አማንዳ ስሚዝ፦ የሕይወት ታሪክ
የመቀደስ በረከት

ምዕራፍ 9 · 27 ደቂቃ ንባብ · 35 ደቂቃ ማዳመጥ

የመቀደስ በረከት

እሑድ ጠዋት ልክ እንደ ሌሎቹ ቀናት ሁሉ ማልጄ እነሣ ነበር። ቁርሴን በልቼ ቤቴን አጸዳሁ፤ ጠዋት በሦስት ሰዓት ትንሿ ሜዚ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት ሄደች። እርሷ እስክትመለስ ድረስ የምሳዬን ምግብ ሁሉ አብስዬ ሁሉን ነገር አዘጋጅ ነበር። በሳምንቱ ውስጥ ብዙ ለማብሰል ጊዜ አልነበረኝም፤ ብዙ ጊዜ ልብሶቹን በቤት ውስጥ ማድረቅ ነበረብኝ፣ የምግብ ሽታም እንዲኖር አልችልም ነበርና። ስለዚህ በእውነት ጥሩ ምሳ የምበላው እሑድ ብቻ ነበር፤ ነገር ግን ምግብ ለማብሰል ብዬ ከቤተ ክርስቲያን ቀርቼ አላውቅም። ስለዚህ ሕፃኔን አጥቤ በአልጋው አስተኛሁት፤ ከዚያም ተንበርክኬ ወደ ግሪን ስትሪት ቤተ ክርስቲያን ሄጄ እስክመለስ ጌታ ዊልን እንዲያስተኛልኝ፣ ጄምስንም እንዳይገሥጸኝ በጥሩ ስሜት እንዲያቆይልኝ ጸለይሁ፤ መገሠጽን እጅግ አድርጌ እጠላው ነበርና። ጄምስ እንግዳ ጠባይ ነበረው። ሲመጣ እኔ በአጋጣሚ ከቤት ወጥቼ ብገኝ፣ ልብስ ለማድረስ ሄጄ ቢሆን እንኳ ይናደድ ነበር። ስለዚህ ሜዚ ስትመጣ፦ «አሁን የቤተ መጻሕፍት መጽሐፍሽን አንብቢ፤ ጥሩ ልጅም ሁኚ፤ ዛሬ ጠዋት ወደ ግሪን ስትሪት ቤተ ክርስቲያን እሄዳለሁ፤ እዚያ ከእኛ ቤተ ክርስቲያን አስቀድሞ ይበተናሉና በጊዜ ቤት እደርሳለሁ። እኔ ሳልመለስ አባትሽ ቢመጣ ልትነግሪው ትችያለሽ። ዊል ቢያለቅስ አትሸከሚው፤ ዝም ብለሽ አልጋውን አወዛውዢው» አልኋት።

እርሷ ጠንካራ ጥሩ ልጅ ነበረች፤ ዕድሜዋ አሥራ ሦስት ዓመት ነበር፤ እርሱን ለመጠበቅ በሚገባ ትችል ነበር፤ እንደ እኔም አድርጋ ልትይዘው ትችል ነበር፤ ስለዚህ ትቻቸው ሄድሁ። ወደ ግሪን ስትሪት ስሄድ ዲያብሎስ የደረሰብኝ መሰለኝ። ልክ ወደ ካርማይን ስትሪት ስታጠፍ አንድ ሰይጣናዊ ኃይል ከጎኔ እየሄደ፦ «እንግዲህ ታውቂያለሽ፣ ጄምስ ወደ ቤት መጥቶ ወጥተሽ ቢያገኝሽ የሚደርስብሽን ታውቂያለሽ፤ ብትፈልጊ ወደ ቤድፎርድ ስትሪት ሄደሽ ጆን ኩክማንን ብትሰሚ ይሻልሻል» እያለ ሲያንሾካሹክ ተሰማኝ።

«እሺ፣ እሄዳለሁ።»

ስለዚህ ማዕዘኑ ደርሼ ወደ

ብሊከር ስትሪት ልታጠፍ ስል አንድ ድምፅ፦ «አይሆንም፣ ቀጥዪ» አለ። ቀጠልሁ። ግማሽ ብሎክ ያህል እንደ ሄድሁ ሰይጣን እንደ ገና፦ «መቀደስን እየፈለግሽ ነው አይደል?» ብሎ አንሾካሾከ።

«አዎን።»

«እንግዲያውስ ጄምስ ወደ ቤት መጥቶ አንቺ ከሌለሽ እጅግ ይቈጣል፤ ያም ኃጢአት ይሆናል፤ አንቺም ማንንም ማስኰነን የለብሽም።»

«አይ» አልሁ፤ «አላደርገውም።»

ከዚያም ሰይጣን፦ «በሂዩስተንና በፕሪንስ ስትሪቶች ማዕዘን ያለውን ያን የፕሬስቢቴሪያን አገልጋይ ሄደሽ ብትሰሚ ይሻልሻል» አለኝ። እነርሱ ለጥቁር ሰዎች ምን ያህል ደግ እንደ ሆኑ ሰምቼ ነበር፤ ይህንንም አገልጋይ ሄጄ እንደምሰማ ብዙ ጊዜ ቃል ገብቼ ነበር፤ ዲያብሎስ ይህን በሆነ መንገድ ደርሶበት ነበር፤ እንዴት እንዳወቀው ልነግራችሁ አልችልም፤ ግን አውቆታል። «ሄደሽ እርሱን ብትሰሚ ይሻልሻል፤ ደግሞም ለቤትሽ ይቀርባል፣ በሦስት ብሎክ ይቀርባል፤ ፈጥነሽም ወደ ቤት ልትደርሺ ትችያለሽ።»

«አዎን» አልሁ፤ «ልክ ነው።»

ማዕዘኑ ደርሼ ልታጠፍ ስል በለስላሳ መሳብ አንድ ጣፋጭ ድምፅ፦ «አይሆንም፣ አይሆንም፣ ቀጥዪ» ብሎ አንሾካሾከ።

«ጌታ ሆይ፣ እርዳኝ!»

ኦ፣ በዚያች አስፈሪ ሰዓት ስላሳየኝ ርኅሩኅ ፍቅሩና ታማኝነቱ እግዚአብሔርን መቼ በበቂ ሁኔታ አመሰግነዋለሁ! ለደከመው መንፈሴ ኃይልን ሰጠ፤ ጕልበትም ባልነበረኝ ጊዜ ብርታትን አበዛልኝ። ሃሌ ሉያ! ሃሌ ሉያ! ጌታ ይመስገን!

ጥቂት ወደ ፊት ሄድሁ፤ ብዙም ሳይቆይ ጠላት በብርቱ ቍጣ እንደ ገና የቀረበኝ መሰለ። እንዲህም አለኝ፦ «አሁንስ ከቶ ከነበሩት ሁሉ የምትበልጪ ሞኝ ነሽ። ጆን ኢንስኪፕን ልትሰሚ የምትሄጂ ይመስልሻል፤ እርሱ እዚያ የለም፤ ፋይቭ ፖይንትስ ነው ያለው።»

«ኦ፣ ወንድም ኢንስኪፕ እዚያ እንደሌለ ባስብ ኖሮ አልሄድም ነበር። ወደ ኋላ እመለስ ነበር።»

ቀጠልሁ። ደረጃዎቹ ጋ ስደርስ ወንድም ኢንስኪፕ ሲጸልይ በሰማሁ ጊዜ በልቤ ውስጥ ያለፈውን የደስታ ትርታ ፈጽሞ አልረሳውም። በቀረችኝ ጥቂት ብርታት፦ «እግዚአብሔር ይመስገን፣ እዚህ ነው ያለው እንጂ ፋይቭ ፖይንትስ አይደለም» አልሁ። ሰይጣናዊው መገኘት አጠገቤ እየተወረወረ አልፎ፦ «ኦ፣ ደረሰችበት» ያለ መሰለኝ። ሽማግሌው ሰይጣን ከታላላቅ ውሸቶቹ በአንዱ እንደ ያዝሁት አውቆ ነበር። ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብቼ ከበሩ ሦስት ወንበር ያህል ርቄ ተቀመጥሁ። ወደዚያ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ቀደም የሄድሁት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር፤ ያም ወንድም ኢንስኪፕ ያገለገለበት የመጀመሪያው እሑድ ነበር። ዮርክ ስትሪት በኖርሁበት ጊዜ እጅግ ታምሜ ስለ ነበር እስከ አባልነቴ ቤተ ክርስቲያን እስከ ሱሊቫን ስትሪት ቤቴል ቤተ ክርስቲያን ድረስ በእግሬ መሄድ አልቻልሁም፤ ስለዚህ በዚያ እሑድ ወደዚያ ገባሁ። የተቀመጥሁትም

በላይኛው ሰገነት ነበር። ሰዎቹ እጅግ ደጎች ነበሩ፤ አንድ ወንድም መጽሐፍ ሰጠኝ፤ እንደ ገናም እንድመጣ ለመነኝ። በዚያን ዘመን በግሪን ስትሪት ለነበረው ለዚያ መንፈስ፣ ለጥቁር ሰዎች እንኳ ለነበረው፣ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። በረከቱን ባገኘሁበት እሑድ ፎቅ ላይ አልተቀመጥሁም፤ ነገር ግን ኦ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ስገባ እንዴት ደክሜ ነበር! ራሴን ወደ ፊት ደፍቼ እግዚአብሔር ብርታት እንዲሰጠኝ ጸለይሁ። ወንድም ኢንስኪፕ ጸሎቱን ሲጨርስ ተነሥቶ ማስታወቂያዎቹን ተናገረ፤ የመጨረሻው መዝሙር ተዘመረ፤ ከዚያም ጥቅሱ መጣ፦ ኤፌሶን፣ ምዕራፍ 4 ቍጥር 24፦ «ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።» እንዲህም አለ፦ «ዛሬ ጠዋት ከዚህ ጥቅስ ስሰብክ ወንድሞች እንደሚያስተውሉት ከጥቂት ሰንበታት በፊት ስለ መቀደስ ወደ ሰበክሁት ስብከት መጠነኛ ማመላከት ይኖርብኛል።»

ደነገጥሁ፤ ከዚህ በፊት አንድ አገልጋይ ስብከቱን ሲጀምር ያን ቃል ሲናገር ሰምቼ አላውቅም ነበርና፤ እንዲህም አልሁ፦ «ኦ፣ ዕድሌ አመለጠኝ፤ ከሁለት ሰንበት በፊት ወደዚህ ለመምጣት ብርቱ ስሜት ሳበኝ፤ እኔ ግን አላደረግሁትም፤ ኦ ጌታ ሆይ፣ ያን መንፈስ አልታዘዝሁም፤ እጅግም አዝኛለሁ፤ እባክህ ይቅር በለኝ፤ እርዳኝም።»

ኦ፣ እንዴት አለቀስሁ! ዕድሌን አጥቼ ነበርና፤ ለበረከቱም እጅግ ተርቤአለሁ፤ ነገር ግን «ጌታ ሆይ፣ ይቅር በለኝ፤ አሁን እንዳዳምጥም እርዳኝ።»

ራሴን አቅንቼ ዓይኖቼንና ሐሳቤን በሰባኪው ላይ ተከልሁ፤ በጣምም ስለ ተመሰጥሁ በቀጥታ ለእኔ የሚሰብክ መሰለኝ፤ እያንዳንዷንም ቃል ተቀበልሁ። ብዙም ሳይቆይ ሕፃኔ ጮኾ ሲያለቅስ ሰማሁ፤ አንድ ሕፃን ሲጮኽ ሰምቼ እንደማውቀው ሁሉ ጥርት አድርጌ ሰማሁት። «ሜዚን ያን ሕፃን እንዳትሸከመው ነግረሻት ነበር፤ እርሷ ግን አንሥታው ጥላዋለች» ብሎ ሰይጣን ሐሳብ አቀረበልኝ።

ለአንድ አፍታ ነገሩ በእውነት የተፈጸመ ያህል በዓይኔ ፊት ነበር። ልቤ ቆመ፤ አንድ ድምፅም፦ «በጌታ ታመኚ» አለ።

«እታመናለሁ» አልሁ፤ ሐሳቤንም እንደ ገና አሰባስቤ አዳመጥሁ፤ ውዱ ወንድም ኢንስኪፕ እየጋለ ሲሄድና እኔም ስመገብ ሕፃኔ እንደ ገና ጮኸ። ዘለልሁ፤ በቤተ ክርስቲያኑ ያሉ ሰዎች ሁሉ የሰሙት መሰለኝ፤ እጅግ ግልጽ ነበርና።

«አየሽ» ይላል ዲያብሎስ፤ «ጄምስ ቤት መጥቷል፤ ሜዚም እንዳዘዝሻት አላደረገችም፤ ቤት ስትደርሺም ይደርስብሻል።»

ኦ፣ ክንፍ ቢኖረኝ በበረርሁ ብዬ ተሰማኝ። መጮኽ ፈለግሁ። አንድ ጣፋጭ ድምፅ፦ «በጌታ እታመናለሁ ብለሽ ነበር» አለኝ።

«አዎን፣ ብያለሁ» አልሁ፤ ስለዚህ ወደ ኋላ ተደግፌ እያዳመጥሁና

እየጠጣሁ ሳለሁ አሁን ሁሉ መልካም ነው ብዬ አሰብሁ። ሕፃኔ ሲጮኽ እንደ ገና ሰማሁ።

«አየሽ» አለ ዲያብሎስ፤ «ሜዚ ጥላው ጀርባውን ሰብራዋለች።» እኔም ተነሥቼ እስከ ወንበሩ ጫፍ ድረስ ሄድሁ።

«ምንም ጥቅም የለውም» አልሁ፤ «እዚህ እሠቃያለሁ፤ ወደ ቤት እሄዳለሁ።» አንድ ሰው በፊቴ ቆሞ፦ «ያን ሕፃን በጌታ እታመናለሁ አላልሽም ነበርን?» ያለኝ ያህል ሆነ።

«አዎን» አልሁ፤ «ሞቶ እንኳ ቢሆን በጌታ እታመናለሁ፤» ተቀመጥሁም። ልክ እንደ ተቀመጥሁ ወንድም ኢንስኪፕ፦ «ስለ መቀደስ በረከት የሚጨነቁ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ቢያገኙትስ እንዴት ሊጠብቁት እንደሚችሉ» አለ።

«ኦ!» አልሁ፤ «እኔን ማለቱ ነው፤ ይህ እኔ ያልሁት ነውና። ባለብኝ መከራና በልዩ ጠባዬ፣ በምታገለውም ነገር ሁሉ፣ በረከቱን ባገኘው እንዴት ልጠብቀው እችላለሁ? አሁን አንድ ሰው ነግሮታል፤ በቀጥታ እኔን እያየ ነውና፤ እኔን ማለቱም እንደ ሆነ አውቃለሁ።» ከምሰሶውም ኋላ ለመደበቅ ሞከርሁ፤ እርሱም ወደዚያ ዞሮ የሚያይ መሰለኝ። ከዚያም፦ «እንግዲህ እኔን ማለቱ ነው፤ የሚለውንም ዝም ብዬ እቀበላለሁ» አልሁ። ይህንም ምሳሌ ተጠቀመ፦ «ቀኑን ሙሉ በብርቱ ሠርታችሁ እጅግ ስትደክሙ፣—» «አዎን» አልሁ፤ በቅጽበትም ሐሳቤ ሌሊቱን ሙሉ በማጥበውና በምተኩሰው ልብስ ውስጥ አለፈ፤— «ሌሊት ወደ መኝታ ስትሄዱ እንዴት እንደምትተነፍሱ ምንም ዝግጅት አታደርጉም፣»— «አይ» አልሁ፤ «ስለዚያ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም፣»— «ትተኛላችሁ፤ ሌሊቱን ሙሉ ትተነፍሳላችሁ፤ ከመተንፈሳችሁ ጋር ምንም ጕዳይ የላችሁም፤ ጠዋት ትነቃላችሁ፤ በዚያ ምንም አላደረጋችሁም።»

«አዎን፣ አዎን፣ ገባኝ።»

ቀጠለ፦ «እግዚአብሔር በእናንተ ውስጥ እንዲኖር ምንም ዝግጅት ማድረግ አያስፈልጋችሁም፤ እግዚአብሔርን በሙላቱ ሁሉ በውስጣችሁ አግኙት፤ እርሱም ራሱ ይኖራል።»

«ኦ!» አልሁ፤ «ገባኝ።» እንደ ምንም ብዬ ከራሴ እይታ ርቄ ወደ ታች የሰመጥሁ፣ ከዚያም ወደ ላይ የተነሣሁ መሰለኝ፤ ሁሉም በቅጽበት ሆነ። በአንድ ጊዜ በሁለት አቅጣጫ፣ ወደ ታችና ወደ ላይ፣ የሄድሁ መሰለኝ። ልክ በዚያን ጊዜ እንዲህ ያለ ማዕበል መጣብኝ፤ በልቤም እንዲህ ያለ ምንጭ ፈለቀ፤ እነዚህም ቃላት እንደ ደወል በውስጤ አስተጋቡ፦ «እግዚአብሔር በአንቺ ውስጥ፣ እግዚአብሔር በአንቺ ውስጥ፤» እኔም ምን እያደረገ? ብዬ አሰብሁ። እያንዳንዱን ምኞትና ፍላጎት እየገዛ፣ አሳብንም ሁሉ ለፈቃዱ ለመታዘዝ እየማረከ። እንዴት በሕይወት እንደ ተረፍሁ መናገር አልችልም፤ የፍቅሩን፣ የሰላሙንና የኃይሉን ብፅዕና ግን ፈጽሞ ልገልጸው አልችልም። ኦ፣ ነፍሴን ምን ዓይነት ክብር ሞላት! በነፍሴ ውስጥ የነበረው ታላቅ ባዶነት መሙላት ጀመረ፤ እንደ ጣፋጭ የቀዝቃዛ ውኃ መጠጥ ነበር፤

ተሰማኝም። «ክብር ለኢየሱስ!» ብዬ እልል ማለት ፈለግሁ፤ ሰይጣን ግን፦ «አሁን ድምፅ ብታሰሚ ያስወጡሻል» አለኝ።

በዚያ ብቸኛዋ ጥቁር ሰው እኔ ነበርሁ፤ ደግሞም ለጨዋነትና ለሥርዓት ጥልቅ ስሜት ነበረኝ፤ እንዲያ ተምሬ ነበር፤ ሰይጣንም ይህን ያውቅ ነበር። እነዚህን በእኔ ውስጥ ያሉትን ትንንሽ ነጥቦች ሁሉ እንዴት እንዳወቃቸው ይገርመኛል፤ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ኢየሱሴ አሸናፊ ሆኖ ወጣ። እኛ ጥቁሮች ባለፉት ዓመታት እንዘምር እንደ ነበረው፦


«ኢየሱስ ኃያል አለቃ ነው፣
ኢየሱስ ኃያል አለቃ ነው፣
ኢየሱስ ኃያል አለቃ ነው፣
አንተ የመስቀሉ ወታደር።»


«ኢየሱስ ጦርነት ተሸንፎ አያውቅም፣
ኢየሱስ ጦርነት ተሸንፎ አያውቅም፣
ኢየሱስ ጦርነት ተሸንፎ አያውቅም፣
አንተ የመስቀሉ ወታደር።»

ሃሌ ሉያ! ሃሌ ሉያ! አሜን።

እልል አላልሁም፤ ብዙም ሳይቆይ ወንድም ኢንስኪፕ ወደ ሌላ ምሳሌ መጣ። ስለ እምነት ሲናገር እንዲህ አለ፦ «እንግዲህ ይህ የንጽሕና በረከት ልክ እንደ ይቅርታ በእምነት ይቀበላል፤ በእምነት ከሆነ ደግሞ ለምን አሁን አይሆንም?»

«አዎን» አልሁ።

«በቅጽበት የሚሆን ነው» ብሎ ቀጠለ። «ለማስረዳት ያህል፣ የበራ መብራት ወደ ጨለማ ክፍል ስታስገቡ ክፍሉ ለምን ያህል ጊዜ ጨለማ ሆኖ ይቆያል?»

«ኦ» አልሁ፤ «ገባኝ!» እንደ ገናም ታላቅ የክብር ማዕበል በነፍሴ ላይ ጠረገ — ሌላ የሚያቀዘቅዝ የውኃ መጠጥ — የዋጥሁት መሰለኝ፤ ከዚያም በልቤ ውስጥ የሚፈልቀው ምንጭ ይበልጥ ጥቂት የሞላ መሰለ። ስለዚያች ቀን ጌታ ለዘላለም ይመስገን!

ስለ እግዚአብሔር ኃይል ሲናገር ሌላ ምሳሌ ይዞ ቀጠለ። እንዲህ አለ፦ «እግዚአብሔር በዓይን ጥቅሻ እነዚህን የተዋረዱትን ሥጋዎቻችንን ለውጦ የራሱን እጅግ ክቡር ሥጋ እንዲመስሉ ሊያደርጋቸው ከቻለ፣ አንዲትን ነፍስ ለመቀደስ እግዚአብሔርን ምን ያህል ጊዜ ይወስድበታል?»

«እግዚአብሔር በዓይን ጥቅሻ ሊያደርገው ይችላል» አልሁ፤ ከተመታ ብረት እንደሚወጣ ብልጭታ ፈጥኖ የእግዚአብሔር ንክኪ ከራሴ አናት እስከ እግሬ ጫማ ድረስ ተሰማኝ፤ ምንጩም ፈለቀ፤ እልል ማለት እንዳለብኝም ተሰማኝ፤ ነገር ግን ሰይጣን ኢያሱን እንደ ተቃወመው እኔንም አሁንም ይቃወመኝ ነበር። የጌታ ሠራዊት አለቃ ግን አጠገቤ ቆሞ፦ «እድፋሙን ልብስ ከእርሱ ላይ አውልቁ» አለ፤ ሰይጣንም ተናደደ። ዳሩ ግን እንደ ገና ለፈታኙ ተሸነፍሁ፤ እልልም አላልሁም። ከዚያም መንፈስ ሲለየኝ ተሰማኝ። እንደ ሄደ አወቅሁ፤ እንዲህም አልሁ፦ «ኦ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ ብቻ ብትመለስ እመሰክርልሃለሁ።» እግዚአብሔር

የመመስከርን ቃል በአፌ ስላኖረ እጅግ ደስ ብሎኛል። መንፈስ እንደ ገና ሲመጣ እልል እንድል ልዘጋጅ አሰብሁ፤ ነገር ግን ሳላውቀው፣ ልክ አንድ ሰው ፊቴ ላይ አንድ ሳህን ውኃ የደፋብኝ ያህል፣ ታላቅ ማዕበል መጣ፤ «ክብር ለኢየሱስ!» ልል ስል ዲያብሎስ፦ «ተመልከቺ፣ ነጮቹን ተመልከቺ፤ ተጠንቀቂ፣ ያስወጡሻል» አለ፤ እኔም እጆቼን ወደ አፌ አድርጌ ጸጥ አልሁ፤ እንደ ገናም መንፈስ ትቶኝ ሲያልፍ ተሰማኝ።

ከዚያም ሰይጣን፦ «እንግዲህ መንፈስ ቅዱስን ዋሽተሻል፤ መንፈስ ቅዱስ ቢመለስ እመሰክርልሃለሁ ብለሽ ነበርና፤ እርሱም ተመለሰ፤ አንቺ ግን አልመሰከርሽም፤ መንፈስ ቅዱስንም ዋሽተሻል» አለ።

ኦ፣ የዚያችን ሰዓት ድንጋጤ መቼም እረሳው ይሆን? ይቅር የማይባል ኃጢአት የሠራሁ፣ ስለዚህም ለዘላለም የተፈረደብኝ መሰለኝ። ተስፋ ሁሉ ጠፋ፤ የሚያስፈራ ጨለማም መንፈሴን ወረረው። ለአምስት ደቂቃ ያህል በሲኦል ያለሁ መሰለኝ፤ ነገር ግን እንደ ምንም፣ እንዴት እንደ ሆነ አላውቅም፣ «እንግዲህ ጌታ ነፍሴን እንደ ቀደሳት አውቃለሁ» — እንደዚያ እርግጠኛ ሆኜ ተሰማኝ — «ወደ ቤተ ክርስቲያኔም ሄጄ እመሰክራለሁ» አልሁ።

ልክ በዚያን ጊዜ ሰይጣን፦ «በረከቱን እዚያ ስላላገኘሽው አያምኑሽም» ይላል።

ያን ጊዜ በአንዳንዶች ዘንድ ጥቂት ቅናትና አድልዎ እንደ ነበረ አውቅ ነበር፤ ስለዚህ፦ «ግድ የለም፤ ለማንኛውም ጌታ ነፍሴን እንደ ቀደሳት አውቃለሁ» አልሁ። ለመውጣትም ልነሣ ሞከርሁ፤ ነገር ግን በእግሬ መቆም አልቻልሁም። ኦ፣ እንዴት ደክሜ ነበር! ራሴ የውኃ ወንዝ፣ ዓይኖቼም የእንባ ምንጭ የሆኑ መሰለኝ። መሐረቤን ለማውጣት እጄን ወደ ኪሴ ከተትሁ፤ ነገር ግን ላወጣው አልቻልሁም። ልክ በዚያን ጊዜ የመዝጊያውን መዝሙር ለመዘመር ተነሡ፤ ያን የተባረከ መዝሙር፣ «የመጨረሻዋ ፀሐዬ በፍጥነት እየጠለቀች ነው» የሚለውን። ልነሣ ሞከርሁ፤ ነገር ግን አልቻልሁም፤ ከዚያም ዲያብሎስ፦ «እዚህ ማንም አያውቅሽም፤ ሰክራለች ብለውም ያስባሉ» ይላል።

«ጌታ ሆይ፣ ምን ላድርግ?» አንድ ድምፅም በግራ ጆሮዬ ያንሾካሾከ መሰለኝ፤ ሰይጣን በቀኜ ቆሞ የራሱን ሐሳብ ያንሾካሹክ ነበርና፦ «ለመቆም ብርታት እንዲሰጥሽ ጸልዪ።» በፊቴ ያለውን ወንበር ያዝሁ፤ ከራሴ እስከ እግሬ እየተንቀጠቀጥሁ ቆምሁ፤ ወንበሩን ግን አጥብቄ ያዝሁ። ልክ በደንብ እንደ ቆምሁ የመዝሙሩን የመጨረሻ ስንኝ ጀመሩ፦


«ኦ! የሚናፍቀውን ልቤን ወደ እርሱ ውሰደው፣
ስለ እኔ ደሙን አፍስሶ ለሞተው።
ደሙ አሁን ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻ፣
ድልንም የሚሰጠኝ።»

«ደሙ አሁን የሚያነጻ» የሚሉትን ቃላት ሲዘምሩ ኦ፣ ምን ዓይነት የክብር ማዕበል በነፍሴ ላይ ጠረገ! «ክብር ለኢየሱስ» ብዬ እልል አልሁ። ወንድም ኢንስኪፕም፦ «አሜን፤ ክብር ለእግዚአብሔር» ብሎ መለሰ። ኦ፣ ለንጉሣችን ለአማኑኤል እንዴት ያለ ድል ነበር! ምን እንደምመስል በትክክል አላውቅም፤ ነገር ግን እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ እንግዳ ሆኖ ተሰማኝ፤ ሆኖም ክብር የሞላብኝ ሆኖ ተሰማኝ። ስወጣ በበሩ ላይ ከነበሩት መልካም የቤተ ክርስቲያን ኃላፊ ወንድሞች አንዱ፦ «እንግዲህ አክስቴ፣ ስብከቱ እንዴት ነበር?» አለኝ፤ እኔ ግን መናገር አልቻልሁም፤ ተናግሬ ቢሆን ኖሮ እልል ባልሁ ነበር፤ ስለዚህ ራሴን ብቻ ነቀነቅሁ። ልክ እግሬን በላይኛው ደረጃ ላይ እንዳኖርሁ ንክኪውን ልገልጸው የማልችለው አንድ እጅ የተሰማኝ መሰለ። በራሴ አናት ላይ በለስላሳ የሚጫነኝ መሰለ፤ አንድ ነገር ተከፍሎ ተንከባልሎ ሲወርድና እንደ ታላቅ ካባ ሲሸፍነኝ ተሰማኝ! ጥርት አድርጌ ተሰማኝ፤ በቅጽበት ተፈጸመ፤ ኦ፣ እንዴት ያለ ታላቅ ሰላምና ኃይል ያዘኝ! በግሪን ስትሪት ሽቅብ መሄድ ጀመርሁ። መንገዶቹ ከልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት በየአቅጣጫው በሚመጡ ሰዎች ተሞልተው ነበር። ልክ ከፊቴ ከቤተ ክርስቲያናችን ዋና ዋና እኅቶች ሦስቱ ይሄዱ ነበር። ከእነርሱ ይልቅ ሌላ ማንንም ባገኝ እመርጥ ነበር። እፈራቸው ነበር። እንግዲህ ለምን እንደ ሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን ጥበብ ከእነርሱ ጋር እንደምትኖር እንዲሰማችሁ የሚያደርጉ ዓይነት ነበሩ። በዕድሜ የገፉ ዋና እኅቶች ነበሩ፤ እንደነዚህ ያሉ ራሳቸውን አስፈላጊ አድርገው የሚቈጥሩ ዋና እኅቶች ያሉባቸው የጥቁሮች አብያተ ክርስቲያናት ብቻ እንዳልሆኑም ተረድቻለሁ። እንግዲህ እየቀረብኋቸው ስሄድ እርስ በርሳቸው አንድ ነገር ሲባባሉ አየሁ፤ እጅግም የተከበሩ መስለው ታዩ። በዚህ ጊዜ ዲያብሎስ እንደ ቀድሞው አልቀረበኝም ነበር፤ ከኋላዬ ራቅ ብሎ ያለ ይመስል ነበር፤ ነገር ግን ከኋላዬ፦ «እንደ ተቀደስሽ አትነግሪያቸውም» ብሎ ጮኸብኝ።

«አይ» አልሁ፤ «ምንም አልነግራቸውም፤» ነገር ግን እነርሱ ዘንድ ስደርስ በቀኝ ክንዴ ልዩ ኃይል ያለ መሰለኝ፤ ወንዶች ልጆች አንዳንድ ጊዜ እንደሚያደርጉት ክንዴን እያወዛወዝሁ ነበር! ለምን እንደ ሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን ኦ፣ ወደ እነዚያ እኅቶች ስቀርብ ኃያል ሆኖ ተሰማኝ። እነርሱም፦ «እንግዲህ ስሚዝ፣ ዛሬ ጠዋት የት ነበርሽ?» አሉኝ።

«ጌታ» አልሁ፤ «ነፍሴን ቀደሳት።» እነርሱም የሚናገሩት አጡ! ከዚያ በላይ ምንም አልተናገርሁም፤ ነገር ግን ክንዴን እያወዛወዝሁ አልፌ ሄድሁ! ሰዎቹ አብዳለች ብለው ያሰቡ ይመስለኛል፤ በእርግጥም እንደዚያ ነበርሁ፤ እግዚአብሔር በእሳት አቀጣጥሎኝ ነበርና! «ኦ» ብዬ አሰብሁ፤ «በዓለም ዙሪያ የሚዞር መድረክ ቢኖር ኖሮ በላዩ ወጥቼ እየሄድሁ ስለዚህ ስለሚቀድሰው የእግዚአብሔር ኃይል ለሰው ሁሉ ለመናገር ፈቃደኛ በሆንሁ ነበር!»


«በሰይጣን ኃይል ላይ ስላገኘነው ድል፣
የተዋጁት ሁሉ ይዘምሩ፣
በሞትም ሰዓት ድል ያድርጉ
በንጉሣችን በጌታ በክርስቶስ።»


«ኦ! ፍቅር ነበር፣
ድንቅ ፍቅር ነበር፣
ለእኔ የሆነው የእግዚአብሔር ፍቅር፣
አዳኜን ከላይ ያመጣው፣
በቀራንዮ እንዲሞት።»

እንደ ምንም ብዬ ሁልጊዜ ነጮችን እፈራ ነበር — ይህም ማለት ጕዳት ያደርሱብኛል ወይም እንደዚያ ያለ ነገር ያደርጉብኛል በሚል ስሜት አልፈራቸውም ነበር — ነገር ግን እነርሱ ነጮች ስለ ሆኑና በዚያ ስለ ነበሩ፣ እኔም ጥቁር ስለ ሆንሁና በዚህ ስለ ነበርሁ የሆነ ዓይነት ፍርሃት ነበረብኝ! ነገር ግን በዚያች ጠዋት በግሪን ስትሪት እየተንቀጠቀጥሁ በእግሬ ቆሜ ሳለሁ እነዚህን ቃላት ጥርት አድርጌ ሰማሁ። ከቤተ ክርስቲያኑ ሰሜን ምሥራቅ ማዕዘን በዝግታ፣ ነገር ግን በግልጽ የመጡ መሰሉ፦ «አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።» (ገላትያ 3:28)። ያን ጥቅስ ከዚያ በፊት አስተውዬው አላውቅም ነበር። አሁን ግን መንፈስ ቅዱስ ግልጽ አደረገልኝ። ሁልጊዜ የምፈራቸው የሚመስሉኝን ነጮች ስመለከት አሁን እጅግ ትንንሽ መስለው ታዩኝ። ታላቁ ተራራ የፍልፈል ኵይሳ ሆነ። «እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ።» ምስጋና ሁሉ ለአሸናፊው ክርስቶሴ ይሁን!


«ታስሬ ሳለሁ አዳነኝ፣
ቈስዬም ሳለሁ ቍስሌን ፈወሰ።
ስቅበዘበዝ ፈልጎ አቀናኝ፣
ጨለማዬንም ብርሃን አደረገ።»

ሃሌ ሉያ! ሃሌ ሉያ! ጌታ ይመስገን!

ቤት ስደርስ በሩን ከፈትሁ፤ ሕፃኑ ገና ተኝቶ ነበር። «ሜዚ፣ አቶ ስሚዝ መጥቷል?» አልሁ።

«አልመጣም።»

«ዊል በደኅና ተኝቷል?»

«አዎን፣ ፈጽሞ አልነቃም።»

«እንግዲህ ጌታ ዛሬ ጠዋት ነፍሴን ቀደሳት» አልኋት፤ እርሷም፦ «እውነት፣ እማዬ?» አለች።

«አዎን» አልሁ፤ «ሄጄም ለአክስቴ ስኮት መንገር እፈልጋለሁ።» እርሷ መልካሚቱ የጸሎት ቡድን እኅቴ ነበረች። የምትኖረው ከስምንተኛው ጎዳና ገባ ብሎ ባለው በክሊንተን ኮርት ነበር። በሩ ጋ ስደርስ እያንኳኳሁ ከፈትሁ። ወንድም ስኮት በሶፋው ላይ ተጋድሞ ነበር፤ እርሱ የእኔ የክፍል መሪ ለነበሩት ለወንድም ሄንሪ ደ ሺልድ ረዳት የክፍል መሪ ነበር። እርሳቸው በቅድስና ትምህርት ያምኑ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ግን ተሞክሮውን ገና አላገኙም ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ይመስገን፣ በእርሱ ያምኑ ነበር፤

በእርሱም ላይ ምንም አይናገሩም ነበር፤ ስለዚህ ያ ለእኔ ይጠቅመኝ ነበር። ወንድም ስኮት ግን «በአጥሩ ላይ» ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ በእርሱ የሚያምን መስሎ እንዳገኘው ሆኖ ይናገር ነበር፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ አጥብቆ ይቃወመው ነበር፤ ስለዚህ መቼ በአንተ ላይ እንደሚዞር ፈጽሞ አታውቅም ነበር። በዚያች ጠዋት ስገባ፦ «አባባ ስኮት፣ ጌታ ዛሬ ጠዋት ነፍሴን ቀደሳት» አልሁት።

ቀና ብሎ፦ «ቀ—ቀደሳት?» አለ (ትንሽ ይንተባተብ ነበር)። ከዚያ በላይ አልጠበቅሁም፤ ባለፉት ዘመናት በፍቅር ግብዣዎቻችንና በክፍል ስብሰባዎቻችን ሲዘመር ብዙ ጊዜ የሰማሁትን፣ እውነተኛው የነፍሴ ዝማሬ የሚመስለውን አንድ የቈየ መዝሙር መዘመር ጀመርሁ። በሕይወቴ ከዚያ በፊት ከኢየሱስ ጋር እንዲህ ያለ የነፍስ አንድነት ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር፤ ስለዚህ እንዲህ ብዬ ዘመርሁ፦


«ከኢየሱስ ጋር ተጋብቻለሁ
ከአንድ ዓመት በላይ፣
ከኢየሱስ ጋር ተጋብቻለሁ
ጦርነቱ እስኪያልቅ።»

ሽማግሌው ተመለከተኝና ፈገግ አለ፤ ለክርክርም ተዘጋጀ። ልጆቹ ሁሉ ተደንቀው ተመለከቱ። እኅት ስኮት ከቤተ ክርስቲያን ገና አልተመለሰችም ነበር። ስንኙን ስጨርስ «ደኅና ዋሉ» አልሁ፤ ለመውጣትም በሩን ስከፍት እኅት ስኮት ልክ እየገባች ነበር። «ኦ፣ ስኮት! ጌታ ዛሬ ጠዋት ነፍሴን ቀደሳት» አልኋት።

እጅግ ደስ ይላታል ብዬ አሰብሁ፤ ከብዙ ዓመታት በፊት በካናዳ በወይዘሮ ዶ/ር ፓልመር አማካይነት በረከቱን እንዳገኘች ነግራኝ ነበርና። ስለ እርሱ በግልጽና በትክክል ተናግራ አታውቅም ነበር፤ ስለዚህ ስለ እርሱ ምንም ነገር አልገባኝም ነበር፤ ነገር ግን በጣም የገረመኝ ነገር እጅግ በቀዝቃዛ ሁኔታ፦ «እንግዲህ እንደምትጠብቂው ተስፋ አደርጋለሁ» ብላ አጠገቤ አልፋ ገባች፤ ሌላ አንድ ቃልም አልተናገረችም። ወጣሁ። ኦ፣ እንዴት ያለ ድንጋጤ ነበር!

«አየሽ» ይላል ዲያብሎስ፤ «በረከቱን እንዳገኘሽ አታምንም።»

«ኦ ጌታ ሆይ» አልሁ፤ «ተሳስቼ ሊሆን ይችላልን? ተመልሼስ መንገዱን ሁሉ ከመጀመሪያው መሄድ ይኖርብኛልን? ይልቅስ እዚሁ በቆምሁበት ብሞት እመርጣለሁ።»

ከስምንተኛው ጎዳና ወደ ስድስተኛው አቨኑ ስታጠፍ፦ «ኦ ጌታ ሆይ፣ እርዳኝ፤ ይህ በረከት መቀደስ ካልሆነ ታዲያ ምንድር ነው?» ብዬ ጮኽሁ። ጌታም በእርግጥ ረዳኝ። ወዲያውኑ እነዚህ ቃላት በኃይል ወደ ልቤ መጡ፦ «ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው።» «ለሚያምኑ» የሚለው ቃል በብርቱ አጽንዖት የተሰጠው መሰለ፤ እኔም፦ «ጌታ ሆይ፣ ነፍሴን እንደ ቀደስሃት በእርግጥ አምናለሁ» አልሁ፤ የእግዚአብሔርም ኃይል

በእኔ ላይ ወረደ፤ ስለዚህም ጕልበቶቼ ተብረከረኩ፤ ልክ በጥይት እንደ ተመታ ሰው እዚያው በስድስተኛው አቨኑ ላይ ወደቅሁ። ሰዎች ያልፉ ነበር፤ ተመለከቱኝ፤ ምንም ግን አልተናገሩም። ጭንቅላቷ ትንሽ ተነክቷል ብለው ያሰቡ ይመስለኛል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ምርኮዬን መልሶ ነበር፤ አፌም ሣቅ ተሞልቶ ነበር። እንደ ቻልሁ እየተፍጨረጨርሁ ተነሣሁ፤ በግንባሬ አልተደፋሁም ነበርና፤ ጕልበቶቼ ተብረክርከው በእጆቼ ላይ ወደቅሁ እንጂ፤ ጌታ በአፌ ያኖረውን ቃል፣ «ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው» የሚለውን፣ በተናገርሁ ቍጥር ሌላ የኃይል ማዕበል በላዬ ይወርድ ነበር። እንደ ገና ወደቅሁ፤ እንዲሁም ቤት ሳልደርስ ሦስት ጊዜ በእግዚአብሔር ታላቅ ኃይል ሥር ወደቅሁ። ሃሌ ሉያ! ዛሬም ያው ነው፤ «ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው፤» እኔም እግዚአብሔርን አምናለሁ፤ እርሱም በግሩም ሁኔታ ድኜ እንድኖር ጠብቆኛል። ሃሌ ሉያ! በነፍሴ ውስጥ ታላቅ የድል ደስታ አለ። ዲያብሎስ ወዴት እንደ ሄደ አላውቅም፤ ለአንድ ሳምንት ግን ስለ እርሱ ምንም አልሰማሁም፤ ከዚያም መጥቶ ጐበኘኝና፦ «ሰዎች ሲቀደሱ በዙሪያቸው ያለው ነገር ሁሉ ይሻሻላል» አለኝ።

«አዎን» አልሁ።

«እንግዲህ አየሽ፣ ጄምስ ምንም አልተሻሻለም፤ እንዲያውም ብሶበታል።»

ይህ እውነት ነበር፤ ከተቻለስ ከዚያም የባሰ፤ እኔም እንደዚያው እንደማስብ ተናገርሁ፤ ነገሩም አልገባኝም ነበር፤ የበለጠ ሃይማኖት እንዳገኘሁ ሲያውቅ ደስ ይለዋል ብዬ አስቤ ነበርና።

«እንግዲያውስ» አለ፣ «መቀደስሽን የሚያረጋግጥ ምስክር የለሽም።»

«እንግዲህ» አልሁ፣ «እግዚአብሔር ቢረዳኝ አሁኑኑ አገኘዋለሁ።»

ቀኑ ዓርብ ነበር። ልብስ እየተኮስሁ ነበር፤ ካውያዬን አስቀምጬ ሄጄ ለኢየሱስ ነገርሁት። እንዲህም አልሁ፦ «ጌታ ሆይ፣ ነፍሴን እንደ ቀደስሃት አምናለሁ፤ ሰይጣን ግን ምስክር የለሽም ይለኛል። እንግዲህ ጌታ ሆይ፣ ለዚህ በረከት ቀጥተኛ ምስክር ይሆን ዘንድ ምን እንደምለምን አላውቅም፤ ነገር ግን በሕይወት እስካለሁ ድረስ ዲያብሎስ በዚህ ጉዳይ ዳግመኛ እንዳያጠቃኝ እጅግ ግልጽና ለይቶ የሚታወቅ አንድ ነገር ስጠኝ።»

አጭር ጸሎት ካደረግሁ በኋላ ለጥቂት ጊዜ በዝምታ ጠበቅሁ፤ ከዚያም «እንግዲህ ጌታ ሆይ፣ አንተ ራስህ እስክትናገረኝ ድረስ እጠብቃለሁ» አልሁ። ጥቂት ጊዜ አለፈ፤ እነዚህም ቃላት መጡልኝ፦ «ስለ ወይዘሪት ቼፕል መለወጥ ለምኚ።»

እኔም «ጌታ ሆይ፣ ነፍሴን እንደ ቀደስሃት እውነተኛ ማስረጃ ይሆነኝ ዘንድ ከአሁን ጀምሮ እስከ እሑድ ጠዋት ድረስ ወይዘሪት ቼፕልን እንድትለውጣት እለምንሃለሁ» አልሁ።

ወዲያውም እነዚህ ቃላት በነፍሴ ውስጥ እንደ መብረቅ ብልጭ አሉ፦ «ብታምን፥

ለሚያምን ሁሉ ይቻላል።» እኔም «ጌታ ሆይ፣ እንደምታደርገው አምናለሁ» አልሁ፤ የብርሃንና የደስታ ጎርፍም ሞላኝ። ኦ፣ ጌታን አመሰግናለሁ! እግዚአብሔርን እያመሰገንሁ ከተንበረከክሁበት ተነሣሁ። ወደ ተኳሴ ተመለስሁ፤ ጥቂት ቆይቶም ሰይጣን እንደ ገና መጣ።

«ይህን ያህል እርግጠኛ ከመሆንሽ በፊት ሄደሽ ሴቲቱ ተለውጣ እንደ ሆነ ማየት ይገባሽ ነበር።»

«አዎን፣ መሄድ ደስ ባለኝ ነበር፤ ነገር ግን ሁለት ማይል ይርቃል፤ ዊልም ነቅቶ ያለቅስ ይሆናል ብዬ እፈራለሁ።»

ጠላት ግን «በጣም እርግጠኛ ባትሆኚ ይሻልሻል፤ ሄደሽ ማየት ይገባሻል» እያለ ገፋፋኝ፤ እኔም ክፉኛ ተፈተንሁ። ልቤን በጸሎት ወደ እግዚአብሔር አንሥቼ «ጌታ ሆይ፣ እርዳኝ፤ እንደምታደርገው አምናለሁ፤ በአንተም እታመናለሁ» አልሁ። ከዚያም ጸጥታና እርጋታ በመላ ሰውነቴ ላይ ወረደ፤ እኔም እየዘመርሁ ልብሱን መተኮሴን ቀጠልሁ። ጌታ ይመስገን!

ቀደም ብዬ የጠቀስኋት ወይዘሪት ቼፕል ክርስቲያን ባትሆንም እጅግ ደግ ወጣት ሴት ነበረች። በጣም ቀጥተኛና ሥነ ምግባር ያላት ሰው ነበረች። ታመመች፤ እጅግ ልባዊ ክርስቲያን የነበረችው እኅቷም ስለ ነፍሷ ሁኔታ በጣም ተጨንቃ እኔንና ሌሎችን መጥተን አብረናት እንድንጸልይ ለመነችን። አንድ ቀን ሄድሁ፤ እዚያም እማማ ጆንስንና ሌሎች ብዙዎችን አገኘሁ። አብረናት ዘመርን፣ ጸለይንም፤ ትተናትም ሄድን። አሁን አንድ ሳምንት አልፎ ነበር፤ ስለ እርሷም ምንም አልሰማሁም ነበር፤ ጠላት ዓርብ ዕለት እንዲያ በብርቱ ያጠቃኝ ስለዚህ እንደ ሆነም አሰብሁ። እሑድ ጠዋት ደረሰ፤ እኔም «ብታምን፥ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል» እንደሚለው ቃሉ ማመኔንና እግዚአብሔርን ማመስገኔን አላቋረጥሁም ነበር። ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄድሁ፤ ስብከቱ አልቆ መባ ሲሰበሰብ በወንበሬ ተቀምጬ ሳለሁ፣ በተቃራኒው ወንበር ተቀምጣ የነበረችው እኅት ጆንስ ተነሥታ ወደ እኔ መጥታ «ስሚዝ፣ ቼፕል በረከቱን አገኘች» አለችኝ። እኔም «ጌታ ይመስገን፤ መቼ አገኘችው?» አልሁ። እርሷም «ትናንት ከሰዓት በኋላ» አለች። ከዚያም እነዚህ ቃላት በኃይል ለልቤ ተነገሩ፦ «እንግዲህ ማስረጃሽ ይኸው ነው»፤ እኔም «ጌታ ሆይ፣ በእውነት አመሰግንሃለሁ፤ ጸሎቴን ሰምተህ ነፍሴን እንደ ቀደስሃት ይህን ግልጽ ምስክር ሰጥተኸኛል» አልሁ።

ከዚያ ወዲህ ብዙ ጊዜ እምነቴ ክፉኛ ተፈትኗል፤ ብዙ የምታገለውም ነገር ገጥሞኛል፤ የሰይጣን የሚንበለበሉ ፍላጾችም አንዳንድ ጊዜ እጅግ አሳምመውኛል፤ ነገር ግን ከዚያች ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር ይህን የተባረከ ሥራ አልሠራም ብሎ ሊነግረኝ ፈጽሞ አልደፈረም። ሃሌ ሉያ! እንዴት ያለ አዳኝ ነው!

ሁሉም ሰው ስለ መቀደሱ

ወይም ስለ መጽደቁ በዚህ መንገድ ቀጥተኛ ምስክር አያገኝም፤ ነገር ግን ስለ መጽደቅም ስለ መቀደስም የመንፈስን ግልጽና ለይቶ የሚታወቅ ምስክር ማግኘት መብታቸው ነው። በአብዛኛውም ይህን ግልጽ ምስክር የማያገኙ ሰዎች በክርስትና ሕይወታቸው ያልተረጋጉ ናቸው፤ ብዙ ጊዜ ይዋልላሉ፣ ያመነታሉም፤ ወደ አዳዲስ ፍልስፍናዎችና ትምህርቶችም በቀላሉ ፈቀቅ ይላሉ። እግዚአብሔር ግን ይመስገን፤ አሳቤ በእርሱ ላይ ተደግፎ በእርሱም ስታመን በፍጹም ሰላም ጠብቆኛል። ስሙ ለዘላለም ይመስገን!

ጄምስ ለሁለት ሳምንት ወደ ቤት አልመጣም። በመጣ ጊዜ ጭኑ ላይ ተቀምጬ እጆቼን በአንገቱ ዙሪያ አድርጌ ሁሉንም ነገር ነገርሁት። በትዕግሥት አዳመጠኝ። ጨርሼ ስጨርስ የቀድሞ ክርክሩን ጀመረ። እኔም «ውዴ ሆይ፣ እንደማልከራከር ታውቃለህ» አልሁት።

«እንግዲህ» አለ፣ «ልትናገሪው የማትችዪው ነገር አግኝተሽ ከሆነ፣ እኔ አላምንበትም።»

«እንግዲህ» አልሁ፣ «የምችለውን ሁሉ ነግሬሃለሁ፤ ልከራከር ግን አልችልም።» ኦ፣ በሁሉም መንገድ እንዴት አበሳጨኝ! እግዚአብሔር ግን ነፍሴን እጅግ ጸጥ አድርጎ ጠበቃት፤ ምስኪኑ ባሌም ስላልተከራከርሁት እጅግ ተበሳጨ። ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ አውቅ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ይመስገን፤ አዳነኝ። ማልቀስና መጸለይ ብቻ ነበር የምችለው።

ከተለወጥሁ ብዙም ሳይቆይ ለልብ ንጽሕና በረከት ጥልቅ የሆነ የልብ ወቀሳ ተሰማኝ፤ የሚያስተምረኝ ሰው ቢኖር ኖሮ ወደዚያ የተባረከ ልምምድ እንዴት ልገባ እንደምችል አሁን ይታየኛል። ነገር ግን ተገቢ ትምህርት ስላላገኘሁ፣ እንደ ጥንቱ እስራኤል በጥርጣሬና በፍርሃት፣ በመውጣትና በመውረድ ምድረ በዳ ውስጥ ለአሥራ ሁለት ዓመት ተንከራተትሁ። ቄስ ጆን ኤስ. ኢንስኪፕ ራሱ ያንን ልምምድ ባያገኝና በሴፕቴምበር 1868 በኒው ዮርክ በሚገኘው በአሮጌው የግሪን ስትሪት ቤተ ክርስቲያን በዚያ የማይረሳ የእሑድ ጠዋት ባይሰብክ ኖሮ፣ ምናልባት ወደ ሙሉ መዳን የተባረከ ብርሃን ፈጽሞ ባልገባሁ ነበር።

ለልብ ንጽሕና በረከት እንዲያ በጥልቅ በተወቀስሁ ጊዜ፣ በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘሁ የሚያሳየው ማስረጃ እንዲያ የተረጋገጠና ግልጽ ስለ ነበረ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ያም ሆኖ ትግሉ ከባድ ነበር፤ ነገር ግን ይህ ነጥብ እንዲያ በግልጽ ባይረጋገጥ ኖሮ እጅግ የከፋ ይሆን ነበር — በሁለቱ ወቀሳዎች ማለትም ስለ ይቅርታና ስለ ንጽሕና በሚሰማው ወቀሳ መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው። ስለ ኃጢአት በተወቀስሁ ጊዜ ከፍርድ በታች ነበርሁ፤ የጠፋሁና ጐስቋላ ኃጢአተኛ እንደ ሆንሁም ተሰማኝ። አሁን ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ኃጢአቴን ሁሉ ይቅር ባለኝ ጊዜ ፍርድን ሁሉ ከእኔ አስወገደ፤ በማመንም ደስታንና ሰላምን ሰጠኝ። ሃሌ ሉያ!

አሁን ግን ስለ ንጽሕና ወይም ስለ መቀደስ በተወቀስሁ ጊዜ፣ ወቀሳው

የጥልቅ ጉድለት ስሜት ነበር — ሊገለጽ የማይችል ጉድለት፤ ፍርድ አልነበረም። ነገር ግን ኦ! ያ ጥልቅ የልብ ረሃብ! ልክ ጥሩ የጠገበ ቁርስ በልተህ ቀኑን ሙሉ በትጋት ከሠራህ በኋላ ለምሳህ ወይም ለእራትህ በጣም እንደምትራብ ያለ ነበር። እንግዲህ ልቤ «ንጋትን እንደሚጠባበቅ» ሰው ጮኸ፣ ናፈቀም። ያም ሆኖ የፈለግሁትን በትክክል የምገልጽበት መንገድም ቃልም አልነበረኝም። አንድ ቀን አንዲት ወዳጄ ልትጠይቀኝ መጣች። በዚያን ጊዜ በላንካስተር በኮሎኔል ኤስ. ማክግሮ ቤት እኖር ነበር። እርሷ እጅግ የተከበረች ጥቁር ሴት ነበረች፤ የፖርተርን ቤተሰብ ሁሉም ያውቀው ነበርና፤ ሁልጊዜም በጥቁሮች መካከል ከዋነኞቹ ቤተሰቦች እንደ አንዱ ይቆጠሩ ነበር። አባትየው በኬንት ካውንቲ ትልቅ ገበሬ ነበሩ፤ ወንዶች ልጆቹም ሁሉ ጥሩ ወጣቶችና በደንብ የተማሩ ነበሩ፤ ሴት ልጁም እንዲሁ። እርሷ ለብዙ ዓመታት አስተማሪ ሆና ሠርታ ነበር፤ አሁን ግን በላንካስተር የዩኒየን ቤተ ክርስቲያን ፓስተር የነበሩትን ቄስ ሉዊስ ሁድን አግብታ ነበር። ስለዚህ ልቤን ልከፍትላት እንደምችልና እርሷም ልትረዳኝ እንደምትችል አሰብሁ። ስለዚህ «እኅት ሁድ፣ ምን እንደ ሆንሁ አላውቅም። እንዴት እንደ ሆነ አላውቅም፤ አንድ ነገር የምፈልግ ይመስለኛል፤ ምን እንደ ሆነ ግን በትክክል መናገር አልችልም። እጸልያለሁ፤ ነገር ግን እንደምፈልገው ዓይነት እርዳታ አላገኝም» አልኋት።

«ታዲያ» አለች፣ «ምን ሆነሻል? አልተለወጥሽም እንዴ?»

«ኦ! አዎን» አልሁ፣ «እርሱ አይደለም።»

«ታዲያ የመንፈስ ምስክር የለሽም?»

«ኦ! አለኝ፤ እርሱ አይደለም።»

«እንግዲህ» አለች፣ «እንዲህ ከቀጠልሽ ታብጃለሽ።»

በዚህ ጊዜ ፈራሁና እንዲህ አልሁ፦ «ኦ! አልገባትም፤ አሁን ደግሞ ያልሁትን ለማንም ብትነግር አይገባቸውም፤ ወደ ኋላ እንዳፈገፈግሁ ያስባሉ፤ እኔ ደግሞ የክፍል መሪና የሴቶች የጸሎት ስብሰባ መሪ ነኝ።»

ስለዚህ እርሷ እንደ ሄደች ወደ ምድር ቤቱ እየሮጥሁ ወርጄ ተንበረከክሁ፤ እንዳትደግመውም ያልሁትን ሁሉ ከእኅት ሁድ አእምሮ እንዲያወጣው ጌታን ለመንሁ። እጅግ ተጨንቄ ነበር።

ከዚህ ከብዙ ቀናት በኋላ መጽሐፍ ቅዱሴን እያነበብሁ ሳለ ወደ አርባ ሁለተኛው መዝሙር፣ ወደ መጀመሪያው ቁጥር ገለጥሁ፦ «ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደምትናፍቅ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ትናፍቃለች።» ልቤ ዘለለ። «ኦ!» አልሁ፣ «የፈለግሁት ያ ነው — እግዚአብሔርን! አሁን ማንም ሰው እንደ እኅት ሁድ የምፈልገውን ቢጠይቀኝ፣ የፈለግሁት እግዚአብሔርን እንደ ሆነ ልነግረው እችላለሁ።» መጽሐፍ ቅዱሴን ባነበብሁ፣ በጾምሁና በጸለይሁ ቁጥር ረሃቤ እየጠለቀ ሄደ። አንድ ቀን

ወደ ጆርጅ ጄምስ ሄድሁ — ብዙ ጊዜ «አባ ጄምስ» እያልሁ እጠራቸው ነበር — ረጅም፣ በዕድሜ የገፉ፣ በጠባያቸው እጅግ የተከበሩ፣ ግን ደግ ሰው ነበሩ። እጅግ ጥቁር ነበሩ፤ ጠጕራቸው ነጭ ነበር፤ በዚያን ጊዜ እኔ አባል በነበርሁበት በላንካስተር የአፍሪካ ሜቶዲስት ኤጲስ ቆጶሳዊ ቤተ ክርስቲያን (A. M. E.) ዋና የአጥቢያ ሰባኪና ዲያቆን ነበሩ። ስለዚህ ወደ እርሳቸው ሄጄ እንዲህ አልኋቸው፦ «አባ ጄምስ፣ ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስን እያነበብሁ ነበር፤ ይህንም አየሁ፦ ‹ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።› ይህ ምን ማለት ነው?»

«ታውቂያለሽ» አሉ፣ «ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው የቻልሽውን ያህል ወደ እርሱ እንድትቀርቢ ነው። ነገር ግን ‹ልበ ንጹሕ› ፈጽሞ ልትሆኚ እንደማትችዪ እግዚአብሔር ያውቃል።»

ከዚያም በራሳቸው መንገድ ገለጡልኝ። እርግጥ ብዙ ብርሃን አላገኘሁም። ነገሩን ሁሉ እያሰላሰልሁ ወደ ቤት ስሄድም ዲያብሎስ «ለአንቺ ያልሆነን ነገር ትፈልጊያለሽ» አለኝ።

«እንግዲህ» አልሁ፣ «ሰዎች ይህን በረከት ያገኛሉ። ጆብ ሞሪስ፣ ፖሊ ዋተርስና ሌሎችም አሉ፤ የተቀደሱ እንደ ሆኑ ይናገራሉ፤ ሁሉም ያምናቸዋል።»

«ኦ! እነርሱ ግን ሊሞቱ የተቃረቡ ናቸው። አንቺ ግን ወጣት ነሽ፤ እነርሱ ያላቸውን ልታገኚ መጠበቅ አትችዪም።»

«እንግዲህ ምናልባት እንዲያ ይሆናል» አልሁ።

«ደግሞም ታውቂያለሽ፣ አባ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ማለቱ አይደለም ብለዋል።» ሆኖም እንደምንም የተሻለው ማስተዋሌ ተሳስተዋል አለኝ። «መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን አምናለሁ፤ ይህ ጸጋ የሚገኝበት አንድ መንገድ መኖር አለበት፤ አለዚያ እግዚአብሔር ፈጽሞ ጽፎ ባላስቀመጠው ነበር።» ነገር ግን እንዴት እንደምይዘው አሁንም አላወቅሁም። መጽሐፍ ቅዱሴን አነብ፣ እጸልይ፣ መጸለዬንም እቀጥል ነበር። ብርሃን የለም — ጥልቁ ረሃብ ብቻ። እርግጥ ግዴታዬን በመፈጸም መጽናናት ነበረኝ — የክፍል ስብሰባዬንና የጸሎት ስብሰባዎችን እካፈል ነበር፤ እየዞርሁም ከበሽተኞችና ከሚሞቱ ሰዎች ጋር እጸልይ፣ በመነቃቃት ስብሰባዎች እሠራ፣ በቻልሁትም መንገድ ሁሉ አገለግል ነበር። ቀኑን ሙሉ በትጋት ከሠራሁ በኋላ ብዙ ጊዜ እኩለ ሌሊት ወይም ከሌሊቱ በሰባት ሰዓት ታምሞ ወይም እየሞተ ካለ ሰው ጋር እንድጸልይ እጠራ ነበር። ዝናብም ሆነ ፀሐይ፣ ብርድም ሆነ ሙቀት ለመሄድ ፈጽሞ እምቢ አላልሁም፤ ግዴታዬ እንደ ሆነ ይሰማኝ ነበር፤ ሁልጊዜም ይህን በማድረጌ ደስ ይለኝ ነበር። ከዚያም ወደ ቤት እመለስ ነበር — አንዳንድ ጊዜ ከሌሊቱ በዘጠኝ ሰዓት — በጣም ጥቂት እተኛለሁ፤ በሚቀጥለው ጠዋት ቤት ውስጥ ሥራ ከሌለኝ ተነሥቼ እንደ ገና ወደ ሥራ እሄድ ነበር። መብሌና መጠጤ ነፍሳት ወደ ክርስቶስ ሲመጡ ማየት ነበር። ወደ ጉባኤ ገብቼ ወንዶችንም ሴቶችንም፣ ወጣቶችንም ሽማግሌዎችንም ለማነጋገር ፍርሃት አልነበረኝም። በልዩ ስብሰባዎች ጊዜ በጉባኤ

ውስጥ ያሉ ሰዎችን ቀርቤ ሳነጋግር ወደ ፊት ሳይወጡ የቀሩበት ጊዜ እምብዛም አልነበረም፤ ብዙዎቹም ተለወጡ። እግዚአብሔር ለዘላለም ይመስገን!

ያም ሆኖ አንዳንድ ጊዜ መንፈሴ ይዋልል ነበር። አንዳንድ ጊዜ በተራራው ላይ ከፍ ብዬ እሆን ነበር። የተሰማኝን ተመስጦና ደስታ ስናገር አንዳንድ ጊዜ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እኅቶች «አዬ ልጄ፣ እኔም መጀመሪያ እንደ ተለወጥሁ እንዲሁ ነበርሁ፤ ነገር ግን ዲያብሎስ ጥቂት ቦምቦችን እስኪተኩስብሽ ድረስ ቆይ፤ ያን ጊዜ ይህን ያህል ደስታ አይኖርሽም» ይሉኝ ነበር። ምስኪኗ እኔ! እነዚህን ቦምቦች በጥንቃቄ ለመጠበቅ ሞከርሁ። ኦ! ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ስለ ዘይትም ምድር፣ የካሌብና የኢያሱ አምላክም ብቻ በእርሱ ብታመን ሊያስገባኝ እንደሚችልና እንደሚያስገባኝም ለምን አልነገሩኝም? ነገር ግን ውድ ነፍሳት፣ እነርሱ ራሳቸው አያውቁትም ነበርና ሊረዱኝ አልቻሉም። ስለዚህ አንድ ቀን ሄጄ ከአባ ጄምስ ጋር መነጋገር እንዳለብኝ ተሰማኝ፤ የሁለተኛ ተሰሎንቄን አራተኛ ምዕራፍ ሦስተኛ ቁጥር አንብቤ ነበርና፦ «ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና።» ስለዚህ «አባ ጄምስ፣ ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስን እያነበብሁ ነበር፤ ይህንም አየሁ» አልሁ። ከዚያም ጥቅሱን ጠቀስሁላቸው።

«ኦ!» አሉ፣ «ልጄ፣ ሰዎች እጅግ ደስ ብሏቸው ሲሞቱ አታውቂም?»

«አዎን» አልሁ።

«እንግዲህ ታውቂያለሽ፣ እግዚአብሔር የሚቀድስሽ ልትሞቺ ስትቃረቢ ብቻ ነው። እርግጥ ቅድስት ካልሆንሽ ወደ ሰማይ መሄድ አትችዪም፤ መቀደስ ደግሞ ቅድስት ያደርግሻል፤ ቅድስት ብትሆኚ ደግሞ በዚህ ኃጢአተኛ ዓለም መኖር አትችዪም። ስለዚህ ብትቀደሺ ትሞቻለሽ።»

«አዎን» አልሁ። «እንግዲህ የሚገድለኝ ከሆነ አልፈልገውም። መሞት አልፈልግም። ጌታ ብዙ ነገር አድርጎልኛል። እኔም ለእርሱ ጥቂት ማድረግ እችላለሁ፤ ስለዚህ የምችለውን ሁሉ እያደረግሁ እቀጥላለሁ።» ስለዚህ ቀጠልሁ።

ከዚህ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የማቴዎስን አምስተኛ ምዕራፍ እያነበብሁ ሳለ አሥራ አንደኛውና አሥራ ሁለተኛው ቁጥር ላይ ስደርስ እንዲህ አልሁ፦ «የእኔ ልምምድ ከዚህ አይደርስም፦ ‹ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።› ‹ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ።› ማንም በውሸት ሲያወራብኝ ደስ ሊለኝ አይችልም፤ ምንም ፋይዳ የለውም፤ አልችልም።» ከዚያም መልካም ሥራዎቼ ሁሉ ትዝ አሉኝ። «ወደ ቤተ ክርስቲያን እሄዳለሁ፤ ግዴታዎቼን ሁሉ እፈጽማለሁ፤ በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ እየገባሁ አልዞርም፤ የራሴን ጉዳይ እይዛለሁ፤ ማንም ስለ እኔ እውነት ያልሆነ ነገር ሲናገር ደግሞ ፍትሕ ማግኘት አለብኝ። አልታገሠውም።»

«በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ» የሚለውን ገና አላነበብሁም ነበር። ኦ! ከዚያ ወዲህ ግን እንዴት አድርጌ ተማርሁት! አንድ ቀን እኔ እንደማስበው ከሁሉ የምወዳት ወዳጄ በእኔ ላይ እውነተኛ ውሸት ተናገረች። ብዙ ሁከት አስነሣ። በየአቅጣጫው ይህ ሁሉ ቅዝቃዜ ከየት እንደ መጣ ገረመኝ፤ እውነተኛውን ምክንያት ግን አላወቅሁም። ስለዚህ ሄጄ ሰዎቹን ነገሩ ምን እንደ ሆነ ልጠይቃቸው ቈረጥሁ። ስለዚህ ተንበርክኬ ጌታ ትክክለኛውን መንፈስ እንዲሰጠኝ፣ እንዳልበሳጭ፣ ሰዎቹም እንዳይበሳጩ፣ ነገሩ ምን እንደ ሆነም እንዲነግሩኝ እንዲያደርግ ጸለይሁ። ከዚያም ጠዋት ከሦስት ሰዓት ጥቂት አለፍ ብሎ ተነሣሁ። ከሰዓት በኋላ እስከ ስምንት ሰዓት ገደማ ድረስ ተጓዝሁ፤ ስቆምም ስነሣ ከነበርሁበት ይልቅ ወደ እውነቱ የቀረብሁ አልነበርሁም። መጀመሪያ በጐበኘሁት ቦታ ወዳጄን በስሟ ጠርቼ «እንዲህና እንዲህ ሰምቻለሁ፤ ነገሩ ምንድን ነው ብዬ ልጠይቅሽ መጣሁ» አልኋት።

«እኔ የማውቀው» ብላ መለሰች፣ «ጆን ቢ. ሜሪ ኤስ. አለች ያለውን፣ ሜሪ ኤስ. ደግሞ አንቺ አልሽ ያለችውን፣ አንቺ ደግሞ እኔ አልሁ ያልሽውን፣ እኔ ደግሞ እርሷ አለች ያልሁትን ብቻ ነው» እያለች ቀጠለች።

እንግዲህ ወደ ቀጣዮቹ ሰዎች ሄድሁ። እነርሱም ያንኑ ነገር አሉ፦ «እኔ ስለ ነገሩ የማውቀው፣ እንትና የምትባለው ኣን አንቺ አልሽ ያለችውን፣ አንቺ ደግሞ እርሷ አለች ያልሽውን፣ እርሷ ደግሞ እኔ አልሁ ያለችውን፣ እኔ ደግሞ እነርሱ አሉ ያልሁትን ብቻ ነው» ወዘተ። ዞሬ ሁሉንም ካየሁ በኋላ እጅግ አፍሬና ተማርሬ ወደ ቤት ተመለስሁ። ቤት እንደ ደረስሁ ነጠላዬን አውልቄ ወደ ምድር ቤቱ ወረድሁና ተንበረከክሁ፤ ከባድ ችግሮችን ለመፍታት ሁልጊዜ የምሄደው ወደዚያ ነበር። እንዲህም አልሁ፦ «ኦ! ጌታ ሆይ፣ ብትረዳኝ፣ በሕይወት እስካለሁ ድረስ ሌላ ውሸት ተከትዬ ፈጽሞ አልሄድም።» እግዚአብሔር ይመስገን፤ አንዳንድ ጊዜ ብፈተንም ከዚያ ወዲህ ፈጽሞ እንዲያ አላደረግሁም፤ ጌታ ግን ሁልጊዜ አድኖኛል። ውድ ስሙ ይመስገን! አሜን።

ከዚህ ከጥቂት ወራት በኋላ የጥምቀት ጉዳይ አሳሰበኝ፤ ሙሉ በሙሉ በውኃ ውስጥ ብጠመቅ መንገዱን በተሻለ ለማየት እንደሚረዳኝ አሰብሁ። ስለዚህ ወደ አባ ጄምስ ሄጄ በውኃ ውስጥ ገብቼ መጠመቅ እንደምፈልግ ነገርኋቸው። አባቴና እናቴ የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንደሚያዝዘው ልጆቻቸውን ሁላችንንም አስጠምቀውን ነበር፤ እኔ ግን ለራሴ ራሴ መልስ መስጠት ብችል የተሻለ እንደሚሆን አሰብሁ። ከዚያም እኔ እስከማውቀው ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ሁሉ ብፈጽም፣ ጌታ የምፈልገውን ታላቅ በረከት ሊሰጠኝ ይገደዳል ብዬ አሰብሁ። አባ ጄምስ በዚህ ተስፋ አላስቈረጡኝም፤ እንዲያውም ደግፈውኝ ነበር። ስለዚህ ይህ አሁን በትክክለኛው መንገድ ላይ እንዳለሁ እንዳስብ ረዳኝ። በውኃ ውስጥ መጠመቅ የፈለጉ ሌሎች አራት ወይም አምስት ሰዎችም ነበሩ፤ ስለዚህ እየዞርሁ አየኋቸው፤ በአፍሪካ ሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገለግል የነበረውን ደግ ወንድምና የአጥቢያ ሰባኪ፣ ወንድም

ጆንስ የተባለውን የተቀደሰ ሰው ከፊላዴልፊያ እንዲጠራ ተወሰነ። ከጥቂት ዓመታት በፊት በኮሎምቢያ ታላቅ መነቃቃት ሆኖ ነበር፤ ከተለወጡትም ስድስት ወይም ስምንት ያህሉ መጠመቅ ፈለጉ። ስለዚህ ወደ ፊላዴልፊያ ልከው በዘመኑ ኃይለኛ ሰባኪና በአፍሪካ ሜቶዲስት ኤጲስ ቆጶሳዊ ቤተ ክርስቲያን (A. M. E.) ውስጥ ዋና አገልጋይ የነበሩትን ቄስ ቦብ ኮሊንስን አስመጡ። ወቅቱ የክረምቱ ጽኑ ብርድ ነበር። የሰስኩሃና ወንዝ ሙሉ በሙሉ ቀዝቅዞ በረዶ ሆኖ ነበር፤ በረዶውን ቈረጡ፤ ወንድም ኮሊንስም ስምንቱን፣ እንደማስበው ስምንት ነበሩ፣ አጠመቃቸው። እነርሱም እልል አሉ፤ ዘመሩም። ሰዎች በመቶዎች ሆነው በወንዙ ዳርና በበረዶው ላይ ዙሪያውን ቆመው ነበር። ጊዜው ማለዳ አሥራ ሁለት ሰዓት ነበር። ኦ! እንዴት ያለ ጊዜ ነበር! እርግጥ ባፕቲስቶች ሁሉ በዚያ ያምኑ ነበር፤ እነርሱም ወጥተው ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ አላቸው። በዚያን ጊዜ የእኛ አገልጋይ ቄስ ሳንፎርድ ነበሩ። የሚስታቸው እኅት ሄኒ ጆንሰን በጽኑ ታምማ ነበር፤ እርሷም ተለውጣ ነበር። ነገር ግን ወደ ባፕቲስቶች ታዘነብል ነበር። ስለዚህ ለቤተ ክርስቲያኗ እንድትቀር በዚያ እሑድ ተጠመቀች፤ ከዚያም በኋላ ተፈወሰች፤ ይህም ለብዙዎች ታላቅ ድንቅ ነበር። እኅት ሃሪየት ኤን. ቤከር በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከጠንካራ አባላት አንዷ ነበረች። እርሷም በዚያው የእሑድ ጠዋት ተጠመቀች። ላንካስተር ከኮሎምቢያ አሥራ ሁለት ማይል ብቻ ይርቅ ነበር፤ ስለዚህ እኛም በላንካስተር ያለነው በውኃ ጥምቀት ተለከፍን! በላንካስተር የነበሩት ጥቁሮች ሁሉ ማለት ይቻላል ለሩብ ዓመት ስብሰባ ወደ ኮሎምቢያ ይሄዱ ነበርና። ኦ! የእግዚአብሔር ኃይል በነፍሳት መዳን ሲገለጥ እንዴት አይቻለሁ! በዚያ ዘመን የነበሩት ወንዶችና ሴቶች እንዴት ያሉ የጸሎት ሰዎች ነበሩ! ካንዴስ ዋትሰንን፣ ሳራ ሄንደርሰንን፣ ክሪስ ስቶክስን፣ ሳይመን ሞሪስን፣ ጆን ሞሪስን፣ ጄክ ስናይቭሊንና ሌሎች ብዙዎችን እንዴት አስታውሳለሁ! ነገሩን ሁሉ ሳስብ አሁን እንዴት ፊቴ ይመጣሉ! እነዚህ ሁሉ ግን አልፈዋል፤ ምንም እንኳ እንደ ትናንት ቢመስልም።

ነገር ግን ወደ ታሪኬ ልመለስ። ሰዎቹን ካየሁ በኋላ ወደ አባ ጄምስ ሄጄ ለወንድም ጆንስ ጽፈው ወጪው ምን ያህል እንደሚሆን እንዲጠይቁ ለመንኋቸው። እርሱም ሃያ ዶላርና ከፊላዴልፊያ የመምጫና የመመለሻ የጉዞ ወጪውን እንድንከፍለው መለሰ። ሌሎቹ ቀሪውን ቢሞሉ እኔ የአንድ ወር ደመወዜን፣ ማለትም ስድስት ዶላር፣ ለመክፈል ፈቃደኛ ነበርሁ። ስለዚህ ሊሞክሩ ተስማሙ። ጥቂት ሳምንታት አለፉ፤ ከዚያም ከቡድኑ ዋነኞች አንዷ የነበረችው እኅት ማክስዌል ታመመች፤ ባሏም ወደ ውኃው እንድትገባ አልፈቀደላትም። ወንድም ዊልያምስ ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። እኔ ቀሚሴን አዘጋጅቼ ነበር፤ ሌሎቹ ግን ሁሉም ወደ ኋላ አፈገፈጉ። ከዚያም አባ ጄምስ ታመሙ። ስለዚህ ማርች ወደ ውኃ ለመግባት መጥፎ ወር ስለ ሆነ እስከ ኤፕሪል ወይም ሜይ ብጠብቅ ሥርዓቱን እንደሚፈጽሙ ነገሩኝ። ነገር ግን ወዮ! ምስኪን ሰው! ኤፕሪል መጀመሪያ ገደማ በአልጋቸው አጠገብ ቆሜ ሲሞቱ አየሁ፤ የመጨረሻ ቃላቸውንም ሰማሁ።

ዕለቱ እሑድ ምሽት ነበር፤ ከቤተ ክርስቲያን ከመጣሁ በኋላ ከሚስታቸው ከእኅት ጄምስ ጋር ለመቀመጥ ሄድሁ። ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ወይም አምስት ሰዓት ገደማ ነበር፤ ሽማግሌውም በጸጥታ የተኙ ይመስሉ ነበር። ድንገት ብንን ብለው ሳሉ፤ በጕሮሯቸውም አንድ ነገር እንዳለ ዓይነት ድምፅ አሰሙ። እኔም «አባ ጄምስ፣ ምን ሆኑ? ውኃ መጠጣት ይፈልጋሉ?» አልሁ።

«አይ» አሉ፣ «አንድ ትልቅ ጥቁር ሰው አጠገቤ ቆሞ በእሳት የጋሉ ብረቶችን በጕሮሮዬ የሚሰድድ መሰለኝ።»

ኦ! እንዴት ተስፋ ቈረጥሁ! እርሳቸው እንዳስተማሩኝ ከመሞታቸው ጥቂት ደቂቃዎች በፊት እንዲቀደሱ እፈልግ ነበርና። አሁን ግን ሁሉ አልቆ ነበር፤ ሄጄ የማነጋግረው ማንም አልነበረኝም፤ በጨለማ ውስጥ መንከራተቴን መቀጠል ነበረብኝ። አንዲት የብርሃን ጭላንጭል እንኳ ማየት አልቻልሁም።

ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ ፊላዴልፊያ ሄድሁ። በዚያም ሁለተኛ ባሌን ጄምስ ስሚዝን አገባሁ። በዚያን ጊዜ በረከቱን ለይቼ መፈለጌን ትቼ ነበር፤ እንዲሁም ቀጠልሁ። ከብዙ ዓመታት በኋላ ወደ ኒው ዮርክ ተዛወርን፤ ቀደም ብዬ ከጠቀስኋቸው ከብዙ ተጨማሪ መከራዎች በኋላም ስለ ልብ ንጽሕና አስፈላጊነት እንደ ገና በጥልቅ ተወቀስሁ። ደግሞም በሥራ ልፈልገው ጀመርሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ «እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል» (ዮሐንስ 13:14) የሚለውን አነበብሁ። እርስ በርሳችን ለመረዳዳት ለመጸለይ በአንድ ቡድን የተባበርን አራት እኅቶች ነበርን፤ እኅት ስኮት፣ እኅት ባንግስ፣ እኅት ብራውንና እኔ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚለውን ነገርኋቸው፤ ሁሉም ተስማሙ። የቅድስናን በረከት እየፈለግሁ እንደ ሆነ አልነገርኋቸውም። ከመንገዴ የሚያስወጣኝ ነገር ይናገሩ ይሆናል ብዬ ፈራሁ፤ እጅግ ተርቤም ነበር። ስለዚህ ተዘጋጀሁ፤ አራት ብቻ ስለ ሆንንና እርስ በርሳችን ለመረዳዳት ስለምንሞክር በዚህ ጊዜ አራታችንም በአንድነት መሆናችን ትክክል እንደሚሆን አሰብሁ። አሁን ግን ጌታ ይህ እንዲሆን ስላልፈቀደ አመሰግነዋለሁ፤ ምንም እንኳ እርሱ እንዳይመጡ ይከለክላቸው እንደ ነበር እንደ አሁኑ ያን ጊዜ ባላውቅም። ትንሽ ሕፃን የነበረኝ እኔ ብቻ ነበርሁ። እኅት ባንግስና እኅት ብራውን ቤተሰብ አልነበራቸውም፤ የእኅት ስኮት ልጆች ደግሞ ሁሉም አድገው ነበር። ስለዚህ በየሰኞው ከሰዓት በኋላ መጥተው ቤቴ እንዲሰበሰቡ አደረግሁ። እኅት ስኮት ሁልጊዜ ትመጣ ነበር። እኅት ባንግስ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ትገኛለች፤ እኅት ብራውን ግን አትገኝም። ከዚያም እኅት ብራውን በተገኘች ጊዜ እኅት ባንግስ አትገኝም። ስለዚህ ሁሉም በአንድ ጊዜ ፈጽሞ ተገኝተው አያውቁም። ያም ሆኖ ጸናሁ፤ ሁላችንም በአንድነት ካልሆንን በቀር ይህን የእግር እጥበት አለማድረጉ የተሻለ እንደ ሆነ አሰብሁ። ስለዚህ ለእኅቶቹ ነገርኋቸው፤ እነርሱም አራታችን በአንድነት መሆን እንዳለብን ከእኔ ጋር ተስማሙ። የዚህ ዓይነት ማኅበር

ለማቋቋም አልሞከርንም፤ ነገር ግን እኛ አራታችን ብቻ እርስ በርሳችን ለመረዳዳት ተባበርን። ሦስት ወይም አራት ሳምንታት አልፈው በየጊዜውም ዕቅዳችን ሲከሽፍ፣ ላለማድረግ ወሰንሁ። ስለ ጉዳዩ ጸለይሁ፤ እንዳላደርገውም የተነገረኝ መሰለኝ። ጌታ መዳንን በሥራ ከመፈለግ ስሕተት ያዳነኝ በዚህ መንገድ ነው። ስለ ፍቅራዊ ቸርነቱ፣ ስለ ርኅሩኅ ምሕረቱ፣ ስለ ታላቅ ትዕግሥቱና ቻይነቱም ሁልጊዜ እንዴት አመሰግነዋለሁ! እንዲያ ባልተከለከልሁ ኖሮ ለመቀደስ በውኃ ውስጥ መጠመቅና የእግር እጥበት አስፈላጊ ናቸው እያልሁ ማስተማሬ እንደማይቀር አሁን ይታየኛል፤ ይህም ታላቅ ስሕተት በሆነ ነበር፤ ጌታ ግን ከዚያ አዳነኝ። ስሙ ይመስገን። አሜን።

ቀዳሚ ቀጣይ