ምዕራፍ 31 · 10 ደቂቃ ንባብ · 12 ደቂቃ ማዳመጥ
አባሪ ሠ፦ አቶ ሙለርን የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት እንዲያቋቁም ያደረጉት ምክንያቶች
በዘመናችን የእግዚአብሔር ልጆች በተለይ ከሚያስፈልጓቸው ነገሮች አንዱ እምነታቸው እንዲጠነክር ማድረግ መሆኑን የሚያሳዩ ጉዳዮች ዘወትር ይቀርቡልኝ ነበር። ለምሳሌ፦ በሙያው በቀን አሥራ አራት ወይም አሥራ ስድስት ሰዓት እንኳ የሚሠራን አንድ ወንድም ልጠይቅ እችል ነበር፤ የዚህም የግድ ውጤት ሥጋው መጎዳቱ ብቻ ሳይሆን ነፍሱም መክሳቷና በእግዚአብሔር ነገሮች ደስታ ማጣቱ ነበር። በዚህ ሁኔታ ሥጋዊ ጤናው እንዳይጎዳ፣ የእግዚአብሔርንም ቃል በማንበብ፣ በእርሱ ላይ በማሰላሰልና በጸሎት ለውስጠኛው ሰውነቱ ኃይል እንዲያገኝ ሥራውን መቀነስ እንዳለበት ልመክረው እችል ነበር። የማገኘው መልስ ግን ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለ ነበር፦ «ሥራዬን ብቀንስ ግን ቤተሰቤን የሚያኖር በቂ ገቢ አላገኝም። አሁን እንኳ ይህን ያህል እየሠራሁ የሚበቃኝን በጭንቅ አገኛለሁ። ደመወዙ እጅግ ዝቅተኛ ስለ ሆነ የሚያስፈልገኝን ለማግኘት አጥብቄ መሥራት አለብኝ።» በእግዚአብሔር መታመን አልነበረም። «አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።» በሚለው ቃል እውነትነት እውነተኛ እምነት አልነበረም። እኔም እንዲህ ያለ መልስ ልሰጠው እችል ነበር፦ «ውድ ወንድሜ ሆይ፣ ቤተሰብህን የሚያኖረው ሥራህ ሳይሆን ጌታ ነው፤ በሕመም ምክንያት ፈጽሞ መሥራት ባልቻልህ ጊዜ አንተንና ቤተሰብህን የመገበ እርሱ፣ ለውስጠኛው ሰውነትህ ምግብ ለማግኘት ስትል ለብቻህ ለመሆን በቂ ጊዜ የሚተውልህን ያህል ሰዓት ብቻ በቀን ብትሠራ ለአንተና ለቤተሰብህ በእርግጥ ያቀርብላችኋል። ደግሞስ አሁን ለጸሎት ጥቂት የችኮላ ደቂቃዎችን ብቻ ወስደህ የዕለቱን ሥራ የምትጀምር አይደለህምን? ማታስ ሥራህን ትተህ ከእግዚአብሔር ቃል ጥቂት ለማንበብ ስታስብ፣ በሥጋም በአእምሮም እጅግ ደክመህ ስለምትገኝ ልትደሰትበት አትችልም፤ መጻሕፍትን እያነበብህ ወይም በጉልበትህ ተንበርክከህ እየጸለይህ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ አይወስድህምን?» ወንድሙ ነገሩ እንዲህ መሆኑን ያምን ነበር፤ ምክሬም መልካም መሆኑን ይቀበል ነበር፤ ነገር ግን በቃሉ ባይናገረውም እንኳ «ምክርህን ብፈጽም እንዴት እኖራለሁ?» የሚለውን በፊቱ ላይ አነብብ ነበር። ስለዚህ አምላካችንና አባታችን ቀድሞ እንደ ነበረው ዛሬም ያው ታማኝ አምላክ መሆኑን፣ በእርሱ ለሚታመኑ ሁሉ እንደ ቀድሞው በዘመናችንም ሕያው አምላክ መሆኑን ለማረጋገጥ እንደ ወትሮው ፈቃደኛ መሆኑን የሚያሳይ በዓይን የሚታይ ማስረጃ፣ ወንድሙን የማመለክትበት አንድ ነገር እንዲኖረኝ ናፈቅሁ።—ደግሞም አንዳንድ ጊዜ ከእንግዲህ መሥራት የማይችሉበት የእርጅና ዘመን ስለሚመጣባቸው በአእምሮአቸው የተጨነቁና ስለዚህም ወደ ድሆች መጠለያ እንገባ ይሆናል በሚል ፍርሃት የሚታወኩ የእግዚአብሔር ልጆች አገኝ ነበር። እንዲህ ባለው ጊዜ የሰማዩ አባታቸው በእርሱ የሚታመኑትን ሁልጊዜ እንዴት እንደ ረዳቸው ባሳያቸው፣ ምናልባት ዘመኑ ተለውጧል ብለው ሁልጊዜ ባይናገሩም፣ እግዚአብሔርን እንደ ሕያው አምላክ እንደማይመለከቱት ግን በግልጥ ይታይ ነበር። መንፈሴ በዚህ ብዙ ጊዜ ይዝል ነበር፤ በእርሱ የሚታመኑትን በዘመናችንም እንደማይተዋቸው የሚያዩበትን አንድ ነገር በእግዚአብሔር ልጆች ፊት ለማቅረብ ናፈቅሁ።—ሌላው ወገን ደግሞ ልክ ያልተለወጡ ሰዎች በሚያደርጉት መንገድ ንግዳቸውን በማካሄዳቸው በነፍሳቸው የተጎዱና በሕሊናቸው ላይ በደል ያመጡ ነጋዴ ወንድሞች ነበሩ። የንግድ ፉክክር፣ ክፉው ዘመን፣ ከሕዝብ ብዛት የተጨናነቀው አገር፣ ንግዱ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ብቻ ቢካሄድ ይሳካል ተብሎ የማይጠበቅበት ምክንያቶች ሆነው ይቀርቡ ነበር። እንዲህ ያለው ወንድም ምናልባት ሁኔታው ሌላ ቢሆንለት እንደሚመኝ ይናገር ይሆናል፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር የቆመ አቋም፣ መልካም ሕሊና ተጠብቆ እንዲኖር በሕያው አምላክ ለመታመንና በእርሱ ለመደገፍ የተደረገ ቅዱስ ቁርጠኝነት ያየሁት እጅግ አልፎ አልፎ ነበር። ለዚህም ወገን እግዚአብሔር የማይለወጥ ያው መሆኑን በዓይን በሚታይ ማስረጃ ላሳይ ተመኘሁ።—ከዚያም ደግሞ ሌላ ወገን ነበር፤ በመልካም ሕሊና ሊቀጥሉበት በማይችሉት ሙያ ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ ወይም በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ በሆነ አቋም ላይ የነበሩ ሰዎች፤ ሁለቱም ወገኖች ግን ከሥራ እንዳይፈናቀሉ በመስጋት፣ ከሚያስከትለው ውጤት የተነሣ ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖሩበት የማይችሉትን ሙያ ለመተው ወይም አቋማቸውን ለመልቀቅ ይፈሩ ነበር። መንፈሴ በእርሱ የሚታመኑትን ሁሉ ለመርዳት ፈቃደኛና ብርቱ መሆኑን የሚገልጡ ምሳሌዎችን ከእግዚአብሔር ቃል በመስጠት ብቻ ሳይሆን፣ በዘመናችንም ያው መሆኑን በማስረጃ በማሳየት እምነታቸውን ለማጠንከር መሣሪያ ለመሆን ናፈቀ። የእግዚአብሔር ቃል በቂ ሊሆን እንደሚገባው በሚገባ አውቅ ነበር፤ በጸጋም ለእኔ በቂ ነበረ፤ ነገር ግን በምንም መንገድ ቢሆን ስለ ጌታ የማይለወጥ ታማኝነት በሚሰጠው በዚህ በዓይን የሚታይ ማስረጃ እጃቸውን በእግዚአብሔር ላበረታ እችል እንደ ሆነ፣ ለወንድሞቼ የእርዳታ እጅ መዘርጋት እንዳለብኝ አሰብሁ፤ ጌታ ከባሪያው ከአ. ሔ. ፍራንኬ ጋር ባደረገው አያያዝ የራሴ ነፍስ ምን ያህል ታላቅ በረከት እንደ ተቀበለች አስታውሼ ነበርና፤ እርሱ በሕያው አምላክ ብቻ በመደገፍ እጅግ ግዙፍ የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት አቋቁሞ ነበር፤ ያንንም ብዙ ጊዜ በገዛ ዓይኔ አይቼዋለሁ። ስለዚህ ምሕረትን ባገኘሁበት በዚያ በተለየ ነጥብ፣ ማለትም እግዚአብሔርን በቃሉ ይዞ በእርሱ ላይ መደገፍ በመቻል፣ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የመሆን ግዴታ እንዳለብኝ ቈጠርሁ። የማውቃቸው ብዙ አማኞች በጌታ ባለመታመናቸው የተነሣ በአእምሮአቸው የታወኩና የተጨነቁ፣ ወይም በሕሊናቸው ላይ በደል ያመጡ በመሆናቸው ምክንያት የመጣው ይህ ሁሉ የነፍሴ ትግል፣ እግዚአብሔር ፈጽሞ እንዳልተለወጠ የሚያሳይ ማስረጃ በመላው ቤተ ክርስቲያንና በዓለም ፊት የማቅረብ ምኞትን በልቤ ለማንቃት በእግዚአብሔር ጥቅም ላይ ዋለ፤ ይህም የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት በማቋቋም ቢደረግ ይሻላል መሰለኝ። በሥጋዊ ዓይን እንኳ ሊታይ የሚችል ነገር መሆን ነበረበት። እንግዲህ እኔ ድሀው ሰው በጸሎትና በእምነት ብቻ፣ ማንንም ሰው ሳልለምን፣ የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት ለማቋቋምና ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ባገኝ፣ ይህ ባልተለወጡት ሰዎች ሕሊና ፊት ለእግዚአብሔር ነገሮች እውነተኛነት ምስክር ከመሆኑም በላይ፣ በጌታ በረከት የእግዚአብሔርን ልጆች እምነት ለማጠንከር መሣሪያ ሊሆን የሚችል አንድ ነገር ይሆናል። እንግዲህ የወላጅ አልባ ሕፃናትን ቤት ለማቋቋም ዋናው ምክንያት ይህ ነበር። አባትና እናታቸውን ያጡ ድሀ ሕፃናትን በሥጋቸው ለመጥቀም፣ በሌላም ረገድ በእግዚአብሔር እርዳታ ለዚህ ሕይወት መልካም ለማድረግ በእግዚአብሔር ጥቅም ላይ እንድውል በእርግጥ ከልቤ ተመኘሁ፤—እንዲሁም ውድ የሆኑትን ወላጅ አልባ ሕፃናት እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲያድጉ ለማድረግ በእግዚአብሔር ጥቅም ላይ እንድውል በተለይ ናፈቅሁ፤—ነገር ግን የሥራው የመጀመሪያና ዋና ዓላማ በእኔ ወይም ከእኔ ጋር በሚሠሩት ማንም ሰው ሳይለመን፣ በእኔ እጅ ያሉት ወላጅ አልባ ሕፃናት የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በጸሎትና በእምነት ብቻ በማግኘታቸው እግዚአብሔር እንዲከብር ነበር (አሁንም ነው)፤ በዚህም እግዚአብሔር ዛሬም ታማኝ እንደ ሆነ፣ ዛሬም ጸሎትን እንደሚሰማ ይታይ ዘንድ ነው።
የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት ለማቋቋም ሦስቱ ዋና ምክንያቶች እነዚህ ናቸው፦ 1. እግዚአብሔር ገንዘቡን ሊሰጠኝ ፈቃዱ ቢሆን፣ በእርሱ መታመን ከንቱ ነገር እንዳልሆነ በመታየቱ እግዚአብሔር እንዲከብር፤ በዚህም የልጆቹ እምነት እንዲጠነክር። 2. አባትና እናት የሌላቸው ሕፃናት መንፈሳዊ ደኅንነት። 3. ሥጋዊ ደኅንነታቸው።
አእምሮዬ በተለይ ያዘነበለበት ነገር አባትና እናት የሌላቸው ችግረኛ ሕፃናት ምግብና ልብስ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የሚያገኙበት የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት ማቋቋም ነው። ስለዚህ ሊቋቋም ስለ ታሰበው የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት እንዲህ እላለሁ፦
1. በሪፖርቶቹ፣ በሒሳቦቹ፣ በቍጥጥሩና በሚመራባቸው መርሆች ረገድ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ተቋም ጋር የተያያዘ እንዲሆን ታስቧል፤ ስለዚህ በአንድ በኩል የተቋሙ አዲስ ዓላማ ተደርጎ ሊቈጠር ይችላል፤ ነገር ግን ለወላጅ አልባ ሕፃናት ቤቱ የሚውለው ለእርሱ ተብሎ በግልጥ የተሰጠው ገንዘብ ብቻ እንዲሆን በሚል ልዩነት ነው። ስለዚህ ማንም አማኝ እስከ አሁን በዚህ ተቋም ገንዘብ ሲረዱ የነበሩትን ዓላማዎች ወይም ሊቋቋም የታሰበውን የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት መርዳትን ቢመርጥ፣ ገንዘቡ በዚያው መሠረት ሥራ ላይ እንዲውል መጥቀስ ብቻ በቂ ነው።
2. የሚቋቋመው ጌታ ለእርሱ የሚያስፈልገውን ገንዘብና የሚመሩትን ተስማሚ ሰዎች ሁለቱንም ከሰጠ ብቻ ነው።
ገንዘቡን በተመለከተ የሚከተለውን ማሳሰቢያ እሰጣለሁ፦ ሥራውን ለማስፋት ያቀድነው በቅርቡ በተለይ ገንዘብ ስለ በዛልን አይደለም፤ እንዲያውም ይልቁን ተቸግረን ነበር። ነገር ግን ጌታ ስለዚህ ተቋም የሰጠን ብዙ የጸጋ መልሶች፣ ዕዳ መግባትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ እንደ ሆነ ስለምንቈጥረው፣ እኔና ወንድም ሲ——ር ሥራውን የምናካሂድበትን ገንዘብ እንዲሰጠን እየለመንነው ራሳችንን ለጸሎት እንድንሰጥ መራን። አምስት ቀን በአንድነትም በየግላችንም ብዙ ጊዜ ጸለይን። ከዚያ በኋላ ጌታ ጸሎታችንን ይመልስ ጀመር፤ ስለዚህም በጥቂት ቀናት ውስጥ 50 ፓውንድ ያህል ተሰጠን። ደግሞም እላለሁ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ምንም የተወሰነ ገቢ ሳይኖረኝ ለጸሎት መልስ የራሴን ሥጋዊ ፍላጎቶች በማሟላቱ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ያደረገው እጅግ ቸርና ርኅሩኅ አያያዝ፣ እጅግ በተቸገርሁባቸው ጊዜያት ገንዘብ፣ ቀለብና ልብስ በትንሽ ብቻ ሳይሆን በብዙ መጠን ተልኮልኛልና፤ ከእኔ ጋር በአንድ ስፍራ ከሚኖሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ከሩቅ ስፍራም፣ ከቅርብ ወዳጆች ብቻ ሳይሆን ፈጽሞ አይቻቸው ከማላውቃቸው ሰዎችም፤ ይህ ሁሉ፣ እላለሁ፣ ጌታ ይህን በእርሱ ላይ የመደገፍ ቀላል እምነት የሰጠኝ ለራሴ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጭምር እንደ ሆነ ከአራት ዓመት በፊት ጀምሮ እንኳ ብዙ ጊዜ እንዳስብ አድርጎኛል። በቲንማውዝ ጎዳናዎች ላይ የተጣሉ ድሀ ሕፃናት ሲሯሯጡ ባየሁ ጊዜ ብዙ ጊዜ በልቤ፦ «ለእነዚህ ሕፃናት ገንዘቡን እንዲሰጠኝ እየለመንሁት ትምህርት ቤቶችን እንዳቋቁም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሆን ይሆን?» እል ነበር። ቢሆንም ለሁለት ወይም ለሦስት ዓመት በአእምሮዬ ውስጥ እንደ ሐሳብ ብቻ ቀረ። ከሁለት ዓመት ከስድስት ወር ገደማ በፊት ብዙ ችግረኛ ሕፃናት በብሪስቶል ጎዳናዎች ሲለምኑና ወደ በራችን ሲመጡ በማየቴ ለእነርሱ አንድ ነገር እንዳደርግ እንደ ገና በተለየ ሁኔታ ተነሣሣሁ። እንግዲህ ሳይደረግ የቀረው በጌታ ባለመታመን ሳይሆን የወንድሜ የክሬክንና የእኔን ጊዜና ኃይል ሁሉ የሚጠይቁ ሌሎች ብዙ ነገሮች ስለ ነበሩ ነው፤ ጌታ እምነትን ሰጥቶ ነበርና፤ ደግሞም ከብዙ ሌሎች ምሳሌዎች በተጨማሪ በሚከተለው ምሳሌ ምን ማድረግ እንደሚችልና ምን እንደሚያደርግ አሳይቶ ነበር። አንድ ቀን ጠዋት በክፍሌ ተቀምጬ ሳለሁ ስለ አንዳንድ ወንድሞች ጭንቀት አሰብሁና በልቤ እንዲህ አልሁ፦ «ኦ፣ እነዚህን ድሀ ወንድሞች የምረዳበትን ገንዘብ ጌታ ሊሰጠኝ ደስ ቢለው!» ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ አይቼው ከማላውቀውና ያን ጊዜም አሁንም ከዚህ ብዙ ሺህ ማይል ርቆ ከሚኖር አንድ ወንድም ለራሴ ስጦታ ተብሎ 60 ፓውንድ ተላከልኝ። እንዲህ ያለው ተሞክሮ በዮሐንስ 14:13-14 እንዳለው ካሉ ተስፋዎች ጋር፣ ለራሳችንም ለሌሎችም ሥጋዊና መንፈሳዊ በረከቶችን በሙሉ ድፍረት እንድንለምን ሊያበረታታን አይገባምን? ጌታ፣ እርሱ እንደ ሆነ ከማሰብ ልቆጠብ አልችልምና፣ ስለ እነዚህ ድሀ ሕፃናት ያለውን ሐሳብ ደጋግሞ ወደ አእምሮዬ አመጣው፤ በመጨረሻም «ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ተቋም» በመቋቋሙ ተፈጸመ፤ ይህ ከተቋቋመ ወዲህ ደግሞ፣ በመጀመሪያ ከአሥራ አራት ወር ገደማ በፊት፣ ከዚያም ወዲህ ደጋግሞ፣ በተለይ ግን በእነዚህ ባለፉት ሳምንታት፣ የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት ለማቋቋም የሚለው ሐሳብ በዚያው መንገድ ወደ አእምሮዬ ተመልሶ መጣ። በቅርቡ ዘወትር የምጸልየው ጸሎት፣ ነገሩ ከእግዚአብሔር ከሆነ እንዲፈጸም እንዲያደርግ፣ ካልሆነ ግን ስለ እርሱ ያለኝን ሐሳብ ሁሉ ከእኔ እንዲያስወግድ ነው። የኋለኛው አልሆነም፤ ይልቁንም ነገሩ ከእርሱ ሊሆን እንደሚችል ይበልጥ እየተረዳሁ ሄድሁ። እንግዲህ እንዲህ ከሆነ፣ እኔንና ጌታ በዚህ ሥራ ሊረዳኝ ፈቃደኛ ያደረገውን ወንድም ሲ——ርን በገንዘቡ እንዲያምኑን ሕዝቡን በየትኛውም የዓለም ክፍል ሊያነሣሣ ይችላል (እኔ የምመለከተው ወደ ብሪስቶል ወይም ወደ እንግሊዝ እንኳ ሳይሆን ወርቁና ብሩ የእርሱ ወደ ሆነው ወደ ሕያው አምላክ ነውና)። ገንዘቡ እስኪኖረን ድረስ ቤት በመከራየት፣ የቤት ዕቃ በማሟላትና በመሳሰሉት ረገድ ምንም ማድረግ አንችልም። ነገር ግን ለዚህ የሚያስፈልገው ያህል ገንዘብ፣ እንዲሁም በሥራው የሚሰማሩ ተስማሚ ሰዎች አንድ ጊዜ ከተላኩልን፣ የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤቱ ቋሚ ሀብት እስኪመደብለት ወይም በየዓመቱ የሚያዋጡ ብዙ ሰዎች እስኪገኙለት ድረስ መጠበቅ አስፈላጊ ነው ብለን አናስብም፤ ይልቁንም የዕለት እንጀራችንን እንድንለምን ያስተማረን ጌታ፣ በእጃችን ሊያኖራቸው ደስ የሚለውን የእነዚያን ሕፃናት የዕለት ፍላጎት እንዲያሟላልን ወደ እርሱ እንድንመለከት እንደሚያስችለን እንታመናለን። ማናቸውም ስጦታ በቤቴ ይቀበላል። ማናቸውም አማኞች ለቤቱ ማሟያ የሚሆኑ ትርፍ ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮች፣ አልጋዎች፣ የአልጋ ልብስ፣ የሸክላ ዕቃዎች ወይም ማናቸውም ዓይነት የቤት ዕቃ፤ ወይም ቍርጥራጭ ጨርቅ፣ የጥጥ ጨርቅ፣ የተልባ እግር ጨርቅ፣ የሱፍ ጨርቅ፣ ሌላ ጨርቅ ወይም ለልብስ መሥሪያ የሚጠቅም ማናቸውም ነገር፤ ወይም ያገለገሉ ልብሶች ቢኖሯቸው በምስጋና ይቀበላሉ።
ገንዘብ ከማግኘት ያላነሰ አስፈላጊ ጉዳይ ስለ ሆኑት ሥራውን ለማካሄድ ስለሚያስፈልጉት ሰዎች፣ እንደ ገንዘቡ ሁሉ እነርሱንም የምንጠብቀው ከራሱ ከእግዚአብሔር መሆኑን እገልጣለሁ፤ እንደ ተቋሙ ትንሽነት ወይም ትልቅነት እንደ አስተማሪዎች፣ እንደ ሞግዚቶችና እንደ ረዳቶች የሚቀጠሩ ሁሉ እውነተኛ አማኞች መሆናቸውን ማወቅ አለብን፤ ከዚህም በላይ መፍረድ እስከምንችለው ድረስ ለሥራው ብቃት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል።
3. ሥራው መቼ ሊጀመር እንደሚችል፣ ተቋሙ የሁለቱንም ፆታ ሕፃናት የሚያካትት ወይም ለወንዶች ብቻ ወይም ለሴቶች ብቻ የሚወሰን እንደ ሆነ፣ በምን ዕድሜ እንደሚቀበሉና በውስጡ እስከ መቼ እንደሚቆዩ በአሁኑ ጊዜ ምንም ማለት አይቻልም፤ ስለ እነዚህ ነገሮች አስበን ቢሆንም በእነዚህ ዝርዝሮች ረገድ ጌታ በእጃችን በሚያኖረው የገንዘብ መጠንና ተቋሙን እንዲመሩ በሚሰጣቸው ሰዎች ቍጥር ብንመራ እንመርጣለንና። ጌታ እኛን እንደ መሣሪያ ሊጠቀምብን ዝቅ ብሎ ፈቃዱ ቢሆን፣ ይበልጥ የተወሰነ ነገር መናገር እንደ ተቻለ ወዲያውኑ አጭር የታተመ መግለጫ ይወጣል።
4. አባትና እናታቸውን ያጡትን ችግረኛ ሕፃናት ብቻ መቀበል መልካም መስሎ ታየን።
5. ሕፃናቱ ሴቶች ከሆኑ ለቤት አገልግሎት፣ ወንዶች ከሆኑ ለሙያ እንዲያድጉ ታስቧል፤ ስለዚህ እንደ ችሎታቸውና እንደ ሥጋዊ ኃይላቸው በጠቃሚ ሥራዎች ይሰማራሉ፤ በዚህም ራሳቸውን ለማኖር ያግዛሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ ቀላል ትምህርት እንዲቀበሉ ታስቧል፤ ነገር ግን የተቋሙ ዋናና ልዩ ዓላማ በእግዚአብሔር በረከት መጻሕፍትን በማስተማር እነርሱን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕውቀት ለማምጣት መጣር ይሆናል።
ስለ ወላጅ አልባ ሕፃናት ቤትና ስለ ሌሎችም የቀረበ ተጨማሪ ዘገባ።
በቅርቡ በጌታ በመደገፍ የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት የማቋቋም ሐሳብ በአእምሮዬ እንደ ገና ሲነሣሣ፣ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት የጸለይሁት ነገሩ ከጌታ ከሆነ እንዲፈጽመው፣ ካልሆነ ግን ስለ እርሱ ያለኝን ሐሳብ ሁሉ ከአእምሮዬ እንዲያወጣልኝ በቸርነቱ ደስ እንዲለው ብቻ ነበር። የጌታን ፈቃድ ስለ ማወቅ የነበረብኝ ጥርጣሬ፣ ለችግረኛ አባትና እናት የሌላቸው ሕፃናት መኖሪያና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት መዘጋጀቱ በፊቱ ደስ የሚያሰኝ እንደ ሆነ ከመጠራጠር የመጣ አልነበረም፤ ነገር ግን እጆቼ ቀድሞውኑ ከሞሉ በላይ ስለ ነበሩ፣ እንዲህ ያለውን ሥራ ለመጀመር መሣሪያ የምሆነው እኔ እንድሆን ፈቃዱ ነው ወይ የሚለው ነበር። ማጽናኛዬ ግን፣ ፈቃዱ ከሆነ ገንዘቡን ብቻ ሳይሆን ሕፃናቱን የሚንከባከቡ ተስማሚ ሰዎችንም እንደሚሰጥ ነበር፤ ስለዚህም የሥራው የእኔ ድርሻ ከጉዳዩ አስፈላጊነት አንጻር ብዙ ሌሎች ኃላፊነቶች ቢኖሩብኝም ልሰጠው የምችለውን ያህል ጊዜዬን ብቻ ይወስዳል። በእነዚያ ሁለት ሳምንታት ሁሉ ገንዘብን ወይም በሥራው የሚሰማሩ ሰዎችን ከጌታ ፈጽሞ አልለመንሁም። ዲሴምበር 5 ቀን ግን የጸሎቴ ርእስ በድንገት ተለወጠ። መዝሙር 81ን እያነበብሁ ነበር፤ ከቀድሞው ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ ቍጥር 10 በተለይ ልቤን ነካው፦ «አፍህን አስፋ፥ እሞላዋለሁ።» በእነዚህ ቃላት ላይ ለጥቂት ጊዜ አሰብሁ፤ ከዚያም በወላጅ አልባ ሕፃናት ቤቱ ጉዳይ ላይ እንዳውላቸው ተመራሁ። ስለ እርሱ መቋቋም ወይም አለመቋቋም ፈቃዱን ለማወቅ ካልሆነ በቀር ስለዚህ ጉዳይ ከጌታ ምንም እንዳልለመንሁ ታወቀኝ፤ ከዚያም በጉልበቴ ተንበርክኬ አፌን አስፍቼ ብዙ ለመንሁት። ለፈቃዱ በመገዛትና መልሱን የሚሰጥበትን ጊዜ ሳልወስን ለመንሁ። ቤት እንዲሰጠኝ ጸለይሁ፤ ማለትም በውሰት፣ ወይም አንድ ሰው ለአንድ ቤት ኪራይ እንዲከፍል እንዲመራ፣ ወይም ለዚህ ዓላማ አንድ ቤት በቋሚነት እንዲሰጥ፤ በተጨማሪም 1000 ፓውንድ ለመንሁት፤ እንዲሁም ሕፃናቱን የሚንከባከቡ ተስማሚ ሰዎችን ለመንሁ። ከዚህም በተጨማሪ ለቤቱ የቤት ዕቃዎችን፣ ለሕፃናቱም ጥቂት ልብሶችን እንዲልኩልኝ በሕዝቡ ልብ እንዲያኖር ጌታን እንድለምን ከዚያ ወዲህ ተመርቻለሁ። ልመናውን ሳቀርብ የማደርገውን በሚገባ አውቅ ነበር፤ ማለትም ከማውቃቸው ወንድሞች የማግኘት ምንም ሰብአዊ ተስፋ የሌለኝን፣ ነገር ግን ጌታ ሊሰጠው የማይበዛበትን ነገር እየለመንሁ እንደ ነበረ።