ነገር ሁሉ ለበጎ
እጅግ መልካም የሆኑት ነገሮች እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ለበጎ ይሠራሉ

ምዕራፍ 3 · 13 ደቂቃ ንባብ · 17 ደቂቃ ማዳመጥ

እጅግ መልካም የሆኑት ነገሮች እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ለበጎ ይሠራሉ

በመጀመሪያ እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ሰዎች ለበጎ የሚሠሩት ምን ምን ነገሮች እንደ ሆኑ እንመለከታለን፤ በዚህም እጅግ መልካም የሆኑትም እጅግ ክፉ የሆኑትም ነገሮች ለበጎአቸው እንደሚሠሩ እናሳያለን። እጅግ መልካም በሆኑት ነገሮች እንጀምራለን።

1. የእግዚአብሔር ባሕርያት እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ለበጎ ይሠራሉ።

(1). የእግዚአብሔር ኃይል ለበጎ ይሠራል። ክቡር ኃይል ነው (ቆላስይስ 1:11)፤ ለተመረጡትም በጎ ነገር ተሰልፏል።

የእግዚአብሔር ኃይል በመከራ ውስጥ ደግፎ በመያዝ ለበጎ ይሠራል። «ከበታችህም የዘላለም ክንዶች አሉ» (ዘዳግም 33:27)። ዳንኤልን በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ ደግፎ የያዘው ምንድን ነው? ዮናስንስ በዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ? ሦስቱን ዕብራውያንስ በእቶኑ ውስጥ? የእግዚአብሔር ኃይል ብቻ ነው። የተቀጠቀጠ ሸምበቆ ሲያድግና ሲለመልም ማየት አያስደንቅምን? ደካማ ክርስቲያን መከራን መታገሥ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ደስ መሰኘትም እንዴት ይችላል? ሁሉን በሚችለው አምላክ ክንዶች ተደግፎ ነው። «ኃይሌ በድካም ይፈጸማል» (2ኛ ቆሮንቶስ 12:9)።

የእግዚአብሔር ኃይል የሚጐድለንን በመሙላት ስለ እኛ ይሠራል። መንገዶች ሲያልቁ እግዚአብሔር መጽናናትን ይፈጥራል። ለነቢዩ ኤልያስ በቍራዎች አማካይነት ምግብ ያመጣለት እርሱ ለሕዝቡም ምግብን ያመጣላቸዋል። እግዚአብሔር «በማሰሮው ያለውን ዘይት» እንዳይጐድል ሊጠብቅ ይችላል (1ኛ ነገሥት 17:14)። ጌታ በአካዝ የፀሐይ ሰዓት ላይ ፀሐይን አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንድትመለስ አደረገ፤ እንዲሁም ውጫዊ መጽናናታችን እያሽቈለቈለ ፀሐይዋም ልትጠልቅ ስትቃረብ፣ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ መነቃቃትን ያመጣል፤ ፀሐይዋንም ብዙ ደረጃ ወደ ኋላ ይመልሳታል።

የእግዚአብሔር ኃይል ርኵሰታችንን ያሸንፋል። «በደላችንን ይረግጣል» (ሚክያስ 7:19)። ኃጢአትህ ብርቱ ነውን? እግዚአብሔር ኃያል ነው፤ የዚህን ሌዋታን ራስ ይሰብራል። ልብህ ደንድኗልን? እግዚአብሔር ያንን ድንጋይ በክርስቶስ ደም ያቀልጠዋል። «ሁሉን የሚችል አምላክ ልቤን ያለሰልሰዋል» (ኢዮብ 23:16)። እንደ ኢዮሣፍጥ፦ «በሚመጣብን በዚህ በታላቅ ሠራዊት ፊት ኃይል የለንም» ስንል፣ ጌታ ከእኛ ጋር ይወጣል፤ ጦርነታችንንም እንድንዋጋ ይረዳናል። ለእኛ ከአቅም በላይ የሆኑትን የእነዚያን ጎልያድ መሰል ክፉ ምኞቶች ራስ ይቈርጣል።

የእግዚአብሔር ኃይል ጠላቶቻችንን ድል ይነሣል። የጠላቶችን ትዕቢት ያረክሳል፤ መተማመናቸውንም ይሰብራል። «በብረት በትር ትቀጠቅጣቸዋለህ» (መዝሙር 2:9)። በጠላት ውስጥ ቍጣ፣ በዲያብሎስ ውስጥ ክፋት አለ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ኃይል አለ። የክፉዎችን ሠራዊት ሁሉ እንዴት በቀላሉ ሊበትን ይችላል! «አቤቱ፥ መርዳት በአንተ ዘንድ ምንም አይደለም» (2ኛ ዜና መዋዕል 14:11)። የእግዚአብሔር ኃይል ከቤተ ክርስቲያኑ ጎን ነው። «እስራኤል ሆይ፥ ብፁዕ ነህ፤ በእግዚአብሔር የዳንህ ሕዝብ ሆይ፥ እርሱ የረድኤትህ ጋሻ የክብርህም ሰይፍ ነው» (ዘዳግም 33:29)።

(2). የእግዚአብሔር ጥበብ ለበጎ ይሠራል። የእግዚአብሔር ጥበብ የሚያስተምረን የምክር ምንጫችን ነው። እርሱ ኃያል አምላክ እንደ ሆነ ሁሉ፣ እንዲሁ መካርም ነው (ኢሳይያስ 9:6)። ብዙ ጊዜ በጨለማ ውስጥ ነን፤ በተወሳሰቡና አጠራጣሪ በሆኑ ጕዳዮችም የትኛውን መንገድ እንደምንይዝ አናውቅም፤ እዚህ እግዚአብሔር በብርሃን ይገባል። «በዓይኔ እመራሃለሁ» (መዝሙር 32:8)። እዚያ «ዓይን» የተባለው የእግዚአብሔርን ጥበብ ለማመልከት ነው። ቅዱሳን እጅግ አርቀው ከሚያዩት የፖለቲካ ሰዎች ይልቅ አርቀው የሚያዩት ስለ ምንድን ነው? ክፉውን አስቀድመው አይተው ይሰወራሉ፤ የሰይጣንን የማታለያ ክርክሮች ያያሉ። የእግዚአብሔር ጥበብ በፊታቸው የሚሄድና የሚመራቸው የእሳት ዓምድ ነው።

(3). የእግዚአብሔር ቸርነት እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ለበጎ ይሠራል። የእግዚአብሔር ቸርነት እኛን መልካም የሚያደርገን መንገድ ነው። «የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ» (ሮሜ 2:4)። የእግዚአብሔር ቸርነት ልብን አቅልጦ እንባ የሚያደርግ መንፈሳዊ የፀሐይ ጨረር ነው። ነፍስ እንዲህ ትላለች፦ ኦ፣ እግዚአብሔር ለእኔ እንዲህ ቸር ሆኖልኛልን? ይህን ያህል ጊዜ ከሲኦል ታግሦኛልን? ታዲያ ከእንግዲህ መንፈሱን አሳዝናለሁን? በቸርነት ላይ ኃጢአት እሠራለሁን?

የእግዚአብሔር ቸርነት በረከትን ሁሉ የሚያስገባ በመሆኑ ለበጎ ይሠራል። የምንቀበላቸው ሞገሶች ከእግዚአብሔር ቸርነት ምንጭ የሚፈስሱ የብር ጅረቶች ናቸው። ይህ የቸርነት መለኮታዊ ባሕርይ ሁለት ዓይነት በረከቶችን ያስገባል። የጋራ በረከቶች፦ ከእነዚህ ሁሉም ይካፈላሉ፤ ክፉዎችም መልካሞችም፤ ይህ ጣፋጭ ጠል በጽጌረዳ ላይ እንደሚወርድ በኵርንችትም ላይ ይወርዳል። የዘውድ በረከቶች፦ ከእነዚህ የሚካፈሉት እግዚአብሔርን የሚፈሩ ብቻ ናቸው። «በቸርነቱ ዘውድ የሚያቀዳጀን» (መዝሙር 103:4)። እንዲህ የእግዚአብሔር ብፁዓት ባሕርያት ለቅዱሳን ለበጎ ይሠራሉ።

2. የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ለበጎ ይሠራሉ።

የተስፋ ቃሎች በእግዚአብሔር እጅ የተጻፉ የዋስትና ሰነዶች ናቸው፤ ዋስትና መያዝ መልካም አይደለምን? የተስፋ ቃሎች የወንጌል ወተት ናቸው፤ ወተትስ ለሕፃኑ መልካም አይደለምን? «የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋ» ተብለዋል (2ኛ ጴጥሮስ 1:4)። ለመዛል ለተቃረበች ነፍስ እንደ ልብ ማበርቻ ናቸው። የተስፋ ቃሎች በኃይል የተሞሉ ናቸው።

በኃጢአት በደል ሥር ነንን? የተስፋ ቃል አለ፦ «እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር፥ መሓሪና ሞገስ ያለው አምላክ» (ዘጸአት 34:6)፤ በዚህም እግዚአብሔር የከበረ ጥልፍ ልብሱን የሚለብስ ያህል ነው፤ የሚንቀጠቀጡ ምስኪን ኃጢአተኞች ወደ እርሱ እንዲመጡ ለማበረታታትም የወርቅ በትረ መንግሥቱን ይዘረጋል። «እግዚአብሔር፥ መሓሪ»። እግዚአብሔር ከመቅጣት ይልቅ ይቅር ለማለት ይበልጥ ፈቃደኛ ነው። ኃጢአት በእኛ ውስጥ ከሚበዛው ይልቅ ምሕረት በእርሱ ዘንድ ይበልጥ ትበዛለች። ምሕረት ባሕርዩ ነው። ንብ በተፈጥሮዋ ማር ትሰጣለች፤ የምትናደፈው ስትነካካ ብቻ ነው። በደለኛው ኃጢአተኛ «ነገር ግን» ይላል፣ «ምሕረትን ልገባው አልችልም።» ቢሆንም እርሱ ሞገስ ያለው ነው፤ ምሕረትን የሚያሳየው ምሕረት ስለሚገባን ሳይሆን እርሱ በምሕረት ደስ ስለሚለው ነው። ታዲያ ይህ ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ምናልባት ስሜ በይቅርታው ደብዳቤ ውስጥ የለ ይሆናል። «ምሕረትን ለሺህ ትውልድ የሚጠብቅ» ነው፤ የምሕረት ግምጃ ቤት አልተሟጠጠም። እግዚአብሔር ተከማችቶ ያለ ብዙ ሀብት አለው፤ ታዲያ አንተ የልጅ ድርሻህን ለምን አትቀበልም?

በኃጢአት ርኵሰት ሥር ነንን? ለበጎ የሚሠራ የተስፋ ቃል አለ። « ክዳታቸውን እፈውሳለሁ» (ሆሴዕ 14:4)። እግዚአብሔር ምሕረትን ብቻ ሳይሆን ጸጋንም ይሰጣል። መንፈሱንም እንደሚልክ ተስፋ ሰጥቷል (ኢሳይያስ 44:3)፤ መንፈሱም ከሚቀድሰው ባሕርዩ የተነሣ በመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ ዕቃን ከሚያጠራ ውኃ፣ አንዳንድ ጊዜ እህልን ከሚያበጥርና አየርን ከሚያጠራ መንሽ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ማዕድናትን ከሚያነጥር እሳት ጋር ተመስሏል። እንዲሁ የእግዚአብሔር መንፈስ ነፍስን ያነጻታል ይቀድሳታልም፤ ከመለኮት ባሕርይም ተካፋይ ያደርጋታል።

በታላቅ መከራ ውስጥ ነንን? ለበጎአችን የሚሠራ የተስፋ ቃል አለ፦ «በመከራው ጊዜ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ» (መዝሙር 91:15)። እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ መከራ አምጥቶ በዚያ አይተዋቸውም። ከጎናቸው ይቆማል፤ ሲዝሉም ራሳቸውንና ልባቸውን ይደግፋል። ሌላም የተስፋ ቃል አለ፦ «በመከራ ጊዜ ኃይላቸው እርሱ ነው» (መዝሙር 37:39)። ነፍስ «ኦ!» ብላ፣ «በፈተና ቀን እዝላለሁ» ትላለች። እግዚአብሔር ግን የልባችን ኃይል ይሆናል፤ ኃይሉን ከእኛ ጋር ያስተባብራል። ወይ እጁን ያቀልልናል፣ ወይም እምነታችንን ያበረታል።

ውጫዊ እጦትን እንፈራለንን? የተስፋ ቃል አለ። «እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ግን ከመልካም ነገር ሁሉ አይጐድሉም» (መዝሙር 34:10)። ለእኛ መልካም ከሆነ እናገኘዋለን፤ ለእኛ መልካም ካልሆነ ግን መከልከሉ መልካም ነው። «እንጀራህንና ውኃህን እባርካለሁ» (ዘጸአት 23:25)። ይህ በረከት በቅጠል ላይ እንደሚወርድ የማር ጠል ይወርዳል፤ ያለንን ያችን ጥቂት ነገር ያጣፍጣታል። በረከቱን እስካገኘሁ ድረስ የአደን ሥጋው ቢቀርብኝ ግድ የለኝም። ነገር ግን መተዳደሪያ እንዳላገኝ እፈራለሁን? ያንን የመጽሐፍ ክፍል አንብብ፦ «ጐበዝ ነበርሁ አሁንም ሸመገልሁ፤ ጻድቅ ሲጣል ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም» (መዝሙር 37:25)። ይህን እንዴት እንረዳዋለን? ዳዊት ይህን የሚናገረው የራሱ ምልከታ አድርጎ ነው፤ እንዲህ ያለ ግርዶሽ ከቶ አላየም፤ በአፉ የሚያደርገው ቍራሽ እንጀራ እስኪያጣ ድረስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንዲህ ዝቅ ሲል አላየም። ዳዊት ጻድቃንና ዘራቸው ሲቸገሩ ከቶ አላየም። ጌታ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ወላጆችን ለጊዜው በእጦት ሊፈትናቸው ቢችልም፣ ዘራቸውን ግን ደግሞ አይፈትንም፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ዘር የሚያስፈልገውን ያገኛል። ዳዊት ጻድቁ እንጀራ ሲለምንና ሲጣል ከቶ አላየም። ወደ ታላቅ ጭንቀት ሊወርድ ቢችልም አይጣልም፤ አሁንም የመንግሥተ ሰማያት ወራሽ ነው፤ እግዚአብሔርም ይወደዋል።

ጥያቄ፦ የተስፋ ቃሎች ለበጎ የሚሠሩት እንዴት ነው?

መልስ፦ ለእምነት ምግብ ናቸው፤ እምነትን የሚያበረታ ነገርም ለበጎ ይሠራል። የተስፋ ቃሎች የእምነት ወተት ናቸው፤ ሕፃን ከጡት እንደሚጠባ እምነትም ከእነርሱ ምግብን ትጠባለች። «ያዕቆብም እጅግ ፈራ» (ዘፍጥረት 32:7)። መንፈሱ ሊዝል ተቃርቦ ነበር፤ አሁን ወደ ተስፋው ቃል ሄደ፦ «አቤቱ፥ መልካም እንደምታደርግልኝ ተናግረሃል» (ዘፍጥረት 32:12)። ይህ የተስፋ ቃል ምግቡ ነበረ። ከዚህ የተስፋ ቃል እጅግ ብዙ ብርታት ስላገኘ ሌሊቱን ሁሉ ከጌታ ጋር በጸሎት ሊታገል ቻለ፤ እስኪባርከውም ድረስ አልለቀውም።

የተስፋ ቃሎች ደግሞ የደስታ ምንጮች ናቸው። በዓለም ውስጥ ካለው ከሚያስጨንቀው ነገር ይልቅ በተስፋ ቃሎች ውስጥ ያለው የሚያጽናናው ነገር ይበዛል። ኡርሲኑስ፦ «ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም» በሚለው የተስፋ ቃል ተጽናና (ዮሐንስ 10:29)። የተስፋ ቃሎች በድካም ጊዜ የልብ ማበርቻ ናቸው። «ቃልህ ተድላዬ ባይሆን ኖሮ በመከራዬ በጠፋሁ ነበር» (መዝሙር 119:92)። የተስፋ ቃሎች ልብ በጥልቅ የጭንቀት ውኃ ውስጥ እንዳይሰጥም ደግፈው እንደሚያንሳፍፉ የመረብ ቡሾች ናቸው።

3. የእግዚአብሔር ምሕረቶች እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ለበጎ ይሠራሉ።

የእግዚአብሔር ምሕረቶች ትሑት ያደርጋሉ። «ንጉሡ ዳዊትም ገብቶ በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጠ፥ እንዲህም አለ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እስከዚህ ድረስ ያመጣኸኝ እኔ ማን ነኝ? የአባቴስ ቤት ምንድን ነው?» (2ኛ ሳሙኤል 7:18)። አቤቱ፥ ንጉሥ እሆን ዘንድ ይህ ክብር ለምን ተሰጠኝ? በጎችን እከተል የነበርሁ እኔ በሕዝብህ ፊት እገባና እወጣ ዘንድ? እንዲሁ ጸጋ ያለው ልብ እንዲህ ይላል፦ «አቤቱ፥ ከሌሎች ይልቅ ለእኔ መልካም ይሆንልኝ ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ? ሌሎች የእሬት ጽዋን ብቻ ሳይሆን የደም ጽዋን (ማለትም እስከ ሞት የሚያደርስ መከራን) ሲጠጡ፣ እኔ ከወይኑ ፍሬ እጠጣ ዘንድ? ከእኔ የተሻሉ ሌሎች የጐደሏቸውን እነዚያን ምሕረቶች አገኝ ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ? አቤቱ፥ እጅግ የማልገባ ብሆንም በየዕለቱ አዲስ የምሕረት ማዕበል የሚመጣልኝ ስለ ምንድን ነው?» የእግዚአብሔር ምሕረቶች ኃጢአተኛን ትዕቢተኛ፣ ቅዱስን ግን ትሑት ያደርጋሉ።

የእግዚአብሔር ምሕረቶች በነፍስ ላይ የሚያቀልጥ ተጽእኖ አላቸው፤ በእግዚአብሔር ፍቅር ያቀልጧታል። የእግዚአብሔር ፍርዶች እንድንፈራው ያደርጉናል፤ ምሕረቶቹ ግን እንድንወደው ያደርጉናል። ሳኦል በቸርነት እንዴት ተነካ! ዳዊት በእጁ አግኝቶት ነበር፤ የልብሱን ጫፍ ብቻ ሳይሆን ራሱንም ሊቈርጥ ይችል ነበር፤ ነገር ግን ሕይወቱን አተረፈለት። ይህ ቸርነት የሳኦልን ልብ አቀለጠው። «ልጄ ዳዊት ሆይ፥ ይህ ድምፅህ ነውን? ሳኦልም ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ» (1ኛ ሳሙኤል 24:16)። የእግዚአብሔር ምሕረት እንዲህ ያለ የሚያቀልጥ ተጽእኖ አለው፤ ዓይኖችን የፍቅር እንባ ያስፈስሳቸዋል።

የእግዚአብሔር ምሕረቶች ልብን ፍሬያማ ያደርጋሉ። በእርሻ ላይ ብዙ ወጪ ስታወጣ የተሻለ አዝመራ ይሰጣል። ጸጋ ያላት ነፍስ ጌታን በሀብቷ ታከብራለች። እስራኤል በጌጦቻቸውና በጕትቻዎቻቸው የወርቅ ጥጃ እንደ ሠሩ በምሕረቶቹ እንዲሁ አያደርግም፤ ይልቁንም ሰሎሞን ወደ ግምጃ ቤቱ በገባው ገንዘብ እንዳደረገው ለጌታ ቤተ መቅደስ ይሠራበታል። የምሕረት ወርቃማ ዝናብ ፍሬያማነትን ያመጣል።

የእግዚአብሔር ምሕረቶች ልብን አመስጋኝ ያደርጋሉ። «ስለ ሰጠኝ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምን እመልሳለሁ? የመድኃኒትን ጽዋ እቀበላለሁ» (መዝሙር 116:12-13)። ዳዊት እዚህ የሚያመለክተው የእስራኤልን ሕዝብ ነው፤ እነርሱ በደኅንነት መሥዋዕታቸው ጊዜ ጽዋ በእጃቸው ይዘው ስለ መዳናቸው እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። እያንዳንዱ ምሕረት የነጻ ጸጋ ምጽዋት ነው፤ ይህም ነፍስን በምስጋና ያሰፋታል። መልካም ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ምሕረቶች የሚቀብር መቃብር ሳይሆን ምስጋናውን የሚዘምር ቤተ መቅደስ ነው። አምብሮስ እንደሚለው እያንዳንዱ ወፍ በየወገኑ ለፈጣሪው ምስጋናን የሚዘምር ከሆነ፣ ሕይወቱ በምሕረት የበለጸገና መዓዛ ያገኘ ቅን ልብ ያለው ክርስቲያንማ እንዴት አብልጦ ያመሰግን!

የእግዚአብሔር ምሕረቶች ያነቃቃሉ። ለፍቅር የሚስቡ ማግኔቶች እንደ ሆኑ ሁሉ፣ ለመታዘዝም የሚስሉ መሳያዎች ናቸው። «በሕያዋን ምድር በእግዚአብሔር ፊት እሄዳለሁ» (መዝሙር 116:9)። በረከቶቹን መለስ ብሎ የሚመለከት ሰው ራሱን ለእግዚአብሔር የተገባ ባለ ዕዳ አድርጎ ይመለከታል። ከምሕረት ጣፋጭነት ተነሥቶ መንፈሳዊ ተግባርን በፍጥነት ወደ መፈጸም ያመዛዝናል። ስለ ክርስቶስ ያለውን ይከፍላል ራሱንም ይከፍላል፤ ራሱን ለእግዚአብሔር ይቀድሳል። በሮማውያን ዘንድ አንዱ ሌላውን በቤዛ ሲያወጣ፣ የተቤዠው ከዚያ በኋላ ሊያገለግለው ይገባ ነበር። በምሕረት የተከበበች ነፍስ በእግዚአብሔር አገልግሎት በቅንዓት ትተጋለች።

የእግዚአብሔር ምሕረቶች ለሌሎች ርኅራኄን ያስገኛሉ። ክርስቲያን በዚህ ዓለም ለሌሎች ጊዜያዊ አዳኝ ነው። የተራቡትን ያበላል፤ የተራቈቱትን ያለብሳል፤ ባልቴቶችንና ድሀ አደጎችን በጭንቀታቸው ይጐበኛል፤ በመካከላቸውም የበጎ አድራጎቱን ወርቃማ ዘር ይዘራል። «ደግ ሰው ይራራል፥ ያበድራልም» (መዝሙር 112:5)። ከዛፍ ከርቤ እንደሚንጠባጠብ በጎ አድራጎት ከእርሱ በነጻ ይንጠባጠባል። እንዲህ እግዚአብሔርን ለሚፈሩ የእግዚአብሔር ምሕረቶች ለበጎ ይሠራሉ፤ ወደ ሰማይ የሚያነሡአቸው ክንፎች ናቸው።

መንፈሳዊ ምሕረቶችም ደግሞ ለበጎ ይሠራሉ።

የተሰበከው ቃል ለበጎ ይሠራል። የሕይወት ሽታ ነው፤ ነፍስን የሚለውጥ ቃል ነው፤ ልብን የክርስቶስን መልክ ያስመስለዋል፤ ሙሉ መረዳትንም ያስገኛል። «ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣም» (1ኛ ተሰሎንቄ 1:5)። የመዳን ሰረገላ ነው።

ጸሎት ለበጎ ይሠራል። ጸሎት የልብ ዝንባሌዎችን የሚያራግብ ወናፍ ነው፤ ቅዱሳን ምኞቶችንና የነፍስን ግለት እፍ ብሎ ያቀጣጥላል። ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ኃይል አለው። «እዘዙኝ» (ኢሳይያስ 45:11)። የእግዚአብሔርን የምሕረት ግምጃ ቤት የሚከፍት መክፈቻ ነው። ጸሎት ልብን ለእግዚአብሔር ክፍት፣ ለኃጢአት ግን ዝግ አድርጎ ይጠብቀዋል፤ ልክ የሌለውን የልብ ግለትና የምኞትን እብጠት ያበርዳል። ሉተር አንድ ወዳጁ ፈተና ሊነሣበት ሲጀምር ባስተዋለ ጊዜ ወደ ጸሎት እንዲሸሽ መከረው። ጸሎት ክርስቲያን በጠላቶቹ ላይ የሚተኵሰው ጠመንጃ ነው። ጸሎት የነፍስ ፍቱን መድኃኒት ነው። ጸሎት ምሕረትን ሁሉ ይቀድሳል (1ኛ ጢሞቴዎስ 4:5)። የኀዘን አባራሪ ነው፤ ኀዘንን በማውጣት ልብን ያቀልላል። ሐና ከጸለየች በኋላ «መንገድዋን ሄደች፥ ከዚያም በኋላ አላዘነችም» (1ኛ ሳሙኤል 1:18)። እንዲህ ያሉ ድንቅ ውጤቶች ካሉት እንግዲያስ ለበጎ ይሠራል።

የጌታ እራት ለበጎ ይሠራል። የበጉ የሰርግ እራት ምሳሌ ነው (ራእይ 19:9)፤ በክብር ከክርስቶስ ጋር የሚኖረን የኅብረት መያዣም ነው። የሰቡ ነገሮች ግብዣ ነው፤ ሕይወትን የሚጠብቅና ሞትን የሚከላከል ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይሰጠናል። እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሰዎች ልብ ውስጥ የከበሩ ውጤቶች አሉት። የልብ ዝንባሌዎቻቸውን ያነቃቃል፤ ጸጋዎቻቸውን ያበረታል፤ ርኵሰታቸውን ይገድላል፤ ተስፋቸውን ያድሳል፤ ደስታቸውንም ይጨምራል። ሉተር፦ «የተጨነቀችን ነፍስ ማጽናናት ሙታንን ወደ ሕይወት የማስነሣትን ያህል ታላቅ ሥራ ነው» ይላል፤ ይህም ቢሆን በተባረከው እራት እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ሰዎች ነፍሳት ሊደረግ ይችላል፤ አንዳንድ ጊዜም ይደረጋል።

4. የመንፈስ ጸጋዎች ለበጎ ይሠራሉ።

ብርሃን ለዓይን፣ ጤና ለሥጋ እንደ ሆነ ጸጋ ለነፍስ እንዲሁ ነው። ጸጋ ለነፍስ ልባም ሚስት ለባልዋ እንደምታደርገው ያደርጋል፦ «በሕይወትዋ ዘመን ሁሉ መልካም ታደርግለታለች» (ምሳሌ 31:12)። ጸጋዎች ምንኛ ተወዳዳሪ የሌለው ጥቅም አላቸው! እምነትና ፍርሃት እጅ ለእጅ ተያይዘው ይሄዳሉ። እምነት ልብን ደስተኛ አድርጎ ይጠብቃል፤ ፍርሃት ልብን ቍም ነገረኛ አድርጎ ይጠብቃል። እምነት ልብ በተስፋ መቍረጥ እንዳይሰጥም ይጠብቀዋል፤ ፍርሃት ደግሞ በትምክህት እንዳይንሳፈፍ ይጠብቀዋል። ጸጋዎች ሁሉ ውበታቸውን ያሳያሉ፤ ተስፋ « ራስ ቁር» ነው (1ኛ ተሰሎንቄ 5:8)፤ የዋህነት «ልብስ» ነው (1ኛ ጴጥሮስ 3:4)፤ ፍቅር «የፍጻሜ ማሰሪያ» ነው (ቆላስይስ 3:14)። የቅዱሳን ጸጋዎች የሚከላከሉባቸው የጦር ዕቃዎች፣ ከፍ የሚያደርጓቸው ክንፎች፣ የሚያበለጽጓቸው ዕንቍዎች፣ መዓዛ የሚሰጧቸው ሽቶዎች፣ የሚያስጌጧቸው ከዋክብት፣ የሚያድሷቸውም የልብ ማበርቻዎች ናቸው። ይህ ሁሉ ለበጎ አይሠራምን? ጸጋዎች ለመንግሥተ ሰማያት ማስረጃዎቻችን ናቸው። በሞት ሰዓት ማስረጃዎቻችንን መያዝ መልካም አይደለምን?

5. መላእክት ለቅዱሳን በጎ ነገር ይሠራሉ።

መልካሞቹ መላእክት ለእግዚአብሔር ሕዝብ የፍቅር አገልግሎትን ሁሉ ለማድረግ የተዘጋጁ ናቸው። «ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?» (ዕብራውያን 1:14)። ከቤተ ክርስቲያን አበው አንዳንዶቹ እያንዳንዱ አማኝ ጠባቂ መልአክ አለው የሚል አስተያየት ነበራቸው። ይህ ጕዳይ የጦፈ ክርክር አያስፈልገውም። የመላእክት ሥርዓተ ማዕረግ በሙሉ ለቅዱሳን በጎ ነገር እንደ ተሰማራ ማወቅ ይበቃናል።

መልካሞቹ መላእክት በሕይወት ዘመን ቅዱሳንን ያገለግላሉ። መልአኩ ድንግል ማርያምን አጽናናት (ሉቃስ 1:28)። መላእክት ዳንኤልን እንዳይጐዱት የአንበሶችን አፍ ዘጉ (ዳንኤል 6:22)። ክርስቲያን በዙሪያው የማይታይ የመላእክት ዘብ አለው። «በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል» (መዝሙር 91:11)። መላእክት የቅዱሳን የሕይወት ዘብ ናቸው፤ እንዲያውም የመላእክት አለቆችም ጭምር፦ «የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?» ከፍተኛዎቹ መላእክት ዝቅተኛዎቹን ቅዱሳን ይንከባከባሉ።

መልካሞቹ መላእክት በሞት ጊዜ ያገለግላሉ። መላእክት ቅዱሳንን ለማጽናናት በታመሙበት አልጋ ዙሪያ ይገኛሉ። እግዚአብሔር በመንፈሱ እንደሚያጽናና እንዲሁ በመላእክቱ ያጽናናል። ክርስቶስ በጭንቀቱ ጊዜ በመልአክ ተበረታ (ሉቃስ 22:43)፤ አማኞችም በሞት ጭንቀት እንዲሁ ይበረታሉ፤ የቅዱሳንም እስትንፋስ ሲያልፍ ነፍሳቸው በመላእክት አጀብ ወደ ሰማይ ትወሰዳለች (ሉቃስ 16:22)።

መልካሞቹ መላእክት በፍርድ ቀንም ያገለግላሉ። መላእክት የቅዱሳንን መቃብሮች ይከፍታሉ፤ የክብሩን ሥጋ እንዲመስሉ በሚደረጉበት ጊዜም ወደ ክርስቶስ ፊት ይመሩአቸዋል። «መላእክቱንም … ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ» (ማቴዎስ 24:31)። በፍርድ ቀን መላእክት እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ከጠላቶቻቸው ሁሉ ያገላግሏቸዋል። እዚህ ቅዱሳን በጠላቶች ይሠቃያሉ። «መልካሙን ነገር ስለ ተከተልሁ ጠላቶቼ ሆኑ» (መዝሙር 38:20)። እንግዲህ መላእክት በቅርቡ ለእግዚአብሔር ሕዝብ የዕረፍት ደብዳቤ ይሰጧቸዋል፤ ከጠላቶቻቸውም ሁሉ ነጻ ያወጧቸዋል፦ «እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው፤ እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል» (ማቴዎስ 13:38-42)። በፍርድ ቀን የእግዚአብሔር መላእክት እንክርዳድ የሆኑትን ክፉዎችን ወስደው በነዶ ያስሩአቸዋል፤ ወደ ሲኦል እቶንም ይጥሉአቸዋል፤ ከዚያም በኋላ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ከእንግዲህ በጠላቶች አይታወኩም፤ እንዲህ መልካሞቹ መላእክት ለበጎ ይሠራሉ። የአማኝን ክብርና ማዕረግ እዚህ ተመልከት። የእግዚአብሔር ስም በእርሱ ላይ ተጽፏል (ራእይ 3:12)፤ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ይኖራል (2ኛ ጢሞቴዎስ 1:14)፤ የመላእክትም ዘብ ያጅበዋል።

6. የቅዱሳን ኅብረት ለበጎ ይሠራል።

«ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን» (2ኛ ቆሮንቶስ 1:24)። አንድ ክርስቲያን ከሌላው ጋር መነጋገሩ እርሱን ለማጽናት መንገድ ነው። በቅስት ውስጥ ያሉ ድንጋዮች እርስ በርሳቸው እንደሚደጋገፉ፣ አንድ ክርስቲያን ልምዱን በማካፈል ሌላውን ያሞቀዋል ያነቃቃዋልም። «ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ» (ዕብራውያን 10:24)። በቅዱስ ውይይት ጸጋ እንዴት ይለመልማል! ክርስቲያን በመልካም ንግግሩ የእምነቱ መብራት ይበልጥ እንዲበራ የሚያደርገውን ዘይት በሌላው ላይ ያንጠባጥባል።

7. የክርስቶስ ምልጃ ለበጎ ይሠራል።

ክርስቶስ በግንባሩ ላይ የወርቅ ቅጠል እንዳደረገውና የከበረ ዕጣኑን እንደ ያዘው እንደ አሮን በሰማይ ነው፤ ስለ ሐዋርያት እንደ ጸለየ ሁሉ ስለ አማኞችም ሁሉ ይጸልያል። «ስለ እነዚህም ብቻ አልለምንም፥ በእኔ ስለሚያምኑ ሁሉ ደግሞ እንጂ» (ዮሐንስ 17:20)። ክርስቲያን ደካማ ሲሆንና ለራሱ እንኳ መጸለይ ሲያቅተው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እርሱ ይጸልያል፤ ስለ ሦስት ነገሮችም ይጸልያል። አንደኛ፣ ቅዱሳን ከኃጢአት እንዲጠበቁ (ዮሐንስ 17:15)። «ከክፉ እንድትጠብቃቸው»። በዓለም ውስጥ እንደ ወረርሽኝ ቤት እንኖራለን፤ ክርስቶስ ቅዱሳኑ በዘመኑ በሚተላለፍ ክፋት እንዳይለከፉ ይጸልያል። ሁለተኛ፣ ሕዝቡ በቅድስና እንዲያድጉ። «በእውነትህ ቀድሳቸው» (ዮሐንስ 17:17)። የመንፈስ የማያቋርጥ ብርታት ይኑራቸው፤ በአዲስ ዘይትም ይቀቡ። ሦስተኛ፣ ስለ ክብራቸው፦ «አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ» (ዮሐንስ 17:24)። ቅዱሳን በእቅፉ እስኪሆኑ ድረስ ክርስቶስ አይረካም። በምድር ሳለ ያቀረበው ይህ ጸሎት በሰማይ ለሚያቀርበው ጸሎቱ ቅጂና አብነት ነው። ይህ እንዴት ያለ መጽናናት ነው፤ ሰይጣን ሲፈትን ክርስቶስ ይጸልያል! ይህ ለበጎ ይሠራል።

የክርስቶስ ጸሎት የጸሎታችንን ኃጢአት ያስወግዳል። አምብሮስ እንደሚለው፣ ለአባቱ የአበባ እቅፍ ሊሰጥ የወደደ ሕፃን ወደ አትክልት ቦታ ገብቶ አንዳንድ አበቦችንና አንዳንድ አረሞችን በአንድነት ይለቅማል፤ ወደ እናቱ በመጣ ጊዜ ግን እርስዋ አረሞቹን ለቅማ አውጥታ አበቦቹን ታስራቸዋለች፤ እንዲሁም ለአባቱ ይቀርባል፤ እንዲሁ እኛ ጸሎታችንን ባቀረብን ጊዜ ክርስቶስ መጥቶ አረሞቹን፣ ማለትም የጸሎታችንን ኃጢአት፣ ለቅሞ ያወጣል፤ ለአባቱም ከአበቦች በቀር ምንም አያቀርብም፤ እነርሱም የጣፋጭ ሽታ መዓዛ ናቸው።

8. የቅዱሳን ጸሎቶች እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ለበጎ ይሠራሉ።

ቅዱሳን ስለ ምሥጢራዊው አካል ብልቶች ሁሉ ይጸልያሉ፤ ጸሎታቸውም እጅግ ያሸንፋል። ከሕመም ለመዳን ያሸንፋል፦ «የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል» (ያዕቆብ 5:15)። በጠላቶች ላይ ድል ለማግኘት ያሸንፋል። «ስለ ቀረው ቅሬታ ጸሎትህን አንሣ» (ኢሳይያስ 37:4)። «የእግዚአብሔርም መልአክ ወጥቶ ከአሦራውያን ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ» (ኢሳይያስ 37:36)። ከወኅኒ ለመውጣት ያሸንፋል። «በቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አጥብቆ ይደረግ ነበር። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና … ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ» (የሐዋርያት ሥራ 12:5-7)። መልአኩ ጴጥሮስን ከወኅኒ አወጣው፤ መልአኩን ያመጣው ግን ጸሎት ነበር። ለኃጢአት ይቅርታም ያሸንፋል። «ባሪያዬ ኢዮብም ስለ እናንተ ይጸልያል፤ እርሱንም እቀበላለሁ» (ኢዮብ 42:8)። እንዲህ የቅዱሳን ጸሎቶች ለምሥጢራዊው አካል ለበጎ ይሠራሉ። ይህም ለእግዚአብሔር ልጅ ትንሽ መብት አይደለም፤ ስለ እርሱ የማያቋርጥ የጸሎት ንግድ ይካሄድለታልና። ወደ የትኛውም ስፍራ ሲመጣ እንዲህ ሊል ይችላል፦ «እዚህ አንዳንድ ጸሎት አለኝ፤ እንዲያውም በዓለም ሁሉ ስለ እኔ የሚሠራ የጸሎት ሀብት አለኝ። እኔ ሳልዘጋጅና መንፈሴ ሲደክም፣ ንቁዎችና ሕያዋን የሆኑ ሌሎች ስለ እኔ ይጸልያሉ።» እንዲህ እጅግ መልካም የሆኑት ነገሮች ለእግዚአብሔር ሕዝብ ለበጎ ይሠራሉ።

ምዕራፍ 3 ተጠናቋል

እጅግ መልካም የሆኑት ነገሮች እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ለበጎ ይሠራሉ

ገጽ 1 / 1 · 13 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ