ምዕራፍ 31 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ቀን 30 — «አንተ ተከተለኝ!»
«ጴጥሮስም ይህን አይቶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል? አለው። ኢየሱስም። እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ፥ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ አለው።»
— ዮሐንስ 21:21-22
ኢየሱስ ጴጥሮስን ወደ ቦታው መልሶ በጎቹን እንዲያሰማራ ከነገረው በኋላ ወዲያውኑ ስለ ወደ ፊት ሕይወቱ አንድ ነገር ነገረው። ጴጥሮስ ሲሸመግል ኢየሱስን በመከተሉ መከራ እንደሚቀበል ተናገረ።
ጴጥሮስ ከኋላቸው ይመጣ ወደ ነበረው ወደ ዮሐንስ ዞር ብሎ ተመለከተ። ከዚያም «ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል?» ብሎ ጠየቀ።
በሌላ አነጋገር፦ ዮሐንስስ ምን ይገጥመዋል? የእርሱም ሕይወት ከባድ ይሆናል? ይህ ፍትሐዊ ነው?
አንተስ እንዲህ አድርገህ ታውቃለህ? ሕይወትህን ከሌላ ሰው ሕይወት ጋር አወዳድረህ ታውቃለህ? እርሱ ያን እንዲያደርግ ለምን ይፈቀድለታል፣ እኔ ግን ለምን አይፈቀድልኝም? ለምን ለእርሱ ቀለለት? ለምን እርሱ ብዙ ዕቃ፣ ብዙ ችሎታ ወይም ብዙ ጓደኞች አሉት?
ኢየሱስ ለጴጥሮስ ቀላል መልስ ሰጠው፦ «ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ!»
በሌላ አነጋገር፦ ስለ ዮሐንስ ታሪክ አትጨነቅ። ያ በእኔና በእርሱ መካከል ያለ ጉዳይ ነው። አንተ እኔን በመከተል ላይ አተኩር።
ኢየሱስ ለእያንዳንዱ ተከታዩ የተለየ መንገድ አለው። የጴጥሮስ መንገድ ከዮሐንስ መንገድ የተለየ ነበረ። የአንተም መንገድ ከጓደኞችህ መንገድ የተለየ ይሆናል። አንዳንድ ወንዶች ፓስተሮች፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የቧንቧ ሠራተኞች ይሆናሉ። አንዳንዶቹ ዝነኞች ይሆናሉ፤ አብዛኞቹ ግን አይሆኑም። አንዳንዶቹ ቀላል ሕይወት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከባድ ሕይወት ይኖራቸዋል። ነገር ግን የሁላችንም ሥራ አንድ ነው፦ ኢየሱስን መከተል።
ይህ መጽሐፍ የሚያበቃው እዚህ ላይ ነው። ታማኝ መሆንን ተምረሃል፦
- በቅንነት፦ ከውስጥ እስከ ውጭ እውነተኛ በመሆን፣ በትክክል በመጫወት፣ ማንም በማያይበት ጊዜ ትክክለኛውን በማድረግና ኃጢአትን ባለመደበቅ፤
- ከስክሪኖች ጋር፦ ኢየሱስን አለቃ አድርገህ በመጠበቅ፣ ቀኖችህን በመቍጠር፣ ቍጣህን በመቈጣጠር፣ ለክፋት የዋህ ሆነህ በመኖር፣ ከእውነተኛው ሕይወት ባለመጥፋትና በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘት፤
- ፈተናን በመቋቋም፦ እንዴት እንደሚሠራ በማወቅ፣ በመትጋትና በመጸለይ፣ ከክፉ በመሸሽና መልካሙን በመከታተል፣ ከጓደኞች እርዳታ በማግኘት፣ ዘላለማዊውን ነገር በአንድ ሳህን ወጥ ባለመለወጥና ወደ ኢየሱስ በመሮጥ፤
- በማሸነፍና በመሸነፍ፦ ለማሸነፍ በመሮጥ፣ ለእግዚአብሔር መምሰል ራስህን በማሠልጠን፣ በተሸነፉት ላይ ባለመሳለቅ፣ ወደ ፊት በመገስገስ፣ ባለመመካትና ሁሉን በኢየሱስ ስም በማድረግ፤
- ደግሞም ኢየሱስን በመከተል፦ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ እንደሚያመጣው እንደ እንድርያስ፣ በቅንነት እንደ ጠየቀው እንደ ቶማስ፣ መውደድን እንደ ተማረው የነጎድጓድ ልጅ እንደ ዮሐንስ፣ እንዲሁም ወድቆ ወደ ቦታው እንደ ተመለሰው እንደ ጴጥሮስ።
ስለ ሌላ ሰው መንገድ አትጨነቅ። ኢየሱስ ለጴጥሮስ የተናገረውን ቃል አሁን ለአንተ እየነገረህ ነው፦ «አንተ ተከተለኝ!»
እውነተኛ ታሪክ፦ ሃድሰን ቴለር ለቻይና ሕዝብ ስለ ኢየሱስ ለመናገር የፈለገ ከእንግሊዝ የመጣ ወጣት ነበር። እዚያ ሲደርስ ሚስዮናውያኑ እንደ እንግሊዛውያን እንደሚለብሱና እንደሚኖሩ አስተዋለ፤ በዚህም ምክንያት ቻይናውያን እንደ እንግዶች ያዩአቸው ነበር። ስለዚህ ሀድሰን አስደንጋጭ ነገር አደረገ። የእንግሊዝ ልብሶቹን አስቀምጦ እንደ ቻይና ሰዎች ለበሰ፤ እንዲያውም የቻይና ወንዶች እንደሚያደርጉት ጠጕሩን አሳድጎ ጐነጐነ። አንዳንድ ጓደኞቹ ሳቁበት። እርሱ ግን ሌሎች የሚያደርጉትን ግድ አልሰጠውም። እግዚአብሔር እየጠራው እንደ ሆነ ባመነበት መንገድ ኢየሱስን ተከተለ። የሚያስፈልገውን እንዲሰጥ በእግዚአብሔር ብቻ በመታመን፣ በመቶዎች የሚቈጠሩ ሠራተኞችን ወደ ቻይና ውስጠኛ ክፍል የላከ ሚስዮን ጀመረ። ሙሉ ታሪኩን ለእግዚአብሔር ደፋር በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ማንበብ ትችላለህ።
አስብበት፦ ሕይወትህን ከሌላ ሰው ሕይወት ጋር ታወዳድራለህ? ኢየሱስን በመከተል ላይ ብቻ ማተኮር ምን ይመስላል?
ሞክረው፦ ዛሬ ራስህን ከሌሎች ጋር ስታወዳድር ባገኘኸው ቍጥር የኢየሱስን ቃል አስታውስ፦ «አንተ ተከተለኝ!»
ውድ ኢየሱስ ሆይ፣ ስለ ሌላ ሰው መንገድ መጨነቅ አልፈልግም። አንተን ብቻ መከተል እፈልጋለሁ። በቅንነት፣ ከስክሪኖች ጋር፣ ፈተናን በመቋቋም፣ በማሸነፍና በመሸነፍ፣ በሕይወቴም ዘመን ሁሉ በየቀኑ አንተን በመከተል ታማኝ እንድሆን እርዳኝ። በስምህ፣ አሜን።