ምዕራፍ 34 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ
አባሪ ሸ፦ እግዚአብሔር በማቅረብ ያሳየው ታማኝነት
አቶ ፔሪ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ በሀንትሊ በተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ በልዩ ጥያቄ መሠረት አቶ ሙለር ከወላጅ አልባ ሕፃናት ሥራ ጋር በተያያዘ እግዚአብሔር ለጸሎት መልስ በመስጠት ያሳየውን ታማኝነት የሚገልጹ ምሳሌዎችን አቀረበ፤ ከእነዚህም የሚከተሉት ይገኙበታል፦
ሀ. በሥራው መጀመሪያ ላይ ብቻ ሳይሆን በኋለኞቹ ዓመታትም በተለያዩ ጊዜያት እግዚአብሔር እምነቱን እስከ መጨረሻው ድረስ ሊፈትን እንደ ወደደ ተናገረ፤ ይህንንም ያደረገው ከታማኝ፣ ኪዳኑን ከሚጠብቅ አምላኩ በቀር ሌላ ፈጽሞ እንደማይሆን ይበልጥ በግልጽ ሊያረጋግጥለት ብቻ ነበር። ለዚህም ምሳሌ እንዲሆን ልጆቹ የዕለቱን የመጨረሻ ምግባቸውን ከበሉ በኋላ ለማግስቱ ጠዋት ቁርሳቸው በገንዘብም ሆነ በዓይነት ምንም ያልቀረበትን ጊዜ አነሣ። አቶ ሙለር ወደ ቤቱ ሄደ፤ ነገር ግን ምንም አልመጣም፤ እግዚአብሔርም እንዲያሟላው ችግሩን ለእርሱ አደራ ሰጥቶ ለሌሊቱ ዐረፈ። በማግስቱ ማልዶ ሊንሸራሸር ወጣ፤ ለሚያስፈልገውም እርዳታ እየጸለየ ሳለ ሳያውቀው ወደ አንድ መንገድ ታጠፈ፤ ጥቂት ርቀት እንደ ሄደም አንድ ወዳጁ አገኘውና ስላገኘው ምን ያህል ደስ እንዳለው ነግሮ ለወላጅ አልባ ሕፃናቱ 5 ፓውንድ እንዲቀበለው ለመነው። እርሱም አመሰገነው፤ ስለ ችግሩ ጊዜ ለሰጪው አንዲት ቃል እንኳ ሳይተነፍስ ስለዚህ ቀጥተኛ የጸሎት መልስ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወዲያውኑ ወደ ወላጅ አልባ ሕፃናት ቤቶቹ ሄደ።
ለ. በሌላ ጊዜ ደግሞ ለወላጅ አልባ ሕፃናቱ ቁርስ የሚያቀርቡበት ገንዘብ በእጅ ባልነበረበት ጊዜ አንድ ጨዋ ሰው ከቁርስ ሰዓት በፊት መጥቶ በዚያን ጊዜ የነበረባቸውን ፍላጎት ሁሉ የሸፈነ ስጦታ ትቶ ሄደ። የዚያ ዓመት ሪፖርት በወጣ ጊዜ፣ እግዚአብሔር በሚያስፈልግበት ጊዜ ልክ እርዳታ በመላክ ያሳየው ይህ የታማኝነቱ ማስረጃ ተመዘገበ፤ ብዙም ሳይቆይ ሰጪው መጥቶ ራሱን አስተዋወቀ፤ ስጦታው በእንዲህ ያለ ልዩ የችግር ጊዜ በመሰጠቱ ገንዘቡን የሰጠበትን ሁኔታ መናገር እንዳለበት እንደ ተሰማው ገለጸ፤ ሁኔታውም እንዲህ ነበር፦ በዚያች ጠዋት ከቁርስ በፊት በማለዳ በብሪስቶል ወደሚገኘው ቢሮው መሄድ ነበረበት፤ በመንገድም ሳለ «ወደ አቶ ሙለር የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት ሄጄ ስጦታ እሰጣቸዋለሁ» የሚል ሐሳብ መጣለት፤ በዚህም መሠረት ተመልሶ ወደ ወላጅ አልባ ሕፃናቱ ቤት ሩብ ማይል ያህል ከሄደ በኋላ ቆም ብሎ ለራሱ «ልከታተለው የወጣሁትን ሥራ ቸል ማለቴ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! ለወላጅ አልባ ሕፃናቱ በሌላ ጊዜ ገንዘብ መስጠት እችላለሁ» አለ፤ ዞሮም ወደ ቢሮው ተመለሰ፤ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ መመለስ እንዳለበት ተሰማው። ለራሱም እንዲህ አለ፦ «ወላጅ አልባ ሕፃናቱ ገንዘቡን የሚያስፈልጋቸው አሁን ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር እንድረዳቸው ልኮኝ ሳለ በችግር ውስጥ ትቻቸው እየሄድሁ ይሆናል፤» ይህም ስሜት እጅግ ጠንካራ ስለ ነበረ እንደ ገና ዞሮ ወደ ወላጅ አልባ ሕፃናቱ ቤቶች እስኪደርስ ድረስ ተጓዘ፤ በዚህም ሁኔታ ቁርሳቸውን ያቀረበላቸውን ገንዘብ አስረከበ። አቶ ሙለር በዚህ ላይ የሰጠው አስተያየት «ልክ እንደ ቸሩ የሰማዩ አባቴ!» የሚል ነበር፤ ከዚያም አድማጮቹ እንዲታመኑና እርሱ በእርሱ ለሚታመኑት ምን ያህል ታማኝ፣ ኪዳኑን የሚጠብቅ አምላክ እንደ ሆነ እንዲያረጋግጡ አጥብቆ መከራቸው።