ምዕራፍ 12 · 36 ደቂቃ ንባብ · 46 ደቂቃ ማዳመጥ
ዲሴምበር
ዲሴምበር 1
«ስለ ቸርነቱ፥ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ተኣምራቱ እግዚአብሔርን ምነው ባመሰገኑት!» (መዝሙር 107:8)
ማጕረምረማችንን ብንቀንስና ምስጋናችንን ብናበዛ፥ እኛ ደስተኞች እንሆን ነበር፤ እግዚአብሔርም ይበልጥ ይከብር ነበር። ስለ ተራ ምሕረቶች እግዚአብሔርን ዕለት ዕለት እናመስግን፤ ብዙ ጊዜ ተራ ብለን እንጠራቸዋለን፤ ነገር ግን ስንነፈጋቸው ልንጠፋ እስክንደርስ ድረስ ዋጋ የማይወጣላቸው ናቸው። ፀሐይን ስለምናይባቸው ዓይኖች፥ ወደ ውጭ ለመመላለስ ስለሚያስችለን ጤናና ብርታት፥ ስለምንበላው እንጀራ፥ ስለምንለብሰው ልብስ እግዚአብሔርን እንባርክ። ተስፋ ቢስ ከሆኑት መካከል ስላልተጣልን፥ ወይም ከበደለኞች ጋር ስላልታሰርን እናመስግነው፤ ስለ ነጻነት፥ ስለ ወዳጆች፥ ስለ ቤተ ሰብ ኅብረትና መጽናናት እናመስግነው፤ በእውነትም ከለጋሱ እጁ ስለምንቀበለው ነገር ሁሉ እናመስግነው፤ የሚገባን ጥቂት ነውና፥ ሆኖም እጅግ በብዙ ተሰጥቶናል። ነገር ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በምስጋና መዝሙራችን ውስጥ እጅግ ጣፋጭና እጅግ ከፍ ያለው ድምፅ ስለ ቤዛ የሆነ ፍቅር ሊሆን ይገባዋል። እግዚአብሔር ለመረጣቸው ያደረገው የቤዛነት ሥራ ለዘላለም የምስጋናቸው ተወዳጅ ርእስ ነው። ቤዛነት ምን ማለት እንደ ሆነ የምናውቅ ከሆንን የምስጋና ቅኔያችንን አንከልክል። ከርኵሰታችን ኃይል ተቤዠን፤ በተፈጥሮ ከተዘፈቅንበት ከኃጢአት ጥልቀት ወጥተን ከፍ ከፍ አልን። ወደ ክርስቶስ መስቀል ተመራን፤ የበደል እግር ብረታችን ተሰበረ፤ ከእንግዲህ ባሪያዎች አይደለንም፥ የሕያው እግዚአብሔር ልጆች ነን እንጂ፤ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንብን በዙፋኑ ፊት የምንቀርብበትን ጊዜ አስቀድመን ልንመለከት እንችላለን። አሁንም እንኳ በእምነት የዘንባባ ዝንጣፊ እናውለበልባለን፤ የዘላለም ልብሳችን በሚሆነው በጥሩ በፍታም ራሳችንን እንጠቀልላለን፤ ታዲያ ቤዛችን ለሆነው ለጌታ ሳናቋርጥ ምስጋና አናቀርብምን? የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፥ ዝም ልትል ትችላለህን? እናንተ የክብር ወራሾች፥ ንቁ፥ ንቁ፤ ከዳዊት ጋር «ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ የውስጥ ሕዋሳቴም ሁሉ የተቀደሰ ስሙን» እያላችሁ ስትጮኹ ምርኮአችሁን ማርኩ። አዲሱ ወር በአዲስ መዝሙር ይጀመር።
ዲሴምበር 2
«እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነው።» (መክብብ 1:14)
ከጌታ ፍቅርና ከጌታ ራሱ በቀር ሰውን በሙሉ ሊያረካው የሚችል ምንም ነገር የለም። ቅዱሳን በሌሎች መልሕቅ መጣያዎች ለመቆም ሞክረዋል፤ ነገር ግን ከእነዚያ ገዳይ መጠጊያዎች ተባረዋል። ከሰዎች ሁሉ ይልቅ ጠቢብ የነበረው ሰሎሞን ለሁላችን ሙከራ እንዲያደርግ፥ እኛ ለራሳችን ልናደርገው የማይገባንን ነገር ስለ እኛ እንዲያደርግ ተፈቀደለት። ምስክርነቱ በራሱ ቃል ይኸው፦ «ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ታላቅ ሆንሁ፥ በለጠግሁም፤ ጥበቤም ከእኔ ጋር ነበረች። ዓይኖቼም የተመኙትን ሁሉ አልከለከልኋቸውም፤ ልቤ በድካሜ ሁሉ ደስ ብሎት ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አልከለከልሁትም፤ ከድካሜም ሁሉ ዕድል ፈንታዬ ይህ ነበረ። እጆቼም የሠሩትን ሥራ ሁሉ፥ የደከምሁበትንም ድካም ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱና ነፋስን እንደ መከተል ነበረ፥ ከፀሐይም በታች ትርፍ አልነበረም።» «የከንቱ ከንቱ፥ ሁሉ ከንቱ ነው።» ምን! ሁሉም ከንቱ ነውን? አንተ የተወደድህ ንጉሥ ሆይ፥ በሀብትህ ሁሉ ውስጥ ምንም የለምን? ከወንዝ እስከ ባሕር በሚደርሰው በዚያ ሰፊ ግዛት ውስጥ ምንም የለምን? በፓልሚራ ክቡራን ቤተ መንግሥቶች ውስጥ ምንም የለምን? በሊባኖስ ዱር ቤት ውስጥ ምንም የለምን? በዜማህና በዘፈንህ ሁሉ፥ በወይን ጠጅህና በቅምጥልነትህ ውስጥ ምንም የለምን? እርሱም «ምንም የለም፤ ከመንፈስ ድካም በቀር» ይላል። የደስታን መንገድ ሁሉ ዞሮ ከረገጠ በኋላ የሰጠው ፍርድ ይህ ነበር። ጌታችንን ኢየሱስን ማቀፍ፥ በፍቅሩ መኖር፥ ከእርሱ ጋር አንድ መሆናችንን በሙሉ ማረጋገጥ፤ ሁሉ በሁሉ ይህ ነው። ውድ አንባቢ፥ ከክርስቲያን ሕይወት የሚሻሉ እንደ ሆኑ ለማየት ሌሎችን የሕይወት ዓይነቶች መሞከር አያስፈልግህም፤ ዓለምን ዙሪያዋን ብትዞር የአዳኙን ፊት እንደ ማየት ያለ ትዕይንት አታይም፤ የሕይወትን ምቾት ሁሉ ብታገኝ፥ አዳኝህን ግን ብታጣ፥ ጐስቋላ ትሆናለህ፤ ክርስቶስን ብታገኝ ግን በወህኒ ቤት ውስጥ ብትበሰብስ እንኳ ገነት ሆኖ ታገኘዋለህ፤ በተሰወረ ስፍራ ብትኖር፥ ወይም በራብ ብትሞት፥ ገና በሞገስ ትጠግባለህ፥ የጌታም ቸርነት ይሞላብሃል።
ዲሴምበር 3
«በሰልፍ ኃያል እግዚአብሔር።» (መዝሙር 24:8)
አምላካችን ለሕዝቡ፥ በእነርሱ ውስጥና በእነርሱ በኩል እንዲህ ያሉ ድንቆችን ስለ ሠራ በሕዝቡ ዓይን የከበረ ቢሆን ተገቢ ነው። ለእነርሱ ጌታ ኢየሱስ በቀራንዮ ላይ ጠላትን ሁሉ አሸነፈ፤ በፍጹም በሆነው አርኪ የመታዘዝ ሥራው የጠላትን መሣሪያ ሁሉ ሰባበረ፤ በድል ትንሣኤውና በዕርገቱ የገሃነምን ተስፋ ፈጽሞ ገለበጠ፤ ምርኮን ማረከ፤ ጠላቶቻችንን በግልጥ አሳያቸው፤ በመስቀሉም ድል ነሣቸው። ሰይጣን በእኛ ላይ ሊወረውረው የሚችለው የበደል ፍላጻ ሁሉ ተሰብሯል፤ «እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል?» የገሃነም ክፋት የተሳሉ ሰይፎችና የእባቡ ዘር የማያቋርጡ ጦርነቶች ከንቱ ናቸው፤ በቤተ ክርስቲያን መካከል አንካሶች ብዝበዛውን ይበዘብዛሉና፥ እጅግ ደካሞቹ ተዋጊዎችም አክሊል ይቀዳጃሉና።
የዳኑት በእነርሱ ውስጥ ስላደረገው ድል ጌታቸውን ቢያመልኩ ተገቢ ነው፤ የተፈጥሮ ጥላቻቸው ፍላጻዎች ተቈርጠዋልና፥ የዓመፃቸውም መሣሪያዎች ተሰብረዋልና። ጸጋ በክፉ ልባችን ውስጥ ምንኛ ድሎችን አገኘ! ፈቃድ ሲገዛ፥ ኃጢአትም ከዙፋኑ ሲወርድ ኢየሱስ ምንኛ የከበረ ነው! የቀረው ርኵሰታችንም እንዲሁ የተረጋገጠ ሽንፈት ይደርስበታል፤ ፈተና ሁሉ፥ ጥርጣሬም፥ ፍርሃትም ፈጽሞ ይጠፋሉ። ሰላም ባለበት ልባችን ሳሌም ውስጥ የኢየሱስ ስም ወደር የሌለው ታላቅ ነው፤ ፍቅራችንን አሸንፏል፥ ይለብሰውማል። እንዲሁም በተረጋገጠ ሁኔታ በእኛ በኩል ድሎችን ልንጠብቅ እንችላለን። በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። በዓለም ያሉትን የጨለማ ኃይላት በእምነታችን፥ በቅንዓታችንና በቅድስናችን እንጥላለን፤ ኃጢአተኞችን ለኢየሱስ እናገኛለን፤ የሐሰት ሥርዓቶችን እንገለብጣለን፤ አሕዛብን እንመልሳለን፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና፥ ማንም በፊታችን አይቆምምና። ዛሬ ማታ ክርስቲያን ተዋጊ የጦርነት መዝሙሩን ይዘምር፤ ለነገውም ሰልፍ ይዘጋጅ። በዓለም ካለው ይልቅ በእኛ ያለው ታላቅ ነው።
ዲሴምበር 4
«ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን።» (ሮሜ 8:23)
ይህ መቃተት በቅዱሳን ሁሉ ዘንድ ያለ ነው፤ በብዙም በጥቂትም ሁላችን እንሰማዋለን። የማጕረምረም ወይም የማማረር መቃተት አይደለም፤ ከጭንቀት ይልቅ የናፍቆት ድምፅ ነው። መያዣውን ስለ ተቀበልን ድርሻችንን በሙሉ እንመኛለን፤ መንፈስ፥ ነፍስና ሥጋ የሆነው ሦስትነት ያለው ሰውነታችን ሁሉ ከውድቀቱ የመጨረሻ ቅሪት ነጻ እንዲወጣ እንቃትታለን፤ መበስበስን፥ ድካምንና ውርደትን አውልቀን አለመበስበስን፥ አለመሞትን፥ ክብርን፥ ጌታ ኢየሱስ ለሕዝቡ የሚሰጠውን መንፈሳዊ አካል ለመልበስ እንናፍቃለን። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን እንዲገለጥ እንናፍቃለን። «እንቃትታለን»፤ ነገር ግን «በውስጣችን» ነው። ጐስቋላ ስለ ሆነ ቅዱስ እንደ ሆነ ሰዎችን ለማሳመን የሚፈልግ የግብዝ መቃተት አይደለም። ትካዜዎቻችን ቅዱሳን ነገሮች ናቸው፤ በውጭ ለማውራት እጅግ የተቀደሱ ናቸው። ናፍቆታችንን ለጌታችን ብቻ እንጠብቀዋለን። ከዚያም ሐዋርያው «እየተጠባበቅን» ይላል፤ ከዚህም እንደ ዮናስ ወይም እንደ ኤልያስ «ልሙት» ባሉ ጊዜ እንደ ተቈጡ መቈጣት እንደሌለብን እንማራለን፤ ሥራ ስለ ሰለቸን እያለቀስን የሕይወትን ፍጻሜ መናፈቅ የለብንም፤ የጌታ ፈቃድ እስኪፈጸም ድረስም ከአሁኑ መከራችን ለማምለጥ መመኘት የለብንም። ስለ መክበር መቃተት አለብን፤ ጌታ የሚወስነው የሚበልጥ መሆኑን አውቀን ግን በትዕግሥት ልንጠብቀው ይገባናል። መጠበቅ መዘጋጀትን ያመለክታል። ውዱ በሩን ከፍቶ ወደ ራሱ እንዲወስደን እየጠበቅን በደጅ ልንቆም ይገባናል። ይህ «መቃተት» መፈተኛ ነው። ሰውን በሚቃትትለት ነገር ልትመዝነው ትችላለህ። አንዳንዶች ሀብትን ለማግኘት ይቃትታሉ፤ ማሞንን ያመልካሉ፤ አንዳንዶች ከሕይወት ችግሮች በታች ዘወትር ይቃትታሉ፤ እነርሱ ትዕግሥት የሌላቸው ብቻ ናቸው፤ እግዚአብሔርን የሚናፍቅ፥ ክርስቶስን እስኪመስል ድረስ የማያርፍ ሰው ግን እርሱ የተባረከ ሰው ነው። እግዚአብሔር ስለ ጌታ መምጣትና እርሱ ስለሚያመጣልን ትንሣኤ እንድንቃትት ይርዳን።
ዲሴምበር 5
«እግዚአብሔርም አራት ጠራቢዎችን አሳየኝ።» (ዘካርያስ 1:20)
በዚህ ምዕራፍ በተገለጠው ራእይ ነቢዩ አራት አስፈሪ ቀንዶችን አየ። ወዲህና ወዲያ እየወጉ ብርቱዎቹንና ኃያላኑን ይጥሉ ነበር፤ ነቢዩም «እነዚህ ምንድር ናቸው?» ብሎ ጠየቀ። መልሱም «እስራኤልን የበተኑ ቀንዶች እነዚህ ናቸው» የሚል ነበረ። የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያስጨነቁትን ኃይላት የሚያሳይ ምስል በፊቱ አየ። ቀንዶቹ አራት ነበሩ፤ ቤተ ክርስቲያን ከአራቱም ማዕዘን ትጠቃለችና። ነቢዩ ቢደነግጥ ተገቢ ነበር፤ ነገር ግን ድንገት አራት ጠራቢዎች በፊቱ ታዩ። «እነዚህ ምን ያደርጋሉ?» ብሎ ጠየቀ። እነዚህ እግዚአብሔር እነዚያን ቀንዶች እንዲሰባብሩ ያገኛቸው ሰዎች ናቸው። እግዚአብሔር ለሥራው ሰዎችን ሁልጊዜ ያገኛል፤ በትክክለኛውም ጊዜ ያገኛቸዋል። ነቢዩ የሚሠራ ነገር ሳይኖር ጠራቢዎቹን አስቀድሞ አላየም፤ አስቀድሞ «ቀንዶቹን»፥ ከዚያም «ጠራቢዎቹን» አየ። ደግሞም ጌታ በቂ ሰዎችን ያገኛል። ሦስት ጠራቢዎችን አላገኘም፥ አራት እንጂ፤ ቀንዶቹ አራት ነበሩና፥ ሠራተኞቹም አራት መሆን ነበረባቸው። እግዚአብሔር ትክክለኞቹን ሰዎች ያገኛል፤ የሚጽፉ አራት የብዕር ሰዎችን አይደለም፥ ንድፍ የሚያወጡ አራት የሕንፃ ባለሙያዎችንም አይደለም፥ ሸካራውን ሥራ የሚሠሩ አራት ጠራቢዎችን እንጂ። ስለ እግዚአብሔር ታቦት የምትንቀጠቀጡ እናንተ ሆይ፥ «ቀንዶቹ» ሲያስቸግሩ «ጠራቢዎቹ» እንደሚገኙ እርግጠኞች ሁኑ። ስለ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ድካም በማንኛውም ጊዜ መጨነቅ አያስፈልጋችሁም፤ አሕዛብን የሚያናውጥ ጀግና ተሐድሶ አራማጅ በተሰወረ ስፍራ እያደገ ሊሆን ይችላል፤ ክሪሶስቶሞች ለድኾች ልጆች ከተከፈቱት ትምህርት ቤቶቻችን፥ አውግስጢኖሶችም ከለንደን ድኽነት ድቅድቅ ጨለማ ሊወጡ ይችላሉ። ጌታ አገልጋዮቹን የት እንደሚያገኛቸው ያውቃል። ብዙ ኃያላን ሰዎችን በድብቅ አዘጋጅቶ ይዟል፤ በቃሉም ወደ ሰልፍ ይነሣሉ፤ «ሰልፉ የእግዚአብሔር ነውና»፥ ድሉንም ለራሱ ያገኛል። ለክርስቶስ ታማኞች ሆነን እንኑር፤ እርሱም በግል በምንቸገርበት ቀን ቢሆን ወይም ቤተ ክርስቲያኑ በአደጋ ላይ በምትሆንበት ወቅት በትክክለኛው ጊዜ መከላከያ ያስነሣልናል።
ዲሴምበር 6
«ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር።» (ራእይ 1:13)
«የሰው ልጅ የሚመስለውን» ዮሐንስ በፍጥሞ ተገለጠለት፤ የተወደደው ደቀ መዝሙርም የወርቅ መታጠቂያ እንደ ታጠቀ አስተዋለ። መታጠቂያ ነው፤ ኢየሱስ በምድር ሳለ ከቶ ሳይታጠቅ አልነበረምና፥ ሁልጊዜም ለአገልግሎት ተዘጋጅቶ ቆሞ ነበርና፤ አሁንም በዘላለሙ ዙፋን ፊት የተቀደሰ አገልግሎቱን አላቋረጠም፤ እንደ ካህን «በብልሃት የተሠራውን የኤፉዱን መታጠቂያ» ታጥቋል እንጂ። ለእኛ ያለውን የፍቅር አገልግሎቱን መፈጸም አለማቋረጡ ለእኛ መልካም ነው፤ ስለ እኛ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት መኖሩ ከሁሉ ከሚበልጡ መጠበቂያዎቻችን አንዱ ነውና። ኢየሱስ ከቶ ሥራ ፈት አይደለም፤ አገልግሎቱ እንዳበቃ ያህል ልብሱ ከቶ አይላላም፤ የሕዝቡን ጉዳይ በትጋት ያካሂዳል። የወርቅ መታጠቂያ ነው፤ የአገልግሎቱን ብልጫ፥ የማንነቱን ንጉሣዊነት፥ የክብሩን ከፍታ፥ የዋጋውን ግርማ ለማሳየት። ከእንግዲህ ከአፈር ውስጥ አይጮኽም፤ ካህን ብቻ ሳይሆን ንጉሥም ሆኖ በሥልጣን ይማልዳል። ጉዳያችን በዙፋን ላይ በተቀመጠው በመልከ ጼዴቃችን እጅ ፍጹም ደኅና ነው።
ጌታችን ለሕዝቡ ሁሉ ምሳሌ ይሰጣል። መታጠቂያችንን ከቶ መፍታት የለብንም። ይህ በምቾት የምንተኛበት ጊዜ አይደለም፤ የአገልግሎትና የሰልፍ ወቅት ነው። የእውነትን መታጠቂያ በወገባችን ዙሪያ ይበልጥ አጥብቀን ልንታጠቅ ያስፈልገናል። የወርቅ መታጠቂያ ነው፤ ስለዚህ እጅግ ባለ ጠጋ ጌጣችን ይሆናል፤ እጅግም ያስፈልገናል፤ እውነት በኢየሱስ እንዳለ በእውነትና መንፈስ በሚሠራው ታማኝነት በሚገባ ያልጠነከረ ልብ በዚህ ሕይወት ነገሮች በቀላሉ ይጠላለፋልና፥ በፈተናም ወጥመዶች ይሰናከላልና። መጻሕፍትን እንደ መታጠቂያ በዙሪያችን ካልታጠቅናቸው፥ ተፈጥሮአችንን ሁሉ እንዲከብቡ፥ የጠባያችንንም ክፍል ሁሉ በሥርዓት እንዲጠብቁ፥ ሰውነታችንንም ሁሉ እንዲያጸኑ ካላደረግናቸው፥ መያዛችን ከንቱ ነው። ኢየሱስ በሰማይ መታጠቂያውን ካልፈታ፥ እኛማ በምድር ላይ እንዴት እንፈታለን! እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ ቁሙ።
ዲሴምበር 7
«በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ።» (1ኛ ቆሮንቶስ 9:22)
የጳውሎስ ታላቅ ዓላማ ማስተማርና ማሻሻል ብቻ ሳይሆን ማዳን ነበር። ከዚህ ያነሰ ማንኛውም ነገር ባሳዘነው ነበር፤ ሰዎች በልባቸው እንዲታደሱ፥ ይቅር እንዲባሉ፥ እንዲቀደሱ፥ በእውነትም እንዲድኑ ይፈልግ ነበር። የክርስቲያን ድካማችን ከዚህ ታላቅ ግብ በታች ወዳለ ነገር ያነጣጠረ ነበርን? እንግዲያስ መንገዳችንን እናቅና፤ ሰዎችን አስተምረንና የሥነ ምግባር ትምህርት ሰጥተን በኋለኛው ታላቅ ቀን ሳይድኑ በእግዚአብሔር ፊት ቢቀርቡ ምን ይጠቅማል? በሕይወታችን ሁሉ ዝቅተኛ ዓላማዎችን ፈልገን ሰዎች መዳን እንደሚያስፈልጋቸው ብንረሳ የልብሳችን ዘርፍ በደም ይቀላል። ጳውሎስ የሰውን ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ጥፋት ያውቅ ነበር፤ ሊያስተምረው አልሞከረም፥ ሊያድነው እንጂ፤ ሰዎች ወደ ገሃነም ሲሰምጡ አየ፤ ስለ ማሠልጠናቸው አልተናገረም፥ ከሚመጣው ቍጣ ስለ ማዳናቸው እንጂ። መዳናቸውን ለማግኘት ወንጌልን በየስፍራው ለማውራት፥ ሰዎችን ለማስጠንቀቅና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ለመለመን በማይደክም ቅንዓት ራሱን ሰጠ። ጸሎቱ የማያቋርጥ ልመና፥ ድካሙም የማያባራ ነበር። ነፍሳትን ማዳን የሚበላው ፍላጎቱ፥ ምኞቱና ጥሪው ነበር። ለሰዎች ሁሉ ባሪያ ሆነ፤ ስለ ወገኑ ደከመ፤ ወንጌልን ባይሰብክ በውስጡ ወዮታ ይሰማው ነበር። ጥላቻን ለመከላከል የራሱን ምርጫ ተወ፤ ግድ በማይሰጡ ነገሮች ፈቃዱን አስገዛ፤ ሰዎች ወንጌልን ብቻ ቢቀበሉ ስለ ሥርዓትና ስለ ወግ ምንም ጥያቄ አላነሣም፤ ወንጌል ለእርሱ ከሁሉ የሚበልጥ ብቸኛ ጉዳይ ነበር። አንዳንዶችን ማዳን ቢችል ይረካ ነበር። ይህ የሚጋደልለት አክሊል፥ የድካሙና ራሱን የመካዱ ሁሉ ብቸኛና በቂ ዋጋ ነበር። ውድ አንባቢ፥ አንተና እኔ ነፍሳትን ለማሸነፍ በዚህ ክቡር መጠን ኖረናልን? ያው ሁሉን የሚውጥ ምኞት ይዞናልን? ካልያዘን ለምን? ኢየሱስ ስለ ኃጢአተኞች ሞተ፤ እኛስ ስለ እነርሱ መኖር አንችልምን? ርኅራኄያችን የት አለ? በሰዎች መዳን የእርሱን ክብር ካልፈለግን ለክርስቶስ ያለን ፍቅር የት አለ? ጌታ ለሰዎች ነፍሳት በማይጠፋ ቅንዓት ፈጽሞ ቢያጠግበን ምንኛ መልካም ነበር!
ዲሴምበር 8
«አቤቱ፥ በቸርነትህ ለድሆች አዘጋጀህ።» (መዝሙር 68:10)
የእግዚአብሔር ስጦታዎች ሁሉ አስቀድሞ ለታዩ ችግሮች ተከማችተው የተዘጋጁ ስጦታዎች ናቸው። ፍላጎታችንን አስቀድሞ ያያል፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ካከማቸው ሙላትም በቸርነቱ ለድሆች ያዘጋጃል። ሊደርስ ለሚችለው ችግር ሁሉ በእርሱ ልትታመን ትችላለህ፤ እያንዳንዱን ያለ ስሕተት አስቀድሞ አውቆታልና። በማንኛውም ሁኔታ ስለ እኛ «እንዲህና እንዲህ እንደምትሆን አውቄ ነበር» ሊል ይችላል። አንድ ሰው በምድረ በዳ ይጓዛል፤ የአንድ ቀን መንገድ ሄዶ ድንኳኑን ከተከለ በኋላ በጓዙ ያልያዛቸው ብዙ የምቾትና የግድ የሚያስፈልጉ ነገሮች እንደሚጐድሉት ያገኛል። «ወይ!» ይላል፤ «ይህን አስቀድሜ አላሰብሁም ነበር፤ ይህን መንገድ እንደ ገና ብሄድ ለምቾቴ እጅግ የሚያስፈልጉትን እነዚህን ነገሮች ይዤ እሄድ ነበር።» እግዚአብሔር ግን የሚንከራተቱትን የድሆች ልጆቹን ፍላጎት ሁሉ አስቀድሞ በሚያይ ዓይኑ ተመልክቶአል፤ ያ ችግር በደረሰ ጊዜም ስንቁ ተዘጋጅቶ ይጠብቃል። በልብ ድሆች ለሆኑት ያዘጋጀው ቸርነት ነው፤ ቸርነት፥ ቸርነት ብቻ። «ጸጋዬ ይበቃሃል»። «እንደ ዘመንህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል።»
አንባቢ ሆይ፥ ዛሬ ማታ ልብህ ከብዶአልን? እግዚአብሔር እንዲህ እንደሚሆን ያውቅ ነበር፤ ልብህ የሚፈልገው መጽናናት በጥቅሱ ጣፋጭ ማረጋገጫ ውስጥ ተከማችቶአል። አንተ ድሃና ችግረኛ ነህ፤ እርሱ ግን አስቦሃል፤ የሚያስፈልግህንም ትክክለኛ በረከት አዘጋጅቶ አስቀምጦልሃል። በተስፋው ቃል ተማጸን፤ እመነውም፤ ፍጻሜውንም ተቀበል። እንደ አሁኑ ርኩስ መሆንህ ተሰምቶህ የማያውቅ ይመስልሃልን? እነሆ፥ ያ ቀይ ምንጭ ኃጢአትህን ለማጠብ የቀድሞ ኃይሉን ሁሉ ይዞ አሁንም ክፍት ነው። ክርስቶስ ሊረዳህ የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ከቶ አትገባም። ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቋቋመው የማይችለው ጭንቅ በመንፈሳዊ ጉዳይህ ከቶ አይደርስም፤ ታሪክህ ሁሉ በኢየሱስ አስቀድሞ ታውቆአልና፥ ተዘጋጅቶለታልምና።
ዲሴምበር 9
«ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ፥ በታመነም መኖሪያ፥ በጸጥታም ማረፊያ ይኖራሉ።» (ኢሳይያስ 32:18)
ሰላምና ዕረፍት ዳግመኛ ላልተወለዱ አይደሉም፤ የጌታ ሕዝብ ብቻ የራሳቸው የሆነ ልዩ ርስት ናቸው። የሰላም አምላክ ልባቸው በእርሱ ላይ ለተደገፈ ፍጹም ሰላምን ይሰጣል። ሰው ገና ሳይወድቅ አምላኩ ያበቡትን የዔድን ጥላዎች ጸጥ ያሉ ማረፊያዎቹ አድርጎ ሰጠው፤ ወዮ! ኃጢአት ያን ውብ የንጽሕና መኖሪያ ምንኛ ፈጥኖ አጠፋው! ጥፋት ውኃ በደለኛውን ትውልድ ባጠፋበት በዓለም አቀፉ የቍጣ ቀን የተመረጠው ቤተ ሰብ በመርከቡ ማረፊያ ውስጥ በጸጥታ ተጠበቀ፤ መርከቡም ከተፈረደበት ከአሮጌው ዓለም ወደ ቀስተ ደመናውና ወደ ኪዳኑ አዲስ ምድር አንሳፍፎ አሻገራቸው፤ በዚህም የመዳናችን መርከብ የሆነውን ኢየሱስን አመለከተ። አጥፊው መልአክ በኵሮችን በመታ ጊዜ እስራኤል በግብፅ ደም በተረጨባቸው መኖሪያዎቻቸው ውስጥ በደኅና ዐረፉ፤ በምድረ በዳም የደመናው ዓምድ ጥላና ውኃ የሚፈስስበት ዓለት ለደከሙት መንገደኞች ጣፋጭ ዕረፍት ሰጡ። በዚህ ሰዓት ቃሉ እውነትና ኃይል የሞላበት መሆኑን አውቀን በታማኙ አምላካችን ተስፋዎች እናርፋለን፤ መጽናናት ራሱ በሆኑት በቃሉ ትምህርቶች እናርፋለን፤ የደስታ ወደብ በሆነው በጸጋው ኪዳን እናርፋለን። በዓዶላም ከነበረው ከዳዊት፥ ወይም በቅሉ ሥር ከነበረው ከዮናስ ይልቅ እጅግ የተወደድን ነን፤ መጠጊያችንን ማንም ሊወርረው ወይም ሊያጠፋው አይችልምና። የኢየሱስ ማንነት ለሕዝቡ ጸጥ ያለ ማረፊያ ነው፤ እንጀራውን በመቍረስ፥ ቃሉን በመስማት፥ መጻሕፍትን በመመርመር፥ በጸሎት ወይም በምስጋና ወደ እርሱ ስንቀርብ፥ ወደ እርሱ የምንቀርብበት መንገድ ሁሉ ለመንፈሳችን የሰላም መመለስ ሆኖ እናገኘዋለን።
«የፍቅርን ቃል እሰማለሁ፥ ደሙንም እመለከታለሁ፤
ታላቁን መሥዋዕት አያለሁ፥ ከእግዚአብሔርም ጋር ሰላም አለኝ።
እንደ ይሖዋ ስም የጸና የዘላለም ሰላም ነው፤
እንደ ጽኑ ዙፋኑ የማይናወጥ፥ ለዘላለም ያው ነው፤
ደመናት ይሄዳሉ ይመጣሉ፥ ዐውሎ ነፋስም ሰማዬን ይጠርጋል፤
በደም የታተመው ይህ ወዳጅነት አይለወጥም፤ መስቀሉም ሁልጊዜ ቅርብ ነው።»
ዲሴምበር 10
«ጌታ ልብዋን ከፈተላት።» (የሐዋርያት ሥራ 16:14)
በልድያ መለወጥ ውስጥ ብዙ ትኩረት የሚስቡ ነጥቦች አሉ። የተፈጸመው በእግዚአብሔር አሠራር በተዘጋጁ ሁኔታዎች ነበር። እርስዋ ከትያጥሮን ከተማ የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ ነበረች፤ ነገር ግን ጳውሎስን ለመስማት ልክ በትክክለኛው ጊዜ በፊልጵስዩስ እናገኛታለን፤ የጸጋ ሠራተኛ የሆነው የእግዚአብሔር አሠራር ወደ ትክክለኛው ስፍራ መራት። ደግሞም ጸጋ ነፍስዋን ለበረከቱ ያዘጋጅ ነበር፤ ጸጋ ለጸጋ ያዘጋጅ ነበር። አዳኙን አታውቀውም ነበር፤ ነገር ግን አይሁዳዊት እንደ መሆንዋ ኢየሱስን ለማወቅ መልካም መወጣጫ ደረጃዎች የሆኑ ብዙ እውነቶችን ታውቅ ነበር። መለወጥዋ የተፈጸመው መንገዶቹን በመጠቀም ነበር። በሰንበት ቀን ጸሎት ወደሚደረግበት ስፍራ ሄደች፤ በዚያም ጸሎት ተሰማ። የጸጋን መንገዶች ከቶ ቸል አትበል፤ እግዚአብሔር በቤቱ ሳንሆን ሊባርከን ይችላል፤ ከቅዱሳኑ ጋር በኅብረት ስንሆን ግን እንደሚባርከን ተስፋ የምናደርግበት የበለጠ ምክንያት አለን። «ጌታ ልብዋን ከፈተላት» የሚለውን ቃል ልብ በል። የገዛ ልብዋን የከፈተችው እርስዋ አይደለችም። ጸሎትዋ አላደረገውም፤ ጳውሎስም አላደረገውም። ለሰላማችን የሚሆነውን ለመቀበል ልብን መክፈት ያለበት ጌታ ራሱ ነው። በበሩ ቀዳዳ መክፈቻውን አግብቶ ከፍቶ ለራሱ መግቢያ ማግኘት የሚችል እርሱ ብቻ ነው። የልብ ፈጣሪ እንደ ሆነ የልብ ጌታም ነው። የተከፈተው ልብ የመጀመሪያው የውጭ ማስረጃ መታዘዝ ነበር። ልድያ በኢየሱስ እንዳመነች ተጠመቀች። የእግዚአብሔር ልጅ ለመዳኑ የግድ ያልሆነውን፥ በራስ ወዳድነት የኵነኔ ፍርሃት ያልተጫነበትን፥ ነገር ግን ለጌታው የቀላል መታዘዝና የኅብረት ሥራ የሆነውን ትእዛዝ ለመፈጸም ፈቃደኛ ሲሆን ይህ የትሑትና የተሰበረ ልብ ጣፋጭ ምልክት ነው። ቀጣዩ ማስረጃ ለሐዋርያት በምስጋና በተደረገ የደግነት ሥራ የተገለጠ ፍቅር ነበር። ለቅዱሳን ያለ ፍቅር ሁልጊዜ የእውነተኛ ተለዋጭ ምልክት ነው። ለክርስቶስ ወይም ለቤተ ክርስቲያኑ ምንም የማያደርጉ ሰዎች «የተከፈተ» ልብ እንዳላቸው የሚያሳዩት ማስረጃ ደካማ ነው። ጌታ ሆይ፥ ሁልጊዜ የተከፈተ ልብ ስጠኝ።
ዲሴምበር 11
«የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና።» (ቈላስይስ 3:24)
ይህ ቃል የተነገረው ለየትኞቹ ምርጥ ባለ ሥልጣናት ነበር? መለኮታዊ መብት አለን ብለው በትዕቢት ለሚመኩ ነገሥታት ነውን? አይደለም! ብዙ ጊዜ ራሳቸውን ወይም ሰይጣንን ያገለግላሉ፤ ለአጭር ሰዓታቸው የአስመሳይ ግርማቸውን እንዲለብሱ በትዕግሥቱ የፈቀደላቸውንም አምላክ ይረሳሉ። እንግዲያስ ሐዋርያው የሚናገረው «በእግዚአብሔር እጅግ የተከበሩ አባቶች» ለሚባሉት ለጳጳሳት ወይም «ለተከበሩ ሊቃነ ዲያቆናት» ነውን? በፍጹም አይደለም፤ ጳውሎስ ስለ እነዚህ የሰው ፈጠራዎች ብቻ ስለ ሆኑት ምንም አያውቅም ነበር። ይህ ቃል የተነገረው ለእረኞችና ለአስተማሪዎች ወይም በአማኞች መካከል ላሉ ባለ ጠጎችና የተከበሩ ሰዎች እንኳ አልነበረም፤ ለአገልጋዮች፥ አዎን፥ ለባሪያዎች ነበር እንጂ። ሐዋርያው በሚደክሙት ብዙ ሰዎች፥ በቅጥር ሠራተኞች፥ በቀን ሠራተኞች፥ በቤት አገልጋዮች፥ በማድ ቤት ተላላኪዎች መካከል፥ ዛሬም እኛ እንደምናገኘው፥ ከጌታ ምርጦች አንዳንዶችን አገኘ፤ ለእነርሱም «ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥ ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና። የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና» ይላቸዋል። ይህ ቃል አሰልቺ የሆነውን የምድራዊ ሥራ ድግግሞሽ ያከብራል፥ በእጅግ ዝቅተኛ ሥራዎችም ዙሪያ የክብር ብርሃን ያፈስሳል። እግርን ማጠብ የባሪያ ሥራ ሊሆን ይችላል፤ የእርሱን እግር ማጠብ ግን የንጉሥ ሥራ ነው። የጫማን ጠፍር መፍታት የተናቀ ሥራ ነው፤ የታላቁን ጌታ ጫማ መፍታት ግን የልዑል መብት ነው። ወንዶችና ሴቶች ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር ሲያደርጉ ሱቁ፥ ጎተራው፥ የዕቃ ማጠቢያው ክፍልና የብረት ሠሪው ቤት መቅደሶች ይሆናሉ! ያን ጊዜ «መለኮታዊ አገልግሎት» የጥቂት ሰዓታትና የጥቂት ስፍራዎች ነገር አይሆንም፤ ሕይወት ሁሉ ለጌታ ቅድስና ይሆናል፤ ስፍራና ነገርም ሁሉ እንደ ማደሪያው ድንኳንና እንደ ወርቁ መቅረዝ የተቀደሰ ይሆናል።
«አምላኬና ንጉሤ ሆይ፥ በነገር ሁሉ አንተን ማየት አስተምረኝ፤
በማንኛውም ነገር የማደርገውንም ለአንተ እንደማደርገው ላደርገው።
ሁሉ ከአንተ ሊካፈል ይችላል፤ ምንም ነገር እጅግ የተናቀ አይደለም፥
በዚህ ቅባት፥ ስለ አንተ በሚለው፥ የማይደምቅና የማይነጻ።
ይህን ቃል የያዘ አገልጋይ አድካሚውን ሥራ መለኮታዊ ያደርጋል፤
ለሕግህ ብሎ ክፍልን የሚጠርግ ክፍሉንም ሥራውንም ያሳምራል።»
ዲሴምበር 12
«እግዚአብሔርን ከድተዋል።» (ሆሴዕ 5:7)
አማኝ ሆይ፥ ይህ የሚያሳዝን እውነት ነው! አንተ በጌታ የተወደድህ፥ በደም የተዋጀህ፥ በጸጋ የተጠራህ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ የተጠበቅህ፥ በተወደደው ልጁ ተቀባይነት ያገኘህ፥ ወደ ሰማይ በመንገድ ላይ ያለህ ነህ፤ ሆኖም «ከድተሃል»፤ ከሁሉ የሚበልጥ ወዳጅህ የሆነውን እግዚአብሔርን ከድተሃል፤ የእርሱ የሆንህለትን ኢየሱስን ከድተሃል፤ ለዘላለም ሕይወት ሕያው ያደረገህን መንፈስ ቅዱስን ከድተሃል! በስእለትና በተስፋ ነገር ምንኛ ከዳተኛ ሆነሃል! የታጨህበትን ፍቅር፥ ያን ደስተኛ ጊዜ፥ የመንፈሳዊ ሕይወትህን የጸደይ ወራት ታስታውሳለህን? ያን ጊዜ ከጌታህ ጋር ምንኛ ተጣብቀህ ነበር! እንዲህም አልህ፦ «በግድየለሽነት ከቶ አይከሰኝም፤ በአገልግሎቱ መንገድ እግሮቼ ከቶ አይዘገዩም፤ ልቤ ሌሎችን ፍቅሮች ተከትሎ እንዲቅበዘበዝ አልፈቅድም፤ ሊነገር የማይችል ጣፋጭነት ሁሉ በእርሱ ውስጥ አለ። ስለ ጌታዬ ስለ ኢየሱስ ሁሉን እተዋለሁ።» እንዲህ ሆኖአልን? ወዮ! ኅሊና ቢናገር እንዲህ ይላል፦ «መልካም ተስፋ የሰጠው እጅግ ክፉ አድርጎ ፈጸመ። ጸሎት ብዙ ጊዜ በችኮላ ተደርጎአል፤ አጭር ነበር፥ ጣፋጭ ግን አልነበረም፤ ፈጣን ነበር፥ የጋለ ግን አልነበረም። ከክርስቶስ ጋር ያለው ኅብረት ተረስቶአል። በሰማያዊ አሳብ ፋንታ ሥጋዊ ጭንቀት፥ ዓለማዊ ከንቱነትና የክፋት አሳብ ነበረ። በአገልግሎት ፋንታ አለመታዘዝ፥ በትጋት ፋንታ ለብታ፥ በትዕግሥት ፋንታ ቍጣ፥ በእምነት ፋንታ በሥጋ ክንድ መታመን ነበረ፤ የመስቀል ወታደር እንደ መሆንም እጅግ በሚያሳፍር መጠን ፍርሃት፥ አለመታዘዝና መክዳት ነበረ።» «ከድተሃል።» ኢየሱስን መክዳት! ይህን ለመኰነን ምን ቃላት ይበቃሉ? ቃላት ብዙም አይጠቅሙም፤ በእኛ ውስጥ በእርግጥ ያለውን ኃጢአት የንስሐ አሳባችን ይጸየፈው። ኢየሱስ ሆይ፥ ቍስሎችህን ከድተናል! ይቅር በለን፤ ዳግመኛም እንዳንበድል አድርገን! ከቶ የማይረሳንን፥ ዛሬም ስሞቻችንን በደረት ኪሱ ላይ ቀርጾ በዘላለሙ ዙፋን ፊት የሚቆመውን እርሱን መክዳት ምንኛ ያሳፍራል!
ዲሴምበር 13
«መስኮቶችሽንም ከኬልቄዶን ድንጋይ አደርጋለሁ።» (ኢሳይያስ 54:12)
ቤተ ክርስቲያን በሰማያዊ ኃይል በተሠራና በመለኮታዊ ጥበብ በተነደፈ ሕንፃ እጅግ አስተማሪ በሆነ መንገድ ትመሰላለች። እንዲህ ያለው መንፈሳዊ ቤት ጨለማ ሊሆን አይገባውም፤ እስራኤላውያን በመኖሪያዎቻቸው ብርሃን ነበራቸውና፤ ስለዚህ ብርሃን እንዲገባ፥ የሚኖሩበትም ወደ ውጭ እንዲመለከቱ መስኮቶች ሊኖሩ ይገባል። እነዚህ መስኮቶች እንደ ኬልቄዶን ውድ ናቸው፤ ቤተ ክርስቲያን ጌታዋን፥ ሰማይንና በአጠቃላይ መንፈሳዊ እውነትን የምታይባቸው መንገዶች እጅግ ከፍ ያለ ግምት ሊሰጣቸው ይገባል። ኬልቄዶን ከዕንቍዎች መካከል እጅግ ግልጽ የሆነው አይደለም፤ ቢበዛ በከፊል ብቻ ብርሃን የሚያሳልፍ ነው፦
«ስለዚያ ሕይወት ያለን እውቀት ጥቂት ነው፤
የእምነት ዓይናችንም የደበዘዘ ነው።»
እምነት ከእነዚህ ውድ የኬልቄዶን መስኮቶች አንዱ ነው፤ ነገር ግን ወዮ! ብዙ ጊዜ እጅግ ጭጋጋማና በደመና የተሸፈነ ስለ ሆነ በድንግዝግዝ ብቻ እናያለን፥ ከምናየውም ብዙውን እንሳሳታለን። ሆኖም በአልማዝ መስኮቶች ትኩር ብለን ማየትና እኛ እንደ ታወቅን ማወቅ ባንችልም፥ መስተዋቱ እንደ ኬልቄዶን የደበዘዘ ቢሆንም እንኳ ፈጽሞ የሚወደደውን እርሱን መመልከት የከበረ ነገር ነው። ልምድ ሌላው ደብዛዛ ግን ውድ መስኮት ነው፤ የረጋ የአምልኮ ብርሃን ይሰጠናል፤ በዚያም ብርሃን በገዛ መከራችን በኩል የሕማም ሰው የሆነውን የእርሱን መከራ እናያለን። ደካሞቹ ዓይኖቻችን የጌታን ክብር የሚያስገቡ ጥርት ያሉ የብርጭቆ መስኮቶችን ሊቋቋሙ አይችሉም ነበር፤ በልቅሶ በደበዘዙ ጊዜ ግን የጽድቅ ፀሐይ ጨረሮች ይለዝባሉ፥ በኬልቄዶን መስኮቶችም በኩል ለተፈተኑ ነፍሳት ከቃል በላይ በሚያጽናና ለስላሳ ብርሃን ያበራሉ። መቀደስ፥ ጌታችንን እንድንመስል ስለሚያደርገን፥ ሌላው የኬልቄዶን መስኮት ነው። ሰማያውያን በሆንን መጠን ብቻ ሰማያዊ ነገሮችን ልናስተውል እንችላለን። ልበ ንጹሖች ንጹሑን አምላክ ያያሉ። ኢየሱስን የሚመስሉ እርሱን እንዳለ ያዩታል። እርሱን የምንመስለው እጅግ ጥቂት ስለ ሆነ መስኮቱ ኬልቄዶን ብቻ ነው፤ በጥቂቱም ቢሆን ስለምንመስለው ግን ኬልቄዶን ነው። ስላለን ነገር እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፥ ተጨማሪውንም እንናፍቃለን። እግዚአብሔርንና ኢየሱስን፥ ሰማይንና እውነትን ፊት ለፊት የምናየው መቼ ነው?
ዲሴምበር 14
«ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ።» (ገላትያ 2:20)
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባደረገው ነገር ሁሉ እንደ ታላቅ የሕዝብ ወኪል ሆኖ ሠራ፤ በመስቀል ላይ መሞቱም በውጤቱ የሕዝቡ ሁሉ ሞት ነበረ። በዚያን ጊዜ ቅዱሳኑ ሁሉ ለፍትሕ የሚገባውን ከፈሉ፥ ስለ ኃጢአታቸውም ሁሉ ለመለኮታዊ በቀል ማስተስረያ አቀረቡ። የአሕዛብ ሐዋርያ ከክርስቶስ ምርጥ ሕዝብ አንዱ እንደ መሆኑ በክርስቶስ ሆኖ በመስቀል ላይ እንደ ሞተ ማሰብ ደስ ያሰኘው ነበር። ይህን እንደ ትምህርት ከማመን አልፎ ተስፋውን በላዩ አሳርፎ በሙሉ መታመን ተቀበለው። በክርስቶስ ሞት ኃይል መለኮታዊውን ፍትሕ እንዳረካ፥ ከእግዚአብሔርም ጋር መታረቅን እንዳገኘ አመነ። ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስ በክርስቶስ መስቀል ላይ ራሷን እንደ መዘርጋት ያህል ስትዘረጋና እንዲህ ሲሰማት እንዴት የተባረከ ነገር ነው፦ «ሞቻለሁ፤ ሕጉ ገድሎኛል፤ ስለዚህም ከኃይሉ ነጻ ነኝ፤ በዋሴ ውስጥ እርግማኑን ተሸክሜአለሁና፥ በምትኬም አካል ሕጉ በፍርድ መንገድ ሊያደርገው የሚችለው ሁሉ በእኔ ላይ ተፈጽሞአል፤ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁና።»
ጳውሎስ ግን ከዚህም የበለጠ ማለቱ ነበር። በክርስቶስ ሞት ማመንና በእርሱ መታመን ብቻ ሳይሆን የቀድሞው የረከሰ ባሕርዩ እንዲሰቀል በማድረግ ኃይሉን በራሱ ውስጥ በእውነት ተሰማው። የኃጢአትን ተድላዎች ባየ ጊዜ «በእነዚህ ደስ ሊለኝ አልችልም፤ ለእነርሱ ሞቻለሁ» አለ። የእውነተኛ ክርስቲያን ሁሉ ልምድ እንዲህ ነው። ክርስቶስን ከተቀበለ በኋላ ለዚህ ዓለም ፈጽሞ እንደ ሞተ ሰው ነው። ሆኖም ለዓለም መሞቱን እያወቀ በዚያው ጊዜ ከሐዋርያው ጋር ሆኖ ሕያው ነኝ ብሎ ሊጮኽ ይችላል። ለእግዚአብሔር ፍጹም ሕያው ነው። የክርስቲያን ሕይወት አቻ የሌለው እንቆቅልሽ ነው። ማንም ዓለማዊ ሰው ሊረዳው አይችልም፤ አማኙ ራሱ እንኳ ሊያስተውለው አይችልም። ሞቶአል፥ ሆኖም ሕያው ነው! ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎአል፥ ሆኖም በዚያው ጊዜ በአዲስ ሕይወት ከክርስቶስ ጋር ተነሥቶአል! መከራ ከተቀበለውና ደሙን ካፈሰሰው መድኃኒት ጋር አንድ መሆን፥ ለዓለምና ለኃጢአትም መሞት ነፍስን የሚያስደስቱ ነገሮች ናቸው። ኦ፥ በእነርሱ ይበልጥ ደስ ባለን!
ዲሴምበር 15
«መሠረትሽንም በሰንፔር እመሠርታለሁ።» (ኢሳይያስ 54:11)
የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን የሚታየው ብቻ ሳይሆን የማይታየውም ውብና ውድ ነው። መሠረቶች ከዓይን የተሰወሩ ናቸው፤ ጽኑዎች እስከ ሆኑ ድረስም ውድ እንዲሆኑ አይጠበቅም፤ በይሖዋ ሥራ ግን ሁሉ ነገር ወጥ ነው፤ በቸልታ የተሠራ ምንም የለም፥ የተናቀ ምንም የለም። የጸጋ ሥራ ጥልቅ መሠረቶች በውድነታቸው እንደ ሰንፔር ናቸው፤ ክብራቸውን ሊለካ የሚችል የሰው አእምሮ የለም። ከአልማዝ ይልቅ በጸናውና ዘመን በከንቱ እንደሚደክምባቸው ዕንቍዎች በሚዘልቀው በጸጋ ኪዳን ላይ እንሠራለን። የሰንፔር መሠረቶች ዘላለማውያን ናቸው፤ ኪዳኑም ሁሉን የሚችል አምላክ በሕይወት እስካለ ድረስ ይኖራል። ሌላው መሠረት የጌታ ኢየሱስ አካል ነው፤ እርሱም እንደ ሰንፔር ጥሩና ነውር የሌለበት፥ ዘላለማዊና ውብ ነው፤ ያለ ማቋረጥ የሚንከባለለውን የምድር ውቅያኖስ ጥልቅ ሰማያዊ ቀለምና ሁሉን የሚያቅፈውን የሰማይዋን ብሩህ ሰማያዊነት በአንድነት ያዋሕዳል። ጌታችን በገዛ ደሙ ተሸፍኖ በቆመ ጊዜ በአንድ ወቅት ከቀይ ዕንቍ ጋር ሊመሰል ይችል ነበር፤ አሁን ግን በለስላሳው የፍቅር ሰማያዊ ቀለም ሲያበራ እናየዋለን፤ የተትረፈረፈ፥ ጥልቅና ዘላለማዊ ፍቅር ነው። ዘላለማዊ ተስፋዎቻችን እንደ ሰንፔር ጥሩና ደመና የሌላቸው በሆኑት በእግዚአብሔር ፍትሕና ታማኝነት ላይ የተሠሩ ናቸው። የዳንነው በድርድር፥ ምሕረት ፍትሕን በማሸነፍ ወይም ሕግ ሥራውን በማቆም አይደለም፤ አይደለም፤ በመታመናችን መሠረት ውስጥ ጉድለትን እንዲያገኝ የንስርን ዓይን እንገዳደራለን—መሠረታችን ሰንፔር ነው፤ እሳትንም ይቋቋማል።
ጌታ ራሱ የሕዝቡን ተስፋ መሠረት ጥሎአል። የእኛ ተስፋ በእንዲህ ያለ መሠረት ላይ የተሠራ መሆኑን አለመሆኑን አጥብቆ መመርመር ይገባል። መልካም ሥራዎችና ሥርዓቶች የሰንፔር መሠረት አይደሉም፤ የእንጨት፥ የሣርና የአገዳ ናቸው እንጂ፤ የጣላቸውም እግዚአብሔር ሳይሆን የገዛ ትምክህታችን ነው። መሠረቶች ሁሉ በቅርቡ ይፈተናሉ፤ ረጅም ግንቡ በሚያሰጥም አሸዋ ላይ ስለ ተመሠረተ በታላቅ ድምፅ ለሚፈርስበት ወዮለት። በሰንፔር ላይ የተሠራ ግን ማዕበልንም እሳትንም በእርጋታ ሊጠብቅ ይችላል፤ ፈተናውን ይቋቋማልና።
ዲሴምበር 16
«አልሰማህም፥ አላወቅህም፥ ከጥንትም ጀምሮ ጆሮህ አልተከፈተም።» (ኢሳይያስ 48:8)
ይህ ክስ በተወሰነ መጠን በአማኞችም ደጅ ላይ ሊቀመጥ እንደሚችል ማስታወስ ያሳምማል፤ እነርሱ ብዙ ጊዜ በከፊል በመንፈስ የደነዘዙ ናቸውና። እኛ የእግዚአብሔርን ድምፅ እንደሚገባን ስለማንሰማ በራሳችን ብናለቅስ ይገባናል፤ «አልሰማህም»። በነፍስ ውስጥ ያላስተዋልናቸው የመንፈስ ቅዱስ ረጋ ያሉ እንቅስቃሴዎች አሉ፤ እንደ እርሳስ በከበደው አእምሮአችን ሳይስተዋሉ የቀሩ የመለኮታዊ ትእዛዝና የሰማያዊ ፍቅር ሹክሹክታዎች አሉ። ወዮ! በቸልታ አላዋቂዎች ሆነናል—«አላወቅህም»። በውስጣችን ልናያቸው የሚገባን ነገሮች አሉ፤ ሳይታወቁ እየገፉ የሄዱ ርኵሰቶች፥ እኛ ሳንከባከባቸው በውርጭ እንዳሉ አበቦች እየጠወለጉ ያሉ ጣፋጭ ፍቅሮች፥ የነፍሳችንን መስኮቶች በግንብ ባንዘጋ ኖሮ ልናያቸው የምንችላቸው የመለኮታዊ ፊት ብልጭታዎች። እኛ ግን አላወቅንም። ይህን ስናስብ እጅግ ጥልቅ በሆነ ራስን ማዋረድ እንዋረዳለን። ይህ ሁሉ ሞኝነትና አለማወቅ ከእኛ በኩል በእግዚአብሔር አስቀድሞ የታወቀ እንደ ነበረ፥ ያም አስቀድሞ ማወቁ ሳይከለክለው በምሕረት መንገድ ሊያደርግልን እንደ ወደደ ከዐውዱ ስንማር የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዴት ልናመልክ ይገባናል! ይህን ሁሉ እያየ ሊመርጠን የቻለውን ድንቅ ሉዓላዊ ጸጋ አድንቅ! ክርስቶስ ምን እንደምንሆን እያወቀ ስለ እኛ በተከፈለው ዋጋ ተደነቅ! በመስቀል ላይ የተሰቀለው እርሱ የማናምን፥ ወደ ኋላ የምንመለስ፥ ልባችን የቀዘቀዘ፥ ግድ የለሾች፥ ቸልተኞች፥ በጸሎትም የላላን መሆናችንን አስቀድሞ አየ፤ ሆኖም እንዲህ አለ፦ «እኔ አምላክህ እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ መድኃኒትህ ነኝ ... በዓይኔ ፊት ክቡር ስለ ሆንህ የተከበርህ ነህ፥ እኔም ወድጄሃለሁ፤ ስለዚህ ሰዎችን በአንተ ፋንታ፥ ሕዝቦችንም በነፍስህ ፋንታ እሰጣለሁ!» ኦ ቤዛነት ሆይ፥ እኛ ምን ያህል ጥቁሮች እንደ ሆንን ስናስብ እንዴት እጅግ አንጸባርቀህ ታበራለህ! ኦ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ ከዛሬ ጀምሮ የሚሰማ ጆሮንና የሚያስተውል ልብን ስጠን!
ዲሴምበር 17
«በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል።» (ዮሐንስ 10:9)
ራሱን ታላቁ እኔ ነኝ ብሎ የገለጠው ኢየሱስ ወደ እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን መግቢያ፥ ወደ እግዚአብሔርም ራሱ የመቅረቢያ መንገድ ነው። በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር ለሚመጣ ሰው አራት ምርጥ መብቶችን ይሰጠዋል።
1. ይድናል። ሰውን የገደለው ሸሽቶ የመማጸኛይቱን ከተማ በር አልፎ ገባ፥ በደኅናም ሆነ። ኖኅ በመርከቡ በር ገባ፥ ተጠበቀም። ኢየሱስን ለነፍሳቸው የእምነት በር አድርገው የሚቀበሉ ማንም አይጠፉም። በኢየሱስ በኩል ወደ ሰላም መግባት በዚያው በር ወደ ሰማይ ለመግባት ዋስትና ነው። ኢየሱስ ብቸኛው በር፥ የተከፈተ በር፥ ሰፊ በር፥ ደኅንነት ያለበት በር ነው፤ ወደ ክብር ለመግባት ተስፋውን ሁሉ በተሰቀለው ቤዛ ላይ የሚያሳርፍ ብፁዕ ነው።
2. ይገባል። የልጆችን እንጀራ እየተካፈለ፥ በክብራቸውና በደስታቸውም ሁሉ እየተሳተፈ ወደ መለኮታዊው ቤተሰብ መካከል የመግባት መብት ይኖረዋል። ወደ ኅብረት እልፍኞች፥ ወደ ፍቅር ግብዣዎች፥ ወደ ኪዳኑ መዝገቦች፥ ወደ ተስፋዎቹ ጎተራዎች ይገባል። በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ ነገሥታት ንጉሥ ይገባል፤ የጌታም ምሥጢር ከእርሱ ጋር ይሆናል።
3. ይወጣል። ይህ በረከት ብዙ ጊዜ ይረሳል። ለመሥራትና መከራ ለመቀበል ወደ ዓለም እንወጣለን፤ ነገር ግን በኢየሱስ ስምና ኃይል መውጣት እንዴት ያለ ምሕረት ነው! ለእውነት እንድንመሰክር፥ ያዘኑትን እንድናጽናና፥ ግድ የለሾችን እንድናስጠነቅቅ፥ ነፍሳትን እንድንማርክና እግዚአብሔርን እንድናከብር ተጠርተናል፤ መልአኩም ጌዴዎንን «በዚህ በኃይልህ ሂድ» እንዳለው፥ እንዲሁ ጌታ በስሙና በብርታቱ እንደ መልእክተኞቹ እንድንሄድ ይወዳል።
4. መሰማሪያም ያገኛል። ኢየሱስን የሚያውቅ ከቶ አይቸገርም። መግባቱም መውጣቱም እኩል ይጠቅሙታል፤ ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ኅብረት ያድጋል፥ ሌሎችንም በማጠጣት እርሱ ራሱ ይጠጣል። ኢየሱስን ሁሉ ነገሩ ስላደረገ በኢየሱስ ሁሉን ያገኛል። ነፍሱ እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለች።
ዲሴምበር 18
«የበጎችህን ሁኔታ አጥብቀህ እወቅ፥ መንጎችህንም በሚገባ ተመልከት።» (ምሳሌ 27:23)
ጥበበኛ ነጋዴ ሁሉ አልፎ አልፎ የንብረት ቆጠራ ያደርጋል፤ በዚያን ጊዜ ሒሳቡን ይደምራል፥ በእጁ ያለውን ይመረምራል፥ ንግዱ እየበለጸገ ወይም እያሽቆለቆለ መሆኑን በእርግጥ ያረጋግጣል። በመንግሥተ ሰማያት ጥበበኛ የሆነ ሰው ሁሉ «አቤቱ፥ መርምረኝ፥ ፈትነኝም» ብሎ ይጮኻል፤ በእግዚአብሔርና በነፍሱ መካከል ነገሮች ትክክል መሆናቸውን ለማወቅም ራሱን ለመመርመር ልዩ ጊዜያትን ብዙ ጊዜ ይለያል። የምናመልከው አምላክ ታላቅ ልብን መርማሪ ነው፤ ከጥንትም ባሪያዎቹ «የሰው ልጆችን ልብ የሚመረምርና ኩላሊትን የሚፈትን እግዚአብሔር» ብለው ያውቁት ነበር። ከተስፋው ዕረፍት እንዳትጐድል በስሙ ሁኔታህን በትጋት እንድትመረምርና በጥብቅ እንድትፈትን ላነሣሣህ። ጥበበኛ ሰው ሁሉ የሚያደርገውን፥ እግዚአብሔርም ራሱ ከሁላችን ጋር የሚያደርገውን፥ ዛሬ ማታ ከራስህ ጋር እንድታደርገው እመክርሃለሁ። ሽበት ጥቁር ልብን ሊሸፍን ይችላልና እጅግ ያረጀው ቅዱስ የአምልኮውን መሠረታዊ ነገሮች በሚገባ ይመልከት፤ የወጣትነት ልምላሜ ከግብዝነት ብስባሽ ጋር ሊጣመር ይችላልና እምነቱን የሚመሰክር ወጣትም የማስጠንቀቂያውን ቃል አይናቅ። አልፎ አልፎ ዝግባ በመካከላችን ይወድቃል። ጠላት አሁንም በስንዴ መካከል እንክርዳድን መዝራቱን ቀጥሎአል። ዓላማዬ በአእምሮህ ውስጥ ጥርጣሬንና ፍርሃትን ማስገባት አይደለም፤ በእውነት አይደለም፤ ይልቁንም ራስን የመመርመር ብርቱ ነፋስ እነርሱን ለማባረር እንዲረዳ ተስፋ አደርጋለሁ። ልንገድለው የምንወደው ዋስትናን ሳይሆን ሥጋዊ ዋስትናን ነው፤ ልንገለብጠው የምንወደው መታመንን ሳይሆን ሥጋዊ መታመንን ነው፤ ልናጠፋው የምንወደው ሰላምን ሳይሆን የሐሰት ሰላምን ነው። ግብዝ ሊያደርግህ ሳይሆን ቅን ነፍሳት ምስጋናውን እንዲያወሩ በፈሰሰው በክርስቶስ ክቡር ደም እለምንሃለሁ፤ በመጨረሻ ስለ አንተ «ማኔ፥ ማኔ፥ ቴቄል፤ በሚዛን ተመዘንህ ቀልለህም ተገኘህ» እንዳይባል መርምር፥ ተመልከትም።
ዲሴምበር 19
«ባሕርም ወደ ፊት የለም።» (ራእይ 21:1)
ያን የከበረ ጥንታዊ ውቅያኖስ እናጣለን ብለን ስናስብ ደስ ሊለን አይችልም ማለት ይቻላል፤ የሚያብረቀርቁ ማዕበሎቹና ቅርፊት የሞላባቸው ዳርቻዎቹ ያሉት ታላቅና ሰፊ ባሕር በእውነት ቃል በቃል የማይኖር ከሆነ አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር በምናባችን ይበልጥ ውብ አይሆኑም። ጥቅሱ በጥንት ዘመን የምሥራቅ ሰዎች አእምሮ በአጠቃላይ ባሕርን ይመለከትበት በነበረው ጭፍን አመለካከት የተነካ ምሳሌ ሆኖ መነበብ የለበትምን? ባሕር የሌለበትን እውነተኛ ግዙፍ ዓለም ማሰብ ያሳዝናል፤ ውድ ያደረገው ሰንፔር የሌለበት የብረት ቀለበት በሆነ ነበር። እዚህ መንፈሳዊ ትርጉም መኖር አለበት። በአዲሱ ዘመን መለያየት አይኖርም—ባሕር ሕዝቦችን ይለያያል፥ ወገኖችንም እርስ በርሳቸው ያራርቃል። በፍጥሞ ለነበረው ለዮሐንስ ጥልቅ ውኃዎቹ ከወንድሞቹና ከሥራው የሚለዩት እንደ እስር ቤት ቅጥሮች ነበሩ፤ በሚመጣው ዓለም እንዲህ ያሉ እንቅፋቶች አይኖሩም። ዛሬ ማታ በጸሎት በምናስባቸው በብዙ ዘመዶቻችንና በእኛ መካከል ብዙ ርቀት የሚሸፍኑ የሚንከባለሉ ማዕበሎች ተዘርግተዋል፤ ወደምንሄድበት ብሩህ ዓለም ግን ለተቤዠው ቤተሰብ ሁሉ ያልተቋረጠ ኅብረት ይኖራል። በዚህ ትርጉም ባሕር ወደ ፊት አይኖርም። ባሕር የለውጥ ምልክት ነው፤ በመጕደሉና በመሙላቱ፥ እንደ መስተዋት በለሰለሰው ጸጥታውና እንደ ተራራ በሚነሡት ማዕበሎቹ፥ በረጋው ማጕረምረሙና በሁከተኛው ጩኸቱ ከቶ ለረጅም ጊዜ በአንድ ሁኔታ አይቆይም። የተለዋዋጮቹ ነፋሳትና የሚለዋወጠው ጨረቃ ባሪያ ነው፤ አለመረጋጋቱም በምሳሌ የታወቀ ነው። በዚህ ሟች ሁኔታ ከዚህ ዓይነቱ እጅግ ብዙ አለብን፤ ምድር የምትጸናው በአለመጽናቷ ብቻ ነው፤ በሰማያዊው ሁኔታ ግን የሚያሳዝን ለውጥ ሁሉ አይታወቅም፤ ከእርሱም ጋር ተስፋችንን የሚሰብርና ደስታችንን የሚያሰጥም የማዕበል ፍርሃት ሁሉ ይጠፋል። የብርጭቆው ባሕር በማዕበል ባልተሰበረ ክብር ያበራል። በገነት ሰላማዊ ዳርቻዎች ምንም ዐውሎ ነፋስ አያጓራም። መለያየትና ለውጥ ዐውሎ ነፋስም ወደሚያበቁባት ወደዚያች ደስተኛ ምድር በቅርቡ እንደርሳለን! ኢየሱስ ወደዚያ ያሻግረናል። በእርሱ ውስጥ ነን ወይስ አይደለንም? ታላቁ ጥያቄ ይህ ነው።
ዲሴምበር 20
«ሠራተኞችን ጥራና ... ደመወዝ ስጣቸው።» (ማቴዎስ 20:8)
እግዚአብሔር መልካም ከፋይ ነው፤ ባሪያዎቹን ሥራውን ከፈጸሙ በኋላ ብቻ ሳይሆን ገና በሥራ ላይ ሳሉም ይከፍላቸዋል፤ ከክፍያዎቹም አንዱ ይህ ነው፦ ያረፈ ሕሊና። ስለ ኢየሱስ ለአንድ ሰው በታማኝነት ተናግረህ ከሆነ ሌሊት ወደ መኝታህ ስትሄድ «ዛሬ ከዚያ ሰው ደም ሕሊናዬን ነጻ አድርጌአለሁ» ብለህ በማሰብ ደስ ይልሃል። ለኢየሱስ አንድ ነገር በማድረግ ታላቅ መጽናናት አለ። ኦ፥ በዘውዱ ላይ ዕንቍዎችን ማኖርና ከነፍሱ ድካም ፍሬ እንዲያይ ማድረግ እንዴት ያለ ደስታ ነው! ደግሞም የኃጢአት መረዳት የመጀመሪያ ቡቃያዎች በአንዲት ነፍስ ውስጥ ሲፈነዱ በማየት እጅግ ታላቅ ዋጋ አለ! በክፍሉ ውስጥ ስላለችው ልጃገረድ «ልቧ ርኅሩኅ ነው፤ በውስጧ የጌታ ሥራ እንዳለ ተስፋ አደርጋለሁ» ማለት! ከሰዓት በኋላ ከፈራኸው ይልቅ ስለ መለኮታዊ እውነት የበለጠ ማወቅ እንዳለበት እንድታስብ ያደረገህን ነገር ስለ ተናገረው ስለዚያ ልጅ ወደ ቤት ሄዶ መጸለይ! ኦ፥ የተስፋ ደስታ! ስለ ፍሬ የማፍራት ደስታ ግን! ሊነገር የማይችል ነው። ይህ ደስታ የሚያጥለቀልቅ ቢሆንም የተራበ ነገር ነው—ይበልጥ ትናፍቀዋለህ። ነፍሳትን የሚማርክ መሆን በዓለም ላይ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። ወደ ክርስቶስ በምታመጣት ነፍስ ሁሉ በምድር ላይ አዲስ ሰማይ ታገኛለህ። ነገር ግን በላይ የሚጠብቀንን ብፅዕና ማን ሊያስበው ይችላል! ኦ፥ «ወደ ጌታህ ደስታ ግባ» የሚለው ቃል እንዴት ጣፋጭ ነው! ክርስቶስ በዳነ ኃጢአተኛ ላይ ያለው ደስታ ምን እንደ ሆነ ታውቃለህን? በሰማይ የምንወርሰው ይህንኑ ደስታ ነው። አዎን፥ እርሱ ወደ ዙፋኑ ሲወጣ አንተም ከእርሱ ጋር ትወጣለህ። ሰማያት «መልካም፥ መልካም» በሚል ድምፅ ሲያስተጋቡ አንተም በሽልማቱ ትካፈላለህ፤ ከእርሱ ጋር ደክመሃል፥ ከእርሱ ጋር መከራ ተቀብለሃል፥ አሁን ከእርሱ ጋር ትነግሣለህ፤ ከእርሱ ጋር ዘርተሃል፥ ከእርሱ ጋር ታጭዳለህ፤ ፊትህ እንደ እርሱ ፊት በላብ ተሸፍኖ ነበር፥ ነፍስህም እንደ ነፍሱ ስለ ሰዎች ኃጢአት አዝና ነበር፤ አሁን ግን ፊትህ እንደ እርሱ ፊት በሰማይ ግርማ ያበራል፥ ነፍስህም እንደ ነፍሱ በብፁዕ ደስታ ትሞላለች።
ዲሴምበር 21
«በጥልፍ ሥራ ልብስ አለበስሁሽ፥ የአቆስጣም ቍርበት ጫማ አጫማሁሽ፥ በቀጭን በፍታም አስታጠቅሁሽ፥ በሐርም ከደንሁሽ።» (ሕዝቅኤል 16:10)
ጌታ ለሕዝቡ ልብስ በምን ያህል ተወዳዳሪ የሌለው ልግስና እንደሚያዘጋጅ ተመልከት። እንዲህ ተጐናጽፈዋልና መለኮታዊው ጥበብ ባሕርዩ ሁሉ ድርሻውን የሚወስድበትንና መለኮታዊ ውበት ሁሉ የሚገለጥበትን ወደር የሌለውን ጥልፍ ሥራ ሲያወጣ ይታያል። በመዳናችን እንደ ተገለጠው ያለ ጥበብ የለም፤ በቅዱሳን ጽድቅ እንደሚታየው ያለ ረቂቅ የእጅ ሥራ የለም። መጽደቅ በቤተ ክርስቲያን ዘመናት ሁሉ የሊቃውንትን ብዕር ይዞአል፤ በዘላለምም የአድናቆት ርእስ ይሆናል። እግዚአብሔር በእርግጥ «በጥበብ ሠራው»። ከዚህ ሁሉ ጥበብ ጋር ጥቅምና ጽናት ተቀላቅሎአል፤ ይህም የአቆስጣ ቍርበት ጫማ ከመጫማታችን ጋር ይነጻጸራል። እዚህ የተጠቀሰው እንስሳ አይታወቅም፤ ቍርበቱ ግን ማደሪያውን ይሸፍን ነበር፤ ከታወቁትም ቆዳዎች እጅግ ጥሩና ብርቱ ከሆኑት አንዱ ነበረ። ከእግዚአብሔር በእምነት የሆነው ጽድቅ ለዘላለም ይኖራል፤ በዚህ መለኮታዊ ዝግጅት የተጫማም በምድረ በዳ በደኅና ይራመዳል፥ እግሩንም በአንበሳና በእፉኝት ላይ እንኳ ሊያኖር ይችላል። የቅዱሱ ልብሳችን ንጽሕናና ክብር በቀጭኑ በፍታ ይገለጣሉ። ጌታ ሕዝቡን ሲቀድስ እንደ ካህናት ንጹሕ ነጭ ልብስ ይለብሳሉ፤ በረዶ ራሱ እንኳ አይበልጣቸውም፤ በሰዎችና በመላእክት ዓይን ለመታየት ውቦች ናቸው፤ በጌታም ዓይን እንኳ ነውር የለባቸውም። ደግሞም ንጉሣዊው ልብስ እንደ ሐር ለስላሳና ውድ ነው። ምንም ወጪ አይቆጠብም፥ ምንም ውበት አይከለከልም፥ ምንም ማማር አይነፈግም።
እንግዲህ ምንድር ነው? ከዚህ የሚወሰድ ትምህርት የለምን? በእርግጥ የሚሰማ ምስጋናና የሚገለጥ ደስታ አለ። ልቤ ሆይ፥ ና፤ የማታ ሃሌ ሉያህን አትከልክል! እምቢልታህን አዘጋጅ! አውታሮችህን ምታ!
«ነፍሴ ሆይ፥ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተጐናጽፈሻል
በታላቁ ቅዱስ ሥላሴ!
በጣፋጭ የምስጋና ስምምነት
ኃይሎችሽ ሁሉ ይስማሙ።»
ዲሴምበር 22
«የልጆቹ ምልክት።» (ዘዳግም 32:5)
የእግዚአብሔርን ልጅ በማይሳሳት ሁኔታ የሚያመለክተው ምሥጢራዊ ምልክት ምንድር ነው? ይህን በራሳችን ፍርድ መወሰን ከንቱ ትዕቢት በሆነ ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ይገልጥልናል፤ መገለጥ መሪያችን በሆነበትም ስፍራ በእርግጠኝነት ልንራመድ እንችላለን። ስለ ጌታችንም እንዲህ ተነግሮናል፦ «ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው።» እንግዲህ ክርስቶስ ኢየሱስን ወደ ልቤ ተቀብዬው ከሆነ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ። ያ መቀበል በዚያው ቍጥር በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ማመን ተብሎ ተገልጦአል። እንግዲህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የማምን ከሆነ—ማለትም በቀላሉ ከልቤ ራሴን ለተሰቀለው፥ አሁን ግን ከፍ ከፍ ላለው ቤዛ አደራ ብሰጥ—የልዑሉ ቤተሰብ አባል ነኝ። ሌላ የሌለኝ ነገር ምንም ቢሆን፥ ይህ ካለኝ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን መብት አለኝ። ጌታችን ኢየሱስ በሌላ መልክ ያስቀምጠዋል፦ «በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል።» ነገሩ በአጭሩ ይህ ነው። ክርስቶስ ለሌሎች ሳይሆን ለገዛ በጎቹ እረኛ ሆኖ ይገለጣል። ልክ እንደ ተገለጠ የገዛ በጎቹ ያውቁታል—ይታመኑበታል፥ ሊከተሉትም ተዘጋጅተዋል፤ እርሱ ያውቃቸዋል፥ እነርሱም ያውቁታል—የእርስ በርስ መተዋወቅ አለ—በመካከላቸውም የማያቋርጥ ትስስር አለ። ስለዚህ የዳግም መወለድና የልጅነት አንዱ ምልክት፥ እርግጠኛው ምልክት፥ የማይሳሳተው ምልክት በተሾመው ቤዛ ላይ ያለ የልብ እምነት ነው። አንባቢ ሆይ፥ ትጠራጠራለህን? የእግዚአብሔርን ልጆች ምሥጢራዊ ምልክት መሸከምህን እርግጠኛ አይደለህምን? እንግዲያስ «አቤቱ፥ መርምረኝ፥ ልቤንም እወቅ» እስክትል ድረስ አንድ ሰዓት እንኳ በራስህ ላይ አይለፍ። እማጸንሃለሁ፥ በዚህ ነገር አትቀልድ! የግድ በአንድ ነገር መቀለድ ካለብህ በሁለተኛ ደረጃ ባለ ነገር ይሁን፤ ብትፈልግ በጤናህ ወይም በርስትህ የባለቤትነት ሰነዶች፤ ስለ ነፍስህ ግን፥ ስለማትሞተው ነፍስህና ስለ ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታዋ በቁም ነገር እንድትይዝ እለምንሃለሁ። ለዘላለም የሚሆነውን አስተማማኝ አድርግ።
ዲሴምበር 23
«ሌሊቱም የአንተ ነው።» (መዝሙር 74:16)
አዎን፥ ጌታ ሆይ፥ ፀሐይ ስትጠልቅ ዙፋንህን አትለቅም፤ በእነዚህ ረጅም የክረምት ሌሊቶችም ሁሉ ዓለምን ለክፋት ብዝበዛ አትተዋትም፤ ዓይኖችህ እንደ ከዋክብት ይጠብቁናል፥ የከዋክብት መቀነት ሰማይን እንደሚታጠቅ ክንዶችህ ይከብቡናል። የአስደሳች እንቅልፍ ጠልና የጨረቃ ተጽእኖዎች ሁሉ በእጅህ ናቸው፤ የሌሊት ድንጋጤዎችና ግርማዎችም እንዲሁ ከአንተ ጋር ናቸው። በእኩለ ሌሊት ሰዓታት ስነቃ ወይም በጭንቀት ወዲያና ወዲህ ስገላበጥ ይህ ለእኔ እጅግ ጣፋጭ ነው። በፀሐይ እንደሚወጡ በጨረቃም የሚወጡ ውድ ፍሬዎች አሉ፤ ጌታዬ በእነርሱ የተወደደ ተካፋይ ያድርገኝ።
የመከራ ሌሊት ሁሉ ነገር ብፅዕና እንደ ሆነባቸው ብሩህ የበጋ ቀኖች ሁሉ በፍቅር ጌታ ዝግጅትና ቁጥጥር ሥር ነው። ኢየሱስ በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ነው። ፍቅሩ ሌሊትን እንደ መጐናጸፊያ በራሱ ላይ ይጠቀልላል፤ ለእምነት ዓይን ግን ጥቁሩ ልብስ ማስመሰያ ሊባል እንኳ አይችልም። ከሌሊቱ የመጀመሪያ ክፍለ ሌሊት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ ዘላለማዊው ጠባቂ ቅዱሳኑን ይመለከታል፥ የእኩለ ሌሊትን ጥላና ጠልም ለሕዝቡ ታላቅ መልካም ነገር እንዲሆን ይመራዋል። ስለ ሥልጣን የሚፋለሙ የመልካምና የክፉ ተፎካካሪ አማልክት እንዳሉ አናምንም፤ ነገር ግን «ብርሃንን እፈጥራለሁ፥ ጨለማንም እፈጥራለሁ፤ ይህን ሁሉ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር ነኝ» የሚለውን የይሖዋን ድምፅ እንሰማለን።
የሃይማኖት ግድየለሽነትና የማኅበራዊ ኃጢአት የጨለማ ዘመናትም ከመለኮታዊው ዓላማ ውጭ አይደሉም። የእውነት መሠዊያዎች ሲረክሱ፥ የእግዚአብሔርም መንገዶች ሲተዉ የጌታ ባሪያዎች በመራራ ሐዘን ያለቅሳሉ፤ ነገር ግን ተስፋ መቍረጥ የለባቸውም፤ እጅግ ጨለማ የሆኑት ዘመናት በጌታ ይገዛሉና፥ በትእዛዙም ወደ ፍጻሜያቸው ይደርሳሉ። ለእኛ ሽንፈት የሚመስለው ለእርሱ ድል ሊሆን ይችላል።
«በጨለማ ሌሊት ብንጠቀለልም፥
አንዲት የብርሃን ጨረር ባናይም፥
ጌታ ራሱ እዚህ ስላለ
ልንፈራ አይገባንም።»
ዲሴምበር 24
«የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፥ ሥጋም የለበሰ ሁሉ በአንድነት ያየዋል።» (ኢሳይያስ 40:5)
ዓለም ሁሉ ወደ ክርስቶስ የሚመለስበትን ደስተኛ ቀን እንጠባበቃለን፤ የአሕዛብ አማልክት ለፍልፈልና ለሌሊት ወፎች የሚጣሉበትን፥ የሮማ ሥርዓት የሚፈነዳበትን፥ የመሐመድም ጨረቃ ከስማ ዳግመኛ ጎጂ ጨረሯን በአሕዛብ ላይ የማትጥልበትን፥ ነገሥታት በሰላም አለቃ ፊት የሚሰግዱበትን፥ አሕዛብም ሁሉ ቤዛቸውን ብፁዕ ብለው የሚጠሩበትን ቀን። አንዳንዶች በዚህ ተስፋ ቆርጠዋል። ዓለምን እንደሚፈርስና ተሰባብሮ ዳግመኛ እንደማይንሳፈፍ መርከብ ይመለከቱታል። ዓለምና በእርሱ ያለው ሁሉ አንድ ቀን እንደሚቃጠል እናውቃለን፤ ከዚያም በኋላ አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርን እንጠብቃለን፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስናነብ እንዲህ የሚል እርግጠኛ እምነት ያድርብናል—
«ፀሐይ ተከታታይ ጉዞዋን በምትሮጥበት
ስፍራ ሁሉ ኢየሱስ ይነግሣል።»
በመዘግየቱ ርዝመት ተስፋ አንቆርጥም፤ ቤተ ክርስቲያን በጥቂት ስኬትና በብዙ ሽንፈት እንድትታገል በሚሰጣት ረጅም ዘመንም አንዝልም። አንድ ጊዜ የክርስቶስ ደም ሲፈስበት ያየው ይህ ዓለም ሁልጊዜ የዲያብሎስ ምሽግ ሆኖ እንዲኖር እግዚአብሔር ፈጽሞ እንደማይፈቅድ እናምናለን። ክርስቶስ ይህን ዓለም ከተጠላው የጨለማ ኃይሎች ግዛት ለማዳን ወደዚህ መጣ። ሰዎችና መላእክት በአንድነት ሆነው «ሃሌ ሉያ፥ ሃሌ ሉያ፤ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና!» ብለው ሲጮኹ ያ እንዴት ያለ እልልታ ይሆናል! በዚያን ቀን በውጊያው ድርሻ እንደ ነበረን፥ የቀስቱን ፍላጻዎች ለመስበር እንደ ረዳን፥ ለጌታችንም ድሉን በማሸነፍ እንደ ተባበርን ማወቅ እንዴት ያለ እርካታ ይሆናል! ራሳቸውን ለዚህ ድል ነሺ ጌታ በአደራ የሰጡ፥ በስሙና በብርታቱ ትንሿን ድርሻቸውን እያደረጉ ከእርሱ ጋር ጎን ለጎን የሚዋጉ ብፁዓን ናቸው! በክፋት ወገን ያሉ እንዴት ጐስቋሎች ናቸው! የሚሸነፍ ወገን ነው፤ በዚህም ነገር መሸነፍ ማለት መሸነፍና ለዘላለም መጥፋት ነው። አንተ በማን ወገን ነህ?
ዲሴምበር 25
«የግብዣውም ቀኖች በተፈጸሙ ጊዜ ኢዮብ ልኮ ይቀድሳቸው ነበር፤ ማልዶም ተነሥቶ እንደ ሁሉም ቍጥር የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ ኢዮብ፦ ምናልባት ልጆቼ ኃጢአት ሠርተው በልባቸውም እግዚአብሔርን ሰድበው ይሆናል ይል ነበርና። ኢዮብም ሁልጊዜ እንዲህ ያደርግ ነበር።» (ኢዮብ 1:5)
ያ የጥንት አባት ከቤተ ሰቡ በዓል በኋላ በማለዳ ያደረገውን፥ አማኝ ዛሬ ሌሊት ከማረፉ በፊት ለራሱ ቢያደርገው መልካም ነው። በቤተ ሰብ ስብሰባ ደስታ መካከል ወደ ኃጢአት ወዳለበት ቀልድ መንሸራተትና ክርስቲያኖች መሆናችንን የመሰከርንበትን ማንነታችንን መዘንጋት ቀላል ነው። እንዲህ ሊሆን ባይገባም፥ እንዲሁ ግን ነው፤ የግብዣ ቀኖቻችን የተቀደሰ ደስታ ቀኖች የሚሆኑት እጅግ አልፎ አልፎ ነው፤ ብዙ ጊዜ ግን ወደ ርኩስ ፈንጠዝያ ያዘቀዝቃሉ። በኤደን ወንዞች እንደ ታጠበ ያህል ንጹሕና የሚቀድስ የደስታ መንገድ አለ፤ ቅዱስ ምስጋና እንደ ሐዘን ያህል የሚያነጻ ነገር ሊሆን ይገባዋል። ወዮ ለደካማ ልባችን! የለቅሶ ቤት ከግብዣ ቤት እንደሚሻል እውነታው ያረጋግጣልና። አማኝ ሆይ፥ ና፤ ዛሬ በምን በድለሃል? ከፍ ያለውን መጠራትህን ረስተሃልን? በከንቱ ቃልና በልቅ ንግግር እንደ ሌሎች ሆነሃልን? እንግዲያስ ኃጢአትህን ተናዘዝ፥ ወደ መሥዋዕቱም ሽሽ። መሥዋዕቱ ይቀድሳል። የታረደው በግ ክቡር ደም በደሉን ያስወግዳል፥ ባለማወቅና በቸልተኝነት የሠራነውን ኃጢአት ርኩሰትም ያነጻል። ለገና ቀን ከሁሉ የሚሻል ፍጻሜ ይህ ነው፦ በሚያነጻው ምንጭ እንደ ገና መታጠብ። አማኝ ሆይ፥ ወደዚህ መሥዋዕት ዘወትር ና፤ ዛሬ ሌሊት እንዲህ መልካም ከሆነ በየሌሊቱ ሁሉ መልካም ነው። በመሠዊያው አጠገብ መኖር የንጉሥ ካህናት መብት ነው፤ ለእነርሱ ኃጢአት ምንም ያህል ታላቅ ቢሆን የተስፋ መቍረጥ ምክንያት አይሆንም፤ ስለ ኃጢአት ወደሚያስተሰርየው መሥዋዕት እንደ ገና ይቀርባሉና፥ ሕሊናቸውም ከሞተ ሥራ ይነጻል።
ይህን የበዓል ቀን በደስታ እዘጋለሁ፥
የመሠዊያውን የተቀደሰ ቀንድ ጨብጬ፤
ስሕተቴና ጥፋቴ ታጥቦ ተወግዶአል፥
በጉ በደሌን ሁሉ ተሸክሞአልና።
ዲሴምበር 26
«እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።» (ማቴዎስ 28:20)
ጌታ ኢየሱስ በቤተ ክርስቲያኑ መካከል ነው፤ በወርቅ መቅረዞች መካከል ይሄዳል፤ የተስፋ ቃሉም «እነሆ፥ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ» የሚል ነው። ደቀ መዛሙርቱ በባሕሩ ዳር ፍምና ዓሣ በላዩ ተቀምጦ እንጀራም ባዩ ጊዜ ከእነርሱ ጋር እንደ ነበረ፥ አሁንም እንዲሁ በእርግጥ ከእኛ ጋር ነው። በሥጋ አይደለም፤ ነገር ግን በእውነት ኢየሱስ ከእኛ ጋር ነው። ይህም የተባረከ እውነት ነው፤ ኢየሱስ ባለበት ስፍራ ፍቅር ይነድዳልና። በዓለም ካሉ ልብን ሊያቃጥሉ ከሚችሉ ነገሮች ሁሉ እንደ ኢየሱስ መገኘት ያለ ምንም የለም! እርሱን በጨረፍታ ማየት እንዲህ ያሸንፈናል፤ ስለዚህም «ዓይኖችህን ከእኔ መልስ፥ አሸንፈውኛልና» ለማለት እንዘጋጃለን። ከሽቱ ልብሱ የሚንጠባጠበው የእሬቱ፥ የከርቤውና የብርጕዱ መዓዛ እንኳ ድውዩንና የዛለውን ያበረታል። በዚያ ጸጋ በሞላበት እቅፍ ላይ ለአንድ አፍታ ራስን ማስደገፍና መለኮታዊ ፍቅሩን ወደ ደካማውና ወደ ቀዘቀዘው ልባችን መቀበል ብቻ ይሁን፤ ከዚያ በኋላ አንቀዘቅዝም፤ ነገር ግን እንደ ሱራፌል እንግላለን፥ ለድካም ሁሉ ብቁ፥ መከራንም ሁሉ ለመቀበል የምንችል እንሆናለን። ኢየሱስ ከእኛ ጋር እንደ ሆነ ካወቅን ኃይል ሁሉ ይገለጣል፤ ጸጋም ሁሉ ይጠነክራል፤ በልብም በነፍስም በኃይልም ራሳችንን ለጌታ አገልግሎት እንሰጣለን፤ ስለዚህ የክርስቶስ መገኘት ከሁሉ በላይ ሊናፈቅ ይገባዋል። መገኘቱ ከሁሉ ይልቅ የሚታወቀው እርሱን ከሁሉ ይልቅ በሚመስሉት ዘንድ ነው። ክርስቶስን ለማየት ብትወድ እርሱን እየመሰልህ ማደግ አለብህ። በመንፈስ ኃይል ራስህን ከክርስቶስ ምኞት፥ ዓላማና የሥራ ዕቅድ ጋር አንድ አድርግ፤ ያን ጊዜ ከእርሱ ጋር የመሆንን ሞገስ ታገኛለህ። መገኘቱ ሊገኝ እንደሚችል አስታውስ። የተስፋ ቃሉ እንደ ቀድሞው እውነት ነው። ከእኛ ጋር መሆንን ይወዳል። ባይመጣ ግን በግድየለሽነታችን ስለምንከለክለው ነው። ለልባዊ ጸሎታችን ራሱን ይገልጣል፤ በልመናችንና በእንባችንም እንድናቆየው በጸጋው ይፈቅዳል፤ እነዚህ ኢየሱስን ከሕዝቡ ጋር የሚያስሩ የወርቅ ሰንሰለቶች ናቸውና።
ዲሴምበር 27
«እግዚአብሔርም ዘወትር ይመራሃል።» (ኢሳይያስ 58:11)
«እግዚአብሔር ይመራሃል።» መልአክ አይደለም፥ እግዚአብሔር ራሱ ይመራሃል። እርሱ በምድረ በዳ በሕዝቡ ፊት እንደማይሄድ፥ ነገር ግን በመንገድ እንዲመራቸው መልአክ በፊታቸው እንደሚሄድ ተናገረ፤ ሙሴ ግን «ፊትህ ከእኔ ጋር ካልሄደ ከዚህ አታውጣን» አለ። ክርስቲያን ሆይ፥ እግዚአብሔር በምድራዊ ጕዞህ ለመልአክ አመራር አልተወህም፤ እርሱ ራሱ ከፊት ሆኖ ይመራል። የደመናውንና የእሳቱን ዓምድ ላታይ ትችላለህ፤ እግዚአብሔር ግን ፈጽሞ አይተውህም። ይመራሃል የሚለውን ቃል ልብ በል፤ «እግዚአብሔር ይመራሃል።» ይህ ነገሩን ምንኛ የተረጋገጠ ያደርገዋል! እግዚአብሔር እንደማይተወን ምንኛ እርግጥ ነው! «አደርጋለሁ» እና «ይሆናል» የሚሉት ውድ ቃላቱ ከሰዎች መሐላ ይበልጣሉ። «አልለቅህም ከቶም አልተውህም።» ደግሞም ዘወትር የሚለውን ተውሳከ ግሥ ተመልከት። አንዳንድ ጊዜ ብቻ የምንመራ አይደለንም፤ ነገር ግን የማያቋርጥ መካሪ አለን፤ አልፎ አልፎ ለራሳችን ማስተዋል ተትተን የምንቅበዘበዝ አይደለንም፤ ነገር ግን የታላቁን እረኛ የሚመራ ድምፅ ዘወትር እንሰማለን፤ ተረከዙንም ተጠግተን ብንከተለው አንስትም፤ ነገር ግን ወደምንኖርበት ከተማ በቀና መንገድ እንመራለን። በሕይወትህ ያለህን ስፍራ መለወጥ ቢኖርብህ፥ ወደ ሩቅ ዳርቻዎች መሰደድ ቢኖርብህ፥ ወደ ድህነት ብትጣል፥ ወይም አሁን ካለህበት ይልቅ ወደሚበልጥ ኃላፊነት ድንገት ብትነሣ፥ በእንግዶች መካከል ብትጣል፥ ወይም በጠላቶች መካከል ብትወድቅ፥ አትንቀጥቀጥ፤ «እግዚአብሔር ዘወትር ይመራሃል»ና። ወደ እግዚአብሔር ቀርበህ ብትኖርና ልብህ በቅዱስ ፍቅር ሞቆ ቢጠበቅ ልትድንበት የማትችለው ጭንቅ የለም። ከእግዚአብሔር ጋር የሚሄድ አይስትም። እንደ ሄኖክ ከእግዚአብሔር ጋር ተመላለስ፤ መንገድህንም ልትስት አትችልም። የማትሳሳት ጥበብ ትመራሃለች፥ የማይለወጥ ፍቅር ያጽናናሃል፥ የዘላለም ኃይልም ይጠብቅሃል። «እግዚአብሔር»—ቃሉን ልብ በል—«እግዚአብሔር ዘወትር ይመራሃል።»
ዲሴምበር 28
«በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።» (ማቴዎስ 10:34)
ክርስቲያን ጠላቶችን ማፍራቱ አይቀርም። ማንንም ጠላት እንዳያደርግ መጣር ከዓላማዎቹ አንዱ ይሆናል፤ ነገር ግን ትክክለኛውን ማድረግና እውነተኛውን ማመን ምድራዊ ወዳጆቹን ሁሉ የሚያሳጣው ቢሆን፥ ይህን እንደ ትንሽ ጕዳት ይቈጥረዋል፤ በሰማይ ያለው ታላቅ ወዳጁ ይበልጥ ወዳጅ ይሆንለታልና፥ ከቀድሞውም ይልቅ በጸጋ ራሱን ይገልጥለታልና። እናንተ መስቀሉን ያነሣችሁ ሆይ፥ ጌታችሁ ያለውን አታውቁምን? «ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤ ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል።» ክርስቶስ ታላቁ ሰላም አድራጊ ነው፤ ነገር ግን ከሰላም በፊት ጦርነትን ያመጣል። ብርሃን በመጣበት ስፍራ ጨለማ ማፈግፈግ አለበት። እውነት ባለበት ስፍራ ሐሰት መሸሽ አለበት፤ ቢቆይ ግን ብርቱ ትግል ይሆናል፤ እውነት ሰንደቋን ዝቅ ልታደርግ አትችልም፥ አትፈቅድምም፤ ሐሰትም ከእግር በታች መረገጥ አለበት። ክርስቶስን ብትከተል የዓለም ውሾች ሁሉ ከተረከዝህ በኋላ ይጮኹብሃል። በመጨረሻው ፍርድ ፊት ጸንተህ ለመቆም በሚያስችል ሁኔታ ልትኖር ብትወድ፥ ዓለም በጎ እንደማይናገርልህ እርግጠኛ ሁን። የዓለም ወዳጅ የሆነ የእግዚአብሔር ጠላት ነው፤ ነገር ግን ለልዑል እውነተኛና ታማኝ ብትሆን፥ የማያወላውል ታማኝነትህ በኃጢአታቸው ላይ ምስክር ስለ ሆነ ሰዎች ይቈጡብሃል። የሚመጣው ሁሉ ሳያስፈራህ ትክክለኛውን ማድረግ አለብህ። የቅርብ ወዳጅህን ወደ ብርቱ ጠላትህ የሚለውጠውን መንገድ ሳታመነታ ለመከተል የአንበሳ ድፍረት ያስፈልግሃል፤ ነገር ግን ስለ ኢየሱስ ፍቅር እንዲህ ደፋር መሆን አለብህ። ስለ እውነት ብሎ መልካም ስምንና ፍቅርን አደጋ ላይ መጣል፥ ይህን ዘወትር ለማድረግ የእግዚአብሔር መንፈስ ብቻ በአንተ ውስጥ ሊሠራው የሚችለው የግብረ ገብ ጽናት የሚያስፈልገው ሥራ ነው፤ ሆኖም እንደ ፈሪ ጀርባህን አታዙር፥ ነገር ግን ጐበዝ ሁን። ይህን አስቸጋሪ መንገድ ከአንተ በፊት ስለ ተጓዘበት የጌታህን ፈለግ በወንድነት ተከተል። ከሐሰተኛ ሰላምና ከዘላለም ሥቃይ ይልቅ አጭር ጦርነትና የዘላለም ዕረፍት ይሻላል።
ዲሴምበር 29
«ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል?» (ማቴዎስ 22:42)
የነፍስህ ጤንነት ታላቁ መፈተኛ ስለ ክርስቶስ ምን ይመስልሃል? የሚለው ነው። እርሱ ለአንተ «ከሰው ልጆች ይልቅ ውብ»፥ «ከአሥር ሺህ የተመረጠ»፥ «ሁለንተናው ያማረ» ነውን? ክርስቶስ በዚህ መንገድ በሚከበርበት ስፍራ ሁሉ፥ የመንፈሳዊ ሰው ችሎታዎች ሁሉ በብርታት ይሠራሉ። በዚህ የአየር ግፊት መለኪያ መንፈሳዊነትህን እፈርዳለሁ፦ ክርስቶስ በአንተ ዘንድ ከፍ ብሎ ነው ወይስ ዝቅ ብሎ? ስለ ክርስቶስ ጥቂት ብቻ ካሰብህ፥ ያለ እርሱ መገኘት መኖር ቢበቃህ፥ ለክብሩ ጥቂት ብቻ ብትጨነቅ፥ ሕጎቹን ቸል ብትል፥ ነፍስህ እንደ ታመመች አውቃለሁ፤ ለሞት የሚያደርስ ሕመም እንዳይሆን እግዚአብሔር ይስጥ! ነገር ግን የመንፈስህ የመጀመሪያ ሐሳብ ኢየሱስን እንዴት አከብረዋለሁ የሚል ከሆነ፥ የነፍስህ የዕለት ምኞት «እርሱን የት እንዳገኘው ባወቅሁ ኖሮ!» የሚል ከሆነ፥ እልሃለሁ፦ ሺህ ድካሞች ሊኖሩብህ ይችላሉ፤ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን እንኳ በጭንቅ ላታውቅ ትችላለህ፤ ሆኖም ኢየሱስ በአንተ ዘንድ ታላቅ ስለ ሆነ ደኅና መሆንህን ያለ ጥርጥር ተረድቻለሁ። ስለ ጨርቅህ ግድ የለኝም፤ ስለ እርሱ የንግሥና ልብስ ምን ይመስልሃል? ስለ ቍስሎችህ ግድ የለኝም፥ እንደ ጎርፍ ቢደሙም እንኳ፤ ስለ እርሱ ቍስሎች ምን ይመስልሃል? በአንተ ዘንድ እንደሚያብረቀርቁ ቀይ ዕንቍዎች ናቸውን? እንደ አልዓዛር በጕድፍ ላይ ብትተኛና ውሾች ቢልሱህ እንኳ አላቃልልህም፤ በድህነትህ አልፈርድብህም፤ ስለ ንጉሡ በውበቱ ምን ይመስልሃል? በልብህ ውስጥ የከበረ ከፍ ያለ ዙፋን አለውን? ብትችል ኖሮ ከዚህ ይልቅ ከፍ ታደርገው ነበርን? ምስጋናውን በሚያውጀው ዜማ ላይ አንድ መለከት ብቻ መጨመር ብትችል ለመሞት ፈቃደኛ ትሆን ነበርን? እንግዲያስ መልካም ሆኖልሃል። ስለ ራስህ ምንም ብታስብ፥ ክርስቶስ በአንተ ዘንድ ታላቅ ከሆነ ብዙ ሳይቆይ ከእርሱ ጋር ትሆናለህ።
«ዓለም ሁሉ በምርጫዬ ቢሣለቅ፥
ኢየሱስ ግን ድርሻዬ ይሆናል፤
ከእርሱ በቀር በማንም ደስ አይለኝምና፥
ከውቦች ሁሉ ይልቅ ውብ እርሱ ነው።»
ዲሴምበር 30
«በመጨረሻው መራራ እንዲሆን አታውቅምን?» (2ኛ ሳሙኤል 2:26)
አንባቢዬ ሆይ! በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን እምነት የምትናገር ብቻ እንጂ ባለቤቱ ባትሆን፥ የሚከተሉት መስመሮች የፍጻሜህ እውነተኛ ሥዕል ናቸው።
አንተ በአምልኮ ስፍራ በጨዋነት የምትገኝ ሰው ነህ፤ የምትሄደው ሌሎች ስለሚሄዱ ነው እንጂ ልብህ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ስለ ሆነ አይደለም። መጀመሪያህ ይህ ነው። ለሚመጡት ሃያ ወይም ሠላሳ ዓመታት እንደ አሁኑ እንድትቀጥል በሕይወት ትቆያለህ እንበል፤ በጸጋ መንገዶች ላይ በውጫዊ መገኘት ሃይማኖትን እየተናገርህ፥ ልብህ ግን በነገሩ ውስጥ ሳይኖር። ቀስ ብለህ ተራመድ፤ አንተን የመሰለውን ሰው የሞት አልጋ ላሳይህ ነውና። በእርጋታ እንመልከተው። የሚያጣብቅ ላብ በግንባሩ ላይ አለ፤ እየጮኸም ይነቃል፦ «አምላኬ ሆይ፥ መሞት ከባድ ነው። አገልጋዬን አስጠራችሁልኝን?» «አዎን፥ እየመጣ ነው።» አገልጋዩ ይመጣል። «ጌታዬ፥ እየሞትሁ እንደ ሆነ እፈራለሁ!» «ተስፋ አለህን?» «አለኝ ማለት አልችልም። በአምላኬ ፊት መቆምን እፈራለሁ፤ ኦ! ጸልይልኝ።» ጸሎቱ በቅን ልባዊነት ይጸለይለታል፤ የመዳንም መንገድ ለአሥር ሺህኛ ጊዜ በፊቱ ይቀርብለታል፤ ነገር ግን ገመዱን ሳይይዝ ሲሰምጥ አየዋለሁ። ጣቴን በእነዚያ በቀዘቀዙ የዓይን ሽፋኖች ላይ ላኖር እችላለሁ፤ ዳግመኛ በዚህ ምንም አያዩምና። ነገር ግን ሰውየው የት ነው? የሰውየው እውነተኛ ዓይኖችስ የት ናቸው? «በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ» ዓይኖቹን አነሣ ተብሎ ተጽፎአል። ኦ! ስለ ምን ቀድሞ ዓይኖቹን አላነሣም? ወንጌልን መስማት እጅግ ስለ ለመደ ነፍሱ በሥሩ አንቀላፍታ ነበርና። ወዮ! አንተ በዚያ ዓይኖችህን ብታነሣ ዋይታህ ምንኛ መራራ ይሆናል። የአዳኙ የራሱ ቃላት ወዮታውን ይግለጡ፦ «አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ።» በእነዚህ ቃላት ውስጥ የሚያስፈራ ትርጉም አለ። በእግዚአብሔር ቍጣ ቀይ ብርሃን ፊደል በፊደል ልታነብበው ፈጽሞ ግድ አይሁንብህ!
ዲሴምበር 31
«መከሩ አለፈ፥ በጋውም ተፈጸመ፥ እኛም አልዳንንም።» (ኤርምያስ 8:20)
አልዳንህም! ውድ አንባቢ ሆይ፥ ይህ የአንተ አሳዛኝ ሁኔታ ነውን? ስለሚመጣው ፍርድ ተነግሮህ፥ ነፍስህን እንድታድን ታዝዘህ፥ ይኸው በዚህች ሰዓት እንኳ አልዳንህም! የመዳንን መንገድ ታውቃለህ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ታነበዋለህ፥ ከመድረክ ትሰማዋለህ፥ ወዳጆችህም ያብራሩልሃል፤ ሆኖም ቸል ትለዋለህ፤ ስለዚህም አልዳንህም። ጌታ በሕያዋንና በሙታን በሚፈርድበት ጊዜ የምታመካኘው አይኖርህም። መንፈስ ቅዱስ በፊትህ በተሰበከው ቃል ላይ ጥቂትም ብዙም በረከት ሰጥቶአል፤ ከመለኮታዊ ሀልዎትም የመታደስ ዘመናት መጥተዋል፤ ሆኖም ያለ ክርስቶስ ነህ። እነዚህ ሁሉ ተስፋ የሚሰጡ ወቅቶች መጥተው ሄደዋል—በጋህና መከርህ አልፈዋል—አሁንም ግን አልዳንህም። ዓመታት አንዱ ሌላውን እየተከተለ ወደ ዘላለም ሄደዋል፤ የመጨረሻው ዓመትህም በቅርቡ ይደርሳል፤ ወጣትነት አልፎአል፥ ጕልምስናም እያለፈ ነው፤ አሁንም ግን አልዳንህም። ልጠይቅህ—ከቶ ትድን ይሆን? የዚህስ ዕድል አለን? እጅግ የተመቹ ወቅቶች ሳትድን ትተውህ አልፈዋል፤ ሌሎች አጋጣሚዎች ሁኔታህን ይለውጡ ይሆን? መንገዶች ሁሉ በአንተ ላይ ከሽፈዋል—ከመንገዶች ሁሉ የተሻሉት፥ በትዕግሥትና በፍጹም ፍቅር የተሠራባቸው—ከዚህ የበለጠ ምን ሊደረግልህ ይችላል? መከራም ብልጽግናም በአንተ ላይ ምንም ስሜት ሊያሳድሩ አልቻሉም፤ እንባ፥ ጸሎትና ስብከት በመካኑ ልብህ ላይ በከንቱ ባከኑ። ዕድሉ ሁሉ ከቶ እንዳትድን በብርቱ የሚያመለክት አይደለምን? ሞት የተስፋን በር ለዘላለም እስኪዘጋ ድረስ እንዳለህ የምትቆይ መሆንህ ይበልጥ የሚመስል አይደለምን? ይህን ግምት ትሸሻለህን? ሆኖም እጅግ ምክንያታዊ ግምት ነው፤ በእነዚህ ሁሉ ውኆች ያልታጠበ ሰው በሁሉ ዕድል ርኩስ ሆኖ ወደ ፍጻሜው ይሄዳል። የሚመችህ ጊዜ ከቶ አልመጣም፤ ስለ ምን ደግሞ ይመጣል? ከቶ እንደማይመጣ፥ እንደ ፊልክስም በሲኦል እስክትሆን ድረስ የሚመች ጊዜ እንዳታገኝ መፍራት ምክንያታዊ ነው። ኦ ያ ሲኦል ምን እንደ ሆነ፥ በቅርቡም ወደ እርሱ ልትጣል እንደምትችል ያለውን አስፈሪ ዕድል አስብ!
አንባቢ ሆይ፥ ሳትድን ብትሞት ዕጣ ፈንታህን ምንም ቃል ሊገልጸው አይችልም። አስፈሪውን ሁኔታህን በእንባና በደም ጻፈው፤ በመቃተትና ጥርስ በማፋጨት ተናገርበት፤ ከጌታ ፊትና ከኃይሉ ክብር ተለይተህ በዘላለም ጥፋት ትቀጣለህ። የወንድም ድምፅ አስደንግጦ ወደ ትጋት ሊያነቃህ ይመኛል። ኦ ጥበበኛ ሁን፥ ጊዜው ሳያልፍ ጥበበኛ ሁን፤ ሌላ ዓመትም ሳይጀምር ፈጽሞ ሊያድን በሚችለው በኢየሱስ እመን። እነዚህን የመጨረሻ ሰዓታት ለብቻህ ለማሰላሰል ቀድሳቸው፤ ጥልቅ ንስሐ በውስጥህ ቢወለድ መልካም ይሆናል፤ በኢየሱስ ወደ ትሑት እምነት ቢያደርስህ ደግሞ ከሁሉ የሚሻል ይሆናል። ኦ ይህ ዓመት ይቅርታ ያላገኘህ መንፈስ ሆነህ ሳለ እንዳያልፍ ተጠንቀቅ። የአዲሱ ዓመት የእኩለ ሌሊት ደወል ደስታ በሌለው መንፈስ ላይ አይደውል! አሁን፥ አሁን፥ አሁኑኑ እመን፥ በሕይወትም ኑር።
«ነፍስህን አድን፤
ወደ ኋላህ አትመልከት፥
በዚህም ሜዳ ሁሉ አትቁም፤
ወደ ተራራው አምልጥ፥
እንዳትጠፋ።»