አሥርቱ ትእዛዛት
2.4 አራተኛው ትእዛዝ

ምዕራፍ 8 · 49 ደቂቃ ንባብ · 1 ሰዓት 3 ደቂቃ ማዳመጥ

2.4 አራተኛው ትእዛዝ

«የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራ፥ ሥራህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ በእነርሱም ያለውን ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባረከው ቀደሰውም።» ዘጸ 20፥8-11።

ይህ ትእዛዝ በእግዚአብሔር በገዛ ጣቱ በድንጋይ ላይ ተቀርጾ ነበር፤ በልባችንም ላይ ተቀርጾ ቢኖረን መጽናናታችን ይሆናል።

የሰንበት ቀን ለእግዚአብሔር የተከበረ አምልኮ የተለየ ነው፤ የእርሱ የራሱ የተከለለ ስፍራ ነውና ለተራ ጥቅም ተላልፎ መሰጠት የለበትም። ለዚህ ትእዛዝ መቅድም አድርጎ ማስታወሻ አኑሮበታል፤ «የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ።» ይህ «አስብ» የሚለው ቃል የሰንበትን ቅድስና ለመርሳት የተጋለጥን መሆናችንን ያሳያል፤ ስለዚህ ቀኑን መቀደስ እንድናስታውስ ማስታወሻ ያስፈልገናል።

I. በእነዚህ ቃላት ውስጥ የተከበረ ትእዛዝ አለ። «የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ።»

[1] የትእዛዙ ጉዳይ። ይህም ሰንበትን መቀደስ ነው፤ የሰንበት መቀደስ ደግሞ በሁለት ነገሮች ይፈጸማል፤ ከራሳችን ሥራ በማረፍና ሃይማኖታዊ ተግባራችንን በቅን ሕሊና በመፈጸም።

[2] ሰንበትን የመቀደስ ትእዛዝ የተሰጣቸው ሰዎች። እነርሱም ወይ የበላዮች ናቸው፤ እነዚህም በግል ደረጃ ያሉ እንደ ወላጆችና አሳዳሪዎች፥ ወይም በሕዝብ ደረጃ ያሉ እንደ ገዢዎች ናቸው፤ ወይ የበታቾች ናቸው፤ እንደ አገሩ ተወላጆች፥ ልጆችና አገልጋዮች፥ «ወንድ ልጅህም ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም ገረድህም»፤ ወይ የውጭ አገር ሰዎች ናቸው፤ «በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ»።

II. ሰንበትን የመቀደስን ይህን ትእዛዝ እንድንታዘዝ የሚያነሣሡ ምክንያቶች እነዚህ ናቸው፤

[1] ከአስተዋይነቱ። «ስድስት ቀን ሥራ፥ ሥራህንም ሁሉ አድርግ፤» እግዚአብሔር እንዲህ ያለ ያህል ነው፤ እኔ ጨካኝ ጌታ አይደለሁም፤ ሙያህን ለመከታተልና ሀብት ለማፍራት ጊዜ አልነፍግህም። ሥራህን ሁሉ የምትሠራበት ስድስት ቀን ሰጥቼሃለሁ፤ ለራሴም አንድ ቀን ብቻ ወስጃለሁ። ስድስት ቀን ለራሴ አስቀርቼ አንድ ቀን ብቻ ልፈቅድልህ በቻልሁ ነበር፤ ነገር ግን ለሙያህ ሥራ ስድስት ቀን ሰጥቼህ ለአገልግሎቴ አንድ ቀን ብቻ ወስጃለሁ። ስለዚህ ይህን ቀን ለአምልኮዬ በተለየ ሁኔታ ብትለየው ትክክልና አስተዋይነት ነው።

[2] ሰንበትን ለመቀደስ ሁለተኛው ምክንያት ከፍትሐዊነቱ የተወሰደ ነው። «ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው፤» እግዚአብሔር እንዲህ ያለ ያህል ነው፤ የሰንበት ቀን የእኔ ድርሻ ነው፤ በእርሱ ላይ የተለየ መብት እጠይቃለሁ፤ ሌላ ማንም በእርሱ ላይ ይገባኛል የሚለው የለም። ይህን ቀን የሚሰርቀኝና ለተራ ጥቅም የሚያውለው ቅዱስ ነገርን የሚዘርፍ ሰው ነው፤ ከሰማይ ዘውድ ይሰርቃል፤ እኔም በምንም ዓይነት ንጹሕ አድርጌ አልቈጥረውም።

[3] ሰንበትን ለመቀደስ ሦስተኛው ምክንያት እግዚአብሔር ራሱ ከጠበቀው የተወሰደ ነው። «በሰባተኛው ቀን ዐረፈ፤» ጌታ እንዲህ የሚል ያህል ነው፤ እኔን እንደ አርአያ አትከተሉምን? የፍጥረት ሥራዬን ሁሉ ከፈጸምሁ በኋላ በሰባተኛው ቀን ዐረፍሁ፤ እናንተም እንዲሁ ዓለማዊ ሥራችሁን ሁሉ በስድስቱ ቀናት ከሠራችሁ በኋላ አሁን ከሙያችሁ ድካም ልታርፉና ሰባተኛውን ቀን የቅዱስ ዕረፍት ቀን አድርጋችሁ ለእኔ ልትቀድሱት ይገባችኋል።

[4] ሰንበትን ለመቀደስ አራተኛው ምክንያት ab utili [ከጥቅሙ]፥ ማለትም ሰንበትን በሃይማኖት ከመጠበቅ ከሚገኘው ጥቅም የተወሰደ ነው። «እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም።» እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን የሾመው ብቻ ሳይሆን ባርኮታል። ለእግዚአብሔር የክብር ቀን ብቻ ሳይሆን ለእኛ የበረከት ቀን ነው፤ እኛ ለእግዚአብሔር አምልኮ የምንሰጥበት ቀን ብቻ ሳይሆን እርሱ ጸጋን የሚሰጠን ቀን ነው። በዚህ ቀን ከሰማይ በረከት ይንጠባጠባል። እግዚአብሔር ራሱ በእርሱ አይጠቀምም፤ በባሕርያዊ ክብሩ ላይ አንዲት ክንድ ልንጨምር አንችልም፤ የምንጠቀመው ግን እኛው ራሳችን ነን። ይህ ቀን በሃይማኖት ሲጠበቅ በነፍሳችን፥ በሀብታችንና በዘራችን ላይ በረከትን ያወርሳል። አለመጠበቁ ግን መርገምን ያመጣል። ኤር 17፥27። እግዚአብሔር የሰውን በረከቶች ይረግማል። ሚል 2፥2። የሚበላው እንጀራ በመርገም ይመረዛል፤ እንዲሁ ሰንበትን በቅን ሕሊና መጠበቅ ዓይነቱ ሁሉ በረከትን ይዞ ይመጣል። ሰንበትን ወደ መቀደስ የሚያነሣሡት ምክንያቶች እነዚህ ናቸው።

አሁን እንድታስተውሉት የምወደው ነገር ይህ ነው፤ ሰንበትን የመጠበቅ ትእዛዝ ከሥርዓተ አምልኮ ሕግ ጋር አልተሻረም፤ ፈጽሞ የሥነ ምግባር ትእዛዝ ነው እንጂ፤ መጠበቁም እስከ ዓለም ፍጻሜ ሊቀጥል ይገባል። እግዚአብሔር ከሰባት ቀን አንዱን ከመጠበቅ ነጻ እንዳደረገን የት ሊታይ ይቻላል?

እግዚአብሔር ሰንበትን ለምን ሾመ?

(1) ከራሱ አንጻር። እግዚአብሔር ከሰባት ቀናት አንዱን ለራሱ ቀጥተኛ አገልግሎት ማስቀረቱ ተገቢ ነው፤ ይህም አምልኮን ለማዘዝና የሚመለክበትንም ጊዜ ለመወሰን በእኛ ላይ ሥልጣን ያለው ታላቁ ባለ ሙሉ ሥልጣን፥ ማለትም ሉዓላዊ ጌታ መሆኑ እንዲታወቅ ነው።

(2) ከእኛ አንጻር። የሰንበት ቀን ለጥቅማችን ነው፤ በእኛ ውስጥ ቅድስናን ያሳድጋል። የሳምንቱ ቀናት ሥራ እግዚአብሔርንና ነፍሳችንን እንድንረሳ ያደርገናል፤ ሰንበት ግን እርሱን ወደ መታሰቢያችን መልሶ ያመጣዋል። የሚወድቀው የዓለም አቧራ የፍቅራችንን መንኰራኵሮች ዘግቶ ወደ እግዚአብሔር በጭንቅ እንዲንቀሳቀሱ ሲያደርጋቸው፥ ሰንበት መጥቶ የፍቅራችንን መንኰራኵሮች ዘይት ይቀባል፤ እነርሱም በፍጥነት ይሄዳሉ። እግዚአብሔር ሰንበትን የሾመው ለዚህ ዓላማ ነው። በዚህ ቀን አሳብ ወደ ሰማይ ይወጣል፤ አንደበት ስለ እግዚአብሔር ይናገራል፤ እንደ ፈጣን ጸሐፊ ብዕርም ይሆናል፤ ዓይኖች እንባ ያፈስሳሉ፤ ነፍስም በፍቅር ትቃጠላለች። ሳምንቱን ሁሉ በረዶ ሆኖ የነበረው ልብ በሰንበት በቃሉ ይቀልጣል። ሰንበት የሃይማኖት ወዳጅ ነው፤ የጸጋዎቻችንን ዝገት ይፍቃል፤ ነፍስ ከፈጣሪዋ ጋር ለመነጋገር የምትዘጋጅበት መንፈሳዊ ኢዮቤልዩ ነው።

ቀጥዬ የሰንበትን ቀን እንዴት መቀደስ እንዳለብን መንገዱንና ሁኔታውን ላሳያችሁ በተገባኝ ነበር፤ ነገር ግን ወደዚያ ከመድረሴ በፊት የምንመረምረው ታላቅ ጥያቄ አለን።

በመጀመሪያው ሥርዓት እንደ ነበረው የሰባተኛውን ቀን ሰንበት የማንጠብቀውና ወደ ሌላ ቀን የለወጥነው እንዴት ነው?

የአይሁድ ሰንበት የነበረው የቀድሞው የሰባተኛ ቀን ሰንበት ተሽሯል፤ በእርሱም ስፍራ የክርስቲያን ሰንበት የሆነው የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ተተክቷል። የአራተኛው ትእዛዝ የሥነ ምግባር ይዘት ወይም ፍሬ ነገር ሰባተኛውን ቀን በትክክል በመጠበቅ ላይ አይደለም፤ እግዚአብሔር የሾመው ከሰባት ቀን አንዱን መጠበቅ ነው እንጂ።

ነገር ግን የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በሰባተኛው ቀን ስፍራ የተተካው እንዴት ነው?

በቤተ ክርስቲያን ሥልጣን አይደለም። ሚስተር ፐርኪንስ «ቤተ ክርስቲያን ሰንበትን ለመሾም ሥልጣን የላትም» ይላል።

(1) ሰንበት ከሳምንቱ የመጨረሻ ቀን ወደ መጀመሪያው ቀን የተለወጠው በክርስቶስ በራሱ ሹመት ነው። እርሱ «ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው።» ማር 2፥28። ታዲያ ቀንን ሊሾም የሚችል ከጌታዋ በቀር ማን ነው? ይህን ቀን የሠራው እርሱ ነው። «እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት።» መዝ 118፥24። አርኖቢየስና አብዛኞቹ ተርጓሚዎች ይህን «የጌታ ቀን» ተብሎ ስለሚጠራው ስለ ክርስቲያን ሰንበት እንደ ተነገረ ይረዱታል። ራእ 1፥10። ጌታ እንጀራውንና ወይኑን ስለ ሠራውና ከተራ ጥቅም ለተለየና ለተቀደሰ ጥቅም ስለ ለየው «የጌታ እራት» እንደ ተባለ፥ እንዲሁ ጌታ ስለ ሠራውና ከተራ ቀናት ለተለየ አምልኮውና አገልግሎቱ ስለ ለየው የጌታ ቀን ተባለ። ክርስቶስ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ከመቃብር ተነሣ፤ በዚያም ቀን ለደቀ መዛሙርቱ ሁለት ጊዜ ተገለጠ፤ ዮሐ 20፥19, 26፤ ይህም አውግስጢኖስና አትናቴዎስ እንደሚሉት የአይሁድን ሰንበት ወደ ጌታ ቀን እንዳዛወረው ሊያመለክታቸው ነበር።

(2) የመጀመሪያውን ቀን መጠበቅ የሐዋርያት ልማድ ነበር። «ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ ... ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር።» ሐዋ 20፥7፤ 1ቆሮ 16፥2። በዚህ ቀን ስብከትም እንጀራ መቁረስም ነበረ። አውግስጢኖስ፥ ኢኖሰንቲየስና ኢሲዶር የወንጌል ሰንበታችንን መጠበቅ በሐዋርያት የጸና እንደ ሆነ ያስረዳሉ፤ በሐዋርያት ልማድ ኃይልም ይህ ቀን ለመለኮታዊ አምልኮ መለየት እንዳለበት ያረጋግጣሉ። ሐዋርያት ያደረጉትን በመለኮታዊ ሥልጣን አደረጉት፤ በመንፈስ ቅዱስ የተመሩ ነበሩና።

(3) የጥንቲቱ ቤተ ክርስቲያን አሁን የምናከብረውን የጌታን ቀን እጅግ ታከብረው ነበር። ይህን ቀን መጠበቅ የሃይማኖታቸው ታላቅ ምልክት ነበር። በሐዋርያው ዮሐንስ ዘመን የኖረው ከአባቶች እጅግ ጥንታዊው ኢግናጥዮስ እንዲህ የሚሉ ቃላት አሉት፤ «ክርስቶስን የሚወድ ሁሉ የሳምንቱን የመጀመሪያ ቀን፥ የጌታን ቀን፥ ይቀድስ።» ሊቁ ቡሰር እንደሚያስረዳው ይህ ቀን በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ከአሥራ ስድስት መቶ ዓመታት በላይ ሲጠበቅ ኖሯል። እንግዲህ የሰባተኛው ቀን ሰንበት ወደ መጀመሪያው ቀን ሰንበት እንዴት እንደ ተለወጠ ታያላችሁ።

የአይሁድን ሰንበት ወደ ጌታ ቀን ለመለወጥ ዋናው ምክንያት «በክርስቶስ የተፈጸመውን የቤዛነታችንን ምሥጢር» የሚያሳስበን መሆኑ ነው። እግዚአብሔር የቀድሞውን ሰንበት የሾመበት ምክንያት የፍጥረት መታሰቢያ እንዲሆን ነበር፤ አሁን ግን ከፍጥረት ይልቅ የከበረውን ሥራ፥ ማለትም ቤዛነትን ለማሰብ የሳምንቱን የመጀመሪያ ቀን በስፍራው አምጥቷል። የፍጥረት ሥራ ታላቅ ነበር፤ የቤዛነት ሥራ ግን ከዚያ የበለጠ ነበር። «የዚህ የኋለኛው ቤት ክብር ከፊተኛው ይበልጣል» እንደ ተባለ፥ ሐጌ 2፥9፥ እንዲሁ የቤዛነት ክብር ከፍጥረት ክብር በለጠ። እኛን በመፍጠር ታላቅ ጥበብ ታየ፤ እኛን በማዳን ግን ይበልጥ ድንቅ የሆነ ጥበብ ታየ። ከምንም በማምጣታችን ታላቅ ኃይል ታየ፤ ከምንም በከፋን ጊዜ በመርዳታችን ግን የበለጠ ኃይል ታየ። እኛን ከመፍጠር ይልቅ እኛን መቤዠት የበለጠ ዋጋ አስከፈለ። በፍጥረት ቃልን መናገር ብቻ ነበር (መዝ 148፥5)፤ በቤዛነት ግን ደም መፍሰስ ነበረ። 1ጴጥ 1፥19። ፍጥረት የእግዚአብሔር ጣቶች ሥራ ነበር፥ መዝ 8፥3፤ ቤዛነት ግን የክንዱ ሥራ ነበር። ሉቃ 1፥51። በፍጥረት እግዚአብሔር ራሳችንን ሰጠን፤ በቤዛነት ግን ራሱን ሰጠን። በፍጥረት በአዳም ሕይወት አለን፤ በቤዛነት በክርስቶስ ሕይወት አለን። ቈላ 3፥3። በፍጥረት በምድራዊ ገነት ላይ መብት ነበረን፤ በቤዛነት በሰማያዊ መንግሥት ላይ ባለ መብትነት አለን። ከፍጥረት የከበረ ሥራ የሆነውን ቤዛነታችንን ስለሚያሳስበን ክርስቶስ የሳምንቱን ሰባተኛ ቀን ወደ መጀመሪያው መለወጡ የተገባ ነው።

የመጀመሪያው ትግበራ። ከዚህ የማደርገው ትግበራ ይህ ነው፤ አሁን የምናከብረውን የክርስቲያን ሰንበት እጅግ ልናከብረው ይገባል። አይሁድ ሰንበትን «የቀናት ምኞትና የቀናት ንግሥት» ብለው ይጠሩት ነበር። እኛም ይህን ቀን «ደስታ፥ የእግዚአብሔር ቅዱስ፥ የከበረ» ብለን ልንጠራው ይገባል። ኢሳ 58፥13። የንጉሥ ማኅተም ያለበት ማዕድን የከበረና ታላቅ ዋጋ ያለው ነው። እግዚአብሔር በሰንበት ላይ ንጉሣዊ ማኅተሙን አኑሯል፤ የእግዚአብሔር ሰንበት ነው፤ ይህም የከበረ ያደርገዋል። ይህን ቀን ከሳምንቱ ቀናት ሁሉ የሚበልጥ አድርገን ልናየው ይገባል። ፊኒክስ በወፎች መካከል፥ ፀሐይ በፕላኔቶች መካከል እንደ ሆነ የጌታ ቀን በሌሎች ቀናት መካከል እንዲሁ ነው። «እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት።» መዝ 118፥24። እግዚአብሔር ቀናትን ሁሉ ሠራ፤ ይህን ግን ባረከው። ያዕቆብ ከወንድሙ በረከትን እንዳገኘ፥ እንዲሁ ሰንበት ከሳምንቱ ቀናት ሁሉ በረከትን አገኘ። ከእግዚአብሔር ጋር በተለየ ሁኔታ የምንነጋገርበት ቀን ነው። አይሁድ ሰንበትን «የብርሃን ቀን» ብለው ይጠሩት ነበር፤ እንዲሁ በዚህ ቀን የጽድቅ ፀሐይ በነፍስ ላይ ያበራል። ሰንበት የነፍስ የገበያ ቀን፥ የጊዜ ቅቤ ነው። ክርስቶስ ከመቃብር የተነሣበትና መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድር የወረደበት ቀን ነው። እንደ ዕጣን ወደ ሰማይ በሚወጣው የጸሎት መዓዛ የታጠነ ነው። በዚህ ቀን የመላእክት ምግብ የሆነው መና ይወርዳል። ይህ ጸጋዎች ድርሻቸውን የሚጫወቱበት የነፍስ የበዓል ቀን ነው፤ ሌሎቹ የሳምንቱ ቀናት አብዛኛውን ጊዜ በምድር ጉዳይ ይያዛሉ፤ ይህ ቀን ግን በሰማይ ጉዳይ፤ ያን ጊዜ ገለባ ትሰበስባላችሁ፤ አሁን ግን ዕንቍ። አሁን ክርስቶስ ነፍስን ወደ ተራራው ያወጣታል፤ የሚለውጥ የክብር ራእይም ያሳያታል። አሁን ሙሽራይቱን ወደ ወይን ቤት ያገባታል፤ የፍቅሩንም ዓላማ በላይዋ ይዘረጋል። አሁን የተቀመመ የወይን ጠጁንና የሮማኑን ጭማቂ ይሰጣታል። መኃ 2፥4፤ 8፥2። ጌታ አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ቀን ራሱን ለነፍስ አብልጦ ይገልጣል። ሐዋርያው ዮሐንስ በጌታ ቀን በመንፈስ ነበረ። ራእ 1፥10። በዚህ ቀን በመለኮታዊ ንጥቀት ወደ ሰማይ ተነጠቀ። በዚህ ቀን ክርስቲያን በከፍታዎች ላይ ነው፤ ከእግዚአብሔር ጋር ይሄዳል፤ በሰማይም ከእርሱ ጋር እንደሚመላለስ ይሆናል። 1ዮሐ 1፥3። በዚህ ቀን ቅዱስ ስሜቶች ይነቃቃሉ፤ የጸጋ ሀብት ይበዛል፤ የውስጥ ርኵሰቶች ይደክማሉ፤ ሰይጣንም በቃሉ ግርማ ፊት እንደ መብረቅ ይወድቃል። ክርስቶስ አብዛኞቹን ተአምራቱን በሰንበት አደረገ፤ አሁንም እንዲሁ ያደርጋል፤ የሞቱ ነፍሳት ይነሣሉ፤ የድንጋይ ልቦችም ሥጋ ይሆናሉ። ይህን ቀን እንዴት አብልጠን ልናከብረውና ልንፈራው ይገባል! ከቀይ ዕንቍ ይልቅ የከበረ ነው። እግዚአብሔር ከባልንጀሮቹ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀብቶታል። በሰንበት የመላእክትን ሥራ እንሠራለን፤ አንደበታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ተቃኝቷል። በምድር ያለው ሰንበት እግዚአብሔር መቅደስ፥ በጉም መብራቷ በሚሆንበት በሰማይ ተስፋ የምናደርገው የክብር ዕረፍትና የዘላለም ሰንበት ጥላና ምሳሌ ነው። ራእ 21፥22, 23።

ሁለተኛው ትግበራ። «ስድስት ቀን ሥራ።» እግዚአብሔር ማንም ያለ ሙያ እንዲኖር አይፈልግም፤ ሃይማኖት ለሥራ ፈትነት ፈቃድ አይሰጥም። በሰባተኛው ቀን ቅዱስ ዕረፍትን መጠበቅ ግዴታ እንደ ሆነ ሁሉ ስድስት ቀን መሥራትም ግዴታ ነው። «ሥራ ከቶ ሳይሠሩ፥ በሰው ነገር እየገቡ፥ ያለ ሥርዓት ከእናንተ ዘንድ ስለሚሄዱ ስለ አንዳንዶች ሰምተናልና። እንደነዚህ ያሉትንም በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን ይበሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን እንመክራቸውማለን።» 2ተሰ 3፥11። ክርስቲያን ሰማይን ብቻ ሳይሆን ሙያውንም ሊያስብ ይገባዋል። የመርከብ መሪ ዓይኑን ወደ ኮከቡ ሲያደርግ እጁን በመሪው ላይ ያደርጋል። ያለ ሥራ የሕዝብ ማኅበር ምሰሶዎች ይፈርሳሉ፤ ምድርም እንደ ሰነፍ እርሻ በኵርንችት ትወረሳለች። ምሳ 24፥31። አዳም በንጽሕናው ዘመን የዓለም ንጉሥ ቢሆንም ሥራ ፈት መሆን አልነበረበትም፤ ምድርን ሊያለማና ሊጠብቅ ይገባው ነበር። ዘፍ 2፥15። እግዚአብሔርን መምሰል ትጋትን አያስቀርም። የቆመ ውኃ ይገማል። ሕይወት የሌላቸው ፍጥረታት በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው። ፀሐይ በዙረቷ ትሄዳለች፤ ምንጭ ይፈስሳል፤ እሳትም ይፍለቀለቃል። ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ይሠራሉ። ሰሎሞን ሥራን እንድንማር ወደ ገብረ ጉንዳን ይልከናል። ምሳ 6፥6፤ 30፥25። ንብ የትጋት ምሳሌ ናት፤ ከንቦች አንዳንዶቹ ማሩን ያስተካክላሉ፥ ሌሎች ሰሙን ይሠራሉ፥ ሌሎች እንጀራውን ያዘጋጃሉ፥ ሌሎችም ሰነፉን ወንድ ንብ ለማስወጣት በቀፎው ደጅ ዘብ ይቆማሉ። ታዲያ ሰው ራሱን ለሥራ እጅግ አብልጦ ሊያለማምድ አይገባውምን? ያ በገነት የተሰጠው ሕግ ፈጽሞ አልተሻረም። «በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ።» ዘፍ 3፥19። በእምነት ስለ መኖር እያወሩ ያለ ሙያ የሚኖሩ እንዲህ ያሉ ሃይማኖተኞች የሚወደዱ አይደሉም፤ «አይደክሙም አይፈትሉምም» እንደ ተባለላቸው አበቦች ናቸው። ማቴ 6፥28። ቅዱስና ሊቅ የሆነው ሚስተር ፐርኪንስ እንዲህ ብሏል፤ «ሰው ግሩም ስጦታዎች ይኑሩት፥ ቃሉንም በአክብሮት ይስማ፥ ምሥጢረ ቍርባንንም ይቀበል፤ የሙያውን ተግባሮች ካልፈጸመ ግን ሁሉም ግብዝነት ብቻ ነው።» ሥራ ፈት ሰው ለምን ይጠቅማል? ሁልጊዜ በዳርቻ ላይ የተኛች መርከብ ምን ጥቅም አላት? ወይስ ተሰቅሎ የሚዝግ የጦር ዕቃ? ያለ ሙያ መኖር ሰውን ለፈተና ያጋልጣል። ሜላንክቶን ሥራ ፈትነትን የዲያብሎስ መታጠቢያ ይለዋል፤ በሥራ ፈት ነፍስ ውስጥ በደስታ ይታጠባልና። መሬት ጦም ሲያድር ዘር አንዘራበትም፤ ሰይጣን ግን አብዛኛውን የፈተና ዘሩን ጦም በሚያድሩና ያለ ሙያ በሆኑ ሰዎች ላይ ይዘራል። ሥራ ፈትነት የክፋት ሞግዚት ነው። የጥንቱ አሕዛብ ሴኔካ እንኳ Nullus mihi per otium dies exit ማለት ቻለ፤ «ያለ ሥራ የሚያልፍብኝ አንድም ቀን የለም።» ሥራ ፈት ሰው በዓለም ውስጥ እንደ ዜሮ ነው፤ እግዚአብሔርም በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ዜሮዎችን አይጽፍም። በመጽሐፍ ቅዱስ «የሥራ ፈትነትን እንጀራ» ስለ መብላትና «የግፍን ወይን» ስለ መጠጣት እናነባለን። ምሳ 31፥27፤ 4፥17። «የሥራ ፈትነትን እንጀራ» መብላት «የግፍን ወይን» እንደ መጠጣት ኃጢአት ነው። ሥራ ፈት ሰው ስለ ጊዜው ሒሳብ ሊሰጥ አይችልም። ጊዜ በግል ሙያችንም በአጠቃላይ ጥሪያችንም የምንነግድበት መክሊት ነው። ሰነፍ ሰው «መክሊቱን በምድር ይቀብራል»፤ ምንም መልካም አያደርግም፤ ጊዜውም ጠፋ እንጂ አልተኖረም። ሥራ ፈት ሰው ያለ ጥቅም ይኖራል፤ መሬትን በከንቱ ያጠፋል። እግዚአብሔር ሰነፉን ባሪያ «ክፉ» ብሎ ይጠራዋል። «አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ።» ማቴ 25፥26። ሕጎቹ በደም የተጻፉት ድራኮ ለኑሮአቸው መሥራት የማይፈልጉትን ሕይወታቸውን ያሳጣቸው ነበር። በኤትሩሪያ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ያሳድዱ ነበር። ሥራ ፈቶች «ስድስት ቀን ሥራ» የሚለውን ትእዛዝ እየጣሱ ይኖራሉ። ከሰማይ እንዳይሰደዱ ይጠንቀቁ። ሰው ባለማመን ወደ ሲኦል እንደሚሄድ ሁሉ በሙያው ባለመሥራትም ወደ ሲኦል ሊሄድ ይችላል።

ሰንበትን የመቀደስን ምክንያቶች ከተናገርሁ በኋላ አሁን ወደዚህ እመጣለሁ፤

III. ሰንበትን የመቀደስ ሁኔታ።

[1] በአሉታዊ መልኩ። በእርሱ ምንም ሥራ ልንሠራ አይገባንም። ትእዛዙ ይህ ነው፤ «በእርሱ ምንም ሥራ አትሥራ።» እግዚአብሔር ይህን ቀን ለራሱ ለይቶታል፤ ስለዚህ ማንኛውንም ዓለማዊ ሥራ በመሥራት እንደ ተራ ቀን ልንጠቀምበት አይገባንም። አብርሃም ሊሠዋ በሄደ ጊዜ አገልጋዮቹንና አህያውን ከተራራው ግርጌ እንደ ተወ፥ እንዲሁ በዚህ ቀን እግዚአብሔርን ልናመልክ ስንሄድ ዓለማዊ ጉዳይን ሁሉ በኋላችን ልንተው፥ አህያውን ከተራራው ግርጌ ልንተው ይገባናል። ዘፍ 22፥5። ዮሴፍ ከወንድሞቹ ጋር ሊነጋገር በወደደ ጊዜ ግብፃውያንን እንዳስወጣ፥ እንዲሁ በዚህ ቀን ከእግዚአብሔር ጋር ልንነጋገር ስንወድ ምድራዊ ሥራን ሁሉ ልናስወጣ ይገባናል። የጌታ ቀን የቅዱስ ዕረፍት ቀን ነው። ዓለማዊ ሥራ ሁሉ ቀኑን ማርከስ ነውና መቅረትና መቆም አለበት። «በዚያም ወራት በይሁዳ በሰንበት ቀን የወይን መጭመቂያ የሚረግጡትን፥ ነዶም የሚያመጡትን፥ በአህዮችም የሚጭኑትን፥ ደግሞም የወይን ጠጅና ወይን በለስም ሸክምም ሁሉ በሰንበት ቀን ወደ ኢየሩሳሌም የሚያመጡትን አየሁ፤ መሰከርሁባቸውም። የይሁዳንም ታላላቆች ተጣላኋቸው፥ ‹ይህ የምታደርጉት ክፉ ነገር ምንድር ነው? የሰንበትንስ ቀን ታረክሳላችሁን?› አልኋቸውም።» ነህ 13፥15, 17። እግዚአብሔር ለአምልኮው የለየውን ጊዜ ለዓለማዊ ሥራ መዝረፍ ቅዱስ ነገርን መዝረፍ ነው። ከሰንበት ጊዜ ማንኛውንም ለዓለማዊ ጉዳይ የሚያውል በአውራ ጎዳና ላይ ከሚዘርፍ የከፋ ሌባ ነው፤ ያኛው ሰውን ብቻ ይዘርፋልና፥ ይህኛው ግን እግዚአብሔርን ይዘርፋል። ጌታ መና በሰንበት እንዳይለቀም ከለከለ። ዘጸ 16፥26። መና «የሕይወታቸው ምርኵዝ» ስለ ነበረ የሚፈቀድ ይመስል ነበር፤ የሚወርድበትም ጊዜ ከንጋቱ በአምስትና በስድስት ሰዓት መካከል ስለ ነበረ በማለዳ ሊለቅሙት ይችሉ ነበር፤ የቀረውም የሰንበት ጊዜ ሁሉ በእግዚአብሔር አምልኮ ሊውል ይችል ነበር፤ ደግሞም ለእርሱ ብለው ረጅም መንገድ መሄድ አያስፈልጋቸውም ነበር፤ ከደጃቸው መውጣት ብቻ ነበርና፥ በድንኳኖቻቸውም ዙሪያ ይወድቅ ነበር፤ ቢሆንም በሰንበት ሊለቅሙት አልተፈቀደላቸውም፤ ይህን ለማድረግ ስላሰቡ ብቻም እግዚአብሔር እጅግ ተቈጣ። «በሰባተኛውም ቀን ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ሊለቅሙ ወጡ፥ ምንም አላገኙም። እግዚአብሔርም አለ፤ ትእዛዜንና ሕጌን ትጠብቁ ዘንድ እስከ መቼ እንቢ ትላላችሁ?» ዘጸ 16፥27, 28። ክርስቶስን በሞተ ጊዜ መቀባት በእርግጥ የሚመሰገን ሥራ ነበር፤ ነገር ግን መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብ እናት ማርያም የክርስቶስን ሥጋ ለመቀባት ሽቱ ቢያዘጋጁም ሰንበት እስኪያልፍ ድረስ ሊቀቡት ወደ መቃብሩ አልሄዱም። «በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ።» ሉቃ 23፥56። እጅ በጌታ ቀን በሥራ ከተጠመደ ልብ መርከሱ አይቀርም። አሕዛብ እንኳ በተፈጥሮ ብርሃን ለሐሰተኛ አማልክቶቻቸው አምልኮ በለዩት ጊዜ ምንም ዓለማዊ ሥራ አይሠሩም ነበር። የእስክንድርያው ቀሌምንጦስ ከሮም ነገሥታት አንዱ ለአማልክቱ በተወሰነው የአምልኮ ቀን የጦርነት ጉዳዮችን አቁሞ ጊዜውን በአምልኮ እንዳሳለፈ ይተርካል። በሰንበት የባርነት ሥራ መሥራት ሃይማኖት የሌለው ልብን ያሳያል፤ እግዚአብሔርንም እጅግ ያሳዝናል። በዚህ ቀን ዓለማዊ ሥራ መሥራት የዲያብሎስን ማረሻ መከተል ነው፤ ነፍስን ማዋረድ ነው። እግዚአብሔር ይህን ቀን የሠራው ልብን ወደ ሰማይ ለማንሣት፥ ከእርሱ ጋር ለመነጋገርና የመላእክትን ሥራ ለመሥራት ብሎ ነው፤ በምድራዊ ሥራ መጠመድ ደግሞ ነፍስን ከክብሯ ማዋረድ ነው። እግዚአብሔር ቀኑ በትንሹ ነገር እንኳ እንዲደፈር ወይም እንዲረክስ አይፈቅድም። በሰንበት እንጨት የለቀመውን ሰው በድንጋይ እንዲወገር አዘዘ። ዘኍ 15፥35። እሳት ለማንደድ ጥቂት እንጨት መልቀም ትንሽ ነገር ይመስል ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ይህ ቀን በትንሹ ነገር እንኳ እንዲጣስ አልፈቀደም። ይልቁንም ለመቅደሱ ግንባታ ድንጋይ መጥረብ እንደ ሆነው ያለ ከሃይማኖታዊ ጥቅም ጋር የተያያዘ ሥራ እንኳ በሰንበት ሊሠራ አልተፈቀደም። ድንጋዮቹን የሚጠርበውና ለመቅደሱ እንጨቱን የሚቀርጸው ባስልኤል በሰንበት ይህን ከማድረግ መታቀብ ነበረበት። ዘጸ 31፥15። መቅደስ የእግዚአብሔር የአምልኮ ስፍራ ነው፤ ነገር ግን በጌታ ቀን መቅደስን መሥራት ኃጢአት ነበር። ማንኛውንም የባርነት ሥራ ባለመሥራት የሰንበትን ቀን በአሉታዊ መልኩ መቀደስ ይህ ነው።

ይሁን እንጂ በዚህ ቀን የግድ አስፈላጊ የሆኑና የምሕረት ሥራዎች ሊሠሩ ይችላሉ። በእነዚህ ጉዳዮች እግዚአብሔር ምሕረትን ይወዳል እንጂ መሥዋዕትን አይደለም። (1) ለሰውነት የሚያስፈልገውን ምግብ መውሰድ ተፈቅዶአል። ምግብ ለሰውነት ዘይት ለመብራት እንደ ሆነ ነው። (2) የምሕረት ሥራዎችን መሥራት ተፈቅዶአል፤ ለምሳሌ የባልንጀራ ሕይወት ወይም ንብረት አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ መርዳት። በዚህ ረገድ አይሁድ ከመጠን በላይ ጥንቁቆችና ደረቆች ነበሩ፤ በሰንበት የምሕረት ሥራ እንዲሠራ አይፈቅዱም ነበርና። ሰው ቢታመም በዚህ ቀን ለመዳኑ መድኃኒት መጠቀም የማይገባ ይመስላቸው ነበር። ክርስቶስ በሰንበት ሰውን ስለ ፈወሰ እንደ ተቈጡበት ይወቅሳቸዋል። ዮሐ 7፥23። ቤት በእሳት ቢያያዝ አይሁድ ለማጥፋት ውኃ ማምጣት የማይገባ ይመስላቸው ነበር፤ መርከብም በዚህ ቀን ብታፈስ ቀዳዳዋን መድፈን የማይገባ ይመስላቸው ነበር። «ከመጠን በላይ ጻድቃን» ነበሩ፤ ቅንዓት የሚመስል ነገር ነበረ፤ ነገር ግን የሚመራው ማስተዋል ጐድሎት ነበር። ከእነዚህ ከሁለቱ ጉዳዮች፣ ማለትም ከአስፈላጊነትና ከምሕረት በቀር፣ ዓለማዊ ሥራ ሁሉ በጌታ ቀን ሊቆምና ሊተው ይገባዋል። «በእርሱ ምንም ሥራ አትሥራ።» ይህ በዚያ ቀን ጣቶቻቸውን በሥራ እጅግ የሚያረክሱትን በመካከላችን ያሉትን ብዙዎችን ይከስሳቸዋል ይፈርድባቸዋልም፤ አንዳንዶቹ ታላላቅ ግብዣዎችን ያዘጋጃሉ፤ ሌሎቹ የሱቃቸውን በር ይከፍታሉ፣ በሰንበትም ሥጋ ይሸጣሉ። መርከበኛው ከሰንበት በቀር ወደ ባሕር አይወጣም፤ እንዲሁም ሸራውን ሙሉ ዘርግቶ ይህን ትእዛዝ ወደ መተላለፍ ይሮጣል። ሌሎች በዚህ ቀን በስውር ይሠራሉ፤ የሱቃቸውን መስኮት ይዘጋሉ፣ ንግዳቸውንም በቤት ውስጥ ይቀጥላሉ፤ ነገር ግን ኃጢአታቸውን በመጋረጃ ሥር ለመሰወር ቢያስቡም እግዚአብሔር ያየዋል። «ከፊትህ ወዴት እሸሻለሁ?» «ጨለማ ከአንተ አይሰወርም።» መዝ 139፥7, 12። እንደነዚህ ያሉት ቀኑን ያረክሳሉ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ የበደል ክስ ያቀርባል።

[2] በአዎንታዊ መንገድ። የሰንበትን ቀን የምንቀድሰው ይህን ቀን «ለልዑል አምላክ አገልግሎት በመቀደስና በመለየት» ነው። በሰንበት ቀን ከሙያችን ሥራ ማረፍ መልካም ነው፤ ነገር ግን ከድካም አርፈን ከዚያ ሌላ ምንም ባናደርግ፣ በሬውና አህያውም እንደ እኛ ሰንበትን ይጠብቃሉ፤ እነርሱም ከድካም ያርፋሉና። ቀኑን ለእግዚአብሔር መቀደስ አለብን፤ «ሰንበትን መጠበቅ» ብቻ ሳይሆን ሰንበትን «መቀደስ» አለብን። የሰንበት መቀደስ በሁለት ነገሮች ይገኛል፤ (1) ለእርሱ በጥንቃቄ መዘጋጀት። አንድ መስፍን ወደ ቤትህ ቢመጣ እርሱን ለመቀበል ምንኛ ዝግጅት ታደርግ ነበር! ለእንደዚህ ያለ ታላቅ ሰው ክብርና ማዕረግ የሚስማማ ነገር እንዲኖር ቤቱን ትጠርግ፣ ወለሉን ታጥብ፣ ክፍሉንም እጅግ ውድ በሆኑ ምንጣፎችና መጋረጃዎች ታስጌጥ ነበር። በተባረከው ሰንበት እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ጣፋጭ ኅብረት ሊያደርግ ያስባል፤ ክርስቶስ ለዘኬዎስ እንዳለው ለአንተም የሚል ይመስላል፤ «ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ።» ሉቃ 19፥5። እንግዲህ ይህን የክብር ንጉሥ ለመቀበል ምን ዓይነት ዝግጅት ልታደርግ ይገባሃል? ቅዳሜ ምሽት ሲቃረብ የማፈግፈግ ጥሪ አሰማ፤ አእምሮህን ከዓለም መልሰህ ሐሳብህን በአንድነት ሰብስብ፤ በሚመጣውም ቀን ስላለው ታላቅ ሥራ አስብ። ለሰንበት ሥራ የማትመች የሚያደርጉህን ርኩሳን ስሜቶች ሁሉ አስወግድ። የምሽት ዝግጅት እንደ መሣሪያ ቅኝት ይሆናል፤ ልብን ለሚመጣው ሰንበት ተግባሮች ይበልጥ ያዘጋጀዋል።

(2) በቅድስና ማክበሩ። ለነፍሳችን ሽልማት የምናገኝበት፣ የእግዚአብሔርንም ሀልዎት አብዝተን የምንደሰትበት ቀን ስለ ሆነ ቀኑ ሲቀርብ ደስ ይበልህ። ዮሐ 8፥56። «አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ።» እንዲሁ የሰንበት ብርሃን ሲበራ ስናይ ደስ ሊለን ይገባል፤ «ሰንበትንም ደስታ ብለን ልንጠራው» ይገባናል፤ ይህ እግዚአብሔር በበረከት ያቀዳጀው የቀናት ንግሥት ነው። ኢሳ 58፥13። እግዚአብሔር ከሌሎቹ ቀናት ሁሉ እጥፍ መና ያዘነበበት አንድ ቀን በሳምንቱ ውስጥ እንደ ነበረ፣ እንዲሁ በሰንበት ከሌላው ቀን ሁሉ እጥፍ የሰማያዊ በረከቶችን መና ያዘንባል። ክርስቶስ ነፍስን ወደ ወይን ቤት የሚያገባበት፣ የፍቅርንም ዓላማ በላይዋ የሚዘረጋበት ቀን ይህ ነው፤ በዚህ ጊዜ የመንፈስ ጠል በነፍስ ላይ ይወርዳል፤ በዚህም ትነቃቃለች ትጽናናለችም። ብዙዎች የጌታን ቀን የዳግመኛ ልደታቸው ቀን ብለው ሊጽፉት ይችላሉ! ይህ የዕረፍት ቀን በሰማይ ላለው የዘላለም ዕረፍት መያዣና ቀብድ ነው። እንግዲህ ሲቀርብ ደስ አይለንምን? የጽድቅ ፀሐይ የሚበራበት ቀን የሐሤት ቀን ሊሆን ይገባዋል።

በሰንበት ማለዳ በጊዜ ተነሣ። ክርስቶስ በዚህ ቀን ፀሐይ ሳትወጣ በማለዳ ተነሣ። ዮሐ 20፥1። እርሱ እኛን ለማዳን በማለዳ ከተነሣ፣ እኛ እርሱን ለማምለክና ለማክበር በማለዳ አንነሣምን? «በማለዳ እፈልግሃለሁ።» መዝ 63፥1። በሌሎች ቀናት በጊዜ መነሣት እንችላለንን? ገበሬ በማለዳ ወደ ማረሻው ይሄዳል፤ መንገደኛም መንገዱን ለመሄድ በማለዳ ይነሣል፤ በዚህ ቀን ወደ ሰማይ የምንጓዝ እኛስ አንነሣምን? በእርግጥ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ብንወደው ነፍሳችን የምትወደውን እንድናገኘው በዚህ ቀን በጊዜ በተነሣን ነበር። በፊተኛው ሌሊት እስከ ምሽት በሥራ የሚያመሹ ግን በእንቅልፍ ስለሚዋጡ በሰንበት ማለዳ በጊዜ ለመነሣት ይቸገራሉ።

IV. ሰውነታችሁን ካለበሳችሁ በኋላ ቃሉን ለመስማት ነፍሳችሁን ማልበስ አለባችሁ። የእስራኤል ሕዝብ ሕጉ ከመሰጠቱ በፊት ራሳቸውን መታጠብ እንደ ነበረባቸው፣ እንዲሁ እኛም ነፍሳችንን ማጠብና ማንጻት አለብን፤ ይህም በንባብ፣ በማሰላሰልና በጸሎት ይሆናል። ዘጸ 19፥10።

[1] ቃሉን በማንበብ። ቃሉ ልብን ለመቀደስና ወደ ሰንበት መንፈስ ለማምጣት ታላቅ መንገድ ነው። «በእውነትህ ቀድሳቸው፤» ወዘተ። ዮሐ 17፥17። ቃሉን በግድየለሽነት ሳይሆን በቁም ነገርና በፍቅር አንብብ፤ እንደ ሰማይ ቃል፣ እንደ መዳን ምንጭ፣ እንደ ሕይወት መጽሐፍ። ዳዊት ስለ ክቡርነቱ ከወርቅ፣ ስለ ጣፋጭነቱም ከማር አብልጦ ቈጠረው። መዝ 19፥10። ቃሉን በትክክል በማንበብ ልባችን ሲደነዝዝ ይነቃቃል፤ ሲደነድን ይለሰልሳል፤ ሲቀዘቅዝና ሲረጋ ይቀጣጠላል፤ እንደ ደቀ መዛሙርቱም «ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?» ማለት እንችላለን። አንዳንዶች ከአልጋቸው ወጥተው በቀጥታ ወደ መስማት ይሄዳሉ። ብዙዎች በሰንበት ከተሰበከው ቃል ብዙ ጥቅም የማያገኙበት ምክንያት በማለዳ ቃሉን በማንበብ ከእግዚአብሔር ጋር ቁርስ ስላልበሉ ነው።

[2] ማሰላሰል። ወደ ማሰላሰል ተራራ ውጣ፤ በዚያም ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋገር። ማሰላሰል ማለት ነፍስ ወደ ውስጧ መመለሷ ነው፤ ይኸውም ስለ እግዚአብሔር በቁም ነገርና በጽሞና በማሰብ ልብ ወደ መለኮታዊ ስሜቶች ከፍ እንዲል ነው። ይህ ለሰንበት ማለዳ የሚገባ ሥራ ነው። በአራት ነገሮች ላይ አሰላስል።

(1) በፍጥረት ሥራዎች ላይ። ይህ በትእዛዙ ውስጥ ተገልጦአል። «እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም ፈጠረ፤» ወዘተ። ፍጥረት የእግዚአብሔር ጥበብና ኃይል በክብር ተገልጦ የምናይበት መስተዋት ነው። እግዚአብሔር ይህን ያማረ የዓለም ሕንጻ ቀድሞ ከነበረ ቁስ ሳይሆን በቃል ብቻ አስገኘው። «በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ጸኑ።» መዝ 33፥6። ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ባሕርን በቃል ጸጥ ማድረግ በመቻሉ ተደነቁ፤ ባሕርን በቃል መፍጠር ግን ከዚያ እጅግ የሚያስደንቅ ነበር። ማቴ 8፥26። በሰንበት ስለ ፈጣሪ ወሰን የለሽነት እናሰላስል። ወደ ጠፈር ቀና ብለህ ተመልከት፤ «በጥልቁም የእግዚአብሔርን ተአምራት» እይ። መዝ 107፥24። ወደ ምድርም ተመልከት፤ በዚያ የማዕድናትን ባሕርይ፣ የማግኔት ድንጋይን ኃይል፣ የዕፀዋትን ፈውስ፣ የአበባዎችንም ውበት ማየት እንችላለን። በእነዚህ እጅግ በጥበብ በተጠለፉ የፍጥረት ሥራዎች ላይ በማሰላሰል እግዚአብሔርን ማድነቅና ማመስገን እንማራለን። «አቤቱ፥ ሥራህ እንዴት በዛ! ሁሉን በጥበብ አደረግህ።» መዝ 104፥24። በፍጥረት ሥራዎች ላይ በማሰላሰል በእግዚአብሔር መታመንን እንማራለን። መፍጠር የሚችል ሊያቀርብም ይችላል፤ ምንም ሳንሆን ሊሠራን የቻለ ስንዋረድ ሊያነሣን ይችላል። «ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ በእግዚአብሔር ስም ነው።» መዝ 124፥8።

(2) በእግዚአብሔር ቅድስና ላይ አሰላስል። «ስሙ ቅዱስና የተፈራ ነው።» መዝ 111፥9። «ክፉን እንዳታይ ዓይኖችህ ንጹሓን ናቸው።» ዕን 1፥13። እግዚአብሔር በባሕርዩ፣ በመሠረቱና በሥራው ቅዱስ ነው። በሰዎችና በመላእክት ያለው ቅድስና ሁሉ ከዚህ ክቡር ምንጭ የሚፈስ የጠራ ጅረት ብቻ ነው። እግዚአብሔር ቅድስናን ይወዳል፤ የራሱ መልክ ነውና። ንጉሥ የራሱ ምስል በገንዘብ ላይ ታትሞ ማየትን ከመውደድ አይቀርም። እግዚአብሔር ቅድስናን ክብሩ፣ የዘውዱም እጅግ የሚያንጸባርቅ ዕንቍ አድርጎ ይቈጥረዋል። «በቅድስና የከበረ።» ዘጸ 15፥11። ሰንበትን ለመጀመር የሚገባ ማሰላሰል ይህ ነው። ይህን ማሰላሰላችን ለቅዱስ አምላክ የሚስማማ የልብ ሁኔታ በውስጣችን ያደርጋል፤ ስሙን እንድናከብርና ቀኑን እንድንቀድስ ያደርገናል። ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ቅድስና ስናሰላስል ወደ እርሱ አምሳል መለወጥ እንጀምራለን።

(3) ክርስቶስ እኛን በመዋጀት ባሳየው ፍቅር ላይ አሰላስል። ራእ 1፥5። ቤዛነት ከፍጥረት ይበልጣል፤ አንዱ የእግዚአብሔር ኃይል መታሰቢያ ነው፣ ሌላው የፍቅሩ። ለሰንበት የሚገባ ሥራ ይህ ነው። ወይ፣ የወደቁትን ምስኪን ፍጥረታት ከበደልና ከኵነኔ ሁኔታ ያነሣው የክርስቶስ ወሰን የለሽና አስደናቂ ፍቅር! አምላክ የነበረው ክርስቶስ መሞቱ! ይህ የከበረ የጽድቅ ፀሐይ መጨለሙ! ይህን ፍቅር በሰማይም እንኳ በበቂ ልናደንቀው አንችልም። ክርስቶስ ለኃጢአተኞች መሞቱ! ለኃጢአተኞች መላእክት ሳይሆን ለኃጢአተኞች ሰዎች። እንደነዚህ ያሉ የአፈርና የኃጢአት ጓሎች የክብር ብሩሃን ከዋክብት መደረጋቸው! ወይ፣ የክርስቶስ አስደናቂ ፍቅር! ይህ Illustre amoris Christi mnemosynum (የክርስቶስ ፍቅር ድንቅ መታሰቢያ) ነበር። ብሩጌንሲስ። ክርስቶስ ለኃጢአተኞች መሞቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ኃጢአተኛ መሞቱ! «ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።» 2ቆሮ 5፥21። በሥላሴ የከበሩ አካላት መካከል የነበረው እርሱ «ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ።» ኢሳ 53፥12። ኃጢአት ነበረበት ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ኃጢአታችን ተቈጥሮበት እንደ ኃጢአተኛ ሆነ። ኃጢአት በእርሱ ውስጥ አልኖረም፤ ነገር ግን በላዩ ተጫነበት። እኛን በመደነቅ ሊመታን የሚበቃ የፍቅር ብዛት እዚህ ነበረ። ክርስቶስ ምንም ነገር ለማትረፍ ወይም በእኛ በምንም ለመጠቀም ሳይጠብቅ እኛን መዋጀቱ! ሰዎች ትርፍ ካላስገኘላቸው በቀር ገንዘባቸውን ለግዢ አያወጡም፤ ነገር ግን ክርስቶስ እኛን በመግዛትና በመዋጀት ምን ጥቅም ሊጠብቅ ይችል ነበር? የክርስቶስን ፍቅር ልንገባውም ልንመልሰውም በማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ነበርን። ልንገባው አንችልም ነበር፤ በደማችን ውስጥ ነበርንና። ሕዝ 16፥6። እርሱን የሚማርክ መንፈሳዊ ውበት አልነበረንም። ይልቁንም በደማችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ላይ ጦር አንሥተን ነበር። «ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥» ሮሜ 5፥10። እርሱ ደሙን ሲያፈስስ እኛ መርዝ እንተፋ ነበር። ልንገባው እንዳልቻልን እንዲሁ ልንመልሰውም አንችልም ነበር። ስለ እኛ ከሞተ በኋላ እንኳ እርሱ እንድንወደው እስኪያደርገን ድረስ ልንወደው አልቻልንም። ስለ ፍቅሩ ምትክ ምንም ልንሰጠው አንችልም ነበር። «ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው?» ሮሜ 11፥35። በድህነት ውስጥ ወድቀን ነበር። ውበት ቢኖረን ከእርሱ ነው፤ «በአንቺ ላይ ባኖርሁት በጌጤ ፍጹም ነበረ።» ሕዝ 16፥14። መልካም ፍሬ ብናፈራ ከራሳችን የበቀለ አይደለም፤ ከእርሱ፣ ከእውነተኛው የወይን ግንድ ይመጣል። «ፍሬህ ከእኔ ዘንድ ይገኛል።» ሆሴ 14፥8። ክርስቶስ በእርግጥ ከእነርሱ ይጠቀማል ብሎ ሊጠብቅ የማይችላቸውን ለመዋጀት ደሙን ማፍሰሱ ከንጹሕ ፍቅር በቀር ሌላ አልነበረም። ክርስቶስ እንዲህ በፈቃዱ መሞቱ! «ነፍሴን አኖራለሁ።» ዮሐ 10፥17። እርሱ ባያኖራት ኖሮ አይሁድ ሊወስዷት ባልቻሉ ነበር። ጠባቂዎቹ እንዲሆኑ ብዙ ሌጌዎን መላእክትን ከአባቱ ሊጠራ ይችል ነበር፤ ነገር ግን የራሱ አምላክነት ከጥቃት ሁሉ ሊጠብቀው ሲችል ያ እንኳ ምን ያስፈልግ ነበር? ነፍሱን አኖረ። አይሁድ ለሞቱ ከተጠሙት ይልቅ እርሱ ለቤዛነታችን ተጠምቶ ነበር። «ነገር ግን የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፥ እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ?» ሉቃ 12፥50። መከራውን ጥምቀት ብሎ ጠራው፤ በገዛ ደሙ ሊጠመቅና ሊረጭ ነበረው፤ መከራውንም እስኪቀበል ድረስ ጊዜው ረዘመበት። ክርስቶስ ለመሞት ፈቃደኛ መሆኑን ለማሳየት መከራው መሥዋዕት ተብሎ ተጠርቶአል። «የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ» ዕብ 10፥10። ሞቱ በፈቃድ የቀረበ መሥዋዕት ነበር። ክርስቶስ በመከራው ሁሉ አለማጕረምረሙና እንደ ብዙ አለመቍጠሩ! ቢገረፍም ቢሰቀልም በሠራው ረክቶ ነበር፤ ቢያስፈልግም ዳግመኛ ያደርገው ነበር። «ከነፍሱ ድካም የተነሣ ያያል፥ ይጠግባልም።» ኢሳ 53፥11። ከባድ ምጥ ያጋጠማት እናት ልጅ ተወልዶ ስታይ ስለ ምጥዋ እንደማትጸጸት ይልቁንም እንደምትረካ፣ እንዲሁ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከባድ ምጥ ቢኖርበትም እንደ ብዙ አይቈጥረውም፤ የቤዛነት ወንድ ልጅ ወደ ዓለም ተወልዶ ስለሚያይ አይታወክም፤ ይልቁንም ላቡና ደሙ በሚገባ እንደ ተሰጠ ያስባል። ክርስቶስ ቤዛነትን ለአንዳንዶች እንጂ ለሌሎች ውጤታማ አለማድረጉ! እዚህ አስገራሚ ፍቅር አለ። ሁሉን ለማዳን በሥራው ዋጋ በቂነት ቢኖርም የማዳን ኃይሉን የሚካፈሉት አንዳንዶች ብቻ ናቸው፤ ሁሉ አያምኑምና። «ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ።» ዮሐ 6፥64። ክርስቶስ ስለ ሁሉ አይጸልይም። ዮሐ 17፥9። አንዳንዶች ይንቁታል። ይህ «ግንበኞች የናቁት ድንጋይ» ነው። መዝ 118፥22። ሌሎች ያፌዙበታል። ሉቃ 16፥14። ሌሎች ቀንበሩን ይጥላሉ። «ይህ በላያችን ሊነግሥ አንወድም» ሉቃ 19፥14። ስለዚህ ሁሉ በእርሱ የመዳን ጥቅም አያገኙም። የሞቱ ኃይል ለአንዳንዶች እንጂ ለሌሎች አለመድረሱ የክርስቶስ የሚለይ ፍቅር በዚህ ይገለጣል። «እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም።» 1ቆሮ 1፥26። ክርስቶስ ትውልድና ችሎታ ያላቸውን ብዙዎችን አልፎ የነጻ ጸጋ ዕጣ በአንተ ላይ መውደቁ፤ ደሙንም በአንተ ላይ መርጨቱ፤ «ወይ፣ የክርስቶስ ፍቅር ጥልቀት!» ክርስቶስ እንዲህ ባለ እጅግ የላቀ ፍቅር መውደዱ! ሐዋርያው «ከእውቀት የሚያልፍ ፍቅር» ብሎ ይጠራዋል። ኤፌ 3፥19። ከመላእክት አብልጦ መውደዱ! እነርሱን እንደ ወዳጆቹ ይወዳቸዋል፤ አማኞችን ግን እንደ ሙሽራው። እግዚአብሔር አብ ለእርሱ ባለው ዓይነት ፍቅር ይወዳቸዋል። «አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤» ዮሐ 15፥9። ወይ፣ ክርስቶስ እኛን በመዋጀት ምንኛ የበዛ ፍቅር ያሳያል! ክርስቶስ በቤዛነታችን ያሳየው ፍቅር ዘላለማዊ መሆኑ! «የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።» ዮሐ 13፥1። የክርስቶስ ፍቅር አቻ የሌለው እንደ ሆነ እንዲሁ ፍጻሜ የለውም። የፍቅሩ አበባ ጣፋጭ ነው፤ ይበልጥ ጣፋጭ የሚያደርገው ደግሞ ፈጽሞ አለመጠውለጉ ነው። ፍቅሩ ዘላለማዊ ሆኖአል። ኤር 31፥3። የተመረጠችውን ሙሽራውን ፈጽሞ አይፈታም። የሕዝቡ ድካሞች ፍቅሩን ፈጽመው ሊያስወግዱት አይችሉም፤ ሊያጨልሙት ይችላሉ እንጂ ፈጽመው ሊያርቁት አይችሉም፤ ድካማቸው ክርስቶስን በእነርሱ ላይ ሊያስቈጣው ይችላል፤ እንዲጠላቸው ግን አያደርገውም። ድካም ሁሉ የጋብቻን ማሰሪያ አይበጥስም። የክርስቶስ ፍቅር እንደ ቅዱሳን ፍቅር አይደለም። እነርሱ አንዳንድ ጊዜ ለእርሱ ብርቱ ፍቅር አላቸው፤ በሌላ ጊዜ ግን ስሜቱ ይበርዳል፤ በውስጣቸውም ጥቂት ወይም ምንም ፍቅር የሚንቀሳቀስ አያገኙም፤ የክርስቶስ ፍቅር ለእነርሱ ግን እንዲህ አይደለም፤ የዘላለም ፍቅር ነው። የክርስቶስ የመረጠ ፍቅር ፀሐይ አንድ ጊዜ በነፍስ ላይ ከወጣች በኋላ ፈጽሞ አትጠልቅም። ሞት ሕይወታችንን ከእኛ ሊወስድ ይችላል፤ የክርስቶስን ፍቅር ግን አይወስድም። እነሆ በሰንበት ማለዳ ለማሰላሰል ብርቅ የሆነ ርዕስ። ክርስቶስ እኛን በመዋጀት ባሳየው አስደናቂ ፍቅር ላይ ማሰላሰል በውስጣችን የሰንበት ልብ ሁኔታን ያደርጋል።

ይህ ማሰላሰል ስለ መንፈሳዊ ውለታ ቢስነታችን በእንባ ያቀልጠናል፤ እንዲህ ባለ ጣፋጭ አዳኝ ላይ መበደላችን፤ በፍቅሩ ከዚህ በላይ አለመነካታችን፣ ይልቁንም በበጎ ፈንታ ክፉ መመለሳችን፤ አርስጢድስ ብዙ መልካም አገልግሎት ቢያደርግላቸውም ከከተማቸው እንዳሳደዱት እንደ አቴና ሰዎች፣ እኛም እርሱን ከመቅደሳችን ማሳደዳችን፤ በትዕቢታችን፣ በችኩል ቍጣችን፣ በፍሬ ቢስነታችን፣ በጠላትነታችንና በእንግዳ መለያየቶቻችን ማሳዘናችን። ከወዳጃችን በቀር የምንበድለው የለንምን? ከአዳኛችን ርኅራኄ በቀር የምንረግጠው የለንምን? ክርስቶስ በመስቀል ላይ በቂ መከራ አልተቀበለምን፣ እኛ ደግሞ አብልጠን መከራ ልናጸናበት ይገባናልን? ተጨማሪ «ሐሞትና ሆምጣጤ እንዲጠጣ» እንሰጠዋለንን? ወይ፣ ልብን በኀዘን የሚያቀልጥና ዓይንን በእንባ የሚያፈስስ ነገር ቢኖር በክርስቶስ ላይ የሚደረግ ውለታ ቢስነት ነው። ጴጥሮስ ክርስቶስ እንዴት እንደ ወደደው፣ እንዴት ሐዋርያ እንዳደረገው፣ የልቡንም ምሥጢር እንደ ገለጠለት፣ ወደ መልክ መለወጫውም ተራራ እንደ ወሰደው፣ ሆኖም እርሱ እንደ ካደው ባሰበ ጊዜ ልቡ በኀዘን ተሰበረ፤ «ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።» ማቴ 26፥75። በሰንበት ዓይን እንባ ሲያፈስስ ምንኛ የተባረከ ነገር ነው! የክርስቶስን ለእኛ ያለውን ፍቅርና የእኛን ለእርሱ ውለታ ቢስነት ከማሰላሰል ይበልጥ ፈጥኖ እንባን የሚያመጣ ምንም የለም።

በጌታ ቀን ማለዳ የክርስቶስን ፍቅር ማሰላሰል በልባችን ለእርሱ ፍቅርን ያቀጣጥላል። ስለ እኛ ደሙን ሲያፈስስና ሲሞት እያየን ልባችን ለእርሱ በፍቅር እንዴት አይሞቅም? ፍቅር የሃይማኖት ነፍስ፣ እጅግ የጠራ ስሜት ነው። ክርስቶስ የሚያከብረው የዘይት ወንዞችን ሳይሆን የፍቅር ፍንጣሪዎችን ነው። በእርግጥም ዳዊት «ሳሰላስል እሳት ነደደ» (መዝ 39፥3) እንዳለ፣ እንዲሁ ክርስቶስ እኛን በመዋጀት ባሳየው ፍቅር ላይ ስናሰላስል የፍቅራችን እሳት ወደ እርሱ ይነድዳል፤ ክርስቲያኑም እንደ ሱራፌል ለክርስቶስ በፍቅር ሲነድድ በዚያን ጊዜ በተባረከ የሰንበት ልብ ሁኔታ ውስጥ ይሆናል።

(4) በሰንበት ማለዳ ስለ ሰማይ ክብር አሰላስል። ሰማይ የደስታ ፍሬ ነገርና ዋና ነገር ነው። መንግሥት ተብሎ ተጠርቶአል። ማቴ 25፥34። ስለ ባለ ጠግነቱና ስለ ግርማው መንግሥት ተባለ። በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቍ ደጆች ተገልጦአል። ራእ 21፥19, 21። በዚያ በእውነት የከበረ ሁሉ አለ፤ የጠራ ብርሃን፣ ፍጹም ፍቅር፣ ያልጐደፈ ክብር፣ ያልተቀላቀለ ደስታ፤ የሰማያዊቱንም ገነት ደስታ የሚያቀዳጀው ዘላለማዊነቱ ነው። የምድር መንግሥታት ካሉበት ይልቅ የከበሩ ቢሆኑ፣ መሠረታቸው ወርቅ፣ ቅጥራቸው ዕንቍ፣ መስኮቶቻቸውም ሰንፔር ቢሆኑ እንኳ የሚጠፉ ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት ግን ዘላለማዊ ናት፤ እነዚያ የደስታ ወንዞች «ለዘላለም» ይፈስሳሉ። መዝ 16፥11። የክብር ዋና ነገር የሆነውና ሰማይን ሰማይ የሚያደርገው የተባረከውን እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየትና በእርሱ መደሰት ነው። «በነቃሁ ጊዜ በመልክህ እጠግባለሁ።» መዝ 17፥15። ወይ፣ በላይ ስላለችው ኢየሩሳሌም አስብ!

ይህ ለሰንበት የሚገባ ነው። ስለ ሰማይ ማሰላሰል ልባችንን ከዓለም በላይ ከፍ ያደርገዋል። ወይ፣ አእምሮአችን ከሚታዩ ነገሮች በላይ ቢወጣና ክብርን አሻግረን ብናይ ምድራዊ ነገሮች እንዴት በጠፉና ወደ ምንምነት በጠበቡ ነበር! ስለ ሰማይ ማሰላሰል በሰንበት አምልኮአችን እንዴት ሰማያውያን ባደረገን ነበር! ስሜትን ያነቃቃል፣ ለአምልኮ ክንፍ ይጨምራል፣ «በጌታ ቀን በመንፈስ» እንድንሆንም ያደርገናል። ራእ 1፥10። የክብር አክሊል ሁልጊዜ በዓይኑ ፊት ያለው ሰው እግዚአብሔርን እንዴት በብርታት ያገለግላል!

[3] በሰንበት ማለዳ ነፍሳችንን የምናለብሰው በጸሎት ነው፤ «አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ» ወዘተ። ማቴ 6፥6። ጸሎት ሰንበትን ይቀድሳል።

(1) በሰንበት ማለዳ ልንጸልይላቸው የሚገቡን ነገሮች። በሚሰበከው ቃል ላይ በረከትን እንለምን፤ ለእኛ የሕይወት መዓዛ እንዲሆን፣ በእርሱም አእምሮአችን ይበልጥ እንዲበራ፣ ብልሹ ምኞቶቻችን ይበልጥ እንዲደክሙ፣ የጸጋችንም ሀብት ይበልጥ እንዲበዛ። የእግዚአብሔር ልዩ ሀልዎት ከእኛ ጋር እንዲሆን፣ እግዚአብሔር ሲናገር ልባችን በውስጣችን እንዲቃጠል፣ ቃሉን በየዋህና በትሑት ልብ እንድንቀበል፣ ለእርሱም እንድንገዛና ፍሬ እንድናፈራ እንጸልይ። ያዕ 1፥21። ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ልንጸልይ ይገባናል።

ቃሉን ለሚያካፍለው ጸልይ፤ አንደበቱ ከእግዚአብሔር መሠዊያ በተወሰደ ፍም እንዲነካ፤ ሌሎችን ለማሞቅ የሚረዳውን የእርሱን ልብ እግዚአብሔር እንዲያሞቀው። ጸሎታችሁ አገልጋዩን ለማነቃቃት መንገድ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ከተሰበከው ቃል ምንም ጥቅም እንዳላገኙ ያማርራሉ፤ ምናልባት ለአገልጋያቸው እንደሚገባ አልጸለዩለት ይሆናል። ጸሎት መሣሪያን እንደ መሳልና እንደ ማሾል ነው፤ ይበልጥ እንዲቈርጥ ያደርገዋል። ከቤተሰብህ ጋር ጸልይ፤ ስለ እነርሱም ጸልይ። ደግሞም በዚህ ቀን በእግዚአብሔር ፍርሃት ለሚሰበሰቡ ጉባኤዎች ሁሉ ጸልይ፤ የመንፈስ ጠል ከቃሉ መና ጋር እንዲወርድ፣ አንዳንድ ነፍሳት እንዲመለሱ ሌሎችም እንዲበረቱ፣ የወንጌል ሥርዓቶች እንዲቀጥሉና ምንም ዕንቅፋት እንዳይጣልባቸው። ልንጸልይላቸው የሚገቡን ነገሮች እነዚህ ናቸው። የምሕረት ዛፍ በጸሎት እጅ ካልተነቀነቀ ፍሬውን አይጥልም።

(2) የጸሎታችን ሁኔታ። ጸሎትን መናገር ብቻ አይበቃም፤ እግዚአብሔር እምቢ እንዲል በሚጠይቅ በደነዘዘና በቀዘቀዘ ሁኔታ መጸለይም አይበቃም፤ ነገር ግን በአክብሮት፣ በትሕትና፣ በትጋትና በእግዚአብሔር ምሕረት ተስፋ በማድረግ መጸለይ አለብን። ሉቃ 22፥44። ክርስቶስ አጽንቶ ይጸልይ ነበር። ይበልጥ በትጋት እንድንጸልይ ጕድለታችን እየተሰማን መጸለይ አለብን። በችግር የተጨነቀ ምጽዋት ሲለምን ይተጋል። ይበልጥ እየተሰማው የሚጸልይ ይበልጥ በትጋት ይጸልያል። የሰንበትን ማለዳ መቀደስ ይህ ነው፤ ለሚሰበከውም ቃል መልካም ዝግጅት ነው። መሬት በማረሻ ሲታረስ ዘርን ለመቀበል ይዘጋጃል፤ ልብም በጸሎት ሲሰበር የተሰበከውን ቃል ዘር ለመቀበል ይዘጋጃል።

V. እንዲህ ነፍሳችሁን በማለዳ ካለበሳችሁ በኋላ ሰንበትን ይበልጥ ለመቀደስ የተሰበከውን ቃል ለመስማት ራሳችሁን አቅርቡ።

በመቀመጫህ ስትቀመጥ በሚካፈለው ቃል ላይ በረከትን ለመለመን ዓይንህን ወደ ሰማይ አንሣ፤ የተሰበከው ቃል እንደ መድኃኒት በራሱ ባለው ኃይል ሳይሆን ከሰማይ በሆነ ኃይልና በመንፈስ ቅዱስ አብሮ መሥራት እንደሚሠራ ማወቅ አለብህና። ስለዚህ ለአንተ ውጤታማ እንዲሆን በቃሉ ላይ በረከትን የሚለምን አጭር የልብ ጸሎት አቅርብ።

ቃሉ መሰበክ ሲጀምር በአክብሮትና በቅዱስ ትኩረት ስማው። «ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።» ሐዋ 16፥14። ንጉሠ ነገሥቱ ቆስጠንጢኖስ ቃሉን በአክብሮት በማዳመጡ ይታወቅ ነበር። ክርስቶስ ዕለት ዕለት በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ «ሕዝቡ ሁሉ ሲሰሙት ተንጠልጥለውበት ነበርና።» ሉቃ 19፥48። በግሪኩ «በከንፈሩ ላይ ተንጠልጥለው ነበር» ይላል። ለሰዎች ስለ ባለ ጠጋ ግዢ ብንነግራቸው በትጋት ያዳምጡ ነበር፤ የጸጋ ወንጌል ሲሰበክላቸውማ እንዴት አብልጠው አያዳምጡም? ሰንበትን በትኩረት በመስማት እንድንቀድስና እንድናከብር በመስማት ጊዜ ከእነዚህ ከሁለት ነገሮች ተጠንቀቁ፤ ከሐሳብ መበተንና ከእንቅልፍ ማንጐላጀት።

[1] የሐሳብ መበተን። «ሳትባክኑም በጌታ እንድትጸኑ» 1ቆሮ 7፥35። ስለ በርናርድ ወደ ቤተ ክርስቲያን በር በደረሰ ጊዜ «ምድራዊ ሐሳቦቼ ሁሉ ሆይ፣ በዚህ ቆዩ» ይል እንደ ነበር ይነገራል። እንዲሁ እኛም በእግዚአብሔር ቤት ደጅ ስንደርስ ለራሳችን «ዓለማዊ ጭንቀቶቼና ተቅበዝባዥ ሐሳቦቼ ሁሉ ሆይ፣ በዚህ ቆዩ፤ እኔ አሁን ጌታ የሚለኝን ልሰማ እሄዳለሁ» ማለት ይገባናል። የሐሳብ መበተን አምልኮን ያደናቅፋል። አእምሮ በከንቱ ሐሳቦች ይናወጣል፤ ከያዘውም ሥራ ይመለሳል። እንደ ፈሳሽ ብር የሚንቀዠቀዥ ልብን ማጽናት ከባድ ነው። ጀሮም ስለ ራሱ ያማርራል፤ «አንዳንድ ጊዜ በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ሳለሁ per porticus diambulo፣ በሰገነቶቹ ውስጥ እመላለሳለሁ፤ አንዳንድ ጊዜም ሒሳብ እሠራለሁ።» ቃሉን በመስማት ጊዜ ሐሳቦች ምን ያህል ጊዜ ወዲያና ወዲህ ይዘላሉ፤ ዓይን በአገልጋዩ ላይ ሳለም አእምሮ በሌሎች ነገሮች ላይ ነው። የተበተነ መስማት ሰንበትን ከመቀደስ እጅግ የራቀ ነው። በዚህ ጊዜ ለከንቱ ሐሳቦች ቦታ መስጠት እጅግ ኃጢአት ነው፤ ቃሉን ስንሰማ በእግዚአብሔር ልዩ ሀልዎት ፊት ነንና። በንጉሥ ፊት የክህደት ድርጊት መፈጸም እጅግ ታላቅ ድፍረት ነው። «በቤቴ ውስጥ ደግሞ ክፋታቸውን አገኘሁ።» ኤር 23፥11። እንዲሁ ጌታ «በቤቴ ውስጥ ቃሌን ሲሰሙ ክፋትን አገኘሁ፤ ዓይኖቻቸው ሴሰኞች ናቸው፤ ነፍሳቸውም በከንቱነት ላይ ተተክላለች» ሊል ይችላል።

እነዚህ በመስማት ጊዜ የሚቅበዘበዙና የሚበትኑ ሐሳቦች ከየት ይመጣሉ?

(1) በከፊል ከሰይጣን። ዲያብሎስ በጉባኤዎቻችን ውስጥ መገኘቱ አይቀርም። ከመስማት ሊከለክለን ባይችል በመስማት ውስጥ ያደናቅፈናል። «የእግዚአብሔር ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ሊቆሙ በመጡ ጊዜ ሰይጣን ደግሞ በመካከላቸው መጣ።» ኢዮ 1፥6። ዲያብሎስ ትኩረትን ለማስቀየር ከንቱ ነገሮችን በምናብ ፊት ያቀርባል። ታላቁ ዓላማው ቃሉን ፍሬ ቢስ ማድረግ ነው። አንድ ሰው ሲጽፍ ሌላው ቀጥ አድርጎ መጻፍ እንዳይችል እንደሚገፋው፣ እንዲሁ ስንሰማ ዲያብሎስ ለተሰበከው ቃል እንዳናዳምጥ በፈተና ይገፋናል። «ታላቁንም ካህን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ፣ ሰይጣንም ሊቃወመው በቀኙ ቆሞ አሳየኝ።» ዘካ 3፥1።

(2) እነዚህ በመስማት ጊዜ የሚቅበዘበዙ ሐሳቦች በከፊል ከራሳችን ይመጣሉ። ነቀፋውን ሁሉ በሰይጣን ላይ መጣል የለብንም።

ከዓይን ይመጣሉ። የሚቅበዘበዝ ዓይን የሚቅበዘበዙ ሐሳቦችን ያመጣል። ሌባ በመስኮት ወደ ቤት ሊገባ እንደሚችል፣ እንዲሁ ከንቱ ሐሳቦች በዓይን ሊገቡ ይችላሉ። ወደ እግዚአብሔር ቤት ስንገባ እግራችንን እንድንጠብቅ እንደ ታዘዝን (መክ 5፥1)፣ እንዲሁ ሌሎች ነገሮችን በማየት እንዳንበተን ከዓይናችን ጋር ቃል ኪዳን ማድረግ ያስፈልገናል። ኢዮ 31፥1።

በመስማት ጊዜ የሚቅበዘበዙ ሐሳቦች ከልብ ይነሣሉ። እነዚህ ፍንጣሪዎች ከራሳችን እቶን ይወጣሉ። ከንቱ ሐሳቦች ልብ እንደ ተናወጠ ባሕር የሚተፋው ጭቃ ናቸው። «ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥» ማር 7፥21። የሆድ ርኩሰት ወደ ራስ ጢስ እንደሚያወጣ፣ እንዲሁ የልብ ብልሹነት ወደ አእምሮ ክፉ ሐሳቦችን ይልካል።

በመስማት ጊዜ የሚበተኑ ሐሳቦች ከክፉ ልማድ ይወጣሉ። በሌላ ጊዜ ራሳችንን ከከንቱ ሐሳቦች ጋር እናለማምዳለን፤ ስለዚህ በሰንበት ልንከለክላቸው አንችልም። ልማድ ሁለተኛ ተፈጥሮ ነው። «ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? እንዲህ ከሆነ ክፉ ማድረግን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ መልካም ማድረግ ትችላላችሁን?» ኤር 13፥23። ከክፉ ባልንጀሮች ጋር መዋልን የለመደ እንዴት እንደሚተዋቸው አያውቅም፤ እንዲሁ ሳምንቱን ሙሉ ከንቱ ሐሳቦች አብረዋቸው የሚኖሩ በሰንበት እንዴት እንደሚገላገሏቸው አያውቁም። እነዚህ በመስማት ጊዜ የሚበትኑ ከንቱ ሐሳቦች ምን ያህል ክፉ እንደ ሆኑ ላሳያችሁ፤ —

[1] በመስማት ጊዜ ልብ መበተኑ የእግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂነት አለማክበር ነው። እግዚአብሔር ሁሉን የሚያይ መንፈስ ነው፤ ቃላት በጆሮአችን ከሚሰሙት ይልቅ ሐሳቦች በጆሮው አብልጠው ይጮኻሉ። «አሳቡንም ለሰው የሚናገር» አሞ 4፥13። በመስማት ጊዜ ስለ ተቅበዝባዥ ሐሳቦች ግድ አለማለት ልባችንን እንደማያውቅ ወይም የሐሳባችንን ቋንቋ እንደማይሰማ ያህል የእግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂነት መድፈር ነው።

[2] በመስማት ጊዜ ለተቅበዝባዥ ሐሳቦች ቦታ መስጠት ግብዝነት ነው። እግዚአብሔር የሚለውን የምንሰማ እንመስላለን፤ አእምሮአችን ግን ፈጽሞ በሌላ ነገር ላይ ነው። ሰውነታችንን ለእግዚአብሔር እናቀርባለን፤ ልባችንን ግን አንሰጠውም። ሆሴ 7፥11። እግዚአብሔር ስለዚህ ግብዝነት ያማርራል። «ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፥ በከንፈሩም ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው።» ኢሳ 29፥13። ይህ በእግዚአብሔር ፊት ማወላወልና በሐሰት መመላለስ ነው።

[3] በመስማት ጊዜ ከንቱ ሐሳቦች ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር እጅግ መጕደሉን ይገልጣሉ። ብንወደው ኖሮ ቃሉን እንደ መለኮታዊ ቃል ባዳመጥን፣ በልባችንም ጽላት ላይ በጻፍነው ነበር። ምሳ 3፥3። የምንወደው ወዳጅ ሲያናግረንና ምክር ሲሰጠን በቁም ነገር እናዳምጣለን፤ ቃሉንም ሁሉ እንመጥጣለን። በቅዱስ ተግባሮች ውስጥ ሐሳባችን እንዲንከራተት መፍቀዳችን ለእግዚአብሔር ባለን ፍቅር ታላቅ ጕድለት እንዳለ ያሳያል።

[4] በመስማት ጊዜ የማይገቡ ከንቱ ሐሳቦች ሥርዓትን ያረክሳሉ። በሽቱ ዕቃ ውስጥ እንዳሉ የሞቱ ዝንቦች ናቸው። የበገና አውታር ቅኝቱ ሲጠፋ ሙዚቃውን ያበላሻል፤ እንዲሁ የሐሳብ መበተን አእምሮን ከቅኝት ያወጣል፣ አገልግሎታችንንም ሻካራና የማያስደስት ድምፅ ያሰማዋል። ተቅበዝባዥ ሐሳቦች ተግባርን ይመርዛሉ፣ ወደ ኃጢአትም ይለውጡታል። «ጸሎቱም ኃጢአት ትሁንበት።» መዝ 109፥7። የሰው ጸሎትና ቃሉን መስማቱ ኃጢአት ከመሆን ምን የከፋ ነገር አለ? የምንበላው ምግብ ክፉ ደዌን ቢያበዛ አያሳዝንምን? የነፍስ ምግብ የሆነውን ቃል መስማት ወደ ኃጢአት ሲለወጥማ ምንኛ ይብሳል!

[5] በመስማት ጊዜ ከንቱ ሐሳቦች እግዚአብሔርን ያስቀይማሉ። ንጉሥ ከተገዢዎቹ አንዱን ሲያናግር፣ ያ ሰው ንጉሡ ለሚለው ትኩረት ሳይሰጥ ስለ ሌላ ጉዳይ ቢያስብ ወይም በላባ ቢጫወት፣ ንጉሡ አይቈጣምን? እንዲሁ በእግዚአብሔር ፊት ሆነን እርሱ በቃሉ ሲናገረን የሚለውን ብዙም ሳንከታተል ልባችን ግን ስስትን ቢከተል፣ እንዲህ መናቁ እግዚአብሔርን አያስቀይመውምን? ሕዝ 33፥31። በእንደነዚህ ያሉት ላይ እርግማንን አውጆአል። «በመንጋው ውስጥ ተባዕት እያለው ለጌታ ነውረኛውን የሚሠዋ አታላይ ርጉም ይሁን።» ሚል 1፥14። ብርቱና ሕያው ስሜት መኖር በመንጋ ውስጥ ተባዕት እንዳለ ነው፤ ቃሉን በመበተን መስማት ግን በከንቱ ሐሳቦች በዝንብ እንደ ተበላሹ ተግባሮችን ለእግዚአብሔር መስጠትና እርግማንን የሚያመጣ ነውረኛ ነገር ለጌታ ማቅረብ ነው። «አታላይ ርጉም ይሁን።»

[6] በመስማት ጊዜ ከንቱ ሐሳቦች ሲፈቀዱና ሳይቃወሙ ሲቀሩ ለልብ መደንደን መንገድ ይከፍታሉ። በልብ ያለ ድንጋይ በኩላሊት ካለው ይከፋል። በመስማት ጊዜ የሚበተኑ ሐሳቦች ልብን አያሻሽሉትም፤ ይልቁንም ያደነድኑታል። ከንቱ ሐሳቦች በልብ ላይ ሊሆን የሚገባውን ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍርሃት ያስወግዳሉ፤ ሕሊናን ርኅራኄ የሌለው ያደርጋሉ፤ ቃሉም በልብ ላይ ሊኖረው የሚገባውን ኃይል ያደናቅፋሉ።

[7] ከንቱና የሚበትኑ ሐሳቦች የሥርዓትን መጽናናት ይሰርቁናል። ጸጋ ያላት ነፍስ ብዙ ጊዜ በመቅደስ ከእግዚአብሔር ጋር ትገናኛለች፤ «ነፍሴ የምትወድደውን አገኘሁት» ማለትም ትችላለች። መኃ 3፥4። በበትሩ ላይ ያለውን ማር በቀመሰ ጊዜ ዓይኖቹ እንደ በሩለት እንደ ዮናታን ናት። ከንቱ ሐሳቦች ግን ጥቁር ደመና የፀሐይን ሞቃትና አጽናኝ ጨረሮች እንደሚሰውር የሥርዓትን መጽናናት ያደናቅፋሉ። አእምሮአችን ሲንከራተትና ሐሳባችን እስከ ምድር ዳርቻ ሲጓዝ እግዚአብሔር ሰላምን ይነግረናልን? ምሳ 17፥24። ቃሉን በትኩረት ልትሰሙ ብትወዱ አብርሃም ወፎችን ከመሥዋዕቱ ባባረረ ጊዜ እንዳደረገ አድርጉ። ዘፍ 15፥11። በመስማት ጊዜ እነዚህን መውጣቶችና ኃጢአተኛ መንከራተቶች ስታገኙ ወፎቹን ለማባረር ትጉ፤ እነዚህን ከንቱ ሐሳቦች አስወግዱ፤ ተንከራታቾች ናቸው፤ ሊስተናገዱም አይገባቸውም።

እነዚህን ተንከራታች ሐሳቦች እንዴት እናስወግዳቸዋለን?

(1) በእነርሱ ላይ ጸልዩና ተጠበቁ። (2) ሁሉን የሚያውቀው የእግዚአብሔር ዓይን ስሜት ልባችሁን በፍርሃት ይግዛው። ባሪያ በጌታው ፊት አይጫወትም። (3) ቅዱስ የልብ ሁኔታ እንዲኖራችሁ ትጉ። ልብ ይበልጥ መንፈሳዊ ቢሆን አእምሮ እንደ ላባ ቀላል አይሆንም ነበር። (4) ለቃሉ የበለጠ ፍቅር አምጡ። አእምሮአችንን በምንወደው ነገር ላይ እናጸናለን። ተድላውንና መዝናኛውን የሚወድ አእምሮውን በእነርሱ ላይ ያጸናል፤ ያለ መበተንም ሊከተላቸው ይችላል። ፍቅራችን በተሰበከው ቃል ላይ ይበልጥ ቢሆን አእምሮአችን በእርሱ ላይ ይበልጥ ይጸና ነበር፤ በእርግጥም የተሰበከውን ቃል እንድንወደው የሚያደርግ በቂ ነገር አለ፤ የሕይወት ቃል፣ የእውቀት መግቢያ፣ የኃጢአት መድኃኒት፣ የቅዱስ ስሜቶች ሁሉ አነቃቂ ነውና። ልዩ ልዩ ጣፋጭ ጣዕም ያለበት እውነተኛው መና ነው፤ ልባቸው የተሰበረውን ለመፈወስ የሕይወት ወንዞች የሚፈልቁበት የቤተ ሳይዳ መጠመቂያ ነው፤ ያዘነውንም መንፈስ የሚያነቃቃ ዋና ፍቱን መድኃኒት ነው። ለተሰበከው ቃል ፍቅር ይኑራችሁ፤ በመስማትም ጊዜ እንዲህ አትበተኑም። ልብ በሚደሰትበት ነገር ላይ ሐሳብ ይኖራል።

[2] በመስማት ጊዜ ከማንቀላፋት ተጠንቀቁ። ማንቀላፋት ታላቅ አክብሮት ማጣትን ያሳያል። ብዙዎች በዓለም ጉዳይ ላይ ሲሆኑ እንዴት ንቁዎች ናቸው፤ በእግዚአብሔር አምልኮ ግን ዲያብሎስ እንዲተኙ የሚያደነዝዝ መድኃኒት የሰጣቸው ይመስል እንዴት ያንቀላፋሉ! በዚህ ስፍራ ማንቀላፋት እጅግ ኃጢአት ነው። በጸሎት የኃጢአትን ይቅርታ አትለምኑምን? እስረኛ ምሕረትን እየለመነ ሳለ ያንቀላፋልን? በቃሉ ስብከት የሕይወት እንጀራ አይቈረስላችሁምን? ሰውስ በምግቡ ላይ ያንቀላፋልን? ከስብከት መቅረትና በስብከት ጊዜ መተኛት የትኛው የከፋ ነው? እናንተ ተኝታችሁ ሳላችሁ ምናልባት ነፍሳችሁን ሊመልስ የሚችል እውነት ተነግሮ ይሆናል። ደግሞም በቅዱስ ጉባኤ መተኛት እጅግ የሚያሰናክል ነው፤ የእግዚአብሔርን መንፈስ ማሳዘኑ ብቻ ሳይሆን የጻድቃንንም ልብ ያሳዝናል። ሕዝ 13፥22። ማንም እግዚአብሔርንና አምልኮውን እንዲህ ሲንቅ፥ በሱቅ ትጉ በመቅደስ ግን አንቀላፊ ሆኖ ሲያዩት ያስጨንቃቸዋል። ስለዚህ ክርስቶስ «ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን?» እንዳለ፥ እንዲሁ አንዲት ሰዓት እንኳ ነቅታችሁ ልትቆዩ አትችሉምን? ማቴ 26፥40። የእግዚአብሔር ልጅ አንዳንድ ጊዜ ከድካምና ከሰውነት ሕመም የተነሣ በስብከት ጊዜ ሊያንቀላፋ እንደሚችል አልክድም፤ ነገር ግን በፈቃዱ ወይም በልማድ አይደለም። ፀሐይ ልትጨልም ትችላለች፤ ግን ብዙ ጊዜ አይደለም። መተኛት ልማድ ከሆነና ከተፈቀደ ግን እጅግ መጥፎ ምልክት ነው፤ ሥርዓቱንም ማርከስ ነው። ማንቀላፋትን የሚከላከል መልካም መድኃኒት በሰንበት ቀን በልክ መብላት ነው። በሰንበት ሆዳቸውን አብዝተው የሚያስደስቱ በመቅደስ ከመጸለይ ይልቅ በአልጋ ላይ ለመተኛት የተገቡ ናቸው። በጌታ ቀን የሚበታትኑ አሳቦችንና ማንቀላፋትን አስወግዳችሁ ቃሉን በአክብሮትና በትኩረት እንድትሰሙ፥ ይህን አስቡ፦

(1) በቃሉ የሚናገረን እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ የቃሉ ስብከት «የከንፈሩ እስትንፋስ» ተብሎ ተጠርቷል። ኢሳ 11፥4። ንጉሥ በመልእክተኛው በኩል እንደሚናገር፥ ክርስቶስ አሁን «ከሰማይ» ይናገረናል ተብሏል። ዕብ 12፥25። አገልጋዮች ቱቦዎችና መሣሪያዎች ብቻ ናቸው፤ በእነርሱ የሚተነፍሰው የሕያው እግዚአብሔር መንፈስ ነው። ወደ ቃሉ ስንመጣ በልባችን፦ እግዚአብሔር በዚህ ሰባኪ ይናገራል ብለን ማሰብ ይገባናል። የተሰሎንቄ ሰዎች ጳውሎስ የሰበከውን ቃል እግዚአብሔር ራሱ እንደ ተናገራቸው አድርገው ሰሙት። «ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።» 1ተሰ 2፥13። ሳሙኤል የሚናገረው እግዚአብሔር መሆኑን ባወቀ ጊዜ ጆሮውን ሰጠ። 1ሳሙ 3፥10። እግዚአብሔር ሲናገረን እኛ ልብ ካላልነው፥ ወደ እርሱ ስንጸልይ እርሱም ልብ አይለንም።

(2) የሚነገሩን ነገሮች ምን ያህል ከባድና ታላቅ እንደ ሆኑ አስቡ። ሙሴ፦ «ሕይወትንና ሞትን በፊታችሁ እንዳኖርሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን እመሰክርባችኋለሁ» አለ። ዘዳ 30፥19። የዘላለም ታላላቅ ጉዳዮች በፊታቸው ሲቀርቡ ሰዎች ቃሉን ቸል ሊሉ ወይም ሊያንቀላፉ ይችላሉን? እኛ እምነትን፥ የሕይወትን ቅድስና፥ የፍርድን ቀንና የዘላለምን ብድራት እንሰብካለን። በዚህ ሕይወትና ሞት በፊታችሁ ተቀምጠዋል፤ ይህ ሁሉ ልባዊ ትኩረትን አይጠይቅምን? ሕይወቱንና ንብረቱን የሚመለከት ደብዳቤ ለአንድ ሰው ቢነበብለት በጥንቃቄ አያዳምጠውምን? በቃሉ ስብከት የእናንተ መዳን ተያይዟል፤ መቼም ልታደምጡ ብትፈልጉ አሁን ነው። «ይህ ሕይወታችሁ ነውና ለእናንተ ከንቱ ነገር አይደለም።» ዘዳ 32፥47።

(3) በመስማት ጊዜ ለከንቱ አሳቦችና ለማንቀላፋት ስፍራ መስጠት ሰይጣንን ደስ ያሰኛል። አንድን ሃይማኖታዊ ተግባር ልብ አለማለት በሃይማኖት ዘንድ ያለማድረግ ያህል እንደ ሆነ ያውቃል። «ልብ የማያደርገው አልተደረገም።» ስለዚህ ክርስቶስ ስለ አንዳንዶች፦ «እየሰሙ አይሰሙም» ይላል። ማቴ 13፥13። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ቃሉ በጆሮአቸው ቢሰማም የተነገራቸውን ልብ አላሉም፤ አሳባቸው በሌላ ነገር ላይ ነበር፤ ስለዚህ እንዳልሰሙ ያህል ሆነ። ሰዎች ወደ ቃሉ መጥተው ቢቀሩ የሚሻላቸው ሆነው ሲያያቸው ሰይጣንን ደስ አያሰኘውምን? ከንቱ አሳቦች ያሳድዱአቸዋል፤ በተግባሩ ውስጥ ሳሉ ከተግባሩ ይወሰዳሉ፤ ሥጋቸው በጉባኤ ነው፥ ልባቸው ግን በሱቃቸው። «እየሰሙ አይሰሙም።»

(4) እያንዳንዱ ሰንበት የምንጠብቀው የመጨረሻው ሊሆን ይችላል፤ ከመስሚያው ስፍራ ወደ ፍርድ ስፍራ ልንሄድ እንችላለን፤ ታዲያ ቃሉን በአክብሮት አናዳምጥምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ስንገባ፦ «ምናልባት እግዚአብሔር ስለ ነፍሳችን የሚመክረን ይህ የመጨረሻው ጊዜ ይሆናል፤ ሌላ ስብከት ሳይመጣ የሞት ደወል በጆሮአችን ይጮኻል» ብለን ብናስብ፥ በምን ዓይነት ትኩረትና መሰጠት በሰማን ነበር፤ በመስማትም ጊዜ ስሜታችን ሁሉ እንዴት በነደደ ነበር!

(5) ለምትሰሙት ስብከት ሁሉ ሂሳብ ትሰጣላችሁ። Redde rationem: «የመጋቢነትህን ሂሳብ አስረክበኝ።» ሉቃ 16፥2። እግዚአብሔርም እንዲሁ፦ «የመስማትህን ሂሳብ አስረክበኝ። በቃሉ ተነክተሃልን? ተጠቅመህበታልን?» ይላል። በመስማት ጊዜ ተበታትነን የተነገረንንም ልብ ሳንል ቀርተን ከሆነ እንዴት መልካም ሂሳብ ልንሰጥ እንችላለን? ሂሳብ የምንሰጠው ዳኛ እግዚአብሔር ነው። ለሰው ሂሳብ ብንሰጥ ኖሮ ሂሳቡን ልናጭበረብር እንችል ነበር፤ ሂሳብ የምንሰጠው ግን ለእግዚአብሔር ነው። Nec donis corrumpitur, nec blanditiis fallitur. በርናርድ። «ጉቦ እንዳይቀበል እጅግ ጻድቅ፥ እንዳይታለልም እጅግ ጥበበኛ አምላክ ነው።» ስለዚህ ለእንዲህ ያለ አድልዎ ለሌለበት ዳኛ ሂሳብ የምንሰጥ ከሆንን፥ ሂሳቡን እያሰብን የሚሰበከውን ቃል ሁሉ እንዴት ልናስተውል ይገባናል! ይህ ሁሉ በመስማት ጊዜ መበታተንንና ማንቀላፋትን አራግፈን ጆሮአችን ከቃሉ ጋር የታሰረ እንዲሆን ያድርገን።

VI. ቃሉን በትክክል ለመስማት የሚከተሉትን ነገሮች ልብ በሉ፦

[1] የተሰበከውን ቃል ፍሬ ቢስ የሚያደርጉትን ዝንባሌዎች አስወግዱ። እነርሱም፦

(1) የማወቅ ጉጉት። አንዳንዶች የተሰበከውን ቃል ለመስማት የሚሄዱት ጸጋን ለማግኘት ሳይሆን በአሳቦች ራሳቸውን ለማበልጸግ ነው፤ ጆሮቻቸው «የሚያሳክክ» ነው። 2ጢሞ 4፥3። አውግስጢኖስ ከመመለሱ በፊት አምብሮስን ለመስማት የሄደው ስለ ነገሩ መንፈሳዊነት ሳይሆን ስለ አንደበተ ርቱዕነቱ እንደ ነበር ይመሰክራል። «እነሆ፥ አንተ ለእነርሱ መልካም ድምፅ እንዳለውና በገና በደኅና እንደሚደረድር ሰው እንደ ተወደደ ዝማሬ ነህ።» ሕዝ 33፥32። ብዙዎች ወደ ቃሉ የሚሄዱት ጆሮአቸውን ብቻ ለማስደሰት ነው፤ የድምፁን ዜማ፥ የአነጋገሩን ማር የመሰለ ጣፋጭነትና የአሳቦቹን አዲስነት ይወዳሉ። ሐዋ 17፥21። ይህ ከምግቡ ይልቅ የሳህኑን ጌጥ መውደድ ነው፤ ከመታነጽ ይልቅ ደስ መሰኘትን መሻት ነው። ፊቷን እንደምትቀባ ጤናዋን ግን ቸል እንደምትል ሴት፥ እነርሱም በረቂቅ ግምቶች ራሳቸውን ይቀባሉ ያስጌጣሉም፤ የነፍሳቸውን ጤና ግን ቸል ይላሉ። እንዲህ ያለ መስማት ልብንም ሰንበትንም አይቀድስም።

(2) ጭፍን ጥላቻን አስወግዱ። ጭፍን ጥላቻ አንዳንድ ጊዜ በሚሰበኩት እውነቶች ላይ ነው። ሰዱቃውያን በትንሣኤ ትምህርት ላይ ጭፍን ጥላቻ ነበራቸው። ሉቃ 20፥27። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጭፍን ጥላቻው በሰባኪው ላይ ነው። «እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት ሚክያስ የሚባል አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን እጠላዋለሁ።» 1ነገ 22፥8። ይህ የቃሉን ኃይል ያግዳል። በሽተኛ ስለ ሐኪሙ መጥፎ አሳብ ካለው፥ መድኃኒቶቹ ምንም ያህል መልካም ቢሆኑ አንዱንም አይወስድም። በአእምሮ ያለ ጭፍን ጥላቻ የምግቡን የመመገብ ኃይል እንደሚያግድ የሆድ መዘጋት ነው። ቃሉን ይመርዘዋል፥ ኃይሉንም እንዲያጣ ያደርገዋል።

(3) ስስትን አስወግዱ። ስስት የዓለምን ትርፍ በግፍ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ከልክ በላይ መውደድም ነው። ይህ ለተሰበከው ቃል ታላቅ እንቅፋት ነው። በእሾህ መካከል የወደቀው ዘር ታነቀ፥ ማቴ 13፥22፤ ይህም ለስስታም ሰሚ የተሰበከ ቃል ተገቢ ምሳሌ ነው። ስስታም ሰው በሚሰማበት ጊዜ ስለ ዓለም ያስባል፤ ልቡ በሱቁ ነው። «እንደ ሕዝቤ በፊትህ ይቀመጣሉ፥ ቃልህንም ይሰማሉ፤ ልባቸው ግን ስስታቸውን ይከተላል።» ሕዝ 33፥31። ስስታም ሰሚ በቃሉ ያፌዛል። «ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር።» ሉቃ 16፥14።

(4) አድልዎን አስወግዱ። በመስማት ያለ አድልዎ ማለት አንዳንድ እውነቶች ሲሰበኩ መስማትን ስንወድ ሁሉንም ግን ሳንወድ ስንቀር ነው። ስለ መንግሥተ ሰማያት መስማት እንወዳለን፥ ስለ ራስን መካድ ግን አይደለም፤ ከክርስቶስ ጋር ስለ መንገሥ እንጂ ከእርሱ ጋር ስለ መከራ መቀበል አይደለም፤ ቀለል ስላሉት የሃይማኖት ተግባሮች እንጂ ይበልጥ ስለሚያስቸግሩትና ስለሚከብዱት አይደለም፤ ለምሳሌ ሥጋን መግደል፥ መጥረቢያን በሥሩ ላይ ማኖርና የምንወደውን ኃጢአት መቍረጥ። «የሚያለዝበውን ተናገሩን» (ኢሳ 30፥10)፤ ሕሊናን የማይቧጭረውን ማለት ነው። ብዙዎች ስለ ክርስቶስ ፍቅር መስማት ይወዳሉ፥ ጠላቶቻቸውን ስለ መውደድ ግን አይደለም፤ የቃሉን መጽናናት ይወዳሉ፥ ተግሣጹን ግን አይደለም። ሄሮድስ መጥምቁ ዮሐንስን በደስታ ሰማው፤ ብዙ እውነቶችን ወደደ፥ ስለ ሕገ ወጥ ጋብቻው በተናገረው ጊዜ ግን አልወደደም።

(5) ነቃፊነትን አስወግዱ። አንዳንዶች ስለ ኃጢአታቸው በራሳቸው ላይ ከመፍረድ ይልቅ በሰባኪው ላይ ዳኞች ሆነው ይቀመጣሉ፤ ስብከቱ ወይ ከመጠን በላይ መራራ ነበር፥ ወይ በጣም ረዘመ ይላሉ። ስብከትን ከመፈጸም ይልቅ ቶሎ ይነቅፋሉ። እግዚአብሔር በፈራጁ ላይ ይፈርዳል። ማቴ 7፥1።

(6) አለመታዘዝን አስወግዱ። «ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ።» ሮሜ 10፥21። ስለ አይሁድ እግዚአብሔር በቃሉ ስብከት እጆቹን እንደ ዘረጋ፥ እነርሱ ግን ክርስቶስን እንደ ናቁ ተነግሯል። ከእናንተ መካከል የቃሉን ምክር በገዛ ፈቃዱ እምቢ የሚል ማንም አይኑር። የእፉኝት ጆሮና እንደ አልማዝ የጠነከረ ልብ መያዝ የሚያሳዝን ነው። ዘካ 7፥11, 12። እግዚአብሔር በቃሉ ሲናገረን እኛ ደንቆሮዎች ብንሆን፥ እኛ በጸሎት ስንናገረው እርሱ ዝም ይላል።

[2] ቃሉን በትክክል መስማት ብትወዱ፥ በመስማታችሁ መልካም ዓላማ ይኑራችሁ። «የተሻላችሁ ለመሆን ወደ ቃሉ ኑ።» አንዳንዶች በመስማታቸው ሌላ ዓላማ የላቸውም፤ የሚሰሙት ልማድ ስለ ሆነ፥ ወይም ስም ለማግኘት፥ ወይም የሕሊናን አፍ ለመዝጋት ነው፤ እናንተ ግን ይበልጥ ቅዱሳን ለመሆን ወደ ቃሉ ኑ። በደረቷ የምታደርገውን አበባ ለመልቀም ወደ አትክልት ቦታ በምትሄድ ሴትና ሽሮፕና መድኃኒት የሚሠራበትን አበባ ለመልቀም በሚሄድ ሰው መካከል ታላቅ ልዩነት አለ። ሶርያዊው ንዕማን ከለምጹ ለመፈወስ ወደ ዮርዳኖስ እንደ ሄደ፥ እኛም የሚፈውሰንን መድኃኒት ለማግኘት ወደ ቃሉ መሄድ ይገባናል። «በእርሱ ታድጉ ዘንድ ተንኰል የሌለበትን የቃሉን ወተት ተመኙ።» 1ጴጥ 2፥2። ወደ እርሱ መልክ እንድትለወጡ ወደ ቃሉ ሂዱ። ማኅተም በሰም ላይ ምልክቱን እንደሚተው፥ እንዲሁ የተሰበከው ቃል የራሱን የቅድስና ምልክት በልባችሁ ላይ እንዲተው ጣሩ።

«ቃሉ» እንደ ቅንዓት ውኃ ሊገድልና ፍሬያማ ሊያደርግ የሚችል እንዲህ ያለ ኃይል በእናንተ ዘንድ እንዲኖረው ጣሩ፤ ኃጢአታችሁን እንዲገድልና ነፍሳችሁን በጸጋ ፍሬያማ እንዲያደርግ። ዘኍ 5፥27።

[3] ቃሉን በትክክል መስማት ብትወዱ፥ በደስታ ወደ እርሱ ሂዱ። የተሰበከው ቃል የሰባ ነገር ግብዣ ነው። ሰዎች ወደ ግብዣ በምን ያህል ደስታ ይሄዳሉ! የተሰበከው ቃል የታወረውን ዓይን ይቀባል፤ እንደ ዓለት የጠነከረውን ልብ ያለሰልሳል፤ እስራታችንን ይሰብራል፥ «ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር» ይመልሰናል። ሐዋ 26፥18። ቃሉ የዳግም ልደት ዘር የመዳንም መሣሪያ ነው። ያዕ 1፥18። ቃሉን በደስታና በእርካታ ስሙ። «ቃልህ ተገኘ፥ በላሁትም፤ ቃልህም ለልቤ ሐሤትና ደስታ ሆነልኝ።» ኤር 15፥16። «ቃልህ ለጕሮሮዬ እንዴት ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ይልቅ ጣፋጭ ነው።» መዝ 119፥103። ወደ ሕሊና አብልጦ የሚደርሰውን ቃል ውደዱ፤ ክፉ ዝንባሌያችሁ በተገኘ ጊዜ፥ የመንፈስ ሰይፍ በእናንተና በኃጢአታችሁ መካከል በለየ ጊዜ እግዚአብሔርን አመስግኑ። የማይሠራን መድኃኒት ማን ይፈልጋል?

[4] ቃሉን በትክክል መስማት ብትወዱ፥ ከእምነት ጋር አዋሕዱት። የተሰበከው ቃል እውነት እንደ ሆነና የምትፈረዱበት ቃል እንደ ሆነ እመኑ። ለተሰበከው ቃል እምነት መስጠት ብቻ ሳይሆን ለገዛ ነፍሳችሁ ተጠቀሙበት። እምነት ቃሉን ያፈጫል፥ ወደ መንፈሳዊ ምግብም ይለውጠዋል። ብዙዎች ቃሉን ይሰማሉ፤ ነገር ግን በመዝ 106፥24 እንዳለው፦ «በቃሉ አላመኑም» ሊባልላቸው ይችላል። ሜላንክቶን በአንድ ወቅት ለአንዳንድ ጣሊያውያን፦ «እናንተ ጣሊያውያን እግዚአብሔር በሰማይ እንዳለ ሳታምኑ በእንጀራው ውስጥ ታመልኩታላችሁ» እንዳለ፥ እንዲሁ ብዙዎች የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማሉ፥ እግዚአብሔር መኖሩን ግን አያምኑም፤ የቃሉን እውነት ይጠራጠራሉ። ቃሉን ከእምነት ጋር ካላዋሐድነው፥ ዋናውን ንጥረ ነገር ከመድኃኒት ውስጥ እንደ መተው ነው፤ ይህም መድኃኒቱን ፍሬ ቢስ ያደርገዋል። አለማመን የሰዎችን ልብ በቃሉ ላይ ያደነድናል። «አንዳንዶች እልከኞች ሆኑ፥ አላመኑምም።» ሐዋ 19፥9። ሰዎች ስለ ክርስቶስ ክቡርነት፥ ስለ ቅድስና ውበትና ስለ ክብር ሁኔታ ደስታ ብዙ እውነቶችን ይሰማሉ፤ ነገር ግን ከአለማመንና ከአምላክ የለሽነት የተነሣ እነዚህን እውነቶች ቢጠራጠሩ፥ ለእነርሱ መናገር ለድንጋዮችና ለቤተ ክርስቲያን ምሰሶዎች እንደ መናገር ነው። ያልታመነ ቃል ፈጽሞ በተግባር ሊውል አይችልም። Ubi male creditur, ibi nec bene vivitur [እምነት በሚናወጥበት ስፍራ አካሄድም ይናወጣል]። ጀሮም። አለማመን የተሰበከውን ቃል ከንቱ ያደርገዋል። «ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም።» ዕብ 4፥2። ቃሉ ለማያምን ሰው በሞተ ሰው አፍ ውስጥ እንደ ተጨመረ የሚያበረታ መጠጥ ነው፤ ኃይሉን ሁሉ ያጣል። በጉባኤዎቻችን ውስጥ የማያምኑ ቢኖሩ፥ አገልጋዮች በመጨረሻው ቀን ስለ እነርሱ ለእግዚአብሔር ምን ይላሉ? ጌታ ሆይ፥ ለላክኸን ሕዝብ ሰብከናል፤ ተልእኮአችንን አሳይተናቸዋል፤ ምክርህን ሁሉ ነግረናቸዋል፤ እነርሱ ግን ከተናገርነው አንዲትም ቃል አላመኑም። የኃጢአት ፍሬ ምን እንደሚሆን ነገርናቸው፥ እነርሱ ግን አልሰሙም። በጽዋው ውስጥ ሞት ቢኖርም የጣፈጠውን መጠጣቸውን ጠጡ። ጌታ ሆይ፥ ከደማቸው ንጹሐን ነን። አገልጋዮች ይህን ዘገባ ስለ ሕዝባቸው ለእርሱ እንዲያቀርቡ እግዚአብሔር አያድርገው። ነገር ግን ሰሚዎቻቸው በአለማመን ቢኖሩና ቢሞቱ ይህን ለማድረግ ይገደዳሉ። ቃሉን በትክክል በመስማት ሰንበትን ልትቀድሱ ትወዳላችሁን? በእምነት ስሙት። ሐዋርያው ሁለቱን፥ «እምነትንና መዳንን» አንድ ላይ ያደርጋቸዋል። «እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።» ዕብ 10፥39።

[5] ቃሉን በትክክል መስማት ብትወዱ፥ በየዋህ መንፈስ ስሙት። ያዕ 1፥21። ቃሉን in mansuetudine፥ «በየዋህነት» ተቀበሉ። የዋህነት ለቃሉ የሚገዛ የልብ ሁኔታ ነው። የዚህ የዋህነት ተቃራኒ የመንፈስ ጭካኔ ነው፤ ይህም ሰዎች በቃሉ ላይ በቍጣ ሲነሡ ነው፤ በሽተኛ ክፉውን የሰውነት ፈሳሽ የሚያስወጣለትን መድኃኒት በሰጠው ሐኪም ላይ እንደሚቈጣ ያህል ነው። «ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት [በእስጢፋኖስ]።» ሐዋ 7፥54። «አሳም በባለ ራእዩ ላይ ተቈጣ፥ በግዞት ቤትም አኖረው።» 2ዜና 16፥10። ትዕቢትና በደል ሰዎችን በቃሉ ላይ ያስቈጣሉ። አሳን ያስቈጣው ከትዕቢት በቀር ምን ነበር? ንጉሥ ነበርና ስለ ኃጢአቱ ሊነገረው የማይገባው ታላቅ ሰው እንደ ሆነ አሰበ። እግዚአብሔር ቃየንን፦ «ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?» ባለው ጊዜ ያስቈጣው ምን ነበር? እርሱም፦ «እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?» ብሎ መለሰ። እንዲህ ቶሎ እንዲቈጣ ያደረገው ከበደል በቀር ምን ነበር? እጆቹን በወንድሙ ደም አጥልቆ ነበርና። ቃሉን በትክክል መስማት ብትወዱ፥ ቍጣችሁን አስወግዱ። «ቃሉን በየዋህነት ተቀበሉ»፤ ለሚነገሩት እውነቶች የሚገዙ ትሑታን ልቦችን አግኙ። እግዚአብሔር የዋሁን ሰው ደቀ መዝሙሩ አድርጎ ይወስደዋል። «ለየዋሆች መንገዱን ያስተምራቸዋል።» መዝ 25፥9። የዋህነት የተሰበከውን ቃል «የተተከለ ቃል» ያደርገዋል። ያዕ 1፥21። መልካም ቅርንጫፍ በመጥፎ ግንድ ላይ ሲተከል የግንዱን ባሕርይ ይለውጣል፥ መልካምና የከበረ ፍሬም እንዲያፈራ ያደርገዋል፤ እንዲሁም የተሰበከው ቃል በሰዎች ልብ ውስጥ ሲተከል ይቀድሳቸዋል፥ ጣፋጩን የጽድቅ ፍሬም እንዲያፈሩ ያደርጋቸዋል። በየዋህነት የተተከለ ቃል ይሆናል።

[6] ቃሉን በትክክል መስማት ብትወዱ፥ አድማጮች ብቻ ሳይሆን ጠባቂዎችም ሁኑ። በመታሰቢያችሁና በልባችሁ አኑሩት። «በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።» ሉቃ 8፥15። «መጠበቅ» ለሚለው የግሪኩ ቃል ቃሉ ከእኛ እንዳያመልጥ አጥብቆ መያዝ ማለት ነው። ዘሩ በመሬት ውስጥ ሳይቆይ ወዲያው ቢታጠብ፥ የተዘራው በከንቱ ነው፤ እንዲሁም የተሰበከው ቃል በመታሰቢያችሁና በልባችሁ ካልተጠበቀ የተሰበከው በከንቱ ነው። ብዙ ሰዎች እንደሚያፈሱ ዕቃዎች ያለ መታሰቢያ አላቸው። ቃሉ እንደ ገባ ፍጥነት ቢወጣ እንዴት ሊጠቅም ይችላል? ሀብት በሣጥን ውስጥ ቢቀመጥና ሣጥኑ ባይቈለፍ በቀላሉ ሊወሰድ ይችላል፤ እንዲሁ መጥፎ መታሰቢያ ቍልፍ የሌለው ሣጥን ነው፤ ዲያብሎስም ሀብቱን ሁሉ በቀላሉ ይወስድበታል። «በመንገድ ዳርም ያሉት የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚህ በኋላም ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።» ሉቃ 8፥12። የምትሰሙትን እውነቶች በመታሰቢያችሁ ለመጠበቅ ጣሩ። የምናከብራቸው ነገሮች በቀላሉ አይረሱም። «ቆንጆ ጌጥዋን፥ ሙሽራም ልብስዋን ትረሳለችን?» ኤር 2፥32። ቃሉን አብልጠን ብናከብረው ኖሮ ቶሎ ባልረሳነው ነበር። ምግብ በሆድ ውስጥ ሳይቆይ እንደ በላነው ፍጥነት ቢመለስ ሊመግብ አይችልም፤ እንዲሁም ቃሉ በመታሰቢያ ውስጥ ሳይቆይ ወዲያው ቢጠፋ ለነፍስ የሚያደርገው መልካም ነገር ጥቂት ነው።

[7] በትክክል መስማት ብትወዱ፥ የምትሰሙትን አድርጉ። ማድረግ የሁሉ ሕይወት ነው። «ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው ትእዛዛቱን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው።» ራእ 22፥14። በፍርድ ቀን መስማት ብቻ ምንም ማመካኛ አይሆንም፤ «ጌታ ሆይ፥ ብዙ ስብከቶችን ሰምቻለሁ» ማለት ብቻ። እግዚአብሔር፦ «ምን የመታዘዝ ፍሬ አፍርታችኋል?» ይላል። የተሰበከው ቃል የሚያስተምራችሁ ብቻ ሳይሆን የሚያሻሽላችሁም ነው፤ እይታችሁን ብቻ ሳይሆን ወደ መንግሥተ ሰማያት በሚወስደው መንገድ አካሄዳችሁንም ያቃናል። መልካም ሰሚ የፀሐይ አበባ ለፀሐይ እንደሚከፈትና እንደሚዘጋ ለእግዚአብሔር ይከፈታል ይዘጋልም።

(1) ቃሉን በተግባር ለመፈጸም ብላችሁ ካልሰማችሁ ድካማችሁን ሁሉ ታጣላችሁ። በመስማት ካልተሻሻላችሁ ስንት አድካሚ እርምጃ ተራመዳችሁ፥ ሰውነታችሁ በሕዝብ መካከል ተጨናነቀ፥ መንፈሳችሁም ደከመ! እንደ ቀድሞው ትዕቢተኞች፥ ከንቱዎችና ምድራውያን ከሆናችሁ መስማታችሁ ሁሉ ጠፍቶአል። በከንቱ መነገድን ትጠላላችሁ፤ ታዲያ ስብከትን በከንቱ መስማትን ለምን አትጠሉም? «እንግዲህ በከንቱ የምደክመው ስለ ምንድር ነው?» ኢዮ 9፥29። ይህን ጥያቄ ለራሳችሁ ነፍስ አቅርቡ፦ በከንቱ የምደክመው ስለ ምንድር ነው? ለመስማት ይህን ሁሉ ድካም እየደከምሁ በተግባር ለመፈጸም ጸጋ የሌለኝ ስለ ምንድር ነው? እንደ ቀድሞው ክፉ ነኝ! እንግዲህ በከንቱ የምደክመው ስለ ምንድር ነው?

(2) ቃሉን ሰምታችሁ ካልተሻሻላችሁበት፥ በእሳት ውስጥ ሆኖ እንደማይሞቀው እንደ ሰላማንደር ናችሁ፤ መስማታችሁም ፍርዳችሁን ያበዛል። «የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤» ሉቃ 12፥47። የት እንደሚሰሙ የማያውቁትን እናዝንላቸዋለን፤ እንዴት እንደሚሰሙ ግድ የሌላቸው ግን የባሰ ይሆንባቸዋል። ጸጋ ለሌላቸውና ለማይታዘዙ ሰሚዎች እያንዳንዱ ስብከት ሲኦልን የሚያሞቅ የማገዶ እንጨት ይሆናል። በሥርዓቶች ተጭኖ ወደ ሲኦል መውረድ እንዴት ያሳዝናል! የተሰበከው ቃል ውጤታማ እንዲሆን መንፈስን ለምኑ! አገልጋዮች ወደ ጆሮ ብቻ ይናገራሉ፤ መንፈስ ግን ወደ ልብ ይናገራል። «ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።» ሐዋ 10፥44።

[8] ቃሉን በቅድስናና በመንፈሳዊ ሁኔታ ከሰማችሁ በኋላ፥ ሰንበትን አብልጦ ለመቀደስ ስለ ቃሉ ተነጋገሩ። በዚህ ቀን የራሳችንን ቃል እንዳንናገር ተከልክለናል፤ ስለ እግዚአብሔር ቃል ግን መናገር ይገባናል። ኢሳ 58፥13። አብራችሁ ስትቀመጡ ስለ ስብከቶቹ ተነጋገሩ፤ ይህም ሰንበትን የመቀደስ አንዱ ክፍል ነው። መልካም ንግግር ቅዱሳት እውነቶችን ወደ ትዝታችን ያመጣል፤ በልባችንም ላይ ያጸናቸዋል። «በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።» ሚል 3፥16። በመልካም ንግግር ታላቅ ኃይልና ብርታት አለ። «የቅን ቃል ኃይል እንዴት ብርቱ ነው!» ኢዮ 6፥25። በሰንበት በሚደረግ ቅዱስ ውይይት አንዱ ክርስቲያን ሌላውን በቀዘቀዘ ጊዜ ያሞቀዋል፤ በደከመም ጊዜ ያበረታዋል። ላቲመር ከሰማዕቱ ከሚስተር ቢልኒ ጋር በመወያየቱ በሃይማኖት እጅግ እንደ ተረዳ መስክሯል። «አንደበቴ ቃልህን ይናገራል።» መዝ 119፥172። በሰንበት የቃሉ ስብከት ከዚህ የበለጠ መልካም የማያደርግበት አንዱ ምክንያት መልካም ውይይት እጅግ ጥቂት መሆኑ ነው። ስብከቶች ዳግመኛ የማይነገሩ ምሥጢሮች ይመስል፥ ወይም የሚያድነንን ነገር መናገር ነውር ይመስል፥ ስለ ሰሙት ቃል የሚናገሩ ጥቂቶች ናቸው።

[9] የሰንበትን ምሽት የሰማችሁትን በመድገም፥ በማንበብ፥ መዝሙራትን በመዘመርና በጸሎት ፈጽሙ። እግዚአብሔር የሰማችሁትን ቃል እንዲባርክ ለምኑ። ሰንበትን እንዲህ ብናሳልፍ «በጌታ ቀን በመንፈስ» እንሆን ነበር፤ ነፍሳችን ትመገብና ትጽናና ነበር፤ አሁን የምንጠብቃቸውም ሰንበቶች በሰማይ ለምናከብራቸው ለዘላለማዊ ሰንበቶች መያዣ ይሆኑ ነበር።

የመጀመሪያው ትግበራ። እዚህ የክርስቲያንን ተግባር ተመልከቱ፤ እርሱም «የሰንበትን ቀን መቀደስ» ነው።

(1) ሰንበት ሁሉ ለእግዚአብሔር መሰጠት አለበት። «ከሰንበት ከፊሉን ቀድስ» አልተባለም፤ ቀኑ ሁሉ በሃይማኖታዊ ሁኔታ መከበር አለበት። እግዚአብሔር ስድስት ቀን ሰጥቶን ለራሱ አንድ ብቻ ከወሰደ፥ ከዚያ ቀን ማንኛውንም ክፍል እንነፍገዋለንን? ይህ ቅዱስ ነገርን መዝረፍ በሆነ ነበር። አይሁድ ቀኑን ሁሉ ለጌታ ጠበቁ፤ አውግስጢኖስም እንደሚለው እኛ ሰንበትን ከአይሁድ ይበልጥ ማሳጠርም ሆነ መቀነስ አይገባንም። አሕዛብ እንኳ በተፈጥሮ ብርሃን ለሐሰተኛ አማልክት ክብር ቀኑን ሁሉ ለዩ፤ ከሊቀ ካህናቶቻቸውም አንዱ ስካይቮላ ያንን ቀን ሆን ብሎ መተላለፍ ማስተስረያም ይቅርታም እንደሌለው አረጋግጦአል። ማንም ከክርስቲያን ሰንበት ማንኛውንም ክፍል ለባርነት ሥራ ወይም ለመዝናኛ ቢሰርቅ፥ የአሕዛብ አማልክት ሊቀ ካህናት ስካይቮላ ሊኰንነው በፍርድ ይነሣል። ሰንበትን ሁሉ መጠበቅ እጅግ የአይሁድ ልማድ ነው የሚሉ፥ እግዚአብሔር ከአምልኮው ጊዜ ምን እንደ ቀነሰ፥ «ከሰንበት ከፊሉን ብቻ ጠብቁ» ብሎ የት እንደ ተናገረ ያሳዩ፤ ይህን ማሳየት ካልቻሉ ግን እግዚአብሔርን የሚገባውን ይዘርፉታል። ጴጥሮስ ማርቲር እንደሚለው፥ ቀኑ ሁሉ ለልዩ አምልኮው ተወስኖ መለየቱ ቤተ ክርስቲያን በምድር ላይ እስካለች ድረስ የዘላለም ሥርዓት ነው። ቴዎድሮስ፥ አውግስጢኖስ፥ ኢሬኔዎስና የአባቶች ዋነኞችም የዚህ አሳብ ነበሩ።

(2) ሰንበት ሁሉ ለእግዚአብሔር እንደሚሰጥ እንዲሁ በቅድስና መጠበቅ አለበት። የጌታን ቀን በማንበብ፥ በማሰላሰል፥ በጸሎት፥ ቃሉን በመስማትና ለጌታ ዜማ ለማቅረብ መዝሙራትን በመዘመር የመቀደሱን መንገድ አይታችኋል። አሁን ይህን ቀን ስለ መቀደስ ከተናገርሁት በተጨማሪ በዚያ የመጽሐፍ ክፍል ላይ አጭር ማብራሪያ ልስጥ። «ከሰንበት እግርህን ብትመልስ፥ በቅዱሱ ቀኔ ፈቃድህን ከማድረግ ብትከለከል፥ ሰንበትንም ደስታ፥ የእግዚአብሔርንም ቅዱስ ክቡር ብትለው፥ የራስህንም መንገድ ሳታደርግ፥ ፈቃድህንም ሳታገኝ፥ የራስህንም ቃል ሳትናገር ብታከብረው፥» ኢሳ 58፥13። ሰንበትን በትክክል የመቀደስ መግለጫ ይህ ነው።

«ከሰንበት እግርህን ብትመልስ።» ይህ በቃል ትርጉሙ ወይም በመንፈሳዊ ትርጉሙ ሊረዳ ይችላል። በቃል ትርጉሙ በሰንበት ቀን ረጅም መንገድ ከመሄድና ከመጓዝ እግርህን ብትከለክል ማለት ነው። የአይሁድ መምህራን እንዲሁ ይተረጕሙታል። በመንፈሳዊ ትርጉሙ ደግሞ ፍቅርህን (የነፍስህን እግሮች) ወደ ማንኛውም ዓለማዊ ጉዳይ ከማዘንበል ብትመልስ ማለት ነው።

«በቅዱሱ ቀኔ ፈቃድህን ከማድረግ።» ይህም በጨዋታና በመዝናኛ እንደሚሆን ሥጋዊውን ክፍል ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማድረግ የለብህም ማለት ነው። ይህ በእግዚአብሔር ቀን የዲያብሎስን ሥራ መሥራት ነው።

«ሰንበትንም ደስታ ብትለው።» ደስታ በለው ማለት እንዲሁ ቍጠረው ማለት ነው። ሰንበት ለሥጋዊ ደስታ የሚሆን ቀን ባይሆንም ቅዱስ ደስታ አልተከለከለም። ነፍስ በሰንበት ተግባሮች ደስ ሊላት ይገባል። የጥንት ቅዱሳን ሰንበትን ደስታ አድርገው ቈጠሩት፤ አይሁድ ሰንበትን dies lucis፥ ማለትም የብርሃን ቀን ብለው ጠሩት። የጽድቅ ፀሐይ የሚያበራበት የጌታ ቀን የብርሃንም የደስታም ቀን ነው። ይህ በእግዚአብሔርና በነፍስ መካከል ጣፋጭ ኅብረት የሚደረግበት ቀን ነው። በዚህ ቀን ክርስቲያን ወደ ሰማይ ይወጣል፤ ነፍሱ ከምድር በላይ ከፍ ትላለች፤ ይህስ ያለ ደስታ ሊሆን ይችላልን? ወፍ ከፍ ብላ በበረረች መጠን ዜማዋ ይጣፍጣል። በሰንበት ነፍስ ፍቅሯን በእግዚአብሔር ላይ ታኖራለች፤ ፍቅር ባለበትም ደስታ አለ። በዚህ ቀን የአማኙ ልብ በቅዱሳት ተግባሮች ይቀልጣል፥ ሕያው ይሆናል፥ ይሰፋልም፤ ታዲያ ይህ ሁሉ ሆኖ ስውር ደስታ አብሮት እንዴት አይሄድም? በሰንበት ጸጋ ያላት ነፍስ «በጥላው ልቀመጥ እጅግ ወደድሁ፥ ተቀመጥሁም፤ ፍሬውም ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነበረ» ማለት ትችላለች። መኃ 2፥3። መንፈሳዊ ልብ ሰንበትን ደስታ ከማለት እንዴት ይመለሳል? ንግሥት ሙሽራዋን ንጉሡን የምትገናኝበትን የሠርግ ልብሷን ስትለብስ ደስ አይላትምን? በሰንበት ተግባሮች ላይ ስንሆን ሰማያዊ ሙሽራችንን ጌታ ኢየሱስን የምንገናኝበትን የሠርግ ልብሳችንን እየለበስን ራሳችንን እያስጌጥን ነን፤ ይህስ ደስ የሚያሰኝ አይደለምን? በሰንበት እግዚአብሔር የሰባ ግብዣ ያዘጋጃል፤ ጆሮን በቃሉ፥ ልብንም በጸጋው ይመግባል። እንግዲህ ሰንበትን ደስታ ብንለው ይገባናል። ይህን ቅዱስ ደስታ ማግኘት «በጌታ ቀን በመንፈስ» መሆን ነው።

«የእግዚአብሔርንም ቅዱስ ክቡር ብትለው።» በዕብራይስጥ «የከበረ» ነው። ሰንበትን ክቡር ማለት፥ የአይሁድ መምህራን በስሕተት እንደሚተረጕሙት፥ በዚህ ቀን የተሻለ ልብስ በመልበስ ወይም የተሻለ ምግብ በመብላት የሚሰጠውን ውጫዊ ክብር ያህል አይደለም። አንዳንዶች ለዚህ ቀን የሚሰጡት ዋና ክብር ይህ ነው፤ ሰንበትን ክቡር ማለት ግን ለቀኑ የምንሰጠውን የልብ ክብር ማለት ነው፤ ይኸውም ማክበርና የቀኖች ንግሥት አድርጎ መቍጠር ነው። እግዚአብሔር ስላከበረው ሰንበትን ክቡር አድርገን ልንቈጥረው ይገባል። በሥላሴ ያሉት አካላት ሁሉ አክብረውታል። እግዚአብሔር አብ ባረከው፥ እግዚአብሔር ወልድ በእርሱ ተነሣ፥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ወረደ። ሐዋ 2፥1። ይህ ቀን በመልካም ክርስቲያኖች ሁሉ ሊከበርና እጅግ ሊፈራ ይገባዋል። የምሕረት ወርቅ በትረ መንግሥት የሚዘረጋበት ዝነኛ ቀን ነው። የክርስቲያን ሰንበት የሰማያዊው ሰንበት crepusculum፥ ማለትም ጎሕ ነው። በዚህ ቀን «እግዚአብሔር ወደ እኛ ወርዶ ስለሚጐበኘን» ክቡር ነው። የሰማይ ንጉሥ በጉባኤዎቻችን በልዩ ሁኔታ መገኘቱ የሰንበትን ቀን ክቡር ያደርገዋል። ደግሞም በዚህ ቀን የሚሠራው ሥራ ክቡር ያደርገዋል። ስድስቱ ቀኖች በባርነት ሥራ ተሞልተዋል፤ ይህም ከክብራቸው ብዙውን ያሳጣቸዋል፤ በዚህ ቀን ግን የተቀደሰ ሥራ ይሠራል። ነፍስ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር አምልኮ ተይዛለች፤ ትጸልያለች፥ ትሰማለች፥ ታሰላስላለች፤ እግዚአብሔርን እያመሰገነችና እየባረከች የመላእክትን ሥራ ትሠራለች። ደግሞም ቀኑ በመለኮታዊ ሥርዓት ምክንያት ክቡር ነው። ብር በራሱ ዋጋ አለው፤ የንጉሥ ማኅተም ሲታተምበት ግን ክቡር ይሆናል፤ እንዲሁም እግዚአብሔር በዚህ ቀን ላይ የተቀደሰ ማኅተም፥ የመለኮታዊ ሥልጣንና የመለኮታዊ በረከት ማኅተም አትሞበታል። ይህ ክቡር ያደርገዋል፤ ሰንበትን ደስታና ክቡር ብሎ መጥራትም ሰንበትን መቀደስ ነው።

«የራስህንም መንገድ ሳታደርግ።» ማለትም ማንኛውንም የባርነት ሥራ በመሥራት ቀኑን አታርክሰው።

«ፈቃድህንም ሳታገኝ።» ማለትም በመንሸራሸር፥ በመጠየቅ ወይም በመዝናኛ ሥጋዊውን ክፍል ደስ አታሰኝ።

«የራስህንም ቃል ሳትናገር።» ማለትም ከሰንበት ጋር የማይስማሙና የማይገቡ ቃላትን፥ ከንቱና የማይረቡ ቃላትን፥ ስለ ዓለማዊ ጉዳዮች የሚደረጉ ንግግሮችን አትናገር።

ሁለተኛው ትግበራ። የሰንበት ቀን በቅድስና መጠበቅ ካለበት፥ ሰንበትን ከመቀደስ ይልቅ የሚያረክሱት ይገሠጻሉ። ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ሊሰጥ የሚገባውን ጊዜ ወስደው ለዲያብሎስና ለምኞታቸው አገልግሎት ያውሉታል። ጌታ ይህን ቀን ለራሱ አምልኮ ለይቶታል፤ እነርሱ ግን ተራ ቀን ያደርጉታል። በዚህ ትእዛዝ ዙሪያ «አስብ» ብሎ አጥር አጥሯል፤ እነርሱ ይህን አጥር ያፈርሳሉ፤ አጥርን የሚያፈርስ ግን እባብ ይነድፈዋል። መክ 10፥8። የሰንበት ቀን በእንግሊዝ እየደማ ተኝቷል፤ ኦ! ፓርላማችን በደረሰበት ቍስል ላይ ቅባት ቢያፈስስ! በቤት ሥራ ፈትቶ በመቀመጥ፥ ሥጋ በመሸጥ፥ በከንቱ ንግግር፥ በኃጢአተኛ ጉብኝት፥ በሜዳ በመንሸራሸርና በጨዋታ ይህ ቀን እንዴት ይረክሳል! የእስራኤል ሕዝብ በሰንበት መና እንዲለቅሙ አልተፈቀደላቸውም ነበር፤ እኛስ በዚህ ቀን ጨዋታና ዘፈን እናደርጋለንን? በእውነት ይህን ያህል የሰንበት መርከስ ማየት ሊያሳዝነን ይገባል። ከዳርዮስ ጃንደረቦች አንዱ እስክንድር እግሩን በዳርዮስ ውድ ጠረጴዛ ላይ ሲያኖር አይቶ አለቀሰ። እስክንድርም ለምን እንደሚያለቅስ ጠየቀው። እርሱም ጌታው እጅግ ያከብረው የነበረው ጠረጴዛ አሁን የእግር መረገጫ ሲሆን በማየቱ እንደ ሆነ ተናገረ። እንዲሁ እግዚአብሔር እጅግ የሚያከብረው፥ ያከበረውና የባረከው የሰንበት ቀን የእግር መረገጫ ሆኖ በኃጢአተኞች እግር ሲረገጥ በማየት እናልቅስ። ሰንበትን ማርከስ ታላቅ ኃጢአት ነው፤ እግዚአብሔርን ሆን ብሎ መናቅ ነው፤ ሕጉን ወደ ኋላ መጣል ብቻ ሳይሆን ከእግር በታች መርገጥ ነው። እርሱ «ሰንበትን ቀድስ» ይላል፤ ሰዎች ግን ያረክሱታል። ይህ እግዚአብሔርን መናቅ፥ የእምቢተኝነትን ሰንደቅ ማውለብለብ፥ የፍልሚያ ጓንት መጣልና እግዚአብሔርን ራሱን መገዳደር ነው። እግዚአብሔር በትዕቢተኛ አፈር እንዲህ በድፍረት መጋፈጥን እንዴት ሊታገሥ ይችላል? በእርግጥ ይህን ታላቅ ድፍረት ሳይቀጣ አይተወውም። የእግዚአብሔር እርግማን በሰንበት ሻሪው ላይ ይመጣል፤ በመጣበትም ያደርቃል። የአገሩ ሕግ ሰንበትን የሚሽሩትን ይተዋቸዋል፤ እግዚአብሔር ግን አይተዋቸውም። ክርስቶስ የበለስን ዛፍ እንደ ረገመ ወዲያው ደረቀች። እግዚአብሔር ነገሩን በገዛ እጁ ይይዘዋል፤ የሰንበትን መሻር መቅጣት ይከታተላል። እንዴትስ ይቀጣዋል?

(1) በመንፈሳዊ መቅሠፍቶች። ሰንበትን የሚያረክሱትን ለልብ ድንዳኔና ለደነዘዘ ሕሊና አሳልፎ ይሰጣቸዋል። መንፈሳዊ ፍርዶች ከሁሉ ይልቅ ከባድ ናቸው። «ስለዚህ እንደ ልባቸው ምኞት ተውኋቸው።» መዝ 81፥12። በሕሊና ላይ ያለ የጋለ ብረት ጠባሳ የመጣል ምልክት ነው።

(2) እግዚአብሔር ይህን ኃጢአት ሰዎችን ሌሎች ኃጢአቶች እንዲሠሩ አሳልፎ በመስጠት ይቀጣዋል። ሰንበቱን መሻራቸውን ለመበቀል ቤቶችን ሰብረው እንዲገቡ ይተዋቸዋል፤ በዚህም በዳኛ ይቀጣሉ። ሊገደሉ የሚሄዱ ሌቦች እንዲህ ያለውን ስንት ኑዛዜ ሰምተናል! ሰንበትን ከቶ አላከበሩም፤ እግዚአብሔርም ስለ እነርሱ የሚሞቱበትን ኃጢአት እንዲሠሩ ተዋቸው።

(3) እግዚአብሔር ሰንበትን መሻርን በዚህ ኃጢአት ምክንያት በሰዎች ላይ በሚመጡ ድንገተኛና በሚታዩ ፍርዶች ይቀጣዋል። በንብረታቸውና በአካላቸው ይቀጣቸዋል። አንድ ሰው በጌታ ቀን እህል ወደ ጎተራው ሲያስገባ ቤቱም እህሉም ከሰማይ በወረደ እሳት ተቃጠሉ። በዊልትሻየር በጌታ ቀን የዳንስ ውድድር ተዘጋጅቶ ነበር፤ ከተሰበሰቡትም አንዱ ሲደንስ ድንገት ወድቆ ሞተ። «የእግዚአብሔር ፍርዶች ትያትር» የተባለው መጽሐፍ በየጌታ ቀኑ በስብከት ሰዓት አደን ይሄድ ስለ ነበረ አንድ ሰው ይተርካል፤ ከሚስቱ የውሻ ራስ ያለው ልጅ ተወለደለት፤ እንደ አዳኝ ውሻም ይጮኽ ነበር። ኃጢአቱ ጭራቃዊ ነበረ፤ በጭራቃዊ ልደትም ተቀጣ። ጌታ አይሁድን የሰንበትን ቀን ባይቀድሱ በበሮቻቸው እሳት እንደሚያነድድ አስፈራራቸው። ኤር 17፥27። በለንደን የተነሣው አስፈሪ እሳት በሰንበት ቀን ጀመረ፤ እግዚአብሔር ያን ጊዜ ስለ ሰንበት ማርከሳችን እንደሚቀጣን ከሰማይ ሊነግረን የፈለገ ይመስል። በዚህ ሕይወት በሞት ብቻ ሳይሆን በኋላም በኵነኔ ይቀጣዋል። የእግዚአብሔርን ሰንበት የሚሽሩ፥ እነርሱና አጋንንት የሚታሰሩበትን የጨለማ ሰንሰለት መስበር ይችሉ እንደ ሆነ ይዩ።

ሦስተኛው ትግበራ። ወደ ሰንበት ቅድስና ይመክረናል።

ይህን ቀን በቅድስና መጠበቅን የሕሊና ጉዳይ አድርጉት። ሌሎቹ ትእዛዛት አዎንታዊ ብቻ ወይም አሉታዊ ብቻ አላቸው፤ ይህ አራተኛው ትእዛዝ ግን አዎንታዊም አሉታዊም አለው። «የሰንበትን ቀን ቀድስ» እና «በእርሱ ምንም ሥራ አትሥራ» የሚለው፥ እግዚአብሔር ይህን ቀን በጥንቃቄ እንድንጠብቅ ምን ያህል እንደሚፈልግ ያሳያል። እናንተ ራሳችሁ ይህን ቀን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከእጃችሁ በታች ያሉት ሁሉ እንዲጠብቁት ተጠንቀቁ፤ «አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም»፤ ይህም አለቃ፥ ወላጅ ወይም ጌታ የሆንህ አንተ፥ አንተ ራስህ ብቻ ሳትሆን በአደራህና በትምህርትህ ሥር ያሉትም ቀኑን እንዲቀድሱ መጠንቀቅ አለብህ ማለት ነው። አገልጋዮቻቸው እንዲያገለግሏቸው የሚጠነቀቁ፥ እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ ግን ግድ የሌላቸው የቤተ ሰብ ጌቶች ተወቃሾች ናቸው፤ ሰውነታቸው እስካገለገላቸው ድረስ አገልጋዮቻቸው ዲያብሎስን ቢያገለግሉ ግድ የላቸውም። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ Serva depositum ብሎ «መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።» ያለው ሰፊ ትርጉም አለው። 2ጢሞ 1፥14። ለራስህ ነፍስ ብቻ ሳይሆን በአደራ ለተሰጡህ ነፍሳትም ተጠንቀቅ። ከእጅህ በታች ያሉት ሰንበትን እንዲቀድሱ ተመልከት። የእግዚአብሔር ሕግ አንድ ሰው የባዘነ በሬ ወይም አህያ ቢያገኝ እንዲመልሰው አዝዞአል፤ የልጅህ ወይም የአገልጋይህ ነፍስ ከእግዚአብሔር ስትባዝንና ሰንበቱን ስትሽር ብታይ፥ ይህን ቀን በሃይማኖት ወደ መጠበቅ ልትመልሰው እንዴት እጅግ አብልጦ ይገባሃል!

ሰንበትን ወደ መቀደስ እንድገፋፋችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ቀን አጥብቀው ለሚጠብቁት የሰጠውን ታላላቅ በረከቶች ተመልከቱ። ኢሳ 58፥14። (1) የደስታ ተስፋ። «በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል።» በእግዚአብሔር ደስ መሰኘት ተግባርም ዋጋም ነው። በዚህ ክፍል ዋጋ ነው፤ «በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል»፤ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ ይመስላል፦ ሰንበትን በሕሊና ብትጠብቅ በደስታ የሚሞላህን እሰጥሃለሁ፤ ሰንበትን በፈቃደኝነት ብትጠብቅ በደስታ እንድትጠብቀው አደርግሃለሁ። በተግባርህ መስፋትንና አብዝቶ የሚያረካህን ውስጣዊ መጽናናት እሰጥሃለሁ፤ ነፍስህ በደስታ ጅረት ትትረፈረፋለች፤ ስለዚህ «ጌታ ሆይ፥ ሰንበትህን በመጠበቅ ታላቅ ዋጋ አለ» ትላለህ። (2) የክብር ተስፋ። «በምድርም ከፍታዎች ላይ አስቀምጥሃለሁ።» ይህም ወደ ክብር ከፍ አደርግሃለሁ ማለት ነው፤ ascendere faciam፤ ሙንስተር እንዲህ ይተረጕመዋል። አንዳንዶች የምድርን ከፍታዎች ይሁዳ ብለው ይረዱታል፤ ግሮቲየስ እንዲሁ ይላል፤ በዙሪያው ካሉት አገሮች ከፍ ብሎ ወደ ተቀመጠው ወደ ይሁዳ ምድር አገባሃለሁ። (3) የምድርና የሰማይ ተስፋ። «የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ»፤ ይህም በከነዓን ጣፋጭ ነገሮች ሁሉ እመግብሃለሁ፤ ከዚያም በኋላ ከነዓን ምሳሌው ብቻ ወደ ነበረው ወደ ሰማይ አፈልስሃለሁ ማለት ነው። ሌላም ተስፋ አለ፤ «ይህን የሚያደርግ ሰው፥ ሰንበትን ከማርከስ የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።» ኢሳ 56፥2። «ብፁዕ ነው»፤ በዕብራይስጥ «ብፅዕናዎች» ነው። ሰንበትን ለሚቀድስ ብፅዕና በብፅዕና ላይ ይሆንለታል፤ በላይኛውና በታችኛው ምንጮች ይባረካል፤ በስሙ፥ በንብረቱ፥ በነፍሱና በዘሩ ይባረካል። ይህን ያህል በረከት ለእርሱና ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የሚወረስለት ሆኖ ሰንበትን ከማርከስ የማይጠብቅ ማን ነው? ደግሞም ሰንበትን በሕሊና መጠበቅ ሳምንቱን ሁሉ ልብን ለእግዚአብሔር አገልግሎት ያዘጋጃል። ክርስቲያን ሆይ፥ በሰንበት ይበልጥ በተቀደስህ መጠን በሚቀጥለው ሳምንት ይበልጥ ቅዱስ ትሆናለህ።

ጨርሰዋል፦ 2.4 አራተኛው ትእዛዝ

ቀዳሚ ቀጣይ