤ ተመሳሳይ መልስም አገኘች። ለእኔ ይህ በቂ ነበር፤ ወደ በሩ መንገዴን አድርጌ ወጣሁ። ቀድመው የወጡት ብዙዎቹ በቤቱ ፊት ለፊት ቆመው የተነገሩትን ነገሮች በብርቱ እየተከራከሩባቸው ነበር። ወደማርፍበት ወደ አቶ ጊልበርት ቤት ለመሄድ በመንገዶቹ ሳልፍ፥ መንገዶቹ በመናወጥና በክርክር ተሞልተው አገኘኋቸው። ሰዎቹ አመለካከታቸውን ያነጻጽሩ ነበር፤ ሳልፍም እኔን ካላስተዋሉኝ ሰዎች አፍ ካመለጡት ጥቂት ቃላት፥ ስሜቱ የተነገረውን በቍርጥ የሚደግፍ እንደ ነበረ አየሁ።
ወደ አቶ ጊልበርት ቤት በደረስሁ ጊዜ፥ ገና እንደ ገባሁ ሚስታቸው፦ «አቶ ፊኒ፥ እንዴት ያለውን ነገር በመድረካችን ለመስበክ ደፈሩ?» ብለው ተናገሩኝ። እኔም፦ «ወይዘሮ ጊልበርት፥ ሌላ ምንም ነገር ለመስበክ አልደፈርሁም፤ የእግዚአብሔር እውነት ነውና» ብዬ መለስሁ። እርሳቸውም እንዲህ ብለው መለሱ፦ «እንግዲህ፥ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ማስተሰረያ ሊያደርግ በፍትሕ የታሰረ እንደ ነበረ እውነት ነው። ለመናገር ባልደፍርም ሁልጊዜ ይሰማኝ ነበር። አቶ ጊልበርት የሚሰብኩት ትምህርት እውነት ከሆነ፥ እግዚአብሔር ማስተሰረያ ሊያደርግ፥ ራሴን ልረዳ ከማልችልበት ሁኔታና ካልተገባኝ ፍርድ ሊያድነኝ በፍትሕ ረገድ ግዴታ እንዳለበት አምን ነበር።» ልክ በዚህ ጊዜ አቶ ጊልበርት ገቡ። እኔም፦ «እነሆ፥ ወንድም ጊልበርት፥ የስብከትዎን ፍሬ እዚሁ በገዛ ቤተሰብዎ ውስጥ ያያሉ» አልሁ፤ ከዚያም ሚስታቸው አሁን የተናገሩትን ደግሜ ነገርኋቸው። እርሳቸውም፦ «አንዳንድ ጊዜ ሚስቴ ካወቅኋቸው ሴቶች ሁሉ እጅግ ጽኑ ሃይማኖተኞች ከሆኑት አንዷ እንደ ሆነች አስባለሁ፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ምንም ሃይማኖት የላትም ብዬ አስባለሁ» ብለው መለሱ። እኔም፦ «ምነው! እግዚአብሔር በክርስቶስ የተዘጋጀውን መዳን በፍትሕ ረገድ ዕዳ እንዳለበት ሁልጊዜ ስታስብ ኖራለች፤ እንዴት ክርስቲያን ልትሆን ትችላለች?» ብዬ ጮኽሁ። ይህ ሁሉ በሁለታችንም በታላቅ ጭምትነትና አጥብቆ በመፈለግ ተነገረ። የመጨረሻውን ቃል በተናገርሁ ጊዜ ተነሥተው ከክፍሉ ወጡ። ቤቱ እጅግ ጭምት ሆነ፤ ለሁለት ቀንም ያህል ያላየኋቸው ይመስለኛል። ከዚያም በእውነቱ ብቻ ሳይሆን በገዛ አእምሮአቸውም ሁኔታ ግልጽ ሆነው ወጡ፤ በአመለካከትና በልምምድ ፍጹም ለውጥ ውስጥ አልፈው ነበርና።
ከዚህ ነጥብ ጀምሮ ሥራው ወደ ፊት ገፋ። እውነቱ በመንፈስ ቅዱስ እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተሠራ። የአቶ ጊልበርት አመለካከት እጅግ ተለወጠ፤ የስብከት ስልታቸውና ወንጌልን የሚያቀርቡበት መንገድም እንዲሁ። እኔ እስከማውቀው ድረስ እስከ ሞቱበት ቀን አመለካከታቸው እንደ ታረመ ቈየ፤ ይኸውም ቀድሞ ይዘውት ከነበረው ከአሮጌው ትምህርት ቤት አመለካከት በተቃራኒ የአዲሱ ትምህርት ቤት አመለካከት ነበር።
ይህ ስብከት በብዙዎቹ የአቶ ጊልበርት ቤተ ክርስቲያን አባላት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እጅግ ልዩ ነበር። ስለ እርሱ ምን እንደሚያስቡ ስለ ጠየቀቻቸው ሴት ተናግሬአለሁ። እርሷ ከጊዜ በኋላ ስለ ሃይማኖት የነበራት አመለካከት ሁሉ እንዲህ እንደ ተገለበጠ በማሰቧ እጅግ ተቈጥታ ስለ ነበር፥ ዳግመኛ ፈጽሞ እንዳትጸልይ ለራሷ ቃል እንደ ገባች ነገረችኝ። ከኃጢአተኛ ባሕርይዋ የተነሣ ራሷን እስከዚያ ድረስ የማጽደቅ ልማድ ነበራት፤ በአእምሮዋም ወይዘሮ ጊልበርት ይዘውት የነበረውን የመሰለ አቋም ይዛ ስለ ነበር፥ በዚያ ጉዳይ ላይ የሰበክሁት ስብከት አመለካከቷን፥ ሃይማኖቷንና ሁሉን ፈጽሞ ገለበጠው። በትክክል የማስታውስ ከሆነ ዳግመኛ ከመጸለይዋ በፊት ለስድስት ሳምንት ያህል በዚህ የዓመፅ ሁኔታ ቈየች። ከዚያም ተሰበረች፤ በአመለካከቷና በሃይማኖታዊ ልምምዷም ፈጽማ ተለወጠች። የዚያች ቤተ ክርስቲያን ብዙ ሰዎችም ሁኔታ እንዲሁ እንደ ነበረ አምናለሁ።
በዚህ መካከል በሳምንት ሁለት ጊዜ ወደ ፊላዴልፊያ ሄጄ ለአቶ ፓተርሰን እንድሰብክ ተገፋፍቼ ነበር። በእንፋሎት መርከብ ወጥቼ በምሽት እሰብክ ነበር፤ በማግሥቱም ተመልሼ በዊልሚንግተን እሰብክ ነበር፤ በዚህም የምሽት አገልግሎቶቼን በዊልሚንግተንና በፊላዴልፊያ መካከል እያፈራረቅሁ ነበር። ርቀቱ አርባ ማይል ያህል ነበር። ቃሉ በፊላዴልፊያ እጅግ ከመሥራቱ የተነሣ፥ በዊልሚንግተን ያለውን ሥራ አቶ ጊልበርት እንዲቀጥሉት ትቼ ጊዜዬን ሁሉ በፊላዴልፊያ ለመሥራት መስጠት ግዴታዬ እንደ ሆነ አሳመነኝ።
በፊላዴልፊያ መጀመሪያ አብሬአቸው የሠራሁት ቄስ ጄምስ ፓተርሰን በዚያን ጊዜ በፕሪንስተን ይያዝ የነበረውን፥ ከጊዜ በኋላም የአሮጌው ትምህርት ቤት ፕሪስባይቴሪያኖች ሥነ መለኮት ተብሎ የታወቀውን የሥነ መለኮት አመለካከት ይዘው ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰው ነበሩ፤ ስለ ችሎታና ስለ አለመቻል ከሚነሡ ረቂቅ ጥያቄዎች፥ ወይም የአሮጌውና የአዲሱ ትምህርት ቤት ፕሪስባይቴሪያኖች ከሚለያዩባቸው ከእነዚያ የትምህርተ እምነት ነጥቦች ከማናቸውም ይልቅ ስለ ነፍሳት መዳን እጅግ አብልጠው ይጨነቁ ነበር። ሚስታቸው የኒው ኢንግላንድን የሥነ መለኮት አመለካከት ይዘው ነበር፤ ይኸውም ከውሱን ማስተሰረያ በተቃራኒ ሁሉን አቀፍ ማስተሰረያን ያምኑ ነበር፤ ከፕሪንስተን ቀጥተኛ እምነት ተለይቶ የኒው ኢንግላንድ ቀጥተኛ እምነት ተብሎ ከሚጠራውም ጋር ይስማሙ ነበር።
በዚህ ጊዜ እኔ ራሴ የፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን አባል እንደ ነበርሁ ይታወሳል። በአብዛኛው በፕሪንስተን የተማሩ ሰዎች ባሉበት ፕሪስባይተሪ ፈቃድ ተሰጥቶኝ ተሾምሁ። ደግሞም ወንጌልን ለመስበክ ፈቃድ በተሰጠኝ ጊዜ፥ የፕሪስባይቴሪያንን የእምነት መግለጫ የክርስቲያን ትምህርት ፍሬ ነገርን እንደያዘ አድርጌ እቀበለው እንደ ሆነ እንደ ተጠየቅሁ ተናግሬአለሁ። እስከ ተረዳሁት ድረስ እንደምቀበለው መለስሁ። ነገር ግን እንዲህ ያለ ጥያቄ ይቀርብልኛል ብዬ ስላልጠበቅሁ፥ ፈጽሞ በጥንቃቄ መርምሬው አላውቅም ነበር፤ ከዳር እስከ ዳር ያነበብሁትም አይመስለኝም። የእምነት መግለጫውን ወደ ማንበብና ወደ ማሰላሰል በመጣሁ ጊዜ ግን፥ አሁን እጅግ ብዙ ፕሪስባይቴሪያኖች እንደሚያደርጉት እንደማውቀው፥ የክርስቲያን ትምህርት ፍሬ ነገርን እንደያዘ አድርጌ ልቀበለው ብችልም፥ በፕሪንስተን የተሰጣቸውን ትርጓሜ ልሰጣቸው የማልችላቸው ብዙ ነጥቦች እንዳሉ አየሁ፤ ስለዚህም በየቦታው ያንን ትርጓሜ እንደማልቀበል፥ ወይም ያ እውነተኛው ትርጓሜ ከሆነ ከእምነት መግለጫው ፈጽሞ እንደምለይ ለሕዝቡ አስረዳሁ። አቶ ፓተርሰን ከእርሳቸው ጋር ለመሥራት ከመሄዴ በፊት ይህን ተረድተውት ነበር ብዬ አስባለሁ፤ በመድረካቸው ያንን መንገድ በተከተልሁ ጊዜ ምንም መደነቅ አላሳዩምና። በእርግጥም ፈጽሞ አልተቃወሙትም።
መነቃቃቱ በጉባኤያቸው ውስጥ እጅግ ሥር ሰድዶ እርሳቸውን እጅግ እስኪማርካቸው ድረስ ደረሰ፤ እኔ ባቀረብሁት መንገድ እግዚአብሔር ቃሉን እንደሚባርክ ባዩ ጊዜ፥ ከጎኔ በጽናት ቆሙ፤ ባቀረብሁትም በማናቸውም ነገር ላይ በምንም ሁኔታ ተቃውሞ አላነሡም። አንዳንድ ጊዜ ከስብሰባ ስንመለስ ወይዘሮ ፓተርሰን ፈገግ ብለው፦ «አቶ ፓተርሰን፥ እንግዲህ ብዙ ጊዜ በተነጋገርንባቸው በእነዚያ ነጥቦች ላይ አቶ ፊኒ ከእርስዎ ጋር እንደማይስማሙ ያያሉ» ይሉ ነበር። እርሳቸውም በክርስቲያናዊ እምነታቸውና በፍቅራቸው ታላቅነት ሁልጊዜ፦ «እንግዲህ፥ ጌታ ይባርከዋል» ብለው ይመልሱ ነበር።
ፍላጎቱ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ ጉባኤዎቻችን በየስብሰባው ጢም ብለው ይሞሉ ነበር። አንድ ቀን አቶ ፓተርሰን፦ «ወንድም ፊኒ፥ በዚህች ከተማ ያሉት የፕሪስባይቴሪያን አገልጋዮች አመለካከትዎንና ለሕዝቡ የሚሰብኩትን ቢያውቁ፥ ተኵላን እንደሚያባርሩ ከከተማይቱ ያሳድዱዎታል» አሉኝ። እኔም እንዲህ ብዬ መለስሁ፦ «ምንም ማድረግ አልችልም። ሌላ ትምህርት መስበክ አልችልም፤ ከከተማይቱ ሊያስወጡኝ ግድ ከሆነባቸው ያድርጉት፤ ኃላፊነቱንም ይውሰዱ። ነገር ግን ሊያስወጡኝ ይችላሉ ብዬ አላምንም።»
ይሁን እንጂ አገልጋዮቹ እርሳቸው የተነበዩትን መንገድ በምንም ዓይነት አልተከተሉም፤ ይልቁንም ሁሉም ማለት ይቻላል ወደ መድረኮቻቸው ተቀበሉኝ። በአቶ ፓተርሰን ቤተ ክርስቲያን የሚሆነውን፥ ብዙዎቹም የራሳቸው ቤተ ክርስቲያን አባላት እጅግ እንደ ተማረኩ ባወቁ ጊዜ፥ እንድሰብክላቸው ጋበዙኝ፤ በትክክል የማስታውስ ከሆነም በአርች ስትሪት ካለው ቤተ ክርስቲያን በቀር በፕሪስባይቴሪያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሰበክሁ።
በዚያን ጊዜ ፊላዴልፊያ በፕሪንስተን በሚያዘው የሥነ መለኮት አመለካከት ረገድ አንድ ማለት ይቻል ነበር። ዶ/ር ስኪነር ከጊዜ በኋላ የአዲሱ ትምህርት ቤት አመለካከት ተብሎ የታወቀውን በተወሰነ መጠን ይዘው ነበር፤ በዙሪያቸው ከነበረው የሥነ መለኮት ቃና በበቂ ሁኔታ ይለዩ ስለ ነበር፥ በሰፈነው ቀጥተኛ እምነት መሠረት ፈጽሞ ጤናማ እንዳልሆኑ ይጠረጠሩ ነበር። እኔ እስከማውቀው ድረስ የትምህርተ እምነት አመለካከቴ በዚያች ከተማ የመሰናከያ ድንጋይ አለመሆኑ፥ ቀጥተኛ እምነቴም በማናቸውም አገልጋዮች ወይም አብያተ ክርስቲያናት በግልጽ አለመጠየቁ ሁልጊዜ እጅግ አስደናቂ ነገር ሆኖ ይታየኛል። በደች ቤተ ክርስቲያን ለዶ/ር ሊቪንግስተን ጉባኤ ሰበክሁ፤ እርሳቸውም ከአመለካከቴ ጋር እንደሚስማሙ፥ ጌታ የነገረኝንም ስብከት እየሰበክሁ እንድቀጥል በተጽዕኖአቸው ሁሉ እንዳበረታቱኝ አገኘሁ። በየቦታውና በየአጋጣሚው የራሴን የሥነ መለኮት አመለካከት፥ በየቦታውም ለአብያተ ክርስቲያናት ሳቀርበው የነበረውን ለማቅረብ አላመነታሁም።
አቶ ፓተርሰን ራሳቸው ከሥነ መለኮት አመለካከቴ የተነሣ ከአገልጋዮቹ ወይም ከአብያተ ክርስቲያናቱ ግልጽ ተቃውሞ ስላልገጠመኝ እጅግ የተደነቁ ይመስለኛል። በእርግጥም አመለካከቴን ፈጽሞ በክርክር መንገድ አላቀረብሁትም፤ ይልቁንም ለቅዱሳንና ለኃጢአተኞች በምሰጠው ትምህርት ውስጥ እንዲሁ በተፈጥሮአዊ መንገድ ተጠቀምሁበት፤ ስለዚህም ምናልባት ልዩነትን ከሚለዩ የሥነ መለኮት ሊቃውንት በቀር ብዙ ትኵረት አልሳበም። ነገር ግን የተናገርኋቸው ብዙ ነገሮች ለሕዝቡ አዲስ ነበሩ። ለምሳሌ አንድ ምሽት በዚህ ጥቅስ ላይ ሰበክሁ፦ «አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፥ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ።» ይህ ስለ ማስተሰረያ የተሰበከ ስብከት ነበር፤ በእርሱም ስለ ባሕርዩና ስለ ሁሉን አቀፍነቱ ሁልጊዜ የያዝሁትን አመለካከት ወሰድሁ፤ በራሴ አመለካከትና ውሱን ማስተሰረያን በሚያምኑ የሥነ መለኮት ሊቃውንት በተያዘው አመለካከት መካከል ያሉትን የልዩነት ነጥቦች በተቻለኝ መጠን አጥብቄ ገለጽሁ። ይህ ስብከት እጅግ ብዙ ትኵረት ስለ ሳበና እጅግ ብዙ ፍላጎት ስለ ቀሰቀሰ፥ በዚሁ ጉዳይ ላይ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እንድሰብክ አጥብቀው ለመኑኝ። በእርሱ ላይ በሰበክሁ መጠን ሕዝቡ ለመስማት ይበልጥ ይጓጓ ነበር፤ መናወጡም እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሣ በዚያ ጉዳይ ላይ በተከታታይ ሰባት የተለያዩ ምሽቶች በሰባት የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ሰበክሁ።
ሕዝቡ ሆፕኪንሳዊነት ተብሎ በሚጠራው ላይ ብዙ ተቃውሞ የሰሙ ይመስል ነበር፤ የእርሱም ሁለቱ ታላላቅ ነጥቦች፥ ሰው ለእግዚአብሔር ክብር ሲል ለመኰነን ፈቃደኛ መሆን ይገባዋል፥ እግዚአብሔርም የኃጢአት ደራሲ ነው የሚሉ እንደ ሆኑ ይታወቁ ነበር። በስብከቴ አንዳንድ ጊዜ እነዚህን ነጥቦች አነሣሁ፤ ሆፕኪንሳዊነትንም ለማውገዝ አጋጣሚውን ተጠቀምሁ፤ በፊላዴልፊያም ከእርሱ እጅግ ብዙ ያላቸው እንደሚመስሉ ተናገርሁ፤ ስለ ነፍሶቻቸው መዳን ለመጨነቅ ያላቸው ታላቅ ቸልተኝነት ለመኰነን ፈቃደኞች እንደ ሆኑ የሚያሳይ እጅግ እንደሚመስል፥ ተፈጥሮአችን ኃጢአተኛ ነው ብለው ስለሚያምኑም እግዚአብሔር የኃጢአት ደራሲ ነው ብለው ማመን ግድ እንደሚሆንባቸው ተናገርሁ። ይህን ደጋግሜ አገላበጥሁት፤ በእነዚህም ሁለት ነጥቦች ላይ አተኰርሁ። ሕዝቡ፦ «እንግዲህ፥ እርሱ ሆፕኪንሳዊ አይደለም» እንዳሉ ደጋግሜ ሰማሁ። በእርግጥም የኃጢአተኞችን መሸሸጊያዎች ሁሉ ማጋለጥ፥ ተመሽገውባቸው ካገኘኋቸው ከእነዚያ ልዩ የቀጥተኛ እምነት አመለካከቶች ሥርም አድኜ ማውጣት ግዴታዬ እንደ ሆነ ተሰማኝ።
መነቃቃቱ ተስፋፋ፤ በብርቱም ሥር ሰደደ። ለስብከት፥ ለጸሎትና ለጥያቄ የምናደርጋቸው ስብሰባዎቻችን ሁሉ ተጨናንቀው ነበር። በሚገባ ልንከታተላቸው ከምንችለው እጅግ የሚበልጡ ጠያቂዎች ነበሩ። በፊላዴልፊያ ማረፊያዬን የያዝሁት በመከር መገባደጃ ላይ ነበር፤ እስከሚቀጥለው ኦገስት 1828 ድረስም ያለ ምንም ማቋረጥ በዚያ መሥራቴን ቀጠልሁ።
እንደ ሌሎቹ ስፍራዎች ሁሉ፥ ከግለሰቦች በኩል እጅግ መራራ ተቃውሞ የታየባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ነበሩ። በአንዱ ሁኔታ፥ ሚስቱ በኃጢአት እጅግ የተወቀሰችበት አንድ ሰው እጅግ ተቈጥቶ ገባና ሚስቱን በኃይል ከስብሰባ አውጥቶ ወሰዳት። ሌላውን ሁኔታ እጅግ አስደናቂ እንደ ሆነ አስታውሰዋለሁ፤ ይህም ስሙን አሁን ማስታወስ የማልችለው የአንድ ጀርመናዊ ነው። ትንባሆ ሻጭ ነበር። እጅግ ተወዳጅና አስተዋይ ሚስት ነበረችው፤ እርሱም ራሱ ከጊዜ በኋላ ስተዋወቀው እንዳገኘሁት አስተዋይ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ተጠራጣሪ ነበር፤ በሃይማኖትም ላይ ምንም እምነት አልነበረውም። ሚስቱ ግን ወደ ስብሰባዎቻችን መጣች፤ ስለ ነፍሷም እጅግ ተጨነቀች፤ ለብዙ ቀናትም ከከባድ ትግል በኋላ ፈጽማ ተለወጠች። ብዙ ጊዜ ስብሰባዎችን ስለምትካፈልና እጅግ ስለ ተማረከች፥ ብዙም ሳይቆይ የባሏን ትኵረት ሳበ፤ እርሱም ክርስቲያን መሆኗን ይቃወም ጀመር። እንደ ተረዳሁት ቍጡ ሰው ነበር፤ ብርቱ አካል ያለውና ታላቅ ቍርጠኝነትና የዓላማ ጽናት ያለው ሰው ነበር። ሚስቱ ይበልጥ እየተማረከች ስትሄድ ተቃውሞው እየጨመረ ሄደ፤ በመጨረሻም ከዚያ ወዲያ ወደ ስብሰባዎች እንዳትሄድ ከለከላት።
ከዚያም ልታየኝ መጣች፤ የትኛውን መንገድ መከተል እንዳለባትም ምክሬን ጠየቀችኝ። የመጀመሪያ ግዴታዋ ለእግዚአብሔር እንደ ሆነ፥ ትእዛዛቱ ከባሏ ትእዛዛት ጋር ቢጋጩ እንኳ ትእዛዛቱን የመታዘዝ ግዴታ ያለባት መሆኑ ጥርጥር እንደሌለው ነገርኋት፤ የምትችል ከሆነ እርሱን ከማስቀየም እንድትጠነቀቅና ለእግዚአብሔር ያለባትን ግዴታ እንድትፈጽም ብመክራትም፥ ፈቃዱን ለመፈጸም ብላ ለእግዚአብሔር ያለባት ግዴታ ነው ብላ የምታምነውን በምንም ሁኔታ እንዳትተው ነገርኋት። እርሱ የማያምን ሰው ስለ ሆነ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ያለው አስተያየት ሊከበር እንደማይገባና ምክሩን ያለ ስጋት ልትከተል እንደማትችል ነገርኋት። ይህን በሚገባ ታውቅ ነበር። እርሱ ሃይማኖትን ከመቃወም በቀር ምንም ትኵረት የማይሰጠው ሰው ነበር።
በምክሬ መሠረት አጋጣሚ ባገኘች ቍጥር ስብሰባዎችን ተካፈለች፤ ትምህርትም ተቀበለች፤ ብዙም ሳይቆይ ወደ ወንጌል ነጻነት ገባች፤ ታላቅ እምነትና የአእምሮ ሰላም አገኘች፤ የእግዚአብሔርንም ሀልዎት አብዝታ ተደሰተችበት።
ይህ ባሏን እጅግ አስቈጣው፤ በመጨረሻም ዳግመኛ ወደ ስብሰባ ብትሄድ ሕይወቷን እንደሚያጠፋ እስከ መዛት ደረሰ። ብዙ ጊዜ ተቈጥቶ ስላየችው ዛቻውን ይፈጽማል የሚል እምነት አልነበራትም። ምንም ቢያስከፍላት ለእግዚአብሔር ያለባትን ግዴታ ለመፈጸም ቍርጥ ውሳኔ እንዳደረገች፥ የሚያስፈልጋትን ትምህርት ለማግኘት አጋጣሚውን መጠቀም ግዴታዋ እንደ ሆነ እንደሚሰማት፥ ለቤተሰቧ ያለባትን ግዴታ ሳትዘነጋ በቻለች ቍጥርም በእነዚያ ስብሰባዎች መገኘት እንዳለባት በእርጋታ ነገረችው።
አንድ የሰንበት ምሽት ወደ ስብሰባ ልትሄድ እንደ ሆነ ባወቀ ጊዜ፥ ብትሄድ ሕይወቷን እንደሚያጠፋ ዛቻውን አደሰ። ከንቱ ዛቻ እንጂ ሌላ ነገር ነው ብላ ፈጽሞ እንዳላሰበች ከጊዜ በኋላ ነገረችኝ። ግዴታዋ ግልጽ እንደ ሆነ፥ ምክንያት የሌለውን ፍላጎቱን ከመፈጸም በቀር በዚያን ጊዜ በቤት የምትቀርበት ምንም ምክንያት እንደሌለ፥ በእንዲህ ያለ ሁኔታ በቤት መቅረትም ለእግዚአብሔርና ለራሷ ካለባት ግዴታ ጋር ፈጽሞ የማይስማማ እንደሚሆን በእርጋታ መለሰችለት። ስለዚህ ወደ ስብሰባ ሄደች። ከስብሰባ በተመለሰች ጊዜ በታላቅ ቍጣ ውስጥ አገኘችው። በሩን እንደ ገባች ከኋላዋ ቈለፈው፤ ቍልፉንም አወጣው፤ ከዚያም ጩቤ መዝዞ ሕይወቷን እንደሚያጠፋ ማለ። ወደ ላይ ደረጃውን ሮጣ ወጣች። ሊከተላት መብራት አነሣ። ሠራተኛዪቱ ልጅ በአጠገቧ ሲያልፍ መብራቱን እፍ ብላ አጠፋችው። ይህም ሁለቱንም በጨለማ ውስጥ ተዋቸው። እርሷ ወደ ላይ ሮጣ በሁለተኛው ፎቅ ክፍሎች ውስጥ አለፈች፤ ወደ ማድቤቱ፥ ከዚያም ወደ ምድር ቤቱ መንገዷን አገኘች። እርሱ በጨለማ ሊከተላት አልቻለም፤ እርሷም በምድር ቤቱ መስኮት ወጥታ ወደ አንድ ወዳጇ ቤት ሄደች፤ ሌሊቱንም በዚያ አሳለፈች።
እስከ ጠዋት ድረስ በቍጣው ያፍራል ብላ በመገመት በማለዳ ወደ ቤት ሄደች፤ ወደ ቤቱም ገባች፤ ነገሮችንም እጅግ ተመሰቃቅለው አገኘች። አንዳንድ የቤት ዕቃዎችን ሰባብሮ ነበር፤ እንደ ዕብድ ሰውም ሆኖ ነበር። ወደ ቤቱ በሚገባ እንደ ገባች እንደ ገና በሩን ቈለፈው፤ ጩቤም መዝዞ በጕልበቱ ተንበርክኮ እጆቹን አነሣ፤ በዚያው ሕይወቷን እንደሚያጠፋም እጅግ የሚያስፈራ መሐላ ማለ። በመደነቅ ተመለከተችውና ሸሸች። ደረጃውን ሮጣ ወጣች፤ ነገር ግን ብርሃን ነበርና ተከተላት። ከክፍል ወደ ክፍል ሮጠች፤ በመጨረሻም ማምለጫ ወደሌለበት ወደ መጨረሻው ክፍል ገባች። ዘወር ብላ ፊት ለፊት ገጠመችው። በጩቤው ሊወጋት ሲል በጕልበቷ ተንበረከከች፤ እጆቿንም ወደ ሰማይ አንሥታ ለራሷና ለእርሱ ምሕረትን ለመነች። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ያዘው። ለአፍታ እንደ ተመለከታት፥ ጩቤውን እንደ ጣለ፥ በወለሉም ላይ ወድቆ እርሱ ራሱ ምሕረትን እንደ ለመነ ተናገረች። በዚያው ስፍራና በዚያው ቅጽበት ተሰበረ፤ ኃጢአቱን ለእግዚአብሔርና ለእርሷ ተናዘዘ፤ እግዚአብሔርንና እርሷንም ይቅር እንዲሉት ለመነ።
ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ በሚያስደንቅ ሁኔታ የተለወጠ ሰው ሆነ። እጅግ በቅንዓት ከተሞሉ ክርስቲያን አማኞች አንዱ ሆነ። ከእኔ ጋር እጅግ ተቈራኘ፤ ከዚህ በኋላ አንድ ወይም ሁለት ዓመት ያህል ቈይቶ በአንድ የእንፋሎት መርከብ ወደ ፊላዴልፊያ እንደምመጣ በሰማ ጊዜ፥ በፊላዴልፊያ ተቀብሎ ሰላም ያለኝ የመጀመሪያው ሰው እርሱ ነበር። ከፊላዴልፊያ ከመሄዴ በፊት እርሱንና ሚስቱን ወደ ቤተ ክርስቲያን ተቀበልኋቸው፤ ልጆቻቸውንም አጠመቅሁ። ለብዙ ዓመታት አላየኋቸውም፤ ስለ እነርሱም አልሰማሁም። ነገር ግን ልዩ መራርነትና ለሃይማኖት ተቃውሞ የታየባቸው የግለሰቦች ሁኔታዎች ቢኖሩም፥ ሕዝባዊ ተቃውሞ በሚመስል በማናቸውም ነገር አልተረበሽሁም ወይም አልተደናቀፍሁም። አገልጋዮቹ በደግነት ተቀበሉኝ፤ እኔ በማስታውሰው በአንድም ሁኔታ በሚካሄደው ሥራ ላይ በአደባባይ አልተናገሩም፤ በግልስ ቢሆን ተናግረው እንደ ሆነ አላውቅም።
በአቶ ፓተርሰን ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ወራት፥ በከተማይቱም ውስጥ ባሉ የፕሪስባይቴሪያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ማለት ይቻላል ይብዛም ይነስም ከሰበክሁ በኋላ፥ ማዕከላዊ ስፍራ ይዤ በአንድ ቦታ ያለማቋረጥ ብሰብክ የተሻለ እንደሚሆን ታሰበ። በሬስ ስትሪት አንድ ታላቅ የጀርመን ቤተ ክርስቲያን ነበረ፤ እረኛውም አቶ ሄልፈንስታይን የሚባሉ ሰው ነበሩ። የጉባኤው ሽማግሌዎች ከእረኛቸው ጋር ሆነው መድረካቸውን እንድይዝ ጠየቁኝ። ቤታቸው በዚያን ጊዜ በከተማይቱ ካሉት የአምልኮ ቤቶች ሁሉ እጅግ ትልቁ ነበረ ብዬ አስባለሁ። ሁልጊዜ ተጨናንቆ ነበር፤ ቤቱ ጢም ብሎ ሲሞላና መተላለፊያዎቹ ሲሞሉ ሦስት ሺህ ሰዎችን ይይዝ ነበር ይባል ነበር። በዚያ ለብዙ ወራት በመደበኛነት ሰበክሁ። ለእጅግ ብዙ የሰንበት ትምህርት ቤት መምህራን የመስበክ አጋጣሚ አገኘሁ። በእርግጥም በከተማይቱ ሁሉ ያሉ የሰንበት ትምህርት ቤት መምህራን በአብዛኛው አገልግሎቴን ይካፈሉ እንደ ነበር ይነገር ነበር።
በ1829 የበጋ አጋማሽ ገደማ ለአጭር ጊዜ ከዚያ ሄጄ በኦናይዳ ካውንቲ የሚኖሩትን የባለቤቴን ወላጆች ጠየቅሁ፤ ከዚያም ወደ ፊላዴልፊያ ተመልሼ እስከ ክረምቱ አጋማሽ ድረስ እዚያ ሠራሁ። ትክክለኛዎቹን ቀኖች አላስታውስም፤ ነገር ግን በጠቅላላው በፊላዴልፊያ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል የሠራሁ ይመስለኛል። በዚህ ሁሉ ጊዜ እኔ እስካየሁት ድረስ መነቃቃቱ ምንም አልቀዘቀዘም። በከተማዪቱ በየክፍሉ የተለወጡት ሰዎች እጅግ በዙ፤ ሆኖም ትክክለኛ ቁጥራቸውን ፈጽሞ አላወቅሁም፤ ግምትም ልሰጥበት አልቻልሁም። ከዚያ ይበልጥ ሞቅ ባለ ልብ የተቀበሉኝና ክርስቲያኖች፥ በተለይም አዲስ የተለወጡት፥ ከዚያ የተሻለ ሆነው የታዩበት ስፍራ ሠርቼ አላውቅም። እኔ እስከማውቀው ድረስ በመካከላቸው ምንም ዓይነት አለመግባባት ወይም መለያየት አልነበረም፤ ከዚያ መነቃቃት የተነሣ የመጣ ምንም ጎጂ ውጤት እንዳለም ፈጽሞ አልሰማሁም።
ከዚህ መነቃቃት ጋር የተያያዙ እጅግ ብዙ ልብ የሚስቡ ነገሮች ነበሩ። የአሮጌው ትምህርት ቤት ዓይነት አመለካከት የነበራቸው የአንድ አገልጋይ ልጅ የሆነች አንዲት ወጣት ሴት በአቶ ፓተርሰን ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቴን ትከታተል እንደ ነበረችና በአስፈሪ ሁኔታ የኃጢአት ወቀሳ እንደ ያዛት አስታውሳለሁ። ወቀሳዋ እጅግ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሣ በመጨረሻ እጅግ አሠቃቂ በሆነ ተስፋ መቍረጥ ውስጥ ወደቀች። ከተመረጡት አንዷ ብትሆን በጊዜው እንደምትለወጥ፥ እስክትለወጥና ተፈጥሮዋ በእግዚአብሔር መንፈስ እስኪለወጥ ድረስም መጽሐፍ ቅዱሷን ከማንበብና አዲስ ልብ እንዲሰጣት ከመጸለይ በቀር ለራሷ ምንም ልታደርግ እንደማትችል አባቷ ከልጅነቷ ጀምሮ እንዳስተማራት ነገረችኝ።
ገና በጣም ልጅ ሳለች ኃጢአቷ እጅግ ወቅሷት ነበር፤ ነገር ግን የአባቷን ትምህርት ተከትላ መጽሐፍ ቅዱሷን አነበበች፥ አዲስ ልብም እንዲሰጣት ጸለየች፤ ከእርሷ የሚጠበቀውም ይህ ብቻ እንደ ሆነ አሰበች። እስክትለወጥ ድረስ፥ በዚህም ከተመረጡት አንዷ መሆኗን የሚያሳይ ማስረጃ እስክታገኝ ድረስ ጠበቀች። ስለ መዳኗ ጉዳይ ነፍሷ በታላቅ ትግል ውስጥ ሳለች፥ ጋብቻን የሚመለከት አንድ ጉዳይ ተነሣ፤ እርሷም ክርስቲያን እስክትሆን ድረስ ለማንም ሰው እጇን እንደማትሰጥ ለእግዚአብሔር ቃል ገባች። ቃሉን በገባች ጊዜ እግዚአብሔር በጣም በቅርቡ ይለውጠኛል ብላ ትጠብቅ እንደ ነበረ ነገረችኝ። ነገር ግን ወቀሳዋ አለፈ። አልተለወጠችም፤ ያም ለእግዚአብሔር የገባችው ቃል አሁንም በነፍሷ ላይ ነበረ፤ ልታፈርሰውም አልደፈረችም።
ዕድሜዋ አሥራ ስምንት ዓመት ገደማ በሆነ ጊዜ አንድ ወጣት ሚስት ሊያደርጋት ጠየቃት። እርሷም ወደደችው፤ ነገር ግን ያ ስእለት በላይዋ ስለ ነበረ ክርስቲያን እስክትሆን ድረስ ለመጋባት ልትስማማ አልቻለችም። እርስ በርሳቸው እጅግ ይዋደዱ እንደ ነበረና እርሱም ሳይዘገዩ እንዲጋቡ አጥብቆ ይለምናት እንደ ነበረ ነገረችኝ። እርሷ ግን እውነተኛውን ምክንያቷን ሳትነግረው፥ በትክክል የማስታውስ ከሆነ ለአምስት ዓመት ያህል፥ እግዚአብሔር እስኪለውጣት እየጠበቀች ጊዜ በጊዜ ታስተላልፈው ነበር። በመጨረሻም አንድ ቀን ወጣቱ በሰረገላ ሲሄድ ከሰረገላው ተወርውሮ ወደቀና ወዲያውኑ ሞተ። ይህም በልቧ ውስጥ በእግዚአብሔር ላይ ያለውን ጠላትነት ቀሰቀሰው። እግዚአብሔርን በእርሷ ላይ ጨክኗል ብላ ከሰሰችው። እንዲለውጣት ስትጠብቀው እንደ ነበረች፥ እስክትለወጥ ድረስ ላለማግባት ለገባችው ቃል ታማኝ እንደ ሆነች፥ ፍቅረኛዋን ራሷን እስክታዘጋጅ ድረስ ለዓመታት እንዲጠብቃት እንዳደረገች፥ አሁን ግን፥ እነሆ! እግዚአብሔር እርሱን እንደ ቀጠፈውና እርሷ ግን አሁንም ያልተለወጠች እንደ ሆነች ተናገረች።
ወጣቱ ዩኒቨርሳሊስት እንደ ነበረ አውቃ ነበር፤ አሁንም ዩኒቨርሳሊዝም እውነት መሆኑን ለማመን እጅግ ፈለገች፤ እግዚአብሔር እርሱን ወደ ሲኦል እንደ ላከውም ልታምን አልፈለገችም፤ ወደ ሲኦል ልኮት ከሆነ ደግሞ ከዚህ ጋር በምንም ዓይነት ልትታረቅ አልቻለችም። በዚህ ሁኔታ ወደ ስብሰባዎቻችን ከመምጣቷ በፊት ለረጅም ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ስትዋጋ ቆየች፤ ያለመለወጧም ጥፋት በራሷ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ የሚወድቅ እንደ ሆነ ታስብ ነበር።
ስብከቴን በሰማች ጊዜና የሐሰት መጠጊያዎቿ ሁሉ እንደ ተገፈፉ ባወቀች ጊዜ፥ ከብዙ ጊዜ በፊት ልቧን ለእግዚአብሔር መስጠት እንደሚገባት፥ ይህን አድርጋ ቢሆን ኖሮም ሁሉ መልካም ይሆን እንደ ነበረ አየች፤ ጥፋቱ ሙሉ በሙሉ የራሷ እንደ ነበረ፥ በእነዚያ ነጥቦች ሁሉ ላይ የአባቷ ትምህርትም ፍጹም ስሕተት እንደ ነበረ ተገነዘበች፤ እግዚአብሔርን እንዴት እንደ ወቀሰችውና በፊቱ ምን ያህል የስድብ አቋም ይዛ እንደ ቆየች ስታስታውስ፥ ምሕረት አገኛለሁ የሚለውን ተስፋ መቍረጧ የሚያስደንቅ አልነበረም። ከእርሷ ጋር ተወያየሁ፤ የእግዚአብሔርን ትዕግሥት ላሳያት ሞከርሁ፤ ተስፋ እንድታደርግ፥ እንድታምንና የዘላለምን ሕይወት እንድትይዝ አበረታታኋት። ነገር ግን የኃጢአቷ ስሜት እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ የተስፋውን ቃል መጨበጥ ያቃታት ይመስል ነበር፤ ከቀን ወደ ቀንም ይበልጥ እየጠለቀች ወደ ተስፋ መቍረጥ ትሰምጥ ነበር።
ከእርሷ ጋር ብዙ ከደከምሁ በኋላ ስለ ጉዳይዋ እጅግ ተጨነቅሁ። በእያንዳንዱ ስብሰባ መጨረሻ ተስፋ በቈረጠ ሮሮዋ እስከ ቤቴ ድረስ ትከተለኝ ነበር፤ ለነፍሷ እንዳዝንና ክርስቲያናዊ ርኅራኄ እንዳሳያት በምታቀርበው ልመናም ታደክመኝ ነበር። ይህ ሁኔታ ለብዙ ሳምንታት ከቀጠለ በኋላ፥ አንድ ቀን ጠዋት ስለ እርሷ እጅግ ከተጨነቀችና ፈጽሞ ወደ ማይመለስ እብደት አፋፍ ላይ ደርሳለች ብላ ከምታስብ አክስቷ ጋር ሆና ልትጠይቀኝ መጣች። እኔም ራሴ ባታምን ነገሩ ወደዚያ እንደሚያደርስ አስቤ ነበር። ካትሪን — ስሟ ይህ ነበርና — እንደ ልማዷ ተስፋ በቈረጠ ሁኔታ ወደ ክፍሌ ገባች፤ ነገር ግን ሊቋቋሙት የማይቻል የአእምሮ ሁኔታ ላይ መድረሷን የሚያመለክት የእብደት መልክ በፊቷ ላይ ይታይ ነበር፤ በዚያን ጊዜም ከዚህ ቀደም ከወሰድሁት ፈጽሞ የተለየ መንገድ ከእርሷ ጋር እንድከተል በአእምሮዬ ያሳሰበኝ የእግዚአብሔር መንፈስ ይመስለኛል።
እንዲህ አልኋት፦ «ካትሪን፥ እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ አምናለሁ ትያለሽ።» እርሷም፦ «አዎን! ይህንማ አምናለሁ» አለች። «እንግዲያው ቸርነቱ ምሕረት እንዳያደርግልሽ እንደሚከለክለው — ኃጢአትሽ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ ይቅር ቢልሽና ቢያድንሽ ለእርሱ ውርደት እንደሚሆን — ብዙ ጊዜ ነግረሽኛል። እግዚአብሔር በጥበብ ሊያደርገው ቢችል ኖሮ ይቅር እንደሚልሽ ታምኚ እንደ ነበር፥ ነገር ግን ይቅርታሽ በእርሱ፥ በመንግሥቱና በፍጥረተ ዓለሙ ላይ ጉዳት ስለሚያደርስ ይቅር ሊልሽ እንደማይችል ብዙ ጊዜ ተናዘሽልኛል።» እርሷም፦ «አዎን፥ ይህን አምናለሁ» አለች። እኔም፦ «እንግዲያው ችግርሽ አንቺን ለማዳን ሲል እግዚአብሔር ኃጢአት እንዲሠራ፥ ያለ ጥበብ እንዲያደርግና ራሱንና ፍጥረተ ዓለሙን እንዲጎዳ መፈለግሽ ነው» ብዬ መለስሁላት። ትልልቅ ሰማያዊ ዓይኖቿን ገልጣ ትኩር ብላ ተመለከተችኝ፤ በከፊል የተደነቀች በከፊልም የተቈጣች ትመስል ነበር። እኔ ግን ቀጠልሁ፦ «አዎን! እግዚአብሔር ስሕተት ስለማይሠራ፥ በአንቺ ላይ የሚደርሰው ምንም ይሁን ምን ቸር ሆኖ መኖሩን ስለማይተው፥ አንቺ በታላቅ ችግርና በአእምሮ ጭንቀት ውስጥ ነሽ። እግዚአብሔር የራሱን የተገቢነትና የግዴታ ስሜት እንዲጥስና በራሱና በፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ ላይ ጉዳት እያደረሰ እንዲያድንሽ ሊያግባቡት ስለማይቻል፥ እጅግ በከፋ የአእምሮ ጭንቀት ተውጠሽ ትንከራተቻለሽ። ራስሽን ከእግዚአብሔርና ከፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ የበለጠ አስፈላጊ አድርገሽ ትቈጥሪያለሽ፤ እግዚአብሔርም አንቺን ደስተኛ ለማድረግ ሲል ራሱንና ሌላውን ሰው ሁሉ ደስታ ቢስ ካላደረገ ደስተኛ ልትሆኚ አትችዪም።»
ይህን አጥብቄ አስረዳኋት። እጅግ በመደነቅ ተመለከተችኝ፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ተገዛች። ልክ እንደ ትንሽ ልጅ ወዲያውኑ የለዘበች ይመስል ነበር። እንዲህም አለች፦ «እቀበለዋለሁ። ሊደረግ የሚገባው ከሁሉ የተሻለ ነገር ይህ ነው ብሎ ካሰበ እግዚአብሔር ወደ ሲኦል ይላከኝ። በራሱ ኪሳራና በፍጥረተ ዓለሙ ኪሳራ እንዲያድነኝ አልፈልግም። ደስ ያሰኘውን ያድርግ።» ወዲያውኑ ተነሥቼ ከክፍሉ ወጣሁ፤ ከእርሷ ፈጽሞ ለመራቅም ወጥቼ ሰረገላ ውስጥ ገባሁና ሄድሁ። በተመለስሁ ጊዜ እርሷ በእርግጥ ሄዳ ነበር፤ ነገር ግን ከሰዓት በኋላ እግዚአብሔር ለነፍሷ ያደረገውን ለመናገር እርሷና አክስቷ ተመልሰው መጡ። በደስታና በሰላም ተሞልታ ነበር፤ እኔ ካወቅኋቸው አዲስ ከተለወጡት ሰዎች ሁሉ እጅግ የተገዛች፥ ትሑትና ውብ ከሆኑት አንዷ ሆነች።
ሌላ ወጣት ሴትም፥ አስታውሳለሁ፥ ምናልባት ሃያ ዓመት የሚሆናት እጅግ ውብ ልጃገረድ፥ በታላቅ የኃጢአት ወቀሳ ውስጥ ሆና ልታየኝ መጣች። ከሌሎች ነገሮች መካከል፥ እግዚአብሔር በፍትሕ ወደ ሲኦል ሊልካት እስኪችል ድረስ ክፉ እንደ ነበረች አምና እንደ ሆነ ጠየቅኋት። እርሷም በጠንካራ ቃል፦ «አዎን! አንድ ሺህ ሲኦል ይገባኛል» ብላ መለሰች። ያጌጠ ልብስ ለብሳ ነበር፤ ውድ ልብስ ነበር ብዬም አስባለሁ። ከእርሷ ጋር እጅግ የተሟላ ውይይት አደረግሁ፤ ልቧም ተሰበረ፤ ራሷንም ለክርስቶስ ሰጠች። እጅግ ትሑትና ልቧ የተሰበረ አዲስ ክርስቲያን ሆነች። ወደ ቤቷ ሄዳ ራሷን ታስጌጥባቸው የነበሩትንና እጅግ ትመካባቸው የነበሩትን ብዙ ሰው ሠራሽ አበቦቿንና ጌጣጌጦቿን ሰብስባ በእጆቿ ይዛቸው በክፍሉ ውስጥ እንዳለፈች ሰማሁ። በእነርሱ ምን ልታደርግ እንደ ሆነ ጠየቋት። ልታቃጥላቸው እንደ ሆነ ነገረቻቸው። «ዳግመኛ ፈጽሞ አላደርጋቸውም» አለች። እነርሱም፦ «መልካም፥ የማታደርጊያቸው ከሆነ ልትሸጪያቸው ትችያለሽ፤ አታቃጥያቸው» አሏት። እርሷ ግን፦ «ብሸጣቸው፥ እኔ ራሴ እንደ ተመካሁባቸው ሌላ ሰው ይመካባቸዋል፤ አቃጥላቸዋለሁ» አለች። በእርግጥም ወደ እሳቱ ጣለቻቸው።
ከዚህ ከጥቂት ቀናት በኋላ ልታየኝ መጥታ፥ በዚያው ቀን ጠዋት ይመስለኛል፥ በገበያው ውስጥ ስታልፍ እጅግ ውድ ልብስ የለበሰች አንዲት እመቤት በገበያው ውስጥ እንዳየች ነገረችኝ። ርኅራኄዋ እጅግ ከመነሣሣቱ የተነሣ ወደ እርሷ ቀርባ ልታነጋግራት ትችል እንደ ሆነ ጠየቀቻት። እመቤቲቱም ልታነጋግራት እንደምትችል መለሰችላት። እርሷም፦ «ውድ እመቤቴ፥ በልብስሽ አትመኪምን? ከንቱ ትምክህተኛ ሆነሽ የነፍስሽን መዳን ቸል አላልሽምን?» አለቻት። ይህን ስትናገር እርሷ ራሷ እንባዋ እንደ ፈሰሰ፥ ለእመቤቲቱም ስለ ራሷ ተሞክሮ ጥቂት እንደ ነገረቻት፥ እንዴት ከልብስ ጋር ተጣብቃ እንደ ነበረችና ልብሱ ነፍሷን ሊያጠፋት ምን ያህል እንደ ተቃረበ እንዳጫወተቻት ነገረችኝ። «አሁንም» አለች፥ «አንቺ ውብ እመቤት ነሽ፤ ያማረ ልብስም ለብሰሻል፤ እኔ ራሴ ውስጥ በነበርሁበት በዚያው የአእምሮ ሁኔታ ውስጥ አይደለሽምን?» እመቤቲቱም እንዳለቀሰችና ይህ ወጥመዷ እንደ ነበረ እንደ ተናዘዘች፥ የልብስና የማኅበራዊ ኑሮ ፍቅሯ ነፍሷን እንዳያጠፋባትም እንደምትፈራ እንደ ተናገረች ነገረችኝ። ከምትንቀሳቀስበት ክበብ እንዴት ተላቅቃ እንደምትወጣ ስላላወቀች የነፍሷን መዳን ቸል ብላ እንደ ነበረች ተናዘዘች። ወጣቷም ለእመቤቲቱ በተናገረችው ነገር ስሕተት ሠርታለች ብዬ እንደማስብ ለማወቅ ፈለገች። እኔም፦ «በፍጹም!» አልኋት፤ ክርስቲያኖች ሁሉ እንደ እርሷ ታማኞች ቢሆኑ እንደምመኝ፥ ነፍሷን ሊያጠፋት ጥቂት ስለ ቀረው ነገርም የራሷን ጾታ ከማስጠንቀቅ ፈጽሞ እንዳታቋርጥ ተስፋ እንደማደርግ ነገርኋት።
በ1829 የጸደይ ወራት የደላዌር ወንዝ በሞላ ጊዜ፥ የእንጨት ሠራተኞች በክረምቱ ጊዜ እንጨት ሲያወጡበት ከነበረው ከደጋማው አካባቢ በእንጨት ጀልባዎቻቸው ወረዱ። በዚያን ጊዜ በፔንስልቬንያ ሰሜናዊ ክፍል በኩል ብዙዎች «የእንጨት ግዛት» ብለው የሚጠሩት፥ ወደ ደላዌር ወንዝ መነሻ ውኆች አቅጣጫ የሚዘረጋ ሰፊ ምድር ነበረ። በዚያ በበጋም በክረምትም እንጨት በማውጣት ሥራ የተሰማሩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ከዚህ እንጨት አብዛኛው በዓመቱ የጸደይ ወራት ውኃው በሞላ ጊዜ በወንዙ ላይ እየተንሳፈፈ ወደ ፊላዴልፊያ ይወርድ ነበር። ወንዙ ዝቅ ባለ ጊዜ እንጨታቸውን ያወጡ ነበር፤ በረዶው ቀልጦ የጸደይ ዝናብ በመጣ ጊዜም እንጨቱን ወደ ወንዙ ይጥሉትና የእንጨት ጀልባ ወደሚሠሩበት ስፍራ፥ ወይም በሌላ መንገድ ለፊላዴልፊያ ገበያ ወደሚጭኑበት ስፍራ በውኃው ላይ እያንሳፈፉ ያወርዱት ነበር።
ከእንጨት ሠራተኞቹ ብዙዎቹ በዚያ አካባቢ ቤተሰብ ያሳድጉ ነበር፤ በዚያም ከእነዚህ የእንጨት ሠራተኞች በቀር ሰው ያልሰፈረበትና ያልያዘው ሰፊ ምድር ነበረ። ትምህርት ቤት አልነበራቸውም፤ በዚያን ጊዜም ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ዕድል ፈጽሞ አልነበራቸውም። በዚያ የእንጨት ግዛት እንደ ተወለደ፥ ሃያ ዓመት በሆነው ጊዜም አንድም ሃይማኖታዊ ስብሰባ ተካፍሎ እንደማያውቅና ፊደል እንኳ እንደማያውቅ የነገረኝን አንድ አገልጋይ አውቃለሁ።
ከእንጨት ጋር የወረዱት እነዚህ ሰዎች ስብሰባዎቻችንን ተካፈሉ፤ ከእነርሱም ቍጥራቸው ቀላል ያልሆነ ሰዎች ተለወጡ ብለን ተስፋ አደረግን። ወደ ምድረ በዳው ተመልሰው መንፈስ ቅዱስ እንዲፈስስ መጸለይ ጀመሩ፤ በፊላዴልፊያ ያዩትን በዙሪያቸው ላሉት ሰዎች መናገርና ለመዳናቸው እንዲተጉ መምከርም ጀመሩ። ጥረታቸው ወዲያውኑ ተባረከ፤ መነቃቃቱም ሥር መስደድና በእነዚያ የእንጨት ሠራተኞች መካከል መስፋፋት ጀመረ። እጅግ በኃይልና በሚያስደንቅ ሁኔታ ቀጠለ። ምንም ስብሰባ ያልተካፈሉና እንደ አሕዛብ ያህል ማለት ይቻላል ምንም የማያውቁ ሰዎች በብዙ ሁኔታዎች የኃጢአት ወቀሳ ይዟቸው እስኪለወጡ ድረስ ተስፋፋ። እንጨት የሚያወጡና በትንንሽ ጎጆዎች ውስጥ ብቻቸውን፥ ወይም ሁለትና ሦስት ወይም ከዚያ በላይ ሆነው በአንድነት የሚኖሩ ሰዎች ተቅበዝብዘው ወጥተው ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲጠይቁ የሚያደርስ ወቀሳ ይይዛቸው ነበር፤ እነርሱም ይለወጡ ነበር፤ መነቃቃቱም በዚህ መንገድ ተስፋፋ። በተለወጡት ሰዎች ዘንድ እጅግ ታላቅ የዋህነት ይታይ ነበር።
በዚያ ስላለው ሁኔታ በመጠኑ የሚያውቁ አንድ ሽማግሌ አገልጋይ በዚያ እየሆነ ስለ ነበረው ነገር ምሳሌ እንዲሆን የሚከተለውን እውነተኛ ታሪክ ነገሩኝ። በአንድ ስፍራ አንድ ሰው ሌሊት የሚተኛባት የራሱ ብቻ የሆነች ትንሽ ጎጆ እንደ ነበረችውና ቀን ቀን የጣራ ሳንቃዎቹን ያወጣ እንደ ነበረ ነገሩኝ። ኃጢአተኛ መሆኑ ይሰማው ጀመር፤ ልቡ እስኪሰበር ድረስ ወቀሳው እየበረታበት ሄደ፤ ኃጢአቱንም ተናዘዘ፤ ንስሐም ገባ፤ የእግዚአብሔር መንፈስም ከመዳን መንገድ ይህን ያህል ገለጠለት፤ በዚህም አዳኙን እንዳወቀ በግልጽ ይታይ ነበር። ነገር ግን እስከሚያስታውሰው ድረስ በሕይወቱ የጸሎት ስብሰባ ተካፍሎ ወይም ጸሎት ሰምቶ አያውቅም ነበር። ስሜቱ ወደዚህ ደረጃ ደረሰ፤ በመጨረሻም በሌላ ስፍራ እንጨት ለሚያወጡ ለአንዳንድ ወዳጆቹ ምን እንደሚሰማው ሄዶ ሊነግራቸው ግድ ሆነበት። እዚያ በደረሰ ጊዜ ግን ከእነርሱ ብዙዎቹ ልክ እንደ እርሱ ይሰማቸው እንደ ነበረና የጸሎት ስብሰባዎች ያደርጉ እንደ ነበረ አገኘ። በጸሎት ስብሰባዎቻቸው ተገኝቶ ሲጸልዩ ሰማ፤ በመጨረሻም ራሱ ጸለየ፤ የጸሎቱም ቃል ይህ ነበር፦ «ጌታ ሆይ፥ አንተ አውርደኸኛል፤ እንደ ወረድሁም እንድታኖረኝ ተስፋ አደርጋለሁ። በእኔም ይህን ያህል ስለ ተሳካልህ ሌሎችንም ኃጢአተኞች እንድትሞክር ተስፋ አደርጋለሁ።»
ይህ ሥራ በ1829 የጸደይ ወራት እንደ ጀመረ ተናግሬአለሁ።
በ1831 የጸደይ ወራት እንደ ገና በኦበርን ነበርሁ። ከዚህ የእንጨት ግዛት ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች እኔን ለማየትና ወደዚያ የሚሄዱ አገልጋዮችን እንዴት ሊያገኙ እንደሚችሉ ለመጠየቅ ወደዚያ መጡ። በዚያ የእንጨት ግዛት ከአምስት ሺህ ያላነሱ ሰዎች እንደ ተለወጡ፥ መነቃቃቱም ለሰማንያ ማይል ያህል እንደ ተዘረጋ፥ በዚያም አንድም የወንጌል አገልጋይ እንደሌለ ነገሩኝ።
እኔ ወደዚያ አካባቢ ሄጄ አላውቅም፤ ነገር ግን ስለ እርሱ ከሰማሁት ሁሉ በመነሣት፥ ያንን በዚህች አገር ከተከሰቱት መነቃቃቶች ሁሉ እጅግ አስደናቂ ከሆኑት እንደ አንዱ እቈጥረዋለሁ። ለማናቸውም ተራ ትምህርት እጅግ ባዕድ በሆኑ ሰዎች መካከል፥ ከአገልጋዮች ነጻ በሆነ መንገድ ማለት ይቻላል ተካሄደ፤ ሆኖም የእግዚአብሔር ትምህርት እጅግ ግልጽና አስደናቂ ስለ ነበረ፥ መነቃቃቱ ከአክራሪነት፥ ከስሜታዊ ብሶት ወይም ከማናቸውም ሊነቀፍ ከሚችል ነገር በሚያስደንቅ ሁኔታ ነጻ እንደ ነበረ ሁልጊዜ ተረድቻለሁ። በአንዳንድ ነገሮች የተሳሳተ መረጃ ደርሶኝ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ነገሩን እኔ በተረዳሁት መሠረት እዘግበዋለሁ። «እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል።» ወደ ፊላዴልፊያ በመጡት በእነዚያ ጥቂት የእንጨት ሠራተኞች ልብ ውስጥ የተጫረው ፍንጣሪ በዚያ ጫካ ሁሉ ላይ ተዛመተ፤ የብዙ ሕዝብ ነፍሳትንም መዳን አስገኘ።
አቶ ፓተርሰን አብሬአቸው ከሠራኋቸው ሰዎች ሁሉ እጅግ እውነተኞችና ቅዱሳን ከሆኑት አንዱ ሆነው አገኘኋቸው። ስብከታቸው በእጅጉ ልዩ ነበር። በታላቅ ትጋት ይሰብኩ ነበር፤ ነገር ግን በሚናገሩት ነገር ውስጥ ብዙ ጊዜ ምንም ትስስር አልነበረም፤ ከጥቅሳቸውም ጋር የነበረው ግንኙነት እጅግ ጥቂት ነበር። ብዙ ጊዜ፦ «ስሰብክ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ እሰብካለሁ» ይሉኝ ነበር። አንድ ጥቅስ ይወስዱና በእርሱ ላይ ጥቂት አስተያየት ከሰጡ በኋላ፥ ወይም ምናልባት ምንም ሳይሰጡ፥ ሌላ ጥቅስ ወደ አእምሮአቸው ይመጣላቸው ነበር፤ በእርሱም ላይ እጅግ ተገቢና ልብ የሚነካ አስተያየት ይሰጡ ነበር፤ ከዚያም ሌላ ጥቅስ፤ በዚህ ሁኔታ ስብከቶቻቸው በአእምሮአቸው ውስጥ በተነሡት በብዙ ጥቅሶች ላይ በሚሰጧቸው ጥልቅ ትርጉም ባላቸውና ልብ በሚነኩ አስተያየቶች የተሠሩ ነበሩ።
ቁመተ ረጅም፥ ግርማ ሞገስ ያላቸውና ኃይለኛ ድምፅ ያላቸው ሰው ነበሩ። እንባቸው በጉንጮቻቸው ላይ እየወረደ፥ እጅግ ልብ በሚነካ ትጋትና ስሜት ይሰብኩ ነበር።
ሲሰብኩ እየሰማ የጽኑ ትጋታቸውና የታላቅ ቅንነታቸው ስሜት ያልተሰማው ሰው ሊኖር አይችልም ነበር። እኔ ሲሰብኩ የሰማኋቸው አልፎ አልፎ ብቻ ነበር፤ መጀመሪያ በሰማኋቸው ጊዜ ስብከታቸው እጅግ የተበታተነ ከመሆኑ የተነሣ ውጤት ሊያመጣ አይችልም ብዬ በማሰብ አዘንሁ። ሆኖም መሳሳቴን ተረዳሁ። ስብከታቸው የተበታተነ ቢሆንም እንኳ፥ ታላቅ ትጋታቸውና ቅብዓታቸው እውነቱን በሰሚዎቻቸው ልብ ውስጥ እንደሚያጸናው አስተዋልሁ፤ በተናገሩት ነገር አንዳንድ ሰዎች ጥልቅ የኃጢአት ወቀሳ ሳይዛቸው ሲሰብኩ የሰማኋቸው ጊዜ ፈጽሞ ያለ አይመስለኝም።
በየክረምቱ ሁልጊዜ የሃይማኖት መነቃቃት ይሆንላቸው ነበር፤ ከእርሳቸው ጋር በሠራሁበት ጊዜም ለአሥራ አራት ተከታታይ ክረምቶች መነቃቃት እንደ ሆነላቸው የነገሩኝ ይመስለኛል። የሚጸልይ ሕዝብ ነበራቸው። ከእርሳቸው ጋር እየሠራሁ ሳለሁ አንድ ጊዜ ለሁለት ወይም ለሦስት ቀናት አንድ እንቅፋት ያለ ይመስል እንደ ነበረ አስታውሳለሁ። ሥራው በመጠኑ የቆመ ይመስል ነበር፤ እኔም አንድ ነገር መንፈስ ቅዱስን አሳዝኖት ይሆን ብዬ መሥጋት ጀመርሁ። ይህ ሁኔታ ግልጽ እየሆነ በመጣበት ጊዜ፥ አንድ ምሽት በጸሎት ስብሰባ ላይ ከሽማግሌዎቻቸው አንዱ ተነሥቶ ተናዘዘ። እንዲህም አለ፦ «ወንድሞች ሆይ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ አዝኗል፤ ያሳዘንሁትም እኔ ነኝ። ቅዳሜ ማታ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ስለ ወንድም ፓተርሰንና ስለ ስብከቱ መጸለይ ልማዴ ነበር» አለ። «በሰንበት ለሚሠራው ሥራ የእግዚአብሔርን በረከት በመለመን ቅዳሜ ማታን እስከ እኩለ ሌሊት ማሳለፍ ለብዙ ዓመታት ልማዴ ሆኖ ቆይቷል። ባለፈው ቅዳሜ ማታ» ሲል ቀጠለ፥ «ደክሞኝ ስለ ነበር ተውሁት። ሥራው እጅግ በሚያስደስትና በኃይል እየቀጠለ ስለ ነበር ራሴን ማዝናናት እንደምችል፥ በሰንበት ለሚሠራው ሥራ ከእግዚአብሔር በረከት ሳልለምን ወደ መኝታ መሄድ እንደምችል አሰብሁ። በሰንበት ቀን» አለ፥ «መንፈስን እንዳሳዘንሁት የሚል ወቀሳ ተሰማኝ፤ በጉባኤውም ላይ የተለመደው የመንፈስ አሠራር መገለጥ እንዳልነበረ አየሁ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ወቀሳ ተሰምቶኛል፤ ይህንንም በሕዝብ ፊት መናዘዝ ግዴታዬ እንደ ሆነ ተሰምቶኛል። ከእኔ በቀር የእግዚአብሔርን መንፈስ ያሳዘነ ማን እንደ ሆነ አላውቅም» አለ፤ «እኔ ግን እንዳሳዘንሁት እርግጠኛ ነኝ።»
ስለ አቶ ፓተርሰን የትምህርት ቀጥተኝነት ተናግሬአለሁ። ከእርሳቸው ጋር መሥራት በጀመርሁ ጊዜ፥ በአንዳንድ አጋጣሚዎች የኃጢአት ወቀሳ ለያዛቸው ኃጢአተኞች በሚናገሩት ነገር በእጅጉ ተፈትኜ ነበር። ለምሳሌ፦ ባደረግነው የመጀመሪያው የጠያቂዎች ስብሰባ የተገኙት ሰዎች ቍጥር እጅግ ብዙ ነበረ። ከተለያዩ ሰዎች ጋር እየተነጋገርንና ከቦታ ቦታ እየተዘዋወርን ትምህርት በመስጠት የተወሰነ ጊዜ አሳለፍን። ሳላስበው አቶ ፓተርሰን ተነሡና በእጅጉ በተነሣሣ ሁኔታ፦ «ወዳጆቼ ሆይ፥ ፊታችሁን ወደ ጽዮን አዙራችኋል፤ አሁንም ወደ ፊት እንድትገሠግሡ እመክራችኋለሁ» አሉ። ለጥቂት ደቂቃዎች ምክራቸውን ቀጠሉ፤ በዚህም አሁን በትክክለኛው መንገድ ላይ እንዳሉ፥ አሁን እንደሚያደርጉት ወደ ፊት መገሥገሥ ብቻ እንደሚቀራቸውና እንደሚድኑ የሚያሳይ ስሜት በግልጽ ፈጠሩ። ንግግራቸው እጅግ አሳዘነኝ፤ ምክንያቱም ወደ ራስ ጽድቅ የሚያዘነብል፥ እጅግ መልካም እያደረጉ እንዳሉና አሁን እንደሚያደርጉት ግዴታቸውን መፈጸም ከቀጠሉ እንደሚድኑ የሚያስመስል መሰለኝ።
ስለ ሁኔታቸው የነበረኝ አመለካከት ይህ ፈጽሞ አልነበረም፤ እንዲህ ያለ ትምህርት ሲሰጥ በመስማቴ አዘንሁ፤ እንዴትስ ልቃወመው እችላለሁ በሚለው ጥያቄም ግራ ተጋባሁ። ሆኖም በስብሰባው መጨረሻ እንደ ልማዴ የውይይታችንን ውጤት ጠቅልዬ ንግግር ባደረግሁላቸው ጊዜ፥ አቶ ፓተርሰን የተናገሩትን ጠቅሼ የተናገሩትን በተሳሳተ መንገድ መረዳት እንደሌለባቸው ገለጽሁላቸው፤ የተናገሩት ነገር ልባቸውን ለእግዚአብሔር በመስጠት በእውነት ወደ እግዚአብሔር ለተመለሱትና ፊታቸውን ወደ ጽዮን ላቀኑት እውነት እንደ ሆነ ነገርኋቸው። ነገር ግን ይህን የኃጢአት ወቀሳ ይዟቸው ሳለ ገና ንስሐ ላልገቡ፥ ላላመኑና ልባቸውን ለእግዚአብሔር ላልሰጡት በመካከላቸው ላሉት ሰዎች የሚመለከት አድርገው እንዳይወስዱት አሳሰብኋቸው፤ እነዚህ ፊታቸው ወደ ጽዮን የዞረ ከመሆን ይልቅ በእውነቱ ጀርባቸውን ለክርስቶስ እየሰጡ እንደ ነበሩ፥ አሁንም መንፈስ ቅዱስን እየተቃወሙ እንደ ነበሩ፥ አሁንም ወደ ሲኦል በሚወስደው መንገድ ላይ እንደ ነበሩ፥ በሚቃወሙበት በእያንዳንዱ ቅጽበት እየከፉ እንደሚሄዱ፥ ንስሐ ያልገቡ ሆነው ሳይገዙ፥ ሳይጸጸቱና ሳያምኑ በሚቆዩበት በእያንዳንዱ ቅጽበትም ፍርዳቸውን እያበዙ እንደ ነበረ ነገርኋቸው። ጌታም ስለ ጉዳዩ እጅግ ግልጽ የሆነ ማስተዋል ሰጠኝ። አቶ ፓተርሰን በተቻለ መጠን ሁሉ በከፍተኛ ትኩረት አዳመጡ። በምን ያህል ትጋት እንደ ተመለከቱኝና የለየኋቸውን ልዩነቶች በምን ያህል ፍላጎት እንደ ተረዱ ፈጽሞ አልረሳውም።
የተነገረው ነገር የፈጠረው ስሜት መታረሙ ብቻ ሳይሆን ወዲያውኑ እንዲገዙ ታላቅ ግፊት በላያቸው እንዳረፈ እስካየሁና እስኪሰማኝ ድረስ ንግግሬን ቀጠልሁ። ከዚያም እንዲንበረከኩና በዚያው ቅጽበት በዚያው ስፍራ ኃጢአታቸውን ሁሉ ክደው፥ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ራሳቸውን ለሉዓላዊው ቸርነት ፈቃድ አሳልፈው በመስጠት ራሳቸውን ለዘላለም ለጌታ እንዲያስረክቡ ጠራኋቸው። የማስተሰረያውን ምንነትና በወንጌል የቀረበውን መዳን በተቻለኝ መጠን ግልጽ አድርጌ አስረዳኋቸው። ከዚያም ከእነርሱ ጋር ጸለይሁ፤ ከእነርሱም እጅግ ብዙዎቹ በዚያው ስፍራ እንደ ተለወጡ የማምንበት ምክንያት አለኝ።
ከዚህ በኋላ አቶ ፓተርሰን ለሚጠይቁ ኃጢአተኞች ትምህርት ሲሰጡ በምንም መንገድ ሊነቀፍ የሚችል ነገር ሲናገሩ ፈጽሞ አልሰማሁም። እንዲያውም እጅግ ለመማር ዝግጁ፥ አእምሮአቸውም ለትክክለኛ ልዩነቶች ክፍት ሆኖ አገኘኋቸው። ለሚጠይቁ ኃጢአተኞች መቅረብ ያለባቸውን እውነቶች በመጨበጥ በተለይ ፈጣን ይመስሉ ነበር፤ እስከሞቱበት ቀን ድረስም ቀደም ብዬ የጠቀስሁትን ያን ዓይነት አመለካከት ዳግመኛ ፈጽሞ ያላቀረቡ ይመስለኛል። ስማቸውን እንኳ አከብራለሁ፤ በታላቅ ክብርም አስበዋለሁ። ተወዳጅ ክርስቲያን ሰውና የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ ነበሩ።