የእምነት ባንክ የቼክ ደብተር
የጁላይ ወር

ምዕራፍ 8 · 24 ደቂቃ ንባብ · 30 ደቂቃ ማዳመጥ

የጁላይ ወር

ጁላይ 1

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር

«እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል» ዘፍጥረት 48:21

ደጉ ሽማግሌ ያዕቆብ የሚሞትበት ሰዓት ደርሶ ስለ ነበር ከዚያ በኋላ ከዮሴፍ ጋር ሊሆን አልቻለም፤ ነገር ግን «እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል» ብሎ በእርግጠኝነት ስለ ተናገረ ልጁን ያለ ጭንቀት ተወው። በጣም የምንወዳቸው ዘመዶቻችን ወይም እጅግ የሚረዱን ወዳጆቻችን በሞት ወደ ቤታቸው ሲጠሩ፥ ጌታ ከእኛ እንዳልተለየ፥ ነገር ግን ለእኛ ሕያው እንደ ሆነና ለዘላለም ከእኛ ጋር እንደሚኖር በማሰብ ራሳችንን ማጽናናት ይገባናል።

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፥ ድሆችና የተናቅን ብንሆንም እንኳ ክብርን በሚሰጥ ጓደኝነት ውስጥ ነን። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፥ ለጌታ የሚያቅተው ምንም ነገር ስለሌለ ሁሉን የሚበቃ ኃይል አለን። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፥ በጥላው ሥር የሚሄዱትን ማንም ሊጎዳቸው ስለማይችል ሁልጊዜ በሰላም ነን። ኦ፥ እዚህ ምንኛ ደስታ አለን! እግዚአብሔር አሁን ከእኛ ጋር ብቻ አይደለም፤ ወደ ፊትም ከእኛ ጋር ይሆናል። ከእያንዳንዳችን ጋር፥ ከቤተሰቦቻችን ጋር፥ ከአብያተ ክርስቲያናቶቻችንም ጋር ይሆናል። የኢየሱስ ስም ራሱ አማኑኤል፥ ማለትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አይደለምን? ከሁሉ የሚበልጠው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑ አይደለምን? እንግዲህ በድፍረት እንትጋ፥ በደስታም ተስፋ እናድርግ። ጌታ ከእርሱ ጋር ካሉት ጋር ስለ ሆነ ዓላማችን ይከናወናል፥ እውነትም ያሸንፋል።

ወደ «የእምነት ባንክ የቼክ ደብተር» የሚመለስ አማኝ ሁሉ ይህን ጣፋጭ ቃል ዛሬ ቀኑን ሙሉ ይደሰትበት። ከዚህ የሚበልጥ ደስታ ሊኖር አይችልም።

ጁላይ 2

የሚያድስ እንቅልፍ

«ለወዳጆቹ እንቅልፍን ይሰጣልና» መዝሙር 127:2

ሕይወታችን የጭንቀት ሕይወት ሳይሆን የደስተኛ እምነት ሕይወት ነው። የሰማዩ አባታችን የልጆቹን ፍላጎት ይሞላል፤ ሳንለምነውም የሚያስፈልገንን ያውቃል። ስለዚህ በተገቢው ሰዓት ወደ መኝታችን መሄድ እንችላለን፤ ለማሴር፥ ለማቀድና ዘዴ ለመፈለግ አምሽተን በመቀመጥ ራሳችንን አናድክም። በአምላካችን መታመንን ከተማርን፥ ፍርሃት ልባችንን እየበላ ነቅተን አንተኛም፤ ነገር ግን ጭንቀታችንን በጌታ ላይ እንተዋለን፤ ስለ እርሱ ማሰባችን ጣፋጭ ይሆንልናል፥ እርሱም የሚያድስ እንቅልፍ ይሰጠናል።

የጌታ ወዳጅ መሆን ከሁሉ የሚበልጥ ክብር ነው፤ ይህ ያለው ሰው ምኞት ራሱ ከዚህ በላይ ሊመኝ እንደማይችል ሊሰማው ይችላል፤ ስለዚህ የራስ ወዳድነት ምኞት ሁሉ ሊያንቀላፋ ይችላል። በሰማይ እንኳ ከእግዚአብሔር ፍቅር በላይ ምን አለ? እንግዲያስ ነፍሴ ሆይ፥ ሁሉ ነገር የአንቺ ነውና እረፊ።

ሆኖም ጌታ ራሱ የእረፍትን ምክንያቶች ብቻ ሳይሆን እረፍትንም ራሱን ካልሰጠን ወዲያና ወዲህ እንገላበጣለን። አዎን፥ እርሱ ይህን ያደርጋል። ኢየሱስ ራሱ ሰላማችን፥ እረፍታችን፥ ሁሉ ነገራችንም ነው። በሕይወትም በሞትም በእቅፉ ውስጥ ፍጹም በሆነ ደኅንነት እናንቀላፋለን።

«ይቅር በሚል ደም እንደ ገና ተረጭቼ፥

ለማረፍ እተኛለሁ፥

በአምላኬ እቅፍ ውስጥ እንዳለሁ፥

ወይም በአዳኜ ደረት ላይ።»

ጁላይ 3

እስከ መጨረሻው የሚመራ

«እርሱ እስከ ሞት ድረስ ይመራናል» መዝሙር 48:14

መሪ ያስፈልገናል። አንዳንድ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብንና ወዴት መዞር እንዳለብን በትክክል የሚነግረን ብናገኝ ያለንን ሁሉ በሰጠን ነበር። ትክክለኛውን ማድረግ እንፈልጋለን፤ ነገር ግን ከሁለቱ መንገዶች የትኛውን መከተል እንዳለብን አናውቅም። ኦ፥ መሪ ቢኖረን!

አምላካችን ጌታ ራሱን ዝቅ አድርጎ መሪያችን ሊሆን ፈቅዶአል። መንገዱን ያውቃል፤ በሰላምም ወደ ጉዞአችን መጨረሻ እስክንደርስ ድረስ በዚያ ይመራናል። ከዚህ የበለጠ የማይሳሳት መመሪያ በእርግጥ አንሻም። ራሳችንን ፈጽሞ በእርሱ አመራር ሥር እናድርግ፤ መንገዳችንንም ከቶ አንስትም። እርሱን አምላካችን ብናደርገው መሪያችን ሆኖ እናገኘዋለን። በምንራመደው እርምጃ ሁሉ በእርሱ መደገፍን አስቀድመን ከተማርን፥ ሕጉን ብንከተል ትክክለኛውን የሕይወት መንገድ አንስትም።

መጽናናታችን ይህ ነው፤ እርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችን እንደ ሆነ፥ መሪያችን ሆኖ ከእኛ ጋር መሆኑን ከቶ አያቋርጥም። «እስከ ሞት ድረስ» ይመራናል፤ ከዚያም ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንኖራለን፥ ደግሞም ወደ ውጭ አንወጣም። ይህ የመለኮታዊ አመራር ተስፋ የዕድሜ ልክ ደኅንነትን ይዟል፤ ወዲያውኑ መዳንን፥ እስከ መጨረሻ ሰዓታችን ድረስ አመራርን፥ ከዚያም ማለቂያ የሌለውን ብፅዕና። እንግዲህ እያንዳንዱ በወጣትነቱ ይህን ሊሻ፥ በጎልማሳነቱ ሊደሰትበት፥ በእርጅናውም ሊያርፍበት አይገባውምን? ዛሬ ከቤት ከመውጣታችን በፊት አመራርን ለማግኘት ወደ ላይ እንመልከት።

ጁላይ 4

ቃሉ፥ የግድ የሚያስፈልግ ምግብ

«ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም» ማቴዎስ 4:4

እግዚአብሔር ቢፈቅድ ኢየሱስ አርባ ቀን እንዳደረገው ያለ እንጀራ መኖር እንችል ነበር፤ ያለ ቃሉ ግን መኖር አንችልም። በዚያ ቃል ተፈጥረናል፤ በእርሱም ብቻ በሕይወት ልንጠበቅ እንችላለን፤ እርሱ ሁሉን በኃይሉ ቃል ደግፎ ይዟልና። እንጀራ ሁለተኛ ምክንያት ነው፤ የምግባችን የመጀመሪያው ምንጭ ጌታ ራሱ ነው። ከሁለተኛው ምክንያት ጋርም ያለ እርሱም ሊሠራ ይችላል፤ እኛም በአንድ የአሠራር መንገድ ብቻ ልናስረው አይገባንም። የሚታየውን ነገር እጅግ አንመኝ፤ ይልቁንም ወደማይታየው እግዚአብሔር እንመልከት። በከፋ ድህነት ውስጥ እንጀራ ሲያጥራቸው የምግብ ፍላጎታቸውም እንዳጠረ አማኞች ሲናገሩ ሰምተናል፤ ለሌሎች ደግሞ የተለመደው ቀለብ ሲያልቅ ጌታ ያልተጠበቀ እርዳታ ልኮላቸዋል። የጌታ ቃል ግን ሊኖረን የግድ ነው። በእርሱ ብቻ ዲያብሎስን መቋቋም እንችላለን። ይህን ከእኛ ውሰዱ፥ ቶሎ ስለምንዝል ጠላታችን በእጁ ያደርገናል። ነፍሳችን ምግብ ያስፈልጋታል፤ ከጌታ ቃል ውጭ ደግሞ ለእርሷ ምግብ የለም። በዓለም ያሉ መጻሕፍትና ሰባኪዎች ሁሉ አንድ ጊዜ የሚበቃ ምግብ እንኳ ሊሰጡን አይችሉም፤ የአማኝን አፍ መሙላት የሚችለው ከእግዚአብሔር አፍ የሚወጣው ቃል ብቻ ነው። ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ሁልጊዜ ስጠን። ከንጉሣዊ ጣፋጭ ምግብ ይልቅ እናከብረዋለን።

ጁላይ 5

ፍጹም መዳን

«በዚያ ቀን ግን እኔ አድንሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ አንተም በምትፈራቸው ሰዎች እጅ አትሰጥም።» ኤርምያስ 39:17

የጌታ ታማኞች ስለ እርሱ መከራ ሲቀበሉ ከራሱ ዘንድ ጣፋጭ የፍቅር መልእክቶች ይደርሷቸዋል፤ አንዳንድ ጊዜም ለሚያዝኑላቸውና ለሚረዷቸው ሰዎች የምሥራች ይኖራቸዋል። አቤሜሌክ የተናቀ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነበር፤ ነገር ግን ለኤርምያስ ደግ ነበር፤ ስለዚህ ጌታ በነቢዩ አፍ ይህን ልዩ ተስፋ ላከለት። ለሚሰደዱት የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሁልጊዜ እናስብ፤ እርሱም ዋጋችንን ይከፍለናል።

አቤሜሌክ በቀላቸውን ከሚፈራቸው ሰዎች መዳን ነበረበት። ትሑት ጥቁር ሰው ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ይጠብቀው ነበር። ከለዳውያን በሺህ የሚቆጠሩትን ገደሉ፤ ይህ ትሑት ኢትዮጵያዊ ግን ሊጎዳ አልቻለም። እኛም በእኛ ላይ የመረሩ አንዳንድ ታላላቅ ሰዎችን እንፈራ ይሆናል፤ ነገር ግን በስደት ሰዓት ለጌታ ዓላማ ታማኞች ከሆንን፥ እርሱ ለእኛ ታማኝ ይሆናል። ለመሆኑ ሰው ያለ ጌታ ፈቃድ ምን ማድረግ ይችላል? እርሱ በቁጣ አፍ ልጓምን፥ በኃይል ራስም ላይ ገመድን ያደርጋል። ጌታን እንፍራ፤ ሌላ የምንፈራው ማንም አይኖርም። ለተናቀ የእግዚአብሔር ነቢይ የተሰጠ አንድ ጽዋ ቀዝቃዛ ውኃ እንኳ ያለ ዋጋ አይቀርም፤ እኛም ለኢየሱስ ብንቆም ኢየሱስ ለእኛ ይቆማል።

ጁላይ 6

ፍቅሩ፤ ስጦታው፤ ልጁ

«በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።» ዮሐንስ 3:16

በሰማይ ካሉት ከዋክብት ሁሉ ለመርከበኛ ከሁሉ የሚጠቅመው የሰሜን ኮከብ ነው። ይህ ጥቅስ የሰሜን ኮከብ ነው፤ ከማንኛውም ሌላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ይልቅ ብዙ ነፍሳትን ወደ መዳን መርቷልና። በከዋክብት ስብስቦች መካከል ታላቁ ድብ እንደ ሆነ ሁሉ ይህም በተስፋዎች መካከል እንዲሁ ነው።

በውስጡ ያሉ በርካታ ቃላት በልዩ ድምቀት ያበራሉ። እዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር አለ፤ ልክ የሌለውን ታላቅነቱን የሚያመለክት «እንዲሁ» የሚል ቃልም አብሮት አለ። ከዚያም የእግዚአብሔር ስጦታ በነጻነቱና በታላቅነቱ ሁሉ አለ። ይህም ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ የሰማይ አንድያ ልጅ ለሰዎች ሊኖርና ሊሞት እስኪላክ ድረስ ራሱን ሙሉ በሙሉ ሊገልጥ ያልቻለ ፍቅር የሰጠው ልዩና በዋጋ የማይተመን ስጦታ። እነዚህ ሦስት ነጥቦች ብርሃን የሞላባቸው ናቸው።

ከዚያም ቀላሉ የማመን መስፈርት አለ፤ ይህም ለበደለኞች ሰዎች የሚስማማውን የመዳን መንገድ በጸጋ ያሳያል። ይህንንም ሰፊ መግለጫ ይደግፈዋል፤ «በእርሱ የሚያምን ሁሉ»። በጠባብ ቃል ተዘግቶባቸው የነበረ የሚመስላቸው ብዙዎች በ«ሁሉ» ውስጥ ቦታ አግኝተዋል። ከዚያም በኢየሱስ የሚያምኑ እንደማይጠፉ፥ ነገር ግን የዘላለም ሕይወት እንዲኖራቸው የሚናገረው ታላቁ ተስፋ ይመጣል። ይህ ሊጠፋ እንደ ተቃረበና ራሱን ማዳን እንደማይችል ለሚሰማው ሰው ሁሉ የሚያበረታታ ነው። እኛ በጌታ ኢየሱስ እናምናለን፥ የዘላለምም ሕይወት አለን።

ጁላይ 7

የተራሮች መዘምራን

«ሰማያት ሆይ፥ ዘምሩ፤ ምድር ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ ተራሮች ሆይ፥ እልል በሉ፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፥ ለችግረኞቹም ይራራልና።» ኢሳይያስ 49:13

የጌታ መጽናናት እጅግ ጣፋጭ ከመሆኑ የተነሣ ቅዱሳን ራሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሰማያትና ምድር እንኳ መዝሙሩን ሊያነሡት ይችላሉ። ተራራን ለማዘመር ብዙ ይጠይቃል፤ ነቢዩ ግን ብዙ የተራሮች መዘምራንን ይጠራል። ሊባኖስን፥ ስርዮንን፥ የባሳንና የሞዓብንም ረጃጅም ኮረብቶች፥ እግዚአብሔር ለራሱ ጽዮን ስላደረገው ጸጋ ሁሉንም ያዘምራቸው ነበር። እኛም የችግርንና የፈተናን፥ የምሥጢርንና የድካምን ተራሮች ለአምላካችን የምስጋና ምክንያት ልናደርጋቸው አንችልምን? «ተራሮች ሆይ፥ እልል በሉ!»

አምላካችን ለችግረኞቹ እንደሚራራ የሚናገረው ይህ የተስፋ ቃል ብዙ ደወሎች ተያይዘውበታል። ዜማቸውን ስሙ፤ «ዘምሩ!» «ደስ ይበላችሁ!» «እልል በሉ።» ጌታ በማያልቀው ፍቅሩ ምክንያት ሕዝቡ ደስተኞች እንዲሆኑ ይፈልጋል። እንድናዝንና እንድንጠራጠር አይፈልግም፤ የሚያምኑ ልቦችን አምልኮ ከእኛ ይሻል። እርሱ ሊተወን አይችልም፤ ታዲያ የሚተወን ይመስል ለምን እናቃስታለን ወይም እናኮርፋለን? ኦ፥ በሚገባ የተቃኘ በገና ቢኖረን! ኦ፥ በዙፋኑ ፊት እንዳሉት እንደ ኪሩቤል ያለ ድምፅ ቢኖረን!

ጁላይ 8

የመልአክ ሰፈር

«የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።» መዝሙር 34:7

መላእክትን ማየት አንችልም፤ እነርሱ እኛን ማየታቸው ግን በቂ ነው። ሳናየው የምንወደው አንድ ታላቅ የቃል ኪዳን መልአክ አለ፤ ዓይኑም ቀንና ሌሊት ሁልጊዜ በእኛ ላይ ነው። ከእርሱ በታች ብዙ ቅዱሳን ሠራዊት አሉ፤ እነርሱንም በቅዱሳኑ ላይ ጠባቂዎች አድርጎ ከክፉ ሁሉ ይጠብቁአቸው ዘንድ ያደርጋቸዋል። አጋንንት ቢጎዱን፥ የሚያበሩት ያገለግሉናል። የመላእክት ጌታ እንደሚመጣና እንደሚሄድ፥ አጭር ጉብኝትም እንደሚያደርግልን እንዳልሆነ ልብ በሉ፤ ነገር ግን እርሱና ሠራዊቱ በዙሪያችን ይሰፍራሉ። የመዳን ሠራዊት ዋና ሰፈር ሕያው በሆነው እግዚአብሔር የሚታመኑት በሚኖሩበት ስፍራ ነው። ይህ ሰፈር ታማኞችን ይከብባቸዋል፤ ስለዚህ ጠላት የመላእክትን ጌታ ምሽግ ጥሶ ካልገባ በቀር ከየትኛውም አቅጣጫ ሊያጠቃቸው አይችልም። የማይነቃነቅ ጥበቃና ቋሚ ዘብ አለን። በእግዚአብሔር መልእክተኞች እየተጠበቅን፥ በድንገተኛ ጥቃት አንደነግጥም፥ በሚያሸንፉ ሠራዊትም አንዋጥም። በዚህ ቁጥር መዳን ተሰጥቶአል፤ በታላቁ የመዳናችን አለቃ የሚሆን መዳን፤ ያንንም መዳን ጦርነታችን እስኪፈጸምና የግጭትን ሜዳ በእረፍት ቤት እስክንለውጥ ድረስ ደጋግመን እናገኘዋለን።

ጁላይ 9

ታማኝና ጠቃሚ

«ከእኔ ጋር ይቀመጡ ዘንድ ዓይኖቼ በምድር ታማኞች ላይ ናቸው፤ በቅን መንገድ የሚሄድ እርሱ ያገለግለኛል።» መዝሙር 101:6

ዳዊት እንዲህ ከተናገረ፥ የዳዊት ልጅም ተመሳሳይ አሳብ እንደሚኖረው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ኢየሱስ ታማኝ ሰዎችን ይፈልጋል፤ ሊመለከታቸው፥ ወደ ፊት ሊያወጣቸው፥ ሊያበረታታቸውና ዋጋቸውን ሊከፍላቸው ዓይኖቹን በእነርሱ ላይ ያደርጋል። ልቡ እውነተኛ የሆነ ማንም እንደ ተዘነጋ አያስብ፤ ንጉሡ ራሱ ዓይኑን በእርሱ ላይ አድርጎአል።

ከዚህ ንጉሣዊ ትኩረት ሁለት ውጤቶች ይገኛሉ። በመጀመሪያ «ከእኔ ጋር ይቀመጡ ዘንድ» የሚለውን እናነባለን። ኢየሱስ ታማኞችን ወደ ቤቱ ያመጣቸዋል፥ በቤተ መንግሥቱ ያኖራቸዋል፥ ባልንጀሮቹ ያደርጋቸዋል፥ በኅብረታቸውም ደስ ይለዋል። ለጌታችን ታማኞች መሆን አለብን፤ ያን ጊዜም ራሱን ይገልጥልናል። ታማኝነታችን ከሁሉ ይበልጥ ዋጋ ሲያስከፍለን ከሁሉ ይበልጥ ይሸለማል፤ ሰዎች በበለጠ ቁጣ በገፉን መጠን ጌታችን በበለጠ ደስታ ይቀበለናል።

ቀጥሎም ስለ ቅን ሰው «ያገለግለኛል» ይላል። ኢየሱስ የብልጠትን ተንኮል የሚንቁትንና ለእርሱ፥ ለቃሉና ለመስቀሉ ታማኞች የሆኑትን ለራሱ ክብር ይጠቀምባቸዋል። እነዚህ በንጉሣዊ አጃቢዎቹ ውስጥ ይሆናሉ፤ የግርማዊነቱ የተከበሩ አገልጋዮች ይሆናሉ። ኅብረትና ጠቃሚነት የታማኝነት ደመወዝ ናቸው። ጌታ ሆይ፥ ከአንተ ጋር እኖርና አገለግልህ ዘንድ ታማኝ አድርገኝ።

ጁላይ 10

ቤተ ክርስቲያንን ውደዱ

«አንተ ተነሥተህ ጽዮንን ትምራታለህ፤ የምትራራላት ጊዜ፥ የተወሰነውም ጊዜ ደርሶአልና። ባሪያዎችህ ድንጋዮችዋን ወድደዋልና፥ ለትቢያዋም ራርተዋልና።» መዝሙር 102:13, 14

አዎን፥ ስለ ቤተ ክርስቲያን የምናቀርበው ጸሎት ይሰማል። የተወሰነው ጊዜ ደርሶአል። የጸሎት ስብሰባን፥ የሰንበት ትምህርት ቤትን፥ የጌታ ቤት አገልግሎቶችንም ሁሉ እንወዳለን። በልባችን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ጋር ተሳስረናል፤ እንዲህም ብለን በእውነት መናገር እንችላለን፤ «ከመንጋህ መካከል ልመግበው የምንቀው አንድም ጠቦት የለም፤ ስለ ዓላማህ ለመሟገት ፊቱን የምፈራው አንድም ጠላት የለም።»

ይህ የሁሉም ስሜት ከሆነ ብዙም ሳንቆይ ከጌታ ፊት የመታደስ ዘመናትን እናገኛለን። ጉባኤዎቻችን ይሞላሉ፥ ቅዱሳን ይነቃቃሉ፥ ኃጢአተኞችም ይመለሳሉ። ይህ ከጌታ ምሕረት ብቻ ሊመጣ ይችላል፤ ነገር ግን በእርግጥ ይመጣል፤ እኛም እንድንጠብቀው ተጠርተናል። ጊዜው፥ የተወሰነው ጊዜ ደርሶአል። እንግዲህ እንነሣ። ፈርሳ እንኳ ብትሆን የጽዮናችንን ድንጋይ ሁሉ እንውደድ። አንዳንዶች እንደ ትቢያ ብቻ ቢንቋቸውም እንኳ ትንሿን እውነት፥ ትንሿን ሥርዓት፥ ትንሹንም አማኝ ከፍ አድርገን እንያዝ። ለጽዮን ስንራራ፥ እግዚአብሔር ሊራራላት ቀርቦአል። በጌታ ሥራ ደስ ሲለን፥ ጌታ ራሱ ደስ ይሰኝበታል።

ጁላይ 11

ከእግዚአብሔር ፈጽሞ አንለይም

«ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን?» ዮሐንስ 11:26

አዎን፥ ጌታ ሆይ፥ እናምናለን፤ ለዘላለም አንሞትም። ነፍሳችን ከሥጋችን ልትለይ ትችላለች፤ ይህም በአንድ ዓይነት ሞት ነው፤ ነገር ግን ነፍሳችን ከእግዚአብሔር ፈጽሞ አትለይም፤ እውነተኛው ሞት ይህ ነውና፤ በኃጢአት ላይ የተዛተበት ሞት፥ ሊደርስ ከሚችለው ሁሉ የከፋው የሞት ቅጣት። ይህን በፍጹም እርግጠኝነት እናምናለን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ማን ይለየናል? እኛ የክርስቶስ አካል ብልቶች ነን፤ ክርስቶስ የአካሉን ክፍሎች ያጣልን? ከኢየሱስ ጋር ተጋብተናል፤ እርሱ ሚስቱን ያጣልን? መበለትስ ይሆናልን? ይህ የማይቻል ነው። በውስጣችን ከእግዚአብሔር ሊለይ የማይችል ሕይወት አለ፤ አዎን፥ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ያድራል፤ ታዲያ እንዴት ልንሞት እንችላለን? ኢየሱስ ራሱ ሕይወታችን ነው፤ ስለዚህ ለእኛ ሞት የለም፤ እርሱ ዳግመኛ ሊሞት አይችልምና። በእርሱ አንድ ጊዜ ለኃጢአት ሞተናል፤ የሞቱ ፍርድም ሁለተኛ ጊዜ ሊፈጸም አይችልም። አሁን እንኖራለን፥ ለዘላለምም እንኖራለን። የጽድቅ ዋጋ የዘላለም ሕይወት ነው፤ እኛም ከእግዚአብሔር ጽድቅ ያነሰ ምንም የለንም፤ ስለዚህ ከሁሉ የላቀውን ዋጋ ልንጠይቅ እንችላለን።

ሕያዋን ሆነን እያመንን፥ እንደምንኖርና እንደምንደሰት እናምናለን። ስለዚህ ሕይወታችን በሕያው ራሳችን ውስጥ የተጠበቀ መሆኑን በሙሉ እርግጠኝነት አውቀን ወደ ፊት እንገሰግሳለን።

ጁላይ 12

ማንን፥ መቼ፥ እንዴት እንደሚያድን

«ጌታ እግዚአብሔርን የሚመስሉትን ከፈተና እንዴት እንዲያድናቸው፥ ዓመፀኞችንም ለፍርድ ቀን እየተቀጡ እንዲጠበቁ እንዴት እንደሚያደርግ ያውቃል።» 2ኛ ጴጥሮስ 2:9

እግዚአብሔርን የሚመስሉ ይፈተናሉ፥ ይፈተሹማል። ከቶ የማይፈተን እምነት እውነተኛ እምነት አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚመስሉ ከፈተናቸው ይድናሉ፤ ይህም በአጋጣሚ ወይም በሁለተኛ ደረጃ መሣሪያዎች ሳይሆን በጌታ በራሱ ነው። በእርሱ የሚታመኑትን የማዳንን ሥራ እርሱ ራሱ ይወስዳል። እግዚአብሔር ጻድቃንን፥ እርሱን የሚመስሉትን ይወዳል፤ የት እንዳሉና እንዴት እንደሚኖሩም ማወቅን ልዩ ጉዳዩ ያደርጋል።

አንዳንድ ጊዜ መንገዳቸው መውጫ የሌለው ጠመዝማዛ መንገድ ይመስላል፤ ከሚያሰጋቸውም አደጋ እንዴት እንደሚያመልጡ ሊገምቱ አይችሉም። እነርሱ የማያውቁትን ጌታቸው ያውቃል። ማንን እንደሚያድን፥ መቼ እንደሚያድን፥ እንዴትም እንደሚያድን ያውቃል። እግዚአብሔርን ለሚመስሉት እጅግ በሚጠቅም፥ ፈታኙን እጅግ በሚያደቅ፥ ለራሱም እጅግ ክብርን በሚያመጣ መንገድ ያድናል። «እንዴት» የሚለውን ለጌታ ትተን፥ እርሱ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ሕዝቡን በዚህ ሟች ሕይወት አደጋዎችና መከራዎች ፈተናዎችም ሁሉ አሳልፎ በክብር ወደ ቀኙ እንደሚያደርሳቸው በማወቅ ደስ ብሎን ልንረካ እንችላለን።

ዛሬ የጌታዬን ምሥጢር መመርመር የእኔ ድርሻ አይደለም፤ ነገር ግን ምንም ባላውቅም የሰማዩ አባቴ እንደሚያውቅ ተረድቼ ጊዜውን በትዕግሥት መጠበቅ ነው።

ጁላይ 13

ፍጹም መታመን

«በእኔ ታምነሃልና በእርግጥ አድንሃለሁ፥ በሰይፍም አትወድቅም፥ ነፍስህም ምርኮ ሆና ትቀርልሃለች፥ ይላል እግዚአብሔር።» ኤርምያስ 39:18

በእግዚአብሔር የመታመንን የመጠበቅ ኃይል ተመልከቱ። የኢየሩሳሌም ታላላቅ ሰዎች በሰይፍ ወደቁ፤ ድሀው አቤሜሌክ ግን መታመኑ በእግዚአብሔር ስለ ነበር በሰላም ተረፈ። ሰው ከፈጣሪው በቀር በማን ሊታመን ይገባዋል? ፍጡርን ከፈጣሪ አስበልጠን ስንመርጥ ሞኞች ነን። ኦ፥ በሁሉ ነገር በእምነት ብንኖር፥ በአደጋ ጊዜ ሁሉ በዳንን ነበር! በጌታ ታምኖ በከንቱ የቀረ ማንም የለም፤ ወደ ፊትም ማንም አይቀርም።

ጌታ «በእርግጥ አድንሃለሁ» ይላል። መለኮታዊውን «በእርግጥ» ልብ በሉ። ሌላው ሁሉ እርግጠኛ ባይሆን፥ እግዚአብሔር ለአማኞች የሚያደርገው ጥበቃ እርግጠኛ ነው። እግዚአብሔር ራሱ የጸጋ ሰዎች ጠባቂ ነው። አደጋ ሁሉ በየቦታው ቢሆን እንኳ በቅዱስ ክንፉ ሥር ደኅንነት አለ። ይህን ተስፋ እርግጠኛ እንደ ሆነ ልንቀበለው እንችላለንን? እንግዲያስ አሁን ባለንበት ችግር ጸንቶ እንደሚቆም እናገኘዋለን። ወዳጆች ስላሉን፥ ወይም ጠንቃቆች ስለ ሆንን፥ ወይም ተስፋ ሰጪ ምልክቶችን ስለምናይ እንደምንድን ተስፋ እናደርጋለን፤ ነገር ግን ከእነዚህ አንዳቸውም የእግዚአብሔርን ቀላል «በእኔ ታምነሃልና» ግማሽ ያህል እንኳ አይጠቅሙም። ውድ አንባቢ ሆይ፥ ይህን መንገድ ሞክር፤ ስትሞክረውም በሕይወትህ ሙሉ ትጸናበታለህ። እርግጠኛ እንደ ሆነ ሁሉ ጣፋጭም ነው።

ጁላይ 14

በእርሱ ላይ የተጣለ ሸክም

«ሸክምህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፥ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቅም ለዘላለም መናወጥን አይሰጠውም።» መዝሙር 55:22

ሸክሙ ከባድ ነው? ሁሉን በሚችለው ላይ አንከባልለው። አሁን ሸክሙ ያንተ ነው፥ ያደቅቅሃልም፤ ጌታ ሲወስደው ግን እንደ ምንም ያደርገዋል። አሁንም እንድትሸከመው ብትጠራ፥ «እርሱ ይደግፍሃል»። ሸክሙ በአንተ ላይ ሳይሆን በእርሱ ላይ ይሆናል። ከሥሩ ሆነህ እንዲህ ትደገፋለህ፤ ሸክሙም በረከት ይሆናል። ጌታን ወደ ጉዳዩ አስገባ፤ በራሱ ሊያጎብጥህ በሚችለው ነገር ሥር ቀጥ ብለህ ትቆማለህ።

ከሁሉ የሚበልጠው ፍርሃታችን መከራችን ከግዴታ መንገድ ያስወጣናል የሚል ነው፤ ጌታ ግን ይህን ከቶ አይፈቅድም። በፊቱ ጻድቃን ከሆንን፥ መከራችን ከቆምንበት እንዲያናውጠን አይታገሥም። በኢየሱስ ጻድቃን አድርጎ ይቀበለናል፤ በኢየሱስም እንዲሁ ይጠብቀናል።

ስለ አሁኑ ሰዓትስ? ወደ ዛሬው መከራ ብቻህን ልትወጣ ነውን? ደካማ ትከሻዎችህ በሚያስጨንቀው ሸክም እንደ ገና ሊቆስሉ ነውን? እንዲህ ሞኝ አትሁን። ሐዘንህን ሁሉ ለጌታ ንገረው፥ ከእርሱም ጋር ተወው። ሸክምህን አውርደህ እንደ ገና አትሸከመው፤ ነገር ግን በጌታ ላይ አንከባልለውና በዚያ ተወው። ያን ጊዜ ደስተኛና ሸክም የሌለበት አማኝ ሆነህ፥ ታላቁን ሸክም ተሸካሚህን እያመሰገንህ በነጻነት ትመላለሳለህ።

ጁላይ 15

የሚያዝን ይጽናናል

«የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና።» ማቴዎስ 5:4

በልቅሶ ሸለቆ በኩል ወደ ጽዮን እንመጣለን። ማዘንና ብፁዕ መሆን የሚቃረኑ ይመስሉ ይሆናል፤ ማለቂያ የሌለው ጥበበኛ አዳኝ ግን በዚህ ብፅዕና አንድ ላይ ያደርጋቸዋል። እርሱ ያጣመረውን ሰው አይለየው። ስለ ኃጢአት ማዘን፥ ስለ ራሳችን ኃጢአትና ስለ ሌሎች ኃጢአት፥ ጌታ በታማኞቹ ላይ ያደረገው ማኅተም ነው። የጸጋ መንፈስ በዳዊት ቤት ወይም በማንኛውም ሌላ ቤት ላይ ሲፈስ ያዝናሉ። ብርቅ የሆኑ ሸቀጦች በውኃ በኩል እንደሚደርሱን ሁሉ በቅዱስ ሐዘን ከበረከቶቻችን ሁሉ የሚበልጡትን እንቀበላለን። የሚያዝን ወደ ፊት በሆነ ቀን ብፁዕ የሚሆን ብቻ አይደለም፤ ክርስቶስ አሁን እንኳ ብፁዕ ብሎ ይጠራዋል።

መንፈስ ቅዱስ ስለ ኃጢአት የሚያዝኑትን ልቦች በእርግጥ ያጽናናቸዋል። የኢየሱስ ደም ሲደርስላቸውና የመንፈስ ቅዱስ የማንጻት ኃይል ሲሠራላቸው ይጽናናሉ። በከተማቸውና በዘመናቸው ስለ በዛው ኃጢአትም፥ ሰዎች ምንም ያህል ቢያምፁበት እግዚአብሔር ራሱን እንደሚያከብር በማረጋገጥ ይጽናናሉ። ብዙም ሳይቆዩ ከኃጢአት ፈጽመው ነጻ እንደሚወጡና በቅርቡ በጌታቸው ክቡር ፊት ለዘላለም ሊኖሩ እንደሚወሰዱ በመጠበቅ ይጽናናሉ።

ጁላይ 16

ለሚያነክስ የተነገረ ቃል

«የሚያነክሰውን አድናለሁ።» ሶፎንያስ 3:19

እንዲህ ያሉ አንካሶች፥ ወንዶችም ሴቶችም፥ ብዙ ናቸው። «የምታነክሰውን» በአንድ ሰዓት ውስጥ ሃያ ጊዜ ልታገኛት ትችላለህ። በትክክለኛው መንገድ ላይ ናቸው፤ በትጋትም በእርሱ ለመሮጥ እጅግ ይናፍቃሉ፤ ነገር ግን አንካሶች ናቸው፥ አካሄዳቸውም አሳዛኝ ነው። በሰማያዊው መንገድ ላይ ብዙ ሽባዎች አሉ። በልባቸው እንዲህ ይሉ ይሆናል፤ ምን ይደርስብናል? ኃጢአት ይደርስብናል፥ ሰይጣንም ይጥለናል። ለማንከስ የተዘጋጀን መሆን ስማችንም ተፈጥሮአችንም ነው፤ ጌታ ከቶ ጥሩ ወታደሮች ሊያደርገን አይችልም፥ መልእክቱንም ለማድረስ ፈጣን መልእክተኞች እንኳ ሊያደርገን አይችልም። መልካም፥ መልካም! እርሱ ያድነናል፤ ያም ትንሽ ነገር አይደለም። «የሚያነክሰውን አድናለሁ» ይላል። እኛን በማዳኑ ራሱን እጅግ ያከብራል። ሁሉም፥ ይህች አንካሳ ሴት ሩጫውን ሮጣ አክሊሉን እንዴት አገኘች? ብለው ይጠይቃሉ። ያን ጊዜም ምስጋናው ሁሉ ሁሉን ለሚችለው ጸጋ ይሰጣል።

ጌታ ሆይ፥ በእምነት፥ በጸሎት፥ በምስጋና፥ በአገልግሎትና በትዕግሥት ባነክስም፥ እለምንሃለሁ፥ አድነኝ! እንደ እኔ ያለውን ሽባ ማዳን የምትችል አንተ ብቻ ነህ። ጌታ ሆይ፥ ከሁሉ ኋላ ከሚቀሩት መካከል ስለ ሆንሁ አልጥፋ፤ ነገር ግን ከተጓዦችህ ሁሉ እጅግ የዘገየውን፥ እኔንም እንኳ፥ በጸጋህ ሰብስብ። እነሆ፥ እንዲህ እንደሚሆን ተናግሮአል፤ ስለዚህ እንደ ያዕቆብ በጸሎት አሸንፌ፥ ጅማቴ ቢሰለስልም ወደ ፊት እሄዳለሁ።

ጁላይ 17

ለእውነት ጀግና

«አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ግን ይበረታሉ፥ ታላቅ ሥራም ያደርጋሉ።» ዳንኤል 11:32

«እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው።» በዓላማው ሥር የሚመዘገቡ ለጦርነቱ የሚያሠለጥናቸውና ብርታትንም ጀግንነትንም የሚሰጣቸው አዛዥ ይኖራቸዋል። ዳንኤል የጻፈላቸው ዘመናት እጅግ የከፉ ነበሩ፤ በዚያን ጊዜም የእግዚአብሔር ሕዝብ በተሻለ መልካቸው እንደሚገለጡ ተስፋ ተሰጥቶ ነበር፤ ኃያሉን ጠላት ለመጋፈጥ ብርቱዎችና ጽኑዎች ይሆናሉ።

ኦ፥ አምላካችንን፥ ኃይሉን፥ ታማኝነቱን፥ የማይለወጠውን ፍቅሩን ብናውቅ፥ ስለ እርሱም ሁሉን አደጋ ላይ ለመጣል ዝግጁ ብንሆን! ጠባዩ ቅንዓታችንን የሚያነሣሣ፥ ለእርሱም ለመኖርና ለመሞት ፈቃደኞች የሚያደርገን እርሱ ነው። ኦ፥ ከእርሱ ጋር በቅርብ ኅብረት አምላካችንን ብናውቅ! ያን ጊዜ እርሱን እንመስላለን፥ ለእውነትና ለጽድቅ ለመቆምም እንዘጋጃለን። የእግዚአብሔርን ፊት አይቶ ገና የሚወጣ የሰውን ፊት ከቶ አይፈራም። ከእርሱ ጋር ብንኖር የጀግንነትን መንፈስ እንይዛለን፤ የጠላቶች ዓለምም በእኛ ዘንድ እንደ ባልዲ ጠብታ ብቻ ይሆናል። ቁጥር የሌለው የሰዎች ወይም የአጋንንት ሠራዊት እንኳ አሕዛብ በእግዚአብሔር ፊት እንደሚሆኑ ለእኛ ትንሽ ይመስላል፤ እርሱም እንደ አንበጣ ብቻ ይቈጥራቸዋል። ኦ፥ በዚህ የሐሰት ዘመን ለእውነት ጀግና መሆን!

ጁላይ 18

በምድረ በዳ ኅብረት

«እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ።» ሆሴዕ 2:14

የእግዚአብሔር ቸርነት በኃጢአት እንደ ተሳብን ያያል፤ የበለጠ ኃይል ያለውን የፍቅር መሳብ በእኛ ላይ ሊሞክርም ይወስናል። የነፍሳችን ወዳጅ በመጀመሪያ እንደ ማረከንና ከዓለም መሳብ እንዳራቀን አናስታውስምን? በክፉ ልንጠመድ እንደ ቀረብን ባየ ቁጥር ይህን ደጋግሞ ያደርጋል።

ለብቻችን ሊወስደን ተስፋ ይሰጣል፤ በዚያ በተሻለ ሁኔታ ከእኛ ጋር ሊሠራ ይችላልና። ይህ የተለየ ስፍራም ገነት ሳይሆን ምድረ በዳ ነው፤ በእንዲህ ያለ ስፍራ አሳባችንን ከአምላካችን የሚያርቅ ምንም አይኖርምና። በመከራ በረሃዎች የጌታ መገኘት ሁሉ ነገር ይሆንልናል፤ ከወገኖቻችን ጋር ሆነን ከወይናችንና ከበለሳችን በታች ተቀምጠን ሳለን ከሰጠነው ዋጋ በላይ ኅብረቱን እናከብራለን። ብቸኝነትና መከራ ሰዎችን ወደ ራሳቸውና ወደ ሰማዩ አባታቸው ከማንኛውም ሌላ መንገድ ይበልጥ ያመጣሉ።

እንዲህ ተስበንና ተገልለን ሳለን ጌታ ለመጽናናታችን የሚነግረን ምርጥ ነገሮች አሉት። መጀመሪያው ቃል እንደሚለው «ለልባችን ይናገራል»። ኦ፥ አሁን ይህ ተስፋ በሕይወታችን ልምምድ ቢገለጥልን! በፍቅር ተስበን፥ በመከራ ተለይተን፥ በእውነት መንፈስም ተጽናንተን፥ ጌታን እንወቅ፥ በደስታም እንዘምር!

ጁላይ 19

ለከባድ ሥራ የሚሆን ጫማ

«ጫማህ ብረትና ናስ ይሆናል፤ ኃይልህም እንደ ዘመንህ ይሆናል።» ዘዳግም 33:25

ለተጓዡ የተዘጋጁ ሁለት ነገሮች እዚህ አሉ፤ ጫማና ኃይል።

ስለ ጫማው፤ በሸካራ መንገዶች ለመጓዝና ገዳይ ጠላቶችን ለመርገጥ እጅግ አስፈላጊ ነው። ባዶ እግራችንን አንሄድም፤ ይህ ለንጉሣዊ ደም መሳፍንት አይገባም። ጫማችን ከተለመደው ዓይነት ፈጽሞ አይሆንም፤ ጉዞው ረጅምና አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ የማያልቅ ጠንካራ ብረት ሶል ይኖረዋልና። ለመንገዱና ለጦርነቱ ፍላጎት የሚመጥን ጥበቃ ይኖረናል። ስለዚህ በእባቦች ላይ ብንረግጥ ወይም በዘንዶው ራሱ ላይ እግራችንን ብናኖር እንኳ ክፉን ሳንፈራ በድፍረት እንገስግስ።

ስለ ኃይሉ፤ ዘመናችን እስከ ቀጠለ ድረስ ይቀጥላል፤ ለዘመናችን ጫናና ሸክምም የሚመጥን ይሆናል። ቃላቱ ጥቂት ናቸው፤ «እንደ ዘመንህ ኃይልህ»፤ ትርጉሙ ግን የተሞላ ነው። ዛሬ መከራንና ብርታትን የሚጠይቅ ሥራን ልንጠብቅ እንችላለን፤ ነገር ግን የሚመጥን ኃይልን በዚያው እርግጠኝነት ልንጠብቅ እንችላለን። ለአሴር የተሰጠው ይህ ቃል የራሳችን ልናደርገው የሚያስችል እምነት ላለን ለእኛም ተሰጥቶአል። በሚያምን ልብ ውስጥ ሊፈጥረው ወደታሰበው ቅዱስ ድፍረት እንነሣ።

ጁላይ 20

እርሱን መጠባበቅ

«ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል።» ዕብራውያን 9:28

ተስፋችን ይህ ነው። የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ እንደ መጣ አስቀድመን የተመለከትነው እርሱ ለሰው ልጆች ሌላ መገለጥ ይኖረዋል፤ ይህ በራሱ የደስታ ተስፋ ነው። ነገር ግን ያ ዳግመኛ መገለጥ እጅግ የሚያከብሩት የተለዩ ምልክቶች አሉት።

ጌታችን የኃጢአትን ጉዳይ ፈጽሞ ይጨርሳል። ከሕዝቡ እንዲህ አስወግዶታል፥ ቅጣቱንም እንዲህ በሚገባ ተሸክሞአል፤ ስለዚህ በዳግም ምጽአቱ ከእርሱ ጋር የሚያገናኘው ምንም አይኖርም። ኃጢአትን ፈጽሞ ስለሚያስወግድ የኃጢአት መሥዋዕት አያቀርብም።

ያን ጊዜ ጌታችን የሕዝቡን መዳን ይፈጽማል። በመጨረሻና በፍጹምነት ይድናሉ፤ በሁሉም ረገድ የዚያን መዳን ሙላት ይደሰቱበታል። የበደላችንን ፍሬ ሊሸከም ሳይሆን የመታዘዙን ፍሬ ሊያመጣ ይመጣል፤ ኩነኔያችንን ሊያስወግድ ሳይሆን መዳናችንን ሊፈጽም ነው።

ጌታችን እንዲህ የሚገለጠው ለሚጠባበቁት ብቻ ነው። ዓይኖቻቸው በራስ ወዳድነትና በኃጢአት በታወሩ ሰዎች በዚህ መልክ አይታይም። ለእነርሱ አስፈሪ ፈራጅ ይሆናል፤ ከዚያ ሌላ ምንም አይሆንም። በመጀመሪያ ወደ እርሱ መመልከት፥ ከዚያም እርሱን መጠባበቅ አለብን፤ በሁለቱም ሁኔታ ማየታችን ሕይወት ይሆናል።

ጁላይ 21

እንደ ብዙ ከዋክብት አብሩ

«ጥበበኞችም እንደ ሰማይ ጸዳል ይደምቃሉ፤ ብዙዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ።» ዳንኤል 12:3

የሚያነቃኝ ነገር እዚህ አለ። ይህ ሊኖሩለት የሚገባ ነው። ጥበበኛ መሆን በራሱ የተከበረ ነገር ነው፤ በዚህ ስፍራ ጌታ ራሱ ብቻ ሊሰጠው የሚችለውን መለኮታዊ ጥበብ ያመለክታል። ኦ፥ ራሴን፥ አምላኬንና አዳኜን ባውቅ! ሰማያዊውን እውነት በተግባር እንድፈጽምና በብርሃኑ እንድኖር በመለኮት ልማር! ሕይወቴ ጥበበኛ ናትን? ልፈልገው የሚገባኝን እየፈለግሁ ነውን? ለመሞት ስደርስ እንዲህ በኖርሁ ብዬ የምመኘውን ኑሮ እየኖርሁ ነውን? እንደዚያ በፀሐይ እንደ በራው ሰማይ ያለ ዘላለማዊ ድምቀትን ሊያስገኝልኝ የሚችለው እንዲህ ያለው ጥበብ ብቻ ነው።

የነፍሳት አዳኝ መሆን የከበረ ስኬት ነው። አንድን ሰው እንኳ ወደ ጽድቅ ለመመለስ ጥበበኛ መሆን ያስፈልገኛል፤ ብዙዎችን ለመመለስማ ምንኛ አብልጦ ያስፈልገኛል! ወገኖቼን፥ ደግሞም እጅግ ብዙዎቻቸውን ወደ እግዚአብሔር እንድመልስ የሚያስችለኝን የእግዚአብሔርን፥ የሰዎችን፥ የቃሉንና የክርስቶስን እውቀት ምነው ባገኘሁ! ራሴን ለዚህ እሰጣለሁ፥ እስክፈጽመውም ድረስ ከቶ አላርፍም። ይህ በንጉሥ ቤተ መንግሥት የኮከብ ኒሻን ከማግኘት ይበልጣል። ይህ እኔን ኮከብ፥ የሚያበራ ኮከብ፥ ለዘላለም ዓለም የሚያበራ ኮከብ ያደርገኛል፤ እንዲያውም እንደ ብዙ ከዋክብት እንዳበራ ያደርገኛል። ነፍሴ ሆይ፥ ንቂ! ጌታ ሆይ፥ ሕያው አድርገኝ!

ጁላይ 22

ዘላለማዊ ቃል ኪዳን

«ለዘላለምም ለእኔ አጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍርድ፥ በቸርነትና በምሕረትም ለእኔ አጭሻለሁ። በታማኝነትም ለእኔ አጭሻለሁ፤ እግዚአብሔርንም ታውቂያለሽ።» ሆሴዕ 2:19, 20

ለጌታ መታጨት! እንዴት ያለ ክብርና ደስታ ነው! ነፍሴ ሆይ፥ ኢየሱስ ራሱን ዝቅ አድርጎ ስላጨሽ በእውነት የአንቺ ሆኖአልን? እንግዲያስ ልብ በዪ፤ ይህ ለዘላለም ነው። እርሱ የገባውን የመታጨት ቃል ከቶ አያፈርስም፤ በጋብቻ ማሰሪያ ከራሱ ጋር የተጣመረችን ነፍስ ይፈታት ዘንድ የፍቺ ክስ ማቅረቡማ ፈጽሞ አይታሰብም።

ጌታ «አጭሻለሁ» ብሎ ሦስት ጊዜ ይናገራል። መታጨቱን ለመግለጥ እንዴት ያሉ ቃላትን አንድ ላይ ይከምራል! ቃል ኪዳኑን ሕጋዊ ለማድረግ ጽድቅ ይገባል፤ ይህን ሕጋዊ የጋብቻ አዋጅ ማንም ሊከለክል አይችልም። ፍርድ በውሳኔው ጥምረቱን ያጸድቃል፤ በዚህ ጋብቻ ውስጥ ሞኝነትን ወይም ስሕተትን ማንም ሊያይ አይችልም። ቸርነት ይህ የፍቅር አንድነት መሆኑን ያረጋግጣል፤ ፍቅር የሌለበት መታጨት ባርነት እንጂ ብፅዕና አይደለምና። በዚህ መካከል ምሕረት ፈገግ ትላለች፥ ትዘምራለችም፤ እንዲያውም ከዚህ ቅዱስ አንድነት ከሚትረፈረፈው ጸጋ የተነሣ ራስዋን አብዝታ «ምሕረቶች» ትሆናለች።

ታማኝነት መዝጋቢ ነው፥ ጋብቻውንም ይመዘግባል፤ መንፈስ ቅዱስም የታጨው ልብ ለከፍተኛ ዕጣ ፈንታው የሚያስፈልገውን የተቀደሰ እውቀት ሁሉ እንደሚያስተምረው ተስፋ ሲሰጥ በዚህ ላይ «አሜን» ይላል። እንዴት ያለ ተስፋ ነው!

ጁላይ 23

ፈጽሞ አይታሰብም

«ኃጢአታቸውንና ዓመፃቸውንም ደግሞ አላስብም።» ዕብራውያን 10:17

በዚህ በጸጋ ቃል ኪዳን መሠረት ጌታ ሕዝቡን ከቶ ኃጢአት እንዳልሠሩ አድርጎ ይይዛቸዋል። በተግባር በደላቸውን ሁሉ ይረሳል። የትኛውንም ዓይነት ኃጢአት እንዳልነበረ፥ ከትዝታውም ፈጽሞ እንደ ተደመሰሰ አድርጎ ይቆጥረዋል። የጸጋ ተአምር ሆይ! እግዚአብሔር እዚህ በአንዳንድ መልኩ ለእርሱ የማይቻለውን ያደርጋል። ምሕረቱ ከሌሎች ተአምራት ሁሉ እጅግ የሚልቁ ተአምራትን ትሠራለች።

የኢየሱስ መሥዋዕት ቃል ኪዳኑን ካጸናው ወዲህ አምላካችን ኃጢአታችንን አያስብም። ስለ በደላችን በእኛ ላይ ይቈጣል ብለን ሳንፈራ በእርሱ ደስ ሊለን ይችላል። እነሆ! ከልጆቹ መካከል ያኖረናል፤ እንደ ጻድቃን ይቀበለናል፤ ፍጹማን ቅዱሳን እንደ ሆንን አድርጎ በእኛ ደስ ይለዋል። እንዲያውም በአደራ ስፍራ ያኖረናል፤ የክብሩ ጠባቂዎች፥ የዘውዱ ዕንቁዎች ባለ አደራዎች፥ የወንጌል መጋቢዎች ያደርገናል። የተገባን አድርጎ ይቆጥረናል፥ አገልግሎትንም ይሰጠናል፤ ይህ ኃጢአታችንን እንደማያስብ የሚያሳይ ከሁሉ የሚበልጥና ልዩ ማስረጃ ነው። እኛ ጠላትን ይቅር ባልን ጊዜ እንኳ እርሱን ለማመን እጅግ እንዘገያለን፤ እንዲህ ማድረግ ጥበብ የጎደለው እንደ ሆነ እንቈጥራለን። ጌታ ግን ኃጢአታችንን ይረሳል፥ ከቶ እንዳልሳትንም አድርጎ ይይዘናል። ነፍሴ ሆይ፥ ይህ እንዴት ያለ ተስፋ ነው! እመኚው፥ ደስም ይበልሽ።

ጁላይ 24

ፍጹም ንጽሕና

«ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል።» ራእይ 3:5

የመስቀሉ ተዋጊ ሆይ፥ ተዋጋ! ድልህ እስኪፈጸም ድረስ ከቶ አትረፍ፤ ዘላለማዊ ዋጋህ የጦርነት ሕይወት የሚገባው ሆኖ ይገኛልና።

እነሆ፥ ለአንተ ፍጹም ንጽሕና ይኸውልህ! በሰርዴስ ጥቂቶች ልብሳቸውን ሳያረክሱ ጠበቁ፤ ዋጋቸውም ነውር የሌለባቸው መሆን ነው። ፍጹም ቅድስና የከፍተኛ ጥሪያችን ሽልማት ነው፤ እንዳያመልጠን እንጠንቀቅ።

እነሆ፥ ደስታ ይኸውልህ! ሰዎች በሰርግ ግብዣ የሚለብሱትን የበዓል ልብስ ትለብሳለህ፤ ሐሴትን ትጐናጸፋለህ፥ በደስታም ታበራለህ። አሳማሚ ትግሎች በኅሊና ሰላምና በጌታ በሚገኝ ደስታ ይፈጸማሉ።

እነሆ፥ ድል ይኸውልህ! የድል በዓልህን ታከብራለህ። የዘንባባ ዝንጣፊ፥ አክሊልና ነጭ ልብስ ዋጋህ ይሆናሉ፤ እንደ አሸናፊ ትያዛለህ፥ ጌታ ራሱም አሸናፊ መሆንህን ይመሰክርልሃል።

እነሆ፥ የክህነት ልብስ ይኸውልህ! የአሮን ልጆች ይለብሱት በነበረ ዓይነት ልብስ በጌታ ፊት ትቆማለህ፤ የምስጋናን መሥዋዕት ታቀርባለህ፥ በውዳሴ ዕጣንም ወደ ጌታ ትቀርባለህ።

ከታማኝ አገልጋዮቹ ለታናሹ እንኳ እንዲህ ያለ ታላቅ ክብር ለሚሰጥ ጌታ የማይዋጋ ማን ነው? በክብር እንደሚያለብሰን እያወቀ ስለ ክርስቶስ ብሎ የሞኝ ልብስ የማይለብስ ማን ነው?

ጁላይ 25

የሚያስደነግጠን ምንም የለም

«አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ድረስ በመንገድህ ሂድ፤ ታርፋለህና፥ በዘመኑም ፍጻሜ በዕጣህ ትቆማለህ።» ዳንኤል 12:13

ትንቢቶችን ሁሉ ልንረዳ አንችልም፤ ቢሆንም በድንጋጤ ሳይሆን በደስታ እንመለከታቸዋለን። በአብ ውሳኔ ውስጥ ልጁን በእውነት ሊያስደነግጥ የሚገባ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም። የጥፋት ርኩሰት ቢቆምም እውነተኛው አማኝ አይረክስም፤ ይልቁንም ይነጻል፥ ይነጣል፥ ይፈተናልም። ምድር ብትቃጠልም በተመረጡት ላይ የእሳት ሽታ አይደርስም። ፍጥረት ሲፈራርስና ዓለማት ሲጠፉ ጌታ እግዚአብሔር የራሱን ይጠብቃል።

በተግባራችን ተረጋግተንና ቈርጠን፥ በጦርነት ደፋሮች፥ በመከራ ታጋሾች ሆነን፥ ከመንገዳችን ሳንወጣና በእርሱም ላይ ሳንዘገይ መንገዳችንን ጠብቀን እንሂድ። ፍጻሜው ይመጣል፤ እስኪመጣ ድረስ በመንገዳችን እንሂድ።

ዕረፍት የእኛ ይሆናል። ሌሎች ነገሮች ሁሉ ወዲያና ወዲህ ይወዛወዛሉ፥ መሠረታችን ግን ጸንቶ ይቆማል። እግዚአብሔር በፍቅሩ ያርፋል፤ ስለዚህም እኛ በእርሱ እናርፋለን። ሰላማችን እንደ ወንዝ ነው፥ ለዘላለምም እንዲሁ ይሆናል። በሰማያዊቱ ከነዓን ያለው ዕጣ የእኛ ነው፤ የመጣው ቢመጣ በእርሱ እንቆማለን። የዳንኤል አምላክ እንደ ዳንኤል ለእውነትና ለቅድስና ቍርጥ አቋም ለመያዝ ለሚደፍሩ ሁሉ የተገባ ድርሻ ይሰጣቸዋል። የትኛውም የአንበሶች ጕድጓድ የተረጋገጠ ርስታችንን ሊያሳጣን አይችልም።

ጁላይ 26

የስም ለውጥ

«በዚያም ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ኢሺ ብለሽ ትጠሪኛለሽ፥ ደግሞም በኣሊ ብለሽ አትጠሪኝም፤ የበኣሊምን ስሞች ከአፍዋ አስወግዳለሁና፥ በስማቸውም ከእንግዲህ ወዲህ አይታሰቡም።» ሆሴዕ 2:16, 17

ያ ቀን ደርሶአል። አምላካችንን ከእንግዲህ እንደ በኣል፥ እንደ ጨካኝ ገዥያችንና ኃያል ጌታችን አድርገን አንመለከተውም፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደለንምና። አሁን እግዚአብሔርን አምላካችንን እንደ ኢሺያችን፥ እንደ ውድ ባላችን፥ በፍቅር እንደሚገዛን ጌታችን፥ በተቀደሰ ዝምድና ማሰሪያ እንደ ቅርብ ዘመዳችን አድርገን እናስበዋለን። እርሱን የምናከብረው ከቀድሞው ያነሰ አይደለም፥ የምንወደው ግን አብልጠን ነው። የምናገለግለው በታዛዥነት ያነሰ አይደለም፥ የምናገለግለው ግን ከፍ ባለና ይበልጥ በሚያስወድድ ምክንያት ነው። ከእንግዲህ ከጅራፉ በታች አንንቀጠቀጥም፥ በፍቅሩ ግን ደስ ይለናል። ባሪያው ልጅ ሆኖአል፥ ሸክሙም ደስታ ሆኖአል።

ውድ አንባቢ ሆይ፥ ለአንተስ እንዲህ ነውን? ጸጋ የባርነትን ፍርሃት አውጥቶ የልጅነትን ፍቅር ተክሎብሃልን? እንዲህ ያለ ልምምድ ስላለን እንዴት ደስተኞች ነን! አሁን የጌታን ቀን ደስታ ብለን እንጠራዋለን፥ አምልኮም ከቶ አያሰለችም። ጸሎት አሁን መብት ነው፥ ውዳሴም በዓል ነው። መታዘዝ መንግሥተ ሰማይ ነው፤ ለእግዚአብሔር ሥራ መስጠት ግብዣ ነው። እንዲህ ሁሉ ነገር አዲስ ሆኖአል። አፋችን በዝማሬ፥ ልባችንም በዜማ ተሞልቶአል። ሰማያዊው ኢሺያችን ለዘላለም ዓለም የተባረከ ይሁን።

ጁላይ 27

ከባዶ ቃል በላይ

«የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ።» ሐዋርያት ሥራ 13:34

ከሰው የሆነ ምንም ነገር የተረጋገጠ አይደለም፤ ከእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ ግን የተረጋገጠ ነው። በተለይ የቃል ኪዳን ምሕረቶች የታመኑ ምሕረቶች ናቸው፤ ዳዊት «በሁሉ የተዘጋጀና የጸና የዘላለም ቃል ኪዳን» እንዳለ።

ጌታ ምሕረቱን በእውነት አስቦ እንደ ተናገረ እርግጠኞች ነን። ባዶ ቃላትን አልተናገረም፤ በእያንዳንዱ ተስፋው ውስጥ ፍሬ ነገርና እውነት አለ። ምሕረቶቹ በእውነት ምሕረቶች ናቸው። አንድ ተስፋ በሞት ምክንያት የሚቀር ቢመስልም እንኳ ከቶ አይቀርም፤ ቸሩ ጌታ ቃሉን ይፈጽማልና።

ጌታ የተስፋ ምሕረቶቹን በቃል ኪዳኑ ላሉት ሁሉ እንደሚሰጥ እርግጠኞች ነን። በጊዜያቸው ወደ ጌታ የተመረጡ ሁሉ ይደርሳሉ። ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ለዘሩ ሁሉ የተረጋገጡ ናቸው።

ጌታ ምሕረቱን ለሕዝቡ እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን። እርሱ ሰጥቶ የሚወስድ አይደለም። የሰጠን ነገር ለብዙ ተጨማሪ ነገር ምልክት ነው። ገና ያልተቀበልነው አስቀድሞ እንደ መጣልን ሁሉ የተረጋገጠ ነው፤ ስለዚህ በጌታ ፊት እንጠብቅ፥ ዝምም እንበል። ለትንሹ ጥርጣሬ እንኳ ትክክለኛ ምክንያት የለም። የእግዚአብሔር ፍቅር፥ ቃሉና ታማኝነቱ የተረጋገጡ ናቸው። ብዙ ነገሮች አጠራጣሪ ናቸው፤ ስለ ጌታ ግን እንዲህ እንዘምራለን፦ «ምሕረቶቹ ይኖራሉና፥ ሁልጊዜ ታማኝ፥ ሁልጊዜ የጸኑ።»

ጁላይ 28

ዝቅ በል፤ ከፍ ትደረጋለህ

«እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ።» 1ኛ ጴጥሮስ 5:6

ይህ ከተስፋ ጋር እኩል ነው፤ ዝቅ ብንል ጌታ ከፍ ያደርገናል። ትሕትና ወደ ክብር ይመራል፤ መገዛት ወደ ከፍታ የሚያደርስ መንገድ ነው። ወደ ታች የሚጫነን ያው የእግዚአብሔር እጅ በረከቱን ለመሸከም በተዘጋጀን ጊዜ ሊያነሣን ይጠብቃል። ድል ለመንሣት ዝቅ እንላለን። ብዙዎች በሰዎች ፊት ያሸረግዳሉ፥ የሚመኙትን ድጋፍ ግን ያጣሉ፤ ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሱን የሚያዋርድ ግን ሁልጊዜ ቸር በሆነው አምላክ ባለ ጠጋ መሆንን፥ ከፍ መደረግን፥ መደገፍንና መጽናናትን ከቶ አያጣም። ትዕቢተኞችን መጣልና ትሑታንን ከፍ ማድረግ የእግዚአብሔር ልማድ ነው።

ሆኖም ጌታ የሚሠራበት ጊዜ አለው። አሁን፥ በዚህች ቅጽበትም እንኳ ራሳችንን ማዋረድ ይገባናል፤ ጌታ የሚያስጨንቅ እጁን በላያችን ቢጭንም ባይጭንም እንዲሁ ማድረጋችንን መቀጠል አለብን። ጌታ ሲመታ ተግሣጹን በጥልቅ መገዛት መቀበል ልዩ ግዴታችን ነው። ጌታ እኛን ከፍ ስለ ማድረጉ ግን፥ ያ ሊመጣ የሚችለው «በጊዜው» ብቻ ነው፤ ስለዚያ ቀንና ሰዓትም ከሁሉ የተሻለ ፈራጅ እግዚአብሔር ነው። ለበረከቱ ትዕግሥት አጥተን እንጮኻለንን? ጊዜውን ያልጠበቀ ክብር እንመኛለንን? ምን እያደረግን ነው? በእውነት ትሑታን አልሆንንም ማለት ነው፤ አለዚያ በጸጥታ በመገዛት እንጠብቅ ነበር። እንግዲህ እንዲሁ እናድርግ።

ጁላይ 29

ጠላታችንን ያባርራል

«ጠላትሽን አውጥቶ ጥሎአል።» ሶፎንያስ 3:15

ያ እንዴት ያለ ማባረር ነበር! ሰይጣን በሰማይ የነበረውን ስፍራ እንዳጣ፥ በባሕርያችን ውስጥ የነበረውን ዙፋንም አጥቶአል። ጌታችን ኢየሱስ ጠላት በእኛ ላይ የነበረውን የንግሥና ሥልጣን አጥፍቶአል። ሊያስጨንቀን ይችላል፥ የራሱ እንደ ሆንን ግን ሊናገር አይችልም። ማሰሪያዎቹ ከእንግዲህ በመንፈሳችን ላይ አይደሉም፤ ልጁ አርነት አውጥቶናል፥ በእውነትም አርነት ወጥተናል።

ዋናው ጠላት አሁንም የወንድሞች ከሳሽ ነው፤ ነገር ግን ከዚህ ስፍራም እንኳ ጌታችን አባርሮታል። ጠበቃችን ከሳሻችንን ዝም ያሰኛል። ጌታ ጠላቶቻችንን ይገሥጻል፥ የነፍሳችንንም ክርክር ይሟገታል፤ ስለዚህ ከዲያብሎስ ስድብ ሁሉ ምንም ጕዳት አይመጣም።

ክፉው መንፈስ እንደ ፈታኝ አሁንም ያጠቃናል፥ ወደ አእምሮአችንም ሾልኮ ይገባል፤ ነገር ግን ቀድሞ ከነበረው የበላይነቱ አንጻር ከዚያም ተባርሮአል። እንደ እባብ ይጥመለመላል፥ እንደ ንጉሥ ግን ሊገዛ አይችልም። አጋጣሚ ሲያገኝ የስድብ ሐሳቦችን ይወረውራል፤ ነገር ግን ጸጥ እንዲል ሲታዘዝና እንደ ተገረፈ ውሻ ሹልክ ብሎ እንዲሄድ ሲደረግ እንዴት ያለ እፎይታ ነው! ጌታ ሆይ፥ በዚህ ጊዜ በጩኸቱ ለሚጨነቁና ለሚደክሙ ሁሉ ይህን አድርግላቸው። ጠላታቸውን አባርር፥ በዓይናቸውም ፊት ክቡር ሁን። አንተ ጥለኸዋል፤ ጌታ ሆይ፥ አባርረው። ምነው ከዓለም ብታስወግደው!

ጁላይ 30

የወደፊት መገናኘት ተስፋ

«እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል።» ዮሐንስ 16:22

በእርግጥ ሁለተኛ ጊዜ ይመጣል፤ ያን ጊዜም እርሱ ሲያየን እኛም ስናየው በእውነት ደስታ ይሆናል። ያ አስደሳች መመለስ ምነው በደረሰ!

ነገር ግን ይህ ተስፋ በሌላ መልኩ በየዕለቱ እየተፈጸመ ነው። ቸሩ ጌታችን ከእኛ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ብዙ «እንደ ገና» አለው። ይቅርታን ሰጠን፤ አዳዲስ ኃጢአቶች ሲያሳዝኑንም እንደ ገና ያየናል፥ የስርየትንም ቃል ይደግማል። በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነታችንን ገልጦልናል፤ በዚያ በረከት ላይ ያለን እምነት ጥቂት ሲደበዝዝም ደጋግሞ ወደ እኛ ይመጣል፥ «ሰላም ለእናንተ ይሁን» ይላል፤ ልባችንም ደስ ይለዋል።

ወዳጆች ሆይ፥ ያለፉት ምሕረቶቻችን ሁሉ የወደፊት ምሕረቶች ምልክቶች ናቸው። ኢየሱስ ከእኛ ጋር ከነበረ እንደ ገና ያየናል። የትኛውንም ያለፈ ሞገስ እንደ ሞተና እንደ ተቀበረ፥ የሚለቀስለትም ነገር አድርገህ አትመልከተው፤ ይልቁንም የሚያድግ፥ ራሱንም ከአፈር ቀና አድርጎ «እንደ ገና አያችኋለሁ» ብሎ የሚጮኽ የተዘራ ዘር አድርገህ ቍጠረው። ኢየሱስ እንደ ቀድሞው ከእኛ ጋር ስለሌለ ዘመኑ ጨልሞአልን? እንበርታ፤ ብዙ ጊዜ ርቆ አይቆይምና። እግሮቹ እንደ ሚዳቋ ወይም እንደ ዋሊያ ግልገል እግሮች ናቸው፥ ፈጥነውም ወደ እኛ ያመጡታል። ስለዚህ አሁን እንኳ «እንደ ገና አያችኋለሁ» ስለሚለን ደስ መሰኘት እንጀምር።

ጁላይ 31

ልመናና መዳን

«በመከራም ቀን ጥራኝ፤ አድንሃለሁ፥ አንተም ታከብረኛለህ።» መዝሙር 50:15

ይህ በእውነት ተስፋ ነው!

አስቸኳይ ጊዜ ይኸውና፦ «የመከራ ቀን»። በእንዲህ ያለ ቀን በቀትር ጨለማ ነው፥ እያንዳንዱም ሰዓት ከቀደመው ይበልጥ የጠቈረ ይመስላል። ያን ጊዜ ይህ ተስፋ በወቅቱ ነው፤ የተጻፈው ለደመናማው ቀን ነውና።

ራሱን ዝቅ አድርጎ የሰጠው ምክር ይኸውና፦ «ጥራኝ»። ይህ ማሳሰቢያ ሊያስፈልገን አይገባም ነበር፤ ቀኑን ሙሉ በየቀኑም የዘወትር ልማዳችን ሊሆን ይገባዋል። እግዚአብሔርን ለመጥራት ነጻነት ማግኘት እንዴት ያለ ምሕረት ነው! እርሱንም በሚገባ መጠቀም እንዴት ያለ ጥበብ ነው! ወደ ሰዎች መሯሯጥ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! ጌታ ጕዳያችንን በፊቱ እንድናቀርብ ይጋብዘናል፤ በእርግጥ እንዲህ ለማድረግ አናመነታም።

የሚያጽናና ማበረታቻ ይኸውና፦ «አድንሃለሁ»። መከራው ምንም ቢሆን ጌታ ምንም ነገር አይለይም፤ ሙሉ፥ የተረጋገጠና አስደሳች መዳንን ተስፋ ይሰጣል እንጂ። እርሱ ራሱ በገዛ እጁ መዳናችንን ይፈጽማል። እናምነዋለን፤ ጌታም እምነትን ያከብራል።

የመጨረሻ ውጤት ይኸውና፦ «አንተም ታከብረኛለህ»። አቤት! ይህንማ እጅግ አብዝተን እናደርጋለን። ባዳነን ጊዜ በታላቅ ድምፅ እናመሰግነዋለን፤ እንደሚያደርገውም የተረጋገጠ ስለ ሆነ፥ አሁኑኑ እርሱን ማክበር እንጀምር።

ቀዳሚ ቀጣይ