ምዕራፍ 5 · 17 ደቂቃ ንባብ · 22 ደቂቃ ማዳመጥ
2.1 የመጀመሪያው ትእዛዝ
«ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።» ዘጸ 20፥3።
ትእዛዙ «አንተ» ብሎ በሁለተኛ መደብ ነጠላ የተነገረው ለምንድን ነው? እግዚአብሔር «ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑላችሁ» ያላለው ለምንድን ነው?
ትእዛዙ እያንዳንዱን ሰው ስለሚመለከትና እግዚአብሔር እያንዳንዱ በስሙ እንደ ተነገረው አድርጎ እንዲቀበለው ስለሚፈልግ ነው። እኛ መብቶችን ለራሳችን ለመውሰድ ፈጣኖች ብንሆንም ግዴታዎችን ግን ከራሳችን ላይ ወደ ሌሎች ለማሸጋገር ዝንባሌ አለን፤ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው በስሙ እንደ ተጠራ ያህል ለእርሱ መነገሩን ያውቅ ዘንድ ትእዛዙ «አንተ»፥ «አንተ» እያለ በሁለተኛ መደብ ተነገረ። አሁን ወደ ትእዛዙ እንመጣለን፤ «ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።» የእውነተኛ ሃይማኖት ሁሉ መሠረት ስለ ሆነ ይህ ትእዛዝ ግንባር ቀደም ሆኖ መምራቱና በትእዛዛቱ ሁሉ ፊት መቀመጡ ተገቢ ነው። የዚህ ትእዛዝ ፍሬ ነገር እግዚአብሔርን በልባችን እንድንቀድሰውና ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ቅድሚያ እንድንሰጠው ነው። የዚህ ትእዛዝ ሁለት ቅርንጫፎች አሉ፤ 1. አምላክ ሊኖረን ይገባል። 2. አንድ ብቻ ሊኖረን ይገባል። ወይም እንዲህ፤ 1. እግዚአብሔርን አምላካችን አድርገን ልንይዘው ይገባል። 2. ሌላ ሊኖረን አይገባም።
1. እግዚአብሔርን አምላካችን አድርገን ልንይዘው ይገባል። አምላክ ሊኖረን እንደሚገባ ግልጥ ነው፤ «ከእግዚአብሔርም በቀር አምላክ ማን ነው?» 2ሳሙ 22፥32። ጌታ ያህዌ (በሦስት አካላት አንድ አምላክ) እውነተኛ፥ ሕያውና ዘላለማዊ አምላክ ነው፤ እርሱንም አምላካችን አድርገን ልንይዘው ይገባል።
[1] እግዚአብሔር አምላክ እንዲሆንልን ማድረግ እርሱን አምላክ ብሎ መቀበል ነው። የአሕዛብ አማልክት ጣዖታት ናቸው። መዝ 96፥5። ደግሞም «ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደ ሆነ ... እናውቃለን» (1ቆሮ 8፥4)፤ ማለትም በውስጡ ምንም መለኮትነት የለውም። «ጣዖት ሆይ፥ እርዳኝ» ብለን ብንጮኽ ጣዖት ሊረዳ አይችልም፤ ጣዖታቱ ራሳቸው ተማርከው ተወሰዱ፤ ስለዚህ ጣዖት ከንቱ ነው። ኢሳ 46፥2። ከንቱነት ይነገርበታል፤ ስለዚህ አምላክ መሆኑን አንቀበልም። ኤር 14፥22። ነገር ግን ex animo [ከልብ] እርሱ አምላክ መሆኑን ስንቀበል ይህን አምላክ አምላካችን አድርገን እንይዘዋለን። ሕዝቡ ሁሉ በግንባራቸው ወድቀው «እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው! እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው!» አሉ። 1ነገ 18፥39። አዎን፥ እርሱ ብቻ አምላክ መሆኑን እንቀበላለን። «በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ብቻህን አምላክ ነህ።» 2ነገ 19፥15። መለኮትነት የእርሱን ዘውድ ብቻ የሚያስጌጥ ዕንቁ ነው። በተጨማሪም እንደ እርሱ ያለ አምላክ እንደሌለ እንቀበላለን። «ሰሎሞንም በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆመ፤ እንዲህም አለ፦ የእስራኤል አምላክ አቤቱ እግዚአብሔር፥ እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም።» 1ነገ 8፥22, 23። «በሰማያት ከእግዚአብሔር ጋር የሚተካከል ማን ነው? ከኃያላንስ ልጆች እግዚአብሔርን የሚመስል ማን ነው?» መዝ 89፥6። በከለዳውያን ትርጉም «ከመላእክት መካከል ማን ነው?» ይላል። እግዚአብሔር እንደሚያደርገው ማንም ሊያደርግ አይችልም፤ ዓለምን ከምንም አስገኘ፤ «ምድርንም በምንም ላይ አንጠለጠለ።» ኢዮ 26፥7። በልባችን ስናምን፥ በአንደበታችን ስንመሰክር፥ በእጃችንም ስንፈርም እርሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ እንደ ሆነና የሚወዳደረው እንደሌለ፥ እግዚአብሔር አምላክ ይሆንልናል።
[2] እግዚአብሔር አምላክ እንዲሆንልን ማድረግ እርሱን መምረጥ ነው። «የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን»፤ ማለትም እግዚአብሔርን አምላካችን እንዲሆን እንመርጣለን። ኢያ 24፥15። አእምሮ እግዚአብሔርን መቀበሉ አንድ ነገር ነው፤ ፈቃድ እርሱን መምረጡ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ሃይማኖት የአጋጣሚ ጉዳይ ሳይሆን የምርጫ ጉዳይ ነው።
እግዚአብሔርን አምላካችን አድርገን ከመምረጣችን በፊት እውቀት ሊኖር ይገባል። ከመምረጣችን በፊት ልናውቀው ይገባል። ማንም የሚያገባውን ሰው ከመምረጡ በፊት ስለዚያ ሰው አንዳች እውቀት ሊኖረው ይገባል፤ እንዲሁም እግዚአብሔርን አምላካችን አድርገን ከመምረጣችን በፊት ልናውቀው ይገባል። «የአባትህን አምላክ እወቅ።» 1ዜና 28፥9። እግዚአብሔርን በባሕርያቱ፥ በቅድስና የከበረ፥ በምሕረት ባለ ጠጋ፥ በተስፋዎቹም ታማኝ እንደ ሆነ ልናውቀው ይገባል። በልጁም ልናውቀው ይገባል። ፊት በመስተዋት እንደሚታይ፥ እንዲሁ በክርስቶስ እንደ ጥሩ መስተዋት የእግዚአብሔር ውበትና ፍቅር ሲያበራ እናያለን። ይህ እውቀት እግዚአብሔርን ከመምረጥ ሊቀድም ይገባል። ላክታንቲዩስ የፈላስፎች ትምህርት ሁሉ የእግዚአብሔር እውቀት ስለ ጐደለው ራስ የሌለው ነበር አለ። ይህ መምረጥ የበሰለ ማሰላሰል ድርጊት ነው። ክርስቲያን በእግዚአብሔር ያለውን እጅግ የላቀ መልካምነት ካየና በፍጹምነቱ በቅዱስ አድናቆት ከተመታ በኋላ፥ ልቡን የሚያኖርበት እንዲሆን ከሌሎች ነገሮች ሁሉ ለይቶ ይመርጠዋል፤ እንደ ያዕቆብም «እግዚአብሔር አምላኬ ይሆናል» ይላል። ዘፍ 28፥21። እግዚአብሔርን የሚመርጥ ራሱን ለእግዚአብሔር ይሰጣል። «ለፍርሃትህ ለተሰጠ ለባሪያህ።» መዝ 119፥38። የመቅደሱ ዕቃዎች ከተራ አገልግሎት ተለይተው ለቅዱስ አገልግሎት እንደ ተቀደሱ፥ እንዲሁ እግዚአብሔርን አምላኩ እንዲሆን የመረጠ ራሱን ለእግዚአብሔር ቀድሶአል፤ ከእንግዲህም ለርኩስ አገልግሎት አይሰጥም።
[3] እግዚአብሔር አምላክ እንዲሆንልን ማድረግ እርሱ አምላካችን እንዲሆን ከእርሱ ጋር ጽኑ ኪዳን መግባት ነው። ከምርጫ በኋላ የጋብቻ ኪዳን ይከተላል። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ኪዳን እንደሚገባ፥ «የታመነችውን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘላለምን ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ» (ኢሳ 55፥3)፥ እንዲሁ እኛም ከእርሱ ጋር ኪዳን እንገባለን፤ «የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ ቃል ኪዳን ገቡ።» 2ዜና 15፥12። «አንዱ፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ይላል፤ ሌላውም በእጁ፦ ለእግዚአብሔር ብሎ ይጽፋል»፤ ስማቸውን በወታደሮች መዝገብ ላይ እንደሚፈርሙ ወታደሮች። ኢሳ 44፥5። «እግዚአብሔር አምላካችን ይሆናል» የሚለውን ይህን ኪዳን በጌታ እራት ብዙ ጊዜ አድሰነዋል፤ ይህም በውል ላይ እንዳለ ማኅተም ከእግዚአብሔር ጋር አጥብቆ ያስረናል፤ ከእርሱም እንዳንለይ ይጠብቀናል።
[4] እግዚአብሔር አምላክ እንዲሆንልን ማድረግ ስግደትን መስጠት ነው፤ ይህም እርሱን በማክበር ነው፤ «በዙሪያው ባሉት ሁሉ ዘንድ እግዚአብሔር የተፈራ ነው።» መዝ 89፥7። በእግዚአብሔር ዙፋን ዙሪያ የቆሙት ሱራፌል ፊታቸውን ሸፈኑ (ኢሳ 6)፤ ኤልያስም እግዚአብሔር ሲያልፍ ለአክብሮት ምልክት በመጐናጸፊያው ተጠቀለለ። ይህ አክብሮት ለእግዚአብሔር ቅዱስ ግርማ ያለንን ከፍ ያለ ግምት ያሳያል። ስግደትም ለእርሱ በማጐንበስ ወይም እርሱን በማምለክ ነው። «በቅድስና ውበት ለእግዚአብሔር ስገዱ።» መዝ 29፥2። «ራሳቸውንም አዘንብለው በግምባራቸው ወደ ምድር ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ።» ነህ 8፥6። መለኮታዊ አምልኮ ለመለኮት ብቻ የሚገባ ልዩ ክብር ነው፤ እግዚአብሔር ይቀናለታል፤ ማንም ፍጡር እንዲካፈለውም አይፈቅድም። «ክብሬን ለሌላ አልሰጥም።» ኢሳ 42፥8። ገዢዎች ሕዝባዊ አክብሮት ሊሰጣቸው ይችላል፤ ሃይማኖታዊ ስግደት ግን ለእግዚአብሔር ብቻ ሊሆን ይገባል።
[5] እግዚአብሔር አምላክ እንዲሆንልን ማድረግ እርሱን መፍራት ነው። «ይህን የከበረና የሚያስፈራ ስም፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ትፈራ ዘንድ።» ዘዳ 28፥58። እግዚአብሔርን መፍራት (1) ሁልጊዜ በዓይናችን ፊት እንዲሆን ማድረግ ነው፤ «እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አደረግሁት።» መዝ 16፥8። «ዓይኖቼ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው።» መዝ 25፥15። እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የሚያደርገውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚመለከትና እንደ ዳኛም ሥራዎቹን ሁሉ እንደሚመዝን ያስባል። (2) እግዚአብሔርን መፍራት ኃጢአት ለመሥራት እስከማንደፍር ድረስ በልባችን ላይ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍርሃት እንዲኖር ማድረግ ነው። «ፍሩ፥ ኃጢአትንም አትሥሩ።» መዝ 4፥4። ኃጥአን ኃጢአትን ይሠራሉ አይፈሩምም፤ ጻድቃን ግን ይፈራሉ ኃጢአትንም አይሠሩም። «እንግዲህ ይህን ታላቅ ክፋት እንዴት አደርጋለሁ? በእግዚአብሔርስ ፊት እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?» ዘፍ 39፥9። ኃጢአት ሥራ ብትለኝ መርዝ ጠጣ እንደምትለኝ ነው። የአንሴልም አባባል እንዲህ ነው፤ «ሲኦል በአንድ ወገን ኃጢአትም በሌላ ወገን ቢሆን፥ በአምላኬ ላይ በፈቃዴ ኃጢአት ከመሥራት ይልቅ ወደ ሲኦል መዝለልን እመርጣለሁ።» እግዚአብሔርን የሚፈራ ኃጢአቱ የቱንም ያህል የተሰወረ ቢሆን አይሠራውም። «ደንቆሮውን አትስደበው፤ በዕውሩም ፊት ማሰናከያ አታኑር፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።» ዘሌ 19፥14። ደንቆሮውን ሰው ብትረግም ሊሰማህ አይችልም፤ ወይም በዕውር መንገድ ላይ ማሰናከያ አኑረህ ብታወድቀው ስታደርገው ሊያይህ አይችልም፤ እግዚአብሔርን መፍራት ግን በሰዎች ሊሰሙም ሊታዩም የማይችሉትን ኃጢአቶች እንድትተው ያደርግሃል። እግዚአብሔርን መፍራት ሰውን መፍራትን ያጠፋል። ሦስቱ ብላቴኖች እግዚአብሔርን ፈሩ፤ ስለዚህ የንጉሡን ቍጣ አልፈሩም። ዳን 3፥16። ታላቁ ድምፅ ትንሹን ያሰምጣል፤ የነጐድጓድ ድምፅ የወንዝን ድምፅ ያሰምጣል፤ እንዲሁ የእግዚአብሔር ፍርሃት በነፍስ ውስጥ የበላይ ሲሆን ሌላውን የሥጋ ፍርሃት ሁሉ ያሰምጣል። ቅዱስ የልጅነት ፍርሃት ሲኖረን እግዚአብሔርን አምላክ እንዲሆንልን እናደርገዋለን።
[6] እግዚአብሔር አምላክ እንዲሆንልን ማድረግ በእርሱ መታመን ነው። «አቤቱ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዓይኖቼ ወደ አንተ ናቸው፤ በአንተ ታምኛለሁ።» መዝ 141፥8። «የዓለቴ አምላክ፥ በእርሱ እታመናለሁ።» 2ሳሙ 22፥3። ከእግዚአብሔር በቀር ልንታመንበት የምንችል ማንም የለም። ፍጥረታት ሁሉ የሐሰት መጠጊያ ናቸው፤ እንደ ግብጽ ሸምበቆ ናቸው፤ ሊደግፉን እጅግ ደካሞች፥ ሊያቈስሉን ግን በቂ ብርቱዎች ናቸው። 2ነገ 18፥21። Omnis motus fit super immobili [የማይንቀሳቀሰው በምንም ሁከት አይናወጥም]። መታመናችንን የምንገነባበት በቂ መሠረት እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስንታመንበት አምላክ እናደርገዋለን፤ ሳንታመንበት ግን ጣዖት እናደርገዋለን። በእግዚአብሔር መታመን እንደ ፈጣሪ በኃይሉ፥ እንደ አባትም በፍቅሩ መደገፍ ነው። በእግዚአብሔር መታመን ዋናውን ሀብታችንን፥ ማለትም ነፍሳችንን፥ ለእርሱ አደራ መስጠት ነው። «ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ።» መዝ 31፥5። ወላጅ የሌለው ልጅ ርስቱን ለሞግዚቱ አደራ እንደሚሰጥ፥ እንዲሁ ነፍሳችንን ለእግዚአብሔር አደራ እንሰጣለን። ያን ጊዜ አምላክ ይሆንልናል።
ነገር ግን በእግዚአብሔር በትክክል መታመናችንን እንዴት እናውቃለን? በእግዚአብሔር በትክክል ብንታመን በአንድ ጊዜ እንደምንታመንበት በሌላም ጊዜ እንታመንበታለን። «በዘመኑ ሁሉ በእርሱ ታመኑ።» መዝ 62፥8። በችግራችን ልንታመንበት እንችላለንን? በለስ ሳታፈራ፥ የምድር ምርኩዞቻችን ሲሰበሩ፥ በእግዚአብሔር ተስፋ ላይ ልንደገፍ እንችላለንን? መጽናናትን ያመጡልን የነበሩት ቧንቧዎች ሲቈረጡ፥ ትኩስ ምንጮቻችን ሁሉ ባሉበት በእግዚአብሔር ልንኖር እንችላለንን? ከጭንቀት እንጀራ በቀር የምንበላው እንጀራ ሳይኖረን (ሕዝ 12፥19)፥ ከእንባ በቀርም የምንጠጣው ውኃ ሳይኖረን፥ በመዝ 80፥5 እንደ ተባለ፦ «ብዙ እንባን አጠጣሃቸው»፤ ያን ጊዜ ያስፈልገንን እንዲሰጠን በእግዚአብሔር አቅርቦት ልንታመን እንችላለንን? ጥሩ ክርስቲያን እግዚአብሔር ቁራዎችን ከመገበ ልጆቹን እንደሚመግብ ያምናል፤ ለጸጋ ብቻ ሳይሆን ለምግብም በእግዚአብሔር ሁሉን በቂነት ይኖራል። እግዚአብሔር መንግሥተ ሰማያትን ከሰጠው የዕለት እንጀራን እንደሚሰጠው ያምናል፤ በውሉ ይታመናል፤ «በእውነት ትመገባለህ።» መዝ 37፥3። በፍርሃታችን በእግዚአብሔር ልንታመን እንችላለንን? ጠላቶች ሲበረቱ የእምነትን ዓላማ ልናውለበልብ እንችላለንን? «በምፈራበት ቀን እኔ በአንተ እታመናለሁ።» መዝ 56፥3። እምነት የልብን መንቀጥቀጥ ይፈውሳል፤ ዘይት በውኃ ላይ እንደሚንሳፈፍ ከፍርሃት በላይ ይወጣል። በእግዚአብሔር መታመን አምላክ እንዲሆንልን ያደርገዋል።
[7] እግዚአብሔር አምላክ እንዲሆንልን ማድረግ እርሱን መውደድ ነው። በጻድቃን ዘንድ ፍርሃትና ፍቅር ይሳሳማሉ።
[8] እርሱ አምላክ እንዲሆንልን ማድረግ እርሱን መታዘዝ ነው። በዚህ ላይ በሁለተኛው ትእዛዝ በሰፊው እናገራለሁ።
ከእግዚአብሔር ጋር እንደ አምላካችን ልንጣበቅ የሚገባን ለምንድን ነው?
(1) ከፍትሐዊነቱ የተነሣ። ሕልውናችንን ከተቀበልንበት ከእርሱ ጋር መጣበቃችን ትክክል ብቻ ነው። እስትንፋሳችንን ከሚሰጠን የበለጠ በእኛ ላይ መብት ያለው ማን ነው? «እርሱ ሠራን፥ እኛም አይደለንም።» መዝ 100፥3። ፍቅራችንን ወይም አምልኮአችንን ከእግዚአብሔር በቀር ለሌላ መስጠት ኢፍትሐዊ፥ አዎን፥ ውለታ ቢስነትም ነው።
(2) ከጥቅሙ የተነሣ። ከእግዚአብሔር ጋር እንደ አምላካችን ብንጣበቅ ይባርከናል፤ «እግዚአብሔር አምላካችን ይባርከናል።» መዝ 67፥6። በንብረታችን ይባርከናል። «የምድርህ ፍሬ የተባረከ ይሆናል፤ እንቅብህና ቡሓቃህ የተባረኩ ይሆናሉ።» ዘዳ 28፥4, 5። ጆንያችን በእህል የተሞላ ብቻ ሳይሆን በጆንያው አፍ ገንዘብም ይኖረናል። በሰላም ይባርከናል። «እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል።» መዝ 29፥11። በውጫዊ ሰላም ይባርከናል፤ እርሱም የጥጋብ ሞግዚት ነው። «በዳርቻሽ ሰላምን ያደርጋል።» መዝ 147፥14። በውስጣዊ ሰላምም፥ ማለትም ከማር ወለላ ጠብታ በሚጣፍጥ ፈገግ ባለ ሕሊና። እግዚአብሔር ክፉውን ሁሉ ለበጎአችን ይለውጠዋል። ሮሜ 8፥28። ከመርዝ ፍቱን መድኃኒት ያዘጋጃል። የዮሴፍ መታሰር ለከፍታው ምክንያት ሆነ። ዘፍ 50፥20። ከመራራው መድኃኒት ክብሩንና መዳናችንን ያወጣል። ባጭሩ እስከ ሞት መሪያችን፥ በሞት መጽናኛችን፥ ከሞትም በኋላ ዋጋችን ይሆናል። ስለዚህ ጥቅሙ ከእግዚአብሔር ጋር እንደ አምላካችን እንድንጣበቅ ሊያደርገን ይገባል። «እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው።» መዝ 144፥15።
(3) ከአስፈላጊነቱ የተነሣ። እግዚአብሔር አምላካችን ካልሆነ በረከታችንን ይረግማል፤ የእግዚአብሔር እርግማንም በደረሰበት ሁሉ ያጠወልጋል። ሚል 2፥2። እግዚአብሔር አምላካችን ካልሆነ በመከራችን የሚረዳን የለንም። ጠላቶቹን ይረዳልን? የካዱትን ያግዛልን? እግዚአብሔርን አምላካችን ካላደረግነው እርሱ ራሱን ዳኛችን ያደርጋል፤ ቢኰንንም ወደ ላቀ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት የለም። ስለዚህ ለዘላለም ከመከራ ጋር ልንታጭ ካላሰብን በቀር እግዚአብሔርን አምላካችን አድርገን መያዝ አስፈላጊ ነው።
የመጀመሪያው ትግበራ። ጌታ ያህዌን አንድ አምላካችን አድርገን ልንይዘው ከተገባ፥ ይህ አምላክ የሌላቸውን አምላክ የለሾችን ይኰንናል። «ሰነፍ በልቡ፦ አምላክ የለም ይላል።» መዝ 14፥1። የሚያምንበት ወይም የሚያመልከው አምላክ የለውም። እንደነዚህ ያሉ አምላክ የለሾች ዲያጎራስና ቴዎዶሮስ ነበሩ። ሴኔካ ኔሮን ስለ ኃጢአቱ በገሠጸው ጊዜ ኔሮ፦ «እንዲህ ያሉትን ነገሮች እያደረግሁ አምላክ እንዳለ የማምን ይመስልሃልን?» አለ። የሲሌዥያ መስፍን እጅግ ከመታለሉ የተነሣ Neque inferos, neque superos esse ማለትም አምላክም ዲያብሎስም የለም ብሎ አረጋገጠ። እግዚአብሔርን በጣቶቹ ሥራ ልናየው እንችላለን። ፍጥረት መለኮትን የምናነብበት ታላቅ መጽሐፍ ነው፤ አምላክን የሚክድ የገዛ ዓይኖቹን ያወጣ ነው። አርስጣጣሊስ አሕዛብ ቢሆንም «የሕልውናዎች ሁሉ ሕልውና ሆይ፥ ማረኝ» ብሎ በጮኸ ጊዜ እግዚአብሔርን ተቀበለ ብቻ ሳይሆን፥ መለኮትን የማይመሰክር በሕይወት ሊኖር አይገባውም ብሎ አሰበ። በአምላክ ማመን የማይወዱ ይቀምሱታል። «በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው።» ዕብ 10፥31።
ሁለተኛው ትግበራ። እግዚአብሔርን አምላካቸው አድርገው እንደሚቀበሉ እየመሰከሩ አምላካቸው እንደ ሆነ የማይኖሩ ክርስቲያኖች ይኰነናሉ። (1) እንደ አምላክ አያምኑበትም። ኃጢአታቸውን ሲመለከቱ፦ እግዚአብሔር ይቅር ሊል ይችላልን? ለማለት ይቀናቸዋል። ጕድለታቸውንም ሲመለከቱ፦ እግዚአብሔር ሊያቀርብ ይችላልን፥ በምድረ በዳ ማዕድ ሊያዘጋጅ ይችላልን? ይላሉ። (2) እንደ አምላክ አይወድዱትም። የፍቅራቸውን ምርጥ ክፍል አይሰጡትም፤ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሌሎች ነገሮችን ለመውደድ ያዘነብላሉ፤ እግዚአብሔርን እንወዳለን ይላሉ፥ ለእርሱ ግን ምንም አይተዉም። (3) እንደ አምላክ አያመልኩትም። ወደ አምላክ እንደሚጸልዩ ያን ያህል አክብሮት አይሰጡትም፥ በዚያ ያህል ትጋትም አይጸልዩም። ልባቸው ምንኛ የሞተ ነው! በኃጢአት ባይሞቱም ለአገልግሎት ሞተዋል። ዓይን እያለው እንደማያይ፥ ጆሮ እያለው እንደማይሰማ አምላክ ይጸልያሉ። ቃሉን በመስማት ብዙዎች ምን ያህል ይበታተናሉ፥ ልባቸውስ ምንኛ ግድ የለሽ ነው! ስለ ሱቆቻቸውና ስለ ሸቀጦቻቸው ያስባሉ። ንጉሥ ሲያነጋግረን በላባ ብንጫወት ይወድደዋልን? እግዚአብሔር በቃሉ ሲያነጋግረን ልባችንም በዓለም ሐሳብ ሲያዝ ይህ በላባ መጫወት አይደለምን? ወይ፥ እግዚአብሔርን አምላክ እንዲሆንልን አለማድረጋችን ብዙዎቻችንን እንዴት ሊያዋርደን ይገባል! እንደ አምላክ አናምንበትም፥ አንወድደውም፥ አናመልከውም። ብዙ አሕዛብ የሐሰት አማልክቶቻቸውን አንዳንድ ክርስቲያኖች እውነተኛውን አምላክ ከሚያመልኩት በበለጠ ትኩረትና ትጋት አምልከዋል። ኦ፥ ራሳችንን እንገሥጽ፤ እንገሥጽ አልሁን? በሃይማኖት ስላለብን መሞትና ልማዳዊነት ራሳችንን እንጸየፍ፤ እግዚአብሔርን እንዴት እንደ መሰከርን፥ እንደ አምላክ ግን እንዳላመለክነው።
II. ሌላ አምላክ ሊኖረን እንደማይገባ። «ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።»
«ከእኔ በቀር»፥ ማለትም «በፊቴ» የሚለው ቃል ምን ማለት ነው?
በገጼ ፊት ማለት ነው፤ in conspectu meo፥ ማለትም በዓይኔ ፊት። «የተቀረጸውን ምስል ሠርቶ በስውር የሚያኖረው ሰው ርጉም ይሁን።» ዘዳ 27፥15። አንዳንዶች በሌሎች ፊት ለጣዖቱ አይሰግዱም ነበር፥ በስውር ግን ይሰግዱለት ነበር፤ ይህ ከሰው ዓይን የተሰወረ ቢሆንም ከእግዚአብሔር ዓይን የተሰወረ አልነበረም። ስለዚህ እግዚአብሔር «ምስሉን በስውር የሚያኖር ርጉም ይሁን» ይላል። «ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።» 1. በእውነት ሌላ አምላክ የለም። 2. ሌላ አምላክ ሊኖረን አይገባም።
[1] በእውነት ሌላ አምላክ የለም። ቫለንቲናውያን ሁለት አማልክት አሉ ብለው ያምኑ ነበር፤ ብዙ አማልክትን የሚያምኑት ብዙ አማልክት አሉ አሉ፤ ፋርሳዊው ፀሐይን አመለከ፤ ግብፃውያን በሬንና ዝሆንን፥ ግሪኮችም ጁፒተርን አመለኩ፤ ከእውነተኛው አምላክ በቀር ግን ሌላ የለም። «እንግዲህ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደ ሆነ፥ ከእርሱም በቀር ሌላ እንደሌለ ዛሬ እወቅ፥ በልብህም አስብ።» ዘዳ 4፥39። ምክንያቱም፥ (1) ሕልውናው ከራሱ የሆነ፥ ሌሎች ፍጥረታትም ሁሉ በእርሱ ላይ የተመሠረቱበት ፊተኛ ምክንያት አንድ ብቻ ነው። በሰማያት Primum Mobile ሌሎቹን ሉሎች ሁሉ እንደሚያንቀሳቅስ፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ታላቁ አንቀሳቃሽ ነው፤ ለሚኖረው ነገር ሁሉ ሕይወትንና እንቅስቃሴን ይሰጣል።
(2) ሁሉን የሚችል ኃይል አንድ ብቻ ነው። ሁሉን የሚችሉ ሁለት ቢኖሩ፥ በሁለቱ መካከል ሁልጊዜ ክርክር እንዳለ ልንገምት ግድ ይሆንብናል፤ አንዱ ሊያደርግ የሚወድደውን ሌላው በኃይል እኩል ስለ ሆነ ይቃወመዋል፤ እንዲህም ሁሉ ነገር ይታወካል። አንዲት መርከብ እኩል ሥልጣን ያላቸው ሁለት መሪዎች ቢኖሩአት፥ አንዱ ሌላውን ሁልጊዜ ይቃወማል፤ አንዱ ሊጓዝ ሲወድድ ሌላው መልሕቅ ይጥላል፤ ሁከት ይሆናል፥ መርከቢቱም ትጠፋለች። በዓለም ያለው ሥርዓትና ስምምነት፥ የነገሮች ሁሉ የማይለወጥና ወጥ የሆነ አስተዳደር፥ ሁሉን የሚችል አንድ ብቻ፥ ሁሉን የሚገዛ አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ግልጽ ማስረጃ ነው። «እኔ ፊተኛ ነኝ፥ እኔም ኋለኛ ነኝ፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም።» ኢሳ 44፥6።
[2] ሌላ አምላክ ሊኖረን አይገባም። «ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።» ይህ ትእዛዝ የሚከለክለው፦ (1) እውነተኛውን አምላክ ትቶ ሐሰተኛ አምላክን ማገልገልን ነው። «ግንዱን፦ አንተ አባቴ ነህ፥ ድንጋዩንም፦ አንተ ወለድኸኝ ይላሉ።» ኤር 2፥27። (2) ሐሰተኛ አምላክን ከእውነተኛው ጋር ማቆራኘትን ነው። «እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፥ የገዛ አማልክቶቻቸውንም ያመልኩ ነበር።» 2ነገ 17፥33። እነዚህ በትእዛዙ የተከለከሉ ናቸው፤ ሌላውን ሳይሆን እውነተኛውን አምላክ አጥብቀን ልንይዝ ይገባናል። «እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነው»፥ ባላጋራንም አይታገሥም። ሚስት በአንድ ጊዜ ሁለት ባሎች በሕግ ሊኖሩአት እንደማይችሉ፥ እኛም ሁለት አማልክት ሊኖሩን አይገባም። «ለሌላ አምላክ አትስገድ፤ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና።» ዘጸ 34፥14። «ወደ ሌላ አምላክ የሚቸኩሉ ኀዘናቸው ይበዛል።» መዝ 16፥4። እግዚአብሔር ሌላ አምላክን መከተልን «እርሱን እንደ መተው» ይቆጥረዋል። «እግዚአብሔርን ተዉ፥ ሌሎችንም አማልክት ተከተሉ።» መሳ 2፥12። እግዚአብሔር ሕዝቡ የጣዖታትን ስም እንኳ እንዲጠሩ አይወድድም። «የሌሎችንም አማልክት ስም አትጥሩ፥ ከአፋችሁም አይሰማ።» ዘጸ 23፥13። ሌሎችን አማልክት መከተልን እግዚአብሔር የጋብቻን ኪዳን እንደ ማፍረስ ይመለከተዋል። ስለዚህ እስራኤል በወርቁ ጥጃ ጣዖትን ባመለኩ ጊዜ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የነበረውን ድርሻ ካደ። «ሕዝብህ ረከሰ።» ዘጸ 32፥7። ቀድሞ እግዚአብሔር እስራኤልን ሕዝቤ ብሎ ይጠራቸው ነበር፤ ሌሎችን አማልክት በተከተሉ ጊዜ ግን እግዚአብሔር ሙሴን «አሁን ሕዝብህ ናቸው እንጂ ከእንግዲህ ሕዝቤ አይደሉም» አለው። «እናታችሁን ተምዋገቱ፥ ተምዋገቱ፤ እርስዋ ሚስቴ አይደለችምና።» ሆሴ 2፥2። ለእኔ ታማኝነትን አልጠበቀችም፥ በጣዖታት ራስዋን አረከሰች፤ ስለዚህ እፈታታለሁ፤ «እርስዋ ሚስቴ አይደለችም።» ሌሎችን አማልክት መከተል እግዚአብሔር የማይታገሠው ነገር ነው፤ ቍጣውን በፊቱ ያስነሣዋል። «የእናትህ ልጅ ወንድምህ፥ ወይም ወንድ ልጅህ፥ ወይም በብብትህ ያለች ሚስትህ፥ ወይም እንደ ነፍስህ ያለ ወዳጅህ በስውር፦ ኑ፥ ሄደን ሌሎችን አማልክት እናምልክ ብሎ ቢያስትህ፥ እሺ አትበለው፥ ዓይንህም አትራራለት፤ ነገር ግን ፈጽመህ ግደለው፤ ለመግደሉም በመጀመሪያ እጅህ በኋላም የሕዝቡ ሁሉ እጅ በእርሱ ላይ ይሁን።» ዘዳ 13፥6, 8, 9።
ከእውነተኛው አምላክ ሌላ ሌሎች አማልክት መኖር ምን ማለት ነው? ብንመረምር፥ ከምናውቀው በላይ ብዙ ጣዖት አምላኪዎች በመካከላችን እንዳሉ እፈራለሁ።
(1) ከእግዚአብሔር ይልቅ በማንኛውም ነገር መታመን ያንን ነገር አምላክ ማድረግ ነው። በባለጠግነታችን ብንታመን ባለጠግነትን አምላካችን እናደርገዋለን። በእርሱ መጽናናት እንችላለን እንጂ መተማመናችንን በእርሱ ላይ ልንጥል አይገባም። በእርሱ መታመን ሞኝነት ነው። ባለጠግነት አታላይ ነው፤ በሚያታልለን ነገር መታመንም ሞኝነት ነው። ማቴ 13፥22። ጽኑ መሠረት የለውም፤ ነፍስ ስትነቃ ወይም ወደ ልቧ ስትመለስ ባዶዋን እንደሚተዋት እንደ ሥዕል ትዕይንት ወይም እንደ ወርቃማ ሕልም ነው። የሚሰጠውን ተስፋ አይፈጽምም፤ ምኞታችንን ሊያረካ ተስፋ ይሰጣል፥ ነገር ግን ያበዛዋል፤ ከእኛ ጋር ሊኖር ተስፋ ይሰጣል፥ ነገር ግን ክንፍ አውጥቶ ይበርራል። ጐጂም ነው። «ለባለቤቱ ጕዳት የተጠበቀ ባለጠግነት።» መክ 5፥13። በሚጐዳ ነገር መታመን ሞኝነት ነው። ለመደገፍ ብሎ የምላጭን ስለት የሚይዝ ማን ነው? ብዙ ጊዜ ለትዕቢትና ለምኞት ማገዶ ይሆናል። ሕዝ 28፥5። ኤር 5፥7። በባለጠግነታችን መታመን ስንፍና ነው፤ ይሁን እንጂ ስንቶች ይታመኑበታል፥ ገንዘብንም አምላካቸው ያደርጋሉ! «የባለጠጋ ሀብቱ የጸናች ከተማው ነው።» ምሳ 10፥15። የወርቁን ጡብ ተስፋው ያደርጋል። ኢዮ 31፥24። እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር ሠራው፤ ሰው ደግሞ ከምድር አፈር አምላክ ይሠራል። ገንዘብ ፈጣሪው፥ ቤዛውና አጽናኙ ነው፦ ፈጣሪው ነው፥ ገንዘብ ካለው ተሠርቻለሁ ብሎ ያስባልና፤ ቤዛው ነው፥ በአደጋ ውስጥ ቢሆን እንዲቤዠው በገንዘቡ ይታመናልና፤ አጽናኙ ነው፥ ቢያዝን ገንዘብ ክፉውን መንፈስ የሚያባርር የወርቅ በገና ነውና። እንዲህ በገንዘብ በመታመን አምላክ እናደርገዋለን።
በሥጋ ክንድ ብንታመን አምላክ እናደርገዋለን። «በሰው የሚታመን፥ ሥጋንም ክንዱ የሚያደርግ ሰው ርጉም ነው።» ኤር 17፥5። ሶርያውያን አገሩን እስኪሞላ ድረስ እጅግ ብዙ በሆነው ሠራዊታቸው ታመኑ፤ ይህ የሥጋ ክንድ ግን ደረቀ። 1ነገ 20፥27, 29። መታመኛችን የምናደርገውን እግዚአብሔር እፍረታችን ያደርገዋል። በጎች ለመጠለያ ወደ ቅጥሮች ይሮጣሉ፥ ጠጕራቸውንም ያጣሉ፤ እንዲሁ እኛም እንዲረዱን ወደ ሁለተኛ ምክንያቶች ሮጥን፥ ከወርቃማ ጠጕራችንም ብዙውን አጣን፤ የሚከዱን ሸምበቆዎች ብቻ ሳይሆኑ የሚወጉን እሾሆችም ሆኑብን። በላያቸው አብዝተን በመደገፋችን የፓርላማ ምርኩዞቻችንን ሰበርን።
በጥበባችን ብንታመን አምላክ እናደርገዋለን። «ጠቢብ በጥበቡ አይመካ።» ኤር 9፥23። መመካት የመተማመን ጫፍ ነው። ብዙ ሰው አእምሮውንና ችሎታውን ጣዖት ያደርጋል፤ ራሱን አምላክ ያደርጋል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን በተንኰላቸው ስንት ጊዜ ይይዛቸዋል! ኢዮ 5፥13። አኪጦፌል ታላቅ አእምሮ ነበረው፥ ምክሩም እንደ እግዚአብሔር ቃል ነበረ፤ አእምሮው ግን ወደ ገመድ አደረሰው። 2ሳሙ 17፥23።
በጨዋነታችን ብንታመን አምላክ እናደርገዋለን። ብዙዎች ማንም በከባድ ኃጢአት ሊከሳቸው አለመቻሉን መታመኛ ያደርጋሉ። ጨዋነት የተጣራና የሠለጠነ ተፈጥሮ ብቻ ነው፤ ሰው ሊታጠብ ይችላል፥ ነገር ግን ላይለወጥ ይችላል፤ ኑሮው ጨዋ ሊሆን ይችላል፥ በልቡ ግን የሚገዛ ኃጢአት ሊኖር ይችላል። ፈሪሳዊው «አመንዝራ አይደለሁም» ሊል ቻለ (ሉቃ 18፥11)፤ «ትዕቢተኛ አይደለሁም» ግን ሊል አልቻለም። በጨዋነት መታመን በሸረሪት ድር መታመን ነው።
እንዲያድኑን በሃይማኖታዊ ተግባሮቻችን ብንታመን አምላክ እናደርጋቸዋለን። «ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው»፤ በኃጢአት ተበክሎአል። ኢሳ 64፥6። ወርቅን በእሳት ውስጥ አኑር፥ ብዙ ዝቃጭም ይወጣል፤ እንዲሁ እጅግ ወርቃማ የሆኑት ተግባሮቻችን ከድካም ጋር የተቀላቀሉ ናቸው። ወይ ተግባርን ቸል ለማለት ወይ ጣዖት ለማድረግ እናዘነብላለን። ተግባርን ፈጽም፥ ነገር ግን አትታመንበት፤ ያን ጊዜ አምላክ ታደርገዋለህና። በጸሎትህና ቃሉን በመስማትህ አትታመን፤ የመዳን መንገዶች ናቸው እንጂ አዳኞች አይደሉም። ተግባሮችን የምትንሳፈፍባቸው ፊኛዎች ብታደርጋቸው ከእነርሱ ጋር ወደ ሲኦል ልትሰምጥ ትችላለህ።
በጸጋችን ብንታመን አምላክ እናደርገዋለን። ጸጋ ፍጡር ብቻ ነው፤ ብንታመንበት ጣዖት እናደርገዋለን። ጸጋ ፍጹም አይደለም፤ እንዲያድነን ፍጹም ባልሆነ ነገር ልንታመን አይገባም። «እኔ በየዋህነቴ ሄድሁ፤ በእግዚአብሔርም ታመንሁ።» መዝ 26፥1፦ ዳዊት በየዋህነቱ ሄደ፥ በየዋህነቱ ግን አልታመነም። «በእግዚአብሔር ታመንሁ።» በጸጋዎቻችን ብንታመን ክርስቶስ እናደርጋቸዋለን። መልካም ጸጋዎች ናቸው፥ ነገር ግን መጥፎ ክርስቶሶች ናቸው።
(2) ከእግዚአብሔር ይልቅ ማንኛውንም ነገር መውደድ ያንን ነገር አምላክ ማድረግ ነው። ከእግዚአብሔር ይልቅ ሀብታችንን ብንወድድ አምላክ እናደርገዋለን። በወንጌል ያለው ጐበዝ ከአዳኙ ይልቅ ወርቁን ወደደ፤ ዓለም ከክርስቶስ ይልቅ ለልቡ ቀረበች። ማቴ 19፥22። Fulgens hoc aurum praestringit oculos [ይህ ወርቅ በብልጭታው ዓይንን ያሳውራል]። ቫርዩስ። ገንዘብን የሚመኝ ሰው ጣዖት አምላኪ ተብሎ ተጠርቶአል። ኤፌ 5፥5። ስለ ምን? ከእግዚአብሔር ይልቅ ሀብቱን ስለሚወድድ አምላኩ ያደርገዋልና። ለጣዖት ባይሰግድም በገንዘቡ ላይ የተቀረጸውን ምስል ቢያመልክ ጣዖት አምላኪ ነው። ከልባችን የሚበዛውን የሚይዘውን ነገር አምላክ እናደርገዋለን።
ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላችንን ብንወድድ አምላክ እናደርገዋለን። «ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ።» 2ጢሞ 3፥4። ብዙዎች ልጓሙን ይለቅቃሉ፥ ለሥጋዊ ደስታ ሁሉ ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ፤ ተድላን ጣዖት ያደርጋሉ። «ከበሮንና በገናን ይዘው ይዘምራሉ፥ በእምቢልታም ድምፅ ደስ ይላቸዋል። ዘመናቸውን በፈንጠዝያ ያሳልፋሉ።» ኢዮ 21፥12, 13, (በዳር ማስታወሻ)። በአፍሪካ ሕዝቡ ጊዜያቸውን ሁሉ በጭፈራና በፈንጠዝያ የሚያሳልፉበት ስፍራ እንዳለ አንብቤአለሁ፤ እግዚአብሔር በውኃ ውስጥ እንዲጫወቱ እንደ ሌዋታን የፈጠራቸው ይመስል፥ ጊዜያቸውን ቲያትር በማየትና የጭፈራ አዳራሾችን በመጐብኘት የሚያሳልፉ፥ ተድላን አምላክ የሚያደርጉ ብዙዎች በእኛ መካከል የሉምን? መዝ 104፥26። በሰርዲንያ አገር ማንም ከእርሱ አብዝቶ ቢበላ እየሳቀ የሚሞትበት እንደ በለሳን ያለ ቅጠል አለ፤ ተድላም እንዲህ ያለ ቅጠል ነው፤ ማንም ያለ ልክ ቢመገበው እየሳቀ ወደ ሲኦል ይወርዳል። ተድላን አምላክ የሚያደርጉ እነዚህን ሁለት የመጽሐፍ ክፍሎች ብቻ ያንብቡ። «የሰነፎች ልብ በደስታ ቤት ነው።» መክ 7፥4። «ራስዋን እንደ አከበረችና እንደ ተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ኀዘን ስጡአት።» ራእ 18፥7። ስኳር እርጥብ ስፍራ ቢቀመጥ ውኃ ይሆናል፤ እንዲሁ የኃጢአተኞች ስኳር የተቀባ ደስታና ተድላ ሁሉ በመጨረሻ የእንባ ውኃ ይሆናል።
ከእግዚአብሔር ይልቅ ሆዳችንን ብንወድድ አምላክ እናደርገዋለን። «ሆዳቸው አምላካቸው ነው።» ፊልጵ 3፥19። የእስክንድርያው ቀሌምንጦስ ልቡ በሆዱ ውስጥ ስለ ነበረ ዓሣ ጽፎአል፤ ይህም ልባቸው በሆዳቸው ያለ የሆዳሞች ምሳሌ ነው፤ sacrificare lari ይሻሉ፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ለዚህም አምላክ የመጠጥ ቍርባን ያፈስሳሉ። ጌታ ተፈጥሮን ለማደስ የሚገባውን ይፈቅዳል። «ትበላና ትጠግብ ዘንድ ሣርን እሰጣለሁ።» ዘዳ 11፥15። የምግብ ፍላጎትን ከማርካት በቀር ሌላ ነገርን አለማሰብ ግን ጣዖት አምልኮ ነው። «ሆዳቸው አምላካቸው ነው።» የአእምሮን በትረ መንግሥት የምትይዝ፥ ለመላእክትም ዘመድ የሆነች ያቺ ልዕልት ክፍል ነፍስ ለእንስሳዊው ክፍል ባሪያ መሆንዋ እንዴት ያሳዝናል!
ከእግዚአብሔር ይልቅ ልጅን ብንወድድ አምላክ እናደርገዋለን። በዚህ ረገድ ስንቶች በደለኞች ናቸው? ስለ ልጆቻቸው ያስባሉ፥ ከእግዚአብሔርም ይልቅ በእነርሱ ደስ ይላቸዋል፤ ስለ ፊተኛ ፍቅራቸው መጥፋት ይልቅ ስለ በኵር ልጃቸው መጥፋት ያዝናሉ። ይህ ልጅን ጣዖት ማድረግና በእግዚአብሔር ስፍራ ማኖር ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ተቈጥቶ ልጆቻችንን ይወስዳል። ከሰጪው ይልቅ ዕንቁውን ብንወድድ፥ ፍቅራችን እንደ ገና ወደ እርሱ ይመለስ ዘንድ እግዚአብሔር ዕንቁውን ይወስደዋል።
የመጀመሪያው ትግበራ። ይህ ሌሎች አማልክት ያሏቸውን፥ በዚህም እውነተኛውን አምላክ የሚክዱትን ይገሥጻል። (1) ጣዖታትን የሚያቆሙትን። «ይሁዳ ሆይ፥ አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቍጥር ናቸው።» ኤር 2፥28። «መሠዊያዎቻቸው በእርሻ ትልም ላይ እንዳሉ ክምሮች ናቸው።» ሆሴ 12፥11። (2) መናፍስት ጠሪዎችን የሚፈልጉትን። ይህ በእግዚአብሔር ሕግ የተኰነነ ኃጢአት ነው። «በመካከልህ መናፍስት ጠሪ አይገኝ።» ዘዳ 18፥11። ብዙ ጊዜ ሰዎች ከንብረታቸው አንዳች ቢጠፋባቸው እንዴት መልሰው እንደሚያገኙት ለማወቅ ወደ ጠንቋዮችና ወደ ሟርተኞች ይልካሉ። ይህ ዲያብሎስን በማማከርና በእርሱ በመታመን አምላክ ማድረግ ካልሆነ ምንድን ነው? ምን! ንብረታችሁን ስላጣችሁ ነፍሳችሁንም ደግሞ ታጣላችሁን? 2ነገ 1፥6። ዲያብሎስን የምትማከሩት በሰማይ አምላክ የሌለ ስለሚመስላችሁ አይደለምን? ማንም በደለኛ ቢሆን ራሱን ያዋርድ።
ሁለተኛው ትግበራ። ይህ በጆሮአችን የማፈግፈግን መለከት ይነፋል። ማንኛውንም ፍጡር ጣዖት ከማድረግ ይጥራን፥ ሌሎችን አማልክት ክደን እውነተኛውን አምላክና አገልግሎቱን አጥብቀን እንድንይዝ ይምራን። ከእግዚአብሔር ብንርቅ የተሻለ ስፍራ የት እንደምናገኝ አናውቅም።
(1) እውነተኛውን አምላክ ማገልገል ክብር ነው። Servire Deo est regnare [እግዚአብሔርን ማገልገል መንገሥ ነው]። ነገሥታት እኛን ከሚያገለግሉን ይልቅ እግዚአብሔርን ማገልገል የበለጠ ክብር ነው። (2) እውነተኛውን አምላክ ማገልገል ደስ የሚያሰኝ ነው። «በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ።» ኢሳ 56፥7። እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ በሥርዓቱ ውስጥ የፍቅሩን ዓላማ ይዘረጋል፥ የደስታንም ዘይት በልብ ውስጥ ያፈስሳል። የእግዚአብሔር መንገዶች ሁሉ የደስታ መንገዶች ናቸው፤ ጐዳናዎቹም በጽጌረዳ የተነጠፉ ናቸው። ምሳ 3፥17። (3) እውነተኛውን አምላክ ማገልገል ጠቃሚ ነው። ሰዎች እዚህ ታላቅ ትርፍ አላቸው፤ የተሰወረውን መና፥ ውስጣዊ ሰላምን፥ ወደፊትም ታላቅ ዋጋን። እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ሲሞቱ መንግሥትን ያገኛሉ፥ ከገነት አበቦች የተሠራውንም አክሊል ይቀዳጃሉ። ሉቃ 12፥32፤ 1ጴጥ 5፥4። እውነተኛውን አምላክ ማገልገል እውነተኛ ጥቅማችን ነው። እግዚአብሔር ክብሩንና መዳናችንን አንድ ላይ አቆራኝቶአል። እንድናምን ያዘናል፤ ስለ ምን? እንድንድን ነው። ስለዚህ ሌሎችን ሁሉ ክደን እውነተኛውን አምላክ አጥብቀን እንያዝ። (4) ሌሎችን ሁሉ ክዳችሁ እውነተኛውን ያህዌ ልታገለግሉ ኪዳን ገብታችኋል። አንድ ሰው ከጌታው ጋር ኪዳን ቢገባ፥ የውሉም ሰነድ ተጽፎ ቢታተም፥ ወደ ኋላ ሊመለስ አይችልም፤ ዘመኑን ፈጽሞ ማገልገል አለበት። እኛም ሌሎችን ሁሉ ክደን ጌታን አምላካችን አድርገን ልንቀበል በጥምቀት ኪዳን ገብተናል፤ ይህንንም ኪዳን በጌታ እራት አድሰናል፤ ታዲያ የተሳልነውን ስእለትና ኪዳን አንጠብቅምን? እጅግ የከፋውን መሐላ ማፍረስ ሳንፈጽም ከእግዚአብሔር ልንርቅ አንችልም። «ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ [ከሰንደቅ ዓላማው ሾልኮ እንደሚኰበልል ወታደር]፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም።» ዕብ 10፥38። «የቍጣን ጽዋዎች በእርሱ ላይ አፈስሳለሁ፥ ፍላጾቼንም በደም አሰክራለሁ።» (5) እግዚአብሔርንና አገልግሎቱን አጥብቆ በመያዙ የተጸጸተ ማንም የለም። አንዳንዶች ዓለምን አምላክ በማድረጋቸው ተጸጽተዋል። ካርዲናል ዎልዚ «ወይ! ንጉሤን እንዳገለገልሁ አምላኬን ባገለግል ኖሮ፥ እንዲህ ባልተወኝ ነበር!» አለ። እግዚአብሔርን በማገልገሉ ያማረረ ማንም የለም፤ በሞት አልጋቸው ላይ መጽናናታቸውና አክሊላቸው ነበረ።