ምዕራፍ 12 · 13 ደቂቃ ንባብ · 17 ደቂቃ ማዳመጥ
ፈተና
1838.
የሕመም አገልግሎት—የአእምሮ ሰላም—ኢየሱስ የቅርብ ረዳት—ጽኑ ድህነት—ከእግዚአብሔር ጋር መሟገት—የኅብረት ጸሎት።
ጥር 6 ቀን 1838። አጠቃላይ ጤንነቴ የተሻሻለ ቢመስልም ራሴ ብዙም አልተሻለውም፤ ደግ ሐኪሜ ግን እጅግ ተሽሎሃል ይለኛል፤ አሁንም የአየር ለውጥ እንዳደርግ ይመክረኛል። በዚህ ምሽት ከዚህ ሃምሳ ማይል ያህል ርቃ የምትኖር፣ በዚህ ጠዋት ስለ ተሰጠኝ የሕክምና ምክር ምንም የማታውቅ አንዲት እኅት ለአየር ለውጥ ብቻ እንዲውል ብላ አሥራ አምስት ፓውንድ ላከችልኝ፤ እርሷም በተመሳሳይ ሕመም ተሠቃይታ ስለ ነበር፣ በሰው አነጋገር፣ ከጸጥታና ከአየር ለውጥ የበለጠ የሚጠቅመኝ ነገር እንደሌለ እርግጠኛ መሆኗን ጻፈችልኝ።
ጥር 7። በቃሉ ከማገልገል የታገድኩበት ይህ ዘጠነኛው የጌታ ቀን ነው። ሕመሜ ከፍ ካለ የቍጣ ዝንባሌ ጋር ተያይዟል፤ እንዲያውም በተፈጥሮዬ እንኳ እንግዳ ከሆነ ሰይጣናዊ ስሜት ጋር።
ጥር 10። ዛሬ ከቤተሰቤ ጋር ወደ ትሮውብሪጅ ሄድሁ። ጥር 14። የጌታ ቀን። ዛሬ ብዙ ሰዓታት በጸሎት አሳለፍሁ፤ በጕልበቴም ተንበርክኬ አነበብሁ፤ በመዝሙር 63 ላይም ለሁለት ሰዓታት ጸለይሁ። እግዚአብሔር ዛሬ ነፍሴን እጅግ ባረካት። ነፍሴ አሁን ጤንነቴን በሚመለከት በእግዚአብሔር ፈቃድ ደስ ወደምትሰኝበት ሁኔታ ደርሳለች። አዎን፣ አሁን ከልቤ እንዲህ ማለት እችላለሁ፤ እግዚአብሔር በዚህ ሕመም አማካይነት የተላከበትን በረከት እስኪሰጠኝ ድረስ እንዲወገድ አልፈልግም።
ጥር 15። ከትናንት ከሰዓት በኋላ ወዲህ ካለፉት ስምንት ቀናት ይልቅ በራሴ ላይ ያለው ሥቃይ ቀንሷል፤ ሆኖም አሁንም እንኳ ደኅና ከመሆን እጅግ የራቀ ነው። ጌታ ከሰጠኝ መንፈሳዊ በረከቶች የተነሣ፣ በዚህ መከራ አማካይነት ለተባረከው አገልግሎቱ እያነጻኝ ብቻ እንደ ሆነና በቅርቡም ወደ ሥራው እንደምመለስ ውስጣዊ ማረጋገጫ አሁንም አለኝ። ዛሬም ደግሞ እግዚአብሔር ለሦስት ተከታታይ ቀናት ያገኘሁትን የመንፈስ ትጋት አላጓደለብኝም። ዛሬም ደግሞ ነፍሴን ከራሱ ጋር ወደ ብዙ እውነተኛ ኅብረት፣ ለተወደደው ልጁም ይበልጥ እመስል ዘንድ ወደ ቅዱስ ምኞት ሳባት። እግዚአብሔር የጸሎትን መንፈስ ሲሰጥ መጸለይ እንዴት ቀላል ነው! ይሁን እንጂ ይህ የተሰጠኝ መንገዶቹን በመጠቀም ነው፤ ባለፈው ቅዳሜ ቃሉን እያሰላሰልሁ ለማንበብና ወደ ጸሎትም ለመለወጥ በጕልበቴ ተንበርከኩ። ዛሬ በመዝሙር 64 እና 65 ላይ ሦስት ሰዓት ያህል በጸሎት አሳለፍሁ። «ጸሎትን የምትሰማ ሆይ» (መዝ. 65፡2) የሚለውን ያንን ውድ ቃል በማሰብ፣ የሚከተሉትን ልመናዎች ለጌታ አቀረብሁ፤ በሰማይም እንዲመዘግባቸውና እንዲመልሳቸው ለመንሁት።
1. በመከራዬ ውስጥ በታዛዥና በትዕግሥተኛ መንፈስ አከብረው ዘንድ ጸጋን እንዲሰጠኝ።
2. አሁን፣ ደግሞም ከልቤ አሁን ብቻ፣ ስለዚህ መከራ እግዚአብሔርን ማመስገን ስለ ተቻለኝ፣ እስከ ዛሬ ከነበርሁት ይበልጥ ለሥራው እስኪያበቃኝ ድረስ እጁን ከእኔ እንዳያነሣ።
3. በወንድም ክሬክና በእኔ አማካይነት የሚሆነው የመለወጥ ሥራ እንዳይቋረጥ፣ ይልቁንም መጀመሪያ ወደ ብሪስቶል በመጣን ጊዜ እንደ ነበረው አሁንም እንዲቀጥል፣ አዎን፣ ከዚያን ጊዜም ይበልጥ እንዲበዛ ፈቃዱ እንዲሆን።
4. በእኛ እንክብካቤ ሥር ላለችው ቤተ ክርስቲያን እስከ ዛሬ ካገኘነው ሁሉ የበለጠ እውነተኛ መንፈሳዊ ብልጽግና ይሰጥ ዘንድ ፈቃዱ እንዲሆን።
5. ትረካዬ በዚህ ባጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ቅጂዎች ስለ ተሸጡ ካመሰገንሁት በኋላ፣ እያንዳንዱ ቅጂ ሁሉ እንዲሸጥ ለመንሁት።
6. በዚህች ትንሽ መጽሐፍ ላይ ባለጠጋ በረከቱ እንዲያርፍ እንዲቀጥል፣ ደግሞም ይበልጥ እንዲበዛ ለመንሁት፤ ይኸውም ብዙዎች በእርሷ አማካይነት እንዲለወጡ፣ ብዙ የእግዚአብሔር ልጆችም በእውነት እንዲጠቀሙባት፣ እኔም ከንቁ አገልግሎት ብገለልም በእርሷ አማካይነት አሁን እንድናገር ነው።
7. በእኛ እንክብካቤ ሥር ባሉት የሙት ልጆች፣ በሰንበትና በቀን ትምህርት ቤቶች ልጆችም ላይ በመለወጥ መንገድ በረከቱ እንዲያርፍ ለመንሁት።
8. እነዚህን ተቋሞች ለማካሄድና ለማስፋፋት የሚያስፈልገውን ገንዘብ እንዲሰጠኝ ለመንሁት።
ይህን የራሱን ቃል በማሰብ በዚህ ምሽት ከአምላኬ የለመንኋቸው ልመናዎች ከፊሎቹ እነዚህ ናቸው። እንደ ሰማኝ አምናለሁ። እንደ ሰማኝ በራሱ መልካም ጊዜ እንደሚገልጥ አምናለሁ፤ እግዚአብሔር በመለሳቸው ጊዜ በዚህ አማካይነት ስሙ እንዲከብር፣ እነዚህን ልመናዎቼን በዚህ በጥር 15 ቀን 1838 መዝግቤአቸዋለሁ። [ይህን ሁለተኛ ክፍል በምጽፍበት ጊዜ፣ ለጌታ ምስጋናና ለእግዚአብሔር ልጆች ማበረታቻ እንዲሆን፣ ልመናዎች 4፣ 5፣ 6፣ 7 እና 8 ሙሉ በሙሉ እንደ ተመለሱ፣ ሌሎቹም ልመናዎች በከፊል እንደ ተመለሱ እጨምራለሁ።]
ጥር 16። ማክሰኞ። የተባረከ ቀን። ጌታ እንዴት እጅግ መልካም ነው! በጸጋው የመንፈስ ትጋት አሁንም ከእኔ ጋር ነው፤ ምንም እንኳ በዚህ ጠዋት የእግዚአብሔር ርዳታ ባይኖር ኖሮ እንደ ገና ባጣው ነበር። ለብዙ ቀናት አየሩ እጅግ ቀዝቃዛ ነበር፤ ዛሬ ግን ከበፊቱ ይበልጥ ስለ ቀዘቀዘ፣ ወይም ከሰውነቴ ድካምና ብዙ መድኀኒት ከመውሰዴ የተነሣ ይበልጥ ስለ ተሰማኝ እጅግ ተሠቃየሁ። ከጕልበቴ ተነሥቼ እሳቱን ቈሰቈስሁ፤ ነገር ግን አሁንም በጣም በርዶኝ ነበር። በዚህም ጥቂት ተበሳጨሁ። ወደ ሌላ የክፍሉ ክፍል ተዛወርሁ፤ ቅዝቃዜው ግን ይበልጥ ተሰማኝ። በመጨረሻም ለተወሰነ ጊዜ ከጸለይሁ በኋላ ደሜ እንዲዘዋወር ተነሥቼ በእግሬ ለመዘዋወር ተገደድሁ። በመንገዴም ይህ ሁኔታ ባለፉት ሦስት ቀናት ከእርሱ ጋር የነበረኝን ውድ ኅብረት እንዲነጥቀኝ እንዳይፈቀድ ጌታን ለመንሁት፤ ሰይጣን ያለመው ይህን ነበርና። ከቅዝቃዜው የተነሣ የተበሳጨሁበትን ኃጢአቴንም ተናዘዝሁ፤ ኅሊናዬም በኢየሱስ ደም እንዲነጻ ፈለግሁ። እርሱም ማረኝ፤ ሰላሜም ተመለሰልኝ፤ በተመለስሁም ጊዜ ጌታን እንደ ገና በጸሎት ፈለግሁት፤ ያለ ማቋረጥም ከእርሱ ጋር ኅብረት አደረግሁ።
ጤንነቱ ደካማ ሆኖ ስለ ቀጠለ፣ አቶ ሙ. ሚያዝያ 6 ቀን እንግሊዝን ለቅቆ ወደ ጀርመን ሄደ፤ ግንቦት 7 ቀንም ወደ ብሪስቶል ተመለሰ። ትረካውንም እንዲህ ሲል ይቀጥላል፦—
ግንቦት 8። በዚህ ምሽት በጌድዮን ወደ ነበረው የጸሎት ስብሰባ ሄድሁ። መዝሙር 103ን አነበብሁ፤ ስለ ቅርብ ጊዜ መከራዬም ጌታን በይፋ ለማመስገን ቻልሁ። ከኅዳር 6 ቀን 1837 ወዲህ በወንድሞች የሕዝብ ስብሰባዎች ውስጥ ምንም ተሳትፎ ሳደርግ ይህ የመጀመሪያው ጊዜ ነው።
ሐምሌ 12። ልክ የዛሬ ዓመት ሰባት መቶ ሰማንያ ፓውንድ ያህል የነበረው ገንዘብ አሁን ወደ ሃያ ፓውንድ ያህል ወርዷል፤ ነገር ግን ጌታ ይመስገን፣ ብዙው ገንዘብ በእጃችን በነበረ ጊዜ ከነበረው እምነቴ እኩል ወይም የበለጠ ጠንካራ ነው፤ ከሥራውም መጀመሪያ አንሥቶ በማንኛውም ጊዜ እንድጠራጠረው አልፈቀደልኝም። ይሁን እንጂ ጌታችን እንዲለመን ስለሚወድ፣ እውነተኛ እምነትም ወደ ጸሎት በመምራት እውነተኛነቱን ስለሚገልጥ፣ ሊጠይቀኝ ከመጣው ከወንድሞች የሙት ልጆች ማሳደጊያ ወንድም ቲ—— ጋር ራሴን ለጸሎት ሰጠሁ፤ እርሱም ከሚስቴና ከወንድም ክሬክ ሌላ ስለ ገንዘቡ ሁኔታ የምነግረው ብቸኛ ሰው ነው። በመጸለይ ላይ ሳለን ከፍሩም አንድ የሙት ልጅ መጣ፤ በፍሩም ያሉ አንዳንድ አማኞችም በመካከላቸው አምስት ፓውንድ አዋጥተው ይህን ገንዘብ ከልጁ ጋር ላኩ። በዚህም በችግር ጊዜ የመጀመሪያውን መልስ ተቀበልን። ገንዘባችን እጅግ ያነሰ ቢሆንም፣ እግዚአብሔር ችግራችንን እንደሚመለከት ተስፋ በማድረግ ሰባት ልጆች እንዲገቡ አሳውቀናል፤ ሌሎች አምስትም እንዲገቡ ለማሳወቅ አስበናል።
ሐምሌ 17 እና 18። የወንዶችን የሙት ልጆች ማሳደጊያ በይፋ ለጌታ አደራ ለመስጠት በእነዚህ ሁለት ቀናት ከምሽቱ ስድስት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ሁለት ልዩ የጸሎት ስብሰባዎች አደረግን። ገንዘባችን አሁን እጅግ አንሷል። በእጃችን ሃያ ፓውንድ ያህል አለ፤ በጥቂት ቀናት ውስጥም ቢያንስ ሠላሳ ፓውንድ ያስፈልጋል፤ እኔ ግን ስለ አሁኑ ችግራችን ምንም ከመናገር ሆን ብዬ ተቈጠብሁ፤ ቸሩ አባታችን፣ «የድሀ አደጎች አባት»፣ እስከ ዛሬ ስለ ሰጠን ብዛት ለእግዚአብሔር ምስጋና ብቻ ተናገርሁ። ይህን ያደረግሁት እግዚአብሔር ርዳታ በመላክ ረገድ እጁ ይበልጥ ግልጽ ሆኖ እንዲታይ ነው።
ሐምሌ 22። በዚህ ምሽት በትንሿ የአትክልት ቦታችን ውስጥ እየተመላለስሁ «ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው» (ዕብ. 13፡8) የሚለውን እያሰላሰልሁ ነበር። የማይለወጠውን ፍቅሩን፣ ኃይሉን፣ ጥበቡንና የመሳሰሉትን እያሰላሰልሁ፣ ሁሉንም እየቀጠልሁ ስለ ራሴ ወደ ጸሎት እየለወጥሁ ሳለ፣ ደግሞም የማይለወጠውን ፍቅሩን፣ ኃይሉንና ጥበቡን፣ ወዘተ.፣ በአሁኑ መንፈሳዊና ምድራዊ ሁኔታዬ ላይ እየተገበርሁ ሳለ፣—ድንገት የሙት ልጆች ማሳደጊያዎቹ የአሁኑ ችግር ወደ አእምሮዬ መጣ። ወዲያውም ለራሴ እንዲህ ለማለት ተመራሁ፤ ኢየሱስ በፍቅሩና በኃይሉ እስከ ዛሬ ለሙት ልጆች ያስፈለገኝን ሰጥቶኛል፤ በዚያው በማይለወጠው ፍቅርና ኃይልም ወደ ፊት የሚያስፈልገኝን ይሰጠኛል። የሚሰገድለት ጌታችን የማይለወጥ መሆኑን እንዲህ ስገነዘብ የደስታ ጎርፍ ወደ ነፍሴ ገባ። ከአንድ ደቂቃ ያህል በኋላ የሃያ ፓውንድ ሰነድ የያዘ ደብዳቤ መጣልኝ።
ነሐሴ 18። ለሙት ልጆች በእጄ አንዲት ሳንቲም እንኳ የለኝም። በአንድ ወይም በሁለት ቀን ውስጥ እንደ ገና ብዙ ፓውንድ ያስፈልጋል። ዓይኖቼ ወደ ጌታ ናቸው። ምሽት። ይህ ቀን ሳያልፍ ከአንዲት እኅት አምስት ፓውንድ ተቀበልሁ። እርሷ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ለሙት ልጆች ጥቅም እንዲሸጡ ጌጣጌጦቿን አስቀምጣ ነበር። በዚህ ጠዋት በጸሎት ላይ ሳለች፣ «ይህ አምስት ፓውንድ አለኝ፤ ለማንም ዕዳ የለብኝም፤ ስለዚህ ጌጣጌጦቹን ለመሸጥ ጊዜ ሊወስድብኝ ስለሚችል ይህን ገንዘብ ወዲያው ብሰጥ ይሻላል» የሚል ሐሳብ ወደ አእምሮዋ መጣ። ስለዚህ በእጃችን አንዲት ሳንቲም እንኳ እንደሌለ ሳታውቅ አመጣችው።
ነሐሴ 29። ዛሬ አሥራ ስድስት አማኞች ተጠመቁ። ከተጠመቁትም መካከል ዕድሜው ከሰማንያ አራት ዓመት በላይ የሆነ አንድ አረጋዊ ወንድምና ከሰባ በላይ የሆነ አንድ ሰው ነበሩ። ስለ ኋለኛውም አማኝ ሚስቱ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ጸልያ ነበር፤ በመጨረሻም ጌታ በእርሱ መለወጥ ጸሎቷን መለሰላት።
ነሐሴ 31። ከሴቶች የሙት ልጆች ማሳደጊያ የሞግዚቲቱ ሒሳብ መዛግብት ስለ መጡና ለቤት ወጪ የሚሰጥ ገንዘብ በእጃችን ስለሌለ ገንዘብ እንዲሰጠን ጌታን ስጠባበቅ ነበር። ነገር ግን እስከ አሁን ጌታ ርዳታ ለመላክ አልፈቀደም። ሞግዚቲቱ ዛሬ ገንዘብ ለመውሰድ በመጣች ጊዜ ከሠራተኞቹ አንዱ ለአሁኑ ችግር ከራሱ ሁለት ፓውንድ ሰጠ።
መስከረም 1። ጌታ በጥበቡና በፍቅሩ እስከ አሁን ርዳታ አልላከም። ከወዴት እንደሚመጣ የእኔ ጭንቀት አያስፈልገውም። ነገር ግን እግዚአብሔር በጊዜው ርዳታ እንደሚልክ አምናለሁ። ሰዓቱ ገና አልደረሰም። በወንዶች የሙት ልጆች ማሳደጊያም ገንዘብ ያስፈልግ ስለ ነበር፣ አሁን የጠቀስሁት ያው ወንድም ለዚያም ሁለት ፓውንድ ሰጠ። በዚህም በዚህ ጊዜም ደግሞ ዳንን። አሁን ግን የእርሱም ገንዘብ አልቋል። ገንዘብን በሚመለከት በሥራው ውስጥ እስከ ዛሬ ካጋጠመኝ ሁሉ ይህ እጅግ አስቸጋሪው ሰዓት ነው፤ ነገር ግን ስለ ርዳታው ገና ጌታን እንደማመሰግን አውቃለሁ።
መስከረም 5። የፈተናችን ሰዓት አሁንም ቀጥሏል። ጌታ በምሕረቱ የዕለት ችግራችንን የሚያሟላ በቂ ሰጥቶናል፤ አሁን ግን እንደሚያስፈልገን በቀን፣ ይልቁንም በሰዓት ማለት ይቻላል፣ ይሰጣል። ትናንት ምንም አልገባም። ትናንትም ዛሬም ጌታን ደጋግሜ ለመንሁት። ጌታ «ጊዜዬ ገና አልደረሰም» የሚል ይመስላል። እኔ ግን በእግዚአብሔር እምነት አለኝ። ርዳታው ከወዴት እንደሚመጣ ባላውቅም በእርግጥ ርዳታ እንደሚልክ አምናለሁ። በጥቂት ቀናት ውስጥ ብዙ ፓውንድ ያስፈልጋል፤ በእጃችንም አንዲት ሳንቲም እንኳ የለም። በዚህ ጠዋት ከሥራው ሠራተኞች አንዱ ለአሁኑ ችግር ሁለት ፓውንድ ሰጠ። ምሽት። በዚሁ ቀን ጌታ እርሱን መጠባበቄንና በእርሱ መታመኔን እንድቀጥል ሊያበረታታኝ እንደ ገና ጥቂት ርዳታ ላከ። በዚህ ከሰዓት በኋላ ስለ ጉዳዩ ስጸልይ፣ ጌታ ርዳታ እንደሚልክ ሙሉ በሙሉ ተረዳሁ፤ ስለ ርዳታውም አስቀድሜ አመሰገንሁት፤ በእርሱም ልባችንን እንዲያበረታ ለመንሁት። ደግሞም ትናንትና ዛሬ በተለይ እምነቴ እንዲደክም እንዳይፈቅድ ጌታን እንድለምን ተመራሁ። ከጸለይሁ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወንድም ቲ—— መጥቶ በብዙ ትናንሽ ስጦታዎች የገባውን አራት ፓውንድ አንድ ሽልንግ አምስት ፔንስ አመጣ። በዚያው ጊዜም ነገ ከሕፃናት የሙት ልጆች ማሳደጊያ መዛግብቱ እንደሚመጡና ያን ጊዜ ለቤት ወጪ ገንዘብ መሰጠት እንዳለበት ነገረኝ። ከዚህ ገንዘብ ሦስት ፓውንድ ለዚያ ዓላማ ባስቀምጥ መልካም ይሆናል ብዬ ለአንድ አፍታ አሰብሁ። ነገር ግን ወዲያው «ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል» የሚለው ትዝ አለኝ። ጌታ እስከ ነገ ከሚያስፈልገኝ እጅግ የሚበልጥ ሊሰጥ ይችላል፤ ስለዚህ የሩብ ዓመት ደመወዟ ለደረሰ ለአንዲት እኅት ሦስት ፓውንድ ላክሁ፤ የቀረውን አንድ ፓውንድ አንድ ሽልንግ አምስት ፔንስ ለቤት ወጪ ወደ ወንዶች የሙት ልጆች ማሳደጊያ ላክሁ። በዚህ ሁኔታ አሁንም ባዶ እጄን ነኝ። ተስፋዬ በእግዚአብሔር ነው፤ እርሱ ያዘጋጃል።
መስከረም 6። በዚህ ጠዋት ከሕፃናት የሙት ልጆች ማሳደጊያ መዛግብቱ መጡ፤ ሞግዚቲቱም መቼ መጥታ እንድትወስዳቸው ጠየቀች፤ ይኸውም መቼ ተመርምረው እንደሚጨርሱና ለቤት ወጪ ገንዘብ መቼ እንደሚሰጥ ማለቷ ነው። በእጄ አንዲት ሳንቲም እንኳ ባይኖረኝም «ነገ» አልሁ። ከአንድ ሰዓት ያህል በኋላ ወንድም ቲ—— በዚህ ጠዋት አንድ ፓውንድ እንደ ተቀበለ፣ ትናንት ምሽትም አንድ ወንድም ሃያ ዘጠኝ ፓውንድ ጨው፣ አርባ አራት ደርዘን ሽንኩርትና ሃያ ስድስት ፓውንድ የተፈተገ አጃ እንደ ላከ የሚገልጽ ማስታወሻ ላከልኝ።
መስከረም 7። ወደ ሕፃናት የሙት ልጆች ማሳደጊያ ገንዘብ መላክ የነበረብኝ ጊዜ ደረሰ፤ ጌታ ግን ከዚያ በላይ አልላከም ነበር። ስለዚህ ቸሩ ጌታ ተጨማሪ እንደሚልክ በመታመን ትናንት የገባውን ፓውንድና በቤቴ ባለው ሣጥን ውስጥ የተጨመሩትን ሁለት ሽልንግ ሁለት ፔንስ ሰጠሁ።
መስከረም 8። ቸሩ ጌታዬ እስከ አሁን ርዳታ ሊልክልኝ አልወደደም። ትናንትና ዛሬ በቸርነቱ ርዳታ ሊልክ የሚገባበትን አሥራ አንድ ምክንያቶች በእግዚአብሔር ፊት እያቀረብሁ ስሟገት ነበር። በእግዚአብሔር ፊት የማቀርባቸው ምክንያቶች እነዚህ ናቸው፦—
1. ሥራውን የጀመርሁት ለእግዚአብሔር ክብር ነው፤ ይኸውም እግዚአብሔር ለጸሎት መልስ ብቻ የሙት ልጆችን ፍላጎት በማሟላት እርሱ ሕያው አምላክ እንደ ሆነ፣ በእኛም ዘመን እንኳ ጸሎትን ለመመለስ እጅግ ፈቃደኛ እንደ ሆነ የሚታይ ማስረጃ እንዲኖር ነው፤ ስለዚህ ቀለብ ሊልክ ፈቃዱ ይሁን።
2. እግዚአብሔር «የድሀ አደጎች አባት» ነው፤ ስለዚህ እንደ አባታቸው ሊያዘጋጅላቸው ፈቃዱ ይሁን። መዝሙር 68፡5።
3. ልጆቹን በኢየሱስ ስም ተቀብያለሁ፤ ስለዚህ በእነዚህ ልጆች እርሱ ራሱ ተቀብሏል፣ ይመገባልም፣ ይለብሳልም፤ ስለዚህ ይህን ያስብ ዘንድ ፈቃዱ ይሁን። ማርቆስ 9፡36፣ 37።
4. እስከ ዛሬ በዚህ ሥራ የብዙ የእግዚአብሔር ልጆች እምነት ጸንቷል፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት ገንዘቡን ቢከለክል በእምነት የደከሙት ይሰናከላሉ፤ ገንዘቡ ቢቀጥል ግን እምነታቸው ይበልጥ ሊጸና ይችላል።
5. ጌታ ቀለብን ቢከለክል ብዙ ጠላቶች ይስቃሉ፤ ደግሞም፣ ይህ ቅንዓት ከንቱ እንደሚሆን አስቀድመን አልተናገርንምን? ይላሉ።
6. እርሱ ባይረዳኝ፣ ያልተማሩ ወይም በሥጋዊ ሁኔታ ያሉ ብዙ የእግዚአብሔር ልጆች በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ ከዓለም ጋር ያላቸውን ኅብረት ለመቀጠል፣ ገንዘብ ማግኘትን በሚመለከትም በተመሳሳይ ተቋሞች ረገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆነውን አካሄዳቸውን እንደ ቀድሞው ለመቀጠል ራሳቸውን ትክክል አድርገው ይቈጥራሉ።
7. ጌታ ልጁ እንደ ሆንሁ እንዲያስብ፣ በቸርነቱም እንዲራራልኝ፣ እኔ ለእነዚህ ልጆች ማዘጋጀት እንደማልችል እንዲያስብ፣ ስለዚህም ይህ ሸክም ርዳታ ሳይልክ ለረጅም ጊዜ በእኔ ላይ እንዲቆይ እንዳይፈቅድ።
8. በእርሱ የሚታመኑትን፣ ነገር ግን ቀለብን ቢከለክል የሚፈተኑትን በሥራው ያሉትን የሥራ ባልደረቦቼንም እንዲያስብ።
9. ልጆቹን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርታችን አውጥቼ ወደ ቀድሞ ባልንጀሮቻቸው ማሰናበት እንደሚገባኝ እንዲያስብ።
10. ነገሩ አዲስ ሳለ በመጀመሪያ ቀለብ ሊጠበቅ ይችላል፣ ከዚያ በኋላ ግን አይጠበቅም ያሉት እንደ ተሳሳቱ እንዲያሳይ።
11. ገንዘብን ቢከለክል፣ ከዚህ ሥራ ጋር በተያያዘ እስከ ዛሬ የሰጠኝን፣ ሥራውም ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ሙሉ በሙሉ ያሳዩኝን እነዚያን እጅግ አስደናቂ የሆኑ ብዙ የጸሎት መልሶች ሁሉ እንዴት እንደምተረጕማቸው አላውቅም።
በመዝሙራት ጸሎቶች ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚገኘውን «እስከ መቼ» የሚለውን ቃል ትርጕም አሁን በተሞክሮ በጥቂቱ እረዳለሁ። ነገር ግን አሁንም እንኳ፣ በእግዚአብሔር ጸጋ፣ ዓይኖቼ ወደ እርሱ ብቻ ናቸው፤ ርዳታም እንደሚልክ አምናለሁ።
መስከረም 10። ሰኞ ጠዋት። ቅዳሜም ሆነ ትናንት ምንም ገንዘብ አልገባም። አሁን በችግራችን ምክንያት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ መሰለኝ፤ ይኸውም ወደ የሙት ልጆች ማሳደጊያዎቹ ሄጄ ወንድሞችንና እኅቶችን (ከወንድም ቲ—— በቀር ስለ ገንዘቡ ሁኔታ ፈጽሞ ያልተነገራቸውን) መሰብሰብ፣ ጉዳዩን ማስረዳት፣ ለአሁኑ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ማየት፣ በዚህ ሁሉ የእምነት ፈተና መካከል እግዚአብሔር እንደሚረዳ አሁንም እንደማምን መንገርና ከእነርሱ ጋር መጸለይ ነው። በተለይም ደግሞ ልንከፍልበት ገንዘብ ካለን በላይ ምንም ዕቃ እንዳይገዛ፣ ነገር ግን ገንቢ ምግብንና አስፈላጊ ልብስን በሚመለከት ልጆቹ በምንም መንገድ ምንም እንዳይጎድልባቸው ለመንገር ልሄድ አሰብሁ፤ ልጆቹ ከሚጎድልባቸው ይልቅ ወዲያው ባሰናብታቸው እመርጣለሁና። ደግሞም እንዲሸጡ ተብለው የተላኩ ዕቃዎች አሁንም መኖራቸውን፣ ወይም ወደ ገንዘብ እንድንለውጣቸው በእውነት አላስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎች መኖራቸውን ለማየት ልሄድ አሰብሁ። ጉዳዩ አሁን ወደ ከባድ ቀውስ እንደ ደረሰ ተሰማኝ። ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ገደማ በጌድዮን ቤተ ጸሎት ሣጥን ውስጥ ስሙ ሳይታወቅ የተጨመረ ስድስት ፔንስ ገባ። ይህ ገንዘብ እግዚአብሔር እንደሚራራና ተጨማሪ እንደሚልክ መያዣ መሰለኝ። አራት ሰዓት ገደማ፣ ልቤን እንደ ገና ካወጣሁለት ከወንድም ክሬክ ዘንድ ከተመለስሁ በኋላ፣ አሁንም ስለ ርዳታ በጸሎት ላይ ሳለሁ፣ አንዲት እኅት መጥታ ለሙት ልጆች ሁለት ሶቨሪን ለሚስቴ ሰጠች፤ ለመምጣትም እንደ ተነሣሣችና መምጣቷን አስቀድሞ እጅግ እንዳዘገየች ተናገረች። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እርሷ ወዳለችበት ክፍል በገባሁ ጊዜ ሌላ ሁለት ሶቨሪን ሰጠችኝ፤ ይህንም ሁሉ ስለ ችግራችን ምንም ሳታውቅ ነው። በዚህ ሁኔታ ጌታ በታላቅ ምሕረቱ ጥቂት ርዳታ ላከልን፤ ይህም እምነቴን እጅግ አበረታ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ከሕፃናት የሙት ልጆች ማሳደጊያ ገንዘብ ተጠየቅሁ፤ ወደዚያም ሁለት ፓውንድ፣ ወደ ወንዶች የሙት ልጆች ማሳደጊያ አንድ ፓውንድ ከስድስት ፔንስ፣ ወደ ሴቶች የሙት ልጆች ማሳደጊያም አንድ ፓውንድ ላክሁ።
ዛሬ እርሱና ከእኅቶቹ አንዲቱ በትረካዬ አማካይነት ጌታን ወደ ማወቅ የደረሱ አንድ ወጣት ወንድም አየሁ።
መስከረም 11። ቸሩ ጌታ በጥበቡ አሁንም እጅግ ዝቅ አድርጎ ሊያቆየን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል። ነገር ግን በዚህ ከሰዓት በኋላ ወንድም ቲ—— መጥቶ ከሥራ ባልደረቦቻችን አንዱ የብረት ሰዓቱንና ሁለት የወርቅ መርፌዎቹን በአንድ ፓውንድ አንድ ሽልንግ እንደ ሸጠ፣ ዘጠኝ ሽልንግ ስድስት ፔንስ እንደ ገባ፣ ከሥራ ባልደረቦቻችንም ሁለቱ ለሙት ልጆች እንዲሸጡ ቍጥራቸው አሥራ ዘጠኝና ሃያ አንድ የሆኑ የራሳቸውን ሁለት የመጻሕፍት ጥቅሎች እንደ ላኩ ነገረኝ።
መስከረም 12። ፈተናው አሁንም ቀጥሏል። ዛሬ የገባው ከሠራተኞቹ አንዱ የሰጠው ዘጠኝ ሽልንግ ብቻ ነው። በዚህ ታላቅ የእምነት ፈተና መካከል ጌታ በምሕረቱ አሁንም በታላቅ ሰላም ይጠብቀኛል። ድካማችንም ከንቱ እንዳልሆነ እንዳይ ይፈቅድልኛል፤ ትናንት ከሙት ልጆቹ አንዲቱ፣ ዕድሜዋ ዘጠኝ ዓመት ያህል የሆነ ሊያ ካሊፎርድ፣ ሞተች፤ እርሷም ከመሄዷ ከጥቂት ወራት በፊት በእውነት ተለውጣ ወደ እምነት መጥታ ነበር።
መስከረም 13። እስከ አሁን ምንም ርዳታ አልመጣም። በዚህ ጠዋት ለወንድሞችና ለእኅቶች ስለ ገንዘቡ ሁኔታ መንገርና ዕዳ ውስጥ ስለ መግባትና ስለ መሳሰሉት አስፈላጊ መመሪያዎችን መስጠት ፈጽሞ አስፈላጊ መሆኑን አገኘሁ። አብረን ጸለይን፤ እጅግ ደስ የሚል ስብሰባም አደረግን። ሁሉም የተረጋጉ ይመስሉ ነበር። በሦስቱ ቤቶች ካሉት ሣጥኖች አሥራ ሁለት ሽልንግ ስድስት ፔንስ ወጣ፤ ከሠራተኞቹ አንዱ አሥራ ሁለት ሽልንግ ሰጠ፤ ልጆቹ በሠሩት የስፌት ሥራም አንድ ፓውንድ አንድ ሽልንግ ገብቶ ነበር። በሥራው ከተሰማሩት እኅቶች አንዲቱ ለአንድ ዓመት ምንም ስለማትፈልግ ስለ ደመወዟ እንዳልጨነቅ ከኋላዬ መልእክት ላከችብኝ።
መስከረም 14። ጌታ እስከ አሁን ርዳታ ስላልላከ በዚህ ጠዋት እንደ ገና ከወንድሞችና ከእኅቶች ጋር ለጸሎት ተገናኘሁ። ከጸሎቱ በኋላ ከሠራተኞቹ አንዱ ያለውን ሳይሰጥ መጸለይ ቅንነት እንደማይሆን በመናገር ያለውን ገንዘብ ሁሉ፣ አሥራ ስድስት ሽልንግ፣ ሰጠኝ። ከእኅቶቹ አንዲቱ እንደዚህ ላለው የችግር ጊዜ በቁጠባ ባንክ ያስቀመጠችውን ስድስት ፓውንድ በስድስት ቀን ውስጥ እንደምትሰጥ ነገረችኝ። እስከ ዛሬ ድረስ የሦስቱ ቤቶች ሞግዚቶች ለዳቦ ጋጋሪዎቹና ለወተት ሻጩ በየሳምንቱ የመክፈል ልማድ ነበራቸው፤ ምክንያቱም እነርሱ ክፍያውን በዚህ መንገድ መቀበል ይመርጡ ነበርና፤ አንዳንድ ጊዜም ለሥጋ ሻጩና ለሸቀጥ ነጋዴው እንዲሁ ነበር። አሁን ግን ጌታ በቀን ስለሚሰጠን፣ የሳምንቱ ክፍያ ሊደርስ ስለሚችልና የምንከፍልበት ገንዘብ ስለማይኖረን፣ እንዲህም አብረውን የሚሠሩት በእኛ ምክንያት ሊቸገሩ፣ እኛም «ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ» የሚለውን የጌታን ትእዛዝ ተላልፈን ልንገኝ ስለምንችል፣ በዚህ መንገድ መቀጠል ስሕተት እንደ ሆነ እንቈጥራለን። ሮሜ 13፡8። ስለዚህ ከዚህ ቀን ጀምሮ ወደ ፊት፣ ጌታ ቀለባችንን በቀን እስከሚሰጠን ድረስ፣ እያንዳንዱን ዕቃ በተገዛ ጊዜ ወዲያው ለመክፈል፣ ምንም ያህል አስፈላጊ ቢመስልም፣ አብረውን የሚሠሩትም በሳምንት ብቻ እንዲከፈላቸው ምንም ያህል ቢፈልጉም፣ ወዲያው መክፈል ካልቻልን በቀር ምንም ነገር ላለመግዛት አስበናል። የነበረብንም ጥቂት ዕዳ በዚህ ቀን ተከፈለ።
መስከረም 15። ቅዳሜ። በዚህ ጠዋት እንደ ገና ለጸሎት ተገናኘን። እግዚአብሔር ልባችንን ያጽናናል። ርዳታን እንጠብቃለን። ለዛሬና ለነገ በቂ ቀለብ እንዳለ አገኘሁ፤ ነገር ግን ልጆቹ አዲስ የተጋገረ ዳቦ እንዳይበሉ እንደ ልማዱ ዳቦ የምንወስድበት ገንዘብ በእጃችን አልነበረም። በዚህ ከሰዓት በኋላ ለብዙ ቀናት ከብሪስቶል ርቆ የነበረ ከሠራተኞቹ አንዱ ተመልሶ አንድ ፓውንድ ሰጠ። በዚህ ምሽት እንደ ገና ለጸሎት ተገናኘን፤ ያን ጊዜም ከጠዋት ወዲህ ሌላ አሥር ሽልንግ ስድስት ፔንስ እንደ ገባ አገኘሁ። በዚህ አንድ ፓውንድ አሥር ሽልንግ ስድስት ፔንስ፣ በዚህ ቅዳሜ ምሽት እንኳ፣ የተለመደውን የዳቦ መጠን (ሰኞ ጠዋት ያደረ ዳቦ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል) መግዛት ቻልን፤ የተወሰነ ገንዘብም ተረፈን። ዛሬ እንደ ልማዱ ምንም ዳቦ እንዳንወስድ፣ ወዲያው ልንከፍልበት የማንችለውንም ምንም ነገር እንዳንገዛ ወደ መወሰን እንድንደርስ ጸጋን የሰጠን እግዚአብሔር ይመስገን። እርሱ አሁንም እንደሚያስበን፣ በራሱም ጊዜ የሚበልጥ ገንዘብ እንደሚልክልን ማረጋገጫ አድርገን ይህን ገንዘብ ከአባታችን እጅ በምስጋና እየተቀበልን እጅግ ተደስተን ነበር።