የእምነት ባንክ የቼክ ደብተር
የሜይ ወር

ምዕራፍ 6 · 23 ደቂቃ ንባብ · 30 ደቂቃ ማዳመጥ

የሜይ ወር

ሜይ 1

በዝማሬ የተሞላ

«ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልል እያሉ ይዘምራሉ፥ የሜዳም ዛፎች ሁሉ በእጃቸው ያጨበጭባሉ» ኢሳይያስ 55:12

ኃጢአት ይቅር በተባለ ጊዜ ታላቁ ኀዘናችን ያበቃል፥ እውነተኛው ደስታችንም ይጀምራል። ጌታ ከእርሱ ጋር ለታረቁት የሚሰጠው ደስታ ሞልቶ እስኪፈስስና ፍጥረትን ሁሉ በሐሴት እስኪሞላ ድረስ እንዲህ ያለ ነው። ግዑዙ ዓለም በውስጡ የተሰወረ ዜማ አለው፤ የታደሰ ልብም ያንን ዜማ አውጥቶ እንዴት ድምፅ እንደሚያሰጠው ያውቃል። ፍጥረት ኦርጋን ነው፤ ጸጋ ያገኘ ሰውም ቁልፎቹን አግኝቶ እጁን ይጭንባቸዋል፥ የዩኒቨርስንም ሥርዓት ሁሉ ለምስጋና ስምምነት ያነቃዋል። ተራሮችና ኮረብቶች፥ ሌሎችም ታላላቅ ነገሮች የመዘምራኑ ወፍራም ድምፅ ናቸው ማለት ይቻላል፤ የዱር ዛፎችና ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ደግሞ የጣፋጩን መዝሙር ዜማ ይቀበላሉ።

የእግዚአብሔር ቃል በመካከላችን ሲከናወንና ነፍሳት ሲድኑ፥ ሁሉ ነገር በዝማሬ የተሞላ ይመስላል። የአዲሶቹን አማኞች ምስክርነት፥ በሚገባ የተማሩ ቅዱሳንንም ምስክርነት ስንሰማ እጅግ ደስ ስለሚለን ጌታን ከማመስገን ልንቆጠብ አንችልም፤ በዚያን ጊዜም ዐለቶችና ኮረብቶች፥ ዱሮችና እርሻዎች የደስታ ድምፃችንን የሚያስተጋቡና ዓለምን የሙዚቃ ጓድ ያደረጉት ይመስላል። ጌታ ሆይ፥ በዚህች ደስ በምታሰኝ የሜይ ቀን፥ ሙሉ ዝማሬውን እንደሚዘምር ወፍ በምስጋና የበለጸግሁ አድርገህ ዜማ ወደሞላበት ዓለምህ ምራኝ።

ሜይ 2

መንፈሳዊ ዘር

«በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል» ገላትያ 6:8

መዝራት የሚያከስር ሥራ ይመስላል፤ ዳግመኛ ላናየው መልካሙን እህል በመሬት ውስጥ እንቀብራለንና። በመንፈስ መዝራት ደግሞ የቅዠትና የሕልም ሥራ ይመስላል፤ ራሳችንን እንክዳለን፥ በሚታይም ምንም አናገኝበትም። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ለመኖር በመትጋት፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም በመሻትና ክብሩን ለማስፋት ራሳችንን በመስጠት በመንፈስ ብንዘራ፥ በከንቱ አንዘራም። ሕይወት፥ የዘላለም ሕይወት እንኳ፥ ዋጋችን ይሆናል። ይህንንም እዚሁ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ኅብረትና በእግዚአብሔር ወደ መደሰት ስንገባ እናጣጥመዋለን። ይህ ሕይወት ዘወትር እየጠለቀና እየሰፋ እንደሚሄድ ወንዝ ይፈስሳል፥ ወሰን ወደሌለው የተድላ ውቅያኖስም ያደርሰናል፤ በዚያም የእግዚአብሔር ሕይወት ለዘላለም ዓለም የእኛ ይሆናል።

ዛሬ በሥጋችን አንዝራ፤ ሥጋ ዘወትር ወደዚያ ያዘነብላልና መከሩ መበስበስ ይሆናል። ይልቁንም ራሳችንን በቅድስና አሸንፈን ለከፍተኛው፥ ለንጹሑና ለመንፈሳዊው ዓላማ እንኑር፤ እጅግ ቅዱስ የሆነውን ጌታችንን እጅግ ቸር የሆነውን መንፈሱን በመታዘዝ እናክብረው። የዘላለምን ሕይወት የምናጭድበት ያ መከር እንዴት ያለ ይሆን! የማያልቅ ብፅዕና ነዶ እንዴት ያለ ይታጨዳል! ያ መከር እንዴት ያለ በዓል ይሆን! ጌታ ሆይ፥ ስለ ልጅህ ብለህ እንደነዚህ ያሉ አጫጆች አድርገን።

ሜይ 3

ምልክቱን አድምጥ

«በሾላውም ዛፍ ራስ ላይ የሽውሽውታ ድምፅ በሰማህ ጊዜ በዚያን ጊዜ ፍጠን፤ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ይመታ ዘንድ እግዚአብሔር በዚያን ጊዜ በፊትህ ይወጣል» 2ኛ ሳሙኤል 5:24

እኛን ሊያንቀሳቅሱን የሚገቡ የጌታ እንቅስቃሴ ምልክቶች አሉ። የእግዚአብሔር መንፈስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም እንሰማለን። ያን ጊዜ ከመቼውም ይልቅ የምንነቃቃበት ጊዜ ነው። ወርቃማውን አጋጣሚ ይዘን የቻልነውን ያህል ልንጠቀምበት ይገባናል። ፍልስጥኤማውያንን በማንኛውም ጊዜ መዋጋት የእኛ ድርሻ ነው፤ ነገር ግን ጌታ ራሱ በፊታችን ሲወጣ በጦርነቱ በተለየ ሁኔታ ጀግኖች ልንሆን ይገባናል።

ነፋሱ የዛፎቹን ራስ አንቀሳቀሰ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ያንን የአደጋ ምልክት አድርገው ወሰዱት፥ በገሰገሱም ጊዜ ጌታ ራሱ ፍልስጥኤማውያንን መታ። ጌታ ዛሬ ስለ እርሱ ከብዙ ወዳጆቻችን ጋር የምንነጋገርበትን በር ቢከፍትልን እንዴት መልካም ነበር! ተስፋ ሰጪው በር በተከፈተ ጊዜ እንድንጠቀምበት ነቅተን እንጠብቅ። ይህች ቀን የምሥራች ቀን፥ ነፍሳትን የምንማርክበት ወቅት እንደማትሆን ማን ያውቃል? የነፋሱን ሽውሽውታ ለመስማት ጆሮአችንን፥ ምልክቱንም ለመታዘዝ አእምሮአችንን ዝግጁ እናድርግ። ይህ ተስፋ፥ «እግዚአብሔር በዚያን ጊዜ በፊትህ ይወጣል»፥ እንደ ወንድ ለመቆም በቂ ብርታት አይደለምን? ጌታ በፊታችን ስለሚሄድ ወደ ኋላ ለማለት አንደፍርም።

ሜይ 4

በውድቀት ውስጥ ድል

«ጠላቴ ሆይ፥ በእኔ ላይ ደስ አይበልሽ፤ ብወድቅ እነሣለሁ፤ በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛል» ሚክያስ 7:8

ይህ የተረገጠና የተጨቆነ ወንድ ወይም ሴት የሚሰማውን ሊገልጽ ይችላል። ጠላታችን ለጊዜው መብራታችንን ሊያጠፋ ይችላል። ለእኛ ግን በጌታ ዘንድ የተረጋገጠ ተስፋ አለ፤ በእርሱ ብንታመንና ቅንነታችንን አጥብቀን ብንይዝ፥ የመዋረዳችንና የጨለማችን ወቅት በቅርቡ ያልፋል። የባላጋራው ስድብ ለቅጽበት ብቻ ነው። ጌታ በቅርቡ ሣቃቸውን ወደ ልቅሶ፥ ሲቃችንንም ወደ ዝማሬ ይለውጣል።

ታላቁ የነፍሳት ጠላት ከእኛ በሚሻሉ ሰዎች ላይ እንደ ተመካ ለጊዜው በእኛ ላይ ቢመካስ ምን አለበት? አይዞን፤ በቅርቡ እናሸንፈዋለንና። አምላካችን አልወደቀምና ከውድቀታችን እንነሣለን፥ እርሱም ያነሣናል። አሁን በጨለማ ብንቀመጥም በዚያ አንኖርም፤ ጌታችን የብርሃን ምንጭ ነውና፥ በቅርቡም የደስታ ቀን ያመጣልናል። ተስፋ አንቁረጥ፥ አንጠራጠርም። መንኰራኵሩ አንድ ጊዜ ቢዞር የታችኛው ላይ ይወጣል። አሁን ለሚስቁ ወዮላቸው፤ ትምክህታቸው ወደ ዘላለም ውርደት በተለወጠ ጊዜ ያዝናሉ ያለቅሳሉምና። በቅድስና የሚያለቅሱ ግን ሁሉ ብፁዓን ናቸው፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጽናናትን ያገኛሉና።

ሜይ 5

ለምን በምርኮ ትኖራለህ?

«አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልሳል» ዘዳግም 30:3

የእግዚአብሔር የገዛ ሕዝብ በኃጢአት ራሳቸውን ለምርኮ ሊሸጡ ይችላሉ። ይህ እጅግ መራራ ከሆነ ሥር የሚገኝ መራራ ፍሬ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ለኃጢአት ሲሸጥ፥ በሰይጣን ሰንሰለት ሲታሰር፥ ነጻነቱን ሲያጣ፥ የጸሎት ኃይሉንና በጌታ የሚያገኘውን ደስታ ሲቀማ እንዴት ያለ ባርነት ነው! ወደዚህ ባርነት እንዳንገባ እንጠንቀቅ፤ ይህ ግን አስቀድሞ ደርሶብን ከሆነ በምንም መንገድ ተስፋ አንቁረጥ።

ለዘላለም በባርነት ልንያዝ አንችልምና። ጌታ ኢየሱስ በጠላት እጅ ሊተወን ለቤዛችን እጅግ ውድ ዋጋ ከፍሏል። የነጻነት መንገዱ «ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ» የሚለው ነው። መጀመሪያ መዳንን ባገኘንበት ስፍራ ዳግመኛ እናገኘዋለን። በክርስቶስ መስቀል ሥር ኃጢአትን እየተናዘዝን ይቅርታንና መዳንን እናገኛለን። ደግሞም ጌታ ባዘዘን ሁሉ እንደ ቃሉ እንድንታዘዝ ይፈልጋል፤ ይህንንም በፍጹም ልባችንና በፍጹም ነፍሳችን ልናደርገው ይገባል፥ ያን ጊዜም ምርኮአችን ያበቃል።

ብዙ ጊዜ የመንፈስ ድቀትና የነፍስ ታላቅ ጭንቀት ጣዖቶቻችንን እንደ ተውንና በሕያው አምላክ ፊት በመታዘዝ እንደ ሰገድን ወዲያው ይወገዳሉ። ምርኮኞች ሆነን መኖር አያስፈልገንም። ወደ ጽዮን ዜግነት መመለስ እንችላለን፥ ይህንንም ፈጥነን። ጌታ ሆይ፥ ምርኮአችንን መልስ!

ሜይ 6

የቅናት መድኃኒት

«ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፤ ነገር ግን ቀኑን ሁሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር። በእውነት ፍጻሜ አለና፥ ተስፋህም አይቈረጥም» ምሳሌ 23:17, 18

ክፉዎች ሲበለጽጉ ስናይ ልንቀናባቸው እንቃጣለን። የፌሽታቸውን ጩኸት ስንሰማና የገዛ መንፈሳችን ሲከብድ፥ የተሻለውን ዕድል ያገኙት እነርሱ እንደሆኑ በግማሽ እናስባለን። ይህ ሞኝነትና ኃጢአት ነው። እነርሱን በተሻለ ብናውቃቸውና በተለይም ፍጻሜያቸውን ብናስብ እናዝንላቸው ነበር።

የቅናት መድኃኒት ያለው የእግዚአብሔርን ሀልዎት ዘወትር እየተሰማን መኖር ነው፤ ቀኑ ምንም ያህል ረጅም ቢመስል ቀኑን ሁሉ እግዚአብሔርን ማምለክና ከእርሱ ጋር መነጋገር ነው። እውነተኛ ሃይማኖት ነፍስን ፍርድ ይበልጥ ወደሚጠራበትና ምኞት ይበልጥ ወደሚከብርበት ከፍ ወዳለ ስፍራ ያወጣታል። በሕይወታችን ያለው ሰማይ በበዛ መጠን የምንመኘው ምድራዊ ነገር ያንሳል። እግዚአብሔርን መፍራት በሰዎች ላይ መቅናትን ያስወጣል።

ቅናትን የሚገድለው ምት ስለሚመጣው ነገር በእርጋታ ማሰብ ነው። የኃጥኣን ሀብትና ክብር ከንቱ ትዕይንት ነው። ይህ የትዕቢት ገጽታ ለአንድ ሰዓት ብልጭ ይልና ይጠፋል። ፍርድ በደረሰበት ጊዜ የበለጸገው ኃጢአተኛ በብልጽግናው ምን ይጠቀማል? እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ግን ፍጻሜው ሰላምና ብፅዕና ነው፥ ደስታውንም ማንም ሊቀማው አይችልም፤ ስለዚህ ቅናትን ይተው፥ በጣፋጭ እርካታም ይሞላ።

ሜይ 7

ክፋት አይቅር

«እግዚአብሔርም ከቍጣው ጽናት ይመለስ ዘንድ፥ ምሕረትንም ያደርግልህ ዘንድ፥ ይራራልህም ዘንድ፥ ለአባቶችህም እንደ ማለ ያበዛህ ዘንድ፥ ከእርም ነገር ምንም በእጅህ አይጣበቅ» ዘዳግም 13:17

እስራኤል የጣዖት አምላኪዎችን ከተሞች ድል ማድረግና ምርኮውን ሁሉ ማጥፋት ነበረበት፤ በጣዖት አምልኮ የረከሰውን ሁሉ በእሳት የሚቃጠል የተረገመ ነገር አድርጎ መቍጠር ነበረበት። አሁንም ክርስቲያኖች ማንኛውንም ዓይነት ኃጢአት በዚሁ መንገድ ሊይዙት ይገባል። አንዲትም ክፉ ልማድ እንድትቀር መፍቀድ የለብንም። የሥጋም ሆነ የአእምሮ ወይም የመንፈስ፥ በየዓይነቱና በየመጠኑ ካለ ኃጢአት ጋር አሁን እስከ መጨረሻው ጦርነት ነው። ክፋትን መተዋችንን ምሕረት እንደሚያስገኝ አድርገን አንቈጥረውም፤ ይልቁንም በምንም ምክንያት ልናጣው የማንፈልገው የእግዚአብሔር ጸጋ ፍሬ አድርገን እንቈጥረዋለን።

እግዚአብሔር ለኃጢአታችን እንዳንራራ ሲያደርገን፥ ያን ጊዜ እርሱ ለእኛ እጅግ ይራራልናል። እኛ በክፋት ላይ ስንቈጣ፥ እግዚአብሔር ከእንግዲህ በእኛ ላይ አይቈጣም። በበደል ላይ ጥረታችንን ስናበዛ፥ ጌታ በረከታችንን ያበዛል። በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሰላም፥ የእድገት፥ የደኅንነትና የደስታ መንገድ እነዚህን ቃላት በመከተል ይገኛል፦ «ከእርም ነገር ምንም በእጅህ አይጣበቅ።» ጌታ ሆይ፥ ዛሬ አንጻኝ። ኃጢአትን በጽኑ ውሳኔ ለሚያስወግዱ ርኅራኄ፥ ብልጽግና፥ ብዛትና ደስታ በእርግጥ ይሰጣቸዋል።

ሜይ 8

ሠራተኛ ይፈለጋል

«እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም ትቀበላላችሁ» ማቴዎስ 20:7

አዎን፥ በክርስቶስ የወይን አትክልት ውስጥ ለአረጋውያንም ሥራ አለ። ጊዜው አሥራ አንደኛው ሰዓት ነው፥ ቢሆንም እንድንሠራ ይፈቅድልናል። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ጸጋ ነው! በእርግጥ ሽማግሌ ሁሉ በዚህ ጥሪ ሊዘልል ይገባዋል! ሰዎች በዕድሜ ከገፉ በኋላ ማንም አገልጋይ አድርጎ አይፈልጋቸውም፤ ከሱቅ ወደ ሱቅ ይሄዳሉ፥ ቀጣሪዎችም ሽበታቸውን አይተው ራሳቸውን ይነቀንቃሉ። ኢየሱስ ግን አረጋውያንን ይቀጥራል፥ መልካም ደመወዝም ይሰጣቸዋል! ይህ በእውነት ምሕረት ነው። ጌታ ሆይ፥ አረጋውያን አንድ ሰዓት ሳይዘገዩ በአገልግሎትህ እንዲሰለፉ እርዳቸው።

ነገር ግን ጌታ ለደከሙ ሽማግሌዎች ደመወዝ ይከፍላልን? አትጠራጠር። በእርሻው ብትሠራ የሚገባውን እንደሚሰጥህ ይናገራል። በእርግጥ እዚህ ጸጋን፥ ወዲያም ክብርን ይሰጥሃል። የአሁኑን መጽናናትና የሚመጣውን ዕረፍት፥ ለቀንህ የሚበቃ ኃይልን፥ የሞትም ሌሊት በደረሰ ጊዜ የክብርን ራእይ ይሰጥሃል። ጌታ ኢየሱስ እነዚህን ሁሉ በወጣትነቱ ወደ አገልግሎቱ ለገባው እንደሚሰጥ እንዲሁ ለአረጋዊው አማኝ በነጻ ይሰጣል።

ይህንን ላልዳኑ አንድ ሽማግሌ ወይም አንዲት አሮጊት ልንገር፥ ጌታም ስለ ኢየሱስ ብሎ እንዲባርከው ልጸልይ። እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች የት ላገኛቸው እችላለሁ? እነርሱን በንቃት እፈልጋቸዋለሁ፥ ወሬውንም በደግነት እነግራቸዋለሁ።

ሜይ 9

መታመን ደስታ ነው

«ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና» መዝሙር 33:21

የእምነት ሥር የልብን ደስታ አበባ ያስገኛል። መጀመሪያ ላይ ደስ ላይለን ይችላል፤ በጊዜው ግን ደስታው ይመጣል። ስናዝን በጌታ እንታመናለን፥ በወቅቱም ለመታመናችን እንዲህ ይመልስልናል፤ እምነታችን ወደ ፍሬ ይለወጣል፥ በጌታም ደስ ይለናል። ጥርጣሬ ጭንቀትን ይወልዳል፤ መታመን ግን በመጨረሻ ደስታን ያመጣል።

መዝሙረኛው በዚህ ቍጥር የገለጸው መተማመን በእውነት በቅዱስ መተማመን እጆች የቀረበ ተስፋ ነው። ይህንን የራሳችን ለማድረግ ጸጋ ቢሰጠን! አሁን ደስ ባይለን እንኳ፥ የዳዊት አምላክ አምላካችን እንደ ሆነ በእርግጥ ደስ ይለናል።

በተሻለ እንድንታመነውና ይበልጥ በፈቃደኝነት ደስ እንዲለን የጌታን ቅዱስ ስም እናሰላስል። እርሱ በባሕርዩ ቅዱስ፥ ጻድቅ፥ እውነተኛ፥ ቸር፥ ታማኝና የማይለወጥ ነው። እንደዚህ ያለው አምላክ ሊታመን አይገባውምን? እርሱ ሁሉን የሚያውቅ፥ ሁሉን የሚችልና በሁሉ ስፍራ ያለ ነው፤ በደስታ ልንደገፍበት አንችልምን? አዎን፥ አሁኑኑ ያለ ገደብ እናደርገዋለን። ይሖዋ ይርኤ ያዘጋጃል፥ ይሖዋ ሻሎም ሰላምን ይልካል፥ ይሖዋ ጽድቃኑ ያጸድቃል፥ ይሖዋ ሻማ ለዘላለም ቅርብ ይሆናል፥ በይሖዋ ንሲም ጠላትን ሁሉ እናሸንፋለን። አቤቱ፥ ስምህን የሚያውቁ ይታመኑብሃል፤ የሚታመኑብህም በአንተ ደስ ይላቸዋል።

ሜይ 10

እግዚአብሔርን ብቻ ፍራ

«ስለዚህ በድፍረት። ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል? እንላለን።» ዕብራውያን 13:6

እግዚአብሔር ፈጽሞ ስለማይተወንና ስለማይጥለን፥ ባለን ነገር ልንረካ ይገባናል። ጌታ የእኛ ስለ ሆነ ወዳጅ፥ ሀብትና መኖሪያ ሳይኖረን ልንቀር አንችልም። ይህ መተማመን ከሰዎች ፈጽሞ ነጻ እንደሆንን እንዲሰማን ሊያደርገን ይችላል። እንዲህ ባለ ከፍ ያለ ጠባቂ ሥር ስንሆን በባልንጀሮቻችን ፊት ለመሽቆጥቆጥና ሕይወታችንን የራሳችን ለማለት ፈቃድ ለመለመን አንፈተንም፤ ይልቁንም የምንናገረውን በድፍረት እንናገራለን፥ ተቃውሞንም አንፈራም።

እግዚአብሔርን የሚፈራ ሌላ የሚፈራው ነገር የለውም። ሕያውን ጌታ እጅግ ከመፍራታችን የተነሣ፥ እጅግ ትዕቢተኛው አሳዳጅ ሊጠቀምበት የሚችለው ዛቻ ሁሉ ከነፋስ ፉጨት የበለጠ ተጽዕኖ ሊያደርግብን አይገባም። ሐዋርያው በዚህ ገጽ ራስ ላይ ያለውን ቍጥር በጻፈበት ጊዜ ሰው በእኛ ላይ ያደርግ የነበረውን ያህል ዛሬ ሊያደርግ አይችልም። የማሰቃያ መሣሪያዎችና የማቃጠያ እንጨቶች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። ግዙፉ ጳጳስ አሁን ተጓዦቹን ሊያቃጥል አይችልም። የሐሰተኛ አስተማሪዎች ተከታዮች ጨካኝ ፌዝንና ንቀትን ቢሞክሩ አንደነቅም፤ የዚህ ዓለም ሰዎች ሰማያዊውን ዘር ሊወዱ አይችሉምና። ታዲያ ምን ይሁን? የዓለምን ንቀት መሸከም አለብን። አጥንት አይሰብርም። እግዚአብሔር እየረዳን ደፋሮች እንሁን፤ ዓለም ሲቈጣ ይቈጣ፥ እኛ ግን አንፍራው።

ሜይ 11

የመጨረሻውን ውጤት ጠብቅ

«ጋድ፥ ጭፍራ ይወጋዋል፤ እርሱ ግን በመጨረሻ ያሸንፋል።» ዘፍጥረት 49:19

ከእኛ አንዳንዶቻችን እንደ ጋድ ነገድ ሆነናል። ባላጋራዎቻችን ለጊዜው በዝተውብን እንደ ጭፍራ መጡብን። አዎን፥ ለጊዜውም አሸነፉን፤ በጊዜያዊ ድላቸውም እጅግ ፈነደቁ። በዚህም የቤተሰቡ ርስት የመጀመሪያው ክፍል በእርግጥ የእኛ መሆኑን ብቻ አረጋገጡ፤ የክርስቶስ ሕዝብ እንደ ጋድ ጭፍራ ያሸንፋቸዋልና። እንዲህ መሸነፍ እጅግ ያማል፤ የአባታችንን የበረከት ቃል ሁለተኛውን መስመር፥ «እርሱ ግን በመጨረሻ ያሸንፋል» የሚለውን በእምነት ባናምን ኖሮ ተስፋ እንቈርጥ ነበር። የዓለም ገጣሚ «በመልካም የሚያልቅ ሁሉ መልካም ነው» አለ፤ እውነትንም ተናገረ። ጦርነት የሚመዘነው በመጀመሪያ ድሎች ወይም ሽንፈቶች ሳይሆን «በመጨረሻ» በሚሆነው ነው። ጌታ ለእውነትና ለጽድቅ «በመጨረሻ» ድልን ይሰጣል፤ አቶ ባንየን እንደሚለውም ይህ ለዘላለም ማለት ነው፥ ከመጨረሻው በኋላ ምንም ሊመጣ አይችልምና።

የሚያስፈልገን በመልካም ሥራ በትዕግሥት መጽናትና በክቡሩ አለቃችን ላይ የተረጋጋ መተማመን ነው። ክርስቶስ፥ ጌታችን ኢየሱስ፥ «ተፈጸመ» እስክንል ድረስ ሥራውን ወይም መከራውን ለመፈጸም ፊትን እንደ ባልጩት የማጽናትን ቅዱስ ጥበቡን ሊያስተምረን ይወዳል። ሃሌ ሉያ። ድል! ድል! ተስፋውን እናምናለን። «እርሱ ግን በመጨረሻ ያሸንፋል።»

ሜይ 12

የከበሩ አገልጋዮች

«በለስን የሚጠብቅ ፍሬዋን ይበላል፤ ጌታውንም የሚጠብቅ ይከብራል» ምሳሌ 27:18

በለስን የሚንከባከብ ለድካሙ በለስን ያገኛል፤ መልካም ጌታን የሚያገለግልም ክብርን ዋጋው አድርጎ ይቀበላል። በእውነት ጌታ ኢየሱስ ከጌቶች ሁሉ እጅግ የሚበልጥ ጌታ ነው፤ ስለ እርሱም ትንሿን ሥራ እንኳ ለመሥራት መፈቀድ ክብር ነው። አንዳንድ ጌቶችን ማገልገል የኮምጣጣ ዛፍ ጠብቆ ኮምጣጣውን ፍሬ እንደ ደመወዝ መብላት ነው፤ ጌታዬን ኢየሱስን ማገልገል ግን እጅግ ጣፋጭ በለስ ያለበትን የበለስ ዛፍ መጠበቅ ነው። አገልግሎቱ በራሱ ደስታ ነው፤ በእርሱ መጽናት እድገት ነው፤ በእርሱ መከናወን በምድር ብፅዕና ነው፤ ዋጋውም በላይ ክብር ነው።

ታላላቅ ክብሮቻችን የሚሰበሰቡት በለሱ በሚበስልበት ወቅት፥ ማለትም በሚመጣው ዓለም ነው። አሁን የሚያገለግሉን መላእክት የቀን ሥራችን ሲያበቃ ወደ ቤት ይሸከሙናል። ኢየሱስ ያለበት ሰማይ ክቡር መኖሪያችን፥ ዘላለማዊ ተድላ ክቡር ዕድል ፈንታችን፥ ጌታ ራሱም ክቡር ባልንጀራችን ይሆናል። የዚህን ተስፋ፥ «ጌታውንም የሚጠብቅ ይከብራል» የሚለውን፥ ሙሉ ትርጉም ማን ሊገምት ይችላል?

ጌታ ሆይ፥ ጌታዬን እንድጠብቅ እርዳኝ። አንተ ራስህ የምታከብረኝን ሰዓት እስክጠብቅ ድረስ የክብርን ሐሳብ ሁሉ ልተው። መንፈስ ቅዱስህ ትሑትና ታጋሽ ሠራተኛና ጠባቂ ያድርገኝ!

ሜይ 13

ቀኑ ቀርቧል

«የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ» ራእይ 2:28

ቀኑ እስኪነጋና ጥላው እስኪሸሽ ድረስ በኢየሱስ «የንጋትን ኮከብ» ማየት እንዴት ያለ በረከት ነው! የቤተ ልሔም ኮከብ እንደገና ታየ የሚለውን ከንቱ ወሬ በጋዜጦች ያነበብንበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። ስንጠይቅ ግን «የንጋት ኮከብ» ብቻ እንደ ነበረ አገኘን፤ ቢሆንም ብዙም ስሕተት አልተሠራም ነበር።

ኢየሱስን እንደ ፀሐይ ማየት ይበልጣል፤ ይህን ማድረግ ባንችል ግን ቀጣዩ መልካም ነገር ቀኑን የሚያበስርና ዘላለማዊው ብርሃን እንደ ቀረበ የሚያሳይ ኮከብ አድርጎ ማየቱ ነው። ዛሬ ልሆን ተስፋ የማደርገውን ሁሉ ባልሆንም፥ ኢየሱስን አያለሁ፤ ይህም አንድ ቀን እርሱን እንደምመስል ያረጋግጥልኛል። ኢየሱስን በእምነት ማየት በክብሩ ለማየትና ወደ መልኩ ለመለወጥ መያዣ ነው። በዚህ ሰዓት የምመኘው ብርሃንና ደስታ ሁሉ ባይኖረኝም ይኖረኛል፤ የንጋትን ኮከብ በእርግጥ እንደማይ ቀኑንም በእርግጥ አያለሁና። የንጋት ኮከብ ከፀሐይ ፈጽሞ አይርቅም።

ነፍሴ ሆይ፥ ነዪ፤ ጌታ የንጋትን ኮከብ ሰጥቶሻልን? ጌታ የሰጠሽን እውነት፥ ጸጋ፥ ተስፋና ፍቅር አጥብቀሽ ይዘሻልን? እንግዲያስ በዚህ የሚመጣውን ክብር ንጋት አግኝተሻል። ክፉን እንድታሸንፊና በጽድቅ እንድትጸኚ የሚያደርግሽ እርሱ በዚህ የንጋትን ኮከብ ሰጥቶሻል።

ሜይ 14

ለፈውስ የሚደረግ ቀዶ ጥገና

«ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል» ሆሴዕ 6:1

ከመፈወሱ በፊት መቅደድ የጌታ መንገድ ነው። ይህ የልቡ ቅን ፍቅርና የእጁ የተረጋገጠ ቀዶ ጥገና ነው። ደግሞም ከመጠገኑ በፊት ያቈስላል፤ ያለዚያ ሥራው አስተማማኝ አይሆንም ነበር። ሕግ ከወንጌል ይቀድማል፤ የችግር ስሜትም ከመሟላቱ ይቀድማል። አንባቢ ሆይ፥ አሁን በሚወቅሰውና በሚያደቅቀው የመንፈስ እጅ ሥር ነህን? እንደ ገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ ተቀብለሃልን? ይህ ለእውነተኛው የወንጌል ፈውስና ጥገና ጠቃሚ መቅድም ነው።

ውድ ልብ ሆይ፥ ተስፋ አትቍረጥ፤ ይልቁንም የተቦጫጨቀ ቍስልህን፥ ጥቍር ስብራትህንና የሚመግል ቍስልህን ሁሉ ይዘህ ወደ ጌታ ና። እርሱ ብቻ ሊፈውስ ይችላል፥ ማድረግንም ይወዳል። ልባቸው የተሰበረውን መጠገን የጌታችን ሹመት ነው፥ በዚህም በክብር የተካነ ነው። አንዘግይ፤ ከእርሱ ወደ ሳትነው ጌታ ወዲያውኑ እንመለስ። የተከፈተውን ቍስላችንን እናሳየው፥ የገዛ ሥራውን እንዲያውቅና እንዲፈጽመውም እንለምነው። ሐኪም ቀድዶ በሽተኛውን ደሙ ፈስሶ እንዲሞት ይተወዋልን? ጌታ አሮጌውን ቤታችንን አፍርሶ የተሻለውን ሊሠራልን እምቢ ይላልን? አቤቱ፥ የምስኪኖችን የተጨነቁ ነፍሳት መከራ ያለ ምክንያት ታበዛለህን? ይህ ከአንተ ይራቅ፥ አቤቱ።

ሜይ 15

የእግዚአብሔር ከፍታዎች

«ስሜን አውቆአልና ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ» መዝሙር 91:14

ጌታ ይህንን ለእኔ ይላልን? አዎን፥ ስሙን አውቄ ከሆነ። ጌታ ይባረክ፥ ለእርሱ እንግዳ አይደለሁም። ሞክሬዋለሁ፥ ፈትኜዋለሁ፥ አውቄዋለሁም፤ ስለዚህም እታመንበታለሁ። ስሙን ኃጢአትን እንደሚጠላ አምላክ አውቃለሁ፤ በመንፈሱ የመውቀስ ኃይል ክፋትን ፈጽሞ ቸል እንደማይል ተምሬአለሁና። ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር የሚል አምላክ እንደሆነም አውቀዋለሁ፤ በደሌን ሁሉ ይቅር ብሎኛልና። ስሙ ታማኝነት ነው፥ ይህንንም አውቃለሁ፤ መከራዬ ቢበዛብኝም ፈጽሞ አልተወኝምና።

ይህ እውቀት የጸጋ ስጦታ ነው፤ ጌታም ሌላ የጸጋ ስጦታ፥ ማለትም ከፍ ከፍ ማድረግን፥ የሚሰጥበት ምክንያት ያደርገዋል። ይህ በጸጋ ላይ ጸጋ ነው። እኛ ራሳችን ወደ ከፍታ ብንወጣ ስፍራው አደገኛ ሊሆን እንደሚችል፥ ጌታ ግን ቢያስቀምጠን አስተማማኝ እንደሆነ አስተውሉ። ወደ ታላቅ ጥቅም፥ ወደ ልዩ ልምምድ፥ በአገልግሎት ወደ መከናወን፥ በሠራተኞች መካከል ወደ መሪነት፥ በታናናሾቹ መካከል ወደ አባትነት ስፍራ ከፍ ሊያደርገን ይችላል። ይህን ባያደርግ እንኳ በቅርብ ኅብረት፥ በጥርት ያለ ማስተዋል፥ በቅዱስ ድልና የዘላለምን ክብር በጸጋ በመጠባበቅ ከፍ ከፍ ሊያደርገን ይችላል። እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ሲያደርገን ሰይጣን ራሱ ሊያወርደን አይችልም። ዛሬ ቀኑን ሁሉ ይህ ዕድላችን ቢሆን እንዴት መልካም ነበር!

ሜይ 16

እንደምንሰጥ እንቀበላለን

«የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና።» ማቴዎስ 5:7

ይቅር የማይል ሰው ይቅር ሊባል አይገባውም፤ ለድሆች የማይሰጥም ችግሩ አይቃለልለትም። እግዚአብሔር በገዛ መስፈሪያችን ይሰፍርልናል፤ ጨካኝ ጌቶችና ጨካኝ አበዳሪዎች የነበሩ ጌታ በጭካኔ እንደሚያደርግባቸው ያገኙታል። «ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና።»

ዛሬ ለመስጠትና ይቅር ለማለት እንሞክር። ሁለቱን ነገሮች እናስብ፤ መሸከምና መታገሥ። ደጎች፥ ገሮችና ርኅሩኆች እንሁን። የሰዎችን ሥራ በክፉ አንተርጕም፥ አስጨናቂ ድርድር አንደራደር፥ የሞኝ ጠብ አንጫር፥ ለማስደሰትም አስቸጋሪ አንሁን። በእርግጥ ብፁዓን ለመሆን እንወዳለን፥ ምሕረትንም ለማግኘት እንሻለን፤ ምሕረትን እንድናገኝ መሐሪዎች እንሁን። ብፅዕናውን እንድንቀበል ቅድመ ሁኔታውን እንፈጽም። ደግ መሆን ደስ የሚያሰኝ ግዴታ አይደለምን? ከመቈጣትና ከንፉግነት ይልቅ በእርሱ እጅግ የሚበልጥ ጣፋጭነት የለበትምን? በእርግጥ በራሱ በነገሩ ብፅዕና አለ! ደግሞም ምሕረትን ማግኘት ባለጠጋ ዋጋ ነው። ከሉዓላዊ ጸጋ በቀር እንዲህ ያለውን ተስፋ ምን ሊያመጣ ይችላል? እኛ ለሟች ባልንጀራችን በሳንቲም ምሕረት እናደርጋለን፥ ጌታ ግን «ያን ዕዳ ሁሉ» ይተውልናል።

ሜይ 17

መቈጠብ አያስፈልግም

«ቅኖች ግን መልካም ነገርን ይወርሳሉ» ምሳሌ 28:10

የምሳሌ መጽሐፍ የተስፋዎችም መጽሐፍ ነው። ተስፋዎች በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ምሳሌዎች ሊሆኑ ይገባቸዋል። ይህ እጅግ የሚደነቅ ተስፋ ነው። መልካም ነገሮቻችን ወደፊት የሚጠብቁን እንደሆኑ ማሰብ ለምደናል፤ እዚህ ግን አሁን በእጃችን እንደሚሆኑ ተነግሮናል።

የጠላቶቻችን ክፋትና ተንኰል ሁሉ ጥፋታችንን ሊያመጣ አይችልም፤ እነርሱ በቈፈሩት ጕድጓድ ይወድቃሉ። ርስታችን ለእኛ እንዲህ ተጠብቆልናል፤ ከእርሱ አንከለከልም፥ እንዳናገኘውም ከመንገድ ፈቀቅ አንልም።

ታዲያ አሁን ምን አለን? በኢየሱስ ክቡር ደም የተረጋጋ ኅሊና አለን። ከለውጥ ሁሉ በላይ በእኛ ላይ የተደረገ የእግዚአብሔር ፍቅር አለን። በችግር ጊዜ ሁሉ በጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ኃይል አለን። የሚጠብቀን የእግዚአብሔር መግቦት፥ የሚያገለግሉን የእግዚአብሔር መላእክት፥ ከሁሉም በላይ በእኛ የሚኖር የእግዚአብሔር መንፈስ አለን። በእርግጥ ሁሉ ነገር የእኛ ነው። «ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው።» ኢየሱስ የእኛ ነው። አዎን፥ በአንድነት ያለው ቅድስት ሥላሴ የእኛ ነው። ሃሌ ሉያ። መልካም ነገር በእጃችን ስላለ አንማቅቅ፥ አናጕረምርም፥ አንቈጥብ፥ እንደ ባሪያም አንድከም። በአምላካችን እንኑር፥ ቀኑንም ሁሉ በእርሱ ደስ ይበለን። መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ እርዳን!

ሜይ 18

የተሸነፈ ኪሳራ

«አንበጣም የበላውን ዓመታት እመልስላችኋለሁ» ኢዩኤል 2:25

አዎን፥ የምናዝንባቸው እነዚያ የባከኑ ዓመታት ይመለሱልናል። እግዚአብሔር እንዲህ ያለ የበዛ ጸጋ ሊሰጠን ይችላል፤ ስለዚህ በትሑት ንስሐ ለምናለቅስባቸው ዳግመኛ ያልተወለድንባቸው ዓመታት በተወሰነ መጠን የሚካካስ አገልግሎትን በቀሪው ዘመናችን ውስጥ እናጭቃለን።

የኋሊት መመለስ፥ የዓለማዊነትና የለብታ አንበጦችን አሁን እንደ አስፈሪ መቅሠፍት እንመለከታቸዋለን። ፈጽሞ ወደ እኛ ባልቀረቡ ኖሮ! ጌታ በምሕረቱ አሁን አስወግዷቸዋል፥ እርሱንም ለማገልገል በቅንዓት ተሞልተናል። ስሙ ይባረክ፥ የቀድሞው መካንነታችን እንዲጠፋ የሚያደርግ የመንፈሳዊ ጸጋ መከር ልናመርት እንችላለን። በባለጠጋ ጸጋ መራራውን ልምዳችንን ለጥቅም ልናውለውና ሌሎችን ለማስጠንቀቅ ልንጠቀምበት እንችላለን። በቀድሞው ጕድለታችን ምክንያት በትሕትና፥ በልጅነት መደገፍና በንስሐ መንፈሳዊነት ይበልጥ ልንሠረት እንችላለን። ይበልጥ ንቁዎች፥ ቀናተኞችና ርኅሩኆች ብንሆን ከአሳዛኝ ኪሳራችን እናተርፋለን። የባከኑት ዓመታት በፍቅር ተአምር ሊመለሱ ይችላሉ። እጅግ ታላቅ ስጦታ ይመስላልን? ስለ እርሱ እንመን፥ ስለ እርሱም እንኑር፤ ጴጥሮስ ትዕቢቱ በተገለጠው ድካሙ ከተፈወሰ በኋላ ይበልጥ ጠቃሚ ሰው እንደሆነ፥ እኛም ገና ልናገኘው እንችላለን። ጌታ ሆይ፥ በጸጋህ እርዳን።

ሜይ 19

ስለ እግዚአብሔር ልንናገር እንችላለን

«ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ብትመለስ እመልስሃለሁ፥ በፊቴም ትቆማለህ፤ የከበረውንም ከተዋረደው ብትለይ እንደ አፌ ትሆናለህ» ኤርምያስ 15:19

ምስኪን ኤርምያስ! ነገር ግን ስለ ምን እንዲህ እንላለን? የሚያለቅሰው ነቢይ ከእግዚአብሔር ምርጥ አገልጋዮች አንዱ ነበረ፥ ከብዙዎችም ይልቅ በእርሱ ዘንድ የከበረ ነበረ። እውነትን በመናገሩ ተጠላ። ለእርሱ እጅግ ጣፋጭ የነበረው ቃል ለሰሚዎቹ መራራ ነበረ፤ ቢሆንም በጌታው ዘንድ ተቀባይነት አገኘ። በታማኝነቱ እንዲጸና ታዘዘ፥ ያን ጊዜም ጌታ በእርሱ መናገሩን ይቀጥል ነበር። ከሰዎች ጋር በድፍረትና በእውነት ሊሠራ፥ በዘመኑ በነበሩት በሃይማኖት ተናዛዦችም ላይ የጌታን የማበጠር ሥራ ሊፈጽም ነበረበት፤ ያን ጊዜም ጌታ ይህንን ቃል ሰጠው፦ «እንደ አፌ ትሆናለህ።»

እንዴት ያለ ክብር ነው! ሰባኪ ሁሉ፥ አዎን፥ አማኝ ሁሉ ይህን ሊመኘው አይገባውምን? እግዚአብሔር በእኛ ቢናገር እንዴት ያለ ድንቅ ነው! የተረጋገጠና ንጹሕ እውነትን እንናገራለን፤ በኃይልም እንናገረዋለን። ቃላችን በከንቱ አይመለስም፤ ለሚቀበሉት በረከት ይሆናል፥ የሚቃወሙትም በራሳቸው አደጋ ይቃወሙታል። ከንፈሮቻችን ብዙዎችን ይመግባሉ። የተኙትን እናነቃለን፥ ሙታንንም ወደ ሕይወት እንጠራለን።

ውድ አንባቢ ሆይ፥ ከጌታችን ከተላኩ አገልጋዮች ሁሉ ጋር እንዲሁ እንዲሆን ጸልይ።

ሜይ 20

ልንጠራጠር አንደፍርም

«በፊትህ እሄዳለሁ፥ ጠማማውንም አቀናለሁ፤ የናሱን በሮች እሰብራለሁ፥ የብረቱንም መወርወሪያ እቈርጣለሁ» ኢሳይያስ 45:2

ይህ ለቂሮስ ነበረ፤ ነገር ግን ለጌታ መንፈሳዊ አገልጋዮች ሁሉ ዘወትር ርስታቸው ነው። በእምነት ወደ ፊት ብቻ እንሂድ፥ መንገዳችንም ይጠረግልናል። የሰው ብልሃትና የሰይጣን ተንኰል ጠመዝማዛ መንገዶች ይቃኑልናል፤ ተጣማሚ መተላለፊያዎቻቸውን መከተል አያስፈልገንም። የናሱ በሮች ይሰበራሉ፥ ያጠነከሩአቸውም የብረት መወርወሪያዎች ይቈረጣሉ። መደብደቢያ ግንድም ሆነ መፈንቀያ ብረት አያስፈልገንም፤ ጌታ ራሱ የማይቻለውን ያደርግልናል፥ ያልተጠበቀውም እውን ይሆናል።

በፈሪ ፍርሃት አንቀመጥ። በግዴታ መንገድ ወደ ፊት እንግፋ፤ ጌታ «በፊትህ እሄዳለሁ» ብሎአልና። የእኛ ድርሻ ምክንያት መጠየቅ ሳይሆን መድፈርና ወደ ፊት መሮጥ ብቻ ነው። ሥራው የጌታ ነው፥ እንድንሠራውም ያስችለናል፤ እንቅፋት ሁሉ በፊቱ መሸነፍ አለበት። «የናሱን በሮች እሰብራለሁ» ብሎ የለምን? ዓላማውን ምን ሊያግደው፥ ውሳኔውንስ ምን ሊያከሽፈው ይችላል? እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ወሰን የሌለው ሀብት አላቸው። መንገዱ ለሰው ኃይል የተዘጋ ቢሆንም ለእምነት ክፍት ነው። ይሖዋ በዚህ ተስፋ ሁለት ጊዜ እንደሚለው «አደርጋለሁ» ሲል ልንጠራጠር አንደፍርም።

ሜይ 21

ያለ ደመና ዝናብ? ፈጽሞ!

«ደመናት ዝናብ ቢሞሉ በምድር ላይ ያፈስሳሉ» መክብብ 11:3

ታዲያ አሁን ሰማያችንን የሚያጨልሙትን ደመናት ለምን እንፈራለን? እውነት ነው፥ ለጊዜው ፀሐይን ይሰውራሉ፤ ፀሐይ ግን አልጠፋችም፤ በቅርቡ እንደ ገና ትበራለች። እስከዚያው እነዚያ ጥቍር ደመናት በዝናብ ተሞልተዋል፤ ይበልጥ በጠቈሩ መጠን የተትረፈረፈ ዝናብ የማዝነባቸው ዕድል ይበልጣል። ያለ ደመና እንዴት ዝናብ ልናገኝ እንችላለን?

መከራዎቻችን ሁልጊዜ በረከት አምጥተውልናል፥ ወደፊትም ያመጡልናል። እነርሱ የብሩህ ጸጋ ጨለማ ሰረገሎች ናቸው። እነዚህ ደመናት በቅርቡ ይፈስሳሉ፥ ልምላሜም ሁሉ በዝናቡ ደስ ይለዋል። አምላካችን በኀዘን ሊያርሰን ይችላል፥ በቍጣ ግን አያሰጥመንም፤ ይልቁንም በምሕረት ያበረታናል። የጌታችን የፍቅር ደብዳቤዎች ብዙ ጊዜ ጥቍር ጠርዝ ባላቸው ፖስታዎች ይመጡልናል። ሰረገሎቹ ይንጓጓሉ፥ ነገር ግን በበረከት የተጫኑ ናቸው። በትሩ በጣፋጭ አበቦችና በሚመግቡ ፍሬዎች ታብባለች። ስለ ደመናት አንጨነቅ፤ ይልቁንም የሜይ አበቦች በኤፕሪል ደመናትና ዝናብ ስለሚመጡልን እንዘምር።

ጌታ ሆይ፥ ደመናት የእግርህ ትቢያ ናቸው! በደመናማውና በጨለማው ቀን ምንኛ ቅርብ ነህ! ፍቅር ያይሃል፥ ደስም ይለዋል። እምነት ደመናት ራሳቸውን ባዶ ሲያደርጉና ትናንሾቹን ኮረብቶች በየአቅጣጫው ደስ ሲያሰኙ ያያል።

ሜይ 22

የመታመን መዝሙር

«በመከራ መካከል ብሄድ አንተ ሕያው ታደርገኛለህ፤ በጠላቶቼ ቍጣ ላይ እጅህን ትዘረጋለህ፥ ቀኝህም ታድነኛለች» መዝሙር 138:7

በመከራ መካከል መሄድ ምንኛ ጐስቋላ ነው! አይደለም፤ ልዩ ተስፋ ስለ ተሰጠው የተባረከ መሄድ ነው። ተስፋን ስጠኝ፥ መከራውስ ምንድር ነው? ጌታዬ በዚህ ስፍራ ምን እንድል ያስተምረኛል? ይህንኑ ነው፤ «አንተ ሕያው ታደርገኛለህ።» የበለጠ ሕይወት፥ የበለጠ ብርታት፥ የበለጠ እምነት ይኖረኛል። ሰው ሊዝል ሲል እንደሚነፍስበት ቀዝቃዛ አየር፥ መከራ ብዙ ጊዜ ሕያው የሚያደርገን አይደለምን?

ጠላቶቼ፥ በተለይም ዋናው ጠላት፥ ምንኛ ተቈጥተዋል! እጄን ዘርግቼ ባላጋራዎቼን ልዋጋን? አይደለም፤ እጄ ለጌታዬ አገልግሎት ብትሠራ ይሻላታል። ደግሞም አያስፈልግም፤ አምላኬ ሩቅ የምትደርሰውን ክንዱን ይጠቀማልና፥ እኔም ብሞክር ከምችለው እጅግ በተሻለ ሁኔታ እርሱ ያስተናግዳቸዋል። «በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ።» እርሱ በኃይሉና በጥበቡ ቀኝ እጅ ያድነኛል፤ ከዚህ በላይ ምን እመኛለሁ?

ልቤ ሆይ፥ ና፤ ይህን ተስፋ የመታመንህ መዝሙር፥ የብቸኝነትህም መጽናኛ አድርገህ እስክትጠቀምበት ድረስ ከራስህ ጋር ተነጋገርበት። አንተ ራስህ ሕያው እንድትሆን ጸልይ፥ የቀረውንም ሁሉ ለአንተ ሁሉን ለሚፈጽም ለጌታ ተውለት።

ሜይ 23

በእግዚአብሔር ላይ ፍጹም መደገፍ

«ችግረኛውን ሲጮኽ፥ ረዳት የሌለውንም ድሀ ያድናልና» መዝሙር 72:12

ችግረኛው ይጮኻል፤ ሌላ ምን ማድረግ ይችላል? ጩኸቱን እግዚአብሔር ይሰማዋል፤ ሌላ ምን ማድረግ ያስፈልገዋል? ችግረኛ የሆነው አንባቢ ወዲያውኑ መጮኽ ይጀምር፤ ጥበቡ ይህ ነውና። በወዳጆች ጆሮ አትጩኽ፤ ሊረዱህ ቢችሉ እንኳ ይህ የሆነው ጌታ ስላስቻላቸው ብቻ ነው። ከሁሉ የቀረበው መንገድ በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር መሄድና ጩኸትህ በፊቱ እንዲደርስ ማድረግ ነው። ቀጥ ብሎ የሚሮጥ ከሁሉ የተሻለ ሯጭ ነው፤ ወደ ሁለተኛ ምክንያቶች ሳይሆን ወደ ጌታ ሩጥ።

«ወዮ!» ትላለህ፤ «ወዳጅም ረዳትም የለኝም።» እንዲያውስ ይሻላል፤ በሁለቱም ረገድ — ስንቅ እንደሌለው፥ ረዳትም እንደሌለው — በእግዚአብሔር ልትደገፍ ትችላለህ። ድርብ ችግርህን ድርብ ልመናህ አድርገው። ለዚህ ዓለም ምሕረቶች እንኳ እግዚአብሔርን ልትጠብቅ ትችላለህ፤ በእነዚህ ጊዜያዊ ጉዳዮች ለልጆቹ ያስባልና። ከሁሉ የሚከብዱትን መንፈሳዊ ችግሮች በተመለከተ ደግሞ ጌታ ጩኸትህን ይሰማል፥ ያድንሃል፥ የሚያስፈልግህንም ያሟላልሃል።

አንተ ድሀ ወዳጅ ሆይ፥ ባለጠጋውን አምላክህን ሞክረው። አንተ ረዳት የሌለህ ሆይ፥ በእርዳታው ተደገፍ። እርሱ ከቶ አልጣለኝም፥ አንተንም ከቶ እንደማይጥልህ እርግጠኛ ነኝ። እንደ ለማኝ ና፥ እግዚአብሔርም እርዳታን አይከለክልህም። ከጸጋው በቀር ሌላ ልመና ሳትይዝ ና። ኢየሱስ ንጉሥ ነው፤ በችግር እንድትጠፋ ይተውሃልን? ምን! ይህን ረስተኸው ነበርን?

ሜይ 24

አንድ ሰው ብዙኃን ነው!

«አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራችሁ ስለ እናንተ የሚዋጋ እርሱ ነውና ከእናንተ አንዱ ሰው ሺህ ያሳድዳል» ኢያሱ 23:10

ራስ ለምን ትቈጥራለህ? ከእግዚአብሔር ጋር ያለ አንድ ሰው በሌላው ወገን ሺህ ቢሆኑም እንኳ ብዙኃን ነው። አንዳንድ ጊዜ ረዳቶቻችን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንዲሠራ እጅግ ይበዛሉ፤ የጌዴዎን ሁኔታ እንዲሁ ነበር፤ ሠራዊቱን በማሳነስ እስኪያበዛው ድረስ ምንም ማድረግ አልቻለም። የጌታ ሠራዊት ግን ከቶ አያንስም። እግዚአብሔር ሕዝብን ሊመሠርት በወደደ ጊዜ አብራምን ብቻውን ጠርቶ ባረከው። ትዕቢተኛውን ፈርዖንን ሊያሸንፍ በወደደ ጊዜ ሠራዊትን አልተጠቀመም፥ ሙሴንና አሮንን ብቻ እንጂ። አንዳንድ ጥበበኞች እንደሚሉት «የአንድ ሰው አገልግሎት» ከሠለጠኑ ጭፍሮችና ከአለቆቻቸው ይልቅ በጌታ እጅግ በበለጠ ጥቅም ላይ ውሏል። እስራኤላውያን ሁሉ በአንድነት ሶምሶን ብቻውን የገደለውን ያህል ገድለዋልን? ሳኦልና ሠራዊቱ ሺዎቻቸውን ገደሉ፥ ዳዊት ግን አሥር ሺዎቹን።

ጌታ ለጠላት ብዙ ብልጫ ሰጥቶም ሊያሸንፈው ይችላል። እምነት ካለን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤ ታዲያ የሰዎች ብዛት ምንድር ነው? አንድ የእረኛ ውሻ ታላቅ የበጎች መንጋን በፊቱ መንዳት ይችላል። ወንድሜ ሆይ፥ ጌታ ልኮህ ከሆነ ኃይሉ መለኮታዊ ዓላማውን ይፈጽማል። ስለዚህ በተስፋው ተደገፍ፥ እጅግም በርታ።

ሜይ 25

የእግዚአብሔር ግምጃ ቤት

«እግዚአብሔር መልካሙን መዝገቡን ይከፍትልሃል» ዘዳግም 28:12

ይህ በመጀመሪያ የሚያመለክተው ዝናብን ነው። ጌታ በወቅቱ ይሰጠዋል። ዝናብ ጌታ ለሕዝቡ ሊሰጣቸው የተዘጋጀውን የሰማያዊ መታደስ ሁሉ ምልክት ነው። የጌታን ርስት የሚያድስ የበዛ ዝናብ ምነው በወረደ!

የእግዚአብሔር ግምጃ ቤት ሊከፈት የሚችለው እንደ ኤልያስ ባለ ታላቅ ነቢይ ብቻ እንደሆነ የምናስብ እንመስላለን፤ ነገር ግን እንዲህ አይደለም፤ ይህ ተስፋ በእስራኤል ላሉ ታማኞች ሁሉ፥ እንዲያውም ለእያንዳንዳቸው ነውና። አንተ የምታምን ወዳጅ ሆይ፥ «እግዚአብሔር መልካሙን መዝገቡን ይከፍትልሃል።» አንተም ሰማይ ተከፍቶ ልታይ፥ እጅህንም አስገብተህ ድርሻህን ልታወጣ፥ አዎን፥ በዙሪያህ ላሉ ወንድሞችህ ሁሉም ድርሻን ልታወጣ ትችላለህ። በክርስቶስ ብትኖር ቃሎቹም በአንተ ቢኖሩ የምትወደውን ለምን፥ አትከለከልም።

የጌታህን መዝገቦች ሁሉ ገና አላወቅህም፤ እርሱ ግን ለማስተዋልህ ይከፍትልሃል። የኪዳኑን ባለጠግነት ሙላት ገና እንዳልተደሰትህበት የተረጋገጠ ነው፤ እርሱ ግን ልብህን ወደ ፍቅሩ ይመራል፥ ኢየሱስንም በአንተ ይገልጣል። ይህን ለአንተ ሊያደርግ የሚችል ጌታ ራሱ ብቻ ነው፤ ነገር ግን ተስፋው ይኸውልህ፤ ድምፁን በትጋት ብትሰማ ፈቃዱንም ብትታዘዝ፥ በክብር ያለው ባለጠግነቱ በክርስቶስ ኢየሱስ የአንተ ይሆናል።

ሜይ 26

ተራ ነገሮች ተባረኩ

«አምላካችሁን እግዚአብሔርን ታመልካላችሁ፥ እርሱም እንጀራህንና ውኃህን ይባርካል» ዘጸአት 23:25

ይህ እንዴት ያለ ተስፋ ነው! እግዚአብሔርን ማገልገል በራሱ ታላቅ ደስታ ነው። ነገር ግን የጌታ በረከት በነገር ሁሉ በእኛ ላይ ማረፉ እንዴት ያለ ተጨማሪ መብት ነው! እኛ ራሳችን ለጌታ በተቀደስን ጊዜ ተራ ነገሮቻችን የተባረኩ ይሆናሉ። ጌታችን ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ እነሆ፥ እኛም የተባረከውን እንጀራ እንበላለን። ኢየሱስ ውኃን ባርኮ የወይን ጠጅ አደረገው፤ የምንጠጣው ውኃ ሰዎች ደስ ከሚሰኙበት ከማንኛውም የወይን ጠጅ ይልቅ ለእኛ እጅግ ይሻለናል፤ እያንዳንዱ ጠብታ በረከትን ይዟል። መለኮታዊው በረከት በእግዚአብሔር ሰው ላይ በነገር ሁሉ ነው፥ በዘመኑም ሁሉ ከእርሱ ጋር ይኖራል።

እንጀራና ውኃ ብቻ ቢኖረንስ! ቢሆንም የተባረከ እንጀራና ውኃ ነው። እንጀራና ውኃ ይኖረናል። ይህ በውስጡ ተገልጧል፤ እግዚአብሔር እንዲባርከው በዚያ መኖር አለበትና። «እንጀራህ ይሰጥሃል፥ ውኃህም የታመነ ይሆናል።» እግዚአብሔር በማዕዳችን ሳለ በረከትን የምንለምን ብቻ ሳንሆን በረከትም አለን። የሚባርከን በመሠዊያው ብቻ ሳይሆን በማዕዱም ነው። በመልካም የሚያገለግሉትን እርሱ በመልካም ያገለግላቸዋል። ይህ የማዕድ በረከት ከጸጋ እንጂ ከዕዳ አይደለም። በእርግጥም ሦስት እጥፍ ጸጋ አለ፤ እርሱን እንድናገለግል ጸጋን ይሰጠናል፥ በጸጋው እንጀራን ይመግበናል፥ ከዚያም በጸጋው ይባርከዋል።

ሜይ 27

ሕይወቱ እንደ ሆነ — ፍሬውም እንዲሁ

«እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና» 2ኛ ጴጥሮስ 1:8

ጌታችንን በፍሬያማነት ልናከብረው ብንወድ አንዳንድ ነገሮች በውስጣችን ሊኖሩ ይገባቸዋል፤ አስቀድሞ በውስጣችን ያልነበረ ነገር ከእኛ ሊወጣ አይችልምና። የበጎነት ሁሉ መሠረት በሆነው በእምነት መጀመር አለብን፤ ከዚያም በትጋት በጎነትን፥ እውቀትን፥ ራስን መግዛትንና ትዕግሥትን ልንጨምርበት ይገባናል። ከእነዚህም ጋር እግዚአብሔርን መምሰልና የወንድማማች መዋደድ ሊኖረን ይገባል። እነዚህ ሁሉ በአንድነት ሲሆኑ የሕይወታችን ፍሬ አድርገን የጠቃሚነትን ዘለላዎች እንድናፈራ በእርግጥ ያደርጉናል፤ ሥራ ፈት አዋቂዎች ብቻ ሳንሆን እውነተኛ የቃሉ አድራጊዎች እንሆናለን። እነዚህ ቅዱሳን ነገሮች በእኛ መኖር ብቻ ሳይሆን መብዛትም አለባቸው፤ አለዚያ ፍሬ ቢሶች እንሆናለን። ፍሬ ከሕይወት ሞልቶ የሚፈስስ ነው፤ ሞልተን ሳንፈስስ በፊት መሙላት አለብን።

ብዙ ችሎታና ዕድል የነበራቸው ሆነው ሳለ ነፍሳትን በመመለስ እውነተኛ መልካም ነገርን ለማድረግ ያልተሳካላቸውን ሰዎች ተመልክተናል፤ በጥንቃቄም ከተከታተልን በኋላ ፍሬ ለማፍራት ፈጽሞ አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ጸጋዎች እንደጐደሏቸው ደመደምን። ለእውነተኛ ጠቃሚነት ጸጋዎች ከስጦታዎች ይሻላሉ። ሰውዬው እንደ ሆነ ሥራውም እንዲሁ ነው። የተሻለ ልንሠራ ብንወድ የተሻልን መሆን አለብን። ይህ ጥቅስ ፍሬ ለሌላቸው አማኞች ነን ባዮች፥ ለእኔም ደግሞ፥ የለዘበ ማሳሰቢያ ይሁን።

ሜይ 28

እግዚአብሔርን ተስፋውን አሳስበው

«አንተም፦ በእውነት መልካም አደርግልሃለሁ ብለህ ነበር» ዘፍጥረት 32:12

ይህ በጸሎት ጌታን የምናሸንፍበት እርግጠኛ መንገድ ነው። የተናገረውን በትሕትና ልናሳስበው እንችላለን። ታማኙ አምላካችን ከቃሉ ከቶ ወደ ኋላ አይመለስም፥ ሳይፈጸምም አይተወውም፤ ቢሆንም ሕዝቡ እንዲጠይቁትና ተስፋውን እንዲያሳስቡት ይወዳል። ይህ ትዝታቸውን ያድሳል፥ እምነታቸውን ሕያው ያደርጋል፥ ተስፋቸውንም ያለመልማል። የእግዚአብሔር ቃል የተሰጠው ለእኛ ስንል እንጂ ለእርሱ ብሎ አይደለም። ዓላማዎቹ የጸኑ ናቸው፤ ሕዝቡን መልካም የማድረግ ሐሳቡን የሚያስረው ምንም አያስፈልገውም፤ ነገር ግን ተስፋውን የሚሰጠው ለብርታታችንና ለመጽናናታችን ነው። ስለዚህ ተስፋውን አቅርበን «አንተ ብለሃል» እንድንለው ይወዳል።

«በእውነት መልካም አደርግልሃለሁ» የሚለው የጌታ የጸጋ ቃላት ሁሉ ዋና ፍሬ ነገር ነው። «በእውነት» በሚለው ቃል ላይ ልዩ ትኩረት አድርግ። መልካም ያደርግልናል፤ እውነተኛ መልካም፥ ዘላቂ መልካም፥ መልካም ብቻ፥ መልካም ሁሉ። እርሱ መልካሞች ያደርገናል፥ ይህም ከሁሉ በላቀ ደረጃ መልካም ማድረግ ነው። እዚህ ሳለን ቅዱሳኑን እንደሚያደርግላቸው ያደርግልናል፥ ይህም መልካም ነው። ብዙም ሳይቆይ ከኢየሱስና ከተመረጡቹ ሁሉ ጋር እንድንሆን ይወስደናል፥ ይህም እጅግ የላቀ መልካም ነው። ይህ ተስፋ በልባችን ሳለ የተቈጣውን ዔሳውን ወይም ሌላ ማንንም መፍራት አያስፈልገንም። ጌታ መልካም የሚያደርግልን ከሆነ ማን ሊጐዳን ይችላል?

ሜይ 29

አጥማጆች እርሱን ይከተላሉ

«ኢየሱስም። በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው» ማርቆስ 1:17

ኢየሱስን በመከተል ብቻ የልባችንን ምኞት ልናገኝና ለወገኖቻችን በእውነት ጠቃሚዎች ልንሆን እንችላለን። ኦ፥ ለኢየሱስ የተሳካልን አጥማጆች ለመሆን ምንኛ እንናፍቃለን! ነፍሳትን ለመማረክ ሕይወታችንን እንሠዋለን። ነገር ግን ኢየሱስ ከቶ ያልሞከራቸውን ዘዴዎች ለመሞከር እንፈተናለን። ለዚህ የጠላት ምክር እንሸነፍን? እንዲህ ብናደርግ ውኃውን እናናውጥ ይሆናል፥ ዓሣውን ግን ከቶ አንይዝም። እንዲሳካልን ብንወድ ኢየሱስን መከተል አለብን። ስሜት ቀስቃሽ ዘዴዎች፥ መዝናኛዎችና የመሳሰሉት — እነዚህ ኢየሱስን መከተል ናቸውን? ጌታ ኢየሱስ ዛሬ በብዛት በሚሠራባቸው በእንደዚህ ያሉ መንገዶች ጉባኤን ሲሰበስብ ልናስበው እንችላለንን? የእንደዚህ ያሉ ብልሃቶች ውጤት ምንድር ነው? ውጤቱ ኢየሱስ በመጨረሻው ታላቅ ቀን የሚቈጥረው አንዳች ነገር አይደለም።

ጌታችን እንዳደረገው ስብከታችንን አጥብቀን መያዝ አለብን፤ በዚህ መንገድ ነፍሳት ይድናሉና። የጌታችንን ትምህርት ልንሰብክ፥ ሙሉና ነጻ ወንጌልንም ልናውጅ ይገባናል፤ ነፍሳት የሚያዙበት መረብ ይህ ነውና። በየዋህነቱ፥ በድፍረቱና በፍቅሩ ልንሰብክ ይገባናል፤ የሰውን ልብ የማሸነፍ ምሥጢር ይህ ነውና። በመለኮታዊ ቅብዓት ሥር፥ በቅዱሱ መንፈስ ተደግፈን መሥራት አለብን። እንዲህ ኢየሱስን በመከተል፥ ከፊቱ ሳንሮጥ ከእርሱም ፈቀቅ ሳንል፥ ሰዎችን አጥማጆች እንሆናለን።

ሜይ 30

ቅዱስ አርቆ ማየት

«ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ» ማቴዎስ 26:64

አቤቱ፥ በአሳዳጆችህ ፊት እንደ ወንጀለኛ እንድትቆም በተደረግህ ጊዜ በዝቅተኛው ሁኔታህ ነበርህ! ቢሆንም የእምነትህ ዓይኖች ከአሁኑ ውርደትህ አልፈው የወደፊቱን ክብርህን ማየት ቻሉ። «ነገር ግን — ከእንግዲህ ወዲህ» የሚሉት እነዚህ ቃላት እንዴት ያሉ ናቸው! ቅዱሱን አርቆ ማየትህን ልመስል እወዳለሁ፤ በድህነትም ቢሆን፥ በሕመምም ቢሆን፥ በስም ማጥፋትም መካከል እኔም «ነገር ግን — ከእንግዲህ ወዲህ» ማለት እወዳለሁ። በድካም ፋንታ ኃይል ሁሉ አለህ፤ በውርደት ፋንታ ክብር ሁሉ፤ በፌዝ ፋንታ ስግደት ሁሉ። መስቀልህ የዘውድህን ግርማ አላደበዘዘውም፥ ምራቁም የፊትህን ውበት አላበላሸውም። ይልቁንም በመከራህ ምክንያት የበለጠ ከፍ ከፍ ያልህና የከበርህ ነህ በል።

ስለዚህ ጌታ ሆይ፥ እኔም ከ«ከእንግዲህ ወዲህ» ብርታትን ልወስድ እወዳለሁ። የአሁኑን መከራ በወደፊቱ ድል ልረሳው እወዳለሁ። ስለ ስምህ በተዘበተብኝ ጊዜ እንዳልናወጥ፥ ይልቁንም ስለ ከእንግዲህ ወዲህ ይበልጥ እያሰብሁ ስለ ዛሬ ያነሰ እንዳስብ፥ ወደ አባትህ ፍቅርና ወደ ራስህ ትዕግሥት በመምራት እርዳኝ። በቅርቡ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ክብርህንም አያለሁ። ስለዚህ አላፍርም፥ ነገር ግን በውስጠኛው ነፍሴ «ነገር ግን — ከእንግዲህ ወዲህ» እላለሁ።

ሜይ 31

«አይዞአችሁ»

«በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ» ዮሐንስ 16:33

የጌታዬ ቃላት ስለ መከራ እውነት ናቸው። ከዚህ ድርሻዬን ያለ ጥርጥር አግኝቻለሁ። መውቂያው ከመንገድ ተነሥቶ አልተሰቀለም፤ በአውድማው ላይ እስከ ተኛሁ ድረስ ይቀመጣል ብዬም ተስፋ ማድረግ አልችልም። በጠላት አገር እንደ ቤቴ ልሆን፥ በስደት ሳለሁ ደስተኛ ልሆን፥ ወይም በምድረ በዳ ልመቸኝ እንዴት እጠብቃለሁ? ይህ ዕረፍቴ አይደለም። ይህ የእቶን፥ የወናፍና የመዶሻ ስፍራ ነው። ተሞክሮዬ ከጌታዬ ቃላት ጋር ይስማማል።

«አይዞህ» እንዳለኝ አስተውላለሁ። ወዮ! እኔ ለመተከዝ እጅግ ፈጣን ነኝ። በብርቱ ስፈተን መንፈሴ ቶሎ ይዝላል። ነገር ግን ለዚህ ስሜት እጄን መስጠት የለብኝም። ጌታዬ አይዞህ ሲለኝ ለመተከዝ መድፈር የለብኝም።

እኔን ለማበረታታት የሚጠቀምበት ምክንያት ምንድር ነው? እንግዲህ የገዛ ራሱ ድል ነው። «እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ» ይላል። የእርሱ ውጊያ ከእኔ እጅግ የከበደ ነበር። እኔ ገና እስከ ደም ድረስ አልተቃወምሁም። ለማሸነፍ ለምን ተስፋ እቈርጣለሁ? ነፍሴ ሆይ፥ እይ፤ ጠላት አንድ ጊዜ ተሸንፎአል። የምዋጋው ከተሸነፈ ጠላት ጋር ነው። ዓለም ሆይ፥ ኢየሱስ አስቀድሞ አሸንፎሃል፤ በእኔም ውስጥ በጸጋው እንደገና ያሸንፍሃል። ስለዚህ ልቤ ተጽናንቶአል፥ ለአሸናፊው ጌታዬም እዘምራለሁ።

ቀዳሚ ቀጣይ