በጠባቧ በር አጠገብ
ያለ እምነት መዳን የለም

ምዕራፍ 10 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

ያለ እምነት መዳን የለም

አንዳንዶች በኢየሱስ ክርስቶስ ለማመን እምቢ ቢሉ ከጥፋት በቀር ሌላ ነገር የማይጠብቃቸው መሆኑ ከባድ ነገር ይመስላቸዋል፤ ነገር ግን ለአንዲት ደቂቃ ብታስብ ይህ ትክክልና ምክንያታዊ እንደ ሆነ ታያለህ። ሰው ብርታቱን የሚጠብቅበት ከመብላት በቀር ሌላ መንገድ የለም ብዬ አስባለሁ። «ከእንግዲህ አልበላም፤ እንዲህ ያለውን የእንስሳነት ጠባይ እንቃለሁ» ብትል፣ ወደ ማዴይራ ልትሄድ ወይም በአገሮች ሁሉ ልትዞር ትችላለህ (ይህን ለማድረግ በሕይወት ከቆየህ!)፤ ነገር ግን ምግብን እምቢ ካልህ የትኛውም የአየር ጠባይ ወይም የትኛውም የአካል እንቅስቃሴ በሕይወት ሊያኖርህ እንደማይችል በእርግጥ ታገኘዋለህ። ታዲያ፦ «በመብላት ስለማላምን መሞቴ ከባድ ነገር ነው» ብለህ ታማርራለህን? ሳትበላ እስክትቀር ድረስ ሞኝ ብትሆን መሞትህ ግፍ አይደለም። ማመንም ልክ እንዲሁ ነው። «እመን፣ ትድናለህም።» ባታምን ግን መጥፋትህ ከባድ ነገር አይደለም። ይህ ባይሆን ኖሮ በእርግጥ እንግዳ ነገር በሆነ ነበር።

የተጠማ ሰው በምንጭ ፊት ቆሟል። እርሱም፦ «አይሆንም፤ በሕይወት እስካለሁ ድረስ አንዲት የውኃ ጠብታ አልነካም። ጥሜን በራሴ መንገድ ማርካት አልችልምን?» ይላል። አንችልም፤ መጠጣት አለዚያም መሞት አለበት ብለን እንነግረዋለን። እርሱም፦ «ከቶ አልጠጣም፤ ነገር ግን በዚህ ምክንያት መሞቴ ከባድ ነገር ነው። ይህን መንገር ጭፍን አክራሪነትና ጭካኔ ነው» ይላል። ተሳስቷል። ጥሙ የተፈጥሮን ሕግ ቸል የማለቱ የማይቀር ውጤት ነው። አንተም እንዲሁ ማመን አለዚያም መሞት አለብህ፤ ታዲያ ትእዛዙን ለመታዘዝ ለምን እምቢ ትላለህ? ሰው ሆይ፣ ጠጣ፣ ጠጣ! ክርስቶስን ተቀበልና በሕይወት ኑር። የመዳን መንገድ ይኸው ነው፤ በእርሱም ለመግባት በክርስቶስ መታመን አለብህ፤ በአዳኙ ባትታመን መጥፋትህ ግን ምንም ከባድ ነገር የለበትም። እነሆ፣ አንድ ሰው በባሕር ላይ ነው፤ የባሕር ካርታ አለው፤ ያም ካርታ በሚገባ ቢጠናና በኮምፓስ እርዳታ ቢታገዝ እስከ ጉዞው ፍጻሜ ይመራዋል። የሰሜን ኮከብ በደመናው ስንጥቆች መካከል ያበራል፤ እርሱም ደግሞ ይረዳዋል። እርሱ ግን፦ «አይሆንም፤ ከከዋክብታችሁ ጋር ምንም ጉዳይ የለኝም፤ በሰሜን ዋልታ አላምንም። በሳጥኑ ውስጥ ላለችው ለዚያች ትንሽ ነገር ግድ የለኝም፤ አንዱ መርፌ እንደ ሌላው መርፌ ነው። በካርታችሁ ምንም እምነት የለኝም፤ ከእርሱም ጋር ምንም ጉዳይ አይኖረኝም። የመርከብ መንዳት ጥበብ ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት ብለው ሆን ብለው ያዘጋጁት ከንቱ ነገር ብቻ ነው፤ እኔም በእርሱ አልታለልም» ይላል። ሰውየው ከቶ ወደብ አይደርስም፤ እርሱም ይህ እጅግ ከባድ ነገር ነው—እጅግ ከባድ ነገር ነው ይላል። እኔ ግን እንዲህ አላስብም። ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ፦ «መጽሐፍ ቅዱስን አላነብም፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምትናገረውንም አልሰማም፤ በእንዲህ ያሉ ነገሮች አላምንም» ትላላችሁ። ያን ጊዜ ኢየሱስ፦ «ያላመነ ግን ይፈረድበታል» ይላል። አንተም፦ «ይህ እጅግ ከባድ ነው» ትላለህ። ነገር ግን እንዲህ አይደለም። ኮምፓሱንና የሰሜን ኮከብን ብትጥል ወደብህ አለመድረስህ ከሚከብደው አይበልጥም። ሌላ መፍትሔ የለውም፤ እንዲህ መሆኑ የግድ ነው።

ከኢየሱስና ከደሙ ጋር ምንም ጉዳይ እንደማይኖርህ ትናገራለህ፤ ሃይማኖትንም ሁሉ በንቀት ታጣጥላለህ። ለመሞት በምትቃረብበት ጊዜ፣ የሚያጣብቅ ላብ ከግንባርህ መጠረግ ሲያስፈልግ፣ ልብህም ዘሎ ወጥቶ ከእግዚአብሔር ፊት ሊበር የፈለገ ይመስል የጎድን አጥንቶችህን ሲደበድብ፣ በእነዚህ ነገሮች ላይ ስቆ ማለፍ ከባድ ሆኖ ታገኘዋለህ። ነፍስ ሆይ! ያን ጊዜ እነዚያ እሑዶች፣ እነዚያ የአምልኮ ሥርዓቶች፣ ይህም አሮጌ መጽሐፍ ካሰብኸው በላይና የተሻሉ እንደ ሆኑ ታገኛለህ፤ ለመዳን የሚረዳህን እውነተኛ እርዳታ ቸል እስክትል ድረስ እንዲህ የዋህ በመሆንህም ትደነቃለህ። ከሁሉም በላይ መርከበኛውን ወደ ዕረፍት ወደብ ብቻውን ሊመራ የሚችለውን ያንን የሰሜን ኮከብ፣ ክርስቶስን፣ ቸል ማለት ምንኛ ወዮታ ይሆናል!

የምትኖረው የት ነው?

ምናልባት የምትኖረው በወንዙ ማዶ ይሆናል፤ ወደ ቤትህ ከመድረስህም በፊት ድልድይ መሻገር አለብህ። በድልድይ፣ በጀልባ፣ ወይም ውኃ የሚባል ነገር መኖሩን አላምንም የሚለውን አሳብ እስክትንከባከብ ድረስ ሞኝ ሆነሃል። «በየትኛውም ድልድያችሁ ላይ አልሻገርም፤ ወደ የትኛውም ጀልባችሁም አልገባም። ወንዝ መኖሩን፣ ወይም ውኃ የሚባል ነገር መኖሩን አላምንም» ትላለህ። ወደ ቤትህ እየሄድህ ነው፤ ብዙም ሳትቆይ ወደ አሮጌው ድልድይ ትደርሳለህ፤ ነገር ግን አትሻገረውም። በዚያ ጀልባ አለች፤ አንተ ግን ወደ እርስዋ ላለመግባት ቈርጠሃል። ወንዙ ይኸው አለ፤ አንተም በተለመደው መንገድ ላለመሻገር ወስነሃል፤ ሆኖም ወደ ቤትህ መድረስ አለመቻልህ እጅግ ከባድ ነገር እንደ ሆነ ታስባለህ። በእርግጥ አንድ ነገር የማመዛዘን ችሎታህን አጥፍቶታል፤ በአእምሮህ ብትሆን ኖሮ ይህን እንዲህ ከባድ አድርገህ አታስበውም ነበር። ሰው ለአንድ ግብ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ካላደረገ ያንን ግብ እንዴት ሊደርስበት ይጠብቃል? መርዝ ጠጥተሃል፤ ሐኪሙም ማርከሻ አምጥቶ፦ «ቶሎ ውሰደው፤ አለዚያ ትሞታለህ፤ ቶሎ ብትወስደው ግን መርዙ እንደሚከሽፍ ዋስትና እሰጥሃለሁ» ይላል። አንተ ግን፦ «አይሆንም፣ ሐኪም ሆይ፣ በማርከሻ አላምንም። ሁሉም ነገር በራሱ መንገድ ይሂድ፤ እያንዳንዱ በራሱ ይቁም፤ ከመድኃኒትህ ጋር ምንም ጉዳይ አይኖረኝም። ደግሞም ለጠጣሁት መርዝ ምንም መድኃኒት እንዳለ አላምንም፤ ከዚህም በላይ መድኃኒት ቢኖርም ባይኖርም ግድ የለኝም» ትላለህ።

እንግዲህ ጌታዬ፣ ትሞታለህ፤ የሞትህን ምክንያት የሚመረምረው ችሎት በሬሳህ ላይ በተቀመጠ ጊዜም ውሳኔው፦ «የሚገባውን አገኘ!» የሚል ይሆናል። የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ከሰማህ በኋላ፦ «እኔ እጅግ የገፋሁ ሰው ስለ ሆንሁ ከዚያ ኋላቀር የሆነ የመተካት አሳብ ጋር ምንም ጉዳይ አይኖረኝም። ሰባኪው ስለ መሥዋዕትና ስለ ደም መፍሰስ የሚናገረውን ግድ አልሰጠውም» ብትል፣ በአንተም ላይ እንዲሁ ይሆናል። ያን ጊዜ ስትጠፋ፣ በመጨረሻ በንጉሡ ችሎት ላይ የሚቀመጠው ሕሊናህ የሚሰጠው ውሳኔ እንዲህ ይላል፦ «ራሱን ገደለ፤ የገዛ ነፍሱን አጠፋ»። አሮጌው መጽሐፍም እንዲሁ ይላል፦ «እስራኤል ሆይ፣ ራስህን አጥፍተሃል!» አንባቢ ሆይ፣ እንዲህ እንዳታደርግ እለምንሃለሁ።


ምዕራፍ 10 ተጠናቋል

ያለ እምነት መዳን የለም

ገጽ 1 / 1 · 3 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ