ምዕራፍ 36 · 4 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ
አባሪ በ፦ የቤተ ክርስቲያን ኅብረት፣ ጥምቀትና ሌሎችም
ወንድም ክሬክና እኔ በብሪስቶል መሥራት በጀመርንና በዚህም ምክንያት አንዳንድ አማኞች ከእኛ ጋር በኅብረት ተባብረው በቤተ ሳይዳ መሰብሰብ በጀመሩ ጊዜ፣ ምንም ዓይነት የቤተ ክርስቲያን ደንብ ሳይኖረን በተጻፈው ቃል ላይ ብቻ ተመሥርተን በአንድነት መሰብሰብ ጀመርን። ገና ከመጀመሪያው፣ ጌታ እንደ ረዳን መጠን ሁሉን ነገር በእግዚአብሔር ቃል እንድንፈትን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ሊረጋገጥ የሚችለውን ብቻም እንድናስገባና አጥብቀን እንድንይዝ የታወቀ ነበር። ይህን ውሳኔ በኦገስት 13 ቀን 1832 ስናደርግ በእርግጥ በድካም ነበር፤ ነገር ግን በልብ ቅንነት ነበር።—ስለዚህም፣ ወደ ኅብረት መቀበል ያለብን ካመኑ በኋላ የተጠመቁትን ብቻ ነው ወይስ ጥምቀትን ሳንመለከት በጌታ ኢየሱስ ያመኑትን ሁሉ በሚለው ጉዳይ እኛ ራሳችን ገና ሙሉ በሙሉ ስላልጸናን፣ በዚህ ነጥብ ላይ ምንም ነገር አልተወሰነም። ካልተጠመቁት ጋር እንጀራ ለመቁረስና በኅብረት ለመሆን ነጻነት ይሰማን ነበር፤ ስለዚህም ቢያንስ በመጀመሪያ አብዛኞቹ ቅዱሳን ባልተጠመቁበት በጌዴዎን በንጹሕ ሕሊና መሥራት እንችል ነበር፤ ሆኖም በዚያው ጊዜ በቤተ ሳይዳ ከተጠመቁ አማኞች በቀር ማንም ከእኛ ጋር እንዳይተባበር በውስጣችን የተሰወረ ምኞት ነበረን። ለዚህም ምክንያታችን የተጠመቁና ያልተጠመቁ አማኞች በአንድ ኅብረት በመሆናቸው ምክንያት መጣ ብለን ያሰብነውን ብዙ አሳዛኝ መለያየት በዴቨንሻየር አይተን ስለ ነበር ነው። ስለዚህ የቤተ ሳይዳ ቤተ ክርስቲያን ኅብረቷ ለተጠመቁት ብቻ የተወሰነ እንዲሆን ደንብ ባናደርገውም፣ ለኅብረት የሚያመለክቱት ስለ ጥምቀት እንዲማሩ ግን እንጠነቀቅ ነበር። ለብዙ ወራት ምንም ችግር አልተፈጠረም፤ ምክንያቱም ለኅብረት የሚያመለክቱት ቀድሞ የተጠመቁ፣ ወይም ለመጠመቅ የሚፈልጉ፣ ወይም ካነጋገርናቸው በኋላ የአማኞች ጥምቀት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን ያመኑ ብቻ ነበሩ፤ በኋላ ግን አንዳቸውም ያልተጠመቁ ሦስት እኅቶች ለኅብረት አመለከቱ፤ ካነጋገርናቸውም በኋላ አመለካከታቸው አልተለወጠም። ሆኖም ወንድም ክሬክና እኔ እውነተኛ አማኞች እንደ ሆኑ ስላመንንና እኛ ራሳችን በእንዲህ ያለ ጉዳይ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ሙሉ በሙሉ ስላልተረዳን፣ እነዚህን እኅቶች መቀበል እንዳለብን አሰብን፤ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያናችን ውሳኔዎች ሁሉ በዚያን ጊዜ ይደረጉ እንደ ነበረው በሙሉ ስምምነት እንዲሆን ነው፤ ይሁን እንጂ ያልተጠመቁ አማኞችን በሕሊናቸው መቀበል የማይችሉ በርካታ ሰዎች ከእኛ ጋር በኅብረት እንዳሉ እስከዚያ ጊዜ አውቀን ነበር። ስለዚህ የሦስቱን እኅቶች ስም ለቤተ ክርስቲያን ተናገርን፤ የአማኞች ጥምቀት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን እንደማያዩም ገለጽን፤ ከወንድሞችም ማንም በዚህ ምክንያት እንዳንቀበላቸው የሚያደርግ ምክንያት ካየ እንዲያሳውቀን አልን። ውጤቱም በርካቶች መቃወማቸው ነበር፤ ሁለት ወይም ሦስት ስብሰባዎችም ተደረጉ፤ በእነርሱም የወንድሞችን ተቃውሞ ሰማን፣ እኛም ራሳችን በዚህ ነጥብ ላይ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ለማወቅ ፈለግን። ጉዳዩ ከመወሰኑ በፊት በዚህ ሁኔታ ብዙ ቀናት ሲያልፉ፣ ከሦስቱ እኅቶች አንዷ መጥታ ሳትጠመቅ ስላልተቀበልናት አመሰገነችን፤ ወደ ኋላ ያስቀራት ኀፍረትና ሰውን መፍራት ብቻ እንደ ነበረ አሁን ተረድታለችና፤ ጌታም አሁን ለመጠመቅ ፈቃደኛ አድርጓት ነበር። በዚህ ሁኔታ፣ ሁሉም ወደ ኅብረት ከመቀበላቸው በፊት መጠመቅ አለባቸው የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ብለው ያምኑ የነበሩት ወንድሞች በአመለካከታቸው ጸኑ፤ ወንድም ክሬክንና እኔን ግን ቢያንስ እነዚያ ወንድሞች ትክክል ይሆኑ እንደ ሆነ ይበልጥ እንድንጠራጠር አደረገን፤ ስለዚህም በእንዲህ ያለ የአእምሮ ሁኔታ ልንቃወማቸው እንደማንችል ተሰማን። ስለዚህ ለመጠመቅ የፈለገችውን አንዷን እኅት ወደ ኅብረት ተቀበልናት፤ ሁለቱን ግን አልተቀበልናቸውም። ይህ ሕሊናችንን ብዙም ያልነካው፣ ሁሉም ባይጠመቁም፣ ወደ ሙሉ ኅብረት ባንቀበላቸውም፣ በቤተ ሳይዳ ከእኛ ጋር የጌታን እራት መውሰድ ይችሉ ስለ ነበር ነው፤ ደግሞም የተጠመቁና ያልተጠመቁ አማኞች በነበሩበት በጌዴዎን ወደ ሙሉ ኅብረት እንኳ ልንቀበላቸው እንችል ስለ ነበር ነው፤ ምክንያቱም ከግለሰቦች ጋር በኅብረት በመሆንና ከእነርሱ ጋር እንጀራ በመቁረስ መካከል መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ ልዩነት እንደሌለ በዚያን ጊዜ ገና በግልጽ አላየንም ነበርና። ጉዳዩም ለብዙ ወራት በዚህ ሁኔታ ቆየ፤ ይኸውም አማኞች ባይጠመቁም በቤተ ሳይዳ እንኳ እንጀራ ለመቁረስ እንቀበላቸው ነበር፤ ነገር ግን ለኅብረት መብቶች ሁሉ አንቀበላቸውም ነበር።—በ1836 ኦገስት ከወንድም ኬ. ሲ. ጋር ያልተጠመቁትን ወደ ኅብረት ስለ መቀበል ተነጋገርሁ፤ ይህ ጉዳይ ለዓመታት አእምሮዬን ይብዛም ይነስም ሲያስጨንቀው የኖረ ነበር። ይህ ወንድም ጉዳዩን እንዲህ አድርጎ አቀረበልኝ፦ ወይ ያልተጠመቁ አማኞች ያለ ሥርዓት በሚሄዱ ሰዎች ወገን ይመደባሉ፤ እንደዚያ ከሆነ ከእነርሱ መለየት ይገባናል (2ኛ ተሰሎንቄ 3:6)፤ ወይም ያለ ሥርዓት አይሄዱም። አንድ አማኝ ያለ ሥርዓት የሚሄድ ከሆነ ከእርሱ መለየት ያለብን በጌታ ማዕድ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ከእርሱ ጋር በምንገናኝበት ወይም በማንኛውም መንገድ በምንተዋወቅበት በማንኛውም አጋጣሚ ለእርሱ ያለን ጠባይ ያለ ሥርዓት የማይሄድ ቢሆን ኖሮ ከሚሆነው በግልጽ የተለየ ሊሆን ይገባዋል። እንግዲህ የተጠመቁ አማኞች ያልተጠመቁ ወንድሞቻቸውን የሚይዙበት ሁኔታ እንዲህ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። መንፈስ እንዲህ እንዲሆን አይፈቅድም፤ ይልቁንም አለመጠመቃቸው የግድ ያለ ሥርዓት እየሄዱ እንደ ሆኑ እንደማያሳይ ይመሰክራል፤ ስለዚህም በተጠመቁና ባልተጠመቁ አማኞች መካከል እጅግ ውድ የሆነ ኅብረት ሊኖር ይችላል። መንፈስ በጸሎት፣ መጻሕፍትን በማንበብና በመመርመር፣ በማኅበራዊና በቅርብ ግንኙነት፣ በጌታም ሥራ ከእነርሱ ጋር ኅብረትን እንድንከለክል አይፈቅድልንም፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱ ቢሆኑ ግን እንዲህ ሊሆን በተገባው ነበር።—ወንድም ኢ. ሲ. የጠቀሰው ይህ ክፍል፣ 2ኛ ተሰሎንቄ 3:6፣ በዚህ ጉዳይ የጌታን ሐሳብ እንዳይ መንገድ ሆነልኝ፤ ይኸውም ክርስቶስ የተቀበላቸውን ሁሉ መቀበል እንዳለብን ነው (ሮሜ 15:7)፤ የደረሱበት የጸጋ ወይም የዕውቀት መጠን ምንም ይሁን ምን።—ከዚህ ንግግር ጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በሜይ 1837፣ ጌታ ሊሰጠን የወደደውን ብርሃን በተግባር እንድናውል የተጠራንበት አጋጣሚ ተገኘ (ወንድም ክሬክም ያንኑ እውነት አይቶ ነበርና)። ያልተጠመቀች፣ ለመጠመቅም ምንም ግዴታ እንዳለባት የማታስብ አንዲት እኅት ለኅብረት አመለከተች። እንደ ሌሎቹ ጉዳዮች ሁሉ በዚህም ጉዳይ አነጋገርናት፤ ንግግራችን መጠመቅ እንዳለባት ባያሳምናትም ለኅብረት አቀረብናት። ይህም ቤተ ክርስቲያንን እንደ ገና ይህን ነጥብ እንድትመረምር አደረጋት። ይህችን ያልተጠመቀች እኅት ለእግዚአብሔር ልጆች መብቶች ሁሉ መቀበል ትክክል ነው የምንልበትን ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ሰጠን፤ ነገር ግን ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ፣ ምናልባት አንድ ሦስተኛው፣ እርስዋን ለመቀበል የሕሊና ችግር እንዳለባቸው ገለጹ። በተለይ የተጠቀሰው ሐዋርያት የመጀመሪያዎቹን አማኞች እምነታቸውን በመመስከራቸው ያጠመቁበት ምሳሌ ነበር፤ ይህም እውነት ለረጅም ዘመን ከስሕተት ጋር ባይደባለቅ ኖሮ በእርግጥ ሊታለፍ የማይችል ችግር በሆነ ነበር፤ ስለዚህም በዘመናችን አንድ ሰው ካመነ በኋላ ለመጠመቅ እንቢ ቢል ይህ ሆን ብሎ አለመታዘዝን አያረጋግጥም። ይሁን እንጂ ጌታ እውነቱን ለወንድሞች በማመልከት ብዙ ረዳን፤ ስለዚህም በኅብረት መሆን ያለባቸው የተጠመቁ አማኞች ብቻ ናቸው ብለው የሚያስቡት ቁጥር በየዕለቱ ማለት ይቻላል እየቀነሰ ሄደ። በመጨረሻም፣ ከእነርሱ ጋር ብዙ ከተነጋገርን በኋላ፣ ከ180 በላይ ከሆኑት መካከል አሥራ አራት ወንድሞችና እኅቶች ብቻ በዚህ በኦገስት 28 ቀን 1837 ከእኛ መለየት ትክክል መስሎ ታያቸው። [ከእነዚህ ከአሥራ አራቱ እንኳ አብዛኞቹ በኋላ ስሕተታቸውን አይተው ወደ እኛ እንደ ተመለሱ፣ ጥምቀትን ሳንመለከት ጌታችን ኢየሱስን የሚወዱትን ሁሉ ወደ ሙሉ ኅብረት መቀበላችንም ከዚያ ወዲህ ከሃምሳ ሰባት ዓመታት በላይ ቢያልፉም በመካከላችን አንድም ጊዜ የመለያየት ምክንያት እንዳልሆነ ልጨምር በመቻሌ ደስ ይለኛል።]