ምዕራፍ 8 · 15 ደቂቃ ንባብ · 20 ደቂቃ ማዳመጥ
በብሪስቶል የአገልግሎት ጅማሬ
1832-1835.
«በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንም»—ለክርስቲያን መንገደኛ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ—አዲስ የመልካም ምልክቶች—የተጠረገው መንገድ—የጠያቂዎች ስብሰባዎች—እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላም—ፍራንኬ፣ «ሞቶም ሳለ ይናገራል»—የዕለት እንጀራ ተሟላ—ለርስቱ የተለየ ወገን።
ኤፕሪል 8። ቲንማውዝ ከእንግዲህ ስፍራዬ እንዳልሆነና እንደምለቅቀው ዛሬ በብርቱ ተሰማኝ። ልገልጸው የምወደው፣ በ1831 ኦገስት ወር በቲንማውዝ ሥራዬ እንደ ተፈጸመና ወደ ሌላ ስፍራ መሄድ እንዳለብኝ በብርቱ ይሰማኝ ጀመር። ጉዳዩን በጥልቀት እንዳስብበት ተመራሁ፤ በመጨረሻም እንዲህ ብዬ ወሰንሁ፤—በአንዳንድ ምክንያቶች ቲንማውዝን መልቀቅ በተፈጥሮዬ ደስ ይለኝ ስለ ነበር ይህ ከእግዚአብሔር ሊሆን አይችልም። ከዚያ በኋላ በዚያ በመቆየቴ ፍጹም ተረጋጋሁ። በ1832 ዓመት መጀመሪያ ቲንማውዝ ስፍራዬ መሆኑን፣ ወይም በአንድ ስፍራ ቆይቼ እንደ እረኛ ከመሥራት ይልቅ ስጦታዬ አማኞችን ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ለመመለስ እየጣርሁ ከስፍራ ወደ ስፍራ መዘዋወር አለመሆኑን እንደገና በብዙ መጠራጠር ጀመርሁ። በቲንማውዝ ባሉት ወንድሞች መካከል ራሴን ለእረኝነት ሥራ መስጠቴን እንድቀጥል የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሆን እንደ ሆነ ለመሞከር ወሰንሁ፤ ከቀድሞው ሁሉ በበለጠ ትጋትና ታማኝነት ራሴን ለዚህ ሥራ ለመስጠት ቻልሁ፤ በእርሱም በእርግጥ እጅግ ታደስሁ ተባረክሁም፤ ከእርሱም በረከቶች ወዲያው ሲገኙ አየሁ። ይህ ተሞክሮዬ ከቀድሞው ሁሉ ይበልጥ በቲንማውዝ የሚያጸናኝ መሰለ። ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን፣ በኤፕሪል 8 ማስታወሻዬ ላይ ያለው ቃል እንደሚያሳየው፣ በዚያ ሥራዬ ተፈጽሟል የሚለው ስሜት ከጊዜ በኋላ ተመልሶ መጣ፤ እየበረታም ሄደ። ከዚህ ጋር የተያያዘ አንድ የሚያስደንቅ ነገር ነበረ። በሄድሁበት ሁሉ ከቲንማውዝ ይልቅ በብዙ ደስታና ኃይል እሰብክ ነበር፤ ወደዚያ መጀመሪያ በሄድሁ ጊዜ ግን ሁኔታው ፍጹም ተቃራኒ ነበር። ደግሞም በሁሉም ስፍራ ማለት ይቻላል ከቲንማውዝ የበለጡ ብዙ አድማጮች ነበሩኝ፤ ሰዎቹም ምግብን ተርበው አገኘኋቸው፤ ይህ ደግሞ በአጠቃላይ ሲታይ በቲንማውዝ ከእንግዲህ እንዲህ አልነበረም።
ኤፕሪል 11። ቲንማውዝ ከእንግዲህ ለብዙ ጊዜ መኖሪያዬ እንደማይሆን እንደገና በብርቱ ተሰማኝ። ኤፕሪል 12። ቲንማውዝ ከእንግዲህ ስፍራዬ አይደለም የሚለው ስሜት አሁንም ይሰማኛል። ኤፕሪል 13። ልሰብክ ሄጄበት ከነበረው ከቶርኪ ስመለስ ከብሪስቶል ከወንድም ክሬክ የተላከ ደብዳቤ አገኘሁ። መጥቼ እንድረዳው ይጋብዘኛል። ከጻፈው እንደምረዳው እንደ ብሪስቶል ያሉ ስፍራዎች ለስጦታዎቼ ይበልጥ የሚስማሙ ይመስለኛል። አቤቱ ጌታ ሆይ፣ አስተምረኝ! ቲንማውዝን በቅርቡ እንደምለቅቅ ዛሬ ከቀድሞው ሁሉ ይበልጥ ተሰማኝ። ነገር ግን ከዚህ ጋር የሥጋ ሽታ ያለው ብዙ ነገር የተያያዘ እንደ ሆነ እሰጋለሁ፤ ይህም ያስፈራኛል። ጌታ ቢፈቅድ በቅርቡ ወደ ብሪስቶል የምሄድ ይመስለኛል። ኤፕሪል 14። የጌታ ፈቃድ መሆኑን በግልጽ ካየሁ እንደምመጣ የገለጽሁበትን ደብዳቤ ለወንድም ክሬክ ጻፍሁ። ቲንማውዝን በቅርቡ እንደምለቅቅ ዛሬ እንደገና እጅግ፣ አዎን ከቀድሞው ሁሉ እጅግ በበለጠ ተሰማኝ።
ኤፕሪል 15። የጌታ ቀን። ዛሬ ምሽት ጊዜ በፈቀደልኝ መጠን ስለ ጌታ ዳግም ምጽአት በሰፊው ሰበክሁ። ይህን ካደረግሁ በኋላ ይህ ትምህርት መጀመሪያ በተቀበልሁት ጊዜ በእኔ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ፣ ይኸውም ለንደንን ትቼ በመላው መንግሥት እንድሰብክ እስከ መወሰን እንዳደረሰኝ ለወንድሞች ነገርኋቸው፤ ነገር ግን ጌታ ለእነዚህ ሁለት ዓመትና ሦስት ወራት በዋናነት በቲንማውዝ እንዳቆየኝ፣ አሁንም ከእነርሱ የምለይበት ጊዜ የቀረበ እንደሚመስለኝ ነገርኋቸው። እንድጠብቃቸው በጠየቁኝ ጊዜ የነገርኋቸውን አሳሰብኋቸው፤ ይኸውም ምንም የተረጋገጠ ቃል ኪዳን ልገባ እንደማልችል፣ ነገር ግን የጌታ ፈቃድ መሆኑን እስካየሁ ድረስ ብቻ ከእነርሱ ጋር እንደምቆይ ነው። ከዚያ በኋላ ብዙ ልቅሶ ሆነ። እኔ ግን አሁን እንደገና በሰላም ነኝ።
ኤፕሪል 16። ዛሬ ጠዋት አሁንም በሰላም ነኝ። ጌታ ቢወስደኝ ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ለወንድሞች በመናገሬ ደስ ብሎኛል። ዛሬ ወደ ዳርትማውዝ ሄድሁ፤ በዚያም ምሽት ላይ ሰበክሁ። ዛሬ አምስት የጸሎት መልሶች አገኘሁ። 1. ትናንት ምሽት ጌታን እንደ ለመንሁት ከሌሊቱ አሥራ አንድ ሰዓት ነቃሁ። 2. ጌታ ውድ ባለቤቴን ታምማበት ከነበረው ሕመም አዳናት። በዚያ ሁኔታ ትቻት መሄድ ቢኖርብኝ ኖሮ ያስጨንቀኝ ነበር። 3. ጌታ ገንዘብ ላከልን። 4. በቲንማውዝ በማለፍ ብቻ በሚሄደው የዳርትማውዝ ሠረገላ ላይ ባዶ ቦታ ተገኘ። 5. ዛሬ ምሽት በስብከቴ ተረዳሁ፤ የራሴም ነፍስ ታደሰች።
ኤፕሪል 21። እዚህ ለአማኞች የማስጠንቀቂያ ቃል ላቀርብ እወዳለሁ። ብዙ ጊዜ የጌታ ሥራ ራሱ ለነፍሳችን ጥቅም እጅግ አስፈላጊ ከሆነው ከእርሱ ጋር ካለው ኅብረት እንዲከለክለን ፈተና ሊሆን ይችላል። በ19ኛው ቀን ዳርትማውዝን ትቼ ወጣሁ፤ በዚያ ቀን ብዙ ተነጋገርሁ፣ ምሽት ላይ ሰበክሁ፣ ከዚያም ስምንት ማይል በእግር ሄድሁ፣ አምስት ሰዓት ያህል ብቻ ተኛሁ፣ በማግሥቱ እንደገና ሃያ አምስት ማይል ተጓዝሁ፣ ሁለት ጊዜ ሰበክሁ፣ በተጨማሪም እጅግ ብዙ ተነጋገርሁ፣ ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ተኛሁ፣ ከሌሊቱ አሥራ አንድ ሰዓት በፊትም ተነሣሁ። ይህ ሁሉ ሥጋዬና መንፈሴ ዕረፍት እንደሚያስፈልጋቸው ያሳያል፤ ስለዚህም ለወንድሞቼ ስለ ጌታ ሥራ ግድ የለሽ ብመስልም፣ ለጸሎትና ቃሉን ለማንበብ ብዙ ጸጥ ያለ ጊዜ ሊኖረኝ ይገባ ነበር፤ በተለይም በዚያ ቀን ረጅም ጉዞ ከፊቴ ስለ ነበረና ራሱ ብዙ ጸሎት ወደሚያስፈልገው ወደ ብሪስቶል ስለምሄድ ነው። ይልቁንም ለጥቂት ደቂቃዎች በግሌ ከጸለይሁ በኋላ ወደ ጸሎት ስብሰባው ቸኮልሁ። ነገር ግን የሕዝብ ጸሎት በእልፍኝ የሚደረገውን ኅብረት እንደሚተካ ማንም አያስብ። ደግሞም ከዚያ በኋላ፣ ከተወደዱ ወንድሞችና እኅቶች ኅብረት በግድ እንደሚባል ራሴን ለይቼ ከጌታ ጋር የግል ኅብረት እንደሚያስፈልገኝ በመንገር ለጌታ ምስክርነቴን መስጠት በተገባኝ ጊዜ (በእርግጥም ልሰጣቸው የምችለው ምርጥ ምስክርነት ይሆን ነበር)፣ ይህን አላደረግሁም፤ ነገር ግን ሠረገላው እስኪመጣ ድረስ ከእነርሱ ጋር በመጨዋወት ጊዜዬን አሳለፍሁ። አሁን በዚያ ጠዋት ከእኔ ጋር ለነበሩት በአንዳንድ መንገድ ምንም ያህል ጠቃሚ ሆኖ ቢሆንም፣ የራሴ ነፍስ ግን ምግብ ያስፈልጋት ነበር፤ ስላላገኘችውም ከሳሁ፤ ውጤቱንም ቀኑን ሙሉ ተሰማኝ፤ ስለዚህም በሠረገላው ላይ ዲዳ የሆንሁት፣ ለክርስቶስም አንዲት ቃል ያልተናገርሁት፣ ኪሶቼን ሆን ብዬ በበራሪ ጽሑፎች ሞልቼ ሳለ አንዲት እንኳ ያልሰጠሁት ከዚህ የተነሣ እንደ ሆነ አምናለሁ።
ኤፕሪል 22። ዛሬ ጠዋት በብሪስቶል በጌዴዎን ቤተ ጸሎት ሰበክሁ። ከሰዓት በኋላ በፒቴይ ቤተ ጸሎት ሰበክሁ። ይህ ስብከት ለብዙ፣ ብዙ ነፍሳት በረከት ሆነ፤ ብዙዎችም በእርሱ ምክንያት ከዚያ በኋላ ወንድም ክሬክንና እኔን ለመስማት መጡ። ከእነዚህም መካከል የታወቀ ሰካራም የነበረውን አንድ ወጣት ለመለወጥ ምክንያት ሆነ፤ ይህ ወጣት እንደገና ወደ መጠጥ ቤት እየሄደ ሳለ አንድ የሚያውቀው ሰው አግኝቶት አንድ የውጭ አገር ሰው ሲሰብክ ለመስማት አብሮት እንዲሄድ ጠየቀው። እንዲሁ አደረገ፤ ከዚያችም ቅጽበት ጀምሮ ፈጽሞ ስለ ተለወጠ ዳግመኛ ወደ መጠጥ ቤት አልሄደም፤ ሚስቱም እንደ ነገረችኝ ከዚያ በኋላ በጌታ እጅግ ደስተኛ ስለ ነበር ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብ ካለው ጉጉት የተነሣ ብዙ ጊዜ ራቱን ይተው ነበር። ከአምስት ወር ገደማ በኋላ ሞተ። ዛሬ ምሽት ወንድም ክሬክ ሲሰብክ በመስማቴ ብዙ ተማርሁ። ጌታ እንድሠራበት የሚፈልገው ስፍራ ብሪስቶል እንደ ሆነ አሁን ፈጽሞ ተረድቻለሁ።
ኤፕሪል 27። እዚህ በምናየው ነገር ሳንነካ በጸጥታ ስለ እኛ የጌታን ፈቃድ ይበልጥ እንድንመረምር በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ቤት እንድንሄድ የጌታ ፈቃድ እንደ ሆነ ለወንድም ክሬክና ለእኔ ይመስለናል። በተለይም እንድንቆይ የሚፈልጉትን ብቻ በምናይበት እዚህ በብሪስቶል ሳይሆን፣ እንባቸውን በምናይባቸውና ከእነርሱ ጋር እንድንቆይ ልመናቸውን በምንሰማባቸው በዴቨንሻየር ባሉ ወንድሞችና እኅቶች መካከል ትክክለኛ ውሳኔ ላይ የመድረሳችን ዕድል እጅግ የላቀ እንደ ሆነ ይታየናል።
ኤፕሪል 28። ስለ ብሪስቶል ለመጸለይ ጸጥ ያለ ጊዜ እንዲኖረን ሁለታችንም በቅርቡ መሄዳችን አሁንም የጌታ ፈቃድ መስሎ ይታየናል። ኤፕሪል 29። ዛሬ ጠዋት ከራእይ 3፥14-22 ሰበክሁ። በኋላ እንደ ታየው፣ በራሴ ነፍስ ደስታ ቢጎድለኝም ያ ምስክርነት ለብዙዎች በረከት ሆነ። ዛሬ ከሰዓት በኋላ ወንድም ክሬክ ለቤተ ጸሎት በተዘጋጀች ክሊፍተን አርክ በምትባል መርከብ ውስጥ ሰበከ። ምሽት ላይ እኔ በዚያችው መርከብ ሰበክሁ። እግዚአብሔር እነዚህንም ምስክርነቶች እጅግ አከበራቸው፤ ያን ጊዜ የሰሙንን ብዙዎች ከዚያ በኋላ ወደ መሰብሰቢያ ስፍራዎቻችን ለማምጣትም ምክንያት አደረጋቸው። እግዚአብሔር እንዴት ከእኛ ጋር ነበረ፣ እንዴትስ ረዳን፤ በዚህም ወደዚህች ከተማ የላከን ራሱ እንደ ሆነ በግልጽ አሳየ!
ኤፕሪል 30። ከውድ የእግዚአብሔር ልጆች መሰናበት እጅግ ልብ የሚነካ ነበር፤ በደርዘን የሚቆጠሩ በቶሎ እንድንመለስ አጥብቀው ለመኑን፤ የብዙዎቹም ዓይኖች እንባ ሞልተው ነበር። ጌታ ለአገልግሎታችን የሰጠው በረከት እጅግ ታላቅ ይመስላል። በምን ሁኔታ እንደሆነ ባናይም ወደዚህ መምጣት ፍጹም የጌታ ፈቃድ እንደ ሆነ ሁለታችንም እናያለን። አንድ ወንድም ቤተ ሳይዳ ቤተ ጸሎትን ሊከራይልንና ለኪራዩ ክፍያ ኃላፊ ሊሆን ቃል ገብቷል፤ እንዲሁ ሁለት ትላልቅ ቤተ ጸሎቶች ይኖሩናል። ዛሬ እንደገና ስብከቴ በረከት የሆነባቸውን ሁለት አጋጣሚዎች አየሁ።
ሜይ 1። ወንድም ክሬክና እኔ ዛሬ ጠዋት ወደ ዴቨንሻየር ሄድን።
ሜይ 3። ዛሬ ከወንድሞች ብዙዎቹን አየሁ፤ ወደ ብሪስቶል መሄዴ የጌታ ፈቃድ እንደ ሆነ ፍጹም ስለ ተረዳሁ ይህንኑ ነገርኋቸው። ዛሬ ምሽት ከሦስቱ ዲያቆናት ጋር ስብሰባ አደረግሁ፤ ስለ ጉዳዩም በግልጽ ነገርኋቸው፤ በዚህ ጉዳይ በእኔ ላይ ስሕተት ቢያዩ እንዲነግሩኝ ጠየቅኋቸው። የሚቃወሙት ነገር አልነበራቸውም፤ አዎን፣ እንድቆይ እጅግ ቢፈልጉም መሄዴ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ራሳቸው ተረዱ።
ሜይ 5። ቲንማውዝን መልቀቄ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ለአእምሮዬ ሌላው ግልጽ ማስረጃ፣ አንዳንድ በእውነት መንፈሳውያን የሆኑ አማኞች እንድቆይ እጅግ ቢፈልጉም ወደ ብሪስቶል መሄድ እንዳለብኝ ራሳቸው ማየታቸው ነው።
ሜይ 7። ሜይ 5 ቀን ከብሪስቶል ደብዳቤ ስለ ደረሰን፣ ጉዳዩ ከእርሱ ካልሆነ ጌታ መሄዳችንን የሚከለክልበት ሌላ አጋጣሚ እንዲያገኝ ዛሬ በሚያስችል መንገድ መልስ ተሰጠው።
ሜይ 15። ስለ ብሪስቶል በጸሎት ላይ ሳለሁ ወደ ወንድም ክሬክ እንድመጣ ተጠራሁ። ከብሪስቶል ሁለት ደብዳቤዎች ደርሰው ነበር። በጌዴዎን የሚሰበሰቡት ወንድሞች ባቀረብናቸው ቅድመ ሁኔታዎች ለመምጣት ያቀረብነውን ሐሳብ ተቀበሉ፤ ይኸውም ለጊዜው በምንም የተወሰነ የእረኝነት ግንኙነት ሳይሆን በመካከላቸው የምናገለግል ብቻ አድርገው እንዲቆጥሩን፣ ስለዚህም እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ ነው ብለን በምናምነው መንገድ እንድንሰብክ፣ በመካከላቸው ያሉትን ደንቦች ሳንመለከት፤ የወንበር ኪራዮች እንዲቀሩ፤ ሥጋዊ ፍላጎቶቻችንን በተመለከተም በዴቨንሻየር እንደ ነበረው እንድንቀጥል ነው። ስለ ቤተ ሳይዳ ቤተ ጸሎት ምንም የተወሰነ ነገር ባይኖርም፣ ጌታ ቢፈቅድ በአንድ ሳምንት ገደማ ውስጥ ለመሄድ አስበናል።
ሜይ 21። ዛሬ በቲንማውዝ ያሉትን ወንድሞች እያንዳንዳቸውን እየጎበኘሁ መሰናበት ጀመርሁ። አስጨናቂ ቀን ነበር። በቅዱሳኑ ዘንድ ብዙ ልቅሶ ሆነ። ወደ ብሪስቶል መሄዳችን የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ሆነ ፍጹም ባልተረዳ ኖሮ ልሸከመው ባልቻልሁም ነበር።
ሜይ 22። በቲንማውዝ ያሉ ወንድሞች በቅርቡ እንደምንመለስ እንደሚጠብቁ ይናገራሉ። እግዚአብሔር ከልጆቹ ጋር የሚያደርገውን አያያዝ እስከምረዳው ድረስ ይህ የማይመስል ነው። ወደ ምሽት ገደማ ጌታ ከተደጋገመ ጸሎት በኋላ ለመጨረሻው የምክር ቃል ቆላስይስ 1፥21-23ን ሰጠኝ። ስለ ራሴ በተቻለ መጠን ጥቂት፣ ስለ ክርስቶስ ደግሞ በተቻለ መጠን ብዙ መናገር የተሻለ መሰለኝ። ስለ መለያየታችን እምብዛም አልጠቀስሁም፤ በመዝጊያው ጸሎትም ራሴንና ወንድሞችን ለጌታ አደራ መስጠት ብቻ ነበር። የመለያየቱ ትዕይንቶች እጅግ አስጨናቂ ናቸው፤ ነገር ግን መለያየቱ ከጌታ እንደ ሆነ ፍጹም አምናለሁ። ሜይ 23። ባለቤቴ፣ አማቴ ሚስተር ግሮቭስ፣ እና እኔ ዛሬ ጠዋት ወደ ኤክሰተር ሄድን። ውድ ወንድም ክሬክ ነገ ሊከተለን አስቧል።
ቲንማውዝን ከመልቀቃችን ጥቂት ቀደም ብሎ ሳናስበው አሥራ አምስት ፓውንድ ያህል ተቀብለን ነበር፤ አለዚያ ከመልቀቅ፣ ከመጓዝ ወዘተ ጋር የተያያዙትን ወጪዎች ሁሉ መሸፈን ባልቻልን ነበር። በዚህም ደግሞ ጌታ ወደ ብሪስቶል ስለ መሄዳችን ሐሳቡን አሳየ።
ወደ ብሪስቶል መሄዳችን የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ሆነ ስላለኝ እርግጠኝነት የተናገርሁት ምን ያህል በእውነታዎች እንደ ተረጋገጠ የሚከተለው መዝገብ ለሚያምን አንባቢ አሁን ያሳያል።
ሜይ 25 ቀን 1832። ዛሬ ምሽት ብሪስቶል ደረስን። ሜይ 27። ዛሬ ጠዋት በዴቨንሻየር የምትኖር አንዲት እኅት የላከችልንን አንድ ሶቨሪን ተቀበልን፤ ይህንንም ጌታ እዚህም እንደሚያሟላልን እንደ መያዣ እንወስደዋለን። ሜይ 28። የጌዴዎን ቤተ ጸሎትን ሥጋዊ ጉዳዮች የሚያስተዳድሩትን ወንድሞች የወንበር ኪራዮችን ስለ መተው፣ መቀመጫዎቹን ሁሉ ነጻ ስለ ማድረግና የበጎ ፈቃድ መባዎችን በሣጥን ስለ መቀበል ልናነጋግራቸው ስንሄድ—ይህ ጉዳይ ወንድም ክሬክና እኔ እንዳሰብነው በእነርሱ በኩል ሙሉ በሙሉ አልተወሰነም ነበርና—ጌታ ይህን ጉዳይ በቸርነቱ እንዲህ አስተካክሎልን ስለ ነበር ከእነዚህ ወንድሞች በኩል ትንሽ ተቃውሞ እንኳ እንዳልነበረ አገኘን።
ጁን 4። ለብዙ ቀናት ማረፊያ ስንፈልግ ቆይተናል፤ ነገር ግን በበቂ ሁኔታ ቀላልና ርካሽ የሆነ ስላላገኘን ይህንንም የትጋት ጸሎት ጉዳይ እንድናደርገው ተመራን፤ አሁንም ወዲያው ከዚያ በኋላ ጌታ የሚስማማንን ሰጥቶናል። ለሁለት የመቀመጫ ክፍሎችና ለሦስት መኝታ ክፍሎች፣ ለከሰልና ለአገልግሎት በሳምንት አሥራ ስምንት ሺልንግ ብቻ እንከፍላለን። ወንድም ክሬክና እኛ አብረን ስለምንኖር የሚያስፈልጉንን አምስት ክፍሎች በአንድ ቤት ውስጥ የያዘ ርካሽ የቤት ዕቃ የተሟላለት ማረፊያ ማግኘት በተለይ አስቸጋሪ ነበር። ለጸሎት መልስ እንዲህ ስለ እኛ የተገለጠ ጌታ እንዴት ቸር ነው፤ ሁሉንም ነገር በጸሎት ለእርሱ አደራ ለመስጠትስ እንዴት ያለ ማበረታቻ ነው!
ጁን 25። የቤተ ሳይዳን ቤተ ጸሎት ለአንድ ዓመት እንድንይዘው ዛሬ በመጨረሻ ተወሰነ፤ ይኸውም አንድ ወንድም ኪራዩን ወዲያውኑ እንዲከፍል፥ ጌታ በዚያ ስፍራ ድካማችንን ባርኮ አማኞች በኅብረት ቢሰበሰቡ እንዲረዱት እንደሚጠብቅ፥ ይህ ካልሆነ ግን ሁሉንም ራሱ እንደሚከፍል በመስማማት ነው። ጸሎት ቤቱን ልንይዝ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ይህ ነበር፤ ምንም እንኳ ታላቅ የጥቅም ተስፋ ቢኖርበት፥ ጸሎት ቤቱን መያዛችን በማናቸውም መንገድ ባለ ዕዳ ቢያደርገን ኖሮ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ልናስብ አንችልም ነበርና።
ጁላይ 6። ዛሬ በቤተ ሳይዳ ቤተ ጸሎት መስበክ ጀመርን። መልካም ቀን ነበር። ጁላይ 13። ዛሬ በብሪስቶል የመጀመሪያዎቹን የኮሌራ በሽተኞች ወሬ ሰማን። ጁላይ 16። ስለ ነፍሳቸው ሊያነጋግሩን ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር በጸሎት ቤቱ የጎን ክፍል አንድ በአንድ ለመነጋገር ለዛሬ ምሽት ከአሥራ ሁለት ሰዓት እስከ ሦስት ሰዓት ቀጠሮ ይዘን ነበር። ሰዎቹ እጅግ ብዙ ስለ ነበሩ ከአሥራ ሁለት ሰዓት እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ከሃያ ደቂቃ ድረስ ተጠምደን ቆየን።
እነዚህን ስብሰባዎች ኃይላችንና ጊዜያችን እንደ ፈቀደልን ወይም እንደ አስፈላጊነታቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ፥ ወይም በሳምንት አንድ ጊዜ፥ ወይም በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ፥ ወይም በወር አንድ ጊዜ ከዚያ ወዲህ ቀጥለንባቸዋል። በሚከተሉት ነገሮች ጠቃሚ ሆነው አግኝተናቸዋል፦—
1. ብዙ ሰዎች ከዓይን አፋርነት የተነሣ ወደ ቤታችን መጥተው ከሚጠይቁን ይልቅ በተወሰነ ጊዜ ወደ ጎን ክፍሉ መጥተው ከእኛ ጋር መነጋገርን ይመርጣሉ። 2. ስለ ዘላለም ነገሮች በግል ለመነጋገር ሰዎችን የምናይበትን ጊዜ መወሰናችን ራሱ፥ በሰው አስተሳሰብ በሌላ ሁኔታ ፈጽሞ ወደ እኛ የማይመጡትን አንዳንዶችን አምጥቶአል፤ እንዲያውም ስለ እግዚአብሔር ነገር የሚገዳቸው መስሎ ቢታያቸውም ፈጽሞ የማያውቁትን አምጥቶአል፤ በዚህም እነርሱን ለማነጋገር አጋጣሚ አግኝተናል። 3. እነዚህ ስብሰባዎች በሥራው ለራሳችንም ታላቅ ብርታት ሆነውልናል፤ ብዙ ጊዜ እንዲህና እንዲህ ያለው የቃሉ ማብራሪያ ምንም ጥቅም አላመጣም ብለን ስናስብ፥ በእነዚህ ስብሰባዎች አማካይነት ነገሩ በተቃራኒው ሆኖ ተገኝቶአልና፤ እንዲሁም እጆቻችን በደከሙ ጊዜ፥ ጌታ እንደ መሣሪያ ሊጠቀምብን ራሱን ዝቅ ያደረገባቸውን አዳዲስ ምሳሌዎች በእነዚህ ስብሰባዎች ስናይ፥ በጌታ ሥራ ወደ ፊት እንድንገፋና ዘሩን በተስፋ መዝራታችንን እንድንቀጥል እንደ ገና ተበረታተናል፤ በተለይም በዚህ መንገድ አንዳንድ ሰዎች ከጥቂት ወራት በፊት ብቻ ሳይሆን ከሁለት፥ ከሦስትና ከአራት ዓመታት በፊት እንኳ ከአገልግሎታችን ስላገኙት ጥቅም የነገሩን ጊዜያት ነበሩ።
ከላይ ስለ ተጠቀሱት ምክንያቶች ሌሎች የክርስቶስ አገልጋዮችን፥ በተለይም በትልልቅ ከተሞች የሚኖሩትን፥ እንደዚህ ያለውን ዘዴ እስካሁን ካልጀመሩ፥ ጠያቂዎችን የሚያገኙበትን እንዲህ ያለ ጊዜ መለየት ለእነርሱም መልካም ይሆን እንደ ሆነ እንዲያስቡበት በተለይ እመክራቸዋለሁ። ይሁን እንጂ እነዚህ ስብሰባዎች ለሚመጡት ሁሉ እንደየፍላጎታቸው በትክክል መናገር እንዲቻል ብዙ ጸሎት ይሻሉ፤ ሰውም ለእነዚህ ነገሮች በራሱ የበቃ እንዳልሆነ፥ ብቃታችን ግን ከእግዚአብሔር ብቻ እንደ ሆነ ዘወትር እንዲሰማው ይመራል። እነዚህ ስብሰባዎች ከሥራችን ሁሉ እጅግ አድካሚው ክፍል ነበሩ፤ በዚያው ጊዜ ግን እጅግ የሚያድሰውም ነበሩ።
ጁላይ 18። ጸጥ ያለ ጊዜ ለማግኘት ዛሬ ጠዋቱን ሁሉ በጎን ክፍሉ አሳለፍሁ። ከሥራው ብዛት የተነሣ ለጸሎት፥ ቃሉን ለማንበብና ለማሰላሰል ጊዜ እንዲኖረኝ ለማረጋገጥ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ ብቸኛው መንገድ ይህ ሆኖአል። ጁላይ 19። ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት ድረስ በጎን ክፍሉ ቆየሁ፤ ከጌታም ጋር እውነተኛ ኅብረት አደረግሁ። የጎን ክፍሉን የብቻ መሆኛ ስፍራ አድርጌ እንድጠቀምበት በልቤ ያሳደረ ጌታ ይመስገን!
ኦገስት 5። ዛሬ ገንዘባችን ሁሉ ባለቀ ጊዜ ጌታ እንደ ገና በቸርነቱ ጉድለታችንን ሞላ። ኦገስት 6። ዛሬ ከቀኑ ስምንት ሰዓት እስከ ምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ካለፈ በኋላ ድረስ እኔና ወንድም ክሬክ ጠያቂዎችን ለማየት በጎን ክፍሉ ቆየን። በድካማችን ላይ የወረደውን በረከት የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን በማየታችን፥ ጌታ ወደ ብሪስቶል ስለ ላከን እርሱን ለማመስገን የተትረፈረፈ ምክንያት እንደ ገና በፊታችን ቀረበ።
ኦገስት 13። ዛሬ ማታ አንድ ወንድምና አራት እኅቶች በቤተ ሳይዳ ከወንድም ክሬክና ከእኔ ጋር በቤተ ክርስቲያን ኅብረት ተባበሩ፤ ምንም ደንብ ሳይኖረን፥ ጌታ በቃሉ በኩል ብርሃን ሊሰጠን እንደ ወደደ ብቻ ለመሥራት እየተመኘን።
ሴፕቴምበር 17። ዛሬ ጠዋት ጌታ ከሌሎቹ ምሕረቶቹ ሁሉ በተጨማሪ ትንሽ ሴት ልጅ ሰጠን፤ እርስዋም ከእናቷ ጋር ደኅና ናት።
ኦክቶበር 1። ዛሬ ከቀኑ ስምንት እስከ አሥራ አንድ ሰዓት የጠያቂዎች ስብሰባ ነበር። ከእኔ ስብከት ይልቅ በወንድም ክሬክ ስብከት እጅግ ብዙ ሰዎች ስለ ኃጢአት ይወቀሳሉ። ይህ ሁኔታ ምክንያቱን እንድመረምር መራኝ፤ ምክንያቶቹም ምናልባት እነዚህ ናቸው፦ 1. ወንድም ክሬክ ከእኔ ይበልጥ መንፈሳዊ አሳብ ያለው መሆኑ። 2. ስለ ኃጢአተኞች መለወጥ ከእኔ ይበልጥ አጥብቆ የሚጸልይ መሆኑ። 3. በሕዝብ አገልግሎቱ ኃጢአተኞችን እንደ ኃጢአተኞች ከእኔ ይበልጥ ደጋግሞ የሚያነጋግር መሆኑ። ይህም ስለ ኃጢአተኞች መለወጥ አዘውትሬ አጥብቄ እንድጸልይና እንደ ኃጢአተኞች ደጋግሜ እንዳነጋግራቸው መራኝ። ሁለተኛውን ነገር ሆን ብዬ ቸል ብዬው አላውቅም፤ ነገር ግን ወንድም ክሬክን እንደሚያሳስበው ያህል ደጋግሞ ወደ አሳቤ አልመጣም ነበር። ከዚያ ወዲህ ጌታ ለመለወጥ እንደ መሣሪያ ሊጠቀምብኝ የወደደባቸው ጊዜያት ወንድም ክሬክ ከተጠቀመባቸው ያላነሱ ሆነዋል።
ፌብሩዋሪ 9, 1833። የፍራንከን የሕይወት ታሪክ በከፊል አነበብሁ። እርሱ ክርስቶስን እስከ ተከተለበት ድረስ እርሱን እንድከተል ጌታ በቸርነቱ ይርዳኝ። በብሪስቶል የምናውቃቸው አብዛኞቹ የጌታ ሰዎች ድሆች ናቸው፤ ጌታም ይህ ውድ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ኖረ አብልጠን እንድንኖር ጸጋ ቢሰጠን፥ ለድሆች ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ከሰማያዊ አባታችን ባንክ እስካሁን ካደረግነው እጅግ የበለጠ ባወጣን ነበር። ማርች 2። አንድ ሰው በመንገድ ላይ ወደ ወንድም ክሬክ ሮጦ መጥቶ አሥር ሺሊንግ የያዘ ወረቀት በእጁ አስጨበጠውና «ይህ ለአንተና ለሚስተር ሙለር ነው» ብሎ ፈጥኖ ሄደ። ሜይ 28። ዛሬ ጠዋት በክፍሌ ተቀምጬ ሳለሁ የብዙ ወንድሞችና እኅቶች ችግር ወደ አሳቤ መጣ፤ በልቤም «ኦ ጌታ እነርሱን የምረዳበትን ገንዘብ ሊሰጠኝ ቢወድ!» አልሁ። ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ አይቼው ከማላውቀው፥ በዚያን ጊዜም እንደ ዛሬው ብዙ ሺህ ማይል ርቆ ከሚኖር አንድ ወንድም ስድሳ ፓውንድ ተቀበልሁ።
ሜይ 29። በብሪስቶል የድካማችንን ፍሬ በተመለከተ ያለፉት አሥራ ሁለት ወራት ግምገማ፦ 1. በዓመቱ ውስጥ ወደ እኛ የተጨመሩት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር አንድ መቶ ዘጠኝ ነው። 2. በእኛ አማካይነት የተለወጡት፥ ስለ ግለሰቦቹ እስከ ሰማንና ልንፈርድ እስከ ቻልን ድረስ፥ ስድሳ አምስት ናቸው። 3. ወደ ኋላ የተመለሱ ብዙ ሰዎች ተመልሰዋል፤ ብዙ የእግዚአብሔር ልጆችም በእውነት መንገድ ተበረታተዋል፤ ጸንተዋልም።
ጁን 12። ለተወሰነ ጊዜ በየዕለቱ እንጀራ ስንሰጣቸው ለነበሩት ለእነዚያ ድሆች ወንዶችና ሴቶች ልጆች፥ ለጎልማሶችና ለአረጋውያንም ትምህርት ቤት በማቋቋም፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብላቸውና ስለ ጌታ በመንገር ለነፍሳቸው አንድ ነገር ልናደርግ እንደምንችል ዛሬ ጠዋት ተሰማኝ። ይህ ምኞት ተግባራዊ አልሆነም። ዋናው እንቅፋት በዚያው ጊዜ ገደማ በእኔና በወንድም ክሬክ ላይ የመጣው የሥራ ጫና ነበር። ብዙም ሳይቆይ እንጀራ ለመቀበል የሚመጡት ድሆች ቁጥር በቀን ከስድሳ እስከ ሰማንያ ደረሰ፤ ለማኞቹም በመንገድ ላይ በቡድን ተኝተው ስለ ነበር ጎረቤቶቻችን ተቸገሩ፤ በዚህም ምክንያት ከእንግዲህ ለእንጀራ እንዳይመጡ ልንነግራቸው ተገደድን። ይህ አሳብ በመጨረሻ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ተቋም እንዲመሠረትና የሙት ልጆች ማሳደጊያዎች እንዲቋቋሙ ምክንያት ሆነ።
ዲሴምበር 17። ዛሬ ማታ እኔና ወንድም ክሬክ ከአባላቱ አምስቱ በእኛ አማካይነት ወደ ጌታ እውቀት ከመጡለት አንድ ቤተሰብ ጋር ሻይ ጠጣን። በራሳቸው ባልሆነ ቋንቋ ወንጌልን ለመስበክ ለሚመኙ ወንድሞች ማበረታቻ እንዲሆን፥ ከዚህ ቤተሰብ መጀመሪያ የተለወጠችው አባል በትክክል ያልጠራኋቸው አንዳንድ ቃላት ተነግረዋት የውጭ አገር አነጋገሬን ለመስማት በጉጉት ብቻ እንደ መጣች ልጠቅስ እወዳለሁ።
ዲሴምበር 31። ማስታወሻዬን ስመለከት የሚከተለውን አገኘሁ፦—1. ቢያንስ ሁለት መቶ ስድሳ ሰዎች (በጻፍነው የስም ቁጥር መሠረት፤ ነገር ግን ከዚህ የሚበልጡ ብዙ ነበሩ) ስለ ነፍሳቸው ጉዳይ ከእኛ ጋር ለመነጋገር መጥተዋል። ከእነዚህም ውስጥ አንድ መቶ ሃምሳ ሦስቱ በእነዚህ ባለፉት አሥራ ስምንት ወራት በኅብረት ወደ እኛ ተጨምረዋል፤ ከእነርሱም ስድሳው በእኛ አማካይነት ወደ ጌታ እውቀት መጥተዋል።
2. ጌታ በምድራዊ ነገሮች ያደረገልኝን ስመለከት፥ ባለፈው ዓመት ይህን እንደ ላከልኝ አገኛለሁ፦—
1. በሣጥኖቹ በኩል ከገባው የፈቃድ ስጦታ፥ የእኔ ድርሻ £152 14 5¼
2. በገንዘብ የተሰጡኝ ስጦታዎች 25 1 3
3. በልብስና በምግብ የተሰጡ ስጦታዎች፥ ዋጋቸው ቢያንስ 20 0 0
4. አንድ ወንድም ከሩቅ የላከልኝ 60 0 0
5. ያለ ኪራይ እንኖራለን፤ ዋጋውም ለእኛ ድርሻ 10 0 0
£267 15 8¼
ምድራዊ ጉድለቴን እንዲሞላልኝ በጌታ ብቻ መታመን ከጀመርሁ ልክ አሁን አራት ዓመት ሆነኝ። በዚያን ጊዜ የነበረኝን፥ ቢበዛ በዓመት አንድ መቶ ፓውንድ የሚያወጣውን ጥቂት ሀብቴን ሁሉ ለጌታ ብዬ ተውሁት፤ ከአምስት ፓውንድ ገደማ በቀር ምንም አልቀረልኝም ነበር። ጌታ ይህችን ትንሽ መሥዋዕት እጅግ አከበራት፤ በምትኩም የተውሁትን ያህል ብቻ ሳይሆን እጅግ የበለጠ ሰጠኝ። በመጀመሪያው ዓመት ከቤተሰብ በኩል የመጣልኝንም ጨምሮ በአንድም በሌላም መንገድ አንድ መቶ ሠላሳ ፓውንድ ገደማ ላከልኝ። በሁለተኛው ዓመት አንድ መቶ ሃምሳ አንድ ፓውንድ አሥራ ስምንት ሺሊንግና ስምንት ፔንስ። በሦስተኛው ዓመት አንድ መቶ ዘጠና አምስት ፓውንድ ሦስት ሺሊንግ። በዚህ ዓመት ሁለት መቶ ስድሳ ሰባት ፓውንድ አሥራ አምስት ሺሊንግና ስምንት ከሩብ ፔንስ። የሚከተሉት ነጥቦች ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፦ 1. ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት ማንንም ምንም ነገር ለምኜ አላውቅም፤ ነገር ግን በጌታ እርዳታ ጉድለቴን ሁልጊዜ ወደ እርሱ ለማቅረብ ችያለሁ፤ እርሱም ሁሉንም በቸርነቱ ሞልቶልኛል። 2. ገቢዬ በአንጻራዊነት ታላቅ ቢሆንም፥ በእነዚህ በአራቱ ዓመታት በእያንዳንዳቸው መጨረሻ የቀረልኝ ጥቂት ሺሊንግ ብቻ ወይም ምንም ነበር፤ ዛሬም በእግዚአብሔር እርዳታ እንዲሁ ነው። 3. ባለፈው ዓመት የገቢዬ ትልቅ ክፍል ብዙ ሺህ ማይል ርቆ ካለ፥ አይቼው ከማላውቀው ወንድም መጥቶአል። 4. ከጎረቤቶቻችን የተነሣ በየቀኑ ወደ ሃምሳ ለሚጠጉ ድሆች እንጀራ መስጠታችንን ለማቆም ከተገደድን ወዲህ፥ በዚህ ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ ገቢያችን እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ያህል አልነበረም፤ ግማሽ እንኳ አልደረሰም።
ጃንዋሪ 9, 1834። እኔና ወንድም ክሬክ በእነዚህ አሥራ ስምንት ወራት በብሪስቶል አጠገብ ባለችው ብሪስሊንግተን በምትባል መንደር በወር አንድ ጊዜ ሰብከናል፤ ነገር ግን በዚያ የድካማችንን ፍሬ አላየንም። ይህም በዚያ ስፍራ ስላሉት ኃጢአተኞች መለወጥ ዛሬ ወደ ጌታ እጅግ አጥብቄ እንድጸልይ መራኝ። በጸሎት ቤቱም ውስጥ ስለዚሁ እንደ ገና እንድጸልይ በተለይ ተመራሁ፤ ጥቂት ብርታት እንድናገኝም ዛሬ ማታ ቢያንስ አንዲት ነፍስ እንዲለውጥ ጌታን በተለይ ለመንሁት። በብዙ እርዳታ ሰበክሁ፤ ዛሬ ማታም መልካም ነገር እንደ ተደረገ ተስፋ አደርጋለሁ። ጌታም እንደ ልመናዬ አደረገ። አንድ ወጣት ወደ እውነት እውቀት መጣ።
ጃንዋሪ 14። ኦክቶበር 20 ጠዋት የምሰብክበትን ጥቅስ ለመምረጥ በነበረው ችግር እጅግ ተፈትኜ ነበር፤ በመጨረሻም ያለ ደስታ ሰበክሁ። ይህ ስብከት የተባረከበትን ዘጠነኛውን ምሳሌ ዛሬ ሰማሁ።
ጃንዋሪ 31። ዛሬ ማታ ከእኛ ጋር በኅብረት ካሉት እኅቶች መካከል የዶርቃ ማኅበር ተመሠረተ፤ ነገር ግን ወደ ብሪስቶል ስንመጣ ያገኘነው ማኅበር በነበረበት ሁኔታ አይደለም፤ እውነተኛ አማኞች ያልሆኑትን አስተማሪዎች ሁሉ ከሰንበት ትምህርት ቤት እንዳሰናበትን፥ አሁንም ለድሆች ልብስ ለመስፋት የሚሰበሰቡት አማኝ ሴቶች ብቻ ይሆናሉ። ከማያምኑ ጋር መቀላቀል በእኅቶች መካከል ለመንፈሳዊ ንግግር እንቅፋት ከመሆኑም በላይ በብዙ መንገድ ለሁለቱም ወገኖች ጎጂ ሳይሆን አይቀርም። አሁን ከእኛ ጋር በኅብረት የተባበረች አንዲት እኅት፥ ከመለወጧ በፊት ከዶርቃ ማኅበር ጋር መያያዟ በተወሰነ መጠን በሐሰተኛ ዋስትና ውስጥ እንድትቆይ ምክንያት እንደ ሆነ መሰከረች፤ እንደዚህ ያሉትን ነገሮች በመርዳት በመጨረሻ መንግሥተ ሰማያትን ልታገኝ እንደምትችል ታስብ ነበርና። ኦ ቅዱሳን በታማኝ ፍቅር በእግዚአብሔር ቃል መሠረት (2 ቆሮ. 6:14-18) በመንፈሳዊ ነገሮች ሁሉ ከማያምኑ ይበልጥ ቢለዩ፥ ከእነርሱም ጋር በማይመች አካሄድ ባይጠመዱ!