ምዕራፍ 12 · 2 ደቂቃ ንባብ
የመዳን ጸሎት
ክርስትና ሃይማኖት አይደለም፤ የእግዚአብሔርን ዓይነት ሕይወት መኖር ነው።
እግዚአብሔር ዓለሙን እጅግ ስለ ወደደ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ ሁሉ እንዲሞት ሰጠ። ለምን? እኔና አንተ እንዳንጠፋ ነገር ግን የዘላለም ሕይወት እንዲኖረን ነው! እንዴት ድንቅ ነው! እኔ የዘላለም ሕይወት አለኝ፤ አንተም ዳግመኛ ተወልደህ ከሆነ የዘላለም ሕይወት አለህ። ገና ዳግመኛ ካልተወለድህ፣ ይህች ቅጽበት ዕድልህ ናት። በኢየሱስ ክርስቶስ በልብህ ብታምንና በሕይወትህ ላይ ጌታ እንደ ሆነ ብትመሰክር የዘላለም ሕይወት ይኖርሃል!
«ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁሉ ሞተ አልሽ፤ ታዲያ የዘላለም ሕይወት ያላቸው ዳግመኛ የተወለዱት ብቻ ናቸው የምትዪው ለምንድን ነው?» ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አንድ ወዳጅህ ለአንተ ቼክ እንደ ፈረመልህ በሚናገረው ምሳሌ ልጀምር። እንደሚታወቀው ገንዘቡ የአንተ ነው። ነገር ግን ገንዘብህን ለመውሰድ ወደ ባንክ ካልሄድህና ይልቁንም ቼኩን ከጣልኸው፣ ለአንተ ፈርመውልህ እንኳ ያንን ገንዘብ አታገኘውም። የዘላለም ሕይወትም እንዲሁ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለሙ ሁሉ ሞተ። ነገር ግን የዘላለም ሕይወት የሚሰጠው ጌታችን ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ፣ እንደ መጣ፣ እንደ ሞተ፣ እንደ ተነሣና ዛሬም ሕያው እንደ ሆነ ለሚያምኑ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወትህ ጌታ መሆኑን ስታውቅ፣ ስትቀበልና ስትመሰክር የዘላለም ሕይወት ወዲያውኑ በመንፈስህ ውስጥ ይሰጣል። የዘላለም ሕይወትን የምትቀበለው በዚህ መንገድ ነው። ጌታ ይመስገን!
አሁን ይህን የዘላለም ሕይወት፣ የእግዚአብሔርን ዓይነት ሕይወት ልትቀበል ትፈልጋለህ? ገና ካላደረግህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትህ ጌታ እንድታደርገው እጋብዝሃለሁ። እባክህ እመን፤ እንዲህም ብለህ ጸልይ፦ «ጌታ አምላክ ሆይ፥ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ልቤ አምናለሁ። ስለ እኔ እንደ ሞተና እግዚአብሔር ከሙታን እንዳስነሣው አምናለሁ። ዛሬ ሕያው እንደ ሆነ አምናለሁ። ከዛሬ ጀምሮ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወቴ ጌታ እንደ ሆነ በአፌ እመሰክራለሁ። በእርሱና በስሙ የዘላለም ሕይወት አለኝ፤ ዳግመኛ ተወልጃለሁ። ጌታ ሆይ፥ ነፍሴን ስላዳንኻት አመሰግንሃለሁ! አሁን የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ። ሃሌ ሉያ!»
እንኳን ደስ አለህ! አሁን ከእግዚአብሔር ቃል የተወለድህ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ። ጌታ ክርስቶስ አሁን በአንተ ውስጥ ስለሚኖርና ጽድቁ ስላደረገህ፣ እጅግ ፍጹምና ጻድቅ የሆንህ አዲስ ፍጥረት ነህ። ሊሰማህ አያስፈልግም፤ ነገር ግን አሁን ሌላ ሰው እንደ ሆንህ፣ እጅግ አሸናፊ እንደ ሆንህና ከመቼውም ይልቅ ጥበብ የተሞሉ ውሳኔዎችን ለማድረግ እንደምትችል እመን። አሁን ለአንተ የሚሳንህ ነገር የለም! መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀምር፤ እግዚአብሔርም እንዲናገርህና በፍጹም ፈቃዱ እንዲመራህ ፍቀድለት።
እግዚአብሔር ይባርክህ!
ተፈጸመ
ምዕራፍ 12 ተጠናቋል
የመዳን ጸሎት