ምዕራፍ 13 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ቀን 12 — ከእግዚአብሔር ጋር ከመስመር ውጭ
«ማለዳም ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ ወጣ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ በዚያ ጸለየ።»
— ማርቆስ 1:35
ከዚያ በፊት በነበረው ቀን ኢየሱስ እጅግ በጣም ተጠምዶ ውሎ ነበር። በምኩራብ አስተምሮ ነበር። የጴጥሮስን አማት ፈውሶ ነበር። ምሽት ሲሆን ደግሞ የከተማው ሕዝብ ሁሉ በቤቱ ደጃፍ ተሰበሰበ። ኢየሱስ ብዙ ሕመምተኞችን ፈወሰ፤ ብዙዎችንም ከክፉ መናፍስት ነጻ አወጣ። በጣም አድካሚ ቀን እንደ ነበር ጥርጥር የለውም።
ታዲያ ኢየሱስ በማግስቱ ጠዋት ምን አደረገ?
«ማለዳም ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ ወጣ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ በዚያ ጸለየ።»
ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር። ቢሆንም ከአባቱ ጋር ብቻውን የሚሆንበት ጊዜ ያስፈልገው ነበር። ሕዝቡ ሳያገኙት፣ የቀኑ ሩጫ እንደ ገና ሳይጀምር፣ ለመጸለይ ወደ ጸጥ ያለ ስፍራ ሄደ።
ዛሬ ብዙዎቻችን ከእንቅልፍ ስንነሣ ወዲያው ስክሪን እናነሣለን። ከአልጋችን እንኳ ሳንወርድ መልእክቶችን እናያለን፣ ገጾችን እናንሸራትታለን ወይም ጌም እንከፍታለን። ጠዋት መጀመሪያ የምንሰማው ድምፅ የእግዚአብሔር አይደለም። የስልክ ማሳወቂያ ነው።
ኢየሱስ ያደረገውን ብታደርግስ? ኢንተርኔት ላይ ከመግባትህ በፊት ከእግዚአብሔር ጋር «ከመስመር ውጭ» ጊዜ ብታሳልፍስ?
ረጅም ጊዜ መሆን የለበትም። ውጭም መጨለም የለበትም! ነገር ግን እነዚህን ልትሞክር ትችላለህ፦
- ስልክህን ወይም ታብሌትህን ሌሊቱን በሌላ ክፍል አሳድረው።
- ማንኛውንም ስክሪን ከመክፈትህ በፊት ጥቂት ደቂቃዎች መጽሐፍ ቅዱስህን አንብብ።
- መጀመሪያ ጸልይ። ከማንም ጋር ከመነጋገርህ በፊት ስለ ቀንህ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋገር።
- የራስህን «ምድረ በዳ» ፈልግ፤ ለምሳሌ መኝታ ቤትህን፣ የቤቱን አንድ ጥግ ወይም ከቤት ውጭ ያለ አንድ ቦታ፣ ከእግዚአብሔር ጋር በጸጥታ የምትሆንበት ስፍራ።
በዚህ ሳምንት ስክሪኖችህን ስለ መቆጣጠር ተምረሃል፤ አለቃህ ስክሪን ሳይሆን ኢየሱስ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ዘመንህን መቍጠር፣ ቍጣህን መግዛት፣ ስለ ክፉ ነገር የዋህ ሆኖ መቆየት እና ከእውነተኛው ሕይወት አለመጥፋት። ስክሪኖችን በቦታቸው ለማቆየት ከሁሉ የተሻለው መንገድ እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ስፍራ እንዲይዝ ማድረግ ነው።
እውነተኛ ታሪክ፦ አዶናይራም ጃድሰን ስለ ኢየሱስ ለሰዎች ለመንገር በ1812 ከአሜሪካ ወደ በርማ በመርከብ ተጓዘ። ገጽ በገጽ እየሠራ መጽሐፍ ቅዱስን ከአዲስ ኪዳን ጀምሮ ወደ በርማ ቋንቋ በመተርጎም ብዙ ዓመታት አሳለፈ። ከዚያም ጦርነት ተነሣ፤ አዶናይራምም ወደ አስከፊ እስር ቤት ተወርውሮ ሁለት ዓመት ያህል ታሰረ። ትልቁ ጭንቀቱ ውድ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሙ ተገኝቶ እንዳይጠፋ ነበር። ስለዚህ ሚስቱ አን ገጾቹን ጠንካራና ጐርባጣ በሆነ ትራስ ውስጥ ሰፍታ ወደ እስር ቤቱ አመጣችለት። ጠባቂዎቹ እንዲህ ያለውን አስቀያሚ ትራስ ስላልፈለጉት ተዉት። አዶናይራም ሌሊት በሌሊት በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተኛ፤ ቃሉም ተጠበቀ። መጽሐፍ ቅዱስን እጅግ ይወድደው ስለ ነበር በሕይወቱ ጠበቀው። ሙሉ ታሪኩን ለእግዚአብሔር ደፋር በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ማንበብ ትችላለህ።
አስብበት፦ ከእንቅልፍህ ስትነሣ ብዙ ጊዜ መጀመሪያ የምታደርገው ምንድን ነው? የቀንህን የመጀመሪያ ክፍል ለእግዚአብሔር መስጠት ምን ሊመስል ይችላል?
ሞክረው፦ ነገ ጠዋት ማንኛውንም ስክሪን ከመንካትህ በፊት አምስት ደቂቃ ከእግዚአብሔር ጋር አሳልፍ፤ አንድ መዝሙር አንብብና ጸልይ።
ኢየሱስ ሆይ፣ አንተ እንኳ ከአባትህ ጋር ብቻህን የምትሆንበት ጊዜ ያስፈልግህ ነበር። ስክሪኖቼን አስቀምጬ ከአንተ ጋር ጊዜ እንዳሳልፍ እርዳኝ። የቀኔን የመጀመሪያ ክፍል ለአንተ እንድሰጥ እርዳኝ። በስምህ፣ አሜን።