የመታመን ሕይወት
ልጅነትና ወጣትነት

ምዕራፍ 4 · 7 ደቂቃ ንባብ · 9 ደቂቃ ማዳመጥ

ልጅነትና ወጣትነት

1805-1825.

ልደት—የልጅነት ሌብነት—ደንዳናነት—በመንግሥት ቤተ ክርስቲያን መጽናት (ኮንፊርሜሽን)—የሕይወት ብልግና—የበደለኞች መንገድ ጭንቅ ነው—በኖርድሃውዘን የነበረው ጂምናዚየም—የሃሌ ዩኒቨርሲቲ—መንከራተት።

በፕሩሺያ መንግሥት በሃልበርሽታት አቅራቢያ በምትገኘው በክሮፐንሽቴት ሴፕቴምበር 27 ቀን 1805 ተወለድሁ። በጃንዋሪ 1810 ወላጆቼ ከክሮፐንሽቴት 4 ማይል ያህል ወደምትርቀው ወደ ሃይመርስሌበን ተዛወሩ፤ በዚያም አባቴ የቀረጥ ሰብሳቢ ሆኖ ተሾመ።

ልጆቹን በዓለማዊ መርሆች ያሳደገው አባቴ ከዕድሜያችን አንጻር ብዙ ገንዘብ ይሰጠን ነበር። ውጤቱም እኔንና ወንድሜን ወደ ብዙ ኃጢአት መራን። ገና 10 ዓመት ሳይሞላኝ ለአባቴ በአደራ ከተሰጠውና እርሱም ሊተካው ከሚገደደው የመንግሥት ገንዘብ ደጋግሜ እወስድ ነበር፤ በመጨረሻም አንድ ቀን ገንዘብ ደጋግሞ ስለ ጎደለበት፥ የተቈጠረ ገንዘብ እኔ ባለሁበት ክፍል አስቀምጦ ለጥቂት ጊዜ ብቻዬን ትቶኝ ሌብነቴን ደረሰበት። ብቻዬን በቀረሁ ጊዜ ከገንዘቡ ጥቂት ወስጄ በጫማዬ ውስጥ ከእግሬ በታች ደበቅሁት። አባቴ ተመልሶ ገንዘቡን ቈጥሮ ባጣው ጊዜ ተፈተሽሁ፤ ሌብነቴም ተገለጠ።

ዕድሜዬ ከ10 እስከ 11 ዓመት ሳለ ለዩኒቨርሲቲ እንድዘጋጅ ወደ ሃልበርሽታት ተላክሁ፤ አባቴ ቄስ እንድሆን ይፈልግ ነበርና፤ ይህም እግዚአብሔርን እንዳገለግል ሳይሆን የተመቸ ኑሮ እንዳገኝ ነበር። ጊዜዬንም አሁን በማጥናት፥ ልብ ወለድ መጻሕፍትን በማንበብና ገና ልጅ ብሆንም በኃጢአት ልማዶች በመዘፈቅ አሳልፍ ነበር። እናቴ በድንገት እስከ ተወሰደችበት እስከ 14 ዓመቴ ድረስ እንዲሁ ቀጠለ። እርስዋ በምትሞትበት ሌሊት እኔ መታመምዋን ሳላውቅ እስከ ሌሊቱ 8 ሰዓት ካርታ እጫወት ነበር፤ በማግሥቱም፥ የጌታ ቀን ሆኖ ሳለ፥ በኃጢአት ከሚተባበሩኝ ጓደኞቼ ጋር ወደ መጠጥ ቤት ሄድሁ፤ ከዚያም ግማሽ ሰክረን በመንገዶች ላይ ዞርን።

ይህ ሐዘን በአእምሮዬ ላይ ዘላቂ ስሜት አላሳደረም። እየባሰብኝ ሄድሁ። በኮንፊርሜሽን ጸንቼ የጌታ እራትን እንድካፈል ከመፈቀዱ 3 ወይም 4 ቀን በፊት በከባድ ብልግና በደልሁ፤ ኮንፊርሜሽን ከመቀበሌ አንድ ቀን አስቀድሞ ኃጢአቴን ለመናዘዝ፥ ለወጉ ብቻ፥ ከቄሱ ጋር በልብሰ ተክህኖ ክፍል ሳለሁ አታለልሁት፤ አባቴ ለእርሱ የሰጠኝን ክፍያ 12ኛውን እጅ ብቻ ሰጠሁት። በዚህ የልብ ሁኔታ፥ ያለ ጸሎት፥ ያለ እውነተኛ ንስሐ፥ ያለ እምነት፥ የድነትን ዕቅድ ሳላውቅ፥ ከፋሲካ በኋላ ባለው እሑድ በ1820 ኮንፊርሜሽን ተቀበልሁ፤ የጌታ እራትንም ወሰድሁ። ይሁን እንጂ ስለ ነገሩ ክብር ጥቂት ስሜት አልጠፋብኝም፤ ከእኔ ጋር ኮንፊርሜሽን የተቀበሉት ሌሎቹ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በሜዳ ሲዘዋወሩ እኔ ከሰዓት በኋላና ማታ ቤት ቀረሁ።

እስከ 1821 የበጋ አጋማሽ ድረስ ጊዜዬ በከፊል በጥናት፥ በአብዛኛው ግን ፒያኖና ጊታር በመጫወት፥ ልብ ወለድ በማንበብ፥ መጠጥ ቤቶችን በማዘውተር፥ ለመለወጥ በመወሰንና ውሳኔዎቹን ልክ እንደ ወሰንኋቸው በፍጥነት በማፍረስ አለፈ። ገንዘቤ ብዙ ጊዜ በኃጢአት ደስታዎቼ ላይ ይባክን ነበር፤ በዚህም ምክንያት አልፎ አልፎ ችግር ውስጥ እገባ ነበር፤ አንድ ጊዜም ረሃቤን ለማስታገስ፥ በምኖርበት ቤት ውስጥ ሰፍሮ የነበረ ወታደር ድርሻ የሆነውን አንድ ቍራሽ ደረቅ ዳቦ ሰረቅሁ።

በ1821 የበጋ አጋማሽ አባቴ በማግደቡርግ አቅራቢያ በሾነቤክ ሹመት አገኘ፤ እኔም ወደ ማግደቡርግ ካቴድራል የጥንታውያን ቋንቋዎች ትምህርት ቤት እንዲያዛውረኝ ለመለመን አጋጣሚውን ተጠቀምሁ፤ ከኃጢአት ጓደኞቼ ብለይ፥ ከአንዳንድ ወጥመዶችም ብወጣ፥ በሌሎች መምህራንም ሥር ብሆን የተለየ ሕይወት እኖራለሁ ብዬ አስቤ ነበርና። አባቴ ተስማማ፤ ሃልበርሽታትን ለቅቄ እስከ ቅዱስ ሚካኤል በዓል ድረስ በሃይመርስሌበን እንድቆይ ተፈቀደልኝ። በዚህ ሁኔታ ፈጽሞ የራሴ ጌታ በመሆኔ ይበልጥ ሰነፍ ሆንሁ፤ እንደ ቀድሞውም በልዩ ልዩ ኃጢአት ኖርሁ። የቅዱስ ሚካኤል በዓል በደረሰ ጊዜ አባቴ እስከ ፋሲካ በሃይመርስሌበን እንዲተወኝና በዚያው ቦታ ከሚኖር አንድ ቄስ ጋር የጥንት ሥነ ጽሑፍ እንዳነብ እንዲፈቅድልኝ አሳመንሁት። አሁን የምኖረው የአባቴ በሆነው ግቢ ውስጥ ነበር፤ እውነተኛ ቍጥጥር አልነበረብኝም፤ ለአባቴ ዕዳ ካለባቸው ሰዎች የምሰበስበው ብዙ ገንዘብም በአደራ ተሰጥቶኝ ነበር። ልማዶቼ ብዙም ሳይቆዩ የዚህን ገንዘብ ትልቅ ክፍል እንዳባክን አደረጉኝ፤ ለልዩ ልዩ ገንዘቦች ደረሰኝ እሰጥ ነበር፤ አባቴን ግን እንዳልተቀበልኋቸው እንዲያስብ እተወው ነበር።

በኖቬምበር ወር ለመዝናናት ወደ ማግደቡርግ ሄጄ 6 ቀን በብዙ ኃጢአት አሳለፍሁ፤ ከዚያ ከመመለሴ በፊት አባቴ ከቤት መቅረቴን ቢያውቅም፥ የቻልሁትን ገንዘብ ሁሉ ይዤ በብዙ ውሸት ከመምህሬ ፈቃድ ካገኘሁ በኋላ ወደ ብሩንስዊክ ሄድሁ። በብሩንስዊክ ውድ በሆነ ሆቴል አንድ ሳምንት አሳለፍሁ። በሳምንቱ መጨረሻ ገንዘቤ አለቀ። ከዚያም ገንዘብ ሳይኖረኝ በብሩንስዊክ አቅራቢያ ባለ መንደር ወደሚገኝ ሌላ ሆቴል ሄጄ ሌላ ሳምንት በውድ ኑሮ አሳለፍሁ። በመጨረሻም የሆቴሉ ባለቤት ገንዘብ እንደሌለኝ ጠርጥሮ ክፍያ ጠየቀኝ፤ እኔም ምርጥ ልብሶቼን በመያዣነት ለመተው ተገደድሁ። ከዚያም 6 ማይል ያህል በእግሬ ወደ ቮልፈንቡተል ሄጄ ወደ አንድ ማረፊያ ቤት ገባሁ፤ ብዙ ገንዘብ እንዳለው ሰው እንደ ገና መኖር ጀመርሁ። በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ቀን ጠዋት በጸጥታ ከግቢው ወጥቼ ሮጥሁ፤ ነገር ግን ተጠርጥሬ ስለ ነበርና ስለ ተጠበቅሁ ስሄድ ታየሁ፤ ወዲያውም ተጠራሁ፤ ስለዚህ ለመመለስ ተገደድሁ። ተያዝሁ፤ ሌባ እንደ ሆንሁ ተጠርጥሬ 3 ሰዓት ያህል ተመረመርሁ፤ ከዚያም ወደ ወኅኒ ተላክሁ። አሁን በ16 ዓመቴ ከሌቦችና ከነፍሰ ገዳዮች ጋር በአንድ ቤት ውስጥ የምኖር ሆንሁ። ከክፍሌ እንድወጣ ሳይፈቀድልኝ ቀንና ሌሊት በዚያ ተዘግቶብኝ ነበር።

ከዲሴምበር 18 ቀን 1821 እስከ ጃንዋሪ 12 ቀን 1822 ድረስ በእስር ቤት ነበርሁ፤ በዚያን ቀን ጠባቂው ከእርሱ ጋር ወደ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት እንድሄድ ነገረኝ። እዚያም በፊቱ የተዳኘሁበት ኮሚሽነር ስለ ጠባዬ ለአባቴ እንዳሳወቀው ተረዳሁ፤ ስለዚህ አባቴ ለጉዞዬ ወጪ፥ በማረፊያ ቤቱ ያለብኝን ዕዳ ለመክፈልና በእስር ቤት ለቀለቤ የሚያስፈልገውን ገንዘብ እስኪልክ ድረስ በእስር ቤት ቆየሁ። አንድ እስረኛ ባልንጀራዬ ላደረገልኝ ለአንዳንድ ትንንሽ ቸርነቶች አሁን እጅግ ውለታ ቢስ ስለ ነበርሁ፥ መልእክቱን ለእኅቱ ላደርስ ቃል ገብቼ የነበረ ቢሆንም አላደረግሁትም፤ በዚህ ቅጣቴም በጣም ጥቂት ብቻ ስለ ተጠቀምሁ፥ ወደ ተቈጣ አባቴ ቤት የምሄድ ብሆንም፥ ታስሬ ከነበርሁበት ከተማ ከወጣሁ ከ2 ሰዓት በኋላ ብቻ፥ ለአብዛኛው ጉዞዬ ክፋቱን በግልጽ የሚያውጅ ሰው የጉዞ ጓደኛ አድርጌ መረጥሁ።

ሃይመርስሌበን ከደረስሁ ከ2 ቀን በኋላ የመጣው አባቴ ክፉኛ ከደበደበኝ በኋላ፥ በፋሲካ በጥብቅ ሥርዓትና በመምህር የዘወትር ክትትል ሥር እንድሆን በሃሌ ወደሚገኝ የጥንታውያን ቋንቋዎች ትምህርት ቤት ሊልከኝ አስቦ ወደ ሾነቤክ ወሰደኝ። ፋሲካ ደረሰ፤ እኔም እስከ ቅዱስ ሚካኤል በዓል ድረስ ቤት እንድቆይ በቀላሉ አሳመንሁት። ከዚያ ጊዜ በኋላ ግን ከእርሱ ጋር ከዚያ በላይ እንድቆይ አልፈቀደም፤ እኔም ለፈተና ወደ ሃሌ የምሄድ መስዬ ከቤት ወጣሁ። ነገር ግን ስለ ሰማሁት ጥብቅ ሥርዓት ከልቤ ስለ ጠላሁት ወደ ኖርድሃውዘን ሄጄ ወደዚያ ትምህርት ቤት ለመግባት ተፈተንሁ። ከዚያም ወደ ቤት ተመለስሁ፤ ነገር ግን ከመሄዴ አንድ ቀን አስቀድሞ እስከማለት ድረስ ስለዚህ ማታለል ሁሉ ለአባቴ አንድ ቃል አልነገርሁትም፤ ይህም ተከታታይ ውሸቶችን ለመፍጠር አስገደደኝ። ያን ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ በመጨረሻ ግን በልመናዬና በማግባባቴ ተሸንፎ እንድሄድ ፈቀደልኝ። ይህ የሆነው በኦክቶበር 1822 ነበር።

በኖርድሃውዘን 2 ዓመት ከ6 ወር ቆየሁ። በዚህ ጊዜ የላቲን ጥንታውያን ጽሑፎችን፥ ፈረንሳይኛን፥ ታሪክን፥ የራሴን ቋንቋና ሌሎችንም በብዙ ትጋት አጠናሁ፤ በዕብራይስጥ፥ በግሪክና በሒሳብ ግን ጥቂት ብቻ ሠራሁ። በዳይሬክተሩ ቤት እኖር ነበር፤ በጠባዬም በእርሱ ዘንድ እጅግ ተወደድሁ፤ ስለዚህም በመጀመሪያው ክፍል ለሌሎቹ ምሳሌ አድርጎ ያቀርበኝ ነበር። አሁን በክረምትም በበጋም ዘወትር ከሌሊቱ 10 ሰዓት እነሣ ነበር፤ አብዛኛውን ጊዜም ከጥቂት በቀር ቀኑን ሙሉ እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ አጠና ነበር።

በውጭ የሰዎችን አክብሮት እያገኘሁ ሳለሁ ግን ስለ እግዚአብሔር ቅንጣት ታህል ግድ አልነበረኝም፤ በስውር በብዙ ኃጢአት እኖር ነበር፤ በዚህም ምክንያት ታመምሁ፤ ለ13 ሳምንታትም በክፍሌ ውስጥ ተወሰንሁ። በሕመሜ ጊዜ እውነተኛ የልብ ሐዘን አልነበረኝም፤ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ተፈጥሯዊ የሃይማኖት ስሜቶች ሥር ስለ ነበርሁ የክሎፕስቶክን ሥራዎች ሳይሰለቸኝ አነበብኋቸው። ስለ እግዚአብሔር ቃል ግድ አልነበረኝም። የራሴ የሆኑ 300 ያህል መጻሕፍት ነበሩኝ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን አልነበረኝም። አልፎ አልፎ የተለየ ሰው መሆን እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር፤ በተለይም ከሌሎቹ ወጣቶች ጋር በዓመት ሁለት ጊዜ እንደማደርገው ወደ ጌታ እራት በሄድሁ ጊዜ ጠባዬን ለማሻሻል እሞክር ነበር። ከዚያ ሥርዓት አንድ ቀን አስቀድሞ ከአንዳንድ ነገሮች እታቀብ ነበር፤ በዕለቱም ጭምት ነበርሁ፤ የተቈረሰው ሥጋ ምልክት በአፌ ውስጥ ሳለ፥ ስለ መሐላው ስል እንድታረም እገደዳለሁ ብዬ በማሰብ፥ እሻሻላለሁ ብዬ በእግዚአብሔር አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ማልሁ። ነገር ግን አንድ ወይም ሁለት ቀን ካለፈ በኋላ ሁሉም ተረሳ፤ እንደ ቀድሞዬም ክፉ ሆንሁ።

በ1825 ፋሲካ እጅግ በተከበረ የምስክር ወረቀት የሃሌ ዩኒቨርሲቲ አባል ሆንሁ። በዚህም በሉተራን ቤተ ክርስቲያን ለመስበክ ፈቃድ አገኘሁ፤ ነገር ግን እንደ ቀድሞው ሁሉ በእውነት ደስታ የሌለኝና ከእግዚአብሔር የራቅሁ ነበርሁ። አሁን በመጨረሻ የሕይወቴን አካሄድ ለመለወጥ በሁለት ምክንያቶች ጽኑ ውሳኔ አድርጌ ነበር፤ አንደኛ፥ ያለዚያ ማንም ደብር እረኛ አድርጎ እንደማይመርጠኝ ስላሰብሁ፤ ሁለተኛ፥ ብዙ የሥነ መለኮት ዕውቀት ከሌለኝ ጥሩ ኑሮ ፈጽሞ እንደማላገኝ ስላሰብሁ ነው። ነገር ግን የዩኒቨርሲቲዋ ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ሃሌ በገባሁበት ቅጽበት ውሳኔዎቼ ሁሉ ከንቱ ሆኑ። አሁን ከመቼውም ይልቅ የራሴ ጌታ በመሆኔ፥ ምንም እንኳ አሁን የሥነ መለኮት ተማሪ ብሆንም፥ የብልግና ሕይወቴን እንደ ገና አደስሁ። ይሁን እንጂ በዚህ ሁሉ መካከል ይህን ምስኪን ሕይወት የመተው ፍላጎት ነበረኝ፤ ደስታ አላገኘሁበትምና፥ መጨረሻውም አንድ ቀን የሚያሳዝን እንደሚሆን ለማየት በቂ ማስተዋል ቀርቶልኝ ነበርና። ነገር ግን እግዚአብሔርን በማሳዘኔ ምክንያት የልብ ሐዘን አልነበረኝም።

አንድ ቀን ከአንዳንድ ልቅ ባልንጀሮቼ ተማሪዎች ጋር በመጠጥ ቤት ሳለሁ፥ ከ4 ዓመት በፊት በሃልበርሽታት የማውቀውን፥ በዚያን ጊዜ ግን ጸጥተኛና ጭምት ስለ ነበረ የናቅሁትን ቤታ የተባለውን የቀድሞ የትምህርት ቤት ጓደኛዬን በመካከላቸው አየሁት። አሁን የተሻሉ ባልንጀሮች ቢኖሩኝ በዚያ ጠባዬን አሻሽላለሁ ብዬ በማሰብ እርሱን ወዳጅ አድርጌ መምረጥ መልካም መሰለኝ። «በሰው የሚታመን፥ ሥጋንም ክንዱ የሚያደርግ ሰው ርጉም ነው።»

ይህ ቤታ ወደ ኋላ ያፈገፈገ ሰው ነበር። ቀድሞ በትምህርት ቤት እጅግ ጸጥተኛ በነበረ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በልቡ ይሠራ ስለ ነበረ እንደ ሆነ ለማመን ምክንያት አለኝ፤ አሁን ግን ከጌታ ስለ ራቀ የእግዚአብሔርን መንገድ ይበልጥ እያራቀ፥ ቀድሞ ጥቂት ብቻ የሚያውቀውን ዓለም ለመደሰት ይሞክር ነበር። እኔ ወደ ጽኑ ሕይወት ይመራኛል ብዬ ስላሰብሁ ወዳጅነቱን ፈለግሁ፤ እርሱም ኋላ እንደ ነገረኝ ወደ ተድላኛ ማኅበር ያገባኛል ብሎ ስላሰበ ከእኔ ጋር በደስታ ተዋወቀ።

በኦገስት መጀመሪያ እኔና ቤታ ከሌሎች ሁለት ተማሪዎች ጋር ለ4 ቀናት በአገሩ ውስጥ በሠረገላ ተዘዋወርን። በተመለስን ጊዜ ስለዚህ ኃጢአት በእውነት ከማዘን ይልቅ አዲስ ደስታዎችን አሰብን፤ በዚህ በመጨረሻው ጉዞ ባየሁት ነገር ምክንያት የጉዞ ፍቅሬ ከቀድሞው ይልቅ በርትቶ ስለ ነበር፥ ወደ ስዊዘርላንድ እንድንሄድ ለጓደኞቼ ሐሳብ አቀረብሁ። በመንገዱ ላይ የነበሩትን እንቅፋቶች፥ የገንዘብና የፓስፖርት እጦትን ያስወገድሁት እኔ ነበርሁ። ከወላጆቻችን እንደ ተላኩ አስመስለን ባዘጋጀናቸው ደብዳቤዎች ፓስፖርት አገኘን፤ የቻልነውን ሁሉ፥ በተለይም መጻሕፍታችንን በማስያዝ በቂ ይሆናል ብለን ያሰብነውን ያህል ገንዘብ አገኘን። ለ43 ቀናት ዕለት ዕለት ተጓዝን፤ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል በእግር ነበር።

አሁን የልቤን ምኞት አገኘሁ። ስዊዘርላንድን አየሁ። ነገር ግን አሁንም ደስተኛ ከመሆን እጅግ የራቅሁ ነበርሁ። በዚህ ጉዞ እንደ ይሁዳ ነበርሁ፤ የጋራውን ከረጢት ይዤ ሌባ ነበርሁና። ጉዞው ለጓደኞቼ ከፈጀባቸው ሁለት ሦስተኛውን ብቻ እንዲፈጅብኝ አድርጌ አካሄድሁ። ስለ ጉዞው ወጪ አባቴን ለማሳመን ብዙ ውሸት መዋሸት ነበረብኝ። ቤት በቆየሁባቸው 3 ሳምንታት ወደ ፊት በተለየ መንገድ ለመኖር ወሰንሁ። ለጥቂት ቀናት ተለውጬ ነበር፤ ነገር ግን የዕረፍቱ ጊዜ ሲያልቅ፥ አዲስ ተማሪዎችና ከእነርሱም ጋር አዲስ ገንዘብ ሲመጡ ሁሉም ቶሎ ተረሳ።


ጨርሰዋል፦ ልጅነትና ወጣትነት

ቀዳሚ ቀጣይ